Items filtered by date: Thursday, 07 June 2018

ዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ቀን አስመልክቶ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ መልዕክቶች ይተላለፋሉ። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (አይ ኤ ኤ ኤፍ) የአየር ብክለትና የፕላስቲክ መሣሪያዎች አጠቃቀም መቀነስን የተመለከቱ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ስፖርቶች እንደሚካሄዱ አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት ትናንት በዓለም ላይ በተመረጡ ሃያ አራት ከተሞች የአንድ ማይል ወይንም የአንድ ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች ተካሂደዋል። ለውድድሩ ከተመረጡ ሃያ አራት ከተሞች መካከል አዲስ አበባ አንዷ ስትሆን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አማካኝነት መነሻና መድረሻውን ቦሌ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ያደረገ ውድድር ተካሂዷል። አዲስ አበባ ለዚህ ውድድር ከተመረጡ ከተሞች አንዷ መሆኗ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሰጠውን ትልቅ ግምትና ክብር አመላካች መሆኑ ተገልጿል።
የሩጫው ዋነኛ አላማ አትሌቲክስ የማንኛውም እንቅስቃሴ ማሳያ መሆኑንና የእርስ በርስ ትስስር መፍጠሪያ መድረክ መሆኑን በማመን ዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ከሁለት ዓመት በፊት ይህንን የንቅናቄ መድረክ ተቀላቅሏል። አይ ኤ ኤ ኤፍ የዓለም የአየር ብክለትን በተመለከተ መልዕክቶችን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ አማካኝነት ማስተላለፍ በመቻሉ የተሰማውን ደስታ አስታውቋል።
ኃይሌ ከፌዴሬሽኑ ድረ ገፅ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ «በየዓመቱ በአየር ብክለት ምክንያት በዓለም ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፤ አሁን ግን ይበቃል» በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። ኃይሌ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ እንደተመረጠም የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ከአዲስ አበባ ውጪ ልምምዳቸውን እንዲሰሩ የማድረግ እርምጃ መውሰዱን በማስታወስ፤ አትሌቶች ከከተማ ውጪ ባለ ስፍራ ልምምድ ማድረጋቸው ለጤናቸውም ይሁን ብቃታቸውን ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳ ገልጿል። ይህም ያልተበከለ የአየር ንብረት በስፖርቱ ያለውን አስተዋጽኦ የሚያሳይ መሆኑ ነው የተመለከተው፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ ሩጫን እንደሚያዘወትሩ የተናገሩት የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንት ሴባስቲያን ኮ የአየር ንብረት ጉዳይ በስፖርቱ ላይ ያለውን ተፅዕኖ አብራርተዋል። የአትሌቲክሱ ጀግኖችም የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆናቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንፁህ አየር ንብረት ንቅናቄና የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይ ኦ ሲ) ቀስቃሽነት የተጀመረው እንቅስቃሴም ዓለምና ቀጣዩን ትውልድ ጤናማ ለማድረግ መልካም ጅማሬ መሆኑን ኮ ከድረ ገፁ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ የዓለም ስጋት እየሆነ በመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ለብክለት የሚዳርጉ ምክንያቶችን ለመቀነስ ስፖርቱ ለግንዛቤ መፍጠሪያ ሁነኛው መሣሪያ እየሆነ ይገኛል። የዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በዓለም ላይ ካሉ ሰባት ዋና ዋና ስፖርቶች አንዱ በመሆን የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ ከአውሮፓና ኦሽኒያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አሳውቋል።
የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ለአየር ንብረት ብክለት ዋነኛ ምክንያት ተደርገው የሚቆጠሩ የፕላስቲክ ምርቶችን ለመቀነስ ወደ ፊት በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የግንዛቤ ሥራዎችን ለመስራት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ይታወቃል። ሌሎች የማህበሩ አባል ፌዴሬሽኖችም ይህን ተሞክሮ ቀስመው በሚያዘጋጁት ውድድር ተግባራዊ እንዲያደርጉ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ይህን መልካም አላማ በመደገፍ የዓለም አቀፉ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን፤ የዓለም አቀፉ ጎልፍ ፌዴሬሽን፤ ሆኪ ፌዴሬሽንና ራግቢ ፌዴሬሽኖችን የመሳሰሉ በዓለም ላይ ትልቅ ተቀባይነት ያላቸው ስፖርቶች ተመሳሳይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን አውጥተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ቦጋለ አበበ

 

