Items filtered by date: Saturday, 02 June 2018

የአንድ አገር ስፖርት ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው በታዳጊና ወጣት ስፖርተኞች ላይ መስራት ግዴታ ነው። በተለያዩ ስፖርቶች ውጤታማ የሆኑ አገራት ስምና ዝናቸውን ይዘው መዝለቅ የቻሉትም በታዳጊና ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገው በመስራታቸው ነው። ኢትዮጵያ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስምና ዝናን ባተረፈችበት አትሌቲክስ ስፖርት ውጤቷ ቀጣይነት እንዲኖረው በታዳጊዎችና በወጣቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባት በተደጋጋሚ ይነሳል። በዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ቢሆን በተለያዩ ስፖርቶች የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶች በተለያዩ ክልሎች ተከፍተው እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በአገር አቀፍ ደረጃ የታዳጊ ወጣቶች አካዳሚ በአዲስ አበባና በአሰላ ተከፍቶ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እየተመለከትን እንገኛለን። 

የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶች ጉዳይ ሲነሳ ምን ጊዜም የማይዘነጋው የእድሜ ተገቢነት ነው። ይህ ችግር በአገሪቷ ስፖርት በተደጋጋሚ የሚነሳ ቢሆንም፤ በአንዳንድ የስፖርት አይነቶች ላይ ውስን ለውጦችን መመልከት ተችሏል። ለምሳሌ ያህል በእግር ኳስ የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ አሳሳቢ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች መጥተዋል። ለዚህም ውስንነቶች ቢኖሩበትም ዘመናዊው የህክምና መሳሪያ ኤም አር አይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታዳጊና ወጣት ቡድኖች ላይ ለውጦችን እያሳየ መምጣቱ አይካድም። በዚህም የወጣት ብሔራዊ ቡድኖች ላይ ከዚሁ ከእድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ተስፋ ሰጪ ወጣቶችን መመልከት ተጀምሯል።
የደምስር በሆነውና ተተኪ ታዳጊ ወጣቶችን ማፍራት ይቆይ በማይባልበት የአትሌቲክስ ስፖርት ላይ ግን አሁንም የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ ስር የሰደደ ችግር ሆኖ ቀጥሏል። በታዳጊዎችና ወጣቶች አትሌቲክስ ውድድሮች ላይም ይህ ችግር ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት ሄዷል። ባለፈው ሳምንት በአሰላ አረንጓዴው ስቴድየም ለስድስተኛ ጊዜ በተካሄደው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮናም የእድሜ ተገቢነት ችግር ተሻሽሎ ሳይሆን ብሶበት ተገኝቷል። ከአስራ ስድስት እስከ ሃያ ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አትሌቶች የሚሳተፉበት፤ ይህ ውድድር በትክክለኛው የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ አትሌቶች እንደናፈቁት ተጠናቋል።
በውድድሩ እንደ ሲዳማ ቡና ያሉ አዳዲስ የአትሌቲክስ ክለቦች በተለያዩ ርቀቶች ጠንካራ ተፎካካሪዎችን ይዘው ብቅ ማለታቸው መልካም ዜና ሆኖ እነዚህ ክለቦችን ጨምሮ በታዳጊና ወጣቶች ላይ ይሰራሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ለውድድር ያቀረቧቸው አትሌቶች ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው። ሌላው ይቅርና ታዳጊ ወጣቶች ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ተብሎ የሚታሰበው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እንኳን ለውድድር ያቀረባቸው አትሌቶች በተገቢው የእድሜ ክልል ውስጥ እንደማይገኙ መታዘብ ይቻላል።
የአንድን ስፖርተኛ እድሜ ያለ ህክምና ምርመራ ይህን ያህል ነው ብሎ መናገር ባይቻልም ቻምፒዮናው ከሃያ ዓመት በታች ሳይሆን ከሰላሳ ዓመት በታች ይመስል እንደነበር በስፍራው የነበረ ሊመሰክር ይችላል። አንዳንድ አትሌቶች እድሜዬን የት ታውቃለህ? በማለት ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ አይን አይቶ ልብ እንደሚፈርደው ሁሉ በትክክለኛው እድሜ ወደ ውድድር እንዳልመጡ የሚናገሩ አትሌቶችም ነበሩ።
የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ አንስተውት ያልተፈታ፤ የሚመለከተውም አካል ችላ ብሎት የተደጋገመ የዘወትር የአትሌቲክሱ ጩኸት ነው። በዚህ ችግር ምክኒያት የበርካታ ታዳጊና ወጣቶች ህልም እንዲጨልም ማድረጉ ጉዳዩን ምን ጊዜም እንዲነሳ ያደርገዋል።
የአገሪቷ ስፖርተኞች ሁሉም ባይሆኑም በብዛት የእድሜ ጉዳይ እንዲነሳባቸው አይፈልጉም። በተለያዩ አጋጣሚዎች የምናስተውለው የስፖርተኞቻችን የእድሜ ጉዳይ ስር የሰደደ ችግር እንደሆነ ነው። በእድሜ ጉዳይ ላይ ስፖርተኞች ከጋዜጠኞች ጋር በተደጋጋሚ ሲጣሉ የምናይበት አጋጣሚ የሩቅ ጊዜ ትዝታ ሳይሆን አሁን ላይም የምናስተውለው እውነታ ነው። አሁን አሁን ስፖርተኞች ከጋዜጠኞች የእድሜ ጉዳይ ጥያቄ የሚያመልጡበት ቁልፍ ፓስፖርት ሆኗል። « ትክክለኛውን ወይንስ የፓስፖርቱን» በሚል በእድሜ ጉዳይ ላይ መዘባበትም የዘመኑ ፋሽን ሆኗል። ዳሩ ግን አይን አይቶ ልብ ለሚፈርደው ነገር በፓስፖርት ማጭበርበር ቢቻልም ተክለ ሰውነት እውነቱን ያጋልጣል።
ይህን ስር የሰደደ የእድሜ ጉዳይ ለመፍታት የተለያዩ መፍትሄዎች በፌዴሬሽኖች በኩል ተግባራዊ ሊደረጉ ቢሞከርም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም። ለዚህ ሁሉ ችግር ዋነኛ መንስዔ ሆኖ የምናገኘው ሽልማት ነው።
ሽልማት ስንል የተለያዩ ክልሎችና ክለቦች አሰልጣኞች በአገር አቀፍ ቻምፒዮናዎች ላይ ወክለው ከመጡበት አካል ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት የሚበረከትላቸውን ሽልማት ነው። እነዚህ አሰልጣኞች በአገር አቀፍ ቻምፒዮናዎች ላይ ውጤታማ ሆነው ሲገኙ የወከሉት ክልል ወይንም ክለብ የተለያዩ ሽልማቶች፤ ማዕረግና እድገት ያገኛሉ። ለዚህም የትኛውም አሰልጣኝ በውድድሮች ላይ ውጤታማ ሆኖ ለመገኘት የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። ለእዚህ ውጤት ለመብቃት ደግሞ በተለይም በታዳጊዎችና ወጣቶች ቻምፒዮናዎች ላይ በተገቢው እድሜ ስፖርተኞችን ማሰለፍ ለእነሱ አዋጭ አይደለም። ምክኒያቱም ተፎካካሪ በተገቢው እድሜ ስፖርተኞችን አያወዳድርምና ለምን እንበለጥ የሚል የጥርጣሬ ስሜት በአሰልጣኞች መካከል አለ።
ለዚህ ማስረጃነት አንዳንድ ክልሎች ወይንም ክለቦች በእድሜ ተገቢውን ስፖርተኛ አሰልፈው ተገቢ ያልሆነ ስፖርተኛ ባሰለፉት የሚወሰድባቸው የበላይነት በቂ ነው። ዛሬ በተገቢው እድሜ ስፖርተኞችን አሰልፎ ተገቢ ባልሆኑት ስፖርተኞች የበላይነት የተወሰደበት አሰልጣኝ ነገ ላይ ምኑን ተማምኖ በተገቢው መንገድ ወደ ውድድር ይመጣል? ታዳጊና ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ጥቂት አሰልጣኞች አሉ። እነዚህ አሰልጣኞች የት ደረሱ? እነዚህ አሰልጣኞች ውጤትን እንጂ የእድሜን ተገቢነት ትኩረት ሰጥተው በማይሰሩት አሰልጣኞች ተውጠው እናገኛቸዋለን። ማንም ሰው ከዛሬ ነገ የተሻለ ለውጥና እድገት ይፈልጋል። ስለ እዚህም በተጭበረበረ መንገድ ወደ ውጤት በርካቶች እየገሰገሱ በትክክለኛው መንገድ የሚሰሩት አሰልጣኞች እሰከ መቼ ተደብቀው ይኖራሉ?
ከአሰልጣኞቹም በላይ የነገ ተስፋዎች ይሆናሉ ተብለው ትልቅ ተስፋ የሚጣልባቸው ታዳጊዎች ለሽልማት በሚሮጡ አሰልጣኞች ምክንያት እየተዋጡ ናቸው። በርካታ ታዳጊዎች ሽልማት ባመጣው ጣጣ ተስፋቸው በጊዜ እየጨለመ ነው። ታዳጊዎች ታዳጊነን በሚሉ ታላላቆቻቸው በስፖርቱ ያላቸው ተሰጥኦ እየተደበቀ አገሪቱም ማግኘት የሚገባትን ተተኪዎች እያጣች ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይህን ችግር ለመፍታት ከአቅሙ በላይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ፌዴሬሽኑ ማህደሮችን አገላብጦ በመመርመር እድሜን በማጣራት ከውድድር የቀነሳቸው ተወዳዳሪዎች ከዚህ ቀደም ነበሩ። ይህ አካሄድ ሁሉንም መለየት የሚያስችል አልነበረም አሁንም ቀርቷል። ምክንያቱ ደግሞ አትሌቶች ስም ቀይረው አዲስ ፓስፖርት በማውጣት በእድሜያቸው ላይ ማስተካከያ አድርገው መምጣታቸው ነው። ችግሩ ፌዴሬሽኑ ብቻ ሊፈታው የሚችለው አይደለም። ችግሩን ለመፍታት ክለቦች፤ ክልሎች፤ አሰልጣኞችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ኃላፊነትና ቀናነት የተሞላበት መንገድ ሊከተሉ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ፌዴሬሽኑ የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርግ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው። ፌዴሬሽኑ ፓስፖርትን ጨምሮ ሌሎች ሰነዶችን መርምሮ የቀረቡትን ተወዳዳሪዎች ከማወዳደር በዘለለ ማስረጃዎቹን ውድቅ አድርጎ ተገቢ አይደለም ያለውን ስፖርተኛ የማገድ መብት የለውም። ይህ ችግር በስፋት የሚታየው ጠንካራ ፉክክር በሚያደርጉ ክለቦችና ክልሎች እንጂ በአዳጊ ክልሎች ላይ አይደለም። በርካታ ታዳጊዎችን በስፋት ለአገር የማበርከት አቅም ባላቸው መሆኑ፤ በችግሩ እሳት ላይ ቤንዝል እንደ ማርከፍከፍ ይሆናል።
በተለያዩ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮች እንዲሁም በአገር ውስጥና በውጪ አገራት የአገር አቋራጭ ውድድሮች የምናውቀው አትሌት ኮማንደር አበበ መኮንን አሁን ላይ በአዲስ አባባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ክፍል ሰብሳቢና ስራ አስፈፃሚ አባል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በአሰላው ቻምፒዮናም የአዲስ አባባ ቡድን መሪ ሆኖ በስፍራው ተገኝቷል። «የወጣቶች ቻምፒዮና ሳይሆን አዲስ አባባ ላይ የተካሄደው የአዋቂዎች ቻምፒዮና ነው» በማለትም አበበ በውድድሩ ጎልቶ የሚታይ የእድሜ ተገቢነት ችግር እንዳለ ይናገራል። አንዳንዱ ወጣቶችን ይዞ ሲቀርብ ሌላኛው ነባርና አዋቂዎችን ለውድድር እንዳመጣም ትዝብቱን ያካፍላል። ይህም የፉክክር አለመመጣጠን እንዲያይ አድርጎታል። «በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውስጥ አሳሳቢው ችግር የአበረታች መድሃኒት ተጠቃሚነት ሳይሆን የእድሜ ጉዳይ ነው » የሚለው አትሌት ኮማንደር አበበ በዚህ መልኩ ስፖርቱን ማራመድ አስቸጋሪ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ይጠቁማል። ክልሎች፤ ክለቦችና ፌዴሬሽን ይህን ጉዳይ ቆም ብለው በማሰብ በህክምና በመታገዝ ጭምር ሊያርሙ እንደሚገባም ይናገራል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ በበኩላቸው «የአመለ ካከት ችግር አለ፤ ፌዴሬሽኑ ህግና ደንብን ማውጣት እንጂ ክለቦችና ክልሎችን ተክቶ ሊሰራ አይችልም፤ ህጉን ያላከበረና በህጉ መሰረት ያልሰራ ክለብ፤ ቡድን ወይንም ግለሰብ ላይ እርምጃ መውሰድ ነው» ይላሉ። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ አሁን የተቸገረው ክልሎችና ክለቦች እንዲሁም አካዳሚዎች የተባለውን መመሪያና ደንብ አንብበውና ተረድተው ባለመምጣታቸው መሆኑን ያብራራሉ።
«ፌዴሬሽኑ ቢያንስ ከስድስት ወር በፊት የውድድር ደንብ ይልካል፤ አንዱ ደንብ እድሜ ነው፤ ወጣት ላይ ሊሰለፍ የሚችል አትሌት እድሜው ከሃያ በታች የሆነ ከአስራ ስድስት በታች ያልሆነ በሚል አስቀምጠናል፤ ይሄን ተከታትሎ መስራትና ማስፈፀም የክልልና ክለቦች ኃላፊነት ነው፤ እኛ ስርዓት ዘርግተን ማወዳደር ነው፤ አሰልጣኞችን ማብቃት ደንብ ማዘጋጀት ነው፤ ክልሎች ራሳቸውን የቻሉ መንግስት ስለሆኑ ጣልቃ መግባት አንችልም፤ የቸገረን ይሄው ነው» የሚሉት አቶ ዱቤ ችግሩን ለመፍታት ከነዚህ አካላት ጋር መወያየት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
የእድሜ ጉዳይ ይህን ያህል አትሌቲክሱን ከተፈታተነ እግር ኳስ ላይ በአንፃራዊነት ለውጥ ያመጣው ወይንም ተስፋ የሰጠው የኤም አር አይ የህክምና ምርመራ አትሌቲክሱ ላይ ለምን ተግባራዊ አይሆንም? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዱቤ የኤም አር አይ ምርመራ ለመጀመር በቅድሚያ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (አይ ኤኤ ኤፍ ) መጀመር እንደሚኖርበት ያብራራሉ። ኢትዮጵያ ብቻ ይህን ምርመራ ተግባራዊ ብታደርግ ትርጉም እንደማይኖረው የሚናገሩት አቶ ዱቤ የዓለምን አትሌቲክስ የሚመራው አካል ሌሎች አገራት ምርመራውን እንዲጀምሩ ኢትዮጵያ የማትጀምርበት ምክንያት እንደሌለ ተናግረዋል።
የታዳጊ ወጣቶችን ውድድር አይ ኤኤ ኤፍ አንድ ጊዜ አካሂዶ መሰረዙን ያስታወሱት አቶ ዱቤ፤ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት የነበረው የእድሜ ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ አይ ኤኤ ኤፍ ታዳጊዎች ወደ ላይ መምጣት እንዳልቻሉ በጥናት ማረጋገጡ ነው። « አትሌቶች ልማት ላይ መሰራት አለበት፤ ተመሳሳይ አትሌት እያመጣን አገር አንለውጥም፤ አትሌቱ የሚሮጠው አቅም ባለው ወቅት ነው፤ በጊዜው ካልሮጠ ከሁለትና ሦስት ዓመት በኋላ ዋጋ አይኖረውም፤ ከስር እየተካን ካልሄድን ትርጉም የለውም፤ ከስር የሚመጣው ደግሞ ከታዳጊ ጀምሮ ወደ ወጣትና አዋቂ እያለ መምጣት ይኖርበታል፤ አትሌቱ ያለው ከታች ነው፡፡ እታች ወርዶ የሚሰራ ሰው ደግሞ የለም፤ ሁሉም ጊዜያዊ ውጤት ይዞ መሄድ እንጂ የነገን አያስብም፤ ያ ደግሞ የትም አያደርሰንም፤ ስለዚህ የአትሌት ልማት ላይ ካልተሰራ ወደ ፊት ትልቅ ችግር ያመጣል ብዬ ሰጋለሁ» በማለትም አቶ ዱቤ የችግሩን ስር መስደድ ይናገራሉ። ስለዚህም እንደ መንግስት ከላይ ጀምሮ በመነጋገር፤ የክልል መንግስታትም ጣልቃ በመግባት ሊያስቡበት እንደሚገባ ያስቀምጣሉ።
አትሌቶቻችን ሰንደቅ አላማችንን በዓለም ከፍ ከማድረግ በላይ በኢንቨስትመንት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውና ከዚህም በላይ የውጪ ምንዛሬ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ዱቤ፤ እንደነ አሜሪካና እንግሊዝ አትሌቲክሱን እያጠናከርን ከሄድን የአገሪቱ ዓመታዊ በጀት ግማሹን ድርሻ ሊወስዱ ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ በተገቢው እድሜ መስራት ወሳኝ ይሆናል። ዋናው የስፖርቱ አካል ወጣቱ ነው፤ ወጣቱን መያዝ የግድ ነው፤ ስለዚህ እንደ መንግስትም እዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ይላሉ።
የእድሜ ማጭበርበር ዞሮ ዞሮ መንስዔውም መፍትሄውም ክለቦች፤ ክልሎች፤ አሰልጣኞችና ራሳቸው ስፖርተኞቹ እንደሆኑ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ካገኘነው አስተያየት መረዳት ይቻላል። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ በእነዚህ ባለ ድርሻ አካላት ላይ ኃላፊነት ጥሎ መቀመጥ አይገባውም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩ እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ ካልመጣ ፌዴሬሽኑ ያልታመነበትን ውድድር በማከናወን ገንዘብና ጊዜን ከማባከን ይልቅ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጊዜ ወስደው ችግሮቻቸውን እስኪፈቱ ድረስ ውድድሮችን መዝጋት አማራጭ እንደሆነ የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው።

