Items filtered by date: Sunday, 10 June 2018

አንጋፋ ስፖርተኛ ናቸው። ለተሳተፉበት የስፖርት ዘርፍ በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም ኦሎምፒክ ፈር ቀዳጅ ናቸው። ይሄ ግነት ሳይሆን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ በገፆቹ የከተበው እውነት ነው። እኚህ ሰው ለአገር ባለውለታ ናቸው። ስፖርቱ አሁን ካለበት አንፃር ከተመለከትነው የእርሳቸው ሚና የእውነትም ገኖ ሊታየን ይችላል። ለመሆኑ እኚህ ስፖርተኛ ማን ናቸው? በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሳይክል ተወዳዳሪ፣ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ፈር ቀዳጅ፣ አሰልጣኝ እንዲሁም የጠንካራ ስብዕና ባለቤት ጋሽ ገረመው ደንቦባ።

ተነግሮ ከማያልቀው ስፖርቱ ዓለም ትዝታቸው ጥቂት እንዲያወጉን፤ የህይወት ጉዟቸውን እንዴት እንዳሰመሩት እንዲያጫውቱን፤ ለሚወዱት ስፖርት ዕድገት ያላቸውን ልምድ እንዲያጋሩን ከመኖሪያ ቤታቸው ተገኘን። ጋሽ ገረመውን ግን በጥሩ ጤንነት ላይ ሆነው አላገኘናቸውም። ጠንካራው ሰው ህመም አሸንፏቸው ከቤት ውለዋል። በህክምና ላይ እንደነበሩ ለመረዳት አያዳግትም። በአፍንጫቸው ላይ ኦክስጂን ሰክተዋል። እግራቸው ላይ ያጋጠማቸው ጉዳት ብዙም አያራምዳቸውም። እንደዚያም ሆኖ ግን እኛን በእንግድነት መቀበል አላቃታቸውም። እንዳደጉበት ባህል ተቀበሉን። ለጥያቄያችንም ሳይሰስቱ ከታሪክ ባህራቸው እየጨለፉ አጫወቱን። ብዙ የመውጣት እና የመውረድ የህይወት ሂደቶች ላይ አወጋን። ነገር ግን ወደኋላ ተመልሰን የጋሽ ገረመውን የስፖርት ህይወት ከመዳሰሳችን በፊት በቅድሚያ ይህን ማለት ወደድን።
እኚህ ባለታሪክ ከቤት ውለዋል። በእርሳቸው ዘመን ባላቸው ጥንካሬ ለአገር በብስክሌት ስፖርት ፈር ቀዳጅ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። እነ አበበ ቢቂላን፣ ማሞ ወልዴ፣ ይድነቃቸው ተሰማ ለዚህች አገር ከሰሩት ውለታ በማይተናነስ በብስክሌት ስፖርት ላይ ተጠቃሽ ሥራ የሠሩ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የታሪክ ዶሴዎችን በቀላሉ መግለጥ በቂ ነው። ስለዚህ እኚህን ጀግና ማወደስ፤ ከዚያም ባለፈ በህመማቸው ሰዓት ከጎናቸው መሆን ይኖርብናል። ጀግናን በህይወት እያለ የማወደስ ልምድ ሊኖረን ይገባል። እንደ እድል ሆኖ ብዙ ጀግኖቻችንን ሳናሞግሳቸው ካጠገባችን ተለይተውናል። ይህን ስህተት ሁሌም መድገም ሊበቃን ይገባል። ሁሉም ባለው አቅም ባለውለታ የሆኑ ስፖርተኞችን እውቅና ሊሰጥ ይገባል ።
የጣሊያን ወረራ
የጋሽ ገረመው የትውልድ ከተማ አዲስ አበባ ነው። አንዋር መስጊድ ፊት ለፊት ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ነው ተወልደው ያደጉት። ጣሊያን ዓይኑን በጨው አጥቦ ኢትዮጵያን በድጋሚ ለመውረር ሲገባ የያኔው እምቦቃቅላ የዛሬው አንጋፋ ስፖርተኛ ጋሽ ገረሞ ከተወለዱ የአንድ ዓመት እድሜ አስቆጥረው ነበር። በወቅቱ ለኢትዮጰያውያን መርገምትን ይዞ ከተፍ ያለው ፋሽስት ግን ለርሳቸው የወደፊት ህልም ፈር የቀደደ አጋጣሚን ፈጥሮ ነበር። መቼም ሁሉም ነገር መጥፎ አይሆንም። ወራሪ ወታደሮቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የጣሊያን ስሪት የሆኑትን እነ ቢያንኪሊ፣ባርታሊ እንዲሁም ቦንሲት የሚል ስያሜ ያላቸው ብስክሌቶችን ይዘው ገብተው ነበር። ታዲያ እነዚህ ብስክሌቶች ፋሽስት በጀግኖች ዓርበኞች ድል ተደርገው ከኢትዮጵያ ሲወጡ በምርኮነት አገር ውስጥ ቀርተው ነበር።
ፋሽስት በአምስት ዓመት የቆይታ ጊዜው ወታደሮቹ በአዲስ አበባ ብስክሌቶችን በጎዳናዎች ላይ በመንዳት፣ ሰዎችን በማለማመድ እና ውድድር በማካሄድ የኢትዮጵያውያንን ልብ ለመማረክ ጥረት ያደርግ ነበር። በወቅቱ በዓለም ላይ በተለይ በፈረንሳይ፣ ቤልጄም እንዲሁም ሆላንድ የመሳሰሉ አገራት ብስክሌት ተወዳጅ እና ቀዳሚው ስፖርት ነበር። ለዚህ ስፖርት ኢትዮጰያውያኑ እንግዳ ቢሆኑም በቀላሉ እውቀቱን በመቅሰም ጥሩ ችሎታን አዳብረው ነበር። በጎዳናዎች ላይ እንደድንገት ከወራሪዎቹ ጣሊያኖች ጋር ሲገናኙ እንኳን በቀላሉ እያለፏቸው ይጓዙ ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ ፋሽስት ከአገሪቷ ሳይወድ በግዱ ተባረረ። የብስክሌት ስፖርት ግን በኢትዮጵያ ተወዳጅነቱ ቀጠለ። ድሮውንም ኢትዮጵያውያን ከፋሽስት እንጂ ከስፖርቱ ቂም አልነበራቸውም። የወደፊቱ ባለታሪክ ጋሽ ገረመውም ጣሊያን ሲወጣ ስድስት ዓመት ሞላቸው። ዕድሜያቸው ለአስኳላ ደርሶ ዘመናዊውን ትምህርት ተያይዘውት ነበር።
ከብስክሌት ጋር ወዳጅነት
የጋሽ ገረመው ብስክሌትን የተዋወቁት ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ውድድሮችን በመመልከት ነው። በአምስት እና ስድስት ዓመታቸው እነ ካሳ ፈዲር፣ ኤርትራዊው ካሳ ርእሶም፣ ሙሉጌታ ካሳ፣ታዬ ክፍሌ የሚባሉ ብስክሌተኞች ከአንዋር መስጊድ ፊት ለፊት እነኡስማን ኪኪያ ሱቆች አካባቢ እነ እራስ ሃይሉን የመሳሰሉ ታላላቅ መሳፍንት እና መኳንንቶች በክብር ቦታቸው ላይ ተቀምጠው ውድድር ሲያደርጉ ሲመለከቱ ጋሽ ገረመውም በራፋቸው ላይ ሆነው በደረታቸው ተኝተው ይከታተሉ ነበር። ከስፖርቱ ጋር ወዳጅነት የጀመሩትም በዚያን ወቅት ነበር።
ጋሽ ገረመው በአንዋር መስጊድ ቢያጆ ተራ ብስክሌት እያከራዩ የሚያለማምዱ ልጆች ጋር በሰባት ዓመታቸው ግንኙነት ጀመሩ። አምስት እና አስር ሳንቲም ከቤተሰቦቻቸው እየወሰዱ በመክፈል ልምምዳቸውን አጧጧፉት። ቁመታቸው ገና ቢሆንም እግራቸውን በፔዳሉ መሀከል እያሾለኩ ቆመው በመጋለብ ተለማመዱ። በዘጠኝ ዓመታቸው የብስክሌቱ ኮርቻ ላይ መቀመጥ ቻሉ። እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ግን ከብስክሌቱ ጋር ግንኙነታቸው እየጠነከረ መጣ።
ጋሽ ገረመው ለቤተሰቦቻቸው አስራ አንደኛ ልጅ ናቸው። ሆኖም እናታቸው ወይዘሮ ቶላ ኢጀሬ ለእርሳቸው የተለየ ፍቅር ነበራቸው። በኮኮበ ፅባህ ትምህርት ቤት በእግራቸው እየተመላለሱ ይማሩ ስለነበርም ለልጃቸው ብስክሌት በ30 ብር ገዝተው ለመስጠት አላመነቱም ነበር። የግል ብስክሌት ገና በልጅነታቸው በእጃቸው በማስገባት ከቤት ወደ ትምህርት ቤት፤ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ጓደኞቻቸውን እያፈናጠጡ (ከኋላ እየጫኑ) ይመላለሱ ጀመር። ይሄ ደግሞ የብስከሌት የመንዳት ብቃታቸውን እና ጥንካሬያቸውን እየጨመረው መጣ።
ጊዜው 1943 ዓ.ም ነው። በአካባቢያቸው የታዳጊዎች እና ወጣቶች የብስክሌት ውድድሮች ይካሄዱ ነበር። ታዲያ የያኔው ታዳጊ ጋሽ ገረመው በዚህ ውድድር ላይ በመሳተፍ ድል ማድረግን አሀዱ አሉ። ለተራ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚጠቀሙባት ብስክሌት ጓደኞቻቸውን ከኋላ አስከትለው ውድድሩን ሰባተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀቁ። 70 የሚደርሱ ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ነበሩ። በጊዜው ለርሳቸው ጥሩ ውጤት ቢሆንም እንዴት አንደኛ መውጣት አልችልም? የሚል ቁጭት ውስጥ ከቷቸው ነበር። ጓደኞቻቸውን እያፈናጠጡ የጀመሩት የሳይክል ስፖርት በውድድሮችም እየተገነባ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስፖርት ተክለ ሰውነታቸው እና ጡንቻቸው እየፈረጠመ መጣ። ከተራ ፍቅር ቅልጥ ወዳለው የብስክሌት ሱስ ውስጥ ተንደርድረው ገቡ።
ጊዜው 1945 ዓ.ም። ጋሽ ገረመው እግሮቻቸው ደንበኛ የብስክሌት ሞተር ሆነዋል ድካም የሚባል ነገር አይታይባቸውም። ትምህርታቸውን እየተማሩ አንድ ውድድር ላይ ተካፈሉ። መነሻ እና መድረሻው አሮጌው ፖስታ ቤት የነበረውን አስራ አምስት ዙር ሁሉንም ተወዳዳሪዎች (ሁለተኛ የወጣውንም ጭምር) በመደረብ በድል አጠናቀቁ። አንድ እና ሁለት ተጨማሪ ልጆችን በብስከሌታቸው ላይ በመደረብ ትምህርት ቤት የሚመላለሱት ሰው ብቻቸውን ውድድር ላይ ሲቀርቡ ሁሉም ነገር ቀሏቸው ነበር። ውድድሩን በበላይነት በማጠናቀቃቸው 25 ብር እና እሽግ ብስኩቶችን ተሸለሙ። ሽልማታቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው ሲገቡ እናታቸው የማሪያም ፀበል ፀዲቅ ከጎረቤቶቻቸው ጋር እየቀመሱ ነበር። ብስኩቱ ለማህበርተኛው ታደለ። እናታቸው «ልጄ አሸንፎ መጣ እንኳን ደስ አላችሁ» አሉ ማህበርተኞቹም የምርቃት መዓት አዥጎደጎዱ። ሌላ ተጨማሪ ድል።
ውድድሩን ኤርትራ ውስጥ ያደገው የያኔው ሲዳሞ ተወላጅ ፈረደ ካሳ ፣ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ እንዲሁም አንድ ሌላ ኤርትራዊ በጋራ በመሆን ነበር እንዲጀመር ያደረጉት። ፈረደ በጊዜው የብስክሌት መካኒክ እና እውቅ ባለሙያ ነበር። እያደር ግን ክለቦች መቋቋም እና ብስክሌት ስፖርት ፈር እየያዘ መምጣት ጀምሮ ነበር። ለገሀር ፣መቻል፣ የምድር ጦር እንዲሁም አውራ ጎዳናን የመሳሰሉ ክለቦችም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ጋሽ ገረመው በዚህ አይነት ሁኔታ ለሁለተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ውድድር ላይ በድጋሚ ከአስራ አምስት ቀን በኋላ አሸናፊ ሆኑ። የ50 ብር እና የብስክሌት ጎማ እንዲሁም አንድ ቪኖ ተሸለሙ። ድልን ገና በልጅነታቸው የጀመሩት ጋሽ ገረመው በግዜው በነበሩ ክለቦች ዓይን ማረፊያ ሆኑ። በግል ስለሚወዳደሩም አድራሻቸው ጠፍቷቸው ብዙ ባከኑ። አንድ ወቅት ላይ ግን ያልተጠበቀ አጋጣሚ ተፈጠረ።
ያልተጠበቀው ስምምነት
ውድድሮችን በአዲስ አበባ በማዘጋጀት ይታወቃል። የብስክሌት አባት ነው ይሉታል ጋሽ ገረመው። ጊዜው በ1940ዎቹ ነው። የወልዎል ብስክሌት ክለብ የያኔውን ጠንካራ ብስክሌተኛ ለማድረግ አጥብቆ ይፈልጋል። ሁለተኛው ድላቸውን ባጣጣሙ ማግስት ሰኞ ዕለት ትምህርት ቤት አቶ ፈረደ «ቮልሲክ» የምትባል ታዋቂ የመወዳደሪያ ብስክሌት ይዘው በቀበና ትምህርት ቤት ከተፍ አሉ። ጋሽ ገረመው ከጓደኞቻቸው ጋር ነበሩ። «ገ ገረመው ይሄ ብስክሌት ያንተ ነው ያዝ። አሁን ለኛ ክለብ ትወዳደራለህ እናስፈርምሀልን» አሏቸው። ያልተጠበቀ ንግግር ነበር። በዚያ ላይ አዲስ ብስክሌት ሰጧቸው። በውስጣቸው ግርታ ተፈጠረ። እናታቸውን ይወዳሉ። ቃላቸውን ይጠብቃሉ። በዚህ ክለብ ቢሳተፉ ሊቆጧቸው ይችላል። ስለዚህ ችግሩን ለአቶ ፈረደ አጫወቷቸው። እርሳቸው ከእናታቸው ጋር እንደሚነጋገሩ እና እንደሚያስፈቅዱላቸው አሳምነው አዲሱን ብስክሌት ሰጧቸው። እየበረሩ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
አቶ ፈረደ ከእናታቸው ጋር ተነጋግረው አስፈቀዱ። የሚወዷቸው እናታቸው ትምህር ታቸውን ሳይቦዝኑ ከተከታተሉ በብስክሌቱም ቢሳተፉ ቅር እንደማይላቸው ገለፁ። አቶ ፈረደም በዚህ ተስማምተው የመጀመሪያውን ክለባቸውን አስተዋወቋቸው። አዲስ ብስራት፤ ሌላኛው የህይወት መንገድ ነበር። ለጋሽ ገረመው በእርግጥም ከብስክሌት ስፖርት እንደማይለዩ ማረጋገጫ ነበር። እናታቸው የመጀመሪያውን ብስክሌት በመግዛት ፈር የቀደዱ ናቸው። ባለውለታ።
አሁን እድሜያቸው15 ዓመት ሞልቷል። ገና ታዳጊ ናቸው። ወደ ወልወል ክለብ ተቀላቅለዋል። አራት እና አምስት ውድድሮችን አድርገው ጠንካራ በመሆናቸው ከታዳጊዎቹ ተነጥለው ወደ ወጣት ተወዳዳሪዎች ጋር ተቀላቀሉ። በየውድድሩ ላይ ትልቅ ፈተና ይሆኑባቸውም ጀመር። የመጀመሪያው ውድድር ላይ 13ተኛ፤ በሁለተኛው 4ተኛ፤ በሦስተኛው ደግሞ አንደኛ ደረጃን በመያዝ በፍጥነት ከወጣቶቹ ጋር ፉክክር ውስጥ ገብተው ድል ማድረግ ጀመሩ። አሁን እርሳቸውን ማቆም ከባድ ነው። በክለቡ ቴክኒካል እውቀቶችን እና ሳይንሳዊ የብስክሌት ታክቲኮችን ለመዱ። ይህ ደግሞ ተስፈንጣሪ እና ፈጣን ተወዳዳሪነታቸውን አስመሰከረላቸው። ከባድ በሆነው ቁልቁለት ላይ እንኳን ከተፎካካሪዎቻቸው አፈትልከው መውጣት ቻሉ። ዳገትን ደግሞ ንብረታቸው አደረጉት።
ጋሽ ገረመው ከ1945 እስከ 1955ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና በዓለም የኦሎምፒክ ታሪክ ላይ ታሪክ የሰሩበት ዘመን ነው። በ1946 ከጠንካራ ኤርትራዊያን ጋር በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሆለታ ደርሶ መልስ 20 ዙር ውድድር ላይ 11 ዙር ታዋቂና ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን በመደረብ ጣፋጭ ድል አስመዘገቡ። ጃንሆይ በተገኙበት በዚህ ውድድር ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ለጋሽ ገረሞ በልዩ ብቃታቸው ተማርከው የወርቅ ሰዓታቸውን ከእጃቸው በማውለቅ ሸልመ ዋቸዋል።
ሜልበርን የመጀመሪያው
የኦሎምፒክ ተሳትፎ
በአገር ውስጥ ጋሽ ገረመውን ማቆም ከባድ ነው። በብስክሌት ስፖርት ታዋቂ የነበሩትን ኤርትራዊያንን ሳይቀር በማንበርከክ በርካታ ድሎችን ተጎናፅፈዋል። አሁን አዲስ ታሪክ የሚያስመ ዘግቡበት ወቅት ነው። ለዚህ ደግሞ አንድ አጋጣሚ ተፈጥሯል። በጊዜው ዓለም ላይ ስፖርቱ ተወዳጅነቱ ከፍተኛ ነበር። የኦሎምፒክ ስፖርት ላይ ደግሞ በቀዳሚነት ተካቶ ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን ያፎካክር ነበር። ኢትዮጵያውያን የስፖርቱ ወዳዶች ደግሞ ጋሽ ገረመው በዚህ ውድድር ላይ ቢሳተፉ አሸናፊ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምታቸውን ያስቀምጡ ነበር። ለእርሳቸ ውም ተሳታፊ እንዲሆኑ ግፊት ያደርጉላቸው ጀመር። «እንኳን ዘንቦብሽ...» እንደሚባለው የአገሬ ብሂል እርሳቸውም በዚህ መድረክ ላይ ተሳትፈው ፈር ቀዳጅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ለመሆን ትልቅ ፍላጎት አደረባቸው። ከዚያስ ምን ተፈጥሮ ይሆን?
ጋሽ ገረመው ከንጉስ ከቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ እጅ በስፖርቱ አሸናፊ በመሆናቸው ሁለት ዋንጫዎችን ተሸልመዋል። ይሄ ደግሞ በጃንሆይ እንዲታወቁ ዕድሉን አመቻችቶላቸዋል። በመሆኑም በአውስትራሊያው ሜልቦርን የኦሎምፒክ ውድድር ተሳታፊ ሆነው ታሪክ ለመስራት ለሚያቀርቡት የድጋፍ ጥያቄ ቀና መልስ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ አልተጠራጠሩም። ስለዚህ ደብዳቤ ለንጉሱ ለመፃፍ ተነሱ። «በአገሬ ለበርካታ ዓመታት የብስክሌት ሻምፒዮና ሆኛለሁ። በሜልቦርን በሚካሄደው ኦሎምፒክ ላይ በዚሁ ስፖርት ተሳታፊ ብሆን ለአገሬ ጥሩ ስም አስገኛለሁ» በማለት በራሳቸው የእጅ ፅሁፍ ጥያቄያቸውን አቀረቡ።
ጃንሆይ እሁድ እሁድ ወደ ደብረዘይት ያቀናሉ። ጋሽ ገረሞ ደብዳቤውን በአካል ለጃንሆይ ለማቅረብ ፈልገዋል። በአራተኛ ክፍለጦር መሿለኪያ በሚባል አካባቢ ነበር ንጉሱ ወደ ደብረዘይት የሚያልፉት። ሦስት እሁዶችን በዚህ አካባቢ ጥያቄውን ለማቅረብ መጠባበቅ ጀመሩ። በአራተኛው ተሳካላቸው። በብስክሌታቸው ላይ ሙሉ ትጥቃቸውን እንደለበሱ፤ ደብዳቤያቸውን ይዘው ወደ ጃነሆይ መኪና ተጠጉ። በንፋስ ስልክ አድርገው አቃቂ አብረዋቸው በብሰክሌት ተከተሏቸው። ደብዳቤያቸውን ከኪሳቸው በማውጣት ከጃንሆይ መኪና ትይዩ በመሆን ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ንጉሱ ትእዛዝ በመስጠት አስቆሙ።
ጄኔራል መኮንን ደነቀ የእልፍኝ አስከልካይ ፅህፈት ቤት ሹም ጋሽ ገረመውን ወደ ጃንሆይ ይዘዋቸው ቀረቡ። እርሳቸውም «ከዓለም መወዳደር እፈልጋለሁ» ሲሉ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ኢትዮጵያ ተሳትፎ እንዲኖራት ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ አቀረቡ። ጃንሆይም «ከዓለም መወዳደር እንደምችል በምን አወቅክ» የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው በሰዓት 42 ኪሎ ሜትር እንደሚፈጥኑ መተማመኛ ሰጧቸው። በጊዜው የዓለም ፈጣን ብስክሌተኞች ሰዓትም ተመሳሳይ ነበር። ጃንሆይ ይህን ሲያውቁ «ማለፊያ» በማለት ለማክሰኞ በቤተ መንግሥት ቀጠሮ ሰጧቸው። ይህ ወቅት ለርሳቸው የፈንጠዝያ እና የደስታ ሲቃ ያስተናገዱበት የማይረሳ ጊዜ ነበር።
በቀጠሮው መሰረት ማክሰኞ በቤተ መንግሥት ተገኙ። ሙሉ ልብሳቸውን ግጥም አድርገዋል። በጊዜው ታዋቂ ስፖርተኛ ስለነበሩ በቤተ መንግሥት ሲገኙ እልፍኝ አስከልካዩ ቅድሚያ እንዲሰጧቸው አደረጉ። ከጃንሆይ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወደ ደብረዘይት ሲሄዱ ያደረጉትን ቆይታ በድጋሚ በማንሳት የኦሎምፒክ ተሳትፎው እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቀረቡ። ጃንሆይ ፍቃዳቸውን ሰጧቸው። በሚያስፈልገው ሁሉ ትብብር እንዲደረግላቸው ትእዛዝ አስተላለፉ። የደስታ ሲቃ። የሀሴት መቅበዝበዝ በጋሽ ገረመው ላይ ይስተዋል ነበር። ጊዜ ማጥፋት አላስፈለጋቸውም ከአጋሮቻቸው ጋር ተሳትፎውን እውን ለማድረግ ሩጫውን ተያያዙት። አዲስ የታሪክ ዶሴ ኢትዮጵያ በሜልቦርን ኦሎምፒክ አንድ ብላ ከፈተች። የፊት አውራሪነቱን ሚና ደግሞ ጋሽ ገረመው ተረከቡ።
በጊዜው ተሳትፎውን ለማድረግ ፈተና የነበረው በአገሪቷ በሁሉም ስፖርቶች ላይ ፌዴሬሽኖች እና የተጠናከሩ ክለቦች አለመኖራቸው ነበር። በኦሎምፒክ ላይ ተሳታፊ ለመሆን የግዴታ አንድ አገር አምስት የተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ሊኖሯት እና ልታሳትፍ ይገባ ነበር። ነገሮች ትንሽ ቢወሳሰቡም በግሪካዊው ሙሴ ኤድዋርዶ ቢልቢሪስ ዓለም አቀፍ የውድድር ልምድ፤ በንጉሴ ሮባ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፀሃፊ፤ እስጢፋኖስ መንግስቱ የቦክስ ፌዴሬሽን ፀሀፊ እንዲሁም ጋሽ ገረመው ደንቦባ የብስክሌት ፌዴሬሽን ፀሀፊ በማድረግ በፍጥነት አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ኢትዮጵያ በኦሎምፒኩ እንድትሳተፍ ተደረገ። ይህ ሁሉ የሆነው ጋሽ ገረመው «በኦሎምፒክ ልሳተፍ» በማለት ባስገቡት ደብዳቤ መሰረት ነበር።
ያልተጠበቀው ክስተት
የብስክሌት፣ የቦክስ እንዲሁም የአትሌቲክስ ስፖርት ቡድን በ1948 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውስትራሊያ አቀና። ሰባት ቀን ሰባት ሌሊት የፈጀ ከባድ ጉዞ ነበር። ሜልቦርን እንደደረሱም በሆቴል ላይ መጉላላት ደርሶባቸዋል። ማረፊያ ሆቴላቸው ምቹ አልነበረም። በኢትዮጵያ የሰሩት ልምምድ መና ቀርቷል። የአትሌቲክስ ተወዳዳሪዎቹ ባሻዬ ፈለቀ፣ ገብሬ ብርቄ፣ ማሞ ወልዴ ፣መራዊ ገብሩ፣ንጉሴ ሮባ በአስር ሺ፣በመቶ እና በስምንት መቶ እርቀት በኦሎምፒኩ ላይ ተሳታፊ ነበሩ። ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ስፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትሳተፍ ፈር የቀደደው የጋሽ ገረመው ቡድን ደግሞ መንግስቱ ንጉሴ፣ ፀሀይ ባህታ፣ መስፍን ተስፋዬ የያዘ ነበር። በውድድሩ ወቅት እንደ ቡድን ከዓለም ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ጋሽ ገረመውም በግል ከአገራቸው ቀዳሚ በመሆን የ24ተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን አጠናቀዋል።
በዓለም ታሪክ በኦሎምፒክ ስፖርት ኢትዮጵያ በጋሽ ገረመው ጥረት የመጀመሪያው ጥቁር ተሳታፊ እና አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ቻለች። በታሪክ ዶሴ ላይም ከአፍሪካውያን ቀዳሚ ሆነች። ባለውለታው ጋሽ ገረመው እንዲህ ይላሉ «አፍሪካውያን በሙሉ ጨርሶ ነፃነታቸውን ባልተጎናፀፉበት ወቅት ኢትዮጵያ የዓለም ኦሎምፒክ ተሳታፊ ሆናለች» ከዚህ በላይ ጎልቶ የሚታይ የኮራ ስብእና ከየት ይገኛል። ለዚህ የደመቀ ታሪክ መሰራት ደግሞ ጋሽ ገረመው የፊት መስመሩን ይይዛሉ። እርሳቸውም በኦሎምፒክ ታሪክ በሳይክል ውድድር ላይ የተሳተፈ የመጀመሪያው ጥቁር ተወዳዳሪ በመሆን አኩሪ ገድል ሰሩ
ሮም ኦሎምፒክ አሳዛኙ አጋጣሚ
ጊዜው 1962 ነበር። የሮም ኦሎምፒክ ተሳትፎ። አሁን ፈር ተቀዷል። በድጋሚ ኢትዮጵያን ለመወከል ጋሽ ገረመው፣ አድማሱ መርጊያ፣ አላዛር ክፍሎም እና ጆቫኒ ማሶላ ሮም ላይ ተገኝተዋል። ውድድሩ ተጀምሯል። በመጀመሪያው የኦሎምፒክ ተሳትፎ ጥሩ ብቃት ያሳዩት ጋሽ ገረመው በዚህኛው ውድድር ከፍተኛ የማሸነፍ እድልን ይዘዋል። አጠቃላይ ውድድሩ 11 ዙሮች ነበሩት። ከመጀመሪያው ጀምሮ ተስፈንጣሪው ጋሽ ገረመው መሪ ሆኑ። አንደኛው፣ ሁለተኛው፣ ሶስተኛው ዙር። አሁንም እየመሩ ነው። እንዴት ነው ነገሩ። ሰባተኛው ዙር። አሁንም ጋሽ ገረመው ከፊት ናቸው። ስምንተኛው ዙር ተመሳሳይ ነበር። ዘጠነኛው ዙር ላይ ግን ቀዳሚ የማሸነፍ እድል የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ያልተጠበቀ አደጋ አጋጠማቸው። ከብስክሌታቸው ላይ ወደቁ። መገፋፋት ነበር። ነገርዬው ሳይሳካ ቀረ። ሆኖም ለ9 ዙር የሮሙን የብስክሌት ውድድር በመምራት ሰፊ ሙገሳ እና ክብርን በማግኘት በድጋሚ ታሪክ ሰሩ። ጋሽ ገረመው በድንገተኛው አጋጣሚ ከውድድሩ በጉዳት ቢወጡም፤ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮምን ወሮ የጓደኛውን ሀዘን በደስታ አካካሰው። ሌላ ታሪክ በሮም አደባባይ ተሰራ።
ጋሽ ገረመው በብስክሌት ስፖርት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይም የብስክሌቱን ልኡካን ቡድን በአሰልጣኝነት በመምራት አገልግለዋል። ከዚያም በኋላ ለረጅም ዓመታት በአሰልጣኝነት ለአገር ውለታ ሰርተዋል። በምላሹ ግን ለአገራቸው ክብር እግራቸው ተሰብሮ ብረት ሲያጠልቁ «አባ ከና» ያላቸው አካል የለም።
በመጨረሻም እንመሰጋገን...እንወቃቀስ
ከግል ጥረቶች በቀር እርሳቸውን ለማክበር እና ለማስታወስ እጃቸውን የያዛቸው አካላት ምን አጋጥሟቸው ይሆን? እርሳቸው ግን «አረ የኔስ ይቅር» ከኔ በተሻለ ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት ህይወታቸውን በመክፈል ፈር ለመጣል የታገሉት እነ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማስ ቀጨኔ በር ላይ ተጥለው አስታዋሽ አጥተዋል» ይላሉ። አዲስ ዘመን ስፖርትም ይህን ትጠይቃለች «ይህ አይነት ቸልተኝነት እውነት ተገቢ ነው?»
ጋሽ ገረመው አሁንም ለአገሬ ውለታዋን ከፍዬ አልጨረስኩም ይላሉ። ባላቸው አቅም እና ልምድ አሁንም ድረስ የማማከር ሥራ መሥራት እንደሚችሉም ይናገራሉ። በግል ትግል የብስክሌት ስፖርትን ለማሳደግ ጥረት የሚያደርጉትን የብስክሌት የበላይ ጠባቂ አቶ ነብዩ ሳሙኤል ፈረንጅን እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትንም ያመሰግናሉ። የዘኮሊና ኮንስትራክሽን እና የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ወደ ከአዲስ አበባ መነሻውን ያደረገ ቱር በማዘጋጀት እኚህን አንጋፋ ሰው ለማስታወስ ጥረት አድርገዋል። የሰሜን አሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም እንዲሁ በተመሳሳይ እውቅና ሰጥቷቸዋል። ለእርሳቸው ግን ይሄ ብቻ በቂ አይደለም። ምክንያቱ ጀግና በዚህ ብቻ አይከበርም። የኦሎምፒክ ኮሚቴና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የት ነው ያሉት? ነው «በእጅ የያዙት ወርቅ...» ሆኖባቸው ይሆን? ሰላም!

