Items filtered by date: Monday, 04 June 2018
Monday, 04 June 2018 18:50

አዲስ አበባና ክረምቷ

ሰላም እንዴት ሰነበታችሁ፤ ክረምቱስ እንዴት ይዟችኋል? የዘንድሮው ክረምት «ሰኔ ግም አለ» ሳይባል ዘው ብሎ በግንቦት ነው የገባው። በአቋራጭ ቀድሞ መገኘት ከአዲስ አበባ ጩልሌዎች አልፎ ዝናቡም ላይ የተጋባ ይመስል ሰኔ ሲጠበቅ በግንቦት የኋላ በር ሾልኮ «መጣሁ» ብሎናል። አንዳንዴ ግን ነገሮችን በመልካም ማሰብ ደግ ነውና ከመዲናይቱ ወጣቶች ተምሮ ሊያስደንቀን (ሰርፕራይዝ ሊያደርገንም) ይሆናል እኮ ቀድሞ መምጣቱ ብለን ማሰብ እንችላለን። የሰሞኑ ሁኔታው ግን ከማስደነቅም ባለፈ የለየለት የክረምት ጸባይን የሚያሳይ በመሆኑ ቀድሞ መዘጋጀት እንደሚገባ ላስታውስ።
የክረምት መምጣት ከእርሻ ሥራ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ዝግጅቱ ተገቢ ቢሆንም ነጥቤ በአዲስ አበባና በአዲስ አበቤያውያኑ ላይ የሚያጠነጥን ነው። እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ክረምት ከመጋነኑም በላይ ያኮረፈ ህጻን ጸባይ ይታይበታል። ፊቱን አጨፍግጎ (የልጅ ውበቱ ከፍልቅልቅነቱም አይደል?፤ ከተማዋም ስታኮርፍ ውበቷ ሁሉ ይሸሸጋል) ያለቃቅስና ዝም፤ ደግሞ ጥቂት አርፎ ይጀምረዋል እንዲሁ ሄድ መጣ እያለም ተነጫንጮ ያነጫንጫል።
በብርድ ልብስ እንደተጀቦነች ውበቷን ሊያዩ እንደሚጓጉላት ልጃገረድ፤ ጥቅልሏን መጣል ስትጀምር ይበልጥ እየጎላች ይብሱን እያማረች እንደምትሄድ ሴት ትሆንብኛለች፤ አዲስ አበባ። ከተማ ላይ ክረምት እንደ ገጠሩ አካባቢ ውበት አይዘራም ያደበዝዛል እንጂ። በእኔ እይታ ገጠር እንደተከበረች እመቤት ነው፤ በሸማዋ ላይ ካባ ሲደረብላት ግርማዋ እንደሚጎላ ሁሉ ክረምቱ የሚያላብሰው አረንጓዴ ሸማ ውበት ይሆነዋል። በአንጻሩ ከተማ የሚያምረው እርቃኑን ነው፤ የለመድነው እንደዛ ነዋ!
አዲስ አበባ ሞቃታማው ወራት ተጠናቆ የክረምቱ ወቅት መተካት ሲጀምር ምጥ እንደያዛት ወላድ ጭንቅ ጥብብ ማለት ትጀምራለች። ዝናቡ ሲጀማምር ሁሉም ነገር አቅጣጫውን ስቶ እንዳልነበር መሆን ይጀምራል። መንገዶቿማ ፈተው እንደለቀቁት እምቦሳ እንዳሻቸው የሄደውን መላሽ የተመለሰውንም ወሳጅ ይሆናሉ። በዚህ ጊዜ የመንገድ ዳር የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎቹም ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ፍሳሹን ሁሉ በ«በቃኝ» እየተፉ ለእግረኛውም ለተሽከርካሪውም ጠንቅ ይሆናሉ።
ጠንከር ያለ ዝናብ የጣለ ዕለትማ መንገዱቹ በከፊል የወንዝነት ማዕረግ ይላበሳሉ፤ ተሽከርካሪውን ከእግረኛ አግረኛውንም ከተሽከርካሪ ላለማገናኘት የቆረጡ ይመስላሉ። መንገዱ ራሱ፤ መንገድ ለማቋረጥ አሊያም ውሃ ከሚፈሩት የከተማዋ መኪኖች ጋር ለመድረስ እግረኞች በሚያደርጉት መዝለልና የመዝለል ሙከራ የሚሳለቅ ይመስለኛል።
ሌላው የሚገርመውና የመንገዱ እምቢተኝነት የሚታየው በትራፊክ እንቅስቃሴው መጨናነቅ ነው። መዝነብን አሊያም መዳመንን ተከትሎ ተሽከርካሪዎች በኤሊ ፍጥነት መጓዛቸው የተለመደ ሆኗል። የአንድ መንገድ በወቅቶች መፈራረቅ የመንገድ መዘጋጋትን ማስከተል ምናልባትም በጥናት የታገዘ ምላሽ የሚያስፈልገው ይሆናል። አንዳንዴ ግን የተሽከርካሪዎቹ በዝቅተኛ ፍጥነት መጓዝ አስፈላጊ ሊሆንም ይችላል፤ ምክንያቱማ ተሽከርካሪዎቹ በየመንገዱ የሚታቆረውን ውሃ ረግጠው ሲያልፉ እግረኛውን እንደ ጥምቀት ጸበል እንዳይረጩ ያደርጋል። አንዳንዱ አሽከርካሪማ እድሜውም ጭምር ያጠራጥራል በልጅነቱ ተጫውቶ ያልጠገበ ይመስል የሚሳለቀው ውሃ በመርጨት ነው። እንዲህ ዓይነቱ አሽከርካሪ ልቦና ይስጠው እንጂ ሌላ የሚባል አይኖርም።
ከጠቅላላው የከተማዋ ሁኔታ ስመለስ የአንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎችና ክረምት የማይዋደዱ ይመስለኛል። በተለይ ገና የዝናብ ጉርምርምታ ሲሰማ በድንጋጤ የሚርገበገብ። በተመሳሳይ «እንኳን ዘንቦብሽ...» የተባለላቸው ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ ምስኪኖች፤ ክረምት አስቸጋሪ ይሆናል። በበጋው «ቤቴ ጠባብ ነው» ብለው ዕቃ ያልገዙ ሁሉ በክረምት መቆጨታቸውም አይቀርም። የሚያፈስ ጣሪያ፣ ንፋስ የሚያስገባ የግድግዳ ስንጥቃት፣ ጎርፉን «ግባ በሞቴ» እያለ ወደቤት የሚጋብዝ በረንዳ ያላቸውማ፤ እዚህ ጋር ባልዲ፣ እዚያ ጋር የእጅ ማስታጠቢያ፣ ወዲያ ሳፋ ሲደቅኑ፣ ሌላው ጋር ጨርቅ በመወተፍ፣... በዚህ ሁሉ ግብ ግብ ሌሊቱ አልፎ በቀን ይተካባቸዋል።
ሌላኛው ክረምት የሚከብድበት ከሥራ መልስ ብርዱንም ዝናቡንም ተሽቀዳድሞ ከቤቱ የሚደርስ ላጤ ነው። ሙቀትና እንቅልፍ ፍለጋ የተዘጋ በር ከፍቶ መግባትና ቀዝቃዛ አንሶላ ገልጦ እንደመተኛት አስቸጋሪ ነገርም አይኖርም። ለነገሩ ለዚህስ መፍትሄ አለው፤ ያው እንደተለመደው «ልጠለል» በሚል ሰበብ ጥላ ተጋርቶ መቀለጣጠፍና ለሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ከአንድ ጥላ ስር መጠቃለል ነው።
የአዲስ አበባ ክረምት ሲታወስ በየመንገዱ ዳር በቀዩ ፍም ላይ ተጋድሞ «ዷ፣ ዶሽ» እያለ የሚጣራው የበቆሎ ጥብስ ቅድሚያ የሚጠቀስ ነው። መልካቸውን አሳምረው ሙቅ ትንፋሻቸውን ወደላይ እያትጎለጎሉ ሽታቸው ጭምር የ«ብሉኝ» ግብዣ የሚያቀርቡት ቅቅል በቆሎዎችም በብርድ ለተቆራመደ ሌላ አማራጭ ናቸው። ይህንን በቅድሚያ አነሳሁ እንጂ የክረምቱ መልካም ትዝታዎችስ እኚህ ብቻም አይደሉም።
ከጨዋታው ስንመለስ ግን፤ በዝናቡ ምክንያት በየቦታው ጎርፍ መከሰቱ አይቀርምና መጠንቀቁ ይበጃል። በተለይ ታዳጊዎች ሲወራ ከሚሰሙት ተነስተው ለመጫወትና ለዋና ከወንዞች አቅራቢያ መገኘታቸው አይቀርምና፤ ወላጆች የሚደርሰውን አደጋ ቀድሞ ማሳወቅ ተገቢ ነው። ከትራፊክና ከመሰል አደጋ እንዲጠበቁ መንገርና መቆጣጠር ያሻልም መልዕክቴ ነው። ለዛሬ በክረምቱ መግቢያ ላይ ይህን ያህል ካልኩ ላብቃ፤ በቸር ይግጠመን።

 

የተማሪዎችን ፊት የሚያጠናው መሳሪያ

 

ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችንና ወላጆችን ለመሳብ ሲሉ የመማሪያ ክፍሎችንና ግቢውን በማሰማመር ይጠመዱ ይሆናል። በእውቀት የዳበሩና ከፍተኛ ልምድ ባላቸው መምህራን ትምህርት እንደሚሰጥም ሲያውጁ ይሰማል። በቤተ-መዛግብት እና በቤተ-ሙከራ ከመታገዝም በላይ ተማሪዎች በአእምሮና በአካል ብቃት እንዲዳብሩ ስለማድረጉም ያሳውቃሉ። ይህ ዓይነቱ ማስታወቂያ ተማሪዎችን በመልካም ምግባር እንዲሁም በእውቀት አንጾ የተሻለ ዜጋ ያደርጋቸዋል ከሚል እሳቤ የሚመነጭም ነው። በቻይና የሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ግን፤ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ አንዴ ብቻም ሳይሆን ሁለቴ ያጤነ ይመስላል።
ሃንግዦሆ በተባለ ግዛት የሚገኘው ይህ ትምህርት ቤት ምንም እንኳ የመምህራን የትምህርት አሰጣጥ መልካም የሚባል ቢሆንም ተማሪዎች ከቤታቸው ይዘውት የሚመጡት ስሜት ተከትሏቸው የመማሪያ ክፍል ከገባ በትምህርት አሰጣጡ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል ባይ ነው። ስለዚህም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ተማሪዎች ያላቸውን ስሜት በማጥናት ትምህርት አሰጣጡ ምን መምሰል አለበት የሚለውን ይወስናል።
በትምህርት ክፍል ውስጥ ከሚገኘው ሰሌዳ በላይ የሚገጠመው ካሜራ የተማሪዎቹን ገጽ ፊት ለፊት መመልከት እንደሚችል የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ያሳያል። የእያንዳንዱ ተማሪ የፊት ገጽ ላይ የሚነበበውን ስሜትም በሶፍትዌሩ አማካኝነት በመተንተን በምስል ያስቀምጣል። ካሜራው የሚያነባቸው የስሜት ዓይነቶች ሰባት ሲሆኑ እነርሱም፤ ደስተኛ፣ ያዘነ፣ የተበሳጨ፣ የተቆጣ፣ የፈራ፣ የጓጓ እንዲሁም ብቸኝነትን የሚያንጸባርቅ ናቸው። ታዲያ መምህራኑ የተማሪዎቻቸውን ስሜት ከመሳሪያ ላይ በማንበብ በምን ዓይነት መንገድ ማስተማር እንዳለባቸው የሚጠቁም ሆኖ ተገኝቷል።
መምህር እያስተማረ ሳለ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ተማሪዎች ፊት ላይ የመረበሽ ስሜት የሚታይ ከሆነም በቀጥታ ለመምህሩ በማሳወቅ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋልም ተብሏል ቴክኖሎጂው። በዚህም በክፍል ውስጥ የሚኖሩ ረብሻዎች መቀነስ እንዳለ ሆኖ ከተማሪዎች ስሜት በመነሳት የመምህራን የማስተማር ብቃትም ግምት ውስጥ ሊገባ ችሏል። መምህራኑ ስለ አዲሱ ቴክኖሎጂ ሲጠየቁ «የትኛው ተማሪ በትክክል ይማራል የትኛውስ አይማርም» የሚለውን ለመለየት ጥሩ መላ እንደሆነላቸው ነው ያስታወቁት። አንድ ተማሪ በበኩሉ «በፊት ትምህርቴን በደንብ ከመከታተል ይልቅ ድብርትና ስንፍና ስለሚጫጫነኝ መምህራኑ ሳያዩኝ እተኛ ነበር። አሁን ግን ስውር አይኖች እንደሚመለከተኝ ስለማውቅ ትምህርቴን በደንብ መከታተል ጀምሬያለሁ» የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው «ህጻናት ላይ አምባገነን መሆን አያስፈልግም፤ ያሉት ትምህርት ቤት እንጂ ካምፕ ውስጥ አደለም» ሲሉም ተደምጠዋል። «ስውር ካሜራ መኖሩ እየታወቀ እንዴት ሃሳብን ሰብስቦ መማር ይቻላል?» ሲሉ ግራ መጋባታቸውን በጥያቄ ያቀረቡም አልጠፉም።
በዚህ አጋጣሚ ሰሞኑን እየተሰጠ በሚገኘው የ10ኛና 12ኛ ብሄራዊ ፈተና ኩረጃ አንዱ የስጋት ምንጭ መሆኑን ሳስታውስ ምነው ይህንን መሳርያ ወደኛ አምጥተን እንዲህ አይነት የፈተና ቀበኞችን ብንጠብቅበት ብዬ ተመኘሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እርስዎስ ምን ይላሉ?