 

  የፌዴሬሽኑ የምርጫ ድራማ ነገ ይፈፀማል

 

ባለፈው ጥቅምት ወር መካሄድ የነበረበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንትና ስራ አስፈፃሚ ምርጫ ከእጩዎች ተገቢነት አንስቶ በተለያዩ ድራማዎች ታጅቦ ለአራት ጊዜ ቢራዘምም ነገ ድራማው የሚፈፀምበት እለት እንደሚሆን ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ባደረገው ስብሰባ የስራ አስፈፃሚዎች ምርጫ አካሄድ ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አልቀረም።
ፌዴሬሽኑን የሚመሩ አንድ ፕሬዚዳንት እና አስር የስራ አስፈፃሚ አባላትን ለመምረጥ ነገ በአፋር ክልል ሰመራ ላይ ቀጠሮ ተይዟል። የድራማው መሪ ተዋናዮችም በፕሬዚዳንታዊ ፉክክሩ የወቅቱ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻና አቶ ተካ አስፋው እንደሚሆኑ ይጠበቃል። የምርጫውን ሂደት እንዲያስፈፅሙ ሚያዚያ 27 በካፒታል ሆቴል በተካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡት አምስት አባላትን የያዘውና በአቶ አስጨናቂ ለማ ሰብሳቢነት የሚመራው የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመጨረሻዎቹ እጩ ተወዳዳሪዎች የፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ ዝርዝር እና ሌሎች የስራ ተግባራትን በማጠናቀቅ ከሃያ አራት ሰዓት ያነሰ ጊዜ የሚቀረውን ምርጫ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
አስመራጭ ኮሚቴው ከትናንት በስቲያ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ምርጫው በምን መልኩ ይደረግ በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት ሲደረግ በዋናነት የስብሰባው አጀንዳ የነበረው አስር አባላት የሚመረጡበት የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫው በምን መልኩ ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ ሁለት ሀሳቦች ተነስተዋል።
አንደኛው በየክልሉ አንድ ተወካይ ይመረጥ የሚለው ነው። ይህ ማለት ከአንድ ክልል አራት ሰው ቢወከል አንዱ ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው ብቻ ይግባ የሚል ሲሆን ይህ የሚፀድቅ ከሆነ አፋር፣ ደቡብ፣ ኢትዮ ሶማሌ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ በእጩነት የቀረቡት ተወዳዳሪዎች ያለምርጫ በቀጥታ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ይሆናሉ።
በሁለተኝነት የተነሳው ሀሳብ ደግሞ ለሁሉም (22) እጩ ተወዳዳሪዎች እኩል የማሸነፍ እድል የሚሰጠው ምርጫ ነው። በዚህ ሀሳብ ግለሰቡ ከየትኛውም ክልል የመጣ ቢሆን በምርጫው የተሻለ ድምፅ ካገኘ የኮሚቴው አባል መሆን ይችላል። አስመራጭ ኮሚቴው አባላት በሁለቱ ሀሳቦች ዙርያ ሰፊ ውይይት እና ክርክር አድርገው በመጨረሻም ከውሳኔ ላይ ሳይደርሱ ለትናንት በይደር ትተው ይታወቃል። ይህ ስብሰባ ትናንት ማተሚያ ቤት እስከ ገባንበት ሰዓት ድረስ ቀጥሎም ነበር። የምርጫው አስፈፃሚው ኮሚቴ በዚህ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ አዲስ አባባ ላይ የማይሰጥ ከሆነ ነገ ሰመራ ላይ በሚደረገው የምርጫ ጉባኤ ላይ በተሳታፊዎች በኩል ትልቅ የክርክር ርዕስ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ቦጋለ አበበ

 

Published in ስፖርት

ሰላም ሰላም! እንዴት ነን? እንዴት ከረምን? አለን ወይ? ሰዎች ከቆይታ በኋላ ሲገናኙ በሚያደርጉት የሰላምታ ልውውጥ ላይ የተለመደ ችው ይህቺ፤ «አለሽ?» ወይም «አለህ?» ጥያቄ አትገርማችሁም? አንዳንድ ሰው «አለሽ እንዴ?» ሲለኝ፤ «አልሞትሽም እንዴ?» የሚለኝ ስለሚመ ስለኝ ድንግጥ እላለሁ። ‹አለሽ?› ብሎ የሰላምታ ጥያቄ መኖር ነበረበት? ቢሆንም እንደዛ የሚለውን ሰው አልቀየምም፤ የሆነ ጊዜ አለመኖር ይኖራል የሚለውን አስባለሁ። እንጂ ለምን ልቀየም? አስቡት! አሁን ያስቀየማችሁን ሁሉ ተቀይሞ ለመኖር ይቻላል እንዴ? አስቡታ! ሁላችንም እርስ በእርስ እየተቀያየምን ነው፤ ሁሉም ሆድ ስለባሰው ምን ዓይነት ጉዳይ ማንን ሊያስቀይም ይችላል ብሎ መገመት ራሱ ከባድ ነው። «ለምን ‘ምን ሆነህ ነው ፊትህ የጠቋቆረው?’ ብለሽ አልጠየቅ ሺኝም?» ብሎ የተቀየመኝ ዘመድ አለ። እንደዛ በማለቱ ብቀየመው ትክክል መባል አልነበረብኝም? ትክክል ነበርኩ ግን አልተቀየምኩትም፤ ችላ ብሎ ማለፍን የመሰለ ምን አለ?
ብቻ ግን ‹አለሽ?› ሲሉኝ አለሁ እላለሁ፤ ሲባል ሰምቼ። አንዲት ጎረቤታችን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የልደ ታን ቡና እንድት ጠጣ ተጠርታ በተቀ መጠችበት፤ የቀረበውን የቡና ሲኒና ጀበና ተመልክታ፤ «ይህቺ ጀበና አለች እንዴ?» አለች። ‹ምን ማለቷ ነው? ጀበና ደግሞ የት ይሄዳል?› ሲል አስቦ የነበረው ሰው ሳቀ፡፡ «የት ትሄዳለች ብለሽ ነው?» አለቻት ሌላዋ ሳቋን ገታ አድርጋ፤ «አብለጭላጭና አብረቅራቂ የሆኑ የሴራሚክ ጀበናዎች በዝተውብኝ ይህቺን ረስቻት ነበር» ብላ መልሳ ሳቀች። አብዛኛውን የቡና ታዳሚ ግን ነገሩ እንደመጀመሪያው የሚያስቅ አልሆነለትም።
ጀበና ስል፤ መቼም ተብሎ ተብሎ የበቃው ነው፤ ግን እንደው ፍቀዱልኝና መለስ እንበልበት። የአገር ባህል ልብሳችንን አይታችኋል? «ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው» እንደሚባለው ይህቺ ቻይና ግን እያሳሳቀች የት ልትወስደን ነው? መቀየምስ ቻይናን ነው፡፡ እኛ ባለሀብቱን በማነቃቃት፣ በመደጎም፣ በማበረታታት፣ በማስቀደም፣ ተንጠባረርብን ብለን እድሉን በመስጠት፣ መሬታችንን በማስረከብ...ወዘተ ውጤታማ ያላደረግነውንና ያልሆነልንን ቻይና በአንድ ጀንበር ላፍ አደረገችው።
«ላፍ አርጋት!» የሚሉ ይመስለኛል በቋንቋቸው፡፡ ላፍ አድርገው እንዳይጨርሱን መፍራት ነው፡፡ በዛች ትንንሽ ዐይናቸው የማያዩት የለም ልበል? የአገር ባህል ልብስን ሺፎን በሚባለው የጨርቅ ዓይነት አትመው በትነውልናል። አለ አይደለ፤ እናቶቻችን ፊታቸው ተቀምጣችሁ የሆነ ሥራ የያዛችሁ እንደሆነ፣ ሁኔታችሁን ያዩና አያያዛችሁ ካላማራችው፤ ሳያስጨርሱ ከእጃችሁ ንጥቅ አድረገው ይሠሩታል። ቻይና አሁን ላይ ትዕግስቷ እልቅ ብሎ፤ «የማትሠሩበት ከሆነ እስቲ ወዲህ አምጡት» ብላም ይመስለኛል የወሰደችው።
ይህ ጉዳይ ከቻይና ጋር ያቀያይመናል፡፡ በዛ ላይ ብዙ የሽሮ ሜዳ ሰዎችን አሳስቧል። ይህ የቻይና ልብስ ገበያውን ሰብሮ በቅናሽ ዋጋ ስለሚገባ የብዙ ሸማኔዎችን ሥራና የሥራ ፍላጎት ሊያዳክም ይችላል። በተጓዳኝ ደግሞ ምስኪን፣ ሀብታም ለብሶት እንጂ የአገር ባህል ልብስን ወደሰውነቱ አስጠግቶ የማያውቅ፤ አንድ ብትኖረውም እንዴት ላጥበው ነው? የት ላስቀምጠው ነው? ወዘተ ብሎ የሚጨነቅ በቅናሽ ዋጋ ብሎም ብዙ ጥንቃቄ ሳያደርግ ሊለብሰው የሚችለውን ጨርቅ አግኝቷል፣ አምሳለ አገር ባህል ልብስ፡፡ ጎበዝ! ይሄ ነገር ማስታወቂያ መሰል እንዴ?
በአንድ ጎን በደኅና ጊዜ የአገር ባህል ጨርቅ ለሁሉም እንዲሆን አድርጎ መሥራት ሲቻል አለመሠራቱ ያበሳጫል፡፡ አንደኛ ልበሱ የክት ነው፡፡ ሲቀጥል ዋጋው የሚቀመስ መሆን ካቆመ ቆይቷል፡፡ እዩልኝ! ምርጥ ምርጡን ለህፃናት እንደሚባለው ምርጥ ምርጡን ለኤክስፖርት ነው እኛ’ጋ፡፡ ጥሩውን ነገር ለውጪ ገቢ ልከን እኛ ግን ቀሪውን፣ ገለባውን ነው የምንጠቀመው፡፡
በእርግጥ እንዲያም ሆኖ ቢያልፍልን ጥሩ ነበር፡፡ ይኸው አሁን ጭራሽ ለዳያስፖራ ተብሎ ዋጋው ከሌለው አገር ባህል ልብስ ኮፒ ተደርጎ ከቻይና ይመጣ ጀመረ፡፡ እሱስ በነጋዴው መፈረድ ከባድ ነው፤ የጥጡን የክሩን ዋጋ ማሰብ ነው፡፡ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ስሙ ይነሳል እንጂ እንደውም ቻይና የወሰደችው ነው የሚመስለኝ፤ ማን ያውቃል? እንጂ በጨርቃ ጨርቅ ላይ የሚሠራ አካል ካለ፤ ያም አካል ቻይናዊ ካልሆነ በቀር እንዴት ባህላዊ አልባሳት ላይ አልሠራም?
እኛ እንዲህ ነን፤ አለን እንጂ የለንም። በተለይ ቻይና? መንገድ ሠርቻለሁ ብላ ወስዳ እንዳትጨርሰን ያሰጋል፡፡ አንድ ጊዜ ለአንድ የመስክ ሥራ ወደአድዋ ከተማ መሄድ እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ከዛም አለፍ ብለን አክሱምን አይተን ጽዮንን ተሳልመን ስንመለስ ባዶ እጅ ላለመግባት ከአንዱ የባህል አልባሳት ቤት ገብተን ማየት መመራረጥ ጀመርን፡፡
አንድ እንደ በረዶ ነጭ የሆነ ነጠላ ተመልክተን ያስተናገደንን ሻጭ ብንጠይቅ ዋጋው ረከስ ያለ እንደሆነ ነገረን፡፡ ምነው ስንለው ለካ ከቻይና የመጣ ስለሆነ ነው፡፡ ስትጀምር እንግዲህ በነጠላ ነው የጀመረችው፤ ልክ በመሥሪያ ቤት ተጀምሮ በአገር እንደሚያልቅ ስርቆት፡፡ አሁን ያው በጉዳዩ ላይ ራሷን ብቁ አድርጋ ከተፍ አለች፡፡
የአገር ባህል ጨርቅና የሽመና ሥራ ከአኛ ጋር ስንት ዘመን ኖረ ? ግን ልክ ስንነጠቅ ነው የምንባንነው፡፡ ጤፍን አስታውሱ፤ ተቀማን ብለን ኡኡ ስንል ነበር፡፡ ከዛም ጭራሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ አእምሯዊ ንብረት ከሚባለው ጋር ይመዝገብልን፣ የእኛ መሆኑ ይታወቅ አልን፡፡ ጠለቅ ተብሎ ነገሩ ሲታይ ግን በገዛ አገሩ ላይ ጤፍ በክብር የሠፈረበት መዝገብ የለም፡፡ ሌሎች የእኛን እንዲያከብሩልን በድፍረት እንድንጠይቅ የሚያስችል አክብሮት እኛ ለራሳችን ነገር አልሰጠንም፡፡
ጤፍን ግን ቻይና እንዴት እንዳላየችው ይገርመኛል፡፡ ደቃቅ ሆኖባት አይሆንም መቼስ! ያው የእኔው ናቸው፤ እዛም ብሄድ የምበላው የጤፍ እንጀራ ነውና ጡር አለው ብላ ካልሆነ በቀር፡፡ ብቻ በዚህ አካሄድ አንዴ ዳሩ እንደተቀደደ ሰፌድ ድህነታችን መንገዱ ከፎተላታል፤ ያም ይሄም ለጥርሴ ለጥፍሬ እያለ ከሰፌዱ ሰበዝ እንደሚመዝ ሁሉ መዝዛ መዝዛ እንዳትጨርሰን፡፡ ከዛ ወይ ጠቅልላ ትመጣለች አልያም ጠቅልለን እርሷን እንሆናለን፡፡
ለአገር ባህል ልብሳችን ከልብስ ፋሽን ዲዛይነሮች ባሻገር ያገባኛል የሚል እንደሚኖር በተስፋ መጠበቅ ነው፡፡ እንጂ አትግዙ አይባል! እኔ በበኩሌ ‹ዋናው ባህላዊ ጨርቅ ውድ ሆኖብኝ ነው፤ አትግዛ ካልሽ ሙይልኝና የራሳችንን ልግዛ› ቢሉኝ መልስ አይኖረኝም፡፡ አቅምና ለአገር ባህል አልባሳት የሚራራ ልብ ያለው ይግዛ፤ በተረፈ ደስ እንዳለን፡፡
‹ቁርጥ የአገር ባህል ልብስ› እያለ ሰው በሚገዛቸውና ቻይና አትማ በምታስገባቸው ልብሶች ላይ ቀረጡን ከፍ አድርጎም ቢሆን ባህሉን መጠበቅ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ይህና ሌላም እርምጃ ሊወሰድ የሚችለው ታድያ ‹ያገባኛል› የሚል የመንግስት አካል ካለ ነው፡፡ በእርግጥ አለ…ያው ነገሩ ከዚህ በላይ ሳይገፋና የገዛ ልብሳችንን ቻይና ወደ አውሮፓ መሸጥ ሳትጀምር መንቃት ከቻለ ነው፡፡
ባህሉን በሚመለከት ባህልና ቱሪዝም፣ ደግሞ የጨርቅ ጉዳይ ነው በዛ ላይ ነጋዴው መጎዳቱ እይቀሬ ነውና ንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሥራ ያላቸው ሁሉ ባያረፍዱ ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ ከባሰ ለውጥ አናመጣም እንጂ እንቀየማቸዋለን፡፡ ቻይናም መቼም ‹መንገድ እየሠራሁ ምንአለ ይህን እንኳን ለቀቅ ብታደርጉ› ብላ ይሉኝታ ልታሲዘን ትችላለች፤ አብራን ኖራማ ይህን ሳትለምደው ትቀራለች? ብቻ ግን ብትቀየም ትቀየመን እንጂ በችርቻሮ ተወስደን ማለቅ የለብንም ባይ ነኝ፡፡ ደግሞ መንገዱን በነጻ አትሠራ፤ ከፍለን ነው፡፡
ውይ ሀሜት! ይህቺን ቻይና አማኋት አይደለ? ሞፈር ከሰው ደጅ ከቆረጠው ይልቅ ሞኝ የተባለው የጊቢው ባለቤት ነው ብዬ የእኛን ችግር ብጠቃቅስ ነበር ጥሩ የሚሆነው መሰለኝ፡፡ ይሁን! ለማንኛውም አለን ለማለት ነው፤ አንዱ ጤፋችንን ሌላው ጨርቃችንን ቢወስዱም፤ ባዶ ሆድ አንሆንም አንራቆትም ብለን በማሰብና በማመን አለን፡፡ ወርውረው እየጣሉብን ያለው በረጅም ገመድ ላይ ያለው ሸምቀቆ መቼ እንደሚቋጠርብን ባናውቅም አለን፡፡ የራሳችንን ነገር አስኮብልለው አስኮብልለው ወይ መጥታችሁ ውሰዱ ወይም አስገቡን ብለው አንድ ቀን ያስጨንቁን ይሆናል ብለን ብናስብም አለን፡፡ በችርቻሮ ተሸጠን ተሸጠን ተሸጠን እንዳናልቅ ብንሰጋም አለን፡፡ ያኑረን፤ ሰላም!

