Items filtered by date: Wednesday, 06 June 2018

ከ280 እስከ 550 ምዕተ ዓለም ባለው ጊዜ በምስራቅ ህንድ አካባቢ እንደተፈጠረ ይነገራል። መነሻውን አንድ አገር ቢያደርግም፤ መዳረሻውን መላውን ዓለም ለማድረግ ችሏል። በአሁኑ ወቅት ከግማሽ ቢሊዮን በላይ አዘውታሪዎች እንዳሉትም የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ - የቼዝ ስፖርት፡፡ስፖርቱ ባህርይን ለማሻሻል፣በራስ መተማመንን ለማጎልበት፣ ምክንያታዊነትን ለማዳበር፣ በስሌት ችሎታ ውጤታማ በሆነ መልኩ ከሌሎች ጋር መስራትን የመገንባት አቅም አለው፡፡ በአነስተኛ ኢንቨስትመንት በየትኛውም የዕድሜ ክልል ሊዘወተር የሚችል መሆኑ በዓለም ላይ የተደራሽነት አድማሱ እንዲሰፋ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵ ያም አምስት መቶ ዓመት ማስቆጠሩን የታሪክ ድርሳናትና፤የዘርፉ ሊሂቃን ያስረዳሉ።
የዓለም ቼዝ ፌዴሬሽን ኢንስትራክተር አቶ አበባው ከበደ፤ ቼዝ በቀደሙት ዘመናት በመኳንንት ቤቶችና በፍርድ ቤት አካባቢ ይዘወተር እንደነበር ይገልፃሉ፡፡ ጨዋታው በአማርኛ ሰንጠረዥ የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን በዓረብኛ ዛትራንጅ፣ በፐርሺያ ቻትሪንግ እንዲሁም በጥንታዊ የሕንድ ቋንቋ ቻቱራንጋ ይባላል ፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አፄ ልብነ ድንግል፤ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ደግሞ የሸዋው ንጉስ ሳህለ ስላሴ ቼዝን ይጫወቱ እንደነበር አስረድተዋል።
ስፖርቱ ጅማሬው ሩቅ ቢሆንም፤ በአገሪቱ ያለበት ወቅታዊ ደረጃ የዕድሜውን ያህል ማደግ አልቻለም፡፡ ለዚህም የክለቦች አለመስፋፋት በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳል። የቼዝ ስፖርት ክለቦችን የሚያሳትፍ የውድድር መድረክ ሳይኖር ዓመታትን መጓዙ ለስፖርቱ አለማደግ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፉ ይነገራል፡፡
በቼዝ ስፖርት ላለፉት ሦስት ዓመታት ያሳለፈችው አስቴር መላክ በቼዝ ስፖርት በአህጉር አቀፍ ደረጃ አገሯን የመወከል አጋጣሚ አግኝታ እንደነበር ታስታውሳለች። በአገሪቱ የክለቦች እንቅስቃሴ የጎላ አለመሆኑን ጠቅሳ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉት ክለቦች ከአራት እንደማይበልጡ ትጠቅሳለች፡፡ የክለቦች መቋቋም በስፖርቱ መነቃቃት ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ታስገነዝባለች፡፡ ይሁንና ክለቦችን ከማስፋ ፋትና ከማጠናከር አኳያ የተሰራው ሥራ እጅግ በጣም ደካማ ነው ትላለች፡፡ በመሆኑም የክለቦች አለመጠናከርና አለመስፋፋት ስፖርቱ እንዳያድግ ማድረጉ ከግንዛቤ ገብቶ ለለውጥ የሚረዳ ሥራ መከናወን አለበት።
አቶ አበባው ‹‹ በአሁኑ ወቅት የቼዝ ክለቦች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የስፖርቱን አስፈላጊነት ተረድቶ በአገር አቀፍም ሆነ በክልሎች ደረጃ ክለቦችን ለማጠናከርና ለማስፋፋት የተደረገው ጥረት ደካማ በመሆኑ ነው። በስፖርቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ያለነው ሰዎች ክለቦችን ለማቋቋም ጥረት ብናደር ግም፤ስለ ስፖርቱ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን በሚፈለገው ደረጃ መጓዝ እንዳይቻል አድርጓል። ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም፤ለስፖርቱ ፍቅርና ቅርበት ካላቸው ሰዎች ጋር በመሆን አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ የቼዝ ክለብን መስርተናል›› ይላሉ።
የቴራስ ቼዝ ክለብ ተጫዋች የሆኑት አቶ አቤል ማቲዎስ ፤በስፖርቱ እንቅስቃሴ ውስጥ ክለቦችን የማቋቋም ሥራዎች አለመሰራታቸውን ይናገራሉ፡፡ ያሉትን ክለቦች ለማጠናከርም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሚገባ አልተንቀ ሳቀሱም ይላሉ፡፡ ይህም የክለቦችን እንቅስቃሴ ከመገደቡም በላይ ስፖርቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይጠናከር እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ የክለቦች ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር፤ ክለቦችን ብቻ የሚያሳትፍ የውድድር መድረክ የለም። ይህም የቼዝ ክለቦችን የሚያሳትፍ የውድድር መድረክ አስፈላጊነት መዘንጋቱን ያሳያል ይላሉ። በቀጣይ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባውም ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡
ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ክለቦችን የማጠናከርና የመመስረቱ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ይፈልጋል። ክለቦቹ በውድድር ራሳቸውን የሚፈትሹበት ራሱን የቻለ መድረክ በማዘጋጀት ሊደገፍ እንደሚገባው ተመል ክቷል፡፡ የቼዝ ስፖርትን ለማሳደግ ፌዴሬሽኑ ለክለቦች የውድድር አጋጣሚ መፍጠር የመጀመ ሪያውና ትልቁ ሥራው አድርጎ ተንቀ ሳቅሷል፡፡ በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በኩል የክለቦችንም ቁጥር ሆነ፤ የውድድር መድረኮችን መፍጠር አስፈላጊነቱ ታምኖበት በመሰራቱም በዚህ ዓመት ጥረቱ ፍሬ አፍርቷል፡፡
በዚህም የተነሳ ከግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የነበረውና ከቀናት በፊት የተጠናቀቀው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የቼዝ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ተካሂዷል፡፡ ውድድሩ የአገሪቱ የቼዝ ክለቦች ቁመናን ያሳየ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በተወሰነው በዚህ ውድድር በወንድ ፆታ አቡጊዳ፣ አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ፣ አዲስና ቴራስ የተሰኙ የቼዝ ክለቦች ተሳትፈዋል፡፡ በዚህ የመጀመሪያው የውድድር ተሳትፎ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች በኩል ለስፖርቱ የተሰጠውን ቦታ ቅልብጭ አድርጎ ያሳየ እንደሆነም የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቼዝ ክለቦች ሻምፒዮና መጀመሩን ተከትሎ አስተያየቷን የሰጠችው ልደት አያሌው ውድድሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ክለቦች አቅማቸውን እንዲለኩ አጋጣሚ መፍጠሩን ትናገራለች፡፡ ያሉት ክለቦች እንዲጠናከሩና አዳዲስ ክለቦች እንዲፈጠሩ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብላለች።ፌዴሬሽኑ ክለቦችን ለማብዛት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማሳካትም ይረዳዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ለሚያመጣቸው ክለቦች በበጎ ፍቃደኝነት ለመስራትና ለማገዝ እርሷን ጨምሮ ብዙ ተጫዋቶች መመዝገባቸውንም ገልፃለች፡፡ የፌዴሬሽኑ ጥረት በብዙዎች ዘንድ ድጋፍና አድናቆት ማግኘቱን መረጃው እንዳላትም ነው የጠቆመችው፡፡
አቶ አበባው እንዳሉት፤ በሻም ፒዮናው የተሳተፉት ክለቦች ቁጥር ጥቂት ነው። ከዚህም በላይ ደግሞ ተሳታፊ የነበሩት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ክለቦች ብቻ ናቸው። ይህም ለውድድሩ መደብዘዝ አንድ ምክንያት ሆኗል። እንደ መጀመሪያ ውድድር ጥሩ ቢባልም በቀጣይ ግን በደንብ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እንደ አዲስ አበባ ሁሉ የሌሎች ክልል ፌዴሬሽኖች ክለቦች እንዲመሰረቱ ማድረግና ወደ ውድድር እንዲመጡ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቼዝ ፌዴሬሽን ለክለቦች እያደረገ ያለውን ሙያዊ ድጋፍ በይበልጥ ማጠናከር አለበት። አሁን ያሉት ክለቦች መጠናከር ሌሎች አዳዲስ ክለቦች እንዲመጡ ያነቃቃል፡፡
የኢትዮጵያ ቼዝ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ በበኩላቸው ፤ስፖርቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ ውጤታማ ለመሆን የውስጥ ውድድሮችን ማድረግ እንደሚገባ ያነሳሉ። በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ያሉ ተጫዋቾች ራሳቸውን የሚፈትሹበት መድረክ ያስፈልጋል። ክልሎች በኢትዮጵያ የቼዝ ስፖርት ዉድድር ላይ ያላቸው ተሳትፎ በመላ የኢትዮጵያ ጨዋታ እና አገር አቀፍ የቼዝ የግል የበላይነት ውድድር ላይ ብቻ የተገደበ ነው። ክለቦችን ብቻ የሚያሳትፍ ራሱን የቻለ የውድድር መድረክ አለመኖር ክለቦች እንዳይቋቋሙና ያሉትም ጠንክረው እንዳይወጡ ሸብቦ ይዟቸዋል ይላሉ።
በመሆኑም በአገሪቱ የቼዝ ስፖርት የክለቦችን ቁጥር ለማሳደግና ስፖርቱን ለማጠናከር አልሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው «የኢትዮጵያ የቼዝ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር» ለስፖርቱ ትልቅ መነቃቃትን መፍጠሩን አቶ ሰይፈ ተናግረዋል፡፡ በሻምፒዮናው ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ክለቦቻቸ ውን እንዲያሳትፉ ጥሪ መቅረቡን አስታውሰው፤ ከበጀት እጥረትና ከክለቦች አለመቋቋም ጋር በተያያዘ ሊሳተፉ አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
ክልሎች ክለቦችን በማቋቋም በሻም ፒዮናው ውድድር ላይ አለመሳተፋቸው ለስፖርቱ ትኩረት ሰጥተው እንዳልሰሩ ማሳያ መሆኑን አቶ ሰይፈ በአፅንዖት ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቼዝ ስፖርትን ለማሳደግ ፌዴሬሽኑ ለክልሎች ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ፤ ለስፖርቱ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም ክልሎች የሚጠበቅባቸውን በመወጣት ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ እንዳልሆነም ነው የተናገሩት፡፡
የቼዝ ስፖርት ክለቦች እጅግ አነስተኛ ቢሆኑም ፌዴሬሽኑ በአራት ክለቦች የጀመረው የሻምፒዮና ውድድር በቋሚነት እንደሚቀጥል አቶ ሰይፈ ገልፀዋል፡፡ የክለቦች ቁጥርም እየጨመረ ይሄዳል የሚል እምነት አላቸው፡፡ የሻምፒዮናው ዓላማ በዘርፉ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትና ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ከዚህም ሌላ ስፖርቱ በአገሪቱ እንዲስፋፋና እንዲጠናከር ለማድረግ ያግዛል፡፡ ‹‹የኢት ዮጵያ ቼዝ ፌዴሬሽን ክለቦች እንዲፈጠሩ በእጅጉ እየሰራ ነው።በቅርቡ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅትም ብዙ ድርጅቶችና ባለሀብቶች የቼዝ ክለብ ለመያዝ ቃል ገብተዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህ በፌዴ ሬሽኑ ጥረት ብቻ ሊፈፀም የሚችል ጉዳይ አይደለም›› ያሉት አቶ ሰይፈ ሁሉም የቼዝ ማህበረሰብ ከፌዴሬሽኑ ጋር አብረው እንዲሰሩና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበ ዋል።
ኢትዮጵያ እና የቼዝ ስፖርት ትውው ቃቸው ጥንታዊነትን ቢላበስም ዕድገቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ብዙ ርቀት መጓዝ ግድ ይላል፡፡በተለይም ደግሞ ክለቦችን ማጠናከርና ማስፋፋት ትልቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። የክለቦች ሻምፒዮና መጀመሩ አንድ እርምጃ ተደርጎ ቢወሰድም፤ክልሎች ክለቦችን ለመመስረት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ስፖርቱ በሚፈለገው ደረጃ እያደገ ይሄዳል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም ስፖርቱ በኢትዮጵያ ውያን ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ለማሳደግ በስፋት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ በቼዝ ስፖርት ዘርፍ የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ አካላትን ተሞክሮ መቅሰም ያስፈልጋል፡፡ ለስፖርቱ ማደግ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡

ዳንኤል ዘነበ

 

Published in ስፖርት
Wednesday, 06 June 2018 17:01

እራትና መብራት ...