ዳግም ከበደ

 

Published in ስፖርት
Sunday, 10 June 2018 22:47

ሰኔ ግን 30 ቀን ብቻ ነው?

እስኪ ስለሰኔ ሳይንሳዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተረታዊ ብያኔዎቹ እናውራ፡፡ እንዲያውም የሰኔን ተረታዊነት እናስቀድም፡፡ ከወራት ሁሉ ስማቸው ተደጋግሞ የሚጠሩ ወሮች መስከረምና ሰኔ ይመስሉኛል፡፡ በተረትና ምሳሌ እንዲያውም ሰኔ ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ «ሰኔ መቃጠሪያ ህዳር መገናኛ»፣ «ሰኔ ነግ በኔ»፣ «ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ»፣ «ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል»፣ «በሰኔ ገመሻ በበጋ ጤፍ እርሻ…» የሚሉ ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉ፡፡ ምሳሌያዊ አነጋገር ብቻ ሳይሆን ፈሊጣዊ አነጋገሮችም አሉት፡፡ ‹‹ሰኔና ሰኞ›› የሚለውን አታውቁትም? ይህንማ ማንም ያውቃል፡፡
ሰኔና ሰኞ ማለት እንደ ፈሊጣዊ አነጋገር ድንገተኛ አጋጣሚ ማለት ነው፡፡ ይሄውም ሰኔ አንድ ሰኞ ዕለት ሲውል ማለት ነው፡፡ አይ እኮ የልማድ ነገር፡፡ ሰኔ አንድ ቀን ሰኞ ዕለት ከዋለ አደጋ ይፈጠራል ተብሎ ይፈራል፡፡ ይሄ ለምን ሆነ ብለን ብንጠይቅ ከአፈ ታሪክ የዘለለ ተጨባጭ ነገር ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ምናልባት ግን እንዲህ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነ ዓመት ላይ ሰኔ አንድ ቀን ሰኞ ዕለት ይውላል፤ በአጋጣሚ በዚያን ዓመት የሆነ አስገራሚ ነገር ከተፈጠረ በዚያው ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሌላ አጋጣሚ ይጨመርብህ ካለው ደግሞ ከተወሰነ ዓመታት በኋላም ሰኔ አንድ ቀን ሰኞ ዕለት ውሎ ያጋጠመ ነገር ካለ በዚያው ይለመዳል፡፡
እስኪ አሁን ደግሞ ከተረታዊ የሰኔ ብያኔዎች ወደ ሳይንሳዊ እንሂድ (አንዳንዴ የሳይንስ ሊቅም ያደርገኛል)፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ የተማርኩት የሳይንስ ትምህርት የህልም ያህል ትንሽ ትንሽ ትዝ ይለኛል፡፡ እናም ከ6ኛ ክፍል ትምህርቴ አንፃር (ሻሼ ስታይል) ሰኔን ስተነትነው የክረምት ወር መጀመሪያ ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው ብዙ ተረትና ምሳሌዎች ከታታሪነት ጋር የተያያዙት፡፡ «ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል» የተባለው ገበሬ ጠንካራ መሆን ያለበት በሰኔ ስለሆነ ነው፡፡ «ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ» የተባለውም ሰኔ የክረምት ወር መጀመሪያ ስለሆነ በወቅቱ መሰራት አለበት ለማለት ነው፡፡ «ሰኔ መቃጠሪያ ህዳር መገናኛ» የተባለውስ ለምንድነው?
ይቺኛዋን ለማብራራት አሁን ካለንበት ዘመን ወደኋላ መለስ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ ይህ የተባለው እንደ አሁኑ ድልድይና መኪና ባልነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ከሰኔ ጀምሮ ክረምቱን ሙሉ ወንዞች ስለሚሞሉ የወዲያ ማዶ ሰውና የወዲህ ማዶ ሰው የሚገናኘው የክረምት ወራት አልቆ ወንዞች ሲጎሉ ነው፡፡ ሰኔ ሲመጣ ወንዝ እንደሚሞላ ስለሚያውቁት ‹‹በሚቀጥለው ዓመት እንገናኝ›› ብለው ይቀጣጠራሉ ማለት ነው፡፡
ኢ-ሙያዊ ትንተናዬ ይቀጥላል፡፡ የሰኔ ወር ባህላዊ አንደምታም አለው፡፡ እንዴት? ማለት ጥሩ ነው፡፡ አሁን ቀጥ ብለን ወደ እኛ ቤት ፓርላማ እንገባለን! በነገራችን ላይ የእኛ ቤት በየዓመቱ ሰኔ ወር ላይ በጀት ያጸድቃል፡፡ እንዲያውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚያጸድቀው ይለያል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እኮ የሚያጸደቀው ብር ብቻ ነው፡፡ የእኛ ቤት ፓርላማ ግን የሚያጸደቀው ሽሮና በርበሬ ጭምር ነው፡፡ በየዓመቱ የሰኔ ወር ላይ እኮ ‹‹የእኛ ቤት ፓርላማ›› እያልኩ ነግሪያችሁ ነበር፤ ወይስ ትንሽ መገረብ ያስፈልጋችኋል? በነገራችን ላይ «መገረብ» ማለት አራድኛ ሲሆን መድገም ማለት ነው (እግረ መንገዳችንን አራድኛም እንማር ብየ ነው)፡፡
ወደ እኛ ቤት ፓርላማ እንመለስ፡፡ ፓርላማው የሚያቀርበው የሽሮና የበርበሬ በጀት በሙሉ ድምጽ ላይጸድቅ ይችላል፡፡ ድምጸ ታቅቦ የሚባል ነገር ግን የለም፤ ወይ መቃወም ነው ወይ መደገፍ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የፓርላማው አባላት(የቤተሰቡ አባላት በሚል መረዳት እኮ ነው) ወስነው ለክረምት የሚበቃ ሽሮና በርበሬ ይጸድቃል፡፡ የምር ግን እዚህ ላይ አንድ ቁም ነገር እናውራ፡፡
በገጠር አካባቢ የሰኔ ወር የተለየ ቦታ አለው፡፡ የክረምት ወር መጀመሪያ ስለሆነ ሁሉ ነገር መዘጋጀት አለበት፡፡ ምክንያቱም ዋናው ክረምት ከገባ ሁሉም የቤተሰብ አባላት በሥራ የሚዋክቡበት ነው፡፡ ከዱር ያለው የግብርና ሥራ ላይ እንጂ ሽሮና በርበሬ ማዘጋጀት ላይ ሥራ መፍታት አይፈልጉም፡፡ ምክንያቱም ሽሮና በርበሬው ቀድሞ መዘጋጀት ይችላል፤ የእርሻ ሥራ ግን ወቅታዊ ነው፤ የዝናቡን መኖር ተከትሎ ብቻ የሚታረስ ነው፡፡ በተለይ የጤፍ እርሻ ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ወቅት ማንም ወለም ዘለም ማለት አይችልም፡፡
የሰኔ ወር የክረምት መጀመሪያ መሆን አካባቢያዊ ብቻ ሳይሆን ፌዴራላዊ አንደምታም አለው፡፡ ለምሳሌ በሰኔ ወር ብዙ ነገሮች ይዘጋሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ፣ አንዳንድ ተቋማት ይዘጋሉ(በተለይ በገጠር አካባቢ)፣ የመንግስት ዓመታዊ በጀት እንኳን የሚጸድቀው በሰኔ ወር ነው፡፡ ለምሳሌ የዘንድሮው የ2011 በጀት ጸድቋል፡፡ የሰኔ ወር የክረምት መጀመሪያ መሆኑ እንደ ልማድ ባይሆን ኖሮ የ2011 በጀት የሚጸድቅ መስከረም ወር ላይ ነበር፤ ምክንያቱም ሰኔ ማለት ገና 2010 ነው፡፡
የሰኔ ወር ብዙ ትዝታዎች አሉት፡፡ ለሰራተኛ ትዝታ አለው፣ ለተማሪ ትዝታ አለው፤ ለእረኛ ትዝታ አለው፡፡ ደግሞ የእረኛ ትዝታ ምንድነው የሚል ካለ የከተማ ልጅ ነውና ወደ እኔ ይምጣ፡፡
እረኛ ከሌሎች ወራት በተለየ ክረምት ጫና ይበዛበታል፡፡ ምክንያቱም በክረምት በየአካባቢው የሰብል ቡቃያ ነው፤ ያንን ደግሞ ከብቶች እንዳይበሉት መጠበቅ አለበት፡፡ በዚያ ላይ የክረምት ዝናብ በየሰዓቱ ድንገት እየመጣ ያወርደዋል፤ መጠለያ እንኳን አያገኙም ዝናቡ የሚያልቀው ከላያቸው ላይ ነው፡፡
ሌላውና ትልቁ ትዝታ ደግሞ የተማሪዎች ነው፡፡ ተማሪ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የሰኔ ትዝታ አለበት፡፡ ከአንደኛ እስከ መሰናዶ ትምህርት ቤት እያለ ከክፍል ጓደኞቹ ጋር ስለሚላመድ የሰኔ ወር መለያየትን ይዞ ሲመጣ ቅር ይላል፡፡ በሌላ ምክንያት ደግሞ የሰኔ ወር የዓመቱ መውደቅና ማለፍ የሚታወቅበት ነው፡፡ በልጅነት አዕምሮ እኮ የሞት ፍርድ እንደመጠባበቅ በሉት፡፡ ለደረጃ የሚፎካከሩ ተማሪዎች ደግሞ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚባባሉበትና የሰኔ ወር ቁርጣቸውን የሚነግራቸው ነው፡፡
ስለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ ትንሽ እንበል፡፡ ይሄ ነገር በተለይም ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችና ለተመራቂዎች የተለየ ቦታ ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተሰብ የሚለይበት ነው፡፡ እነዚህን ቤተሰቦቹን የሚያገኛቸው በሰኔ ወር ነው፡፡ እዚህ ጋ የቤተሰብ ናፍቆት አለ፤ እዚህ ጋ ደግሞ ከተለያየ የአገሪቱ ክፍል ከተውጣጡ ጓደኞቹ ጋር ሌላ ሕይወት ጀምሮ ሌላ ትዝታ ፈጥሯል፤ ሰኔ ላይ እነዚህን ልጆች ይለያቸዋል፡፡ የሰኔ ወር ለዚህ ተማሪ የትዝታ ምስቅልቅሎሽ ያለው ነው፡፡
ወደባሰው ትዝታ እንምጣ(አይ ሰኔ ወር ስንቱን ነገር አስታወሰን እኮ)፡፡ የሰኔ ወር ለተመራቂ ተማሪዎች ከማንም በላይ ትዝታ አለው ብንል ትክክል ነን፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ሲመኘው የነበረውን ሙያ የሚያረጋግጠው በዚህ ወር ነው፡፡ እንደገና መወለድ ልንለው እንችላለን፡፡ ያ ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ›› የሚለው መዝሙር ሆድን የሚያላውሰው በዚህ ወር ነው፡፡ ይሄ ትዝታ ለተመረቅንበት ዓመት ብቻ ሳይሆን የሰኔ ወር በመጣ ቁጥር የቴሌቪዥን ዜና ላይ ስናየው በትዝታ ወደተመረቅንበት ዩኒቨርሲቲ የሚወስደን ነው፡፡
የሰኔ ትዝታ ለሰራተኛውስ? እዚች ላይማ አንድ ነገር ወረፍ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ‹‹የበጀት መዝጊያ›› የሚባል ነገር ታውቃላችሁ አይደል? እሷ ነገር ብዙ ጥሩ ያልሆነ አሰራር አላት አሉ፡፡ እንዲያው በአጭሩ ምን ለማለት ነው፤ የበጀት መዝጊያ ላይ ብር ላለመመለስ ተቋማት ያልሰሩትን ሥራ ሁሉ የሰሩ ለመምሰልና ለሪፖርት መሯሯጥ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ብሩ ላልታሰበለት ዓላማ ይውላል ማለት ነው፡፡ ኧረ እንዲያውም አሸሸ ገዳሜ ሁሉ ይኖራል፡፡ ቆይ ግን ይህን ሁሉ ሁነት የያዘው የሰኔ ወር እንደሌሎቹ 30 ቀን ብቻ ነው?
ሰራተኞች እንዴት ናችሁ?(ሰው እንዴት በመጨረሻ ሰላምታ ይጠይቃል?) ወድጄ አይደለም እኮ የዘንድሮ ክረምት የተገላበጠ መስሎኝ ነው፡፡ ቆይ ግን አዲስ አበባ ውስጥ ሐምሌና ግንቦት ቦታ ተቀያየሩ እንዴ? እኔማ ያ ሐምሌ ደርሶልኝ እስከማረጋግጥ ነው የቸኮልኩት! ኧረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን፤ ሐምሌም ግንቦትም ዝናብ ይሁኑ!
የዘንድሮ ግንቦት እኮ ወሩን ሙሉ ዝናብ በዝናብ አደረገን! ምን ዋጋ አለው በልግ የሚታረስበት ገጠር ውስጥ የለም አሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ግን አላስወጣ አላስገባ ብሏል፡፡ የአዲስ አበባ ዝናብ የጠቀመው ነገር ቢኖር ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ማስተጓጎሉ ብቻ ነው፡፡ እኔማ እኮ ዝናብ በመጣ ቁጥር ድህነቴን ነው የሚያስታውሰኝ፡፡ አንድ ቢሉ ጫማየ ከሥር ውሃ እያስገባ ድህነቴን ያስታውሰኛል፡፡ ሌላኛው እንኳን ስቀብጥ ነው እንጂ በዚህ መበሳጨት አልነበረበኝም፡፡ ድንገተኛ ዝናብ በመጣ ቁጥር የምጠለለው ካፌ አካባቢ ነው፤ በር ላይ ሆኜ ወደ ውስጥ አያለሁ(መቼም ዓይኔ አያርፍ)፡፡ ከውስጥ ያሉ ሰዎች ኬክ፣ በርገር፣ ፒዛ እያማረጡ ሲበሉ እያየሁ ስለኑሮ ልዩነት ማሰብ እጀምራለሁ፤ በኋላ ራሴን በራሴ ለማጽናናት ‹‹ግደለም ደራሲ ለመሆን ይረዳኛል›› እላለሁ፡፡
በሉ ዝናቡ እንዳባራልኝ ልሄድ ነው፤ በሌላ ዝናብ እንገናኝ!