ብርሃን ፈይሳ

Published in መዝናኛ
Monday, 04 June 2018 18:38

የፊፋ ዓለም «ዋንጫ»

 

ሃገራትም ሆኑ ተጫዋቾች በስፖርቱ ከሚያገኟቸው ክብሮች ሁሉ ይሄን የሚያህል አይኖርም። የብሄራዊ ቡድኖች የስኬት መለኪያ፤ የተጫዋቾች ህልምም መፍቻ ነው፤ የፊፋ ዓለም ዋንጫ። በዓለም ላይ ከሚካሄዱ ስፖርታዊ ሁነቶች በተወዳጅነታቸው ቀዳሚ ከሆኑት መካከል ይገኛል። በየአራት ዓመቱ በሃገራት መካከል ለሚካሄደው ሰላማዊ ፍልሚያ ብሄራዊ ቡድኖች ከምንጊዜውም በላይ ይዘጋጃሉ፤ በውድድሩ የተሻለ አቋም ያሳየውም በዓለም እግር ኳስ ደረጃ አናት የመገኘት እድል ያገኛል።
በእግር ኳስ ስፖርት አውራ በሆነው በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ መልካም ነገር ቢሆንም፤ ዋንጫውን ማንሳት ግን የተለየ እርካታና ክብርን ያስገኛል። 32 ሃገራት የሚሳተፉበት የሩሲያው የዓለም ዋንጫም ሊካሄድ ከ10 ያልበለጠ ቀናት ብቻ ይቀረዋል። ቡድኖቹ በአንድ መድረክ ተገናኝተው ከፍተኛ ትግል ስለሚያደርጉለት የዓለም ዋንጫ በጥቂት እናስታውስ።
ፊፋ ለአሸናፊዎች የሚያበረክተው ዋንጫ አሁን ያለውን ቅርጽ ከመያዙ በፊት አሸናፊዎች የሚበረከትላቸው በሌላ ቅርጽ የተዘጋጀ ዋንጫ ነበር። ለመጠሪያ የሆነውን ስምም ለዓለም ዋንጫ መካሄድ መሰረት ከሆኑት ሰው በውሰት ያገኘው ነው። በፊፋ ሶስተኛው ፕሬዚዳንት የሆኑት ፈረንሳዊው «ጁሊየስ ሪሚት» እኤአ ከ1922 ጀምሮ ውድድሩ እንዲካሄድ ሃሳብ ከማቅረብም በላይ ግፊት በማድረግ ይታወቃሉ።
እኤአ በ1929 ህይወታቸው ካለፈ በኋላ በቀጣዩ ዓመት የተጀመረው የዓለም ዋንጫ በስማቸው እንዲሰየም ተደርጓል። ዲዛይኑ አቤል ላፍሊየር በተባለ ባለሙያ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በግሪክ የ«ድል» ምልክት እንደሆነ በሚታመነው ቅርጽ ተምሳሌት ከወርቅና ብር የተሰራም ነው። እኤአ እስከ 1970 ባሉት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ለአሸናፊው ቡድን ይኸው ዋንጫ ሲበረከትለት ቆይቷል። ዋንጫው 35 ሣንቲ ሜትር የሚረዝም ሲሆን፤ 3ነጥብ8 ኪሎ ግራም ክብደትም አለው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሳችውም ኡራጓይ ናት።
ሁለተኛው የዓለም ዋንጫ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመር በመደናቀፉ ከስምንት ዓመታት በኋላ ነበር የተካሄደው። በጦርነቱ ወቅት ውድድሩ ባይካሄድም የወቅቱ የፊፋ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ጣሊያናዊው ኦቶሪኖ ባራሲ ዋንጫውን ከናዚ ጥቃት ለመታደግ ሲሉ ከሚቀመጥበት ባንክ አውጥተው አልጋቸው ስር ሸሽገውት እንደነበርም ታሪክ ያወሳል። ጦርነቱ ካበቃ በኃላ በተካሄደው ውድድርም ጣሊያን የዋንጫው ባለቤት ነበረች።
እኤአ የ1966ቱ ዓለም ዋንጫ ሊካሄድ አራት ወራት ሲቀሩት ዋንጫው ለእይታ በዓለም ሃገራት እየተዘዋወረ ሳለ ግን ለስርቆት ተዳረገ። በጊዜው ጉብኝቱ በእንግሊዟ ለንደን በሚገኝ አንድ አዳራሽ እየተካሄደ እንዳለም ነበር አደጋው ያጋጠመው። ይሁን እንጂ ከሰባት ቀናት በኃላ በደቡባዊው የለንደን ክፍል በሚገኝ ኮረብታማ ስፍራ ፒክልስ በተባለ የፖሊስ ውሻ አማካኝነት ሊገኝ ችሏል። ውሻው ለዚህ ተግባሩ ዕድሜ ልኩን ምግብ ሊገዛለት እንደሚችል በማመን የ6ሺ ፓውንድ ሽልማት ተበርክቶለታል።
ከዚህ አጋጣሚ በኋላም ነው በየሃገራቱ ለእይታ የሚጓጓዙት ዋንጫዎች በዋናው የዓለም ዋንጫ አምሳል እንዲዘጋጁ የተደረገው። የዋንጫው ቅጂ እኤአ1997 ፊፋ በ254ሺ 500 ፓውንድ እስኪገዛው ድረስም በፈጣሪዎቹ እጅ በሚስጥር የተያዘ ነበር። ይህ ዋጋም ዋናው ዋንጫ በቅድሚያ ከተገዛበት ዋጋ አስር እጥፍ ብልጫ ያለው ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በእንግሊዟ ማንቺስተር ከተማ በሚገኝ ሙዚየም ለጎብኚዎች እይታ በሚመች መልኩ ተቀምጧል። ብራዚል ለሶስት ጊዜያት ይህንን ዋንጫ በማንሳቷ እውነተኛውን ዋንጫ በ1970 የወሰደች ሲሆን፤ ኡራጋይና ጣሊያን ሁለት ሁለት ጊዜ እንዲሁም ጀርመንና እንግሊዝ አንድ አንድ ጊዜ አንስተዋል።
የብራዚል እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ንብረት የሆነው ዋንጫ እኤአ በ1983 ከሪዮ ስርቆት ተፈጽሞበታል። ዋንጫውን ሰርቀዋል የተባሉ አራት ግለሰቦች ቢያዙም ዋንጫው ግን ሊገኝ ባለመቻሉ «ቀልጧል አሊያም በግለሰቦች ቁጥጥር ስር ውሏል» የሚል መላምት ላይ ተደርሷል። በዚሁ አደጋ ምክንያትም ሃገሪቷ በአምሳሉ የተዘጋጀ ሌላ ዋንጫ ወስዳለች።
እኤአ ከ1974 በኃላ ግን «የፊፋ ዓለም ዋንጫ» በሚል አዲስ ስያሜ አዲሱ ዋንጫ ለዓለም ተዋወቀ። ከ18 ካራት ወርቅ (75 ከመቶ የሚሆነው የተጣራ ወርቅ) የተዘጋጀው 36ነጥብ 5ሳንቲ ሜትር ርዝማኔ ያለውና 5ኪሎ ግራም የሚመዝነው ዋንጫ በጣሊያን ካምፓኒ የተዘጋጀ ነው። እኤአ 2017 በነበረው የዋጋ ተመን መሰረትም ይኸው ዋንጫ 150ሺ የአሜሪካ ዶላር እንደሚያወጣ ተረጋግጧል።
ከ1994ቱ የዓለም ዋንጫ ጀምሮ የአሸናፊውን ሃገር እንዲሁም ቀድሞ ዋንጫ ያነሱ ብሔራዊ ቡድኖችን ስም በቀላሉ በማይታይ መልኩ በማስፈርም መጠነኛ መሻሻል ተደርጎለታል። ዋንጫ የሚያነሱ ሃገራት ከዋናው የወርቅ ዋንጫ ተቀራራቢ የሆነው የሚበረከትላቸው ሲሆን፤ ዋናው ግን በዙሪክ በሚገኝ ሙዚየም ውስጥ ይገኛል። ጀርመን እኤአ በ1974 ይህንኑ ዋንጫ በማንሳት የመጀመሪያዋ ሃገር ስትሆን በጥቅሉ ሶስት የፊፋ የዓለም ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለች ሃገርም ናት። አርጀንቲና ጣሊያንና ብራዚል ሁለት ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ያነሱ ሃገራት ሲሆኑ፤ ፈረንሳይና ስፔን አንድ አንድ ጊዜ የዋንጫው ባለቤቶች ሆነዋል።

ብርሃን ፈይሳ

 

Published in ስፖርት

 

በክብረወሰን የታጀቡ ድሎችን ማስመዝገብ የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መለያ ነው። ሃገሪቷ የምትታወቅበት ይኸው ስፖርትም በንጽህና ላይ የተመሰረተ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል። ተፈጥሮአዊው የአየር ንብረት እና የቦታ አቀማመጥ ለስፖርቱ ከፍተኛ እገዛ ያለው በመሆኑ፤ አትሌቶች በተፈጥሮአዊ መንገድ በሚያደርጉት ጉዞ ከእውቅና ማማ ላይ ደርሰው ዓለምን አስደምመዋል። ከዘመኑ ጋር ተያይዞ ግን ይህ መልካም ምግባር የመበረዝ ምልክት እየታየበት ነው።
በዚህ ወቅት በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት የሚነሳውና የዓለምን ስፖርት በማጠልሸት ላይ የሚገኘው የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው። ዓለም አቀፉ የጸረ አበረታች መድሃኒቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲም በሃገራትና በአትሌቶች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉና በስፖርቱ ስመጥር በሆኑ ሃገራትም ክትትሉ ይበልጥ የተጠናከረ ይሆናል። ሃገራት በራሳቸው አቅም የግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የመቆጣጠር እንዲሁም የመቅጣት አቅም እንዲያጎለብቱም ያስገድዳል። ኢትዮጵያም ጽህፈት ቤት በማቋቋም፣ የህግ ማእቀፎችን በማዘጋጀት እንዲሁም ምርመራ በማድረግ ተጠቃሚ አትሌቶችን በመቅጣት ጭምር ይበል የሚያሰኝ ተግባር የፈጸመች ሃገር ናት። ይህንንም የዓለም አቀፎቹ ተቋማት አመራሮች ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ተገኝተው በማረጋገጣቸው እውቅና ማግኘቷ የሚታወስ ነው።
ሃገሪቷ በመልካም ተግባር እውቅናውን ታግኝ እንጂ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አበረታች ንጥረነገሮቹን እንደተጠቀሙ የተረጋገጠባቸው አትሌቶች እና ተቀጪዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን መታዘብ ይቻላል። እስካሁን አምስት የሚሆኑ አትሌቶች ለአራት ዓመታት በየትኛውም የአትሌቲክስ ውድድር እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ቅጣት ተላልፎባቸዋል። በጉዳዩ ላይ ያለው እውቅና ሲጨምር የጥፋተኞች ቁጥር መጨመርም የስፖርት ቤተሰቡን ብዥታ ውስጥ የሚከት ሆኗል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የጸረ አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል፤ ጽሕፈት ቤቱ ሁለት ኃላፊነቶችን ወስዶ እየሰራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የመጀመሪያው ኃላፊነት ግንዛቤ ማስጨበጥ ሲሆን፤ ስፖርተኞችን እንዲሁም ከስፖርቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አካላት ማስተማር በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ የተቀመጠ ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ሌላው የክትትልና ቁጥጥር ስራ፤ በውድድር ጊዜ እንዲሁም ከውድድር ውጪ በድንገት የደምና የሽንት ናሙናዎችን ከስፖርተኞች መውሰድ ነው። ይህን ተከትሎ በሚመጣው ውጤት መሰረት ጥፋተኛ የሆኑትም ይቀጣሉ፤ ቅጣቱም እንደ ሁኔታው አስተዳደራዊ አሊያም በወንጀል ህጉ ሊታይም ይችላል።
በቅርቡ እንደተሰማው ቅመሙን እንደወሰዱ የተረጋገጡባቸው አምስት አትሌቶች እኤአ ከ2016 ጀምሮ በተደረጉ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የተሳተፉ ናቸው። በቻይና በተካሄዱ ውድድሮች የተያዙት ሶስት አትሌቶች አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ። የተቀሩት ሁለት አትሌቶች ደግሞ በደቡብ አሜሪካ እና ደቡብ አፍሪካ በተካሄዱ ውድድሮች ላይ የተያዙ ናቸው። በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በሚዘጋጁ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ አንድም አትሌት ቅመሙን ወስዶ አልተገኘም።
እንደ ጽህፈት ቤቱ መረጃ፤ ለቅጣት ከተዳረጉት አትሌቶች ለመረዳት የተቻለው አበረታች ቅመሙን የወሰዱት እያወቁ መሆኑን ነው። ስለ አበረታች መድሃኒት ምንነት ብቻም ሳይሆን ሲደረስባቸው ስለሚወሰድባቸው ቅጣትም ጭምር እያወቁ በመውሰዳቸውም ነው ለአራት ዓመታት እገዳ የተዳረጉት። እነዚህ አትሌቶች ቅጣታቸውን ከጨረሱ በኃላም በድጋሚ በዚህ ተግባር ላይ ቢገኙ ከስፖርቱ ሙሉ ለሙሉ ሊወጡ የሚችሉበት ሁኔታም ይኖራል።
አትሌቶቹ በማናጀር የሚሰለጥኑ (ከመከላከያው አሊ አብዶሽ በቀር) መሆኑም ተረጋግጧል። እነዚህ አትሌቶች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እውቅና የሌላቸውና ማረጋገጫ ያላገኙ ከመሆናቸውም በላይ በራሳቸው መንገድ ውድድሮቹ ላይ የተሳተፉ እና ሃገሪቷን በየትኛውም ውድድር ያልወከሉ ናቸው።
ቅጣቶቹ በቅርብ ጊዜ ይገለጹ እንጂ ምርመራውና አጠቃላይ ሂደቱ ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ። የአንድ አትሌት ናሙና ከተወሰደ በኃላ ምልክቶች ከታዩ በድጋሚ ሌላ ናሙና በመውሰድ ምርመራና ማጣሪያው የሚቀጥል ሲሆን፤ የተገኘበት አትሌትም ከቅጣት በፊት በዳኝነት ሂደቱ ላይ እንዲከራከር እድል ይሰጠዋል። እነዚህን ሂደቶች ለማሳለፍ የሚኖረው ቆይታ ምናልባትም እስከ አንድ ዓመት ሊደርስ ስለሚችል እንጂ፤ በዚህ ወቅት ተጠቃሚነቱ ጭማሪ በማሳየቱ እንዳልሆነም ያረጋግጣሉ።
እርግጥ ነው በሌሎች ሃገራት በአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት በርካታ ቁጥር ያላቸው አትሌቶች በየዓመቱ ይቀጣሉ። እአአ የ2016ቱን ለማሳያነት ቢጠቀስ፤ ጣሊያን በ147 አትሌቶች ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች። ፈረንሳይ በ86፣ አሜሪካ በ76፣ አውስትራሊያ በ75፣ ቤልጂየም በ73 አትሌቶች እስከ አምስት ባለው ደረጃ ይከተላሉ። ደቡብ አፍሪካ በ50 አትሌቶች ከዓለም ዘጠነኛ ስትሆን በአፍሪካ የመጀመሪያውን ስፍራ ይዛለች። ኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገራት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር አምስት አትሌቶች መያዛቸው በርካታ የማይባል ቁጥር ነው።
ነገር ግን በንጹህ ስፖርት ለምትታወቀው ኢትዮጵያ ይህ ቁጥር ትንሽ የሚባል አይሆንም። ዳይሬክተሩ በበኩላቸው፣ «መታወቅ ያለበት የጽህፈት ቤቱ አቅም ይበልጥ ሲጎለብት የሚያዙ አትሌቶች ቁጥርም ሊጨምር እንደሚችል መሆኑን ነው» ይላሉ። አሁን ሃገሪቷ በምርመራ ያላት አቅም ከ600 ያልበለጠ ነው፤ ይህ ማለትም በሁሉም ክለቦችና በማናጀር የሚሰለጥኑ እንዲሁም በውጪ ሃገራት ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችን ማዳረስ አልተቻለም። እስካሁን እየተሰራ ያለው በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ሲሆን፤ አቅም በተጠናከረ ጊዜ በግላቸው የሚሰለጥኑ አትሌቶችንም ጭምር ስለሚያሳትፍ ከዚህም የበለጠ ቁጥር ይመዘገባልና በዚህ መደናገጥ እንደማይገባ ይገለጻሉ። ይሁን እንጂ የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት በሃገሪቷ ስፖርት ውስጥ ስለመኖሩ ማሳያና ማንቂያ በመሆኑ ብዙ መስራት እንደሚገባ የጽህፈት ቤቱ እምነት ነው።
ተጠቅመው እንደተገኙ የተረጋገጠባቸው አትሌቶች ቁጥር መበራከት ሃገሪቷን ወደ ስጋት የሚከታት እንዳልሆነም አቶ መኮንን ማረጋገጫቸውን ይሰጣሉ። የዓለም አቀፎቹ ተቋማት የመጀመሪያ ትኩረት በቁጥሩ መብዛት ሳይሆን ሃገራት በጉዳዩ ላይ ባላቸው አቋም ነው። ይህም ማለት በህገወጡ ቁጥር ሳይሆን ህገወጡን ለመያዝ ያለው ዝግጁነት ምን ይመስላል በሚለው የሚመዘኑ በመሆኑ፤ የቁጥሩ ነገር አሳሳቢ የሚሆነው በሁለተኛ መሆኑን ነው።
ከምርመራው ሂደት ማወቅ እንደተቻለው ንጥረነገሩን እንደተጠቀሙ ከተረጋገጠባቸው አምስት አትሌቶች መካከል አራቱ በፌዴሬሽኑ ጭምር ስለአትሌትነታቸው ዕውቅና ያልተሰጣቸው ናቸው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በተመሳሳይ በግላቸው የሚሰለጥኑና ውድድሮች ላይም የሚሳተፉ አትሌቶች ቁጥር በውል አይታወቅም። የእነዚህ አትሌቶች ተጋላጭነት በዚህ ልክ የሚጎላ ከሆነ ጽህፈት ቤቱ በምን ዓይነት መንገድ የክትትልና ቁጥጥር ስራውን ተደራሽ ሊያደርግ ይችላል ለሚለውም ዳይሬክተሩ ምላሽ አላቸው።
ጽህፈት ቤቱ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ጋር ባደረገው ግንኙነት በተለያዩ ሃገራት የሚካሄዱ ውድደሮችን ለመለየት እየተሞከረ ነው። ከልየታው በኃላ ከአዘጋጆቹ በመነጋገር በውድድሩ ለመሳተፍ የተመዘገቡ አትሌቶችን ለጽህፈት ቤቱ እንዲያሳውቁ በማድረግ የክትትልና የቁጥጥር ስራውን ለማከናወን ታቅዷል። ሌላው በቻይና በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ከፌዴሬሽኑ ጋር በመስራት እውቅና አግኝተው በህጋዊ መንገድ እንዲጓዙና ቁጥጥሩንም ጠንካራ ማድረግ ነው። በዚህ ረገድ የሚያጋጥመው ተግዳሮት አትሌቶች በቱሪስት ቪዛ መግባታቸው ነው።
በዓለም አቀፉ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ተጋላጭነቱ የሚሰፋው በአትሌቲክስ ስፖርት ነው። ከዚህ ባሻገር ሃገሪቷ የምትታወቀውም በዚህ ስፖርት በመሆኑ እንጂ፤ በፓራሊምፒክ፣ በብስክሌትና በቦክስ ስፖርቶችም ናሙናዎች እየተወሰዱ መሆኑን አቶ መኮንን ይገልጻሉ። በእግር ኳስ ስፖርት ላይም እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። እስካሁን ከተወሰዱ ናሙናዎች የተለየ ነገር አልተገኘም፤ የሚኖር ከሆነ ግን ተመሳሳይ እርምጃ የሚወሰድ ነው የሚሆነው። እኤአ ከ2012ቱ የለንደን ኦሊምፒክ ጀምሮ በተመረጡ ውድድሮች እንዲሁም አብዛኛውን ናሙና ከውድድር ውጪ ስፖርተኞቹን በድንገት ባሉበት ቦታዎች ላይ በመገኘት ናሙና የሚወሰድ መሆኑንም ጨምረው ይገልጻሉ።
በቀጣይም ማስተማሩ የሚጠናከር ሲሆን፤ ከዚህ በተጓዳኝ የምርመራና የቁጥጥር ስራዎችንም እስካሁን ያልተኬደባቸው ስፍራዎችም ጭምር በመገኘት አድማሱን ማስፋት የጽህፈት ቤቱ እቅድ ነው። የውጪ ሃገራት ውድድሮች ተሳታፊነትም አንድ አቅጣጫ እንዲይዝ፣ ማናጀሮችና የተለያዩ ተቋማት ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እንዲጠብቅ፣ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከአትሌቶች ጋር የሚሰሩ ሰዎችም ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ካልሆነ ግን አስተዳደራዊ ቅጣትም ብቻ ሳይሆን በወንጀል ህጉ እንዲጠየቁ ማድረግ እንዲሁም ቅመሞቹን እንደወሰዱ የተረጋገጠባቸው አትሌቶች ላይ ያለ ምህረት ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ ትኩረት የሚሰጥባቸው ስራዎች ናቸው።
ይህንን ማድረግ አጥፍተው የተገኙ አትሌቶች ከጥፋታቸው እንዲታረሙ ሌሎች አትሌቶችም ትምህርት እንዲወስዱበት ያደርጋል። ጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎችን በመቅጠር በሙሉ አቅሙ ስራ መጀመሩ በቀጥታ ወደ ስራ ለመግባት ከማስቻሉም በላይ እቅዶቹን ወደተግባር ለመለወጥ እንደሚያስችልም ዳይሬክተሩ ያረጋግጣሉ፡፡

