Items filtered by date: Friday, 01 June 2018

ኳሷ የምታርፍበትን ትክክለኛውን ነጥብ ለማሳየት የምትለጋዋን የፈጣንዋን ኳስ እንቅሥቃሴ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቀርጹ በርካታ ካሜራዎች ያግዛሉ፡፡ እናም ዳኛው ኳሷ ከመሥመር ውጭ መሆን አለመሆኗን በተረጋገጠ ሁኔታ መወሰን ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህም ይግባኝ የማይልበት የመጨረሻ ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ሂደት በዘመናዊ ቴክኒክ በመታገዝ፣ ለአካራካሪ የስፖርት ውድድር ውጤት፣ ፍጹም ትክክለኛ የሆነውን ብይን መስጠትም ይቻላል፡፡
የተጫዋቾችንና የኳስን ፍጥነት፣ በአጠቃላይ የውድድር እንቅስቃሴን ምንጊዜም በዓይን ብሌን ብቻ ተመልክቶ ትክክለኛ ብይን መስጠት ያዳግታል፡፡ ውድድሮች በሚካሄዱባቸው ጊዜያት አልፎ አልፎ አከራካሪ ውጤትን ለማስተካከልም ሆነ ለማጽናት፣ በቪዲዮ የተቀረፀውን መልሶ መመልከት የሚቻልበት ሁኔታ በዓለም ላይ ቢፈጠርም፤ ኢትዮጵያውያን ዳኞች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ስላልሆኑና ቅጽበታዊ ውሳኔን ስለሚሰጡ በእርጋታ እንዲያመዛዝኑና ውሳኔያቸውን እንዲከልሱ ዕድል ሳያገኙ ለበርካታ ዓመታት ሰርተዋል፡፡
በስህተትም ሆነ በሌላ ምክንያት የተላለፈ ውሳኔን ባለመቀበል ከተለያዩ አካላት ጥቃት ሲሰነዘርባቸውም ተስተውሏል፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዳኝነት ሥርዓት ምን ይመስላል? ዳኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት መነሻው ምንድነው? ችግሩን ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረስት? እነዚህንና ሌሎች ከእግር ኳስ የዳኝነት ሥርዓት ጋር የሚነሱ ጉዳዮችን ለመዳሰስ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ፌዴራል ዳኛና የኢትዮጵያ ዳኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሚካኤል አርዓያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፦ የእግር ኳስ ዳኝነት ሙያን እንዴት ያዩታል?
አቶ ሚካኤል፦ ዳኝነትን በአጭሩ ለመግለጽ ያህል በተሰጠው ህግ መነሻነት ሜዳ ላይ ተጋጣሚ የሆኑ ሁለቱንም ተፎካካሪ አካላት በእኩል ማየትና ያልተዛባ ፍትህ መስጠት ነው፡፡ በእግር ኳሱ ለዳኝነት የተቀመጡ ወደ 17 ህጎች አሉ፡፡ እነዚህን ህጎች በሚታወቀውና ግልጽ በሆነው መንገድ ልክ እንደ ፍርድ ቤት አሰራር በጥንቃቄ ብይን መስጠት ነው፡፡ ህጎችንም በትክክል እፈፅማለሁ ተብሎ ነው ቃለ መሃላ የሚፈጸመው፡፡
አዲስ ዘመን፦ የእግር ኳስ ዳኝነትን ከሌሎች የስፖርት ዓይነቶች ዳኝነት ምን ልዩ ያደርገዋል?
አቶ ሚካኤል፦ በእርግጥ በእግር ኳሱ ዳኝነት የሚሰጡት አካላት ከሌሎች የስፖርት አይነቶች ዳኞች የጎላ ልዩነት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም የስፖርት አይነት ውስጥ ዳኝነት ፍርድ መስጠት ነው፡፡ ስፖርቶች የየራሳቸው የውድድር ህግ ቢኖራቸውም፤ ፍትህ በመስጠት በኩል ያለው አሰራር ግን ተመሳሳይነት አለው፡፡ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ የእግር ኳስ ስፖርት ደጋፊው ብዙ በመሆኑ ልዩ ኩረት እንዲሰጠው ሆኗል፡፡
አዲስ ዘመን፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዳኝነት ብቃት እንዴት ያዩታል?
አቶ ሚካኤል፦ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ዳኞች በብቃት አይታሙም፡፡ ይህ ደግሞ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለው የነበሩ ኢንተርናሽናል ዳኞቻችን ይህንን አስመስክረዋል፡፡ በብቃት ማነስም ሆነ ጉቦ ከመቀበል አኳያ ስማቸው አይነሳም፡፡ ብቃት ባይኖራቸው ኖሮ እነ ባምላክ ተሰማ እና ሊዲያ ታፈሰ የመሳሰሉት ዳኞች በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሲዳኙ ማየት ባልተቻለ ነበር፡፡ በእርግጥ ሁሉም ተመሳሳይ የሆነ ብቃት ላይ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን እንደየ ባህሪያቸው የአቅም ውስንነት ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ በዚህም አንዱ ከአንዱ የሚበልጥበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ለዚህም ክህሎትን በየጊዜው ሊያዳብር የሚችል ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ ከብዙ ውድድሮች ጥቂት ስህተት ሲፈፀም ጠቅላላ ዳኛ ተሳሳተ ተብሎም መፈረጅ የለበትም፡፡ እንደውም ብዙ እገዛ ሳይኖራቸው ይህን ያህል መሥራታቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል፡፡ በሌላው አገር ዳኞች ልምምድ የሚያደርጉበት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንኳ ሳይቀር ይፈቀድላቸዋል፤ እዚህ አገር ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ዳኞች በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጭ ምን አይነት ተጽዕኖዎች ይደርስባቸዋል?
አቶ ሚካኤል፦ አብዛኛውን ጊዜ ህግን በመተርጎም ሂደት ሜዳ ላይ ችግሮች ይደርሳሉ፡፡ ከሥነ ምግባር ውጭ የሚሆኑ ስፖርተኞች በዳኞች ላይ ከድብደባ ጀምሮ ሥነ ልቦናን እስከ መጉዳት የሚያደርስ ጸያፍ ተግባራትን ሲከውኑ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ውጭ አገሪቷ በእግር ኳስ ዳኝነቱ የምትመራበት ህግ እያላት ህጉ በአግባቡ ሳይተረጎም ሲቀርም ተጎጂው ዳኛ ነው፡፡ ችግሩ በዋናው ፕሪሚየር ሊግ ለሚዲያ ተጋላጭ በመሆኑና ብዙ ሰው የማየት እድሉን ስላገኘ እንጂ፤ ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሉ ከስር ባሉ ሊጎች ላይ ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡
ከፍተኛ ሊግ ላይ የሚያጫውቱ ዳኞች ተደብድበው ለኩላሊት ህመም እስከመዳረግ የደረሱ አሉ፡፡ ብሄራዊ ሊግ ላይ የሚያጫውቱ ዳኞች የተለያዩ ማስፈራሪያና ዛቻ የደረሰባቸውም አሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን መመልከት የተቻለው ሁሉም ተጫዋች ሥርዓት አልባ እንዳልሆኑ፣ ከደጋፊዎችም ጥቂቶች እንጂ አብዛኞቹ ስፖርቱን በጨዋነት የሚደግፉ እንዳሉና እንደ ማሳያም ሊሆን የሚችለው አልፎ አልፎ ከሥርዓት ውጭ የሆኑ ተጫዋቾች ዳኛው ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲቃጡ ሜዳ ድረስ በመዝለቅ የሚከላከሉና ምሳሌ የሚሆኑ ደጋፊዎችም አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፦ የእግር ኳስን ህግ ከመተርጎም አንፃር ምን ክፍተት ይታያል?
አቶ ሚካኤል፦ ቅጣት ሲቀመጥ የፍትህ አካላት አብረው ነው መስራት ያለባቸው፡፡ ዳኞች ተጽዕኖ እየደረሰባቸው ያሉት በፍትህ አሰጣጥ ጉድለት ነው፡፡ ከተቀመጠው ደንብ ውጭ ሌላ ህግ በመጣስ ኮሚቴ ሲዋቀርና ከዳኞች ውሳኔ ውጭ የሆኑትን ውሳኔዎች ሲያስተላልፍም በብዙ መልኩ ዳኞችን ዋጋ ያስከፈለ ጉዳይ ነው፡፡ ህጉ በአግባቡ ቢተረጎም ኖሮ ግን ሜዳ ላይ ተጫዋቾችም ሆኑ አሰልጣኞች ስፖርቱን ሊያደፈርሱ ከሚችሉ ፀብ አጫሪ ክስተቶች ራሳቸውን ይቆጥቡ ነበር፡፡
የአውሮፓ አገራትን ተሞክሮ መመልከት እንደሚቻለው ህጋቸው ጠንካራ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በአግባብ መተርጎም መቻሉ ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡ ህጋቸው ጥብቅ ስለሆነ ዳኛ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ አሰልጣኝ፣ ደጋፊው፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ባለሙያዎች የመተቸት መብት አላቸው፡፡ ትችቱም ሲቀርብ የተቀመጠ ህግ በመኖሩና ህግን ጥሶ የተገኘ አካል በህግ ይቀጣል የሚል ደንብ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ ሲተረጎምና ሥራ ላይ ሲውል አይታይም፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው ህግ አንድ አጥፊ አካል መጀመሪያ የሚቀጣው በዲሲፕሊን ነው፡፡ አንድ የሚቀጣ አካል ከስድስት ጨዋታ እስከ እድሜ ልክ ምንም አይነት ጨዋታ እንዳያደርግ ሲቀጣና የተቀጣበትን ግማሽ ያህል ጊዜ ሲያደርስ ይቅርታ መጠየቅ እንደሚችልና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴውም ይቅርታ ሊያደርግለት እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ ከዚያ በታች ባለው ገደብ በቁጥርም ሆነ በገንዘብ የተቀጣ ግን ምህረት የለውም ነው የሚለው፡፡ ይህ ህግ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ሲጣስ ነው የሚታየው፡፡ ለምሳሌ ጥፋት ያጠፋን ተጫዋች ዳኞች በቀይ ሲያስወጡ ተጫዋቹ አምስት ሺህ ብር ወይም አራት ጨዋታ ሊሆን ይችላል የሚቀጣው፡፡ እንደ ፊፋ ህግ ተጫዋቹ የተጣለበትን ቅጣት ግዴታ መቀበል አለበት፡፡ ይሁንና ይህ ተጫዋች ቅጣቱን ሳይጨርስ በሁለተኛው ጨዋታ ሜዳ ገብቶ ሲጫወት ይታያል፡፡ ምህረት አድራጊው አካልም አይታወቅም፡፡ ይህ ልምድ እያደገ በመምጣቱም ነው ህጎች ተጥሰው ውጥረት ውስጥ ስንገባ የሚታየው፡፡
