Items filtered by date: Tuesday, 05 June 2018

በአነጋጋሪ ክስተቶች ተሞልቶ ለስምንት ወራት ያህል ሲጓተት የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ድራማው ከትናንት በስቲያ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ መቋጫ አግኝቷል። የድራማው ፍፃሜም ያልተጠበቁትን አቶ ኢሳይያስ ጂራን አዲሱ ፕሬዚዳንት አድርጎ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት እግር ኳሱን እንዲመሩ በአብላጫ ድምፅ መርጧል።
ከምርጫው 144 ድምፆች ከቀረቡት አራት ዕጩዎች መካከል አቶ ተስፋይ ካሕሳይ 3፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ 28፣ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው 47 ሲያገኙ አቶ ኢሳይያስ ጂራ 66 ድምፅ በማግኘት ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ሆኖም የአስመራጭ ኮሚቴው የምርጫ ውጤቱን ይፋ አድርጎ አቶ ኢሳይያስ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ፤ በምርጫ ህጉ ላይ የተቀመጠው የአብላጫ ድምፅ ሳይሆን ‹‹የ50+1 ህግ ነው›› በሚል ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኗል። በድጋሚ ምርጫው አቶ ጁነይዲ እና አቶ ተስፋይ ከምርጫው ራሳቸውን ሲያገሉ በአቶ ኢሳይያስ እና አቶ ተካ መካከል በተደረገው ምርጫ አቶ ኢሳይያስ ጂራ 87ለ58 በማሸነፍ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነታቸው ተረጋግጧል።
በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ከተመረጡት አስር አባላት መካከል በተካሄደው የምክትል ፕሬዚዳንትነት ምርጫ ስድስት አባላት ቀርበው የቀድሞው የደደቢት ክለብ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂምም በአብላጫ ድምፅ ተመርጠዋል። አስሩን የሥራ አስፈፃሚ አባላት ለመምረጥ በተደረገው ሂደት ‹‹ምርጫ ሳይሆን ውክልና ነው›› በሚል ብዙ ወቀሳዎች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ በተለይም የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው አንድ ክልል ከአንድ በላይ የሥራ አስፈጻሚ አባል አይኖረውም የሚለውን የፌዴሬሽኑን ደንብ መሠረት ተከትሎ አቶ አሊ ሚራ መሀመድ ከአፋር፤ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ከደቡብ፤ ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን ከቤኒሻንጉል እና አቶ አብዱራዛቅ ሐሰን ከሶማሌ ክልል ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል መሆናቸውን ገና ምርጫው ሳይጀመር አረጋግጠዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከየክልላቸው ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው በመቅረባቸው ነው፡፡ እግር ኳሱ በአዲስ አስተሳሰብና አዲስ አመራር መለወጥ አለበት በሚል ተስፋ ተጥሎበት በነበረው ምርጫ አዳዲስ ሰዎች የመካተታቸውን ያህል እንደ አቶ አሊሚራህ ለሦስተኛ ጊዜ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በመመረጥ ሃትሪክ የሠሩበት አጋጣሚ በርካቶችን አስገርሟል። ከነዚህ በተጨማሪ በበፊቱ አመራር ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት አቶ አበበ ገላጋይ ከድሬዳዋ፤ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ከአዲስ አባባ፤ ቻን ጋት ኮት ከጋምቤላ እንዲሁም የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ከአማራ ክልል በሥራ አስፈፃሚነት ሊመረጡ ችለዋል። ከአዲሶቹ አመራሮች መካከል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው መርጠን ከዚህ ቀደም በእግር ኳሱና በሌሎች መስኮች የሠሯቸውን ሥራዎች እንደሚከተለው ቃኝተናል።
አቶ ኢሳያስ ጂራ - ፕሬዚዳንት
የአርባ ስድስት ዓመቱ አቶ ኢሳያስ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በ1964 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን፣ በስነ ህይወት የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው። ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት የሠቃ ወረዳ ስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ የሰበታ ስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ የጅማ ከተማ ክለብ ፕሬዚዳንት፣ የሰበታ ከተማ ክለብ ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የጅማ ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ አሁን እስካሉበት ጊዜ ድረስም የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ ሆነው እየሠሩ ቆይተዋል።
ኮሎኔል አወል አብዱራሂምም- ምክትል ፕሬዚዳንት
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የቅርብ ዓመታት ታሪክ ውስጥ ተፅእኖ መፍጠር ከቻሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት ኮሎኔል አወል፣ በ1989 ደደቢትን በመመስረት እስከ 2005 ዓ.ም በፕሬዚዳንትነት የቆዩ ሲሆን፣ በ2002 ዓ.ም ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገው ቡድን ጋር አንድ የሊግ እና አንድ የኢትዮጵያ ዋንጫን አሳክተዋል። ኮሎኔል አወል ስታድየም ገብተው ጨዋታዎችን ከመመልከት ባሻገር ትልቅ የእግር ኳስ ፍቅር ያላቸው መሆኑም ይነገራል።
አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው - ሥራ አስፈፃሚ
ለበርካታ ዓመታት በክለብና በብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነታቸው የሚታወቁት አቶ ሰውነት ቢሻው፣ ለእግር ኳስ ቤተሰቡ እንግዳ አይደሉም። የአሠልጣኝነታቸው ወርቃማ ዘመን ከአምስት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ በማሳለፍ የተፃፈ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም ዘመን ከአፍሪካ ዋንጫው ማግስት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ አስር አገራት አንዱ ሆኖ ከጫፍ ሲመለስ የቡድኑ መሪ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው እንደነበሩ ማንም አይዘነጋው። አሠልጣኝ ሰውነት ከብሔራዊ ቡድኑ ከተሰናበቱ በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተነቃቃበት በቀጥታ ወደ አዘቅጥ ሲወርድ ታይታል። አሠልጣኝ ሰውነትም ለዚህ መፍትሔ ይሆን ዘንድ የሰውነት ቢሻውና ቤተሰቡ የታዳጊና ወጣቶች የእግር ኳስ ማሠልጠኛ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከፍተው በእግር ኳስ የመሠልጠን ፍላጎት ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶች ከስር ጀምረው በማሠልጠን ላይ ይገኛሉ።
ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን - ሥራ አስፈፃሚ
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚነት ብቸኛ ዕጩ የሴት ተወዳዳሪ በመሆን የቀረቡት ወይዘሮ ሶፊያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ነው የቀረቡት። በተለያዩ ስፖርቶች ክልሉን ወክለው ከመወዳደር ባሻገር ውጤታማም ነበሩ። በርካታ የቤንሻንጉል ውጤታማ ተጫዋቾችን ያፈራው የንስር ክለብ መስራች እና የረጅም ጊዜ የቡድኑ መሪ ሆነው ቆይተዋል። በሰዓቱ በቡድኑ እጅግ ተወዳጅ እና ምስጉን አመራርም እንደነበሩ ዛሬም ድረስ በክለቡ ያለፈ ሁሉ ይመሰክርላቸዋል። በአመራር በክልሉ የስፖርትና የወጣቶች ቢሮ በተጨማሪ በተለያዩ ቢሮዎች አገልግለዋል።

ቦጋለ አበበ 

 

የአዲሶቹ የፌዴሬሸኑ አመራሮች የቤት ሥራ

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ በታቀደለት ጊዜ መከናወን አቅቶት ቆይቷል፡፡ ከውዝግብና ንትርክ አልፀዳ ብሎም ለአራት ጊዜያት ያህል መራዘሙም ይታወቃል፡ ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስቲያ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ባካሄደው ምርጫም መቋጫውን በማግኘት አዲስ ፐሬዚዳንትና የሥራ አስፈፃሚ አባላትን አግኝቷል። አቶ ኢሳያስ ጂራ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
አወዛጋቢ አከራካሪ አለፍ ሲልም አስቂኝ ትዕይንቶችን በማሳያት አንድ ዓመት ሊያስቆጥር ጥቂት ወራት ሲቀሩት መቋጫውን ባገኘው በዚህ የምርጫ ሽኩቻ ምክንያት ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ በብዙ መልኩ ወደ ኋላ ቀርቷል። የአገሪቱ እግር ኳስ ሂደት ትኩረት የነፈጋቸው አብይት ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነትና በመጠን ጨምረው ታይተዋል። በአሁኑ ወቅት በጊዜ ሂደት የስፖርቱ ደጋፊ ከፍ ሲል ስፖርቱ ግን በውጤት እያሽቆለቆለ ሄዷል።
በእርግጥም ለአገሪቱ እግር ኳስ ስፖርት አለማደግ የተለያዩ ምክንያቶችን ማቅረብ ቢቻልም ድምር ውጤቱ ግን ፌዴሬሽኑ በበላይነት ወደሚመራው ሥራ አስፈጻሚ መጓዙም እየቀሬ ነው። ይሁንና የፌዴሬሽኑ የምርጫ ሁነት መቋጫውን በማግኘቱ እነዚህ ችግሮች ተመልካች እንደሚያገኙ ብዙዎች ተማምነዋል።
አዲስ ዘመንም ከወቅታዊ የእግር ኳሱ ገፅታና የተዋናዮቹ አስተያየት በመነሳት አዲሱ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ በቀጣይ ምን የቤት ሥራዎች ከፊቱ ተደቅነውበታል በሚል ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ ታደሰ እንደሚገልጹት፤ አዲሱ የፌዴሬሽኑ አመራር የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት «ያለፈውን መኮነንና ስላለፈው ማውራት ምንም ጥቅም እንደማይሰጥ በመገንዝብ ከዚህ መታቀብ ይኖርበታል፤ ትኩረት መስጠት ያለበትም ደካማው እንዴት ይሻሻል? ምን በጎ ነገሮች ነበሩ? የሚሉትን ጨምሮ መውሰድ ይኖርበታል» ይላሉ።
ከዚህ በተጓዳኝ አዲሶቹ አመራሮች ራዕይ ሊኖራቸው የግድ እንደሚል የሚገልጹት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ አመራር መሆን ብቻውን ለአገሪቱ እግር ኳስ የሚፈይደው አለመኖሩንና መልካምና ጥሩ አጋጣሚዎችን ከራዕይ ጋር በማዛመድ የአጭርና የረጅም ጊዜ እስትራቴጂክ እቅድ ማዘጋጀት ፋይዳው የጎላ መሆኑም ያመለክታሉ።

ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ ታደሰ


በዚህ አካሄድ መጓዝ ካልተቻለም «ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ» ዓይነት ውጤት ከመሆን እንደማይዘል፤ የሚጠቁሙት ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ እውቀትን መሰረት አድርጎ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣትም ከግል ጥረት በተጓዳኝ ከሌሎች የዘርፉ ሙያተኞች ጋር መቀራረብና በጋራ መሥራት እንደሚገባ ያስገንዝባሉ።
«ይህን ለማድረግ በቀዳሚነት የስፖርቱ ሂደት በሰላም መታጀብ ይኖርበታል፣ሰላም ሳይኖር ስለ ስፖርት ልማትና ለውጥ ማውራት አይቻልም» የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ አዲሱ አመራር ለስላማዊ የስፖርት መድረክ ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል ይላሉ፡፡ ይህን ለማድረግም በቀዳሚት ቅጣትን መሰረት ማድረግ ውጤት እያመጣም፤ ይልቅስ የስፖርት ፅንስ ሃሳብን ለባለድርሻዎች ለማስተማርና ግንዛቤ ለመስጠት መትጋት አለበት፤ ወቅታዊና አንገብጋቢው ጉዳይ ይህ ተግባር ነው፤ ይህም በአንድ ቦታ ሳይወሰን እስከ ክልል መዝለቅ ይኖርበታል» ነው ያሉት።
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድሙ አዲሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት በተለይ በአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ ላይ መሰረት ያደረገ ጠንካራ ተግባር ማከናወን እንዳለበት ያስገንዝባሉ፡፡ በእቅድ መመራትም የተጠያቂነት አሠራርን ለመዘርጋት አጋዥ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ይህም የአፍሪካ ዋንጫ ሲደርስ ተጫዋቾችን ከዚህም ከዚያም ማሰባሰብና መራወጥን ማስቆምን ጨምሮ ሌሎች ለውጦችን ማምጣት እንደሚያስችል አመላክተዋል። ይህ ሲሆን «መገናኛ ብዙሃንም ሆነ የስፖርቱ አፍቃሪዎች አሁን ውጤት ውለዱ ብሎ ማስጨነቅ የለባቸውም›› ነው ያሉት።
የኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ አቶ አድማሱ ሳጂ «የእግር ኳሳችን በሁሉም መልኩ እያሽቆለቆለና እየሞተ ነው፤ ተወዳዳሪ መሆንም አቅቶታል፤ ህብረተሰቡም ይህን ውድቀት ደጋግሞ እየገለጸና መፍትሔ ስጡት እያለ በመማፃን ላይ ነው ያላሉ። ለዚህ ምላሽ ለመስጠት የእግር ኳሱን ደረጃና ተወዳዳሪነት ከፍ ማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች መሥራት የግድ እንደሚል ያመላክታሉ።
እንደ አቶ አድማሱ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት እግርኳሱን ወደ ተሻለ ደረጃ በሚያሸጋግር መልኩ እየተሠራ አይደለም። ለውድድር እንጂ ለሥልጠና ትኩረት እየተሰጠ አይደለም። ህግ ደንብና መመሪያዎች በአግባቡ አይተገበሩም። ፌዴሬሽኑ የደንብና መመሪያ ጥሰት ሲፈፅም የሚወስዳቸው ዕርምጃዎችና ውሳኔዎች ወጥነት የጎደላቸው ናቸው። የፌዴሬሽኑ አመራሮች በአንድ ጉዳይ ላይ ያላቸው ግንዛቤም ሆነ እውቅት ውጥና ተመሳሳይ አይደለም።
እነዚህን የአገሪቱ ስፖርት ነቀርሳዎች ታሳቢ በማድረግ አስፈላጊውን መልስ ለመስጠት አዲሱቹ አመራሮች፤ በቀዳሚነት ማህበረሰቡ ለአገሪቱ እግር ኳስ ያለው እይታና ፍላጎት እንዲሁም እግር ኳሳችንን ከዓለም አቀፍ መስፈርትና ደረጃ አንፃር ያለበትን ደረጃ ጠንቅቅው መረዳትና በቂ መረጃ መሰብስብና ማጥናት ይኖርባቸዋል ይላሉ።
ለሁሉም ስኬት አሊያም ለውጥ አጠቃላይ እግርኳሱ የሚመራበትን ስርዓትና መርህ መከተልና ከዓለም አቀፍ ህግጋትና ምስፈርቶች፣ ነባራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ያመለክታሉ። መተግበር ብቻም ሳይሆን ለሚመለከታቸው አካላት የማስገንዘብ ተግባር መከናወን እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
የአገሪቱን እግር ኳስ ለመታዳግና በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የተለመደና ባህላዊ የሆነ የሥልጠና ሂደት ብዙ ርቀት እንደማያስኬድ የሚያስረዱት አቶ አድማሱ፤ ዘመናዊና ሳይንሳዊ የሥልጠና ሂደቶችን ማካተት ጊዜው የሚጠይቅው ተግባር ነው ይላሉ፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ ፌዴሬሽኑ ለሥልጠና የሚሰጠውን ትኩረት ማጎልበትና አካሄዱን ማጤን እንዳለባትም ይጠቁማሉ፡፡
ሥልጠናው በጨዋታና በተጫዋቾች ላይ ብቻ መወሰን አይኖርበትም፡፡ ለአሠልጣኞችና ለዳኞች ለፌዴሬሽንና ክለብ አመራሮችም ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ አድማሱ፤ ለአገሪቱ እግር ኳስ ከባድ ነቅርሳ የሆነው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልን ለመከላከል ለተመሳሳይ ጥፋት ወጥ የሆነ ተመሳሳይ ቅጣት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግና በሚሰጣቸው ውሳኔዎችም ፌዴሬሽኑ ደፋር መሆን አለበት ሲሉም ያብራራሉ፡፡ ይህ ካልሆነ የሚፈለገው ለውጥ ማምጣት አይቻልም ነው ያሉት። እነዚህ ሥራዎችም በርካታ እንጂ ከባድ አለመሆናቸውን በማስገንዝብ ባለድርሻ አካላትም የእነዚህ የለውጥ ሥራዎች ተባባሪና የፌዴሬሽኑ አጋዥ እንዲሁኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት አካዳሚ ዲን ዶክተር ዘላለም መልካሙ በበኩላቸው አዲሱቹ የፌዴሬሽኑ አመራሮች የአገሪቱ ስፖርት አፍቃሪን ፍላጎት መስረት ላደረጉ ተግባራት ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባቸው ያስገነዝባሉ።
እንደ ዶክተር ዘላላም ገለጻምን፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ህመም ላይ ነው። እግር ኳሱን ከህመሙ ለማዳን አዳዲሶቹ ሥራ አስፈፃሚዎች በሰከነ መልኩ ህብረተሰቡ ከለቦችና ሌሎችም የስፖርቱ ተዋናዮች የሚፈልጉትን ማጤን እና ለፍላጎታቸው መሥራት አለባቸው። በተለይ በሥልጠና ሂደት ፕሮጀክቶችን መሰረት ያደረጉና እግር ኳስ በግብዓት በሥልጠና ምን ይፈልጋል የሚለውን ማጤን ይጠይቃል፡፡የስፖርቱ ተዋናዮች ህግና ድንቦችን በአግባቡ ጥንቅቀው የመረዳታቸው አቅም በአቅም ግንባታ ሥልጠና መጠናከር ይኖርበታል። በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት መትጋት አለባቸው፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህር አቶ ተሾመ አጀበው፤ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያደር እየጎላ የመጣው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በመልካም ይሁን በቁጥር መጨመሩን ታሳቢ በማደረግ ፌዴሬሸኑ ቅድሚያ ሥራው ይህን ማስቆም መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ።