ከስራ መልስ ወደቤቴ ለመግባት እርምጃዬን ጀምሪያለሁ። የመንገዱን ዳርቻ ይዤ የእግር መንገዱን እንደጀመርኩ እንደተለመደው አይኖቼን ወርወር አድርጌ ባሻገር ለመቃኘት ሞከርኩ። «አይይይይ... ዛሬም በመንደሩ መብራት የለም። ኡፍፍፍፍ... ሁሌ ጨለማ፣ ሁሌ ችግር..» ደጋግሜ እያማረርኩ ወደፊት እንደያዝኩ ድንገት እንደኔው ማማረር ያለበት ድምጽ ለጆሮዬ ሲደርስ ተሰማኝ።
ከፊቴ ፈጠን ፈጠን እያሉ የሚራመዱ ሶስት ሴቶች ልክ እንደኔው የመብራት ተደጋግሞ መጥፋት ያሰለቻቸው ይመስላል። በተለይ አንደኛዋ በየቀኑ እንጀራ መግዛቱና ማታ ገብቶ በጨለማ መንጎዳጎዱ በእጅጉ አማሯታል። ለነገሩ ለምን አያሰለች? በጣም ያሰለቻል እንጂ። በተለይ ህይወትን በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ላደረገ ነዋሪ የመብራት መጥፋትን ችግር በቀላሉ ሊገልጸው ይቸገራል።
ወዳጆቼ! ህይወት በጋራ ህንጻ ላይ ሲሆን እኮ የውሀና መብራት መጥፋትን ጉዳይ «እስቲ ይሁን» ብለው የሚያልፉት ብቻ አይሆንም። በተለይ መደዳውን ለቀናት ድርግም ያለ እንደሆን ችግሩ በጣም ይሰፋል። የኮንዶሚኒየም ኑሮ ደግሞ ሁሉንም ስራ በኤሌክትሪክ አድርጎታልና እንደሌሎች ሁሉ ወጣ ብለው በእንጨት በኩበቱ ጋግረው ለእራት የሚያደርሱበት አይሆንም።
እንዲህ በሆነ ሰሞን ታዲያ ይመለከታቸዋል የሚባሉ የመብራት ሀይል ባለሙያዎች እንደችግሩ መጠን ፈጥነው ላይደርሱ ይችላሉ። ለተለመደው የብልሽት ጥሪ በርካቶች የሚያውቁት ነጻ የስልክ መስመርም ሲያንቋርር ውሎ ቢያድር የሚያነሳው አይኖርም። ይሄኔ ታዲያ በብዙዎቹ ኮንዶሚኒየሞች ጣራ ስር መብራት ብቻ ሳይሆን ራትም ላይኖር ይችላል።
ሴቶቹ ደጋግመው የሚያወሩት ችግር የእኔም ችግር ሆኖ ሆድ ቢያስብሰኝ ስሜታቸውን በመጋራት ዓይንና ጆሮዬን አልነቅል አልኩ። ከሁሉም ግን በጨዋታቸው መሀል ጣል ያደረጉት አንድ ጉዳይ ውስጤን ይከነከነኝ ይዟል።እነሱ ተደጋግሞ የሚጠፋው የአካባቢያቸው መብራት ብቻ ሳይሆን ሌላም ጉዳይ ጉዳያቸው ሆኗል።ለችግሩ መፍትሄ የሚሉት አማራጭ እውነት ከሆነ ደግሞ እኔንም ሆነ ሌሎችን የሚያሳስብ ይሆናል።
ከሁለቱ መሀል ድምጿ ከፍ ብሎ የሚሰማው አጭሯ ሴት ለተደጋጋሚው ችግር መፍትሄ የምትለውን ሀሳብ አጥብቃ እያነሳች ነው። ሃሳቧ በአካባቢያቸው ተደጋግሞ የተሞከረና መፍትሄ የሚባል አቋራጭ መንገድን ያስገኘ ነው።እሷ እንደምትለው ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ የግቢያቸው መብራት ከህንጻ ህንጻ እየለየ መጥፋት ጀምሯል።ከዚህ ባለፈም በአንዳንዶቹ ቤቶች የሻማ ብርሀን ታህል ጭል ጭል እያለ ብልጭ ድርግም የሚለው መብራት ብዙዎችን ለስጋት ዳርጓል።
እንዲህ በሆነ ጊዜ ማንኛውም በኤሌክትሪክ የሚሰራ መገልገያ እርባና ቢስ መሆኑ አይቀርም።የሀይሉ ከፍና ዝቅ ማለትም ዕቃዎችን ከማበላሸት አልፎ ሊያቃጥልም ይችላል። ይህ አይነቱ አጋጣሚ በሚደርስ ጊዜ ደግሞ ጉዳቱ የሚያመዝነው ለተወሰነ ነዋሪ ብቻ ይሆንና እኩል ችግርን የመካፈሉ ጉዳይ ሳስቶ ይታያል።አንዱ ቤት እየበራ አንዱ ዘንድ ጨለማ መሆኑም ለጉዳዩ ባለቤት ካልሆነ በቀር ለሌሎቹ ትርጉም ላይሰጥ ይችላል።
ወዳጆቼ! እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ በሉልኝ።በአካባቢው ይህ አይነቱ ሁኔታ በተከሰተ ጊዜ ነዋሪዎች ደግመው ደጋግመው ለሚመለከታቸው አካላት ጥሪ ማቅረባቸውን ዘንግተው አያውቁም።የተባሉት ባለሙያዎችም ቢያንስ ከአስሩ ጥሪ ሁለት ያህሉን መቀበላቸው አይቀርም። ይሁን እንጂ ጥሪያቸውን እንደመስማታቸው ፈጥነው ከተባለው ስፍራ አይደርሱም።
ይህን ጊዜ ታዲያ ከአሁን አሁን ደርሰው ከጨለማ ወደ ብርሀን ይመልሱናል የሚሉት ጥቂቶች ጉዳዩ ሲያሳስባቸው የራሳቸውን መላ ይፈጥራሉ።በመላው የመጀመሪያ ምዕራፍም ሰብሰብ ብለው በሚያዋቅሯት ቀጠን ያለች ኮሚቴ ገንዘብ እንዲዋጣ ይወስናሉ። ይህ ገንዘብ የሚዋጣው ለሌላ ጉዳይ እንዳይመስላችሁ።እነዚህ መንግስት በሙያቸው አምኖ ህዝቡን አገልግሉ ላላቸው አንዳንድ ራስ ወዳዶች የእጅ መንሻ እንጂ።
ይህን የጥቅም ቅብብሎሽ ከአንዳንድ መንደሮች የለመዱ አንዳንድ ባለሙያ ነን ባዮች ታዲያ ይህቺን ማላሻ ከነዋሪው ካልቀመሱ እግራቸውን ወደተባለው ስፍራ አያነሱም።ይህን ያልተገባ ድርጊት ያለማመዱ ነዋሪዎችም ችግሮቻቸውን በአግባቡ ከመፍታት ይልቅ የተሻለ ነው በሚሉት የሙስና መንገድ ማለፍን መርጠዋል።ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ እንደደህና ተሞክሮ አሰራሩን ለሌሎች አካባቢዎች ጭምር እያስተዋወቁት መሆኑ ነው።
መንገደኞቹ ሴቶች በአንድም ይሁን በሌላ መፍትሄ ነው ባሉት መንገድ ተጠቅመው የጠፋባቸውን መብራት መመለስ እንደቻሉ በኩራት ይናገራሉ። አሁን ደግሞ ከጠፋ ቀናት ያስቆጠረው የመንደራቸው መብራት ስለመምጣቱ ተስፋ ቢያጡ ያለፈውን ዳግም አስታውሰውና ኪስና መቀነታቸውን ዳብሰው የደንቡን መፈጸም እንደሚኖርባቸው በግልጽ እየመከሩ ነው።
የዛንዕለታ በሰማሁት ድንገቴ ጨዋታ እንደተገረምኩ ወደሰፈሬ ደርሻለሁ። መንገደኞቹን በአይኖቼ ሸኝቼ ወደግቢዬ ሳቀና ሴቶቹ ያለምንም መሳቀቅ ሲያወሩት የነበረው የ«ስጡ ይሰጣችኋል» አይነት ወግ እንዳስደመመኝ ነበር። ወይጉድ...ህገወጥነት ህጋዊ ሆኖ እንዲህ በገሀድ ለወግ መብቃቱ አሁንም በጣም ያስገርማል። በጣም!
ከአግራሞቴ ሳልላቀቅ ወደጨለማው ግቢያችን እንደደረስኩ ሰብሰብ ብለው ከቆሙ ነዋሪዎች መሀል ተቀላቀልኩ። በጊዜው ጨለማው «አይን ቢወጉ አይታይም» የሚባልለት ባይሆንም ጥቂቶቹን በድምጻቸው እንጂ በእይታ ለመለየት ቸግሮኝ ነበር።የስብሰባቸው ምክንያት ከሰሞኑ መብራት መጥፋት ጋር እንደሚያያዝ በመገመቴ በሰላምታ ብቻ ላልፋቸው አልፈለግሁም።አዎ!ሁሉም እኔ እንደገመትኩት ነው።ሰዎቹ ዋናው ጉዳያቸው የመብራት መጥፋትና ሰሞንኛው ችግር ሆኗል።
ከጨዋታቸው መሀል ድንገት ወደጆሮዬ የደረሰው አንድ ጉዳይ ግን እንደአመጣጤ «ደህና እደሩ» ብዬ ልሰናበታቸው አላስቻለኝም።እነሱም እያወሩት ያለው እውነት ከጨለማው መበርታት ጋር ተያይዞ መደረግ ስላለበት አንድ መላ ነበር።አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ መላ የሚባለው ሀሳብ በመንገዴ ካጋጠሙኝ ሴቶች ጨዋታ ጋር አንድ መሆኑ ነው።
የሰማሁትን ባለማመን ደጋግሜ ለማረጋገጥ ሞከርኩ።ጆሮዬ አልተሳሳተም። ሰዎቹ ለቀናት የጠፋውን መብራት ለማስመለስ እንደመፍትሄ ያስቀመጡት ለባለሙያዎቹ የእጅ መንሻ ማቅረብ ብቻ ሆኗል።ከእነሱ መሀል «ለየት ያለ ሀሳብ አለኝ »ያለው አንድ ሰው የሚሉትን በመቃወም የራሱን አስተያየት መስጠት ጀምሯል።እሱ ጎረቤቶቹ ለማድረግ ያሰቡት ጉዳይ ህገወጥ መሆኑንና ይህም አካሄድ ወንጀልን ከመተባበር እንደሚቆጠር እየደጋገመ ይናገራል።
ወዳጆቼ! «ልፋ ያለው» እንዲሉ ሆነና የሰውዬውን አስተያየት ከምንም የቆጠረው አልነበረም።እንደውም አባባሉን በመቃወም በሌሎች ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር በሚል ከስፍራው ገለል እንዲል ተደረገ ።እኔ በሰማሁት እውነት በእጅጉ ተገርሜያለሁ።እራሳችን በምናመጣውና በምናስለምደው አጉል አካሄድ መተብተባችንም አሳዝኖኛል።ሆኖም የሁሉም ሁኔታ ተጨማሪ ሀሳብ የሚያሰነዘር ሆኖ አላገኘሁትም።እናም «ደህና እደሩ» ከማለት ሌላ ምርጫ አልነበረኝም።
በማግስቱ በተለመደው ሰአት ከግቢው ስደርስ ምሽቱ በብርሀን መድመቁን አስተዋልኩ።የትላንቱን ጨለማ አስታውሼም ስለተገኘው መፍትሄ ለማወቅ ውስጤ በጉጉት ተሞላ።በሰአቱ ዛሬን በግቢው መብራት ስለመምጣቱ እንጂ በምን አግባብ ይህ እንደሆነ የሚነግረኝ አላገኘሁም።ዋል አደር ሲል እውነታውን እንደማውቀው ቢገባኝም ይህ የሙስና አካሄድ በዚህ መልኩ እየተለመደ መሆኑ ደግሞ አሁንም ከልቤ አሳዝኖኛል።ለነገሩ አቀባይ ካለ ተቀባይ «አይሆንም» ሊል አይችልም።ግን ለምን ?
ወዳጆቼ!ሰሞኑን በግቢያችን ለቀናት ብርሀን ሆኗልና ራትም መብራትም አላጣንም።ከእኛ ዘንድ እየተለመደ ያለው ይህ የጥቅም ቅብብሎሽ ግን ጨለማ ሳያግደው በቀን ብርሀን መፈጸሙ ወዴት እያመራን ይሆን ?የሚለውን ጥያቄ እየመለሰው አይደለም። እውነት ግን ብርሀን ለማግኘት ብር ብቻውን መፍትሄ ነውን? መንግስትና የሚመለከታችሁ አካላት ሆይ! እስቲ ብዙ ስለሚባሉት ባለሙያዎቻችሁ ማንነት ፈተሽ አድርጉና ውስጣችሁን እወቁት። አበቃሁ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

Published in መዝናኛ
Wednesday, 06 June 2018 16:58

ያለሰበብ….

በሀገራችን በተለያዩ ሙያዎች ስማቸው ደምቆ ከተጻፈ እንስቶች መሀል አንጋፋና ወጣት ሴት ጋዜጠኞች ይገኙበታል። እነዚህ ሴቶች ታዲያ በሙያቸው አጋጣሚ በርካታ የሚባሉ ውጣውረዶችን ሊያሳልፉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አጋጣሚዎቹ ሰበብ ሆነዋቸው ሽንፈትን መቀበል እንደማይፈልጉ ደግሞ ብዙዎቹ  ሲናገሩ ይደመጣሉ። የአዲስ ዘመኗ መልካምስራ አፈወርቅም  እንዲህ አይነት ጠንካራ ተሞክሮ ያላቸውንና ድክመትን አምኖ ለመቀበል ሴትነታቸውን ምክንያት ማድረግ ከማይሹ ጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርጋ የተጋራችውን  ተሞክሮ እንዲህ ታካፍለናለች።