ክለቦችም ነጥባቸው እስከመቀነስ የሚደያርስና በዝግ ስታዲየም እንዲጫወቱ የሚያደርግ ቅጣት የተላለፈባቸው ጊዜ ነበር፡፡ ነገር ግን ውሳኔዎች ተሽረው ይታያሉ፡፡ እግር ኳሱን የሚያስተዳድረው አካል በፈጠረው ክፍተት ችግሮች እየሰፉ በዳኞች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይፈጠራል፡፡ ሜዳ ላይ ቅጣት ሲሰጡ ‹‹ዛሬ ብትቀጣኝ ነገ እገባለሁ›› የሚል ስፖርተኛ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ዳኞችን ጫና ላይ የጣለ ችግር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ ለሚከሰተው ችግር ኃላፊነቱን ማነው የሚወስደው?
አቶ ሚካኤል፦ ሁሉም የየድርሻውን መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ቁጥሩ ይነስ እንጂ ዳኞችም ጥፋቱ ላይ ይኖራሉ፤ አሰልጣኞች፣ ክለቦች፣ የፌዴሬሽን አመራሩ፣ ኃላፊነትን መውሰድ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ችግሩ በዳኞች ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ አንዳንድ ክለቦች የአቅማቸውን ማነስ ወደ ዳኛ ጥፋት ያመጡታል፡፡ ይህ ጥፋተኝነትን ወደ አንድ አካል ያመዘነ ድምዳሜ ስፖርቱን ያዳክመዋል፡፡
ብዙ ጊዜ የሚታዩ የጣልቃ ገብነቶች አሉ፡፡ ክለቦች ይህ ዳኛ አይመደብብኝ ይላሉ፤ የውድድር አመራርም እከሌ የሚባል ዳኛ አትመድብ በማለት አስተያየት የሚሰጥበት አጋጣሚ አለ፡፡ ዳኞችን ለመገምገም የተቀመጠው አካል እስካለ ድረስ በአሰራሮች ላይ ጣልቃ ገብነት ፈጽሞ መታየት የለበትም፡፡ በተለይ የምርጫ ሰሞን ተወዳጅነትን ለማትረፍ በማይመለ ከታቸው ነገር ጣልቃ የሚገቡ አሉ፡፡ ጨዋታዎች በሚካሄዱበት ወቅት ለተፈጠሩት ክስተቶች ጨዋታ ማቋረጥ ወይም አለማቋረጥ የዳኛ ስልጣን ነው፡፡ በዚህ ሂደትም እጃቸውን ለማስገባት የሚጥሩ አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮሚሽነሮች በሚመድቧቸው አካላት ተጽዕኖ ስለሚፈጠርባቸው ዳኛ ተደበደብኩኝ አላጫውትም ሲል በግድ አጫውት በማለት ያስገድዳሉ፡፡ ውሳኔ በሚሰጠው አካል አሰራር ውስጥ ገብቶ ውሳኔ መስጠት ወዳልተገባ አቅጣጫ ይወስዳል፡፡ የግለሰቦች ጣልቃ ገብነት ስፖርቱን እንዲዳከም ካደረጉት ምክንያች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ የዳኞች ውሳኔ ፍፁም ትክክል ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ሚካኤል፦ በእርግጥ ዳኞች የሰው ልጆች በመሆናቸው ስህተቶች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ እግር ኳስን ያለ ስህተት መዳኘትም አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት አዳማ ከነማና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚጫወቱበት ወቅት ቢጫውንና ቀዩን ካርድ በደረት ኪሶቼ ላይ አቀያይሬ በማስቀመጤ ቢጫ ለሚገባው ተጫዋች በስህተት ቀይ አውጥቼ ሰጠሁት፡፡ በኋላም ተጫዋቹ ሜዳውን ጥሎ ሊወጣ ሲል ግባ አልኩት፡፡ ቀይ ካርድ እንደሰጠሁት ነገረኝ፤ በስህተት ያደረግኩት መሆኔን ነግሬው እንዲጫወት አደረግኩት፣ በወቅቱ ስታዲየሙ ውስጥ የነበረው ደጋፊ በሙሉ ለተወሱ ደቂቃዎች መነጋጋሪያ አድርገውኝ ነበር፡፡ አንዳንድ ስህተቶች አዝናኝም ሆነው ያልፋሉ፡፡ ነገር ግን የገባው ጎል ትክክል ሆኖ መሻር አሊያም አግባብ ያልሆነ ጎል ማጽደቅ ዋጋ የሚያስከፍል ስህተት ነው፡፡ ስህተቶችን ላለመስራት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚወሰድ ግን መታወቅ አለበት፡፡
ዳኞችን በእኩል ደረጃ የሚያስኬድ የስልጠና አሰጣጥ ሥርዓቱ ክፍተት ስላለበት የዳኞች አቅም ላይ የሚያሳርፈው አንዳች ተጽዕኖ አለው፡፡ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማህበር ለሁሉም የሚሰጠው የኢንስትራክተሮች ስልጠና አንድ አይነት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን ስልጠናዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በጨዋታ ወቅት አንዳንድ ረዳት ዳኞች ባንዲራ ዘርግተው ይገባሉ፤ ሌሎች ደግሞ ይህን አይቀበሉም፡፡ ይህንን ያመጣው በዚህ ዘርፍ የሚሰጠው ትምህርት ቋሚና ሁሉን አንድ ያደረገ ባለመሆኑ ነው፡፡ ይህ በሜዳ ላይም ሲተገበር ይታያል፡፡ ስለዚህ የሚሰጡ ትምህርቶች ወደ አንድ መምጣት ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ ህግ ተርጓሚው አካል ሲያስተምር የዓለም አቀፉን ልምድ ወስዶ ነው ግንዛቤ መስጠት ያለበት፡፡
በዳኝነት የመለኪያ መስፈርት ዳኞች የሚጠበቅባቸውን ያህል ካልሰሩና ካጠፉ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ሂደት የኢትዮጵያውያን ዳኞች የጎላ ችግር ባኖርም ጥፋተኞች ካስባለንም በዳኞች የሚፈጸም አንዱ ትልቅ ስህተት ግን ተጫዋቾች ላይ የበዛ እርምጃ አለመውሰዳችን ነው፡፡ ይህ በብሄራዊ ቡድናችንም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያደርጉት ውድድሮች ላይ ንትርክ ውስጥ በመግባት ቅጣት ሲተላለፍባቸው ይስተዋላል፡፡ ይህም የሆነው እዚህ የሚወሰደው ውሳኔ አናሳ በመሆኑና ብዙ ጊዜ በልምምጥ ስለሚታለፉ ነው፡፡ ይህንንም ማስተካከል ከዳኞች የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፦ የዳኞች ማህበር ዳኞች ላይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ምን ምን ጉዳዮችን አከናውኗል? ከፌዴሬሽን የተገኘው ግብረ መልስ ምን ይመስላል
አቶ ሚካኤል፦ ይህ ማህበር ከተመሰረተ ሰባት ዓመት ሆኖታል፡፡ በጉዞውም በሚከሰቱት ችግሮች ዙሪያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የደብዳቤ ምልልሶችን ጨምሮ ብዙ ጊዜ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በተለይ ህጎች አይፍረሱ፤ በትክክል ይተርጎሙ፣ ዳኞ በሚወስኑት ውሳኔ ላይ ጣልቃ ገብነት አይኑር በሚሉ ጉዳዮች መፍትሄ እስከሚገኝ ድረስ ብዙ ርቀቶችን ሄደንበታል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ሳይስተካከል እንዲሁ በመጓተት ሂደት ውስጥ ሆነ፡፡ ችግሩ ስር እየሰደደ በመምጣት በቅርብ ጊዜ የምናስታውሰውን ፍጹም ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጠና ዳኞችን ለድብደባ የጋበዘ ክስተት እንዲፈጠር አደረገ፡፡ የአገሪቱም የእግር ኳስ ስፖርት በመልካም ስም እንዳይነሳ ምክንያት እየሆነ መጥቷል፡፡
የሜዳ ላይ ችግሮች መፍትሄ እስከሚያገኙ ውድድር እንዲቋረጥ በጠቅላላ ጉባኤው ተነጋግር ወስኖ ነበር፡፡ ይህም አድማ ሳይሆን ቆም ብሎ በማሰብና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ነበር፡፡ ከዚህ ውጭ ችግሮች እንዲቃለሉ በዳኞች ማህበር በኩል ቅድመ ሁኔታዎችም ተቀምጠዋል፡፡ ከኢንሹራንስ፣ ከለላ ከመስጠት፣ ከአውሮፕላን ቲኬት፣ ወንጀለኞችን ለህግ ከማቅረብ፣ ትምህርትና ስልጠና ከማግኘት አንጻር ጥያቄዎችን በማቅረብ ለጊዜው መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡
በተለይ የኢንሹራንስ ጉዳይ ከምንም በላይ አስቸኳይ እንዲሆን ስለታሰበ የመፍትሄ ምላሽ ተሠጥቶበታል፡፡ በዚህም መሰረት በዚህኛው አመት 30 ሰዎች ኢንሹራንስ እንዲያገኙ፣ ለሚቀጥለው ዓመት ደግሞ 461 ዳኞችና 160 ኮሚሽነሮች ኢንሹራንስ እንዲገቡና ይህ ካልሆነ ግን ውድድሩ እንደማይጀመር በደብዳቤ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በትምህርትና ስልጠናው ላይም በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈጽሟል፡፡ ከለላ በማግኘት በኩል ያለው ሂደትም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን ማስከበር ደግሞ ጥቅሙ የዳኞች ብቻ ሳይሆን የጋራ ነው፡፡ የዳኞች ማህበር እንዲወሰንና ስምምነት ላይ እንዲደረሱ የሚሻቸው ጉዳዮች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ በቀጣይ ፌዴሬሽኑ ከሚመሩ አካላት ጋር እየተነጋገርን ጥያቄዎችም እያቀረብን መልስ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፦ ችግሮችን በማረም ረገድ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት?
አቶ ሚካኤል፦ ሜዳ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች እየተባባሱ ከሄዱ የሰው ህይወትም ሊጠፋ ይችላል፡፡ ስሜታዊ በመሆኑ የሚወሰዱ እርምጃዎች ከባድ ጉዳት ያስከትላሉ፡፡ አሁን ላይ አገሪቷ በተረጋጋ ችበት ሰአት የእግር ኳስ ስፖርቱም ተረጋግቶ መከናወን አለበት፡፡ ስፖርትን ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ ነጻ ማድረግ አለብን፡፡ ብሄር ተኮር አመለካከቶችም መጽዳት አለባቸው፡፡ በውሳኔዎች ላይ ጣልቃ የሚገቡ አካላት ከተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ዳኞችን በስፋት ዋጋ እያስከፈለ ያለው ይህ በመሆኑ፡፡ ፌዴሬሽኑ ጾታዊ ስብጥርን መሰረት ያደረገ የአመራር ሥርዓትም ሊኖረው ይገባል፡፡ ዳኝነት ፍጹማዊነት እንዳልሆነ በመገንዘብ ዳኞች ጥፋት ሲያጠፉ ስለሚጠየቁ ይህንን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ በጥቃቅን ስህተት ችግሩን አጉልቶ በማሳየት ባላደገው ስፖርት ላይ መርዝ የመጨመር አባዜ እንዲቀረፍ ፌዴሬሽኑና በስሩ ያሉት አካላት ዘወትራዊ ምክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሚካኤል፦ እኔም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