አቶ አድማሱ ሳጂ


እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ፤በአሁኑ ወቅት የመከባበርና የወንድማማችነት ምሳሌ የሆነው እግር ኳስ መልክ ባህሪና መገለጫውን ተነጥቋል። የስፖርታዊ ጨዋነት ተጓድሏል። የሜዳ ውስጥ ነውጦች ተለምደዋል። በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት ደጋፊዎች፣ ተጫዋቾች አሠልጣኞች እንዲሁም ሌሎች ለአካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል።
አዲሶቹ የፌዴሬሽኑ አመራሮች፤ በተለይ ለስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት መሥራት እንዳለባቸው የሚያስገንዝቡት አቶ ተሾመ፤ መሰል ክስተቶችን ለመከላከልና ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማጉላት ሌሎች አገራት የቀረፁትን ዘዴና ህግ መመልክትና መቀመር ጠቃሚ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
ወጥነት የጎደላቸው ሚዛናዊ ያልሆኑ ውሳኔዎችን ማስቅረት፤ በተለይ ለስነ ምግባር ኮሚቴዎች ነፃነት መስጠት፤ ውሳኔዎች ከተሰጡ በኋላ የማይሻሩና ተጥንቶባቸው የሚወሰኑ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
የዳኝነት ውሳኔ አሰጣጥ ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓዳል እንዱ ምክንያት እንደ መሆኑ የዳኞችን ውሳኔ አሰጣጥና የጨዋታ መምራት ብቃት ለማጎልበት የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠናዎችን ማዘጋጀት ይገባል ይላሉ። ፌዴሬሸኑ ክለቦችም ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማረጋጋጥ ተጫዋቾቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን የማስተማር ትግባር እንዲያከናውኑ ግፊት ማድረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።
ምሁራኑ የሥራ አስፈፃሚ አባላቱ የሥራ ኃላፊነት ብቻም ሳይሆን መልካም የሥራ ጊዜንም እንዲሆንላቸውም ምኞታቸውን አድርሰዋል።

ታምራት ተስፋዬ

Published in ስፖርት

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ተልዕኳቸውን በመወጣት ለነበሩት ኢንግሊዛውያን ወታደሮች ከአገራቸው ንግስት ለገና በዓል በገጸ-በረከትነት የተላከ ቸኮሌት ከ103 ዓመታት በኋላ ሳይበላሽ እንደተገኘ ቢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ የወሬ ምንጮች በዘገባቸው አመልክተዋል።
እ.አ.አ በ1915 በባለአራት ማዕዘን ጣሳ ውስጥ የታሸገው ቸኮሌቱ ፥ በጦርነቱ ዘመን የገናን በዓል ከአገራቸውና ከቤተሰባቸው ተለይተው በፈረንሳይ ማሳለፍ ግድ ከሆነባቸው የኢንግሊዝ ወታደሮች አንዱ ለሆነው ሪቻርድ ቡሊሞር የተላከ ነበር ተብሏል።
ንግስቲቷ ለአገራቸው ወታደሮች የላኩዋቸው የቸኮሌት ማሸጊያ ጣሳዎች በውስጣቸው አሥር አሥር ቸኮሌቶችን የያዙ መሆናቸውን ዘገባዎቹ ጠቁመው፣ አሁን በተገኘው ጣሳ ውስጥ ከአሥሩ አንድ ብቻ ጎድሎ ዘጠኝ ቸኮሌቶች ሳይበላሹ መገኘታቸውን አስነብበዋል።
ለወታደሩ ከቸኮሌቱ በተጨማሪ በተመሳሳይ የማሸጊያ ዕቃ ሲጋራዎችና ትምባሆም ጭምር መላካቸውን በወታደሩ የህይወት ዘመን የሽልማትና ስጦታዎች ስብስቦች ውስጥ ተካተው መገኘታቸውም ተጠቁሟል። በውጊያ ወቅት ለነበረው ተሳትፎና ለሰጠው አገልግሎት በአገሩ መንግሥት የተበረከቱለት የተለያዩ ሜዳልያዎችም በስብስቡ ይገኛሉ፡፡
103 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረውና ባልዩ ማሸጊያው ቸኮሌት፣ ከቸኮሌቱ ጋር የተላኩለት ሲጋራና ትምባሆ፣ ሜዳልያዎቹና ሌሎች ቁሳቁስ የሚገኝበት የቡሊሞር የስጦታና ሽልማት ስብስቦች፣ በያዝነው ሳምንት በጨረታ ለገበያ እንደሚቀርቡም ተጠቁሟል።
ወታደሩ ሪቻርድ ቡሊሞር ከግዳጁ በኋላ እ.አ.አ በ1916፥ በሃገሩ እንግሊዝ የሰሌስተር ክፍለ-ሃገር የፖሊስ ኃይል አባል ሆኖ አገልግሎ የሱፐር ኢንቴንዴትነት ማዕረግ አግኝቷል። ቡሊሞር እ.አ.አ በ1967 ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱም ተገልጻል።

 

  21ኛ አባሉን በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ቤተሰብ

 

ልጆች የቤ-ሰብ ሀብት፣ የምድር ቆይታ ትሩፋትና የወላጆች ተተኪ ናቸው የሚል ተደጋጋሚ አባባል ይሰማል። ታድያ ይህን አስተሳሰብ በደንብ የተረዱ የሚመስሉ እንግሊዛውያን ባልና ሚስት የትዳር ህይወታቸው 21ኛ ልጅ ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አይ.ኦ.ኤል የተሰኘ አንድ የዜና ምንጭ ጽፏል።

እንደ ወሬ ምንጩ መረጃ ኑዌልና ራድፎርድ የተሰኙ እነዚህ ጥንዶች ከዚህ ቀደም ያፈሯዋቸው 20 ልጆች አሏቸው። ባለፈው ዓመት 20ኛ ልጃቸውን ባገኙበት ወቅት እናት ራድፎርድ የመጨረሻ ልጇን እንደወለደች ብትናገርም፤ አሁን የስምንት ወር ነፍሰ ጡር መሆኗ ታውቋል። ቀጣይዋ የቤተሰቡ አባል ሴት ልጅ መሆኗን በምርመራ መረጋገጡን የተነገረ ሲሆን፤ ባልና ሚስት የመጀመሪያ ልጃውን ካገኙ 30 ዓመት ሊደፍኑ መቃረባቸውም ታውቋል። ባልና ሚስት በእንግሊዝ ቀዳሚ የልጆች ባለፀጋ ቤተ - ሰብ ባለቤት ናቸውም ተብሏል።

በሪሁ ብርሃነ

 

አንድም -ነገር …

«ሰኞ» ሲመጣ- «ሰኞ»
«ማክሰኞ»ም ያው እንደ -ማክሰኞ
ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ…ሲያሰኝ
በዘልማድ ቋንቋ ሲያስጠራ
እሱ ግን …
አንዴም አንድ «ሰኞ»ን «ማክሰኞ»ን
በወስጡ አላበራ!!
ስንት ቀን፣ በቀን፣
ሰንት ዘመን- በዘመን ሲያልቅ
አንድም- ቀን ፣አንድም- ዘመን
ራሱን መልሶ አያውቅም።
«ትናንት»ና - «ዛሬ»ን ሳይሆን
«ዛሬ» ም-«ነገ»ን ሳይመስል
‹‹አምና››ም - ዘንድሮን ሳይሆን
‹‹ዘንድሮ›› ም ‹‹ከርሞ››ን ሳይወክል
ሰኔ‹‹ም›› - ያው ያመቱ ሰኔ
የ‹‹ዘንድሮ›› - ሰኔ ሆኖ ሲያልቅ
አንድም- ‹‹መስከረም›› - ያምና ‹‹መስከረም››
የ‹‹ከርሞ›› ‹‹መስከረም›› ሆኖ አያውቅም።
ስንት ነገር - በነገር
በ‹‹ይለፍ -ይለፍ›› ሲተላለፍ
ስንት ጊዜ - በጊዜ
ዘመን - በዘመን ሲሸራረፍ
ሁሉም - በስም…
በስም እንጂ ሁሉም በስም
አንድም -ነገር ፣ አንድ ዘመን፣
ራሱን መልሶ አያውቅም።

አንድ ቀን የግጥም መድብል ከክፍሌ አቦቸር

Published in መዝናኛ

የልብ ህመም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በስፋት ይታያል፤ ለበርካታ ዜጎች ድንገተኛ ሞት መንስኤ እየሆነ የመጣ በሽታም ነው። ባልተጠበቀ ቅፅበት ህይወትን ሊነጥቅ የሚችል በመሆኑም በሽታው አሳሳቢ የጤና ችግር እየሆነ መምጣቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ 

