Items filtered by date: Sunday, 03 June 2018

ሐሙስ ግንቦት 2 ቀን 2010 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 «ህዳሴ» ጤና ጣቢያ ተገኝቻለሁ። ዓላማ ከኤች አይቪ /ኤድስ ጋር የተገናኘ መፍትሄዎችን ከሰዎች ወይም ከህትመት ውጤቶች ከበራሪ ወረቀቶች ብሮሸሮች ቡክሌቶች ወዘተ... ለማግኘት ነበር። በሚገርም ሁኔታ ደስ ብሎኝ ተመልሻለሁ። የምፈልገውንም አግኝቻለሁ። የኤች አይቪ ክፍል ሠራተኞች በተሟላ ሁኔታ ከሥራ ሰዓት ቀደመው ተገኝተዋል ንፁህ ነጭ ጋዋን ለብሰዋል የደረት ባጃቸውን አድርገዋል። ቢሮአቸውን በሥርዓት አደራጅተው ተገልጋዮችን እየተጠባበቁ ነው። በዚያው ቀን በዚሁ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 «ጥበብ በቀጨኔ» ጤና ጣቢያ ልክ ከጠዋቱ በ4 ሰዓት ተገኝቻለሁ። የቢሮ አካባቢ 3ኛ ፎቅ ላይ ይገኛል ውብና ንፁህ አካባቢ ነው። ሠራተኞች ተሟልተው ጋዋን ለብሰዋል ባጅ አድርገዋል መስተንግዷቸው ማራኪ ነው የምፈልገውን ነገርኳቸው። የነፈጉኝ ነገር የለም እንዲያውም ትንሽ አረፍ በሉና የ15 ደቂቃ ገለፃ በኤች አይቪ ላይ እንስጥዎት ብለውኛል። ለማንኛውም ከእነዚህ ሁለት ጤና ጣቢያዎችና ግንቦት 3 ቀን 2010 ዓ.ም አርብ በቅድስት ማርያም ላብራቶሪ እና የኤች አይ ቪ የምክርና የማህበራዊ አገልግሎት ተገኝቼ ካደረግሁት ምልከታና ከሰበሰብኩት ማቴሪያሎች ለዛሬ የማቅርብላችሁ በኤች አይ ቪ መድሐኒቶች ዙሪያ ያሉትን አንኳር ጉዳዮች ነው።
የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው ሰዎች ጤንነታቸውን ለማሻሻል የሚወስዱት መድኃኒት ነው፡፡ መድኃኒቱን መውሰድ ከተጀመረ አይቋረጥም በህይወት እስካሉ ድረስ በየቀኑ የሚወሰድ ነው፡፡ መድኃኒቱን መወሰድ የሚጀምረው ቫይረሱ በደም ውስጥ መገኘቱ ከታወቀበት ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ መድኃኒቱን በወቅቱ መጀመር ካልተቻለ በሰውነት የቫይረሱ መጠን ይጨምራል፡፡ የሰውነት በሽታ መከላከል አቅም ይዳከማል፡፡ የአፍ እና የምላስ መቁሰል አልማዝ ባለጭራ የቆዳ ሽፍታና የሳንባ በሽታ (ቲቢ) የመሳሰሉት ተያያዥ በሽታዎች ይከሰታሉ። የመድኃኒቱን አወሳሰድ፣ ጥንቃቄና መሰል ጉዳዮች የሚወስነው የጤና ባለሙያ ብቻ ነው። መድኃኒቱ ኤች አይ ቪን ሙሉ በሙሉ ከሰውነት ውስጥ አያጠፋም። ነገር ግን ቫይረሱ እንዳይራባ በማድረግ መጠኑን ይቀንሰዋል። በሰውነት ውስጥ ያለው የቫይረሱ መቀንስ ደግሞ የሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅምና ጤንነታችን እንዲሻሻል ያደርጋል። በሰውነት ውስጥ የኤች አይቪ መጠን ሲጨምር ሰውነት በሽታ የመከላከል አቅሙ ተዳክሞ የተለመዱ በሽታዎችን ለመዋጋት ጉልበት ያጣል። በመሆኑም ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች በሽታ የመከላከል አቅማቸውን በማጠናከር በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኘውን የቫይረስ መጠን መቀነስ አለባቸው፡፡ ለመጠበቅ የሚረዱ ምግቦችን መመገብ አለባቸው። በቂ እንቅልፍና እረፍት ማግኘት አለባቸው። ዘወትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የግልና የአካባቢ ንጽህንና መጠበቅ አልኮል መጠጣት ሲጋራ ማጨስና ጫት መቃም የመሳሰሉ ጐጂ ሱሶችን ማስወገድና በህክምና ባለሙያው የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው፡፡ ከአባላዘር በሽዎች ለኤች አይቪ ላለመጋለጥ ወሲባዊ ግንኙነትን በጥንቃቄ መፈፀም ሆስፒታልና ጤና ጣቢያ በመሄድ የጤና ክትትል ማድረግ ስለሚገጥሙአቸው የጤና ችግሮች ከጤና ባለሙያዎች ጋር በግልፅ መነጋገር አለባቸው።
የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒቶች የተለያዩ ዓይነቶች ቢኖሩም በጣም የተለመዱት ላማቩዲን፣ ዚደቩዲን፣ ስታቡዲን፣ ኔቪራፒን፣ ኢፋቪረንዘ የተባሉት መድኃኒቶች ናቸው። ሁሉም ሰው ሁሉንም አይነት መድኃኒት ይወስዳል ማለት አይደለም። የሚወሰነው በጤና ባለሙያው ነው። መድኃኒቱ ሳይስተጓጐል በትክክል በትዕዛዙ መሠረት ከተወሰደ ሰውነት ውስጥ የሚገኘውን የቫይረስ መጠን በፍጥነት በመቀነስ በሽታ የመከላከል አቅም እንዲታደስና ሰውነትም ጤናው እንዲመለስ ያስችለዋል። መድኃኒትን በአግባቡ አለመጠቀም፣ መድኃኒቶቹ የሚጠበቅባቸውን ተግባር በትክክል እንዲያከናውኑ ስለሚያደር ጋቸው የቫይረሱ መጠን ይጨምራል። ይህም የግለሰቡን በሽታ የመከላከል አቅም በማዳከም ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣል።
ኤች አይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ማድረግ የሌለባቸውን ነገሮች ማወቅና ማክበር አለባቸው። ለምሳሌ ያልበሰሉ (ጥሬ) የሆኑ ምግቦችን አለመገገብ (ጥሬ ሥጋ፣ ቲማቲም፣ ሠላጣ) አብስሎ መመገብ ንጽህናውን ያልተጠበቀ ውሃ (በውሃ አጋር ያልታከመ ፊልቶ ያልቀዘቀዘ) ውሃን አለመጠቀም፣ ጥንቃቄ የጐደለው ወሲብ አለማድረግ፣ መድኃኒቱን በሰዓቱ አለመውሰድ፣ ተጨማሪ ኃይል ሰጪ ምግቦችን አለመመገብ፣ ሲታመም ወዲያውኑ ወደ ህክምና ቦታ አለመሄድ የመሳሰሉትን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። መቼም መድኃኒት ነው የማዳንና የመከላከል ኃይል ያለው መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም አንዳንድ የጐንዮሽን ውጤቶች ሊኖሩት ይችላል። ሰውነታችን መድኃኒቱን ስላልመደው ምቾት ላይሰጥ ይችላል። የጐንዮሽ ውጤቶች ብዙዎቹ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ ሲሆኑ መድኃኒቱን ዕለት ተዕለት መውሰድ ሲቀጥሉ እየቀነሱ ይሄዳሉ። ሌላው የጐንዮሽ ውጤት የምግብ ፍላጐትና ማጣት ነው። ለዚህም መፍትሄው ሀኪሙን ከማማከር በተጨማሪ የሚወሰዱትን ምግብ ለመብላት መሞከርና ምግብ በትንሽ በትንሹ በአጭር ጊዜ ልዩነቶች ይመገቡ ማቅለሽለሽና ማስመለስ ሲያጋጥም ሀኪሙን ቢያማክሩ ማቅለሽለሽን የሚያሰቀር መድኃኒት ሊያዝልዎት ይችላል። የአፍ ድርቀት ወይም የምግብ ጣዕም መቀየር ሲያጋጥም ቶሎ ቶሎ ውሃ መጠጣትና የምራቅ መማንጭትን ለማፋጠን ማስቲካ ማኘክ ጥሩ ነው። አንዳንድ መድኃኒቶች ፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት በሚሠራበት ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ስለሚችሉ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ መድኃኒት አይውሰዱ። የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒትን መውሰድ አያቋርጡ።
መድኃኒቱን ከዋጡ በኋላ በ30 ደቂቃ ውስጥ ቢያስመልስዎት መድኃኒቱን በድጋሚ ይውሰዱ ነገር ግን ከ30 ደቂቃ በኋላ ካስመለስዎና መድኃኒቱን ወጥቶ ካላዩት በድጋሚ አይወሰዱ ማንኛውንም የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት ያለሀኪም ትዕዛዝ አይወሰዱ።
የመውሰጃ ሰዓትዎን ለማስታወስ ለእርስዎ የሚመችዎትን ዘዴ ይፍጠሩ ሳይወስዱ የዘነጉትን መድኃኒት ለማካከስ እጥፍ መድኃኒት አይውሰዱ ማንኛውንም የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት አይወሰዱ እርግዝንና ካሰቡ ሃኪሙን ማመከር አለብዎት። በማንኛውም ምክንያት መድኃኒትዎን ከመውሰድ ማቋረጥ የለብዎትም። ፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት ከመውሰድዎ በፊት እየወሰዱት ያለ መድኃኒት ማቋረጥ የለብዎትም። ፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት ከመውሰድዎ በፊት እየወሰዱት ያለ መድኃኒት ካለ ወይም ፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት እየወሰዱ ሌሎች ተጨማሪ መድኃኒቶች ከመውሰድዎ በፊት እውነታውን ሳይደብቁ ለሀኪም ቢነግሩ መድኃኒቶቹ በተለይ ጥምሮዡ (የቴኖፎ ቬ፣ ላሙቪዲን እና ኢፋቨረንዘ ጥም መድኃኒቶች ሲወሰድ በሁሉም ላይ ሳይሆን በአንዳንድ ተጠቃሚዎች ላይ የሚታዩ የጐንዮሽ ውጤቶች (ችግሮች) ይኖራሉ። እነሱም፡-
የቆዳ ሽፍታ፣ የዐይን ቀለም ቢጫ መሆን-- የወንዶች ጡት መተለቅ (ማደግ) የሚጥል በሽታ ካለ ማገርሸት አስፈሪ ህልም (ቅዠት) ማየት የሽንት መጠን እየቀነሰ መሄድ የአጥንት መሳሳት ያለባቸው ሰዎች ህመም መባባስ ናቸው፡፡ በተለይ የሽንት መጠን መቀነስ፣ የዐይን ቢጫ መሆንና የአጥንት ህመም ሲያስተውሉ በአስቸኳይ የጤና ባለሙያ ማማከር አለብዎት። ማንኛውም የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት ህፃናት (ልጆች) ከማይደር ሱበትና ከፍተኛ ሙቀት በሌለበት እና የፀሐይ ብርሃን በማይደርስበት ቦታ ያስቀምጡት። የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት በፆም በጠበል እንዲሁም በሌሎች ሃይማኖታዊ ሆነ ባህላዊ ምክንያት መቋረጥ የለበትም። የባህል መድኃኒት ከፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት ጋር ላይጣጣም ስለሚችል የባህል መድኃኒት ከመውሰድዎ በፊት የጤና ባለሙያ ያማክሩ።