ሊድያ ተስፋዬ

Published in መዝናኛ
Saturday, 02 June 2018 19:16

መብት አስከባሪዎች

የሴቶችን መብትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግሥት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ቢሆንም በዛው መጠን ደግሞ በተለያየ መንገድ ጥቃትና በደል የሚፈጸምባቸው ሴቶች አሉ፡፡ እየደረሱባቸው ካሉ ችግሮች መካከል ፆታዊ ትንኮሳ፤ የቤተሰብ ውርስ አለማግኘት፤ ተገዶ መደፈር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ሴቶች እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች ሲያጋጥ ማችው ጉዳያቸውን ተቀብሎ መብታቸውን የሚያስከብርና ተጠቃሚነታቸው ሊያረጋግጥ የሚችል አደረጃጀት ከወረዳ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ጀምሮ እስከ ሚኒስቴር ደረጃ ተቋቁሟል፡፡ ሴቶች መብቶቻቸው እንዲከበርና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚሰሩ ተቋማት ሴቶችን ምን ያህል እያገዟቸው ይገኛሉ? ሴቶቹስ በትክክል ተጠቃሚ ሆነዋል የሚለውን አብይ ጥያቄ ለማየት ሞክረናል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሸዋዬ አስፋው፤ ከባለቤታቸው ጋር ተጣልተው መፍትሄ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት ቢሮ የህግ አማካሪ ክፍል እንደሄዱ ይናገራሉ፡፡በወቅቱ ከባለቤታቸው ጋር ለተፈጠረው አለመስማማት የህግ አማካሪ ክፍሉ ስማቸውን ወረቀት ላይ መዝግቦ «ጉዳዩ ወደሚመለከተው አካል እንልኮታለን» ከሚል ምላሽ በስተቀር መፍትሄ አልሰጣቸውም ፡፡ ይህ አካሄድ ተስፋ እንዳስቆ ረጣቸው ይናገራሉ፡፡
የሴቶችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የተቀመጠ አካል ሴቶችን እስከ መጨረሻው ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
«ነፃ የህግ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ የሚሄዱ ሴቶች በኢኮኖሚ ደካማ በመሆናቸው ችግራቸው ከግንዛቤ ገብቶ ነጻ የህግ ድጋፍ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ወንዶችም እንደነዚህ ዓይነት ሴቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱት አቅም ስለሌላቸው ወደፍትህ አካል አይሄዱም ብለው በማሰብ ነው»ይላሉ፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ የህግ አማካሪ ወይዘሪት ታሪኳ መብሬ እንደሚሉት በወረዳው በማንኛውም መንገድ በደል ደርሶባቸው ለሚመጡ ሴቶች የህግ ማማከር እና ነጻ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ለበርካታ ሴቶች የምክርና ነፃ የህግ ድጋፍ እንዲያገኙም ለአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ደብዳቤ ይፃፍላቸዋል፡፡
ብዙ ጊዜ ወደ ወረዳ የሚመጡት ሴቶች የልጅ የማንነት ጥያቄ ይዘው ነው።በመሆኑም የህግ አማካሪዎች በቅድሚያ የልጁን አባት በማስጠራት ልጁ የሱ ከሆነ የማሳመንና የማስማማት ሥራ ይሰራል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ በህግ እንዲታይ ይደረጋል፡፡ በዚህም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የዘረመል ምርመራ (ዲ ኤን ኤ) እንደሚመረመር ተደርጎ የልጁ ማንነት እንዲታወቅ እስከማ ድረግ የሚደርስ ድጋፍ ይሰጣል ፡፡
የባልና ሚስት ጸብ፤የውርስ ጥያቄ፣ በሴቷ ላይ የሚፈጸም ወንጀል በስፋት በወረዳው ሴቶች ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮች ናቸው፡፡
በ2010 ዓ.ም ብቻ ከ50 በላይ ሴቶች በተለያዩ ችግር ምክንያት ወደ ወረዳ ነፃ የህግ አገልግሎትና ምክር ለማግኘት መምጣታቸውን ይናገራሉ። ወረዳው ከእነዚህም መካከል የ10 ሴቶችን ጉዳይ ተከታትሎ መፍትሄ እንዳገኙ አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ሴቶች ማህበር የፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሪት እየሩስ ሰለሞን እንደምትናገረው ማህበሩ የሴቶችን መብት ለማስከበር ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲያከናውን ቋይቷል፡፡ከነዚህም ውስጥ ለሴቶች ነፃ የህግ ድጋፍ መስጠት አንዱ ነው፡፡ ከተመሰረተ ጀምሮ ከ170 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሴቶች የህግ ድጋፍ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
ሴት ብቻ ሆና ችግሯን ይዛ ከመጣች በማህበሩ የህግ ባለሙያዎች አገልግሎት እንድታገኝ ይደረጋል። በቤተሰብ ህግ ጉዳይ፤ በውርስ፣ በንብረት ክፍፍልና በወንጀል ጉዳዮች ችግር የገጠማቸውን ሴቶች ማህበሩ አዲስ አበባ ዋናው መስሪያ ቤት እና ክልል ባሉት ስድስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አማካይነት አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ ነው፡፡
እንደ ወይዘሪት እየሩስ ገለፃ ማህበሩ የቤተሰብና የወንጀል ህግ እንዲሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ቀደም ብሎ ያለው የቤተሰብ ህግ ለባል ብዙ መብቶችን የሚሰጥ ነው፡፡ ሚስቱን የመቅጣት ኃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ግን ሴቶችን የተሻለ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ከዚህም በሻገር በወንጀል ህጉ ህግ ሆነው ያልተካተቱ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡
አብዛኛው ሴቶች ከባለቤታቸው የህጻናት ቀለብ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ ወደ ማህበሩ የህግ ድጋፍ ለማግኘት እንደሚመጡ ያብራራችው እየሩስ፤ ማህበሩ አብዛኛውን ጊዜ ሴቷ አባቱ ነው ብላ የምታስበውን ሰው ጠርቶ የማስማማት ሥራ ይሰራል፡፡ ጉዳዩ በዚህ ሂደት የማያልቅ ከሆነ የቀለብ ገንዘብ እንዲከፍል አሊያም ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄድ እና ዲኤን ኤ ተመርምሮ የልጁ አባት እንዲታወቅ ነጻ የህግ ጠበቃ ያቆ ምላቸዋል፡፡በዚህም ሁኔታ ማህበሩ በርካታ የቀለብ ጥያቄ ያላቸውን ሴቶች እያስተናገደ ነው፡፡
ማህበሩ በቀን በዋናው ጽህፈት ቤት ብቻ ከሰላሳ በላይ ሴቶችን ያስተናግዳል። ከነዚህም ውስጥ አስራ አምስት ያህሉ የቀለብ ጥያቄ የሚያቀርቡ ናቸው፡፡
ወደ ማህበሩ ከሚመጡ ጉዳዮች መካከል 80 በመቶ ያህሉ የባልና ሚስት አለማስማማት ነው። በመሆኑም ቤተሰብ ትልቅ ተቋም እንደ መሆኑ መጠን ማህበሩ ባለ ትዳሮችን የማስ ማማት ሥራ በሥፋት በመስራት ላይ ይገ ኛል፡፡
በዋናው ጽህፈት ቤት ብቻ ከሀያ በላይ ነጻ የህግ ድጋፍ አገል ግሎት የሚሰጡ ጠበ ቆች እንዳሉ የተናገ ረችው እየሩስ ውስብስብ ጉዳይ የገጠማቸ ውንና ሴቶች በራሳቸው ተከራክረው ሊያሸንፉ አይችሉም ተብለው የሚታሰበውን ችግር ጠበቃ እንዲ ያዝላቸው ይደረጋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ የህግ አማካሪና የስልጠና ባለሙያ አቶ ሙላት ደንብሌ በበኩላቸው ቢሮው በአዋጅ ቁጥር35/2004 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ጥቃት ደርሶባቸው የሚመጡ ሴቶችን ነፃ የህግ እና የምክር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ይገልፃሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት ተበድለው ወደ ቢሮው ለመጡ ሴቶች ነጻ የአቤቱታ ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ የማህበራዊ መጠለያ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የቀለብ ጥያቄ ለሚያቀርቡ ሴቶች ቀለብ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህጻናት ፍትህ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ልጆቹ ቀለብ እንዲያገኙ ያደረጋል፡፡ በንብረት ክርክርና ተዛማች ጉዳዮች ጠበቃ ቀጥረው መከራከር ለማይችሉ ደካማ ሴቶችና አረጋዊያን ከቀበሌያቸው ደሃ መሆናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ አጽፈው ካመጡ በደብዳቤው መሰረት ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የጥብቅና ዳይሬክቶሬት ደብዳቤ ተጽፎ ጠበቃ ተቀጥሮላቸው ጉዳያቸውን እንዲ ታይላቸው ይደረጋል፡፡
በትዳር ህይወት ውስጥ ግጭት ተፈጥሮ ወደ ቢሮ የሚመጡትን የማስማማት ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ሙላት በዚህም ከተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ጋር በማዛመድ ትዳር ማለት ምን ማለት እንደሆነ እውቀት እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ በግጭት ወቅት ንብረት የማሸሽ እና ታማኝ ያለመሆን ችግሮች አሉ፡፡ በዚህም ሴቷ ጉዳዩን በራሷ አቅም ተከራክራ ልትወጣው የማትችል ሲሆን ቢሮው በጠበቃ እንድት ከራከር ያደርጋል፡፡
‹‹አዲስ አባባ በርካታ ሴቶች ከክልል ጭምር መጥተው የሚኖሩባት ከተማ እንደመሆኗ መጠን ሴቶቹ የኢኮኖሚ ጥገኛ ናቸው፡፡ በቂ የትምህርት ዝግጅት የላቸውም፡፡ ወደ ከተማዋ ሲገቡ በቂ ግንዛቤ የላቸውም፡፡ አዲስ አባባ ላይ ሠርቼ ብር አገኛለሁ እንጂ ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አያስቡም።›› የሚሉት አቶ ሙላት በዚህም የተነሳ በቀላሉ ይታለላሉ፡፡ እርግዝና ከተከሰተ በኋላ ወንዱ ጥሎ ይጠፋል፡፡
ሴቶቹ የኢኮኖሚ ጥገኛ በመሆናቸውና አገሩን በሚገባ ባለማወቃቸው የሚፈጠርባቸው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ብቻቸውን ልጅ ለማሳደግ ይገደዳሉ።
በተለይ በቀን ሥራ ላይ ሴቶቹ ሲሰማሩ በወንዶቹ የመታላል ሁኔታ ይገጥማቸዋል። በዚህም እርግዝና ይከሰታል። የእርግዝና መከሰቱን ወንዶቹ ሲያውቁ የመሸሽ ነገር ይኖራል። አድራሻቸውን ይቀይራሉ። በዚህ ወቅት ሴቶቹ የተሟላ መረጃ ስለማይኖራቸው የሰውየውን ስምና አድራሻ ስለማያቁ በህግ ጉዳዩን ለመያዝ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው አባት አልባ ህጻኖች በመሆናቸው መንግሥት ድጋፍ እያደረገላቸው ነው፡፡በአሁኑ ወቅት በቢሮው ስር በሚገኝ የጨቅላ ህጻናት ማሳደጊያ ‹‹ክበበ ፀሐይ›› በሚባለው ድርጅት ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ህጻናት እያደጉ ነው፡፡
ከፆታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ አብዛኛው ችግር እየተፈጸመ መሆኑን ያስረዱት አቶ ሙላት ቢሮው በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወር ውስጥ በአጠቃላይ 68 ሴቶች አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

ሰብስቤ ኃይሉ

 

 