የልብ ህመም በድንገት ህይወትን ሊቀጥፍ የሚችል ከመሆኑ አኳያ ህብረተሰቡ አስቀድሞ ጤናውን መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ የልብ ህመም እንዳይከሰት ሊደረጉ ስለሚገቡ ጥንቃቄዎችና ህመሙ ከተከሰተ በኋላም ሊወሰዱ ስለሚገቡ የህክምና አማራጮችም ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌና የልብ ህክምና ሰፔሻሊስት ሃኪም ከሆኑት ከዶክተር ስንታየሁ አበበ ጋር ያደርግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዋነኛዎቹ የልብ ህመም አይነቶች የትኞቹ ናቸው?
ዶክተር ስንታየሁ አበበ፡- የተለያዩ የልብ ህመም አይነቶች በሰዎች ላይ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በዋናነት ይታይ የነበረው ከሰዎች የአኗኗር ሁኔታና በጉሮሮ ላይ በሚፈጠር ኢንፌክሽን ምክንያት የሚከሰተው /rheumatic heart disease/ የተሰኘው የልብ ህመም ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የሰዎች የአኗኗር ሁኔታ በመለወጡ፣የስኳርና የደም ግፊት በሽታዎች እየጨመሩ በመምጣታቸውና የሲጋራ አጫሾች ቁጥር በመጨመሩ /iscaemic heart disease/ ወይም የልብ ደም ስር መጥበብና መዘጋት ዋነኛው የልብ ህመም ሆኗል፡፡ ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ሌሎች የልብ ህመም አይነቶችም ያሉ ሲሆን ባጠቃላይ እንዚህ ሶስቱ የልብ በሽታ አይነቶች ሰማንያ በመቶ የሚጠጋውን የልብ በሽታ የሚወክሉ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከባድና የተለመደ የሚባለው የልብ ህመም አይነት የትኛው ነው?
ዶክተር ስንታየሁ አበበ፡- በኢትዮጵያ በተለይም በገጠሪቱ የሃገሪቱ ክፍሎች ህፃናትንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተስብ ክፍሎችን የሚያጠቁት የልብ ህመም አይነቶች ሬሄማቲክ የልብ በሽታ /rheumatic heart disease/ የተሰኙት ቢሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት ግን የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ መለወጥን ተክትሎ፣ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር በመጨመሩ፣ የስኳርና የደም ብዛት በሽታዎች በመጨመራቸው የልብ ደም ስር መጥበብና መዘጋት ዋነኛ የልብ ህመም በሽታ /iscaemic heart disease/ ሆኗል፡፡
አዲስ ዘመን፡-የልብ ህመም ዋነኛ አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ስንታየሁ አበበ፡- በኢትዮጵያ ለልብ ህመም የሚያጋልጡ ዋናዎቹ ምክንያቶች የደም ግፊትና የስኳር በሽታ ፣የሰውነት ክብደት እና በሰውነት ውስጥ የሚገኘው የኮሌስትሮል መጠን መጨመር፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የእድሜ መግፋትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የልብ ህመም ዋነኛዎቹ ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?
ዶክተር ስንታየሁ አበበ፡- የልብ ደም ስር መጥበብና መዘጋት ወይም /iscaemic heart disease/ ዋነኛ መገለጫ ባህሪው በግራ ደረት በኩል ቀስፎ መያዝና የመጫን ስሜት መሰማት ነው፡፡ አንዳንዴ በግራ ትከሻ በኩል ህመሙ የመሰራጨት ባህሪ ይኖረዋል፡፡ ይህ አይነቱ ህመም የሚሰማቸው ሰዎች ላብ ላብ ማለትና ከፍተኛ የድካም ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ እንዲህ አይነቱን የህመም ምልክት ታማሚዎች ሲያዩ ህመሙ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑና ለከፋ አደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል በአስቸኳይ ወደ ህክምና ቦታ መሄድ ይኖርባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የልብ ህመም የሚከሰተው በየትኛው የእድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ነው?
ዶክተር ስንታየሁ አበበ፡- ከጉሮሮ ኢንፌክሽን ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የልብ በሽታ /rheumatic heart disease/ በዋናነት የሚከሰተው እድሚያቸው ከሶስት እስከ አስራ አምስት አመት ባሉ ህፃናት ላይ ነው፡፡ ሁለተኛው የልብ ደም ስር መጥበብና መዘጋት በሽታ /iscaemic heart disease/ በአብዛኛው የሚከሰተው እድሚያቸው ከአርባ አምስት አመት በላይ ባሉ አዋቂ ሰዎች ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-እነዚህ የልብ ህመሞች እንዳይከሰቱ መከላከያ መንገዶቹ ምንድን ናቸው?
ዶክተር ስንታየሁ አበበ፡- በቶንሲልና የጉሮሮ ኢንፌክሽን የሚከሰተውን የልብ ህመም /rheumatic heart disease/ ለመከላከል የቶንሲል ህመም ሲያጋጥም መታከምና ህመሙ ደጋግሞ የሚከሰት ከሆነም በወር አንድ ጊዜ ለህክምናው ሚያስፍልገውን መርፌ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
የልብ ደም ስር መጥበብና መዘጋት ወይም /iscaemic heart disease/ የተሰኘውን የልብ በሽታ ለመከላከል ሰዎች የአኗኗር ዘይቤያቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይም የደም ግፊታቸውንና የስኳር መጠናቸውን በየጊዜው መለካት ይኖርባቸዋል፡፡ በሰውነት ውስጥ የሚገኘውን የኮሌስትሮል መጠን እንዳይበዛ መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ሲጋራ ባለማጨስና ያልተቋረጠ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ በሽታውን መከላከል ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የልብ ህመምን ቀድሞ መከላከል የማይቻልና ህመሙ የሚከሰት ከሆነ የህክምና አማራጮቹ ምንድን ናቸው?
ዶክተር ስንታየሁ አበበ፡- የልብ ህመም ከተከሰተ በኋላ የታማሚውን የህመም ስሜት ለአብነትም ደረት አካባቢ የመውጋት ስሜት የሚያሻሽሉ ህክምናዎች ይደረጋሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዋናው የበሽታ መንስኤ በተለያዩ የህክምና ዘዴዎች እንዲጠፋ ይደረጋል፡፡ ታማሚው ያጋጠመው የልብ ህመም የደም ስር መዘጋት ከሆነ በልብ ደም ስር ውስጥ ቀጭን ቱቦዎችን በማስገባት የተዘጋው የደም ስር እንዲከፈት ይደረጋል፡፡ የልብ ህመምን ለመታከም አማራጮች ቢኖሩም ህመሙ እንዳይከሰት መከላከሉ ግን ወሳኝ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡-በኢትዮጵያ የልብ ህመም ያለበት ደረጃ እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ስንታየሁ አበበ፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በብዛት እየተስተዋለ ያለው የልብ ደም ስር መጥበብና መዘጋት በሽታ /iscaemic heart disease/ ነው፡፡ ቀደም ሲል በአመት ውስጥ በሁለት ወይም በሶስት ሰዎች ላይ የሚከሰት የልብ ህመም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የህብረተሰቡ የአኗኗር ሁኔታ መቀየሩን ተከትሎ በሽታው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የልብ ህክምና የደረሰበት ደረጃ ምን ይመስላል?
ዶክተር ስንታየሁ አበበ፡- በኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተሻለ የልብ ህመም ህክምና ለማግኘት ፈተና ነበር፡፡ የልብ ምትን ከፍ ለማድረግ የልብ ባትሪ ለማስገባትም አስቸጋሪ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የልብ ምት ባትሪ በነፃ ለታማሚዎች እየተገጠመ ይገኛል፡፡ በውጪ ሃገር ህክምናቸው የሚካሄዱ የልብ ህመሞች ሙሉ በሙሉም ባይሆን በአብዛኛው በሀገር ውስጥ እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ የሚቀረው ክፍት የልብ ቀዶ ህክምና ብቻ ቢሆንም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ብዛት ያላቸው የልብ ቀዶ ህክምና ባለሞያዎች መሰልጠን በመቻላቸው እስካሁን 20 የሚሆኑ የልብ ቀዶ ህክምናዎችን በእነዚሁ ኢትዮጵያውያን የልብ ቀዶ ህክምና ባለሞያዎች በተሳካ ሁኔታ ማድርግ ተችሏል፡፡ በቀጣይም በነዚህ ሃኪሞች የልብ ቀዶ ህክምናው በተጠናከረ መልኩ የሚከናወን ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የልብ ህክምናን አስቸጋሪ የሚያደርገው ምንድን ነው?
ዶክተር ስንታየሁ አበበ፡- የልብ ህክምናን አስቸጋሪ የሚያደርገው ለህክምናው የሚውሉት መሳሪያዎች ውድ መሆናቸውና እንደለብ አለመገኘታቸው ነው፡፡ በመንግስት ሁሉንም የህክምና መሳሪያዎች መሸፈንም አስቸጋሪ ነው፡፡ በዘርፉ እየሰለጠኑ ያሉ ባለሞያዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያያዞ ግን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይም ዜጎች በጤና መድህን ስርዓት ውስጥ የሚገቡ ከሆነ መንግስት አለም አቀፍ ጨረታዎችን በማውጣት ከውጪ ድርጅቶች የልብ ህክምና መሳሪያዎችን በቀላሉ መግዛት ያስችለዋል፡፡ በመሆኑም የጤና መድህን ስርዓቱ መጠናከር ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡
ዶክተር ስንታየሁ ፡ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

 

