Items filtered by date: Monday, 11 June 2018

የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ አባይ ነው። ከኢትዮጵያዊያንም አልፎ ለሌሎች ሃገራትም ጭምር አለኝታ የሆነው ይኸው ወንዝ የሚጋሩትን ሁሉ በታሪክና በባህል ያስተሳስራል። በጎጃምና በወለጋ ህዝቦች መካከል የሚፈሰው አባይ የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች የአንድነትና የትስስር ማሳያ ሆኖ ኖራል። አባይ እነዚህን ህዝቦች በጋራ ከማጠጣት ባለፈ በጋራ ውለው እንዲያድሩና የጋራ እሴት እንዲገነቡም አድርጓል፡፡ ታሪክ እንደሚያወሳው አባይ ሲሞላ ከንግድ ጋር በተያያዘ ወደ ወለጋ የሄደ የጎጃም ሰው አሊያም ጎጃም የደረሰ የወለጋ ነጋዴ፤ ወንዙ እስኪጎድል በሚኖራቸው ቆይታ ከህብረተሰቡ ጋር ያላቸው መስተጋብር ይበልጥ ሊጠናከር ችሏል።
ከዚህ ባለፈም ሁለቱ ህዝቦች በመልከአ ምድር፣ በታሪክ፣ በአኗኗር ዘይቤና በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም የተሳሰሩ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ የህዝቦች አንድነት በተለያዩ ምክንያቶች ክፍተቶችን እያስተናገደ መምጣቱ ታይቷል። በመሆኑም ሁለቱ ብሄሮች በተነሳሽነት የህዝብ ለህዝብ የግንኙነት መድረኮችን በመፍጠር መስተጋብራቸው እንዲጠናከር አቅደው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። በተለይም በህዝቦች መካከል ያለው የጋራ አብሮነት በሳይንሳዊ ጥናቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተደግፎ ከሄደ፤ የህዝቦቹን ግንኙነት በተሻለ መልኩ ለማካሄድ መድረኩ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል።
በዚህም የመጀመሪያው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተካሄዶ ነበር። በመድረኩ ላይም መቀራረብና የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት ለማጠናከር አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ተገቢ እንደሆነ ተመልክቷል። ልዩነቶችን በማጥበብ አንድ ሊያደርጉ የሚችሉ ታሪካዊ ዳራዎች ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ የግድ የሚል ሲሆን፤ በታሪክ ሂደት የተፈጠሩ ልዩነቶችን በአግባቡ ማስቀመጥም ለታሪክ ባለሙያዎች የሚተው ነው። ከሚያለያዩ ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉት ነገሮች ይበልጣሉና በጋራ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መንግሥትም እንደ መንግሥት፣ ምሁሩም እንደ ምሁር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት የሚገባ መሆኑም ተነስቷል።
ሁለተኛው መድረክ ደግሞ በሁለቱም ክልሎች ያሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችና ተማሪዎች በተገኙበት ሰሞኑን በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል። በመድረኩ ላይም ከደብረ ማርቆስና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች በተወጣጡ ምሁራን የተሠራ «በጎጃምና ወለጋ ህዝቦች መካከል ያለው ታሪካዊና ባህላዊ መስተጋብር» የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል። በጥናቱም ላይ ሁለቱን ህዝቦች የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች የቀረቡ ሲሆን፤ በጥናቱ መነሻነትም በተሳታፊዎች መካከል ውይይት ተካሂዷል።
ጥናታዊ ጽሑፍ ካቀረቡት ምሁራን መካከል በወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዕጩ ዶክተር ደሳለኝ ቶሌራ አንዱ ሲሆኑ፤ ጥናቱ የሁለቱን ህዝቦች መስተጋብር በተለይ ከ16ኛው ክፍለዘመን ወዲህ ያለውን ሁኔታ ለመዳሰስ የሞከረ መሆኑን ይገልጻሉ። በዚህም የጎጃምና የወለጋ ህዝቦች የቆየ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ትስስር እንዳላቸው ጥናቱ ማመላከቱን ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም የነበሩ ጥናቶች በጉልህ ሲያሳዩ የነበረው ግን፣ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ግጭት እንደነበር ያብራራሉ፡፡ በመድረኩ ላይ የቀረበው ጥናት ግን ከዚያ ባሻገር በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ መስተጋብሮችን የሚዳስስ እንደሆነም ያስረዳሉ።
እንደ ጥናት አቅራቢው፤ በተለይ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ኦሮሞዎች አባይን አቋርጠው ከነባህላቸው ከጎጃም ህዝቦች ጋር ሲቀላቀሉ ነበር፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የኦሮሞ ጎሳ በጎጃም በመስፈር በወቅቱ የነበሩትን የአስተዳደር ክፍሎች ከመሰረቱት መካከል አንዱ እንደሆነም በጥናቱ ታይቷል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ደግሞ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አባይን አቋርጦ ወለጋ ድረስ በመሄድ የባህል መስፋፋት አካሂዷል። የክርስትና እምነት ወደ ወለጋ ከተስፋፋ በኋላም «በአበልጅ፣ በጉዲፈቻ እና በጡት ማጥባት (ሃርመ ሆዻ)» ስርዓቶች ይበልጥ በመተሳሰር በዘርና በደምም ጭምር የተዋሃዱ መሆኑንም ጥናቱ ያመላክታል።
ጥናት አቅራቢው እንዳስረዱት፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ትኩረቱን አድርጎ የቆየው በፖለቲካ ላይ ነው፡፡ በዚህም ማህበረሰባዊው፣ ኢኮኖሚያዊውና ባህላዊው ሁነት በስፋት ሳይጠና ቀርቷል። ህብረተሰቡ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ በተሻለ የተያያዘ በመሆኑም፤ ለወደፊቱም ትኩረት መደረግ ያለበት ህዝቡን ይበልጥ በሚያቀራርብ ነገር ላይ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም፣ ህዝቦች ከነገሥታቱ ጋር በጦርነቶች ላይ ቢካፈሉም፤ ግጭቱ ነገሥታቱ ግዛታቸውን ለማስፋፋት የሚያደርጉት ሽኩቻ እንጂ በህዝቡ መካከል በተፈጠረ ተቃርኖ እንዳልሆነ ሊታወቅ የሚገባው ሀቅ ነው። የጥናቱም ዓላማ የህዝቡን አንድነትና መስተጋብር የሚያሳዩ ተመሳሳይ ሁነቶችን በማሳወቅ በትውልዱ ዘንድ ይህ አስተሳሰብ እንዲሰርጽ ለማድረግና ይሄን የሚያሳዩ የሰነድ ማስረጃዎችም እንዲዘጋጁ ለማድረግ ነው።  
እንደ ታሪክ ምሁሩ አባባል፣ ሁለቱ ብሄረሰቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፍ የሆኑና የሃገሪቷን ፖለቲካም ሊያራምዱም ሆነ ሊያጠፉ የሚችሉ ናቸው። ነገር ግን ቀደም ሲል ሁለቱ ብሄሮች ጠላት እንደሆኑ ሲነገር እንደነበር በጥናቱ ታይቷል፡፡ ዓለም አንድ በሆነችበት በዚህ ወቅት ደግሞ ይህ አስተሳሰብ የሚያስኬድ አይሆንም፤ ለህዝቡ የሚጠቅመውም መጥፎ ነገሮችን ከማሳየት ይልቅ መልካም መስተጋብራቸውን ማመላከት ነው። ከዚህ ቀደም አንድ የአማራ ምሁር በአንድ ጉዳይ ላይ ከጻፈ የኦሮሞውም ተነስቶ በዚያ ላይ ምላሽ የመስጠት ነገር ይታይ ነበር። ይህ ደግሞ እውነታውን እያፈነ፣ ለህዝቡ መራራቅ ምክንያት ሆኗል። ምክንያቱም ህብረተሰቡ አሁንም በጋራ እየኖረ ቢሆንም በፖለቲካ ላይ ያሉ ሰዎችና የታሪክ ምሁራን እያበላሹ ናቸው። ስለዚህም በጥናቱ ላይ እንደታየው ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ ምሁራን በጋራ እሴቶች ላይ የተመሰረተና መስተጋብራቸውን የሚያጠናክር የጋራ ታሪካቸውን አጉልቶ በማውጣት ህብረተሰቡን ይበልጥ ማቀራረብ ይጠበቅባቸዋል።
በአማራ ክልል የሚገኙ አስር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ፀሐፊ ዶክተር ንጉሴ ምትኩ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው መሆኑን ይጠቁማሉ። አጎራባች ከሆኑት ህዝቦች ባሻገር በሩቅ የሚገኙትም ቢሆኑ በንግድ፣ ሃገርን በመጠበቅ፣ በእምነትና በሌሎች ነገሮች ላይም የተጠናከረ ግንኙነት ያላቸው ህዝቦች ናቸው። አሁንም በባህል፣ በታሪክና በቋንቋ የተጠናከረ መስተጋብር አላቸው፡፡ በጎጃም በርካታ ስፍራዎችና ኩነቶች የኦሮምኛ ስያሜ መያዛቸው፤ ህዝቡም በባህልና ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በዘርም የተገናኘ ለመሆኑ፤ ስማቸው ወደ ኋላ ሲቆጠር ከሁለቱም ብሄር የተቀላቀለ ሆኖ መገኘት ደግሞ ለዚህ አብይ ማሳያ ነው፡፡
ዶክተር ንጉሴ እንደሚናገሩት፤ ባለፉት ጊዜያት ለተወሰኑ ዓመታት በልዩነት ላይ በመሠራቱ የተዛባ ነገር ቢኖርም ግንኙነቱ ግን አሁንም ጠንካራ ነው፡፡ በምሁራኑ ዘንድ ግን ጥቂት መሻከር ይታያል። በመሆኑም የህዝቦችን ትስስር ለማሳየት እንዲያገለግል በሚመክረው በዚህ ዓይነት መድረግ የህዝቦችን ትስስር የሚያሳዩ እንዲህ ዓይነት ጥናቶች መቅረባቸው ለህዝቡ አንድነት መጠናከር ትልቅ ፋይዳ አለው።
ላለፉት 27 ዓመታት ብዝሃነት የተያዘበት መንገድ መልካም ጎን እንዳለው ሁሉ መልካም ያልሆነ ጎንም ያለው እንደነበር የሚናገሩት ዶክተር ንጉሴ፤ «የሃይማኖት፣ የብሄር፣ የቋንቋ፣ ወዘተ ብዝሃነት በደንብ ከያዝነው ጸጋ ቢሆንም፤ አንድ በሚያደርጉን ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ግን መላላት ነበር፤» ይላሉ፡፡ ከዚህ አኳያም «የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ግንኙነት ላለፉት 27 ዓመታት ሲገለጽ የነበረው በዚህ መልክ አልነበረም። ይልቁንም ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ሁለቱ ህዝቦች የተቀራረቡ እንዳልሆኑ፣ ወንድማማች ህዝቦች እንዳልሆኑ ለየብቻ ታሪካቸው ይነገር ነበር። ይህም ሁለቱን ህዝቦች በጠላትነት የመፈራረጅ አዝማሚያ የነበረበት ዓመት ነበር» ይላሉ።