በሬዲዮ ያደመጧት ብዙዎች ድምፀ መረዋነቷን ይመሰክራሉ። የህትመት ላይ አንባቢዎችዋ ደግሞ የብዕር አጣጣሏን እያዩ ያደንቋታል። እሷ ለዓመታት የጋዜጠኝነትን ህይወት ኖራበታለች። በዚህ ሙያ ይበልጥ እውቅናን ታትርፍ እንጂ በሌሎች የማስታወቂያና ኪነጥበብ ስራዎችም ላይ ስሟ ደምቆ እንደተጻፈ ነው። ጋዜጠኛ ቅድስት ክፍለዮሀንስ።
ቅድስት ከዓመታት በፊት ሚዲያውን ስትቀላቀል ሙያውን ያሟሸችው በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ነበር። ሬዲዮ ፋና ሲመሰረት ጣቢያውን ካቋቋሙት ባለሙያዎች መሀል አንዷ ነች። ከመንግስት ለውጥ በኋላ በሀገሪቱ ግንባር ቀደም ሆነው መታተም ከጀመሩትና ተነባቢ ከነበሩት የህትመት ውጤቶች አንዱ በሆነው የእፎይታ መጽሄት ላይም ተቀጥራ ሰርታለች። የዛኔ ከመጽሄቱ ገጾች ተወዳጅ የነበረውን የስፖርት አምድ በማዘጋጀት ብቸኛዋ ሴት የስፖርት ጋዜጠኛ ነበረች።
በወቅቱ በሀገሪቱ ይታወቁ የነበሩ ሴት የእግር ኳስ ተጫዋቾችንና የ«እነእቱ መላምቺ» ቡድንን በማስተዋወቅ አሻራዋን ያኖረችው ጋዜጠኛዋ በእነዚህ ታሪካዊ ስራዎቿ ተወዳጅነትን ለማትረፍ በቅታለች። ቅድስት በጋዜጠኝነት ዓለም ከስራው ጋር በተያያዘ በርካታ ውጣ ውረድ እንደሚኖር ታምናለች። እንደራሷ ዕምነት ግን ይህን እውነታ ከሴትነቷ ጋር አያይዛው አታውቅም።
እሷ በየትኛውም መስክ ተደጋግሞ የሚነገረውንና አሁንም ድረስ በወጉ ያልተቀረፈውን የሴቶችን የበታችነት ስሜት አምኖ የመቀበል እሳቤ ኖሯት አያውቅም። ይህን ስሜት ይዘው የሚጓዙ አንዳንዶችንም በግልጽ ስትቃወም ትደመጣለች። የዚህ አይነቱ አመለካከት የሚዳብርና የሚከስመው ከራስ ማንነት ሲነሱ ይሆናል ትላለች። ይህ እውነታ በሴት ጋዜጠኞች ላይ ሲሆን ደግሞ ትርጉሙን ይበልጥ አጉልቶ ለማየት ይቻላል ባይ ነች።
ጋዜጠኛዋ በስራ ባሳለፈቻቸው ዓመታት በርካታ የሚባሉ በአድልዎ የታጀቡ ድርጊቶችን አስተውላለች። ‹‹ይህ የሴቶች፣ ይህ ደግሞ የወንዶች›› ተብለው በሚለዩ ስራዎችም የሴቷ ይሁንታ ያልታከለበት ክፍፍል እንደሚደረግም ታውቃለች። በአንድ የሚዲያ ተቋም ስትሰራ ያጋጠማትን ጉዳይ አትዘነጋውም። በወቅቱ የሴቶች ፕሮግራም አዘጋጇ አንዲት ባለሙያ ነበረች። የአጋጣሚ ጉዳይ ይሆንና የዛኔ ሴቶችን የሚመለከትና ለፕሮግራሙ የሚያግዝ የውጭ ሀገር ስልጠና ይመጣል። አብዛኞቹም ዕድሉ ለአዘጋጇ እንደሚሰጥ ይገምታሉ። ይሁን እንጂ የታሰበው ቀርቶ ጉዳዩ የማይመለከተው ሌላ ባለሙያ ወደ ውጭ እንዲሄድ ይደረጋል። በወቅቱ ድርጊቱ በርካቶችን ቢያስገርምም ‹‹ለምን ይህ ሆነ ?›› ሲል የተጋፈጠ አካል ግን አልነበረም።
እንደ ቅድስት ዕምነት ማንኛውንም ችግር ተጽዕኖ ነው ብሎ መቀበል በጉዳዩ ላይ እንደመተባበር ይቆጠራል። የማይሆን አካሄድ ሲያጋጥም በአግባቡ ተከራክሮና አሳምኖ መጋፈጥ አዋቂነት ነው። በሴቶች ላይ በየጊዜው ሊሆን የሚችል ተመሳሳይ ችግር መፈታት የሚኖርበት በዚህ ጥንካሬ ሊሆን ይገባል።
ጋዜጠኛዋ ይህን ርዕስ ስታነሳ የራሷን ልምድና በይሁንታ ተቀብሎ ያለማለፍ ተሞክሮን ጭምር አብራ ታወሳለች። እስከ ዛሬ በነበራት ሙያዊ መሰረትም ከስራ ዕቅድ ጀምሮ ከሌሎች የሚመጣውን «የአይሆንም» ተጽዕኖ በሽንፈት ተቀብላ አታውቅም። ሁሌም ቢሆን ማመን ያለባትንና መስራት የሚገባትን ድርሻ የምትወስነው በአለቆች ሀሳብ ብቻ ተደግፋ አይደለም። ይህ መሆኑ በብርታቷ አድማጭ የሆነ ጆሮን እንድታገኝና በራሷ እንድትተማመን አድርጓታል።
‹‹ብዙ ነገሮችን መለወጥ የሚቻለው ነገሮችን አሜን ብሎ በመቀበል ብቻ አይደለም›› የምትለው ቅድስት እስከመጨረሻው ጠንካራ አቋም ይዞ ለመዝለቅም ትግሉ የሚጀምረው ከራስ በሚፈልቅ ቁርጠኝነት ነው ስትል ታረጋግጣለች። በተለይ ሴት ጋዜጠኞች ለሚኖሩበት ስራ አመኔታና ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል። ይህን ማድረግ ከተቻለ በእርግጠኝነት ተጽዕኖን ሰብሮ ለማለፍ ቀላል ነው። እንዲህ ሲሆንም አብሮን የቆየውን ልማድና ባህላዊ ዕንቅፋትን ተሻግሮ ውጤትን ለመጨበጥ መንገዱ አጭር ይሆናል። ለዚህም ያለሰበብ አስባብ ማንነትን በተግባር ማሳየት ግድ እንደሚል አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ቅድስት ትናገራለች፡፡
የኮሚኑዩኬሽንና የሚዲያ ባለሙያዋ ቤተልሄም ነጋሽ በፖለቲክስና ማስሚዲያ ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪዋን ከሊቨር ፑል ዩኒቨርስቲ አግኝታለች። ቤተልሄም ለሰባት አመታት በቆየችበት የጋዜጠኝነት ሙያ በአማራ ክልል ብዙሀን መገናኛ በዜና አስተባባሪነትና በሬዲዮ ዜና ኤዲተርነት ላይ ድርሻ ነበራት ። በተመሳሳይ ሁኔታም በሪፖርተር ጋዜጣ ከከፍተኛ ሪፖርተር እስከ አዘጋጅነት ደርሳለች። በእነዚህ ዓመታት መሀልም ባገኘችው የትምህርት ዕድል ወደ ዛምቢያ ተጉዛ በሀገሪቱ ታዋቂ በሚባሉ ሁለት ጋዜጦች ላይ የመስራት አጋጣሚ አግኝታለች።
ቤተልሄም ልክ እንደ ቅድስት ሁሉ በሴት ጋዜጠኞች ላይ የሚደረጉ ተጽዕኖዎች እንዳሉ ታምናለች። እንደ እሷ አተያይም የሴቶችና የወንዶች በሚል ክፍፍል የሚደረግባቸው ስራዎች ጥቂቶች አይደሉም። እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ለመደጋገማቸው አንዱ ምክንያት ደግሞ ራሳቸው ሴቶቹ ይዘውት የዘለቁት በራስ ያለመተማመን ልማድ እንደሆነ ትናገራለች።
እንደ ቤተልሄም ዕምነት በአብዛኞቹ የሚዲያ ተቋማት ጠንካራ ሀሳብ አላቸው የሚባሉ ጉዳዮችን ለሴቶች አሳልፎ የመስጠቱ ልማድ የሳሳ ነው። ርዕሰ ጉዳዮቹ ጊዜ የሚወስዱ፣የሚያመራምሩና አጠያያቂ ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብም ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በብቃት ይወጡታል ተብሎ ይታመናል። ሴቶችም ቢሆኑ ባለባቸው ማህበራዊ ጫናና የቤተሰብ ኃላፊነት ምክንያት በቀላሉ መረጃ የሚገኝባቸውንና ጊዜ የማይወስዱ ስራዎችን ቢከውኑ ይመርጣሉ።
ቤተልሄም በተለይ በጋዜጣ ስራ ላይ በቆየችባቸው አመታት ለሁሉም ጋዜጠኛ ስራን ፈልጎና መርጦ የመስራት ዕድል ይሰጥ እንደነበር ታስታውሳለች። በዚህ ጊዜ ታዲያ የአብዛኞቹ ሴት ጋዜጠኞች ምርጫ ከፖለቲካ፣ቢዝነስና ወቅታዊ ጉዳዮች ይልቅ ኪነጥበብና መዝናኛ፣ማህበራዊና ሴቶች፣ህጻናትና ጤና የመሳሳሉ አምዶችን መሸፈን ላይ ያመዝን ነበር። ይህ ልማድም ባለሙያዎቹ በነዚህ ስራዎች ላይ ብቻ ተወስነው እንዲቀሩ ምክንያት ፈጥሯል ትላለች፡፡
እንደ ጋዜጠኛዋ ዕምነት እነዚህ ተጽዕኖዎች የሚንጸባረቁት በስራ አካባቢዎች ብቻ አይደለም። ሴት ጋዜጠኞች በሙያቸው አጋጣሚ ሲንቀሳቀሱም ከአንዳንድ ሰዎች የሚደርስባቸው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም። በጾታቸው ከሚያጋጥማቸው ትንኮሳ በዘለለ የያዙትን የዘገባ ሀሳብ በተለያየ ጥረት ለማስለወጥ ሲባል የሚደረግባቸው የውዴታና ግዴታ ሙከራዎች ጠንከር ሊሉ ይችላሉ።
ቤተልሄም በአንድ ወቅት ይዛው በነበረው የምርመራ ዘገባ ስራዋን ጫፍ ከሚያደርስላት መቋጫ ላይ ትደርሳለች። ይህን እውነታ በትክክል የሚያውቀው የጉዳዩ ባለቤት ታዲያ ዜናው ለህዝብ እንዳይደርስ የማድረግ ጥረቱን ይቀጥላል። በወቅቱ ግለሰቡ የነበረው ጥረት ከውዴታ ጋር የተለወሰ አስገዳጅነት ነበር። ይሁን እንጂ በማስፈራራትና በጥቅማ ጥቅም ተከልሎ ያደረገው ሙከራ የተሳካ አልነሆነም። የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ለጋዜጠኛዋ የሰጠው የህግ ከለላ ጭምር መንገዱን በአጭር እንዲቋጭ አደረገው ።
ብዙ ጊዜ የአንዳንድ ተቋማትን ብልሹ አሰራር አስመልክቶ ለዘገባ ባዋላቻቸው ዜናዎች ምክንያት ብዙ ችግሮች ደርሰውባታል። ማስፈራራትን ጨምሮ ስድብና ቁጣ ያለበት ተግሳጽንም አስተናግዳለች። እንደ ቤተልሄም ዕምነት ይህ ሁሉ የሆነው ሴት በመሆኗና አንዳንዶች በእሷ መሆኑን መቀበል ባለመፈለጋቸው ነው። አንዳንዴ ደግሞ አንዳንድ ሴቶች ብቃታቸውን አውጥተው ከመጠቀም ይልቅ ሽንፈትን አምኖ የመቀበል ልማድ አላቸው። እንዲህ ሲሆን ደግሞ የነበረ አመለካከት እንዳይቀየርና የተሻለ ለውጥ እንዳይመጣ ምክንያት ይሆናልና ማንኛዋም ሴት ጋዜጠኛ ያለሰበብ አስባብ ጥንካሬዋን ልታሳይ ይገባታል ትላለች።
ገነት ገብረ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የአቅም ግንባታ ክፍል የምትሰራ ባለሙያ ናት። ገነት በቅርቡ ለሁለተኛ ዲግሪዋ የሰራችው የሟሟያ ወረቀት በሚዲያዎች ውስጥ የሚታየውን የስርአተ ፆታ ክፍተትን የሚመለከት ነበር። ጥናቷን መሰረት አድርጋ በተንቀሳቀሰችባቸው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ተቋማት የአለም አቀፍ ህጎችን መሰረት ያደረገ ጥናት ስታደርግ ቆይታለች።
የሚዲያ ተቋማቱ ህጎቹን በአግባቡ ከመረዳት ጀምሮ ያላቸውን ግንዛቤና በወንዶችና ሴቶች ባለሙያዎች መካከል የሚኖረውን ልዩነት በተመለከተም ዳሰሳዎች አድርጋለች። ተቋማቱና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ያላቸውን ድርሻም በጥናቷ ለመለየት እንደሞከረችም ትናገራለች። በሁለቱም የሚዲያ ተቋማት ባገኘችው ውጤት መሰረትም የስርአተ ፆታ ጉዳዮች ክፍተት የሚታይባቸው ሆነው አግኝታቸዋለች።
ሁለቱም የሚዲያ ተቋማት የሴቶችን ጉዳይ የሚፈርጁት በተለያየ አተያይ ላይ ተመስርተው ነው። ለዚህ አባባሏም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እየተሰራበት ያለውን ሂደት እንደምሳሌ ታነሳለች። በአዲስዘመን ጋዜጣ ላይ ሴቶችን በተመለከተ የሚወጣው አምድ ራሱን ችሎና የሴቶች ገጽ በሚል የተለየ አይደለም ። ይህ ገጽ ማህበራዊን ከሴቶች የሚያጋራ ሲሆን በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚፃፍበት።
በገነት ዕምነት የሀገሪቱ ማህበረሰብ ለወንዶች የሚያደላ ሆኖ ታገኘዋለች። ራሳቸው ሴቶችም ቢሆኑም አብዛኛውን ጊዜ ሴቶችን የሚጎዱ አስተሳሰቦችን ሲያራምዱ አስተውላለች። ይህ እውነታ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ሲመነዘር ደግሞ ከኋላ ቀር አመለካከት የጸዳ ዘገባን ለማስተላለፍ የማያስችል ይሆናል። ከዚህ አስተሳሰብ ያልወጣ ማንኛውም ሰው ሴትና ወንድ መባሉ ብቻ ሳይሆን በሚይዘው የአመለካከት ሚዛንም ተጽዕኖውን ሊያሳርፍ ይችላል።
‹‹የስርአተ ፆታ ጉዳይ ለአንድ የመንግስት አካል ብቻ የሚተው ሊሆን አይገባም›› የምትለው ገነት ሌሎች ኃላፊነቱ የተጣለባቸው ተቋማትም በአለም አቀፍ ደረጃ የተፈራረምንባቸውን የስርአተ ፆታ ጉዳዮችን መሰረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ ትናገራለች። ከሁሉም በላይ ግን የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች ካልተገቡ አመለካከቶች ተላቀው በመልካም መንገድ ሊራመዱ ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በተለይ ሴቶችን አስመልክቶ የተለመዱ ምክንያትና ሰበቦችን አርቆ ማስወገድ ግድ ይላል። ሰበብ ለማንምና ለምንም አይበጅምና።

 