አዲሱ ገረመው

Published in ስፖርት

በአጋጣሚም ይሁን ታስቦበት … ግንቦት በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ወር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ታዋቂ ልጆቿን ወልዳለች፤ ወደማይቀረው ዓለምም ሸኝታለች፤ መሪዎቿን ወደ ሥልጣን አምጥታለች፤ ከሥልጣናቸው ሽራለች፤ አስከፊ ጦርነቶችን አስተናግ ዳለች፤ ከነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች በተጨማሪ ግንቦት ያልተለመዱ ክስተቶች የተስተናገዱበት ወርም ነው፡፡ ታዲያ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ልዩ ቁርኝት ያለውን ይህን ወር ከመሰናበታችን በፊት ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ካስተናገደቻቸው ታሪካዊ ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክር፡፡
ግንቦት የልደት ወር ነው፡፡ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2004 ዓ.ም መገባደጃ ድረስ በመጀመሪያ በፕሬዚዳንትነት፣ በመቀጠልም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ኢትዮጵያን የመሩት አቶ መለስ ዜናዊ የተወለዱት በግንቦት ወር ነው፡፡ አቶ መለስ ኢትዮጵያ አሁን ያለውን የፌዴራላዊ አስተዳደር ሥርዓት እንድትከተልና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከሚያስመዘግቡ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ የአንበሳውን ድርሻ የያዙ ሰው ናቸው፡፡
የገናናው የሸዋ ንጉሥ የንጉሥ ሳህለሥላሴ የልጅ ልጅ፣ የታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ የአክስት ልጅ እንዲሁም የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አባት የሆኑት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተወለዱትም በግንቦት የመጀመሪያው ቀን በ1844 ዓ.ም ነበር፡፡ ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የሐረርጌን ግዛት በማቅናትና በሚገባ በማስተዳደር ለንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) ሀገር የማቅናት ተግባር ብርቱ አጋዥ የሆኑ ሰው ነበሩ፡፡ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ተወካይ በመሆን ሁለት ጊዜ ወደ አውሮፓ ሀገራት የተጓዙት ልዑል ራስ መኮንን፣ ወደ ኢጣሊያ በሄዱ ጊዜም የኢጣሊያ ጋዜጦች የውጫሌ ውልን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ጥገኝነት ስር እንዳለች አድርገው የሚጽፉትን ጽሑፍ በመመልከታቸው ተቃውሟቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የውሉን መበላሸት ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ አሳውቀው ውሉ በይፋ እንዲሰረዝ አድርገዋል።
የውጫሌ ውል ያስከተለው የትርጉም ለውጥ መፍትሄው ጦርነት ሲሆንም ልዑል ራስ መኮንን ሠራዊታቸውን ይዘው ከአምባላጌ እስከ አድዋ በተደረጉት ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ጀምረው በወታደርነት፣ በጦር መሪነት፣ በግዛት አስተዳዳሪነትና በዲፕሎማትነት በፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራት ምክንያት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የዙፋናቸው ወራሽ ሊያደርጓቸው ያስቡ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡
በግንቦት ወር መፈንቅለ መንግሥት የተሞከረ ባቸውና በግንቦት ወር አገር ጥለው የሸሹት የደርግ ሊቀመንበር ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም የተወለዱት በግንቦት ወር ነው፡፡
ግንቦት የእረፍት/ሞት ወርም ነው፡፡ በቀዶ ጥገና ህክምና ዘርፍ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሐኪም የሆኑት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ያረፉት በግንቦት ወር 1991 ዓ.ም ነው፡፡ በታዋቂ የውጭ አገራት የሕክምና ሳይንስ ትምህርት ቤቶች የተማሩት ፕሮፌሰር አስራት «የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ሥልጣንን አልፈልግም፤ የተማርኩት ሐኪም ሆኜ አገሬን ላገለግል ነው» በማለት ወገናቸውን አገልግለዋል፡፡
ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የህክምና ማሰልጠኛ እንዲከፈት በተደጋጋሚ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምና ትምህርት ቤትን እውን አደረጉ፡፡ የሕክምና ት/ቤቱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዲን ሆኑ፡፡ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋምም የቴክኒክ ኮሚቴውን የመሩት እርሳቸው ነበሩ፡፡
ፕሮፌሰር ዶክተር አስራት በወቅቱ በተደጋጋሚ ወደ ዘመቻ የተላኩ ሲሆን፤ የሄዱባቸውንም ዘመቻዎች በብቃትና በክብር ለመወጣት በቅተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በ1968 እና በ1969 ዓ.ም በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት በቃኘው ሆስፒታል፣ አስመራ፤ በ1970 ዓ.ም በራዛ ዘመቻ በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት እና ቡድን መሪነት በመቐለ ሆስፒታል፤ እንዲሁም በሰኔ 1971 ዓ.ም በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት ምጽዋ ዘምተው ግዳጃቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡
ፕሮፌሰር አስራት በህክምናው ዘርፍም «አስራት የተባለ ጸበል ፈልቋል» እስከመባል የደረሰ አንቱታን ያተረፉ ብቁ ሐኪም ነበሩ፡፡ የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴም የግል ሐኪም ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር ዶክተር አስራት በመንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች ይደርስባቸው የነበረውን ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው ሀገራቸውን ሳይለቁ ሕዝባቸውን ሲያገለግሉ የቆዩ አንጋፋ ባለሙያ ናቸው፡፡
ገናናውና መናኙ የታላቋ አክሱም ንጉሥ አፄ ካሌብ ያረፉት በግንቦት ወር በ20ኛው ቀን ነበር፡፡ አፄ ካሌብ ከአክሱምና አካባቢው አልፈው ቀይ ባሕርን ተሻግረው የደቡብ አረቢያ ሕዝቦችን ያስገበሩ ታላቅ ንጉሥ ነበሩ፡፡ ከአይሁዳዊው ንጉሥ ፊንሐስ ጋር ያደረጉትን ጦርነት በድል ካጠናቀቁ በኋላም አባ ጰንጠሌዎን ገዳም ገብተው መነኑ፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱት እንስቶች መካከል አንዷ የሆኑት እቴጌ ምንትዋብ ያረፉትም በግንቦት ወር ነው፡፡ የአፄ በካፋ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ምንትዋብ፣ ጎንደር የኢትዮጵያ ነገሥታት ማዕከል በነበረችበት ወቅት የነበራቸው ተፅዕኖ ከፍ ያለ እንደነበር ታሪክ ያሳያል፡፡ ባለቤታቸው አፄ በካፋ ከሞቱ በኋላ በተከታታይ በነገሡት በልጃቸው ዳግማዊ አፄ ኢያሱ እንዲሁም በአፄ ኢዮአስ ዘመነ መንግሥታት ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ ከፖለቲካ ተሳትፏቸው በተጨማሪም ዛሬ ድረስ በበርካታ ጎብኚዎች የሚጎበኙ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንፀዋል፡፡ ከዚሁ ከመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ሳንወጣ አፄ ሠይፈአርዕድ እና አፄ እስክንድር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በግንቦት ወር ነው፡፡
የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ባለቤት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ ያረፉትም በግንቦት ወር 1860 ዓ.ም ነው፡፡ እቴጌ ጥሩወርቅ የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም በደጃዝማች ካሣ ኃይሉ (በኋላ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ) ደረስጌ ላይ የተሸነፉት የደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ልጅ ናቸው፡፡ እቴጌዋ ያረፉትም ከባለቤታቸው ሞት በኋላ ከልጃቸው ከልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ጋር ወደ እንግሊዝ ሲሄዱ ነው፡፡
አንጋፋውና ዝነኛው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ይቺን ዓለም በሞት የተለያት ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም ነው፡፡ የጳውሎስ ኞኞ ስም ሲነሳ ወደአብዛኛው ሰው አዕምሮ የሚመጣው በቀለም ትምህርት ብዙም ሳይገፋ በድፍን ኢትዮጵያ ዝነኛና ተወዳጅ ለመሆን ያበቃው የጋዜጠኝነት ሥራው ነው፡፡ በዘመናዊ ትምህርት አራተኛ ክፍልን ያልተሻገረው ጳውሎስ፣ በተፈጥሮ የታደለው የማንበብ፣ የመጠየቅና የመመራመር ተሰጥኦ በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፎለታል፡፡ በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ሲሰራ «ጋዜጠኝነትስ እንደጳውሎስ!» የተባለለት ይህ ሰው፣ በርካታ መጽሐፍትንና ቲያትሮችንም ለአንባቢያን አበርክቷል፡፡ «ሁሉን እወቅ፤ የሚሆንህን ያዝ» የሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት በውስጡ ሰርፆ እንደነበር በተደጋጋሚ ሲናገር ነበር፡፡ መንገድ ላይ ወድቃ የሚያገኛትን ቁራጭ ወረቀት ሁሉ በማንሳት ማንበብ ልማዱ የነበረው ይህ አስደናቂ ሰው፣ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችንም ይናገር ነበር፡፡
ጳውሎስ የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር በተባ ብዕሩ ሞግቷል፡፡ ይህ ተጋድሎውም ለማስፈራሪያ፣ ለዛቻና ለእንግልት ዳርጎታል፡፡ ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም፤ ብዙ የሙያ ዓይነቶችን ከባለሙያዎቹ ባላነሰ መልኩ ይከውን ነበር ይባላል፡፡ ግልፅነት፣ ድፍረት፣ ለወገንደራ ሽነትና ጨዋነትም የጳውሎስ መገለጫዎች እንደነበሩ ብዙዎች ምስክር ናቸው፡፡ ባለውለታችንና «የፊደል ገበታ አባት» ቀኛዝማች ተሥፋ ገብረሥላሴ ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም የመጨረሻ ቀናቸው ነበረች፡፡
ግንቦት የንግሥናና የሹመት ወር ነው፡፡ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ወራሻቸው የልጅ ልጃቸው ልጅ ኢያሱ ሚካኤል መሆኑን በአዋጅ ያሳወቁት ግንቦት በገባ በ10ኛው ቀን በ1901 ዓ.ም ነው፡፡ የልጅ ኢያሱ አባት ራስ ሚካኤል አሊ ደግሞ «ንጉሠ ወሎ ወትግራይ» ተብለው የነገሱት በግንቦት ወር መገባደጃ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) አዲስ አበባን የተቆጣጠረውና ሥልጣን የያዘውም በግንቦት ወር በ20ኛው ቀን በ1983 ዓ.ም ነው፡፡
ግንቦት የሽረት ወርም ነው፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም አገር ጥለው የሄዱትና ደርግ የወደቀውም በግንቦት ነው፡፡ ግንቦት ለብዙ የጎንደር ነገሥታት የሥልጣናቸው ማብቂያ እንደነበርም በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
ደም አፋሳሽ ጦርነቶች የታዩበት ግንቦት፣ የንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) እና የንጉሥ ተክለሃይማኖት ጦር እምባቦ ላይ በግንቦት የመጨረሻው ቀን ከባድ ውጊያ አድርጓል፡፡ የደጋማው ክርስቲያን ነገሥታት እና የግራኝ አሕመድ ጦርነቶች የከፉት በግንቦት ወር ነበር፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ዘርፎ መነኮሳቱን በግፍ የጨፈጨፈውም በዚሁ በግንቦት ወር ነው፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት) እና የአንጋፋው «አዲስ ዘመን» ጋዜጣ ምስረታ የተከናወ ነው በግንቦት ወር ነው፡፡ እሥራኤል ቤተ-እሥራኤ ላውያንን ከኢትዮጵያ ወደ እሥራኤል ለመውሰድ «ዘመቻ ሰለሞን (Operation Solomon)»ን ያካሄደችው በዚሁ በግንቦት ወር ነው፡፡ በዘመቻ ሰለሞን 14ሺ325 ቤተ-እሥራኤላውያን በ36 ሰዓታት ውስጥ፣ በ35 አውሮፕላኖች ከኢትዮጵያ ወደ እሥራኤል ተወስደዋል፡፡
ፎቶ ግራፍና ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያውያንም የተዋወቁት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ግንቦት 13 ቀን 1875 ዓ.ም በተነሱት የመጀመሪያ ፎቷቸው ነው፡፡
በአጠቃላይ ግንቦት ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ከተቆራኙ ወራት መካከል አንዱ ነው፡፡ ግንቦት እና ኢትዮጵያ የቀን ምልኪያ አላቸው የሚያስብል ትስስር አላቸው፡፡

አንተነህ ቸሬ

Published in መዝናኛ

የቲቢ በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው፣ከሰው ወደ እንስሳት እንደሚተላለፍ ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? የምናውቅስ ምን ያህል ጥንቃቄ እናደርጋለን? ሰዎች በቲቢ በሽታ የተጠቃ እንስሳ ተዋጽኦ መጠቀም እንደሌለባቸው ይመከራል፡፡ በሽታው ከእንስሳት ወደ ሰው ወይም ከሰው ወደ እንስሳት በመተላለፍ ከሚያስከትለው ጉዳት በተጨማሪ በእንስሳት ላይ መከሰቱ በሀገር ኢኮኖሚ ላይም ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በእንስሳት የሳምባ በሽታ ላይ ምርምር ያደረጉት ዶክተር አቅናው ዋቅጋሪ ያስረዳሉ፡፡
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ህክምና ትምህርት ክፍል ውስጥ በመምህርነት በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶክተር አቅናው እንዳስረዱት የሳምባ በሽታ እንስሳቱን በማክሳትና የምግብ ፍላጎት እንዳይኖራቸው በማድረግ ጤናቸውን ከመጉዳቱ በተጨማሪ ከሀገር ውጭ የሚላከውን የሥጋ ምርት ገበያ ያሳጣል፡፡
እንስሳቱ ተመርምረው ጤንነታቸው ሳይረጋገጥ ታርደው ሥጋቸው ለገበያ የሚቀርብ ከሆነ ሁለት ዓይነት ጉዳት ያስከትላል፡፡ አንዱ በሽታውን ወደ ሰው በማስተላለፍ የሚያስከትለው ጉዳት ሲሆን፣ሌላው ደግሞ ጤንነቱ ያልተረጋገጠ የሥጋ ምርት መላኩ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያሳጣል፡፡ ምርቱን የሚቀበሉ ሀገራት ችግሩን ከደረሱበት ምርቱን ዳግም ለመቀበል ፈቃደኛ አይሆኑም፤ የሀገር ገፅታንም ያበላሻል፡፡
ዶክተር አቅናው ችግሩ ምን ያህል እንደሆነ በአንድ ወቅት የእንስሳት እርድ በሚከናወንበት ቄራ ውስጥ ለእርድ በተዘጋጁ በሬዎች ላይ ምርምር አካሂደዋል፡፡ ምርምራቸው ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አንዱ ለእርድ የተዘጋጁ በሬዎች የጤና ሁኔታ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጠው ለማሳየት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ የቆየና አዲስ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ በወቅቱ ለእርድ ከተዘጋጁት በሬዎች መካከል በስድስት መቶዎቹ ላይ ነበር ጥናቱን ያካሄዱት፡፡ ለምርምር ከተመረጡት ከብቶችም ከሳምባቸው፣ከአንጀትና ጭንቅላታቸው የተወሰደው ናሙና በቤተሙከራ ውስጥ በተለያዩ ሂደቶች አልፎ ነው ምርምሩ የተሠራው፡፡
ናሙናቸው ተወስዶ ምርምር ከተደረገባቸው ስድስት መቶ ከብቶች መካከልም አምስቱ በቲቢ በሽታ የተያዙ መሆናቸው ተለይቷል፡፡ በጥናት የተለዩት የእነዚህ ከብቶች ስጋም ጥቅም ላይ እንዳይውል ተደርጓል፡፡ የምርምር ግኝቱ ችግሮችን ለይቶ ማውጣት ብቻ ሳይሆን፣በሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስም በመታደግ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ችግሩን በምርምር በመለየት ሰዎችን መታደግ ቢቻልም ሥጋ ለተጠቃሚው የሚያቀርቡ ድርጅቶች ካሳ እንደሚያስፈልጋቸው ዶክተር አቅናው ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት የአንዳንድ ሀገሮች ቄራዎች ኪሳራ እንዳይደርስባቸው ካሣ ይከፍላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን እንዲህ ያለው አሠራር አለመለመዱንና ግንዛቤው እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ቄራዎች ድጋፍ ቢደረግላቸው ወይም ካሣ ቢከፈላቸው ኃላፊነት እንደሚሰማቸውና ጥንቃቄ እንደሚያደርጉም አመልክተዋል፡፡
ግንዛቤው በህብረተሰቡ ውስጥም መፈጠር አለበት ያሉት ዶክተር አቅናው ከብት ሲታመም ቶሎ ባርኮ መመገብ የተለመደ መሆኑንና ይህ ግን መቅረት ያለበት ልማድ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የታመመው ከብት ምናልባትም የቲቢ በሽታ ያለበት ሊሆን ስለሚችል ስጋውን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡የሳምባ በሽታ ካለባቸው ላሞች የሚገኝ የወተት ምርትንም መጠቀም እንደማይገባ መክረዋል፡፡
የምርምር ግኝቱ ጤንነቱ ያልተረጋገጠ የእርድ እንስሳ ለተጠቃሚ ማቅረብ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንደሚያስከትል ቢያሳይም ችግሩን በማስወገድ በኩል ዘለቄታ እንዲኖረው በሥጋ አቅራቢዎችም የእንስሳት ዘርፍ የሚከታተለው አካል ትኩረት ሊያደርግ ይገባል፡፡