ብርሃን ፈይሳ

Published in ስፖርት

የአንድ አገር ኢኮኖሚ እየጎለበተ በሄደ ቁጥር እድገቱን የሚመጥንና ያንኑ ተሸክሞ ወደ ተሻለ ደረጃ የማስጓዝ ኃላፊነት የሚጣልበት ብቁ የሰው ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ከማድረግ አኳያ ደግሞ የትምህርት ተቋማት ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡ በተለይ ገበያው የሚፈልገውን ባለሙያ ከማፍራት አኳያ ጉልህ ሚና እንዳለው ታምኖና በዘርፉ ውጤታማ ከሆኑ አገራት ልምድ ተቀስሞ የተተገበረው የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ የማይተካ ሚና አለው፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ያለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? በሚለው ጥቅልና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በሬቻ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ለንባብ በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና አስፈላጊነት
የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከማፋጠንና ቀጣይነቱንም ከማረጋገጥ አኳያ የተማረ የሰው ኃይል ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ይህ የሰው ኃይል ደግሞ የተማረ ብቻ ሳይሆን የሙያ ክህሎት ያለውና ሙያውም በኢኮኖሚው ውስጥ የድርሻውን እንዲያበረክት የሚያደርገው መሆን አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዋና ዓላማ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ማቅረብ ሲሆን፤ በተለይ በመለስተኛና በመካከለኛ ደረጃ ያሉ ብቁ ባለሙያዎችን በማውጣት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የማቅረብ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማረጋገጥ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት መፈልፈያ የመሆን አቅጣጫ ተይዞም እየተተገበረ ያለ ነው፡፡
የተከናወኑ ተግባራትና ውጤታማነታቸው
የኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና በዘመናዊ መንገድ ከተጀመረ የተወሰኑ ዓመታት ያለፉት ቢሆን፤ በተደራጀ አግባብ ውጤት ተኮር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ስትራቴጂው ወጥቶ ወደሥራ ከተገባ ግን ገና አስር ዓመታት ብቻ እንደተቆጠሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ተግባር የተገባውም በዓለም ላይ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ አገሮችን ተሞክሮ ወስዶ ነው፡፡ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፤ አበረታች ውጤቶችም ተመዝ ግበዋል፡፡
በዚህም ከቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ፖሊሲ አንጻር አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ይሄን መሰረት አድርጎ በተሠሩ ሥራዎችም በተወሰኑ ከተሞች ላይ ብቻ ሲሰጥ የነበረው የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአገር ደረጃ የግል ተቋማትን ሳይጨምር በመንግሥት ብቻ ከ500 በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡ ሁለተኛውም በገበያው ውስጥ የሚፈለጉ ከ600 በላይ ሙያዎች የሙያ ደረጃ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ በ300 ያህሉ ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በአገር ደረጃ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና አመራሮችንና መምህራንን ለብቻ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ፣ የሚያሠለጥን ተቋም ተደራጅቶ ወደሥራ ገብቷል፡፡ እነዚህ አበረታች ውጤቶች ናቸው፡፡
ተቋሙ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስፈላጊ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማቅረብ የቻለ ሲሆን፤ አሁን ላይ በመደበኛ ሥልጠና ብቻ ከ300ሺ በላይ ሠልጣኞችን፤ በአጫጭር ሥልጠናዎችም አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ባለሙያዎችን በየዓመቱ በሥልጠና ሥርዓቱ ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህም በተለይ በአጫጭር ሥልጠና የሚያልፉ ዜጎች ወደ 80 በመቶ የሚሆኑት ተመርቀው ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደሥራ የሚሰማሩበት ሁኔታ አለ፡፡ በመደበኛ ሥልጠና የሚወጡትም የመቀጠር ምጣኔያቸው ወደ 70 በመቶ ነው፡፡ ይህም ሥራ አጥነትን ከመቀነስ፤ እንዲሁም የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት መፈልፈያ ከመሆን አንጻር የቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ረዥም ርቀት መሄዱን የሚሳይ ነው፡፡
ዘርፉ የቴክኖሎጂ መፍለቂያ ከመሆን አንጻር አሁን ላይ እየተከናወነ ያለው ቴክኖሎጂን መቅዳት ነው፡፡ በዚህም ባለፉት ዓመታት አቅም እየተገነባ ነው፡፡ ሆኖም የህዳሴው ጉዞ የቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታው እንደሚያሳየው እስከ 2017 ድረስ ቴክኖሎጂ የመቅዳቱን ሥራ ማጠናቀቅ ይገባል፡፡ ይሄን ከማድረግ አኳያ ሁሉም በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ ያሉ መምህራን ለደረጃ እድገታቸውም ይሁን ለሥራቸው በሚስተምሩበት ጊዜ ቴክኖሎጂን ሰርቶ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት፣ ለአርሶ አደሩና ለተለያዩ ዘርፎች እንዲያሸጋግሩ እየተሠራ ነው፡፡ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ቴክኖሎጂዎች ወደ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እየተሸጋገሩ በመሆኑም የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ምርታማነት ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ማሠልጠን ብቻ ሳይሆን ከሥራ ጋር የተሳሰሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በመስጠት ይደግፋል፡፡ እነዚህ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ አካላት ተደራጅተው ወደሥራ ከተሰማሩ በኋላ የኢንተርፕርነር ሺፕ፣ የእውቀት፣ የቴክኖሎጂና መሰል ድጋፎችን ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም በሁሉም የአገሪቱ ቦታዎች በሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እነዚህን መሰረት ያደረገ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ አሁን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው እየሠሩ ከመሆናቸው አንጻር የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የቴክኖሎጂ መፍለቂያ በመሆን በዋናነት አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን ከመደገፍ አንጻር እያከናወኑት ያለው ተግባር ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ለረዥም ዓመታት እጅጉን የተናቀ ዘርፍ ሆኖ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ በተሠሩ የአመለካከት ለውጥ የማምጣት ሥራዎች መሻሻሎች አሳይተዋል፡፡ የእጅ ሙያን አክብሮ መሥራት እየተለመደ፤ ገቢ የሚያስገኝ እንደመሆኑም እየተወደደና እየተከበረም መጥቷል፡፡ በዚህም በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ወደዘርፉ እንዲገቡ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡
የነበሩ ክፍተቶችና ፈታኝ ሁኔታዎች
በዚህ መልኩ የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱ በህብረተሰቡም ሆነ በተማሪዎች ዘንድ ለቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የነበረውና አሁንም ድረስ ያለው አመለካከት ነው፡፡ ተማሪው ሥልጠናውን የመጀመሪያ ምርጫው ሳይሆን የመጨረሻ አማራጭ አድርጎ ማየት፤ ሥልጠና ከገቡ በኋላም ተነሳሽ ሆኖ አለመማር ሂደቱን ፈታኝ አድርጎታል፡፡ በአንዳንድ ተቋማት ላይ የሚከፈቱ የሥልጠና መስኮች ካለው የገበያ ፍላጎት ጋር የሚሄድ አለመሆንም ሠልጣኞች ከተመረቁ በኋላ ቶሎ ወደሥራ እንዳይገቡ የሚያደርግ ፈታኝ ሁኔታ ነው፡፡
ሌላውና ትልቁ ጉዳይ ደግሞ ተቋማቱን ማስፋፋት የተቻለውን ያክል የትምህርት ጥራት አለመኖሩ ነው፡፡ ተቋማቱን አሠልጥነው ከጨረሱ በኋላ ባለሙያዎች ተመዝነውና ለገበያው ብቁ መሆን አለመሆናቸው ተረጋግጦ ነው ወደ ሥራ የሚቀላቀሉት፡፡ ከዚህ አንጻር መሻሻሎች ቢኖሩም፤ ሁሉም በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ውስጥ የሚያልፉ ሠልጣኞችን ብቁ አድርጎ ወደ ኢንዱስትሪው ከመቀላቀል አኳያ ክፍተቶች አሉ፡፡
ለጥራት ችግር ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር የሚገናኝ ቢሆንም፤ ቀዳሚው የኢንዱስትሪው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን ነው፡፡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ትልቅ ወጪ የሚጠይቅ ሥልጠና እንደመሆኑ በተቋሙ ውስጥ በሚሰጥ ሥልጠና ብቻ ችግሩን መወጣት ስለማይቻል ሠልጣኞች ኢንዱስትሪ ውስጥ ሄደው መሠልጠን፤ ምዘናም መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ሂደት ላይ ግን ኢንዱስትሪዎች ተባባሪና ዝግጁ አይደሉም፡፡
ከአሠልጣኞች ብቃት ጋር የተያያዙ የጥራት ችግሮችም አሉ፡፡ አብዛኞቹ ቴክኒክና ሙያ ደረጃ ያሉ አሠልጣኞች ቀጥታ ከተቋማት የመጡ እንደመሆናቸው የተግባር ክህሎታቸው ላይ እጥረት አለ፡፡ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ውድ የሚባል ዘርፍ እንደመሆኑም ለሥልጠና ሂደት የሚውሉ ግብዓቶች አቅርቦት ችግርም ለጥራት መጓደል እንደ ምክንያት የሚነሳ ነው፡፡
ዘርፉ አገራዊ ድርሻውን እንዲያበረክት ለማስቻል
ዘርፉ የሚጠበቅበትን ድርሻ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፤ በዋናነት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ወይም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ እንደ አገር 90 በመቶ የሚሆነው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተመራቂ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሥራ ጋር ለማስተሳሰር እንዲቻል ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ይህ በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ ዴሎቨሮሎጂ በሚባለው እቅድ የተያዘ ነው፡፡ ይህ ተግባር ግን ዝም ብሎ የሚመጣ ሳይሆን፤ በርካታ ሥራዎችን ማከናወንን የሚጠይቅ ነው፡፡
ከሚሠሩ ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ፣ የገበያ ፍላጎት ጥናትን መሰረት አድርጎ ማሠልጠን ሲሆን፤ ማንኛውም ሙያ ከመከፈቱ በፊት የገበያ ጥናት ተደርጎና ፍላጎቱ ላይ ተመስርቶ እንዲከናወን እየተሠራ ነው፡፡ ሁለተኛው፣ የሙያ ደረጃዎቹንና የሥርዓተ ትምህርቱን የማሻሻል ሥራ ሲሆን፤ ሶስተኛው፣ በአጫጭርም ሆነ በረዥም ጊዜ ሥልጠናዎች የመምህራንን አቅም መገንባት ነው፡፡ የአመራሩን አቅም መገንባት፣ ተቋማትን የማስፋፋት፣ ማሽነሪዎችን ማሟላትና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችም በመንግሥት ደረጃ በትኩረት የሚሠሩ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ በመንግሥት በጀት ብቻ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ አሁን እየተሠራበት ያለው ዋናው ጉዳይም ኢንዱስትሪው ለሥልጠናም ሆነ ለምዘና በሩን እንዲከፍትና ለቴክኒክና ሙያ ሥልጠናው የራሱን አስተዋጽዖ ማድረግ እንዲችል የኢንዱስትሪ ንቅናቄ መፍጠር ነው፡፡ ኢንዱስትሪውም ከቴክኒክና ሙያ የሚወጡ ሠልጣኞች ነገ እሱ ጋ ተቀጥረው የሚሠሩና ለምርታማነቱ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ተገንዝቦ ለጥራት መጠበቅ የድርሻውን እንዲያበረክት ያስፈልጋል፡፡
የአመለካከት ቀረጻና የሥነምግባር ግንባታ፣ የገበያ ትስስርን መፍጠር፣ እንዲሁም የኢንተርፕርነር ሽፕ ሥልጠናን ማስፋፋትም ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከአመለካከት ጀምሮ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ከማቃለል አኳያ የመገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ በየደረጃው ያለ አካል የድርሻውን ሊያበረክት ይገባል፡፡