Published in ማህበራዊ

ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ ዴሞክራሲያዊነት እና እኩል የመልማት ተሳትፎ አስፈላጊነት የሚነሳበት ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህንን ለማስፈፀም አቅም፣ ብቃትና ፍጥነት በሚጠይቅበት በዚህ ወቅት አገሪቱን መርቶ ለተሻለ ውጤት የሚያበቃ አመራር ያስፈልጋታል፡፡ ለዚህ የሚመጥን አመራር ሲሾም የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምድ እንደተጠበቁ ሆነው ተሿሚ የተለየ ሰብዕና እንደሚያስፈልግ ይታመናል፡፡

ከዛሬው እንግዳችን የህግ ተመራማሪው አቶ ዘፋኒያህ አለሙ ጋር በሹመት አሰጣጥ መርህና በአተገባበሩ ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሹመት ወይንም ደግሞ ኃላፊነት የሚሰጠው እንዴት ነው?
አቶ ዘፋኒያህ፡- ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ደረጃ ስለሹመት ወይም ስለአመራር ስናወራ በቅድሚያ መታየት ያለበት በአገሪቱ ያለው የአመራር ሥርዓት ነው፡፡ ሹመት አገሪቱ የምትመራበት ሥርዓት፣ የምትከተለው ርዕዮተ ዓለም፣ በሕዝቦቿ ሁለንተናዊ እምነትና አገራዊ ስሜት ይመራል፡፡ አንድ ሰው የሚሾመው አንድን አላማ ለማስፈጸም ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡ በተጨማሪም ጉዳዩን በትክክል ያስፈጽምልኛል፣ ራሱንም መርቶ ሌሎችን ያስከትላል፣ የተሰጠውን ፖሊሲ የመምራት፣ የማስተባበርና የማብቃት ክህሎትና ብቃት አለው ተብሎ ሲታመን ነው፡፡
የሹመት ብቃት የትምህርት ዝግጅት ብቻ አይደለም፡፡ የአመራር ብቃትን መሰረት ያደርጋል፡፡ የአሰራር፣ የአተገባበር፣ የአፈጻጸም፣ ጥሩ ስብዕና እና ስነ ምግባር የመላበሰ ጉዳይም ነው፡፡ ሹመት አመራር ላይ መቀመጥ እና አንድን ጉዳይ እንዲመራ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንድን ግለሰብ አመራር ለማድረግ ከሌሎች የላቀ ችሎታ ያለው፣ የሌሎችን ፍላጎት ቀድሞ መረዳት የሚችል መሆን ይጠበቅበታል፡፡
ሃሳቦችን የማመንጨት፣ የፈጠራ ችሎታና የአመራር ጥበብ የተላበሰ ሊሆንም ይገባል፡፡ እንዲሁም የሚመራውን ህዝብ ቀድሞ የመረዳት ችሎታ የተካነና መፍትሄ የማፈላለግ ችሎታ ያለው መሆን አለበት፡፡
የሚሾም ሰው መሪ የሚሆን ነውና በላቀ ሁኔታ ጥልቅ የአስተሳሰብ ክህሎት ተላብሶ፣ ኃይል ፈጥሮና አሰባስቦ የሚመራውን ህዝብ ወደ ታለመው ግብ ለማስገባት የሚያስችል ብቃት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡
በተቋም ደረጃ ደግሞ የተቋሙን ራዕይ፣ ተልዕኮና የተቀመጡ አላማዎችን ሙሉ በሙሉ የማስፈጸም አቅሙ በትክክል የተገነባ መሆኑ መታየት አለበት፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ሲታይ አገሪቱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትከተል፣ ላለፉት 27 ዓመታት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትመራ አገር ናት፡፡ ስለዚህ ይህ ሲፈጸም በአገሪቱ የፌዴራልና የክልል የሥልጣን ክፍፍሎች አሉ፡፡ ከእነዚህ የጎንዩሽ የስልጣን ክፍፍል ደግሞ አስፈጻሚ፣ ህግ አውጪና ህግ ተርጓሚ አካላት አሉት፡፡ እዚህ ላይ የፌዴራሉን ሹመት ብቻ ወስደን ስናይ የፌዴራሉ ህገ መንግሥት አጠቃላይ ለአገሪቱ ተፈጻሚ ቢሆንም ሹመት መነሻው ህገ መንግሥቱ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህገ መንግሥቱ ስለሹመት ምን አስቀምጧል?
አቶ ዘፋኒያህ፡- የተዘረጋው የፖለቲካና የህግ ሥርዓት የሚመራው ሹመት ማን እንደሚመራ እና እንደሚያጸድቅ ያሳያል፡፡ በህገ መንግሥቱ መሰረት ትልቁ የሥልጣን አካል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ስለዚህ ሁል ጊዜ ሿሚው፣ አጽዳቂው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ሁሉም የስልጣን ምንጭ በኢትዮጵያ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዝቦች ናቸው፡፡ ይህንን ሥልጣናቸውን ደግሞ ተግባር ላይ የሚያውሉት አንደኛው በተወካዮቻቸው አማካኝነት ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸው አማካኝነት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በቀጥታ በሚያደርጉት ተሳትፎ ነው፡፡ ስለሹመት ሲነሳ በተወካዮቻቸው አማካኝነት የሚተገበሩ ሥራዎችን ለማከናወን ሲባል የሚሰጡ ሹመቶችን ነው፡፡
ህግ አስፈጻሚው አካል ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ አቅጣጫዎችንና መስመሮች ወደ መሬት ለማውረድ ይሠራል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በህዝብ መመረጥ ግዴታ ነው፡፡ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ለመመረጥ ሲቀርብ የያዛቸውን ፖሊሲዎች፣ እቅዶች፣ ተግባራት እና ታላላቅ ሃሳቦች ወደ መሬት አውርዶ ተግባር ላይ ለማዋል መንግሥት ማዋቀር ይጠይቀዋል፡፡ መጀመሪያ መንግሥቱን ሲያዋቅር የሚያስቀድመው አስፈጻሚውን ነው፡፡ በመቀጠል ህግ አውጪና የዳኝነት አካሉ ይዋቀራል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመቀጠልም የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ሹመት ይፈልጋሉ፤ በመሆኑም የሚመራቸው አካል ይሾማል፡፡ እነዚህ የሚመጡት ህገ መንግሥቱ አንቀጽ 74 እና 81 ላይ እንዳስቀመጠው በኢትዮጵያ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሹመት አሰጣጥን ተመስርተው ነው፡፡ በምርጫ ያሸነፈው ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች የፌዴራሉን መንግሥት ይመሰርታሉ፡፡ አሁን ባለው ልምድና አሰራር መሰረት የአሸናፊው ፓርቲ ሊቀመንበር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ይሰየማል፤ ይህ ትልቁ ሹመት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥትንና የሚኒስትሮች ምክር ቤትን የሚመሩ፣ የአገሪቱን ጦር ኃይል የሚያዝዙ፣ የአገሪቱ ርእሰ መስተዳድር ሆነው የሚያገለግሉትን ባለሥልጣናቱን ይሰይማሉ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ሁሉም ሹመት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይወርዳል፡፡ በመጀመሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል በመምረጥ ወይም ለሥራው ብቃት ያላቸውን ግለሰቦች በመመልመል እርሳቸውን ለሰየመው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ያጸድቃሉ፡፡
ኮሚሽነሮች፣ ዋና ኦዲተር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንትንም በተመሳሳይ መልኩ አቅርበው ያሾማሉ፡፡ ከህገ መንግሥቱ በመነሳት ደግሞ ሌሎች ሹመቶች አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን ካዋቀሩ በኋላ ሚኒስትር ዴኤታዎችና በአጠቃላይ የመንግሥትን ቅርጽ ለማስያዝ ከካቢኔያቸው ውጪም ሹመት ይሰጣሉ፡፡ ዳኞችም የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ነው፡፡ በህገ መንግሥት እውቅና የተሰጠው እና በአዋጅ የተቋቋመው የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ዳኞችን መልምሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀርባል፡፡ እስካሁን የተመለከትናቸው ከፖሊሲ አፈጻጸም፣ ከህገ መንግስት፣ ከስትራቴጂና የፖለቲካ ብቃትን በሚጠይቁ አሸናፊ ፓርቲና መንግሥት ሙሉ በሙሉ በሚያዋቅርበት መንገድ የሚሰጥ ሹመት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ አሁን ባለው የመንግሥት ሥርዓት መሰረት የሚሾሙ ሰዎች የሚመረጡት እንዴት ነው?
አቶ ዘፋኒያህ፡- አንድ አገር የሚመራው በሚከተለው የፖለቲካ ሥርዓት አማካኝነት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት በተረጋገጠበት፣ ዴሞክራሲ ወሳኝ በሆነበት፣ እኩል የልማት ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ በሆነበት አቅም፣ ብቃትና ፍጥነት በሚጠይቅበት ወቅት ላይ ያለች አገር ናት፡፡ ሹመት ሲነሳ አንድ ግለሰብ በግላዊ ታሪኩ (CV) ተወዳድሮ የሚቀጠርበት አይደለም፡፡ የተለየ ብቃት ያስፈልገዋል፡፡ የትምህርት ዝግጅት፣ የሥራ ልምዶች እንደተጠበቁ ሆነው ተሿሚ ለመባል የተለየ ስብእና ሊኖረው ይገባል፡፡ ፓርቲው የሚመለምላቸው አካላት ያሸነፈበትን ፖሊሲ፣ ፖለቲካዊ አመለካከት ወደ መሬት ማውረድ የሚችሉ አካላትን ነው፡፡
ፖለቲካ ሁል ጊዜ የለውጥ ማዕበልን የሚመራ ነው፡፡ ስለህዝብና ስለመንግሥት አስተዳደር የሚጨነቅ አስተሳሰብ ማለት ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ ይዞ የመጣ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በትክክል የሚፈጽሙለትን ማዋቀር አለበት፡፡ የሚሾማቸው ሰዎች ይህንን መስፈርት ማሟላት አለባቸው፡፡
የተለያዩ አገራት የተለያዩ ልምዶች አሏቸው፡፡ ምስራቅ እና ምእራብ አገራት አስተሳሰባቸው፣ የሚመሩበት ርዕዮተ ዓለም የተለያየ ነው፡፡ ዴሞክራሲን በምርጫ ብቻ የሚያምኑ እና ዴሞክራሲን የልማት መሳሪያ አድርገው በሚያምኑ አገሮች መካከል ልዩነት አለ፡፡ ስለዚህ ብቃት ላይ ይመሰረታል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው መሪ ድርጅትም በተለያየ አጋጣሚ እንደሚገልጸው ሲሾም የሚከተለው መንገድ፣ እቅዶቹንና ፕሮግራሞቹን ህዝብ አምኖ በመረጠው ልክ ሊፈጽሙለት የሚችሉ ብቃት ያላቸው ሰዎችን ነው፡፡
በድርጅቱ እንደሚታወቀው ሶስት አይነት የአመራር ደረጃዎች አሉ፤ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ጀማሪ፡፡ ለሹመት የሚመጡትም እነዚህ ናቸው፡፡ ከድርጅቱ ውጪ ቢሆኑም ይህንን ማለፍ አለባቸው፡፡ ወደ እዚህ የሚያመጣቸው ያላቸው ልዩ ተሞክሮ ነው፡፡ በየደረጃው የሚገቡት የተለያየ ደረጃ ያላቸው ናቸው፡፡ ጀማሪ አመራር የቀበሌ፣ የዞን፣ የኤጀንሲ አመራሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መካከለኛ አመራሮች ደግሞ ችሎታቸው የአገሪቱን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመፈጸም በሥልጠና ያለፈ፣ የቀለም ትምህርቱም የተሻለ ሊሆን ይገባል፡፡ ከፍተኛ አመራር የሚባሉት ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎችን ሲሆን፤ እነዚህ ፖሊሲ በማመንጨት ስልታዊ አመራር መስጠት የሚችሉ ናቸው፡፡
ከፍተኛ አመራር የአገሪቱን ቁልፍ የአመራር ቦታ መያዝ የሚችል፣ ለእዚህም ብቃቱ የተረጋገጠ፣ አገሪቱ የምትመራበትን ልማታዊ እና ፖለቲካል ኢኮኖሚ ጠንቅቆ ያወቀ፣ ይህንን ለማስፈጸምም የአመራር ጥበብ የተካነ፣ እነዚህን ወደ ተግባር ለመለወጥ የፈጠራ ችሎታው እጅግ የላቀ ሊሆን ይገባል፡፡ የህዝብ ጥያቄዎችን የሚያነፈንፍና ወዲያው መልስ የሚሰጥ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ የሚችልም እንዲሆን ይጠየቃል፡፡ እንዲሁም ተለዋዋጩን ዓለም መተንበይ የሚችል፣ ጥልቅ የአስተሳሰብ ክህሎት ያለው፣ ስትራቴጂያዊ አመራር መስጠት የሚችል አመራር መሆንም ይኖርበታል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አመራሮች ስትራቴጂያዊና ስልታዊ፣ በብቃታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው የላቁ ናቸው፡፡ የሌሎቹ ፓርቲዎች አሸናፊ ሆነው በተግባር ሲመጡ የሚታይ ነው፡፡ መሪው ድርጅት ሲያቀርብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የሚታዩት የድርጅቱንና አገሪቱ የምትከተለውን ፖለቲካል ኢኮኖሚ በትክክል መተግበር የሚችሉ መሆናቸው መታየት ይኖርበታል፡፡ ድርጅቱ እነዚህን ብቃት ያላቸው አመራሮችን ማውጣት የሚችል ተቋም አቋቁሟል፡፡ ተቋሙ ወደፊት እየተደራጀ ሲሔድ በየትኛውም ደረጃ ያለ አመራር ከመሾሙ አስቀድሞ በተቋሙ ሥልጠና ማለፍ አለበት፡፡
ሹመት በኢትዮጵያ በዘፈቀደ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ዳኛ ለመሆን መስፈርቱን ከማሟላት አንስቶ የጽሁፍ ፈተናውንና የቃል ፈተናውን ማለፍ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ህዝብ የሚሰጠው አስተያየት ለተሿሚው ወሳኝ ነው፡፡ ሚኒስትር ለመሆንም በሶስት ደረጃ የተከፈሉትን የአመራር ብቃት መላበስ ይጠይቃል፡፡ ዋና ኦዲተር ለመሆንም ቦታው በሚጠይቀው ልክ መለካት ይጠበቃል፡፡ የካቢኔ ቦታዎች በአብዛኛው የሹመት ቦታዎች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወቅቱ የሚጠይቀውን የአመራር ክህሎት፣ የዳኝነት አሰራር በትክክል ስለመተግበራቸው ቁጥጥር የሚደረግበት ሥርዓት ምን መሆን አለበት? በአገራችን ያለውን አሰራሩ እንዴት ያዩታል ?
አቶ ዘፋኒያህ፡- ከላይ አንስተን የተነጋገርነው መርሁን ነው፡፡ ኢትዮጵያ መርህ አላት፡፡ የዳኞችን አሿሿም አሰራሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አገሪቱ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘች መሆኑን ያመለክተናል፡፡ በተለይ የምትመራበት የፈጠነ ፍትህ፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ እና የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ግዴታዬ ነው ብላ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ይህ ካልሆነ አደጋ ይገጥመኛል ብላ እየተጋች ያለች አገር ናት፡፡ ስለዚህ እስካሁን ተፈጽሞ ነበር ወይ? ብለን ብንጠይቅ ብዙ ቅሬታ የሚቀርብበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ሙሉ ለሙሉ ተተግብሯል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱ ተዘርግቷል፡፡ በተለይ ተጠያቂነትና ግልጽነት እንዲሰፍን በተለያየ መንገድ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ዳኝነት ላይ በተለያየ መንገድ ተጠያቂነት መኖሩን ማየት ይቻላል። ከዛ ውስጥ አንዱ ይግባኝ ነው፡፡ ሥነ ምግባር ሁለተኛው የቁጥጥር መለኪያ ሲሆን፤ የህዝብ አስተያየትም እንደ መመዘኛ ይቀመጣል፡፡ ህዝቡ አለመርካቱ በራሱ የቁጥጥር ሥርዓት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ መብቱን ጠያቂ ህዝብ ተፈጥሯል፡፡ ዛሬ ህዝቡ አቤት ያለውን ጉዳይ ካልተመለሰለት ምን እያደረገ እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ አብዛኛው ህገ መንግስቱ ያስቀመጠው የተለያዩ የአሰራር ዘዴዎች ባለመተግበራቸው ምክንያት የሚፈጠሩ አንዳንድ ችግሮች አሉ፡፡ መንግሥትም የተቀመጡ አሰራሮች በትክክል አለመተግበራቸውን አምኗል፡፡ ይህ የሚያሳየው በአገሪቱ ተጠያቂነት ቅርብ መሆኑን ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተገነባው ሥርዓት የትኛውም የተልፈሰፈሰ መንግሥት መተኛት የማይችልበት መሆኑን ነው፡፡ በህዝቡ በኩል ጠያቂነት፤ በመንግሥት በኩል ደግሞ ተጠያቂነት ሰፍኗል ተብሎ ይታሰባል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያሳየችው ለውጥ አንድ ምስክር ነው፡፡
ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የፍትህ አሰጣጥ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል እንደገጠመና ህዝብም እንዳልረካ መንግስትም አምኗል፡፡ የህግ የበላይነት ሙሉ ለሙሉ ሰፍኖ ዴሞክራሲ ተረጋግጦ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የበለጸገ ማህበረሰብ በመገንባት ረገድ ቀዳሚ ሚና መጫወት የነበረበት ፍርድ ቤት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህዝቡ ዛሬ መንግስት ተመስርቶ ነገ ሊያፈርሰው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ህገ መንግስቱ መንግስት ፖሊሲ ነድፎ ህዝቡ የሚጠይቃቸውን መልሶ በህዝቡ ፍላጎት ልክ መሄድ እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ ይህ የለውጥ ሃዋርያ የሚባለው የህገ መንግሥት አይነት ነው፡፡ ተጠያቂነቱ በመንግሥት ከተዘረጋው በተጨማሪ ህዝብም በቀጥታ የሚጠይቅበት መንገድ ያለው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተሿሚዎች የዕድሜ ገደብ አለመቀመጡ የራሱ ተጽእኖ አለው፡፡ አንድ ቦታ በመቆየታቸው የመላመድ፣ ለተተኪዎችም ያለመልቀቅ ችግር አለ፤ ይህንን እንዴት ያዩታሉ?
አቶ ዘፋኒያህ፡- አንድ ፓርቲ ለረጅም ጊዜ ሊመረጥ ይችላል፡፡ እንደየአገሩ ሥርዓት ይለያል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የምትመራው በፓርላሜንታዊ የመንግሥት ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ አይነት ሥርዓት ደግሞ አንድ ፓርቲ በመንግሥትነት ለ50 እና ለ60 ዓመታት ሊመረጥ ይችላል፡፡ በዚህ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲው ሰዎች ጥንካሬያቸው እንዳለ ሊቀጥልና ረጅም ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ መታየት ያለበት መቆየት ስላለባቸው ሳይሆን ለተሿሚዎቹ መቆየት ዋስትና የሚሆነው ብቃታቸው መሆኑን ነው፡፡ በሹመት ደረጃ ሲታይ ዕድሜው አምስት ዓመታት ነው፡፡ ግን ፓርቲው ድጋሚ ከተመረጠ የመቀጠል ዕድል አላቸው፡፡
ፓርቲው የሚመረጠው ውጤታማ ስለሆነ ነው፡፡ ለውጤቱ አስተዋጽኦ ያደረጉ አባላት ባደረጉት አስተዋጽኦ ምክንያት ይቀጥላሉ፡፡ ሥርዓቱ የሚፈቅድላቸው ውጤታማ እስከሆኑ ድረስ ብቻ ነው፡፡ አንድ አገር የሚያድግበት የተለያዩ መለኪያዎች አሉት፡፡ ነጻ ገበያ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ብቃት፣ ተግባራዊነት፣ የህግ የበላይነት፣ ሰላም እና ትምህርት ይጠቀሳሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ብቃት ዋናው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር ብቃት ተገንብቶ አላለቀም፡፡ አንድ ሰው ሥልጣን ላይ የሚቆየው ተሿሚ ሲሆን ነው፡፡ ረጅም ጊዜ በሥልጣን የመቆየት ዋስትናው ደግሞ ብቃቱ ነው፡፡
ሹመት ዋና ዓላማው የህዝብ ፍላጎት ማርካት፣ በህገ መንግሥቱ የተቀመጡ መርሆዎችን መተግበር ነው፡፡ መነሻው ብቃት ሊሆን ይችላል፡፡ ብቃት መለኪያ አለው፡፡ ተቆጥሮ ይሰጥሃል ቆጥረህ ትመልሳለህ፡፡ ሹመኛ የተቀመጠበት ወንበር አምስት ዓመትም ላይቆይበት ይችላል፡፡ የመቆየቱ ዋስትና ውጤቱ ብቻ ነው፡፡ በህግ መገደብ ብቻ ሳይሆን ብቃት ይወስነዋል፡፡ ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ የሥልጣን ጊዜ ሁለት የምርጫ ዘመን እንደሚሆን ነው፡፡ ይህ ይፈጸማል ብለን እናስባለን፡፡ የሚኒስትሩንም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትርን የሹመት ዘመን ሁለት የምርጫ ዘመን ሆኖ በህገ መንግሥት ውስጥ ሊካተት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዓለም አቀፍ ተሞክሮ በተሿሚዎች የዕድሜ ገደብን አስመልክቶ ያስተዋሏቸው ነገሮች ምን ይመስላሉ?
አቶ ዘፋኒያህ፤ አንዳንዶቹ የሚገድቡ አሉ፤ የማይገድቡ አገራትም አሉ፡፡ ለምሳሌ የዴሞክራሲ ቁንጮ የምትባለው አሜሪካን አሁን የሚመሯት ፕሬዚዳንት ሥልጣን የያዙት በ71 ዓመታቸው ነው፡፡ በአሜሪካ በዕድሜ ከፍ እያልክ ስትሄድ ለህዝብ የምታስብበት ወርቃማ ዘመን ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ወደ ምዕራብ አገራት ስንሄድ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ፣ ልማታዊ አገራት የተሿሚዎችን እድሜ ይገድባሉ፡፡ ለፓርቲያቸው አባል ሲመለምሉም የሚቀበሉት ፈትነው ብቃትን አረጋግጠው ነው፡፡
አንድ የቻይና ፕሬዚዳንት ሲያገለግል የነበረው 10 ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ተሞክሮዎች አሉ፡፡ አሜሪካ አንድ ሰው መምራት የሚችለው ለሁለት የምርጫ ዘመን ብቻ ነው፡፡ በፕሬዚዳንታዊ የሥልጣን ዘመን የሚመሩ አገሮች የሥልጣን ገደብ አላቸው፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንቱ በቀጥታ በህዝብ ስለሚመረጥ የሥልጣን ገደብ ያስቀምጣሉ፡፡ የፓርላሜንታዊ ሥርዓት ሲታይ ደግሞ ፓርቲው ስለሚመረጥ የግለሰብ ጉዳይ አይደለም ብለው ስለሚያስቡ አብዛኛዎቹ ገደብ የላቸውም፡፡
እንግሊዝ፣ እስራኤል፣ ካናዳ፣ ጃፓን እንደ አብነት መመልከት ይቻላል፡፡ ስለዚህ አንዳንዱ አለው፤ አንዳንዱ የለውም፡፡ በተለይ የኢትዮጵያን የተለየ የሚያደርገው እና ከህዝቡ ፍላጎት ጋር ለመጓዝ ለመገደብ መወሰኑ ያስመሰግነዋል፡፡ ሥርዓቱንም የበለጠ ተጠያቂነትንና ተሳታፊነትን ያመጣል፡፡
ኢትዮጵያ የመርህ ችግር የለባትም፡፡ የህግ አወጣጡ አንዳንድ እንከኖች ሊኖርበት ይችላል፡፡ የዚህ አገር ዋናው ነገር ብቃት ነው፡፡ በተለይ ትምህርት ቤቶች የብቃት ማዕከል መሆን አለባቸው፡፡ አሁን የጥራት ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡ ተቋሞች በብቃት መመራት አለባቸው፡፡ አመራሮቹ አገሪቱን በቅንነት ለማገልገል አመለካከታቸውን መቀየር አለባቸው፡፡ የአመራር ጥበቦችን መካን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፈጠራ ላይ መሰማራት፣ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ሁል ጊዜም በተወዳዳሪነትና በብቃት ማመን ተገቢ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ !
አቶ ዘፋኒያህ፡- እኔም አመሰግናለሁ !