Published in ማህበራዊ

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች መከሰታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ተስተጓ ጉለዋል፡፡ ለግጭቶቹ መከሰት ገዥው ፓርቲ የመልካም አስተዳደር እጥረትን በቀዳሚነት ሲያስቀምጥ፤ ሌሎች ደግሞ ቋንቋን መሰረት ያደረገው የፌዴራል ሥርዓቱ የግጭቱ መንስዔ ነው ሲሉ ተደምጧል፡፡
«ገዥው ፓርቲ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን ያበረታታል፤ ከኢትዮጵያዊነት ብሔርተኝነት ጎልቷል» የሚሉ ሃሳቦችም ይንሸራሸራሉ፡፡ በእነዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከፌዴራልና አርብቶ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ፡፡
አዲስ ዘመን፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሆነው ያልተማከለ አስተዳደር በአሃዳዊ ሥርዓትም ስላለ ፌዴራሊዝም ይዞት የመጣው አዲስ አስተዳደር አይደለም የሚሉ አሉ?
አቶ ሙሉጌታ፤ ፌዴራሊዝም ሁለትና ከሁለት በላይ የሆኑ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በጋራ ለመኖር በቃል ኪዳን ላይ መነሻ ተደርጎ የሚመሰርቱት አጋርነት ነው፡፡ ፌዴራሊዝም ካልተማከለ አስተዳደር ይለያል፡፡ ያልተማከለ አስተዳደር የፌዴራሊዝም አንዱ ገፅታ እንጂ ሁሉ ነገር አይደለም፡፡ ያልተማከለ አስተዳደር እየተከተሉ ፌዴራል ያልሆኑ አገራት አሉ፡፡
ያልተማከለ አስተዳደር በአሃዳዊ ሥርዓት ውስጥም አለ፡፡ እነዚህ መንግሥታት ለታችኛው የመንግሥት እርከን የተገደበ ነፃነት ነው የሚሰጡት፡፡ ዕዙ ከላይ ሆኖ የታችኛው አንፃራዊ ነፃነት አለው፡፡ ፌዴራሊዝም ግን ለታችኛው ያልተገደበ ሥልጣንና ሰፊ ነፃነት ነው የሚሰጠው፡፡ ቆርሶ የሚሰጠው ሥልጣን የለም፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት እንዲፈቅድ ሳይጠበቅ በራስ ጊዜ መሪዎችን መምረጥ፣ በአካባቢው ያለውን ሀብት ማስተዳደር፣ መምራት፣ ክልልና አካባቢን ማሳደግና ቋንቋን ማጎልበትን ይፈቅዳል፡፡
አዲስ ዘመን፤ ዴሞክራሲን ሳይገነቡ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን መተግበር አዳጋች ነው የሚሉ አካላት አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ሙሉጌታ፤ ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲ የሚጋጩ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ትክክለኛ ፌዴራሊዝም ያለ ዴሞክራሲ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም፡፡ አንዱ ያለ ሌላው ሊኖሩ የማይችሉ አብረው የሚጀመሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምን የመረጠችበት አራት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ አንደኛው ብዝኃነት ነው፡፡ ከ76 በላይ የሆኑትን ብሔሮች በአግባቡ አቻችሎ፣ አግባብቶ በሠላም ለማኖር ተመራጩ ፌዴራሊዝም ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የምንፈልጋትን ጠንካራ አገር ለመመስረትና የአገር አንድነትን ለመጠበቅ ፌዴራሊዝም ወሳኝ ሥርዓት መሆኑ ነው፡፡ ህዝቦቿ ያለ ስጋት የሚኖሩባት ሠላማዊ አገር መፈለግ በሦስተኛ ምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከመምጣቱ በፊት በአገሪቱ ሠላም አልነበረም፤ የተለያዩ ግጭቶችና ጦርነቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን በማስወገድ ሠላምን ማስፈን እንደሚገባ ታምኖ ነው ወደ ሥራ የተገባው፡፡
ዴሞክራሲን በዚህች አገር ለማስፈን ማሰብ አራተኛው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ምርጫ ምክንያት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ዕኩልነት፣ የሃሳብ ነፃነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነው፡፡ ብዝኃነትን በአግባቡ የሚያስተዳድረው ዘይቤ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ልዩነቶችን አቻችሎ ለማስተዳደር ደግሞ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ እናም ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን፤ ግጭትን የሚያቆም ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ባህሉ እየጎለበተ ሲሄድ የፌዴራል ሥርዓቱ በትክክለኛ ጎዳና ላይ ይራመዳል፡፡ ይህ ሲሆን ዴሞክራሲው እየዳበረ ይሄዳል፡፡ ሁለቱ የሚመጋገቡ በመሆናቸው አንዱን ጥሎ ሌላውን ይዞ መሄድ የማይታሰብ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፤ የፌዴራል ሥርዓቱ አደረ ጃጀት በቂ ጥናት ሳይደረግበትና ህዝቡ ሳይመክርበት ነው ተግባራዊ የተደረገው የሚል ትችት ይቀርባል፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
አቶ ሙሉጌታ፤ የፌዴራል ሥርዓቱ አደረጃጀት የብሔር ብሔረሰቦችን ቋንቋ፣ ፈቃደኝነትና አሰፋፈርን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ክልሎቹ ህገ መንግሥቱ ከመፅደቁ በፊት ነው የተካለሉት፡፡ ይህም ሲሆን ግን የፌዴራል ሥርዓቱ የተደራጀበት መስፈርቶች ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ መስፈርቶችም በኋላ ህገ መንግሥቱ ሲጸድቅ እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ ውይይቱ በቂ ላይሆን ይችላል ቢባልም በወቅቱ ህዝቡን ለማወያየት ጥረት ተደርጓል፡፡ ክልሎቹ ከተካለሉ በኋላ ቅሬታና ይግባኝ ያቀረቡ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በደቡብና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ቅሬታዎች ቀርበው ምላሽ አግኝተዋል፡፡ በዚህም በኦሮሚያ ተካለው የነበሩ ወደ ደቡብ፤ እንዲሁም በደቡብ ተካለው የነበሩ ወደ ኦሮሚያ ክልል የተመለሱበት አግባብ አለ፡፡ ቅሬታ ያለው አካል አሁንም ድረስ ቅሬታውን እያቀረበ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ይህ በፌዴራል ሥርዓቱ በግልፅ ተቀምጧል፡፡
የኢትዮጵያን የፌዴራል ሥርዓት አደረጃጀት የተከተሉ የተለያዩ የዓለም አገራት አሉ፡፡ ህንድና ስዊዘርላንድን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስዊዘርላንድን የጀርመን፣ የኢጣሊያንና የእስራኤል ህዝቦች በማንነ ታቸው ላይ ተመስርተው ነው የከለሉት፡፡ በዚህም በፌዴራሊዝም ሥርዓት ከአውሮፓ የተሳካላት አገር ተደርጋ ትጠቀሳለች፡፡ በካናዳም እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ህዝቦች የመሰረቱት የፌዴራል አወቃቀር አለ፡፡ በዚህም ጠንካራ አገር መመስረት ችለዋል፡፡
አዲስ ዘመን፤ የተለያዩ አካላት የፌዴራል ሥርዓቱ የግጭቶች መንስዔ ሆኗል ሲሉ ይደመጣል?
አቶ ሙሉጌታ፤ የፌዴራል ሥርዓቱ የግጭት መንስዔ አይሆንም፡፡ ሥርዓቱ እንዲያውም ረጅም ዓመት ያስቆጠሩ ግጭቶች አልባት እንዲያገኙ ረድቷል፡፡ ለምሳሌ ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠረው የአፋርና የሶማሌ የኢሳ ግጭት ተፈትቷል፡፡ በጋምቤላና በደቡብ ክልሎች በቤሮና ዲማ መካከል የነበረው ግጭት እልባት አግኝቷል፡፡ ሌሎች ግጭቶችንም በተጨባጭ መፍታት የተቻለው በፌዴራል ሥርዓቱ ነው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ አዳዲስ ግጭቶች መከሰታቸው አይካድም፡፡ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ግን የሥርዓቱ ችግር አይደለም፡፡ በዕድገት ብልፅግና ተጉዘን የሰዎች ዋናው ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ብሔርና ሃይማኖት ዋናዎቹ መገለጫዎች ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ብሔርና ሃይማኖት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በአግባቡ ተኮትኩተው ካልተያዙ የግጭት መንስዔ ይሆናሉ፡፡ አሁን በተጨባጭ ያጋጠመንም ይሄው ነው፡፡ ድህነትና ኋላቀርነት እስኪወገድ ድረስ ጊዜያዊ ችግሩ ሊያጋጥም ይችላል፡፡
በአውሮፓና በዓለም ኃያል አገር የሆነችው ጀርመን በፊት በከረረ የብሔር ግጭት ውስጥ ነበረች፡፡ ይህም ዜጎቿንና እስራኤላውያንን እንድታጠፋ አድርጓታል፡፡ አሁን በጀርመን የብሔር ጉዳይ በሁለተኛ ደረጃ ነው የሚታየው፡፡ ዋናው ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ነው፡፡ እኛ በዕድገት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለሆን ብሔርን እንደ ዋና የሥልጣን ማግኛ፣ ከውድድር ውጪ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስቡ አካላት አጋጣሚውን ለመጠቀም ይሞክራሉ፡፡ ለዚህ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት መጠንቀቅና መታገል ይገባል፡፡
አሁን የሚታየው ነገር ሊነጋጋ ሲል ያለ ጨለማ ዓይነት ነው፡፡ ሥልጣኔ ሲረጋገጥ በብሔር ተከፋፍሎ መጋጨት ኋላ ቀርነት ይሆናል፡፡ ይሄም በቅርብ ጊዜ እውን እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ተርታ የመሰለፍ ራዕይ ስላላት ዕውን ይሆናል፡፡ ያኔ ኋላ ቀርነት ይጠፋና ግንኙነቱ የኢኮኖሚ ፍላጎት ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፤ ይህ ዕውን እስኪሆን ድረስ ምን መሠራት አለበት?
አቶ ሙሉጌታ፤ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ተደርሶ የግጭት መንስዔዎች እስኪወገዱ ድረስ ግጭቶችን የመከላከልና የመዋጋት ሥራ በስፋት መከናወን አለበት፡፡ እነዚህ አመለካከቶች አንድነትን የማያመጡና ዕኩልነትን የማያረጋግጡ መሆናቸውን ማስተማር ይገባል፡፡ ስለ አንድነት ጠቀሜታና ፋይዳ ማስረዳት፤ ኢትዮጵያ ከክልሎች እንደምትበልጥ ማስገንዘብ፤ በየክልሎቹ የተገኙትን መብቶች በመጠቀም ለዕድገት መሥራት እንደሚገባ በተጨባጭ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ መገናኛ ብዙኃንና የኪነ ጥበብ ተቋማት በትኩረት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ህዝቡ አንድነትን ከማያመጡ አመለካከቶች ራሱን እንዲያርቅ መስበክ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
አንዳንድ ራሱን ለመጥቀም በየአካባቢው ንጉሥ መሆን የሚፈልግ ሰው ይኖራል፡፡ ይህን ራስንና የራስን ብሔር ለመጥቀም የሚደረግን የተሳሳተ አመለካከት ማስወገድ ይገባል፡፡ ጊዜያዊ ህመሙን በመፈወስ አንድነትን ማጠናከር ይቻላል፡፡ እነዚህ ችግሮች ሥርዓቱ እየተጠናከረ ሲሄድ ይወገዳሉ፡፡ ሰው እስካለ ድረስ በዓለም ላይ ግጭትን መቀነስ እንጂ ማስወገድ አይቻልም፡፡ ሥርዓቱ ግጭት ከደረሰ በኋላ ሳይሆን ቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ ነገሮች ወደ ግጭት ከመሄዳቸው በፊት ቀድሞ የማምከን አሰራርን መከተል ይገባል፡፡ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ችግሮቹን የመከላከል ሥራ ይሠራል፡፡
አዲስ ዘመን፤ ኢህአዴግ ከአንድነት ይልቅ ለልዩነት ይተጋል፡፡ ይህም ህዝቡን በመከፋፈል ለግጭት በር ከፍቷል የሚሉ ወገኖች አሉ?
አቶ ሙሉጌታ፤ ኢህአዴግ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን እንደሚያበረታታ የሚገለጸው አስተያየት የተሳሳተ ነው፡፡ ይህን የምለው የመንግሥት ባለሥልጣን ስለሆንኩ ሳይሆን አመለካከቱ ስህተት ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ወዶ ነው ኢትዮጵያዊ የሆነው፡፡ ስለዚህ በፈቃድ የተመሰረተ ህብረት ነው፡፡ አንዱ ቤተኛ ሌላው መሥራች አይደለም፡፡ ህገ መንግሥቱ «ያለፈውን የተዛባ ግንኙነት አስተካክለን፤ መልካሙን መስተጋብር አጠናክረን እንቀጥል» ይላል እንጂ እንለያይ አላለም፡፡ ይህ በግልፅ የተቀመጠ እውነታ ነው፡፡ ለአንድነት እንዳልተሠራ አድርጎ ማስቀመጥ አይገባም፡፡
የህዝቦች የቋንቋ፣ የብሔር፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ በፌዴራሉ ውስጥ ያላቸው ውክልና በግልፅ ተረጋግጧል፡፡ አገር ከምታፈራው ጥሪት ላይ ፍትሀዊ ተጠቃሚ የመሆኑ ዕድሉ እየሰፈነ ነው፡፡ በዚህ በኩል ውስንነት ቢኖርም ሥርዓቱ ተዘርግቷል፡፡ ይሄ ለአንድነት የተከፈለ መስዋዕትነት ነው፡፡ መሰረተ ልማት በፍትሀዊነት እየተከናወነ ነው፡፡ መንገድና ዩኒቨርሲቲዎች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ተሠርቷል፡፡ በኢኮኖሚ የበለጸገች አንዲት አገር የመፍጠሩ ጉዞ የአንድነት ማሳያ ነው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ ሰዎች ተንቀሳቅሰው የመሥራት ነፃነታቸውን የተፃረረ ድርጊት መስተዋሉ አይካድም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ይህን መሰሉን ህገ ወጥ ድርጊት የፈጸሙ አሉ፡፡ እነዚህ አካላት የዜጎችን መብት በመፃረር አባረዋል፡፡ ነባርና መጤ የሚሉ ክፍፍል በመፍጠር የዜጎችን መብት አጓድለዋል፡፡ አንዳንዶቹ ሀብት እስከ መዝረፍና ህይወት ማጥፋት ደርሰዋል፡፡ ይህን አንድነትን የማያጠናክር ህገ ወጥ ድርጊትን መከላከል ይገባል፡፡
አንዳንድ የህግ ማሻሻያዎችም ያስፈልጋሉ፡፡ የአንዳንድ ክልሎች ህገ መንግሥት የዚህ ክልል መሥራቾች እነ እንትና ናቸው ብሎ በግልፅ ፅፏል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፤ ከፌዴራሉ ህገ መንግሥት ጋርም ይፃረራል፡፡ ህገ መንግሥቱን በተንጋደደ መልኩ የመተግበር ሂደትም ይስተዋላል፡፡ ይህ አንድነቱ እንዳይጎለብት አድርጓል፡፡ ዜጎች በነፃነት የሚንቀሳቀ ሱበትን፣ ባለሀብቶች ተዘዋውረው የሚያለሙበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፤ ለተፈጠሩት ግጭቶች ተጠያቂው ማነው? የተጣረሱ ህጎችን በማስተ ካከል በኩል የተወሰደ እርምጃስ አለ ወይ?
አቶ ሙሉጌታ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ኃላፊነቱን የሚወስደው የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ አንድነትን በማጠናከር በኩል በደንብ ያልሠራው የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ ይሁንና ክልሎችም አንድነትን በመገንባት ረገድ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵ ያውያን ተሰባጥረው ነው የሚኖሩት፡፡ ለምሳሌ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፡፡ ክልሉ አንድነትን በመገንባት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን እኩል ማስተዳደር አለበት፡፡
በጉሙዝ ክልል በአማራ ክልል ተወላጆች ላይ ቅሬታ ሲፈጠር ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ነው የሚጋጨው፡፡ እያንዳንዱ ክልል በክልሉ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ዕኩል ማስተናገድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በየክልሉ እንድትኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ክልሎቹን በዝርዝር በመፈተሽ ሁሉም ህገ መንግሥቶች ከፌዴራሉ ህገ መንግሥት ጋር የሚጋጩና የማይጋጩ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል፡፡ አንድነትን የሚያረጋግጡ መሆናቸውንም እንፈትሻለን፡፡ አሁን በአስፈላጊነቱ ላይ የመግባባት ጉዳይ እንጂ እርምጃ መውሰድ አልተጀመረም፡፡ ነገር ግን ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ በመሆኑ በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል፡፡ የምርጫ ህጉን ለማሻሻል ወደ ህገ መንግሥት ማሻሻያ ስለሚገባ እግረ መንገዱን ለአገር አንድነት የሚጠቅሙ ሥራዎችን ክልሎቹ ተገደው ሳይሆን አምነውበት እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፤ አንድነቱን ለማጠናከር ምን መሠራት አለበት
አቶ ሙሉጌታ፤ የአንድነትን ፋይዳ በክልሎች ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ማስተማር ይገባል፡፡ የጋራ ታሪክን መፃፍ፣ ጀግኖቻችንን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ የአፋር ሥርዓተ ትምህርት ስለ ራሱ ብቻ ሳይሆን ስለሌሎቹም ማሳየት አለበት፡፡ ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ጋር እንዴት መኖር እንዳለበት ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ፀረ አንድነት ተግባራት ሲስተዋሉ በፍጥነት ማረምና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ችግር የፈጸመ ሰው ያለ ምህረት ፍርድ ቤት እንዲቀርብና እንዲቀጣ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የተወሰደውን እርምጃ ለህዝብ በማሳወቅ መተማመንን መፍጠር ይገባል፡፡
በፌዴራል ተቋማት የክልሎች ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖር መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የአገር መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊሲ፣ የእርሻና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የመሳሰሉ ተቋማት ብቃት ለድርድር ሳይቀርብ ተመጣጣኝ ውክልና ኖሮ ኢትዮጵያን እንዲመስሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የአገርህን ዕወቅ ክበባትና የባህል ትውውቅ መድረኮችን ማጠናከር ለአንድነቱ ይጠቅማል፡፡
አንዳንድ ክልሎች ላይ የክልሉ ተወላጆች አማርኛን በደንብ አይማሩም፡፡ ቋንቋውን ስለማይችሉ ፌዴራል መሥሪያ ቤት መጥተው መቀጠር አይችሉም፡፡ በዚህም የተነሳ የአንዳንድ ክልሎች ተወላጆች በፌዴራል ተቋማት ላይ የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ይህን በፍላጎት መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ህገ መንግሥቱ አማርኛ የሥራ ቋንቋ መሆኑን በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉልና ደቡብ ክልሎች አማርኛን በፍላጎታቸው የሥራ ቋንቋቸው አድርገዋል፡፡ ወጣቶች ቋንቋውን በደንብ ተምረው በፌዴራል ደረጃ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ለማመቻቸት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ተሳትፎዋቸው እየጨመረ ይሄዳል፡፡
አዲስ ዘመን፤ ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ አለማግኘታቸው ቅሬታዎች ወደ ግጭት እንዲያድጉ አድርገዋል ለሚሉት ትችቶች የእርስዎ ምላሽ ?
አቶ ሙሉጌታ፤ ችግሮች ሲከሰቱ ታች ያለው የአካባቢው አስተዳደር መረጃውን ቶሎ የማግኘት ዕድል አለው፡፡ በየደረጃው ያሉ አካላት ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ፈጣን ምላሽ የመስጠት ችግር አለባቸው፡፡ ለዚህ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት አንዱ ቸልተኝነት ነው፡፡ ይህ ለህዝብ ጥያቄዎች ደንታ ቢስ ከመሆን የዘለለ አይደለም፡፡ ሌላው ችግር መረጃውን አለማግኘት ነው፡፡ ወደ ግጭት የሚወስድ ነገር እያለ በክትትል ማነስ መረጃውን ያለማግኘት ችግር አለ፡፡
አመራሩ ሆን ብሎ ግጭት ሲፈጥርም ይስተዋላል፡፡ ህዝቡ ተጋጭቶ አያውቅም፤ ወደፊትም አይጋጭም፡፡ አንዳንድ አመራር፣ የፀጥታ ኃይል ወይም የጎሳ መሪ ህዝቡን ወደ ግጭት ይመራል፡፡ አመራሩ ለሚደርሰው መረጃ በፍጥነት መልስ መስጠት ቢችል ነገሮች ወደ ግጭት አያመሩም፡፡ ራሱ የግጭት መንስዔ ከመሆን ተቆጥቦ ለህዝቡ ቢሠራ ውጤቱ የተለየ ነው የሚሆነው፡፡ ህዝቡን በአግባቡ በሠላም ጉዳይ ላይ አለማሳተፍም ለግጭቶች መከሰት የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከቱ አይካድም፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱ የፈጠረውን ምቹ ዕድል አልተጠቀምንበትም፡፡ በፊት ሞያሌ ላይ የተፈጠረ ግጭት መረጃው አዲስ አበባ ለመድረስ ሁለት ወር ይፈጅበታል፡፡ የግጭት ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት አልነበረም፡፡ በዚህ በኩል ጠንካራ ሥርዓት አለመዘርጋቱ ክፍተት ፈጥሯል፡፡
አዲስ ዘመን፣አመሰግናለሁ
አቶ ሙሉጌታ፣እኔም አመሰግናለሁ