Published in ስፖርት

ከዛሬ 17 ዓመት በፊት ማለትም በ1993 ዓ.ም አዲስ ዘመን ጋዜጣ 60ኛ ዓመቱን አክብሮ ነበር፡፡ የዘንድሮውንና የ1993ቱን ደግሞ አንድ ነገር ያመሳስለዋል፡፡ ዕለታዊ የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከዛሬ 17 ዓመት በፊት 60ኛ ዓመቱን ሲያከብር በዛሬዋ ቀን ዕለተ ሐሙስ ነበር፡፡ ዕለተ ሐሙስ ግንቦት 30 ቀን 1993 ዓ.ም በወጣው የአዲስ ዘመን ልዩ ዕትም ላይ ከሰፈሩት አስተያየቶች እነዚህን እናስታውሳችሁ፡፡
«…ከማናቸውም አስቀድሜ ለሁላችሁ ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ነገር ይህ ቀን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ ነው፡፡ በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችንም ለመፈጸም ያለብን ሥራ ይጀምራል…»
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ
«…ለመጀመሪያ ጊዜ ከ24 ዓመት በፊት ሲታተም እኔ ኤዲተር ነበርኩ፡፡ ብቻዬን እየተሯሯጥኩ ጋዜጣውን ሳዘጋጅ ሪፖርተር፣ ኤዲተር፣ አራሚና በህትመት ክፍልም እገዛ እሰጥ ነበር፡፡ የአንድ ሰው ጥረት ይታይ ነበር፡፡
«የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት አባት» ተብለው የሚጠሩት ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ 25ኛ ዓመቱን ሲያከብር ከተናገሩት የተወሰደ
«…ከ18 ዓመት የሳምንት አገልግሎትህ በኋላ ወደ ዕለታዊ ጋዜጣነት የተለወጥከው ዕድለኛው አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንኳን ይህን ለመሰለ የመሻሻል ዕድገት አበቃህ…»
ጳውሎስ ኞኞ ታኅሣሥ 20 ቀን 1951 ዓ.ም
«...የዚያን ጊዜው አዲስ ዘመን ዛሬ ከሚታየው ጋዜጣ ለየት ያለ ባህሪ ነበረው፡፡ በእርግጥ ልክ እንደ አሁኑ ያኔም ቢሆን አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመንግሥት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ያኔ ግልጽ የሆነ ሳንሱር ነበር፡፡ ስለዚህ በጋዜጣው የሚወጣ ጽሑፍ በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ምንም እንኳን እኔ በወቅቱ ዋና አዘጋጅ ብሆንም እኔንም እነ ብላታ ወልደጊዮርጊስ እና ሻምበል አጥናፉ ሳንሱር ያደርጉኝ ነበር፡፡ እኔም ደግሞ እንደ አቅሜ ሪፖርተሮችን ሳንሱር አድርግ ነበር…፡፡»
ነጋሽ ገብረማርያም
«… በ1962 ዓ.ም አካባቢ ከውጭ መጽሔት ያገኘሁትን የሁለት ፈረሶች ሥዕል አወጣሁ፡፡ አንዱ ፈረስ ይስቃል፤ ሌላው ያለቅሳል፡፡ እኔም ሁለቱ ፈረሶች በግጥም እንዲናገሩ አደረኳቸው፡፡ አንዱ ፈረስ ጓደኛውን «ለምን ታለቅሳለህ» ብሎ ሲጠይቀው «ጌታዬን ብዙ ጊዜ እንከባከባቸው ነበር፤ በኋላ ግን ጣልኳቸውና አኮረፉኝ» ይለዋል፡፡ ይቺ ነገር በመንግሥት ግልበጣ ተተርጉማ የጋዜጣው ሠራተኞች ስብሰባ ተጠራን፡፡ አብዛኞቹም ይህ ዓምድ ቢቀር ይሻላል የሚል አስተያየት ሰጡ፡፡ ሚኒስትሩም «ጃንሆይ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ካቀረቡልኝ ከሥራህ አባርርሃለሁ» አሉኝ፡፡ ግን ጃንሆይ ሳያዩት ይቅሩ ነገሩን ትተውት ይሁን አላውቅም ሳልባረር ቀረሁ…»
የቀድሞ ጋዜጠኛ አየለ ኪዳኔ
«..ከየካቲት 1966 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1967 አጋማሽ ድረስ የነበረው ጋዜጣ ወርቃማ ነበር፡፡ የተፈለገው ነገር ሁሉ ይጻፋል፡፡ ስለዚህ በእኔ ግምት በጣም ከፍተኛ ለውጥ የታየው በዚያን ዘመን ነበር..»

ሐዲስ እንግዳ

 

ደብዳቤ እየጻፈ አታለለ የተባለው ተከሰሰ


የሰላምታ ደብዳቤ በገዛ እጁ ጽፎ «፬ ጆንያ ጤፍ፣ ፩ ቆርቆሮ የተነጠረ ቅቤ ልኬላችኋለሁና የመሣፈሪያ ከፍላችሁ ውሰዱ» በማለት አታሏል የተባለው ግርማ ወልደ ትንሣኤ ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ።
ተከሳሹ ባሌ ጠቅላይ ግዛት የሚኖሩ ሰው ስም ጠቅሶ የሰላምታና የስጦታ ደብዳቤ አስመስሎ ጽፎ፤ ራሱ ፈርሞ፤ ገዳም ሰፈር ኗሪ ከሆኑት ከአቶ ተስፋዬ ይፍራሸዋ ቤት ሔዶ፤ ደብዳቤውን አስረክቦ፤ ጤፉንና ቅቤውን ለማስመጫ ብሎ ፳ ብር ተቀብሎ ጠፍቶ በብዙ ክትትል መያዙን የቀረበበት የአቃቤ ህግ ክስ ይዘረዝራል። ግርማ ወንጀሉን ፈጽሟል የተባለው ጥቅምት ፲፱ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ከቀኑ በ፭ ሰዓት ላይ ከግል ተበዳዩ ቤት አዲስ አበባ ከተማ መሆኑ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 03/ 1966 ዓ.ም


ተሳዳቢዋ ኢጣሊያዊትወህኒ ቤት ገባች


አምዴዎስ ሳንቲና እምፖርት የተባለች ኢጣሊያዊት ኢትዮጵያውያንን በመዝለፍና በመሳደቧ ፪ ወር እስራት እና ሁለት መቶ ብር መቀጫ ተፈርዶባት ወህኒ ቤት ገብታለች። ምርመራው ተጣርቶ ከነማስረጃው ከቀረበ በኋላ ይህ ቅጣት የተሰጣት በአዲስ አበባ ፱ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት መሆኑ ተገልጧል።
አምዴዎስ ሳንቲና እምፖርት የምትሠራው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጎዳና በሚገኘው በቆንጂት ኤቨርስት የቁንጅና ሳሎን ነበር። ኢትዮጵያውያንን የመሳደብ ወንጀሏን የፈጸመችውም ጥቅምት ፲፭ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ.ም መሆኑን የክሱ ፋይል ይጠቅሳል።
በዚህ በተባለው ቀን አንዲት ኢትዮጵያዊት ጸጉሯን ለመስተካከል ገብታ ክፍት ቦታ ታገኛለች። መንግስቱ አስፋው የተባለው የዚህ ሳሎን ሠራተኛም የኢትዮጵያዊቷን ጸጉር ማስተካከል ይጀምራል። ወዲያው አንዲት ኢጣሊያዊት ትመጣለች። በዚህ ጊዜ አምዴዎስ ሳንቲና «የእርሷን ትተህ ይህቺን ሥራ፤ ይህቺ ትልቅ ሰው ናት» የሚል ትዕዛዝ ትሰጣለች። መንግስቱ አስፋው ግን «ተራ ትጠብቅ» ሲል እምቢ ይላል። በዚህ ጊዜ አምዴዎስ ሳንቲና ብዙ የዘለፋ ንግግር መናገሯም ተረጋግጧል።
አምዴዎስ ፳፱ ዓመት እድሜ ሲኖራት በኢትዮጵያም ውስጥ ፳፱ ዓመት ተቀምጣለች። የምትኖርበት አድራሻ በፊደል ማርሻል መንገድ እንደነበር ተረጋግጧል።
አዲስ ዘመን ጥር 22 ቀን 1956 ዓ.ም