ዋለልኝ አየለ

 

የጠፋው ዕቃ የጠፋበት ቦታ

 

ከቤታቸው አይጠፉም የተባሉ ሰዎች ሁሉ ተጠሩ፤ ጠሪ ወይዘሮ የሻሽወርቅ ናቸው። ከተጠሩት መካከል እኔም ነበርኩበት። እንደው ጉዳዩን ታዘቢ ሲለኝ እንጂ ከአባቴ እኩዮች ኅብረት ጋር ለመቀላቀል እድሜዬ ደርሶ አይደለም። አብሬያቸው ስሆንና በጨዋታቸው መካከል የትውልድ ወቀሳ ከተነሳ የትውልድ ተወካይ ተወቃሽ እኔ ነኝ፤ ደግሞ በወጋቸው መካከል ለዚህ ትውልድ ሀዘኔታ ከተሰማቸው የሚያዝኑት ለእኔ ነው፤ ያልተወከልኩ ተወካይ።
የሻሽወርቅ ቤታቸው ለሻይ ቡና፣ ለጥየቃ፣ ለሰላምታ፣ ለብድር፣ ወሬ ለማቀበል፣ እግር ጥሎት፣ መርዶ ለማርዳት ወይም ደስታን ለማብሰር...ብቻ እግሩ ደጃቸውን የረገጠውን ሁሉ አስጠርተዋል። የተጠሩ ብዙዎች ቢሆኑም በስፍራው የተገኘነው ጥቂት ነበርን። ያለወትሮው ደግሞ ከተጠሩት መካከል እትዬ አደላሽ አልተገኙም፤ ለምን?
«ምነው በሰላም ነው?» አለች አንዷ ጎረቤታቸው፤ የእርሷ ቤታቸው መገኘት ወሬ በማቀበል ላይ የተመሰረተ ነው፤ «መቼም የአቶ አበራ ልጅ ዘንድሮ ሊመረቅ ሲጠበቅ ጉድ እንደረገን፤ እንደማይመረቅ ሰምተው አይደለም?» ብላ አስቀድማ ግምቷንና መረጃውን አቀበለች። «አይመረቅም እንዴ?» ሌላዋ ከቀደመችው አፍ ቀበል አድርጋ ጠየቀች።
«አዎን! እሱማ ሃሳቡ ጋውን ተከራይቶ እናትና አባቱን ሊያታልል ነበር። አይታወቅብኝም ብሎ ነውኮ! ምን ይሳነዋል የነዛ ምስኪን ወላጆቹ አምላክ አጋለጠዋ!» ወሬዋን ቀጠለች። የሻሽወርቅ እስከአሁን ዝም ማለታቸው አዲስ ነገር ሆነብኝ። ሰው ሲታማላቸው አይወዱም፤ ራሳቸው ስም ካላነሱ በቀር። ይህን አስቤ ብዙም ሳልቆይ የተጠራንበት ጉዳይ ይፋ ተደረገ። «አሁን እዚህ የጠራኋችሁ እንድትወያዩ አይደለም፤ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ ፈልጌ ነው» አሉ ፊታቸውን እንዳኮሳተሩ። «ባለፈው አሟቸዋል ያሉኝ ዘመድዎ ደኅና ናቸው? ችግር አለ እንዴ እማማ የሻሽ?» አለች ለቡና እና ሻይ ከቤታቸው የማትጠፋዋ ሌላዋ ሴት።
«ወዲያ! ምንድን ነው ክፋትን መጥራት፤ እኔ ችግር ገጠመኝ የሚል ቃል ከአፌ ወጥቷል? በቃ እንደው መርዶ ለመስማት ነው የምትጓጉት? ምን ያለ ጉድ ነው!» ቆጣም፣ ገልመጥም ብለው ተናጋሪዋን ተመለከቷት። መልስ አልሰጠችም፤ እርሷ ብቻ ሳትሆን ሌሎቻችንም አስተያየት ከመስጠት ታቀብን። አስተያየት መስጠት ብቻ ሳይሆን አስተያየታችንንም አስተካከልን፤ መሬት መሬቱን ማየት ጀመርን። ምን ያህል እንደምናከብራቸው ተመልከቱልኝ!
«እንደው ከዚህ ቤት አትጠፉም፤ በዛ ላይ የሆድ የሆዴን ታውቃላችሁ። እንደውም ከእኔ የተሻለ ነገርንም ሆነ ቁምነገርን የሚያስታውስ ጭንቅላት አላችሁ ብዬ አስባለሁ። መቼ እለት እቁብ ወጥቶልኝ ነበር...» ንግግራቸውን ሳይጨርሱ በቤታቸው የነበርን ሁሉ የደስታ ድምጽ አሰማን። የደስታ ድምጽ ምን ዓይነት ነው? «እሰይ!»፣ «ውይ! እንኳን ደስ አሎት»፣ «ጎሽ!» ፣«ኧረ?» አልን፤ ማጨብጨብ ነው የቀረን። ለምን ደስ አለን የሚለው ጥያቄ ግን የታወቀ መልስ የለውም።
የኢትዮጵያዊነት ባህል ይሆን? ለቡና እና ለሻይ ብሎም ለቡና ቁርስ የሚበጀተው በጀት ከፍ ይላል ብለን ይሆን? ደግሰው ይጋብዙናል ብለን ይሆን? ራሳችንን በእርሳቸው ውስጥ አስቀምጠን አስበነው ይሆን? አልታወቀም።
«እስቲ ቀድማችሁ ስሙኝ፤ ታድያ የእቁቡን ብር ያስቀመጥኩበት ጠፋኝ፤ እና ቤቴ ስትመላለሱ አይታችሁ እንደሆነ ልጠይቃችሁ ነው» አሉ የሻሽወርቅ፤ ይሉኝታ አያውቃቸውም አያውቁትም። «አበስኩ ገበርኩ! የፈጣሪ ያለህ! ድንግል እናቴ ድረሽ! ቅዱስ ገብርኤል! የመልአኩ ያለህ! ብሩ ጠፋ?» ድንጋጤ በእነዚህ ተከሽኖ ቀረበ። የጎረቤቶቻቸው ድንጋጤ ግን እንደውም የሻሽወርቅን ጥርጣሬ አገዘፈው።
«ምን አስደነገጣችሁ! አይታችሁ እንደሆነ ጠየቅሁ እንጂ ሌባ አልኳችሁ? አላልኩም።» አሉ ሁላችንንም በተራ በተራ እያዩን። «ስንት ነው ገንዘቡ? ቆይ ቆይማ እንደውም አይንገሩን፤ የት ነበር ያስቀመጡት?» አለች ብዙ ጊዜ ለብድር ከቤታቸው የምትመጣዋ ሴት፤ መልስ አልሰጧትም።
«እስቲ ተማክራችሁም ቢሆን ንገሩኝ፤ ሰው እንዴት የገዛ ገንዘቡን ያስቀመጠበትን ያጣል?» ሁላችንንም እያዩ። ካለነው መካከል የተናቁ የመሰላቸው ፊታቸውን ጥለው የሚሆነውን ይጠባበቃሉ እንጂ አስተያየት አልሰጡም። የሻሽወርቅ ጭንቀት ይሁን ቁጣ አልያም ግራ መጋባት ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆነ።
«እንደስልክ ብር ላይ አይደወል! ቆይማ አደላሽ የት ሄዱ? እርሳቸው ቢኖሩኮ መፍትሄ አይጠፋም» አለች የወሬ እናት፤ መረጃ አቀባይቷ ሴት። ይሄኔ የሻሽወርቅ ፊታቸው ነጭ ሆነ፤ የቀይ ዳማ መልካቸው በፍጥነት ሲቀየር የበለጠ ደግሞ እኛን አስደነገጡን። እውነትም እትዬ አደላሽ ቢኖሩ እንዴት ጥሩ ነበር፤ እትዬ አደላሽ ግን ለምን አልመጡም?
ይህን እያልን ሳለ እትዬ አደላሽ ብቅ አሉ፤ እድሜያቸው ረጅም ነው። የአደላሽ መምጣት እኛን ሲያስደስተንና ሲያስተነፍሰን እትዬ የሻሽን ግን አስጨነቃቸው፤ ፊታቸው ላይ ጭንቀታቸው በግልጽ ይታያል። የተጨነቁት ግን በገንዘባቸው መጥፋት እንጂ በአደላሽ መምጣት ላይሆን ይችላል፤ ነገሩ በኋላ እስኪገለጥ ድረስ።
«እንዴ! ቤተ-ሰፈሩ ተሰብስቦ የለም እንዴ? ደግሞስ የቆማችሁ ለምን ነው? የሻሽ...ተቀመጡ ማለት ቀረ?» እትዬ አደላሽ በፈገግታቸው ታጅበው ገቡ፤ እኛም ፈገግ ብለን የሰላምታ ቃል እያሰማን ተቀበልናቸው። «ምነው? ቡናም አልቀረበ...በሰላም ነው? አስጨነቃችሁኝኮ!» ነገሩን ለእትዬ አደላሽ ደፍሮ የሚያስረዳ ሰው ጠፋ።
ራሳቸው የሻሽወርቅ መናገር ጀመሩ «የደረሰኝን የእቁብ ብር ያስቀመጥኩበት ጠፋኝ ብዬ አገር ይያዝልኝ ልል ስል መጣሽ!» አሉ፤ «እና እነሱን ለምን አደከምሽ?» አሉ እትዬ አደላሽ በቀላሉ ቀበል አድርገው፤ እኛ የተጨነቅነውን ጭንቀት አያውቁ። «ብሩን ያስቀመጥኩበት ቦታ ጠፋኝ እንጂ ብሩ ጠፋኝኮ አላልኳቸውም፤ የት ላስቀምጥ እችላለሁ የሚለውን ስንመካከር ነበር።» አሉ፤ ይሉኝታ አይፈሩም አይደለ? ከይሉኝታ ይልቅ ጓደኛቸውን እትዬ አደላሽን ያከብራሉ። ይህ ሆነና እኛም በመገረም፤ አንዳንዱም «እኚህ ሴትዮ! እስከመቼ እንዲህ እንዘልቃለን!» ብሎ በለሆሳስ እያጉረመረመ ቤቱን ለቀን ወጣን።
ስወጣ ሞባይሌን ረስቼ ነበር፤ ምሥጢር ሰማሁ። «የሻሽወርቅ! ኧረ ተይ አስተውይ! አረጀሽ እንዴ? ቤቴ ብዙ ሰው ገባ ወጣ ስለሚል አንቺ ጋር ይሁንልኝ ብለሽኮ ለእኔ ብሩን ሰጥተሽኛል፤ ጎረቤቶችሽን በማያውቁት ነገር ማስጨነቅ ምን ማለት ነው?» አሉ እትዬ አደላሽ ድምጻቸውን ቀነስ አድርገው፤ የምክር በሚመስል ድምጸት።
«አንቺ ደግሞ! ረሳሁታ...በዛ ላይ ገንዘብ ጠፋኝ ሳይሆን ያደረኩበት ጠፋኝ ነው ያልኳቸው። ከዛ ይኸው አንቺን አገኘሁ።» ብለው ሳቁ። በሩን መልሼ ሳንኳኳ ሁለቱም በፍጥነት ሳቃቸውን አቆሙ። «የዘንድሮ ልጆችኮ! ተደብቀሽ ስትሰሚ ነበር?» አሉኝ የሻሽ-ወርቅ፤ «ኧረ ምንም አልሰማሁም። ስልኬን ያስቀመጥኩበት ጠፍቶኝ ነበር፤ ትዝ ሲለኝ እዚህ ነበር ለካ!» ብዬ የረሳሁት ተንቀሳቃሽ ስልኬን ይዤ ሹልክ፤ የጠፋብንን ነገር ለማግኘት ያስቀመጥንበትን ቦታ መለየት ለካ ይቀድማል።

ሊድያ ተስፋዬ

Published in መዝናኛ

የኪነጥበብ ስራዎች ልክ እንደ መስታወት በዘመናቸው ያለውን ገሃድ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። መስታወት ጉድፍንም ውበትንም በግልጽ ፊት ለፊት እንደሚያቀርብልን የሥነጽሁፍ ስራዎችም እንዲሁ ናቸው። እንደ ሐዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከመቃብር ያለው መጻህፍ ደግሞ በወቅቱ የነበረውን የንጉሳዊ ዘመን ኢትዮጵያ መስታወት ሆኖ አሳይቷል። ይህ መጻሃፍ በርካታ ጊዜ ብዙ የተባለለት ቢሆንም በየጊዜው ምስጢሩ ቢነገር የማይሰለች ነውና ዛሬም የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ምንዋጋው ተመስገን ስለፍቅር እስከመቃብር መስታወትነት ያነሱትን ጥናት መሰረት አድርጌ ሃሳቡን አቀብላችኋለሁ።