ዳንኤል ንጉሤ

 

Published in ፖለቲካ

በጃፓን ‹‹ካይዘን›› የሚለው ቃል ቀጣይነት ያለው ለውጥ የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ በጃፓን ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም የካይዘንን የፍልስፍና ዘዴ ተግባራዊ ያደረጉ ኩባንያዎች ውጤታማ ሆነዋል፡፡ ብዛትና ጥራት ያለው ምርት በፍጥነት በማምረት በዓለም ገበያ ተወዳድረው ማሸነፍና የደንበኞቻቸውን እርካታ መጠበቅ ችለዋል፡፡ዛሬ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች ተብለው ከሚጠሩት አንዱ የጃፓኑ መኪና አምራች ኩባንያ ቶዮታ ነው፡፡
በጃፓን ቶዮታ ኩባንያ ተጀምሮ ወደ ዓለም የተሰራጨው የካይዘን የአሰራር ፍልስፍና ጥበብ ዛሬ ለብዙ ኩባንያዎች ዕድገት ብቻ ሳይሆን ለአገራትም የብጽግና ካባ የደረበ መሆኑን በኩራት ምስክርነት ይሰጡለታል፡፡ በካይዘን ፍልስፍና ዘዴ በአጭሩ ማቀድ፣ አስፈላጊና አላስፈላጊ ዕቃዎችን መለየት፣የተለዩትን ዕቃዎች ማደራጀት፣ማፅዳት፣አሰራሩን ማላመድና የማዝለቅ ሂደቶች ይተገበሩበታል፡፡
ይህ ዓለም የሚያወድሰው የካይዘን ፍልስፍና በኢትዮጵያ መተግበር የጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ የካይዘን ኢንስቲትዩት ከተቋቋመ አምስት ዓመቱን ይዟል፡፡ በሙከራ ደረጃ በተለያዩ ፋብሪካዎች ተግባራዊ ተደርጎ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በእነዚህ ዓመታትም በተቋማት ይባክን የነበረውን ሀብትና የሰው ሀይል በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል፡፡ በሀምሌ ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተመረጡ 38 ፋብሪካዎች አሰራሩን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ የእነዚህ ፋብሪካዎች አተገባበር ወጣ ገባ የታየበት ቢሆንም የተሻለ የሚባል ለውጥ ማምጣታቸውን በግምገማ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ፣የብክነት ችግር ያለባቸውና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ተክተው የሚያመርቱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት የማኑፋ ክቸሪንግ ዘርፍ የምግብና መጠጥ ኢንዱስት ሪዎች የካይዘን ሽግግርና ልማት ዳይሬክተር አቶ አስናቀ ጉዲሳ ባለፈው አንድ ዓመት ያህል 38 ፋብሪካዎች ተመርጠው የካይዘንን አሰራር ፍልስፍና ሂደት ተግባራዊ እያደረጉ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ ከተመረጡ ኢንዱስትሪዎች መካከልም የስጋና ወተት፣ኬሜካል፣ብረታ ብረት ፣ቆዳና ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ይገኙበታል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ እነዚህ ፋብሪካዎች አሰራሩን ተግባራዊ በማድረጋቸውም የተሻለና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ችለዋል፡፡ በዚህም መሰረት የምርት ብክነት ቀንሷል፤ ምርታማነት ጨምሯል፤ የጥሬ ዕቃ ብክነትና የስራ ቦታ አደጋ መጠን ቀንሷል፤ ለዕቃዎች ፍለጋ የሚባክን ጊዜ ማዳን ተችሏል፤ የተደራጀና ለሥራ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፤ የሥራ ተነሳሽነት ተሻሽሏል፡፡
በፋብሪካዎቹ አላስፈላጊ ዕቃዎችን በመሸጥና የተለያዩ መሳሪያዎችን እንደገና ጥቅም ላይ በማዋላቸውም በስድስት ወራት 13 ሚሊዮን ያህል ብር ማዳን ተችሏል፡፡ ለአብነትም ከጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች አዲስ ጋርመንትና አዳማ ፈትል፣ ከስጋና ወተት ፋብሪካዎች ደግሞ ሾላና ሉና ኤክስፖርት ቄራ ጥሩ ለውጥ የታየባቸው እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
በትግበራው ወቅት ካጋጠሙት ችግሮች መካከልም በከፍተኛ አመራሩ ድጋፍ ያለማግኘት፣ ካይዘንን እንደ ተጨማሪ ሥራ መቁጠርና የተለያዩ ንብረቶችን የማስወገድ ሂደት መዘግየት ይገኙበታል፡፡እንዲሁም ደርባ ስሚንቶና ብሄራዊ ማዕድን ድርጅት በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ የማምረት ሂደት ላይ ባለመሆናቸው ትግበራውን ማቋረጣቸው ነው የተመለከተው፡፡
‹‹የፍልስፍናው ዋና ግብ ብር ማዳን ሳይሆን በተቋማት ውስጥ ቀጣይነት ያለው የለውጥ ባህል ማዳበር ነው›› የሚሉት አቶ አስናቀ ተቋማት በሚያገኙት ውጤት ረክተው እንዳይቀመጡ ሁሌም ቢሆን ለጥራት፣ ለብዛትና ምቹ የስራ ሁኔታ ለመፍጠር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በተለይም አመራሩና ሰራተኛው የካይዘንን ፍልስፍና ለመተግበር እጅና ጓንት ሆነው መስራት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
እንደ አቶ አስናቀ ገለጻ ፤ በካይዘን የአሰራር ፍልስፍና ዘዴ አማካኝነት ሁሌም ቢሆን ብክነት የሚያስከትሉ ነገሮችን ማስወገድ፤ ወጪ መቀነስ ፣ የሥራ ተነሳሽነትን ማሳደግ፣ የደንበኛን ፍላጎት መጠበቅ፣ ጥራትን በቀጣይነት እያሻሻሉ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በሥራ ቦታ የተለያዩ ነገሮች ተደበላልቀውና ተዘበራርቀው ሲቀመጡ ይህን ለመፈለግ የምርት ጊዜ ይባክናል፡፡ በካይዘን ፍልስፍና መሰረት ዕቃዎች በየዓይነታቸው ተደራጅተው ሲቀመጡ የሥራ ቅልጥፍና ጊዜን ይጨምራሉ፡፡ብክነት ሲወገድ ወጪ ይቀንሳል፤ ብዙ ይመረታል፤ ጊዜና ሀብትን መቆጠብ ይቻላል፡፡፡እናም በቀጣይ ጊዜያት የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይገባል፡፡የኩባንያዎች ምዘና ስርዓትን መዘረጋትና የተሻለ አፈጻጸም ላሳየው እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡
ካይዘን የአንድ ሰሞን እንቅስቃሴ ከመሆን በዘለለ ዘላቂነት ባለው መልኩ በተቋማት እየተተገበረ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለዎት? ብለናቸው አቶ አስናቀ ‹‹ የአንድ ሰሞን እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ተቋማት ካሉ በእኔ አመለካከት ይሄ ፍልስፍናውን በአግባቡ ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡ ቀጣይነት ያለው ለውጥ መቼም ቢሆን ፋሽን ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ዓለም ለመኖር ፣ለመወዳደር፣ውጤታማ ለመሆን ቀጣይነት ያለው ለውጥ እያመጡ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ በዓለም ገበያ መወዳደር አይቻልም፡፡ ከድህነት መውጣትም አዳጋች ይሆናል፡፡ስለዚህ እንደፋሽን የሚያዩት አመራሮች ካሉ የእነሱ ችግር እንጂ ፍልስፍናው ያመጣው አይደለም›› ሲሉ ምልሽ ሰጥተዋል፡፡
በአገር ውስጥ ላሉ ኢንዱስትሪዎችን መንግስት ብዙ ድጋፍ እያደረገላቸውም እንኳ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን አልቻሉም፡፡ምክንያቱ ደግሞ የተሻለ የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ ባለማድረግቸው መሆኑን አቶ አስናቀ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ ተቋማት ችግራቸውን ወደ ውስጥ አይተው አሰራራቸውን በቀጣይነት እያሻሻሉ እንዲሄዱ የማስተማር፣ የመምከርና የማነሳሳት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይጋባል ብለዋል፡፡
ካይዘን የተጀመረበት ቶዮታ ኩባንያ በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፍና ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ይህ ኩባንያ እዚህ የደረሰው ሠራተኞቹና አመራሩ ቀጣይነት ያለው ለውጥን ባህል በማድረጋቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡ እናም የኢትዮጵያ ፋብሪካዎችም ይህንን በዓርአያነት በመውሰድ የቶዮታን መንገድ ተከትለው ተወዳዳሪና ግዙፍ ኩባንያ ለመሆን መስራት አለባቸው የሚል ሀሳብ አላቸው ::
ሁሉም የካይዘን ፍልስፍና ተግባራዊ ያደረገ ተቋም ለውጥ አምጥቷል ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም ገና ጅምር ቢሆንም የሥራ ቦታን ምቹ አድርጎ በማደራጀት ብቻ ጊዜ መቆጠብና ምርታማነትን በመጠኑ መጨመር ተችሏል፡፡ ‹‹በዓለም ገበያ ላይ እንዳንወዳደር የሚያደርገን የጥራት ችግር ነው፡፡ለሪፖርት ብለው ሠራተኞችን ያሰለጠኑና ተግባራዊ ያደርጉ ተቋማት እንደ ፋሽን ስለሚቆጥሩት ለውጥ አያመጡም፡፡በአንጻሩ አሠራሩ ለውጥ እንደሚያመጣ አምነው ተግባራዊ ያደረጉ ተቋማት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን አቶ አስናቀ መስክረዋል፡፡
ካይዘን በኢንዱስትሪዎች ብቻ ሳይሆን በሁሉም ተቋማት ተሞክሮ ለውጥ ያመጣ የፍልስፍና ዘዴ መሆኑን የሚገልጹት አቶ አስናቀ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ደግሞ ለኢንዱስትሪ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ተቋማት የሚያስፈልግ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በአዳማ ፈትል ፋብሪካ የካይዘን ቢሮ አስተባባሪ አቶ የኋላሸት ጸጋዬ የካይዘን የአሰራር ፍልስፍና ለፋብሪካዎች ጉልህ ጠቀሜታ አለው የሚለውን የአቶ አስናቀን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ ለአብነትም እሳቸው የሚሰሩበት የአዳማ ፈትል ፋብሪካ የካይዘን ፍልስፍና ተግባራዊ በማድረጉ በስድስት ወራት ውስጥ ለብክነት ተጋልጠው የነበሩ 100 ሺ ብር የሚገመቱ ዕቃዎችን ማዳን ተችሏል፡፡
አቶ የኋላሸት እንደገለፁት፤ ካይዘን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ በፋብሪካ ምርታማነትና ጥራት ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ብክነት ይወገዳል፤ የሥራ ቦታ የተደራጀ ይሆናል፤ቅልጥፍናን ይጨምራል፡፡ደንበኞችን የሚያረካ አገልግሎት መስጠት ይቻላል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አያና ዘውዴ የእስያ አገራት ዛሬ ለደረሰቡት ከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ካይዘን ከፍተኛ አስተዋጸኦ አድርጓል ይላሉ፡፡ ፍልስፍናው በዓለም ገበያ ተወዳድሮ የሚያሸንፍ ምርት የሚያመርቱ ውጤታማ ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ አስችሏል ብለዋል፡፡ ጠንካራ የሥራ ባህል እንዲፈጥሩም ከፍተኛ እገዛ አድርጎላቸዋል፡፡ እናም የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ምርት ለማምረት ይህንኑ መንገድ መከተል ይኖርባችኋል ፡፡ለዚህ ደግሞ መንግሥት ለኢንዱስትሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁና ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
የካይዘን የአሰራር ፍልስፍናን በተቋማት ውስጥ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠትና ዘላቂነት ያለው ትርፍ ለማስገኘት ስለሚረዳ ለተግባራዊነቱ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የተቋማት ስኬት ድምር ውጤት አገርን የብልጽግና ካባ የሚያስደርብ በመሆኑ በተለይ ከፍተኛ አመራሮች ራዕይ ሰንቀው ለለውጥ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጌትነት ምህረቴ