ይህንን ለመቀየርና ሁለቱ ህዝቦች ታሪካዊ ትስስር እንዳላቸው በችግርና በደስታ አብረው የኖሩ እንደሆኑ ማሳየት እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ። ይህንን ለማሳየት ደግሞ ህዝቡን የሚያሳምን ምሁራዊ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ፤ ለህዝቡም በመግለጽ እንዲታወቁ መስረት እንደሚገባ፤ ይህንን ታሪክ ባለማሳየትም ላለፉት ዓመታት እዚህም እዚያም የነበሩ ቁርሾዎች አሁን መጥፋት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥናቶችም ለጋራ አንድነት የሚያግዙ በመሆኑ በስፋት መካሄድ፤ ይህንን ኃላፊነት ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ወስደው ወደኋላ በመመለስ አንድነቱን ማሳየት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡
 በተቋማቱ የሚማሩ ተማሪዎችም ከተለያየ አካባቢ ብዝሃነትን ይዘው የሚመጡ በመሆናቸው፤ መሰል ጥናቶችን ለማቅረብ ዩኒቨርሲቲዎች ተገቢ ቦታዎች መሆናቸውን ዋና ፀሐፊው ይጠቁማሉ። የጋራ እሴቶችን አውጥተው የሚያሳዩ ጥናቶችን በተማሪዎች ማስረጽም ትልቅ ትርጉም ያለው እንደመሆኑም፤ ይሄን ተገንዝቦ መሥራት ከተቻለ ተማሪዎች ተግባብተውና ተቻችለው የመጡበትን አሳክተው እንዲመለሱ፤ እንዲሁም ወደየመጡበት ሲሄዱም አካባቢያቸውን እንዲያስተምሩ የሚያግዛቸው መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይህንን አጠንክረው መያዝና በመድረኮቹም ላይ በብዛት ተማሪዎች መጋበዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ፣ ለመድረኩ መነሻ የሆነው ሁለቱ ክልሎች ባህርዳር ላይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በተደረገው ውይይት የታየው መልካም ነገር መሆኑን ያስታውሳሉ። በዚህም በደብረ ብርሃን የተከናወነው የመጀመሪያው ጉባዔም ሆነ በጅማ የተከናወነው ሁለተኛው ጉባኤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የህዝቡን አንድነት በማጠናከር ታሪካቸው ምን ይመስላል በሚለው ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብ ህዝቡ እንዲነጋገርበት ያስቻለ ነው፡፡ በመድረኮቹ የሚቀርቡት ጥናቶች ይዘትም በምሁራን ተደግፈውና በመረጃዎች ተጠናክረው የተከናወኑ ምርምሮች ስለሆኑ የህዝቦቹ ግንኙነት ምን ይመስላል በሚለውና ወደፊትስ እንዴት ይጠናከር በሚለው ላይ ያተኮረ ነው። የህዝቦች ትስስር ለሃገር ወሳኝ መሆኑን ለማሳየትና ወደፊትም እንዴት መሠራት አለበት የሚለውን ለማስቀመጥ ይረዳል የሚል እሳቤ አላቸው።
«እንደሚታወቀው አሁን በለውጥ ውስጥ ነው ያለነው፤ ለኢትዮጵያ አንድነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ደግሞ ወሳኝ ነው፤» የሚሉት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፤ በተለይ ሁለቱ ህዝቦች በንግድ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ግንኙነት ተቀናጅተውና ተሳስረው የሚኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በጥናቶቹ የታየውም ሁለቱ ህዝቦች በከፍተኛ ሁኔታ የተሳሰሩ፣ ተቻችለውም አብረው እየኖሩ መሆናቸውን ማመላከቱን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ጽሑፎች ይህንን አጉልተው እንደማያሳዩና ልዩነቶች ላይ የሚያተኩሩ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ገለጻ፤ የህዝቦችን አንድነት ዘንግቶ ልዩነትን እያጎሉ መሄድ ራሱን የቻለ ክፍተት ነው፡፡ በመሆኑም ምሁራን የህዝቦችን አንድነትና ትስስር ለህዝቡ በማሳወቅ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል። እስከአሁን ያለው ሂደትም በተቋማት ደረጃም ተቀናጅቶ መሄድ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው። የጋራ ፕሮጀክቶች እንዲኖሩና እርስ በእርስ የመማማር ዕድሎች እንዲፈጠሩ ልዩነቶችን ማቻቻልም ያስፈልጋል። በዚህ መልኩ የሚከናወኑ ጥናቶችንም ወደህዝቡ ማውረድ ይገባል፡፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኮችም ምሁራን በጋራ ውይይት የሚያደርጉበትና አቅጣጫም የሚያስቀምጡበት መሆን ይኖርባቸዋል። ከመድረኩ የሚገኙ ውጤቶችም ለፖሊሲ አውጪዎችና ተጠቃሚዎች ደርሰው ህዝባዊና ተደራሽ መሆን አለባቸው።
ከዚህ ባለፈም ህዝብም ተገናኝቶ በሰፊው ውይይት እንዲያደርግ መድረኮች መመቻቸት አለባቸው። በምሁራኑ አማካኝነት ህዝቡ እርስ በእርሱ የሚገናኝበትን መንገድ በማመቻቸትና ግንኙነቱን በማጠናከር እንዲማማሩ ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን በተጀመረው መልኩም ተማሪዎች በቋንቋ እንዲግባቡ ለማድረግ በተለያዩ  ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት እንደ ባህርዳርና ወሎ ዩኒቨርሲቲዎች የኦሮምኛ ቋንቋ እንዲሰጡ ማድረጉ ትስስሩን ለማጠናከር የሚያግዝ ዕርምጃ ነው፡፡ ይህን መሰል ዕርምጃም በቋንቋ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል።
የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ህዝቦች ድንበር ከመጋራታቸው ባለፈ የማህበራዊና ባህላዊ ቁርኝት እንዳላቸውም ታሪክ እንደሚያስረዳ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሁለት ብሄሮች ብቻም ሳይሆን የአጠቃላይ ህዝቡ መግባባት ውጤት መሆኑን፤ ህዝቡ አንድ ላይ ሲኖር እንደነበርና በሂደት ግን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ከመጠናከር ይልቅ መልኩን የቀየረበትና የተበላሸበትም ሂደት እንደነበር ያስረዳሉ። «ማናችንም በቋንቋ፣ በብሄርና በመሳሰለው ከመለየታችን በፊት ሰው መሆናችን አንድ ያደርገናል፤ በዚህ ደግሞ መከባበርና አብሮነት ተሰጥቶናል፤ ምክንያቱም ሰው ያለ ሰው መኖርም አይችልም፤» ይላሉ።
«የነበረውን ሰላምና መከባበር በማውጣት ጥላቻ የተዘራበት ጊዜም ነበረ፤ ይህ ደግሞ ሁለቱን ህዝቦች ብቻም ሳይሆን ሃገሪቷን ሲጎዳት እንደነበር ይታወቃል። ስለዚህም በዚህ ወቅት ምሁራን ግንኙነቱን ለማጠናከር መሥራታቸው ለሁለቱ ህዝቦች ብቻም ሳይሆን ለሃገር አንድነት የሚጠቅም ነው» ሲሉም ይገልጻሉ። መልካም የሆኑ ነገሮች ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ አዲሱ ትውልድ ከዚያ ተምሮ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባ፤ የህዝብ ለህዝብ መልካም ግንኙነት የአንድ ሃገር ጥንካሬ መገለጫ ስለሆነም ግንኙነቱ ጠንካራ ካልሆነ ሰላም ሊኖር ስለማይችል በዚህ መልኩ የሚካሄደው መድረክ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይገልጻሉ፡፡   
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ባሻገር የኦሮሚያ ክልል ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከርና ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ በጋራ እሴቶች ላይ እየሠራ እንደሚገኝ ዶክተር ነገሬ ይገልጻሉ። የነበሩ መልካም ግንኙነቶች በታሪክ ከተፈጠሩ ቁርሾዎች የበለጠ ማደግ ያለባቸው በመሆኑ፤ በዚህ ላይ መሥራት እንደሚገባ በማመን በተነሳሽነት ወደ ባህርዳርና ሌሎች ክልሎች በመሄድ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ላይም እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ መንግሥት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራኖች ብቻ ሳይሆን መሪዎችም ይህንን አጠናክሮ የማስቀጠል እቅድ እንዳለና በተግባርም አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። «ያለ ህዝብ መንግሥት የለም፤ በፊትም መልካም የሆነውን ማህበራዊ መሰረት ቅድሚያ ባለመስጠት ነው አላስፈላጊ ቁርሾዎች የተፈጠሩት። መሠረታችንን ህዝብ ብናደርግ በፊት የነበረውን መልካም ግንኙነት ከላይ ወደታች የሚፈሱ በገዢዎች መካከል ያሉ ጥሩ ያልሆኑ ግንኙነቶች እንዲበረዙ ነው ያደረገው» ሲሉም የነበረውን የተሳሳተ አቅጣጫ ጉዞ አስረድተዋል።
አሁን ግን ሃገሪቷ ተጠናክራ እንድትቀጥል ማህበራዊ መሰረቶች መጠናከር አለባቸው፤ ሁሌም ከላይ ወደታች ብቻ ሳይሆን ከህዝብም ወደ ላይ መምጣት አለበት። በአጭር ጊዜ ውስጥ እየታየ ያለው የፖለቲካ ዲስኩር ብቻ ሳይሆን ህዝብን በማወያየትና በማዳመጥ፤ የተረጋጋ የፖለቲካ አመራር ለማምጣት ተጠናክሮ እየተሠራ ነው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ብቻም ሳይሆን ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በጋራ እየሠራን እንገኛለንም ብለዋል። ሁለቱ ክልሎች ብቻም ሳይሆን የፌዴራል መንግሥቱ እና ሌሎችም ክልሎች በዚህ ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲጠናከር የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል።     