«የባለቅኔውን ሕይወትና ሥራዎች የምንመረምረው ራሳችንን፣ አገራችንን፣ ባህላችንንና ማንነታችንን ለመመርመር ነው። ባለቅኔው ወደእውነታችን የሚያደርስ መንገድ እንጂ በራሱ የመጨረሻ ግብ አይደለም» በሚለው ሃሳብ አቶ ምንዋጋው ይስማማሉ። በድርሰት ስራዎች ላይ የደራሲውን ፖለቲካዊ አቋም እናይበታለን፤ ርእዮተ ዓለማዊ ድምጹን እናደምጥበታለን። የኪነጥበብ ስራዎች በተለይ ከታላቅ ተመስጦና አንጽሮት የሚወለዱ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ትንቢታዊነት አያጣቸውም። ትናንትን ከመጥቀስ፣ ዛሬን ከመቅረጽ አልፈው ነገን በገሀድ ይተነብያሉ፤ ነገን በገሀድ ይገልጻሉ። ልቦለድም ይሁን ፍልስፍና የመሰሉ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ከማኅበረሰቡ ታሪክ፣ ባህልና ሕይወት ተቀድተው በአዲስ መልክ ተፈጥረው መልሰው ያንኑ የሚያሳዩን መስታወቶች ናቸው።
እንደ አቶ ምንዋጋው ማብራሪያ ከሆነ፤ ፍቅር እስከመቃብር የተጻፈበት ጊዜም ሆነ የአሁኑ ዘመን ማሳያ ይሆናል። ድርሰቱ የሰዎች የተጨናነቀ ማኅበራዊ ዓለም ማሳያ ነው። ገጸ ባሕርያቱ ከተለያዩ የሕይወት አቅጣጫዎች የተሳሉ እንደመሆናቸው በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረውን ሰፊ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ይወክላል። ከገጸ ባሕርያቱ መካከል ባላባቶች (ፊታውራሪ መሸሻና ፊታውራሪ አሰጌ)፣ የቀሳውስት ቡድን (አባ ሞገሴና አለቃ ስርግው)፣ ገበሬዎች (ቦጋለ መብራቱና አበጀ በለው)፣ ባለቅኔዎችና መምህራን (በዛብህና አለቃ ክንፉ)፣ ባሮች (ሀብትሽና ልኩራ በሁሉ)፣ ንጉሠ ነገሥቱ (በስም ያልተጠቀሱ) ይገኙበታል።
ሐዲስ እንደሚነግሩን ለመማር ዓይነ ኅሊናን መክፈት ወሳኝ ነው። ብዙ ጊዜ አካላዊ ዐይኖች ሲዘጉ የማይታየው ይታያል፡፡ ለሰው ሁለት ዓይነት ዐይኖች አሉት። አንዱ ዓይነት አካላዊ ሁለተኛው ዐይነ ኅሊና ናቸው፡፡ ሁለቱ በአንድ ላይ አያዩም፤ ቢያዩም ደኅና አድርገው አያዩም። አካላዊ ዐይኖች ማየት የማይችሉትን ለማየት ዐይነ ኅሊናን መክፈት ያስፈልጋል። ከፍቅር እስከ መቃብርም እንዲሁ ምን እንማራለን? የሚል አጠይቆ አቅርበው ኅሊናችንን በመክፈት ስለ እያንዳንዱ ገጸባህሪ እና መልዕክቶቻቸው ያስረዱናል።
«ላግባሽ አሰጌ» (ፊታውራሪ አሰጌ)
ደራሲው በፊውታራሪ አሰጌ አሳበው ለዚያን ጊዜዎቹ ዋልጌ ባለሥልጣናት ሊነግሩን የፈለጉት ሥነ ምግባራዊ እሴት ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው። በመጻሕፉ በቅጽል ስማቸው «ላግባሽ አሰጌ» ስለተባሉት ፊታውራሪ አሰጌ ሲገልጹ እንዲህ ይሉናል።
«ላግባሽ አሰጌ ከማናቸውም የበለጠ ሴትና ዘፈን አጥብቀው ይወዱ ነበር። ከጀግና ወይም ከሽማግሌ አዝማሪ የሚያከብሩ፣ ከንጉሥ ቀጠሮ ለሴት ቀጠሮ ቅድሚያ የሚሰጡ ነበሩ። ቆንጆ ሴት ከመጠን በላይ ከመውደዳቸው የተነሣ ቆንጆ ሴት ባዩ ጊዜ አእምሮ የሚሰውር በሽታ እንዳለባቸው ሰዎች ራሳቸውን መግዛት ያቅታቸው ነበር። ሴት ከመጠን ያለፈ መውደዳቸውን የሚያውቁ ሰዎቻቸው አንዳንድ ጥቅም ሲፈልጉ ሴት ይዘው በመቅረብ ወይም ሴት ለማቅረብ ተስፋ ይሰጧቸው ነበር። የእርሳቸውን ክብርና ጥቅም የሚጎዳ ወይም ስለአስተዳደርና ስለፍርድ የነበራቸውን ኃላፊነት የሚጎዳ መሆኑን ለጊዜው ማየት አይችሉም ነበር» ተብሎላቸዋል። ሐዲስ በዚህ በኩል የዘቀጠ ማንነት ለፍርድ ሰው እና ለአስተዳደርነት እንደማያበቃ በአግባቡ ነግረውናል።
መንግሥቱ ፊታውራሪ መሸሻ (የመንግሥታዊ ሥነ ምግባር ማሳያ)
ፊታውራሪ መሸሻን ህዝብ ያልወደደው ስራ ለማንም እንደማይጠቅም የታየበት ገጸ ባህሪ ሆኖ እናገኘዋለን። «በጎልማሳነትዎ በፈረስ፣ በጉግስ፣ በተኩስ ተወዳዳሪዎችዎን በማሸነፍዎ፣ በጦር ሜዳ ሄደው ጠላቶችዎን ድል መተው በመመለስዎ ሰዉ ሁሉ ሲያደንቅዎ፣ ሲያከብርዎ፣ ሲፈራዎ ጊዜ፣ ለምነው ሳይሆን ተለምነው፣ የጠየቁትን ብቻ ሳይሆን ያልጠየቁትን ጭምር ሲያገኙ ጊዜ እግዚአብሔር በሰፊ መሬቱ ከእርስዎ በቀር ሌላ ክብሩንና ጥቅሙን የሚወድ ሰው እንዳልፈጠረ፣ ሰዉ ሁሉ የእርስዎን ፈቃድ ለመፈጸም እንጂ የራሱ ፈቃድ የሌለው ሆኖ እንደተፈጠረ በሙሉ ልብዎ አምነው በዚሁ ልመራ ብለው ተነሡ። በዳኝነት መንበር ቢያስቀ ምጥዎ በሕግ ፈንታ ፈቃድዎን ሕግ አድር ገው ልፍረድ አሉ። ሀገር ቢሰጥዎ በሕግ እንዲያስ ተዳድሩትና እንዲጠ ብቁት የተሾሙበትን ሕዝብ እንደቀማኛ ይዘርፉት ጀመር። እንዲ ያው በአጭሩ ሕዝብ የጠላው እግዚአብሔር የጠላው መሆኑን ማወቅ አቃተዎ። ስለዚህ ያደን ቅዎ፣ ያከብርዎ የነበረው ሰው ሁሉ ይጠላዎ ጀመር። ሁሉም ሞትዎን ያለዚያም ሽረትዎን አጥብቆ ፈለገ» በሚል ሐዲስ በመጻህፋቸው በገጽ 266 ላይ በአግባቡ አስተችተዋቸዋል።
የጉድ ማኅበር ምንነት
አብዛኛውን ጊዜ በርካቶች የተሳሳቱበት ነገር እንደ ትክክለኛ ነገር ይቆጠራል ይባላል። ጉዱ ካሳም ዕውነትን ይዞ ቢጓዝም በዙሪያው ከበውት የሚገኙ ሰዎች ጋር ለየቅል የሆነ አካሄድ ስላለው የእርሱ መንገድ የጥፋት ተደርጎ ተቆ ጠረ። ባለንበት ዘመንም አገርና ወገን የሚጠቅም ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎች በአብዛኛው ህዝብ የተሳሳተ አስተሳሰብ ምክንያት እብድ ሊያስብላ ቸው ይችላል።
ጉዱ ካሣ እንደሚነግረን «ጉድ» የሚባለው መጠሪያ ለእርሱ የተሰጠ አላግባብ ሆኖ እንጂ ደገኛው ወይም ትክክለኛው ጉድስ የምንኖርበት ማኅበር ነው። በከበበው ዓለም ውስጥ የግሉን ዓለም ፈጥሮ በሰው መካከል ብቻውን ሆኖ ይኖር የነበረው ጉዱ ካሣ የሚኖርበትን (የምንኖርበትን) ማኅበር «ዐይን እያለው ፍሬውን ከገለባ ለይቶ ማየት የማይችል፣ አእምሮ እያለው የሚጠቅመውን ከሚጎዳው ለይቶ ማስተዋል የማይችል፣ እንደበግ መንጋ በፊቱ የሚሄደውን ተከትሎ የሚንጋጋ፣ እንደጭነት ከብት የጫኑትን ተሸክሞ የሚጎተት የጉድ ማኅበር» ይለው ነበር።
የንጉሥ ግብርንም ሲተች «ከሀብቱ ሀብት ከፍሎ እንደሚገብር ከሰውነቱ ከፍሎ ለንጉሥ የሚገብረው የመንፈስ ግብር ነው!» እያለም እምቢተኛነት መለመድ እንዳለበት ካሳ ያስተምራል። ነገር ግን ምንም ቢሆን በግዕዙ እንደሚባለው «ብዙኃን ይመውዑ» ብዙኃን ያሸንፋል ነውና ብዙኃኑ አሸንፈው ጉዱ የሚለው ቅጥያ የካሣ ዳምጤ ስም ማዳመቂያ ሆነ።
ጉዱ ካሳም ይህንንኑ በእራሱ ላይ የደረሰውን ግፍ ያብራራል። «የእኛስ ዘመን ማኅበራዊ ሥሪት በምን ይለያል? … ባሪያው እንዲሸጥ እንዲለወጥ፣ እጀ ሠሪው እንዲናቅ እንዲጓጠጥ፣ ደሀው በጌታ እንዲገዛ እንዲረገጥ ተመድቧል። የድሀ ሽማግሌ ‘አንተ’ እየተባለ እንዲሞት ተደንግጓል። ከንቱ አስቦ ከንቱ የሚናገር ‘ዘመናይ’ ተብሎ እየተደነቀ ገዥ እንዲሆን፣ ቁም ነገር አስቦ ቁም ነገር የሚሠራ የተናቀ ሆኖ ተገዥ እንዲሆን ተመድቧል፡፡ ይገርምሃል! ይህን የማይረባ ልማድ ይህን በግፍ ላይ የተመሠረተ ክፉ ልማድ ተመልክተህ ‘እንዲህ ያለ ልማድ ሊኖር የማይገባው የሚችልም አይደለምና ይልቅ አወዳደቁ እንዳይከፋ ቀስ ብሎ እንዲለወጥ ማድረግ ይሻላል’ ብለህ የተናገርህ እንደሆነ እንደከሀዲ ተቆጥረህ የምትሰቀልበት ገመድ ይሰናዳልሃል» እያለ ያስረዳናል።
«ዝም ብለህ እያዘንህ ተመልካች የሆንህ እንደሆነም እንዲህ እንደእኔ ‘እብድ፣ ጉድ’ እያሉ ሰላምህን አሳጥተው ከማኅበር አስወጥተው፣ በዘመድ መሐል ባዳ፣ ተወልደህ ባደግህበት ሀገር እንግዳ ሆነህ እንድትኖር ያደርጉሃል። ደግሞኮ ይህን ሁሉ የሚያደርጉብህ ‘የጌታ ዘር ነን’ የሚሉት ሁሉንም ረግጠው እላይ የተቀመጡት ብቻ ቢሆኑ ‘ጥቅማቸው እንዳይጎድልባቸው ነው’ ትላለህ፡፡ ነገር ግን ባሮቹ፣ እጀ ሠሪዎቹ፣ ድሆቹ ሁሉ፣ ግፍ የሚሠራባቸው ሁሉ ከግፍ ሠሪዎች ጋር አንድ ላይ ተባብረው ሲፈርዱብህ ምን ትላለህ? ‘ከልማድ ጋር የማይስማማ እውነት ሁልጊዜ ሀሰት ነው’ የሚባለውን የማይረባ ተረት አስበህ ዝም ማለት ብቻ ነው፡፡ እየውልህ! በጠቅላላው የዚህ ልማድ እስረኞች ነን» እያለ ዕውነት መገለባበጧን እያስረዳ ይቀጥላል።
ቄስ ምሕረቱ፣ ቄስ ሞገሴና አባ ተክለ ሃይማኖት
ቄስ ምሕረቱ በሐይማኖት ምግባራቸው ትክክለኛ ያልነበሩ አሳሳች ነበሩ። «እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ» የተባሉ ካህናትና መነኮሳት ማጣፈጣቸው ቀርቶ ራሳቸው አልጫ ሲሆኑ፣ ብርሃንነታቸውን በጨለማነት ሲተኩ አያድርስ ነው።
ቄስ ምሕረቱ ከሰው ሕይወት ይልቅ የገንዘብ ፍቅር እንደሚበልጥባቸው የአቶ ቦጋለን መሞት ከእመት ውድነሽ ሲሰሙ የመለሱት መልስ ምስክር ይሆናል።
የአባ ምሕረቱን የሥነ ምግባር ደረጃ የአባ ቦጋለን ሬሳ እንዲያመጡ በሚልኳቸው ሰዎች በኩልም ማየት ይቻላል። ገብሬ የተባለ አገልጋያቸውን በተላላፊ በሽታ ነው የሞተ ወደተባለው የቦጋለ መብራቱ ሬሳ ወዳለበት ቤት ልላከው ወይስ ይቅር እያሉ ከተወዛገቡ በኋላ «ይሂድ ግዴለም፤ እግዚአብሔር ለእኔ ካለው ምንም አይሆንም፤ … መቼስ የሰው መፈረጃ ከመሆን የማይሻል የለም» እያሉ ሰው ምን ይለኛል በሚል ስሜት ብቻ መወጠራቸውን ያሳያል። ይህም ሐዲስ በሐይማኖታዊ ግብራቸው ሳይሆን በጥቅም የሚመሩ ሰዎች መኖራቸውን ሲያሳዩን ነው።።
ቄስ ሞገሴ ደግሞ ዕውቀት አጠር ስለነበሩ ድጋፋቸውም ሆነ ተቃውሟቸው የእምነቱን ሕግጋት የተከተለ ሳይሆን የፊታውራሪና የቀራቢዎቻቸው ዓይንና ግንባር ብቻ ነበር። ለጉዱ ካሣ አንዱ ራስ ምታትም እነፊታውራሪን ገሥጸው ወደበጎ ከመመለስ ይልቅ ለግፉ ተግባራት ተባባሪ የሆኑ እነአባ ሞገሴ መሆናቸው ነው። ጉዱ ካሣ ስለዘመናችን አባ ሞገሴዎችም እንዲህ የሚለን ይመስላል፡- «አባ ሞገሴ እንደምታውቋቸው የራሳቸው ሐሳብ የሌላቸው፣ የሰውን ሐሳብ ብቻ ከዓይኑና ከግንባሩ አይተው ለመተርጎም ችሎታ ያላቸው፣ ሆዳቸውን የሞላና በፈለገው መንገድ የሚመራቸው፣ ተግባራቸውን ለሆዳቸው የሸጡ የለወጡ ናቸው» እያለ ይወርፋቸዋል።
ከጉሊትና ከናሞራ ባላገሮች ተልከው የመጡት ሽማግሌ ሲናገሩም አባ ሞገሴ ፊታውራሪ ሲቆጡ አይተው «ዝም ይበሉ እርስዎ ምን ያሉ የሽማግሌ ባሕሪ የሌላቸው ናቸው እባካችሁ! እዚህ ጠብ ለመፍጠር የሰይጣን መላክተኛ ሆነው ነው የመጡት?» ማለታቸው የአባ ሞገሴን የወረደ ሥነምግባር ያሳያል። የሥነ ምግባር ትንተናውን ሙሉ የሚያደርገው አባ ሞገሴንና መሰሎቻቸውን ከቤተ ክህነት አውጥቶ ማየት ከተቻለ ብቻ መሆኑን ደግሞ አጥኚው ያስረዳሉ።
አባ ሞገሴዎች የሌሉ በት የማኅበረሰብ ክፍል ካለ ያ ማኅበረሰብ ከመለ ካውያን የጸዳ ስለሆነ ዕድለኛ ነው፡፡«መለካዊ» ማለት በሃይማኖት ስም የንጉሥን ፈቃድ ብቻ የሚፈጽም እግሩ ቤተ ክርስቲያን ልቡ ቤተ መንግሥት ያለ ጳጳስ ማለት ነው። እንደነዚህ አይነት ሰዎች «ድርጓቸ ውም ሹመታቸውም ከንጉሡ በመሆኑ ፣ ብዙ ጊዜም ከነገሥታቱ ጋር ስለሚውሉ ምንም ዓይነት ችግር ቢያዩ በዝምታ ከማሳለፍ በቀር የሚቃወ ሙበትና የሚገሥጹበት አጋጣሚ አልነበረም» ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለሐይማኖታዊ ግብራቸው በሀቀኝነት የሚቆሙ አይጠፉም። እንደዚህ አይነት ጊዜ ብዙ ጊዜ አለመግባባትና ችግር የሚፈጠረው ሹመ ትና ገንዘብን ንቀው በነበሩ አባቶች እና ለገን ዘብ ሲሉ በመነኮሱትና ክህነት በተቀበሉት መካ ከል ነበር።
ስለ አባ ተክለ ሃይ ማኖት ደግሞ «እየው ልህ! ቤተ እግዚአብሔር እንደዚህ ላሉት ሽፍቶች፣ እንደዚህ ላሉት ዘራፊዎች ዋሻ ሆነች! እየውልህ! ካህናታችን ከሐዋርያታችን የሚበዙት ከአለቆች ጀምሮ በመነኮሳቱ አልፎ እስከተራ ደብተሮች እስከዲያቆናቱ ድረስ አንዱ አስማት አድራጊ። አንዱ አስማት ፈቺ፣ ሌላው ጋኔን ስቦ አምጪ ሌላው አስወጪ፣ አንዱ መቅሰፍት አምጪ ሌላው ምሕረት አሰጪ ነን እያሉ ውሸታቸውን በየጥምጥማቸው በየቆባቸው በየደበሏቸው ሸሽገው ሊመሩት ሊያስተምሩት በተሰጣቸው መንጋ የሚጫወቱ ናቸው!። ታዲያ ከእነዚህ ጋር ማኅበርተኛ ሆኖ በአንድ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት በተቀደሰ ስሙ ማፌዝ አይደለም?። እየውልህ! ይህ ነው ከምወዳት ቤተ እግዚአብሔር ያራቀኝ! ሰው የሚለው ሌላ ነው፡፡ ነገር ግን እውነቱ ይህ ነው» እያለ በመጻህፉ ገጽ 428 ላይ ያስቀምጣቸዋል።
ስለእኝህ አስመሳይ ሰው ወይም አባ ተክለሃይማኖት የቀረበው ምጸታዊ ገለጻ ቤተ እግዚአብሔርን ተጠግተው በሚያረክሱት የካህናት አባላት ላይ ያነጣጠረ ጠንካራ ሂስ ነው። ጉዱ ካሣ ስለብዙኀኑ ካህናት ምግባረ ብልሹነት ለበዛብህ ሲነግረው የነበረውን በተግባር የሚያሳይ ነው። ሰብለ የአባ ተክለሃይማኖትን የመነኩሴ ደበሎና ቆብ መግፈፍ በአንድ በኩል ትእምርታዊ ሆኖ እናገኘዋለን። አባ ተክለሃይማኖት የማይገባቸውን ሃይማኖታዊ ክብር በአስመሳይነት ስለተጎናጸፉ ያን በመግፈፍ እውነተኛ ማንነታቸውን የማጋለጥ ሚና ሲኖረው፣ ያ የተጨማለቁበት ትውኪያ ደግሞ የኃጢአታቸውን፣ የርኩሰታቸውን፣ የዝቅጠታቸውን መጠን ማሳያ ነው።
እንደ አቶ ምንዋጋው ማብራሪያ፤ ይህን የአባ ተክለ ሃይማኖትን «ቤተ እግዚአብሔርን ተጠግተው በሚያረክሱት የካህናት አባላት» ማሳያ ብቻ አድርጎ ማቆም አያስፈልግም። ይልቁንም እርሳቸውን «ቤተ መንግሥትን ተጠግተው» ያልተገባ ሥራ በሚሠሩ የካቢኔ አባላትም መመሰል ይቻላል። ይህ የዘመናችን መንፈስ መገለጫ ስለሆነ ደግሞ ዘረኝነት፣ ጉቦኝነት፣ ሴሰኝነትና ዕብሪት አድርገን ልንተረጉመው እንችላለን።
አበጀ በለውና ነጋዴው ዓሊ ጅብሪል
አበጀ በለው በፊታውራሪና በሹማምንታቸው የሚፈጸመው ግፍ ሲበዛ ተመልክቶ ለብዙኀኑ መብት መጠበቅ ሲል የሸፈተ ገበሬ ነው። ሊዘርፉ የሄዱትን ፊታውራሪ ከማረካቸው በኋላ የሚናገራቸው ነገርም ይህን ዓላማውን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። እርሳቸው ተማርከውም እንኳ ባልተረታ መንፈሳቸው አበጀ በለውን «ሕዝቡን ያሳመጽህ ሽፍታ ነህ» ቢሉትም አበጀ ግን ሲመልስላቸው ዕውነቱን ያግታቸው ነበር።
«ሥልጣንን በዙሪያቸው አጥረው በሥልጣን ውስጥ ተሸሽገው ድሀ የሚዘርፉትን፣ ድሀ የሚቀሙትን፣ በራሳቸው ወንጀል ድሀ አስረው የሚገድሉትን ግፈኞች ሽፍቶች እቃወም ነበር እንጂ ሽፍታ አልነበርሁም። እቤቴ ተቀምጨ ባለሥልጣኖች የሚሠሩትን ግፍ በሕግ ለመቃወም ስላልቻልሁ ቤቴን ትቼ መሰደዴ ሽፍታ አያሰኘኝም። አብረውኝ ሰባት ዓመት በዱር በገደሉ የተንከራተቱት ብዙዎች ስለሆኑ አንዱን በአጋጣሚ አግኝተው ቢጠይቁት እንኳን የሰው የከብት ደም ሲፈስ ማየት የማልወድ መሆኔን ይነግርዎታል። ደም ሲፈስ ከማየቱም ደግሞ የድሀ ሕይወትና ንብረት እንዲጠበቅበት የተሠራው ሕግና የተሰጠው ሥልጣን ተጣሞና ተቆልምሞ ለድሀ ሕይወት ማጥፊያ፣ ለንብረት መዝረፊያ፣ ለአመጽ መፈጸሚያ ሲሆን ማየት ከሁሉ የበለጠ ያስጠላኛል፤ በጣም ያንገፈግፈኛል» እያለ የልቡን ይነግራቸዋል። ይህም በገሃዱ አለም የሚታዩ ለህዝብ ሲሉ የሚታገሉ ሰዎችን ያስታውሰናል።
ነጋዴው ዓሊ ጅብሪል በበኩሉ የንግድ ሥነ ምግባር የሌለውና ለህዝቡ ሲሉ በሚታገሉ ግለሰቦች ጋር አንድ አገር ላይ የሚኖር አስከፊ ሰው ነው። «የገበያ ሽብር ለሌባ ይበጃል» እንደሚባለው ሁሉ የንግድ ሥነ ምግባር ሲጠፋ ነጋዴዎች ሁሉ ሕጋውያን ቀማኞች ይሆናሉ። በዛብህ አዲስ አበባ ወደጉለሌ ሲሄድ ሁለት የጎጃም ነጋዴዎች ሲነጋገሩ ያደመጣቸውን እናንሳ «አሁንኮ ዐሊ ጅብሪል ቆዳችንን መዝንልንና ዋጋ እንነጋገር ብንለው አንድ ጊዜ ‘ሚዛኑ ተሰብሯል’ አንድ ጊዜ ‘መዛኙ ታሟል’ እያለ ዛሬ ነገ የሚለን ፋሲካ እስኪደርስለት ነው» አለ አንዱ ነጋዴ። «ፋሲካ ሚዛን ይሆናል ወይስ መዛኝ?» አለ ሁለተኛው፡፡ «የለም ‘ዛሬ ነገ እያልሁ ፋሲጋ እስኪለግት ካቆየኋቸው ለማጫረት ጊዜ ያጥራቸውና በርካሽ ዋጋ ጥለውልኝ ይሄዳሉ’ ብሎ ነው እንጂ» እያሉ ስለ ዓሊ መጥፎ ስነምግባር አውርተዋል። ይህም ዝም ብሎ ከመጻህፉ ውስጥ የተገኘ አይደለም እንደውም የዘመናችንን የንግድ መንፈስ የሚወክል ይመስላል።
የቦጋለ መብራቱን ቻይነት
ቦጋለ ትዕግስተኛና ቻይ በመሆኑ ደግሞ ለትዳሩ መቆም አቅም ሰጠው። ችግር ሳይሸነፉለት ሲለምዱት ከእርሱ ጋር እየታገሉ እየወደቁ እየተነሡ ሲኖሩ ጥሩ ነው። ከችግር ጋር ሲታገል የኖረ ቆዳው ይወፍራል፤ ጅማቱ ይጠነክራል፤ ጡንቻው ይደነድናል፤ የተጣለበትን ሸክም ሁሉ መሸከም ይችላል፤ የገጠመውን ሁሉ ያሸንፋል። ስለዚህ እድሜ ላሳዳጊያቸው፣ እድሜ ለአስተማሪያቸው፣ እድሜ ለችግር፣ ቦጋለ መብራቱን ቆዳቸውን አወፍሮ፣ ጅማታቸውን አጠንክሮ ትግል እያስተማረ አደንድኗቸዋል። ስድብና ቁጣ፣ የንቀትና የግልምጫ ውሽንፍር እንዳይገባቸው አድርጎ ሁሉን እንዳመሉ እንዲችሉ አድርጎ ላነፃቸው ለቀረጻቸው እድሜ ለችግር አቶ ቦጋለ ሁሉንም ቻይ ነበሩ። ይህ የአቶ ቦጋለ መቻል ትዕግሥታቸውና መሸነፍን እንደውርደት አለመቁጠራቸው ከእመት ውድነሽ ይቅር ባይነት ጋር የተቆጡበትንና ምርር ብለው ያለቀሱበትን ቶሎ የሚረሱ ከመሆናቸው ጋር አንድ ላይ ሆኖ ጠቅሟቸዋል። ይህም ጊዜ ባለፈ መጠን ባልና ሚስት እንዲቻቻሉ፣ ባሕርይ ለባሕርይ እንዲተዋወቁ፣ ለፍሬ እንዲበቁ ‘ማን አለው? ማን አላት?’ እየተባባሉ እንዲተሳሰቡ አድርጎ ትዳራቸውን አጸናላቸው። በዚህ ገጸባህሪም ውስጥ በትዳር እና በማህበረሰብ ውስጥ የትዕግስትንና የጽናትን ተምሳሌትነት መማር እንደሚቻል አጥኚው ያስረዳሉ።
የቀኛዝማች አካሉ «ጽርየት» (ለሌሎች ክብር መኖር)
ቀኛዝማች አካሉ ፊታውራሪ መሸሻን በጣም ይወዷቸዋል። ትውልዳቸውም እኩል ነው። ፊታውራሪ መሸሻና የፊታውራሪ አሰጌ ግጭት በሆነ ጊዜ ደግሞ ቀኛዝማች የራሳቸውን ክብር ረስተው የፊታውራሪ አገልጋያቸው ለመሆን የቆረጡ ሰው መሆናቸው በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ባይሆን ኖሮ የመሰንበቻው ሁኔታቸው የፊታውራሪ አሰጌ ወገን አስመስሎ ባስጠረጠራቸው ነበር። በወሬው ሁሉ የፊታውራሪ መሸሻ ጀግንነትና የፊታውራሪ አሰጌ ፈሪነት ሲነሣ ጥርሳቸው ሌሎችን ለመምሰል ያክል ቢስቅም ግንባራቸው ሲቋጠር ወይም አንዳንድ ምክንያት ፈጥረው ከዘመድ መሐል ተነሥተው ሲወጡ ወይም ሌሎቹ የሚያደርጉትን ሁሉ በማድረግና ባለማድረግ መሐከል መቁረጥ አቅቷቸው ሲያመነቱ ይታዩ ነበር።
ምክንያቱ ሌሎቹ የማያውቁትን የፊታውራሪ አሰጌ ፈሪ አለመሆን እርሳቸው ያውቁ ስለነበረ ነው። ነገር ግን ተነስተው ዘራፍ አላሉም። ይህም ለሌሎች ክብር መኖር የመሰለ ህይወትን ያሳየናል። አቶ ምንዋጋው ሲያጠቃልሉም በአጠቃላይ ፍቅር እስከመቃብር ላይ ያሉ ገጸባህሪያትን ብንመለከት የአሁኑ ዘመንም የማህበረሰቡ ነጸብራቅ ሆነው እናገኛቸዋለን። የሐዲስን ማኅበራዊ ሂስ በታላላቆቹ ገጸባህሪያት ብቻ ሳይሆን በታናናሾቹም ላይ የሚያሳይ በመሆኑ ለዘመናት ቢነገርለት የማይሰለች ልብወለድ ነው። በመሆኑም ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ በስራቸው ለማህበረሰቡ መስታወት ሆነዋል።