ከምኒልክ ትዝታ


ዳግማዊ ምኒልክ ካረፉ ያለፈው ሐሙስ ፸፫ ዓመት ሆናቸው። ዜና ዕረፍታቸው ታኅሳስ ፫ ቀን በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ቤት ሲታሰብ ደራሲ ታደሰ ዘውዴ አጫወቱኝ፥
አፄ ምኒልክን አንድ እንግሊዛዊ «ከጥቁርና ከነጭ ማን ይበልጣል?» ሲል ይጠይቃቸዋል። ምኒልክም «አስበህ እንደጠየቅከኝ አስቤ መልስ እሰጥሃለው» ብለው በቀጠሮ ይለያያሉ። ከዛም ሊቃውንቶቻቸውን ሰብስበው ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ እንዲሰጡ ይጋብዟቸዋል። ለጊዜው ምንም መልስ አልተገኘም።
በኋላ፥ አለቃ ድንቄ የተባሉ ብልህና አዋቂ ሰው «አይቸገሩ ጃንሆይ! መልሱን እኔ እሰጥዎታለሁ» አሏቸው። ምኒልክም በጽሞና ይጠብቋቸው ጀመር።
አለቃ ድንቄም፤ «ፈረንጁ ከጥቁርና ከነጭ ማን ይበልጣል አይደል ያለው? ፍላጎቱ ይገባናል። እርስዎም በፈንታዎ "ከዓይንህ ነጩ ነው ጥቁሩ የሚያይልህ?" ብለው ይጠይቁት፤ መልሱን ከዛ ያገኘዋል» አሏቸው አሉ። እውነትም! ምኒልክ ለፈረንጁ ይህን ሲሉት በነገሩ ተደንቆ ዝም አለ ይባላል። (ን.አ)
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 6 ቀን 1978 ዓ.ም

 