ብርሃን ፈይሳ

Published in ፖለቲካ

አገራችን በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ከሚነገርላት ሰፊ ሀብቷ ውስጥ የቁም እንስሳት አንዱ ነው፡፡ ከአፍሪካ በቀዳሚነት፣ ከዓለምም ከመጀመርያዎቹ አስር አገራት ተርታ ያሰለፋትን የእንስሳት ሀብቷን በአግባቡ ከተጠቀመች በኢኮኖሚ ዕድገቱ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ይታመናል፡፡ በተለይ የእንስሳት ውጤት የሆነው የቆዳ ምርት በአግባቡ ከተሰራበት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘትና ሰፊ የሥራ ዕድልን በመፍጠር ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ በትኩረት ካልተሰራበትና ተገቢው እርምት ካልተደረገበት ካለው ፋይዳ አንፃርነት የሚታይ ጉልህ አከባቢያዊ ተጽዕኖ እንዳለውም እሙን ነው፡፡ በዚህ ልክ የሚገለፀው የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ ረዥም ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ባለድርሻዎችም በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትና ውጤቶቻቸውን፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎቻቸውን በተመለከተ የሚናገሩት አላቸው፡፡
አቶ እንድሪስ ኢብራሂም፣ በ1918 ዓ.ም ተቋቁሞ ለረዥም ጊዜ በመንግሥት ስር ሲተዳደር የቆየውና በኋላም ወደ ግል ሲዞር በመግዛት የግላቸው ያደረጉት የአዲስ አበባ ቆዳ ፋብሪካ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ፋብሪካውን ከገዙት በኋላ ብዙ ማሻሻያዎችና ለውጦች አድርገውበታል፡፡ በበሬ ቆዳ ምርት የሚታወቀው ይህ ፋብሪካ፣ አሁን ላይ የበግና የፍየል ሌጦንም እየሰራ ሲሆን፤ ያለቀለት ቆዳን ለጫማ፣ ለጃኬት፣ ለቦርሳ፣ ለሶፋና መሰል ምርቶች ግብዓትነት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በቀጣይም በሰፊው ወደገበያው የመግባት ዕቅድ ይዘዋል፡፡
በዘርፉ በሚከናወኑ ተግባራት ውጤት እየታየ ቢሆንም፤ በሚፈለገው ልክ እንዳይጓዝ የሚያደርጉ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን አቶ እንድሪስ ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዱ የግብዓት ችግር ሲሆን፤ ይህም ከአገር ውስጥ የሚቀርበው ጥሬ እቃን እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኬሚካል አቅርቦትን የሚመለከት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቆዳና ሌጦ በኩል ከአቅርቦቱ ይልቅ የጥራት ችግር እጅጉን ፈታኝ መሆኑን በመጠቆምም፤ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱንና በተለይ በወጪ ንግዱ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ማሳደሩን ይገልፃሉ፡፡
የግብዓት ጥራት ችግር በምርቶች ላይ ከሚያሳድረው የዋጋ ልዩነት ባለፈ፣ ከየፋብሪካው ሳይወጡ ውድቅ የሚደረጉ ምርቶች በመኖራቸው በፋብሪካዎቹ አቅም ላይም ሆነ በአገር ገቢ ላይ ችግሩን የጎላ እንዳደረገው ያብራራሉ፡፡ ከኬሚካል አቅርቦት ጋር በተያያዘም እስከ 95 በመቶ የሚሆኑት ኬሚካሎች ከውጭ የሚገቡ እንደመሆናቸው ይሄን ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይሄም በዘርፉ ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ እንድሪስ አባባል፤ የቆዳ ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ ሥራው ከአርብቶ አድሩና አርሶ አደሩ ቀዬ የሚጀምር እንደመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ ተቀናጅቶ ሊሰራ ይገባዋል፡፡ ጥራት ያለው ቆዳን ማግኘት የሚቻለው ከብቱ በህይወት ካለበት ጊዜ ጀምሮ በሚሰራ ሥራ እንደመሆኑም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻዎች ከምንጩ ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ በሚደረግበት አግባብ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ አግባብ በመሥራት ብቻ በዘርፉ የሚታየውን የውጭ ምንዛሬ ችግር ማቃለል ይቻላል፡፡ ካልሆነ ግን በትንሽ ብር በሚሰራ ሥራ የቆዳ ጥራትን ባለመጠበቅ በሚከሰት ችግር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ በማጣት የዘርፉን የምንዛሬ ጥያቄ እንኳን መመለስ የማይቻልበት ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም የጥራት ችግርን በማቃለል ብቻ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን በማግኘት ዘርፉንም፣ አገርንም መደጎም ይቻላል፡፡
አቶ እንድሪስ እንደሚያብራሩት፤ የቆዳው ኢንዱስትሪ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ የጎላ ነው፡፡ በአንፃሩ የቆዳ ምርት የአካባቢ በካይነት የሚጀምረው ከእርድ ሂደቱ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የቆዳ ሥራ ከአድካሚነቱም በላይ ለንጽህና በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ጠቃሚነቱ ብቻ እየታሰበ አካባቢን መበከል ስለማይኖርበት ለአካባቢ ተስማሚ በሆነ መልኩ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ቆዳ ፋብሪካ የመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያ አስገንብቶ ሥራ ላይ ያዋለ ሲሆን፤ 30 ሚሊዬን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ በማድረግም ሁለተኛ ደረጃ ማጣሪያ ግንባታም በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ሥራው አካባቢን መሰረት ያደረገ መሆን ስላለበት አብዛናው የቆዳ ፋብሪካዎችም የመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያ ገንብተው ሥራ ላይ አውለዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ማጣሪም እየሰሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በወንዞች ላይ የሚደርስ ብክለትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የማጣሪያ ግንባታ ሥራው ዕውን መሆን የአካባቢ ጥበቃ ሥራውን የማገዝ ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም ገበያን ሰብሮ ለመግባት እንደ ግዴታም የሚታይ ነው፡፡
አቶ እንድሪስ፣ የቆዳ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳና ሰፊ የሰው ኃይል ስለመፈለጉ፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያም ጉልህ ሚና ያለው ስለመሆኑ፣ አገሪቱም ከሰፊው የእንስሳት ሀብቷም ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያደርጋት ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፉ ባለሀብቱን ተጠቃሚ ሳያደርግ በመቆየቱ ከፍተኛ ካፒታልና ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ይገልፃሉ፡፡ የእርሳቸው ፋብሪካ ሁለተኛ ደረጃ ማጣሪያ እየገነባ ቢሆንም፣ ከመሬት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር እያጋጠመው መሆኑን በማሳያነት በማንሳትም፤ ባለሀብቱ አገራዊ ግዴታውን ለመወጣት በዘርፉ ሲሰማራ ከመንግሥት ሰፊ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡ በመሆኑም በዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የዘርፉ ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ተናጥላዊም ሆነ የጋራ ችግሮች ለይቶ በጋራ መሥራትና ለችግሮቻቸው መፍትሄ ማበጀት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቆዳ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ታጠቅ ይርጋ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የቆዳ ሥራ ዘርፉ በኢትዮጵያ ከመቶ ዓመት የዘለለ ታሪክ ያለው ቢሆንም ዛሬም ድረስ በሚፈለገው ልክ ውጤት እየታየበት አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዘርፉ ከፍተኛ ችግር ያለበትና የወጪ ንግዱም ከዓመት ዓመት እየቀነሰ የመጣ ነው፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዱና ትልቁ ችግር የቆዳ ፍሳሽ ማጣሪያ ሲሆን፤ ፋክሪካዎች አካባቢን እየበከሉ መቀጠል እንደሌለባቸው በማመን ችግሩን ለማቃለል ሀብታቸውን አፍስሰው የማጣሪያ ግንባታ እያከናወኑ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ችግር የቆዳ ግብዓት ጥራት ሲሆን፤ ለዚህ ችግር መቃለልም ከግብርናው ዘርፍ ተቋማት ጋር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
አቶ ታጠቅ እንደሚናገሩት፤ ከውጭ ማሽነሪዎች በማስገባት ጭምር የፍሳሽ ማጣራት ሥራው በሰፊው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከጥሬ ቆዳ ጥራት ጋር በተያያዘም ያለው ችግር ዘርፉ የሚፈለገውን ያክል እንዳይጓዝና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆን እያደረጋት በመሆኑ ችግሩን ለማቃለል ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም የቆዳን ጥራት ለማምጣት እንስሳቱ ከመጀመሪያው አንስቶ ተገቢው እንክብካቤ እንዲደረግላቸው የሚያስችሉ አሰራሮች ዙሪያ ከመንግሥት ጋር ይሰራል፡፡ ለውጤታማነቱም ባለሀብቱ ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ መንግሥት በሚገባ መደገፍና ቀጣይነት ባለው መልኩ መሥራት ይኖርበታል፡፡
የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሰ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ በቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰራው ሥራ ውጤት እያሳየ ነው፡፡ በዚህም ቆዳን በጥሬው ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምሮ የተሻለ ዋጋ የሚገኝበትን ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ሳይቀር የሚመረቱ የተለያዩ የቆዳ ውጤቶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እየቀረቡ፤ ውጤቱም ከዓመት ዓመት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ለውጡም በፖሊሲዎችና በቴክኖሎጂ ድጋፎች ታግዞ ለረዥም ጊዜ በተሰራ ሥራ ውጤት ነው፡፡
በዚህ መልኩ የሚታይ ውጤት ቢኖርም ዘርፉ አሁንም ሰፊ ችግር ያለበት መሆኑን ያልሸሸጉት አቶ ወንዱ፤ ከግብዓት፣ ከውጭ ምንዛሬና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ያሉ ችግሮች ተለይተው እየተሰራባቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እንደ እንደሳቸው ገለፃ፤ ከጥሬ ዕቃ ግብዓት ጋር የሚያያዘው አንድ የግብዓት ችግር ሲሆን፤ በዚህ ረገድ የሚስተዋለው የቆዳ ጥራት ችግር ከእንስሳቱ የአረባብና እንክብካቤ ባህል ጋር የሚከሰት እንደመሆኑ ለችግሩ መቃለል የግብርናው መስሪያ ቤት እየሰራበት ነው፡፡ የሚመጡ ቆዳዎችንም አሻሽሎ ጥራታቸውን ማሳደግ በሚቻልበት ዙሪያ ከኢንዱስትሪዎች ጋር እየተሰራ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትን ይጠይቃል፡፡
ከኬሚካል አቅርቦት ጋር በተያያዘም የቆዳ ፍብሪካዎች ችግር ማለት የአገር ችግር ማለት እንደመሆኑ፤ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ኬሚካል አስገብተው ካልሰሩ በስተቀር ቆዳን ማልፋት አይችሉም፤ በተመሳሳይ የጫማና ሌላም ምርት ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን በሚፈለገው መልኩ ለማውጣት የተለያዩ ግብዓቶችን ይፈልጋሉ፤ ለዚህ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ የግድ ይላል፡፡ ሆኖም ኢንዱስትሪዎቹ የውጭ ምንዛሬ ችግር ስላለባቸው ቶሎ ማግኘት አይችሉም፡፡ ይሄን ምንዛሬ ቆይቶ ማግኘትና ቶሎ ማግኘት በራሱ በወጪ ገበያው ላይ የሚያሳድርባቸው ተጽዕኖ አለ፡፡ ይሄን ችግር በመገንዘብም መፍትሄ ለማምጣት በመንግሥት በኩል በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው፡፡
የኢንዱስትሪዎቹን የውጭ ምንዛሬ ችግር ለመፍታት የውጭ ምንዛሬ እንዲጨምር ከሚሰራው ሥራ በተጓዳኝ፤ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዙሪያ ያለውን ችግር ለማቃለልም ሰብ ስቴሽኖች እንዲገነቡ በማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ ከቴክኖሎጂ አቅም ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለልም ከሌሎች በማስገባት ለቆዳ ፋብሪካዎች የማስተላለፍና የማላመድ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
እንደ አቶ ወንዱ ማብራሪያ፤ የአካባቢ ብክለት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ ሳይሆን፤ በሁሉም ዓለም ላይ እስካሁንም ድረስ ያለ ችግር ነው፡፡ ችግሩም በአንድ ጊዜ መፍትሔ የሚገኝለት ባይሆንም፤ ለችግሩ መፍትሄ የሚሆን ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የበካይ ኬሚካሎችና ቆሻሻዎችን ማጣሪያ ግንባታ አንዱ ሲሆን፤ የቆዳ ፋብሪካዎቹ የአንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ የማጣሪያ ግንባታ ሥራ እያከናወኑ ናቸው፡፡ መንግሥትም እየደገፈ ሲሆን፤ ኬሚካሎች ቆዳው ውስጥ እንዲቀሩ የሚያደርጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር በመተግበር ቆሻሻን ከምንጩ የመቀነስ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ በመሆኑም በባለሀብቱ በኩል ለዚህ ተግባር ውጤታማነት በቁርጠኝነት መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥትም በፖሊሲም ሆነ በፋይናንስ የመደገፍ አሰራሮችን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡  