ጌትነት ተስፋማርያም

 

የዓውደ ርዕይ ማድመቂያዎች

 

በባህል ዘርፍ የሚመራመሩ ሰዎች እንደሚሉት ባህል ማለት የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ ነው፡፡ ይሄ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ስለባህል ግልጽ ያልሆነ ግን ሌላ ትርጉም አለ፡፡ ተመራማሪዎቹ የሚሉት ባህል ማለት ያለፈ ሳይሆን አሁን እየተተገበረ ያለ ነው፡፡ የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ ነው ሲባል ያ ማህበረሰብ ያንን ባህል እየተገበረው መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ በፊት ይጠቀምበት የነበረውን ከሆነ የሚያሳየው ቅርስ እንጅ መገለጫው አይደለም፡፡ ያ ማህበረሰብ አሁን ሌላ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ይህኛው የባህል ትርጉም አሁን ላይ ግልጽ ሆኖ የሚሰራበት አይመስልም፡፡
አሁን አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ባህል ብዙ ወቀሳ እየተነሳበት ነው፡፡ የሚሰራው ሥራም የሚያስወቅስ ነው፡፡ ብዙም ሳንሄድ የሚዘጋጁ የባህል መድረኮችን ማየት በቂ ነው፡፡ ከፌዴራሉ የባህልና ቱሪዝም ጀምሮ እስከ ወረዳና ቀበሌ ያሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፤ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ዓመት ጠብቆ ፓናል ከማዘጋጀትና የተጠኑ ጥናቶች ፓናሉ ላይ ከማወያየት ባለፈ ሚናቸው ምን መሆን አንዳለበት የሚያስቡ አይመስሉም፡፡
በየጊዜው የባህል ፌስቲቫሎች ይዘጋጃሉ፡፡ በሚዘጋጁት ፌስቲቫል ላይ የሚቀርቡት ዕቃዎችና አልባሳት ኅብረተሰቡ የሚጠቀምባቸው ሳይሆኑ በፎቶ ብቻ ያሉ ናቸው፡፡ በአካል ያሉ ዕቃዎችም አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሳይሆኑ ለዓውደ ርዕይ ብቻ የሚወጡ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ባህል ሳይሆን ቤተ መዘክር (ሙዚየም) ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብሄራዊ ሙዚየም ውስጥ ቢቀመጡ ይሻላል፡፡
ጥያቄው እነዚህ ዕቃዎች ለምን ዓውደ ርዕይ ላይ ይቀርባሉ? አይደለም፤ ዳሩ ግን የባህል ማዕከላት ሥራ መሆን ያለበት ኅብረሰተቡ እነዚህን ዕቃዎች አውቋቸው መጠቀም እንዲችል የሚያደርግ ሥራ መስራት ነው፡፡ ራሳቸው አዘጋጆቹ እኮ የባህል ልብስ የሚለብሱት ለዚያ መድረክ ብቻ ነው፡፡ እነዚያን የባህል ዕቃዎችና አልባሳት የማየት ዕድል ያለው ዓውደ ርዕዩ የተዘጋጀበት ቦታ የሄደ ሰው ብቻ ነው፡፡ ወይም ደግሞ በቴሌቪዥን ተቀርጸው የማየት ዕድል ያለው ነው፡፡
ባህርዳር ከተማ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የባህል ማዕከልና የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባዘጋጀው የባህል ፌስቲቫል ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ ወደ ሙሉዓለም የባህል ማዕከል ሲገቡ ገና መግቢያው በር ላይ ግራና ቀኝ የተተከሉ ድንኳኖች ይታያሉ፡፡ ወደ ድንኳኖች ሲገባ ከባህል አልባሳት ጀምሮ ብዙ የባህል የመገልገያ ዕቃዎችና ጌጣጌጦች ይታያሉ፡፡ ዕቃዎችንም ብዙ ሰዎች ይሸምታሉ፤ ይጎበኛሉ፤ እኔ ግን በድንኳኑ ውስጥ ጉብኝት የሆኑብኝ ዕቃዎቹ ሳይሆኑ ሰዎቹ ነበሩ፡፡
34 ድንኳኑ ውስጥ ያሉ የዓውደ ርዕይ ዕቃዎች ለዕይታ ብቻ ሳይሆን ለሽያጭ የቀረቡ ናቸው፡፡ የሚጎበኙት ሰዎች ግን ዋጋ የሚጠይቁ እንዳይመስላችሁ! በዋጋ ከሚከራከረው ይልቅ ‹‹ይሄ ደግሞ ምንድነው፣ የየት አገር ባህል ነው፣ ለምን ያገለግላል?›› እያለ የሚጠይቀው ይበልጣል፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ! ኢትዮጵያዊ ሆኖ የባህል መሳሪያው የራሱ መሆኑን የማያውቅ በዝቷል ማለት ነው፡፡ ‹‹የአንዱን ብሄረሰብ አካባቢ የሌላው ብሄረሰብ ላያውቀው ይችላል›› እንዳትሉኝ! ከጎጃም አካባቢ መጥተው የጎጃምን ዕቃ የሚጠይቁ፤ ከኦሮሞ መጥተው የኦሮሞን የባህል ዕቃ የሚጠይቁ ናቸው ያጋጠሙኝ፡፡ ይሄ ማለት እንግዲህ ባህል ላይ በዓመት አንድ ጊዜ ዕቃዎችን ለዓውደ ርዕይ ከማውጣትና ከአዳራሽ ውስጥ ከማክበር በስተቀር ምንም አልተሰራም ማለት ነው፡፡
ወይዘሮ ይታይሽ አታላይ ይባላሉ፡፡ በዓውደ ርዕዩ ላይ የባህል ዕቃዎችን ለሚጎበኘው ያስጎበኛሉ ለሚገዛውም ይሸጣሉ፡፡ ከያዟቸው የባህል ዕቃዎች ውስጥ ለመዋቢያ የሚሆኑት ብቻ ሲሸጡ ሌሎች ዕቃዎች ግን ለምን እንደሚያግለግሉ የሚጠይቃቸው ይበዛል፡፡ እኔም ከጠያቂዎች ሆንኩና አንድ ዕቃ አንስቼ ጠየቅኳቸው፡፡ ከቀንድ የሚዘጋጅ የጠላ ወይም የጠጅ መጠጫ ነው፡፡ ዕቃው በቀላሉ አይሰበርም፤ ወድቆ የመዳን ጥንካሬ አለው፡፡ ይህን ዕቃ ግን እንደ ቅርስ እየጎበኙ ከመሄድ በስተቀር ማንም አይገዛውም፡፡ በየቤቱ ውስጥ በቀላሉ የሚሰባበር ብርጭቆ አለ፤ ይህ ጠንካራ የአገር ስሪት ዕቃ ግን የለም፡፡
ከዚህ ይልቅ ወይዘሮ ይታይሽ እየሸጡ ያሉት የመዋቢያና የጌጣጌጥ ዕቃዎችን ነው፡፡ ለሽታ የሚሆነው ጭስ ይሸጣል፤ ስሪቱ በዘመናዊ መንገድ ቢሆንም የባህል ጭስ ተጨምሮበት ያለው የሽቶ ዓይነት ይሸጣል፡፡ ከዚያ ውጭ ያሉት ዕቃዎች ግን የሙዚየም ዕቃዎች ሆነዋል፡፡


ወደሌላኛው ድንኳን ገባሁ፡፡ አሁን ደግሞ ጭራሽ ስሙም አዲስ የሆነ የባህል ዕቃ አገኘሁ፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የባህል እሴቶች ልማት ባለሙያ አቶ ሃይሌ ሞላ ስለእቃዎቹ ነገሩኝ፡፡ ‹‹እርኮት›› የሚባል አንድ የመገልገያ ዕቃ አሳዩኝ፡፡ ይህ ዕቃ የውሃ መጠጫ ነው፡፡ የሚዘጋጀው ከስፌት ነው፡፡ በዚህ ዕቃ ውስጥ የተቀመጠ ውሃ ልክ በዘመነኛው ማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) ውስጥ እንደማስቀመጥ ማለት ነው፡፡ ውሃውን ያቀዘቅዘዋል፡፡ እስኪ ይህን ነገር ከዘመናዊው ብርጭቆ ጋር እናነጻጽረው፡፡ የብርጭቆ ውሃ ወዲያውኑ ካልተጠጣ እየቀዘቀዘ ሳይሆን እየሞቀ ነው የሚሄደው፡፡
ሌሎችም ዕቃዎች አሉ፡፡ ሴቶች ሹሩባ ተሰርተው እንዳይበላሽባቸው የሚንተራሱት ትራስ በባህላዊ መንገድ የተሠራ ነው፤ ብርኩማ ይባላል፤ ከቆዳ ይዘጋጃል፡፡ ብዙ የጌጣጌጥ ዕቃዎችም አሉ፡፡ እያንዳንዳቸው ዕቃዎች የየራሳቸው ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ እጅ ላይ የሚደረጉ፣ አንገት ላይ የሚደረጉ፣ ጸጉር ላይ የሚደረጉ፣ እግር ላይ የሚደረጉ፡፡ እነዚህ ጌጣጌጦች ሲደረጉ ዝም ብሎ ለመዋቢያነት ብቻ እንዳይመስላችሁ! ሁሉም የየራሳቸው ትርጓሜ አላቸው፡፡ የታጨች ሴት የምታደርገው፣ ያገባች ሴት የምታደርገው፣ ገና ልጅአገረድ የሆነች ኮረዳ የምታደርገው ነው፡፡ ባህሉን የሚያውቅ ሰው ያደረገችውን አይቶ ልጅቷ ያገባችና ያላገባች መሆኑን ያውቃል ማለት ነው፡፡ ይሄም ልክ በዘመነኛው ቀለበት አይቶ እንደሚፈረጀው ማለት ነው፡፡
አሁን ላይ የምናያቸው ዘመናዊ የመገልገያ ዕቃዎች ከመኖራቸው በፊት ሁሉም በባህላዊ መንገድ ነበሩ፡፡ እዚህ ድንኳን ውስጥ ከእንጨት የተዘጋጀ የጸጉር ማበጠሪያ አለ፣ ከእንጨት የተዘጋጀ ማንኪያ አለ፣ ከእንጨት የተዘጋጀ ገበቴ አለ… ብዙ ከእንጨት የተዘጋጁ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ዕቃዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ዛሬም አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ የባህልን ጥበብነት፣ የባህልን የቴክኖሎጂ መነሻነት በግልጽ ማየት እንችላለን፡፡ ያንን የእንጨት ማንኪያ የሰራ ሰው ዘመናዊውን ማንኪያ አይቶ የማያውቅ ነው፡፡ ገበቴ ከእንጨት ሲያዘጋጁ የፕላስቲኩ ሳፋ ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡ የእንጨት የጸጉር ማበጠሪያ ሲሰራ ዘመናዊው ማበጠሪያ አልታሰበም፡፡
ከእንጨት ከሚዘጋጁ የመገልገያ ዕቃዎች ውስጥ ገበቴ ወይም በአንዳንድ አካባቢዎች አጠራር ቆሪ የሚባለውን እንመልከት፡፡ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ይህን ትልቅ ዕቃ ከእንጨት ለማዘጋጀት ማሰብ በራሱ ጥበብ ነው፡፡ እንጨት እንደዚያ አይነት ጥልቀት ያለው ዕቃ ይወጣዋል ብለው መጀመራቸው፡፡ ገበቴውን ተሰርቶ ካበቃ በኋላ ያየ ሰው ከእንጨት የተዘጋጀ ነው ብሎ ማንም አያምንም፡፡ ይህን ሲሠሩ ምንም አይነት ዘመናዊ ማሽን አልተጠቀሙም፤ መጥረቢያ ብቻ በቂ ነው፡፡
ይህ የእንጨት ገበቴ (ቆሪ) ብዙ አግልግሎችን ይሰጣል፡፡ አግልግሎቱም እንደየ ገበቴው አሰራርና መጠን ይለያያል፡፡ አንዳንዱ ገበቴ ከመሃሉ ላይ ሌላ ገበቴ ይኖረዋል(ልክ በቤት ውስጥ እንዳሉ ክፍሎች ማለት ነው)፡፡ የዚህ አይነት ገበቴ ለመመገቢያነት ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ ገንፎ ሲበላ የገበቴው መሃል ክፍል ላይ የገንፎው ማባያ ይቀመጣል፡፡ ገንፎው ዳርዳሩን ይሆናል፡፡ ሌላም ምግብ ቢሆን እንደ አስፈላጊነቱ ምግቦችን በገበቴው ክፍል ውስጥ ይቀመጣሉ፡፡ እንዲያውም ይሄ ነገር በትልልቅ ሆቴሎች ራሱ ቢለመድ ጥሩ ነበር፡፡
የጌጣጌጥ ዕቃዎችንም እንይ፡፡ ሴቶች ጸጉራቸው እንዳይበላሽ በአተኛኘትም ይሁን በሌሎች እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ዛሬም እናያለን፡፡ ይህ በባህላዊው አሰራር ምቹ የሆነ የትራስ አይነት ነበረው፡፡ ሰውነትን የማይጎዳ ከቆዳ የሚዘጋጅ ትራስ ለዚህ አግልግሎት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ከባህል ዕቃዎች ውስጥ ሌላው ‹‹ማጨብጨቢያ›› የሚባለው ነው፡፡ ይህም ከእንጨት የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህኛውን ለማስረዳትስ ዘመነኛውን ማስቀደም ሳይሻል አይቀርም፡፡ በፍርድ ቤት ወይም በአንዳንድ ቢሮዎች ውስጥ አለቆች ጸሐፊዎቻቸውን ለመጥራት የሚጠቀሟትን ‹‹ጭርርርር!›› የምትል ነገር ታውቋታላችሁ አይደል? እንግዲህ እሷ ምናልባት ፈረንጅ የሰራት ልትሆን ትችላለች፡፡ ማንም ይሰራት ማን ግን በአገራችን ውስጥ መጀመሪያ ከእንጨት ተሰርታ ነበር፡፡ አገልግሎቷም እንደዚሁ በድምጽ ለመግባባት ነው፡፡ የእንጨቷ ግን ሌላም ተደራቢ አገልግሎት አላት፡፡ በጨዋታ ጊዜ ለጭብጨባ ማድመቂያም ትሆናለች፡፡
ምን ዋጋ አለው እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች የዓውደ ርዕይ ዕቃዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከማንኛውም ቤት ውስጥ የምናገኛቸው አልሆኑም፡፡ እንኳን ዕቃዎችን ማግኘት የዕቃዎችን ስም ማወቅ ራሱ ብርቅ ሆኗል፡፡ ዕቃዎቹ ብቻ ሳይሆን ስማቸውም ሙዚየም ሊገባ ነው፡፡
ለመሆኑ እነዚህ ዕቃዎች በሱቅ ውስጥስ ይገኙ ይሆን? በባህርዳር ከተማ ውስጥ በፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ወደሚገኙ የባህል ዕቃ መሸጫዎች አመራሁ፡፡ ወጣት ሙሴ ልዑለቃል በአንደኛዋ የባህል ዕቃዎች ሱቅ ውስጥ አገኘሁት፡፡ ወጣት ሙሴ እንደሚለው ከባህል ዕቃዎች ውስጥ የሚሸጠው አልባሳት ብቻ ነው፡፡ በሱቁ ውስጥ የባህል የሙዚቃ መሳሪያዎችን ጨምሮ የጌጣጌጥና የተለያዩ የቅርጻቅርጾች አሉ፡፡ የሀውልትና የነገስታት ቅርጻቅርጾች አልፎ አልፎ የሚሸጡ ሲሆን የባህል የሙዚቃ መሳሪያዎች ደግሞ በጣም አልፎ አልፎ ይሸጣሉ፡፡ ከእንጨት የተዘጋጁ የቤት ውስጥ የመገልገያ ዕቃዎች ግን ጭራሹንም እንደማይሸጡ አጫወተኝ ፡፡
እነዚህ የቴክኖሎጂ መነሻ የሆኑ የባህል ዕቃዎቻችን የዓውደ ርዕይ ማድመቂያ ብቻ ሆነው ቀርተዋል፡፡ እኛም እንደ ፈረንጅ ‹‹ይሄ ምንድነው?›› እያልን መጠየቅ ጀምረናል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ገና ብዙ ዕቃዎችና የፈጠራ ሥራዎች ወደ ሙዚየም ይገባሉ፡፡ ሙዚየም የገባ ዕቃ ባህል ሳይሆን ቅርስ ነው፡፡ ይህ ነገር ከመሆኑ በፊት የባህልና ቱሪዝም አካላት ከታይታ ያለፈ ሥራ ሊሰሩ ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

 

70 ዓመታትን በጥበብ

 

የሙዚቃ ግጥም ጸሐፊ፣ የቴአትር ባለሙያ፣ የፊልምና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ተዋናይ ነው። ኮሜዲነትም ይሞክራል። በተለይ በዓላት ወቅት ከቴሌቪዥን መስኮት ላይ በኢትዮጵያ አልባሳት አሸብርቆ መታየት የተለመደ ነው። በጦር ሠራዊት፣ በፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ባንድ ውስጥም እየተዘዋወረ  ሰርቷል። የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የኪነት ቡድን መስራችና የቴአትር አሰልጣኝ  ነበር። የከፍተኛ፣ የቀበሌ በሚባሉ የኪነት ቡድኖች ውስጥ በመዘዋወር የተለያዩ የኪነጥበብ ስልጠናዎችን ሰጥቷል። በትራንፔት ሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት ይታወቃሉ። የዛሬ የህይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳችን አርቲስት ተረፈ ለማ።  አርቲስት ተረፈ የሰባ ሰባት ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ነው። አንተ ብለን አንድናወራው ስለወደደ  አክብሮታችን እንደተጠበቀ ሆኖ አንተ እያልን እንቀጥላለን። መልካም ንባብ!