በግርማ ለማ

Published in አጀንዳ

በሥራ ወዳድነቱ የሚታወቅ አንድ ንጉሥ ነበር። የማይሠራ ሰው ከሚሠራ ሰው ጋር አብሮ መኖር የለበትም የሚል እምነት ነበረው። እናም ሰዎች ሲሸመግሉና መሥራት ሲያቆሙ ከመጦር ይልቅ ሰው ወደማይደርስበት ቦታ መጣል አለባቸው የሚል ሕግ አወጣ። ያወጣውን ሕግ የሚተላለፍ ላይ ከባድ የሚባል ቅጣት ያሳርፍ ነበር።
ይህ ሥራ ወዳድ ንጉሥ በፍቅር ተንከባክቦ ያሳደገው አባቱ ያረጅና ባወጣው ሕግ መሠረት የሚጣልበት ጊዜ ደረሰ። ይሁን እንጂ ያወጣው ሕግ በራሱ ላይ ሲደርስ ትክክል እንዳልነበረ አመነ። የእርሱ ተራ ደርሶ የሚወደውና እየደገፈ ለንግሥና እንዲበቃ ያደረገውን ብልህ አባት ጨክኖ ሰው ወደማይደርስበት ቦታ መጣል አልዋጥልህ አለው። ይባስ ብሎም በብዙ ነገር የሚያማክረው አባቱ መሆኑን ሲያስብ ይህን ሕግ ያወጣበትን ቀን ረገመ። ይሁን እንጂ «የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ» እንዲሉ ቃሉን ላለማጠፍ ማርጀቱን ሳያሳውቅ ከዋሻ ደብቆ ለማኖር ወሰነ።
ከዕለታት በአንዱ ቀን ፈጣሪ ለዚያች አገር ንጉሥ ተገለጠና ሁለት ጥያቄዎች እንዲመልስ በርዕይ አሳየው። ንጉሡ ይህን እንቆቅልሽ መፍታት ወይ ማስፈታት ካቃተው ደግሞ በከተማዋ ላይ ከፍተኛ ቅጣት ሊያወርድባት መዘጋጀቱን ተናገረው። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተረበሸ።
በርዕይ የታየው የመጀመሪያው ፈተና እንዲህ የሚል ነበር። «ሁለት እባቦች በፊትህ አቀርባለሁ፤ ወንዱንና ሴቷን እባብ ለይ» የሚል ነበር። በንጉሡ ቤተመንግሥት አቅራቢያ የነበሩ መሳፍንትን ሲያማክር አንድም እንዴት መለየት እንደሚቻል የሚያውቅ ሰው አላገኘም። ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት ችግር ሲያጋጥመውና ህልም ሲያይ የሚያስፈታው በብልሁ አባቱ በመሆኑ ያለው አማራጭ ደብቆ ያስቀመጠውን አባቱን ማማከር ብቻ ነበር። በመጨረሻም ጥያቄውን ለአዛውንት አባቱ ተናገረ። አባቱም በቀላሉ በመረዳት ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲህ በማለት ነገሩት። «ሁለቱን እባቦች በምንጣፉ ላይ አስቀምጣቸውና ቀድሞ ወደ አንዱ እባብ የሚሄደው እርሱ ወንዱ ነው፣ ሴቷ ግን ወንዱን ትጠብቃለች እንጂ ወደሱ አትሄድም» ንጉሡም እንደተባለው አድርጎ ትክክለኛውን መልስ በተግባር አሳየ።
ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ «ሁለት በቀለምና አቋም ተመሳሳይ የሆኑ እናትና ልጅ ፈረሶች አቅርብልሃለሁ፤ እናቲቱን ከልጇ ለይተህ ንገረኝ። ለዚህ ምላሽ ካገኘህ አገርህ ይተርፋል» የሚል ነበር። ንጉሡ በድጋሚ በጭንቀት ተውጦ አሮጌነህ ብሎ ወደ ደበቀው አባቱ ዋሻ በመሄድ የቀረበለትን ፈተና በድጋሚ ጠየቀው። አባቱም ጥያቄውን ሰምቶ ትንሽ ካሰላሰለ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለበት እንዲህ በማለት ነገረው። «ሁለቱን ፈረሶች በጋጥ አስገባና ጭድ አቅርብላቸው። ጭዱን በአፏ ወደ ልጇ የምትገፋው እናቲቷ ነች» አለው። ንጉሡም እንደተባለው በማድረግ ትክክለኛውን መልስ አቀረበ። ፈጣሪም ምላሹን እንዴት እንዳገኘው ያውቃልና «እነሆ ለልጆችህና ለወጣቶችህ ያሰብካትን አገር እንዳላጠፋት የሽማግሌዎቹ እውቀት ታደግካት» አለው፡፡
ፈተናውን በአዛውንት አባቱ አስተውሎትና ብቃት ያለፈው ንጉሥ በየትኛውም መንገድ ያለፈ ያረጀና የሸመገለ የሚባል እውቀት እንደማይኖር አመነ። ንጉሡም የቆየውን የአገሪቷን ሽማግሌዎች የሚገፋ ሕግ ሻረ። «ከዛሬ ጀምሮ የማይጠቅም ነገር የለምና ያረጀና ምንም የማይጠቅም ተብሎ ሰው ወደማይደርስበት የሚጣል ሰው አይኖርም። እንዲያውም የተለየ ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ የእነሱን ዕውቀት ልንጠቀም ይገባል። የኋላው ከሌለ የአሁኑ አይኖርምና ዋኖቻችንን እናክብር እንጠብቅም» ሲል አዋጅ አስነገረ።
ነባር እውቀቶቻችን ለዛሬ ማንነታችን መሠረቶች ናቸው። በተለይም ባህላዊ እውቀቶች የሚባሉት በውስን አካባቢዎች ላይ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ገፅታዎች ዙሪያ ላሉ ክፍተቶቻችን መፍትሄ ይሆኑ ዘንድ ባህላዊ በሆነ መንገድ በአንድ ወይም በተወሰኑ ሰዎች የሚመነጩና የሚተገበሩ እውቀቶች ናቸው። በመሆኑም ከዘመናዊው አስተሳሰባችን ጋር አስተሳስረን ልንጠቀምባቸው ይገባል።
ነባር እውቀቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ የሕይወት ገፅታዎች የሚዳሰሱበትና መፍትሄ የሚሰጥባቸው ናቸው። በብዙ ዘመናት ልምድ የዳበረና በባህል ውስጥ ሰርፆ ከትውልድ ወደ ትውልድ በታሪክ፣ በዘፈን፣ በአባባል፣ በእምነት እና በሌሎች መንገዶች በአካባቢው ቋንቋ የሚተላለፍ እውቀት በመሆኑ አሁንም ድረስ በእጃችን ያለ ዕውቀት ነው። ይህን ዕውቀት ለማበልፀግ ደግሞ በየአካባቢው የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ኃላፊነታቸው ግዙፍ ሊሆን ይገባል።
እንደአገራችን ባሉ በተፈጥሮ ሀብት በበለፀጉ አገራት በግብርና፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች፣ ሞራልንና ሰብዕናን በመገንባትና በሌሎችም ዘርፎች የአገር በቀል እውቀቶች ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በማመን ልንጠብቃቸውና ልናበለፅጋቸው ይገባል።
አገር በቀል እውቀቶቻችን መገለጫቸው እልፍ ነው። ባህላዊ መድኃኒቶቻችን በዘመናዊ አሠራር ከተደገፉ ፈዋሽነታው አያጠያይቅም። የአያት ቅድመ አያቶቻችን ምክርና ተግሳፅ መንገዳችንን ቀና ያደርጉታል። የዛሬው አስተሳሰባችን በትናንትናው የብራና መፅሐፍት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ባህላዊ የእርቅ ሥርዓታችን፣ ታላላቆቻችንን የማክበር ልማዳችን፣ ለሠላም ቅድሚያ መስጠታችን፣ የሃይማኖት መቻቻላችን ሁሉ መነሻው የትናንት ነባር ዕውቀት ነው። ዛሬ የትናንት ነፀብራቅ እንጂ የትናንት ግንጣይና ብቻውን የቆመ ጊዜ አይደለም።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በተደጋጋሚ ስፖርት ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር በተለይ ደግሞ ወጣቶች የመልካም ሰብእና ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል ከሌሎች ዘርፎች በተሻለ ሚናው ላቅ ያለ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። እነዚሁ የስፖርቱ ቤተሰቦች የማህበራዊ መስተጋብሩን በላቀ ሁኔታ ከማስተሳሰሩ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳውም የማይናቅ እንደሆነ ነው የሚነግሩን።
በስፖርቱ ላይ የምንመለከታቸው አንዳንድ ህፀፆች መኖራቸው ቢታወቅም ስፖርቱን ለመደገፍ ደግሞ የሚታትሩ ሰዎች መኖራቸው መረሳት የለበትም። ስፖርት እንጀራ ሆኖ ጥቂቶች እራሳቸውን እንዲደጉሙ ከማስቻል በዘለለ የአገር ኢኮኖሚ ዋልታ እንደሚሆን አውሮፓዊቷ አገር እንግሊዝ በቀላሉ አሳይታናለች። ሚሊዮኖች ስፖርት ወዳድ በመሆናቸው ጤናማ ማህበራዊ ህይወት ሲመሩ እና ለአዕምሯቸው ጤናን ሲገበዩ በየእለቱ በመገናኛ ብዙሀን አውታሮች እናዳምጣለን እንመለከታለን። ስፖርት ሁለት የተለያየ ማንነት ውስጥ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማቀራረብ፣ ስለ ፍቅር በመስበክ፣ አንድነት ሀይል መሆኑን በማሳየት ከሚጫወተው ሰፊ ሚና በዘለለ የሰው ልጆች በዘር፣ በቀለም እና በጥቃቅን ልዩነቶች የሚፈጥሩት ሽኩቻ ውሃ የማይቋጥር መሆኑን ፍንትው አድርጎ በማሳየት ፖለቲካዊ ሀላፊነቱን ሲወጣ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ከዚህ ደግሞ ይህንን እንረዳለን ፍቅር፣ አዲስ ትውልድ መገንባት፣ ጤናማ አስተሳሰብ የሁሉም ስፖርቶች መርህ እና ተቀዳሚ አላማው መሆኑን።
ስፖርት በልክ የምንሰፍረው በቁጥር የማናስቀምጠው ቢሆንም በእለት ተዕለት ኑሯችን ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ የሚያስችል ትልቅ ጉልበት እንዳለው ለመረዳት ባለሙያ መሆን የግድ አይልም። ታዲያ በህይወታችን ላይ ሰፊ ድርሻ ያለውን ዘርፍ እንዴት እንመለከተዋለን? በተለይ በአገራችን ኢትዮጵያ ስፖርት አሳድጎ ከፍሬው ለመጠቀም የሄድንበት እርቀት ምን ያህል ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ይህንንም ለመመለስ የግድ አዋቂ መሆን ሳያስፈልግ ስፖርቱ በሚመለከታቸው አካላት በበቂ ሁኔታ ትኩረት እንዳልተሰጠው እና ሁሉም ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ በመጠቀም ይህን ዘርፍ ለማበልፀግ እንዳልሰራ እንመለከታለን። ይህን ስንል ግን አንዳንድ የሚመከሩ እንቅስቃሴዎች ጭርሱኑ የሉም ለማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው አምዱ ስፖርቱን ከሚደግፉ አካላት ውስጥ አንዱን መዞ ሚናው ምን መሆን እንዳለበት ለማመላከት ይሞክራል። በዋናነትም የግል ባለሀብቶች በስፖርት ዘርፉ ላይ ገብተው የበኩላቸውን ድጋፍ ቢያደርጉ የተለያዩ የስፖርት አይነቶች አሁን ካሉበት ደረጃ በብዙ እጥፍ በማሳደግ ከላይ በመግቢያችን ላይ ጠቀስ አድርገን እንዳለፍነው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ፋይዳ በቀላሉ ማሳደግ ይቻላል የሚል አመለካከት አለን። ስፖርትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ላይ ባለሀብቶች በቀጥታ መዋእለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አማራጮችም ከስፖርቱ ጎን በመሆን ሊደግፉ ይችላሉ። በዛሬው ርእሳችን ላይ ስፖርቱ በባለሀብቶች መደገፍ ይኖርበታል በሚል ቀጥተኛ አካሄድ ሃሳቦችን አናነሳም። ይልቁኑ ጉዳይ ስናነሳ እንዲያው በደረቁ ሳይሆን አንድ እንግዳ በመጋበዝ ጭውውት በማድረግ ነው። እኚህ ሰው ማናቸው?
አቶ ነብዩ ሳሙኤል ፈረንጅ ይባላሉ። የታዋቂው ጋዜጠኛ የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ውስጥ የመጀመሪያው ዳይሬክተር በመሆን የሰሩ የአንጋፋው የአቶ ሳሙኤል ፈረንጅ ልጅ ናቸው። ከበርካታ ዓመታት በፊት በአገር ውስጥ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በእናታቸው አማካኝነት በኬንያ፣ በጣሊያን አድርገው አሜሪካን አገር ኑሯቸውን አድርገው ነበር።
አቶ ነብዩ በአሜሪካን አገር ኑሯቸውን ቢያደርጉም ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ግን አልቀየሩም። በዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት አጥንተው ለአመታት በተለያዩ ስራዎች ላይ ቆይተዋል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠርም በኢትዮጵያ መንግስት ጥሪ ተደርጎላቸው አገራቸው ላይ መዋእለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በኢንቨስትመንት ስራ ለመሰማራት ወደዚህ መጥተዋል። ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ነብዩ አሁን በአገራቸው ላይ በኮንስትራክሽን እና በሎሎች ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ። በተለይ ደግሞ የጎልፍ እና ብስክሌት ስፖርቶችን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ላይ ሰፊ አበርክቶ እንዳላቸው የስፖርቱ ባለሙያዎች በተለያየ አጋጣሚ ሲናገሩ ይደመጣል።
አቶ ነብዩ በልጅነት ጊዜያቸው በአካባቢያቸው ላይ እግር ኳስን ይጫወቱ እና ለስፖርቱ ልዩ ፍቅር እንደነበራቸው ይናገራሉ። ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ልዩ ትኩረት እንዲኖራቸው ፈር የቀደደላቸው ደግሞ እግር ኳስን አብዝተው መውደዳቸው ነበር። በችሎታውም ቢሆን የማይታሙ ጎበዝ ተጫዋች ነበሩ። ከስፖርት ጋር ቅርብ የመሆን ፍላጎታቸው አገር ሲለቁም አብሯቸው ተሰዷል። በአሜሪካን አገር እግር ኳስ እምብዛም ባለመዘውተሩ ምክንያት ጨርሶውኑ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ አልራቁም ይልቁንም የግድ ቢሆንባቸውም ወደ «አሜሪካን ፉት ቦል»፣ የቅርጫት ኳስ እና ሌሎች ስፖርቶች ትኩረታቸውን አድርገው ቆይተዋል። በተለይ በሚኖሩበት አካባቢ የጎልፍ ስፖርት መዘውተሩ እርሳቸውም ለዚህ ስፖርት ልዩ ፍቅር እንዲኖራቸው እና በስፋት ተሳታፊ እንዲሆኑ እድሉን ከፍቶላቸዋል።
«ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ የመንግስቱ ወርቁ፣ ሉቺያኖ ቫሳሎ፣ ጌታቸው ዱላ የግብ ጠባቂው አድናቂ ነበርኩ» በማለት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበሩበት ዘመን በአገር ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበራቸው እግር ኳስ ተጫዋቾች ይሳቡ እንደነበር ጊዜውን መለስ ብለው እያስታወሱ ይናገራሉ። አቶ ነብዩ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ቅርብ ቢሆኑም ስራዬ ብለው ሙሉ ለሙሉ በዚያው አልቀሩም። የራሳቸውን መክሊት ተከትለውም በበርካታ የስራ መስኮች ተሰማርተው ሲሰሩ ቆይተዋል። ከሁለት አስርት አመታት የዘለለ ከአገራቸው ውጪ የኖሩ ቢሆንም ወደእናት ምድራቸው ጠቅልለው ከገቡ 15 አመታትን አስቆጥረዋል። በኮንስትራክሽን እና ሌሎች የግል መስኮች ላይ ተሰማርተው ይሰራሉ። በቤት ልማት የተሰማሩት እኚህ ባለሀብት በወንድ እና ሴት ልጃቸው ስም በሰየሙት የዘኮሊና ኮንስትራክሽን በስፋት ይታወቃሉ። ከአስራ አንድ አመታት በላይም በኢትዮጵያ ውስጥ በብስክሌት እና ጎልፍ ስፖርቶች ላይ ቀና ድጋፋቸውን በማድረግ ወደ ተሻለ አቅም እንዲሻገሩ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በተለይ የብስክሌት ስፖርት ላይ ባላቸው ጠንካራ ተሳትፎ ይታወቃሉ።
የጎልፍ ስፖርት አዲስ ምዕራፍ
ጊዜው የዛሬ 15 ዓመት ነው። አቶ ነብዩ በአሜሪካን አገር ኑሯቸውን ቀጥለዋል። በድንገት ግን ወደ አገራቸው ለመግባት ውሳኔ ላይ የሚያደርሳቸው አጋጣሚ ተፈጠረ። በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ ከረጅም ጊዜ ጓደኛቸው ጋር ይገናኛሉ። ይሄ አጋጣሚ ደግሞ ወደ አገራቸው ገብተው ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ ግብዣ ካደረጉላቸው ሰዎች ጋር እንዲገናኙ እድሉን ከፈተላቸው። ወደትውልድ አገራቸው የመግባት ፍላጎት ቢኖራቸውም በመጀመሪያው «ወደ አገርህ ተመልሰህ ኢንቨስት አድርግ» ለሚለው ጥያቄ ፍቃደኛ አልነበሩም። ሆኖም ቡና ኤክስፖርት ሊያደግ የሚችል አንድ የውጭ ዜጋ ጓደኛቸውን ከኢትዮጵያ ምርቱን እንዲወስድ እድሉን አመቻቹለት። የእርሳቸውን መመለስ ግን ለጊዜው አዘገዩት። ምክንያቱም ቢሮክራሲው ያሰራኛል ብለው አላሰቡም ነበር።
በወቅቱ በአሜሪካን አገር የኢትዮጵያ አምባሳደር ከነበሩ ሰው ጋር በመነጋገርም እርሳቸው የሚፈሩት ቢሮክራሲ እንደማይኖር ቃል ስለተገባላቸው ለሁለተኛ ጊዜ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት ወደ አገራቸው ለመምጣት ወሰኑ። በጓደኛቸው የተዋወቋቸው የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከተነጋገሩ በኋላ ጓዛቸውን ጠቅለለው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ወሰኑ። መጀመሪያውኑም ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ያውቁ የነበሩት አቶ ነብዩ ለረጅም አመታት ዜግነታቸውን ሳይቀይሩ ቆይተዋል። የእርሳቸው ወደዚህ መምጣት ደግሞ ሌላ ብስራትም ይዞ መምጣት ቻለ። ምክንያቱም በኢትዮጵያ የጎልፍ ስፖርት አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲጓዝ እድሉን የከፈተ አጋጣሚ።
የጎልፍ ስፖርት
አቶ ነብዩ አገራቸው ሲገቡ ኮሪያዊ ዜግነት ካለው ጓደኛቸው ጋር ወደ አዲስ አበባ መጡ። ከዚሁ ጓደኛቸው ጋር በአዲስ አበባ በሚገኘው የጎልፍ ክለብ ውስጥ ጎልፍ ይጫወቱ ነበር። አቶ ነብዩ ወደ አገራቸው ከገቡ 6 ወራት ተቆጥረዋል። ጊዜው ደግሞ ከ11 አመታት በፊት ነው። ለጎልፍ ጨዋታ ባላቸው ፍቅር እና ተሳትፎ የክለቡ ሊቀመንበር በመሆን ተመረጡ። በዚህ የተነሳ ይህ ስፖርት እንዲያድግ አንድ ስራ መስራት ነበረባቸው። የጎልፍ ስፖርት በኢትዮጵያ ውስጥ ተስፋፍቶ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ አንዳንድ ስራዎች ለመስራት በስፍራው ካፈሯቸው ጓደኞቻቸው ጋር ስምምነት ላይ ደረሱ።
የእንግሊዝ ኤምባሲ ጎልፍ ኮርስ፣ ከኮሚሽነር ዘሪሁን ቢያድግልኝ እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ጎልፍ ፕሬዚዳንት ከሆነው ከአቶ አበባው ቢሆነኝ እና ሌሎች የኮሚቴ አባላቶች ጋር በመሆን የመጀመሪያውን የጎልፍ ማህበር አቋቋሙ። እርሳቸውም ባላቸው ጠንካራ ተሳትፎ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል። በአገራቸው ላይ በልማት ስራ ለመሳተፍ የመጡት አቶ ነብዩ የሚወዱትንም ስፖርት እግረ መንገዳቸውን መደገፍ ጀመሩ። የጎልፍ ስፖርትም ልክ እንደሌሎቹ ፌዴሬሽኖች ሁሉ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ በቻሉት አቅም ደግፈዋል።
«በወቅቱ ብዙ ኢትዮጵያዊ ጎልፈኞች አልነበሩም» በማለት ለስፖርቱ መሰረት ለመጣል ብዙ ስራዎች መስራታቸውን ያስታውሳሉ። በወቅቱ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝም ከእርሳቸው ጋር በመሆን ለምስረታው እና ህጋዊ ፍቃድ ማውጣቱ ላይ ትልቅ ስራ መስራታቸውን ይናገራሉ። አሁን አዲሶቹ አመራሮች ስፖርቱ እንዲስፋፋ ጥረት እያደረጉ ነው። ኢትዮጵያውያኑ ስፖርተኞችም በምስራቅ አፍሪካ አገራት በመሄድ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን እያደረጉ መሆኑንም ይገልፃሉ። ሆኖም እድገቱ በሚፈለገው ደረጃ አጥጋቢ ላይሆን ይችላል ይላሉ። አቶ ነብዩ «አሁን ላይ ስፖርቱን ፈር ለማስያዝ የሚደረገው ጥረት ትልቅ ተራራ የመውጣት ያህል ነው» በማለት ስፖርቱ በኢትዮጵያ ያልተለመደ ከመሆኑ አንፃር ለማስተዋወቅ የሚደረገው ጥረት ከባድ ፈተናዎች እንዳሉት ይናገራሉ።
የብስክሌት ስፖርት
የብስክሌት ስፖርት ጠንካራ የፋይናንስ መሰረት ያላቸው ክለቦችን ይጠይቃል። በመወዳደሪያ ቁሳቁሶች፣ ትጥቆች የተወዳዳሪዎች ደመወዝን ችሎ ካምፕ ለማስቀመጥ የሚችሉ ጠንካራ ክለቦችንም ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ለአዲስ አበባ ብስክሌት ክለቦች መዳከም ምክንያት እንደሆነም ይነገራል። የከተማዋ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ረዘነ በየነም ይህንን ሀሳብ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ አጫውተውን ነበር። «ከ13 ዓመት በፊት እንደነ ማርፌን እና ብርሃንና ሰላም የመሳሰሉ የብስክሌት ክለቦች በፋይናንስ አቅም መዳከም ምክንያት ነበር የፈረሱት» በማለት ነበር በወቅቱ የነገሩን።
ከላይ ከተነሳው ሃሳብ በተጨማሪ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ስፖርቱ እንዲጠናከር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ መዳከሙን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። በተጨማሪም አቅም ያላቸው ባለሀብቶች ክለቦችን በመመስረት ለመደገፍ ያላቸው ፍላጎት የተዳከመ መሆኑ የችግሮቹ ድምር ውጤት ላይ ተፅእኖ ይፈጥራል። ከላይ ስለ ብስክሌት ስፖርት ፈተናዎች ያነሳነው ያለምክንያት አይደለም። እነዚህ ተግዳሮቶች ቢፈታተኑትም በተለይ የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ችግሮቹን ተቋቁሞ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ጥረቶች እያደረገ ነው። ስፖርቱ ለውጥ እንዲያመጣ ጥረት በማድረጉ ላይ ደግሞ ቀዳሚ ተሳታፊ በመሆን የአቶ ነብዩ ሳሙኤል ስም ይነሳል። አሁን ላይ የአዲስ አበባ ብስክሌት ስፖርት ፌዴሬሽን የበላይ ጠባቂ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
አቶ ነብዩ በርካታ ፈተናዎች የተጋረጠበትን ስፖርት ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በመሆን እየደገፉት ይገኛሉ። ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች አካባቢ የማይጠፉት ሰው እንዴት ወደ ብስክሌቱ ሊመጡ ቻሉ? ምን አይነት ተግባራትስ እስካሁን ድረስ አከናውነዋል።
«ጋዜጠኛ ሰለሞን ገብረእግዚአብሄር በአንድ ወቅት ስለጎልፍ ስፖርት ቃለ መጠይቅ ሊያደርገኝ መጥቶ የብስክሌት ስፖርትን ድጋፍ እንዳደርግ ጥያቄ አቀረበልኝ» የሚሉት አቶ ነብዩ ስፖርቱን ለመደገፍ ፍቃደኛ ሆነው ከዚህ ቀደም የጎልፍ ስፖርት ላይ ሲያደርጉ የነበረውን እንቅስቃሴ በብስክሌቱም ለመድገም ጥረት እንዲያደርጉ የእርሱ ጥያቄ ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ። በዚህም በዘኮሊና ኮንስትራክሽን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ያደረገውን ውድድር ስፖንሰር ማድረግ ቻሉ። በዘርፉ «ዘኮሊና የብስክሌት ክለብ» ማቋቋም እና ስፖርተኞችን መደገፍ ችለው ነበር።
አቶ ገረመው ደንቦባ በኢትዮጵያ የሳይክል ስፖርት ጅማሮ ትልቅ ስፍራ አላቸው። እኚህን አንጋፋ ሰው ማመስገን ክብር ለሚገባው ተገቢውን ክብር ከመስጠት ባለፈ ስፖርቱ እንዲነቃቃ ትልቅ እድል የሚከፍት ነው። ይህን ተግባር ደግሞ ከአመታት በፊት አቶ ነብዩ አድርገውታል። ከአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን እንዲሁም ከብስክሌት ፌዴሬሽኑ ጋር በመተባበር ቀዳሚ ስፖንሰር በማድረግ 623 ኪሎ ሜትር የሸፈነ «ጉዞ ወደ አባይ የሳይክል ቱር ውድድር» በማዘጋጀት እኚህ አንጋፋ ሰው በክብር እንግድነት እንዲገኙ እና ለወጣት ስፖርተኞቹ ብርታት እንዲሆኑ ማድረግ ችለዋል። ይህ ውድድር የመጀመሪያው አገር አቋራጭ የብስክሌት ውድድር ሆኖ ተመዝግቧል።
ስፖርቱን ለማሳደግ ምን ይደረግ
በመግቢያችን ላይ ጠቆም አርገን እንዳለፍነው ስፖርት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። ነገር ግን ከዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን የግዴታ ጠንካራ ስፖርተኞች እንዲፈጠሩ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን ማድረግ ያስፈልጋል። ጥሩ ጥላ ሊሰጥ የሚችል ዛፍ ለማግኘት ከተፈለገ መጀመሪያ ችግኝ ተክሎ ተንከባክቦ ማሳደግ ያስፈልጋል። ስፖርትም በዚህ ተመሳሳይ የራሱን አቅም እስኪፈጥር ድረስ ድጋፍ ማድረጉ ተገቢ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ በቀጥታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጎን ለጎን አቅም ያላቸው ባለሀብቶች ድጋፍ ማድረግ ከቻሉ ፈጣን ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
ከላይ የተነሳውን ሃሳብ አቶ ነብዩ ይጋሩታል። « በአገር ውስጥ የስፖርት ውድድሮችን ስፖንሰር ማድረግ የተለመደ አይደለም። ልክ እንደሌሎቹ አገራት በኢትዮጵያም ይሄ ተግባር ሊለመድ ይገባል» በማለት ይህ እንዲሆን በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ስፖንሰር ለማድረግ አቅም ያላቸው አካላት ጋር በመድረስ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል የሚል ምክረ ሃሳብ ያስቀምጣሉ።
«ስፖርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ወጣቶች ላይ እንደመስራት ነው» የሚል አመለካከት ያላቸው አቶ ነብዩ ባለሀብቶች በዚህ ላይ ቢሳተፉ መልካም ሰብእና እና በራሱ የሚተማመን ዜጋን በቀላሉ ማፍራት ይቻላል በማለት አቅሙ ያላቸው አካላት ተሳታፊ መሆን አለባቸው በሚል ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ። ህብረተሰቡ፣ ባለሀብቱ ፣ ወጣቱ እንዲሁም ባለስልጣኖቹ አንድ አይነት አቋም ይዘው ስፖርቱን ለማሳደግ መቀናጀት እንዳለባቸውም ይገልፃሉ።
በስፖርት የታነፀ ተተኪ ትውልድ
«ወጣቱ ተተኪ ትውልድ ነው። ማንኛውም ዜጋ እድሜውን ጨርሶ ይሄን ምድር ጥሎ መሄዱ አይቀሬ ነው» በማለት ከሁሉ ቅድሚያ ወጣቱ ትምህርቱ ላይ ማተኮር ይገባዋል የሚል ሃሳባቸውን ይገልፃሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ጠንካራ ማንነት ለመገንባት የሚጠቅመው ስፖርት ላይ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅበታል ይላሉ። ከዚህም ሌላ በአገር አቀፍ፣ በአህጉር እና በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የሆኑ ስፖርተኞችን ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን ይገልፃሉ። ይህ የሚሆነው ደግሞ በቅድሚያ በወጣቱ ላይ ከታች ጀምሮ መስራት ሲቻል ብቻ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ያስረዳሉ።
አቶ ነብዩ ስፖርቱ ላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ። በጎልፍ፣ በብስክሌት ስፖርቶች ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል። የቴኒስ ፌዴሬሽንም ስፖንሰር እንዲያገኝ ያደረጉት ድጋፍ አለ። እርሳቸው ከላይ የተጠቀሱት ስፖርቶች ላይ ተገድበው እንደማይቀሩ ይናገራሉ። «አቅሜ እስከሚችለው ድረስ ለሁሉም ስፖርቶች በተለያየ መንገድ ድጋፍ አደርጋለሁ» በማለትም አሁን ካለው በተሻለ ሁኔታ ስፖርት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦዋቸውን እንደማያቋርጡ ይናገራሉ።