Published in ማህበራዊ

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በስነ ህይወት እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በተቋም ሥራ አመራር ይዘዋል፡፡ ወደ ሥራው ዓለም በመጀመሪያ የተሰማሩት በመምህርነት ሙያ ሲሆን፣ ከዚያም የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ፣ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ፣ የደቡብ ጎንደር ዞንና የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ የፌዴራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከህዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኮሚሽነርነት እየመሩ ይገኛሉ -ኮሚሽነር አየልኝ ሙሉዓለም፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኮሚሽኑን የማስተማር፣ የመከላከልና ሀብት የማስመዝገብ እንቅስቃሴንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከእርሳቸው ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ቀደም ባሉት ዓመታት በስነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ትምህርትና ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ የሙስና ወንጀሎችን በመመርመርና ክስ በመመስረት ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የትኩረት አቅጣጫውን ሀብት ማስመዘገብ፣ ትምህርት መስጠት እንዲሁም መከላከል ላይ አድርጓል፡፡ ይህን ተግባር ብቻ ማከናወኑ ተቀባይነቱን ዝቅ አድርጎት ይሆን ?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- እንደተባለው ቀደም ሲል ኮሚሽኑ ሲንቀሳቀስ የቆየው ሦስት ዓላማዎችን ይዞ ነበር፡፡ የመጀመሪያው በወንጀል እና በሙስና የተጠረጠሩ ሰዎችን መመርመር ነው፤ በሁለተኛ ደረጃ ይከስ ነበር፤ ሦስተኛው ደግሞ የመከላከል ስልጠናና የሀብት ምዝገባ ሥራ ነው፡፡ ከ2008 ዓ.ም በኋላ ግን መንግሥት የአገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ በመከላከሉ ላይ አተኩሮ ቢንቀሳቀስ ውጤታማ ይሆናል በሚል የአደረጃጀት ለውጥ ተድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት የምርመራና የክስ ጉዳይ ለዓቃቤ ሕግና ለፖሊስ አካላት እንዲሆን ተድርጓል፡፡ ይህ ግን በተወሰኑ አካላት ዘንድ የኮሚሽኑን ተቀባይነት አሳንሶታል የሚል አመለካከት እንዲያድር አርጓል፡፡ በተቋሙ ባሉ ሠራተኞችም ሆነ ከተቋሙ ውጭ ባለው ህብረተሰብ ዘንድም ‹‹ኮሚሽኑ ካልመረመረና ካልከሰሰ ምን ትርጉም አለው፤ በጥቅሉ ስልጣኑን ተቀምቷል፤ ፈዟል›› የሚል አመለካከት መመጣቱን እኛም ተረድተናል፡፡
ይህ የሚያሳየው በአገሪቱ የግንዛቤ ችግር መኖሩን ነው፡፡ ለሙስና ያለው አመለካከት የተዛባ ነው፡፡ ትልቁ ነገር ህብረተሰቡም ሆነ ባለስጣናቱ ሙስናን እንዲጠየፍ ማድረጉ ሥራ ላይ ነው፡፡ በጥቅሉ ትውልዱ ጥሮ ግሮ በወዙና በላቡ መተዳደር የሚያስችል ሀብት ማግኘት እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ ይህን አመለካከት ካላዳበርን በስተቀር በየስርቻው፣ በየአገልግሎት መሰጫ ጣቢያና በየአቅጣጫው የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎችን እየከሰስን በማስቀጣት ሙስናን መከላከልና መቆጣጠር አንችልም፡፡
ስለዚህ ትኩረታችን ማስተማር ላይ ነው፡፡ መሆን ያለበትም እሱ ነው፡፡ ዋነኛ ሥራችን ሙስናን መሸከም የማይችል ህብረተሰብ መፍጠር ነው፡፡ ይህንን የመከላከል ሥራችንን ውጤታማ ሊያደርግልን የሚችለው ደግሞ ሁኔታዎች ለሙስና ተጋላጭ እንዳይሆኑ በመሥራት ነው፤ ህብረተሰቡ ንቃተ ህሊናው አድጎ በሲቪክ ማህበራት ተደራጅቶ ሙስና እንዳይፈፀምና ተፈፅሞ ሲያገኝም ተጠያቂ የሚያድረግበት አሰራር ማጠናከርን ነው፡፡
መንግሥት ‹‹እንክሰስ›› ብሎ እስካሁን የተከሰሱትን ብትቆጥሪያቸው ሙስና ይፈፀማል ተብሎ ከሚጠበቀው አኳያ ሲታይ ዜሮ ነጥብ ዜሮ ዜሮ አንድ ቢሆን ነው፤ በመሆኑም መክሰስ የሚቻለው በጣም ጥቂቱን ነው፡፡ ሙስና ደግሞ በምስጢር የሚፈፀም ነገር ስለሆነ በባህሪው ድብቅ ነው፡፡ ከሰሽም መረጃውን አግኝተሸ የምታስቀጪው በጣም ውስን ነው፡፡ ስለዚህ ትልቁ ሥራ ሙስና የማይሸከም ህብረተሰብ መፍጠሩ ላይ ነው፡፡ ኮሚሽኑም ይህን ተልዕኮ ወስዶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በእርግጥ ካኃለፊነቱ የተወሰነው መወሰዱ ሙሉ ለሙሉ ተጽዕኖ የለውም ማለት ግን አይደለም፡፡ ይሁንና ትልቁን ኃላፊነት ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሀሰተኛ ሰነዶች የሚያስከ ትሉት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች አሉና በዚህ ላይ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ምን እየተሰራ ነው?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- ሀሰተኛ ሰነድ እንደተባለው በዋጋ ያልተገመተ ጥፋት አስከትሏል፤ እያስከተለም ነው፡፡ ይህ ጉዳይ እስከ ህክምና ተቋማት ድረስ በመዝለቅ ‹‹ሀኪም ነኝ›› በሚሉ ወገኖች ውዱ የሰው ልጅ ህይወት እስከ መፈተን ደርሷል፡፡ በሕግ በኩል ደግሞ በፍትህ አካላቱ የተፈረደባቸው ታራሚዎች በሀሰተኛ ሰነድ ከእስር ቤት እየተለቀቁ ነው፡፡ በመማር ማስተማር ሂደቱም መምህራን ምንም አይነት ማስረጃ ሳይኖራቸው በመምህርነት ተቀጥረው በመሥራታቸው የትውልድ ህይወት ጥያቄ ውስጥ እየገባ ነው፡፡
ስለዚህ በዚህ ዓመት በአጠቃላይ የፀረ ሙስና ቀን ተብሎ በዓለም ደረጃ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ይህን ጉዳት በመመዘንና በአገራችንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ በመሆኑ ግንዛቤ መፍጠር አለብን በሚል ይህንን እንደ መሪ ሐሳብ አድርገን በሁሉም ክልሎች ግንዛቤ እንዲፈጠርበት በማድረግ ላይ ነን፡፡
ይህ እንቅስቃሴ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተካሄደ ነው፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት በሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም የተቀጠሩና የደረጃ እድገት ያገኙ ሰዎች ካሉ እያንዳንዱን ሰነድ በመፈተሽ የማጥራት ሥራ እንዲሰሩ እንደ አገር አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራበት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ደግሞ በሀሰተኛ ሰነድ የተጠቀሙም ራሳቸውን እንዲያጋልጡ ዕድል እንዲሰጣቸው ተደርጎ ራሳቸውን ያጋለጡ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በዚህም ምክንያት ከእስርና ከመባረርም ድነዋል፡፡ ራሳቸውን ባላጋለጡ አካላት ላይ መረጃው ተጣርቶ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተደርጓል፡፡
ስለዚህ በአንድ በኩል ግንዛቤ በመፈጠሩ ከበርካታ ሰዎች ‹‹እከሌ እኮ መረጃ የለውም›› የሚሉ ጥቆማዎች በብዛት እየመጡ ናቸው፡፡ ለኮሚሽኑ የሚደርሱ ጥቆማዎችን ለማጥራትም ሰፊ ሥራ ይከናወናል፡፡ በዚህም ረገድ ትክክለኛ ሆነው የተገኙ መኖራቸውን ማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑም እያስከተለ ባለው ጉዳት ላይ ግንዛቤ በተፈጠረው መሰረት አሁን በህብረተሰቡ ውስጥ ትግል ተጀምሯል፡፡
አንዳንድ የትምህርት ተቋማት አንድ ተማሪ ቀሪ ባለመሆኑ አሊያም የመማሪያ ገንዘብ ብቻ በመክፈሉ ወረቀት ይሰጡታል፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ሌላው ደግሞ በተቋሙ ሳይገኝ ገንዘብም ሳይከፍል በየጉራንጉሩ ሆኖ የመመረቂያ ወረቀት ይሰጠዋል፡፡ እነዚህን መሰል ችግሮች ከመሰረቱ ለማቃለል እየተሰራ ነው፡፡ እንቅስቃሴያችን በአብዛኛው እየተገበርን ያለነው በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆን፣ የግሎቹ ደግሞ በአብዛኛው ማህበር አላቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ እስካሁን በሰጠው ትምህርትም ሆነ ስልጠና ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመከላከሉ ረገድ በአሰራሩ ላይ የተፈጠረ ግልፅነትና ተጠያቂነት ይኖር ይሆን?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- የግንዛቤ ፈጠራውም ሆነ የመከላከል ሥራው በአጠቃላይ ከ2008 ዓ.ም በኋላ ሙሉ ለሙሉ ኮሚሽኑ በክስና ምርመራ ላይ የሚወስደው ጊዜ በጣም ሰፊ ስለነበረ ዋና ሥራና ተልዕኮው ማሰተማር ላይ ያድርግ ተብሎ በ2008 ዓ.ም ላይ ተደረገ እንጂ ከዛ በፊትም ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡
እስካሁን በተከናወነው ተግባር ምን ውጤት አስመዘገባችሁ ላልሽው በቀጣዩ ዓመት አንድ ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን፡፡ እንዲህ አይነት ጥናት ከሰባት ዓመት በፊት ተካሂዷል፡፡ በመሆኑም በቀጣዩ ዓመት የተሟላ መረጃ ይኖራል፡፡ አሁን ለጊዜው ግን ከየክልሉ ካሉ ተመሳሳይ ተቋማት ጋር በመሆን ምንድን ነው የተገኘው ውጤት የሚለውን ለመገምገም ሞክረናል፡፡ ከዚህም ማስተዋል የቻልነው በሁለትና ሦስት አመልካቾች በተለይ በሙስና ትግሉ ዙሪያ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን ነው፡፡
አንደኛው ህብረተሰቡ በሚሰጠው ጥቆማ ሁኔታዎችን መረዳት ችለናል፡፡ ከዚህ ቀደም የሚጠቁመው ስለተጣላ ይሆናል፡፡ አሁን ግን ከዚያ አይነት አመለካከት ወጥቶ እውነተኛ በሆነ መንገድ ‹‹የህዝብና የመንግሥት ሀብት ተመዝበሯል›› የሚል መረጃ እያደረሰ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ሙስና ሊፈፀም ነው፤ ድርድር እየተካሄደ ነው›› ተብሎ የሚደርሰንን ጥቆማ መሰረት አድርገን የምናከናውናቸው ጥናቶችና ግምገማዎች አሉ፡፡ በዚህም በርከት ያሉ ጥቆማዎች እንደሚያመለክቱት ሙስናን ለመከላከል በተቋሙ ሠራተኞችም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ መልካም ጅምሮች እንዳሉ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አንዳንድ ጉዳዮች ሲታዩ ሙስና የልማት እንቅስቃሴን እያዳከመ ነው ፡፡ ስለዚህም ጉዳዩ በትኩረት መፈተሸ አለበት የሚል አስተያየት በየመድረኩ ይንፀባረቃል፡፡ ሙስና ያልተገባ ግጭት እንዲፈጠርና ህዝቦች እርስ በእርስ ተከባብረው እንዳይኖሩም እንቅፋት መሆኑ በመታወቁ የማጋለጡ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይህን ለውጥ ያመጣው በተከታታይ የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ነው ብልን እንወስዳለን፡፡
በሦስተኛ ደረጃ በተጠያቂነት ላይም ቢሆን ጥቂት ይሁኑ እንጂ በየክልሉ የተጠየቁ ሰዎች አሉ፡፡ ባለፈው ጊዜ ባቀረብነው ሪፖርት በግምት ወደ 340 ሚሊዮን ብር ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ ተደርጓል፡፡ 97 ሚሊዮን ብር ደግሞ በአስቸኳይ መከላከል እንዲድን ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ኢኮኖሚውም ከመስፋቱ ጋር ተያይዞና አሰራሮችም ውስብስብ በመሆናቸው የተነሳ እኛ እያደረግነው ያለው የማስተማርና የመከላከል ሥራ የተፈለገውን ያህል ውጤት አምጥቷል ማለት አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ይህ የሆነበትም ምክንያት ጉዳዮች አፋጣኝ ምላሽና ውሳኔ ማግኘት እንዲችሉ ነውና በእስካኑ ሂደት አፋጣኝ ምላሽ የተሰጠባቸው ጉዳዮች ይኖሩ ይሆን?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደሞከርኩት ሥራችን በአብዛኛው ማስተማርና መከላከል ነው፡፡ በመሆኑም በየጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንድናገኝ የሚያደርገን ሥራ የለም፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ግን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር በቅርበት ይሰራ እንደነበር መረጃው አለኝ፡፡
ይሁንና አሁን አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር በሁለት ጉዳዮች ላይ ለማነጋገር ቀጠሮ ይዤያለሁ፡፡ አንዱ የሀብት ምዝገባን በተመለከተ ነው፡፡ ሀብት በትክክል ስለመመዝገቡ ኮሚሽኑ የማረጋገጥ ስልጣን ቢኖረውም እስካሁን አልተሰራበትም፡፡ በቀጣይ መሥራት ይኖርብናል፡፡ ህዝቡም የተመዘገበው እውነት ነው ወይ የሚለውን ማወቅ እንዲችል ይረዳዋልና በዚህ ላይ ግን የመንግሥት ቁርጠኝነት እንዲኖርና እንዴት እንሂድበት የሚለውን ለመነጋገር እፈልጋለሁ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እርሳቸው የሚሰጡንን አቅጣጫ ተግ ባራዊ ለማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ በምን መልኩ ልንደግፋቸው እንደምንችልም መነጋገር እንፈልጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመዋጋት በምታደርጉት የመከላከል ሥራችሁ ላይ ምን ተግዳሮት አጋጥሟችሁ ያውቃል?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- በጣም አለ፤ በምናስተምርበት ጊዜ ህብረተሰቡ ከትምህርቱ ይልቅ ፍላጎቱ ሙስና የፈፀመ ሰው እንዲታሰር ነው፡፡ ኮሚሽኑ በማስተማር ሥራው ላይ ብቻ በማተኮሩ በሰዎች ዘንድ ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታ ይታያል፡፡ ሌላው ደግሞ በእኛም በኩል ችግር አለ፡፡ ለምሳሌ የምናሰተምርባቸው መሳሪያዎች የቆዩ ከመሆና ቸውም በላይ በተደጋጋሚ የተጠቀ ምንባቸው በመሆ ናቸው የማስ ተማር ሥራዎ ቻችንን ውስን እንዲሆን አድርጎታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አን ዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች የኮሚሽኑን የሥራ ኃላፊነት በወጉ ካለመረዳ ታቸው የተነሳ እንደቀድሞው እየ መሰላቸው ጥቆማዎችን ሊያደርሷችሁ ይችላሉ፤ ሙስና ከመሰራቱም በፊትም በመከላከል ረገድ እንዲሁ የሚደርሳችሁ ጥቆማ ይኖ ራልና ተቀብሎ ፈጣን ምላሽ በመስጠት በኩል ምን ያህል ውጤታማ ናችሁ?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- ሙስናን ከመከላከል አኳያ የሚመጣው ሁለት አይነት ጥቆማ ነው፡፡ ሙስና ገና ሳይፈፀም ‹‹ሙስና ሊፈፀም ይችላል›› በሚል በተለይ በግዥና ጨረታ ላይ ጥቆማ ሊደርሰን ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ጉዳዩን እናጣራና ችግር አለበት ተብሎ ለተጠቆምነው ተቋም እናሳውቃለን፡፡ የደረሰን መረጃ ትክክለኛ ከሆነ ደግሞ ለምሳሌ ጉዳዩ ጨረታ ከሆነ ጨረታው እንዲቋረጥ እናደርጋለን፡፡ አሊያም ያለው ሥጋት እንዲስተካከል እናደርጋለን፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሙስና ተፈፅሞ ከሆነ ደግሞ በመሸኛ ደብዳቤ ወደ ፖሊሰ እንልካለን፡፡
ሙስና ገና ሳይፈፀም ሊፈፀም ነው ተብሎ ለሚመጣው ጥቆማ ምላሽ እንሰጣለን፡፡ በዚህ ረገድ ያዳነውም አለ፡፡ ይሁንና ሙሉ ለሙሉ ችግሩን ለማስወገድ ተንቀሳቅሰናል የሚል ድፍረት የለንም፡፡ በተለይ ፈጥነን ያለመድረስ ችግር አለብን፡፡ ህብረተሰቡም የሚሰጠውን ምክረ ሐሳብ ያለመቀበል ችግር አለ፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት የአቅም ውስንነት ነው፤ የባለሙያ ችግርም አለብን፡፡ ጉዳዩን አይቶና አጣርቶ እንዲሁም በተገቢው መንገድ መዝኖ ውሳኔ በመስጠት ረገደም እጥረት አለ፡፡
ከዚህ ቀደም ጥሩ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ከምርመራ ሥራው ጋር ሄደዋል፡፡ ምርመራና ክስ ወደሚመለከተው በሚሄድበት ጊዜ ‹‹ኮሚሽኑ የሚፈለግ አይደለም›› በሚል ፍራቻ በርካታ ሠራተኞች ተቋሙን ለቀዋል፡፡ አሁን አዳዲስ ሠራተኞች ናቸው በማሰልጠን ላይ የምንገኘው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ ለመፍጠር በርካታ አጫጭር መልዕክቶች ወደ ህዝቡ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ በእነዚህ ማስታወቂያዎች ለውጥ መጥቷል ተብሎ ይታሰባል?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በምናገኘው አስተያየት የምናስተላልፈው መልዕክት ማስተላለፍ ከፈለግነው ዓላማ ጋር ግንኙነት ቢኖረውም በሌላ ይዘቱ ደግሞ የሚነካው ጉዳይ በመኖሩ ብታስተካክሉ መልካም ነው የሚል ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ደግሞ መልዕክቶቹ አስተማሪ ስለመሆናቸው ይገልፁልናል፡፡ ወደ በርካታ ህብረተሰብ በመድረስ ላይ እንደሆነም ይነግሩናል፡፡ ነገር ግን ምን ውጤት አመጣ የሚለውን ከምንሰማው አስተያየት ውጭ የተካሄደ ጥናት የለም፡፡ በቀጣይ እንሰራበታለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በሙስና ምክንያት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ አካላት ክሳቸው ተቋርጦ ነፃ እንዲሆኑ መደረጋቸው ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲስፋፋ የሚያደርግ አካሄድ ነው የሚሉ አንዳንድ አካላት አሉና በዚህ ላይ የኮሚሽኑ አስተያየት ምንድን ነው?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- መንግሥት በተለያየ ወንጀል የታሰሩ ሰዎችን በመልቀቅ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ነገር ይታይበታል፡፡ ከዚህ አኳያ የሄደበትን መንገድ እናደንቃለን፡፡ ለምሳሌ በወቅቱ በነበሩ አመፆች በተለያየ ወንጀል ተሳትፈው የታሰሩ አካላት መኖራቸው ይታወሳል፡፡ ለዚህ አመፅ መቀሰቀስ ደግሞ መንግሥት የእርሱ ድርሻ እንዳለበት አልካደም፤ በተለይ ዴሞክራሲን በማስፋፋቱም ሆነ በተፈጠረው የመልካም አሰተዳደር ችግር መሥራት የተገባውን ያህል አለመሥራቱን አምኗል፡፡ ለይቅርታ የበቃውም ህዝብ ተበድሏል በሚልም ነው ማለት ይቻላል፡፡ መንግሥት ሥራውን ባለመሥራቱ ምክንያት በተፈጠረ አመፅና የአስተሳሰብ ልዩነት ወንጀል ሰርተዋል የተባሉ ሰዎችን አፍኖ ማስቀመጥ ትክክል አይደለም ብሎ ስላመነ መፍታቱ ልክ ነው፡፡
ከሙሰኞቹ አኳያ እንደ ኮሚሽኑ አስተሳሰብ ለየት ያለ አተያይ ነው ያለን፡፡ ሙስና የፈፀሙ ሰዎች ይቅርታ ማድረግ የመንግሥት ስልጣን ቢሆንም መፈታት አለባቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ መለቀቅም ካለባቸው ትክክለኛውን ሂደት ጠብቀው በሕግ መሆን ነበረበት፡፡ ነገር ግን መንግሥት ደግሞ የገመገመበት ጉዳይ ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንዳንዱን ኬዝ ወስደን ስንመለከት አምስት ዓመት ሙሉ ያለአንዳች ውሳኔ የተቀመጠ ይኖራል፡፡ መንግሥት ውሳኔ ባለመስጠቱ ምክንያት ታሰረዋል፤ ማዘግየታችን ደግሞ የፍትህ ሥራዓችን ድክመት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው፡፡ የተፈረደባቸው ቢሆኑ ኖሮ አይደለም አምስት ዓመት አስርም ዓመት ቢሆን ችግር የለውም፡፡ ስለሆነም ውሳኔው ያለፍርድ ይህን ያህል ዘመን ማሰራችን በራሱ ቅጣትም የመንግሥትም ድክመት ነው ከሚል እይታ የመነጨ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ ፡፡
ከዚህ ውጭ ግን ሙሰኛ ምንጊዜም ቢሆን ሙሰኛ ነው፡፡ ከህዝቡም አካባቢ የተደመጠው አስተያየት ልክ ነው፡፡ አንዳንዱ እጅ ከፍንጅ ሲያዝ አንዳንዱ ደግሞ እንደሱ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህን የሚያጣራው ግን ፍርድ ቤት ነው፡፡ ገንዘብ በቤቱ ያልተገኘበት ሙሰኛ አይደለም ሊባል አይችልም፡፡ ይሁንና በህዝቡ እይታ ገንዘብ በቤቱ የተገኘበትና ያልተገኘበት ዕኩል ሊመዘን አይችልምና የተለያየ አስተያየት ማንፀባረቁ ልክ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ እየሰጠ ያለው ትምህርት እንደሚታወቀው በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ አካላት ሙስና እንዳይሰሩ ለመከላከል ነውና የትምህርት አሰጣጡ እንዴት ነው እየተተገበረ ያለው?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- የትምህርት አሰጣጡ የሚገለፀው በተለያየ መንገድ ነው፡፡ አንደኛ ኤሌክትሮኒክስና የህትመት ሚዲያን እንጠቀማለን፡፡ በተለያዩ ብሮሸሮችም ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን እንሞክራለን፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ ክልሎችና ተቋማት ለተውጣጡ የአሰልጣኞች ስልጠና እንዲሁም ለባለሙያዎች ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ ከዚህ ውጭ የኃይማኖት ተቋማትንም በመጠቀም እንሰራለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባ እድሳት እንደሚያደርግ እየተገለፀ ነው፡፡ የሀብት ምዝገባው የመጀመሪያው መረጃ ለህዝብ በአግባቡ ይፋ ባልሆነበት ሁኔታ አሁን ደግሞ እንደገና ምዝገባ ማስፈለጉ ምን ይጠቅማል ይላሉ?
ኮሚሽነር አየልኝ፡ እንደሚታወቀው የሀብት ምዝገባው አንዴ ብቻ ተከናውኖ አያቆምም፡፡ ሠራተኛውም ሆነ የሚሾመውም አካል ይቀያየራል፡፡ በመሆኑም በተቀያየረ ቁጥር ሀብት ይመዘገባል፡፡ ሌላው ደግሞ ምዝገባው በአዋጁ መሰረት በየሁለት ዓመቱ መታደስ አለበት፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የነበረው ሀብት ከዛሬ ጋር ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የተቀየረ ነገር ካለ ሀብቱን ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ እንዲያም ሆኖ ወጪው ከባድ በመሆኑ በየሁለት ዓመቱ ማደስ አይቻልም በሚል የማሳደሱን ሥራ ትንሽ ለማቆየት ታስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን አዋጁም ስላልተሻሻለ እኛ ያሰብነው በዚሁ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለመቀጠል ነው፡፡ ወደ ማዳሱ ሥራ ለመግባት አቅጣጫ አስቀምጠን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ሁለት ዓመትና ከዛ በላይ የሆነው ሰው ሁሉ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ምዝገባው ይታደሳል ፡፡ አዲስ መመዝገብ ያለባቸው ደግሞ እንዲመዘገቡ እናደርጋለን፡፡
ቀደም ሲል የተመዘገበው ሀብት ህዝብ እንዲያውቀው ይደረጋል የተባለው አካሄድ አሁን ላይ እንዴት ነው የሚሆነው ላልሽው አዋጁ ላይ የግለሰብ መብት መጠበቅ እንዳለበት ያመለክታል፡፡ እንዲያም ሆኖ ደግሞ አዋጁ በሌላ በኩል ግልፅ እንዲሆን ይፈቅዳልና ይህ ግን በምን መንገድ ነው ይፋ መሆን የሚችለው የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ነው፡፡ ነገር ግን መረጃውን በኮምፒውተር መረብ በማስተሳሰር የሚፈልገው አካል ማየት እንዲችል የማድረጉም ነገር ታስቧል፡፡ በእርግጥ ይህ ደግሞ ተቋሙ አሁን ባለው የቢሮ ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ ይህ ራሱ ችግር ሆኗል፡፡ ይሁንና የቢሮው ምቹነት ከተጠናቀቀልን ህዝቡም ማወቅ ይፈልጋልና በርካታ ባለስልጣናትም በጥቂቶች ምክንያት ስማችን አብሮ መነሳት የለበትምና ይፋ ይደረግልን በማለት ላይ ናቸውና ይፋ መሆኑን እኛም እንመርጣለን፡፡ በቀጣይ ዓመት የቢሮው ሁኔታ ምቹ ከሆነ አንድ አስር አስራ አምስት ኮምፒውተሮችን በመዘርጋት ማንኛውም አካል ማየት እንዲችል ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከፌዴራል ዓቃቢ ሕግ ጋር ያላችሁ የሥራ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- እኔ ከመጣሁ በወራት የሚቆጠር ጊዜ ነውና አንድ ጊዜ በሥራ ጉዳይ ተወያየተን አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡ አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ሌሎች ጉዳዮችም ስለነበሩ በተለይ እነሱን የሥራ ውጥረት ውስጥ ከቷቸው በመሰንበቱ የተፈለገውን ያህል ግንኙነት አልፈጠርንም፡፡
በእርግጥ የፀረ ሙስና ትግሉን የምናሰተባብረው እኛ ነን፡፡ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ እንዲሁም የዓለም የፀረ ሙስና ተቋማት ህብረት አባል አባል ናት፡፡ የምትወከለውም በኮሚሽኑ ነው፡፡ የክስ፣ የምርመራ፣ የመከላከል፣ የሀብት አያያዝ ጉዳዮች ሁሉ በኮሚሽኑ ነው የሚገመገሙት፡፡ ይህን የተሟላ መረጃ ደግሞ ኮሚሽኑ ለእነሱ መስጠት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከክልል ተመሳሳይ ተቋማት ጋርስ ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ኮሚሽነር አየልኝ፡- ዓመታዊ ዕቅድ በጋራ እናዘጋጃለን፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ስንገናኝ በአፈፃፀሙ ላይ ግምገማ እናካሂዳለን፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱ የሙስና ትግል ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው፤ እንዴትስ እየተመራ ነው የሚለውን እንደ አገር እንወያይበታለን፤ እንገመግማለን፡፡ የሙስና ትግሉ በምን መንገድ እየሄደ እንደሆነና ምን ውጤት እያስገኘ እንደሆነ እንዲሁም ያሉበት ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑ በጋራ እንገመግማለን፡፡ ክልሎቹ የእኛን ድጋፍ በአብዛኛው የሚፈልጉት ከአቅም ግንባታ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ያንንም እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከልብ አመሰግናለሁ።
ኮሚሽነር አየልኝ፡- እኔም አመሰግናሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