ዋለልኝ አየለ 

Published in መዝናኛ

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የወረዳ ስምንት የወጣት ማዕከል መግቢያ በር ላይ ከቆርቆሮ በተሰራው ፑል መጫወቻ ቤት ውስጥ እስከ 30 የሚሆኑ ወጣቶች ይታያሉ፡፡ ሁለት ፑል ማጫወቻዎች ላይ አራት ወጣቶች እየተጫወቱ ሲሆን፤ የተወሰኑ ወጣቶች መጫወቻውን ከበው ቆመው ተራቸውን እየጠበቁ ናቸው፡፡ የተቀሩት ከቆርቆሮ በተሰራው የፑል ማጫወቻ ቤት ዙሪያውን በተደረደረው አግዳሚ ወንበሮች ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ፑል ለመጫወት ተራቸውን እየተጠባበቁ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል የ11ኛ ክፍል ተማሪው ብሩክ አየለ አንዱ ሲሆን በአካባቢው ለወጣቶች የሚሆን መዝናኛ ባለመኖሩ በፑል ቤት ጊዜን ለማጥፋት መገደዱን ይናገራል፡፡ በተለይም እንደእርሱ ላሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የሳይንስ ካፌ በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ ከመዝናናቱ ጎን ለጎን በፈጠራና ምርምር አቅሙ እንዳይጎለበት ያደረገው መሆኑን ያነሳል፡፡
ፑል ቤቱ ባለበት የወጣቶች ማዕከል ውስጥ የሳይንስ ካፌ ተገንብቶ ጥር 2010 ዓ.ም ቢመረቅም እስካሁን አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩን ይጠቅሳል፡፡ «በግቢው ውስጥ ከመጫወት ውጪ ሌሎች ቤተ መጻሕፍት፣ የተለያዩ የስፖርቶች መስሪያ ጂሞች እና የሳይንስ ካፌዎች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም» ይላል፡፡ በዚህም ምክንያት በትርፍ ሰዓቱ ወደ ወጣት ማዕከሉ ጎራ ብሎ ፑል ተጫውቶ ወደ ቤቱ እንደሚመለስ ነው የተናገረው፡፡
በወጣት ማዕከል ውስጥ የሳይንስ ካፌ እንዲኖር የተጀመረው ጥረት ወጣቶች በማዕከሉ የተለያዩ መዝናኛዎችንና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ ጎን ለጎን የሳይንስ እውቀታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል እድል እንደሚፈጥርላቸው ይናገራል፡፡ እነዚህ የሳይንስ ካፌዎች በተለይም ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ነው ያመለከተው፡፡
እንደ ወጣት ብሩክ ማብራሪያ፤ ይህ የሳይንስ ካፌው እስካሁን አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩ ከሳይንስ ካፌው ማግኘት ያለበትን አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጓል፡፡ በርካቶች ወጣቶችም ወደ ማዕከሉ መጥተው ፑል ብቻ ተጫውተው ይመለሳሉ፡፡ ሳይንስ ካፌዎቹ አገልግሎት ቢጀምሩ ግን ወጣቶቹ ራሳቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅም የፈጠራ ስራዎችን የመስራት ዕድል ይኖራቸዋል፡፡
በተጨማሪም አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የቤተ ሙከራ እጥረት ያለባቸው እንደሆኑ የሚያነሳው ወጣቱ፤ ካፌው አገልግሎት መስጠት ቢጀምር ተማሪዎች በትምህርት ቤቶቻቸው ደረጃ የተማሯቸውን ንድፈ ሀሳቦች ተጠቅመው የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን እንዲያከናውኑም ዕድል ይፈጥራል የሚልም እምነት አለው፡፡
የማዕከሉ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት ለተማሪዎች አጋዥ የሚሆን የተለያዩ የሳይንስ አጋዥ መጻሕፍት እንደሚገባ የተነገረ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ አገልግሎት መስጠት ባለመጀመሩ አጋዥ መጻሕፍቱን በአቅራቢያው ለማግኘት መቸገሩንም ያነሳል፡፡ «በዚህም ምክንያት ቤተመጻሕፍት ለመጠቀም ከፈለኩ ወደ ትምህርት ቤት ተመልሼ ለመሄድ እየተገደድኩ ነው» ይላል፡፡
በመሆኑም የሚመለከተው አካል በአፋጣኝ የሳይንስ ካፌው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን በማድረግ የወጣቱን ቅሬታ መፍታትና ወጣቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀቱ እንዲጎለብት በማድረግ ራሳቸውንና ሀገራቸውን የሚጠቅሙበት እድል ሊፈጠር እንደሚገባ ነው ያስገነዘበው፡፡
ወይዘሮ ሀረጓ ዓለሙ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት የወጣት ማዕከል የግዥ ኦፊሰር ናቸው፡፡ እርሳቸውም የሳይንስ ካፌው በጥር ወር ላይ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መመረቁን ያስታውሳሉ፡፡ ከተመረቀበት ወቅት ጀምሮ ወጣቶች አገልግሎት ፍለጋ ወደ ማዕከሉ እንደሚመጡና አገልግሎት ለምን እንደማይጀመር እንደሚጠይቁም ነው የሚያብራሩት፡፡ ይህ ቅሬታ ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ የቀረበ ቢሆንም፤ እስካሁን ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት አልጀመረም፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት የካፌው ሥራ አለመጀመር ወጣቱ በየጊዜው የሚያነሳው የወረዳው የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚያ ባሻገር ግንባታው ተጠናቆ ለረጅም ጊዜ የቆየው የማዕከሉ ህንፃ መስታወቶች እየተሰባበሩ ናቸው፡፡ በተለይም የምረቃ ሥርዓት ላይ የተገኙና ማዕከሉ እስካሁን አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩን የሚያውቁ ወጣቶች ማዕከላት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ምቹ ሳይሆኑ የውሸት ምርቃት መካሄዱ ተገቢ እንዳልሆነ በየጊዜው የመንግሥት አካል ላይ ትችት ይሰነዝራሉ፡፡ የማዕከሉ ምርቃትም ለወጣቱ ታስቦ ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የተደረገ እንደሆነ ቅሬታቸውን ያነሳሉ፡፡
ይህም በወጣቱና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገበውን መልካም መስተጋብር ሊጎዳ የሚችል መሆኑን ወይዘሮ ሀረጓ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል ወጣቶቹ ራሳቸውን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር ለማስተሳሰር እያሳዩ ያለውን ጥልቅ ስሜት ከግምት በማስገባት በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እንዲሁም በማዕከሉ ላይ የተደቀነውን አደጋ ከግንዛቤ በማስገባት ችግሮቹ ተቀርፈው በአፋጣኝ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ መመቻቸት እንደሚገባውም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣቶች ተጠቃሚነትና ማብቃት ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ አሻግሬም የሳይንስ ካፌዎቹ በጥር ወር ግንባታቸው ተጠናቋል ተብሎ ምረቃ ስነ-ሥርዓት እንደተፈጸመ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንትን ጨምሮ አምስት ካፌዎች እስካሁን ድረስ አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም ምክንያት ወጣቱ ከሳይንስ ካፌው ማግኘት የሚገባው ጥቅም ሊያገኝ አለመቻሉን ያምናሉ፡፡ በተመሰሳይ የቂርቆስ ወረዳ ስድስት ብቻ ሳይሆን የሌሎች ወረዳዎች ወጣቶችም ቅሬታ እያሰሙ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡
የወጣቶች የሰብዕና ግንባታ ማዕከላት ወጣቶች ከቴክኖሎጂ ጋር የሚተዋወቁባቸው እንዲሆኑ በተመረጡ ማዕከላት የሳይንስ ካፌዎች የመገንባት ሥራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሲሰራ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ የሳይንስ ካፌዎቹ በአራዳ፣ በቂርቆስ፣ በቦሌ፣ በአዲስ ከተማ እና በጉለሌ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የወጣት ሰብዕና ግንባታ ማዕከላት በሦስት ወራት ውስጥ የሳይንስ ካፌዎች ግንባታ ለማጠናቀቅ በ2009 ዓ.ም ነሐሴ ወር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መካከል የስምምነት ሰነድ ተፈርሞ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ዘመኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ስለሆነ የወጣት ማዕከላት ሳይንስ እንዲሸቱ በማሰብ ከሳይስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ውል መፈረሙን ያነሳሉ፡፡ በግንበታ ሂደት ላይ በነበረበት ወቅትም በየ15 ቀኑ ግንኙነት በማድረግ የግንባታ ሂደት በምን መልኩ እየሄደ እንደሆነ ግምገማ ሲካሄድ ነበር፡፡ ስራውን በዋነኛነት ይመሩ የነበሩት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ካፌዎቹ እስኪመረቁ ድረስ ስራው በጥሩ ሁኔታ ሄዶ እንደነበርም አመልክተው፤ ይሁንና ምረቃው የተካሄደው ማለቅ ያለባቸው ስራዎች በሙሉ ሳያልቁ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡ የምረቃ ስነ-ሥርዓት ከተከሄደ በኋላ የውጭ ምንዛሪ ተመን መጨመሩን ተከትሎ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ ኮንትራክተሮቹ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቅሬታ ማስገባታቸውን ነው የሚጠቁሙት፡፡ «የኮንትራክተሮችን ቅሬታ ለመፍታት ረጅም ርቀት ተካሂዷል፡፡ ሆኖም ችግሩ ሳይፈታ ወራት አልፈዋል፡፡ ይህ ሂደት መጓተቱ ደግሞ ወጣቱ ቅሬታውን እንዲያሰማ ምክንያት ሆኗል» ይላሉ፡፡
የወጣቶቹን ቅሬታ ከግምት በማስገባት ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ጋር በየጊዜው በመገናኘት የሳይንስ ካፌዎቹ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ለማድረግ ምን መደረግ እንዳለበት ምክክር ሲደረግ እንደነበርም ያነሳሉ፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ በተደረሰው ውሳኔ መሰረት የኮንትራክተሮቹ ውል እንዲቋረጥና ኮንትራክተሮቹ ማዕከላቱን በግድ እንዲያስረክቡ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በመሆኑም ከኮንትራክተሮቹ ጋር ውል በተቋረጠባቸው ካፌዎች ላይ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መሟላት ያለባቸውን ግብዓቶች የማሟላት ሥራ እየሰራ ነው፡፡ እነዚህን ግብዓቶች የማሟላት ሥራ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አቶ መንግሥቱ ይናገራሉ፡፡ ግብዓቶቹን የማሟላት ሥራ እንደተጠናቀቀም ማዕከላቱ ለወጣቶች ክፍት እንደሚሆኑ ነው የጠቆሙት፡፡
የሳይንስ ካፌዎቹ የቴክኖሎጂ ማዘውተሪያ እንዲሆኑ፥ ሳይንሳዊ መረጃዎችን የያዙ መጻህፍት፣ ወጣቶች በሳይንሳዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ አገልግሎት የሚያገኙበት ካፍቴሪያ፣ ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ የፈጠራ ውጤቶች በስፋት ማግኘት የሚቻልበትን ዕድል እንዲፈጥሩ ከአምና ጀምሮ በወጣት ማዕከላት እየተገነቡ ነው፡፡