ዳግም ከበደ

Published in ስፖርት

እኔ እምለው? ይሄ ግን ‹‹እገሌ አንብቦ ነው ያበደ! እገሌን ፊዚክስ ነው ያሳበደው! እገሌን ፍልስፍና ነው ያሳበደው!›› የሚባለው ነገር እውነት ይሆን እንዴ? ኧረ ጎበዝ ይህን ነገር በጣም በተደጋጋሚ ነው የሰማሁት፡፡ ብቻውን የሚያወራ ሰው ሲታይ ‹‹ጎበዝ የፊዚክስ ተማሪ ነበር አሉ›› ሲባል እሰማለሁ፡፡ ቆይ ግን ይሄ ፊዚክስ የሚባል ትምህርት አጋንንት አለበት ማለት ነው? በእውነት ይሄ ነገር ውሸት መሆን አለበት፡፡ የሚያሳብድ ቢሆን ኖሮ እኔን ነበር የሚያሳብደኝ፡፡ ወይስ ፊዚክስ ላይ ጎበዝ የሆኑትን ነው የሚያሳብድ?
እንዲያው ወደ ቁም ነገሩ ስንገባ ‹‹ንባብ ይገድላል፤ ትርጉም ያድናል›› የሚባለው ነገር በጣም ትክክል ነው፡፡ ንባብ ብዙዎችን ገድሏል፡፡ አንድ ነገር ደፍሬ ልናገር፡፡ ይህን ማለት በብዙዎች ዘንድ እንደማያስማማና በጣም እንደሚያከራክር አምናለሁ፡፡ ‹‹ንባብ አይመረጥም›› በሚለው ነገር አልስማማም፡፡ ንባብ ይመረጣል፡፡ ይመረጣል ማለት ግን የግድ አንድ አይነት የሆነ ነገር ብቻ ማንበብ ማለት አይደለም፡፡ አወንታዊም ይሁን አሉታዊ ነገር መነበብ አለበት፡፡ መመረጥ አለበት ስል በፍጹም ከአዎንታዊና አሉታዊነት አንፃር አይደለም፡፡ በቃ ምንም የማይጨምርልኝ ነገር ላይ ጊዜ አላባክንም፡፡
አሁን ትልቅ ችግር የሆነው ይልቅ መመረጥ አለመመረጡ አይደለም፡፡ ችግር የለውም የትኛውንም ነገር እናንብብ፡፡ ትልቁ ችግር ግን ትርጉም ላይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ትርጉም ሲባል ብዙ ሰዎች ከአንድ ቋንቋ ወደሌላ ቋንቋ መተርጎም ይመስላቸዋል(ያው በዚህ አጋጣሚ ልናገር ብዬ ነው)፡፡ ትርጉም በራሱ በተጻፈበት ቋንቋም ይተረጎማል፡፡ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈን ነገር በአማርኛ ቋንቋ ትርጉም መስጠት ማለት ነው፡፡ በአጭሩ ትርጉም እንደ ዓውዱ መረዳት ማለት ነው፡፡
ታዲያ ይሄ የትርጉም ነገር ብዙዎችን አሳስቷል፡፡ በተለይ በዚህ በማህበራዊ ድረ ገጽ ያለውንማ ስንቱ ይጠቀሳል? እንዲያውም አንድ ምሳሌ ትዝ አለኝ፡፡ አንድ ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ታዋቂ የሆነ ሰው ስለ አጼ ምኒልክ አንድ ነገር ጽፎ ነበር፡፡ ያው መቼም ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ያለውን የብሄር ሽኩቻ ታውቃላችሁ፡፡ ጸሐፊው የጻፈው አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ ለማሳየት ነው፡፡ እናም የጸሐፊው መልዕክት ‹‹አጼ ምኒልክ የአማራ ናቸው የምትሉ ሰዎች፤ የመጀመሪያው ትምህርት ቤት የአማራ ነው ማለት ነው? ባቡርን ያስገባው አማራ ነው ማለት ነው? የጣሊያን ወራሪን ያስወጣው አማራ ነው ማለት ነው? እንግዲህ አጼ ምኒልክ የአማራ ናቸው ካላችሁ አጼ ምኒልክ የሰሩት ሁሉ የአማራ ነው›› ይላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትርጉም ልብ በሉ! ለዚህ ጸሐፊ ከሥር የተሰጡት አስተያየቶች አብዛኞቹ ‹‹እንዴት አጼ ምኒልክን አማራ ናቸው ትላለህ? እንዴት የሰሩት ሥራ ሁሉ የአማራ ይሆናል?›› የሚል ነበር፡፡ ጸሐፊው እኮ የአማራ ናቸው የሚለውን ነው የተቃወመው ነበር፡፡ በተቃራኒው ተመሳሳይ ሀሳብ ያዙ ማለት ነው፡፡ ተመሳሳይ ሀሳብ ይዘው ግን አልተግባቡም፡፡ ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ በብዛት የምንታዘበው ይህንን ነው፡፡ አንድ ቃል ሲገኝ ቶሎ ብሎ ወደ ስድብ መሮጥ፡፡ ኧረ ይባስ ብሎ ጽሑፉን ጨርሰው ሳያነቡ ወደ ስድብ ወይም ወደ አድናቆት የሚሮጡም አሉ፡፡ ጸሐፊው እኮ መግቢያ ላይ በምጸትም በቀልድም ሊጀምር ይችላል፡፡
እንግዲህ ይሄ ቀላሉ ምሳሌ ነው፡፡ መጽሐፍ አንብበው የተበላሹ ሰዎችን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ሰው አንብቦ አዋቂ ይሆናል እንጂ እንዴት ወደ ጎዳና ይወጣል? የዚያ መጽሐፍ ጸሐፊ እኮ በሰላም ኑሮውን እየኖረ ነው፤ የሱ ተደራሲ ግን አብዶ መንገድ ላይ ይወድቃል፡፡ ይሄ ታዲያ አያሳዝንም? መጽሐፉ በራሱ እኮ የሚያሳብድ ሆኖ አይደለም፤ ሲጀምር እንዴት የሚያሳብድ መጽሐፍስ ይኖራል?
እንዲያው ይፋዊ እብደቱ ይቅርና አቋማቸው የተበላሸ ሰዎች እኮ በየቅርብ ጓደኞቻችን የምናየው ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ፣ ለምንም ነገር ግድየለሽ መሆን፣ የሌለ ጸባይ ማውጣት በብዙ ወጣቶች ላይ የምናየው ነው፡፡ ለብቻ ተነጥሎ መሄድ ከጊዜ በኋላ የሚያመጡት ጸባይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለብቻ ተነጥሎ መሄድ በእነርሱ ቤት አዋቂ መሆናቸው ነው፤ ግን አዋቂነት ሳይሆን ስንፍና ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ያነበቡ ሲመስላቸው ዳሩ ግን ጭራሽ ከእውቀት እየራቁ ነው፡፡
ንባብ እኮ የሰው ልጅ ሕይወት ውጤት ነው፤ የሰው ልጅ ሀሳብ ነው፡፡ ስለዚህ ከመጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ከሰውም የምናስተውለው ነገር መኖር አለበት፡፡ አንባቢ ብቻ እኮ ሳይሆን ጸሐፊም መሆን አለብን፡፡ ጸሐፊ ደግሞ የሰዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና ማህበራዊ ሕይወት አላየም ማለት ታዲያ ምኑን ጻፈው? ይሄ ማለት እንግዲህ እነዚህ ሰዎች ያነበቡት እውቀት ፈልገው ሳይሆን ‹‹ማንበብ የጎበዝ ሰው መለያ ነው›› ስለተባለ ብቻ ነው፡፡ አንባቢ ለመባል ብቻ ነው፡፡
አንድ ከንባብ ጋር የሚጋጭ የራሴን ልምድ ልንገራችሁ፡፡ በመኪና ረጅም ጉዞ በምሄድበት ጊዜ በፍጹም መጽሐፍም ሆነ መጽሔት አላነብም(ሰነፍ ማለት ይቻላል)፡፡ በእኔ እምነት ግን ስንፍና አይደለም፡፡ ረጅም ጉዞ ስሄድ ከቤቴ ከቆየው መጽሐፍ ይልቅ ዳግም የማላገኘው ብዙ የማየው ነገር አለኝ፡፡ አንዳንዶቹ መጽሐፍን እንደ እንቅልፍ መከላከያ ይጠቀሙታል፡፡ እኔ ደግሞ ተፈጥሮን እያየሁ ስሄድ ነው እንቅልፍ የማይወስደኝ፡፡ በተለይም በማላውቀው አካባቢ ከሆነ የምሄደው እንኳን ከቤቴ የቆየ መጽሐፍ አዲስ የወጣ ነው ቢሉኝ አላነብም፡፡ ይህን መጽሐፍ እኮ ሌላ ቀን የትም ላገኘው እችላለሁ፡፡
ልብ በሉልኝ ንባብን እያጣጣልኩ አይደለም፡፡ ዳሩ ግን ይሄ ስትሄዱም፣ ስትበሉም፤ በታክሲ ስትሄዱም እያነበባችሁ የሚለው ነገር አያስማማኝም፡፡ እንዲህ ከሆነማ ሰው ሳይሆን ማሽን ሆንኩ ማለት እኮ ነው፡፡ የሰው ልጅ ለማወቅ አካባቢውን ማስተዋል አለበት፡፡ ለምሳሌ አንድ ከአውቶብስ ተራ ወደ መገናኛ የሚሄድ ሰው ታክሲ ውስጥ እያነበበ ይሂድ እንበል፡፡ ፒያሳ አካባቢ የሆነ አስገራሚ ነገር ቢታይ ንባቡን ትቶ አሻግሮ እንደሚመለከት ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ያ ፒያሳ ላይ የታየው ነገር እንግዲህ ምናልባትም ራሱን የቻለ መጽሐፍ ሊሆን ይችላል፡፡
ይህ የሆነው እንግዲህ ንባብን አልተረጎምነውም ማለት ነው፡፡ ንባብ ማለት ምን እንደሆነ አላወቅነውም ማለት ነው፡፡ ከተፈጥሮ ውስጥ ብዙ የሚነበብ ነገር አለ፡፡ ከሰዎች ውስጥ ብዙ የሚነበብ ነገር አለ፡፡ እንዲያውም ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ ‹‹አዲስ አበባ ውስጥ በአንበሳ ባስና በሀይገር ያልሄደ ሰው ስለአዲስ አበባ ማውራት አይችልም›› እውነቱን ነው፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ ጉዶች፣ የሸገር ምንድንትስ…›› ከሚሉ መጽሐፎች ይልቅ በአንበሳ ባስ እና በሀይገር መሄድ ስለአዲስ አበባ ብዙ ይናገራል፡፡
‹‹ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል›› ከሚለው መሪ ቃል ፊት ለፊት ‹‹ማንበብ ጎደሎ ሰው ያደርጋል›› የሚል መልዕክትም ይታየኛል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ተምረው ምንም ትምህርት ቤት ካልገባ ሰው በላይ ሲበለሻሹ ይታያል፡፡ ራሳቸውንም ሲጎዱ ይታያል፡፡ የሚነበብ ነገር ለማወቅ እንጂ እያንዳንዱን ነገር እንደወረደ አይተገበርም፡፡ መለወጥ ማለት 10 መጽሐፍ አንብቦ 10 ጊዜ አቋምን መቀያየር ማለት አይደለም፡፡ የሚነበብ መጥፎውንም ደጉንም ለመለየት ነው፡፡ እናንብብ፤ ግን እንተርጉም!

ዋለልኝ አየለ

 

ከ77ዘመን  ጭላፊ ትውስታ

 

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሰባ ሰባት ዓመቱን ሊደፍን ሐሙስን እየጠበቀ ነው፤ እንኳን አደረሰን። ይህ ጋዜጣ አንጋፎችን ያፈራ አንጋፎችም ያደመቁት ነው። ብዕራቸው የተባ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን ጠቅሶ፤ ታሪክን አውስቶ አዲስ ዘመንን አለማንሳት አይቻልም። በየዘመኑ የተከሰቱ ጉዳዮች በአብዛኛው በጋዜጣው ላይ ሰፍረዋል። በዜና መልክ የተሠሩ ነገር ግን አዝናኝ የነበሩ፤ ዜናዎችም በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተለያየ ጊዜ ተነበዋል። እኛም ዛሬ ላይ ከመጻሕፍቱ መገኛ ጎራ ብለን ወደኋላ መለስ ያሉትን የአዲስ ዘመን ህትመቶች ስንገላልጥ አዝናኝ ሆነው ያገኘናቸውን ዜናዎችና ወሬዎች እንዲህ ቀንጨብጨብ አድርገን አቅርበናል።
በነገራችን ላይ ዜናዎቹ በጊዜው ቁም ነገርም ነበሩ። አሁን ባለንበት አውድ ስናያቸው ነው የሚያስቁት። ለምሳሌ ዶሮ አራት ብር መግባቱ ሲሰማ ያኔ ዜና ነበር፤ አሁን ግን ሳቅን ይፈጥራል። የባሰ አለና አላሉም መሰል የባሰውን እኛ አሁን ላይ ስላየን ነው። ደግሞ ወደፊት የዛሬው የእኛ ነገር የሚያስቀው ይመጣ እንደሆነ በምን ይታወቃል?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 1968 ዓ.ም
ርዕስ፦ «ገበያው!»
ጸሐፌ፦ መርስዔ ኃዘን አበበ
«ዘይት፣ ድንች፣ ዱባ፣ ዓሣ፣ ሱፍ፣ ዋጋው እያደገ ሲሔድ፤ ለምን አትጽፉም? የማንን ጎፈሬ ታበጥራላችሁ? ስንት የሚጻፍ እያለ የእናንተ ብርዕ የሚያሾለው ወደሌላው ነው። ሆድ፤ የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል። ጻፉ ዝም አትበሉ» ባለፈው ሳምንት ከአስር ያላነሱ ሰዎች ስልክ እየመቱ የጠየቁን ጥያቄ ነው። ድሮ በስዊዝ ካናል ምክንያት ድንች ተወደደ ይባል ነበር። አሁን ደግሞ በዶላር ምንዛሬ ማዘቅዘቅ ማመካኘት ይቻላል።
እነዘይት፣ እነድንች፣ ቲማቲም ከእንግዲህ እንኳን ያላቸው የተወዳጅነት ዕድሜ ከስምንት ቀን አይበልጥም። (ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ማዕድ ሥጋ አትክልትና ፍራፍሬ እምብዛም ስለማይወደድ ማለቴ ነው) በዚህ ሳምንት አጋማሽ ገደማ ከአየር መንገድ፣ ከአገር ውስጥ ገቢ፣ ከቴሌ፣ ከውሃ ክፍል፣ ከማዘጋጃ ቤት፣ ከንግድ ባንክ፣ ከሌሎች አድራሻ ካልተነገሩን ሰዎች የተላለፈልን የስልክ መልዕክት ተመሳሳይ ነው።...
...በክርስቲያኑ ኅብረተሰብ ልማድ ፋሲካ ከፈንጠዝያ ፈጣሪዎች በዓሎች አንዱ ነው። በሥጋዊ መልኩ ሲታይ። በግ እስከ ፩፻ ብር ደርሷል። የ፳ ብርም አለ፤ በግ ከተባለ። ደኅና ዶሮ ፬ ብር፣ ኪሎ ቅቤ ፭ ብር ገብቷል። ይህን ተዘዋውረን አይተናል። በ፩፻ ብር ሰንጋ መግዛት የለመደ ቢኖር አዲስ አበባ ውስጥ የበግ ዋጋ ሆኗል እንለዋለን።
«ባለበግ ዋጋው ስንት ነው?»
«ይኽኛው ነው? ፩፻ ብር»
«እንዴ! ሰንጋ በሬ እኮ አልገዛም፤ ይልቅ እርግጡን ተናገር፤ ምን ይቀልዳል?»
«ሰንጋማ ከፈለጉ ቄራ ይውረዱ። ይህ የበግ ተራ ነው» ይህ የመሳሰለ ቃላት ገዢና ሻጭ ሲወራወሩ ሰምተናል። የባሰበትም እየገዛ ሔዷል።...የእኛ መጻፍስ እስከዚህ የገበያውን መልክ የሚለውጥ አይመስለንም።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26 ቀን 1956ዓ.ም
ርዕስ ፦ ሴይቸንቶዎች እንደገና በስሙኒ?
ሴይቸንቶም ሆነ፤ ሌላው የሕዝብ ማመላለሻ አውቶሞቢል ሁሉ ታክሲ ሜትር ሊገባለትና «ሴይቸንቶም በኪሎሜትር ሃያ ሳንቲም ሊያስከፍል ነው» ተብሎ ሰሞኑን የወጣው ወሬ እውነት አለመሆኑን፤ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ፕሬስ ክፍል በመጨረሻ በሰጠው ማብራሪያ አስተባብሎታል።
ብርቱ ክርክር ያስነሳውና ይህንን ዜና የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ በተቀዳሚ ሲገለጥ የዜናውን ምንጭ መጥቀሱ ቢታወስም፤ የማዘጋጃ ቤት ፕሬስ ክፍል በኋላ ባወጣው ማብራሪያ፤ ታክሲ ሜትር የሚገባላቸው አውቶሞቢሎች ደንበኛ ታክሲ የሆኑና መቆሚያ ቦታ የተወሰነላቸው፤ በየትልልቅ ሆቴሎች የሚያገለግሉት ብቻ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ሴይቸንቶ ግን ከነበረው ዋጋ ከፍ አድርጎ እንዲጠይቅ ያልተወሰነ ሲሆን፤ እንዲያውም በየምክንያቱ ከተለመደው ዋጋ ለመጨመር መንገደኛውን እንዳይጎዳ ዘዴ መፈለጉን ለማስታወቂያ ክፍሉ አስረድቷል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 1962ዓ.ም
ርዕስ፦ የቢሮ ሴቶች ሥራ ሲፈቱ ምን ያወራሉ?
በእያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ውስጥ የጸሐፊዎች አዳራሽ /ታይፒንግ ፑል/ አለ። ይኸውም ልዩ ጸሐፊ ካልሆነች በስተቀር ለተመሳሳይ ሥራ ሶስት ወይም አራት ከዛም በላይ ሆነው በአንድ ክፍል የሚሠሩ ሴቶች አሉ። ሆኖም ሴቶቹ ሥራ ሲፈቱ አንድ ላይ ተሰብስበው የሚያወሩት ወሬ ምንድን ነው? ስለ አለባበስ? ስለልጆቻቸው? ስለትዳር? ወይስ ስለዓለም ጉዳይ? በዛሬው እለት ትዳር የያዙት የቢሮ ሴቶች ሥራ ሲጨርሱ ስለምን እንደሚያወሩ ለማወቅ የአንድ መሥሪያ ቤትን ታይፒስቶች ጠይቄ ያገኘሁት መልስ የሚከተለው ነው።
«አብዛኛውን ጊዜ የምናወራው ስለትዳራችን ነው። ይኸውም የእኔ ባለቤት እንዲህ ዓይነት ጠባይ አለው፤ ሌላዋ ደግሞ የኔም ይህን አይነት ጠባይ አለው በማለት ታወጋለች። ሌላው አርዕስት ደግሞ የልጆቻችን አስተዳደግና አጠባበቅ ነው። ሌላው የአለባበስ በጠቅላላው የአጋጌጥ ጉዳይ ነው። በወሬያችን መካከል ደግሞ ጣልቃ ሳናስገባ የማናልፈው ይህቺ ስታምር ይህቺኛዋ ስታስጠላ የሚለውን ዓረፍተ ነገር ከአንደበታችን ሳትወጣ አንለያይም» በማለት ገልጠዋል።
«ስለዓለም ሁኔታ ግን የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት፣ የቬትናም ሁኔታ፣ የአንዱ መሾም፣ የሌላው መሻር በእኛ ዘንድ አይወራም። እንዲያውም ታስቦ አያውቅም። ምክንያቱም ብናስበው የእኛ ማሰብ የጦርነቱንም ሆነ የመሻሩን ጉዳይ ካለበት ፈቀቅ አያደርገውምና ነው።» ሲሉ በኅብረት ገልጠዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 1960ዓ.ም
ርዕስ፡ በጎባ የስልክ መስመር ተከፈተ
በባሌ ጠቅላይ ግዛት አዲስ የቴሌፎን አገልግሎት መከፈቱን የኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ቦርድ አስታወቀ።
የቴሌኮሙኒኬሽን የማስታወቂያ ክፍል እንደገለጠው ከጧት ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ ሰባት ሰዓት ድረስ፤ እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ አስራ ሁለት ሰዓት ድረስ ሁል ቀን የጎባ ስልክ ቤት ክፍት በመሆን አገልግሎቱን ይሰጣል።
ከአዲስ አበባ ጎባ ለሚደረገው ጥሪ የሚከፈለው ሰባ ሳንቲም ነው። ከጎባ ዲንሾ ለሚደረገው ጥሪ ሰላሳ ሳንቲም ሲሆን ከጎባ አዳባ ለሚደረገው ጥሪ ደግሞ ሃምሳ ሳንቲም ነው። ከጎባ ዶዶላ፣ ኮፈሬ፣ ሻሸመኔ፣ ነገሌ፣ አርሲና አዋሳ እያንዳንዱ አገር ጥሪ ሰባ ሳንቲም የሚከፈል መሆኑን ቴሌኮሙኒኬሽን አስታውቋል። ቴሌኮሙኒኬሽን የጎባ መደቡ በሻሸመኔ ክፍል ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 26 ቀን 1957ዓ.ም
ርዕስ፡ ፭ የውጭ በጎች በ፭ ሺህ ብር ተገዝተው መጡ
5 በጎች በ 5 ሺህ ብር ከፈረንሳይ አገር ተገዝተው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። በጎቹ የተገዙት በባሌ ጠቅላይ ግዛት ለተቋቋመው የበግ ርባታ ነው። እነዚህ ከፈረንሳይ ሀገር የተገዙት አምስት በጎች በዓለም የታወቁት የበግ ዘሮች ውስጥ ምርጥ የሆኑት ናቸው።
እነዚህ በፊት በአገራችን ካሉት በጎች ጋር ተደባልቀው ዘራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲበዛ ታስቦ የተገዙ ናቸው። ለሱፍ ጠጉር ሥራ የአገራችን በጎች ከውጭዎቹ ጋር በማዳቀል ጥሩ ጠጉራም በጎችን ለማግኘት በቅርብ ጊዜ ምርጥ የሆኑ በጎች ከኬንያ ተገዝተው በባሌ ጠቅላይ ግዛት ለተቋቋመው የበግ ርባታ ሥራ እንደሚደርሱ ታውቋል።
የበጎቹ ርባታ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዋርት በባሌ ጠቅላይ ግዛት የተጀመረው የበግ ርባታ ሥራ በሚገባና ተስፋ ባለው ሁናቴ እንደሚካሄድ ገልጠዋል። ለርባታው ሥራ አስር ሺህ ያገር ውስጥ በጎችን በተጨማሪ ለመግዛት ማስፈለጉን ሚስተር ዋርት ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 07 ቀን 1963ዓ.ም
ርዕስ፡ ሁለት ጠርሙስ አረቄ ሰርቆ ሁለት ዓመት እስራት ተፈረደበት
ደሴ፡- ሊጠጣ ገብቶ ጠርሙስ አረቄ የሰረቀው መላኩ ምርኸቴ የተባለ ግለሰብ በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተፈረደበት።
ከዚህ ቀደም በሌብነት ወንጀል ተከሶ ስምንት ጊዜ የተቀጣው መላኩ ምርኸቴ ዘጠነኛውን የስርቆት ወንጀል ሲፈጽም የተያዘው በደሴ ከተማ በአለፈው ሐምሌ ፳፯ ቀን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም ነው።
ተከሳሹ በዚሁ ቀን እመት የሺ ነዋይ ከተባሉት ሴት መጠጥ ቤት ገብቶ ሁለት ጠርሙስ አረቄ ሰርቆ መውሰዱን እራሱ ከማመኑ በላይ በማስረጃም ተረጋግጧል።
በዚህ አድራጎቱ ተከሶ በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጣ የደሴ ዙሪያ አውራጃ ፍርድ ቤት ትላንት በዋለው ችሎት ወስኖበታል።
አዲስ ዘመን ጥር 23 ቀን 1956ዓ.ም
ርዕስ፡ በየቀኑ አስራ አራት ሺህ ሳባ ጠጅ ያልቃል/ የሳባ ብርዝ በሱዳን ደኅና ገበያ አለው
በየመንደሩ ጠጅ ቤቶች ከሚጣለውና ከሚጠጣው ሌላ በቀን ፲፬ሺህ ጠርሙስ የሳባ ጠጅ እንደሚያልቅ ከሳባ ጠጅ ፋብሪካ የተገኘው ዜና አመልክቷል። ይኸውም በቀን ፯ሺህ ፭፻ መቶ ሊትር መሆኑ ነው።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጣር በ፲፱፻፷፪ዓ.ም መጨረሻ ገደማ ላይ በግርማዊ ንጉሰ ነገስት ተመርቆ የተከፈተው ይህ የጠጅ ፋብሪካ ዛሬ ፩፻፳ ሠራተኞች እንደሚገኙበት እና ከነዚህም ከመቶ ዘጠና ስድስቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ታውቋል።
የንብና የሰፈር አርማ ያለበት የሳባ ጠጅ በሶስት ዓይነት ደረጃ ይጣላል። «ሱፒርየር» የተባለው ፰ በመቶ አልኮል፤ «ኤክስትራ» የተባለው ፲ በመቶ አልኮል፣ «ፍሌወር ዴ ሳባ» የተባለው ደግሞ ፲፭ በመቶ አልኮል እንደሚገኝበት ታውቋል።
የሳባ ጠጅ በመላ ኢትዮጵያ ተወዳጅነትን እያገኘ በመሄዱ ፋብሪካው ደኅና ትርፍ እንደሚያገኝ ታውቋል። በተለይም በቅርቡ ያወጣው ጌሾ የሌለበት ብርዝ በእስላሞች ዘንድ ደኅና ተፈላጊ ሆኗል። የሳባ ብርዝ በሱዳንም ደኅና ገበያ እንዳለው የፋብሪካው ቃል አቀባይ ገልጧል።
ለሳባ ጠጅ የሚሆነው ማር የሚመጣው ከጎጃም፣ ከወሎ እና ከበጌምድር ሲሆን ጌሾው ደግሞ ከደብረ ብርሃን መሆኑ ታውቋል። ከሁሉም የጎጃም ማር በአይነት ብልጫ እንዳለው ለመረዳት ተችሏል። ቃል አቀባዩ እንደገለጡት በሳባ ጠጅ ስኳር ከቶ አይገባበትም።
የሳባ ጠጅ የኢንተርናሲዮናልን የመጠጥ ደረጃ የያዘ ከመሆኑም በላይ በየጊዜው በፓስተር ኢንስቲትዩት እንደሚመረመር ታውቋል።