Published in ኢኮኖሚ

ቬንዝዌላ በቅርቡ የፕሬዚዳንት ምርጫ ብታካሂድም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውሶች እስካሁን አለመፈታታቸውን የአልጀዚራ ዘገባ ያሳያል፡፡ የዋጋ ግሽበት ከቁጥጥር ውጪ መሆን፣ የነዳጅ ምርት መቀነስ፣ የወጪ ንግድ መቀነስ፣ በምግብና በመድኃኒት እጥረት ብዙዎች መሰደዳቸው እንዲሁም የአገሪቱ መንግሥት መሪ ኒኮላስ ማዱሮ ሥልጣን አለመልቀቃቸው ችግሩን አባብሶታል፡፡
አገሪቱ በነዳጅ ሀብት የበለፀገች ሆና እንዴት እንዲህ ልትሆን ቻለች? ለሚለው ጥያቄ አገሪቱ እየተከተለች ያለው የሶሻሊዝም ሥርዓት ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ በርካቶች እንደሚያነሱ ዘገባው ያትታል፡፡ የአገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ችግር የሆነው  የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆልና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው፡፡  በቅርቡ በአገሪቱ ለተከሰተው የኢኮኖሚ ውደቀት እአአ 2014 ላይ የነበረው የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ቢሆንም በደካማ ፖሊሲ ምክንያት ተመሳሳይ ችግር ከአምስት ዓመት በፊት አጋጥሞ እንደነበር ዘገባው ይጠቅሳል፡፡
በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ ያለው እጥረት እንዲባባስ የውጭ ምንዛሬ አለመኖር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ የችግሩ መንስኤም በአገር ውስጥ ያለውን ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ባለመደረጉ ነው፡፡ በመሠረታዊነት በአገሪቱ ላይ የተከሰተውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት የአገር ውስጥ አምራቾችን ለመጠበቅና የመንግሥት ሠራተኛውን ለማበረታታት የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሁጊዮ ቻቬዝ የውጭ ምንዛሬ ላይ ቁጥጥር ዘርግተው እንደነበር ዘገባው ያስታውሳል፡፡ ቀደም ሲል በአገሪቱ ለሚገኙ አቅም የሌላቸው ዜጎች በምግብና በጋዝ ላይ ድጎማ በማድረግ ተጠቃሚ እንደነበሩም ዘገባው ያሳያል፡፡
ነገር ግን የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ቦሊቨር ዋጋ ማጣቱ፣ የአገር ውስጥ ምርቶች ከሌሎች አገር ጋር ያለው ተወዳዳሪነት መቀነሱና የውጭ አገራት ምርቶች ዋጋ መቀነስ የአገር ውስጥ ምርቶች ተፈላጊነት እንዲያጡ ምክንያት መሆኑን ዘገባው ይጠቁማል፡፡ የሚደረገው ድጎማ መነሳት በአገሪቱ የሚታየውን የዋጋ ንረትና የመገበያያ ገንዘብ መውደቅ አስከትሏል፡፡
አብዛኛው ባለሀብትና ግለሰብ ለቁጥጥርና በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚታየው ችግር መፍትሄ ለማምጣት ከፍተኛ ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ ናቸው፡፡ የጥቁር ገበያው እንቅስቃሴ  ዋነኛ የመሠረታዊ ሸቀጦች መግዣ በጀት ከመሆን ባለፈ የምርት ዋጋና አገሪቱ ያስቀመጠችው የመግዣ ዋጋን አጥብቧል፡፡ በዚህም የአገር ውስጥ ምርቶችን ጎድቷል፡፡ የአገር ውስጥ ምርቶች ከገበያ ውጪ መሆን በአገሪቱ ሙስና እንዲንሰራፋ አድርጓል፡፡ በዚህም የአገሪቱ ኢኮኖሚም አሽቆልቁሏል፡፡
በመደበኛው የገንዘብ ምንዛሬና በጥቁር ገበያው መካከል ከፍተኛ የምንዛሬ ልዩነት አለ፡፡ ይህ ደግሞ ለመንግሥታዊ ቀረጥ ክፍያዎች ጥቁር ገበያው እንዲበረታታ አድርጓል፡፡ በአገሪቱም ሆነ በጎረቤት አገራት ነዳጅና በምግብ ምርት ዋጋ ከፍተኛ ልዩነት በመኖሩ ምርቶቹን በማገት በከፍተኛ ዋጋ እየሸጡ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ ዋጋዎች በመኖራቸው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመረቱ ምርቶች እንዳይኖሩ ከማድረጉ በተጨማሪ አገሪቱ በተወሰኑ ምርቶች ብቻ የየዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡
የቀድሞ የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ጆርጅ ጎርዳኒ በማዱሮ መንግሥት ላይ በተቀሰቀሰው ሁከት ምክንያት እንዲለቁ ያደረጋቸው ከእአአ 2003 እስከ 2012 ድረስ ሦስት መቶ ቢሊዮን ዶላር በመጥፋቱ ምክንያት ነው፡፡  በአጭር ጊዜ ውስጥ ቻቬዝ ችግሩን ለመፍታት ምንም ዓይነት ጥረት ያላደረጉ ሲሆን የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ ከመውደቁ በተጨማሪ የጥቁር ገበያው ሁኔታ በእጥፍ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ነገር ግን በረጅም ጊዜ እቅድ የማህበራዊ ኢኮኖሚው ሁኔታን ለማስተካከልና ለውጥ እንዲመጣበት ለማድረግና አምራች ድርጅቶች በተለይ ህብረት ሥራ ማህበራትንና የግል ፋብሪካዎች የአገር ውስጥ ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግና የነቃ ዜጋ መፍጠር ላይ ለማተኮር ነው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት የኢንቨስትመንት ሥራዎች የሚመሩት በአገር በቀል ድርጅቶች ነው፡፡ የህብረት ሥራ ማህበራትም እየቀነሱ ይገኛል፡፡ በተግባር ሲታይ ህብረት ሥራ ማህበራቱ በቂ ካለመሆናቸው በላይ በአሁኑ ወቅት ያሉት ሙሰኞች በመሆናቸው የግል ባለሀብቱ ቁጥር እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ቻቬዝ የመረጡትና የለውጣቸው አካል ያደረጉት 21ኛው ክፍለ ዘመን ሶሻሊዝምን ነው፡፡ ነገር ግን የቬንዝዌላ ኢኮኖሚ የሚፈልገው ገበያ ተኮር የሆነና የግል ባለሀብቱ በብዛት የሚሳተፍበት መሆን እንዳለበት በሥልጣን ቆይታው አረጋግጧል፡፡ የማህበራዊና ኢኮኖሚው እንዲሁም የግል ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ የግል ዘርፉ አገሪቱን በበላይነት እንዲቆጣጠር ይፈለጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ኩባ የምትከተለውን ፖሊሲ ማየት ለቬንዙዌላ ጥቅም የለውም፡፡
ሁለተኛው የአገሪቱ ችግር የሆነው በነዳጅ ሽያጭ የበለፀገች እንደመሆኗና የሶሻሊዝም ርዕዮት ዓለም መገለጫዋ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከሶሻሊዝም መውጣት ካልቻለች አገሪቱ ለከፍተኛ ውድቀት ትዳረጋለች፡፡ የነዳጅ ሽያጭ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው ሲሆን ማዱሮም ይህን በማወቅ ትልቅ ትኩረት ሰጥተውታል፡፡ በአልጀዚራ ዜና ማሰራጫ በቬንዝዌላ ጉዳይ በታየው ጥናታዊ ፊልም ላይ እንደታየው ለቬንዝዌላና ለሕዝቦቿ የነዳጅ ሽያጭ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የፖለቲካ ሁኔታውም በነዳጅ እንደሚወሰን ነው፡፡
እንደ ፖለቲካ ተንታኙ ሙግዌል ቲንከር ገለፃ፤ ቻቬዝ ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ሁለት ቬንዝዌላ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያው ቬንዝዌላ ከነዳጅ ሀብቱ የሚጠቀመው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በነዳጅ ሽያጭ ጥላ ስር የነበረ ነው፡፡   የቬንዝዌላ ተቃዋሚዎች ባቀረቡት ጥያቄ ቻቬዝ የነዳጅ ሽያጩ እኩል ለአገሪቱ ጥቅም ላይ እንደሚውል ቃል ገብተው ነበር፡፡ ነገር ግን ቻቬዝ የአገሪቱን ታሪክ እንደ አዲስ ከሀብታም ሰዎች፣ ከሌላ አገር ዜጎች፣ ከተማሩ እንዲሁም ከምዕራባውያን ውጪ መፃፍ ፈለጉ፡፡
የቬንዝዌላ የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ቦሊቫር በማዱሮ አስተዳደር ወቅት ነበር ዋጋ እያጣ የመጣው፡፡ በዚህም በአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ መነሳት ጀመረ፡፡ በተመሳሳይም በአገሪቱ የሚመረቱ ምርቶች ተፈላጊነት እንዲቀንስና የጥቁር ገበያው የልውውጥ መጠን እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ድርጅቶችና ሀብታም ግለሰቦች በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያደረጉ ሲሆን የሚያወጡት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ቬንዝዌላን ለአስርት ዓመታት ቀውስ ውስጥ ከቷት ነበር፡፡  
በነዳጅ ላይ የተጣበቀው የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጠቀመው የተወሰኑ ቡድኖችን ብቻ ነው፡፡ የአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም የተመሰረተው የነዳጅ ሀብት ላይ እንደመሆኑ መንግሥት የነዳጅ ሀብቱን በመጠቀም የኅብረተሰቡን ሕይወት መለወጥ አለበት፡፡ በአገሪቱ ማህበራዊ ትስስሮች የላሉ ሲሆን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ መስራት የማይታሰብ ጉዳይ ነው፡፡
ፖለቲከኞች ለአገሪቱ መከፋፈል ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ቻቬዝ በአገሪቱ ለተፈጠረው ችግር መንስኤ  እራሱን፣ ወታደራዊ ኃይሉንና ሶሻሊዝምን አስቀምጠው ነበር፡፡ ቻቬዝ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን ኢንስቲትዩሽንና የገንዘብ ምንጮችን ወደ ራሱ በማምጣት እንደ አዲስ እንዲደራጁ ሲያደርግ ምንም ዓይነት ተቃውሞ አልገጠመውም፡፡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ደግሞ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት መስራት ሲጠበቅባቸው በተቃራኒው በአገሪቱ የፋይናንስና እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
እንደ አልጀዚራ ዘገባ በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው ሶሻሊዝም ሥልጣን አሳታፊ በሆነ ዴሞክራሲና በሶሻል ኢኮኖሚ በመታገዝ አገሪቱን ከነዳጅ ጥገኝነት ማውጣት ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ የተቀመጡት ነገሮች አገሪቱን ወደ ባሰ ችግር ውስጥ እንድትገባ አድርገዋታል፡፡ የሥልጣን ሽግግሩን ባህላዊ ከሆነ አሠራር በማውጣት ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ተጠያቂነት የሰፈነበት በማድረግ አገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስና መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ካፒታሊዝም በራሱ ለሙስና በር የሚከፍት አይደለም፡፡ ቻቬዝ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ሶሻሊዝም ለአገሪቱ  ውድቀት መንስኤ አልነበረም፡፡ በማዱሮ ዘመን ግን ሶሻሊዝም የአስተዳደሩ ውድቀት ማሳያ ሆኗል።