«ተረፈ ቁራ»
ቀጨኔ መድኃኒዓለም ማርገጃ አካባቢ ሄደው ተረፈ ለማ ብለው ቢጠይቁ ማንም ሊነግርዎት አይችልም። ምንም እንኳን ውልደቱና ዕድገቱ እዚያ ቢሆንም «ተረፈ ቁራ» ካሉ እርሱን የማያገናኝዎ አይኖርም። ቤተሰቡ ያወጡለት ተረፈ ለማ ቢሆንም በቅጽል ስሙ ተረፈ ቁራ እየተባለ ይጠራል። ተረፈ የሚለው ስም የወጣለት ትልቅ ምክንያት ነበረው። በ1933 ዓ.ም ታኀሣሥ 29 የተወለደው በሰባት ወሩ ነበር። ከመንታው ጋር ነበር ሆስፒታል ውስጥ እናቱ በጭንቅ የተገላገለችው።
በወቅቱ ማንም ይተርፋል ብሎ አላመነም፤ በተለይ መንታው ሲሞት ከዛሬ ነገ ይሞታል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ግን መዳን ከፈጣሪ ተቸረውና ሳይሞት ቀረ። ይህንን የተመለከቱት አባቱም «ተረፈልኝ» ለማለት ፈለጉና ተረፈ የሚል ስም አወጡለት። የአካባቢው ሰው ግን ተረፈ ቁራው በማለት ይጠራዋል። ቅጽል ስሙን ያገኘው ደግሞ በሚሰራቸው ተግባራትና ባለው ጥቁር መልክ የተነሳ ነበር። ስለዚህም ቁራ በጣም ይበራል፤ እርሱም በጣም ፈጣን ሯጭ በመሆኑ ከልጅነቱ ጀምረው የአባቱን ስም ትተው ተረፈ ቁራ ሲሉ ይጠሩታል።
ህጻኑ ተረፈ በልጅነቱ ምርጥ የሚባሉ የጭቃ ላይ ስዕሎችን መሳል የሚወድ ሲሆን፤ ሸርተቴ፣ ሩጫ፣እግር ኳስ ከሚጫወታቸው የጨዋታ ዓይነቶች መካከል ይጠቀሳሉ። በተለይ በእንጨት ሰበራ ማንም የሚችለው አልነበረም። እንደውም በአንድ ወቅት አንድ በዓል ላይ ቤተሰቦቹ ባይፈቅዱለትም ገንዘብ ለማግኘት ሲል በርከት ያለ እንጨት ሰብስቦ ችቦ ሰርቶ በመሸጥ በእጁ ይዞት የማያውቅን ገንዘብ መያዙን ያስታውሳል። አዲስ ዓመት ላይ ልብሱን ሽክ የሚያደርገውም በሚለቅመው እንጨትና በሚሰራቸው ችቦዎች ሽያጭ ነበር። በተለይ መጀመሪያ አካባቢ እንዲህ ሲያደርግ ከቤተሰብ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ያስታውሳል። ይሁንና ለልብስ የሚወጣ ወጪን ለመቀነስና እነርሱን ለማገዝ ሲል እንደሚያደርገው ሲያስረዳቸው ፈቀዱለትና ብዙ ጊዜ ሳያስቸግር የራሱን ልብስ መግዛት ጀመረ።
«አምስት ሳንቲም በወቅቱ ልዩ ቦታ ነበራት፤ ከስንት ትግል በኋላም ነው ለሽልማት ተብላ እጄ ላይ የምትገባው። ለዚያውም እንደማባበያነትና ላደረኩት ነገር ክፍያ ይሆን ዘንድ። ስለዚህም ይህ ሳንቲም አለመልመዴ ለነገሮች ትኩረት እንድሰጥ እረድቶኛል» የሚለው አርቲስት ተረፈ፤ ለቤተሰቡ ዘጠነኛ ልጅ ነው። አጠቃላይ 13 ልጆች ሲሆኑ፤ አባቱ ቄስ ለማ ወልደመስቀል ይባላሉ። እናቱ ደግሞ እማሆይ ወለተስላሴ አብዬ ናቸው። አባቱ እጅግ ሲበዛ ፀሎተኛና ዓለማዊ ነገር ብዙ የማይወዱ በቀያቸው አንቱ የተባሉና ሰው አክባሪ አዛውንት ናቸው። እናቱም እንደዚያው የቤት እመቤትና በአካባቢው ሰው የሚወደዱ ናቸው።
የዛን ጊዜው ህጻን የዛሬው የ77 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አርቲስት ተረፈ በዓላት ላይ ልዩ ልዩ ትዕይንቶች፣ ጭፈራዎች፣ ዘፈኖች ሲቀርቡ ሲመለከት ሁልጊዜ ይሳብ ነበር። ከህሊናው መቼም ቢሆን የማይወጣውና ልቡ ወደ የሚወደው ደግሞ ቀይ ካባ፣ ሰማያዊ ከረባትና ነጭ ሱሪ ለብሰው የተለያዩ ማራኪ ትይንቶችን የሚያቀርቡ ሰልፈኞችን ሲመለከት ነው። ይህ ደግሞ ቀልቡ ወደ ጠራው ሙያ ለመቀላቀል መነሻ ሆኖታል። እነርሱን መሆን ሁልጊዜም ያስባል። ሰልፈኛ ሙዚቃ የሚያሰሙዋቸው ልዩ ልዩ ሙዚቃዎችን በመከተልም በየአደባባዩ ተከትሏቸው ይሮጥ ነበር። «ሳይደግስ አይጣላ» እንዲሉ አንደኛው ወንድሙ በአገር ፍቅር ቴአትር ይሰራ ነበርና ይዞት እየሄደ የቴአትር ፍቅር እንዲኖረውና የሙዚቃ ጥማቱን እንዲያረካ ያግዘው ነበር።
በቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ በሚሰሯቸው ድራማዎችም አቅሙን አሳይቷል። ብቻውንም ሳይቀር ጥላሸት እየተቀባ ተዋናይ ለመሆን የሚያደርገው ግብ ግብ ፍቅሩ ይበልጥ እንዲያይል አስችሎት እንደነበር ያስታውሳል። የአባቱ ካህን መሆን ደግሞ ከቀጨኔ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ቅዳሴ እንዳይቀር ያስገድደው ነበር። በዚህም ዳዊት ደግሟል፤ ቅኔም መዝረፍም ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ ውጥኑ እስኪሳካ ድረስ ብቻ ነበር በመንፈሳዊ ትምህርቶች ውስጥ የቆየው። ምክንያቱም እርሱ ዲያቆን መሆን አይፈልግም። የዘወትር ፍላጎቱ ዘመናዊ ትምህርት መማርና ሙዚቀኛ መሆን ነው። ይህ ደግሞ በተለይ ከታላቅ ወንድሙ ጋር ያጣላቸው ነበር። ወንድሙ እንዲማር አይፈልግም፤ ሙዚቀኛ ሆኖም ማየትን አይሻም።
ለአርቲስት ተረፈ፤ አባተ መኩሪያና መላኩ አሻግሬ የሁልጊዜ አርአያዎቹና የሚወዳቸው ሰዎች ሲሆኑ፤ የልጅነት ምኞቱ እነርሱን መሆን እንደነበር ይናገራል።
ጥበብን ፍለጋ
ወቅቱ ዘመናዊ ትምህርት መማር እምነትን ያስቀይራል ተብሎ የሚታመንበት ነበር። ስለዚህም አባቱ በምንም መልኩ ከቤተክርስቲያን ትምህርት እንዲርቅና ዘመናዊ ትምህርት እንዲማር አይፈልጉም ነበር። እናት ግን ምንም እንኳን የተማሩ ባይሆኑም ዘመናዊ ትምህርት መማር እንደሚለውጠው ያስባሉ። ስለዚህም ፍላጎቱ እንዲሳካ ባላቸውን በማሳመን አመሃ ደስታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲገባ ዕድሉን አመቻቹለት። የስድስተኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ወስዶም ጥሩ ውጤት በማምጣቱ ሰባተኛ ክፍልን እንዲቀጥል ተደረገ። ስምንተኛ ክፍልንም ተከታተለ። ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ወስዶ ካጠናቀቀ በኋላ ግን ትምህርቱ መቀጠል አልቻለም። ምክንያቱ ደግሞ የኪነጥበብ ፍቅሩ አይሎበት ወደ ሀረር በመሄዱ ነበር።
ሀረር የሚገኘው የጦሩ የሙዚቃ ክፍል ሙዚቀኞችን ይቀጥራል የሚል ወሬ ሲሰማ ሳያቅማማ ነበር ወደማያውቃት ሀረር የተጓዘው። ትምህርቱም ቢዚህ ቆመ። ሆኖም በተለያዩ የውትድርና ሙያዎችና የኪነጥበብ ሥራዎች ስልጠናዎችን ወስዷል።
አፍንጫና ከእጅ ጋር በማገናኘት ድምጽ በማውጣት እርስ በርስ ይናበቡ እንደነበርና ለእያንዳንዷ ድምጽ ልዩ ባህሪ እንደነበራቸው አይዘነጋውም። ዛሬ ድረስም በዚህ የመግባቢያ ዘዴ መጠቀም እንደሚችል ይናገራል። በሌላ በኩል በፖሊስ የህግ ትምህርት፣ የጦር መሳሪያና የሙዚቃ መሳሪያ ትምህርትም ወስዷል።
ጥበብን መጠማት የፈጠረው ዙረት
አርቲስት ተረፈ ሥራውን ሀ ብሎ የጀመረው ገና ተማሪ እያለ ነበር። ሰባራ ባቡር ዲ ብረታብረት ክፍሌ ደስታ የሚባል ብረታብረት ድርጅት ውስጥ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀጠረው። ከዚያ ወደ ሀረር አመራና ሀረር ጦር ውስጥ ሙዚቀኛ ሆነ። በ35 ብር ደመወዝም ከ1953 እስከ 1960 ዓ.ም ድረስ በልዩ ልዩ ክፍል እየተዘዋወረ ሰራ። በዚህ መስሪያ ቤት ሀርሞኒካና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይጫወት ነበር። ይህንን የተመለከቱ የጦሩ መሪዎች ሌላ ዕድል አመቻቹለት። ይኸውም ጦሩን ማዝናናት አለበት ተባለና ወደ ኡጋዴን እንዲላክ ተደረገ። በትንሹም ቢሆን ደመወዙ ከፍ አለ። ግን በረሃ ስለነበር ከባድ ፈተና ነበረበት። እንዲህ እንዲህ እያለም ዓመታት ተቆጠሩ።
ለጉብኝት በሚል ኮሎኔል ቶላ በዳኔ ጋር ወደ ሀረር ተመለሰ። ግን ዳግመኛ ወደ ኡጋዴን እንዲመለስ አልተደረገም። ምክንያቱም በዚህ ቢያገለግል የተሻለ ውጤት ማምጣት ይችላል ተብሎ ታመነበትና እዚሁ እንዲቆይ ተደረገ። በጦር ሠራዊት የሙዚቃ ሥራ ውስጥም ተመደበ። ነገር ግን የጉርምስና ነገር አየለና ሥራው ደበረው። ስለዚህም አመመኝ በማለት ሥራውን ለቀቀ። ግን አልሸሹም ዘወር አሉ ሆነና ነገሩ ከሀረር ሳይርቅ በሙዚቃው ዘርፍ ለማገልገል ምስራቅ በረኛ ፖሊስ ኦርኬስትራ ውስጥ በ1960ዎቹ ተቀጠረ። እስከ ለውጡ ድረስም አገለገለ።
አርቲስት ተረፈ በ1966 ዓ.ም ስጋቱ እየሰፋ በመምጣቱና ለኑሮም ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ግርግሩን ተጋፈጠ። ምርጫ መጣናም ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ተብለው ከተመለመሉት መካከል አጃቢ በመሆን አዲስ አበባ ተላከ። ይሁንና የእርሱ ሥራ ሙዚቀኛና የኪነጥበብ ሰው መሆን ብቻ ነው። የተላከበት አላማ ደግሞ በተቃራኒው ሆነ። ግድ ፖለቲከኛ መሆን ይጠበቅበታል። ንግግሩ፣ ተግባሩም፤ ክየናውም ሆነ እንቅስቃሴው ፖለቲካ ብቻ ማድረግ አለበት። «ባልመጣሁ ኖሮ» እስኪል አስመርሮት እንደነበር ያስታውሳል። ይሁን እንጂ በመጨረሻ አንድ ነገር ተከሰተ። ሀረር ውስጥ በሙዚቃው ዘርፍ ምን ያህል ሲያዝናና እንደነበር የሚያውቀውን ሰው አገኘ። መቶ አለቃ ፍስሃ ገዳ የሚባል ሰው፤ የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም አጃቢና ፕሮቶኮል ኃላፊ ነው። ከዚያም ሳያመልጠው «እባክህ ከዚህ ክፍል ቀይረኝ፤ ሥራው ከብዶኛል። ፍላጎቴንም ማሟላት አልቻልኩም» ይለዋል። መቶ አለቃ ፍሰሃም «ትንሽ ጠብቅ ቦታ ይፈለግልሃል» ብሎ ከተለየው በኋላ የተወሰኑ ወራት አልፈው ደርግ ገብቶ መንግሥት ቅየራ በመደረጉ የተነሳ ወደ መንግሥት ንብረትነት የተዘዋወረው ብሔራዊ ሀብት ልማት የሚባል ድርጅትን በሚሊተሪ ውስጥ ሆኖ እንዲመራ ዕድሉ ሰጠው። ተቆጣጣሪ እንዲሆንና ኑሮውም አስኮ ጫማ ፋብሪካ ውስጥ እንዲያደርግ አገዘው። ለእርሱ ግን ይህም ቢሆን ምቹ አልነበረም። ከፖለቲካው አልተላቀቀም። ሠራተኛውም ቢሆን ሊቀበለው አልቻለም፤ «የደርግ አሽከር» እያሉ ሲያሽሟ ጥጡበት መልቀቅን ፈለገ። የሥራ ማስታወቂ ያዎችንም መከታተሉን አጧጧፈው። በተለይም ከኪነጥበቡ ጋር በተያያዘ የሚወጡ ማስታወቂያዎችን አዘውትሮ ይመለከት ነበር።
ይህ ጥረቱ ተሳካና የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሙዚቀኛ መቅጠር እንደሚፈልግ ሰማ። ወዲያው ወደቦታው አመራ፣ ተመዘገበ፣ ለፈተናም ቀረበ። ግን በውስጡ ብዙ ፍራቻዎች ነበሩበት። ምክንያቱም ሁሉም ተወዳዳሪዎች የትምህርት ደረጃቸው ከስምንተኛ ክፍል በላይ ናቸው። ምንም እንኳን አቅሙና እውቀቱ ቢኖረውም የትምህርት ደረጃው የሚጥለው መስሎ ተሰምቶት ነበር። ስለዚህም «ከሆነ ይሆናል ካልሆነም እዚያው እሰራለሁ» በማለት ሁለት ሃሳብ ይዞ ለውድድር ቀረበ።
ከእነ ተሾመ አንዳርጋቸው፣ ከእነ ፈቃዱ ተክለማርያም፣ ከእነ ገለታ ተክለጻዲቅ፣ ከእነ ወለላ አሰፋና መሰል አንጋፋ አርቲስቶች እኩል ቆመ። የሚያቀርቡት የመወዳደሪያ መስፈርት ስሜት ፈጣሪ ግጥም ከስሜት ጋር በተዋሃደ መድረክ ላይ መተግበር ነው። ከተዋቂ ቴአትሮች ውስጥ አንዱን መርጦ መቅረብም ሌላው ፈተና ነው። ወንደሰን ገብረየሱስ፣ ተፈሪ ብዙአየሁና ወጋየሁ ንጋቱ የወቅቱ ፈታኞች ነበሩ። አርቲስት ተረፈም እስካሁን አልረሳሁትም የሚለውን የአቤ ጉበኛ ግጥም እንዲህ በማለት አቀረበ።

አርቲስት ተረፈ ለማ


«በጣም ያስገርማል ወሬ ድፍረትህ
በሥራ በለጥኩኝ እኔ ማለትህ
በእኔ በስራ እንጂ አለም ያደገችው
መቼ በወሬ ነው ጥበብ የጎላችው
ያ ትልቁ መጽሐፍ ለሰው ልጅ የሚለው
ለፍተህ፣ ጥረት፣ ግረህ በላብህ ብላ ነው
አይገባህም እንጂ ወሬኛ እምትኖረው
እሹሹ ጌታዬ ነገር ስትፈትል ነው
ይህቺን አቅርቤያለሁ መቀጠር ጥሩ ነው» ብሎ ሲጨርስ ወዲያው እንዲቀጠር ተፈቀደለት። በ45 ብር ደመወዝ ኮንትራት ሠራተኛ ሆነና ከሚወደው ሙያና ከሚወዳቸው አርቲስቶች ጋር ተቀላቀለ። የቤቱ መሰረት፤ የኑሮውን ቀዳዳ መሙያም ማዘጋጃ ቤትን አደረገ። በዚህ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ቴአትር ለማቅረብ መድረክ ላይ የወጣው «ባለካባ ባለዳባ» በሚለው ሲሆን፤ «መቃብር ቆፋሪው»፣ «ሳር ሲነድ»፣ «ኦቴሎ»፣ «መልዕክተ»፣ «መቅድም» እያለ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የተሰሩ ቴአትሮችን በአብዛኛው ከአጃቢ ተዋናይነት እስከ ዋና ተዋናይነት ሰራ።
አርቲስት ተረፈ የተለያዩ የዘፈን ግጥሞችንም ቢሆን ማዘጋጃ ቤት እያለ ይጽፍ ነበር። ለምሳሌ የሚገጥማቸውን የዘፈን ግጥሞች «ድሮም ገበሬ ነኝ» በጸጋዬ ዘርፉ፣ «አራሹ ግብረ ሃይል» በትረ ወልደ አማኑኤል እና ሌሎች ግጥሞች በእነ ተሾመ ወልዴ መሰል ዘፋኞች ለመድረክ በቅቷል። በየጊዜው ለተለያዩ ቴአትሮችና ፊልሞች ማጀቢያ የሚሆኑ የዘፈን ግጥሞችንም ይጽፍ እንደነበር ይናገራል። በተመሳሳይ እንደ «ቤት አከራዩ»፣ «ያልተሄደበት መንገድ»፣ «እንቅፋት» ና የመሳሰሉት ላይ በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ላይ ሰርቷል። በፊልምም ቢሆን «የእናት ዋጋ»፣ «ሀግዕዝ»፣ «መክሊት»፣ «አንጥረኛው»ና «ፍርሃት» በሚሉት ላይ የትወና አቅሙን አሳይቶባቸዋል። በኮሜዲያንም ሆኖ ሰርቷል።
ቅሬታ
አርቲስት ተረፈ ማዘጋጃ ቤት የሰራ ሰው የሚታወቅበትና ልዩ መረጃ የሚታይበት ስርዓት አለመኖሩ ሁሌም እንደሚያናድደው ይናገራል። ለዚህም ደግሞ እርሱን ጨምሮ ሌሎች ተዋቂ አርቲስቶች እንዲደበቁ በማድረጉ ብዙ ሥራዎች ላይ እንዳይሳተፉ ገድቧቸው ነበር። ለሌላ ሥራ ለመታጨት ዕድሉ አይኖራቸውም። ሌሎች ቴአትር ቤቶች በሥራቸው የሚሰሩ አርቲስቶች ሙሉ መረጃ አላቸው። ስለሰዎቹ ለማወቅ ሲፈለግም ያንን አንብቦ ለመምረጥና ለሥራ ለመመልመልም ምቹ ይሆናል። ማዘጋጃ ቴአትር ቤት ግን ምንም አይነት መረጃዎች ስለሌሉት በዚህ ተጠቃሚ የሚሆን አርቲስት አይኖርም። ስለነሱም ማወቅ የሚፈልግ ሰው ቢመጣ ባለታሪኩን ወይም ስለእርሱ የሚያውቁትን ሰዎች ካልጠየቀ በስተቀር ምንም ማወቅ አይችልም። ይህ ደግሞ በህይወቴ ከሚያሳዝነኝ ነገር አንዱ ነው ይላል። ሌላው ምንም እንኳን በማዘጋጃ ቤቱ ከዓመት በላይ ቢያገለግልም ቋሚ ለመሆን የሚሰራው ሥራ እጅግ እንደፈተነው አይረሳ ውም። ቦታውን ለማግኘት መጸዳጃ ቤት መጥረግ፤ ሸረሪት ያደራበትን አቧራ መጥረግ የመጀመሪያ ሥራውእንደነበር አይዘነጋውም ። ውትድርና ላይ ሆኖ ከጉልበቱ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ጥይት መመታቱ ያለመዳን ስሜት የተሰማውን ቀንን አይረሳውም። ከዚያ ውጪ የሚያሳዝነውም ሆነ የገጠመው ፈተና እንዳልነበር ነው የሚናገረው።
ገጠመኝ
አርቲስት ተረፈ በርካታ ገጠመኞች ባሳለፈው 77 ዓመታት ውስጥ አሉት። ነገር ግን ሁለቱን ብቻ እናንሳ። የመጀመሪያው በ1970ዎቹ አካባቢ የገጠመው የማይረሳው ትዝታው ሲሆን፤ በሰለሞን ክፍሌ የተደረሰ «መስኮት» የተሰኘ የቴሌቪዥን ድራማ ለመስራት በዝግጅት ላይ ሳሉ በቀረጻ ወቅት ሽጉጥ ያስፈልጋልና በወቅቱ ለማግኘት ይቸገራሉ። ከዚያም አዘጋጁ ከሆነ ሰው ይቀበልና ለተረፈ ይሰጠዋል። ሽጉጡ የተሰጠው ተረፈም አርቴፊሻል ስለመሰለው እንደለመደው ለመጠቀም ይሞክራል። በመጀመሪያ የተደረደሩ ተዋናዮችን እያስፈራራ ያስኬዳል። ግን አይተኩስም። በመጨረሻ ግን ጌታሁን ሀይሉ የሚባለው ላይ አነጣጥሮ ያልተፈተሸ ሽጉጡን ይተኩሳል። ግን የተተኮሰበት ሰው በመሸሹ እርሱም ተርፎ ተረፈንም ከተጠያቂነት አውጥቶታል። ዛሬም ድረስ የተተኮሰበት ሰው «ገለኸኝ ነበር እኮ» እያለ እንደሚያነሳበት ይናገራል።
ሌላው ገጠመኝ አስመራ ለሥራ በሄደበት የተከሰተው ነው። ነገሩ እንዲህ ነው። በአንድ ጊዜ እስከመሳሪያቸው ለመላክ መስሪያ ቤቱ ይቸገራል። ስለዚህም ግማሹ ቡድን ቀድሞ ሄዶ ዝግጅት እንዲያደርግ ያዛል። ከዚያም ሁለተኛ ቡድን በዝግጅቱ ወቅት ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ አውሮፕላኑ በመበላሸቱ የተነሳ ይቆያል። ሰውም ዝግጅቱ ይቀርባል ብሎ ይጠባበቃል።
የሥራ ባልደረቦቻቸው በአየር ችግር ምክንያት አውሮፕላኑ ለማረፍ ተቸግሮ ሰዓታትን በአየር ላይ ያሳልፋሉ። በዚህ ጊዜ ካሁን አሁን ሞቱ፤ ተከሰከሰ የሚል ወሬ ይደርሰናል እያሉ በስጋት ሰዓታትን አሳለፉ። ሁሉም በእየእምነቱ መጸለይ ጀመረ። ከሰዓታት በኋላም ፀሎታቸው ተሰማና ምንም ሳይሆኑ አውሮፕላኑ በሰላም አረፈ። ሰዎቹም ወደ ሥራቸው ገቡ። ስለዚህም እነርሱም ራሳቸውን ለመሰብሰብና ጓደኞቻቸውን ለማረጋጋት ሲሉ ቀኑን ያሳለፉበትን ጊዜ እስካሁን ያስታውሰዋል። እንደውም አንዷ ጓደኛቸው የጥር ስላሴን እንደምትዘክር አጫውቶናል።
ሽልማት
ኡጋዴን ሄዶ እያለ በቀላል ሚዛን የስፖርት ውድድር ተመርጦ ሜዳሊያ አግኝቷል። እንደውም አፍንጫው ተሰብሮ እንደነበር ያስታውሳል። በጦር ሠራዊት ሲሰራ የተዋጊ ምልክት ተሰጥቶታል። በማዘጋጃ ቤት ደግሞ በ35 ዓመት አገልግሎቱ የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል። በፊልም ሥራዎችም እንዲሁ ከ35 በላይ የምስክር ወረቀቶችን አግኝቷል። በቴአትርም በተለያዩ ጊዜያት የምስክር ወረቀቶች ተበርክቶለታል። በተለይ «በማዶ ለማዶ» በተሰኘው ቴአትር ከምስክር ወረቀቱ ባሻገር የአምስት መቶ ብር ተሸላሚ ሆኖ ነበር።
ውሃ አጣጭ
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ በኪነጥበቡ ዘርፍ የሰራው አርቲስት ተረፈ፤ ከአገር ውጪ በጀርመን፤ በሆላንድ፣ ፈረንሳይና ሌሎች አገሮች ዞሯል። በዚህም አገሩ ከሌሎች አገራት በምን እንደምትለይ ለይቶ ያውቃል። ስለዚህም ልጆቹን ሁል ጊዜ የሚያስተምረው አገር ወዳድነትን ነው። በአገር ውስጥ በነበረው ቆይታ ሚስት አግብቶ ነበር። ከእርሷም ሁለት ልጆችን አፍርቷል። አሁንም ድረስ ከልጆቹ ጋር ይጠያየቃል።
ሁለተኛዋ ባለቤቱ አሁን አብራው ያለችው ስትሆን፤ ማዘጋጃ ቴአትር ቤት የዳረለት ልዩ ሚስቱ ናት። ግንኙነታቸው የጀመረው ግን በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሰራ በነበረበት ወቅት ነው። ኃላፊ ሆኖ ሲያገለግል ጸሐፊው እንድትሆን ተቀጠረችለት። በዚህም ትህትናዋ፣ እንክብካቤዋና ያላት የሰው ፍቅር ልቡን ረታው። አፈቀራትና ሊያገባት ወሰነ። ፈቃዷንም ጠይቆ ለዚህ የሚያምር የትዳር ህይወት በቁ። ዛሬ የአንዲት ሴትና ሦስት ወንድ ልጆች አባትና እናት ሆነዋል። ሁሉም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። አርክቴክት ልጁ ግን ሁልጊዜ የእርሱን ፈለግ መከተል ትፈልጋለች። እናም የዳንስ ፍቅር ስላላት በእርሱ ክሊፕ ለማውጣት እየጣረች እንደምትገኝ በወጋችን መካከል ነግሮናል።
«ኪነጥበብ ግብረገብነትን ያስተምራል፤ ባህልን ያሳውቃል። ከባህል ውጪ ላለ ተግባር እንዳንቆም ያሳስባል። ይሁንና ወጣቱ ገንዘብ ተኮር እየሆነ በመምጣቱ የተነሳ የኪነጥበብ ፍቅሩንና ግብረገብነቱን እየተወ ስለመጣ ከአንጋፎቹ ይህንን ይማርና ህይወቱ ያድርገው፤ ይኑርበትም። ከእኔና ከቤተሰቦቼ የሚተላለፈውም ይህ ግብረገብነት ነውና ሌሎችም እንዲያደርጉት ፍላጎቴ ነው» በሚለው መልዕክቱ ረጅሙን የህይወት ቅኝት ቋጨን። ሰላም!