ሊድያ ተስፋዬ  

 

Published in መዝናኛ
Sunday, 03 June 2018 20:31

77 ትውስታዎች

ዛሬ የነበረ ቀን ከምኔው ትናንት እንደሚባል አይታወቅም፤ ጊዜው ይሮጣል። ከጊዜው ጋር አብሮ መሮጡና ወደፊት መገስገሱ እንዳለ ሆኖ ታድያ በትዝታም፣ በምሳሌነትም ደግሞ ታሪክን ማወቅ መልካም ነገር ነውና ታሪክን ለማወቅ ወደኋላ መለስ ብሎ ያለፈውን መዳሰስና መቃኘት አስፈላጊ ይሆናል። እንዲህ ባለው ምልሰት ዛሬ ሁለት ርዕሶችን እንዳስሳለን። እነሆ የ77 ዓመታት ትውስታ!

 

እለቱ ቅዳሜ ነው፤ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም። ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በአውቶሞቢል ሆነው በአጀብ የሚሄዱበት ምስል ከፊት ገጽ ላይ የሚገኝ፤ አርበ ጠባብ ቁመቱ 42፣ ስፋቱ ደግሞ 31 ሴንቲ ሜትር የሆነ፤ ከራሱም ላይ «አዲስ ዘመን» የሚል ስም በጉልህ የታተመበት ብሔራዊ ጋዜጣ ለአንባብያን ቀረበ። ከፎቶው ዝቅ ብሎ የሰፈረው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፤ «ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የረዳትነቱን ሥራ ይሠራ ዘንድ ተመሠረተ።»
ስያሜው የተወሰደው አጼ ኃይለሥላሴ ከጣልያን ሽንፈት በኋላ ሚያዝያ 27 ቀን 1933ዓ.ም ካደረጉት ንግግር ነው። ጃንሆይ እንዲህ ብለው ነበር፤ «ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁ ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚሁ በአዲሱ ዘመን ሁላችንም መፈጸም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል» የዚህ ጋዜጣ ምሥረታ ታድያ ከኢትዮጵያ ነጻነት መመለስ በኋላ ጃንሆይ ካከናወኗቸው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ተግባራት አንዱ እንደነበር ይነሳል።
እናም አዲስ ዘመን ሲጀመር ይመራ የነበረው ሰባራ ባቡር አካባቢ የሚገኝ «የጋዜጣ እና ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት» የሚባል ተቋም ነበር። ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓ.ም «አንጸባራቂው ተስፋ» በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በታተመ መጽሔት ላይ፤ «የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጉዞ» በሚል ንዑስ ርዕስ ታሪኩ በይበልጥ ተብራርቶ ይገኛል።
እንዲህ ነው፤ አዲስ ዘመን የተመሰረተ ጊዜ አብዛኛው የጋዜጣው ጽሑፍ ይዘት ስለ ንጉሠ ነገሥቱ ክብርና ስለ አገር ፍቅር የሚሰብክ ነበር። በኋላም የግሪክ ፈላስፋዎችን ሥራዎች በተከታታይ በማተም ሕዝቡ እንዲያውቅ፣ እንዲመራመር ሰፊ ጥረት ይደረግ ጀመር። «ይሁን እንጂ...» ይላል ጽሑፉ፤ «ይሁን እንጂ የዜናም ሆነ የርዕሰ አንቀጽና የአስተያየት ገጽ አልነበረውም። አንዳንድ ጽሑፎችም ልክ እንደሃይማኖታዊ መጻሕፍት «በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ» ብለው የሚጀምሩ ነበሩ። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዋና አዘጋጆቹም ሆኑ ሠራተኞቹ የቤተክህነት እንጂ የጋዜጠኝነት ሥራ ልምድ ያልነበራቸው መሆናቸው እንደሆነ በዛው ጽሑፍ ላይ ይጠቀሳል።
በዚህ ሁኔታም የመጀመሪያው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ነበሩ። እርሳቸውም በጋዜጣው ታሪክ ለረጅም ጊዜ በአዘጋጅነት የቆዩ ሲሆን፤ ቆይታ ቸውም ከግንቦት 1933 ዓ.ም እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ የዘለቀ ነው። በነገራችን ላይ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዜሮ አምስት ሳንቲም የተሸጠበት ጊዜም ነበር። በተለይም ከ1938 ዓ.ም ጀምሮ አርበ ሰፊ ሆኖ እንዲሁም የገጹ ብዛት ወደ ስምንት ያደገበት ጊዜ ነው፤ ያኔ ነው በዜሮ አምስት ሳንቲም ለገበያ ይቀርብ የነበረው። ይህ ዋጋ ታድያ ለአገር ውስጥ እንጂ ለውጭ አገር ደንበኞች በእጥፍ ይጨምራል።
ከላይ በአነሳነው መጽሔት ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ጋዜጣው ከተመሰረተ ጀምሮ እስከ 1953 ዓ.ም ድረስ እጅግ አድካሚ ጉዞ እንደነበረው ይጠቅሳል፤ ይህም በጋዜጠኝነት ሙያ የተደገፈ ባለመሆኑ ነው። ጋዜጣው በባለሙያ ደረጃ ጋዜጠኞችን አሠማርቶ መንቀሳቀስ የጀመረውና አድካሚነቱ የቀነሰው ባህርማዶ በጋዜጠኝነት ትምህርት ሰልጥነው ወደአገራቸው የተመለሱት ነጋሽ ወልደማርያም ዋና አዘጋጅ ሆነው ከተመደቡ በኋላ እንደሆነ ይነገራል።
ከአቶ ነጋሽ በኋላ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ በዓሉ ግርማ፣ ማዕረጉ በዛብህ፣ ጎሹ ሞገስ፣ መርዕድ በቀለ፣ ፀሐዬ ደባልቀው፣ እምሩ ወርቁ፣ ደምሴ ጽጌ፣ ሐሰን ኡስማን፣ ወንድምኩን አላዩ፣ አንተነህ ኃይለብርሃን፣ ንጉስ ወዳጅነው እና ፍቃዱ ሞላ (አሁን) በዋና አዘጋጅነት በቅብብል አዲስ ዘመንን አዘጋጅተዋል።


አቶ ነጋሽ የአዲስ ዘመን 75ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በታተመው አዲስ ዘመን ልዩ እትም ጋዜጣ ላይ በሰፈረው አስተያየታቸው እንዲህ ብለው ነበር፤ «ከአሜሪካን አገር የጋዜጠኝነት ትምህርቴን አጠናቅቄ እንደተመለስኩ ጋዜጣው ላይ በኃላፊነት ተመደብኩ። ያኔ የፊት ለፊት ገፅ የጃንሆይ ንግግሮች፣ ጉብኝቶች፣ ልግስናዎችና ሌሎች ተግባራት የሚመለከቱ ወሬዎች ብቻ ናቸው የሚወጡት ስባል ትንሽ ደነገጥኩ። ምክንያቱም እኔ በውጭ አገር ትምህርቴ የአገሪቱ ገዢ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮችም ፊት ለፊት ገፅ ላይ ይወጣሉ፤ ሙያዊ ትምህርቱም የሚለው ያሄንኑ ነው። ታዲያ እኔ ለምን ሌሎች ትላልቅ ወሬዎች አይወጡም ብዬ ትንሽ ከበላይ አለቆቼ ጋር ተሟገትኩ።
በቀላል የሚሆን ሳይመስለኝ ቀስ እያልኩ ከግርጌ ሌሎችን ዜናዎች ማስገባት ጀመርኩ፤ እየተለመደ መጣ። ትንሽ ችላ ስባል የአስተያየት ኮለም በጀርባ በኩል ሁለተኛው ገጽ ላይ ማስፈርም ጀመርኩ። በዚህ መልኩ ቀስ በቀስ የጋዜጣውን ቅርጽና ይዘት ዘመናዊ መልክ እንዲኖረው ለማድረግ ጣርኩ። ርዕሰ አንቀጽና ሌሎች ዓምዶችም በየዘመኑ እየተፈጠሩ እነሆ እዚህ ላይ ደርሳችኋል። መልካም ነው፡፡»
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ዛሬም ድረስ ስማቸው ተነስቶ የማይጠገብና በተለይ በሥነጽሑፉ ላይ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ሰዎች አሻራ ይገኛል። ጽሑፍና ጸሐፊ ሲነሳም ቀድሞ የሚጠራው አዲስ ዘመን ነው። የአዲስ ዘመን ስልሳኛ ዓመት ልደት የተከበረ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲህ አሉ፤ «...አዲስ ዘመን የዘመኑን የሥነጽሑፍ አቅጣጫ ማስያዝና ሥነጽሑፋዊ ሂስን ለማስለመድ በር ከፍቷል። ብዙ መጻሕፍት ባይታተሙም ያሉት እንዲነበቡ በማስቻል ጉልህ ሚና ነበረው»
ጸሐፍያኑም የሚሉት ይህንኑ ነው። ለምሳሌ አሸናፊ ዘደቡብ። ይህን የብዕር ስም ብዙ የቀድሞ የአዲስ ዘመን አንባቢዎች ያውቁታል፤ ያስታው ሱትማል። በጋዜጣው 75ኛ ዓመት በታተመ ልዩ እትም ላይ አሸናፊ ዘደቡብ እንዲህ ብለው ነበር፤ «በወቅቱ አንባቢውን የሚያዝናኑ ነገሮች በጣም ጥቂት በመሆናቸው እያዝናኑ ቁም ነገር የሚያስጨብጡ በጋብቻ፣ ትዳርና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በማተኮር ይጻፉ ነበር። ጋዜጣው ለአገሪቱ ሥነጽሑፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነው» በተለይም በሚሌኒየሙ መግቢያ ላይ ሊትዮጵያ ስነጽሁፍ አድገት ባደረገው አስተዋፅኦ ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ተሸላሚ መሆኑ ለአብነት ተጠቃሽ ነው።
አዲስ ዘመን በርካታ የሥነጽሑፍ ሰዎችን አሳውቋል፤ እንዲታዩም አድርጓል። በርካታ የሥነጽሑፍ ሰዎችም አዲስ ዘመንን ባለግርማ ሞገስ፤ ተወዳጅና ተነባቢ አድርገውታል። ሰጥተውታል፤ ተቀብለውበታል። ጋዜጣውም ሰጥቶ ተቀብሏል። እናም በአዲስ ዘመን የለጋነት ዘመናት የንባብን ነገር እንዲጨምር ካደረጉና ስማቸው ደምቆ ከሚነሱ ሰዎች መካከል ቀጥሎ የምናነሳው ሰው ሁሌም ተጠቃሽ ነው፤ ጳውሎስ ኞኞ።

የካቲት 1 ቀን 1957 ዓ.ም ነበር፤ ጳውሎስ ኞኞ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ምክትል አዘጋጅ ሆኖ

እንዲያገለግል የዝውውር ደብዳቤ የደረሰው። ደራሲና ጋዜጠኛ ደረጄ ትዕዛዙ «ጳውሎስ ኞኞ 1926-1984» በሚል ርዕስ በ2006 ዓ.ም ባስነበበው መጽሐፍ ላይ የሚከተለውን አስፍሮት እናገኘዋለን።
«ጳውሎስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ መዛወሩ ተመችቶታል፤ ነገር ግን እንደገባ የተሰጡት አምዶች እንደቀድሞው ሁሉ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሂሶችን እንደልቡ መስጠት የሚያስችልበት አልነበሩም።... ይሁንና እርሱ ራሱ የራሱን አምዶች ምቾት ፈጠረባቸው። ቀስ በቀስም ሌሎች ጠንካራ ጽሑፎችን ማቅረብ ጀመረ።»
በዛው ላይ ታድያ ጳውሎስ አንባብያኑን በተለያየ መንገድ ደስ ያሰኛቸው እንደነበር ያወሳል። እንዲህ አድርጎ፤ «ወደአዲስ ዘመን እንደተዘዋወረ መጀመሪያ የሴቶች አምድ እንዲሸፍን ተደረገ። እርሱ ግን ብዙ አስተማረበት፣ አወያየበት፣ ተደሰተበት እንዲሁም ተመሰገነበት። በዚህ አምድ ከበርካታ ሴት አንባብያን የሚደርሱትን ጥያቄዎች ከቻለ ራሱ ካቃተውም ባለሙያ እየጠየቀ መልስ የሚሰጥበት ሲሆን፤ አልፎ አልፎ እርሱም ጥያቄ ጠይቆ ለመላሾች ሽልማት ይሰጥ ነበር። ሲለው ደግሞ የሚላክለትን ፎቶግራፍ እያወጣ የአምዱን ደንበኞች ያስደስት ነበር።» ይላል የጳውሎስ ኞኞ የአዲስ ዘመን ቆይታ በቀረበበት የመጽሐፉ ክፍል።
ከዚህ በኋላ ነው «አንድ ጥያቄ አለኝ» የሚለውን አምድ የጀመረው። ይህ አምድ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ የወጣው መስከረም 1 ቀን 1962 ዓ.ም ነው። ይህ የሆነው በልጆችና ሴቶች አምድ ላይ እንደሚያደርገው ሁሉ ጾታና እድሜ ሳይገድብ ለሁሉም ምላሽ እንዲሰጥ የሚያስችለውን አምድ እንዲከፍት በታዘዘው መሰረት ነው።
«አንድ ጥያቄ አለኝ» አምድ በአንድ በኩል አዲስ ዘመንን በይበልጥ አነጋጋሪና ተነባቢ ጋዜጣ ሲያደርገው በሌላ በኩል ደግሞ ጳወሎስን ከመቼውም በተለየ የማይረሳና የሚታወስ የሚደነቅም ጭምር ባለሙያ አድርጎታል። በዛም አምድ ላይ አንባብያን በሚልኳቸው ጥያቄዎች ጳውሎስን አባባ ጳውሎስ፣ ጋሽ ጳውሎስ፣ ክቡር አቶ ጳውሎስ...ወዘተ እያሉ በተለያየ ቅጽል ይጠሩት ነበር። ያኔ እንደአሁኑ ኢንተርኔትና ማኅበራዊ ድረገጽ አልነበረም። ጳውሎስ ጥያቄዎቹን ይቀበል የነበረው በፖስታ ቤት፤ 30145 በሆነው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፖስታ ሳጥን ቁጥር ነው።
በጋዜጣው ላይ በተለያየ ጊዜ ከታተሙት መካከል አንድ ሁለት ጥያቄና መልሶችን እናስታውስ፤
ጥያቄ፦ አንድ ኃይለኛ የሆነች ጨቅጫቃ

ሚስት ነበረችኝ። አሁን ተፋታን፤ ምን ትለኛለህ?
መልስ፦ እንኳን ደስ አለህ።
ጥያቄ ፦ አንዳንድ ሰዎች ዛሬ ሰከርን ይላሉ፤ መስከራቸውን በምን አወቁት?


መልስ፦ ምላሳቸው ተያይዞ 'ረ' ማለት ሲያቅታቸው፤ እግራቸው ተሳስሮ ሲያወላግዳቸው፤ ቆየት እያለ ሰማይ መሬቱ ሲዞርባቸው መስከራቸውን ያውቁታል።
ደራሲና ጋዜጠኛ ደረጀ ትዕዛዙ ባዘጋጀው መጽሐፍ ላይ ሌላም ያነሳው ነገር ነበር። «ምርመራው እንዴት ነበር?» በሚል ርዕስ ኅዳር 11 ቀን 1967 ዓ.ም በአዲስ ዘመን በወጣ ጽሑፍ ላይ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ጽፏል ይለናል፤ «አንድ ጥያቄ አለኝ የሚለውን አምድ ስሠራ በነበረበት ጊዜ በየቀኑ ሶስት አምድ ለመሙላት ከመቶ የሕዝብ ጥያቄ ደብዳቤዎች ውስጥ በጋዜጣው ሊወጣ የሚችለው አስር ያህሉ ነበር። ቢሮዬን የሚያውቁት ሁሉ እንደሚመሰክሩት ጠረጴዛዬ ስር የሚጣሉ ወረቀቶች ክምር ይሞሉ ነበር።»
ጳውሎስ ከጥቅምት 17 ቀን 1960ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተጠባባቂ አዘጋጅ ሆኖ አገልግሏል፤ ከዛ በተረፈ ግን ዋና አዘጋጅ ሆኖ አያውቅም። ያም ቢሆን ከጋዜጣው በተጓዳኝ በሥራዎ ቹ ስሙ የሚነሳው እርሱ ነው። ብዙ አዳዲስ ሥራ ዎችን ያቀርብ ነበር፤ ለምሳሌ ያኔ እሁድ እሁድ የሚታ ተመው እለተ ሰንበት የመዝ ናኛ ገጽ ማዘጋጀት የጀመረው ጳውሎስ ነው። ይህም የእለተ ሰንበት የአዲስ ዘመን ጋዜጣን አይረሴ አድርጓት እስከዛሬ አለ።
ከዛ ባሻገር ጳውሎስ የሴቶች እምባ፣ እውቀት፣ እንቆቅልሽ፣ ድብልቅልቅ፣ የጌታቸው ሚስቶች፣ የኔዎቹ ገረዶች፣ አስደናቂ ታሪኮች፣ የኢትዮጵያና የጣልያን ጦርነት፣ አጤ ምንሊክ፣ አጤ ቴዎድሮስ፣ የአጤ ዮሐንስ ታሪክ እና ሌሎችም በርካታ መጻሕፍትን ለአንባብያን አድርሷል።
የጳውሎስን የልደት ነገር እስከአሁን አላነሳንም፤ ጳውሎስ ከእናቱ ወይዘሮ ትበልጫለሽ እና ከግሪካዊ አባቱ አቶ ኞኞ ኅዳር ወር በ11ኛው ቀን 1926 ዓ.ም ነው የተወለደው። እናቱ ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ድሬዳዋ ከተማ ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ ኑሯቸውን አድርገው የወለዱትን ብቸኛ ልጃቸውን አማረ ብለው ስም አውጥተ ውለታል።
ይሁን እንጂ በዚህ ስም ሊጸኑ አልቻሉም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ አንብበው በተረዱት መሰረት የቅዱስ ጳውሎስን ታሪክ አብልጠው መውደዳቸው ነበር ያለአባት ብቻቸውን ያሳደጉትን ልጅ ስም መልሰው ጳውሎስ እንዲሉት የሆኑት።
ወደተነሳንበት ቅድመ ነገር እንመለስ፤ እነዚህን ሁለት አንጋፎች ያነሳንበት ምክንያት ይህ ነው። አዲስ ዘመን ጋዜጣ የፊታችን ሐሙስ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም 77ኛ ዓመቱን ይይዛል። እንዲሁም ደግሞ ከአዲስ ዘመን ጋር ወዳጅነቱና ተወዳጅነቱ ጥብቅ የነበረው ጳውሎስ ኞኞ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ 26ኛ ዓመቱን የፊታችን ረቡዕ ግንቦት 29 ቀን ይደፍናል። ጳውሎስ ኞኞ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው በ1984 ዓ.ም ግንቦት 29 ቀን በ58 ዓመቱ ነበር። ይህ ከትውስታችን ማህደር የማይጠፋ ነው። የአንዳቸው ስም ሲጠራ ሌላቸው ይታወሳሉናም አንጋፋውን ጋዜጣ አዲስ ዘመን እና አንጋፋውን ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞን እንዲህ አስታወስን፤ ሰላም!