መላኩ ኤሮሴ

Published in ማህበራዊ

አዲስ ዘመን ጋዜጣን ስሙን ያወጡለት ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ የተባሉ ግለሰብ እንደነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት አባት የሚባሉ ወላጅ እንደነበሩ የጋዜጣው ታሪክ ያወሳል፡፡ ጋዜጣው አፄ ኃይለሥላሴ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ነፃነት የተመለሠ ቀን ንግግር ሲያደርጉ «ይህ አዲስ ዘመን ነው» ካሉት ንግግር ላይ የተወሰደ ነው ይባላል።


ይሁንና ከዚያ በፊት በእንግሊዝ አገር በሲልቪያ ፓንክረስት አማካይነት የሚታተም “New Times and Ethiopian News” የተሰኘ ጋዜጣ ነበር። ይህ ጋዜጣ በአጭር አጠራር “New Times” ይባል ነበር። አዲስ ዘመን እንደ ማለት ነው። ስለዚህ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስም የወጣለት “New Times” ከተሠኘው የሲልቪያ ፓንክረስት ጋዜጣ ነው የሚሉም አሉ።አዲስ ዘመን ሦስት መንግስታት ተፈራርቀ ውበታል። የአፄ ኃይለስላሴ፣ ደርግና እና ኢህአዴግ፡፡ ከውልደቱ እስከ ሽምግልናው በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበረ በመሆኑ ለዘመናት የሙያ ነፃነቱን ሳያገኝ መቆየቱን ብዙዎች ያነሳሉ፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት መንግስታት የሥርዓቶቹ ልሳን በመሆን እንዳገለገለ ነው የሚጠቀሰው፡፡ ስለህዝቡ ለህዝቡ ሳይቆም፤ የህዝቡን ድምፅ ሳያሰማ በመቆየቱም ‹የእድሜውን ያህል ተወዳጅና ገናና እንዳይሆን አድርጎታል› የሚሉም አሉ፡፡ ይህም በአንዳንዶች ዘንድ ዛሬም ድረስ ለዘለቀው በአሉታ ለሚታየው ማንነቱ ሚና እንዳለው ይነሳል፡፡ 

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የለውጥ ጀንበር በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ብቅ ብቅ ማለቱ አይካድም፡፡ በተለይም ጋዜጣው በኤዲቶሪያል ፖሊሲውና በተቋቋመበት አዋጁ መሰረት የህዝብ መሆኑን በሚያንፀባርቅ መልኩ ስለህዝብና ለህዝቡ እየዘመረ ባአሰፈራቸው ፅሁፎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለዘመናት «የመንግስት ልሳን» ሲባል የቆየበትን ማንነት በጥቂቱም ቢሆን ሊያስረሱ የሚችሉ ብዝሃ አስተሳሰቦችን በህጉና በአግባቡ እንዲፈሱ በማድረግ ተወዳዳሪነቱን እያጎለበተ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
ይህንን ሃሳብ ከሚጋሩት ግለሰቦች መካከል የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ አበበ አይነቴ አንዱ ናቸው፡፡ እንደእርሳቸው እምነት፤ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስከቅርብ ዓመታት ድረስ የፖለቲካ ሹመኞች መሳሪያ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት የእድሜውን ያህል አንቱ ሳይባል ቆይቷል፡፡ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አስተሰሳቦችን ያማከሉ ስራዎችን ይዞ ስለማይወጣም ጋዜጣው ተወዳጅ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ እንደ አንጋፋነቱ በሚፈልገው ልክና መጠን ነፃነቱን ጠብቆ ለሙያው እድገት አልተጋም፡፡ በተለይም ጋዜጠኞቹ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው የ«ምን ይሉኛል» አስተሳሰብ የተሸበቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለህዝብ ቀርቶ መንግስትን የሚያረካ ስራ መስራት አልቻሉም፡፡
«በኃላፊነት ላይ የሚቀመጡ ሰዎችም ቢሆኑ ሁሉንም ነገር ከፖለቲካ አይን ብቻ የሚያዩ በመሆናቸው ነው ጋዜጣው ህዝብ ህዝብ እንዳይሸት ያደረጉት» የሚሉት አቶ አበበ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህን የቆየ አስተሳሰብ የሚሸረሽሩ ፅሁፎች ማውጣት መጀመሩን ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይም በአመራሩ ዘንድ የነበረው አስተሳሰብ እየተቀየረ በመምጣቱ ማንኛውንም አስተሳሰብ የሚያራምዱ አካላት በነፃነት ሃሳባቸውን የሚገልፁበት ጋዜጣ እየሆነ መምጣቱን ያነሳሉ፡፡ ይህም ደግሞ የመንግስት ህፀፆች በግልፅ በመተቸትና እንዲታረሙ እስከማድረግ ድረስ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ማሳያ ነው ይላሉ፡፡