Published in ኢኮኖሚ

በአፍሪካ በቀዶ ህክምና ሂደት የሚሞቱ ሰዎች በዓለም ላይ ከሚሞቱት በእጥፍ እንደሚበልጥ የደቡብ አፍሪካ የህክምና ጥናት ምክር ቤት ሪፖርት ሰሞኑን ይፋ ተደርጓል። በ25 የአፍሪካ አገራት የተካሄደው ጥናት በ247 ሆስፒታሎች ቀዶ ህክምና ያገኙ 10ሺ 885 ሰዎች የተሳተፉበት ነው። በጥናቱ ከተካተቱ አገራት መካከል አልጀሪያ፣ ሊቢያ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች በኢኮኖሚ የተሻለ ደረጃ ያሉ የአፍሪካ አገራትን በዋናነት የያዘ ነው። በአንጻሩ በአፍሪካ እጅግ በከፋ ድህነትና ጦርነት ውስጥ ያሉ እንደ ቡርኪና ፋሶ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ያሉ አገራት በጥናቱ ውስጥ አለመካተታቸውን አጥኚዎቹ ገልጸዋል።
በከፋ ድህነት ውስጥ ያሉ አገራት በጥናቱ ባይካተቱም የተገኘው ውጤት አስደንጋጭ መሆኑን አጥኚዎቹ ገልጸዋል። በጥናቱ የተገኘው ውጤት ቀዶ ህክምና ከሚደረግላቸው አፍሪካውያን አንድ በመቶ የሚሆኑት ህይወታቸው ያልፋል። ይህም በዓለም ላይ በቀዶ ህክምና ሂደት ህይወታቸው ከሚያልፈው ዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ ሲነፃፀር በእጥፍ ይበልጣል ።
እንደ ጥናቱ ማብራሪያ ከሆነ በአፍሪካ ቀዶ ህክምና የሚደረግላቸው ታካሚዎች ዕድሜ በአማካይ 38 ነጥብ 5 ዓመት ነው። ይህም በዓለም ላይ በአማካይ ቀዶ ህክምና ከሚደረገው ዕድሜ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ማዳን የሚቻልበት ሰፊ ዕድልና የሚደረገው ቀዶ ህክምና ውስብስብነትም ዝቅተኛ ደረጃ ቢሆንም የሚሞቱት ቁጥር ከፍተኛ ነው። በዓለም ላይ በቀዶ ህክምና ሂደት ከሚሞቱት በእጥፍ መብለጡ እጅግ አሳሳቢና መፍትሄ የሚያሻው መሆኑን አጥኚዎቹ አሳስበዋል ።
አብዛኛዎቹ በቀዶ ህክምና ሂደት ህይወታቸውን እያጡ ያሉት አፍሪካውያን በቀላሉ መዳን የሚችሉ እንደነበሩ አጥኚዎቹ አውስተው ዋና ዋናዎቹ መንስዔዎች በጥቂት የህክምና ባለሙያዎች ቀዶ ህክምና መደረጉ፣ የህክምና መሰረተ ልማት አለመሟላቱ እና ከቀዶ ህክምና በኋላ ክትትል ማነስ የአፍሪካውያን ህልፈት መንስዔ መሆናቸውን የጥናት ቡድኑ ይፋ አድርጓል።
በተለይ ከቀዶ ህክምና በኋላ ክትትል ባለመደረጉ ቀዶ ህክምናው የተደረገበት የሰውነት ክፍል ቁስለት ፈጥሮ ታካሚዎች ለሞት የሚዳርግ መሆኑ ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚያዝ ጥናቱ ያትታል። ቀዶ ህክምና ከሚደረግላቸው አፍሪካውያን መካከል 18 ነጥብ ሁለት በመቶ የሚሆኑት በቀዶ ህክምና ማመርቀዝ ለስቃይና ለሞት ይዳርጋቸዋል። በክትትል ሊድን የሚችለውን ቀዶ ህክምና ወደ ውስብስብ ደረጃ ከፍ ብሎ ለሞት ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም ጥናቱ ያመለክታል።
በደቡብ አፍሪካ የኬፕታውን ሆስፒታል ከፍተኛ የህክምና ባለሙያውና የጥናቱ ቡድኑ መሪ ፕሮፌሰር ጉቲ ሹር፤ በቀዶ ህክምና ከሚሞቱ አፍሪካውያን 95 በመቶ የሚሆኑት ህይወታቸው የሚያልፈው ከቀዶ ህክምና በኋላ ተገቢውን ክትትልና እንክብካቤ ስለማይደረግላቸው መሆኑን በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ። ‹‹ከቀዶ ህክምና በኋላ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ በቀላሉ የአፍሪካውያን ህይወት መታደግ እየቻልን ዜጎቻችንን ወደ ሞት እየላክናቸው ነው›› ሲሉ በቁጭት ይገልጻሉ።
ጥናቱ እንደሚያመላክተው በአፍሪካ በቀዶ ህክምና ሂደት ህይወታቸው የሚያልፈውን ዜጎች ከሞት ለመታደግ ከቀዶ ህክምናው በኋላ በነርሶች ክትትል ማድረግ፣ ለቀዶ ህክምና ወሳኝ የሆኑ መሳሪያዎችን ማቅረብ፣ ኦክስጅን፣ መብራት፣ ደም እና የሆስፒታል መሰረተ ልማት በማስፋፋት የሚሞቱ ዜጎችን መታደግ ይቻላል ተብሏል።
ጥናቱ ከዚህም በተጨማሪ በአፍሪካ ለ100ሺ ህዝብ በአማካይ ዜሮ ነጥብ ሰባት የህክምና ዶክተሮች አገልግሎት እንደሚሰጡ ይፋ አድርጓል። ይህም በዓለም ላይ ካለው በአማካይ 30 በመቶ በጣም ያነሰ ነው። በዚህ የተነሳም በህክምና ሂደት ከሚሞቱት አፍሪካውያን በላይ በብዙ እጥፍ በህክምና እጦት እየሞቱ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።
በአፍሪካ ከ100ሺ ሰዎች 212 ሰዎች ብቻ ቀዶ ህክምና የሚያደርጉ ሲሆን፣ ይህም በዓለም በአማካይ ቀዶ ህክምና ከሚደረግላቸው ሰዎች 20 በመቶ ያነሰ ነው። ከዚህ በላይ የሚደረጉት ቀዶ ህክምናዎች በርካታ ስህተት የሚፈጠርባቸው መሆኑን በአፍሪካ በቀዶ ህክምና ላይ ያለውን ችግር ‹‹በቦሃ ላይ ቆረቆር›› አድርጎታል። በአጠቃላይ በአፍሪካ በቀዶ ህክምና ችግርና በሂደቱ ብዙ አፍሪካውያን እያሸለቡ መሆኑን ጥናቱ ያትታል።
ዘአትላንቲክ ድረ ገጽ ዘገባ እንደሚያመለክተው ደግሞ በአፍሪካ ጠንካራ የህክምና ትምህርት ቤቶች የሉም። ባልተደራጀና ጥራቱን ያልጠበቀ ትምህርት በሚሰጡ ትምህርት ቤቶች ተምረው የሚወጡ ተማሪዎችም ቢሆን ከታካሚው ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ቁጥራቸው አነስተኛ ነው።በዚህ የተነሳ አፍሪካውያን ተገቢ የሆነ የቀዶ ህክምና እያገኙ አይደለም። በርካታ አፍሪካውያን ባልሰለጠኑና በልምድ ሐኪሞች ጭምር ቀዶ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን በቶምሰን የጥናት ማዕከል የተደረገውን ጽሁፍ አብነት በማድረግ ያብራራል።
በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑትና በአፍሪካ ጤና ላይ ምርምር የሚያደርጉት አና ዳሪ በበኩላቸው ከ100ሺ አፍሪካውያን በአማካይ 212 ሰዎች ብቻ የቀዶ ህክምና ያገኛሉ፡፡ይህ የሚያሳየው ብዙ አፍሪካውያን በህክምና እጦት ለህልፈት እየተዳረጉ መሆኑን ነው ይላሉ። ችግሩን ለመቅረፍም የአፍሪካ መንግሥታትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጤና ተቋማትና የህክምና ባለሙያዎችን ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግ ረገድ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት በአማካይ ለ20ሺ ሰዎች አንድ ሀኪም እንደሚያስፈልግ ያስቀም ጣል። በአፍሪካ ግን አንድ ሀኪም ለመቶ ሺ ሰዎችም አይዳረስም። በአፍሪካ በየዓመቱ 56 ሚሊዮን አፍሪካውያን ቀዶ ህክምና ይፈልጋሉ። ከዚህ ውስጥ በርካታዎቹ በባለሙያና በተሟላ የህክምና ዕቃዎች እጥረት ሳቢያ ቀዶ ህክምናውን ማግኘት አይችሉም። ይህም በህመም እየተሰቃዩ ቀዶ ህክምናው ለማድረግ የዓመታትን ወረፋ እንዲጠብቁ ይገደዳሉ።ህመሙ የጠናባቸው ደግሞ ወረፋቸው ከመድረሱ በፊት ህይወታቸው ያልፋል። ወረፋው የደረሳቸውም ቢሆን እንኳ በጊዜ ሂደት በሽታቸው ከቀላል ወደ ውስብስብ ይሸጋገራል። እንዲያም ሆኖ ግን በቀዶ ህክምና ሂደት በተለያዩ ችግሮች መዳን የሚችሉ አፍሪካውያን ለሞት፣ ለዳግመኛ ቀዶ ህክምና ወይም ለከፋ ስቃይ ይዳረጋሉ። የአፍሪካውያን የቀዶ ህክምና ችግር በመርፊ ቀዳዳ እንደምታልፍ ግመል ዓይነት መሆኑንም ጥናቶቹ ያመላክታሉ።
በአፍሪካ ብዙዎች መሰረታዊ ህክምና በቀላሉ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ህመሙ እየጠና ይሄድና ለቀዶ ጥገና ህክምና ይዳርጋቸዋል፡፡ሆኖም ብዙ ወጪ አውጥተው ሆስፒታሎች ቢደርሱም በሚፈጠሩ የህክምና ስህተቶችና በክትትል ችግር ሳቢያ ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡እናም የሚመለ ከታቸው አካላት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት አፍሪካውያን ታክመው የሚፈወሱበትን ሥራ ሊሰሩ ይገባል፡፡
በኢትዮጵያም ይህ ክስተት በበርካታ ሆስፒታሎች የሚታይ ነባራዊ እውነታ ነው። በዘመናዊ ዓለም የህክምና ተቋማትን በር ሳይረግጡ የሚያልፉ ሰዎች በርካታ ናቸው። ህክምናን ፈልገው ወደ ሆስፒታሎች ከመጡ በኋላም ወረፋ የሚያንገላታቸው ህሙማን ብዙ ሲሆኑ፣ ይህን ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሄ ሊገኝለት አልቻለም።