Published in ፖለቲካ

እልም አለ ባቡሩ
እልም አለ ባቡሩ
ወጣት ይዞ በሙሉ…በመባል ይቀነቀን የነበረውን የጥንቱን ሙዚቃ ብዙዎቹ ያስታውሱታል፡፡ በወቅቱ ዘመናዊ በሆነው ባቡርም በርካታ ወጣቶች ሽር ብትን ብለውበታል፡፡ ዛሬ ደግሞ ቴክኖሎጂው በወለደው ባቡር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ሽው እልም እያለ በመጓጓዝ ላይ ያለው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ ያለውን፣ በአርሶ አደሩ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያተረፈውንና በጉጉት የሚጠበቀውን አንድ ወሳኝ ግብአት ማጓጓዝ ጀምሯል፡፡ - የአፈር ማዳበሪያን፡፡
በአሁኑ ወቅት የመኸር እርሻ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ከዝግጅት ምዕራፉ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው መሬት ሲሆን፣ 12 ነጥብ ሰባት ሄክታር ለመኸር እርሻ ተሰናድቷል፡፡ ለዚህ ሥራ በግብዓትነት ከሚያስፈልጉት መካከል አንዱ ማዳበሪያ እንደመሆኑ ግዥው መቶ በመቶ ተጠናቆ የማጓጓዙ ሥራ ላይ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት ግብይት ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ አሰፋ እንደሚሉት፤ በ2010/2011 በጀት ዓመት ወደ አንድ ሚሊዮን 350 ሺ ሜትሪክ ቶን ማለትም 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያዎች ግዥ ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ ቀደም ከጅቡቲ ወደብ የተለያዩ ሸቀጦችን ይዘው የሚከንፉ ተሽከርካሪዎች የሸቀጥ ምልልሱን ለጊዜው ገታ አድርገው ለማዳበሪያ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያ ጓጉዙም ተደርጓል፡፡ የፌዴራል ትራንስፖርት ባሥልጣን ቢያንስ በየቀኑ ከ420 ያላነሰ መኪና ከጅቡቲ ወደብ ማምጣት እንዳለበትም አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡
ዘንድሮ ልዩ የሚያደርገው የማዳበሪያ ምልልሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሌላ አማራጭ መጠቀም መቻሉ ሲሆን፣ ይኸውም በባቡር እንዲጓጓዝ መደረጉ ነው፡፡ ባቡሩ በአንድ ጊዜ ይዞ የሚመጣው 70 መኪናዎች የሚጭኑትን ማዳበሪያ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ማዳበሪያው አርሶ አደሩ እጅ የሚገባበትን ጊዜ የሚያፋጥነው መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መንገድ ባቡሩ በሳምንት ሁለቴ ከተቻለ ደግሞ ሦስቴ ባቡሩ እንዲያጓጉዝ በማድረግ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ብርሃኑ እንደሚሉት፤ የትራንስፖርት እጥረት እንዳይኖር ለማድረግ ባቡርን በአማራጭነት መጠቀም በመቻሉ ቀድመው የሚዘሩ አካባቢዎች የማዳበሪያ እጥረት አያሳስባቸውም፡፡ በተለይ ደግሞ የከረመ ከሁለት ሚሊዮን ኩንታል የማያንስ የአፈር ማዳበሪያ በመኖሩ ፈጥነው ለሚዘሩ አካባቢዎች ስጋት አይፈጠርም፡፡ አሁን ለመኸር እርሻ የተያዘው እቅድ ወደ 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ሲሆን፣ ለስኬታማነቱም የማዳበሪያው በወቅቱ አርሶ አደሩ ዘንድ መድረስ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
እርሳቸው እንደተናገሩት፤ ለዘንድሮው ማዳበሪያ ግዥ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ነው ሲንቀሳቀስ የቆየው፡፡ የግዥ ጨረታውም የተጠናቀቀው ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ በማዳበሪያ አቅርቦት በኩል ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳይፈጠርና ክፍተትን ለመዝጋት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው፤ ማዳበሪያው ወደብ ከደረሰ በኋላ ዩኒየኖች እንደሚረከቡት ይናገራሉ፡፡ ዩኒየኖቹ በተቀመጠላቸው ኮታ መሠረትም አንዳንዶቹ ከወደብ ሌሎቹም ደግሞ ከአዳማ ማዕከላዊ ጣቢያ በመረከብ በየክልሉ፣ ዞን፣ ወረዳና አርሶ አደሩ ወደሚገኝበት የተለያዩ ጣቢያዎች ያደርሳሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የማጓጓዙ ሥራ ላይ እስካሁን የገጠመ ችግር የለም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ቀደም ብሎ ዝግጅት በመደረጉ ነው፡፡ በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራታቸውም ጭምር ነው፡፡ በየአካባቢው ያሉ ዩኒየኖች ለአርሶ አደሩ ምቹና ቅርብ ወደሆኑ ጣቢያዎች የሚያደርሱ ሲሆን፣ የስርጭቱን ሥራ የሚሰሩት መሠረታዊ ዩኒየኖች አባላት ለሆኑትም ሆነ ላልሆኑት አርሶ አደሮች ያሰራጫሉ፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ ሰይፉ እንደገለጹት፤ እስካሁን ወደ አገር ውስጥ የተጓጓዘው 830 ሺ 275.8 ሜትሪክ ቶን ገደማ ነው፡፡ የባቡሩ ጭነት ራሱን የቻለ ጥቂት ቀናት የወሰደ ቢሆንም፤ የመጀመሪያውን የአፈር ማዳበሪያ የጫነው ባቡር ባለፈው ቅዳሜ ረፋድ ላይ ተነስቶ ትናንት ረፋድ ላይ አዳማ ገብቷል፡፡ እያንዳንዱም ፉርጎ እየተነቀለ ተሸከርካዎች ላይ እየተራገፈ ሲሆን፣ ተሽከርካሪዎችም ቀጥታ በመውሰድ ለመሠረታዊ ማህበራት የሚያደርሱ ይሆናል፡፡
ባቡሩ ነጋት ከምትባል የኢትዮጵያና የጂቡቲ ድንበር ተነስቶ በአዳማ ማዕከላዊ ጣቢያ ጭነቱን ያደርሳል፡፡ የሚወስድበት ጊዜ አሰር ሰዓት ያህል ነው፡፡ ከጂቡቲ ወደብ ነጋት ድረስ ደግሞ የሚያመጡት ሌሎች መኪናዎች ናቸው፡፡ ከትናንት በስቲያ ያራገፈው ባቡር ሲመለስ ሌላው ደግሞ ጭኖ ይመጣል፡፡
«ጊዜውን ለማሳጠር በሳምንት ሁለቴ የሚደረገውን ምልልስ ሦስት ለማድረግ እንሰራለን፡፡ ምልልሱ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ማለቅ ይኖርበታል ብለን በመንቀሳቀስ ላይ ነው ያለነው፡፡ በዚህም የመጨረሻው ጭነት ማዳበሪያ በአንድ ሳምንት ውስጥ አርሶ አደሩ እጅ ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡ ከባቡር ጎን ለጎን መኪናው ደግሞ ምልልሱን አያስተጓጉልም» በማለት አብራርተዋል፡፡
አቶ ኡስማን እንዳሉት፤ በአቅርቦቱም ሆነ በማጓጓዙ በኩል ያለው ሂደት ከአምናው ይልቅ ዘንድሮ መሻሻል ይታይበታል፡፡ በ2008 ዓ.ም በየቦታው ያሉ የመጋዘን ሠራተኞች በቦታው ስለማይገኙ ማዳበሪያውን ጭነው በቦታው የተገኙ ተሽከርካሪዎች ለአንድና ሁለት ቀናት ያህል ለመቆም ይገደዱ ነበር፡፡ በዚህም መጉላላት ይፈጠር ነበር፡፡ 2009 ዓ.ም ላይ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ችግሩ ተስተውሎ የነበረ ቢሆንም መሻሻል ግን ማሳየቱ አይካድም፡፡ አምናና አቻምና የነበረውን ችግር በየጊዜው በጋራ በመገምገም ለመፍታት በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡
አቶ ኡስማን፣ ዘንድሮ ትንሽ ክፍተት ታይቷል ተብሎ የታየው የዩሪያ ማዳበሪያ መዝግየት ነው ይላሉ፡፡ ለመዘገግየቱም ምክንያት የሆነው በጨረታ ወቅት የተፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ነው» ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ጨረታው ሁለት ሦስቴ መውጣቱን የሚያስታውሱት አቶ ኡስማን፣ ምንም እንኳ የተወሰነ መጓተት ቢታይበትም በመጨረሻም የተሻለ ዋጋ ተገኝቶ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የጠቀሱት፡፡ መዘግየቱን ለማካካስም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብዙ ርቀት በመሄድ ማዳበሪያው በባቡርም ጭምር እንዲመጣ በመደረግ ላይ ነው ይላሉ፡፡
ዳይሬክተሩ አቶ ሰይፉ በበኩላቸው፤ ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ግዥን በተመለከተ የተሻለ ዋጋ ለማግኘት ሲባል በተደጋጋሚ ጨረታ መውጣቱን ይናገራሉ፡፡ በተደረገውም ተደጋጋሚ ሙከራ የተሻለ ዋጋ የተገኘ ሲሆን፣ በዚህም ወደ አምስት ነጥብ አምስት የኢትዮጵያ ብር ወጪ ማዳን መቻሉን ያስረዳሉ፡፡
አቶ ሰይፉ እንደሚገልጹት፤ ከዛሬ አራትና አምስት ዓመታት በፊት ያለው የማዳበሪያ አቅርቦቱ ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ለውጥ አለው፡፡ የማዳበሪያ ፍላጎቱም በዚያው ልክ እያደገ ነው፡፡ አምና ወደ አገር ውስጥ የገባው የማዳበሪያ መጠን አንድ ሚሊዮን 23 ሺ ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ወደ አገር ውስጥ እየገባ ያለው አንድ ሚሊዮን 350 ሺ ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ይህ ማለት የ326 ሺ ሜትሪክ ቶን ወይም ደግሞ ሦስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ አሳይቷል ማለት ነው፡፡
ይህ ማለት ግን ይላሉ አቶ ሰይፉ፣ «አምና ለማጓጓዝ የፈጀው ጊዜ ከዘንድሮው ጋር ሊነጻጽር አይገባም፡፡ በእርግጥ ከጊዜው አንጻር የጀመርንበት ጊዜ የተሻለ ነው፡፡ የምናጠናቅቀውም ከአምናው በዘገየ አይደለም፡፡ አምና ሰኔ 30 ላይ ሙሉ ለሙሉ አጠናቀናል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ የፍላጎቱ መጠን ከፍ በማለቱ እንጂ የጊዜ መጎተትን አያሳይም፡፡ ፍላጎቱ ግን አሁንም አላባራም፤ አቅም ቢኖረን እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ድረስ ይሄድ ነበር» በማለት ያብራራሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የከረመው ማዳበሪያ ቀድመው ለሚዘሩ አርሶ አደሮች ተሰራጭቷል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ዘንድሮ እስከ አሁን ከገባው 800 ሺ ሜትሪክ ቶን ላይ ወደ 600 ሺ ሜትሪክ ቶን ለአርሶ አደሩ ተሰራጨቷል፡፡ ይህ ማለት ከገባው 80 በመቶው ወደ አርሶ አደሩ እጅ ደርሷል ማለት ነው፡፡ ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎች በአፋጣኝ እንዲደርስ እየተደረገም ነው፡፡ ምክንያቱም በቆሎ የሚዘራውና ሰኔ 30 ወይም ሐምሌ አምስት ላይ ጤፍ የሚዘራ አርሶ አደር እኩል ማዳበሪያ መውሰድ የለባቸውም፡፡ በቆሎ ለሚዘራው ቀደሞ መሰጠት አለበት፡፡ በቂ መጋዘንና በቂ የጉልበት ሠራተኛም በማዘጋጀት ርክክቡን ማፋጠን ከተቻለ የተሽከርካሪ ምልልሱም የዚያኑ ያህል መጠኑ ይጨምራል፡፡
እንደሚታወቀው የአፈር ማዳበሪያ የሚገዛው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ነው፡፡ በከፍተኛ ወጪ ተገዝቶ በሱዳንና በጅቡቲ ወደብ ያለው ማዳበሪያም ያላሰለሰ ጥረት በማካሄድ ወደ አገር ውስጥ በባቡርም በመኪናም በመግባት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የቅብብሎሽ ሥራ ደግሞ በክልሎቹም ሆነ በዩኒየኖቹ ተጠናክሮ በመቀጠል እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ግብዓቱን ፈላጊ አርሶ አደሮች በወቅቱ የማያገኙት ከሆነ ግን በቀጣይ በጀት ዓመት ከ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ይገኛል ተብሎ በእቅድ የተያዘው 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ይሆናል፡፡ ስለሆነም ርብርቡ በተያዘው ፍጥነት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