Published in ማህበራዊ

መንግስት ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በተሳለጠ መልኩ ከማስኬድ ባለፈ፤ ከልማቱ ተጠቃሚ ከሆነው ህዝብ ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአገሪቱ የሚታዩ ክፍተቶች እንዳሉ የተለያዩ አካላት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ መንግስትም ይሄን ወስዶ ለችግሮች መፍትሄ ያመጣሉ ያላቸውን እርምጃዎችን እየወሰደ፣ ብሄራዊ መግባባት ያመጣሉ ያላቸውን ተግባራት በዕቅድ እየተመራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ እኛም ለዛሬ መንግስት ባለፉት 27 ዓመታት በሰራቸው ስራዎች፣ በአሁኑ ወቅት ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ እንዲሁም ቀጣይ ምን መደረግ ይኖርበታል? በሚል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፡፡

በቀደሙት ጊዜያት
መንግስት ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ያመጣቸው የልማት ውጤቶች አሉ፡፡ ለአንድ አገር ልማት ወሳኝ የሆኑት የመሰረተ ልማቶች በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆንም ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ህዝቡ ያነሳቸው የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መንግስት ያለመስማትና ዞሮ አለመመልከት ክፍተት እንደነበረበት በመንገድ ላይ ንግድ ሲያከናውን ያገኘነው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው ወጣት ግርማ ከበደ ይናገራል፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ፕሬዚደንት ወይዘሪት ቃልኪዳን ሽመልስ በበኩሏ እንደምትለው፤ መንግስት ባለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት ውስጥ ከአካል ጉዳተኞች አንፃር ቀድሞ ይነሱ የነበሩ በርካታ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ሰጥቷል፡፡ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ አገሪቱ ከዚህ ቀደም ገዢ የሆኑ አዋጆችና ህጎች አልነበሯትም፡፡ ነገር ግን ከ27 ዓመታት ወዲህ የተለያዩ አዋጆችና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግስታት የወጣ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነቶች (ኮንቬክሽን) እንዲፀድቅና የኢትዮጵያ ህገመንግስት አካል እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም በአገሪቱ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች ትልቅ እመርታን ያሳየ የለውጥ መነሻ ነጥብ ሆኗል፡፡
በስራ ስምሪት ዘርፉ በተመሳሳይ አዋጅ 568/2000 ይህን መሰረት አድርጎ የወጣ 624/2001 እንዲሁም 2008 ላይ ማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ መውጣቱ የእነዚህን አምራች የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመና ግቡን እየመታ እንደሆነም ወይዘሪት ቃልኪዳን ትናገራለች፡፡ አስፈፃሚ አካላት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካተው እንዲሰሩ አሰራሮች መዘርጋታቸውም ሌላው አበረታች ተግባር መሆኑን ትገልጻለች፡፡ በ27 ዓመታት ውስጥ ለውጥ ከታየባቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የአካል ጉዳተኞችን ለመጥቀስ ቢሞከርም ከዚህ ውጪ በርካታ የሚታዩ ስኬቶችን አገሪቱ እንደተቀዳጀች መዘንጋት የለበትም ባይ ናት፡፡ ለማሳያ ያክልም የሴቶች እኩልነት ጥያቄና ምላሹ ይገኝበታል፡፡
በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን እንዲሰጡን ካነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በአዲስ አበባ የሚኖሩት ወይዘሮ ኢትዮጵያ ሙሉጌታ፣ አንዷ ናቸው፡፡ እኚህ እናት 80 ዓመት አዛውንት በመሆናቸው የበርካታ ዓመታት የአገሪቱን ታሪክ የኋሊትም ሆነ የአሁን ቁመና እንደሚያውቁት ነው የነገሩን፡፡ ነገር ግን ንግግራቸውን የጀመሩልን ከ27 ዓመታት በፊት የነበረውን የደርግ ወታደራዊ መንግስት ስርዓት ከነበረበት ሁኔታ በመነሳት ነበር፡፡ ልጆችን የማሳደግ ጉዳይ ትንንቅ የተሞላበትና በርካታ እናቶችንም ለመሪር ሀዘን የዳረገ ወቅት እንደነበር አነሱልን፡፡
ወጣቶች ተምረው ለአገር ልማት ጉልበታቸውን እንዲያፈሱና አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ከማድረግ ይልቅ ያለፍላጎታቸው ግዳጅ እየተላኩ የረገፉበት ወቅት አስከፊው የደርግ ዘመን መሆኑን ወይዘሮ ኢትዮጵያ ያስታውሳሉ፡፡ በጡረታ የተገለሉትን አባት ጡረተኞች በሚል ተወስደው ዳግም ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ቤታቸውን እርግፍ አድርገው በወጡበት የቀሩ አባወራዎች እንዳሉም ያነሳሉ፡፡ በሌላ በኩል የእኩልነት ሚዛን መዛባቱን የሚያሳየው የባለፀጋ ልጆች በየቤታቸው ተሰግስገው የደሃው ልጅ በየደጃፉ ሲረግፍበት የነበረ የሰቆቃ ዘመን ነበር፡፡ በልጆቻቸው መዝመት የሚፈስ እንባቸው ያልደረቀ እናቶችም በግዳጅ ቀበሌ ውስጥ ስራ እንዲሰሩ የሚደረግበት አስከፊ ወቅት እንደነበርም ይናገራሉ፡፡
ባለፉት የመንግስት ስርዓቶች ማንም ቢሆን የመሰለውን ሃሳብም ሆነ ተቃውሞውን ማንሳት አይችልም፡፡ ነገር ግን አገሪቱ በጭንቀት ላይ በነበረችበት የመጨረሻዋ ሰዓት ግንቦት 20 ደርሶ ህዝቡን ከሰቆቃ ገላግሎታል፣ በማለት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡ የዛም ውጤት በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በዘመናዊነት ጎዳና ላይ እንድትረማመድ አድርጓታል፡፡ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተለያዩ ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡና አኗኗሩን ፈጣንና ቀልጣፋ ያደረጉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችም ተከናውነዋል ሲሉ የመጣው ለውጥ የቀድሞውን ችግር ለተመለከተ ፍፁም ደስታን የሚጭር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የአረጋውያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ በበኩላቸው፣ ከ27 ዓመታት በፊት የጭቁኖች ድልን የሚያበስር አገራዊ ህብረ ዜማ በየበሩ እንዳንኳኳ ያወሳሉ፡፡ ሶስት መንግስታትን እንዳዩ የሚገልፁት አቶ ጌታቸው ቀደም ባሉት የመንግስት ስርዓቶች ወቅት ህዝቡ ያሻውን ሃሳብ የማያራምድበት፣ የሰዎች ነፃነት የማይታሰብበት፣ መደራጀት ክልክል የነበረበት፣ ዴሞክራሲ ሊተገበር አይደለም ስሙም የማይታወቅበት ወቅቶች በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ህዝቦች ባደረጉት መራር ትግል ዜጎች መብታቸውን ያወቁበት፣ በተለያዩ መንገዶች አመለካከታቸውን ማንፀባረቅ የቻሉበት፣ የሰው ልጆች በዘርና በቋንቋ የነበራቸው ልዩነት ተሽሮ አንድነታቸው የተመሰረተበት ወቅት እንዲመጣ አስችለዋል፡፡
የአገሪቱ ህዝቦች ባደረጉት የለውጥ ፍላጎት እንቅስቃሴ አገሪቱ ወደ ልማት የገሰገሰችበት፣ ቀድሞ ለነበረው የልዩነት ጥያቄ መልስ ሰጥታ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ያክል ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በጋራ ብሔራዊ መግባባት የጀመረችበት፣ ከድህነት የምትላቀቅባቸው መንገዶች የተቀየሱበት ጊዜ እንዲመጣም አስችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት
መንግስት ኃላፊነት ላይ እንዲወጣ ያስቻለው መነሻ የህዝቦችን ጥያቄ ምላሽ መስጠት ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከህዝቡ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲቀርቡበት ነበር፡፡ ይህን መሰረት አድርጎም የህዝቡን ሃሳብ የማድመጥ ጅማሮዎች እንዳሉ ማሳያ የሆኑ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ወጣት ግርማ ከበደ ትዝብቱን ይገልፃል፡፡ የአገሪቱ ህዝብ ከሁሉ አስቀድሞ የሚያደምጠውን እንደሚፈልግና ይህም መረጋጋትን ለመፍጠር የመጀመሪው እርምጃም ይሆናል ነው ያለው፡፡ አድማጭ ሲያገኝ እንደሚተገበር ተስፋ ይኖረዋል፡፡
ተስፋ ካለም ሁሌም ቢሆን የተሻለ ሁኔታ እንደሚመጣ ዕምነት ስለሚፈጠር ለወደፊቱ በመረጋጋት ላይ ተመስርቶ ለውጦችን ለማምጣት ራሱንም ተሳታፊ እንዲያደርግ ያስችለዋል፡፡ መንግስት ለሚሰራቸው እያንዳንዱ ተግባራት የህዝብ ተቀባይነት ወሳኝ በመሆኑም ከህዝብ ጋር መደማመጥ ከተቻለ ለስራዎቹ ስኬት ትልቁን እርምጃ የሚያራምድ ጅማሮ ያደርገዋል በሚል በአሁኑ ወቅት እየተሰራ ያለው መልካም ጅማሮ ለቀጣይ ስኬት እርሾ እንደሚሆን ወጣቱ ያመላክታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ለውጦች ከመጣባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው የሴቶች ጉዳይ ሲሆን በልማቱ የነቃ ተሳትፏቸው እንዲረጋገጥም እየተሰራ መሆኑ ይታያል፡፡ ቀድሞ የነበረው ለእኩል ስራ ተመሳሳይ ክፍያ የማያገኙበት ዘመን ተሽሮ ይህና ሌሎች መብቶቻቸው የተከበረበትም ነው፡፡ ምንም እንኳ ከሴቶች ጋር ተያይዞ አሁንም መሻገር ያልተቻሉ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም የመጡ ለውጦችም እንዳሉ አይካድም፡፡ ይህንንም በቅርበት የሚከታተል ተቋም ከሚኒስቴር እስከ ወረዳ ደረጃ መቋቋምም መቻሉም ሴቶች በልማቱ ላይ ያላቸው ተሳትፎ የማይተካ ሚና እንዳለው እንደታመነበትና ትኩረት እንደተሰጠው ያመላክታል፣ እንደ ፕሬዚደንቷ ገለፃ፡፡
በአገሪቱ በርካታ ለውጦች እንዳሉ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ቢናገሩም፣ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ክፍተቶች መኖራቸውንም አልደበቁም፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት ዜጎችን እያማረረ ያለው የሸቀጦች ዋጋ ውድነት ጋር ተያይዞ መንግስት በትኩረት ሊመለከታቸው የሚገቡ ቀሪ የቤት ስራዎች አሉ፡፡ ለችግሩ ቀዳሚ መነሻ የሆነው አርሶ አደሮች መሬታቸውን እየጣሉ ከገጠር ወደ ከተማ የሚያደርጉት ፍልሰት ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን አገሪቱ በከተሞች መስፋፋት ሳቢያ የእርሻ መሬቶች እየተመናመነ ይገኛል፡፡ ይህም በአንድ በኩል የአገሪቱን ኢኮኖሚ በመጉዳት በሌላ በኩል ልመና ተበራክቶ የከተሞችን ገፅታ በማበላሸት አሉታዊ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ባለሀብቶች የአገሪቱን ዕድገት ማረጋገጥ በሚችሉበት መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ያስቻለ ልማታዊ አሰራር የመጣው ባለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት መሆኑን የሚያስረዱት ደግሞ አቶ ጌታቸው ናቸው፡፡ የከተሞች መስፋፋትና ማደግ የተረጋገጠበት በዚህ ውስጥም የህዝቦች ተጠቃሚነት መረጋገጥ እንደቻለ ይገልፃሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ አገራዊ ዕድገትን ሊያመጡ የሚችሉ ስራዎች መሰራታቸውንና በዚህም ቀድሞ የነበረው የእኩልነትና መሰል ጥያቄዎች በልማት ጥያቄ እንዲቀየሩ ሆነዋል፡፡
አገሪቱን ለትውልድ በአደራ ተቀብለው ያቆዩና ያሳለፉ አረጋውያንም መብታቸው እንዲከበር መንግስት ያለማንም ጎትጓችነት ለተጠቃሚነታቸው እየሰራ ይገኛል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አረጋውያን የመደራጀት መብታቸው ተከብሮ እየተወያዩና ለችግሮች በጋራ መፍትሄ እያፈላለጉም ነው፡፡ በህገመንግስቱ በተቀመጠው መሰረት አረጋውያን አንዱ የህብረተሰብ ክፍል በመሆናቸው አቅም በፈቀደው ልክ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንክብካቤ እንዲቀርብላቸውም ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡
ከሁለት አስርት ዓመታት አስቀድሞ የተደረገው ትግል ለአገሪቱ ነፃነት ካበረከታቸው ገፀበረከቶች መካከል አንዱን መዝዞ ቢታይ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት መረጋገጥ ተጠቃሽ ውጤት እንደሆነ አቶ ጌታቸው ያስረዳሉ፡፡ የነበረውን የመደራጀትም ሆነ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በማጎናፀፍ የዴሞክራሲ ስርዓቱ የሰፋበት ወቅትም እንደሆነ በአገሪቱ ያሉ ተግባራት አጉሊ ማሳያ ይሆናሉ፡፡ ለአገር ዕድገት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የተማረ የሰው ኃይል በመሆኑ መንግስት ለዕድገት ካለው ቁርጠኛ አቋም የተነሳ የትምህርት ዘርፉን በቁልፍ ዘርፍነት በመምራት ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡
ትምህርት ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝነቱ የማይካድ በመሆኑም ቀድሞ ከሁለት ያልዘለሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንኳ በአሁኑ ወቅት 53 ደርሰዋል፡፡ ይህም በየአቅራቢያው ተከፍቶ ቀለም ያልጠገቡ ዜጎች እንዳይኖሩ ከማስቻሉ በተረፈ የበርካቶችን ጭንቅላት በማልማት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ዘርፎች ስኬቶችን ማምጣት ተችሏል፡፡ ነገር ግን የትምህርት ተደራሽነቱ በሰፋው ልክ ስራ ፈጠራ ላይ የሚታዩም ክፍተቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡
በአገር ውስጥ ያሉ እንዲሁም ከአገር ውጪ የሚገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ ዕድገት ተኮር ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር እንዲያድግ እየተደረገ የሚገኘው ተግባርም የትየለሌ መሆኑን ፕሬዚደንቱ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በሰላም ያላት ምቹ ሁኔታ፣ ለመልማት ያላት ፍላጎትና የመጡ ለውጦች በርካቶችን የመሳቡ ሚስጥር ያደርገዋል፡፡
ምን ይጠበቃል?
መንግስት እያደረገ ያለው ህዝቦችን የማድመጥና አገሪቱን ወደነበረችበት ሰላማዊ ሁኔታ የመመለስ ተግባር ቀዳሚ ማድረጉ የተሻለ ቢሆንም የመተግበር ሂደቱን ግን አሁንም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ወጣት ግርማ ያስገነዝባል፡፡ በተመሳሳይ ከምንም በላይ ለዜጋው ትኩረትን መስጠት ይኖርበታል፡፡ ለዜጋው ክብር የሰጠ መንግስት ከህዝቡ ጋር መግባባት ፈጥሮ ለመምራትም ያስችለዋል፡፡ ህዝቡ ደግሞ በሌላ በኩል መንግስት ያለውን ተነሳሽነት በመመልከት ከጎኑ ሊቆም ይገባል፡፡
መንግስት ለማድመጥ ዝግጁ መሆኑን እየገለፀና እያሳየ ቅሬታን በሁከት መግለፅና የአገሪቱን ዕድገት የኋሊት ማሽከርከር ተገቢነት የጎደለውና ሊታረም የሚገባ ጉዳይ ነው በማለት ባለፉት ጥቂት ጊዜያት የተፈፀሙት ጥፋቶች በመነጋገር ሊፈቱ የሚችሉ ሆነው ውድመትን ያደረሱ ችግሮች መሆናቸውንም በሀዘን ያስታውሳል፡፡ አመፃና ረብሽ በኢኮኖሚ ገና ላልዳበረችው ኢትዮጵያ ይቅርና ለሌሎች አደጉ ለተባሉ አገራትም ዕድገታቸውን ታሪክ አድርጎ የሚያስቀር ጥቁር ጠባሳ ነውና ህዝቡ ከዚህ ሊማር ይገባል፡፡ መሪ ብቻውን ለመምራትና ውጤታማ ለመሆን እንደሚያዳግተው በመግለፅም መንግስት ይህን አውቆ የህዝቡን ተሳትፎ እያረጋገጠ መሄድ እንዳለበት ያሳስባል፡፡
ያለፉት 27 ዓመታት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያቆጠቆጠባቸው ዓመታት ናቸው የምትለው ወይዘሪት ቃልኪዳን፤ ዴሞክራሲ እንዴት ይመጣል? የትኛው ተሞክሮስ መወሰድ ይኖርበታል? የሚለው አጠያያቂ መሆኑን ትገልፃለች፡፡ ዴሞክራሲውን በተሻለ ደረጃ ለማስፋትና አገሪቱ እንድትበለፅግ ሰላም የማይተካ ሚና አለው፡፡ በመሆኑም ሰላም እንዲመጣ በሚደረገው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ውስጥ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን መሰራት እንዳለበት ትጠቁማለች፡፡
መንግስት የህዝብ ኃላፊነት ተቀብሎ እየመራ በመሆኑ የህዝቡን ትርታ ማድመጥ ብሎም ፍላጎትና ምርጫውንም ሊያከብር ይገባል የምትለው ወይዘሪት ቃልኪዳን ቀጣይ ከህዝቡ ጋር አንድነት በመፍጠር ረገድ የተጀመሩት ተግባራት ሳይቀዛቀዙ መቀጠል እንደሚገባቸው ትናገራለች፡፡ አገር እንደ አገር የምትቆጠረው ህዝቦቿ ሲኖሩ፣ ደህንነታቸው ሲጠበቅ እንዲሁም በልተው ሲጠግቡ ነው፡፡ በመሆኑም መጥገብ ደረጃ ባይደረስም መጉረስ መቻልም አንድ እርምጃ በመሆኑ ዜጎች የተለያዩ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩና በመልካም አስተዳደር ችግርነት የተለየው የስራ አጦች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረግም ትልቁ የቤት ስራ ነው፡፡
አገሪቱ ከሚሊኒየም የልማት ግቦች ቀጥሎ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውን የዘላቂ ልማት ግቦችን እንደተቀበለች ወይዘሪት ቃልኪዳን ታወሳለች፡፡ በውስጡ ከተዘረዘሩት ግቦች መካከል የመጀመሪያው ረሃብን መቀነስ ነው፡፡ እዚህ ላይም በትኩረት በመስራት የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ይገባል፡፡ ይህም ማረጋገጥ ሲቻል ህዝቡ እርካታው ተረጋግጦ ለጋራ አገራዊ አጀንዳዎች እንዲሰለፍ ያስችለዋል፡፡ የልማትን ጉዳይ የራሱ በማድረግ ሊንቀሳቀስበት የሚያስችለውን ስሜትም ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም ይህ አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ጥረት መንግስት ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ በመገንዘብ ህዝቡ በስፋት ሊያሳትፍ ይገባል፡፡ ይህ ከሆነም ሰላምን ማስፈን ብሎም ይህን ተከትሎ ዕድገትና ብልፅግና ማረጋገጥ ይቻላል በማለት ህዝቡ ከመንግስት ጎን መቆም እንደሚገባው ታስገነስባለች፡፡
እንደ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ገለፃ፤ አገራችን ሰፊ ግብርና ያለበት አገር ቢሆንም አትክትልና ፍራፍሬ ማርና ወተትን በመሳሰሉ የአገር ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ማሻቀብ በራሱ ምን ያክል ችግር እንዳለ ያመላክታል፡፡ በመሆኑም መንግስት አርሶ አደሮች ባሉበት ሆነው እንዲሰሩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይኖርበታል፡፡
“በአሁኑ ወቅት ከከተሞች አልፎ በየክልሉ የመሰረተ ልማት አቅርቦቱ አድጓል፡፡ ነገር ግን ሰላሙ በትግል ላይ ነው፡፡ ህዝቡ ለዘመናት የቆየ ጥያቄን አዝሎ የመጣ በመሆኑም ህዝቡን በአቅም መምራት የሚችል ከስርቆት የፀዳ መሪን ይፈልጋል” በማለት ወይዘሮ ኢትዮጵያ ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ በመሆኑም መንግስት በየደረጃው የመስራትና የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችሉ የስራ ኃላፊዎችን ማስቀመጥ ላይ ማተኮር ይገባዋል ይላሉ፡፡ አክለውም በተመሳሳይ ዜጎች በአቅማቸውና በትምህርት ደረጃቸው የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው በማድረግ በዝምድናና ባልተገባ ትስስር የማይገባቸው ስራ ላይ እንዳይቀመጡ መቆጣጠር ይገባል፤ ይህም በአሁኑ ወቅት የሚነሳውን ለህዝብ እንግልት መንስዔ የሆኑ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በሰፊው ያቃልላል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
አቶ ጌታቸው በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት እየመጡ ያሉ ለውጦች እንዲቀጥሉ ችግሮችን ወደ መንግስት ብቻ መግፋት አይገባም ይላሉ፡፡ አገሪቱ ባለፉት ዓመታት እየመጡ ያሉ ለውጦች ቢኖሩም በስራዎች ላይ የሚስተዋሉም ክፍተቶች አሉ፡፡ በዋናነት እዚህ ላይ የሚነሳው ደግሞ ከግንዛቤ ማነስ አልያም አመለካከት ክፍተት ለሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ መንግስትን ተጠያቂ ማድረጉ ነው፡፡ ሰላም ለአንድ አገር ወሳኝና ከራስ የሚጀምር ለራስ ጥቅም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ቢኖርበትም ለዕድገትም ሆነ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ የሆነው ሰላም ዋነኛ ባለቤት ግን ህዝቡ ነው፡፡
መንግስት ፖሊሲ አውጪ ስትራቴጂ የሚቀይስ መመሪያ ደንቦችን የሚያወጣ አካል ነው፡፡ የህግ ማዕቀፎቹ ተግባር ላይ ውለው ውጤት እንዲያመጡ እያንዳንዱ ዜጋ ሰላምን ለማምጣት መጣር አለበት፡፡ ህዝቡ የሚያነሳቸው የመልማት ፍላጎት ጥያቄዎችም ትክክለኛ ምላሽን ማግኘት የሚቻላቸው ሰላም ሲኖር መሆኑ መታወቅ እንደሚኖርበት ፕሬዚደንቱ ያስገነዝባሉ፡፡ ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባትም ሆነ ከግለሰብ ዕቅድና ኑሮ እስከ አገር የተያዘውን ግብ ለመምታት አዳጋች ይሆናል፡፡ በጉዳዩ ላይ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀስበት የስራ አጥነት ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተውና ሁሉም ዜጋ ተቀጣሪ መሆን አለበት የሚለው አመለካከት ሊቀየር ይገባል፡፡
ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትልቁ ድርሻ የመንግስት ቢሆንም ዜጎች ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ግን የባለሃብቱና የእያንዳንዱ ዜጋ ከአመለካከት እስከ ተግባር ያለው ንቃተ ህሊና ነው፡፡ በተመሳሳይ መንግስትም የተለያዩ አምራች ተቋማት መስፋፋት የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሽግግር ከመሆኑ በተጨማሪ በውስጣቸው የሚፈጥሩት የስራ ዕድል የማይተካ ሚና እንዳለው ተገንዝቦ በትኩረት መስራት ይገባዋል፡፡ አቶ ጌታቸው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን የአገር ተረካቢው ይህ ትኩስ ኃይል በመሆኑ በቅርበት ሊሰራና ሊያሳትፋቸውም ይገባል ይላሉ፡፡
በተለይ በወጣቱ ኃይል የሚነሳው ስራ አጥነት ጥያቄም ሆነ ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄ መሰረት ያደረገው ሰላም ላይ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አቶ ጌታቸው ያብራራሉ፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ ይህንን ተረድቶ ችግሮችን በመነጋገርና የጋራ መፍትሄ በማበጀት የመፍታት ባህሉን ሊያዳብር እንደሚገባም መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡
ማጠቃለያ
መንግስት ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸው በርካታ ተግባራት በተለያዩ መስኮች ለውጦች ማምጣታቸውን ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ገልፀውልናል፡፡ ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ህዝቡ የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በማንሳት ምላሽ እንዲሰጠው ሲሞግት መስተዋሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ጥያቄያቸውን ልማትን በማውደም ያቀረቡ አካላት እንዳሉም ታይቷል፡፡ መንግስትም የችግሮቹ መነሻ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የራሱ እንደሆነ አምኖ የለውጥ እርምጃዎችን ጀምሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግስት የኃላፊነት ሽግሽግና የተለያዩ አገራዊ መግባባት ይፈጥራሉ ያላቸውን እርምጃዎች እየወሰደ ይገኛል፡፡ ለህዝቦች ጥያቄም ምላሽ እንደሚሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ሃሳባቸውን ያካፈሉን የህብረተሰብ ክፍሎችም መንግስት በገባው ቃል መሰረት ጥያቄዎቹን በተግባር ሊመልስ እንደሚገባና የአገሪቱን ቀጣይ ዕድገት ማረጋገጥ የሚስችሉ ስራዎችን እንዲያከ ናውንም አሳስበዋል፡፡ በተለይ የጀመራቸውን ዘርፈብዙ የለውጥ ስራዎች ከዳር ለማድረስ በስራ አጥነት፣ በመልካም አስተዳደር እጦትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ ትኩረት በመስጠት የህዝቡን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ መስራት ይጠበቅበታል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ፖለቲካ