ዶክተር መረራ ጉዲና፤


ይሁንና አሁን ቢሆን በውስጡ ካለው እምቅ አቅምና ከተሰጠው ህዝባዊ ሃላፊነት አኳያ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት ያመልክታሉ፡፡ ጋዜጣው በዋናነት የሃሳብ ልዩነትን በበጎ መልኩ የሚረዳ አመራር ያስፈልገዋል፡፡ ሁሉም ሃሳቦች አንድ አይነት እንዲሆኑ መጠበቅም ተገቢ አለመሆኑን አንስተው፣ ይልቁንም የተሻለ ተነባቢ ለመሆን የሚያግዘው በመሆኑ አገሪቱ በደረሰችበት የእድገት ደረጃ ልክ የአስተሳሰብ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል መደላደል መፍጠር እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡
የሙያ ስነምግባሩን በአግባቡ ሊተረጉም የሚችልና ከተፅዕኖ ነፃ የሆነ ባለሙያ እንደሚያስፈልገውም አቶ አበበ ያምናሉ፡፡ ለዚህም ደግሞ ባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፤ ጋዜጠኛው ለእውነት የቆመ ስለእውነት የሚሞግት ጠንካራ አቋም ያለው ሊሆን እንደሚገባም ያነሳሉ፡፡ ይህ ሲሆንም ጋዜጠኛው በሙያ ታፍሮና ተከብሮ እንዲኖር ያደርገዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ይህንን ማድረግ ከቻለ እንደ አንጋፋነቱ ሁሉ ለሌሎች አርአያ ሆኖ ይቀጥላል ይላሉ፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ «አፄ ሃይለስላሴ ካወጁበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ አዲስ ዘመን አዲስ ዘመንን ለኢትዮጵያ ህዝብ ማብሰር አልቻለም፡፡ እንዳውም የኢትዮጽያ ህዝቦች ድምፅ ከመሆን ይልቅ የአምባገነን ሥርዓቶችን አፍ ሆኖ ቆይቷል» ይላሉ፡፡ በተለይም በፖለቲካው አንፃር ድምፁ ለታፈነበት የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅ ሆኖ አላገለገለም የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው ነው የሚጠቅሱት፡፡ ጋዜጣው ያሳለፋቸው 77 ዓመታትም በአብዛኛው ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈ እንጂ የነፃ ሚዲያ ተምሳሌት ሆኖ አለመቀጠሉን ይናገራሉ፡፡
«አሁን አሁን የሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል ሃሳብ በማንፀባረቅ ረገድ ለውጥ እየመጣ ነው» በሚለው ሃሳብ ፈፅሞ አይስማሙም፡፡ አሁንም ቢሆንም ልክ እንዳለፉት መንግስታት ሁሉ የመንግስትን አቋም ብቻ በማራመድ የሌሎችን ደግሞ ገለል በማድረግ የአንድ ወገን አቀንቃኝ ሆኖ መቀጠሉን ይከራከራሉ፡፡ «በእኔ እምነት በተቋቋ መበት ኤዲቶሪያል ፖሊሲ መሰረት በነፃነት የህዝብን ነፃ ሃሳብ ለማስተናገድ ጋዜጣው አሁንም ከፖለቲካ ሹመኞች አስተሳሰብ ነፃ መውጣት አለበት» ይላሉ፡፡ ይህ ሲባል ግን ሥርዓት አልበኝነትን ይቀስቅስ፤ በመንግስት ላይ ጦርነት ያውጅ ማለት እንዳልሆነ አስምረው በታል፡፡
«አዲስ ዘመን እንደ እድሜው ብዙም ጠንክሮና ተስፋፍቶ በጥሩ ሁኔታ የህዝብ አገልግሎት እየሰጠ ነበር ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ደግሞም የመንግስት እንደመሆኑ መጠን የመንግስት ልሳን መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው» በማለት የዶክተር መራራን ሃሳብ የሚጋሩት ደግሞ የኢትዮጵውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫኔ ከበደ ናቸው፡፡ እንደ ህዝብ መገናኛ ብዙሃንነቱም የሁሉንም ዜጋ የልብ ትርታ የሚያሰሙ ስራዎችም ስለማያቀርብ ተወዳጅነት እንዳይኖረው አድርጎታልም ባይ ናቸው፡፡
በተጨማሪም ሃቅና እውነታ ላይ ተመርኩዞ የሚሰራቸው ስራዎችም በሚፈለገው ደረጃ ያለመሆኑ በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያሳጣው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ «የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስተሳሰብ በነፃነት የሚገልፁ በመፃፍ ረገድም የሚገባውን ርቀት ያህል አልተጓዘም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም የምንካካደው ነገር የለም» ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከገዢው ፓርቲ አስተሳሰብ ውጭ የሆኑ ፓርቲዎች ሃሳብ በነፃነት የሚስተናገደውም በምርጫ ወቅት ብቻ እንደሆነ አብነት አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡

ዶክተር ጫኔ ከበደ፤


እንደ ዶክተር ጫኔ እምነት ጋዜጣው በተጨባጭ የህዝብ መሆን የሚችለው፤ ራሱን አድሶ ለለውጥ መነሳት ሲችል ነው፡፡ በዋናነትም በየቀኑ የሚወጣ ጋዜጣ እንደመሆኑ ህብረተሰቡ ልክ እንደሌሎቹ የህዝብ መገናኛ ብዝሃን «ጠዋት አዲስ ዘመን ምን አለ?» ብሎ መነበብ እንዲችል ይዘቱ ሊቀየር ይገባል፡፡ ሁሉም ዜጋ በጋዜጣው ላይ የእኔነት ስሜት እንዲኖረው ለማድረግም ሁሉንም በእኩል መንገድ ሊያስተናግዱ የሚችሉ አዳዲስ አምዶች መክፈት ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማህበራዊ መሰረት ለሆናቸው ህዝብ የሚሆን መልክት ማስተላለፍ የሚችሉበት እድል ሊፈጠር ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት፡፡
«አዲስ ዘመን በግብር ከፋዩ ህዝብ የሚተዳደር እንደመሆኑ ስርነቀል የሆነ ሪፎርም ያስፈልገዋል» ያሉት ደግሞ የሰማዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለ ተቋም ቢሆንም የሁሉንም ህዝብ ድምፅ በእኩል መንገድ እንዳያስተናግድ የሚከለክለው ነገር እንደሌለ ያመለክታሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በተጨባጭ በተቋም ደረጃ ነፃ ሊሆን እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡ የመዋቅር ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ በእጅ አዙር በተቋሙ አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ ጫና ከሚያሳድሩ የፖለቲካ ሹመኞችና ለመንግስት ወገንተኝነት አገዛዝ ነፃ መውጣት እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡
በጎረቤት አገር ኬንያ የሚታተሙ የህዝብ ጋዜጦችን ዋቢ አድርገውም «የኬንያ እለታዊ ጋዜጦች በሚሊዮን ደረጃ የሚታተሙትና ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት የቻሉት ትክክለኛውንና ሁሉንም ያሳተፈ ስራ ይዘው ስለሚቀርቡ ነው» ይላሉ፡፡ በመሆኑም አዲስ ዘመንም ሩቅ ሳይሄድ ከጎረቤት አገራት የህዝብ ጋዜጦች ተሞክሮ ሊወስድ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ በተለይ ሚዛናዊነት ላይ በምንም መልኩ ሊደራደር እንደማይገባ ነው የተናገሩት፡፡ ይህ ሲሆን ጋዜጣው ከአንዳንድ የመንግስት ቢሮዎች ባሻገር የሁሉንም ህዝብ ደጃፍ ማንኳኳት ይችላል፡፡
ጋዜጣው በሚጠበቅበት ደረጃ የብዝሃ አስተሳሰብ ነፃብራቅ መሆን የሚችለው ግን ተቋሙ ብቻውን በሚያደርገው እንቅስቃሴ እንዳልሆነ አቶ የሽዋስ ያምናሉ፡፡ ከመንግስት ባሻገር ሁሉም ያገባኛል ባይ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚያስፈልገው ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ረገድም ፓርቲያቸው ወደፊት በጠየቀው መሰረት አደራዳሪ ኖሮ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ድርድር መሳተፍ ከቻለ አዲስ ዘመንም ሆነ ሌሎች በመንግስት መዋቅር ስር ያሉ መገናኛ ብዙሃንን ጉዳይ የድርድሩ አካል ለማድረግ ማቀዱን ያመለክታሉ፡፡ በዋናነትም ጋዜጣው ከፓርቲ ተፅዕኖ ለመላቀቅ በሚችልባቸው ሁኔታዎች ላይ ለመምከር መዘጋጀቱንም ነው የሚጠቁሙት፡፡
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍቃዱ ሞላ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ጋዜጣው በሶስት የመንግስት ሥርዓት ውስጥ ያለፈ እንደመሆኑ በእያንዳንዱ የመንግስት ሥርዓትና የየወቅቱ ፖለቲካ ነፃብራቅ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት ሥርዓታት ጋዜጣው የመንግስት ልሳን እንደሆነ ወገንተኝነቱን በተጨባጭ ያሳየበት አጋጣሚ የማይካድ ነው፡፡ በአገሪቱ የየራሳቸውን አመላከከት የሚያራምዱ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ባልተፈቀደበትና ባልነበሩበት ብዝሃነት ያለውን አስተሳሰብ ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታ ይኖራል ተብሎም አይጠበቅም፡፡
ይሁንና የደርግ መንግስት መውደቅን ተከትሎ በአገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ይፋ ከሆነ በኋላ ለመንግስት ብቻ የመወገን አስተሳሰብ እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ በተለይም ከአራት ዓመታት ወዲህ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አስተሳሰብ የሚያራምድ፣ የመንግስት ልማትና በጎ ስራ ብቻ ሳይሆን ህፀፆችንም ነቅሶ በማውጣት ተነባቢነቱን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ መሆኑን አቶ ፍቃዱ ይጠቅሳሉ፡፡ ምንም እንኳ የተጀመረው ስራ ከሚጠበቅበት አንጻር በቂ ነው ባይባልም ቢያንስ ሁሉንም ማስተናገድ በሚያስችል መስመር ውስጥ መግባቱ የሚሰራቸው ስራዎች ማሳያዎች መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ የመንግስትን መልካም ስራ ብቻ ሳይሆን ህፁንም የሚነቅሱ ፅህፎች ያስተናግዳል፡፡ ይህም ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ለመረጃ ምንጭነት እንዲጠቁሙበት ያስገደዳቸው መሆኑን ነው የሚያብራሩት፡፡
ከአስተሳሰብ ብዝሃነት አኳያም የሚሰራቸው ስራዎች አሁን ካሉት መገናኛ ብዙሃን ተቋማት የሚሰራቸው ስራዎች ያነሱ ስራዎች ይሰራል የሚል እምነትም እንደሌላቸው አቶ ፍቃዱ ይገልፃሉ፡፡ «ምክንያቱም ከሰላም፣ ከልማት፣ ከዴሞክራሲና ከማህበራዊ ተጠቃሚነት ጋር አያይዘን የምንሰራቸው ስራዎች ሁሉንም ህብረተሰብ ያማካሉ እንዲሆኑ ነው ጥረት የሚደረገው» ይላሉ፡፡ ይህ ሆኖ እያለ ግን 'የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ሆኖ አልቀጠለም' የሚለው አስተያየትም በሚዛኑ መታየት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ ዋናው ነገር ህዝቡ የሚፈልገውን አውቆ፣ የህዝብን ፍላጎት የሚዳስሱ ስራዎች ማቅረቡ ላይ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ ዋና አዘጋጁ ማብራሪያ፤ አዲስ ዘመን ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚያሳትማቸው ሌሎች የህትመት ውጤቶች ከኤዲቶሪያል ፖሊሲው ጀምሮ ድርጅቱ ከተቋቋመበት አዋጅ ድረስ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ተብለው ነው የተሰየሙት፡፡ ድርጅቱ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነውም ጋዜጣው የህዝብ ስለህዝብ የተቋቋመ መሆኑን ግልፅ ማሳያ ነው፡፡ የሚተዳደረውም ራሱ ከማስታወቂያና ከሽያጭ በሚያገኘው ገቢ እንጂ ምንም አይነት ድጎማ ከመንግስት አያገኝም፡፡ ይህም የራሱን ነፃነት አስጠብቆ ለመቆም አግዞታል፡፡
ጋዜጣው በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ቢሆንም እንኳ ዛሬም ድረስ የተፃፈውን ፅሁፍ ሳያነቡ በጅምላ የሚፈርጁ ሰዎች ጥቂት አለመሆናቸውን ዋና አዘጋጁ ይጠቅሳሉ፡፡ «አንብበው ትክክለኛ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ሳያነቡ ድሮ በሚያውቁት ብቻ በጅምላ የሚፈርጁ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ አስተሳሰብ የመነጨው ደግሞ ካለፉት ሥርዓቶች ከነበረው መጥፎ ገፅታ አንፃር እንደሆነ ግልፅ ነው» ይላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ሆነ ኢህአዴግ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ብቻ እንደሚሳተፍ ገልፀው፣ የሚስተናገዱ ስራዎች ሁሉ የህዝብን ጥቅም ያማከሉና ህዝቡ መንግስት እየሰራ ያለውን ስራ የማወቅ መብት ተግባራዊ የሚያደርጉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡
ከተፅዕኖ አንፃርም የተነሳው ነገር በተመሳሳይ መልኩ የሚታይ እንደሆነ አቶ ፍቃዱ ያምናሉ፡፡ ጋዜጣው በአደረጃጀትም ሆነ በአሰራር የማንም ተፅዕኖ እንደሌለበት ይጠቅሳሉ፡፡ «ምንም እንኳ አሁንም ድረስ ሲነኩ የሚያኮርፉና ደውለው የሚጮሁ ባለስልጣናት ቢኖሩም በእጅ አዙር የመረጃ ነፃነቱን ተጋፍተው ግን ተፅዕኖ የሚፈጥሩበት እድል የለም» ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡ ጋዜጣው በእነዚህ ባለስልጣናት ተገትቶ ስራውን ያቆመበት አንድም አጋጣሚ እንደሌለ ያመለክታሉ፡፡