ሊድያ ተስፋዬ

 

ፈርጀ ብዙው «ጀፎረ» 

ዕለተ ቅዳሜ ረፋድ ላይ በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አዳራሽ በርካታ ምሁራንና የእምነት አባቶች ታድመዋል። ህጻናትና ወጣቶች እንዲሁም አረጋውያን ጉዳዩን ለማወቅ በጉጉት በቦታው ቀድመው ደርሰዋል። በተለይ የጀፎረን ትክክለኛ ጥቅም አልተረዳንም ብለው የሚያምኑ የጉራጌ አርሶአደሮች በጉራጌ ባህል አልባሳት አምረውና ደምቀው መርሃግብሩ እስኪጀመር በአዳራሹ ይዘዋወራሉ።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሎጎውን «ጀፎረ»ን አድርጓልና ትርጓሜ ምንድነው? ምንስ ጥቅም አለው? በጉራጌ ባህል የሚሰጠው ቦታስ ምን ይመስላል? እና አሁን ያለበት ሁኔታ እንዴት ሊቃኝ ይችላል? የሚሉ ጉዳዮችን ለማስቃኘት ነው መርሃ ግብሩን ያዘጋጀው።
መጀመሪያ «ጀፎረ» ማለት ምን ማለት ነው? ከሚለው ትርጓሜ እንነሳ «ጀፎረ»ን በሚመለከት በርካታ ጥናት አቅራቢዎች የተለያየ ብያኔ ሰጥተውታል። ሆኖም ሁሉንም የሚያስማማው ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር መተርጎማቸው ነው። ለአብነት ጥቂቶቹን ብናነሳ የመጀመሪያው ጥናት አቅራቢ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ መምህሩ አቶ አብነት ሽፈራውን እናገኛለን። እንደእርሳቸው ትርጓሜ ከሆነ «ጀፎረ ማለት የጉራጌ ማህበረሰብ አጠቃላይ ማንነቱ፣ ስብዕናው፣ ኑሮው፣ ባህሉ፣ ከአካባቢው ጋር ያለውን መስተጋብርን የሚያሳይ ነው። በአንድ ቃል ተርጉሞ ማስቀመጥም አይቻልም። ይልቁንም ጠቀሜታውን መዘርዘር ይቻል ይሆናል። ጥቅሙ ወሰን ስለሌለው በተለያየ መልኩ ሊነሳ የሚችልበትን ሁኔታ መጠቆም ካልሆነ በቀር ሙሉ ትርጓሜውን ማስቀመጥ ይከብዳል። መጥቀስ ያስፈልጋል ከተባለ ግን ባህላዊ የመንገድ ዝርጋታ፣ ባህላዊ መሰባሰቢያ ስፍራና ባህላዊ የክወና ማዕከል ልንለው እንችላለን»

ከጀፎረ ጠቀሜታዎች መካከል ጥቂቶቹን የሚያመላክቱ ፎቶዎች፤


ጀፎረ ባህላዊ የምህንድስና ጥበብ ነው፤ ጀፎረ የቤት አሰራር፣ የመንገድ አሰራር ጥበብም ነው። ህጻናት የሚቦርቁበት፣ አረጋውያን ስለ ችግራቸው ለመወያየት የሚታደሙበት፣ ሰርገኞችና ለቀስተኞች በፈረስ ረጅም መንገድን ምንም ሳይጓዙና ሳያደናቅፋቸው ከእነ አጀባቸው ደስ እያላቸው የሚጓዙበት ስፍራ እንደሆነም ጥናት አቅራቢው ይናገራሉ። ለረጅም ዘመናት የቆየ የብሔረሰቡ ልዩ የመንደር ምስረታ መገለጫ ነው። በባህላዊ የምህንድስና ጥበብ ተቀይሶ የተመሰረተ ጥንታዊ የመተላለፊያ ጎዳናም ነው። ያለምንም የብረታ ብረትና የድንጋይ ግብዓቶች በእንጨት፣ በቀርከሀ፣ በሳርና በደረቀ የእንሰት ኮባ ገመድ ወይም ሀረግ ብቻ ተሰርቶ እስከ 3ኛ ትውልድ በመተላለፍ ከ80እስከ100 ዓመት ድረስ ግልጋሎት የሰጡ ጎጆ ቤቶችም ጭምር ናቸው።
የጉራጌ ባህልና ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጎይቴ በበኩላቸው፤ «ጀፎረ ማለት በክንድ ተለክቶ ከሚዘጋጀውና በብሔረስቡ ቋንቋ «ዠር» ተብሎ በሚታወቀው የርዝመት መለኪያ መሳሪያ/ዘንግ/ ተመትሮ የተቀየሰ ጥንታዊ የሆነ የጉራጌ ብሔረሰብ ባህላዊ የመንገድ ምህንድስና ጥበብ ውጤት የሆነ ጎዳና (አውራ መንገድ) መሆኑን ይገልፃሉ።
በጉራጌ ታሪክ ጥንት መሬት የሚሸነሸነው በባህሉ በተመረጡ አባቶች /የዥር ዳኘ/ የመሬት ልኬት ዳኞች አማካይነት ስለነበር /ጀፎረ/ ባህላዊ የአውራ መንገድ ልኬት ቅድሚያ ይሰጠው ነበረ፡፡ ጀፎረ በሁለት ትይዩ መንደሮች መሀል የሚያልፍ ወንዝ ገደል ወይም ጥብቅ ደን እስከሌለ ድረስ ሳይቋረጥ የሚቀጥል የመንገድ አይነት ነው፡፡ የጎን ስፋቱ ከ100 እስከ 150 ሜትር ሲሆን መስቀለኛ መንገዶች በሚያልፉበት አካባቢ እስከ 200 ሜትር ተለክቶ ለወል ግልጋሎት ክፍት ይሆናል፡፡ በጉራጌ ባህል ለባህላዊ አውራ መንገድ የተቀየሰ መንገድ አጥሮ ወደ ግል ግቢ መከለል በምንም መንገድ የተወገዘ ተግባር በመሆኑ በብሄረሰቡ ተወላጆች ዘንድ ለህዝብ አገልግሎት የሚውል አውራ መንገድ ማስፋት ባህል ነው፡፡
ጉራጌ ለጀፎረ ለአውራ መንገድ ትልቅ ትኩረት የሚሰጥበት ዋና ምክንያት በብሄረሰቡ የሰርግ የደስታ የሀዘን እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የጋራ መፍትሄ የሚሰጥበት መንገድም፣ መድረክም ስለሆነ ነው፡፡ ለጋራ ወይም ለወል መሬትም እንዲሁ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል፡፡ የጉራጌ ጀፎረ በማንም ሳይደፈር ዘመናትን ለማስቆጠሩ ሌላኛውና ትልቁ ምክንያት ጉርዳ የተሰኘው ባህላዊ ቃልኪዳን ነው፡፡
ጀፎረ አውራ ጎዳና ብቻም አይደለም። ምክንያቱም ጎዳና ሲባል መኪናና ሰው የሚያልፍበት ብቻ ነው። ጀፎረ ግን ከብቶችም ሆኑ ሰዎች አልፈውበት የሚያቆሙበት ስፍራ ሳይሆን ከዚያ በላይ አገልግሎት ያለው በመሆኑ ለትርጓሜ አስቸጋሪ መሆኑን ነው አቶ ተስፋዬ የሚያስረዱት።
እንደርሳቸው አገላለጽ፤ የጀፎረ ሜዳ አረንጓዴ የስብሰባ ማዕከል ሲሆን፤ ለጉራጌ ህዝብ የሸንጎ መሰብሰቢያ፣ የፍርድ ችሎት፣ የለቅሶ ስነ ሥርዓት ማከናወኛም ነው። ለምሳሌ «ወርኮ» ወይም «የቁንብኼ» የሚባል ለትልልቅ ሰዎች የሚለቀስ ለቅሶ አለ። ለዚህ ሰርአት ሰፊ ሜዳና አረንጓዴ መስክ ያስፈልገዋል። ስለዚህም ጀፎረ ይህንን ማድረጊያ ነው። ጀፎረ የደመራ በዓል ማክበሪያ አደባባይ፣ የሰርገኞች መድመቂያ፣ በመስቀልና በአረፋ በዓላት ልጃገረዶችና ወጣት ወንዶች ለ15 ቀናት ባህላዊ ዜማና ጭፈራ የሚከውኑበት የትርዒት መድረክ ወይም አዳራሽ ነው። ወጣቶች የገና ጨዋታ ውድድር የሚያካሄዱበት፣ ጎልማሶች በቅሎና ፈረስ ከመግራት ጀምሮ የጉግስ ውድድር የሚያካሄዱበት፤ የብሔረሰቡ ዋነኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራም ነው። ከጀፎረው ላይ የግብርና ውጤቶችም አግኝቶ መጠለልና መብላት የሚቻልበት ስፍራ ነው።
ጀፎረ ሩቅም ሆነ ቅርብ ተጓዥ መንገደኛ ያለምንም መልክዓ ምድራዊ ምልክት የሚሄድበትን አቅጣጫ የሚያውቅበት ነው። በጉዞውም የደከመ የሚያርፍበት፣ ለግጦሽ መስክ የዋሉ የቀንድና የጋማ ከብቶች ወደ የቤታቸው ከመግባታቸው በፊት የአፍታ ማረፊያቸው መስክ ነው። ለመንገደኛም ቢሆን ከማረፊያ አልፎ ለባህላዊ ችሎት መሰብሰቢያነት የሚያገለግል ስፍራ ነው። በመሃሉ የዝግባና የዋርካ ዛፎች ስለሚገኙበት የኢ-መደበኛ ትምህርት ማዕከል (Informal Education Center) ሆኖ እንደሚያገለግል የሚገልጹት ደግሞ አቶ መንግስቱ አበራ ከጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር የባህል ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ የብሔረሰቡ ዋነኛ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ መሰረት የሆነው የእንሰት ተክል ተከብቦና ተከብሮ እንዲኖር የሆነው በጀፎረዎቹ ነው። ስለዚህም ጀፎሮዎች ጎጆዎችንና መንደሮችን ያገናኛሉ። «የጉራጌዎች መንደር» መሆናቸውንም ያለምንም ማስታወቂያ መነገር ይችላሉ። ስለዚህም አንድ መለያ ባህሪ ለማስቅመጥ አስቸጋሪ መሆኑን ያስርዳሉ።
ጀፎረ ለብሔረሰቡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ በርካታ ክፍለ ዘመናት የተሻገረ ሲሆን ስለአጠቃቀሙም ቢሆን የብሔረሰቡ ተወላጅ አባቶች ተሰባስበው በመምከር በባህላዊ መልክ የሚዳኝበትን ህግ አርቅቀው ተግባራዊ በማድረጋቸው ጀፎረ ዛሬ ድረስ ተጠብቆ ሰፊ ግልጋሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ጀፎረ ባለቤትነቱ የህዝብ አገልግሎቱ ለህዝብ የደህንነቱም ጠባቂ የአካባቢው ህዝብ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
የጀፎረ ባህል በጉራጌ ምድር መቼ እንደተጀመረ የሚያረጋግጥ የጽሀሁሀኀኁኀኁሁፍ ማስረጃ ማግኘት ባይቻልም ብሔረሰቡ ከአርብቶ አደርነት ወደ ከፊል አርሶአደርነት በመሸጋገር በግብርና ስራ ለመተዳደር ባዘጋጀው የእርሻ መሬቱ ዙሪያ መንደር መስርቶ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተጀመረ የመሬት አስተዳደር ባህሉ ውጤት እንደሆነ እየተሰራበት ካለው የብሔረሰቡ የጀፎረ ባህላዊ አስተዳደር ህግ ታሪክ መረዳት እንደሚቻልም አቶ መንግስቱ በጥናታቸው ጠቅሰዋል።
ጀፎረዎች በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ላሉት የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ትልቅ መሰረቶችና የብሔረሰቡ ልዩ የመንደር ምስረታ መገለጫ ቢሆኑም ዛሬ ላይ ከመሬት ፍላጎት መስፋፋትና ከዘመናዊ የመኪና መንገድ ስራ ጋር ተያይዞ እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች መስፋት ጋር በሚመጡ ችግሮች ሳቢያ አደጋ እያጠላባቸው መሆኑን ይናገራሉ።
«ባህላዊና ተፈጥሯዊ ንብረቶች ከነአገልግሎታቸው ጭምር እየጠፉ ናቸው» የሚሉት አቶ መንግስቱ፤ ለምሳሌነት ይጠቀሱ ከነበሩት እና በቴአትርና በፊልም ስራዎች ጭምር ከሚታወቁት ጀፎረዎች እንደ ዴሰነ፣ ጉራአውያትየና ማፌድ የመሳሰሉት ጀፎረዎች ቅርጻቸውና ይዘታቸው ከመጥፋቱም በላይ የኢ-መደበኛ ትምህርት ማዕከልነታቸው እየተገረሰሰ እንደሚገኝ በጥናት ማረጋገጥ መቻላቸውን ያነሳሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የጀፎረ መጥፋት አጠቃላይ የህብረተሰቡ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ትስስሮቹን አደጋ ላይ ይጥላል። እናም ሁሉም የጉራጌ ጀፎረዎች ወድመው ጀፎረ የተባለው ባህላዊ እሴት እስከነአካቴው አሻራው ከመጥፋቱ በፊት የተወሰኑ ወካይ ጀፎረዎች ተመርጠው እንዲለሙ፣ በቅርስነት እንዲመዘገቡ እና ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ያሳስባሉ።
የጀፎረ መጥፋት እያሳሰባቸው መሆኑና ለጉዳዩ እልባት ለመሰጠት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሲሳይ ሸዋአማረ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የአገር በቀል እውቀቶችን በእውቀትም ሆነ በገንዘብ የመደገፉ ሥራ የሁሉም ማህበረሰብ ድርሻ ቢሆንም የዩኒቨርሲቲው ዋነኛ ተግባሩ ሊሆን ይገባል። ስለዚህም ጀፎረን ከአደጋ ለመጠበቅ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር ሌሎች ሥራዎችንም ለማከናወን ዩኒቨርሲቲው እየሰራ መሆኑን ያስረዳሉ።
የጉራጌ ዞን አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ቤቶች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታጁ ነስሩ ጀፎረ እንዲህ በቀላሉ መጥፋት የሚችል ባህል አለመሆኑን ነው የሚናገሩት። ሆኖም አሁን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ጉዳቶቹ እየሰፉ በመምጣታቸው የተነሳ አይጠፋም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይገባምና የዞን አስተዳደሩ በጥልቀት ለመስራት ችግሮችን ተገንዝቧል። አደጋውን ማስቆም የሚቻለው ስለ ምንነቱ ተረድቶ ወደ ስራ መግባት ሲቻልና ማህበረሰቡም ለጉዳዩ ትኩረት ሲሰጠው ነውና ይህንን ግንዛቤ ለመፍጠር ህብረተሰቡ ድረስ በመውረድ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል። በተለይም ግንዛቤውን የመፍጠሩ ኃላፊነት በቅርብ ያለው አመራር ስለሆነ ዝግጁነት ላይ ይሰራል። ከዚህ በፊትም አባቶችን በማሰባሰብ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ ችግሩ በዚህ ልክ የተቃኘ ስላልነበረ በሦስቱ አካላት ጥምረት በተዘጋጀው መድረክ ብዙ ተጨማሪ ግብአት ለመሰብሰብ ችለዋል። ስለሆነም በቀጣይ በተለይ በመንግስት በሚሰሩ ሥራዎች ላይ ሰፊ ኃላፊነት ተወስዶ የሚሰራበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ፈርጀ ብዙ ትርጓሜ የተሰጠው ጀፎረ የጉራጌዎች ልዩ ምልክት ተደረጎ ሊወሰድ ይገባል። ይህን ባህላዊ እሳቤ መጠበቅና ለትውልድ ማስትላለፍ ደግሞ ከከፍተኛ ተምህርት ተቋማት የሚጠበቅ ሃቅ ነው። በመሆኑም የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲም ሆነ የአካባቢው የመንግስት አካላት አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው ሊቀጥሉበት ይገባል።

ጽጌረዳ ጫንያለው 

 

ትላንት እና ዛሬን ለነገ

 

ባህል የሰው ልጅ ይሁነኝ ብሎ ይዞት የቆየው፤ አብሮትም የከረመ ልማድ ነው። ባህል ይወለዳል፣ ያድጋል እንዲሁም ያልፋል። በጊዜ ሂደት ሰዎች ለአኗኗራቸው እንደሚመርጡት የተለያየ መስመር፤ ባህልም እንደዛው ይለዋወጣል። አንዳንዶች ያንን መስመር ስልጣኔ፣ እድገት፣ መሻሻል...ወዘተ ይሉታል፤ ያም ሆነ ይህ ሁሉም ባለበት ዘመን ትክክል ተብሎ ተቀባይነትን ያገኘ ነውና ባህልም እንደየዘመኑ በልዩነት ይገኛል።
ታድያ ባህል እንደሰው ልጅ በተላበሰው የመወለድ የማደግና የማለፍ ሂደት ውስጥ መወራረስም አለ። በዚህም በአንድ በኩል የተለያዩ አገራት አንዳቸው ከሌላቸው ባህልን ሲወራረሱ በተጓዳኝ በአንድ አገር ውስጥ ከአንዱ ዘመን ወደሌላው ዘመንም የባህል ሽግግር አለ።
ኢትዮጵያውያን ዛሬ ላይ በየአንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ያለንን ባህል ድሮ ከነበረው ጋር ብናነጻጽረው ልዩነቶችን እናገኛለን። በአንድ ወገን የተወራረሱና ዛሬም ድርስ ይዘን የምንከባከባቸው ብዙ ባህሎች አሉን። በሌላ አቅጣጫ የተውናቸውንም እናስታውሳለን፤ ጎጂም ጠቃሚም የሆኑ። ከሁለቱ በተለየ ደግሞ አዲስ የተላበስናቸውና የራሳችን ያደረግናቸውም ይገኛሉ። ምንም እንኳን ከሌሎች በጎ ባህልን ከማምጣት ይልቅ የተጣመመውን ማምጣቱ ቢቀናንም፤ ባህል እንደሚወራረስ ግን በዚህም ውስጥ እናያለን።
አሁን ያለንበት ጊዜ ከየትኛውም እንቅስቃሴ በፊት በነገሩ ዙሪያ ጥናት የመሥራትን ባህል አስፈላጊ አድርጎታል። ታድያ ያለፈው ትውልድ የኖረበትን ባህል ወደተከታዩ ለማሸጋገር፤ ከተረካቢውም ዘመንና የአኗኗር ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድና እንዲገለገልበት ለማድረግ በዘርፉ ላይ የሚደረጉ ጥናቶች አስፈላጊ ናቸው። ማኅበራዊ ብቻ ሳይሆን ከኢኮኖሚም አንጻር ተጠቃሚ ለመሆን ጥናትና ምርምር ማካሄድ የግድ ይላል። በደንብ ሳያውቁ እወቁልኝ ማለት አስቸጋሪ ስለሆነ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በከፊል፤