 

 የመአዛማ ቅጠሎች መጭመቂያ መሣሪያ 

 

ቴክኖሎጂ ፈጠራ ብቻ ሳይሆን አስመስሎም በመሥራት መፍጠር እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ እንደ ሀገርም ቴክኖሎጂን ከሌሎች በመቅዳት ወይም በማላመድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍቻ እንዲሆን ይበረታታል፡፡ ከሌሎች በተቀዱ ቴክኖሎጂዎች በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡
በአሚዮ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ እና እርሻ መሣሪያዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰ የግል ኩባንያ ውስጥ በዲዛይን ሙያ የሚያገለግለው አቶ መልሀዝ አማን ቴክኖሎጂ በመቅዳት የተሠራው ሥራ ከፈጠራ እንደማይነጣጠል ይገልጻል፡፡ የሚቀዳው ቴክኖሎጂ ንድፈሃሳቡ/ሶፍትዌሩ/ መሆኑንና ይህን መሠረት አድርጎ አገልግሎት የሚሰጠውን መሣሪያ መሥራት ትልቅ ሥራ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
አቶ መልሀዝ በሚሠራበት ድርጅት ቴክኖሎጂ ተቀድቶ ስለተሠራው የመዓዛማ ቅጠሎች መሣሪያም እንዲህ አስረድቷል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በግለሰብም ሆነ በማህበርም ተደራጀተው ሊጠቀሙበት የሚያስችል ከመሆኑ በተጨማሪ ትልቅ ፋብሪካ አያስፈልገውም፡፡ በመኖሪያ ቤት ውስጥ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በከሰልና በጋዝ መጠቀም የሚያስችል ተደርጎ ነው የተሠራው፡፡ ለጉንፋን የባህርዛፍ ቅጠል ጨምቆ ለመጠቀም የፈለገ ሰው በዚህ መሣሪያ መጠቀም ይችላል፡፡ ሌላም መዓዛማ ቅጠሎችን ጨምቆ ጥቅም ላይ ለማዋል የፈለገ ሰው በቀላሉ ለመጠቀም ያስችለዋል፡፡ መሣሪያው ቢበላሽ የመለዋወጫ ዕቃ የሚያስፈልገው ባለመሆኑ በቀላሉ ተጠግኖ ሥራ ላይ ይውላል፡፡
አቶ መልሀዝ እንዳስረዳው መጭመቂያ መሣሪያውን በተለያየ መጠን መሥራት ይቻላል፡፡ በተቋሙ የተሠራው መሣሪያ እስከ አንድ ሺ ሊትር የመጭመቅ አቅም አለው፡፡ መሣሪያው ውሃና ቅጠል መያዣና ማቀዝቀዣ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በሦስቱም ክፍሎች በተገጠመለት የማስተላለፊያ ቱቦዎች አማካኝነት ጭማቂ ምርቱ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ መሣሪያው ከዝገት ነፃ በሆነ ብረት የሚሠራ ነው፡፡ መሣሪያው ጥቅም ላይ መዋሉንና የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ግለሰቦች እየተገለገሉበት መሆኑንም ተናግሯል፡፡ የሥራ ዕድልንም እንደሚፈጥርና በማህበር ተደራጅተው መዓዛማ ቅጠሎችን በመጭመቅ ለተጠቃሚው ቢያቀርቡ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አቶ መልሀዝ ገልጿል፡፡ «ዛሬ ለጉፋንፋን እየተባለ ባህርዛፍና የተለያዩ መዓዛማ ቅጠሎች ጭማቂ በጠርሙስ ታሽጎ ገበያ ላይ የሚሸጠው በዚህ መሣሪያ የተሠራ ነው፡፡ ጥሬ ሀብቱ እያለ መሣሪያ በማጣት እስከዛሬ መጠቀም አልተቻለም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በራስ ጥሬ ዕቃና መሣሪያ በሀገር ውስጥ መሠራት አለበት» ሲልም ገልጿል፡፡
እንኳንስ እንዲህ ለአነስተኛ አገልግሎት የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች ቀርቶ ትላልቅ የሚባሉትንም ቴክኖሎጂዎች ብዙ ቦታ ሳይወስዱ ሊሠሩ እንደሚችሉ በአንድ ወቅት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ተናግረዋል፡፡ አግዝፎ በማየት የቴክኖሎጂ ሥራን ጥቅም ላይ ከማዋል መቆጠብ እንደማያስፈልግ ነው ያስረዱት፡፡

ለምለም መንግሥቱ  

Published in ማህበራዊ

በዘመነ ሉላዊነት ዓለም አንድ መንደር ሆናለች፡፡ መስተጋበሯም ተጠናክሯል፡፡ አውሮፓ የተፈጸመ ድርጊት በሰከንዶች ውስጥ የትም አገር መድረሱ እሙን ነው፡፡ ሉላዊነቱ አገሮች ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብራቸው እንዲጎለብት አድርጓል፡፡ ሆኖም አንድ መንደር በሆነችው አፍሪካ ግን የዕርስ በዕርስ ትስስራቸው እስካሁንም ገና ዳዴ እያለ ያለና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን በርካቶች ያነሳሉ፡፡
የተጠናከረ ግንኙነት አለመኖሩ ደግሞ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩም ይገለፃል፡፡ ይህም ሀብት እያላቸው ዕርስ በዕርስ መጠቃቀም እየቻሉ ለኋላ ቀርነት ከመዳረጋቸው ባሻገር የጋራ ጠላታቸው የሆነውን ድህነት ማሸነፍ እንዲሳናቸውና ለርሃብ፣ ስደትና ለእርስ በእርስ ጦርነት ሲዳረጉም ይስተዋላል፡፡
የአፍሪካ አገሮች እርስ በእርስ ያላቸውን ትስስር ለማጎልበትና የጠነከረ ኢኮኖሚ ለመገንባት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ነፃ ማድረግ እንዳለባቸው የአፍሪካ ሕብረት በርካታ ጊዜ ገልጿል፡፡ ሕብረቱ ለጠንካራ ግንኙነት ይረዳሉ ብሎ ከሚወስዳቸው መፍትሄዎች መካከል የአህጉሪቱ ዜጎች ካለ ቪዛ በነፃነት ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አንዱ መፍትሄ መሆኑንም የአፍሪካ ሕብረት መግለፁ ይታወሳል፡፡
በዚህ ረገድ በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው 27ኛው የሕብረቱ ጉባኤ ድንበር አልባ አገሮችን በመፍጠር በአህጉሪቱ ዜጎች መካከል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በማጠናከር በ2063 አጀንዳውን ለማሳካት የአፍሪካ የጋራ ፓስፖርት ማዘጋጀት አንድ እርምጃ መሆኑን ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ ሲሸልስ ካለ ቪዛ እንቅስቃሴ ስትፈቅድ ጋና፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሞሪሽየስና የመሳሰሉት ወደ አገራቸው ሲገቡና ከወራት ቆይታ በኋላ ቪዛ የሚገኝበትን መንገድ አመቻችተዋል፡፡ በዚህም መሰረት 22 በመቶ የአፍሪካ አገሮች ካለ ቪዛ እንቅስቃሴ ሲፈቅዱ፣ 24 በመቶ ወደ አገራቸው ሲገቡ ቪዛ የሚያገኙበትን መንገድ አመቻችተዋል፡፡ 54 በመቶ አገሮች ደግሞ ወደ አገራቸው ለመንቀሳቀስ ቪዛ ይጠይቃሉ፡፡
የአንድ አገርን ቪዛን ለማግኘት በተለይም ወደ አደጉ አገሮች ለመሄድ አዳጋች ነው፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶችን ይጠይቃል፡፡ ወደ አገራቱ የሚሄድ ሰው ለምን እንደሚሄድ፣ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ፣ የት እንደሚያርፍና ዋስትና የሚሆን ነገር ሳይኖረው ፈቃድ አያገኝም፡፡ መስፈርቶችን ሳያሟላ ወደ አገሩ ማስገባት ከጥቅሙ ይልቅ የሚያስከትለው ችግር ከፍተኛ ነው የሚል እሳቤ መኖሩን አንዳንዶች ያነሳሉ፡፡በተቃራኒው ደግሞ ነፃ እንቅስቃሴ ሲኖር ለአገሮች ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለዜጎች እርስ በእርስ ትስስር ተጠሜታው የጎላ መሆኑንም የሚገልፁ አሉ፡፡
ሰሞኑን «አፍሪካን ኒውስ» እና «ኦልአፍሪካ» ባስነበቡት ዘገባ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ከሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር ባደረጉት ውይይት «ኢትዮጵያ የሩዋንዳን ልምድ በመውሰድ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሁሉም አፍሪካዊ ኢትዮጵያን ካለ ቪዛ እንዲጎበኙ ይደረጋል፡፡» ማለታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ዘገባው እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አገሪቱ በቅርብ የሩዋንዳን ተሞክሮ በመውሰድ አፍሪካዊያንና ካለ ቪዛ የሚንቀሳቀሱበት መንገድ የሚመቻች መሆኑንና ፖሊሲው ለምስራቅ አፍሪካ አገሮች እንዲሁም ለአፍሪካ ጎብኝዎች ክፍት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ይህም የህዝቦችን እንቅስቃሴ ነፃ በማድረግ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲያድግ ይረዳል ብለዋል፡፡
ዕቅዱ ይፋ የተደረገው የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በኢትዮጵያ ለሦስት ቀናት በነበራቸው የጉብኝት ቆይታ ወቅት መሆኑን ዘገባው አስታውሶ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ዕቅድ አለመገለፁን አስታውቋል፡፡ ቪዛ የመስጠት አሠራር በርካታ የአፍሪካ አገሮች እየተገበሩት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለፃቸውንና የአፍሪካ ሕበረት 2063 አጀንዳን ተግባራዊ ለማድረግና የዜጎችን እንቅሰቃሴ ለማሳለጥ በራቸውን ክፍት ማድረግ እንደሚገባቸው በአጽንኦት መናገራቸውን አክሏል፡፡
የአፍሪካ ቪዛ ግልፅነት እ.አ.አ 2017 ሪፖርት የህዝቦች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ለአፍሪካ ህዝብ ታሪክ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት፣ እንቅስቃሴዎች ንግድን፣ ኢንቨስትመንትን፣ ፈጠራንና የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማሳደግ እንደሚረዱ ይህም ለንግድ፣ ለትምህርት፣ ለጉብኝትና ለተለያዩ ሥራዎች የሚንቀሳሰሱ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ድንበርን በመዝጋት የሚገኙ ጠቀሜታዎች እንዳሉ ሁሉ ክፍት ማድረግም ለአገር ዕድገትና ብልፅግና የራሱ ጠቀሜታ እንዳለው ያብራራል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት 2063 አጀንዳ የአፍሪካን ህዳሴ ለማረጋገጥ በፓን አፍሪካኒዝም ሃሳብ የተሳሰረና ግንኙነቷ የተጠናከረ አህጉር መፍጠር እንደሚያ ስፈልግ፤ አፍሪካ ለህዝቦቿ ነፃም የሕብረቱ አባል አገሮች ለሁሉም የአፍሪካ ፓስፖርት ለያዙ ዜጎች ከሚደርሱበት ቀን ጀምሮ ለ30 ቀናት የሚቆይ ቪዛ መስጠት አለባቸው ሲል ያስቀምጣል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን የሌሎች አፍሪካ አገር ዜጎች ካለ ቪዛ በኢትዮጵያ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ምን ጠቀሜታና ጉዳት አለው? በሚለው ሃሳብ ላይ ምሁራንን አነጋግረናል፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር እና የስትራቴጂ ጥናት ዳይሬክተር መረሳ ፀሐይ እንደሚሉት፤ በምስራቅ አፍሪካና በመላው አፍሪካ ያሉ ህዝቦች ካለ ቪዛ ወደ አገሪቱ እንዲገቡ መደረጉ ንግድና ኢንቨስትመንትን እንደሚያቀላጠፍ ግልጽ ነው፡፡ ወደ አገሪቱ ለሚገቡ ዜጎችም ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ካለምንም ውጣ ውረድና እንግልት በቀላሉ መግባት እንዲችሉ ስለሚያደርግ፡፡ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ሊያሳድገውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተቀባይነት ከፍ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሆኖም በጥንቃቄ ካልተያዘ ዋጋ ሊያስከፍልና ብዙ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለው የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ነባራዊ ሁኔታ አስጊ ነው፡፡ ለአብነት በሶማሊያ ከጫፍ እስከ ጫፍ አገሪቱን በአግባቡ መምራት የሚችል መንግሥት በሌለበት፣ ኬንያም አብዛኛውን ጊዜ በአሸባሪዎችና አክራሪዎች እየታመሰች በምትገኝበት በዚህ ወቅት፣ ኤርትራም በብዙ ችግሮች ተተብትባ ዜጎቻቸው ካለ ቪዛ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፍቀድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ «ሽብርተኞችና አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች በቀላሉ የሚገቡበት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሊበራከትና በአገር ውስጥ አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በተለይ አገሪቱ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እንደመገኘቷ ሽብርተኝነት ያሰጋታል፡፡ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ አገሪቱ ከምትችለው በላይ የሌላ አገር ዜጎች ሲገቡ ከተማ ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት ሊያስከትል ይችላል፡፡» በማለትም ሥጋታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የምትገኘው በችግሮች በተከበበው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በመሆኗ ሥጋት ይፈጥራል፡፡ ለአብነት ኤርትራዊያን፣ ሶማሊያዊያን ወዘተ... እንደፈለጉ እንዲገቡና እንዲወጡ ፈቃድ ካገኙ ለበጎ እንደሚገቡ እንኳ ማረጋገጫ አይኖርም፡፡ ጉዳዩ በጥንቃቄ ካልታየ ብሄራዊ ደህንነት ላይ ችግር ያስከትላል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ስለፈለገች ብቻ የምታደርገው ሳይሆን ችግሮችን ሊያስቀርና ሊከላከል በሚችል መልኩ ሁሉም አገሮች መግባባት ካልቻሉ ውጤቱ ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆኗና አህጉራዊ ስብሰባዎች በአዲስ አበባ የሚካሄዱ በመሆኑ ወደ አገሪቱ ለመምጣት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም መሥራችና ታጋይ የነበረች አገር መሆኗም አፍሪካዊያን እንዲመጡ ልታበረታታ ትችላለች፡፡ «ሆኖም አሁን ላይ ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አስፈላጊና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚችሉ ሰዎች በቀላሉ የሚያገኙበት አግባብ ያለ ይመስለኛል» የሚሉት ፕሮፌሰር መረሳ፤ ኢትዮጵያ እንደ በለፀጉ አገሮች ለአፍሪካዊያን የተለየ ሕግ ያላት አገር አለመሆኗንና ስደተኞች በቀላሉ እየገቡ መሆናቸውን ገልፀው፤ ማንኛውም አፍሪካዊ እንዲመጣ ድንበርን ክፍት ማድረግ ግን ተገቢ ይሆናል የሚል ዕምነት የለኝም ይላሉ፡፡
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ፤ አውሮፓዊያን ካለ ቪዛ የሚያስገቡበት አግባብ ቢኖርም ኢኮኖሚያቸው አቅም ስላለውና መቋቋም ስለሚችሉ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ቅድሚያ የሚሰጡትና ከየትኞቹ አገሮች መግባት እንደሌለበት የራሳቸው መስፈርት አላቸው፡፡ በመሆኑም ነፃ ቪዛ ማግኘት ያላባቸውን መለየት እንሚገባና ከምን አንፃር መፈቀድ እንዳለበትም በግልፅ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
‹‹በቪዛ ጉዳይ ትላልቅ የፖለቲካና የደህንነት ስምምነቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ከነፃ ቪዛ እንቅስቃሴ በፊት ቀድመው መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በቅድሚ የኢኮኖሚ እድገቱ መምጣት አለበት፣ ሁሉንም የሚያግባባ መገበያያ ገንዝብ ሊኖር ይገባል፡፡ ከዚያም ወደ ፖለቲካና ደህንነት ጉዳዮች እንዲሁም ነፃ እንቅስቃሴና የቪዛ ጉዳይ ይመጣል፡፡ ቅድሚያ ካለ ቪዛ እንቅስቃሴ መፍቀድ ግን ከላይ መጀመር ይሆናል፡፡ ከታሪካዊ ጉዳዮች ተነስተን ብናየውም ሊሆን የሚችለው ይኸው ነው፡፡ ከዚህ በፊት ስለ አፍሪካ አንድነት ሲያቀነቅኑ የነበሩ መሪዎች በቅድሚያ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሩ እንዲጎለብትና አንዱ በሌላው ላይ ያለው ጠቀሜታ ሲታወቅ ወደ ፖለቲካዊ አንድነት መምጣት እንደሚቻል ሲገልፁ ነበር፡፡›› በማለት ረዳት ፕሮፌሰሩ ያስታውሳሉ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ፤ በአሁኑ ወቅት የአደጉ አገሮች እየተከተሉት ያለው መመሪያ ብሄራዊ ጥቅምን ማሰቀደም ነው፡፡ ከዕውነታው ተነስተው መርዳት ያለባቸውን አካል ይረዳሉ፡፡ ይህ ዕውነታ ነው፡፡ ሃሳባዊ በመሆን ክፍት ማድረግ ግን ካለው ዕውነታ ጋር ሊጣረስ ስለሚችል ውሣኔዎች ከአገራዊ ጥቅም አኳያ መለካት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
«የሰለጠነ ቴክኖሎጂ በሌለበትና የቁጥጥር ሥርዓታችን ገና ባልዳበረበት ወቅት ለሁሉም መፍቀዱ ጥሩ አይሆንም፡፡ አንድ ዜጋ ችግር ፈጥሮ ለመሰወር ቢሞክር ቴክኖሎጂን ተጠቅመን መቆጣጠር ከምንችልበት ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት አሸባሪነት መሣሪያ አያስፈልገውም፡፡ በቀላሉ ጥቃት ማድረስ ከሚቻልበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በመሆኑም ቃል የተገባበት ሁኔታ ቢኖርም ውሣኔ ከማሳለፍ በፊት በደንብ ሊታሰብበት ይገባል » ሲሉ ፕሮፌሰሩ ያሳስባሉ፡፡
የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተንታኝ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሁ ተስፋ «የዚህ አይነት ቪዛ በሚጀመርበት ወቅት አገሮች በቅድሚያ ኦንላይን ቪዛ ነው የሚፈቅዱት፡፡ የቪዛ መጠየቂያቸውን ያቀርባሉ፣ ማንነታቸው ይታወቃል፣ የሚሰጠው ቪዛ ምን አይነት እንደሆነም ይረጋገጣል፡፡ ካለ ቪዛ መግባትም የሚፈቀደው ለአንድ ወር ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ለአንድ ወር ካለ ቪዛ እንዲገቡ ቢፈቀድ አህጉራዊ ትስስሩን ለማሳደግ ይረዳል፡፡ በተለይ አገሪቱ የአፍሪካ የስብሰባ ማዕከል እንደመሆኗ ብዙ ሰዎች መምጣት እየፈለጉ በቪዛ ምክንያት ሲስተጓጎሉ ይታያሉ፤ ስብሰባዎችም ሲሰረዙ ይታያል፡፡ የዛሬ 20 ዓመት ከአፍሪካ ሕብረትና ከተባበሩት መንግሥታት ይቀርብ የነበረው ትልቁ ጥያቄ የነበረ የቪዛ ጉዳይ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለባቸው አካባቢዎች ፓስፖርት በፖስታ እየላኩ እየጠፋባቸው የሚስተጓጎሉ ዜጎች ነበሩ» ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ቪዛ ነፃ ሲባል ማንኛውም ተነስቶ የሚመጣበት ማለት እንዳልሆነ የሚገልፁት ዶከተር ቆስጠንጢኖስ አየር መንገድ በሚደርሱበት ወቅት ክትትልና ቁጥጥሩን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡ ለአብነትም ከአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ካናዳና ሌሎች አገሮች ካለ ቪዛ የሚመጡ መኖራቸውንም አስታውሰዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ለስብሰባ የሚመጡ ከሆነ የጋበዛቸው ድርጅት ሊኖር ይገባል፣ ለጉብኝት ከሆነም የጋበዛቸው አካል ወይም ግለሰብ ሙሉ አድራሻ ከያዙ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ አስፈላጊ በሆኑ ሰነዶች ላይ የሚሞሏቸው መረጃዎች መኖራቸውንና ሙሉ መረጃ ማስቀመጣቸው ከተረጋገጠ ሊፈቀድላቸው የሚችልበት አግባብ መኖሩን ገልፀዋል፡፡ የተሟላ መረጃ መኖሩ እንቅስቃሴውን ለማሳለጥ ይረዳል ባይ ናቸው፡፡
እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለፃ የማጣራት፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች መሠራታቸው ስለማይቀር የደህንነት ጉዳይ አያሰጋም፡፡ በተጨማሪም ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ለስብሰባ ወይም ደግሞ በአገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሀብቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አፍሪካ ውስጥ ብዙ ሀብታሞች አሉ፡፡ ናይጀሪያ፣ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎችም ባለሀብቶች አሏቸው፡፡ ካለ ቪዛ ቢፈቀድላቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሩን ያጎለብተዋል፡፡