አጎናፍር ገዛኸኝ

Published in ዓለም አቀፍ
Wednesday, 06 June 2018 16:50

እይታችንን እናስፋ

ሰሞኑን በዳያስፖራው ማህበረሰብ ዘንድ ሁለት ዓይነት ሃሳቦች እየተንሸራሸሩ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ዘንድሮ በዳላስ ከተማ በሚካሄደው 35ኛው የባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል ላይ በመገኘት ንግግር እንዲያደርጉ የቀረበው ጥያቄ መነሻ ሆኗል፡፡ በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያዊያን የስፖርት ፌዴሬሽን ጥያቄውን ሳይቀበለው መቅረቱ በዳያስፖራው ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ፌዴሬሽኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ በሚደረጉ ፌስቲቫሎች ላይ መገኘት እንደሚችሉ በመግለፅ አሁን ለደረሰበት ውሳኔ ለአምስት ሰዓታት የዘለቀ ውይይት፣ ሶስት ቀናትን የፈጀ ሚስጢራዊ የድምጽ አሰጣጥ ሂደትን መከተሉን አስረድቷል፡፡በመጨረሻም የፌዴሬሽኑ የቦርድ አባላት በሰጡት ድምፅ መሰረት ውሳኔውን ማሳለፉን ነው ያስታወቀው፡፡
የፌዴሬሽኑ አብዛኛዎቹ የቦርድ አባላት ጥያቄው በመቅረቡ ክብር እንደተሰማቸው ፌዴሬሽኑ ጠቁሞ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሠላም መረጋገጥና አንድነትን ለማጠናከር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉም አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም ግን በቀጣይ በሚካሄዱ ፌስቲቫሎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲገኙ ፍላጎታቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እኔ በበኩሌ የአገር መሪ ስለ ሠላምና አንድነት፣በአገር ውስጥ ስላለው ነባራዊ እውነታ መልዕክት ለማስተላለፍ የቀረበውን ጥያቄ በደስታ በተሞላ ምላሽ መቀበል እንጂ እንቢታን ማንፀባረቁ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በስፖርት ፌስቲቫሉ ላይ ከአገራቸው የራቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ እናም በዚህ በርካቶችን በሚያሰባስብ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቦታው በመገኘት ንግግር እንዲያቀርቡ እንዲያውም ጥያቄው መቅረብ የነበረበት በፌዴሬሽኑ በኩል ነበር፡፡ የፌስቲቫሉ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ማሰባሰብ ነውና፡፡
በዚህ የዳያስፖራዎች የስብስብ መድረክ ላይ ከተቻለና ከተሳካ የአገር መሪ እንዲገኝ ማድረግ ለአዘጋጆቹ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ይህን መሰሉ የክብር እንግዳ ግብዣ አይሳካም፡፡ የማይሳካው አዘጋጆቹ ሳይፈልጉ ቀርተው ሳይሆን መሪዎቹ ባለባቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነትና መደራረብ ምክንያት ነው፡፡ መሪዎቹ ተመችቷቸው አዘጋጆቹንና ተሳታፊዎቹን አክብረው በዝግጅቱ ላይ ከተገኙ ዝግጅቱ በጣም እንደሚደምቅ አያጠያይቅም፡፡ የበርካቶችንም ቀልብ ይስባል፤ በሌሎች አካላት ዘንድም ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው ያደርጋል፡፡ ይህን ዕድል ለመጠቀም አዘጋጆቹ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡
ከዚህ እውነታ በመነሳት የዳላሱን ዝግጅት ስንመለከት ታዲያ አዘጋጆቹ ዕድሉን አለመጠቀማቸውን እንድታዘብ አድርጎናል፡፡ በአዘጋጆቹ በኩል ይሄ ባይታሰብ እንኳ በመንግስት በኩል ጥያቄ ሲቀርብ በደስታ መቀበል እንጂ መግፋቱ ሚዛን አይደፋም፡፡ለዚህም ነው በርካታ ዳያስፖራዎች ‹‹በአስተባባሪዎች ፍላጎት ዕድሉ መዘጋት አልነበረበትም›› የሚል ቁጭት አዘል አስተያየታቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገልፁ የሰነበቱት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መገኘት በአዲስ ምዕራፍ የተጀመረው ብሔራዊ መግባባትና አንድነትን የማጠናከሩ ጉዞ ዕውን እንዲሆን መልዕክት ማስተላለፍና ከዳያስፖራው የሚነሱ ጥያቄዎችን መቀበልን ዓላማው ያደረገ በመሆኑ በደንብ ሊታይ ይገባ ነበር፡፡ አስተባባሪዎቹም በቦርድ አባላት ድምፅ የብዙኃኑን ፍላጎት ከመጨፍለቅ ቢያንስ አባላቶቻቸውን በማወያየት ወደ ውሳኔው ቢመጡ የተሻለ ነበር፡፡ ለስፖርት ፌስቲቫሉ ድምቀትና ተቀባይነት የሚጫወተውን በጎ አበርክቶ ከግንዛቤ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
የፌዴሬሽኑ የቦርድ አባላት ጥያቄውን ተከትሎ የሚፈጠረውን መልካም ነገር በሚዛን ማየት ነበረባቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ምንም እንኳን ማህበረሰቡን ወክለው የቀረቡ ቢሆንም ከጉዳዩ ክብደት አንፃር ወደ ውሳኔ ከማምራታቸው በፊት ማህበረሰቡን ቢያወያዩት የተሻለ ነበር፡፡ ሶስት ቀናትን በምስጢር ድምፅ ለመስጠት ከማባከን ቢያንስ አንዱ ቀን ለማህበረሰቡ ውይይት ቢሰጥ የተሻሉ ሃሳቦችን ለማግኘት ይረዳል፡፡ ውሳኔው ይህን አካሄድ ቢከተል አሁን ላይ ከዳያስፖራው የሚነሳ ቅሬታ አይኖርም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መገኘት ሲደግፉ የነበሩ የቦርድ አባላትም ፍላጎታቸው በድምፅ ብልጫ በመገደቡ ቅር እንዳላቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ትልቅ መነቃቃትን የመፍጠር አቅም የሚኖረው መድረክ እንዲደበዝዝ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ይህን ዕድል ማሳለፍ ተገቢ አለመሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ውድቅ ለማድረግ ካነሳቸው ጉዳዮች አንዱ ከእርሳቸው ጋር የተፎካካሪ ፓርቲ አባል ተገኝቶ ንግግር ቢያደርግ የሚል ሃሳብ ተነስቷል፡፡ ይህ አመክንዮ በምንም አግባብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቲቫሉ ላይ ከመገኘት ጥያቄው ጋር አግባብነት የለውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያንን ወክለው እንጂ ፓርቲን ወክለው አይደለም በመድረኩ ሊገኙ የተፈለገው፡፡ ስለሆነም የገዥ ፓርቲና የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ዓይነት አተያይ ማንፀባረቁ ተገቢነቱ አልታየኝም፡፡ መድረኩ የገዥና የተፎካካሪ ፓርቲ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን አንድነትና ትብብር ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡
የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ይፋ መሆን ተከትሎ የብዙዎች ስሜት መከፋፈሉን ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ አካላት ተናግረዋል፡፡ ለአንድነትና ለሠላም የሚደረግን ጉዞ ማደናቀፍ ተቀባይነት የለውም፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩን በደንብ ተዘጋጅተን ለመቀበል ስላሰብን›› የሚል ምላሽ እንኳ ቢሰጥ ለሠላምና አንድነት፤ለመከባበርና ለፍቅር ያለውን አመለካከት እንደሚያሳይ አንድ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ በዳላስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡ በቦርድ አባላት አብላጫ ድምፅ ብሎ ውሳኔ ማሳለፉ በእርግጥም በዳያስፖራው ዘንድ ቅሬታ ቢያሳድር ብዙም አይደንቅም፡፡
ሌሎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ያለመገኘት ውሳኔ የደገፉ አካላት በአገሪቱ ውስጥ ሊሰራ ከተነገረውና ተግባራዊ የሆነው ጥቂት መሆኑን በመጥቀስ ሲከራከሩ ይደመጣል፡፡ ይህም ከእውነታው ጋር የሚጋጭ መሆኑ እማኝ አያሻውም፡፡ እውነትን ለሚሻ እውነታው ግልፅ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እንደ መንግስት ‹‹ላይሆኑ ይችላል›› እስከመባል የደረሱ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ ለአገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ሲባል የተደረገ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡
መንግስት ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ በተለያዩ ጉዳዮች ለእስር የተዳረጉ ዜጎችን የመፍታቱን ጥረት ገፍቶ ቀጥሎበታል፡፡ በቅርቡ እንኳን በሽብር ወንጀል ተከሰው በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩትን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በልዩ ሁኔታ መፍታቱ ይታወቃል፡፡ ሌሎች እርምጃዎችም ተወስደዋል፡፡ይህን እውነታ ለተመለከተ ከቃል ያለፈ ተግባር የሚለው ትችት ራስን ለትችት ከመዳረግ ያለፈ ውሃ አይቋጥርም፡፡
እነዚህንና ሌሎች አንድነትን ለማጠናከርና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚረዱ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዳልተሰሩ አድርጎ ማቅረብ ከእውነታው መራቅ ነው የሚሆነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ብዙና ሙሉ ለሙሉ መፍትሄ ለመስጠት ጊዜ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ‹‹ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም›› እንደሚባለው ሁሉም ችግሮች በአንዴ እንዲፈቱ፣ሁሉም ጥያቄዎች በአንዴ ምላሽ እንዲያገኙ መጠበቅ ከአመክንዮው ጋር ይጋጫል፡፡ ነገሮችን ከስሜት በጸዳ መልኩ በስፋት መመልከት ይገባል፡፡ ጥቅምና ጉዳቱን አመዛዝኖ ሚዛናዊ መንገድን መከተል ያስፈልጋል፡፡
ይህን እውነታ በመረዳት ለቀጣዩ ትምህርት እንዲሆን በግብዓትነት መውሰድ ይገባል፡፡ እንኳን የአገር መሪ በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ታላላቅ ሰዎች፣ አትሌቶች፣ ምሁራን፣ አርቲስቶችና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን በመድረኩ በክብር እንግድነት ቢጋበዙ ፋይዳው ምን ያህል የጎላ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሩቅ ሳይኬድ አዘጋጆቹም ምስክር ናቸው፡፡
የተሰሩትን እያደነቁ፣ችግሮች እንዲፈቱ እየጠቆሙ፣ የመፍትሔ ሃሳቦችን እያቀረቡ መጓዝ ለአገር አንድነትና ሠላም ከሚቆረቆር ዜጋ የሚጠበቅ መልካም ተግባር ነው፡፡ ይህን መልካም ባህል አጠናክሮና አጎልብቶ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ የመጨረሻው ጠርዝ ላይ ደርሶ ለውሳኔ ከመቸኮል ነገሮችን ከመነሻቸው መመልከት አርቆ አስተዋይነት ነው፡፡ ነገሮችን የምናይበት መነፅርም በምክንያትና አመክንዮ ሊታገዝ ይገባል፡፡