አስቴር ኤልያስ

Published in ኢኮኖሚ

የቀድሞው ነጋዴና የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተለይ አገራቸው ከሌሎች አገራት ጋር የመሰረተችውን የንግድ አጋርነት የሚመለከቱበት የራሳቸው መነፅር አላቸው።ፕሬዚዳንቱ ከሌሎች አቻዎቻቸው በተለየ መልኩም፤ አገራቸው መመጣጠን በማይታይባት ፍትህ በጎደለው የንግድ ልውውጥ እጅጉን እየተጎዳችና ለከባድ ኪሳራ መዳረጓን አጥብቀው ያምናሉ። አገራቸው የፈረመቻቸውን የተለያዩ ነፃ የንግድ ስምምነቶችን ከጥቅም ይልቅ ጉዳታቸው ጎልቶ ይታያቸዋል።እናም እከተለዋለሁ በሚሉት የንግድ ፖሊሲ መሰል አካሄድ ቦታ እንደማይኖረው ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጀምሮ ሲዝቱ ቆይተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት አንገታቸውን ካስገቡና መንበረ ስልጣኑን ከተረከቡ ወዲህም የአገራቸው የንግድ አጋሮች ያልተገባ ጥቅም አጋባሽ ስለመሆናቸው መወትወታቸውን አላቆሙም። መወትወት ብቻም ሳይሆን እርባና ቢስ የሚላቸውም ነፃ የንግድ ውሎችን ወደ ጎን በመግፋት አገራቸውን ከእነዚህ ውሎች ለመነጠል ጠንካራ የሚባሉ ውሳኔና እቅዶችን ይፋ አድርገዋል። 12 አገሮችን በአባልነት የያዘው ነፃ የንግድ ስምምነት የትራንስ ፓሲፊክ የንግድ ስምምነቱም ትራምፕ ከቀደዷቸው ውሎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።
ፕሬዚዳንቱ ከወራት በፊትም ቢሆን ፍትህ የጎደለው የንግድ አሰራር ተግባራዊ በማድረግ ሌሎችን አገራት በሚጠቅማት መንገድ በመጥቀም ተወጥራለች በሚሏት ቻይና ላይ እስከ 60 ቢሊዮን ዶላር የቀረጥ ጫና ማዕቀብ ጥለዋል። ቻይናም የፕሬዚዳንቱን እርምጃ በዝምታ ከማለፍ ይልቅ አፅፋውን መልሳለች።
የሁለቱ አገራት የንግድ ጦርነት በተጠንቀቅ ላይ ባለበት በዚህ ወቅትም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሌላ የቀረጥ ማዕቀብ ከቀናት በፊት ይፋ አድርገዋል።የአሁኑ የትራምፕ ሰይፍ ደግሞ የአገሪቱ ቀንደኛ የንግድ አጋር ወደሚባሉት የተሰነዘረ ሆኗል።
በአውሮፓ ህብረት አባል አገራት፣ በካናዳና ሜክሲኮ ላይ ገቢራዊ የሚሆነው ይህ የፕሬዚዳንቱ የቀረጥ ሰይፍም ከእነዚህ አገራት በሚገቡ የብረትና አልሙንየም ምርቶች ላይ ያነጣጠረና 25 እና አስር በመቶ ቀረጥን የጨመረ ሆኗል።
ትራምፕ ውሳኔውን በፊርማቸው ካረጋገጡ በኋላ «ፍትሃዊነት የጎደለውና ጥቂቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የንግድ ውል በይፋ ተቀደደ» ሲሉ ቢደመጡም፤ የማዕቀቡ ገፈት ቀማሽ አገራትና መሪዎቻቸውን ጨምሮ በርካታ የኢኮኖሚ ምሁራን እና የፖሊሲ አርቃቂዎች በአንፃሩ የፕሬዚዳንቱን እሳቤ እጅጉን የተሳሳተ ስለመሆኑ ሲሟገቱ ተስተውለዋል። አንዳንድ የህብረቱ አባል አገራትና መሪዎችም ውሳኔውን ሲኮንኑና በሚገቡ የተለያዩ ምርቶች ላይ ተመሳሳይ የአፀፋ ምላሽ ለመስጠት ሲዝቱ ተስተውለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ማኒኤል ማርኮንም የትራምፕን ውሳኔ ዓለም አቀፍ የንግድ ህግጋትን ያላከበረ የተሳሳተና ህገ ወጥ ሲሉ ገልፀውታል። መሰል የኢኮኖሚ ብሄርተኝነት አካሄድም በ1930 ሆኖ እንደታየው አገራትን ወደ ጦርነት እንደሚያስገባ በማስገንዘብ ፕሬዚዳንቱ ውሳኔያቸውን ዳግም እንዲያጤኑት ጠይቀዋል። የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርከልም ቢሆኑ የህብረቱ አባላት አገራት በረቀቀ አሳማኝና የጋራ በሆነ መልኩ አፀፋውን እንደሚመልሱ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ከአውሮፓ ህብረት ፍቺ የጠየቀችውና በሂደት ላይ የምትገኘው እንግሊዝ ሳይቀር የአሜሪካንን ውሳኔ እጅጉን አውግዛዋለች።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጄስቲን ትሩዱ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌላው ሲሉት፤ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዦን ክሎድ ዩንከር በበኩላቸው፤ ለዓለም ንግድ ኦዲት እጅጉን መጥፎ ቀን ብለውታል። የንግዱ ተዋናዮችም ቢሆኑ ችግሩ እጅግ አሳስቧቸዋል። አውሮፓ ግዙፍ የአውቶሞቢል አምራቹ የጀርመኑ « ቮልስ ቫገንም» ውሳኔው ዓለም አቀፍ የንግድ ጦርነት የሚቀሰቅስና ማንም አሸናፊ የማይሆንበት መሆኑን በመግለፅ ስጋቱን አስታውቋል።
እንደ ኒውስ ዊክ ዳርሚየን ሻርኮቭ ዘገባ፤ የሰውየው ውሳኔ በርካታ የፖሊሲ አውጪዎችና የህግ ሰዎችን አብግኗል። የራሳቸውን የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ሳይቀር ማናደዱንም አትተዋል። ውሳኔው ወዳጆቻችንን የሚያስኮርፍ ነው ሲሉም ተደምጠዋል። ቤን ሳሴን የመሳሰሉ የፓርቲው አባላት፤ ጠላቶችን የምታስተናግድበት መጠንና ወዳጆችን ከምታስተናግድበት ተመሳሳይ ሊሆን አይገባም፤ አውሮፓ ካናዳና ሜክሲኮ እንደ ቻይና አይደሉም ሲሉ በቲውተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
ውሳኔው ምናልባት ዛሬ ላይ ለአሜሪካ አስተዳደር የኩራትና የኃይለኝነት ማሳያ ቢሆንም ነገ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው የጠቆረ ጠባሳ ለብዙዎች በቀላሉ የሚታይ ይሆናል ያለው ደግሞ የኒውዮርክ ታይምስ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ኔሊ ኤርዊን ነው። ብሉንበርጉ፣ የትራምፕ አስተዳደር ዋነኛ የንግድ አጋሮቹ ላይ ያወጀው ድንገተኛ ውሳኔ ዓለም አቀፉ የንግድ ጦርነት የሚጀመርበት ቀን መቃረቡን እንደሚያመላክት አስፍሯል።
«የአሜሪካ የንግድ ፖሊሲ ከ17 63» የሚል ርዕስ መፅሀፍ ያሳተመው ኢኮኖሚስቱ ዳግላስ ኤርዊን፤ ያልተጠበቀው የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ የአሜሪካ ሁለንተና በተለይም የንግድ አጋሮቿን ያስቀየመና ከአገሪቱ አጠገብ እንዲርቁ የሚያስገድድ ነው» ብለውታል።
ፕሬዚዳንቱ ይህን ውሳኔ ያሳለፉበት «ብሄራዊ ደህንነትን ከማስጠበቅና የአሜሪካን የአልሙኒየምና የብረት ኢንዱስትሪን ለመታዳግ ነው» የሚል ቢሆንም አንዳንዶች በአንፃሩ የሰሜን አሜሪካ ነፃ የንግድ ስምምነት፣ በምህጻሩ «ናፍታ»ን እንደ አዲስ ለመከለስ ሶስቱ የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ዩኤስ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጠረጴዛ ዙሪያ ቢመክሩም የድርድሩ ውጤት ግን ስኬታማ እንደማይሆን በማስታወስ ትራምፕ ውሳኔ የወሰኑት ጎረቤቶቻቸው ስምምነቱን አገራቸው ያስቀመጠችውን ጥያቄ እንዲፈርሙ ለማስገደድ መሆኑን አመላክተዋል።ይሁንና የውሳኔው ውጤት ፕሬዚዳንቱ በፈለጉት መንገድ እንደማይጓዝ ይልቁንም ሌሎች አደገኛ ቀውሶችን ይዞ እንደሚመጣ ተማምነዋል።
የዋሽንግተን ፖስት ዘገባም፤ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዓለም አቀፉ የንግድ ህግ የሚተዳደርበትን መጽሀፍ አሽቀንጥረው የጣሉበት ውሳኔያቸው፤ አገራቸው ከቻይና ጋር የገባችውን የንግድ ጦርነት ይበልጥ ውስብስብ እንደሚያደርገው አስነብቧል። «ዋሽንግተን ከቤጂንግ ጋር የገጠመችው የንግድ ጦርነትም አቅሟን ያደክመዋልም ነው የተባለው ። በተለይ በንግድ አጋርነቱ ሂደት ያልተገባ ጥቅም እያጋበሰች ነው በሚል አሜሪካ በቻይና ላይ ከምታቀርባቸው ክሶች «አንዳንዶቹ እውነት ስለመሆናቸው እኛም ማረጋገጫው አለን» ከሚሉት የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት ጋር መቆራቆስ ውጤቱ አደገኛ ስለመሆኑም አትቷል።
የትራምፕ ውሳኔ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስህተት ስትል የገለፀችው የዋሽንግተን ፖስቷ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ሄዘር ሎንግ፤ ውሳኔው አሜሪካ ከቻይና ጋር ባላት የንግድ ትንቅንቅ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ከቤጂንግ መንግስት ጎን እንዲሰለፉ የሚያስገድድ መሆኑን አትታለች። ይህ ደግሞ ለቻይና የንግዱ ጦርነት አሸናፊነት ያልተጠበቀ ሲሳይ መሆኑም አመላክታለች።
የቡሽ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማቲው ሩኒ በአንፃሩ፤ መሰል ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ምክንያት አገራዊ ደህንነትን ለመጠበቅ ነው የሚል ምላሽ መስጠት በራሱ እጅግ አደገኛና ሌሎችም መሰል ተግባር በመፈፀም ከነፃ ገበያ ስምምነቱ እራሳቸውን እንዲያገሉ የማድረግ አቅሙ እጅጉን ግዙፍ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
ውሳኔው በአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ ምን ያህል ተፅእኖ ይኖረዋል ለሚለውም 19 ትሪሊዮን ዶላር ከሚንቀሳቀስበት ኢኮኖሚዋ ይልቅ ቢሊዮኖች የሚንቀሳቀሱበት ዓለም አቀፉ የብረትና የአልሙኒየም ንግድ ላይ መጠነ ሰፊ ጫና ይዞ ይመጣል ነው ያሉት።
አንዳንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምሁራን በአንፃሩ፤ የትራምፕ የንግድ ጦርነት ውሳኔ መዳረሻ ተሳታፊዎቹን እያሳዳገ መምጣቱን አስምረውበታል። ፕሬዚዳንቱ ከቀናት በፊት ያሳለፉት ውሳኔም ሁሉን ያማከለ ዓለምአቀፍ የንግድ ጦርነት ይዞ መምጣቱን ያመላክታል ተብሏል።
ለዚህ ዋናው ምክንያት የትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ ተጨማሪ ቀረጥ የተጣለባቸው አገራት አፀፋ መስጠታቸው እርግጥ መሆኑና ተግባሩም ፕሬዚዳንቱን ይበልጥ በማስቆጣት ለተጨማሪ ውሳኔ ስለሚገፋፋቸው ውጤቱም የንግድ ጦርነት ፉክክር ስለሚጦዝበት መሆኑን አብራርተዋል።
የ ዘ ዊክ መፅሄቱ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ጄፍ ስፕሮስ ፤ውሳኔም ምናልባትም የጦርነት መዳረሻውን ከሚያሰፋባቸው መንገዶች መካከል አሜሪካ የኢራን የኒውክሌር ስምምነት ራሷን ማስወጣቷና በአገሪቱ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣሏ ቀዳሚ ምክንያት ሆኖ እንደሚነሳ አስነብቧል።
እንደ ተንታኙ ገለፃ፤ አሜሪካ ከኢራን የኒውክሌር ስምምነት ራሷን ማስወጣቷን ተከትሎ ለኢራን ጀርባቸውን የማይሰጡ አገራት ከዋሽንግተን ጋር ለመፋጠጥ ይገደዳሉ። ይህም ከኢራን ጋር የኢኖሚያዊ አጋርነታቸውን የማያቋርጡ አገራት የትራምፕ በትር ያርፍባቸዋል እንደማለት ነው። ይህ ደግሞ ከኢራን ጎን ከቆሙት አውሮፓውያን በተጓዳኝ ሌሎች የንግድ ጦርነት ተካፋዮችን ወደ ፍልሚያ እንደሚያስገባ እርግጥ ይሆናል። የዚህ ጦርነት ዓለም አቀፍ ውጤት ደግሞ ብዙዎችን አስፈርቷል።
የዘ አትላንቲክ ሪቻርድ ዊኪ በመላ አውሮፓ ፀረ አሜሪካ ድምፆች መሰማትና ተቃውሞዎች መታየት ጀምረዋል ሲል አስነብቧል። በርካቶች ግን ከፀረ አሜሪካ ንቅናቄው የንግድ ጦርነቱ ባሻገር አገሪቱ ራሷን ከዓለም አቀፍ ትብብርና አጋርነት እያገለለች ያለችበት ፍጥነትና የአደጋው አስከፊነት አሳስቧቸዋል።