መርድ ክፍሉ

Published in ዓለም አቀፍ

ኤርትራ የራሷን ሉኣላዊ አገርና መንግስት ከመሰረተች 27 አመታት ብታስቆጥርም ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት ከተቋረጠ ደግሞ 20 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በነዚህ አመታት ጦርነት፣ የህዝቦች መለያየት፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት፣ የድንበር አካባቢ ውጥረት ወዘተ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ እነዚህ  ችግሮች እንዲወገዱ ግን በኢትዮጵያ በኩል ተደጋጋሚ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ለቀረበው የሰላም ጥሪ በኤርትራ በኩል ተገቢው ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ግን የሰላም ጥሪውን አላቆመም፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሃላ ቢፈፀሙ እለት የኤርትራን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አብይ አጀንዳ አድርገው ማንሳታቸው ይታወቃል፡፡ ይህንን ተከትሎም ይህ የሰላም ጥሪ በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል፡፡
የሁለቱን አገራት የኋላ ታሪክ ስንመለከት ጥብቅ ቁርኝት እናገኛለን፡፡ ሁለቱ አገራት በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት በላቀ ደረጃ የጋራ እሴቶች የገነቡ ናቸው፡፡ በተለይ በህዝቡ መካከል የነበረው መስተጋብር ሁለቱን አገራት በጥብቅ ያቆራኘ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቁርኝቱ በአንድ መንግስት ስር ለዘመናት መኖራቸው ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ህዝብ ዕርስ በርሱ መዋለዱና ተመሳሳይ ባህል፣ቋንቋ፣ የአኗኗር ዘይቤ እና ማህበራዊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች በመኖራቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ እስካሁንም ድረስ ስለኤርትራዊ ሲነሳ እንደ አንድ የኢትዮጵያ አካል የሚሰማቸው በርካታ ዜጎች አሉ፡፡ ይህ የተፈጠረው ደግሞ የጋራ እሴት የወለደው ዝምድና ነው፡፡
ባለፉት 20 አመታት ግን ይህ የሁለቱ አገራት ነባራዊ ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት መግባታቸው ብቻ ሳይሆን ከግጭቱ በኋላም ቢሆን ችግሮቻቸውን ፈትተው ወደ መልካም ጉርብትና ለመምጣትና ለዘመናት የቆየውን የሁለቱን አገራት ህዝቦች ጥብቅ ቁርኝት ለመመለስ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ በዚህ የተነሳም ሁለቱ መንግስታት እንደ ጠላት የሚተያዩና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እየተመለከተ አጠገቡ እንደተቀመጠ ፈንጂ የሚያይበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ለሚገኙ ህዝቦችም ሆነ በአካባቢው ለተሰማሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የዘወትር የቤት ስራ ሆኖ እቅልፍ የማያስተኛ የስጋት ቀጠና እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ከዚህም ባሻገር በሁለቱ አገራት ግጭት ምክንያት ያለሃጢያታቸው ከሁለቱ አገራት ዜጎች  በመወለዳቸው ብቻ መብታቸው ተነፍጎ አንዱ የሌላውን ወገንና ዘመድ እንዲሁም ቤተሰቡን ለማየት ያልቻለበት አሳዛኝ ሁኔታዎችም የዚህ የሁለቱ አገራት ሰላም አልባ መሆኑን ውጤቶች ሆነው  ቆይተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ከማውቃቸው ታሪኮች አንዱን ላውጋችሁ፡፡
አቶ ገብረየሱስ በየነ የተወለዱት በትግራይ ቢሆንም አብዛኛውን እድሜያቸውን የኖሩት በአስመራ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም የተከታተሉት በዚህችው ባደጉባት ከተማ ነበር፡፡ ከኤርትራዊት ባለቤታቸውም ጋር እስከሚለያዩ ድረስ በዚህችው ከተማ በፍቅርና በሰላም ኖረዋል፡፡ ሶስት ልጆቻቸውንም የወለዱት በዚህችው ከተማ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን  የመለያየት ወቅት መጥቶ እሳቸውን ወደ አዲስ አበባ ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ደግሞ አስመራ ለያይቶ እነሆ ለአስራ ሰባት አመታት የናፍቆትና የብቸኝነት ኑሮ እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል፡፡ አቶ ገብረየሱስ “ሁል ጊዜ ልጆቼ ይናፍቁኛል፡፡ ልጅን የሚያክል ነገር በባዕድ አገር ትቶ ነገ እንገናኛለን በማይባልበት ሁኔታ መኖር ከሞት አይተናነስም” ይላሉ፡፡ “አሁን የተጀመረው ሁለቱን አገራት የማገናኘት አጀንዳ ምነው ፈጥኖ እውን በሆነና ከልጆቼ ጋር ተገናኝቼ በሞትኩ” በሚልም ያላቸውን የልብ መሻት በጉጉት ይናገራሉ፡፡
ሌላዋ ወጣት ብርክቲ አስፍሃ ደግሞ አባቷ ኤርትራዊ በመሆናቸውና በግጭቱ የተነሳ ወደ ኤርትራ በመሄዳቸው የአባቷን ፍቅር ሳታገኝ ላለፉት 20 አመታት መኖሯን በሃዘን ታስታውሳለች፡፡ ብርክቲ “ባለፉት 20 አመታት እኮ በርካታ ቤተሰቦች ተበታትነዋል፤ እስኪ አስቡት በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሰዎች የሚጋቡት ዘርን ቆጥረው አልነበረም፡፡ በዚህ የተነሳ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረች ሰዓት በርካታ ኤርትራዊያንና ኢትዮጵውያን ተዋልደዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ሁለቱን አገራት ለመለየት እኮ በጣም ከባድ ነው፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ የሁለቱ አገራት ግጭት የአንድ ቤተሰብ መበተን ማለት ነው፡፡ ቤተሰብ ሲበተን ደግሞ ምን ያህል ልጆች ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ማስታወስ ግድ ይላል”ትላለች፡፡
በርግጥ ከግጭቱ በኋላ ሁለቱን አገራት ለማስማማት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ በኩል በታላቁ መሪ መለስ ዜናም ሆነ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሰላም ስምምነት ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡ እነዚህ የሰላም ጥረቶች ግን በጎ ምላሽ ባለማግኘታቸው ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ቁርሾ እንዲያበቃ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚያም በዘለለ የሰላም ድርድሩ እንዲሳካም ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
ሰሞኑን በተካሄደው ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባም የሰላሙን ስምምነት እውን ለማድረግ በኢትዮጵያ በኩል እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ማናቸውንም ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ ኮሚቴው ባካሄደው ስብሰባ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበል አስታውቋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ለሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ቁርጠኛ መሆኗን ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የኤርትራ መንግስት ይህንን የሰላም ጥሪ ሊቀበል ይገባል፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ይህንን ላለመቀበል የሚያስችል ምንም አይነት ምክንያት አይኖርምና፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ረቡዕ አገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጉባኤ ሲካሄድ ባደረጉት ንግግራቸው ውስጥ የኤርትራን ጉዳይ አንስተው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ሁኔታ ‹‹ ሞት አልባ ጦርነት›› ሲሉ ገልፀውታል፡፡ ለዚህም ያቀረቡት ምክንያት ባለፉት 20 አመታት በአካባቢው የነበረው ነባራዊ ሁኔታ ማሳያ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
በነዚህ አመታት በአካባቢው ሰላም ባለመኖሩ ሁሉም ለጦርነት የሚያስፈልጉ ወጪዎች፣ ሁሌም ዝግጅት፣ ሁሌም ስልጠናና ውጥረት እንደነበር በማስታወስ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይም የስነልቦና ስቃይ ሆኖ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ባለፉት 20 አመታት ከኤርትራ ጋር በነበራት ግንኙነት ያተረፈችው ውጥረት ብቻ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ደግሞ ሁለቱም አገራት ተጎጂዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን የሰላም እጦት ለመፍታት ባለፉት ሁለት ወራት በተደረጉ ጥረቶች የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ሰላም በአፍሪካ ቀንድም ያስፈልገናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት እንዲስተካከል በኛ በኩል መስራት ያለብንን ስራ መስራት ይገባናል የሚል መልዕክትም አስተላል ፈዋል፡፡
ስለዚህ ሙሉ አቅማችንንና ጉልበታችንን ወደ ሰላም፣ ወደ ፍቅር እንዲሁም ወደ እርቅ ለማሸጋገርና የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ለማድረግ ሃሳባችንን ከሚከፋፍሉ ማናቸውም ነገሮች ሁሉ ወጥተን ፊታችንን ወደ ዋነኛው የአገራችን ጠላት ወደሆነው ድህነት በማዞር የኢትዮጵን እድገት፣ ሰላም እና ብልፅግና ለማረጋገጥ በጋራ እንድንሰራም ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው ካነሷቸው ሃሳቦች መካከል አንዱ የሁለቱን አገራት ቀጣይ አቅጣጫ የሚያመላክት ነው፡፡ “በአስመራና በአዲስ አበባ መካከል አውቶቡስና ባቡር እንዲመላለስ እፈልጋለሁ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ይህ የተስፋ ቃል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር ኢትዮጵያ ምን ያህል ለሁለቱ አገራት ግንኙነት ጠንክራ እየሰራች መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡
በአገራችን “አንድ በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” የሚል አባባል አለ፡፡ ይህ አባባል ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ አገራት የተረጋጋ ሰላም፣ ልማትና እድገት እንዲያስመዘግቡ ሰላም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ነገር ግን በርካታ ሰላም ፈላጊ በተሰበሰበበት ሁኔታ አንድም ቢሆን ሰላምን የሚያደፈርስ አካል ካለ ሰላም ሊመጣ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያም ዋነኛ አጀንዳዋ ሰላምን ማስፈንና በዚህም ሰላም ውስጥ የህዝቦችን እድገትና ብልፅግና ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ በውስጥም ሆነ በውጭ ያለውን የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ  ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ባለፉት ሁለት ወራት በአገራችን ሰላም እየሰፈነ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጭምር እስከማንሳት ደርሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ስንመለከትም ሰላማዊ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት ከኤርትራ በስተቀርም የነበረው ግንኙነት በጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱ ለጀመረችው የልማት እንቅስቃሴ እውን መሆን ከፍተኛ አወንታዊ ሚና ያለው ነው፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከኤርትራም ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ስኬታማ ለማድረግ ከመንግስት በተጨማሪ ምሁራን፣ አገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ግለሰቦች የሚሳተፉበት አንድ ድርጅትም ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል፡፡ ሰለብረቲ ኢቨንትስ በሚል የሚታወቀው ይህ ድርጅት በተለይ የሁለቱ አገራት ህዝቦች የጉዳዩ ባለቤቶች በመሆናቸው ግፊት ማድረግ አለባቸው በሚል የሁለቱን አገራት ህዝቦች ያስተሳሰረ ግንኙነት ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡
ይህ ሁለቱን አገራት የማቀራረብ እንቅስቃሴ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በምስራቅ አፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ ላይ ለበርካታ አመታት ምርምሮችን ሲደርጉ የቆዩትና በእንግሊዝ ኪንግስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት  ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት  የሁለቱ አገራት ግጭት በአካባቢው ሰላምም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ያስከተለ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡
እነዚህ አገራት በግጭት ውስጥ መቆየታቸው የሁለቱን አገራት ህዝቦች በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳና የህዝቦችን ነፃነት የገደበ ተግባር ከመሆኑን ባሻገር የምስራቅ አፍሪካ አካባቢን ወደ አንድ ለማምጣት በሚደረገው አህጉራዊ ጥረትም እንቅፋት ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ አገራት ግጭት ሊበቃ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ለሁለቱም አገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡
የሁለቱ አገራት ግጭት በሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንጻርም ያስከተለው ችግር ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ የወደብን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል፡፡ ኤርትራ የያዘችው አሰብም ሆነ የምፅዋ ወደቦች ለኢትዮጵያ የተሻለ ስትራቴጂያዊ ቦታዎች ናቸው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት በሰላም ላይ የተመሰረተ ቢሆን ኢትዮጵያ እነዚህን ወደቦች ለመጠቀም ያስችላታል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡
በሌላ በኩል ኤርትራም ቢሆን ከዚህ ወደብ ይበልጥ ጥቅም ልታገኝ የምትችለው ከኢትዮጵያ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ እነዚህ ሁለት ወደቦች ለኢትዮጵያ በሚሰጡት ጠቀሜታ ኤርትራ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ማግኘት ያስችላታል፡፡
በአጠቃላይ በሁለቱ አገራት መካከል ከ17 አመታት በላይ የዘለቀው “ሞት አልባ ጦርነት” ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የዳረገ ነው፡፡ በተለይ አፍሪካን በተለያዩ የልማት ኮሪደሮች ለማስተሳሰር ዘርፈብዙ የልማት ስራ እየተሰራ በሚገኝበትና በዚህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች በምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ በአካባቢው የሚፈጠር ሰላም ለሁለቱም አገራት ከሚሰጠው ጠቀሜታም ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ እና ለአፍሪካ ጭምር ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ በአካባቢው ሰላምን መፍጠር ጠቃሚ ነው፡፡