ወደነገራችን እንምጣ፤ ታድያ እኛስ ባህላችንን እያጠናነው ነው ወይ? የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት፤ ከዓመት በፊት ወይም በ2008ዓ.ም ማብቂያ ላይ ነበር «የሴክተር ልማት ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት» የተሰኘ ክፍል በስሩ ያዋቀረው። ይህም ክፍል ባሳለፍነው ዓመት በጎንደር ከተማ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን የመጀመሪያውን አውደ ጥናት አካሂዶ ነበር።
ባሳለፍነው ሳምንት ግንቦት 16 ቀን 2010ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ «የጋራ ባህላዊ እሴቶች ግንባታ ለዘላቂ አገራዊ ልማትና ሰላም» የሚል መሪ ሃሳብ ይዞ ሁለተኛው አገር አቀፍ አውደ ጥናት በሆሳዕና ከተማ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል። ይህም ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በባህልና ቱሪዝም የተዘጋጀ ሲሆን በተባባሪነት ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ፣ የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ተሳታፊ ሆነውበታል።
አቶ ደስታ ሎሬንሶ የክፍሉ ዳይሬክተር ናቸው። መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም የራሱ ጥናትና ምርምሮችን በማስተባበር በኩል ኃላፊነቱን ወስዶ የሚሠራ ክፍል እንዳልነበረው ያወሳሉ። ምንም እንኳን በተበታተነ መልኩ የሚቀርቡ ጥናትና ምርምሮች ቢኖሩም ለጉዳዩ ትኩረት ሳይሰጥ እንደቆየም ያስታውሳሉ።
ታድያ ይህ የጥናትና ምርምር ክፍል የተቋቋመው ዘርፉን በጥናትና ምርምር የመደገፍ አስፈላጊነቱ በሚገባ ከታወቀ በኋላ ነው። አቶ ደስታ እንዲህ አሉ፤ «ተበታትነው የሚሠሩ ጥናቶች ቅንጅት ፈጥረው ወደ አንድ አገራዊ ቋት እንዲመጡ፤ ያንንም ኅብረተሰቡ በህትመትና በጥናታዊ መጽሔት እንዲያገኘው ለማድረግ፤ ለአመራሩም እንዲደርሱና ለፖሊሲ ግብዓት በመሆን እንዲያግዙ ይህ ክፍል ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።»
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካባቢ በባህልና ቱሪዝም ጉዳይ ላይ በርካታ ጥናታዊ ሥራዎች ይሠራሉ። ይልቁንም የባህልን ነገር ስናይ፤ በተለይ ቱባ የሆነ ባህል እንዳይረሳ፤ በአንድ ዘመን ማኅበረሰቡና አገር ላይ የነበረውን ተጽእኖ ለማየት፣ የደረሱበትን ደረጃ ለማጤን እንዲቻል፤ ያለፈ ማንነትን ለማወቅ...ወዘተ በጥቅሉ የተለያየ ዓላማ ያላቸው የባህል ላይ ጥናቶች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
እነዚህ ጥናቶች ለአጥኚዎቻቸው የትምህርት መመረቂያና ማለፊያ ነጥብ ከማስገኘታቸው በተጨማሪ ለሌሎችም አጥኚዎች መነሻና ማጣቀሻ ሆነዋል፤ ከዛ በዘለለ ግን አልተሠራባቸውም። ነገር ግን ለውጥ ለማምጣት የሚጠቅሙ ሊሆኑ ይችሉ ነበር። የጥናትና ምርምሮች አስፈላጊነትም እዚህ ላይ ነው። በትንታኔ በተደገፈ መልኩ ችግሮችን አጉልቶ ያሳያል፤ የጎንዩሽ ተጽእኖ የሌለውን ወይም አነስተኛ የሆነውን የመፍትሄ ሃሳብም ያቀርባል።
ባህልን የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ውጤታማ ሳይሆኑ የሚቀሩት ለዚህ ነው። ችግሩን በማየትና በመስማት ብቻ መፍትሄ ብሎ ሃሳብ ማቅረብ ውጤታማ አያደርግም። ጠንካራ መሰረት ያለው፤ በግራም በቀኝም የተፈተሸ አሠራር ለመቅረጽ የግድ ጥናታዊ ጽሑፎች መሠረታዊ ይሆናሉ።
አቶ ደስታም በዚህ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ መሥሪያ ቤቱ የሚያከናውናቸውና ድጋፍ የሚያደርግባቸው ጥናቶች ችግር ፈቺና አገራዊ ብሎም የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው። «ይህ ጥናት ግን ዝም ብሎ የሚቀመጥ ሳይሆን ለፖሊሲ አውጪዎችና አመራሮች ቀጥታ ተሰጥቶ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ነው የሚታሰበው።» ብለዋል። የባህል እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፉን በእውቀትና በሳይንሳዊ ዘዴ ለመምራት ይህ የጥናትና ምርምር ክፍል አንድ እርምጃ ወደፊት እንደመራመድ ሊቆጠር ይችላል።
ብዙ ሥራ ያለበት ነገር ግን የዛን ያህል ለውጥ ያልመጣበት መሥሪያ ቤት ይጠራ ቢባል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተጠቃሽ ነው። ይህ ማለት ምንም አልተሠራም ማለት ሳይሆን ዘርፉ በሚፈልገው ልክ ለውጥ አልመጣበትም ነው። እንደ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ መስህብም ሆነ በሰው ሠራሽ ባህል የደመቀ አገር የለም። ትልቁም ሀብታችን ያለው በዚህ በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ነው። በዛ ልክ ትርፋማና ተጠቃሚ ሆነናል ወይ? ነው ጥያቄው።
አቶ ደስታ በግላቸው እንዲሁም እንደመሥሪያ ቤት፤ ክፍሉን እንደተቋም አልያም እንደጥናትና ምርምር ማዕከል የማሳደግ ርዕይ እንዳላቸው ጠቅሰዋል። ይህም ቀስ በቀስ የሚመጣ ነው። ከአምና ዘንድሮ ምን ለውጥ አለ የሚለውን ከመመለስ ይጀምራል። በሁለት ዓመት እንቅስቃሴ ውስጥ ከመጀመሪያው አውደጥናት ወደሁለተኛው ተወስዶ የነበረና የተተገበረ ምክረ ሃሳብ እንደነበረ ታድያ ማሳያ ብለው ዳይሬክተሩ ገልጸውልናል።
ባህል ላይ ነውና ትኩረታችን፤ አምና ጎንደር ከተማ ላይ ተካሂዶ በነበረው የመጀመሪያው አውደጥናት ላይ የቀረበ አንድ ሃሳብ ነበር፤ ይህም «ብሔር ብሔረሰቦች እያንዳንዳቸው የራሳቸውን ባህል አውጥተው አሳይተዋል። ታድያ የጋራ የሚያደርጋቸውስ?» የሚል፤ አቶ ደስታ ቀጥለው አሉ፤ «የጋራ የሆነ ባህል አልተጠናም። በአገር ደረጃ ይህ አስፈላጊ ነው። ለፖሊሲ አውጪዎችና ለአመራሩ ጠቃሚ ነው ብለን ሃሳብ ያመነጨነው አምና ነው።»
ይህን ተከትሎም ዘንድሮ ሆሳዕና ከተማ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተካሄደው መድረክ ላይ በፕሮፌሰር ገብሬ የንቲሶ፤ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያውያን ስለሚጋሯቸው እሴቶች /ጋሩማዎች/ ጥናታዊ ሥራ ቀርቦ ነበር። ታድያ ይህ ጥናታዊ ሥራ ከመድረክ ባለፈ እንዲሁም መገናኛ ብዙኅን ላይ ከሚኖረው የዜና ሽፋን በዘለለ ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው ሊደረግ እንደሚገባ የታወቀ ነገር ነው።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በበኩላቸው እነዚህ በክፍሉ አስተባባሪነት የሚቀርቡና የሚሠሩ የጥናትና የምርምር ሥራዎች አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲሄዱና እንዲያራምዱ መልዕክት አስተላልፈዋል። እንደመልእክታቸው ከሆነ ከዚህ በኋላ በአንዱ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ላይ የቀረቡ የመፍትሄ ሃሳቦችን ተግባራዊ አድርጎ ምን ተሠራ? የሚለውን ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ዘገባ ማቅረብ አለበት።
«የጥናትና ምርምር አውዶች ዝም ብሎ መሰብሰቢያ መሆን የለባቸውም፤ ይህ ለቀጣይ መስተካከል አለበት። በዚህኛው ካገኘነው ግብዓት የተወሰነውን ወስደን በአንድ ዓመት ርቀት ተግባራዊ እናደርጋለን፤ በሚቀጥለው ጉባኤም ላይ ይህን ሠርተናል የሚቀረን ይህ ነው ብለን ዘገባ /ሪፖርት/ እናቀርበናለን። ይህ ለጥናትና ምርምር ባለሙያዎች እውቅና ብሎም የተሻለ እንዲሠሩ ማበረታቻም ይሆናል።» ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።
ከዛም ባሻገር ጥናቶች ባስፈለጉበት እንዲገኙ በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲቀርቡ፤ ከሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር በማስተርጎም ለንባብ መቅረብም እንዳለበት ለምኁራንም ጭምር ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ይህ እንደቃላቸው ከሆነና በጊዜ ሂደት ቸልተኝነት ካልተከተለ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሥራ ውጤታማ ያደርጋልና ከባህል እንዲሁም ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ መሆን፤ ለተከታይ ትውልድ ማቆየት፤ ትላንት የነበረውንና ዛሬም ያለውን ዛሬ ላይ በማጥናት ለነገ ለውጥ ግብዓት ማድረግም ይቻላል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በሆኑት በዶክተር ጣሰው ገብሬ ንግግር እናብቃ፤ «ባህል የሌለው ማህበረሰብ የለም። ባህል ያስተሳስራል፣ ለልማትም ቁልፍ ድርሻ አለው። ይህንንም በምርምር ማሳደግ ይጠበቅብናል። በሂደት የሚገጥሙንን ችግሮች በመለየት ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ግዴታ አለብን ብዬ አምናለሁ።» ሰላም!

ሊድያ ተስፋዬ

 

«አስተዳደጌ ባህልን እንድወድ አድርጎኛል» - ዶክተር ሂሩት ካሳው

 

በተገኙባቸው መድረኮች ላይ የባህል ቀሚስ ለብሰው ነው የሚታዩት፡፡ በንግግሮቻቸው ውስጥ ለባህል ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ የባህል ዓውደ ርዕይ ላይ ከተገኙ የባህል ዕቃዎችን አሠራር እያገላበጡ ያያሉ፡፡ የማያውቋቸውን አካባቢዎች የባህል ቁሳቁስ ስለአገልግሎታቸው ጠይቀው ይረዳሉ፡፡ በባህል ጉዳይ ላይ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ከተገኙ የሚቀርቡ ዝግጅቶችን በትኩረት ይከታተላሉ፡፡ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ከመቀመጥ ይልቅ ከባህል ቡድን አባላት ጋር መጫወትና መወያየትን ይመርጣሉ። በመድረክ ዙሪያ ያሉ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን ማየት ይወዳሉ፡፡ በብዙዎቹ ባለሥልጣናት ላይ የተለመደው የመክፈቻ ንግግር አድርጎ መሄድ እርሳቸው ላይ አይስተዋልም፡፡ የተጋበዙበትን መድረክ እስከመጨረሻው ይከታተላሉ፣ ሃሳብ ይሰጣሉ ሃሳብ ይቀበላሉ፡፡ የዛሬ የ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› እንግዳችን ዶክተር ሂሩት ካሳው፡፡
ዶክተር ሂሩት በአሁኑ ጊዜ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ከመሆናቸው በፊት በባህልና ቋንቋ ላይ ብዙ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በዚሁ በቋንቋና የባህል ዘርፍ ውስጥ ለ25 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመታት የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም ዳይሬክተርና ተመራማሪ ነበሩ፤ ለሁለት ዓመታት የኢትየጵያ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፤ ለ6 ዓመታት በዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ፤ ለ15 ዓመታት ያህል ደግሞ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ ዶክተር ሂሩት ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት ናቸው። ከዶክተር ሂሩት ጋር ያደረገነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ!

ትውልድና ዕድገት
ዶክተር ሂሩት ተወልደው ያደጉት በቀድሞው አጠራር ጎንደር ክፍለ ሀገር በአሁኑ የደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ አካባቢ ቀፎየ በምትባል መንደር ውስጥ ነው፡፡ የተወለዱት ገጠር ውስጥ ሲሆን ገና በልጅነት ዕድሜያቸው አባታቸው የመንግሥት ሠራተኛ ስለነበሩ ወደ ከተማ የመሄድ ዕድል ነበራቸው፡፡ አብዛኛውን የልጅነት ዕድሜያቸውን ያሳለፉት ደብረታቦር ከተማ ውስጥ ነው። ከሁለተኛ ክፍል በፊት ያሉትን ጊዜያት እስቴ ውሰጥ ከዕድሜ አኩዮቻቸው ጋር አፈር ፈጭተው ውሃ ተራጭተው አበባየሆሽ ዘፍነው፣ ቡሄን ጨፍረው አሳልፈዋል። ከሁለተኛ ክፍል ጀምረው እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ደግሞ ደብረታቦር ከተማ ተምረዋል፡፡
የ12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቁ ወደ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ (በቀድሞ አጠራሩ ባህርዳር መምህራን ኮሌጅ) በአማርኛ ቋንቋ በዲፕሎማ ተምርዋል፡፡ ኋላም በባህርዳር ዩኒቨርሲቲም በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተምረዋል፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዓመታት ከሠሩ በኋላ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (PhD) ለመሥራት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመሄድ፤ «ተግባራዊ ስነ - ልሳን በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ማስተማር» (Applied Lingusitcs) ተመርቀው ወደ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በመመለስ የአማርኛ ቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም መስርተው ለሁለት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነት በመሥራት ላይ የሚገኙት።
መምህርነት
ዶክተር ሂሩት ሥራ የጀመሩት ገና በ21 ዓመታቸው ነው፡፡ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቱሉቦሎ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በማስተማር ነበር ሥራቸውን የጀመሩት፡፡ ከቱሉ ቦሎ ወደ ወሊሶ ሄደው ሠርተዋል፡፡ ጉራጌ ውስጥ በምትገኝ እንጅባራ የምትባል ከተማ ውስጥም ለስድስት ወራት ያህል ሠርተዋል፡፡
ወቅቱ 1983 ነበር፡፡ ይህ ዓመት በደርግና በኢህአዴግ መካከል ግርግር የነበረበት ስለሆነ መረጋጋት አልነበረም፡፡ በዚሁ ግርግር ምክንያትም ከአንድ አካባቢ ወደ አንድ አካባቢ እየተዘዋወሩ ለመሥራት ተገደዋል። ለብዙ ዓመታት ያገለገሉት ሰበታ ከተማ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ያገኙትም እዚያው ሰበታ እያሉ ነበር፡፡ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተምረው እንደጨረሱም ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ውስጥ ማስተማር ጀመሩ፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዓመታት ያህል ካገለገሉ በኋላ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ለመማር የሚያስችላቸውን ዕድል አገኙ፡፡
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ከመሆናቸው በፊት ለ25 ዓመታት ያህል ያገለገሉት በመምህርነት ነው፡፡ በዚህ የመምህርነት ሥራቸው ውስጥ ደግሞ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ለመምህርነት ሙያ ያላቸው ከብር ላቅ ያለ ነው። በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያሉ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋምን መስርተዋል፡፡ የተቋሙ ዳይሬክተር በመሆንም ለአማርኛ ቋንቋና የባህል ዘርፎች መበልጸግ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡
ባህልን ወዶ ከባህል ጋር መኖር
ዶክተር ሂሩት በገጠር አካባቢ በቱባው ባህል ውስጥ ማደጋቸው ለባህል ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡ ከእናትና አባት፣ ከአያትና ቅድመ አያት ጋር በቤተሰባዊ መተሳሳብ ውስጥ አድገዋል፡፡ በቤተሰቡ ውስጥ ከአለባበስና ከአጊያጊያጥ ጀምሮ ያልተበረዘው የአገር ባህልና ወግ ሲንጸባረቅ እያዩ ነው ያደጉት፡፡ በአካባቢና በጎረቤት ሁሉ እያዩ ያደጉት ተዝቆ የማያልቀውን ቱባ የአገር ባህል ነው፡፡ ለዚህም ባህላቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ከማወቅ አልፈውም የመጠበቅ፣ የማበልፀግና የማስተላለፍ ኃላፊነት አንዳለባቸው ተረድተው አድገዋል።
ቤተሰባቸው የዘመድ አዝማድና የጎረቤት ባህል ጠባቂ መሆን እንዳለ ሆኖ አባታቸው ደግሞ የጎላውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ አባታቸው የተማሩ ስለነበሩ ታሪካዊና ባህላዊ መጻሕፍትን እንዲያነቡ አግዘዋቸዋል፡፡ ዶክተር ሂሩት ከልጅነታቸው ጀምሮ የታሪክና ባህል ይዘት ያላቸው መጻሕፍትን እያነበቡ ነው ያደጉት፡፡ ይህም የአገር ስሜት እየፈጠረባቸውና የማወቅ ጉጉታቸውን እያሳደገው መጣ፡፡ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሲገቡም ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ አደረጋቸው፡፡ ባህል ማለት የስነ ልቦና ስሪት እንደሆነም ያምናሉ፡፡ ከልጅነት ጀምሮ የተፈጠረ ስሜት ከሆነ ለባህል ቅርብ ያደርጋል፡፡ «አስተዳደጌ ባህልን እንድወድ አድርጎኛል። ሰው የሚያስበው ባደገበትና በተገነባበት ልክ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
የተማሩት ትምህርት ደግሞ ባህል ማለት ምን እንደሆነ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ በልጅነት በተግባር ያዩት የነበረውን ቱባ ባህል በኋላ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሲማሩት የበለጠ ግልጽ ሆነላቸው፡፡ የባህል ምንነት ሲገባቸውም ሰውን ከእንስሳት የሚለየው ባህል እንደሆነ ተገነዘቡ፡፡ የሰው ልጅ ባህሉን የማይጠብቅ ከሆነ ከእንስሳት በምንም እንደማይለይ ተረዱ፡፡
በእርሳቸው አምነት ባህል በዓይን የሚታየው አለባበስና አጨፋፈር ብቻ አይደለም፡፡ ባህል የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ በባህል ውስጥ የሚታዩ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው፤ እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች ደግሞ የአስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው የየራሰቸው የሆነ ፍልስፍና እና ማህበራዊ መስተጋብር ያላቸው ናቸው፤ ማህበረሰቡ የሚግባባባቸው በመሆናቸው እርሳቸውም ያወቁቱን ለማሳወቅ የተቻላቸውን ያህል ጥረት አደረጉ፡፡ በቱባው ባህል ውስጥ ተፈጥረው ከባህል ተቋማት ጋር አብረው አደጉ።
ከቤተሰብ መለየት
ዶክተር ሂሩት ሥራ የጀመሩት በልጅነት ዕድሜያቸው ነው፤ በልጅነት ከቤተሰብ መለየት ደግሞ ከባድ ነው፡፡ ሆኖም ግን ለእርሳቸው ያን ያህል አስቸጋሪ የሚባል ፈተና አላጋጠማቸውም፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩ ልጆች ጠንካራ እንደነበሩም ያምናሉ፡፡ እንደዛሬው «ገጠር አልሠራም፤ እንዲህ ዓይነት ቦታ አልሄድም፣ ይሄን ሥራ አልሠራም» የሚሉ አልነበሩም፡፡ ሁሉንም አካባቢ የማወቅ ስሜት ስለነበር ሥራቸውን የሚሠሩት በደስታ ነበር፡፡ የሥራ ጓደኞቻቸው እንኳን በዚያን ጊዜ የሚረዳዱ ነበሩ፡፡ በብልጣብልጥነት ሳይሆን በየዋህነት ላይ የተመሰረተ ጓደኝነት ነበራቸው፡፡ ከየትም አካባቢ ይምጡ የተገናኙት ሁሉ የልብ ጓደኛሞች ይሆናሉ፡፡ የዋህነት ሲኖር ደግሞ ሰዎችን ማመንና መታመን ይኖራል፡፡ አንድ ሰው ሊታመን የሚችለውም ራሱ ሌላውን የሚያምን መሆን እንዳለበት ጠንቀቅው ያውቁ ነበር፡፡ ችግር እንኳን ቢያጋጥም በጋራ የመወጣት ባህል ነበራቸው፡፡
ወደሥራ ቦታ ለመሄድ ረጅም እርቀት በእገር መጓዝ የተለመደ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ለአንድ ቀን እንኳን የማይታሰበውን በዚያን ጊዜ በየዕለቱ መጓዝ የግድ ነበር፡፡ ወንዝ ተሻግሮ የመሄድ አጋጣሚ ነበር፡፡ ይህ ሲሆን ሥራውን የሚሠሩት በፍቅርና በደስታ ስለነበር ከችግሩ ይልቅ ሌሎችን የመርዳት ደስታ ነበር የሚሰማቸው፡፡ ዶክተር ሂሩት ለዚህ ጥንካሬና ችግሮችን የመጋፈጥ ብቃት አስተዳደጋቸውን ያመሰግናሉ፡፡ በልጅነታቸው የትኛውንም ሥራ ተገደው ሠርተው አያውቁም፡፡ ወላጆቻቸው በምክርና በማስተማር ነበር የሚያሠሯቸው፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርሰው የቤት ውስጥ የጉልበት ብዝበዛና ያለፍላጎት መሥራት አልደረሰባቸውም፡፡ በዚህም ይመስላል በቆዩባቸው የሥራ ጊዜያት ከባድ የሚሉት ፈተና እንዳላጋጠማቸው የሚያምኑት፡፡ አልፎ አልፎ እንኳን የሚያጋጥሙ ችግሮች ቢኖሩም የሥራው ሁኔታ የሚያመጣቸው እንደሆኑ ስለሚያምኑ መፍትሔው ላይ ያተኩራሉ፡፡ እነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት አሁን ላይ ላላቸው ጥንካሬ መሰረት እንደሆኗቸው ይናገራሉ፡፡
ሀገራዊ አበርክቶ
ዶክተር ሂሩት ምንም እንዳልሠሩ ያስባሉ። ይሁን እንጅ የሠሯቸው ትልልቅ ሥራዎች ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ያስመሰገኑና የተደነቁ ናቸው፡፡ ከእነዚህም አንዱ የአማርኛ ቋንቋ እየተበረዘ መምጣትና ትኩረት ማጣት በተደጋጋሚ በሚነሳበት ወቅት ይህን ችግር ለመቅረፍ አንድ ተቋም ማቋቋማቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም በየዓመቱ ምሁራን የተለያዩ ጥናቶችን በማቅረብ ውይይት ያደርጉበታል፡፡ በቋንቋ ላይ ጥናትና ምርምር እንዲሠራና የቴክኖሎጂ ቋንቋ እንዲሆን እያነሳሳ ነው፡፡ አሁንም ከዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጋር በጋር እየሠሩ ነው፡፡ አሁን ባሉበት የሥራ ኃላፊነት ቦታ ላይ ሆነውም አብረው ለመሥራትና ለማገዝ ዝግጁ ናቸው፡፡ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮም ቢሆን ለዚህ ጉዳይ ኃላፊነት ስላለበት ቢሮው ከዩኒቨርሲቲው ጋር አብሮ መሥራት እንዳለበት ያምናሉ፡፡
ሌላው ዶክተር ሂሩት ከሠሩት ሥራዎች መካከል በክልሉ ውስጥ የባህልና ቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ መነቃቃት የፈጠሩበት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ ከዚህ በላይ መነቃቃት በመፍጠርና የክልሉ ባህልና ቱሪዘም ዘርፍ የሚተዋወቅበት ሥራ ለማስፋት እቅድ ይዘዋል፡፡ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅም ከወትሮ በተለይ መልኩ ለመሥራት ተዘጋጅተዋል፡፡ በዚህ ዓመት የአጼ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ከፍተኛ ጥረት ማድርጋቸውም በአገር አቀፍ ደረጃ የታወቁበት ሥራ ነው፡፡
ገጠመኝ
ቱሉቦሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ ዶክተር ሂሩት ለማስተማር ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ አንዲት ተማሪ አየቻቸው፡፡ ዶክተር ሂሩት በዕድሜ ልጅ ከመሆናቸው በተጨማሪ በአካላዊ ሰውነትም ቀጫጫ ነበሩ፡፡ ተማሪዋ መምህር ሂሩትን ጠርታ ‹‹ጠብቂኝ›› በማለት አብረው ሄዱ፡፡ አብረው እየሄዱ ተማሪዋ ‹‹ስንተኛ ክፍል ነሽ›› አለቻቸው፡፡ ‹‹12ኛ ክፍል›› ብለው መለሱ፡፡ ተማሪዋ 9ኛ ክፍል ነበረች፡፡ ወደ ግቢ ሲገቡ ተማሪዋ ወደ ሰልፉ ስትሄድ ዶክተር ሂሩት ወደ ቢሮ ሄዱ፡፡ ተማሪዋም ‹‹ነይ እንጂ እዚህ እንሰለፍ›› ስትላቸው ‹‹አይ ወላጅ አምጪ ስለተባልኩ መምህሮች ጋ ልሄድ ነው›› ብለው መለሱላት፡፡
ሌላው የመምህርነት ገጠመኛቸው ደግሞ ለማስተማር ወደ ክፍል እየገቡ ሳሉ ተማሪዎች መምህርነታቸውን አለማመናቸው ነበር፡፡ ተማሪዎች ደግሞ ከብሔራዊ ውትድርናም የተመለሱ ስለነበሩ ትልልቅና አስፈሪ ናቸው፡፡ ዶክተር ሂሩት ገና ወደ ክፍሉ ሲገቡ ተማሪዎች አዲስ ተማሪ መጣች ብለው ‹‹ነይ እዚህ ነይ እዚህ›› እያሉ ተንጫጩ ፤ ሴቶች ደግሞ እየተነሱ ‹‹ነይ እኔ ጋ›› ይላሉ፡፡ ዶክተር ሂሩትም በጣም ደነገጡ፡፡ በኋላ የክፍሉ ደረጃ ላይ ወጡና ‹‹ ከዛሬ ጀምሮ እኔ የአማርኛ መምህራችሁ ነኝ!›› ብለው ተናገሩ፡፡ ሁሉም ተማሪዎች ተንጫጩ፡፡ ተማሪዎች ሲንጫጩ ዶክተር ሂሩትም ‹‹ቋንቋ ማለት… ›› ብለው በመጀመር ማስተማሩን ቀጠሉ፡፡ ተማሪዎች ጸጥ ብለው መከታተል ጀመሩ፡፡ በኋላም ሙሉ በሙሉ ጸጥ አሉ፤ 40 ደቂቃ ሙሉ በጸጥታ አስተምረው ጨረሱ፡፡ ከተማሪዎች ጋር በጣም ተግባቡ፡፡ እንዲያውም በነገታው ለዶክተር ሂሩት አጨብጭበውላቸው ነበር፡፡
በመጀመሪው ቀን አስተምረው ሲወጡ ‹‹ደግሞ የእናቷን ጡት ጠብታ ያልጨረሰች ይልኩልን ጀመር›› የሚል ድምፅ ከተማሪዎች ሰሙ፡፡ በነጋታው ሊያስተምሩ ሲገቡ ‹‹ትናንት አስተምሪያችኋለሁ፤ እኔ አስተማሪያችሁ ነኝ፤ ማስተማር የጭንቅላት ሥራ እንጂ የጡንቻ ሥራ አይደለም›› ብለው ሲናገሩ ተማሪዎች በአድናቆት አጨበጨቡ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጣም ተግባብተው በፍቅር አብረው ቆዩ፡፡
ስጋት
ዶክተር ሂሩት ምንም እንኳን አሁን ላይ ያለው የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ የሁኔታዎች መለዋወጥ የራሱ ተፅዕኖ ቢኖረውም አሁን ላይ ያሉ ወጣቶች ችግሮችን መቋቋም ላይ እንደ ቀደሞዎቹ አለመሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ እንዲያውም የሥራ ፈላጊ ቁጥር በበዛበት በዚህ ዘመን ነበር ጥንካሬ የሚያስፈልገው፤ ግን በተቃራኒው ሥራን ማማረጥ፣ ቦታን ማመረጥ እየተስተዋለ ነው፡፡ ለዚህም የአስተዳደግ ሁኔታ ከበፊቱ የተለየ መሆኑ ነው፡፡ በፊት እንኳን የገጠር ልጆች ይቅርና የከተማ ልጆች በቤት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠሩ ነበር፡፡ አሁን ላይ ልጆች ሥራ ሲሠሩ ብዙም እንደማይስተዋሉ ታዝበዋል፡፡ በአካባቢያቸው ያሉ ነገሮችን የማስተዋል ዕድል የላቸውም፡፡ በቤት ውስጥ የውጭ ባህልና የውጭ የሆኑ ነገሮችን ነው በቴሌቪዥን የሚያዩት፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ያደገ ልጅ በኋላ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳት መቸገሩ እንደማይቀር ይናገራሉ፡፡
«ልጅን መንከባከብ በጣም አስፈላጊና የግድ ነው፤ ግን መንከባከብ ሲባል ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት? የሚለውን መወሰን አለበት፡፡ ምን ማንበብ እንዳለባቸው፣ ማን ማየት እንዳለባቸው፣ የት መሄድ እንዳለባቸው ክትትል መደረግ አለበት፡፡ ከዕድሜያቸውና ከሁኔታቸው ጋር የሚሄድ መሆን አለበት፡፡ በአካባቢያቸው ያለውን ነገር ማየት አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ በሥራ ጊዜ ይቸገራሉ፡፡ አካባቢውንና አገሩን ሳያውቅ ያደገ ልጅ በኋላ የአገር ተረካቢ ለመሆን ይቸገራል» የሚሉት ዶክተር ሂሩት፤ ልጆችን ቁሳዊ በሆነ ነገር ብቻ ማሳደግ በራስ መተማመን እንዳይኖራቸው እንደሚያደርግ ያምናሉ፡፡
«ቁስ እየሰጡ ማሳደግ ሳይሆን ያ ቁስ ከአካባቢያው ነገሮች እንደተሠራ እንዲያውቁ ማድረግ ነው፡፡ ይሁን አንጂ የሚታየው ነገር ግን ይህ አይደለም፡፡ አሥራ ምናምን ዓመት የሆነው ልጅ ትምህርት ቤት የሚሸኘው በመኪና ነው፡፡ ልብሱን የሚያጥብለት ሠራተኛ ነው፡፡ ይሄ ልጅ ምንም ነገር እንዳያይና እንዳይለማመድ ተደርጓል፡፡ ትምህርት ቤት ራሳቸው እንድሄዱ ማድረግ፣ ልብሳቸውን ራሳቸው ቢያጥቡ፤ ይሄ የጉልበት ብዝበዛ አይደለም፤ ይሄ ልጆችን መጨቆን አይደለም፡፡ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሥራ አይሥሩ እንጂ በአቅማቸው ልክ የሚሠሩት ነገር መኖር አለበት፡፡ በአዋቂነት ለሚገጥሙት ፈተናዎች መፍትሔ ሊሆን የሚችለው የልጅነት አስተዳደጋቸው ነው፡፡ ምንም ነገር እንዳያይ የተደረገ ልጅ ተፈጥሮ ላይ ሊመራመር አይችልም፡፡
«በውጭ አገራት እንዲህ አይደረግም፡፡ ልጆች የፈጠራ ሥራ እንዲሠሩ ነው የሚደረገው፡፡ የሚያሳዩዋቸውም የፈጠራ ሥራ ላይ፣ የተሰጥዖ ሥራ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የውድድር መንፈስ ይፈጥርላቸዋል፡፡ ልጆች በዕረፍት ቀናቸው የሚሠሩት ነገር ይሰጣቸዋል፡፡ በእኛ አገር ግን ይህ ልምድ ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ የሚያዩት ተደጋጋሚ የውጭ ባህል ነው፡፡ የውጭ ባህልና ታሪክ እያዩ በአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ለመመራመር አይችሉም» በማለት ነው በወጣቶች ላይ የታዘቡትን የተናገሩት።