ኢትዮጵያ ዕምቅ ሰብዓዊና ተፈጥሮዓዊ ሀብት ባለቤት ብትሆንም፣ ያለፉት ሥርዓቶች ይከተሏቸው የነበሩ የተዛቡ የልማት ፖሊሲዎችና ሌሎች መዋቅራዊ ችግሮች ምክንያት የግብርናው ዘርፍ ሌሎቹን ዘርፎች ይዞ መውጣት አልቻለም፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በፍጥነት ማራመድና አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ብሎም አጠቃላይ ሕዝቡን ከድኅነት አላቆ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልበት እድል አልተፈጠረም ነበር፡፡ ሆኖም የግብርናው ዘርፍ በሁሉም ሥርዓቶች የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንትና የ85 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ መተዳደሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በመሆኑም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው ደረጃ ለማሳደግና ህዝቡን ከድህነት ለማውጣት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት መስጠት ደግሞ በዚያውኑ ያህል ግድ የሚል ነው፡፡ በዚህም መሰረት መንግስት የግብርናና ሌሎች የምርምር ተቋማት ቴክኖሎጂን ለምርምር ግብአትነት ማዋል ከጀመረ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል። የተሻሻሉ በሽታንና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ አዝርዕቶች በላቦራቶሪ እየተመረቱ ለአርሶ አደሮች ቀርበው ምርታማነት እንዲጨምር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል።
አርሶ አደሩ ገበያን ታሳቢ አድርጎ እንዲያመርት፣ አነስተኛ መስኖዎችን በማስፋፋት የተሻሻሉ ዝርያዎችንና ግብዓቶችን በመጠቀም ምርታማነቱን እንዲያሳድግ፣ በገበያ ላይ ያለውን ተወዳዳሪነት እንዲጨምር፣ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን የመጠቀም ልምዱን እንዲያዳብርና የምርት ብክነቱን እንዲቀንስ በማድረግ ዘርፉ በየዓመቱ የስምንት በመቶ አማካይ ዕድገት እንዲያስመዘግብም ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ቢሆንም፣ ዕቅዱን ለማሳካት የተለያዩ ችግሮች ማነቆ ሆነዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ እንደ ድርቅና ጎርፍ ያሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የድኅረ ምርት ብክነት በምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው የግብርና ምርትም ከማሳ ጀምሮ ባሉ ሒደቶች ይባክናል፡፡
በኢትዮጵያ የግብርና ምርምርና አዳዲስ የምርት ፈጠራ ሂደቶች ከቅርብ አመታት ወዲህ ለውጥ እያመጡ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተለይ ለአርሶ አደሩ አዳዲስ የአመራረት ዘይቤዎችንና ምርቶችን እንዲለማመድና እንዲጠቀም በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ የግብርና ምርቶች ከአገር አልፈው የውጭ ምንዛሬ እንዲያመጡ ለማድረግ የግብርናው ዘርፍ ዘመናዊነትን የተከተለና እሴት ተጨምሮ የሚሰራ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡
ግብርና ለአገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭና የአገሪቱን ዜጎች ከድኅነትና ከኋላቀርነት በማላቀቅ ወደ ተሻለ የኑሮና የብልፅግና ጎዳና እንዲያመሩ የሚያደርግ ዓብይ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ዘርፍ የተጣለበትን አገራዊ ድርሻ ይዞ እንዲቀጥልም መንግሥት ዕምቅ አቅሞቻችንን በስፋትና በላቀ ደረጃ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት እያደረገም ይገኛል፡፡
በየትኛውም የግብርና ልማት ዘርፍ የሚያከናውናቸው ተግባራት ዋነኛ ግብ የሰብልን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ዘላቂነትና ቀጣይነት ያለው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪና ለውጭ ገበያ ጥራት ያለው ምርት በሚፈለገው መጠንና ዓይነት ማምረት የሚቻለው ለዚህ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ሲቻል እንደሆነ እውን ነው፡፡
በዚህም በዋና ዋና ሰብሎች (ብርዕ አገዳና ጥራጥሬ ሰብሎች) በ1983 ዓ.ም. ተገኝቶ የነበረው ምርት መጠን 52 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን፤ ይህ የምርት መጠን የግብርና ገጠር ልማት ፖሊሲው ተነድፎ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በ1992 ዓ.ም. 88ነጥብ9 ሚሊዮን ኩንታል ደርሶ ነበር፡፡ ፖሊሲው ተነድፎ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ በ2004 ዓ.ም. የምርት መጠኑ 231 ሚሊዮን ኩንታል መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ይህ ከላይ የተገለጸው ውጤት የሚያሳየን ግብርና አንድን አገር የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር ለተለያዩ ምርቶች ግብዓት የሚሆን ጥሬ ዕቃ ለማቅረብ እንዲሁም የግብርና ምርት ውጤቶችን ለፋብሪካዎች በማቅረብ ለአገር ፍጆታም ሆነ ለውጭ አገር የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት የአገርን ኢኮኖሚ በፍጥነት ማሳደግ እንደሚቻልና እንደተቻለም ነው፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከግንቦት 2 ቀን 2010 ዓ.ም እስከ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የግብርናና ቱሪዝም ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህም ከ100 በላይ ኩባንያዎች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ የኤግዚቢሽኑ ማጠቃለያ በሂልተን በተከናወነበት ወቅት የግሉ ዘርፍ የግብርና የፈጠራ ስራዎችን ማስተዋወቅና ማባዛት ላይ ያለው ሚና ላይ ጥናታዊ ፅሁፍም ቀርቧል፡፡
ጥናታዊ ፅሁፉን ያቀረቡት ዶክተር አማኑኤል አሰፋ፤ የግብርናውን ዘርፍ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለመምራት ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት መነሻ ስራዎች ማከናወን እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ በአሁን ወቅት ግን ከዩኒቨርሲቲዎች ይሁን ከምርምር ተቋማት የሚወጡ ስራዎች ለአርሶ አደሩ በአግባቡ እየደረሱ አለመሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡
የግብርናውን ዘርፍ የሚመሩ ተቋማት የተገኙ የምርምር ስራዎች ይሁኑ አዳዲስ ምርጥ ዘሮች ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ ማድረግና መረጃ መስጠት ላይ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ በግሉ ዘርፍ በግብርና ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች የግብርናው ዘርፍ ዘመናዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች እንዲስፋፉ ያላቸው ሚና አናሳ ነው፡፡ በተጨማሪም በመንግስት ደረጃ የሚከናወኑ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች የተፈለገውን ያክል አርሶ አደሩ ጋር እየደረሱ አለመሆናቸውን ዶክተር አማኑኤል ያስረዳሉ፡፡
የግብርና ምርቶችን ዘመናዊ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ የፈጠራ ሂደቶች በግል ኩባንያዎች በተለይ በውጭ ባለሀብቱ በብዛት ይታያሉ፡፡ የውጭ ባለሀብቱ ከየአገሩ ይዞት የሚመጣው አዳዲስ የግብርና አመራረት ዘዴዎች ቢኖሩም ኩባንያዎቹ ከሚገኙበት አካባቢ ውጪ ወደ ሌሎች ቦታዎች እየተስፋፉ አይደለም፡፡ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ አናሳ መሆኑንና የግል ዘርፉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት ላይ ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ማሳያዎች ናቸው፡፡ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አካባቢ የአመለካከት ችግሮች መኖራቸው የምርምር ስራዎች በአግባቡ ለአርሶ አደሩ እንዳይደርስ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ ባለሙያዎቹ አርሶ አደሩ እውቀት ሳይኖረው በኋላቀር አካሄድ እያረሰ ይገኛል የሚል አመለካከት በመያዛቸው በተገቢው መንገድ ለአርሶ አደሩ ትምህርት እየሰጡ አደለም፡፡
ከዚህ ባለፈም ለአርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂ ማብዛት ችግር ለመፍታት አዳዲስ የግብርና ምርቶች ሲመጡ በጋራ የመስራት ሂደት፣ ለግብርናው ኢኮኖሚ የሚጠቅሙ አዳዲስ ምርቶች በምርምር ማውጣት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የመንግስት ተቋማትና የግል ዘርፉ በተቀናጀ መንገድ ዘመናዊ የግብርና ምርቶችና ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩ ጋር እንዲደርስ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ዶክተር አማኑኤል አስረድተዋል፡፡
በአገሪቱ የግብርናውን ዘርፍ ዘመናዊ ለማድረግ በተለያዩ መንገዶች የጥናት ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት ለሰብል ምርት የሚያግዙ የምርምር ስራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ የምርምር ስራዎችን ለማሳደግና ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ የሚያግዙ ፖሊሲዎች ተቀርፀው እየተሰራባቸው ነው፡፡ ፖሊሲውም የአገር ውስጥ የምርምር ስራዎችና አዳዲስ ምርቶች ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ሂደት ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ በዚህም በተወሰነ መልኩ በአርሶ አደሩ ላይ የግብርና ስራው እውቀት እንዲጨምር አድርጓል፡፡
በግብርናው መስክ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችም የተገኙ አዳዲስ የምርምር ስራዎችና ቴክኖሎጂዎች በማስተዋወቅ እንዲሁም በሚሰሩባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮችም የምርምር ስራዎችን እንዲጠቀሙ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በሳይስንና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች በኩልም የግብርና ዘርፉን ለመደገፍ ፖሊሲ ተቀርፆ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ ከተለያዩ አገራትም ቴክኖሎ ጂዎችን በመኮረጅና አስመስሎ በመስራት አርሶ አደሩ በዘመናዊ መንገድ የግብርና ስራዎችን እንዲያከናውን እየተደረገም ይገኛል፡፡
በቀጣይም የግሉ ዘርፍ በተለይ የውጭ ባለሀብቱ የግብርና ምርምር ስራዎች እንዲያከናውንና ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም ማድረግና በአገር ውስጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስራው በተጠናከረ መንገድ እንዲቀጥል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ዶክተር አማኑኤል ተናግረዋል፡፡

 

መርድ ክፍሉ

Published in ኢኮኖሚ

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እአአ 2015 ላይ ከተደረገው የኒውክሌር ስምምነት መውጣታቸው በቀጣይ የኢራን ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የአልጀዚራ ዘገባ ያሳያል፡፡ አንዳንዶች ግምታቸውን ሲያስቀምጡ የትራምፕ ውሳኔ በአሉታዊ መንገድ በነዳጅ ገበያው ላይ ተፅዕኖ በማምጣቱ የኢራንን ኢኮኖሚ ቀጣይነት ጥርጣሬ ውስጥ ከቶታል፡፡
ነገር ግን በመረጃ ላይ የተመሰረተ ትንበያ ለመስጠት ስምምነቱ ውድቅ ከሆነ በኋላ በቀጣይ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውን መመለስና ስምምነቱ በተደረገበት ወቅትም ምን ተከስቶ ነበር የሚለው ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ዘገባው ያሳያል፡፡ ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት ኢራን ያገኘችው ምንም አይነት ጥቅም እንዳልነበረም ዘገባው ይጠቁማል፡፡
ኢራን በስምምነቱ ወቅት ከተጣለባት ማዕቀብ ውስጥ እንዲነሳላት የምትፈልገው በፋይናንስ ላይ የተጣለው እቀባ ነው፡፡ ነገር ግን የተጣለባት ማዕቀብ ሊቀነስ ቀርቶ ጭራሽ ተጨማሪ ማዕቀቦች እንደተጣሉባት ዘገባው ያሳያል፡፡ ከዚህ ውስጥ በቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የተፈረመው የቪዛ አሰጣጥ ገደብ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተጨማሪም በትራምፕ አስተዳደር ተጨማሪ ማዕቀቦች ተጥሎባታል፡፡
በዚህም አሜሪካ ስምምነቱን የጣሰች ሲሆን፤ በቀጣይም አሜሪካ ኢራን ከስምምነቱ የምታገኛቸውን ጥቅሞች እንድታጣ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላት ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ በዚህ ምክንያት የኢራን ኢኮኖሚ በተጣለባት ማዕቀብ እያሽቆለቆለ ቢሄድም፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ግን በስምምነቱ መሰረት ይነሳልኛል የሚል ተስፋ እንደነበራት ዘገባው ይጠቁማል፡፡ ኢራን ብዙ ነዳጅ የምትሸጥ ቢሆንም ስምምነቱ ተግባር ላይ ከዋለ በኋላ ግን ከነዳጅ ያገኘችው ገቢ አነስተኛ መሆኑን ዘገባው ይገልፃል፡፡
እንደ ኢራኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሮሀኒስ ግምት፤ በኢራን የምዕራባውያን ድርጅቶች ትርፋማ እንዲሆኑ በማስቻል የተጣለውን ማዕቀብ ማስቀየር ይቻላል የሚል ነበር፡፡ በዚህም ስምምነቱ ተግባር ላይ ከዋለ በኋላ ኢራን የአገሯን ድርጅቶች በማይጎዳ መልኩ ለምራባውያን ገበያዋን ክፍት አደረገች፡፡ ነገር ግን በዚህ ሂደት ኢራን እአአ 2016 እስከ 2017 ባለው ጊዜ 50 በመቶ የገበያ ድርሻዋን ማጣቷን ዘገባው ያሳያል፡፡
ከዚህ ባሻገርም የአገሪቱ የገቢ ፍሰት ባለፈው ዓመት እክል የገጠመው ሲሆን፤ ከስምምነቱ በፊት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኝ የነበረው የካፒታል ፍሰት መጠኑ በ11 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን ነው ዘገባው ያስታወሰው፡፡ የአገሪቱ የገንዘብ ምንዛሬም እያሽቆለቆለ የሄደ ሲሆን፤ ስምምነቱ ወደ ተግባር በገባበት ወቅት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ችግሩን ለመቆጣጠር ቃል ገብተው ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የኢራን የውጭ እዳዋ ከ 777 ሚሊዮን ዶላር ወደ ሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን መድረሱን ዘገባው ይጠቁማል፡፡ ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ አስተያየት ሰጪዎች ስምምነቱ ከተሰረዘ የአራን የኢኮኖሚ ችግር ሊቀረፍ እንደሚችል ይተነብያሉ፡፡
አሜሪካ ከኒውክለር ስምምነቱ መውጣቷ በኢራን ውስጥ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ አንድ እንዲሆን ከማድረጉ በተጨማሪ አሁን ያለባቸውን የኢኮኖሚ ችግር ለመፍታት የተለየ መንገድ እንዲጠቀሙ በር እንደሚከፍት ዘገባው ይጠቁማል፡፡ የስምምነቱ መሻር ኢራናውያን ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ለውጥ እንዳለ ሁሉ በአሜሪካ ላይ ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር እንደሚያደርግና አሜሪካ የኢራን ጠላት መሆንዋን በይፋ እንደሚያሳይ ዘገባው ይጠቁማል፡፡ ስምምነቱ የምራባውያን ኢኮኖሚ የኢራንን የኢኮኖሚ እድገት እንደማይደግፈው ያሳየ እንደነበርም ዘገባው አትቷል፡፡
የሮሀኒ መንግስት የተጣለባቸውን ማዕቀብ ለመቋቋም አገር ውስጥ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አላደረገም፡፡ በተቃራኒው የውጭ ድርጅቶች ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ አንዳንድ የመከላከል እርምጃዎች ወስዷል፡፡ አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ሁለት ሶስተኛው አገሪቱ የምታስገባው ምርት አገር ውስጥ ከሚመረተው ምርት ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ዘገባው ይጠቁማል፡፡
ኢራን በየዓመቱ እነዚህን ተመሳሳይ ምርቶች ለማስገባት 30 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የምታደርግ ሲሆን፤ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ግን 45 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ የሃይማኖት መሪ የሆኑት አያቶላህ ካኻማኒ እንደሚሉት፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ገደብ በመጣል የአገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ ማረጋጋት ይቻላል፡፡ እንደዚህ አይነት እርምጃዎች የአገር ውስጥ አምራቾችን ያበረታታሉ፣ ስራ እጥነትን ይቀንሳሉ፣ የአገሪቱን የገንዘብ የመግዛት አቅም ይጨምራሉ፤ እንዲሁም በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ይቀንሳሉ፡፡
በአገሪቱ ያለው የታክስ ሁኔታም እንዲጨምር መፈለጉ የአገሪቱ በጀት ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ እንዲሆን ለማስቻል ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አማካሪ የሆኑት ማሱድ ኒሊ እንደሚሉት፤ ኢራን ውስጥ አስር በመቶ ያህሉ ነዋሪ ሶስት በመቶ ያህል ግብር ይከፍላል፡፡ በአሜሪካ ደግሞ አስር በመቶ ነዋሪ 70 በመቶ ያህሉን ግብር ይከፍላል፡፡ እንደ ኒሊ አባባል፤ ነዋሪው የሚከፍለው ግብር መጨመር አለበት፡፡
በተጨማሪም በንግድ እንቅስቃሴና በግብር ላይ ለውጦችን በማካሄድ በአሜሪካ የተጣለውን ማዕቀብ መቋቋም እንደሚቻል ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ አሜሪካ በጣለችው ማዕቀብ እየተጎዱ የሚገኙት ባንኮች ሲሆኑ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት ባንኮች አለም አቀፍ ግንኙነት ያላቸውና ለመበደር፣ ለማበደር፣ ለውጥ ለማካሄድና ኢንቨስት ለማድረግ ተቸግረዋል፡፡ ኢራን በተጣለባት ማዕቀብ ኢኮኖሚዋ እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡
ኢራን አሜሪካ ተፅዕኖ ከምትፈጥርበት ሁኔታ ለመውጣት ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡ ኢራን የመጀመሪያውን የምንዛሬ ልውውጥ ከቱርክ ጋር ተፈራርማለች፡፡ አገራቱ እአአ 2018 መጀመሪያ ላይ የመጀሪያውን የምንዛሬ ልውውጥ የሚያደርጉበት አሰራር ዘርግተዋል፡፡ በተጨማሪም ኢራን በንግድ ልውውጥ ከቻይና ጋር በትብብር እየሰራች ሲሆን፤ በቀጣይም የምንዛሬ ልውውጥ ላይ ስምምነት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እአአ 1979 የኢስላሚክ ለውጥ አራማጅ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡ በዚህም የተለያዩ ግንባታዎች ተከናውነዋል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚን ሲደግፍ የነበረው ደግሞ ከነዳጅ ሽያጭ የተገኘው ገቢ ነበር፡፡ ነገር ግን የነዳጅ ሽያጩ ለአገሪቱ እድገት ቀጣይነት መተማመኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ትክክለኛ እድገት የሚባለው በቤት ግንባታ ዘርፍ ለህዝቡ በቂ የሆነ መኖሪያ ቤትና መሰረተ ልማት መሟላት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የቀድሞ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃክ ስትራው እአአ 2014 ላይ ኢራንን በጎበኙበት ወቅት፤ አገሪቱ አሁንም በተጣለባት ማዕቀብ እየተጎሳቆለች ትገኛለች ማለታቸውን ዘገባው ያስታውሳል፡፡
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ አሜሪካ በታሪኳ ከፍተኛ የሆነውን ማዕቀብ እጥላለሁ ማለቷን መንቀፏን የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል፡፡ በአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ የሚወሰዱ እርምጃዎች የሚያሳዩት አሜሪካ በተኮላሸው ፖለቲካዋ እስረኛ እንደሆነችና የሚመጣው መዘዝም ተቋዳሽ እንደምትሆን ተናግረዋል።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ የሆኑት ፌደሪካ ሞገሪኒ በበኩላቸው አሜሪካን ተችተዋል። በአውሮፓውያኑ 2015 የተፈፀመውን የኒውክሌር ስምምነት መሰረዝ ለመካከለኛ ምስራቅ ያለውን ፋይዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማሳየት እንዳልቻሉም ገልፀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ወር መጀመሪያ ስምምነቱን ለመተው መወሰናቸውን ተከትሎ “በስምምነቱ ላይ ሌላ ምርጫ የለም፤ በመሆኑም ኢራን ኃላፊነቷን የምትወጣ ከሆነ የአውሮፓ ህብረት በስምምነቱ ሊቀጥል ይችላል” ብለዋል።
ከኢራን የኒውክሌር ስምምነት በኋላ አንዳንድ በአውሮፓ የሚገኙ ትልልቅ ድርጅቶች በኢራን መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የቸኮሉ ቢሆንም፤ አሜሪካ ስምምነቱን መሰረዟን ተከትሎ ኢራን ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ አሊያም ከአሜሪካ ጋር ንግድ ለመጀመር ምርጫ ውስጥ እንዲገቡ ተገደዋል።
እአአ 2015 በተደረገው የኒውክሌር ስምምነት ኢራን ኒውክሌርን ለመስራት የሚያገለግለውን ዩራኒየምን መጠን ለመቀነስ ተስማምታ ነበር። ይህም ለአስራ አምስት አመታት ለኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያና ለኒውክሌር መሳሪያ እንዲውል የታሰበ ነበር። ፐሉቶኒየም የተሰኘ ለቦምብ መስሪያ የሚውል ኬሚካል አላመርትም በማለትም ተስማምታ ነበር። በዚህም ሳቢያ በተባበሩት መንግስታት፣ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት የተጣለባት ማዕቀብ የኢራን ኢኮኖሚ እንዳያንሰራራ አድርጎታል። ስምምነቱ በኢራንንና በአምስት የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራት አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ ፣ ቻይናና ሩሲያ እንዲሁም ጀርመን ጋር የተደረገ ነበር፡፡