ዑመር እንድሪስ

Published in ፖለቲካ

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ወሳኝ ስፍራ ያለው የግብርናው ዘርፍ በዝናብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የዓለም ከባቢ አየር ሁኔታ ደህንነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ደግሞ በግብርናው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አለው፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያትም የሚያድርበትን ተፅዕኖ ለመቀነስ ብሎም ግብርናውን ከተፅዕኖ ለማላቀቅ ዘመናዊ የአየር ፀባይ ትንበያ መሳሪያዎችን መጠቀም ከመፍትሄ አማራጮቹ መካከል አንዱ ነው፡፡
ይህንንና ሌሎች ችግሮችን ታሳቢ በማድረግ የተቋቋመው የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አገሪቱ የምታስተናግዳቸውን ወቅቶች መሰረት በማድረግ በዓመት ሦስት ጊዜ የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎችን ይፋ ያደርጋል፤ ግምገማም ይሰጣል፡፡ በዚህም መሰረት ኤጀንሲው ጥር 18 እና 19 ቀን 2010 ዓ.ም የበጋውን ወቅት አየር ጠባይ በመገምገም የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በትንበያውም የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚያገኙ አመልክቷል፡፡
የትንበያውን አጠቃላይ ውጤት በመገምገም ለቀጣይ ሥራዎች ልምድ ለመቀመር የ2010 ዓ.ም የበልግ ወቅት የአየር ሁኔታ ጠባይ ትንበያ አፈጻጸም ግምገማ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ የበልግ ወቅት ዝናብ በልዩ ልዩ ዘርፎች ላይ የነበረው አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች የቀረቡ ሲሆን፤ የ2010 ዓ.ም የክረምት ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያም ይፋ ሆኗል፡፡
የበልግ ወቅት ለደቡብና ደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዋነኛ የዝናብ ወቅት ነው፡፡ ለደቡብ ትግራይ፣ ለምስራቅ አማራ፣ ለመካከለኛው፣ ምስራቅና ደቡብ ኦሮሚያ እንዲሁም ለደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው፡፡
በበልግ ወቅት የተመዘገበው ዝናብ በልግ አብቃይ በሆኑ አብዛኞቹ አካባቢዎች ለሚከናወኑ የእርሻ ስራዎች ምቹ ነበር፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ ለአብነትም በመጋቢት ወር በፍቼ፣ በሚያዚያ ወር በጂግጂጋ እና በቡርቃ እንዲሁም በግንቦት ወር ደግሞ በቡሬ፣ በጋምቤላ፣ በብላቴ፣ በመተማ እና በዳንግላ የተመዘገበው ከባድ ዝናብና በሰብል ላይ የደረሱት ጉዳቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በኤጀንሲው የሜቲዎሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር አቶ አሳምነው ተሾመ እንደሚሉት፣ በበልግ ወቅት የዘነበው ዝናብ ኤጀንሲው በትንበያው ካመላከተው ጋር የተጣጣመ ነበር፡፡ በዚህም የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ አግኝተዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ አገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ከባድ ዝናብ ተመዝግቧል፡፡
በበልግ የአየር ጠባይ ትንበያ መሰረት ምዕራብ አጋማሽ ከመደበኛ በላይ፣ ሰሜን ምስራቅ መደበኛ እንዲሁም ደቡብ ምስራቅ ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ እንደነበር ያወሱት ዳይሬክተሩ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ከደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በስተቀር የተመዘገበው ዝናብም ከኤጀንሲው ትንበያ ጋር የተዛመደ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ትንበያዎች መሬት ላይ ከሚከሰተው ነገር የተለዩ ሊሆኑ እንደሚችሉም ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም በዘንድሮው የበልግ ወቅት በደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ቢተነበይም፤ ከትንበያው በኋላ በተፈጠረ የአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት የተተነበየው ሳይሆን ቀርቶ እንዲያውም አካባቢው ከባድ ዝናብ አስተናግዷል፡፡
ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የአጭር (የ72 ሰዓታት)፣ የመካከለኛ (እስከ 10 ቀናት) እና የረጅም ጊዜ የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎችን በማዘጋጀት ለተለያዩ ተቋማት ሲሰጥ መቆቱን የሚናገሩት አቶ አሳምነው፤ ትንበያዎች ሲዘጋጁ ለተለያዩ ዘርፎች አመቺ እንዲሆኑ ተደርገው እንደሆነና በግብርና፣ በውሃና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ የሚያሳዩ ሆነው እንደሚደራጁም ይገልፃሉ፡፡
በግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ፣ ኤጀንሲው የሚሰጣቸው የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎች ጠቃሚ እንደሆኑ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ግብርና የተመሰረተው በዝናብ ላይ እንደመሆኑ መጠን የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎች እጅግ አስፈላጊ ግብዓቶች ናቸው፡፡ ኤጀንሲው ከአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎች በተጨማሪ ለግብርናው ዘርፍ የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦችንም ይሰጣል›› ይላሉ፡፡
ኤጀንሲው መረጃ የሚሰጠው ለሁሉም ተቋማት በመሆኑ ግብርና ተኮር የሆኑ መረጃዎች ላይ ብቻ ለማተኮር መሰናክል ሆኖባቸው እንደነበር የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ይህም ግብርና ተኮር ምክር ሃሳቦችን ለማውጣትና አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች በአካባቢያቸው የእርሻ ስራ ላይ በቀላሉ ለመወሰን እንዳስቻላቸው ይገልጻሉ፡፡
‹‹በተለይ ኤል-ኒኖ ከተከሰተ ወዲህ አርሶ አደሩ የኤጀንሲውን መረጃዎች እየተጠቀመ ነው፡፡ ከኤጀንሲው የሚወጡ የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎችን በመከታተል ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ የመረጃዎቹም ጥራትና ታማኝነት እየጨመረ ነው›› በማለት ይናገራሉ፡፡
በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ በበኩላቸው፣ ከውሃ ዘርፍ አንጻር ኤጀንሲው የሚሰጣቸው መረጃዎች ከመጠጥ ውሃ፣ ከኃይል ማመንጫና ከመስኖ ግድቦች ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ ኤጀንሲው የሚሰጣቸው የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎችም ለውሃ ዘርፍ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ነው፡፡ ‹‹የዝናብ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ሲተነበይ ግድቦቹን ውሃ በቁጠባ ለመጠቀም የትንበያ መረጃዎቹ ፋይዳቸው የጎላ ነው፡፡ በግድቦቹ አካባቢዎችም ከባድ ዝናብ እንደሚዘነብ ከታወቀ የትንበያ መረጃዎቹ ለጥንቃቄ አስፈላጊ ናቸው›› ይላሉ፡፡ በ2008 ዓ.ም የዝናብ እጥረት ሲያጋጥም የመስኖ ግድቦች ያጋጠማቸው የውሃ እጥረት በኤጀንሲው የትንበያ መረጃዎች መሰረት በአርሶ አደሩ ሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ እንደቀረና የርብ ግድብም ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ እንደተቻለ በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
የኤጀንሲው የአየር ጠባይ ትንበያ እንደሚያሳየው የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የአገሪቱ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በመጪው ክረምት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ያገኛሉ፡፡ ክረምት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው ያልሆኑ አካባቢዎች ግን ደረቃማ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ይጠበቃል፡፡ በጥቂት የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ደግሞ የዝናብ መዘግየት ሊከሰት ይችላል፡፡ በአጠቃላይ የዘንድሮው ክረምት ከኤል-ኒኖ ተፅዕኖ ነፃ በመሆኑ ለግብርና ስራው አመቺ ይሆናል፡፡
አቶ አሳምነው እንደሚሉት፤ ኤጀንሲው የሰጠው የክረምት ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ በመኸር እርሻ ሥራ እንዲሁም በግድብና በተፋሰስ አስተዳደር ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ያመላከተ ነው፡፡ በክረምት ከመደበኛ መጠን ያለፈ ዝናብ ሊከሰትባቸው በሚችሉ ቦታዎች የጎርፍ አደጋን ከመከላከል እንዲሁም የዝናብ መጠን አነስተኛ በሚሆንባቸው አካባቢዎች ደግሞ ውሃ አጠራቅሞ ከመያዝ አንፃር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግና ህብረተሰቡ የኤጀንሲውን መረጃዎች በንቃት መከታተልና መተግበር እንደሚኖርበትም ይመክራሉ፡፡
አቶ ኢሳያስም፣ የክረምቱ የእርሻ እንቅስቃሴ በምን መንገድ መመራት እንዳለበት ከኤጀንሲው ባለሙያዎች ጋር በትብብር እንደሚሰራና ከዚህ በተጨማሪም፣ የክረምቱን የአየር ጠባይ ትንበያ መሰረት በማድረግም ምክረ ሃሳቦች እንደሚዘጋጁና መረጃው ተዘጋጅቶ ወደ አርሶ አደሩ እንደሚላክም ጠቁመዋል፡፡
በዝናብ ላይ የተመሰረተውን የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ በተሻለ የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃ ለማገዝ ደግሞ ዘመን ያፈራቸውን የዘርፉ ቴክኖሎጂዎች መተግበርና መጠቀም አማራጭ የሌለው አሰራር ነው፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ኤጀንሲው አቅሙን በማሳደግ አስተማማኝ የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ ዘመናዊ የአየር ትንበያ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች እየተደራጁ ነው፡፡ ኤጀንሲው ብዙ ወጣት ባለሙያዎች እንዲኖሩት ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙ ጥረት እየተደረገም ነው፡፡ ‹‹ኤጀንሲው በየጊዜው መሻሻል እያሳየ ነው፤ ከጥቂት ጊዜያት በኋላም የዓለም የሜቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ኢትዮጵያ ላይ ይሆናል›› ይላሉ፡፡
ከአገሪቱ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት አንጻር የኤጀንሲው የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ለኅብረተሰቡ ደርሰዋል ማለት እንደማይቻል የሚገልጹት አቶ ፈጠነ፣ በቀጣይ ዘመኑ ያፈራቸውን የዘርፉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተደራሽነቱን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ያስረዳሉ፡፡ ምንም እንኳ አርሶ አደሩ የትንበያ መረጃዎችን የመጠቀም ባህሉ እያደገ ቢመጣም ግንዛቤውን የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