 

ታምራት ተስፋዬ

Published in ዓለም አቀፍ

የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እንደተለመደው በሬዲዮና ቴሌቪዥን አንድ ማስታወቂያ ሲያስነግር ሰማሁ፡፡ የውሃ ገንዳ ለማጠብ፣ ለጥገና ሥራ፣ወዘተ በሚል ውሃ ይቋረጣልና ከወዲሁ እወቁት የሚል መልእክት ያዘለ ማስታወቂያ ነው፡፡ ማስታወቂያው በግልባጩ ቢሆን ምናለ ስል ለራሴው ተናገርኩ፡፡ ነገሩ ገርሞኝ ጮክ ብዬ የተናገርኩ ይመስለኛል፡፡

በቅርቡ በሬዲዮ የሆነ ክፍለ ከተማ የአንዱ ቅርንጫፍ ውሃና ፍሳሸ ባለስልጣን ኃላፊ «እንዳውም በእኛ ወረዳ በሳምንት ለሁለት ቀናት አንዳንዴም ለሁለት ቀን ተኩል ለነዋሪዎቹ ውሃ እንዲደርሳቸው ይደረጋል፡፡ ሌሎች ይህን እድል አያገኙም» በማለት በሳምንት የሁለት ቀኑን የውሃ ስርጭት እንደ ጸጋ መቀበል እንደሚገባ የሚያስገነዝብ መረጃ ሲያስተላለፍ ሰምቻለሁ፡፡
ከተማዋ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በከፋ የውሃ ችግር ውስጥ ሆና ውሃ በፈረቃ ለዚያም በሳምንት ሁለት ቀን(አንዳንድ አካባቢ ከዚህም ይከፋል)፤ እያደለች ባለችበት ሁኔታ ይህን ማስታወቂያ ማስነገር ምን ይሉት እንደሆን እንጃ፡፡ ውሃ በሌለበት ውሃ ይቋረጣልና እወቁት ማለት ምን ማለት ነው? ወይ ማስታወቂያውን እንደ ዘመኑ ማድረግ (ከውሃ እጥረቱ ጋር እንዲጣጣም አፕ ዴት ማድረግ) ወይ መተው አይሻልም?
እንግዲህ አዲስ አበባ በከፍተኛ የውሃ ችግር ውስጥ ስለመሆኗ ከተማዋን የሞላት ቢጫ ጀርካን አንድ ማሳያ ነው፡፡ ሳይደግስ አይጣላም እንደሚባለው ይህ ጀሪካን ወደ ሀገር ውስጥ ከገባበት ዓላማ ይልቅ እየጠቀመ ያለው ለውሃ መቅጃ እና መቆያነት ነው፡፡ ጀሪካኑ የሌለበት የሀገሪቱ ክፍል ባይኖርም በአዲስ አበባ ግን የሚብስ ይመስለኛል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ አንድ መንደር ላይ ይህን ቁስ በብዛት ያስተዋሉ አካባቢውን ዳርፉር ማለታቸውም ትዝ አለኝ፡፡ ዳርፉር በውሃና በተለያዩ የሰላም ችግሮች የተተበተበው የሱዳን አንድ ክፍል ነው፡፡
ችግሩ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ምን ያህል እንደሚብስ የጎፋ መብራት ኃይል ኮንደሚኒየም ነዋሪዎችን መጠየቅ ይቻላል፡፡ አሁን አሁን ሁሉም ተመሳሰሉ እንጂ እነዚህ አካባቢዎች የዚህ ችግር ቀደምት ሰለባዎች ነበሩ፡፡
በዚህ መንደር መጀመሪያ አካባቢ ውሃው በጣም ጉልበት እንደነበረውና ቧንቧ እስከ መስበር ይደርስ እንደነበር ነዋሪዎቹ ያስታውሳሉ፡፡ ቆይቶ ቆይቶ ግን በመንደሩ የተወሰነ ክፍል መቆራረጥ ጀመረ፡፡ ችግሩ እየሰፋ መጥቶም ነዋሪዎች አንድ ጀሪካን ውሃ ከ15 እስከ 20 ብር እየገዙ ለመጠቀም እንዲገደዱ እስከ ማድረግ ደርሰ፡፡ ውሃው በአካባቢው ባልተገኘ ጊዜም ከመንደሩ ውጪ በሚገኝ መንደር እየዞሩ ውሃ እየገዙ መጠቀም የግድ እየሆነ መጣ፡፡
ይህ ችግር በጀሪካን ውሃ ለሚሸጡ ‹‹ሸበላዎች›› ገበያ እንዲደራላቸው አድርጓል፡፡ ቀደም ሲል ተነግሯቸው ውሃ ያቀርቡ የነበረ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከአንድም ሁለት ጀሪካን ውሃ ይዘው ገዥዎችን መጠበቅ ጀምረዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከሁለት ጀሪካን በላይ ማቅረብ እስከ አለመፈለግ ደርሰዋል፡፡ ኧረ እነሱንስ ክፉ አይንካብን የሚሉ ነዋሪዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ ውሃው በነፃ ቢገኝ እንኳ አራተኛ ፎቅ ድረስ ማን ይዞት ይወጣል፡፡ አንድ ወይም ግፋ ቢል ሁለት ጀሪካን ተይዞ ሊወጣ ይችላል፤ የጋራ መኖሪያ ቤት የሚፈልገውን ውሃ ሦስተኛ እና አራተኛ ፎቅ ድረስ እንዴት በየቀኑ ይዞ መውጣት ይቻላል? ችግሩ ደግሞ በአቅመ ደካሞች ላይ ይከፋል፡፡
በዚህ ላይ ዋጋው የትየለሌ ነው፡፡ ለአንድ ጀሪካን ውሃ የሚከፈለው ገንዘብ የአንድ ወር የፍጆታ ክፍያ ሊሸፍን ይችላል፡፡ ችግሩ ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገ ነው፡፡ ቤተሰብ ላለው ሰው ለማብሰያና ተያያዥ ጉዳዮች ብቻ በቀን ቢያንስ ሦስት ጀሪካን ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ይሄ የእኔ ግምት ነው፡፡ ይህ በጀሪካን የሚቀርብ ከሆነ በቀን ስንት ብር ሊወጣ እንደሚችል ገምቱ፡፡
ነዋሪዎቹ ውሃ እንደሚጠፋ እያሰቡ የእቃና የመሳሰለውን እጣቢ እያጠራቀሙ ለመጸዳጃ ቤት ያውላሉ፡፡ እሺ ፤ውሃው ተገኝቶ እጣቢው ለዚህ አገልግሎት ይዋል፡፡ እጣቢ በተጠራቀመ ቁጥር የጤና ችግር ሊሆን እንደሚችል መጠራጠር አያስፈልግም፡፡
የጀሪካን ውሃ ሽያጭ የጣማቸው ‹‹ሸበላዎች›› የቧንቧ መስመር ይዘጋሉ እየተባሉም ይጠረጠራሉ፤ እነሱ ብቻም ሳይሆኑ የአካባቢውን ውሃ የሚቆጣጠረው የሚመለከተው አካል የመደበው ክፍልም ቢሆን የሚፈልገውን ለማጠጣት ሲል የሚከለክላቸው እንዳሉ የሚናገሩም አሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ልብስም ሆነ ሰውነትን እንደፈለጉ መታጠብ ተረት ሆኗል፤ የሻወር መታጠቢያው ቧንቧ ሥራ ካቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዝገት ሳይበላቸውም አይቀርም፡፡
‘ሜዳ ሲቃጠል ተራራ ይስቃል’ እንዲሉ ሌሎች የመንደሩ ክፍሎች የእነዚህ ነዋሪዎች ቅሬታ አልተሰማቸውም ነበር፡፡ ችግሩ እየሰፋ መጥቶ በየሕንፃው ደረሰ፡፡ የውሃ ስርጭት መቋረጡ እንዳሻው መሆን ጀመረ፡፡ አንዳንዴ ሌሊት ይመጣና ይጠፋል፡፡ በአጋጣሚ ሰው እቤት ከሌለ ወይም እንቅልፍ ከጣለው ሳምንቱን ሙሉ ጉዱ ይፈላል፡፡ አንዳንዴ ሁለት ወለል ላይ ይኖርና የተቀረው በሙሉ የበይ ተመልካች ሲሆንም ይስተዋላል፡፡
ይህን ጊዜ ጀሪካን ይዞ ውሃ መለመን የግድ ይሆናል፡፡ የኮንደሚኒየም ኑሮ አብሮ ለመኖር ብዙም የማይመች ቢሆንም በዚህና በመሳሰሉት ችግሮች ሳቢያ ትብብር ሲደረግ ይስተዋላል፡፡ እንዲያም ሆኖ ስንት ቀን ከሰው ቤት ውሃ እየተቀዳ ይኖራል፤ ለዚያውም በነፃ፡፡ ደግነቱ ነዋሪው ከቤት ውስጥ በተጨማሪ በየበረንዳው ቧንቧ ያደረገ በመሆኑ በሰው ላይ ሳይረማመዱ መቅዳት ይቻላል እንጂ ቤት እየገቡ ውሃ መደቀን ይቸግር ነበር፡፡
የውሃው ችግር ያማረራቸው አንዳንድ በልማት አማካይነት የጋራ መኖርያ ቤት የገቡ ነዋሪዎች «ደህና ከምንኖርበት አካባቢ አንስተው ፎቅ ላይ አውጥተውን በዚያ ላይ ጉድ አስታቅፈውን(መጸዳጃ ቤት እቤት ውስጥ መሆኑን ማለት ነው) ውሃ ይከለክሉናል፤ አስቲ ምን እናርገው?» እያሉ እንደሚያማርሩ ይነገራል፡፡
ለማንም ቢሆን ውሃ ወሳኝ ነው፡፡ በፎቅ ላይ መኖርን በስፋት እንደ አቅጣጫ ይዛ እየተገበረች የምትገኘው አዲስ አበባ ደግሞ ከዚህም በላይ ውሃ ያስፈልጋታል፡፡ ምግብ ማብሰል ፣ማጠብ፣ መታጠቡ ምድርም ለሚኖር ሆነ ፎቅ ላይ ለሚኖር አንድ ቢሆንም፣ ከመጸዳዳት ጋር ተያይዞ ግን ፎቅ ላይ መኖር መቆራረጥ የሌለበት የውሃ አገልግሎትን እንደሚጠይቅ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡
አንድ ሰው መጸዳጃ ቤት ተቀምጦ ሲነሳ አሁን ሥራ ላይ ባሉት መጸዳጃ ቤቶች ሲታይ ወደ አንድ ባሊ ውሃ ያስፈልጋል፡፡ በቀን ሊኖር የሚችለውን ምልልስ ይህ ደግሞ ከቤተሰብ ብዛት ጋር ሲሰላ የሚያስፈልገው የውሃ መጠን እጅግ ብዙ ስለመሆኑ አያነጋግርም፡፡ የእቃ እጣቢ በበቂ ውሃ ተገፍቶ መሄድ ይኖርበታል፡፡ ይህ አይነቱን ኑሮ እያስለመደች ያለች ከተማ ታዲያ ውሃ እንደፈለጋት ትዘጋለች፤ ትከፍታለች፤ ጭርሱኑ ደግሞ በሳምንት ለሁለት ቀናት ብቻ ይበቃችኋል ብላ ደምድማለች፡፡
ውሃ ከሌለ መጥፎ ጠረን ይመጣል፤ ችግሩ ሄዶ ሄዶም የጤና ችግር መሆኑ አይቀርም፡፡ የሚገርመው ግን የከተማዋ ጤና ቢሮም ሆነ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም በዘርፉ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላት ከኮንደሚኒየም የውሃ ችግር ጋር በተያያዘ ሊከሰት ስለሚችል ወረርሽኝ ብዙም አላሳሰባቸውም፡፡ ለነገሩ ቢሉም ውሃና ፍሳሽ ጉዳዩ አይደለም፡፡
ችግሩ የበሳባቸው የጎፋ ኮንደሚኒየም ነዋሪዎች ግን ሄደው ሄደው የት እንደሚደርሱ ባይታወቅም የቤቱን አቅም የሚገዳደር የውሃ ማቆር ሥራ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ውሃ ለጉድ ይታቆራል፡፡ የበርሜሎች፣ጀሪካኖችና ባሊዎች መጠን ውሃ እየጠፋ ፈረቃው እየሰፋ በሄደ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ አሁን በመንደሩ በሳምንት ለሁለት ቀናት ብቻ ይመጣል፡፡ ልብ በሉ ይህ የሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ አራቱ ቀናት ውሃ ጠብም አይልባቸው፡፡ ስለዚህ የበርሜሎች፣ የጀርካኖችና ባሊዎች መጠን በቀጣይም እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡ መጸዳጃ ቤት፣ ወጥ ቤት /ክቺን/ እንዲሁም በረንዳ ላይ በርሜሎችን ማቆም ተለምዷል፡፡
የበርሜል እየበዛ መሄድ ለሕንፃው ደህንነት ስጋት ከመሆኑም በተጨማሪ በየበረንዳው እንዲቀመጡ የተደረጉ ትላልቅ በርሜሎች መተላለፊያ ስለሚከለክሉ ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡
የጋራ መኖሪያ ሕንፃዎቹ ለውሃ ጋን ማጠራቀሚያ የሚሆን ግንባታ አልተደረገላ ቸውም፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በየቤቱ በዚያም በዚያም እቃ እየተደረገ ውሃ መታቆሩ በሕንፃው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳረፍ የነዋሪዎችን ህልውና አይፈታተንም ተብሎም አይገመትም፡፡
አንዳንድ ነዋሪዎች ደግሞ በዝናብ ወቅት የጣሪያ ውሃ በመደቀን ለመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ማዋል ጀምሯል፡፡ ነዋሪው በውሃ ችግር እየተፈተነ በመሆኑም ዝናብ ጠብ ሲል እንደ ጥንቱ የጣሪያ ውሃ ለመደቀን ወርዶ ወረፋ ይይዛል፡፡ እንዲያውም ለዝናብ ውሃ ወረፋ የያዙ ጎረቤታሞች መጣላታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በየወለሉ የተበላሹ አሸንዳዎችን በመጠቀም ጥላ ይዘው በትናንሽ እቃዎች ውሃ እየደቀኑ ያጠራቅማሉ፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ የበርሜልና የጀሪካን ከተማ፡፡