ሠላም ዘአማን

Published in አጀንዳ

ከመቀነስ የመደመርን ስሌት የተያያዘው የዋጋ ግሽበት የህዝቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ክፉኛ እየተፈታተነው ይገኛል፡፡ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በየዕለቱ ዋጋቸው እየናረ አልቀመስ እያለ ነው፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሰሞኑን ባወጣው የዋጋ ግሽበት መረጃ የሚያዝያ 2010 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ13 ነጥብ ሰባት በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ለዚህም በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም የተመዘገበው አጠቃላይ የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ 187 ነጥብ አንድ በመቶ ሲሆን ይህም በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም ከተመዘገበው 164 ነጥብ ስድስት በመቶ አጠቃላይ የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ በልጦ መገኘቱ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
የሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ16 ነጥብ አንድ በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በወሩ የተመዘገበው የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ12 ነጥብ ሁለት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በዚህም መሰረት የወሩ አማካይ የዋጋ ግሽበት በ15 ነጥብ ስምንት በመቶ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበትም በስምንት ነጥብ አንድ በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋም ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀርም የ10 ነጥብ ስምንት በመቶ፤ከመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በዜሮ ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
የኤጄንሲው መረጃ የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እየጨመረ መሄዱን ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ ዜጎች ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን እንዲያስተናግዱ እያስገደዳቸው ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ ገቢና ወጪው የማይመጣጠነውን ህብረተሰብ ክፉኛ እየተፈታተነው ይገኛል፡፡ መንግስት ስኳር ፣ስንዴና ዘይትን የመሳሰሉ መሰረታዊ ሸቀጦችን በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል የማቅረብ ስልት ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ሸቀጦቹ በሚፈለገው ጊዜና መጠን ለህብረተሰቡ እየቀረቡ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ ህብረተሰቡ ለመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረትና ለእንግልት ተዳርጓል፡፡
በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ኑሮን መግፋት እየተሳነው መሆኑ ፀሃይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ወርሃዊ ደመወዝ እየጠበቀ ሸምቶ የሚኖረው ሠራተኛ በዋጋ ግሽበት የተነሳ ገቢና ወጭው አልመጣጠን ብሎታል፡፡ በመካከለኛ የገቢ ደረጃ ላይ ናቸው የሚባሉ ዜጎች ጭምር ኑሮውን መቋቋም አቅቷቸዋል፡፡
አሁን ለተከሰተው የዋጋ ግሽበት ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ሚዛን እንደሚደፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ለዚህም ገበያው በጥቂቶች ቁጥጥር ሥር መዋሉ፣የግብይት ሠንሰለቱ መራዘም፣የምርት መከዘን፣ ጥቂቶች ዋጋውን እንደፈለጉ ከመተመናቸውም በተጨማሪ ሥርጭቱን በሚፈልጉት መንገድ መዘወር መቻላቸው ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡
አንድ ምርት ከተመረተበት ቦታ አንስቶ ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ የተለያዩ ሂደቶችን ማለፍ የሚጠበቅበት ቢሆንም፤ በሰው ሰራሽ ምክንያት የግብይት ሰንሰለቱን የማራዘም ሂደት ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ እንዳሻቸው የሚሰገስጉት ደላሎች ዋና ተዋናዮች ናቸው፡፡ የግብይት ሰንሰለቱን በማራዘም የምርቱን ዋጋ እንዲንር ያደርጋሉ፡፡
ዋጋን በማረጋጋት የምርቶችንና የሸቀጦችን ሥርጭት ፍትሐዊ ያደርጋሉ የተባሉ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራትም በሚፈለገው ደረጃ ውጤት እያመጡ አይደለም፡፡ እነዚህ ተቋማት ሕዝቡን ከሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ካለመታደጋቸውም በላይ ብዙዎቹ የተቋቋሙበትን ዓላማ እየሳቱ ለጥቂቶች ጥቅም እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
ዕንቁላል፣ዳቦ፣ድንች፣ቲማቲም፣ወተትና ሽንኩርትን የመሳሰሉ ምግብ ነክ ሸቀጦች በየቀኑ ዋጋቸው እየጨመረ ለሸማቹ ራስ ምታት የመሆናቸው ምስጢር ግልፅ አይደለም፡፡ በተለይም የግብርና ምርቶቹ ዋጋ መጨመር ችግሩ ከአቅርቦት ወይስ ሌላ ብሎ ለመጠየቅ ያስገድዳል? የአቅርቦት ችግር እንደሌለ እየተገለፀ፣የነዳጅ ዋጋ ባልጨመረበትና ሌሎች ተያያዥ ሊባሉ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በሌሉበት አግባብ የምርቶቹ ዋጋ መጨመር ጉዳዩን በደንብ ማጤን እንደሚያስፈልግ የሚያመላክት ነው፡፡
ህዝቡ በኑሮ ውድነቱ ተማሮ ቅሬታውን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲያሰማ የግብይት ሥርዓቱን ጤናማነት መከታተልና መቆጣጠር የሚገባቸው መንግሥታዊ አካላት ከ‹‹ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን›› አስተያየት አለፍ ብለው ሲራመዱ አይስተዋልም፡፡ አገሪቱ ከምትከተለው ነፃ ገበያ መርህ አንፃር መንግስት ዋጋ ላይተምን ይችላል፡፡ ነገር ግን አሰራሮችን መፈተሸ፣ የተንዛዙ የግብይት ሰንሰለቶችን ማሳጠር፣ ህገ ወጥ ደላሎችና አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎችን ሥርዓት ማስያዝ ይኖርበታል፡፡ የዋጋ ግሽበቱን ምክንያት በማጥናት ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔዎችን ማበጀት ይጠበቅበታል፡፡
መንግስት ድጎማ እያደረገባቸው ለህዝቡ እንዲሰራጩ የሚደረጉት የስንዴ ዱቄትን የመሳሰሉ ምርቶች በፍትሃዊነት መሰራጨታቸውን መከታተል ይኖርበታል፡፡ የአቅርቦት ችግሩ ቶሎ እንዲፈታ ማድረግና ለህዝቡ በወቅቱ እንዲሰራጩ ማድረግም ይጠበቅበታል፡፡ ጥቂቶች ሲያሻቸው በህግ ከሚፈቀደው በላይ ምርት እየከዘኑ፣ በራሳቸው ዋጋ እየተመኑ የገበያውን ጤና የሚያቃውሱበትን አካሄድን ማስቆም አለበት፡፡ ወቅታዊ የግብይት መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ ባህልም ቢጎለብት ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት ይረዳል፡፡
በተለይም ከንግድ ጋር በተያያዘ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርጉ መንግስታዊ አካላት የተጣለባቸውን ህዝባዊና አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለባቸው፡፡ የህዝቡን የመኖር ህልውና እየተፈታተነ ለከፍተኛ ምሬትና ቅሬታ እየዳረገ ላለው የኑሮ ውድነት አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

@ የመንግሥት ትላልቅ ኩባንያዎች ወደ ግል ሊተላለፉ ነው

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የአልጀርሱ ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወሰነ፡፡ ኮሚቴው በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ኢትዮ-ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሳሰሉ ትላልቅ ተቋማት መንግሥት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ ይዞ ቀሪው አክስዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ትናንት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ መንግሥት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱም ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ መፈጠሩን ኮሚቴው በመግለጫው አመልክቷል፡፡ ይህንኑ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተው ፖሊሲ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡
‹‹የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሰላም ጥሪያችንን ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ እንጠይቃለን›› ሲል ኮሚቴው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በመግለጫው እንደተመለከተው ለኢትዮጵያ ዕድገትና ለሕዝቦች ተጠቃሚነት ሰላም ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው ጦርነት በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ሕይወት ሊጠፋ ችሏል፡፡ ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ መኖሪያ ቀዬ አፈናቅሏል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ጦርነት ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል፡፡
ኮሚቴው በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክስዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግሥት ይዞ ቀሪው አክስዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
አፈፃፀሙም የልማታዊ መንግሥት ባህሪያት በሚያስጠብቅ የኢትዮጵያን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በሚያስቀጥልና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲመራ ገልጾ፣ ዝርዝሩ በባለሙያዎች ተደግፎ በጥብቅ ዲስፕሊን ተግባራዊ እንዲደረግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ወስኗል፡፡

 ጌትነት ምህረቴ

 

 

Published in የሀገር ውስጥ

በኢትዮጵያ በአንድ አሀዝ ተወስኖ የነበረው የዋጋ ግሽበት በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት አሀዝ ተሸጋግሮ ህዝቡን እያስመረረው ይገኛል፡፡ አንገብጋቢውን የዋጋ ግሽበት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዘላቂ መፍትሔ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡

በገበያው ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠንና የሸቀጦች አቅርቦት አለመመጣጠን ለዋጋ ግሽበቱ መጨመር አንዱ ምክንያት መሆኑን የኢኮኖሚ ምሁሩ ክቡር ገና በመጠቆም፤ ችግሩን ለመፍታት መንግሥት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርት አቅርቦትን ማሳደግ አለበት ይላሉ፡፡
የባንኮችን የብድር ጣሪያ ዝቅ ማድረግ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ሌላው አማራጭ እንደሆነ ክቡር ገና ይገልፃሉ፡፡ የደመወዝ ጭማሪ አለማድረግ፣ መንግሥታዊ ወጪዎችን በተቻለ መጠን መቀነስ ፣የተለያዩ ወጪዎችን ለመክፈል የሚታተመውን ገንዘብ መቀነስ ወይም ማቆም፤ ነዳጅ ላይ መደጎም ፣የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ከፍ ማድረግና ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት የዋጋ ግሽበቱ የመቆጣጠሪያ መፍትሄዎች መሆናቸውን ዘርዝረዋል፡፡
‹‹ሌሎች አገራት የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚጠቀሙበት ዘዴ የባንክ ወለድን ከፍ በማድረግ ነው›› የሚሉት የኢኮኖሚ ምሁሩ ይህም ህዝቡ በእጁ ላይ ያለውን ገንዘብ ወደ ባንኮች እንዲወስድ ያበረታታል ብለዋል፡፡ በገበያ ውስጥ የሚንቀሳ ቀሰውን ገንዘብ በእጅጉ ስለሚቀንስም የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት የዋጋ ግሽበት 25 በመቶ ደርሶ እንደነበር ክቡር ገና አውስተው፤ በወቅቱ የባንኮች የማበደር መጠን እንዲቀንስ በማድረግ፣ የመንግሥት ወጪዎችን በመቀነስ፤ ለህብረተሰቡ ወሳኝ በሆኑ መሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ ድጎማ በመደረጉ የዋጋ ግሽበቱ መርገቡን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ክቡር ገና ገለጻ፤ በሰላም መደፍረስ ምክንያት የቆመው ሀብት የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ የአገሪቱን ፀጥታ አስተማማኝ ማድረግ፣ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ፣ የግብርና ምርታማነትን የመጨመር ሥራዎች በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፤
‹‹ከዚህ ቀደም ብዙ ተሰምቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዶላር ለማሸሽ ሲሞከር በፍተሻ እየተያዘ ነው፡፡ ያልተያዘውን ቤት ይቁጠረው፡፡ ይህም በራሱ በውጭ ምንዛሪ ላይ እጥረት በመፍጠር ኢንዱስትሪው ከውጭ የሚያስገባቸው ጥሬ ዕቃዎች እንዲወደዱ ያደርጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችን ዋጋ ያንራል›› ክቡር ገና ወደ ውጭ በሚሸሸው ገንዘብ ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የዋጋ ግሽበት ከአንድ አሀዝ ሲበልጥ አደጋ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ አክሊሉ ውበት ናቸው፡፡ የምርት አቅርቦትና ፍላጎት ሳይመጣጠን ሲቀር የዋጋ ግሽበት ከፍ እንደሚል ገልፀው፤ ዋና መፍትሄው በየትኛውም መስክ አምራቹን በማገዝ ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡
‹‹ በአንዳንድ አካባቢዎች የግብርና ምርት በብዛት ተመርቶ አርሶ አደሩ የሚገዛው አጥቶ ምርቱ ይበላሻል፡፡ በአንጻሩ በሌላ ቦታ ደግሞ ምርት ጠፍቶ ዋጋው በጣም ይወደዳል፡፡ ለምሳሌ በገጠር አካባቢ ወተትን የሚቀበላቸው ጠፍቶ ይደፋል፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ የምርት እጥረት ተከስቶ ግማሽ ሊትር 15 ብር ይሸጣል›› በማለት የሥርጭት ችግር ለዋጋ ንረት ምክንያት መሆኑን በምሳሌ ያስረዳሉ፡፡ እናም ገበያ የማፈላለግና ስርጭቱን የማስተካከል ሥራ ሌላው የመፍትሔ አማራጭ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የግብርና ምርቱን ማሳደግ ቀዳሚ ጉዳይ እንደሆነ የሚገልፁት የኢኮኖሚ ምሁሩ በተለይ የከተማ ግብርናን ፣የእንስሳት እርባታና ሰፋፊ እርሻዎችን ማስፋፋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ እንዲሁም ከአመራረት ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ድረስ ያለውን የንግድ ሰንሰለት ማሳጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
‹‹የግብርናው ዓላማ በምግብ ራስን መቻል፣ የወጪ ንግድን ማገዝ፣ ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆን ምርት ማምረት ቢሆንም የመስኖ ልማቶች ብዙ ዕውቀትና ሀብት ፈሶባቸው የሚፈለገውን ያህል ምርት አለማስገኘታቸው የአቅርቦት እጥረት እንዲከሰት አድርገዋል፡፡ ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ማምረት ያልተቻለበትን፤ ግብርና ላይ የተሰሩ ሥራዎች በታሰበው ልክ ውጤት ያላመጡበትን ምክንያት መፈተሽ ይገባል፡፡ ችግሩ የግብርናው ፖሊሲ ከሆነም አፈጻጸሙን በመፈተሽ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል›› ያሉት አቶ አክሊሉ ለድርቅ አደጋም ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት የዋጋ ግሽበቱን ለመከላከል እንደሚረዳ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በሰው ሰራሽ ምክንያት የዋጋ ግሽበት እንዳይፈጠር በነጋዴዎች በኩል የሚደረገውን የዕቃ ክምችት ለመቆጣጠር ሥርዓት በመዝርጋት ዕቃው ወደ ገበያ እንዲገባ ማድረግ ወሳኝ እንደሆነ ምሁሩ አስረድተዋል፡፡ የንግድ መረጃዎችን ለሁሉም ግልፅ በሆነ መንገድ እንዲደርሱ በማድረግ ከተሰራ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ይቻላል ብለዋል፡፡
የዋጋ ግሽበቱን ለመከላከል ብሄራዊ ባንክ፣ ኢንዱስትሪ ፣ንግድ ፣ ግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የሚመለከታቸው አካላት ሥራቸውን በአግባቡ መስራት እንዳለባቸውም ነው አቶ አክሊሉ ያሳሰቡት፡፡ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀራረብና በመነጋገር አቅርቦትን ለማብዛትና ስርጭቱን ለማስተካከል የቁጥጥር ስርዓትን በማጠናከር በትኩረት መስራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ዶክተር ብርሃኑ ደኖ በበኩላቸው፤ በየጊዜው እየጨመረ በመሄድ በተለይም አነስተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና እያሳደረው ያለውን የዋጋ ንረት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ማስተካከል እንደማይቻል ይገልፃሉ፡፡ የሚታረሰውን የመሬት መጠን በማሳደግና አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አቅርቦቱ ከፍ እንዲል የተለየ ድጋፍ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ የዋጋ ንረቱ ማህበራዊ ቀውስ እንዳያስከትል አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ድጎማ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት በዋጋ ተፎካካሪ፣ ብዛትና ጥራት ያለውን ምርት ማቅረብ ይገባል፡፡ ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች፣ማሽኖችና ሌሎች ምርቶችን በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች መተካት ያስፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚ ዘርፉ ለውጥ ብቻ የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ ስለማይችል ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ያግዛል፡፡
በ2005 ዓ.ም አጠቃላይ አማካይ የዋጋ ግሽበቱ 23 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ በ2009 ዓ.ም ዘጠኝ ነጥብ ሰባት በመቶ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሰሞኑን ባወጣው የዋጋ ግሽበት መረጃ ሚያዝያ 2010 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ13 ነጥብ ሰባት በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም አማካይ የዋጋ ግሽበት በ15 ነጥብ ስምንት በመቶ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበትም በስምንት ነጥብ አንድ በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡
የሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀርም የ10 ነጥብ ስምንት በመቶ፤ከመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በዜሮ ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
የዋጋ ግሽበቱ በዚሁ ከቀጠለ አነስተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ ጫና ያስከትላል፡፡ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የንግድ ውድድር እንዳይሰፍን ያደርጋል፡፡ አገሪቱን ለከፍተኛ የብድር ጫና ይዳርጋል፡፡ በሂደትም የህዝብ ብሶት ገንፍሎ በአገር ሰላምና ፀጥታ ላይ አደጋ ይደቅናል፡፡

 ዜና ትንታኔ

ጌትነት ምህረቴ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።