አንተነህ ቸሬ

Published in ኢኮኖሚ

የሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይሎች ሰሞኑን በፈረንሳይ ፓሪስ ያካሄዱት የሰላም ድርድር እ.አ.አ ከ2011 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በእርስ በርስ ጦርነት ለምትታመሰው ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሰላም ተስፋ ይኖረው ይሆን ወይ ተብሎ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በጉጉት ተጠብቋል፡፡ በፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋባዥነት በተካሄደው የተቀናቃኝ አንጃዎቹ ድርድር መቀመጫቸውን በትሪፖሊና በቶብሩክ ያደረጉት የሊቢያ ሁለቱ ‹‹መንግሥታት›› በዚህ ዓመት መገባዳጃ ላይ ምርጫ እንዲደረግ ተስማምተዋል ተብሏል፡፡ በስምምነቱ መሰረትም እ.አ.አ መስከረም 16 ቀን 2018 አስፈላጊ የሆኑ የምርጫ ሕግጋት ይጸድቃሉ፤ ታኅሳስ 10 ቀን 2018 ደግሞ ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ይካሄዳል፡፡
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ድርድሩ የተደረገበትን ቀን ‹‹ታሪካዊ ቀን›› ሲሉ አሞካሽተ ውታል፡፡ ይሁን እንጂ የዐይን እማኞች በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሳራጅ እና ከሊቢያ ብሔራዊ ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር ጋር በኤሊዜ ቤተ-መንግሥት እጃቸውን ሲጨባበጡ የነበረው ድባብ ድርድሩ ብዙም ተስፋ እንዳይጣልበት የሚያደርግ ነበር ብለዋል፡፡
‹‹ኤጀንሲ አስፔክትስ (Energy Aspects)›› በተባለውና መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገው የጥናትና ምርምር አማካሪ ተቋም የጂኦፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ሪካርዶ ፋቢያኒ፣ ተቀናቃኞቹ ለድርድር መቀመጣቸው ጥሩ ቢሆንም በፍጥነት የሚገኝ ውጤት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በፓሪሱ የሰላም ጉባዔ ላይ የተሳተፉት ተቀናቃኝ ኃይሎች ችግሮቹን በውይይት ለመፍታት ተስማምተዋል፡፡ አሁን ካለው የሊቢያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ውይይቶቹና ሊፈፀሙ የታቀዱት ሌሎች ተግባራት በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ በቀላሉ ይሳካሉ ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ተቃናቃኞቹ ያለምንም የፊርማ ስምምነት በቃል ብቻ መስማማታቸው ከጉባዔው የሚጠበቀውን ተስፋ የመነመነ እንዲሆን ያደርገዋል›› ብለዋል፡፡
‹‹ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ (International Crisis Group)›› የተባለው ተቋም በበኩሉ የፓሪሱ የሰላም ጉባዔ ከመካሄዱ አስቀድሞ ተቀናቃኞቹ ጥልቅ ውይይት ሳያደርጉ ከስምምነት ላይ እንዳይደርሱ አሳስቦ ነበር፡፡ ተቋሙ ጉባዔው ከመካሄዱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ውይይት ሳይደረግ ከስምምነት ላይ ለመድረስ መሞከር ውሎ አድሮ በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የተለመደውን አለመግባባት ሊፈጥር እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
በፓሪሱ የሰላም ጉባዔ ላይ ከተደራዳሪዎቹ ከሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይሎችና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተጨማሪ የ20 አገራት ተወካዮች የተገኙ ቢሆንም በምዕራባዊ ሊቢያ ጠንካራ ይዞታ ያላቸው ተዋጊዎች ግን በገባዔው ላይ አልተሳተፉም፡፡ በምዕራብ ሊቢያ ጠንካራ ኃይል ያላቸውን 13 ታጣቂ ቡድኖችን ያሰባሰበውና ከጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሳራጅ ጋር ደካማ ትብብር ፈጥሮ የነበረው ካውንስል፣ የፓሪሱ የሰላም ጉባዔ የቡድኖቹን ፍላጎት የሚወክል እንዳልሆነ ገልጾ ራሱን ከጉባዔው ማግለሉን አሳውቆ ነበር፡፡ ካውንስሉ ከጉባዔው በፊት ባወጣው መግለጫ ‹‹የእርስ በእርስ ጦርነቱ መቋጫ ካገኘ በኋላ ሊቢያውያንን ያሳተፈና ፍላጎታቸውን የሚወክል ትክክለኛ ጉባዔ ለማዘጋጀት ዝግጁ ነኝ›› ብሎ ነበር፡፡
መቀመጫውን ትሪፖሊ ያደረገው የሳዴቅ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም (Sadeq Institute) መስራች አናስ ኤል ጎማቲ፣ በሊቢያ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ወሳኝ ቦታ ያላቸው ኃይሎች በፓሪሱ የሰላም ጉባዔ ላይ አለመሳተፋቸው በአገሪቱ የሰላም ተስፋ ላይ ተፅዕኖው የጎላ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ጠንካራ ኃይል ያላቸው ቡድኖች ባልተሳተፉበት መድረክ ከ24 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ስምምነት ላይ መድረስ ትርጉሙ ምንድን ነው‹‹ በማለትም ይጠይቃሉ፡፡ እዚህ ላይ በጎረቤት ቱኒዚያ የሆነውን ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡ የ2011 የአረብ አብዮት ጀማሪ የሆነችው የቱኒዚያ ተቀናቃኝ ኃይሎች ለመስማማት ከአንድ ዓመት በላይ ፈጅቶባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተቀናቃኝ ኃይሎቹን ለማስማማት የአገሪቱ ልዩ ልዩ ማኅበራት የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡
ሪካርዶ ፋቢያኒም እስካሁን በተደረጉት የሊቢያ ሰላም ድርድሮች ላይ ጠንካራ ኃይል ያላቸው ቡድኖች አለመሳተፋቸው ድርድሮቹ ፍሬ እንዳያፈሩ መሰናክል እንደሆነ ይገልፀሉ፡፡ ‹‹የፖለቲካ መሪዎችን ለድርድር መጋበዝ ተገቢ ቢሆንም ሰፊ መሬት በቁጥጥራቸው ስር ያደረጉ የጎሳ መሪዎችንና የሚሊሻ አለቃዎችን ወደ ድርድሩ ማምጣት ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ ግን ሊቢያን ከሰላምና ከዴሞክራሲ ጋር ማገናኘት አይታሰብም፤ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ማለት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚገባ ባዶ ቃል ኪዳን ብቻ ነው›› ይላሉ፡፡
መሰረታቸውን ምዕራብ ሊቢያ ላይ ያደረጉት ታጣቂዎች ከፓሪሱ የሰላም ጉባዔ ራሳቸውን ማግለላቸው ትሪፖሊ ከሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሳራጅ መንግሥት ጋር የነበራቸውን የላላ ጥምረት ጨርሰው እንዳይቆርጡት ተሰግቷል፡፡ ራሱን የሊቢያ ብሔራዊ ጦር (Libyan National Army) ብሎ የሚጠራውን ቡድን የሚመሩት የፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር ጤና ማጣትም በቡድኑ ደጋፊዎች ስጋት ፈጥሯል፡፡
በፓሪሱ ስምምነት መሰረት እቅድ የተያዘለት ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ቢደረግ እንኳ ተሸናፊዎቹ አሸናፊውን ለመቀበል የሚኖራቸው ዝግጁነትም በተንታኞች ዘንድ ጥያቄ ያስነሳ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ሪካርዶ ፋቢያኒ እንደሚሉት፣ ድርድሩ ከምርጫው በኋላ ስለሚኖሩት ጉዳዮች ጠለቅ ብሎ የመከረው ነገር ስለሌለ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም፡፡
የሊቢያ ተቀናቃኝ ኃይሎችን ለማደራደር ጥረት ሲደረግ የሰሞኑ የፓሪስ የሠላም ጉባዔ የመጀመሪያው ጥረት/ሙከራ አይደለም፡፡ ፕሬዚዳንት ማክሮን ባለፈው ሐምሌ ወር መሰል የሰላም ጉባዔ አስተናግደው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ በግብፅና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አስተናጋጅነት የተካሄዱት ድርድሮችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከሰሞኑ የፓሪሱ የሰላም ጉባዔ በፊት የተካሄዱትና እነዚህን ታጣቂ ቡድኖች ለማስማማት የተደረጉ ጥረቶችም ምንም ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሊቢያ ልዩ መልዕክተኛ ጋሳን ሳሌም ባለፈው መስከረም ወር የሊቢያ ተቃዋሚዎችን ለማደራደር የሚዘጋጁት ጉባዔዎች ቁጥራቸው እጅግ በርክቷል ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ልዩ መልዕክተኛው ሊቢያን በተመለከተ የሚካሄዱት ቁጥራቸው የበረከተ ድርድሮች ሊቢያውያንን ሳይቀር ግራ እንዳጋቡና ጦርነቱን እንደሚያራዝሙት ተናግረው ነበር፡፡
አናስ ኤል ጎማቲ በፓሪሱም ሆነ ከዚህ ቀደም በተካሄዱት የሰላም ጉባዔዎች ላይ ተስፋ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ‹‹የፓሪሱ ጉባዔ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሊቢያን ቀውስ ለመፍታት እያከናወናቸው ካሉት ተግባራት የተለየ ፍሬ የለውም፤ አራት ዓመታትን የፈጁ ውይይቶች ተካሂደው ጊዜ ከማባከን ውጭ ጠብ ያለ ነገር የለም›› ይላሉ፡፡ ጃለል ሃርሻዊ የተባሉ ምሁር ደግሞ ጉባዔው ለምጣኔ ሀብታዊና ለሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ መነጋር እንደነበረበት ይገልፃሉ፡፡ ‹‹አሁን በሊቢያ ውስጥ አስከፊ የሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት አለ፤ ፈረንሳይ ጉባዔውን ስታስተናግድ ይህን ጉዳይ ከግምት ውስጥ አስገብታ ነበር፤ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንኮች እንዲዋሃዱ ሃሳብ ቢቀርብም ጥልቅ የሆነ ውይይት አልተደረገበትም›› ብለዋል፡፡
ሊቢያን ለ42 ዓመታት ያህል የመሯት ኮሎኔል መሐመድ ጋዳፊ እ.አ.አ በ2011 በሕዝባዊ አመፅ ከስልጣን ተወግደው ከተገደሉ በኋላ ታጣቂ ቡድኖች እንደቅርጫ ስጋ የተከፋፈሏት ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ፣ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች፡፡ በተለይ ደግሞ ምስራቃዊውና ምዕራባዊው የአገሪቱ ክፍሎች እርስ በእርስ በሚዋጉ ታጣቂ አንጃዎች ስር መውደቃቸው ጦርነቱን የከፋ አድርጎታል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና የተሰጠውና በድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግለት ቡድን በፋይዘል አል-ሳራጅ የሚመራው ሲሆን መቀመጫውን በትሪፖሊ አደርጎ ‹‹ገቨርመንት ኦፍ ናሽናል አኮርድ (Government of National Accord)›› የተባለ ‹‹መንግሥት›› መስርቶ ተቀምጧል፡፡ በፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር የሚመራውና ራሱን ‹‹የሊቢያ ብሔራዊ ጦር›› ብሎ የሚጠራው ቡድን ደግሞ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሳራጅን መንግሥት አላውቅም›› ብሎ በምስራቃዊ ሊቢያ በምትገኘው ቶብሩክ ከተማ ላይ ተሰይሟል፡፡ ይህ ቡድን የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሳራጅ መንግሥትም ተፅዕኖ በትሪፖሊ ብቻ እንዲወሰን አስገድዶታል፡፡
የሊቢያ የእርስ በእርስ ጦርነት በተቀናቃኝ ኃይሎች ሽኩቻ ብቻ የሚመራ አይደለም፡፡ እንኳን እንዲህ ያለ ሰፊ ክፍተት ሲያገኙ ይቅርና ራሳቸው ችግር ፈጥረው ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚፈልጉት የምዕራባውያን አገራትም የሊቢያን ወቅታዊ ሁኔታ ለዓላማቸው ማሳኪያ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ይነገራል፡፡
(የመረጃው ምንጮች አልጀዚራ እና ፍራንስ 24 ናቸው)