ፅጌረዳ ጫንያለው

Published in ማህበራዊ

ከዕለታት በአንዱ ቀን አንድ መንገደኛ በስምና በዝና ብቻ ወደሚያውቃት ከተማ ለመሄድ ብቻውን ጉዞ ይጀምራል፡፡ ጥቂት እንደተጓዘም የከተማዋን ስም በመጥቀስ ወደእዚች ከተማ ለመድረስ ምንያህል ሰዓት እንደሚፈጅበት ይጠይቃል። መድረሻውን የማያውቀው መንገደኛ መንገድ ላይ ያገኛቸውን አዛውንት እንዲህ ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ «ቀጥሎ ያለው ከተማ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብኛል?» ተጠያቂው አዛውንት መልስ ሳይሰጡ ዝም ብለውት ይሄዳሉ፡፡
ምላሽ ያጣው መንገደኛም መልስ ባለማግኘቱ እየተናደደ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ትንሽ እንደተጓዘም አዛውንቱ መንገደኛውን በመጥራት «አንድ ሰዓት ይፈጅብሃል» ይሉታል፡፡ በአዛውንቱ ሁኔታ የተበሳጨው መንገደኛ ጉዞውን ገታ አድርጎ «ቅድም ስጠይቅዎ ለምን አልነገሩኝም?» አላቸው። አዛውንቱም የዋዛ አልነበሩምና «ቅድምማ የጉዞ ፍጥነትህን፣ የእርምጃ ርዝመትህን አላወኩትም ነበር» አሉት።
ሁላችንም እኩል አንፈጥንም፤ ሁላችንም እኩል አንራመድም፡፡ በመሆኑም ሁላችንም ከጉዟችን ፍጻሜ እኩል አንደርስም፡፡ የሰው መድረሻው ፍጥነቱና አካሄዱ ሳይታይ የሚገመት ቢሆንማ የሩጫ ውድድሮች ባልተደረጉ ነበር። ሁሉም ሰው በእውቀት ማማ፣ በጥበብ ከፍታ፣ በአስተሳሰብና ንቃት እኩል አይመዘንም፡፡ ሁላችንም ካሰብነው ስኬት ለመድረስ ስናስብ ትክክለኛው ጥያቄ መሆን ያለበት «ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?» ሳይሆን «ምን ያህል ጊዜ ይወስድብኛል?» ነው፡፡ ምክንያቱም መድረሻችን እንደየፍጥነታችን ይወሰናልና።
አንዳንድ ጊዜ ፍጥነት የሚለካው በአካሄድና በአረማመድ ብቻ አይሆንም። ምክንያቱም አረማመዳችን የሚወሰነው ባለንበት የጤንነት ሁኔታ፣ በመንገዱ ምቹነትና ባደረግነው የጫማ አይነት ሊለያይ ይችላል። ብዙ ነገር የተመቻቸላቸው ሰዎች በተሻለ ፍጥነት ብዙ ርቀት ይጓዛሉ። በተቃራኒው ደግሞ ነገሮች ያልተመቻቸላቸው ሰዎች ብዙ ለመጓዝና ለመፍጠን ቢፈልጉም እንደሀሳባቸው ሊጓዙ አይችሉም።
ሀገራችን ከድህነት ለመውጣት ብዙ ዓመታት ጥረት አድርጋለች። በተለይም የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ ስታደርግ ለብዙዎቻችን አስደንጋጭና ሊጨበጥ የማይችል ህልም መስሎ ነበር። በብዙዎች ዘንድም «ሊደረስበት የማይችል የተለጠጠ እቅድ» ተብሎም እንደነበር አንዘነጋውም። ግን ደግሞ ለእቅዱ ስኬት ምቹ የሆኑ ነገሮች ታሳቢ ተደርገው ስለነበር የተፈራውን ያህል ሳይሆን ብዙዎቹ ተግባራዊ ሆነዋል። ያንን ታሳቢ ያደረገው ሁለተኛው የዕድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ ደግሞ እነሆ አጋማሽ ዘመኑ ላይ ይገኛል። ይህ እቅድ ምንያህል ስኬታማ እንደነበር ተገምግሞ ውጤቱ ይፋ ባይደረግም ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በታቀደው ልክ እንዳልተሳካ ለመገመት አያዳግትም።
ከመነሻችን ላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው መድረሻዎች የሚገመቱት በአረማመዳችንና በሚፈጠሩት ምቹ ሁኔታዎች ነው። በመሆኑም በሁለተኛው የእቅድ ዘመን በፍጥነት ለመጓዝ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንዳልነበሩት ለማናችንም የተሰወረ አይደለም። በመሆኑም መጓተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል። አፈጻጸሙ ምንም ይሁን ምን በቀሪዎቹ ጊዜያት ለማካካስ የሚያስችል ስልት ቀይሶ መጓዝ ተገቢ ነው። ከተቻለም በጥናት ላይ ተመስርቶ መከለስና መሻሻል፤ እንዲሁም መለወጥ ያለባቸው እቅዶች ካሉም መፈተሽ ይገባል።
አገራችን መቼ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ መሰለፍ እንዳለባት የረጅም ጊዜ እቅድ አስቀምጣለች። እቅዷ ሊሳካ የሚችለው ደግሞ በአረማመዷ ፍጥነትና የሚፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች ታሳቢ ተድርገው ነው። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንቅፋቶችና መልካም አጋጣሚዎች በተጓዳኝ እየሄዱ እንደሚገኙ ለመረዳት ይቻላል። በአንድ በኩል ዕድገታችንን ወደኋላ ሊጎትቱ የሚችሉ በርካታ ተግዳሮቶች ተፈጥረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ችግሮቹ በፈጠሩት ንቅናቄ አዳዲስ አስተሳሰቦች ተፈጥረው ብሄራዊ መግባባትን ሊያመጡ የሚችሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
በተለይም በአንዳንድ ክልሎች ተፈጥረው የነበሩት ረብሻዎች የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንደጎዱት መካድ አይቻልም። በተጨማሪም የቱሪዝም እንቅስቃሴው መቀነስ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱና ሌሎች ምክንያቶች ተደምረው የኑሮ ውድነቱን አባብሰውታል። እንዲሁም ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም ወጥተው መግባት አለመቻላቸውም በኢኮኖሚው ላይ ጫና ማሳደሩ እንደማይቀር ይታመናል።
ይህ የጉዞ ፍጥነትና ምቾት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ ብቻም ሳይሆን ከዕለት ዕለት የዕድገትና የመለወጥ ፍላጎታችን ጋርም የሚያስተሳስረው ሰንሰለት አለው። ምክንያቱም የእያንዳንዳችን የመለወጥና የማደግ ፍላጎት ወደ ግባችን ለመድረስ በሚኖረን ፍጥነትና ምቹ ሁኔታ ይወሰናል። ነገ የምንመኘውን መልካም ቀን ለማግኘት ዛሬ ላይ ሆነን አረማመዳችንንና የሥራ ፍጥነታችንን ማሻሻል ይኖርብናል።
የእያንዳንዱ ዜጋ መለወጥ የሀገር መለወጥ እንደሚሆን በማመን በተሰማራንበት የሥራ መስክ ፍጥነታችንን ጨምረን ተደማሪ ውጤት ልናስመዘግብ ይገባል። በተለይም አሁን ከተፈጠረው አዲስ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር ራሳችንን አስቃኝተን የለውጡ አካል መሆን ይገባናል።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ወጣት ሰናይት በትሩን ለበርካታ ዓመታት አነስተኛ በሆነች ሱቅ ደንበኞቿን ስታስተናግድና የተለያዩ መገልገያዎችን በችርቻሮ ስትሸጥ አውቃታለሁ። በቤት ኪራይ ምክንያት አንዱ ጋር የጀመረችው ሥራ ተቋርጦ ወደሌላ ስትቀይርና ደንበኞቿን ስታጣ፤ ደግሞ ድጋሚ ሌላ ቦታ ሄዳ ስታላምድ፤ ብዙ ዓመታትን አስቆጥራለች። ለንግድ ሥራ የተፈጠረችና ሥራውንም በደንብ የምትችል መሆኗን የሚያውቁ ሁሉ «እርሷ እኮ ገንዘብ ማጣቷ ነው'ንጂ እንዴት ያለ ሀሳብ ነበራት!» ይላሉ።

ወጣት ሰናይት ኑሮዋን እንዴት መለወጥ እንደምትችል ታውቃለች፤ ለወጡን ለመጀመር ግን በእጇ ላይ ምንም ገንዘብ የለም። ገንዘብ በማጣቷ ምክንያት የስራ ፈጠራ ሃሳቦቿ ሀሳብ ብቻ ሆነው ቀርተዋል። የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውንና ባለሃብቶችን የሚያገናኝ እድል እስኪፈጠር ከእጅ ወደአፍ የሆነውን ስራ እየሰራች ኑሮዋን መግፋቱን ተያይዛዋለች። በፍላጎትና በአቅም አለመመጣጠን ውስጥ ሆነው ኑሮን እየገፉ ያሉና ሃሳባቸውን ወደተግባር መለወጥ የማይቻል ሆኖባቸው እጅ እግራቸው የተሳሰረ ስንት ሰዎች በአቅራቢያችን እንዳሉ ወጣት ሰናይት አንዷ ማሳያናት። በየአካባቢያችን ምርጥ የተባለለት የስራ ሀሳብ ኖሯቸው ገንዘብ በማጣት ብቻ በተጎሳቆለ ኑሮ ውስጥ ህይወትን የሚገፉት ምንያህል እንደሆኑ ቤት ይቁጠራቸው።
በአንጻሩ ደግሞ ይህንን ታሪክ የማያውቁ፤ ያልሰሙ ወይም ሰምተው ግን ብዙ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ያልተረዱ ባለፀጋዎች ብዙ አሉ። እነዚህ ሰዎች በካዝና እና በኪሳቸው ሙሉ ገንዘብ አላቸው፤ ባለሀብትም ናቸው። ገንዘቡ ቢገላበጥና ትርፍ ይዞ ቢመጣ የሚፈልጉ ቢሆንም ገንዘባቸውን ምን ስራ ላይ ማዋል እንዳለባቸው አያውቁም። እነዚህ ሁለት ጫፍ ላይ የቆሙ ሰዎች አልተገናኙም፤ ስለዚህም ሃሳቦች በየቦታው እየባከኑ ገንዘብም በተሻለና በበለጠ ፍሬያማ በሚሆንበት ስፍራ ሳይውል ቀርቷል።
አቶ አዲስ ዓለማየሁ የቱ-ፋይቭ-ዋን ኮሙዩኒኬሽን እና ማርኬቲንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። «በአገራችን የስራ ፈጠራ ሃሳብ ያለው እና ገንዘብ ያለው ሰው ብዙ ጊዜ አይገናኙም። ዋናውና ትልቁ ችግርም ይኸው ነው» ይላሉ።
ከአንዱ ሰው የተሻለ ሃሳብ ከሌላው ደግሞ ገንዘብን አቀናጅቶ ሥራን የማስፋፋት ነገር ብዙውን ጊዜ የሚታየው በቤተሰብ መካከል ነው። በተለይም የሥራ  ፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ላይ ገንዘብን ማፍሰስ ቢለመድ ደግሞ አስፈላጊነቱ ይታወቅ ነበር። አብረን እንደምንበላው አብረን የመሥራቱ ባህል ቢኖረን መልካም ይሆን እንደነበር ይናገራሉ።
አቶ አዲስ ከተመለከቱትና ከገጠማቸው በመነሳት የፈጠራ ሀሳብ ኖሯቸውና ሥራ ጀምረው በገንዘብ እጥረት ብቻ ሥራቸውን ያቋረጡ ወጣቶችን እንደሚያውቁ አውስተዋል። ምንም እንኳ ገበያ ባይጠፋ፣ ከወጣቶቹ ዘንድ ፍላጎቱ ባይጠፋ፣ ብሎም ሥራው ትርፋማ የሚያደርግ ቢሆንም ፤ በገንዘብ ችግር ምክንያት ብዙዎችን ሊጠቅም የሚችለው የሥራ ሃሳብ በራሳቸው ዘንድ ብቻ ይቀራል።
ችግሩ የገንዘብ ማጣት ወይም ማጠር ብቻ ነው ወይ? የሚለው ሌላው ጥያቄ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አዲስ፤ አዳጊ በሆነች አገር ላይ ሌሎች በርካታ ችግሮች መኖራቸው አይቀርምና የንግድ ሥራን ለመጀመር ካለው የአሠራር ርዝመትና አሰልቺነት ጀምሮ ችግሮች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። ገና ሥራው ሳይጀመር ያለው ቢሮክራሲ አልፎም ገና ሥራው እንደተጀመረ የሚከተለው የግብር ጫና «ቢቀርብኝስ!» ብሎ ማፈግፈግን የሚያመጣ ነው።
ብዙ የንግድ ሥራዎች በብድር ይጀመራሉ። አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች የብድር አገልግሎት አግኝተው በሌሎች ግለሰቦች ሳይደገፉ ራሳቸውን አሳድገው ለብዙዎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላሉ፤ ገንዘብ ባለሀብቱ ጋር ብቻ ሳይሆን በባንኮችም ይኖራልና። ነገር ግን ባንኮች ጋር ገንዘብ ቢኖርም ገንዘቡ ለባለሀብት እንጂ ምርጥና አዲስ የሥራ ሃሳብ ለያዘና ገንዘብም ሆነ ዋስትና ለሌለው ወጣት ሥራ ፈጣሪ አይሰጥም። የባንኮች ስርዓት ለዚህ ምቹ ሁኔታን እስኪፈጥር ድረስ ባለሀሳቦችና ባለሀብቶች ቢቀናጁ በጋራ ትርፋማ ሆነው ለሌሎችም የሥራ ዕድልን መፍጠር እንደሚችሉ ይናገራሉ።
«ብዙ ባለሀብቶች ህንጻ መገንባት ላይ ገንዘባቸውን ያፈሳሉ። ይህ ምንአልባት የሚያስተማምን ወይም የማይጎዳ ሀብትን ማስቀመጫ መንገድ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሌሎች ሰፊ እድሎች አሉ» ያሉት የሪኒው ስትራቴጂ ፓርትነር እና ኢንቨስተር ሪሌሽን ወይዘሮ ላውራ ዴቪስ ናቸው።
እኚህ በአገራችን ከስድስት ዓመታት በላይ በሥራ ፈጠራ ዙሪያ ሲሠሩ የቆዩ ባለሀብት ሴት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ክፍለ ዓለም የሥራ ፈጣሪ መሆን ከባድ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ሥራ ፈጣሪነትና ያንን ተከትሎ የሚመጣውን ስኬት መጠበቅ ጽናት ይፈልጋል፤ ቶሎ ይሳካልኛል ብሎ ማሰብም ዘበት እንደሚሆን ይናገራሉ። እንዲያም ሆኖ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ወጣቶች በርካታ ናቸውና የሥራ ፈጠራ አሁንም አስፈላጊ መሆኑ በመሆኑ ባለሀብቶችና የስራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ማገናኘት ፋይዳው ብዙ ይሆናል።
ወይዘሮ ሎራ እንደሚሉት፤ ባለሀብቱና የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ያለውን ወጣት የሚገናኙበትን ምህዳር መፍጠር ያስፈልጋል። ይህን መገናኛ መስመር በመፍጠር በኩል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት «የንግድ ሥራ ፈጠራ ተሰጥኦ ውድድር» በሚል ርዕስ የሚያዘጋጀው መርሃግብር ይጠቀሳል። አሁን ደግሞ በቅርቡ ተመሳሳይ ዓላማን በተለየ መንገድ ይዞ የቀረበ ዝግጅት መጥቷል፤ «ችግኝ ጦብያ» የቴሌቪዥን መርሐግብር። የዚህ መርሃግብር ዋና አዘጋጅ ወጣት የሥራ ፈጣሪ ነው። ግርማይ ኃይለሥላሴ ይባላል። ይህ ወጣት ባለሀብቱና ባለሀሳቡ እንዳልተገናኙ፤ የሥራ ፈጠራ ላይ የተሳተፉ ወጣቶችም እንዳሰቡት መራመድ ያለመቻላቸውን እውነታ ይቀበላል።
«ፍጥነት የሚለካው በአካሄድ ብቻ ሳይሆን በተነጠፈ መንገድና በተደረገ ጫማ ነው። የሌላው ዓለም ሰዎች ለብዙ ነገር የተመቻቸ እድል ስላላቸው ብዙ ርቀት ይሄዳሉ። የእኛ ግን ብዙ መንገዱ የሚያስኬድ ስላልሆነ ብዙ ስንጓዝ አይታይም» ይላል። ምድረ ቀደምት የተባለች አገራችን በርካታ በፈጠራ ሥራ የተካኑ ሰዎች ያሉባት ናት፤ ይህም የፈጠራ ሥራ መንፈስ መቀስቀስ እንዳለበት ነው ወጣት ግርማይ የሚያምነው።
ባሳለፍነው ማክሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2010ዓ.ም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቅርቡ መተላለፍ ይጀምራል የተባለው «ችግኝ ጦብያ» የቴሌቪዥን መርሃ ግብር ገላኒ ቡና በተባለ ስፍራ በይፋ ተመርቋል። ዝግጅቱ በጊዜ ሂደት በስፋትና በጥልቀት የተሳታፊውን ቁጥር ከፍ በማደረግና የአየር ሰዓቱንም በመጨመር ስለሚንቀሳቀስ አልተገናኝቶም የተባለውን የባለሀሳቡና የባለሀብቱ ነገር ለማስቀረት እንደሚጥር ቃል ገብቷል።

ዜና ሐተታ
ሊድያ ተስፋዬ

 

 

Published in የሀገር ውስጥ

በውይይቱ ላይ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን፣ የስብሃት ገብረእግዚአብሔር፣ የበዓሉ ግርማና ሰለሞን ደሬሳ ስም ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ ውይይቱ ‹‹ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በአማርኛ ስነ ጽሑፍ ውስጥ›› ይሰኛል፡፡ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በአማርኛ ስነ ጽሑፍ ውስጥ የእነዚህ ደራሲዎች ስም ተደጋግሞ መነሳት ደግሞ ምክንያት ነበረው፡፡ እነዚህ ደራሲዎች በሌሎች ቋንቋዎች መጻፍ የሚችሉ መሆናቸው ነው፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን፣ በዓሉ ግርማ እና ሰለሞን ደሬሳ በኦሮምኛ ቋንቋ መጻፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር በትግርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋ መጻፍ የሚችል ነው፡፡ ‹‹እኔ በአማርኛ መጻፍ እንደሚቻል ያወቅኩት ዳኛቸው ወርቁን አይቼ ነው›› ሲል በአንድ ወቅት መናገሩ ይታወሳል፡፡ 