ዘላለም ግዛው

Published in ፖለቲካ
Saturday, 02 June 2018 19:03

ያልተፈተሸው ከተማ

የትግራይ ክልል በእሳተ ጎሞራ እንደተፈጠሩ በሚነገርላቸው፣ የጥቁር አፍሪካውያን የነፃት ተምሳሌት በሆኑት የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ትታወቃለች። ከተደራረቡ አለቶች የተፈጠሩት የገርአልታ ተራሮች ለክልሉ ልዩ ውበት ናቸው። የ120 ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት፣ 3ሺ475 አብያተ ክርስቲያናት፣ 6ሺ948 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ደግሞ በቱሪስት ተመራጭ አድርጓታል። ይሁን እንጂ እስካሁን በክልሉ ካሉት ቅርሶች በተገቢው መንገድ ጥናት የሚያውቃቸው ከአምስት ከመቶ እንደማይበልጡ ይነገራል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው ቅርስ አክሱም ብቻ ነው፡፡
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና ቱሪዝም ኢኒስቲትዩት ቱሪዝም ማኔጅመንት መምህርና የትምህርት ክፍሉ ዳይሬክተር አቶ ተክለብርሃን ለገሰ እንደሚያብራሩት የአክሱም ከተማ በክልሉ ከፍተኛው የቱሪስት መስህብ ያለባት ናት። በከተማዋ የሚገኙ ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ቢኖሩም ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት ግን ጥቂት ናቸው፡፡ በጥናት የተለዩትም ሆኑ ያልተዳሰሱት በሚገባቸው ደረጃ ጥበቃ እየተደረገላቸው አይደለም፡፡ በመሆኑም ክልሉም ሆነ ሕብረተሰቡ ከጭስ አልባው ኢንዱስትሪ መጠቀም ያለበትን ያህል እየተጠቀመ አይደለም፡፡
በአክሱም ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ110 ዓመት በፊት በ1906 «ኢኖሊት ማን» በሚባል ጀርመናዊ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ የተጀመረ ሲሆን እስካሁን የተካሄዱ ጥናቶችም የተከናወኑት በውጪ ዜጎች ነው፡፡ የውጪ ተመራማሪዎች ደግሞ ጥናታቸውን ሲያጠናቅቁ ለቱሪስት መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉትን ስፍራዎችን ደፍነው ይሄዳሉ፡፡ እንደአሰራር ግን አንድ አርኪዮሎጂስት ጥናቱን ሲያጠናቅቅ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መጠለያ ሰርቶ ለጉብኝት ክፍት አድርጎ መሄድ ነበረበት፡፡ ለምሳሌ ቤተ ጊዮርጊስ የሚባለውና በተራራ ላይ የተገኘው ከአክሱም ከተማ በፊት እንደነበረ የተገመተው ከተማ ውስጥ በርካታ መቃብሮችና ቤተ መንግስቶች በመገኘታቸው ነው፡፡ ከነዚህ መካከል ስድስቱ ተቆፍረው ጥናት የተካሄደባቸው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ተደፍነው ይገኛሉ፡፡ በእዚህ አካባቢ ካሉት የተወሰኑት የሚታዩ ቢኖሩም ለአደጋ የተጋለጡና እንክብካቤ የሚደረግላቸው አይደሉም፡፡
በተመሳሳይ ከአክሱም ከተማ ስልሳ ኪሎ ሚትር ርቀት ማይ አድራሻ በሚባል አካባቢ ከአክሱም ዘመን በፊት የነበረ አንድ ጥንታዊ ከተማ ተገኝቷል፡፡ በውስጡ ወርቅ ይገኝ ስለነበር ቅርሶቹን ነዋሪው እያወጣ ሲገለገልባቸው ድንጋዩቹንም እየፈነቀሉ ቤት ሲሰሩባቸው ቆይቶ የዛሬ ስድስት ወር የአሜሪካ አርኪዮሎጂስቶች ቡድን በማህበረሰቡ ጥቆማ አግኝተውት ምርምር ሊደረግበት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
በከተማዋ ለቱሪስት አገልግሎት ከሚሰጡት መዳረሻዎች መካካል ዋነኞቹ 53 ክፍሎች ያሉት የንግስት ሳባ ቤተ መንግስቶችና የአክሱም ሀውልቶች ናቸው፡፡ በትግራይ ክልል በአጠቃላይ ከ1ሺ600 በላይ ሀውልቶች ቢኖሩም ጥናት የተካሄደባቸው ግን በጣም ውስን ናቸው፡፡ ከሚንቀሳቀሱት የቱሪዝም መስህቦች መካከል ደግሞ በአፍሪካ የመጀመሪያዎቹ የሆኑት ከወርቅ፣ ከብርና ከነሀስ የተሰሩት ሳንቲሞች (መገበያያ ገንዘቦች) ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በወቅቱ ባለመሰብሰባቸው በአሁኑ ወቅት በርካታ ሳንቲሞችና ሌሎች ተንቀሳቃሽ ሀብቶች በግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ እየተሸጡ ነው፡፡ በዚህ በኩል በተለይ ወጣቶች ቅርስ አለ በሚባልባቸው አካባቢ በመዘዋወር የሚያገኟቸውን ቅርሶች ለውጪ ዜጎች እየሸጡ እንደሆነ መረጃ አለ፡፡ ይህንን ክፍተት የፈጠረው ዋናው ጉዳይ በወቅቱ አለመጠናቱና አለመመዝገቡ ነው፡፡
አቶ ተክለብርሀን እንዳሉት በአለም አቀፍ ደረጃ ጥናት ሲካሄድ ፈቃድ የሚሰጠው አንድ ባለሙያ የዶክትሬት ድግሪና ከዛ በላይ ሲኖረው ነው፡፡ በዚህ በኩል እስከ ቅርብ ጊዜ በሀገሪቱ በቂ ባለሙያ አልነበረም። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ባለሙዎቹ ቢኖሩም በመንግስት በኩል ከፍተኛ የበጀት ችግር አለ፡፡ በመሆኑም የተወሰኑትም ጥናቶች የሚካሄዱት ከውጪ በሚገኝ እርዳታ ነው፡፡ ከውጪ የሚመጣው እርዳታ ደግሞ ያን ያህል ዘላቂና አስተማማኝ አይደለም ፡፡ ለጋሾች የራሳቸው ፍላጎት ስላላቸው በማንኛውም ሰዓት ፕሮጀክቱን ሊያቋርጡት አልያም እነሱ በፈለጉት መንገድ ብቻ ሊያጠኑ ይችላሉ። በዚህም ከፍተኛ ተጠቃሚ የሚሆኑት እነሱ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
በሌላ በኩል የምርምሩና ቅርሶችን ለቱሪዝም ክፍት የማድረጉ ስራ እንደ ሀገር ከባድ ቢሆንም ጥበቃና ቁጥጥር የማድረጉ ነገር ግን ባለው አቅም እንዳልተሰራ ይናገራሉ። ቅርሶቹን ለቱሪዝም በማዋል ጥቅም ማግኘት የሚቻለው በሁለት መንገድ ነው። የመጀመሪያው ቅርሶችን በማጥናትና አለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ በማድረግ ሲሆን ሁለተኛው የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በመጨመር ነው፡፡ በዚህ በኩል በቆይታ ጊዜ በአክሱም ከፍተኛ ክፍተት አለ። በከተማዋ አሁን ያሉትን የቱሪስት መዳረሻዎች ለመጎብኘት እስከ አምስት ቀን የሚወስድ ቢሆንም አሁን ያለው አማካኝ የቆይታ ጊዜ ከሁለት ቀን አይበልጥም። ምክንያቱም በቂ የእንግዳ ማረፊያ ቦታ የለም ፣ የከተማ ጽዳትና የኢንተርኔት አገልግሎት አልተስፋፋም። በመሆኑም የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስፋት፣በመጠበቅና በማስተዋወቅ ረገድ የአክሱም ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት በርካታ ስራ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል በአስጎብኚ ባለሙያዎችም በኩል የሚታይ ችግር እንዳለም ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ በተደረገ ጥናት በአንድ ቦታ ላይ የሚሰሩ አስጎብኚዎች ለእንግዶች የተለያየ መረጃ እንደሚሰጡ ተረጋግጧል፡፡ ለምሳሌ የአክሱምን ሀውልትን የመቃብር ምልክት ነው፣ ለሀይማኖታዊ ስርአት የቆመ ነው፣ ለነገስታት ዝና የቆመ ነው የሚል የተለያየ፣ የተሳሳተና የተዛባ መረጃ ነው ለጎብኚዎች የሚሰጠው፡፡ ይሄ ደግሞ በራሱ በታሪክና በቱሪዝሙ ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ አለ፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድ የአክሱም ዩኒቨርስቲ እያንዳንዷን መዳረሻ ነጥብ የሚያብራራ ካርታ እያዘጋጀ ነው። ይሄ ችግሩን ይፈታዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ከላይ የተቀመጡት ችግሮች ከቱሪዝም ሊገኝ የሚገባውን ተጠቃሚነት እያሳጡ ብቻ ሳይሆን ያሉትንም ሀብቶች ለአደጋ የሚጋልጡ ናቸው፡፡ ምናልባትም ሁኔታዎች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ ከየአካባቢው የሚጠፉት ቅርሶች በርካታ ይሆናሉ ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
የአክሱም ከተማ የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍፁመብርሀን ዘርፉ በየአመቱ መጠነኛ እድገት እያሳየ ቢሆንም ከሚጠበቀው ብቻ ሳይሆን በእቅድ ከተቀመጠውም አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ በተያዘው አመት እስከ ሚያዚያ መጨረሻ 17ሺ664 የውጪና 32ሺ201 የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በማስተናገድ ከትኬት ሽያጭ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡ ይሄ ባለፈው አመት ከነበረው 12 ሺ 700 የውጪና 42 የሀገር ውስጥ ጎብኚ ጋር ሲነፃፀር ለውጥ ቢኖረውም በእቅድ ከተቀመጠው ያነሰ ነው፡፡ በተያዘው በጀት አመት እስካሁን ከትኬት ብቻ ሊሰበሰብ ታቅዶ የነበረው ሁለት ሚሊዮን ብር ነበር፡፡
አሁን የሚጎበኙትን ቅርሶች ጨምሮ በርካታዎች በውስጣቸው ያለው ነገር አልተጠናም፡፡ በቅርብ ጊዜ በአፄ ካሌብና አፄገብረ መስቀል መካነ መቃብር አካባቢ የተገኘውን አዲስ ሳይት ጨምሮ በበርካታ ቦታዎች ግንባታ ሲካሄድና ለእርሻ ሲቆፈር በርካታ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ህብረተሰቡ እንዲህ አይነት ክስተቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ማንኛውንም ግንባታ ሲያካሂድ ለከተማው እንዲያሳውቅና በጥንቃቄ እንዲሰራም እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህ በኩል በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችም ጊዚያዊ መፀዳጃ ቤት እንዲጠቀሙ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ ለችግሩ የመሰረት ልማት አለመሟላትና የበጀት እጥረት ቀዳሚ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ያልተጠኑትን ማስጠናት የሚቻለው በፌደራል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በመሆኑ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነት ቅርሶቹን መጠቆምና ድጋፍ ማድረግ ብቻ ነው። ይሄንን ቢሮው በተቻለው አቅም እየተገበረው ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ ለጥናት ከተለዩ ቦታዎች ነዋሪዎች እንዲነሱ ቢደረግም እስካሁን ጥናቱ ባለመጀመሩ ቦታዎቹ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆነዋል፡፡
ያሉትን ቅርሶች ጠብቆ በማስቀመጡም በኩል ቢሮው ቅርሶች ለጉዳት እንዳይዳረጉ ያለውን አቅም በመጠቀም ጥበቃ እያደረገ ነው፡፡ ቱሪዝም ለማህበረሰቡ አንድ የስራ እድል መፍጠሪያ መስክ እንደመሆኑ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ 32 ወጣቶች የማስጎብኘት ስራ እንዲሰሩ ተለቋል፡፡ ይሄ እንዳለ ሆኖ በአስጎብኚዎች በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶችንም ለመሙላት የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉ ይናገራሉ።