ውቤ ከልደታ

Published in አጀንዳ

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና፣ የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ማዕከል፣ ከ100 በላይ ኤምባሲዎች መቀመጫና የበርካታ ዲፕሎማቶች መኖሪያ መሆኗ በተደጋጋሚ የሚገለፅ እውነታ ነው፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በየጊዜው ወደ ከተማዋ በሚገቡ ዜጎችና ከፍተኛ በሆነው አገራችን የህዝብ ቁጥር ምጣኔ የተነሳም የከተማዋ የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይገኛል፡፡
በከተማዋ የሚካሄደው የመረሰተ ልማትና ሌሎች አገልግሎቶች እድገትም የአገሪቱ እድገት መጠን ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ከተማዋ በየጊዜው በሚካሄዱባት ግንባታዎች የተነሳ “ፈርሳ እየተገነባች ያለች ከተማ” ለመባል ጭምር በቅታለች፡፡
ያም ሆኖ ግን በህዝቧና በግንባታዎቿ እድገት ልክ ማደግ ያልቻለ ባህልም አላት፡፡ የከተማዋ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት በአገሪቱ ከሚገኙ አነስተኛ ከተሞች ጭምር ወደኋላ የቀረና ደካማ ነው፡፡ በተለይ ክረምት በመጣ ቁጥር የከተማዋን የንፅህና ጉድለት አጉልቶ የሚያሳየው  የቆሻሻ ሽታ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የከተማዋን ገጽታ ከማበላሸቱም በላይ ለነዋሪው የበሽታ ምንጭ በመሆኑ ችግሩ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
ባለሙያዎች እንደሚመክሩት የግልና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠር ዋነኛ መንገድ ነው፡፡ አገራችንም መከላከልን መሰረት ባደረገው የጤና ፖሊሲዋ እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት በመላ አገሪቱ ከ39 ሺ በላይ የሚሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በማሰልጠንና በእያንዳንዱ ቀበሌ በመመደብ እየሰራች ትገኛለች፡፡
በመዲናችን ያለው የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ግን ከዚህ በተቃረነ መልኩ ደካማ ነው፡፡ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ደረቅ ቆሻሻን ከቤቱ ማውጣቱ እንጂ በአግባቡ ስለመሰብሰቡና ስለመወገዱ ብዙም ትኩረት አይሰጥም፡፡ በዚህ የተነሳ በአንዳንድ ንፁህ የመኖሪያ ግቢዎች ውጭ ላይ ቆሻሻ ተከምሮ ማየት የተለመደ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ለፍሳሽ ቆሻሻ ያለው አተያይም ተመሳሳይ ነው፡፡ በርካታ መኖሪያ ቤቶችና ንግድ ቤቶች መፀዳጃ ቤቶቻቸውን ከጎርፍ ማስወገጃ ቱቦ ጋር በማገናኘት መጠቀምን እንደነውር የማይቆጥሩበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በየመንገዱም ቱቦ ላይ ወይም አጥር ስር ጠጋ ብሎ መሽናት መብት የሚመስላቸው በርካታ ነዋሪዎች አሉ፡፡
በከተማዋ ይህንን የፅዳት ችግር ለመፍታት በመንግስት በኩል የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ከሰባት ወራት በፊት ጀምሮ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የሚሳተፉበት ወርሃዊ የፅዳት ዘመቻ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱም በየመንደሩ ተፈጥሮ የነበረው ተነሳሽነት አበረታች ነበር፡፡ በተለይ  ሞዴል ለሆኑ መንደሮች ሽልማት እንደሚሰጥ መገለፁን ተከትሎ  በተነሳሽነት አካባቢያቸውን የሚያፀዱና የሚያስውቡ  ነዋሪዎችን ፈጥሮ  ነበር፡፡
ነገር ግን ይህ ተነሳሽነት ዘላቂ ሊሆን አልቻለም፡፡ ይህ በዘመቻ የተጀመረ ስራ የአንድ ሰሞን ተግባር ብቻ ሆኖ እየተቀዛቀዘ ይገኛል፡፡  አሁን የምንገኝበት ወቅት ደግሞ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡
በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ደግሞ ከመልሶ ማልማት ጋር ተያይዞ ፈርሰው የቆዩ አካባቢዎች የቆሻሻ መጣያ ሆነዋል፡፡ ለዚህም በልደታ ክፍለ ከተማ በተለምዶ  የአሜሪካን ግቢ የሚባለው ስፍራ ማሳያ ነው፡፡ የዚህ ስፍራ ነዋሪዎች በመልሶ ማልማት ከተነሱ ከሁለት አመት በላይ ቢሆናቸውም አካባቢው እስካሁን ባለመልማቱ የቆሻሻ መጣያ ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ ከአካባቢው የሚወጣው የቆሻሻ ሽታ ለበሽታ የሚያጋልጥ እንደሆነ ነዋሪዎች ያማርራሉ፡፡
ሌላው የከተማዋ ችግር የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ሁኔታ ነው፡፡ በየቦታው የተቆፈሩት እነዚህ ቱቦዎች የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎች ቢሆኑም አብዛኞቹ ግን በየመንደሩ ከመፀዳጃ ቤት ጋር በመገናኘታቸው  የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ማስወገጃ ሆነው ይታያሉ፡፡ አብዛኞቹ ቱቦዎች ደግሞ ሞልተው ስለሚፈሱ ከተማዋንም ሲበክሉ ይስተዋላል፡፡
የአዲስ አበባ ወንዞችም የአካባቢው ነዋሪዎች የቆሻሻ መጣያ ስፍራዎች ናቸው፡፡ በነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች  ደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻን ወደ ወንዝ መልቀቅ ህጋዊ መብት እስኪመስላቸው ድረስ   ወንዞችን በግልፅ የቆሻሻ መጣያ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ በዚህ የተነሳም ዝናብ በጣለ ቁጥር የከተማዋ ወንዞች ቆሻሻ ማጓጓዣ  እስኪመስሉ ድረስ ተበላሽተው ይታያሉ፡፡
በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ያለው የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ  የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይ ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያዞ እንዲህ አይነት የተበላሸ የቆሻሻ አያያዝ ስርዓት አደገኛ የጤና ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ የከተማችን ነዋሪ ቆሻሻ ዋነኛ የበሽታ ምንጭ መሆኑን በመረዳት፣ የግልም ሆነ የአካባቢውን ንፅህና መጠበቅ ይኖርበታል፡፡  ደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ በአግባቡ ካልተያዘና በአግባቡ ካልተወገደ ለተላላፊ በሽታ መንስኤ በመሆኑ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ


አቶ አንዳርጌ አራጋው የሚኖሩት ግንፍሌ አካባቢ ቢሆንም የመስሪያ ቦታቸው ኮተቤ በመሆኑ በጠዋት ተነስተው 33 ቁጥር አቶቡስ መጠበቅ ግዴታቸው ነበር፡፡ ከሰፈራቸው ይነሳ የነበረው የአንበሳ አውቶቡስ መምጫው ሰዓት ባለመታወቁና አንዳንዴ በሰዎች የተጨናነቀ በመሆኑ ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በትራንስፖርት እጥረት ለበርካታ ዓመታት በሥራ ገበታቸው ላይ በሰዓታቸው መድረስ ይቸገሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ሆኖም መንግሥት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥት ለሠራተኞች ባመቻቸው የትራንስፖርት አቅርቦት የተነሳ ከእንግልት መዳናቸውንና ወደ ሥራቸውም በሰዓቱ ስለሚገቡና ስለሚወጡ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናው እንዳገዛቸው አቶ አንዳርጌ ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተሰጣቸው ሥራ ላይ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲያሳልፉ በማድረግ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ እንዳስቻላቸውም ይጠቁማሉ፡፡
አቶ አንዳርጌ መስተካከል አለበት ያሉትም ሃሳብ አለ፡፡ «አገልግሎቱ ይበልጥ ተደራሽና ሁሉንም ተጠቃሚዎች የሚያረካ ለማድረግ በአንዳንድ አሽከርካሪዎች ላይ የሚታዩ የስነምግባር ጉድለቶችን በመፍታትና ሠራተኛው በሚበዛባቸው አካባቢዎችም ተጨማሪ አቶቡሶችን መመደብ ቢቻል የተሻለ ነው፡፡» ከዚህም ባሻገር ድርጅቱ በየጊዜው ከተገልጋዩ አስተያየቶችን በመቀበል አሠራሩን ማሻሻል እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡
 በአዲስ አበባ በተለያዩ የፌዴራልና የአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች በትራንስፖርት እጥረት ሳቢያ መንግሥት ያስቀመጠውን ስምንት የሥራ ሰዓት ተግባራዊ ማድረግ ሳይቻል ቆይቷል፡፡ አብዛኛው ሠራተኛ ወደ ሥራ ገበታ የሚደርሰው ከ2፡30 ዘግይቶና በትራንስፖርት አጣለሁ ስጋት ከሥራ መውጫ ሰዓት ቀደም ብሎ በመውጣቱ በሀገር ልማታዊ ዕድገት ላይ ከሚያስከትለው ጫና ባልተናነሰ አገልግሎት ፈልጎ ወደ መስሪያ ቤቶች የሚመጣው ዜጋ በመልካም አስተዳደር ችግር መጉላላቱንም ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
መንግሥት ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሰርቪስ አገልግሎት ለፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛው እንደሚያቀርብ የፐብሊክ ሰርቪስ የሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት  በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 298/2006 ዓ.ም ተጠሪነቱ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር ሆኖ ተቋቋመ፡፡  
ሌላው አስተያየት የሰጡት ደግሞ አቶ መልካሙ አለማየሁ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው አባባል፤ በአዲስ አበባ ውስጥ ያለው የትራንስፖርት ችግር ቀደም ብሎ ያለና አሁንም እየተባባሰ የሚገኝ ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ትራንስፖርት በፍጥነት ስለማያገኝ ሥራ ገበታው ላይ እክል ፈጥሮበት ነበር፡፡
 መኖሪያቸውና መስሪያ ቦታቸው የሚራራቁ ሰዎች ትራንስፖርት ባለማግኘታቸው ከሥራ ገበታቸው የማርፈድና የመቅረት ሁኔታዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ባይባልም ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ሠራተኛው የሥራ ገበታው ላይ በሰዓቱ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡
በቀጣይ ሠራተኛውን ያማከለ አገልግሎት መስጠት ከተቻለ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመፍታት ጠቃሚ እንደሆነም አቶ መልካሙ ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ አሠራሮቹን በየጊዜው በማሻሻልና እጥረት ባለባቸው ቦታዎች ላይ ተጨማሪ አቶቡሶች በመጨመር አገልግሎቱን ማስፋት እንደሚገባውም ይጠቅሳሉ፡፡
የፐብሊክ ሰርቪስ የሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አምባቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ሲመሰረት ሦስት ዓላማዎችን ይዞ ነው፡፡ የመጀመሪያው በአዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ የከተማ አስተዳደሩና ለፌዴራል መስሪያቤት ሠራተኞች የሰርቪስ አገልግሎት ለመስጠት፣ ሁለተኛው በከተማዋ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ከሥራ ሰዓት መግቢያና መውጫ ሰዓት ውጪ የታክሲ አገልግሎት ለመስጠት፣ ሦስተኛ በተመጣጣኝ ዋጋ የኮንትራት አገልግሎት ለመስጠት ነው፡፡
 ቀደም ባሉት ጊዜ ሠራተኛው በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት የሥራ ሰዓት አክብሮ መግባትና መውጣት ላይ ችግሮች እንደነበሩ የሚያስታውሱት አቶ ሰለሞን፤ በዚህም ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ላይ እክል ፈጥሮ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ችግሩን ለመፍታት መንግሥት በጀት መድቦ ለሠራተኛው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት 2007 ዓ.ም ላይ ወደ ሥራ መገባቱን ይጠቅሳሉ፡፡ ድርጅቱ ሲጀመር 55 አውቶቡሶችን ይዞ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት በ410 አቶቡሶች ከ82 ሺ በላይ የመንግሥት ሠራተኞችና ከ35 ሺ ለሚበልጡ የከተማዋ ነዋሪዎች የታክሲ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ያመለክታሉ፡፡
 የሰርቪስ አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ ሠራተኛው በሰዓቱ በመግባት ሥራውን በአግባቡ እያከናወነ እንደሚገኝ በየጊዜው ከሠራተኛውም የሚመጡ አስተያየቶች እንደሚያሳዩ ይጠቅሳሉ፡፡ በተገኘው ውጤትም በትራንስፖርት እጥረት ሳቢያ የሚፈጠሩ ችግሮች በተለይ በጊዜ ወደ ቤት አለመግባትና ለትራንስፖርት የሚወጣን ወጪ እንዲቀንስላቸው እንዳደረገ  ይናገራሉ፡፡  
     እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ተጠቃሚው በመብዛቱ መጨናነቆችን ለመቀነስ ሰው የማይበዛበት ቦታ ያሉትን አውቶቡሶች ወደ ተጨናነቁ ቦታዎች የመመደብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ተጨማሪ አውቶቡሶች እንዲገዙ ጥያቄ ቀርቧል፡፡  
     በሌላ በኩል የአውቶቡስ ሹፌሮችን ስነምግባር በተመለከተ አብዛኞቹ በጥንቃቄ የሚያሽከረክሩ በመሆናቸው በዚህ ወር ምንም ዓይነት አደጋ አለመድረሱን አቶ ሰለሞን ነግረውናል፡፡ ሆኖም የስነ ምግባር ችግር ያለባቸው የአውቶቡስ ሹፌሮች ስለሚኖሩ እነዚህን  ለመለየት እርስ በርስ የሚገማገሙበት አሠራር ተፈጥሮ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ ግጭት ሲያጋጥምም ምክንያቱ ምን ነበር? ሾፌሩ ምን ማድረግ ነበረበት? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተው ይወያያሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ከተሳፋሪው የሚመረጡ ሁለት አስተባባሪዎች ጥፋት ሲያዩ ይመክራሉ፡፡ ከባድ ችግር ከተፈጠረ ደግሞ ለዋና መስሪያቤቱ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ በዚህም ጥፋተኛ የሆነ ሾፌር ሲገኝ ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል፡፡ ምንም ዓይነት አደጋ የማያደርሱ የአውቶቡስ ሹፌሮችም  የሚሸለሙበትና የሚበረታቱበት አሠራር በመኖሩ አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ እንዲሆን ማድረጉን አቶ ሰለሞን ገልጸውልናል፡፡

ዜና ሐተታ
መርድ ክፍሉ

Published in የሀገር ውስጥ


ቆሻሻ አውጡ፤ ቆሻሻ አውጡ፤ የሚለው ጥሪ ከእድር ቤት ጡሩንባ ቀጥሎ ጠዋት ጠዋት ከእንቅልፌ የሚበጠብጠኝ ድምፅ ነው፡፡ ወይዘሮ ታደለች አበበ ግን በየቀኑ ጠዋት ጠዋት በየሰፈሩ እየዞሩ በድምፅ ማጉያ ቆሻሻ አውጡ ማለት ሥራቸው ካደረጉት ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እሳቸው በሚሠሩበት አካባቢ የሚገኙት መኖርያዎች በእዚያኛው ወንዝ ዳር በመሆናቸው ህብረተሰቡ ቆሻሻውን በማዳሪያ ከማድረግ ይልቅ ወደ ወንዙ መጣል እንደሚቀለው ይናገራሉ፡፡
የከተማው ነዋሪ ቆሻሻ ከቤቱ እንዲርቅለት እንጂ እንዴት ማስወገድ እንዳለበት አያውቅም የሚሉት ወ/ሮ ታደለች በዚህ የተነሳም የተለያዩ አካባቢዎች በቆሻሻ ተሞልተው እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ አብዛኛው ሰው ደረቅ ቆሻሻዎች እንዴት መወገድ እንዳለባቸው ባለማወቃቸውና አንዳንዶቹ ግዴለሽ በመሆናቸው ሥራቸው ላይ እክል መፍጠሩንም ይገልጻሉ፡፡ በከተማዋ አጠቃላይ የቆሻሻ አወጋገድ ባህሉ ሲታይ ደካማ መሆኑንና ቆሻሻ በአግባቡ በማያስወግዱት ላይ ዕርምጃው መጥበቅ እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች የቆሻሻ አወጋገድ ባህል ሲታይ በጣም ደካማ መሆኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ደረቅም ይሁን ፍሳሽ ቆሻሻዎች ሲወገዱ የከተማዋን ንፅሕና በሚያበላሽ መልኩ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ጋር በተያያዘ በህብረተሰቡ ዘንድ የአመለካከትና የተግባር ችግር መኖር፣ ከየቤቱ የሚሰበሰበውን ቆሻሻ ለተገቢው አካል አለማስረከብ፣ ሁሉም የራሱን ድርሻ አለመወጣትና በአጠቃላይ ቆሻሻ ከምንጩ የሚቀነስበት ሥርዓት አለመኖር ከችግሮቹ መካከል ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አቶ ከበደ አምታታው በመገናኛ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ ያለው ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመሻሻል ይልቅ  እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ነዋሪው ደረቅም ይሁን ፍሳሽ ቆሻሻዎችን ከቤቱ ውጪ ሲጥልና ሲደፋ ለአካባቢው ንጽሕና አያገባኝም በሚል መንፈስ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
በየአካባቢው ተደራጅተው ከየቤቱ ቆሻሻ የሚያወጡ ማህበራት በተወሰነ መልኩ ችግሩን ያቃለሉ ቢሆንም የህብረተሰቡ ግንዛቤ ባለመለወጡ ምክንያት አሁንም በየመንገዱ ቆሻሻዎች ተጥለው እንደሚታዩ ይናገራሉ፡፡ አብዛኛው መንገድ ዳር የሚገኙ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ቆሻሻዎቻቸውን የመንገድ ቱቦ ውስጥ ስለሚጥሉ በክረምት ለጎርፍ ተጋላጭ እያደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ባዩሽ አስራት፤ በአዲስ አበባ የቆሻሻ አወጋገድ ባህሉ ሲታይ ክፍተት እንዳለበትና ህብረተሰቡ ቆሻሻውን ማስወገዱን እንጂ ምን ዓይነት በሽታ ያመጣል የሚለውን ለይቶ ባለማወቁ ለአወጋገዱ ትኩረት እንደማይሰጥ ይናገራሉ፡፡ ለህብረተሰቡ ደካማ የቆሻሻ አወጋገድ ባህል የግንዛቤ ክፍተት  አለመሆኑን በመጥቀስ፤ በየጊዜው ቤት ለቤት በመዞር የቆሻሻ አወጋገድ በምን መልክ መሆን እንዳለበት ግንዛቤና ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡
ከዚህም ባለፈ የህብረተሰቡ አመለካከት እንዲለወጥ በመገናኛ ብዙሃን ሰፊ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ባዩሽ፤ እያንዳንዱ ሰው ቆሻሻ ሲያስቀምጥ የሚበ ሰብሰውንና የማይበሰብሰውን ለይቶ በሰማያዊና በአረንጓዴ ማዳበሪያዎች እንዲያስቀምጥ ትምህርት ቢሰጠውም በተፈለገው መጠን ተግባር ላይ አለመዋሉን ያስረዳሉ፡፡ ሆኖም አልፎ አልፎ ህብረተሰቡ በዚህ መንገድ ማስቀመጥ ቢችልም ቆሻሻ አንሺ ማህበራት የቆሻሻ ማቆያ ስፍራ ስለሚያጥራቸው  ሊቀላቅሉት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ ባዩሽ አባባል፤ እስከአሁን ባለው ሁኔታ የቆሻሻ አወጋገድ ላይ የተሰጡት የግንዛቤ ሥራዎች የተጠበቀውን ያክል ውጤት አላመጡም፡፡ በዚህም የተነሳ የህብረተሰቡን አመለካከት ለመቀየር የህዝብ ንቅናቄ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የፅዳት ሥራው የየቀን ሥራ እንዲሆን ለማድረግ በተሠሩ ሥራዎች አሁን አሁን መጠነኛ ለውጥ እየመጣ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የቆሻሻ አወጋገዱን ስርዓት ለማስያዝና ከተማችንን ንፁሕ ለማድረግ የግንዛቤ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠልና ያሉትን ክፍተቶች ለይቶ የማስተካከያ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡   
ቆሻሻ ያለ አግባብ የሚያስወግዱት ላይም ከደንብ ማስከበር ፅህፈት ቤት ጋር በመሆን የቅጣት ሥራ ቢጀመርም አጥብቆ መሄድ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ የሚጠቅሱት ወይዘሮ ባዩሽ፤ ቅጣት የአመለካከት ለውጥ የሚያመጣ አለመሆኑንና የአመለካከት ለውጥ ከፍላጎት የመነጨ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ዜና ሐተታ
መርድ ክፍሉ