መልዕክት
ማንም ሰው ባህሉ እንዲያድግና እንዲበለጽግ ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ‹‹ባህላችን ተበረዘ፣ ባህላችን አልተጠበቀም›› የሚሉ ወቀሳዎች በተደጋጋሚ የሚሰሙት፡፡ እነዚህ ወቀሳዎች የሚነሱት የህብረተሰቡ ባህሉን የመጠበቅ ስሜት ነው፡፡ ባህሉ እንዳይበረዝበት ስለሚፈልግ ነው፡፡
ዳሩ ግን ይህ ሲሆን ባህልን የመጠበቅና የማበልጸግ ሥራ ደግሞ ወቀሳ ከሚያነሳው ሰው ጀምሮ የእያንዳንዱ ግለሰብ ኃላፊነት ነው፡፡ እንዲያውም ባህል የማህበረሰቡ ስለሆነ የሚጠብቀውም ራሱ ማህበረሰቡ ነው፡፡ ባህል በአንድ ተቋም የሚሠራ አይደለም፤ በተቋም ከሚሠራው ይልቅ ማህበረሰቡ የሚሠራው ይበልጣል፡፡
አገር ማደግ የሚችለው የራስን ቆርጦ በመጣል ሳይሆን የራስን በማሳደግ ነው፡፡ አሁን ላይ በልጽገው የሚታዩ አገራት ለዚህ የበቁበት ምሥጢር የራሳቸውን ሀብት በመጠቀማቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባህል ደግሞ እንኳን ራሷን ሌላውንም ማሳደግ የሚችል ነው፡፡ የዕደ ጥበብ ሥራዎች አሉ፤ ዳሩ ግን እነዚህ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ወደውጭ ወጥተው በመጽሐፍ መልክ ታትመው ሲመጡ ነው ተፈላጊ የሚመስሉት፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ከውጭ እየመጡ አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡ እንዲህ እንዲህ ሲሆን ጭራሽ የኢትዮጵያ እንደነበሩም ሊረሳ ይችላል፡፡ በዚህ ላይ ምሁራንም ማጥናት ገና ብዙ ይቀራቸዋል፤ ባለሀብቱም እዚህ ላይ መሥራት አለበት፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ባህል የሰላም መገለጫም ነው፡፡ የየአካባቢውን ባህል ብናይ ሽምግልና ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ የአባቶችን ምክር መስማት የጨዋነት መገለጫ ነው፡፡ የአባቶችን ምክር የማይሰማ እንደ ባለጌ ነው የሚቆጠረው፤ ይሄ የኢትዮጵያ ባህል ነው፡፡ ሰውና ሰው ተጋድሎ እንኳን የሚታረቅበት አገር ነው፡፡ በሌላው አገር በወንጀል መቅጣት ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባህል ግን ይቅርታና እርቅ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ይህን አኩሪ ባህል ምሁራን ማጥናት አለባቸው፡፡ የኪነ ጥበብ ሰዎች ማሳወቅ አለባቸው፡፡
የኢትዮጵያን ባህል ማሳደግ ቴክኖሎጂን ማሳደግ ነው፡፡ ብዙ ዓይነት የጥበብ ሥራዎች ያሉበት ነው፡፡ ከሕንፃ አሠራር ጥበብ ጀምሮ ብዙ የመገልገያ መሳሪያዎች ከባህል ጥበብ የወጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ ባህልን ማሳደግ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ ቴክኖሎጂን ማሳደግ ማለት ነው፡፡ ለአንዲት አገር ዕድገት ደግሞ ዘመኑ የሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ባህልን ከቴክኖሎጂው ጋር ማስተሳሰር የግድ ይላል፡፡
በባህል ላይ የተጻፉ መጻሕፍት እንኳን አልተነበቡም፤ እነዚያ መነበብ አለባቸው፡፡ አንዳንዶቹ እስከመኖራቸውም አይታወቁም፤ ምሁራን እዚያ ላይ መሥራት አለባቸው፡፡ የባህል መዲሃኒትን በተመለከተ እንኳን ብዙ መጻሕፍት አሉ፡፡ የስነ ሕዋ መጻሕፍትም አሉ፤ ግን አልተሠራባቸውም፡፡ ይህን ፈረንጆች ናቸው እየወሰዱ የሚጠቀሙበት፡፡
በተለይም በአሁኑ ጊዜ የባህል አልባሳት ጥበብን ለህንድ አሳልፈን ሰጥተናል፡፡ ይህ እንግዲህ በቀላሉ በተንቀሳቃሽ ስልክ ተቀርጾ የሚሄድ ነው፡፡ እነዚህ ህንዶች የራሳችን የሆነውን ጥበብ ሠርተው እኛ በውድ ዋጋ እየገዛን ነው፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ዓይነት ክስረት ነው ያጋጠመን፡፡ ይህን አስገራሚ ጥበብ ባለቤትነት እያጣንበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጥበብ ሠሪዎች ሳይሆኑ ህንዶች እየተመሰገኑበት ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የነበረውን የሥራ ዕድል እያጠፋ ነው፡፡ ይህን ሥራ የሚሠሩ ሰዎች የሚገዛቸው እያጡ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጥበብ ይህን ያህል ነው የሚወደደው፡፡ ህንድ ማለት ከውጭ አገር ነጠላ ጫማ እንኳን የማትገዛ ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን እንዲያውም ከውጭ የመጣ ነው የሚበልጥብን፡፡ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ መወገድ አለበት፡፡ መልካም ዕለተ ሰንበት!

ዋለልኝ አየለ

Published in ማህበራዊ

ኢትዮጵያ በባህላዊ ፍትሕ ስርዓቷ ብዙ ችግሮችን እየፈታች ብትገኝም ከዘመናዊው ህግ ጋር አጣጥሞ ባለመሠራቱ የሚፈለገውን ያህል ስኬታማ አልሆነችም። ሁለቱን የፍትሕ ሰርዓቶች አጣጥሞ ለመሥራት ምን መደረግ አለበት?

በአማራ ክልል ራያ ቆቦ ወረዳ የባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት የእቅድ ዝግጅት ባለሙያው አቶ ደመቀ አባተ «የባህል ህግ ከዘመናዊው ህግ ተለይቶ የሚታይ ሳይሆን ደጋፊ ተደርጎ መወሰድ አለበት። የቆየ ቂም እንዳይኖር ባህላዊ ህጎች መፍትሔ ናቸው። ለዚህም እንደ 'ዘወልድ' ዓይነት ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶችን ማንሳት ይበቃል» ይላሉ። ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡ ወንጀሎች ብዛት እንዳይኖራቸው ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ። ሆኖም የተሰጣቸው ትኩረትና በህግ የተሰጣቸው ዝርዝር መረጃ የሚያሠራ ባለመሆኑ በአፈፃፀም ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ይናገራሉ። የሀገር ሽማግሌዎችም ሆኑ በዳይ ከስርዓቱ እንዲወጡ እያደረጋቸው ነው፤ በተለይም በዳዮች «ሁለት ቅጣት እየተቀበልን አንታረቅም» እስከማለት ደርሰዋል።
በ«ዘወልድ» ህግ ሦስት ዓይነት የእርቅ ደረጃዎች ያሉ ሲሆን፤ በሁለቱ ደረጃ ዘመናዊ ህጉ ጣልቃ ስለማይገባ በቀላሉ ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ። ሆኖም ሦስተኛው የእርቅ ስርዓት ወንጀል ነክ ስለሆነ ከህጉ ጋር ተጣጥሞ መጓዝ አልቻለም። የሀገር ሽማግሌዎቹ እርቁን ፈጽመው ቤተሰቡ እንዲስማማ ቢያደርጉም ጉዳዩን አቃቢህግ ስለሚይዘው በህግ ከመጠየቅ የሚያመልጥበት ሁኔታ የለም። ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ በተደረገ ጥናት እንደተመላከተው የሀገር ሽማግሌዎች ከማስታረቁ ሥራ እንዲወጡ እያደረጋቸው በመሆኑ እንደባህል ቢሮ ከፍትህ አካላት ጋር በመነጋገር ህጉንና ባህሉን ማጣጣም ላይ መሥራት እንደሚገባ ይገልጻሉ።
የባህላዊ ህጎችን ፋይዳ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም የሚሉት አቶ ደመቀ፤ ሁለቱን ህጎች አጣጥሞ ለመጓዝ መጀመሪያ መሠራት ያለበት ህጉ ለሀገር ሽማግሌዎች እስከምን ድረስ ቦታ ይሰጣቸዋል? የሚለውን በዝርዝር ማስቀመጥ ነው። የሀገር ሽማግሌዎችም ሆኑ በአካባቢው ያሉ ፈጻሚ አካላት በሚገባ ግንዛቤው ስለሌላቸው ግንዛቤ መፍጠር ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ህጉ አይፈቅድም በሚል ብቻ ማሸማቀቅ ግን መፍትሔ እንደማይሆን ያስረዳሉ። በተለይም እንደ መንግሥት ባህላዊ ህጎች በህገ መንግሥቱ እስከምን ድረስ መደገፍ ይችላሉ? የሚለውን ስርዓት ማመላከት ይገባል። ለፈጻሚ አካላትም በሚገባ ማስገንዘብ ይጠበቃል። የፍትህ አካላትና የሀገር ሽማግሌዎች ተናበው የሚሠሩበትን መመሪያም ማውጣትና ትግበራውን መከታተል ይገባል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የጋራ ባህል እሴቶች ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸው፤ በባህላዊ የፍትህ ስርዓት ስድስት አካባቢዎችን የቃኘ ጥናቶች ተደርገው በመጽሐፍ መልክ ታትመው በመሰራጨታቸው ምን ያህል የፍትህ ስርዓቱን እየደገፉ እንደሆነ ለማየት ተችሏል። አሁንም በተለያየ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጥምረት ባህላዊ እሴቶችን በመለየት ላይ እየተሠራ ነው። እስከአሁንም 18 ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች በጥናት ተለይተው ወደ መጽሐፍ ለመቀየር እየተሞከረ መሆኑን ያስረዳሉ።
«አገር በቀል የፍትሕ ስርዓቶችን ፋይዳ መለየት፤ የትኞቹ ባህሎች አማራጭ የፍትሕ ማስከበሪያ እንደሆኑ ለማወቅ ያግዛል። የፍትሕ አካላትም በዚህ መነሻነት ተናቦ መሥራት እንዲችሉ ይረዳቸዋል» የሚሉት አቶ አለማየሁ፤ ከጠቅላይ አቃቢ ህግ ጋር በመሥራት ችግሩ መፈታት ይኖርበታልና ከህጉ አኳያ ምን ምን ነገሮች ሊካተቱበትና እስከምን ድረስ ያራምዳል? የሚለውን ጠቅላይ አቃቢ ህግ እንዲሠራ ስምምነት ላይ መደረሱን ይናገራሉ። በተለይ በክልሎችና በዞኖች እንዲሁም በወረዳዎች አካባቢ ያለው ችግር የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ያስፈልጋቸዋልና ትኩረት ተችሮት መሠራት እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱን ይገልጻሉ።
እንደ ህግ አማካሪው አቶ ማማሩ አንተነህ ገለጻ፤ ህገ መንግሥቱም ሆነ የወንጀል ስነስርዓት ህጉ እንዲሁም የወንጀል ህጉ ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶችን በእጅጉ ይደግፋቸዋል። ለአብነት በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ንኡስ ቁጥር 1 ላይ እንደተመላከተው «ህገመንግሥቱ የበላይ ህግ ነው። ማንኛውም ህግ ልማዳዊ አሠራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገመንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም» ይላል። ህገመንግሥቱን ሳይቃረን ለህጉ አማራጭ የፍትሕ መስጫ መሆን ከቻሉ ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች የማይደገፉበት ሁኔታ የለም። ለዚህም ባህላዊ ህጎች ህገመንግሥቱ ቦታ ሰጥቷቸው እየተጠቀመባቸው መሆኑን በተለያየ መልኩ መመልከት ይቻላል።
ክፍተቶች መኖራቸው አይካድም የሚሉት አቶ ማማሩ፤ የወንጀል ስርዓት ህጉ ላይ ወንጀልነክ ጉዳዮች በምንም መልኩ ሊቋረጡ እንደማይችሉ ተቀምጧል። በዚህም ከባህላዊው ህግ ጋር ተጣጥሞ መጓዝ እንዳይችል የአፈጻጸም ክፍተት ፈጥሯል። ሁኔታው የሀገር ሽማግሌዎችን ቦታ አልተሰጠንም አሰኝቷል፤ በዳዮችንም ላለመታረቅ እንዲወስኑ እያደረገ ነው። ሆኖም ህጉ ግን ሥራቸውን በየትኛውም በኩል የተወ አይደለም። ከፍርድ በፊትም ሆነ በኋላ ለማቅለያነት የሚያገለግለው የእርቅ ስነስርዓቱ ነው። በዳዮችም ፍርዱ ሊቀልላቸው የሚችለው የሀገር ሽማግሌዎች እገዛ ሲኖራቸው ነው። ነገር ግን ግንዛቤው በሚፈለገው ልክ ስላልተሠራበት ባህላዊውና ዘመናዊው ህግ የተራራቀ እየመሰለ መምጣቱን ያስረዳሉ።
ባህላዊ ህጎች የፍትሐብሔር ክስ እስከማንሳት የሚደርስ አቅም እንዳላቸው የሚገልጹት አቶ ማማሩ፤ የፍትህ ዘርፉ ላይ የሚሠሩ አካላት ማህበረሰቡ ጋር ወርደው ግንዛቤ አለመፍጠራቸው፤ የህግ ምንጭ ባህል መሆኑን፤ ህግንም የሚፈጽመው የባህሉ ባለቤት እንደሆነ አለመገንዘባቸው ችግሮቹን አግዝፏቸዋል። በመሆኑም ከእርሱ የወጣውን ለራሱ ከማቅረብ ውጪ ህገመንግሥቱ ምንም ዓይነት ለወጥ እንዳላመጣ ማስገንዘብ ሲቻልና ባለሙያ ብቻውን መሮጥ እንደሌለበት ማሳወቅ ላይ ሲሠራ እንዲሁም ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ምን ዓይነት ቦታ እንዳላቸው በተለያዩ መድረኮች ማስገንዘብ ከተቻለ ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቱንና ዘመናዊውን አጣጥሞ መሄድ እንደሚቻል ይናገራሉ። በወንጀል ህጉ አንቀጽ 1/ ሠ/ ላይ እንደተቀመጠው ባህላዊ የፍትሕ ህጎች በርካታ ጠቀሜታ አላቸውናም ይህንን በማስፈጸሙ ዙሪያ የፍትሕ አካላት ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልገዋል ይላሉ።
በአገሪቱ ያሉ የባህል የፍትሕ ስርዓቶች ሁሉም አማራጭ የፍትሕ ማስፈኛ ናቸው ተብለው ሊወሰዱ እንደማይችሉ የሚያስረዱት አቶ ማማሩ፤ እስከምን ድረስ ህጋዊ ናቸው የሚለው መታየት አለበት። ከህገመንግሥቱ ጋር የማይቃረኑትን በመለየት አጋዥነታቸውን ማሳየት ያስፈልጋል። በተለይ በፍትሐብሔሩ ላይ ከፍተኛ ፋይዳ ስላላቸው ተጣጥመው የሚጓዙበትን መስመር መዘርጋት ለነገ የሚባል መሆን እንደሌለበት ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ማማሩ ገለጻ፤ ሁለቱ ህጎች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው። በመጀመሪያ ከፍትሕ ባለሙያው የጀመረ ሥራ ሊከናወን ይገባል። የወንጀል ስነስርዓት ህጉም የቆየ በመሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች ህጉን ሲደግፉ እስከምን ድረስ መሆን ይኖርበታል? ኃላፊነታቸውስ እስከምን ድረስ መሆን አለበት? የሚለውን አሁን የወንጀል ስርዓት ህጉ እንዲሻሻል እየተደረገ በመሆኑ በማሻሻያው ውስጥ አስገብቶ ሊያያቸው ይገባል። «የእኔ ለምን አልተሰማም» የሚለው ጉዳይም ከሁሉም አዕምሮ መጥፋት ሲችልና ህጉንና ህጉን ማዕከል አድርጎ መሥራት ሲጀመር ፍትሕን ማስፈን ይቻላል።
ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች የተጻፈው ህግ ሳይኖር በፊት ነበሩ፤ ሰዎች በህገልቦና እየተመሩ ተግባብተውና ተዋደው በሰላም ይኖሩ ነበር። ከዚያም የተጻፈ ህግ በማስፈለጉ በወቅቱ በነበሩት ነገሥታትና በቤተክርስቲያን መካከል ጥብቅ ቁርኝት በመኖሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍትሐ ነገሥት እንዲወጣ ተደረገ። በዚህ ሁሉም ማህበረሰብ እየተገዛ ቆይቶም ከዘመኑ ጋር መዘመን ሲያስፈልግ ዛሬም ድረስ እያገለገለ ያለው ህገመንግሥት መውጣት ቻለ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች ነበሩ የሚሉት አቶ አለማየሁ፤ ህገመንግሥቱ የማንም ሳይሆን የማህበረሰቡ ባህል መነሾ ነውና ባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶችን ይደግፋል እንጂ አይጻረርም። ክፍተቱ የመጣው ባፈጻጸም ችግር ስለሆነ አጣጥሞ መሠራት ላይ መጠናከር ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን በአገሪቱ ላይ ወንጀል መበራከቱና ሰላም መጥፋቱ አይቀሬ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ባህላዊ ህጎችና ዘመናዊ ህጉ በአሠራር ችግራቸው ተፈትቶ መፍትሔ የማይሰጣቸው ከሆነ የእርስ በርስ ግጭቶች ይበራከታሉ፤ ወንጀለኞችንም በቀላሉ መያዝ አይቻልም። ወንጀሎችም ተደብቀው ይቀራሉ። የበቀል ግድያዎች ይበዛሉ። ፍራቻ ስለሚሰፍን ማንም ማንንም አምኖ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ይሆናል። 