መርድ ክፍሉ

Published in ዓለም አቀፍ

ሰሞኑን የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተጠናቋል፡፡ የ12ኛ ክፍል ደግሞ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በእነዚህ የፈተና ወቅቶች ኩረጃ አንዱ የተማሪዎች ስጋት እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ በተለይ የአገራችን የትምህርት ሂደት ከጥራት አንጻር ብዙ ርቀት እንዳልተጓዘ በሚገለጽበት በዚህ ወቅት ኩረጃን መቆጣጠር ካልተቻለ በቀጣይ በዘርፉ ለተያዘው የለውጥ ሂደት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔና አንድ ጓደኛዬም ስለፈተና ስንጨዋወት ከጥቂት ዓመታት በፊት ስለተፈፀመ አንድ ታሪክ አጫወተኝ፡፡ ድርጊቱ አሳዛኝና አስተማሪ ሆኖ ስላገኘሁት ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡
ባለታሪኩ ሱራፌል አለነ በአንድ የመንግሥት ተቋም ውስጥ የቴክኒክ እቃ ማደራጃ ሠራተኛ ነው፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት በተለያዩ የግልና የመንግሥት ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ራሱንና ቤተሰቡን ሲረዳ ቆይቷል፡፡ እነዚያ ዓመታት ግን በህይወቱ ውስጥ ፈታኝ ወቅቶች እንደነበሩ ሱራፌል በምሬት ይገልጻል፡፡ ምክንያቱም የልጅነት ህልሙ ይህ አልነበረምና፡፡ አሁን ላለበት የህይወት መስመር የተዳረገው በአንድ ወቅት ባጋጠመው የህይወት እክል ምክንያት ነው፡፡
ሱራፌል ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ በልጅነቱ ለትምህርት የነበረው ፍላጎት ከፍተኛ ስለነበር ገና ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ውጤታማ ከሚባሉ ተማሪዎች ተርታ እንደሚመደብ ያስታውሳል፡፡ 12ኛ ክፍልን እስከሚያጠናቅቅ ድረስ ከክፍሉ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ነው የተማረው፡፡ በአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ በጓደኞቹ ዘንድም ከጉብዝናው በተጨማሪ በጭምትነቱና በተረጋጋ ባህርይው ይታወቃል፡፡ ተወዳጅና ምስጉን ተማሪም ነበር፡፡ መምህራኑም በትምህርት ቤቱ ጥሩ ውጤት አምጥተው ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡና ከወደፊቱ የአገራችን ምሁራን አንዱ እንደሚሆን እምነቱ ነበራቸው፡፡ ይህ ሁሉ የሱራፌል ተስፋና የመምህራኑ ግምት ግን የ12ኛ ክፍል ፈተና በሚሰጥበት ወቅት ባጋጠመው እንቅፋት ተጨናገፈ፡፡ አጋጣሚው እንዲህ ነበር፡፡
ሱራፌል የ12ኛ ክፍል ፈተናን በስኬት በማጠናቀቅ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የነበረው ጉጉት እጅግ የላቀ ስለነበር ከፈተናው አስቀድሞ ዓመቱን ሙሉ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ቀንና ሌሊት ጭምር በማጥናትም እያንዳንዱን የትምህርት አይነት በሚገባ ተረድቷል፡፡ ቀደም ሲል ሲሰጡ የነበሩ የ12ኛ ክፍል ፈተናዎችንም አንድ በአንድ ተንትኖ በማጥናት እውቀቱን ለማዳበር ጥሯል፡፡
የ12ኛ ክፍል ፈተና ሊሰጥ አንድ ሳምንት ሲቀረው የመፈተኛ መታወቂ ካርድ ወስዶ ለፈተናው ራሱን አዘጋጀ፡፡ ለፈተናው አንድ ቀን ሲቀረው ሁለት ተማሪዎች መጥተው አናገሩት፡፡ ልጆቹን ከዚህ በፊት ያውቃቸዋል፡፡ በትምህርተ ቤቱ ውስጥ በሥነምግባራቸው ብልሹ ከሚባሉ ተማሪዎች ግንባር ቀደምና በየጊዜው ከትምህርት ቤት አንዴ ሲባረሩ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲመለሱ የቆዩ ናቸው፡፡ ከትምህርት ቤት ውጪም ቢሆን በተለያዩ መጠጥ ቤቶችና ጫት ቤቶች የሚውሉና በአካባቢውና በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ የሚታወቁ ቦዘኔዎች ናቸው፡፡
«ስማ ሱራፌል ያው እንደምታውቀው እኛ አንዴ ስንባረር ሌላ ጊዜ ደግሞ በራሳችን ስንቀር ትምህርቱን በአግባቡ አልተከታተልንም፡፡ ለፈተናው አንተን ነው የተማመነው፡፡ ስለዚህ ያለምንም ማመንታት ፈተናውን አንድ በአንድ ትሰጠናለህ፡፡ እኛ ለወደፊቱ ይህንን 12ኛ ክፍል አልፈን ዩኒቨርሲቲ ካልገባን ስማችን ስለተበላሸ ዋጋ የለንም፡፡ ስለዚህ ልብ አድርግ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አንተም ዩኒቨርሲቲ ሳትገባ ዋጋህን ታገኛለህ» በማለት በያዙት ጩቤ አስፈራርተውት ይሄዳሉ፡፡
ሱራፌል ከዛች ሰዓት ጀምሮ ተረበሸ፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበትና ለማን መንገር እንዳለበትም ማሰብ አቃተው፡፡ በአንድ በኩል የልጆቹ ሁኔታና ከዚህ በፊት የነበራቸው የተበላሸ የህይወት መስመር አስፈራው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የራሱም የህይወት መስመር ሲበላሽ ታየው፡፡ እና ምን ያድርግ? በዚህ መንታ ሃሳብ ላይ ሆኖ ያለእንቅልፍ አደረ፡፡ በማግስቱ ተነስቶ ወደ ትምህርት ቤቱ የግዱን ማዝገም ጀመረ፡፡
ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ሲገባ ልጆቹ ከሱ ቀድመው ተገኝተዋል፡፡ ገና ከሩቅ ሲያዩትም ወደ እሱ መጡ፡፡ እናም በወዳጅ አይነት ሰላምታ ከሰጡት በኋላ አንዱ ጠጋ ብሎ በጆሮው ‹‹ሱራፌል የነገርንህን እንዳትዘነጋ›› ብሎት ሄደ፡፡ ሱራፌል ይባስ ተረበሸ፤ የሚያደርገው ጠፋው፡፡ በአንድ በኩል «ሂድና ለፈተና ጣቢያ ኃላፊው ተናግረህ ቦታ እንዲቀይሩህ አድርግ» በሚልና «አይ እንዲህ አታድርግ ልጆቹ ተስፋ የቆረጡ ስለሆነ በኋላ ይጎዱሃል» በሚሉ በልጅነት የፍራቻ ስሜት ሃሳቦች ተወጠረ፡፡ በዚህ ጭንቀት ውስጥ እያለ ወደ መፈተኛ ክፍል ገባ፡፡
ክፍል ገብተው እንደተቀመጡ የፈተና ወረቀት መታደል ጀመረ፡፡ ሱራፌልም በጭንቀት ውስጥ ሆኖ ፈተናውን መስራቱን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን እነዚያ የሌላውን እውቀት ለመውሰድ የቋመጡ ሁለት ጎረምሶች በአንድ በኩል እነርሱ ያልለፉበት በመሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ስለፈተና አሰራር ብዙም ግንዛቤ ስላልነበራቸው ገና ከመጀመርያው ጀምሮ መልስ እዲሰጣቸው ወደ ሱራፌል ማፍጠጥ ጀመሩ፡፡ በመካከልም ከሱራፌል ኋላ የተቀመጠው አንዱ ጎረምሳ ቀስ ብሎ ጩቤ አውጥቶ አሳየው፡፡
ሱራፌል ከዚህ በላይ ተረጋግቶ መሥራት አልቻለም፡፡ የሚያውቀው መልስ ሁሉ ጠፋው፡፡ ማጥቆር ያለበትን ትቶ የሌለበትን እስከማጥቆርም ደረሰ፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ ምንም መሥራት ስላልቻለ የተገኘውን መልስ አጥቆሮ ወጣ፡፡ በቃ የህይወት መስመሩ መበላሸቱ ታወቀው፡፡
በጠዋቱ የፈተና ክፍለ ጊዜ የሚፈልጉትን ማግኘት ያልቻሉት እነዚያ የኩረጃ አንበሶች በምሳ ሰዓት ሱራፌልን ጠብቀው ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጡት፡፡ በተለይ አንዱ ለመማታትም ተጋብዞ በሌላው ጓደኛው ክልከላ ሱራፌል ለጊዜው ሳይመታ ቀረ፡፡ የከሰዓት ውሎውም ተመሳሳይ ነበር፡፡ ሱራፌል አንዴ መንፈሱ ስለተረበሸ ተረጋግቶ መሥራት ባለመቻሉ ተገቢውን መልስ መመለስ ሳይችል ቀረ፡፡ በቃ! የሱራፌል የዓመታት ህልም በዚህ አይነት ሁኔታ ተጨናግፎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቀበረ፡፡
ወቅቱ ደርሶ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ሲታወቅ ሱራፌል ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃውን ውጤት አላመጣም፡፡ እናም ህልሙ በዚሁ አከተመ፡፡ እሱም ቢሆን ከዚያ ከያዘው የፈተና ፍራቻ /ፎቢያ/ ሳይላቀቅ ዳግም ወደ ፈተና ላለመመለስ ወሰነ፡፡ እናም በቀጥታ ራሱንና ቤተሰቡን ለመርዳት ሥራ ማፈላለግ ጀመረ፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታም በተለያዩ የጉልበት ሥራዎች ተቀጥሮ ሠርቷል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ቀስ በቀስ ከዚህ ችግር ለመውጣት ሲል ዳግም ትምህርቱን ማሻሻል እንዳለበት በማሰብ የ12ኛ ክፍል ፈተና ወስዶ በማሻሻል ከአንድ የግል ኮሌጅ በኤሌክትሮኒክስ ዲፕሎማውን ማግኘት ቢችልም የዚያን ጊዜ ትውስታው ግን አሁንም ከልቡ አልወጣም፡፡ ጥላቻና ቂም ያረገዘው ልቡ ዛሬም ስለፈተና ባሰበ ቁጥር ያመረቅዛል፡፡
የሱራፌል የህይወት ታሪክ የአንድ ግለሰብ ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይ አሁን አሁን በአገራችን የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናዎች በሚሰጡበት ወቅት ዋነኛ የትምህርት ቤትና የተማሪዎች ርዕሰ ጉዳይ ኩረጃ ሆኗል፡፡ ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየሰፋ የመጣ የተበላሸ ሥነምግባር ለምን ሊቀረፍ አልቻለም? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡
አንዳንድ ተማሪዎች እንደሚገልፁት አሁን አሁን ኩረጃ በትምህርት ቤት ውስጥ ትልቁ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ሙስና አገርን እንደሚጎዳው ሁሉ ኩረጃም የትምህርት ሥርዓቱን ክፉኛ የሚያበላሽ አፀያፊ ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ይህን አስነዋሪ ተግባር ለመከላከል ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ስለኩረጃ የሚወራውም በፈተና ወቅት ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ስለኩረጃ ከዚያ አስቀድሞም ቢሆን ማሰብና የሚያስከትለውን ጉዳት ጭምር ለእያንዳንዱ ተማሪ፣ የተማሪ ወላጅና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ማስገንዘብ ይገባል፡፡
አሁን አሁን ኩረጃ የሚካሄደው ከጥናት በራቁ ተማሪዎች ብቻ አይደለም፡፡ ለኩረጃ ተባባሪ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶችና መምህራን ጭምር እንዳሉ አንዳንድ ተማሪዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ይህንን ያህል ተማሪዎች አሳለፍን፣ ይህንን ያህል ለኮሌጅ አበቃን በሚል ትምህርት ቤታቸውን ለማስተዋወቅ ሲሉ ኩረጃን በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ሲያበረታቱ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ በተለይም በግል ትምህርት ቤቶች ላይ በስፋት እንደሚስተዋል በተደጋጋሚ ሲገለፅ ይሰማል፡፡ አንዳንድ ምሁራን ደግሞ በፈተና ወቅት ኩረጃን አይተው እንዳላዩ ስለሚያልፉ ለሚኮርጁ ተማሪዎች የልብ ልብ ይሰጣል፡፡ ይህ ለሚኮርጁ ተማሪዎች ድፍረትን፣ ለጎበዝ ተማሪዎች ደግሞ ተስፋ መቁረጥን የሚያስከትል ተግባር ነው፡፡
መመለስ ያለበት አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ግን አለ፡፡ ዓመቱን ሙሉ ሲያጠና የቆየ አንድ ተማሪ በድንገት ዓመቱን ሙሉ ደብተሩን ሳያይ ለከረመ ተማሪ ድካሙን አሳልፎ ሲሰጥ ምን ያህል ያበሳጫል? ለለፋው ተማሪ ድካምስ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባው ማነው? ለዚህ ጉዳይ መንግሥትም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ያጠኑ ተማሪዎች መብትም በአግባቡ መጠበቅ አለበት፡፡
የአንድን ሲያጠና የከረመ ተማሪ ውጤት ሌላው እንዲኮርጅ መፍቀድ አንድ ሀብታም ለዓመታት ጥሮ ግሮ ያፈራውን ሀብት ሌቦች ሲዘርፉት ቆሞ ከማየት የተለየ ባለመሆኑ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
በሌላ በኩል ኮርጀው የሚያልፉ ተማሪዎችም የነገ የአገር ሸክም ስለሚሆኑ ከወዲሁ ይህንን የሀገር በሽታ እያከሙ መሄድ ተገቢ ነው፡፡ መከላከልን መሰረት እንዳደረገው የአገራችን የጤና ፖሊሲ ይህ የኩረጃ በሽታ ፍሬ አፍርቶ ነገ በርካታ የተማረ፤ ግን ያላወቀ ሙሰኛ ከማፍራታችን በፊት ከወዲሁ እያፀዳን መሄድ የግድ ይላል፡፡ አሁን አሁን አገራችን ለተለያዩ የሰላም እጦት ችግሮች የተዳረገችበት አንዱ ምክንያት ሙስና መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በተለያዩ ተቋማት የሚገኙ አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሳይወጡ በመቅረት ህብረተሰቡን ሲያማርሩት ይስተዋላል፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ኪራይ ለመሰብሰብ ከመፈለግ የሚመነጭ ነው፡፡ አሁን በዚህ አይነት ሁኔታ በኩረጃ ዝም የምንላቸው ተማሪዎችም ነገ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በተመሳሳይ ዘዴ የማይመረቁበትና ወደ አገልግሎት አሰጣጡ ጎራ የማይቀላቀሉበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ቀንደና ሙሰኛ ከመሆን የሚያግዳቸው አይኖርምና ተገቢው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡
ሌላው በብሄራዊ ፈተና ብቻ ሳይሆን በየደረጃው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ባለው የትምህርት አሰጣጥ መርሃ ግብርም የኩረጃ ድርጊት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አንድ ተማሪ የኩረጃ ልምድ ሳይኖረው 10ኛ ወይም 12ኛ ክፍል ላይ ሲደርስ ብቻ ለኩረጃ አይነሳሳም፡፡ ከዚያ ቀደም ባሉት የትምህርት ደረጃዎችም በተመሳሳይ ልምድ እያዳበረ ሄዶ ነው በብሄራዊ ፈተናዎች ላይ ቀንደኛ ኮራጅ የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ኩረጃን ለማስቀረት ከታች ጀምሮ መሥራት ይገባል፡፡
ሌላው ለአገር የሚጠቅሙ፤ በላባቸውና በእውቀታቸው ራሳቸውንና አገራቸውን ለማገልገል ከልጅነት እድሜቸው ጀምሮ የሚጥሩ እውነተኛ ዜጎችን መብት ማስጠበቅ ከመንግሥትና ከትምህርት ማህበረሰብ ይጠበቃል፡፡ ልክ እንደ ሱራፌል ሁሉ በኩረጃ ምክንያት እድሜያቸውን ሙሉ በጥናት ያሳለፉ የነገ ተስፈኛ ወጣቶች በመጨረሻ ሰዓት ሥነምግባር በጎደላቸው ኮራጆች ምክንያት ውጤታቸው ሊበላሽ አይገባም፡፡ ይህ ደግሞ የልጆቹ ብቻ ሳይሆን የአገርም፣ የቤተሰብም ጉዳት ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ኩረጃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋምም ቢሆን አንዱ የተማሪዎች መገለጫ እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የተከታታይ ምዘና ስርዓት/Continuous Assessment/ አብዛኛው የምዘና ውጤት በቡድን በሚሰጡ ሥራዎች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ሰነፉን ከጎበዙ ለመለየት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ አሰራር አጋጣሚውን በመጠቀም ሰነፍ ተማሪዎች በጎበዞች ተሸፍነው ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፉና በመጨረሻም እስከምረቃ እንዲደርሱ የሚያደርግ ነው፡፡
የተማሪዎች የመመረቂያ ፅሁፎች በገንዘብ የሚሰሩበት ሁኔታ አሁን አሁን ለአብዛኞቻችን አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ከ10 እስከ 15 ሺህ ብር በመክፈል አንድ የመመረቂያ ፅሁፍ ማሰራት መብት እስኪመስል ድረስ በገሃድ ይሠራል፡፡ ለዚህም ዋነኛው የግንኙነት መስመር «የመመረቂያ ፅሁፍ እናማክራለን» የሚል ነው፡፡
አገራችን በትምህርት ዘርፉ እየተከተለች ያለው ፖሊሲ ከ33 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን በትምህርት ገበታ ላይ ማዋል ያስቻለ ነው፡፡ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረትም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ 53 ዩኒቨርሲቲዎችን ገንብቷል፡፡ ስለዚህ በዚህ ግዙፍ ተቋም ላይ የሚሠሩ ሥራዎች አገርን ለማልማትም ሆነ ለማጥፋት ወሳኝ ኃይል በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይ መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ዘመቻ በጀመረበት በአሁኑ ወቅት ኩረጃን ከመሰረቱ ማስቀረት መሰረታዊ ጉዳይ ሊሆን ይገባል፡፡ ዛሬ ላይ ያልሠራነው የቤት ሥራ ነገ ሊሠራ አይችልም፡፡ ልጅ ‹‹ምነው እናቴ በዕንቁላሉ በቀጣሽኝ›› እንዳለው ዛሬ በዕንቁላሉ ያልተቀጣ ኮራጅ ተማሪ ነገ ተመርቆ ወደ ሥራው ዓለም ሲቀላቀል መልሶ የህዝብ ጠላት፣ የአገር አጥፊ ይሆናል፡፡ እናም ለነገዋ የበለፀገች ኢትዮጵያ እውን መሆን ኩረጃን ከመሰረቱ ማስቀረት የዛሬ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡

ውቤ ከልደታ

Published in አጀንዳ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ እየተከተለች ባለው የፌዴራላዊ ስርዓት ባለፉት 27 ዓመታት በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን መንግሥትና ህዝብ ብቻ ሳይሆን በርካታ የውጭ አገር መንግሥታትና ምሁራን ጭምር የመሰከሩት እውነታ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት በአገራችን የተመዘገበው ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ትልቁ ዕድገት እንደሆነ የተመሰከረለት ነው፡፡
የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርናን ምርታማነት ብንመለከት ባለፉት 27 ዓመታት በሰባት እጥፍ ማደግ ችሏል፡፡ በመንገድ መሰረተ ልማት፣ በጤና፣ በትምህርት፣በሃይል አቅርቦትም ሆነ በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችም የተመዘገበው ስኬት ከፍተኛ ነው፡፡ በፖለቲካውም ዘርፍ የታዩት ለውጦች በተጨባጭ የሚታዩ ናቸው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የተሰራውን ሥራም ቀላል አይደለም ፡፡ በነዚህ ዓመታት የፕሬስ ነፃነትን ለማረጋገጥ የተሰራው ሥራ የሚጠበቀውን ውጤት ባያመጣም መሠረታዊ እመርታ የታየበት ነው፡፡ በአገር ውስጥ ሆነው በነፃነት መታገል የቻሉ ከ60 በላይ የሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የተፈጠሩት በነዚሁ ዓመታት ነው፡፡
በሌላ በኩል ያልተሳኩና ሂደቱንም የፈተኑ በርካታ ችግሮችም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የፕሬስ ነፃነት ቢከበርም ሚዲያው የሚጠበቅበትን የማሳወቅ፣ የማስተማርና የማዝናናት አቅም ፈጥሮ ባለመሰራቱ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ዓቅም አልተፈጠረም፡፡ በፖለቲካውም መስክ በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት አሳድገው ተፎካካሪና አሸናፊ ለመሆን የሚያስችል አቅም የገነቡና ለህዝቡ አማራጭ የፖለቲካ ስርዓት መፍጠር የሚችሉ ተተኪ ፓርቲዎች አልተገነቡም፡፡ በየጊዜው እያደገ የሚሄደውን የህዝብ ፍላጎት ማስተናገድና በአግባቡ መመለስ የሚያስችል ጠንካራ የመንግሥት የማስፈጸም አቅም መፍጠር አልተቻለም፡፡ሙስናና ብልሹ አሰራርም ባለመወገዱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መጥተዋል፡፡
በአጠቃላይ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ይህንን እውነታ በምክንያታዊነት የሚቀበልና የሚተች አስተሳሰብ በሚፈለገው ደረጃ የለም፡፡ ጥንካሬዎቻችንን ተቀብሎ፣ ወደ ፊት እንዲቀጥሉ የሚያበረታታ፣ ድክመቶቻችንን ደግሞ ነቅሶ በማውጣት እንዲታረሙ የሚታገል ምክንያታዊ ማኅበረሰብም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ሳይፈጠር ቆይቷል፡፡ ከዚህ አንጻር በመንግሥት፣ በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሚዲያም ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ ምክንያታዊ አስተሳሰብን ከማዳበርና ከመጠቀም አንፃር ክፍተቶች ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ በአገራችን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያታዊ አስተሳሰብን ከመያዝ ይልቅ ስሜት ላይ የተመረኮዘና አንዴ በጭፍን ጥላቻ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጭፍን ድጋፍ ሲዋከብ የኖረ ሆኖ ይታያል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በሚከተል መንግሥት ስር የሚተዳደር ህዝብ ለመሪው መንገድ የሚያሳይና መንግሥትንም የሚመራ ዋነኛ የለውጥ ሃይል ነው፡፡ ምክንያቱም መሪውንም የሚመርጠው ራሱ ህዝብ እንደመሆኑ የመረጠው የመንግሥት አካል ሲሳሳት “ተመለስ መንገድህን ስተሃል” የማለት፣ በትክክል ሲሰራም በዚሁ ልክ እንዲቀጥል “በርታ፣ ቀጥል” የማለት ሚናና ሃላፊነት የተጣለበት ነው፡፡ መሪውን የማስቀጠልም ሆነ የማውረድ ስልጣኑ የሱ በመሆኑ ሁል ጊዜ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ምክንያታዊ በሆነ አግባብ ሊደግፈው ይገባል፡፡
በአገራችን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ስንመለከት በሁለት የተራራቁ ጫፎች ላይ ቆመው አንዱ ሌላውን ሲኮንንና ሲያማርር ይስተዋላል፡፡ በዚህ ዙሪያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሻሻሎች መታየታቸው ግን አይካድም፡፡ በተለይ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቋቋሞ በጋራ መስራታቸው ርቀቱን ለማጥበብ ያስቻለ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ግን በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ ከመስራትና ምክንያታዊ ሆኖ ሃሳብን ከማንሸራሸር ይልቅ ልዩነቶችን እያጎሉ መሄድ ይታያል፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ አገር የሚኖሩ፣ ለአንድ አገር የሚሰሩ እና ዓላማቸውም የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ መሆኑን መገንዘብ ይገባቸዋል፡፡
በኅብረተሰባችንም ውስጥ ሚዛናቸውን የሳቱ በርካታ ሃሳቦች ይንሸራሸራሉ፡፡ በተለይ አሁን ለሁሉም ሰው ክፍት በሆነው የማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት የሚታዩ አንዳንድ ሃሳቦች ሚዛናችንን እያሳቱን አገራችን ላሰበችው የጋራ መግባባት እንቅፋት እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ በነዚህ ሚዲያዎች የሚንፀባረቁ ሃሳቦች ከፍቅርና ከአብሮነት ይልቅ የጥላቻ ፖለቲካን የሚሰብኩ፣ በጋራ ልንሰራባቸው ከምንችላቸው አገራዊ ጉዳዮች ይልቅ በሚያለያዩን ክፍተቶች ላይ የሚያተኩሩ፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ከህብረብሄራዊነት ይልቅ የከረረ ብሄርተኝነትን የሚያጎሉ ናቸው፡፡
እነዚህ ሁለት ፅንፎች ደግሞ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከልማት ይልቅ ውድመትን፣ ከአብሮነት ይልቅ መለያየትን የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ በተለይ መንግሥት በዘንድሮ የግንቦት 20 በዓል አከባበር “የላቀ ብሄራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ለላቀ አገራዊ ስኬት” በሚል ያሰፈረው መሪ ሃሳብ እውን እንዲሆን ምክንያታዊ አስተሳሰብ የአገራችን ህዝቦች መገለጫ ሊሆን ይገባል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።