አንተነህ ቸሬ

Published in ዓለም አቀፍ

2010 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ክስተቶችን እያስተናገደች ያለችበት ዓመት ነው፡፡ ከመቼውም ጊዜ በማይታመን ፍጥነት በርካቶች በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊትና ሙከራ በቁጥጥር ሥር የዋሉበት በዚያው ልክ ደግሞ መንግሥት ባስተላለፈው ውሳኔ ከተጠረጠሩበት ወንጀል በነፃ በመሰናበት ከሕብረተሰቡ ጋር መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲመሩ የተደረገበት ዓመት ነው፡፡
ለአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት በማሰብ፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ብሎም በመላ አገሪቱ ከአርሶ አደር መንደር እስከ ላይኛው በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ ከግምት ውስጥ በማስገባት በርካታ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡ በርካታ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ተቀልብሰው ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበትና የፖለቲካ ምህዳሩን መመንደግ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ጓዛቸውን ጠቅለው ከማረሚያ ቤት እንዲወጡ ተስፋ ሰጪ ውሳኔ የተላለፈበት ነው፡፡
ዴሞክራሲያቸው አድጓል፤ ምጣኔ ሀብታቸው ተመንድጓል፤ አስተሳሰባቸው ልቋል የሚባሉ አገራትና ተቋማት ኢትዮጵያ ላካሄደችው ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ልባዊ አድናቆታቸውን የገለፁበት ዓመት ነው 2010 ዓ.ም፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የትኩረት አቅጣጫቸውን ወደዚህ ያደረጉበትና፤ በአሁኑ ወቅትም የካሜራ እይታቸው፤ ብዕር የሚጨብጥ ጣታቸው፤ ዜና የሚያነፈንፍ ስሜታቸው ወደ ኢትዮጵያ ያነጣጠሩ በርካቶች መገናኛ ብዙኃን መኖራቸው ሌላኛው ክስተት ነው፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ አሁንም እልባት የሚፈልጉ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና፣ ምጣኔ ሀብታዊ ውጥንቅጦች የተጋረጡበት ወቅት ነው 2010 ዓ.ም ለኢትዮጵ ያውያን፡፡
በሌላ ጎኑ ደግሞ አገራችን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳጋጠማት ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሆኑ በእርሳቸው መንበር የተተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ደጋግመው ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ በእርግጥ ችግሩን ፍርጥ አድርጎ በግልፅ መናገር ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ ይህ መልዕክት በማያሻማ አማርኛ ለባለሀብቶቿ፣ ዜጎቿ፣ ምሁራን፣ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያን ልማት ለሚወዱ አጋሮቿ፤ አገሪቱ ከገባችበት ወቅታዊ ቀውስ እንድትወጣ ከመንግሥት ጎን በመቆምና ዋነኛ ተዋናይ በመሆን ሁነኛ መፍትሄ ለማምጣት በማሰብ ነው፡፡
በዚህ ዓመት መንግሥት ከወሰዳቸው እርምጃዎች ውስጥ በተለያዩ ወንጀል ጉዳዮች ተጠርጥረው በሕግ ከለላ ሥር የነበሩና የጥፋተኝነት ውሳኔ የተበየነባቸው በርካታ ባለሀብቶችም የፍርድ ጊዜ ሳያጠናቅቁ በምህረት ከማረሚያ ቤት ወጥተዋል፡፡ በእኔ አስተሳሰብ ይህ በእጅጉ የሚበረታታና አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ግን እነዚህ አካላት በአገሪቱ ልማት እና አዎንታዊ ለውጦች ላይ ያላቸው ሚና በሚገባ እንደሚገነዘቡት አምናለሁ፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የፈጠሩት ስህተት በሕግ ዓይን የሚታይ ሆኖ በቀጣይም ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል፡፡
እነዚህ ባለሀብቶች ወደ መደበኛ ሥራቸው ሲመለሱ የውጭ ምንዛሪውን በማስገኘትና በማሳደግ ረገድ ድርሻቸው ወደር የለውም፡፡ ድርጅቶቻቸውና ተቋማቶቻቸው ከመቼውም በላይ በወኔ እንዲሰሩ ሠራተኞቻቸውን በልዩ ሁኔታ ሊያበረታቱ ይገባል፡፡ ከአገር ውጭ ያሉ ደንበኞቻቸውን ከሌላው ጊዜ በበለጠ በማግባባትና በጋራ በሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ ትልቅ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡ አገሪቱ ከውጭ ምንዛሪ ድርቅ በፍጥነት እንድትላቀቅም ሌት ተቀን ሊተጉ ይገባል፡፡ የድርጅታቸውን ሥም በማደስ፤ የቀድሞ ስህተቶቻቸውን በማስተካከል ዕድሉን መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡
መንግሥትም ቢሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እነዚህን አካላት ሊያበረታታ ግድ ይለዋል፡፡ ከምህረትና ይቅርታ ባሻገር ሥራቸውን ያቀላጥፉ ዘንድ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በሥራዎቻቸው ላይ እክል የፈጠሩና ሊፈጥሩ የሚችሉ ቁሳዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ መሰናክሎችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡ በአገራችን ታሪክ ችግሮች ሲመጡብን በጋራ መመከት፤ ወራሪ ሲመጣ በኅብረት ሆነን ማሳፈር እንችልበታለን፡፡ ለዚህም በማይዋዥቅ መሠረት ላይ የተገነባው እኛነታችን ሕያው ምስክር ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት አሊያም በዘመናዊ ቋንቋና አነጋገር ማደባበስ ካልሆነ በቀር ነፃነትን ሊያዋርድ የሚችል ችግር እኛ ኢትዮጵያውያን ላይ ተደቅኗል፡፡ ይህም ድህነት ነው፡፡ ድህነትን በጋራ መመከት የማንችል ከሆነ በተናጠል አንዳችም ረብ ያለው ነገር ልንከውን አንችልም፡፡ ችግርን ተረት ለማድረግ ከአርሶ አደሩ ጭስ የሞላበት ቤት እስከ ቤተመንግሥት ድረስ ያሉ ዜጎች ያላሰለሰ ጥረት ይፈልጋል፡፡ እንደቀድሞዎቹ ዘመናት የአሽከርና ሎሌ አሠራር በመከተል ልንወጣው የምንችለው ዳገት የለም፡፡ «አንድ ሰው አስቦ፤ አንድ በሬስ ስቦ» ይሉት ብሂል እንዳይሆንብን የጋራ ችግራችን ላይ የጋራ መፍትሄ ያስፈልገናል፡፡
በመሠረቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲያጋጥም በብዙ መልኩ ማየት ያስፈልጋል፡፡ አንድም አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ያቀደችውን ያህል ሳታገኝ ቀርታ ሊሆን ይችላል፡፡ አሊያም ደግሞ ተፈጥሯዊ ክስተቶች ጫና ፈጥረው የታሰበው ላይሳካ እንደሚችል መገመት አስፈላጊ ሆኖ ለችግር እጅ አለመስጠትን ባህል ማድረግ ይገባል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባው ዓለም አቀፋዊ ምልከታና እውነታ መኖር አለበት፡፡ ምናልባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲኖር በዚህ ወቅት አንዳንዶች አጀንዳ እየሰጡን ሊሆን ይችላል፡፡ የኒዮ ሊበራሊዝም አቀንቃኞችና ከኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ፍልስፍና አሠራር በተቃራኒ የቆሙ አካላት ዓላማቸው ግብ እንዲመታ የማይፈነቅሉት ቋጥኝ አይኖርም፡፡
እንደሚታወቀው ለአገሪቱ ተከታታይ ዕድገትና ለመንግሥትም ትልቅ የገቢ ምንጭ የሆኑ ተቋማት አሁንም ድረስ ከመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ቁጥጥር ሥር ነፃ አልወጡም፡፡ በእኔ እምነት ይህ መሆን አለበት የሚል አቋም አለኝ፡፡ ታዲያ እነዚህ ከኢትዮጵያ በተቃራኒው የቆሙ አካላት እነዚህን ተቋማት ከመንግሥት ቁጥጥር ነፃ እንዲሆኑ ይሻሉ፡፡ በሂደትም በኢንቨስትመንት ስም በበላይነት ሊዘውሩ ይፈልጋሉ፡፡ በንግድ ሽርክና አሊያም ደግሞ በወዳጅነት ገብተው መንግሥትን እጁን መጠምዘዝ ዓላማቸው ነው፡፡ በሂደትም ወዳጅ እየመሰሉ ነገሮችን በሚመቻቸው መንገድ ይዘውራሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በቀጥታ የራሳቸውን የምጣኔ ሀብት፣ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ፍልስፍና በሌላው ላይ ለመጫን ትልቅ አማራጭ ያገኛሉ፡፡ ይህ ክስተት በርካታ ዓለም አገራት ላይ የሆነ እና እየሆነ ያለ ጉዳይ ነው፡፡
በሌላ ጎራ ደግሞ በቀለም አብዮት በርካታ አገራት እንዲበታተኑ እያደረጉ ነው፡፡ ቀደም ሲልም የበርካታ አገራትን ጠንካራ መሠረት እንዲሸረሸር አድርገው አናግተዋል፡፡ በመሰል ሴራ በርካታ አገራትን የማይወጡት ውጥንቅጥ ውስጥ እንዲገቡም አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ 76 ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖራቸው፤ በአንድ በኩል ፀጋ ሲሆን በሌላ በኩል ግን ፈተና እንደሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡ የአገሪቱ ዕድገት የማይዋጥላቸው ዓላማቸውን ለማሳካት ይህን ብዝሃነት እንደ አማራጭ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም እርስ በእርስ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ ያደርጉታል፡፡ ይህ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ደግሞ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማቀዛቀዝ ትልቅ ዕድል ስለሚከፍት ጣልቃ መግባት ለሚፈልጉ አገራት ጮቤ ያስረግጣቸዋል፡፡
መሰል አጋጣሚዎችን በመጠቀም ሲፈልጉ በግብረሰናይ ድርጅት አመካኝተው ዘው ብለው ይገባሉ፡፡ ሲያሻቸው ደግሞ በአሸማጋይ መልክ ድንበር ዘለው ይመጣሉ፡፡ በአንደበታቸው መልካም ነትን ተላብሰው፤ በልባቸው መርዝ ይዘውብን ይመጣሉ፡፡ በእርግጥ ይህን አጀንዳ በአንዲት ጀንበር ለመፈፀም አይፈልጉም፡፡ በተለይ ደግሞ ማንነታቸ ውንና ታሪካቸውን ጠብቀው የቆዩ ኢትዮጵያን የመሰሉ አገራትን በቀላሉ መዳፈሩ አያዋጣቸውም፡፡ ነገር ግን «ውሃ እያሳሳቀ ይወስዳል» እንዲሉ ቀስ ብለው አድፍጠውና አስልተው ቀላል ችግራችንን ውስብስብ ያደርጋሉ፤ ሳቃችንና ደስታችንን በኀዘን ድባብ ይለውጡታል፡፡
ስለሆነም ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ የአገር ባለውለታዎች በስኬት ወቅት የሚመጡ ሳይሆን፤ በችግር ተፈትነው ስኬት የሚያመጡ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ መሆን የሚችሉ በርካታ አንደበቶች፤ ምጥቁ አዕምሮዎች፤ የሚሰሩ እጆች፤ ልባም አመራሮች፤ ታታሪ ሠራተኞች፤ ቅን አስተሳስቦች አሉ፤ ይኖራሉም፡፡ እነዚህን አካላት ደግሞ በአንድነት የሚያስተባብር አመራር ያስፈልጋል፡፡ ይህም እየተሳካ ይመስላል፡፡ በበርካታ ልዩነቶች መካከል ተቻችሎ ለመኖር መንገዶች እየተከፈቱ ናቸው፡፡ ሰንሰለታማ የሆኑ ችግሮቻችንን በማለፍ ወደ ሰፊው ሜዳ የሚስወጣን እርካብ ልናበጅ ይገባል፡፡ በታሪካችን የምንታወቀው ችግሮች ሲያለያዩን ሳይሆን አንድነታችንን ሲያጠናክሩ ነው፡፡ ይህ ዛሬም ስንቃችን መሆን አለበት፡፡
በእነዚህ ችግሮች ደግሞ ኅብረተሰቡ የሚኖረው ሚና ትልቅ ነው፡፡ አንድ እጅ ብቻውን አጭብጭቦ ድምቀት እንደሌለው ሁሉ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይንም ሌላ የሥራ ኃላፊ ብቻውን ስለተሯሯጠ መፍትሄ ሊመጣ አይችልም፡፡ ይህ መላው የአገሪቱን ዜጎች ሊገነዘቡትና ሊሰሩበት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ በጋራ ልፋት የጋራ ውጤት የሚመዘገብበት መሆን አለበት፡፡ በደስታ ጊዜ የምንተቃቀፍ፤ በችግር ጊዜ የምንኮራረፍ ሰዎች መሆን የለብንም፡፡
ጥልቅ አስተውሎት ያስፈልጋል፡፡ አንበሳ ጠላቱን ለማደን በአራቱም አቅጣጫ ዓይኖቹ አያርፉም፡፡ አጋጣሚዎችን በሙሉ ይጠቀማል፤ ዕድል ብቻ አይጠብቅም፡፡ ምንም ክፉ ጠላት ቢገጥመው ከመሸሽ ይልቅ መንጋውን ጠርቶ በሙሉ ወኔ ይፋለማል፡፡ በመጨረሻ ጠላቱን ድል ከመታ በኋላ ከአንዱ መንጋጋ ወደ ሌላ መንጋጋ እያገላበጠ ያላምጠዋል፡፡ አንበሳ ከብዙ ውጣ ውረድና ብርቱ ድካም በኋላ ብቻ ነው ጎንበስ የሚለው፡፡ አንበሳ የሚያጎነብሰው ሲመገብ ነው፡፡ ሲሸነፍ አያጎነብስም፤ ላለመሸነፍ ይፍጨረጨ ራል እንጂ፡፡ ከዚያ ውጪ ሲሄድ፣ ሲቆም፣ ሲራመድ፣ ሲተኛም ዓይኖቹ አሻግረው ይመለከታሉ፤ እረፍት አልባ ናቸው፡፡
እኛ ኢትዮጵያንም ልክ አንድ አንበሳ መሆን አለብን፡፡ ስንበላ ካልሆነ በስተቀር አንገታችን መስበር፤ ለሽንፈት እጅ መስጠት አይገባንም፡፡ ሩቅ ማሰብና ከአድማስ ማዶ አሻግሮ መመልከት ልማዳችን መሆን አለበት፡፡ እንደ አንበሳ መንጋ ችግሮቻችንን በጋራ መመከትና ድል ማድረግ ባህላችን ይሁን፡፡
በእጅ አዙር በጠላት እጅ እንዳንወድቅ ሰፊ ግንዛቤ ሊፈጠር ይገባል፡፡ እውነታውን ማሳወቅ አለብን፡፡ በወቅታዊ ችግሮች ስንከፋፈል ለዘላለማዊ ሰቆቃና ባርነት እንዳንዳረግ ማስተዋል የተሞላው እርምጃ ያስፈልገናል፡፡ አገራችን እየገጠማት ካለውና ሊገጥማት ከሚችለው ችግር ልንወጣ የምንችለው እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ አገር ማሰብ ስንችል ነው፡፡ ታዲያ በአሁኑ ወቅት አገሪቱን የገጠማት ፖለቲካም ይሁን የምጣኔ ሀብት ቀውስ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል የሚለው ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ ሐሳቡ በህብረት ድርጊቱም በህብረት መሆን አለበት፡፡
መንግሥትም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነት፤ ሠላምና ትብብር ጥሪ አስተላልፏል፡፡ ከመቼውም በበለጠ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት ሰፊ ዕድል የሚሰጡና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ አገር አቀፍ የሠላም ጉባዔ ተካሂዷል፡፡ ችግሮች በተፈጠሩባቸው አካባቢዎችና ኅብረተሰቡ ቅር በተሰኘባቸው ጉዳዮች መፍትሄ ለመስጠት ትልቅ ጥረት ተጀምሯል፡፡ ለውጥም እየተስተዋለ ነው፡፡ የሕዝብ ይቅርባይነትና የመንግሥትን አርቆ አስተዋይነትም ማስተዋል የተቻለበት ወቅት ነው፡፡ ከወቅታዊ ችግሮች በፍጥነት ለመውጣት ትልቅ ኃላፊነት ይጠበቅብናል፤ እንደምናሳካውም እተማ መናለሁ፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Published in አጀንዳ