ዜና ትንታኔ
ጽጌረዳ ጫንያለው

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- በጃፓንና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር ባደረጉት አስተዋጽኦ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴ ከጃፓን መንግሥት ሽልማት ተበረከተላቸው።

ትናንት አምባሳደሩ በመኖሪያ ቤታቸው ባደረጉት የዕውቅና መርሃ ግብር ላይ የሁለቱ አገራት የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ለወይዘሮ ሮማን ወርቅና ብር ኮከብ ሜዳሊያ እንዲሁም ኒሻንና ሰርተፊኬት በጃፓን መንግሥት ስም ተበርክቶላቸዋል፡፡
በሽልማቱ ሥነ ሥርዓት ላይ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺኒቺ ሳኢዳ እንደተናገሩት፤ በሁለቱ አገራት መካከል ከዚህ ቀደምም የጠበቀ ወዳጅነት የነበረ ሲሆን ለዚህም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ሲያደርጉ ለቆዩት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለሽልማት በቅተዋል።
ወይዘሮ ሮማን ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሆነው ፓርላማ በነበሩበት ወቅት በሁለቱ አገራት መካከል ጥሩ ግንኙነት መፍጠርን ዓላማ ያደረገው የኢትዮ- ጃፓን የወዳጅነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው በሠሯቸው ስኬታማ ተግባራት እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ከመጡ በኋላም ባከናወኑት ተግባራት ለሽልማት መብቃታቸውን አምባሳደሩ ተናግረዋል።
ምንም እንኳ «ያደረኩት ሁሉ ለህዝቤ ማድረግ ያለብኝን እንጂ ለራሴ ባለመሆኑ ሽልማቱን አልቀበልም›› ያሉ ቢሆንም እስካሁን የነበረው ግንኙነት በተሻለ ደረጃ እንዲቀጥል ባለው አስፈላጊነት መግባባት ላይ ተደርሶ ሽልማቱን መቀበላቸውን አስታውሰዋል፡፡
ወይዘሮ ሮማን ሽልማቱን ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር፤ በወጣው ዕቅድ መሰረት ግንኙነቱን ለማጠናከር የሚያስችል በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የሁለቱ አገራት የባህል ልውውጥና ትውውቅ፤ በአገሪቱ እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብን እንዲጎበኙና ዓላማውን አስመልክቶ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የሚኖረው ፋይዳም የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የተሰጠው ዕውቅናም አገሪቱ ከተለያዩ አገራት ጋር የምታደርገው ግንኙነት የተሻለ እንደሆነ የሚያሳይና በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ ለመሥራት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

 

Published in የሀገር ውስጥ

ከአባቱ ግዕዝ የተወለደው የአማርኛ ፊደል እና ከግሪኩ የተወረሰው የላቲን ፊደል በኢትዮጵያ ፍጥጫ ውስጥ ናቸው። በርካታ ቋንቋዎች ከንግግርነት አልፈው ወደ ጽሑፍነት እየተሸጋገሩ በሚገኙባት ኢትዮጵያ ላይ ግዛታቸውን ለማስፋት ፊደሎቻቸውን አሰማርተዋል። የላቲን ወይም በተለምዶ የእንግሊዝኛ የሚባሉት ፊደላት(ስፔሊንግ) ግን የአማርኛውን ፊደላት ከሦስት እጥፍ በላይ በልጠው በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ላይ ለጽሑፍ አገልግሎትነት ውለዋል። ለእማኝነትም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ፊደል ከተቀረፀላቸው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ውስጥ 44ቱ የላቲን ፊደላትን ሲጠቀሙ 12ቱ ደግሞ የአማርኛን ፊደላት ይጠቀማሉ። የተቀሩት ደግሞ በንግግር ብቻ የሚታወቁ በመሆናቸው ፊደል ወይም ጽሑፍ የላቸውም። ይህ የአማርኛ ፊደላት በእጅጉ መበለጥ ያሳሰባቸው የኢትዮጵያ ምሁራን ደግሞ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ተሰባስበው «የትኛው ይበጃል?» ሲሉ መክረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ የሚነገሩ ቋንቋዎች ቁጥራቸው 86 ይደርሳል። ነገር ግን አሁንም ድረስ ፊደል ሳይቀረጽላቸው በመቅረቱ ሥርዓተ ጽሑፍ የሌላቸው 30 ቋንቋዎች ይገኛሉ። በመሆኑም ጽሑፍ ለሌላቸው ቋንቋዎች የኢትዮጵያን ፊደላትን ማዘጋጀት ቀሪ የቤት ሥራ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ በጽሑፍ ከሚገለጹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ውስጥ የላቲን ፊደላትን የሚጠቀሙት ደግሞ ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ።
ዶክተር ሙሉጌታ ከትምህርት ሚኒስቴር አገኘሁት ባሉት መረጃ፤ የሥርዓተ ጽሑፍ ከተዘጋጀላቸው 52 ቋንቋዎች ውስጥ 40 ቋንቋዎች የላቲን ፊደል ሲጠቀሙ 12ቱ ብቻ የአማርኛ ወይም የግዕዝ ፊደላትን በመጠቀም የሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾላቸው ለማስተማሪያነት እያገለገሉ ይገኛሉ። ይህም የሚያሳየው ዝብርቅርቅ ያለ የፊደል አጠቃቀም በአገሪቷ ውስጥ መኖሩን ነው ይላሉ።
እንደ ዶክተር ሙሉጌታ ማብራሪያ ከሆነ፣ ከኢትዮጵያ ውጪ በአፍሪካ የሚነገሩ ቋንቋዎች በአብዛኛው የላቲን ፊደላትን ለጽሑፎቻቸው ይጠቀማሉ። ይህ አካሄድ ደግሞ በቅኝ ግዛት ዘመን የደረሰባቸው የባህልና የታሪክ ወረራን ያመለክታል። ኢትዮጵያ ግን በቅኝ ግዛት ያልተያዘች በመሆኑ የእራሷን ፊደላት ይዛ እየተጠቀመች ትገኛለች። ነገር ግን በርካታ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ፊደል ሲዘጋጅላቸው የአማርኛ ፊደላትን ሳይሆን የላቲን ፊደላትን እንዲጠቀሙ የውጭ አገራትም ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ። በተጨማሪም በውስጥ ደግሞ የአማርኛ ፊደላትን ከቀድሞ ባላባቶችና ከጭቆና ጋር በማያያዝ ያለመጠቀም ፍላጎት ይስተዋላል። ነገር ግን በቋንቋ ቤተሰብነት ቢታይ የአማርኛ ፊደል ከላቲኒ ፊደል ይልቅ ለሌሎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የቀረበ ዝምድና አለው። በተጨማሪም ድምጾችን ለመወከል ከላቲኑ ይልቅ ይበልጥ ተፈላጊ ነው። በመሆኑም ፊደላቱ የኢትዮጵያ መሆናቸውን አምኖ በመቀበል ለእያንዳንዱ ቋንቋ መጻፊያነት እንዲያገለግል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። በተጨማሪ አንድ አገር የተለያዩ ቋንቋዎች ቢኖሩትም ተመሳሳይ ፊደላትን መጠቀም ከቻለ ሥነልቦናዊ አንድነቱ ይጨምራል፤ በውጤቱም የሕዝቦች ትስስርን ስለሚያጎለብት በጋራ ለመስራት ያለው ተነሳሽነት እንደሚጨምር ያስረዳሉ።
ለ25 ዓመታት በፊደል ታሪክ ላይ ጥናት ያካሄዱት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በከሬ ደግሞ የላቲን ፊደል መጠቀም አለብን ወይም የአማርኛ ፊደላትን በሚል ተቻኩሎ ውሳኔ ላይ መድረስ እንደማያስፈልግ ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው እምነት፤ ሕዝቦች የእራሳቸውን ቋንቋ በየትኛው ፊደል መጻፍ እንዳለባቸው የመምረጥ መብት አላቸው። የየቋንቋዎቹ ባለቤቶች ጉዳዩን በጥሞና ተረድተውና የትኛው ይሻለናል? በሚለው ምርጫ ላይ ተወያይተው ከሌሎቹ የቋንቋ ባለቤቶች ጋር እንዴት መተሳሰር እንዳለባቸው መብቱ ሊሰጣቸው ይገባል። በመሆኑም ሊያግባቡ በሚችሉ ነገሮች ላይ ሕዝቡ እየተወያየ ሊያስተሳስሩ የሚችሉ መንገዶችን እንዲፈልግ ዕድል መስጠት ያስፈልጋል። ነገር ግን የአማርኛ ፊደል ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጻፊያነት መዋል አለበት ወይም ላቲንኛው ይሻላል በሚል ድምዳሜ መስጠት ብቻውን አግባብ ባለመሆኑ ውሳኔውን ለሕዝብ ውይይት መተው ይሻላል የሚል አቋማቸውን አንፀባርቀዋል።
የምርጫው ጉዳይ ለተናጋሪው ይተው ቢባልም ግን እንደባለሙያ የእራሴ ምርጫ አለኝ የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፤ የአንድ አገር ብሔራዊ መንፈስ ምንድን ነው? ተብሎ ሲጠየቅ ብዙ ቋንቋ ይኑርም አይኑር ሕዝቦቹ እርስ በእርስ ለመግባባት መቻላቸውን የሚያጠናክረው ተመሳሳይነት ያለው ፊደል መጠቀምን ነው። በመሆኑም የቋንቋውን ሥነድምጽ እና ሥነምላድ በማጥናት የትኛውን ፊደል መጠቀም ይገባል? የሚለው ላይ ትኩረት መደረግ አለበት። በዚህ አካሄድ ግን ከአማርኛው ይልቅ ምንጩ ከግብጾች የሆነውና በግሪክ ተሸጋግሮ ወደላቲን የተቀየረው ፊደል ድምጾችን በመወከል ረገድ ድክመት እንዳለው ያስረዳሉ።
በጥንታዊ ቋንቋዎች ላይ ጥናት የሚያደርጉት ዶክተር መርሻ አለኸኝ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የቆየ ታሪክ ባህል እና ምርምር የተጻፈው በግዕዝ ቋንቋ ነው። ግዕዝ እና አማርኛ የሚጠቀሙባቸው ፊደላት ደግሞ ተመሳሳይ ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ፊደላት ማወቅ በቀደምትነት በኢትዮጵያውያን የተጻፉ ጥልቅ ምርምርና ዕውቀትን እንዲሁም ታሪክን የያዙ መጻሕፍትን በመመርመር አዲሱ ትውልድ ወደእራሱ ማንነት ለመመለስ ይረዳል። ነገር ግን የላቲን ፊደላትን ተጠቅሞ ቋንቋውን ይማር ቢባል የአገሩን ቀደምት እውነታ መርምሮ ለመረዳት ያለው ዕድል ላይ እንቅፋት ይፈጥራል። በዚህም ምክንያት በላቲኑ ብቻ የተማረው ወጣት ለአገሩ ዕውቀት ባዳ እንዲሆን መገፋፋት እንደሚሆን ያስረዳሉ።
«ለእኔ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ ፊደላትም ልክ እንደ አክሱም ሐውልትና ሌሎች ቅርሶች ለኢትዮጵያ መገለጫዎች ናቸው» የሚሉት ዶክተር መርሻ፤ ፊደል ልክ እንደባንዲራ የአንድ አገር ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። የአገሪቷ ብቻ የሆኑ ሆሄያት ልክ እንደ ሕዝብ ባህል እና ታሪክ ማሳያ ናቸውና። በመሆኑም የኢትዮጵያን ፊደላት መንከባከብ እና ማዳበር ያስፈልጋል። የላቲን ፊደላትን ብቻ እየተጠቀሙ መቀጠል ደግሞ ታሪካችንን እንድንመረምር ለማይፈልጉ የአውሮፓ እና አሜሪካ አገራት ምቹ ሁኔታ መፍጠር በመሆኑ ቋንቋዎችን በኢትዮጵያዊ ፊደላት መጠቀሙ በጎ እንደሚሆን ይናገራሉ። አያይዘውም አማርኛ ሆሄያትን ከመጠም ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ቋንቋዎች ለማሳደግ የሚረዱ ጥናት እና ምርምሮችን ማብዛት እንደሚገባም ይገልጻሉ።

 

ዜና ሐተታ
ጌትነት ተስፋማርያም

Published in የሀገር ውስጥ

ምሥራቅጉጂ፦ ያልተበረዘውን የአገሪቷን ባህል ለአዲሱ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ትውፊት እና ባህል ላይ ያተኮሩ ዝክረ ኪነጥበብ ዝግጅቶች መለመድ እንዳለባቸው ተገለጸ።
«ባህላዊ እሴቶቻችን ለሰላማችን እና ለአብሮነታችን» በሚል መሪ ሃሳብ በነገሌ ከተማ እየተካሄደ ባለው ዝክረ ኪነጥበብ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እልፍነሽ ኃይሌ እንደገለጹት፤ ኪነጥበብ ለባህል መጎልበት ጉልህ ድርሻ አላቸው። ያልተበረዘውን ቱባ ባህል ወደ አዲሱ ትውልድ ለማሸጋገር ዝክረ ኪነጥበባት ዓይነተኛ ሚና አላቸው። በመሆኑም ያልተበረዘውን ባህል የያዙ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች በብዛት ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እንደ ዶክተር እልፍነሽ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔርብሔረሰበች እና ሕዝቦች ባህላዊ እና ኪነጥበባዊ እሴቶቻቸውን ለማጎልበት ማዕከሉ እየሰራ ይገኛል። በዚህም ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር የዝክረ ኪነጥበብ ዝግጅቱ በምሥራቅ ጉጂ እንዲሰናዳ አድርጓል። በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ እሴቶችን በመደገፍ ሳይበረዙ እና ሳይሸራረፉ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ መሰል መሰናዶዎች በተከታታይ ይዘጋጃሉ። የክልሉን ትክክለኛ ባህላዊ እና ኪነጥበባዊ እሴቶች ለመለየትም ጥልቅ ጥናቶች እንደሚደረጉም ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የባህል እና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ዋቅጋሪ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በርካታ ቱባ ባህል እና ኪነጥበብ ስብጥር ባለቤት ናት። በመሆኑም ይህን ሀብት ከመጠበቅ ባሻገር አበልፅጎ ለመጪው ትውልድ ማሸጋገር አስፈላጊ ነው። የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮም ይህን ያልተበረዘውን ቱባ ባህል ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ ከሚመለከተው አካል ጋር በመስራት ዝክረ ኪነጥበባት እያሰናዳ ይገኛል። በኪነጥበባዊ መንገድ ትውልዱ ያልተበረዘውን ባህል እንዲያውቅ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የዝክረ ኪነጥበብ ዝግጅቱ አንዱ ዓላማም እሴቶቹን አጉልቶ ለማውጣት እና ለመደገፍ ታስቦ የተሰናዳ መሆኑን ጠቁመዋል።
የገዳ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትልቁ የኦሮሞ ሕዝብ ፍልስፍና ውጤት ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ይህንን እና ሌሎች ባህላዊ ኪነጥበባዊ ሀብቶችን መጠበቅ፣ ማበልፀግ እንዲሁም ለሰላም እና አንድነት መጠናከር እንዲጠቅሙ መስራት የሁሉም ኃላፊነት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የጉጂ ዞን የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዱቤ አዱላ በበኩላቸው፤ የምሥራቅ ጉጂ ዞን የኦሮሚያ ሕዝብ ዋና መገለጫ የሆነውን የገዳ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በዋናነት ጠብቀው ካቆዩት ውስጥ የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ሥርዓት ውስጥ በርካታ የኪነጥበብ ሀብቶች ይገኛሉ። በዝግጅቱ ላይም ይህን ሀብት አጉልቶ ለማሳየት መቻሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ባህል ማእከል እና የኦሮሚያ ባህልእና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ ባዘጋጁት ዝክረ ኪነጥበብ ላይ 14 የኪነጥበብ ቡድኖች ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች ተውጣጥተው ተሳታፊ ሆነዋል። ላለፉት አምስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ዝክረኪነጥበብ የኦሮሞን ባህል የሚገልፁ ሙዚቃዎች፣ ድራማዎች፣ ውዝዋዜዎች እንዲሁም ግጥሞች ቀርበውበታል። በመዝጊያ ሥነሥርዓቱ ላይም አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን በመዘከር ለወጣት ተከታዮቻቸው ተምሳሌት እንዲሆኑ ታሳቢ በማድረግ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ እውቅና ተሰጥቷቸዋል። በኪነጥበብ እና ባህል ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ዳግም ከበደ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።