ሰለሞን ደሬሳ በእንግሊዘኛና በፈረንሳይኛም መፃፍ ይችላል፡፡ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ከውጭ ቋንቋዎች በፈረንሳይኛና በእንግሊዘኛ መፃፍ ይችላል፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የአፍሪካ ህብረትን መዝሙር በእንግሊዘኛ ከጻፉ ሦስት ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ግን ለምን በአማርኛ ቋንቋ መጻፍ ፈለጉ? ሲባል ስነ ጽሑፍ የፈጠረው ብሄራዊ ስሜት መሆኑን የስነ ጽሑፍ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በየወሩ መጨረሻ ውይይት ያካሂዳል፡፡ የግንቦት ወር መርሐ ግብሩን ባሳለፍነው ሳምንት ግንቦት 30 ቀን በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ የስነ ጽሑፍ ምሁራን በተገኙበት አካሂዷል፡፡ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ፣ ስነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ ናቸው፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ «ከያኒያን ስኬታማ ናቸው፡፡ በስነ ጽሑፍ ሁሉን ይገልጻሉ፤ ስነ ጽሑፍ ስኬታማ ነው፡፡ የእነዚህ ከያኒያን ሥራ ያለ ብሔር ልዩነት፣ ያለ ሃይማኖት ልዩነት፣ ያለ ቋንቋ ልዩነት… ያለምንም ልዩነት ሰዎች ይቀበሏቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሚፈጥሩት የጋራ ስሜት በመሆኑ ነው፡፡ ስነ ጽሑፍ የቋንቋ ልዩነት እንኳን የለውም፡፡ የአማርኛ ስነ ጽሑፍ እንደምናስበው የአማርኛ አይደለም›› በማለት ሀሳባቸውን ይጀምራሉ፡፡
«የአማርኛ ስነ ጽሑፍ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ያደረገው ደግሞ እንደ ባህልም ስለሆነ ነው፡፡ የተፃፈበት ቋንቋ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን ባህልም ሆኗል፡፡ ለዚህም ጸሐፊዎቹን ማየት በቂ ምስክር ነው» የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ፤ በዘመናዊ የአማርኛ ስነ ጽሑፍ ውስጥ ጸሐፊዎቹ አፋቸውን የፈቱት በሌላ ቋንቋ መሆኑንም ያስታውሳሉ።
«ከእነዚህ ሰዎች ውጭ የአማርኛ ስነ ጽሑፍን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ የስነ ጽሑፍ ፈጣሪዎች መስለዋል፡፡ አገራዊ አንድነትን ፈጥረውበታል፡፡ ለአማርኛ ልሂቃን ደረጃ ቢቀመጥ ቀዳሚቹ እነዚህ ሰዎች ናቸው፡፡ በአማርኛ ለምን ጻፉ?›› ለሚለው ጥያቄ የስነ ጽሑፍ ባለሙያው ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ሲያብራሩ የአማርኛ ቋንቋ፤ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ስሜት ስለፈጠረባቸው ነው፡፡
ደራሲዎቹ ቋንቋውን ብሔራዊ መግባባት ይፈጥሩበት ነበር፡፡ የሚጽፉት አገራዊ ጉዳይን የጋራ የሚያደርግ ነው፡፡ ለታዋቂነት ብለው ቢጽፉ ኖሮ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች መጻፍ የሚችሉ ነበሩ፤ ግን በአማርኛ ቋንቋ መፃፋቸው የአገራቸውን አንድነት ለማስቀድም በማሰባቸው መሆኑንም ነው በአብነት የጠቀሱት።
‹‹ዘር እንቁጠር ከተባለ የአማርኛ ቋንቋ ርቃኑን ይቀራል›› ይላሉ ባለሙያው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ምሁራን ተማሪዎቻቸው የአማርኛ ቋንቋ መጽሐፍ ሲያነቡ ሲያዩ ቅር ይላቸዋል፡፡ ለማጣቀሻነት የሚነግሯቸውም የውጭ መጽሐፍትን ነው፡፡ ይሄ ግን እንደነ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ያለውን አገራዊ ስሜት የመፍጠር አቅም ያቀጭጨዋል፡፡ እነዚህ ልጆች አገራዊ ስሜት የሚፈጥር ነገር ለመጻፍ ይቸገራሉ፡፡ እነ ሎሬት ጸጋዬ ግን በአማርኛ ቋንቋ በመጻፋቸው በብሄራዊ ደረጃ የጋራ ስሜት እንዲፈጠር ማድረጋቸው እንደማይካድ ተናግረዋል፡፡
ሎሬት ጸጋዬ በግዙፍ ነገሮች ላይም ሰርተዋል፡፡ ለምሳሌ በዓባይ ላይ፣በአዋሽ ላይ፣ በዓድዋ ላይ፣ በአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ላይ፣ በአጼ ምኒልክ ላይ፣ የተፈጥሮና ታሪካዊ ነገሮች ላይ ተመስርተው ጽፈዋል፡፡ እነዚህን የሎሬት ጸጋዬ ሥራዎች ልብ ብለን ካየናቸው ብሄራዊ ስሜት የፈጠሩ ናቸው፡፡ ስነ ጽሑፍ ምን ያህል ብሄራዊ ስሜት እንደሚፈጥር በሚገባ አሳይተውናል፡፡ በእነ በዓሉ ግርማ ከአድማስ ባሻገር፤ በእነ ዳኛቸው ወርቁ አደፍርስ፤ በእነ ሰለሞን ደሬሳ ግጥሞች፤ በእነ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር መጽሐፎች ባህልና ታሪክ በተለያየ መንገድ መገለጹንም አስታውሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህሩ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በበኩላቸው፤ ከተለያየ ባህልና አካባቢ የመጡ ሰዎች በአማርኛ ቋንቋ መፃፋቸውን የአማርኛ ስነ ጽሑፍ ብሔራዊ ስሜትን እንዲጋሩ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ የትምና ማንም ይጻፈው በአማርኛ ቋንቋ ከተጻፈ ያ የተገለጸው ነገር የአማርኛ ቋንቋ ስነ ጽሑፍ ነው የሚባለው፡፡ ይህም ለቋንቋው መስፋፋትና አገራዊ መግባባት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው፡፡ ለምሳሌ የእንግሊዘኛ ቋንቋ በአየርላንድና በእንግሊዝ አገሮች አካባቢ ነበር የሚጻፈው፤ በኋላ ቋንቋው እያደገና እየበለጸገ ሲሄድ ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የእንግሊዘኛ ስነ ጽሑፍ አድጓል፡፡ ህንድ ውስጥም ይጻፍ አፍሪካ ውስጥ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፈ ነገር የእንግሊዘኛ ስነ ጽሑፍ ተብሎ ይጠራል፡፡ ቋንቋ እንዲህ እየተስፋፋና እየበለጸገ ሲሄድ የመግለጽ አቅሙ ያድጋል፡፡ ደራሲዎች ለመጻፍ እንደሚመርጡት አስታውሰዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የታደሙት አቶ አስናቀው በላይ በሰጡት አስተያየት የአማርኛ ቋንቋ ኢትዮጵያዊነትን በመግለጽና የጋራ ስሜት በመፍጠር የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ይህን ሚናውን እያጣ ነው፡፡ የባህል ወረራና ቴክኖሎጂ በሚል ሰበብ እየተዳከመ ነው፡፡ ነገር ግን የባህል ወረራም ሆነ ቴክኖሎጂ ቋንቋውን ሊያዳክም አይገባ፡፡ እንዲያውም ቴክኖሎጂ ምቹ ሁኔታ ነው የሚፈጥረው፡፡ ችግሩ ቋንቋውን የቴክኖሎጂ ቋንቋ ለማድረግ አለመሰራቱ ነው፡፡ የጥንት ሰዎች ይጠቀሙባቸው የነበረውን ቋንቋ እንኳን መመራመር የሚያስችል ቴክኖሎጂ እያለ ያለውን እያበላሸ ነው ብሎ ማለፍ ስንፍና እንደሆነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የዘርፉ ምሁራን መምህራን የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተወያዮቹ ጠቁመዋል፡፡ የአማርኛ ቋንቋ መጻሕፍትን ለተማሪዎቻቸው የሚከለክሉና የውጭ መጻሕፍትን ብቻ እንዲያነቡ የሚመክሩ ምሁራን ለአገር እየሰሩት ያለው ነገር ትውልድ ከመቅረጽ ይልቅ ተማሪዎቹን ለአገራቸው ባዕድ ማድረግ በመሆኑ ሊያስቡብት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡  

ዜና ሐተታ
ዋለልኝ አየለ

 

Published in የሀገር ውስጥ

ጠዋትና ማታ ወደጊቢያቸው የሚገባው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ድምጽ ያሳስባቸዋል። የረር በር የሚባለው አካባቢ ነው፤ የሰፈሩ ዋና መንገድ በብዛት ስለሚዘጋጋ በእርሳቸው ደጅ የሚያልፈውን አቋራጭ መንገድ ብዙ ባለመኪናዎች ይጠቀሙበታል። መጠቀማቸው ባልከፋ ነገርግን ፍጥነታቸው ልክ የለውም። በተለይ ደግሞ የአካባቢው ህጻናት በእረፍት ቀናት ሰብሰብ ብለው የሚጫወቱት በዚሁ መንገድ ላይ በመሆኑ ጭንቀታቸው በርትቷል።

ይህ የእርሳቸው ጭንቀት ብቻ አይደለም፤ የአካባቢው ነዋሪም ይህን ጭንቀት ይጋራል። ታድያ መንገድን መዝጋት እንደማይችሉ የተረዱት የአካባቢው ነዋሪዎች ገንዘብ አዋጥተው፣ ተባብረው ሲሚንቶ ገዙና በየቅርብ ርቀቱ ከደጃቸው የሚገኘው መንገድ ላይ አኖሩት፤ ፍጥነት መቀነሻ ሠሩ። ከዚህ በኋላ ስጋትና ጭንቀታቸውም ቀነሰ።
ባለታሪካችን አቶ ጫኔ ይማም ይባላሉ፤ የየረር በር አካባቢ ነዋሪ ናቸው። እንደእርሳቸው ገለጻ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች በመተባበር የሠሩት የፍጥነት መቀነሻ ጥሩ እፎይታን ፈጥሮላቸዋል። አሁንም ሊሠራባቸው የሚገቡ የዛው ሰፈር የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንዳሉ ይናገራሉ። ይህ የፍጥነት መቀነሻ ከዋና ግብሩ በተጓዳኝ ሌላ ተግባር አለው፤ የኮብል ንጣፉ እንዳይሸረሸርና ድንጋዮቹ እንዳይነቃቀሉም ከጎርፍ ይጠብቃል።
በብዙ ወጪና በብዙ ድካም የተሠራውን፤ በክረምት በጭቃ ከመቸገር የታደጋቸውን የኮብል ምንጣፍ መንገድ ለመጠበቅም በማሰብ ነው ይህን የፍጥነነት መቀነሻ እንዲሰራ ያደረጉት። ይህን ይ
የፍጥነት መቀነሻ ባዩ በገመቱት ይሠራሉ እንጂ የባለሙያ እገዛ አልታከለበትም። ሲሚንቶ አሸዋ እና ጠጠርን በመቀላቀሉ ሳይሆን የፍጥነት መቀነሻ ስሌት ነበር መሰራት የነበረበት፤ ከዚህ በላይ መሠራት የለበትም፤ የበለጠ ለችግር የሚያጋልጥና ለአደጋ ጊዜም መኪና የማያስገባ ይሆናል ብሎ ሃሳብ የሰጣቸውና የሚሰጣቸው አልነበረም። በራሳቸው ወጪ፣ በራሳቸው ጉልበት፣ በራሳቸው እውቀትና ተነሳሽነት የተሠራ ነው።
አቶ በለጠ በላይ ከመገናኛ ወደ የረር በር መስመር የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ሚኒባስ ይዘው ይሰራሉ። ይህ መንገድ በብዛት የሚዘጋጋ በመሆኑ ለተማሪዎች ሰርቪስ በሚሰጡ ጊዜ እንዲሁም አመቺ ሆኖ በተገኘ ሰዓት አቋራጭ መንገዶች ይጠቀማሉ። እናም በውስጥ ለውስጥ የተሠሩና የሚሠሩት ፍጥነት መቀነሻዎች የእርሳቸውና የሌሎች አሽከርካሪዎች ተሽከርካሪ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ከመሬት ከፍታቸው ዝቅተኛ የሆነ ተሽከርካሪ ያላቸው ሰዎችም እነዚህን መንገዶች አብዝተው ይጠላሉ፤ ይማረሩባቸዋልም።
የመንገዱ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ በለጠ የሚከተለውን አሉ፤ «ፍጥነት መቀነሻ መኖሩ አይደለም ችግሩ። በውስጥ ለውስጥ መንገድ እንኳ ረጋ ብሎ የማያሽከረክር ብዙ አሽከርካሪ በመኖሩ ይህ አደጋን ለመከላከል ጥሩ አማራጭ ነው። ይሁን እንጂ የፍጥነት መቀነሻዎቹ ከፍታ ልክ ሊኖረውና ሊመጠን ይገባል። ፍጥነትን መገደብ የሚችል ግን በእርጋታ ለሚያሽከረክር ሹፌር ጉዳት የማያስከትል መሆን ይገባዋል።»
የአዲስ አበባ የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ዘመናዊ የፍጥነት መቀነሻዎችን እየሠራ የሚገኝ ተቋም ነው። «ማኅበረሰቡ በውስጥ ለውስጥ መንገድ ላይ የገነባቸው ፍጥነት መቀነሻዎች ከእኛ /ከተቋሙ/ እድሜ በላይ ናቸው።» ያሉን በኤጀንሲው የኦፕሬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሹ ስንታየሁ ናቸው።
እነዚህ ሰዎች በኅብረት የሚሠሯቸው የፍጥነት መቀነሻዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ኤጀንሲው ድርሻ እንዳለው ነው አቶ አሹ የገለጹት። ነገር ግን ኤጀንሲው ከተቋቋመ ሶስት ዓመት እንኳ ያልደፈነ በመሆኑ ሁሉም ጋር በፍጥነት ተደራሽ መሆን አልተቻለም። በዚህ እድሜ ውስጥ መሄድ የቻለው አሁን በሰራው ልክ ብቻ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ይህ ኤጀንሲ 86 በመቶ የሚሆነው የመኪና አደጋ የሚደርሰው በአሽከርካሪዎች ችግር መሆኑን በማመኑ፤ የመንገድ ላይ የመኪና አደጋንና ሞትን ለመከላከል አሽከርካሪዎችን መቆጣጠር በሚቻልበት መንገድ ሁሉ በርካታ ሊባሉ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል። ከትንፋሽ መመርመሪያ ጀምሮ ፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር ድረስ፤ አሁን ደግሞ ዘመናዊ የፍጥነት መቀነሻዎችን በዋና ዋና እና አደጋ ይደርስባቸዋል በሚባሉ የከተማዋ መንገዶች ላይ እየሰራ ይገኛል።
አሁን ባለው አቅም ግን ኤጀንሲው በየአካባቢው እየተንቀሳቀሰ ማስተካከል የሚችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ አልቻለም። «ነገር ግን...» አሉ አቶ አሹ፤ «ነገር ግን ጥያቄ ሲመጣልን ያማከርናቸው አሉ። ይህ ጥያቄ ደግሞ ከግንዛቤ ጋር የሚመጣ ነው። ስለኤጀንሲው ሥራ ግንዛቤ ያለው ወደ እኛ መጥቶ፤ በኤጀንሲውም ሙያዊ እገዛዎች ተደርገዋል። ይሁን እንጅ ብዙዎቹ በራሳቸው መንገድ የፍጥነት መቀነሻ እየሰሩ መሆኑን አውቀናል»
በፍጥነት መቀነሻ በተለይም በውስጥ ለውስጥ በሚገነባው ላይ የሚነሳው አንዱ ቅሬታ በድንገተኛ አደጋ በፍጥነት ለሚሄዱ አሽከርካሪዎች የባሰ አደጋ አድራሽ መሆን መቻሉ ነው። አቶ አሹ እዚህ ላይ አስተያየት አላቸው። እርሳቸው እንዳሉትም ፍጥነት መቀነሻ ጥቅሙ ቢልቅም ጉዳትም ይኖረዋል። በፍጥነት ማሽከርከር ግድ ለሚላቸው አምቡላንሶች ጭምር ምቹ አይሆንም። ይህ ታድያ የምርጫ ጉዳይ ነው፤ በምርጫው ደግሞ እየደረሰ ያለውን እጅግ የበዛና ዘግናኝ የመኪና አደጋ መከላከል ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።
«ወደዚህ አስገዳጅ ሁኔታ የመራን የአሽከርካሪዎች ሥነ-ባህሪ ነው። ፖሊስን እያዩ ብቻ ህግ የሚያከብሩ አሽከርካሪዎች በርካታ ናቸው። በከተማችን እየደረሰ ያለው የሞት አደጋ ዋናው ምክንያት የአሽከርካሪ ችግር ነው» ያሉት አቶ አሹ በተለይም የእግረኞች መገጨት ከተሽከርካሪዎች ፍጥነት ጋር እንደሚገናኝ ተናግረዋል።
ምንም እንኳ የጊዜ እና የአቅም ውስንነት ቢኖርም አሁን በአካባቢው ነዋሪዎች በተነሳሽነት የተሰሩትን የፍጥነት መቀነሻዎች የማስፋፋትና እና የማደስ ሥራ መኖሩ አይቀርም። በውስጥ ለውስጥ ለሚሠሩ የፍጥነት መቀነሻዎች ሲሰሩ ምክር ለሚፈልጉ የየአካባቢው ነዋሪዎች ኤጀንሲው በሩ ክፍት መሆኑንም ጠቁመዋል። ጨምረውም «ይህ ማኅበረሰቡ ራሱ ገንብቶ በባለቤትነት ማስተዳደሩ እንደ አገርም ብሎም እንደመንግስት ትልቅ ስኬት ቢሆንም በጥናትና በምክር ቢሰራ ውጤታማ ይሆናል»በማለት ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

ዜና ሐተታ
ሊድያ ተስፋዬ

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ ባለው ደካማ የግዥ ስርዓት ምክንያት በዩኒቨርስቲዎች የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች እየተጓተቱ መሆናቸውን የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ገለፀ፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የምርምር እና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ኘሬዚዳንት ዶክተር ሲሳይ ሸዋ አማረ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው በዩኒቨርስቲዎች ለሚከናወኑ የምርምር ስራዎች ግብአት ለማሟላት የሚሰራበት የግዥ ስርዓት ኋላ ቀር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የምርምር ስራዎች እየተጓተቱ ይገኛሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለፃ፤ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያ ለምርምር የሚያስፈልጉ ግብአት ግዥ ስርዓት ጥራት ያለው ግብአት ለተመራማሪዎች እንዳይቀርብ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ለምርምር ስራዎች የሚያስፈልጉ ወሳኝ የሆኑ ግብአት የሚመረጡበት መንገድ በዋጋ ርካሽ የሆኑትን ብቻ በመለየት ነው፡፡ ነገር ግን በዋጋ ርካሽ የሆኑ ግብአት በጥራት ጉድለት ምክንያት በአብዛኛው በተመራማሪዎች ዘንድ ተመራጭ አይደሉም፡፡ አስፈላጊው የኬሚካል እና ሌሎች የላቦራቶሪ ግብአት ገበያው ላይ ቢኖርም የግዥ ስርዓቱ በዋጋ ዝቅተኛነት ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ ውድቅ ይደረጋል፡፡ በዚህም ምክንያት ግብአት ለተመራማሪዎች በወቅቱ በጥራት ባለመቅረቡ ምርምሮች እየተጓተቱ ነው፡፡
የምርምር ግብአት ላይ ያለው ኋላ ቀር አሰራር ችግሩ አገራዊ ሆኗል የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፤ የምርምር ስራዎች ሳይጓተቱ ውጤታማ ለማድረግ እንዲረዳ የግዥ አሰራሩን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ በምርምር ስራዎች ላይ አስፈላጊ ግብዓት በማሟላት ተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ መለኪያ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ ነገር ግን በኬሚካል እና በተለያዩ ግብአት እጥረት ምክንያት በሚመጣ የምርምር ስራዎች መጓተት ምክንያት ሳይንቲስቶች ተጠያቂ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የምርምር ስራዎች መጓተት ምክንያት በምርምሮቹ ሊገኝ የሚችለው ጥቅም እንዳይገኝ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ሀገር የተደቀነውን የምርምር ስራዎች መጓተት ችግር ለመቅረፍ በተመራማሪዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የግዥ ስርአት መተግበር ያስፈልጋል፡፡
የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የምርምር ዳይሬክተር አቶ አድማስ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ የግዥ ችግሩ በተለይ የባዮ ቴክኖሎጂ የኬሚካል አቅርቦት ላይ ጐልቶ እንደሚታይ ገልፀዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው የሚሰራ አንድ ተመራማሪ ለባዮቴክኖሎጂ ምርምር የሚያስፈልጉ ኬሚካሎችን ከለየ እና በምርምር ገምጋሚዎች ከተፈቀደለት በኋላ ከግዥ ሠራተኞች ጋር ወደ ገበያ ሲወጣ አሰራሩ የሚፈቅደው ጥራት ያለውን ግብአት ሳይሆን በዋጋ የቀነሰውን ነው፡፡ በዋናነትም ለባዮቴክኖሎጂ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎች በግዥ ስርዓት ምክንያት አስፈላጊው ጥራት ያላቸው ኬሚካሎችን ተመራማሪዎች ባለማግኘታቸው የምርምር ስራዎች እየተጓተቱ በመሆኑ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ ሊያበጅለት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ጌትነት ተስፋማርያም

 

Published in የሀገር ውስጥ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።