ራስወርቅ ሙሉጌታ 

Published in ኢኮኖሚ

ዚምባቡዌ ለረጅም ዓመታት ከመሯት ሮበርት ሙጋቤ ውጭ ከሰላሳ ዓመታት ወዲህ ምርጫ ለማከናወን ለመጪው ሐምሌ ቀጠሮ ይዛለች። በአገሪቱ ህገ መንግሥት መሰረትም የፕሬዚዳንትና የሁለቱን ምክር ቤቶች ምርጫ ለማከናወን ሽርጉዷን ከወዲሁ ጀምራለች።
የወቅቱ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በነሐሴ ወር አጋማሽ የቆይታ ጊዜያቸው ሳይጠናቀቅ አገሪቱ ምርጫውን የምታከናውን ይሆናል። የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋጋዋም ይህንን ቀደም ብለው ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቆይታ ማሳወቃቸው ይታወሳል። በዚህም የተነሳ አገሪቱ ሐምሌ ላይ የምታካሂደው ምርጫ ከፍተኛ ትንቅንቅ እየታየበት እንደሚገኝ ተዘግቧል።
የዚምባቡዌ ጋዜጦች ሰሞኑን እንዳስነበቡት የአገሪቱ ዋነኛ ተፎካካሪ ፓርቲ የሆነው ሙቭመንት ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ ውስጥ የቀድሞ ከፍተኛ የፓርቲው አባላት በመጀመሪያው ምርጫ ከፓርቲው ውክልና እንዳላገኙ ታውቋል። በምርጫው የፓርቲው ቁልፍ ሰው የሆኑትና የወቅቱ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኤልያስ ሙዲትሪ ውክልናው ከተነፈጋቸው መካከል አንዱ ናቸው። በምርጫው ዋነኛው የገዢው ፓርቲ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ኤም ዲ ሲ በአንጋፋዎቹ የፖለቲካ ሰዎች ሳይሆን በወጣቶች እንደሚተካ የአልጄዚራ ዘገባ ያመለክታል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሙዲትሪ ይህ ያልተዋጠላቸው ሲሆን፤ እርሳቸውን ከምርጫው ለማግለል ወይንም ከፖለቲካ ለማራቅ የተወጠነ ሴራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገሪቱ ገዢው ፓርቲ ዛኑ ፒ ኤፍ በበኩሉ አንጋፋው ሮበርት ሙጋቤ ባይኖሩም የሚያሰጋው ነገር እንደሌለ እና የዘጠና ሦስት ዓመቱ አዛውንት ሮበርት ሙጋቤ በሌሉበት ምርጫውን ማሸነፍ እንደሚችል እየተናገረ ነው።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በ2017 ዓ.ም በሙጋቤ አስተዳደር ዙሪያ ወንጀለኞች ተከማችተዋል በሚል የአገሪቱ ጦር ጣልቃ ገብቶ አንጋፋውን መሪ ለሰላሳ ሰባት ዓመታት ከመሩበት ዙፋን እንዲነሱ ማድረጉ ይታወሳል። ሮበርት ሙጋቤ በጦሩ ግፊት ከሐራሪው ቤተመንግሥት ቢወጡም አሁንም ድረስ የደጋፊያቸው ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ይነገራል። በዚህም ምክንያት ያለ ሮበርት ሙጋቤ ዛኑ ፒ ኤፍ ቀጣዩን ምርጫ እንዴት ማሸነፍ ይቻለዋል? የሚሉ በርካታ ናቸው።
የሙጋቤ ድጋፍ እንደተቸረው የሚነገረውና በቀድሞው የአገሪቱ ብርጋዴር አንብሩሲ ሙቲንሂር የተመሰረተው ኒው ፓትሪዮቲክ ፍሮንት ፓርቲ በምርጫው ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። ሙቲንሂር ከቀድሞ ፓርቲያቸው ዛኑ ፒ ኤፍ ሙጋቤ ከሥልጣን ሲወገዱ ተቃውመው የለቀቁ ሰው ናቸው።
በዚህም ሙጋቤ አሁን ላይ ድጋፋቸውን ሊሰጧቸው ችለዋል።
ሙቲንሂር በዚምባቡዌ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ሆነዋል። እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ በአገሪቱ የነጮችን የበላይነት ለመግታት በተደረገው ትግልም የነበራቸው አስተዋፅኦ ተቀባይነታቸውን ያጎላዋል። ይህ ፓርቲ ወደ ሥልጣን ይመጣል ተብሎ ባይጠበቅም ዛኑ ፒ ኤፍ በከተሞች አካባቢ በሚያገኘው ድምፅ ይፈታተነዋል ተብሎ ተገምቷል።
በሙጋቤ አስተዳደር ዘመን ፊት ተነስቶ የነበረው የአውሮፓ ህብረት ከአስራ ስድስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጫውን ለመታዘብ ልዑካን እንደሚልክ ታውቋል። የአውሮፓ ህብረትና የዚምባቡዌ መንግሥትም ምርጫውን በመታዘብ ዙሪያ ባለፈው ሳምንት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወቃል። የአውሮፓ ህብረት ከዚምባቡዌ መንግሥት በቀረበለት ጥሪ መሰረት ምርጫውን እንደሚታዘብ የህብረቱ የዚምባቡዌ ልዑክ መሪ ፊሊፕ አንዲ ተናግረዋል። የአውሮፓ ህብረት ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ግልፅ ምርጫ ለማካሄድ እንደሚያግዝም ገልፀዋል።
ይህ የአገሪቱ አዲስ መንግሥት ግልፅ የምርጫ ሂደት እንዲኖር ቁርጠኛ መሆኑን ማሳያ አድርጎ ቢናገርም የኤም ዲ ሲ ፓርቲ መሪው ኔልሰን ቻሚሳ ለማመን እንደሚከብዳቸው ተናግረዋል። የአውሮፓ ህብረት የዚምባቡዌን ምርጫ ለመጨረሻ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2002 ለመታዘብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም በምርጫው ዋዜማ አገሪቱን ለቆ መውጣቱ አይዘነጋም። ከአውሮፓ ህብረት በተጨማሪ ሁለት የአሜሪካ የዴሞክራሲ አቀንቃኝ ቡድኖችም ምርጫው ላይ ታዛቢ ሆነው እንደሚቀርቡ መረጃዎች ወጥተዋል።
ምርጫው በገዢው ፓርቲ ዛኑ ፒ ኤፍና በኤም ዲ ሲ መካከል ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት መሆኑን በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ከወዲሁ ግምታቸውን እያስቀመጡ ይገኛሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ከምርጫው ጋር እየተነሳ የሚገኘው ዝቅጠት ውስጥ ያለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ነው። ዚምባቡዌ በሙስና ምክንያት በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደምትመዘበር መረጃዎች ያሳያሉ። ይህን ችግር መቅረፍም የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ዋነኛ ድምፅ የማግኛ ዘዴ እንደሚሆን ተነግሯል።
የሙስና ወንጀል የሚፈጽሙት የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፖሊስ አባላት መሆናቸውን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም ሪፖርት ማመላከቱ ይታወቃል። በትምህርትና በትራንስፖርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የሚሠሩ የአገሪቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሥራ ኃላፊዎችና የፖሊስ አባላት፣ ዜጎችን በከፋ ሙስና እያሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ በዚምባቡዌ የሙስና ተግባር ተቋማዊ እየሆነና የበለጠ እየረቀቀ መምጣቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በከፍተኛ ደረጃ የሚከናወኑ የሙስና ወንጀሎችን መከላከል አልቻሉም፡፡ በዚህም የውጭ ኩባንያዎች ሙስናን በመፍራት ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ሆነዋል።
ሙጋቤ በሥልጣን በነበሩበት ወቅት ምንም እንኳን ሚኒስትሮቻቸው በሙስና ላይ እንደተሰማሩ በተደጋጋሚ ቢያምኑም አንዳቸውንም ለፍርድ ለማቅረብ አለመሞከራቸውን የሚያረጋግጡ መረጃዎች መገኘታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም የመግዛት አቅሙ በእጅጉ የተዳከመውን የአገሪቱን የገንዘብ አቅም ማጠናከር የፓርቲዎቹ የምርጫ ዘመቻ ዋነኛ አካል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚምባቡዌ አስራ ሦስት ሚሊዮን ህዝብ ከአምስት ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝ ገባቸውን የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን የገለፀ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ለእዚሁ ምርጫ ሰባ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገባቸው ይታወሳል። ቀደም ሲል የአፍሪካ ህብረት ዚምባቡዌ በዚህ ዓመት ለምታካሂደው ምርጫ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚ ያደርግ መግለፁ ይታወሳል።
የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህመት ዚምባቡዌን ለሶስት ቀናት በጎበኙበት ወቅት ህብረቱ ዚምባቡዌ ለምታካሂደው የምርጫ ሂደት ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረው ነበር። ከህብረቱ የሚወከል ቡድንም ምርጫውን ከሚያስፈጽሙ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ወደ ዚምባቡዌ እንደሚያቀኑ ቃል ገብተዋል።
ህብረቱ ዚምባቡዌ ባለፈው ህዳር ወር በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር ካደረገች በኋላ ለምታካሂደው ምርጫ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርጉ አጋሮችን እንደሚያሰባስብ ማሳወቁም አይዘነጋም። ሊቀመንበሩ በሀገሪቱ የተካሄደውን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግሩን በማድነቅ የሽግግር መንግሥቱ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ለሚያደርገው ጥረት የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ አክለው ገልፀዋል።

ቦጋለ አበበ

Published in ዓለም አቀፍ

ወይዘሮ አልማዝ አፈወርቅ በመገናኛ አካባቢ በትንሽ ሬስቶራንት ከሚተዳደሩ አምስት ሴቶች አንዷ ናት፡፡ አብዛኛው ደንበኞቿ በተለያዩ የጉልበት ሥራ፣ በግንባታ ኢንዱስትሪው ውስጥ በኮንትራት ተቀጥረው የሚሠሩ ወጣቶች ናቸው፡፡ እሷ እንደምትናገረው፤ የምታቀርበው ምግብ ዋጋው ዝቅተኛና ከተጠቃሚዎች የዕለት ገቢ ጋር የተመጣጠነ በመሆኑ ደንበኞቿ ሁሌም እንደሚያመሰግኗት ትናገራለች፡፡ ይሁንና ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በመጣው የሸቀጦች ዋጋ ምክንያት ባለቻት ትንሽ ምግብ ቤት ወደ ፊት እሷንና ቤተሰቦቿን ለመርዳት መቻሏን ትጠራጠራለች፡፡