«ልንመሰገንበት በሚገባ ሥራ ወንጀለኛ መባላችን ያሳዝናል_፤እንኳን 16 ቤት አንዲት ደሳሳ ጐጆ የለኝም» ያሉት እኒያ በሙስና ተወንጅለውና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የጉምሩኩ ሰው ዛሬ ላይ ሆኜ የተናገሩትን ንግግር ሳስበው ለካስ እውነት ተናግረው ነበር እንድል ያስገድደኛል፡፡ በወቅቱም «ይህቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው?» ሲሉ የአገሪቱ ጉዞ አሳስቧቸው የመገረም ጥያቄ ያቀረቡም ነበሩ፡፡ በርግጥም የአገሪቱ ጉዞ ያሳስባል፡፡
ኢህአዴግ መንግሥት ሆኖ አገሪቱን እየመራ ባለበት 1980ዎቹ መጨረሻ በ«በሕገወጥ ብልፅግና» ተጠርጥረው የመጀመሪያው ተጠያቂ የሆኑት የወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ነበሩ። ያኔ አቶ ታምራት በራሳቸው አንደበት «ተመክሬ፣ ተዘክሬ አልሰማ ብያለሁ» ሲሉ በመሰማታቸው መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኛ ነው ተባለ፡፡ አቶ ታምራት «ዘርፈዋል» ተብለው ከታሰሩበት በእጅጉ የሚልቅ የሀገር ሀብት «ዘርፈዋል» ተብለው የተጠረጠሩ ደግሞ ዛሬ ክሳቸው ተቋርጦ በነፃ ሲለቀቁ እያየን ነው፡፡ መለቀቃቸው ጥሩ ቢሆንም የአለቃቀቁ ሂደት ግን ቀጣይ የፀረ ሙስና ትግሉን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡
የኢፌዴሪ የፀረ ሙስና ሕግ በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የዋስትና መብት የሚከለክል ሕግ ሆኖ ሳለ አንዳንዶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ተይዘው በዋስትና ይለቀቃሉ፤ አንዳንዶች ዋስትና ተከልክለው ፍርዳቸው እየተጓተተ በእስር ይንገላታሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ «ዘርፈው» ባገኙት ገንዘብ በተቀናጣ ሕይወት ካለ ተጠያቂነት ሲንደላቀቁ፣ ልጆቻቸውን ውድ ክፍያ የሚከፈልበት ትምህርት ቤት ሲያስተምሩ፣ ለትንሽ ሕክምና ውጭ አገር ሲመላለሱ ይታያሉ፡፡ «መንግሥት በሚከፍላቸው ደመወዝ ነው!» እንዳይባል መንግሥት የሚከፍላቸው ደመወዝ መጠኑ የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የተቀናጣ ኑሮ ከየት መጣ? ብሎ የሚጠይቅ ያለመኖሩ ሚዛናዊነትን የሚያጎድል ነው፡፡ ይህ ሚዛናዊነት መጓደል ቀጣይ የፀረ ሙስና ትግሉን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
በሙስና ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ ሰዎች፣ የተከሰሱበት ጭብጥ ታክስ እንዳይሰበሰብ በማድረግ በመንግሥት የገቢ ምንጮች ላይ ጉዳት በማድረስ፣ ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ከብዙ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ንብረትና ገንዘብ በማፍራት፣ በርካታ ሆቴሎች ከቀረጥ ነፃ ያስገቧቸው የሆቴል ዕቃዎችን ከታለመለት ዓላማ ውጪ እየተገለገሉበት መሆኑ መረጃ ደርሶ ክስ እንዳይመሠረትባቸው በማድረግ፣ ቤታቸውና በእርሻ ማሳ ውስጥ ሳይቀር ሻንጣ ሙሉ ዶላርና ዩሮን ጨምሮ የበርካታ አገራት ገንዘቦችና በርካታ የቤት ካርታዎች ተግኝቶባቸዋል... የሚል ነበር፡፡ አሁን ክሱ ሲቋረጥ እነዚህ ድርጊቶች አልተፈጸሙም ማለት ነውን? ይህ ከሆነ ደግሞ መጀመሪያውም በጥርጣሬ መያዝ አልነበረባቸውም ማለት ነው፡፡ ያለ በቂ መረጃ ሰዎችን ለእስር የዳረገ አካልም ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ በቀጣይ ሙስናን የሚጠቁም፣ የሚታገል አካል ዋስትና አይኖረውም፡፡ ስለሆነም ክስ የማቋረጡ ሂደት ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡
መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የታሰሩትን፣ ጦርነት በማወጅና ብጥብጥና ሁከት በማነሳሳት በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን እንዲሁም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ክሳቸውን እያቋረጠ በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡ ይህ ለሰላምና ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ሲባል የተወሰደ እርምጃ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝና የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡
ኪራይ ሰብሳቢነትን በተለይ ደግሞ ሙስና የአገሪቱና የሥርዓቱ አደጋ ነው፣ ሙስናን የሚሸከም ማህበረሰብ መፍጠር የለብንም እየተባለ በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ ተቃራኒ እርምጃ መውሰድ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ብቻ ክስ ማቋረጥ በሚዛኑ መሆን መቻል አለበት፡፡ ለሥርዓቱና ለሀገሪቱ አደጋ በሆነው ሙስና ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከአሁን በኋላ ለሚደረገው የፀረ ሙስና ትግል እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ለጠቋሚዎች፣ መርማሪዎችና አቃቤ ሕጎች ሞራል ይሆናል፡፡ ስለዚህ በሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረገው ክስ ማቋረጥ በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ እክል እንዳይፈጥር እየታሰበ መሆን አለበት፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።