Published in የሀገር ውስጥበአንድ አገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ሚና የጎላ መሆኑን ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ በተለይም የግል ሚዲያው ድርሻ ኮስሷል፡፡
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ፅጋቡ ሞትባይኖር እንደሚሉት፤ አንድ አገር ዴሞክራሲዋን ለመገንባት በምታደርገው ሂደት ውስጥ መንግስት በሚያከናውናቸው ተግባራት ዙሪያ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማስተላለፍና አዳዲስ አስተሳሰቦችን በማስተዋወቅ የመገናኛ ብዙሃን ብዙ ስራዎችን ይሰራሉ፡፡ ይህም በአንድ አገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና እድገት ላይ የመገናኛ ብዙሃንን ሚና የጎላ ያደርገዋል::
አቶ ፅጋቡ እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ ያሉ የመገናኛ ብዙሃን በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የራሳቸው አስተዋፅኦ ቢኖራቸውም የሚጠበቅባቸውን ሚና ግን ተወጥተዋል ማለት አይደለም፡፡ ሚዲያዎች በየኢዲቶሪያል ፖሊሲዎቻቸውና በሌሎች ምክንያቶች ጫና ስር የወደቁና የተገደቡ ናቸው፡፡ ጫናውን ተቋቁመውና በተፈቀደላቸው ልክ ተጠቅመውም ብዙ ለመስራት ሲጥሩ አይታዩም፡፡ ይህ ደግሞ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ላይ ብዙ እንዳይሄዱና ሚናቸውም እንዲቀጭጭ አድርጎታል፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ክብሮም ብርሃነ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ እንደ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ጅምር ላይ ላሉ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ዴሞክራሲ በትክክል እንዲሄድ ከማድረግ አንጻር የመገናኛ ብዙሃን የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ አንድ ሚዲያ በህገ መንግስት በተሰጠው መብት ልክ ከሰራ ከህገ መንግስት ጀምሮ በአንድ አገር በሚወጡ ህጎችና አሰራሮች ዙሪያ በህብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤን በመፍጠር ዴሞክራሲ የሚያድግበትን መንገድ እየከፈተ ይሄዳል፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የመገናኛ ብዙሃን ይሄን ሚናቸውን እየተወጡ ነው ማለት አይቻልም፡፡
እንደ አቶ ክብሮም ገለጻ፤ አንደኛ ሚዲያዎቹ ራሳቸውን የሚመለከቱበት አተያይ፤ ሁለተኛም የመንግስት ተጽዕኖ እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ውስጥ በሚፈለገው ልክ የድርሻቸውን እንዳይወጡ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ሲባል፣ እያንዳንዱ ሚዲያ የአርበኝነት አይነት ስሜት ለራሱ ይሰጣል፤ አንዳንዱም የጋዜጠኝነትና አክቲቪስት ድንበር ተፋርሶበት የሚንቀሳቀስ ነው፤ አንዳንዶቹም ከእኛ በላይ ብልሹ የሆነን ነገር ማውጣት የሚችል የለም ብለው ያምናሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሙያው የሚጠይቀውን ስነ ምግባር ካለማክበርና በትክክል አስቦ ካለመነሳት የሚመነጭ፤ እውነትን ማወቅና መያዝ ብቻ ሳይሆን የያዙትን መረጃንም እንዴት ማቅረብ እንደሚገባቸው ካለማወቅ የሚመጣ ነው፡፡
አብዛኞቹ የግል ሚዲያዎችም ነገርን አመዛዝኖ ከማቅረብ ይልቅ ወደ አንድ ወገን በማዘንበል በተጋነነ መንገድ ማስቀመጥ ላይ ያተኩራሉ፡፡  በዚህ መንገድ የሚያቀርቧቸው መረጃዎች በሙያዊ መመዘኛም ሲታዩም የሚያምታቱና የሚጋጩ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ መንግስት በአንድ በኩል ነጻነቱን ሰጥቷል፤ በሌላኛው በኩል ደግሞ ወደትግበራ ሊገቡ ሲሉ ሊሰሩ ይችላሉ በሚል ፍርሃት ቶሎ የማቀጨጭ ሂደት ይታይበታል፡፡ በዚህ መልኩ መንግስት ፈርቶ የሚያደርገው ነገር ሚዲያዎቹም ሆኑ ጋዜጠኞቹ ምንም ሳይሰሩ ሌላኛውን ጽንፍ ይዘው ለህዝብ የሰሩ በመምሰል እንዲገንኑ፤ በገነኑ ቁጥር ደግሞ የሰሩ እየመሰላቸው በሃሰት ዝና ውስጥ እንዲደበቁና መስራት የሚገባቸውን ሳይሰሩ እንዲረሱት አድርጓቸዋል፡፡
በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት አቶ ፅጋቡ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል በርካታ የህትመት ሚዲያዎች ስለነበሩ ህዝቡ የተለያዩ መረጃዎችን የሚያገኝበት አማራጭ ነበረው፡፡ ሆኖም አንዳንዶቹ ጋዜጦች ከጋዜጠኝነት መህር በወጣ መልኩ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለህዝቡ ዘገባዎችን ማድረስ ሲገባቸው፤ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በመሄድ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የነበራቸውን ድርሻ ገፍተው፣ ሚናቸውንም እንዳይወጡ ሆነዋል፡፡ መንግስትም እንዲጠፉ ከማድረግ ይልቅ ይሄን አካሄድ በማረምና ደግፎ በማስተካከል እንዲቀጥሉ ማድረግ ሲችል፣ እንዲዘጉና ቁጥራቸው እንዲመናመን አድርጓል፡፡ በዚህ መልኩ በራሳቸው ችግርና በመንግስትም አሰራር እነዚህ የግል ሚዲያዎች በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የድርሻቸውን እንዳይወጡ ሆኗል፡፡
እንደ አቶ ፅጋቡ ገለጻ፤ በአፍሪካ እንደ ኬንያና ኡጋንዳ ያሉ አገራት በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና ጋዜጦች አሏቸው፡፡ በኢትዮጵያም የህትመት ሚዲያው ሲዳከም የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ቁጥር እየጨመረ ያለበት ጅማሮ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም ከጥቂቶቹ ያውም በጥቂት ፕሮግራሞቻቸው በስተቀር አብዛኞቹ መዝናኛ ላይ አተኩረው የስፖነሰሮችን ምርት በማስተዋወቅ ገንዘብ ማግኘት ላይ በማተኮራቸው በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ያላቸውን ድርሻ አሳንሰውና ሚናቸውን ዘንግተው ይታያሉ፡፡ በዚህ መልኩ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ባያሳሱና ሚናቸውንም ባይዘነጉ በአገሪቱ የተፈጠረው ችግርም ላይፈጠር ይችል ነበር፡፡
ይሄን ሃሳብ የሚጋሩት አቶ ክብሮም በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ከህዝቡ የማንበብ ችሎታና ፍላጎት፣ እንዲሁም ከወረቀት ዋጋ ጋር ተያይዞ በሚገለጹ ከህዝቡም ሆነ ከመንግስት በመነጩ ምክንያቶች የህትመት ሚዲያው እንዳያድግ፤ እንዲዳከምና ድርሻውን እንዳይወጣ አድርጎታል፡፡ የህትመት ሚዲያውን መዳከም ተከትሎ የተስፋፋው የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችም በይዘታቸው እጅጉን ለተዝናኖት እንጂ የአገርና የህዝብ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ አይደሉም፡፡ የህዝቡን ንቃተ ህሊና ከማሳደግ ይልቅ ፈጥው ትርፍን ወደማካበት ማተኮራቸውም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ውስጥ ድርሻቸውን እጅጉን አሳንሶታል፡፡
አቶ ክብሮም እንደሚገልጹት፤ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ህዝቡ በአገራዊና ማህበራዊ ጉዳዮቹ ላይ በማተኮር ለህዝቡ የሚያስፈልገውን ነገር የማውጣትና የህዝቡን ንቃት እንዲጎለብት ከመስራ ይልቅ ወደትርፍ ማግኛ ይዘቶች በመግባታቸው፣ ጥልቅ ጉዳይ ይዞ የህዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመቀየር በሚያስችል መልኩ አልሄዱም፡፡ በዚህም በአገሪቱ ያለውን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ ዘንግተዋል፤ የአገራቸውን ጉዳይ እነርሱ ሳይሰሩት ሌሎች እንዲሰሩት ሆኗል፤ ህዝቡንም በዚህ ዙሪያ ንቃት እንዳይኖረው አድርገውታል፡፡ ይሄም በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ሶሻል ካፒታል ግንባታው ላይ ሚናቸው የወረደ መሆኑን ያሳያል፡፡
አቶ ፅጋቡ እንደሚሉት የዴሞክራሲዊ ሥርዓት መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ  ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በመለየትና በማጋለጥ ግልፀኝነት እንዲፈጠር ማድረግ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተገቢውን መረጃ መስጠት፣ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለይቶ በማቅረብ መንግስት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ፣ በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ማጋለጥ እንዲሁም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከማስከበር አንፃር የሚታዩ ክፍተቶችን ለይቶ እንዲስተካከሉ መረጃ መስጠት ይጠቀሳሉ፡፡
ይሁን እንጂ ሚዲያው እነዚህን ስራዎች በሚፈለገው ደረጃ ሲሰራ አይታይም፡፡ ለምሳሌ መንግስት ራሱ በተነሳሽነት ሙስና ላይ ዘመቻ ሲከፍት አብሮ የመጮህ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም በተመሳሳይ መንግስትን ተከትሎ የመሄድ እንጂ ሚዲያዎች ራሳቸው አጀንዳ ፈጥረው ቀዳሚ ሚና መጫወት አልቻሉም፡፡ በዚህ የተነሳ ህብረተሰቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው ከማድረግ አንፃር ሰፊ ክፍተቶች ነበሩባቸው ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ የህትመት ኢንዱስትሪ የፕሬስ ነጻነት አዋጅን ተከትሎ ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ ያሻቀበበት ወቅት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከ1984 እስከ 1989 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት ቁጥራቸው 385 የደረሰ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 265ቱ ጋዜጦች፣ 120 ደግሞ መፅሄቶች ነበሩ፡፡ ሆኖም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ግማሽ የሚሆኑት በተለያየ ምክያት ሊዘጉ ችለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በአማርኛ ቋንቋ የሚታተሙና በገበያ ላይ ያሉ የግል ጋዜጦች ቁጥር ሶስት ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የዴሞክራሲ ሥርዓት ተረጋግቶ መጓዝ የሚችለው፣ በአገሩ ጉዳዮች ላይ አውቆ ጠያቂና ተሳታፊ ህብረተሰብ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃ በማነፍነፍና በማቅረብ ለህዝቡም ትክክለኛ መረጃ መስጠት ሲችሉ፣ መንግስትም በነዚህ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ በዴሞክራሲዊ ግንባታ ሂደቱ ውስጥ ተገቢውን ህዝባዊ ሃላፊነት እንዲወጣ ሲቻል ነው፡፡ ሚዲያዎች አሁን ባው ሁኔታ ከቀጠሉ ግን ህዝብን በአግባቡ ከማገልገል  ይልቅ ለትርፍ ብቻ ትኩረት በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነቶቻቸውን ይዘነጋሉ፤ ህዝቡን አማራጭ ሃሳብ በማሳጣት ሁለንተናዊ ተሳትፎውን ይገድባሉ፡፡ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወቱ ውስጥ ክፉና በጎውን ለይቶና አመዛዝኖ እንዳይወስን፤ ከስሜት ወጥቶ በምክንያት እንዳይጓዝም ያደርገዋል፡፡

ዜና ትንታኔ
ወንድወሰን ሽመልስ

Published in የሀገር ውስጥ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።