አሁን በገበያ ላይ ያለው የምግብ እህሎች ዋጋ በእጅጉ ጨምሯል፡፡የአትክልትና የፍራፍሬ ዋጋም የሚቀመስ አልሆነም፡፡ ሌላው ቢቀር መብራት ሲጠፋ ደንበኞቿ ራት ለመብላት የሚገለገሉበት ሻማ እንኳን ከአምስትና ስድስት ብር ተነስቶ ከሰሞኑ ወደ ስምንትና ዘጠኝ ብር ደርሷል፡፡ በእዚህ ሁኔታ የኑሮ ውድነቱ የመጨረሻ መቆሚያ የት እንደሚሆን መገመት አልቻለችም፡፡ ምንአልባት መንግሥት ጣልቃ ቢገባና ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን በቅናሽ ዋጋ በየአካባቢው ማቅረብ ቢጀምር ገበያው መረጋጋት እንደሚጀምር ታስባለች፡፡
ይሁንና የነገን ቀርቶ የዛሬን በአግባቡ የማያስቡና ህዝብን ለማወናበድ የተዘጋጁ ነጋዴዎች በየጥጋጥጉ በተሰገሰጉበት አገር ኅብረተሰቡ ራሱ የመፍትሄው አካል ካልሆነ የመንግሥት ማስተካከያ ብቻውን የት ያደርሳል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡ እንደእነሱ አስተያየት የመንግሥት ማስተካከያ ብቻውን ወደማያባራ የኢኮኖሚ ቀውስና አዙሪት ውስጥ የሚጨምር ነው፡፡ ስለዚህ መሆን ያለበት ከተቻለ አቅርቦትን ማብዛትና የተትረፈረፈ ማድረግ፣ የግብርና ምርትን ማሳደግ ከዚህ አልፎ ደግሞ ተጠቃሚው ራሱ ስግብግብ ነጋዴዎችን በመዋጋት መብቱን እንዲያስከብር ማስቻል የተሻለ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ጋር በተገኘ ከሰሞኑ የወጣው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ፣ በሚያዝያ ወር ባለሁለት አሃዝ የግሽበት መጠን እንደተመዘገበ ያሳያል፡፡ ይህ ስታትስቲካዊ ስሌትንና ንጽጽርን መሠረት ያደረገ አሐዝ ነው፡፡ ገበያው ግን ከተጠቀሰውም በላይ የዋጋ ለውጥ የሚታይበት ነው፡፡ የኤጀንሲው መረጃ እንዳለ ሆኖ፣ በተጨባጭ የምናየው እውነታ አሳሳቢ የዋጋ ለውጥ በየጊዜው እየታየ ስለመሆኑ የሚጠቁም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ ምርቶች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ዕድገት ህዝቡ ያለውን ገቢና አገሪቱ ያላትን ዕድገት ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ፈጣን የዋጋ ለውጦች በበርካታ ምርቶች ላይ እየታየ በመሆኑ የገበያውን በአቅርቦትና በፍላጎት የማመዛዘን ጤናማነት ላይ መመስረት ያጠራጥራል፡፡
ገበያው ላይ የሚታየው የሸቀጦች ዋጋ የመለዋወጥ መጠንና ፍጥነት፣ ኅብረተሰቡ ለዕለታዊ ፍጆታው የሚጠቀምባቸው ምርቶች ብቻም ሳይሆኑ፣ የግንባታ ግብዓቶችን የመሳሰሉ ምርቶችም የሚያሳዩት የዋጋ ለውጥ በየአቅጣጫው እየሰፋ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ለአብነትም በብረትና በሲሚንቶ ዋጋ ላይ የተደረገ ቅኝት እንደሚያሳየው በቅርቡ ሁነኛ መላ ካልተፈለገለት አሁን ያለው የዋጋ ንረት ችግር እያበበ ያለውን የግንባታ ኢንዱስትሪ ሊያስተጓጉ ለውና ጨርሶም ሊያስቆመው ይችላል፡፡
በቅርቡ ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመ ለከተው፣ ብረትን ጨምሮ ሌሎች ለግንባታ ሥራዎች የሚውሉ ግብዓቶች የውጭ የምንዛሪ ለውጡ ከተደረገበት ከጥቅምት ወር ወዲህ በአማካይ ከሃምሳ በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ ይህ ጥናት እስከ ጥር ወር 2010 ዓ.ም. ያለውን መረጃ ተመርኩዞ የተሠራ ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ የተደረገው የዳሰሳ ጥናትም ቢሆን፣ በዘርፉ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከዚህም በላይ እንደሆነ አመላክቷል፡፡
እንደኮንስትራክሽን ግብዓቶች ሁሉ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ዋጋም እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ ተገቢ እንዳልሆነ የሚያመላክቱ መረጃዎች ቢኖሩም፣ በርካታ በአገር ውስጥ እየተመረቱ የሚቀርቡ ምርቶች ግን የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ሰበብ በማድረግ ዋጋ እየተጨመረባቸው መገኘቱ ነገሩን በአንክሮ ለተመለከተ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ምክንያቱም ተገቢነት ይኑረውም አይኑረው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው ተደራራቢ የዋጋ ጭማሪ ግን መጨረሻው የአብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ህልውና እንደሚፈታተነው የታመነ ነው፡፡ የዋጋ ጭማሪው በቀናት ልዩነት ውስጥ መታየት መጀመሩ ብቻም ሳይሆን፣ ይብሱን እየሰፋ መምጣቱ ለከፋ የኑሮ ውድነት የሚዳርግ አካሔድ ውስጥ እየገባ ነው ወደሚለው መደምደሚያ ያደርሳል፡፡
እየታዩ ያሉት የዋጋ ጭማሪዎች የሕዝብን ብሶት ሊቀሰቅሱ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የዋጋ ግሽበቱ ጉዳይ ችላ መባል የለበትም በማለት እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ ገበያው የተወጣጠረበት ምክንያት ምን እንደሆነና ዋጋዎች ያለማቋረጥ የሚንሩበትን መንስዔ በትክክል በማጤን የመፍትሄ እርምጃ ሊሆን የሚችል የማስተካከያ ሥራ መስራት ደሀውን ሸማች ህዝብ ከምሬት እንዲጠበቅ ያስችላል፡፡ አሁን ባለው የገበያ ሁኔታና የኑሮ ውድነት አካሄድ ምንም ዓይነት የሸቀጦች ዋጋ ድጎማ፣ የገቢ ማስተካከያ ወዘተ ያልተደረገለት የኅብረተሰብ ክፍል እየጋለበ ካለው የዋጋ ጭማሪ ጋር መራመድ ወደማይችልበት ደረጃ አድርሶታል፡፡ ለአብነትም የእዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ ካለሁበት የመገናኛ መንደር ከሥራ ስመለስ እንደወትሮው ሁሉ ከኪዮስኮች የምገዛው ወተት አስቀድሞ አለቀ ይባላል፡፡ ይህም ለሳምንታት ተደጋግሟል፡፡ አለ ከተባለም የግማሽ ሊትር ወተት ወደ ሃያ ብር አሻቅቧል፡፡ በአጭር ጊዜ ልዩነት ውስጥ የምግብ ምርቶች ዋጋ ለምን እንደዚህ ሊወደድ እንደቻለ ማንም መልስ ሊሰጥ አልቻለም ወይም ለምን ይህንን ያህል ዋጋው ናረ ብሎ ገበያውን ለማጣራት የደፈረ አልተገኘም፡፡
የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ማሻቀብም የትየለሌ ነው፡፡ እንቁላል፣ፍሮኖ ዱቄት፣ምስር፣ጥራጥሬና ሽንኩርት በአጠቃላይ ደሃው ሕዝብ ዕለት ከዕለት የሚመገባቸው ምርቶች ሁሉ ያላቸው የዋጋ ንረት በቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡ ይህንን ከባንክ የብርና የዶላር ምንዛሬ ማስተካከያ ማግስት የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ የመጣውን ውድነት ማንም ማሰብም ሆነ መጠየቅ አይፈል ግም፡፡ የዋጋ ጭማሪው ከላይ እስከ ታች ያለውን የኅብረ ተሰብ ክፍል የሚሸነቁጥ በመሆኑ ብዙኃኑን ‹‹ኧረ ወደየት እየሄድ ነው?›› በማሰኘት ላይ ነው፡፡ እንደ አንዳንዶቹ ገለጻ፤ መንግሥት አገር ለማረጋጋትና አንድነትን ለማጠናከር እያደረገ ባለው ጥረት ስለተወጠረ ገበያውን ለማረጋጋት፣ ኢኮኖሚ ውንና የንግዱን ዘርፍ መስመር ለማስያዝ ያደርግ የነበረውን እን ቅስቃሴውገድቦታል፤ የሚሰ ጠውንም ትኩረት ቀንሶታል። ይህም የኢኮኖ ሚው ጉዞ የቁልቁለት መንገድ እያደረገው መጥቷል፡፡ በመሆኑም አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ይህንን ጉዳይ በጥልቀት በመፈተሽ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል የሚለው ጥሪ ከብዙኃኑ እየመጣ ነው፡፡
በተለይ መሠረታዊ ምርቶችና ሸቀጦች፣ ያውም በመንግሥት ይደጎማሉ የሚባሉትና እንደ ስንዴ ያሉት የምግብ ሸቀጦች በተፈለገው መጠን አለመገኘታቸው ሳይበቃ ለዋጋ ጭማሪ መባባስ ምክንያት ሆነዋል፡፡ በመሆኑም እንደ ፖለቲካው ሁሉ የሁሉም ነገር መሰረትና አንቀሳቃሽ ለሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍም ልዩ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ የግድ ይላል፡፡
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ማክሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ለከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በጽሕፈት ቤታቸው ባደረጉት ገለጻ አንድ ያወሱት ቁምነገር ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ እያደገች ናት፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ አድጋለች ከማለት ባሻገር ሕዝቡ ምን ያህል ተጠቅሟል የሚለውን መፈተሽና ማረጋገጥ አለብን፤›› በማለት አንኳርና አንገብጋቢ ጉዳይ ተናግረዋል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለአገሪቱ ሕዝብ የመዳረሱ ጉዳይ መቼም ቢሆን ችላ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን አፅንኦት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የግብይት ሥርዓቱ አንዱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል አጠቃላይ የኢኮኖሚው ይዞታ ነው፡፡
የኢኮኖሚውን ጉዳይ በርዕሰ ጉዳይነት አንስቶ ለመነጋገር ሲፈለግ ደግሞ፣ ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው መሠረታዊ አቅርቦቶች መነሳት ተገቢ ነው፡፡ በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ሸቀጦች እጥረትና የዋጋ ግሽበት ሥጋት እየፈጠረ ነው፡፡ በግሽበቱ ምክንያት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገቱን የሚያስተጓጉሉ ችግሮች ከፊቱ እየተጋረጡበት የመጡም ይመስላል (ለምሳሌ ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት)፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለኢኮኖሚው መቀዛቀዝና መድከም ምክንያት ከመሆኑም በላይ፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ አስቸኳይ ዕርምጃ ካልተወሰደ አምራች ኢንዱስትሪው ሙሉ በሙሉ ቀጥ ሊል ይችላል የሚል ትንበያዎች አሉ፡፡
በመሆኑም መንግሥት ይኼንን ሥር የሰደደ ችግር በመረዳት አገር የሚያከስሩና የማያዋጡ ፕሮጀክቶች ካሉ እነሱን በመፈተሽ መቀነስ፣ማዘግየት ወይም የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ይህንን ካደረገ በሕዝብ ላይ ኢንቨስት የማድረግ አቅሙን ይጨምርለታል፡፡ በተጨማሪም ገበያው ላይ ውዥንብርና ምስቅልቅል የሚፈጥሩ ሕገወጥ ደላሎችንና ኮንትሮባንዲስቶችን በመከታተል ማስቆም የግድ ነው፡፡ ቀደም ካሉ ጊዜያት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለአገር ውስጥ ግብይት መዛባት ዋነኛ ምክንያቶች የሚባሉት ገበያው ውስጥ ተደራጅተው የሚገቡ ሕገወጦች የግብይት ሥርዓቱን እያፋለሱት እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡
በመሆኑም መንግሥት ገበያን ለማረጋጋት ያለውን ጉልህ ሚና በአግባቡ መጫዎትና ህዝቡን ከስቃይ የአገርንም ኢኮኖሚ ከውድቀት መታደግ ይኖርበታል፡፡ከዚህ ጎን ለጎን ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመፈተሽ መሠረታዊ ለውጥ ማድረግም ተገቢ ነው። ልብ ያለው ልብ ይበል ከፈረንሳይ አብዮት ጀምሮ የሕዝብን ብሶት ሲቀሰቅስ የሚታየው ዋና ጉዳይ የኢኮኖሚው ቀውስ እንዲሁም እሱን ተከትሎ የሚመጣ የማህበራዊ ቀውስ ነው፡፡ ለብርቱ በሽታ ብርቱ መድሃኒት ማዘዝ ተገቢ ነው።