ዘካርያስ

 

Published in አጀንዳ
Tuesday, 05 June 2018 16:55

ድጋፉ ይጠናከር

መንግስት በከተሞች ያለውን የከፋ ድህነት ለመቀነስ እንዲቻል ከዓለም ባንክ በተገኘ 300 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከመንግስት በተመደበ 150 ሚሊዮን ዶላር በአጠቃላይ 450 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ በ11 ከተሞች የሴፍቲኔት መርሀ ግብር ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡መርሀ ግብሩ ከተጀመረ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥም በመርሀ ግብሩ የታቀፉ በርካታ ዜጎች ህይወታቸው መለወጥ ጀምሯል፡፡
በመርሀ ግብሩ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ሲሆን፣ እስከ አሁንም 150 ሺ ሰዎች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ የመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አቅሙ ያላቸው በልማት ስራዎች እንዲሰማሩ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ሲሆን፣ ሌሎች መስራት የማይችሉት ደግሞ ድጋፉን በቀጥታ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ፡፡ እነዚህ ዜጎች በመርሀ ግብሩ በመታቀፍ እየሰሩ እንዲቆጥቡ በማድረግ ቀስ በቀስ ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡
የመርሀ ግብሩ ሁለተኛ ምእራፍም ከትናንት በስቲያ 200 ሺ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ በሚያርግ መልኩ ለማከናወን ይፋ ተደርጓል፡፡ በዚህ መርሀ ግብር ከታቀፉት ነዋሪዎች 32 ሺ የሚሆኑት በቀጥታ ድጋፍ እንዲሁም 168 ሺ የሚሆኑት ደግሞ በአካባቢ ልማት እንዲሳተፉ በማድረግ ተጠቃሚ ይደረጋሉ፡፡ ይህም በከተማዋ በመርሀ ግብሩ የታቀፉ ነዋሪዎችን ቁጥር 323 ሺ ያደርሰዋል፡፡
በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በመርሀ ግብሩ እየተሳተፉ የሚገኙት ዜጎች ተጠቃሚ ከመሆናቸው በተጓዳኝ በከተማዋ የልማት ስራዎች እየተሰማሩ መሆኑም የከተማዋን የልማት ጥያቄም ይመልሳሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የጽዳት ስራም የእነዚህ ዜጎች ውጤት ነውና መርሀ ግብሩ ሊበረታታ ይገባል፡፡
የአቅማቸውን ያህል መስራት እየቻሉ የሰው እጅ ለማየት እንዲሁም በተለያዩ ጉዳቶች ሳቢያ ለልመናና ለመሳሰሉት ተዳርገው የኖሩት እነዚህ የመርህ ግብሩ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉት፤ በመርሀ ግብሩ ኑራቸው መለወጥ ጀምሯል፡፡ ከገቢያቸው የተወሰነውን ለፍጆታ እያዋሉ የተወሰነውን መቆጠብም ጀምረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ እንዳሉት መርሀ ግብሩ ደካሞችንና ህመምተኞችን በቀጥታ ድጋፍ እንዲሁም መስራት የሚችሉትን በአካባቢያቸው የልማት ስራ ላይ ተሰማርተው ገቢ እንዲያገኙ በማድረግ ውጤታማ እየሆኑ ነው።
ይህም ተስፋ ቆርጠው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ስራ ውለው እንዲገቡ እንዲሁም የሰው እጅ ከማየት እንዲወጡ ያደረገ መርሀ ግብር ቆጣቢ እንዲሆኑ በማስቻል ባለ ራእይ እንዲሆኑ ጭምር እያደረገ መሆኑም በአድናቆት መታየት ያለበት እና ሌሎች ተመሳሳይ ወገኖችንም መድረስ ያለበት ነው ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ከ 2009 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄደው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በተመረጡ 35 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ ተደርጎ 123ሺ 918 ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ያበሰረበት እንዲሁም በሁለተኛው ዙር በ55 ወረዳዎች የሚኖሩ 200ሺ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች የመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ይፋ ያደረገበት ዝግጅት በሚሌኒየም አዳራሽ በተካሄደበት ወቅት እንደተጠቆመው፤መንግስት መርሀ ግብሩን ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም ይዟል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፤መርሀ ግብሩን ድምጻቸው የማይሰማ ሆኖም ሊደመጡ የሚገባቸውን ዜጎችን ያሳተፈና አኗኗራቸውንና የህይወት ቁመናቸውን የለወጠ ሲሉ ገልጸውታል፡፡መርሀ ግብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
መንግስት በዓለም ባንክ ድጋፍና በራሱ ተጨማሪ በጀት እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ መደገፍ እርምጃ መግባቱ ሃላፊነቱ ቢሆንም በአድናቆት ሊታይ የሚገባው ተግባርም ነው፡፡ በተለይ መንግስት 150 ሚሊዮን ዶላር መድቦ እነዚህን ዜጎች ለመደገፍ መነሳቱ ሀገሪቱ እያስመዘገበች ከምትገኘው ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማቋደስ ያለውን ቁርጠኝነት ያመለክታል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ የከፋ ድህነት በሚገባ የሚታይ እንደመሆኑ እነዚህ የደህነት አረንቋ ውስጥ ሰምጠው የበይ ተመልካች ሆነው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ የሚያገኙበትን እና ኑሯቸው የሚሻሻልበትን ቆጥበው ኑሯቸው በዘላቂነት የሚለወጥበትን መንገድ ለማመቻቸት መንግስት የተያያዘውን ጥረት ለመደገፍ በየደረጃው ያለው አመራርም ሃላፊነት አለበት፡፡ የመርሀ ግብሩን ተጠቃሚዎች በመመልመል ሂደት የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮችን መፍታት የሚቻለውም አመራሩ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት እነዚህ ዜጎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ህዝቡም ይህ የመንግስት ቁርጠኝነት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን በመርሀ ግብሩ የሚሳተፉ ዜጎች ሲመለመሉ በንቃት በመሳተፍ ድጋፉ ለትክክለኛው የህብረተበሰብ ክፍል እንዲደርስ በመተባበር ለመርሀ ግብሩ ስኬታማነት ሊሰራ ይገባል፡፡
በመርሀ ግብሩ ታቅፈው ህይወታቸው እየተቀየረ የሚገኝ ዜጎችም ለውጡን ዘላቂ ለማድረግ መንግስት ያመቻቸውን የቁጠባ መርሀ ግብር አጠናክረው መቀጠል እንዲሁም ወደፊት ሊሰሩ ስለሚፈልጉት ስራም ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ነዋሪዎቹን በመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም አሁን ተጠቃሚ የተደረጉት ዜጎች በርካታ ቢሆኑም በከተማ አስተዳደሩ እንዳለ ከሚጠቆመው ስር በሰደደ ድህነት ውስጥ የሚገኝ ነዋሪ አንጻር በቀጣይም ብዙ መስራት ይጠበቃል፡፡አሁን የተገኘውን ለውጥ በማስፋት፣ ሌሎችን የህብረተሰብ ክፍሎችም ተጠቃሚ ለማድረግ ድጋፉ ሊጠናከር ይገባል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ያምራል ሀገሬ፤ ያምራል ሀገሬ
ኧረ ያምራል ሀገሬ
ባንቺ ነው ባንቺ ነው ባንቺ ነው ማማሬ፤ …የሚለውን ዜማ ልብን ሞቅ በሚያደርገው የማርሽ ባንድ ታጅቦ ይሰማል። ከከተማዋ አራቱ ማዕዘናት የመጡ እንግዶችም የአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽን ግቢ አድምቀውታል። ሁሉም ፊት ላይ ደስታ፣ ተስፋና ጠንካራ የሥራ ስሜትም ይነበባል።
እነዚህ ሰዎች ከዚህ ቀደም የመስራት አቅም ቢኖራቸውም ሥራ አጥ ተብለው እቤታቸው ቁጭ ያሉ ወጣቶች፣ የባሎቻቸውን እጅ እየጠበቁ በከፋ ድህነት ውስጥ ሆነው ልጆቻቸውን ማሳደግ ዕጣ ፈንታቸው የነበሩ እማወራዎች እንዲሁም በሚፈልጉት ልክ ቤታቸውን መምራት ተስኗቸው ሲማረሩ የነበሩ አባወራዎች ሲሆኑ፣ በዕለቱ በሚሌኒየም አዳራሽ ቅጥር ግቢ በትልቅ ደስታና ተስፋ ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ከ 2009 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄደው የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር በተመረጡ 35 ወረዳዎች ላይ ተግብሮ 123ሺ 918 ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ያበሰረበት፤ እግረ መንገዱንም በ 2ኛው ዙር በ55 ወረዳዎች ለሚኖሩ 200ሺ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች ለማስጠቀም የሚያስችለውን መርሀ ግብርም ይፋ ያደረገበት ዝግጅት ነበር።
በመርሀ ግብሩ የመጀመሪያ ዙር ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ እማዋይሽ ሙሉ አንዷ ናቸው፤ ወይዘሮዋ ከዚህ ቀደም ሦስት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ ችግር አይተዋል፤ እያዩም ነበር። የባለቤታቸውን እጅ ጠብቀው የሚያገኙት ገቢም ምናልባት ልጆቻቸውን በቀን ለአንድ ጊዜ ያበላላቸው ይሆናል እንጂ ከዚያ ባለፈ የሚተርፍም ገቢ እንዳልነበራቸው በራሳቸው አንደበት ይናገራሉ።
እንደ ወይዘሮዋ ገለጻ፤ ዛሬ ላይ መንግሥት ባመቻቸው የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ታቅፈዋል፡፡ በአቅማቸው ሊሰሩ የሚችሉትን ሥራ እየሰሩና ገቢ እያገኙ ልጆቻቸውንም በአግባቡ እየመገቡና እያስተማሩም ይገኛሉ፡፡
አቶ ፍሬው ዘውዱ ሌላው የመርሀ ግብሩ ተጠቃሚ ናቸው። እርሳቸውም እንደሚሉት፤ የሸክም ሥራና ሌሎች እጅግ አቅምን የሚፈታተኑ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ ይሁንና አቅማቸውን ሲጨርሱ ኖሩ እንጂ የሚሰሩት ሥራ ያን ያህል ገቢ አስገኝቶላቸው አያውቅም፡፡ ከዚህም የተነሳ ቤተሰባቸውንም በአግባቡ መምራት ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡
አሁን ላይ በተመቻቸላቸው የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ኑሯቸው በመጠኑም ቢሆን ለውጥ ማምጣቱን ገልጸው፤ ዛሬ እንደ ቀድሞ የሚበሉትና የሚያበሉት አጥተው እንደማይቸገሩ እርግጠኛ ሆነዋል፡፡ አሁንም ግን በተለይም ሥራው ሰፍቶ ክፍያውም ጨመር ብሎ ወደ ቁጠባም የመግባት ሁኔታ ቢመቻች መልካም መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አቶ ምኒሉህ በላይ በበኩላቸው፤ እርሳቸውን መሰል አዛውንቶች በተለይም ዕድሜያቸው ሲገፋና እራሳቸውን መርዳት ሲሳናቸው ዕጣ ፈንታቸው የሚሆነው ጎዳና ወጥተው በብርድና ፀሐይ መሞት ብቻ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን መንግሥት «ልጡራችሁ» ብሎ እያስፈረመ በየወሩ የሚሰጠው  ገንዘብ ቢያንስ እንዳይርባቸው ከማድረጉም በተጨማሪ እድራቸውን በአግባቡ መክፈል እንዳስቻላቸው ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በመርሀ ግብሩ ላይ እንዳሉትም፤ በከተማዋ በሁለት መንገድ እየተካሄደ ያለው የምገግብ ዋስትና መርሀ ግብር አቅመ ደካሞችንና ህመምተኞችን በቀጥታ ድጋፍ እንዲሁም መስራት የሚችሉትን በአካባቢያቸው የልማት ሥራ ላይ ተሰማርተው ገቢ እንዲያገኙ በማድረግ ውጤታማ እየሆነ ነው።
«በዚህም ነዋሪዎች አካባቢያቸውን እየታደጉ እንዲሁም በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን እየደጎሙ ነው» ያሉት ከንቲባው፣ በ2ኛው ዙርም ሌሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፉት አምስት ወራት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነው አሁን ወደ ትግበራ መገባቱን አስረድተዋል።
በዚህም 32 ሺ ነዋሪዎች በቀጥታ ድጋፍ እንዲሁም 168 ሺ ነዋሪዎች በአካባቢ ልማት በድምሩ 200ሺ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ከባለፈው ዓመት ተጠቃሚ ከሆኑት 123 ሺ ነዋሪዎች ጋር ድምሩ ሲሰላ 323 ሺ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን መገንዘብ እንደሚቻልም ተናግረዋል።
ይህም በከተማዋ ካሉ ስድስት መቶ ሺ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ነዋሪዎች መካከል ግማሽ ያህሉን በመርሃ ግብሩ አቅፎ ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማሸጋገር መቻሉን እንደሚያመላክትም ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዳሉትም፤ መርሃ ግብሩ በተለይም ድምጻቸው የማይሰማ ወገኖችን ሆኖም ሊደመጡ የሚገባቸውን ዜጎችን ያሳተፈና አኗኗራቸውንና የሕይወት ቁመናቸውን የለወጠ ነው፡፡
በዚህ መርሀ ግብርም የከፋ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሕይወት ለመቀየር ያስቻለ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አስገንዝበዋል። ተጠቃሚዎች የጀመሩትን ቁጠባ አጠናክረው በመቀጠል በሕይወታቸው ላይ ለውጥ ማምጣት ያለባቸው ሲሆን፣ በሁለተኛው ዙር የሚካተቱ ነዋሪዎችም በተሻለ ሁኔታ ሰርተው መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ በሚገኘው የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር የመስራት አቅም ቢኖራቸውም ሥራ አጥ የሆኑ እንዲሁም በዕድሜና በበሽታ መስራት የማይችሉ ዜጎችን ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እየተለዩ ተጠቃሚ እየተደረጉ እንደሚገኙ ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

ዜና ሀተታ
እፀገነት አክሊሉ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።