ሚዛን  ገ/ሥላሤ

Published in አጀንዳ

የሰው ልጅ አመሉ ብዙ ነው፡፡ ፀሐይ ሲበረታ «ምነው ፈጣሪዬ ዝናቡን አውርደህ ቀዝቀዝ ብታደርገን» ይላል፡፡ ወቅቱ ደርሶ ዝናብ መዝነብ ሲጀምር ደግሞ ጥቂት ቀናት ሳይቆይ ቅዝቃዜውንና ጭቃውን ተጠይፎ « መራመጃ መንገድ ፣ ከቤት መውጫ ፋታ አሳጣን» ሲል ያማርራል፡፡ ምንም ይሁን ምን የወቅቶች መፈራረቅ የተፈጥሮ ህግ ነውና ሂደቱ አይስተጓጎልም፡፡ ምክንያቱም የክረምት ሆነ የበጋ ወቅቶች ለሰው ልጅ በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው፡፡
አሁን ያለንበት ወቅት የክረምት መግቢያ በመሆኑ ግብርና የኢኮኖሚ መሰረቷ ለሆነው ኢትዮጵያ ወሳኝ ጊዜ ነው። በዚህ ወቅት የእርሻ መሬቶች ታርሰው በዘር ካልተሸፈኑ በበጋው ወቅት ሰብል መሰብሰብ አይታለምም።
አርሶ አደሩ በዚህ የክረምት ወቅት ከፍተኛ ርብርብ የሚያደርግበት ጊዜ ነው። «አንድ ሰኔ የገደለውን አስር ሰኔ አያነሳውም» የሚባለውም ይህ ወቅት በዋዛ ፈዛዛ ከታለፈ መጪው ጊዜ ለረሃብ ስለሚያጋልጥ ነው፡፡ ስለዚህም አርሶ አደሩ የዝናቡና የጭቃው እንደልብ አላንቀሳቅስ ማለት ሳይበግረው ራሱንና ወገኖቹን የሚመግብበትን ምርት ለማምረት በትጋት የሚሠራበት ወቅት ነው፡፡ከእርሻ ሥራ በተጨማሪ የደን ልማትም የሚካሄድበት ወቅትም ነው፡፡
በ1940ዎቹ ዓመታት
የኢትዮጵያ መሬት 420 ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር ወይም 35 በመቶ የሚሆነው በደን የተሸፈነ እንደነበር ጥናቶች ቢያሳዩም፤ በሕዝብ ቁጥር መብዛት፣ በደን ጭፍጨፋ፣በሰደድ እሳት፣ከሰል በማክሰልና በሌሎች ምክንያቶች የሽፋኑ መጠን ከ3 በመቶ ወደማይበልጥ ወርዶ ነበር፡፡
የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2007 ባወጣው ጥናት መሠረት፣ እ.ኤ.አ ከ1973 እስከ 1990 በነበሩት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን መጠን ከ54ሺ410 ወደ 45ሺ55 ካሬ ኪሎ ሜትር ዝቅ ማለቱን፣ ይህ መጠን በየዓመቱ ሲለካም በ1410 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚደርስ አስደንጋጭ መጠን መቀነሱን አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ የደን ዘርፍ ምልከታ ጥናት እንደሚያሳየውም የኢትዮጵያ አጠቃላይ የደን ምርት ፍላጎት በ2033 ዓ.ም. 215ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትር ኩብ እንደሚደረስ ሲገመት፣ ጥናቱ ከተካሄደበት እ.ኤ.አ ከ2013 መነሻ በማድረግ ሲሰላም የ42 በመቶ ጭማሪ እንደሚኖር ተገምቷል፡፡ስለዚህ የደን ልማቱም ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት አለበት፡፡
ባለፉት ጊዜያት በመላ አገሪቱ በሚገኙ የተመናመኑ ተራራማና የደን ማዕከል በነበሩ ስፍራዎች ሕብረተሰቡ በመተባበር የችግኝ ተከላ በማካሄድ ቀድሞ ከነበረው የተመናመነ የደን ሽፋን የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ሥራ ተከናውኗል፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ በተሰሩ ሥራዎች ደግሞ ወደ 15 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ይህ ሥራ ከ 2000ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
አገሪቱ የደን ሀብቷ አደጋ ላይ መውደቁን በመገንዘብ ዜጎቿን በማስተባበር ከአዲሱ ሚሊኒየም ጋር በተያያዘ ልዩ ትኩረት የተሰጠው የደን ልማት በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የዛፍ ችግኞች በመተከላቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ይህንን ተግባር አወድሰውታል።
በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የዛፍ ችግኞች ቢተከሉም ችግኞቹ አድገው ለዛፍነት ከመድረሳቸው በፊት በተንከባካቢ እጦት በመጥፋታቸው ምክንያት የደን ሽፋኑን የተፈለገውን ከፍ ለማድረግ የተያዘውን ርብርብ ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል ማለት አይቻልም፡፡ስለሆነም ከችግኝ ተከላው በአሻገር የመጽደቅ ምጣኔው ከፍ እንዲል መስራት ያስፈልጋል፡፡
አሁንም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ እየተሠራ ያለው የተፋሰስ ልማት ከደን ልማት ጋር በማስተሳሰር የበለጠ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ በተፋሰሶች አካባቢ የሚከናወነው ሥራ የመሬትን ለምነት ከመጠበቅ አንፃር በአርሶ አደሮችና በአካባቢ ነዋሪዎች የሚሠሩ የአፈር ዕቀባ ሥራዎች ቀጣይነታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ከደን ልማቱ ሥራ የሚገኘው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ በመኖሪያ ቤቱ አካባቢ ጭምር ዛፍ የመትከልና እንዲያድግ የመንከባከብ ሃላፊነት አለበት፡፡ ዛሬ ፀሐይ ብቅ ስትል ተቃጠልን ብለን የምንማረረው ፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ የምንጎዳውና በቅዝቃዜ የምንኮራመተው ለደን ሃብታችን መጠበቅ ትኩረት ባለመስጠታችን ነው፡፡
ስለዚህም የጀመርነውን የደን ማልማት ሥራችንን አጠናክረን በመቀጠል ወደፊት ከሚደርስብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እራሳችንን ማዳን የመጀመሪያው ምርጫችን መሆን አለበት፡፡ ባለፉት ዓመታት ካገኘነው የደን ማልማት ተሞክሮና ውጤት በመነሳት የደን ልማትና እንክብካቤ ማስቀጠል ይኖርብናል።

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Saturday, 02 June 2018 18:55

ያልተተገበሩ ፖሊሲዎች

ፈጣን የኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ ፖሊሲዎች ተዘጋጅተው ቢተገበሩም የሚፈለገውን ለውጥ በማምጣት በኩል ክፍተቶች አሉ። 

ከ1980 ዓ.ም በፊት የሚወጡ ፖሊሲዎች አንዳንዶቹ ውጤታማ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ውጤታማ አልነበሩም፡፡ ከ1980 ዓ.ም በኋላ የወጡ ፖሊሲዎችም በሚጠበቀው ልክ ውጤታማ ያልሆኑና ያልተተገበሩ ናቸው ፡፡
የወጡት ፖሊሲዎች ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ ቢሆኑ ዕድገቱም ሆነ ውጤታማነቱ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት በተሻለ ደረጃ ላይ ያደርሳት ነበር የሚሉት፤ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ጥናት ትምህርት ክፍል ሃላፊው ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ደረጄ ተረፈ ናቸው፡፡
ግብርናው ላይ ከፍተኛ በጀት እየተመደበ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና ድርቅ ሲመጣም በሚፈለገው መጠን ሙሉ ለሙሉ ከዕርዳታ መላቀቅ አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ፖሊሲው መታየት እና መፈተሽ ነበረበት፡፡ በትምህርትም ሆነ በሌላው ላይ በየጊዜው ፖሊሲው መፈተሽ ይፈልጋል፤ ዘመን ተሻጋሪ ፖሊሲ አለን ማለት ትክክል አይደለም፡፡ በፊትም ሆነ አሁን በኢትዮጵያ ፖሊሲዎች የተገኙት ውጤቶች ከዜጎች ፍላጎት በታች በመሆናቸው መፈተሽ ነበረባቸው በማለት ያለፈውን ያስታውሳሉ፡፡
ዶክተር ደረጄ እንደሚገልፁት፤ መንግስት ፖሊሲ የሚያወጣው የህዝቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላትና ችግሩን ለመፍታት በመሆኑ ህዝቡ እንዲያውቀውና ለትግበራው እንዲንቀሳቀስ ማስቻል ያስፈልጋል ሲሉ ይናገራሉ።
በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል መሪ ተመራማሪው ዶክተር ግርማ ተሾመም፤ ፖሊሲ በመንግስት ደረጃ ለህዝቡ የሚሰራው ፤ በብዙሃን ችግር ላይ የተመሰረተ እና ችግሩን ለመፍታት የሚቀረፅ የሥራ አቅጣጫ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደዶክተር ደረጄ ገለፃ፤ ከሁሉም በላይ የህዝብ ድጋፍና እንቅስቃሴ ለፖሊሲ ትግበራ ወሳኝ ነው፡፡ መንግስት ፖሊሲን ቢያመጣም ብቻውን አይተገብረውም፡፡ በህዝብ ተሳትፎ የማይጓዝ ፖሊሲ ውጤታማ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግርም ከዚህ ጋር ይያያዛል፡፡ የፖሊሲዎችን ውጤት ለክቶ በቁጥር ለማስቀመጥ ቢያዳግትም በተወሰነ መልኩ ተፈፃሚ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን የትግበራ ክፍተት መኖሩ በፖሊሲ አውጪው መንግስት ሳይቀር እየተነገረ ነው፡፡ የትግበራው ክፍተት ከአስተሳሰብ ይነሳል፡፡ ፖሊሲ ከትግበራ መነጠል የለበትም፡፡ ያልተተገበረ ፖሊሲ ህዝቡን አልጠቀመም፡፡
‹‹ ከመነሻው ጀምሮ በፖሊሲ ውስጥ የህዝብ ተሳትፎ አናሳ ሲሆን ፖሊሲው በአግባቡ አይተገበርም፡፡›› የሚሉት ዶክተር ደረጄ፤ ህዝቡ ፖሊሲውን እንዲያውቀው ማስቻል ብቻ ሳይሆን ፖሊሲው ሳይወጣ በፊት ችግሮች ሲለዩ ጀምሮ ህዝቡን ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ ፖሊሲው ጥሩና ውጤታማ እንዲሆንና ተግባር ላይም እንዲውል የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ዶክተር ግርማም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡
ሌላኛው በመምህሩ የተነሳው ሃሳብ ማንኛውም ፖሊሲ ሲወጣ የአገሪቷን የዕድገት ደረጃ መሰረት ማድረግ ይኖርበታል የሚለው ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታን በተጨማሪ ታሪክንና ባህልን ሳይቀር ማዕከል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ፖሊሲ ውጤታማ መሆን የሚችለው እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች ማዕቀፍ ሲያደርግ ነው፡፡ ሰዎች ባህላቸውንና ማህበራዊ ሁኔታቸውን የሚቃረን ፖሊሲን አይደግፉም፤ ይህ ከሆነ ፖሊሲው ውጤታማ አይሆንም፡፡ ህዝቡ ግብአት ሲጨምር እና ፖሊሲው በጋራ ስምምነት ላይ ሲመሰረት አተገባበሩም ውጤታማ ይሆናል፡፡ የህዝቡም ኑሮ ይቀየራል።
በእርግጥ ግብርናው አድጓል፡፡ ነገር ግን አጠቃላይ ህዝቡን ለመመገብና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ድርቅ ሲመጣ እርዳታ ይጠየቃል፡፡ ይህ የሚያሳየው ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ፖሊሲዎች ውጤት የላቸውም ማለት ባይቻልም ክፍተት መኖሩን ነው፡፡ ፖሊሲን የሚፈታተኑ ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ በፖሊሲ ሳይንስ ውስጥ ማንኛውም መንግስት የሚያበረክተው የራሱ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፤ ሆኖም ችግሮች መኖራቸውም መታወቅ አለባቸው ብለዋል፡፡
ባለፉት አመታት የወጡ ፖሊሲዎች ጠቃሚ ነበሩ፡፡ዛሬ ሲታዩ ግን ብዙ ጉድለት አለባቸው፡፡ ስለዚህ የፖሊሲ ትንተናና ግምገማ መካሄድ አለበት፡፡ በቀጣይ ይህ ከሆነ ጥሩና ህዝቡን የሚጠቅም ፖሊሲን መተግበር ይቻላል ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ፖሊሲ ከመውጣቱ በፊት ፖሊሲው የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? አዲስ ፖሊሲ የምንተገብር ከሆነ ምን ግብአት አለ? ዓላማው ምንድን ነው? በሚል የፖሊሲ ቅድመ ግምገማ ትኩረት አይሰጠውም፡፡ ይህም በፖሊሲ ትግበራ ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡
ዶክተር ግርማ እንዳሉት በኢትዮጵያ ትልልቅ ገዢ የፖሊሲ ማዕቀፎች አሉ፡፡ መነሻቸው ትልልቅ ችግሮች በመሆናቸው የሚተገብሯቸውም የተለያዩ ዘርፎች ናቸው፡፡ የግብርና ፖሊሲ ከኢንዱስትሪ፣ ከጤናና ከሌሎችም ዘርፎች ጋር ይተሳሰራል፡፡ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ በግብርና እየተዳደረ ለግብርናው ቅድሚያ መሰጠቱ ተገቢ ነው፡፡ አቅጣጫው ትክክል ነው፡፡ ውጤቶቹ ሁሉንም በሚያግባባ መልኩ ባይገኙም ምርታማነቱ መጨመሩ አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን በታቀደው ልክ ለውጥ ባለመምጣቱ ሙሉ ለሙሉ ተተግብሯል ማለት አይቻልም ፡፡
ፖሊሲው የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ያልቻለበት የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን የሚገልጹት ዶክተር ግርማ፤ ከፍተኛ አቅምና ግብአትን ይፈልጋል፡፡ እነዚህን ተጠቅሞ በሙሉ አቅም መተግበር ላይ ትልቅ ክፍተት አለ ብለዋል፡፡ ባለሙያን ይዞ ሥራው ላይ የማቆየት ችግር አለ፡፡ በተሿሚዎች በኩልም ፖሊሲውን አውቆ ሊተገበርበት በሚችል መልኩ በአግባቡ መምራት ላይ ክፍተት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶክተር ገብረክርስቶስ ኑርዬም፤ ፖሊሲ ሊፈፀም የሚችል መሆን አለበት፡፡ የሰው ሃይል ልማቱ በቂ አይደለም ከሚለው አንስቶ የፋይናንስና የመሰረተ ልማት ችግር አለ በሚል ፖሊሲዎችን መተግበር ላይ ያለውን ክፍተት ያቀርባሉ፡፡ ፖሊሲ የሚዘጋጀው ከማስፈፀም ስትራቴጂ ጋር ነው፡፡ ፖሊሲዎች ከሌላ ቦታዎች ከተቀዱ የአገሪቷን የፋይናስ አቅምና የሰው ሃይል መጠን ካላገናዘቡ ለመፈፀም አስቸጋሪ መሆናቸው አይቀርም ይላሉ፡፡
ፖሊሲው ከአውሮፓም ሆነ ከሌላ ቢመጣ ዋጋ የለውም፡፡ ፖሊሲ ሁኔታን መፍጠር ሳይሆን ቀድሞ ከሁኔታው መነሳት አለበት፡፡አቅም እያደገ ሲመጣ ከፍ ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ፖሊሲዎች ያልተፈፀሙበት ምክንያት የአገሪቷን አቅም አለማገናዘባቸው መሆኑን በመንስኤነት ይጠቅሳሉ፡፡
ዶክተር ግርማም ከዚህም ባሻገር ያለውን አቅም በአግባቡ አውቆ ያለመጠቀም ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ የአርሶ አደሩን አቅም አሟጦ መጠቀም፤ አገር በቀል ልማዶችን ማዕከል በማድረግ ሥራ ላይ የማዋል ክፍተትም ችግር የፈጠረ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ አመራሩ ፖሊሲውን ተረድቶ ችግሩን ለመፍታት በሙሉ ተነሳሽነትና በቅንነት መስራት ላይ ክፍተት ያለበት መሆኑ ውጤታማነቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ፖሊሲ ህብረተሰቡና ፈፃሚው በግልፅ አላማውን መረዳት አለበት በማለት ያለመተግበሩ ሌላኛው መንስኤ ፖሊሲውን በትክክል ካለማወቅ ጋር የተያያዘ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ዶክተር ደረጄ፤ ጨምረውም ፖሊሲን የሚፈታተኑ ተግባራት ቢኖሩም የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ምንጊዜም ቢሆን ያለማቋረጥ ፖሊሲን መፈተሽና ማሻሻል ይጠበቃል ፡፡ በቀንና በሰዓታት ሁኔታዎች ይቀያየራሉ፡፡ ስለዚህ በየጊዜው መፈተሽና ከጊዜው ጋር ማስጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ የህዝብን ሰፊ ፍላጎት ማሟላት አይቻልም፡፡ ፖሊሲ አንድ ወጥ እና እስከ ትግበራ የሚዘልቅ ሲሆን፤ ከጊዜው ጋር የሚራመድ ተለዋዋጭ መሆኑንም ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ዶክተር ግርማ ለፖሊሲ ግብአት መሆን የሚችሉትን ጉዳዮች መለየትና መጠቀም ይገባል፡፡ ፖሊሲ በየጊዜው መፈተሽ አለበት፡፡ ከተነሳበት ችግር ጋር ተያይዞ ችግሩን መፍታቱን ፣ በትክክለኛ መስመር ላይ መሆኑ መዳሰስ አለበት፡፡ ዋና ዋና ፖሊሲዎች ቆይተዋል፡፡ የግብርና፣የጤና እና የትምህርት ፖሊሲው መፈተሽ አለበት ብለዋል፡፡
ፖሊሲዎቹን የሚተገበሩና ውጤታማ ለማድረግ በቅድሚያ ችግሮችን መለየት፤ ከመነሻው ጀምሮ ህዝብን ማሳተፍ፤ ሁሉም አላማውን እንዲረዳና እንዲተገብረው ማስቻል እንዲሁም ባለው አገራዊ አቅም ላይ መመስረት ይገባል፡፡ ያሉትን ፖሊሲዎች በየጊዜው በመፈተሽ የማሻሻል ሥራ ከተሰራ ወደፊት ፖሊሲን መተግበር አዳጋች አይሆንም፡፡ነገር ግን የአገሪቷን የፋይናንስ አቅምና የሰው ሃይል ካላገናዘበ፣ አመራሩም ቁርጠኝነትን የተላበሰ ካልሆነ የፖሊሲው ተፈፃሚነት ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል።  

ምህረት ሞገስ
ዜና ትንታኔ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።