አቶ ፍቃዱ ሞላ፤


በመሆኑም ከኤዲቶሪያል ፖሊሲው ጀምሮ ብዝህነት ያለው አስተሳሰብ ለማስተናገድ የሚያግድ ነገር በሌለበት ጋዜጣው የመንግስት ልሳንና ወገንተኛ ነው የሚለው አስተሳሰብ መታረም እንደሚገባው ነው ያስገነዘቡት፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ በበቂ ሁኔታ አሰምቷል፣ ዳሷል ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማስተናገድ ላይ ለተነሳው ሃሳብም ሲመልሱ እንዳሉትም፤ ከምርጫ ወቅት ባሻገር በተለያዩ አጋጣሚዎችና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመንተራስ የፓርቲዎችን ሃሳብ ለማስተናገድ ጥረት የሚደርግበት አግባብ አለ፡፡ በተለይም በሳምንት ስድስት ቀናት ውስጥ በሚወጣው የፖለቲካ አምድ ከእለታዊ ጥቆማዎች ባሻገር አጀንዳ በመቅረፅ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲያንሸ ራሽሩ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ፓርቲዎቹ መግለጫ በሚሰጡ በት ወቅት ጋዜጣው እለታዊ እንደመሆኑ ከጊዜና ከባለሙያ እጥረት መግለጫው የማይሸፈንበት ሁኔታ መኖሩን አልካዱም፡፡
«ግን በደፈናው አያስተናግዱንም የሚለው ሃሳብ ትክክል አይደለም፤ ከዚህ በላይ መሄድ አለበት የሚለው ግን ተገቢ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ዎችን ብቻ የሚያሳትፍ ራሱን የቻለ አምድ ባይከፈትም አጀንዳ በሚለው አምድ ማንኛውም ፓርቲ ወይም ግለሰብ ህግና ህግን መሰረት አድርጎ መፃፍ ሃሳቡን ማንፀባረቅ ይችላል» ይላሉ፡፡ ይህ አባባላቸው ምን ማለት እንደሆነ ተጠይቀውም «ህዝብን ከህዝብ፤ ብሄርን ከብሄር የማያጋጭ እውነታ ላይ የተመሰረተ ፅሁፍ ይዘው ከመጡ አሁንም ቢሆን የኛ በር ክፍት ነው» በማለት አብራርተዋል፡፡ አሁን ባሉት አምዶች የፓርቲዎች ሃሳብ ማስተናገድ የሚቻል ቢሆንም ፣በቀጣይ ግን ፓርቲዎች በነፃነት ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበትና ከምርጫ ወቅት ውጭ የሚከራከሩበት ገፅ እንዲኖር በፓርቲዎች የተነሳው ሃሳብ ተገቢ በመሆኑ በሂደት የሚታይ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

Published in ፖለቲካ

ያለፉት ሶስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ መልካም አልነበሩም፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ዘርፉን አቀዛቅዞታል፡፡ የሰላም መደፍረስ ጉዳቱ ለአገር የሚተርፍ ቢሆንም፤ በተለይም በየደረጃው ላሉ የቱሪዝም ዘርፍ አንቀሳቃሾች ፈተናው የበረታ ነው፡፡ ዘርፉ ከአነስተኛ አገልግሎት ሰጪዎች እስከ ከፍተኛ ሆቴሎች ድረስ ሁሉንም የሚነካ ነው፡፡
ባለፉት ሶስት ወራት ለሁለተኛ ጊዜ ተደንግጎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለዘርፉ መቀዛቀዝ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ጉባኤው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አንስቷል፡፡ ምክር ቤቱ አዋጁን ለመሻር በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በመምከር በስምንት ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ አዋጁ እንዲነሳ የወሰነ ሲሆን፤ ባለፉት ወራት ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያንሰራራ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይነገራል፡፡
የሂላላ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ ብስራት በላይ በአስጎብኚ ድርጅት ስራ ከተሰማሩ ስምንት አመት አሳልፈዋል፡፡ የአስጎብኚ ስራ በጥናት አዋጭ ቢሆንም ወደ ተግባር ሲገባ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ወቅትን ጠብቀው ነው ይላሉ፡፡
አቶ ብስራት፤ ለአስጎብኚ ድርጅቶች መኪኖችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ቢፈቀድም መኪኖቹን ማከራየት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ቱሪስቶች ከሚጎበኙባቸው ወቅቶች ውጭ ስራ ስለማይሰራባቸው የሰራተኛ ደመወዝ፣ የቤት ኪራይና መሰል ወጪዎችን መሸፈን ከባድ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ቱሪስቶች ሲመጡ መኪኖች በቀን ሁለት ሺ ብር ይከራያሉ፡፡ ጎብኚ የሌለ ጊዜ ግን መኪኖቹ ያለ ስራ ስለሚቆሙ ድርጅቱ ወጪዎችን ለመሸፈን ይቸገራል፤ አትራፊም አይደለም፡፡ ዘርፉ ላይ ያለው አሰራርና አመለካከት የተዛባ በመሆኑ ለስራ አያበረታታም፡፡ በዚህ ሳቢያም በርካታ የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤቶች ከአስጎብኚነት ወደ ሌላ ስራ እየዞሩ ትርፋማ ወደሆነና ገቢያቸውን ወደሚያሳድግ ስራ እየቀየሩ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
እንዲሁም ለተለያዩ ስራዎችና ለስብሰባ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ዜጎች በቂ የመኪና አገልግሎት አያገኙም፡፡ የውጭ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ አሰራር የለም፡፡ የመኪና አከራዮች ደግሞ የጉዞ መኪናዎች የሏቸውም፡፡ ይህም ቱሪዝሙን እየጎዳው ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
ለማስጎብኘት መኪና ከምገዛ ማሽነሪ አስመጥቼ ባከራይ የተሻለ ትርፍ አገኛለው በሚል፤ በዘርፉ ውስጥ ያሉት ባለሀብቶች ከስራው እየሸሹ ነው፡፡ ምክንያቱም ስራው ወቅትን መሰረት ያደረገ መሆኑ መኪኖች ያለ ስራ የሚቆሙበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ ለአብነትም መኪናው ከቀረጥ ነጻ ገብቶ ቱሪስቶች በሚመጡበት ወቅት ብቻ እየሰራ መቆሙ አዋጪ አይደለም፡፡ ስለዚህ አስጎብኝ ድርጅቱ ቀረጡን ልክፈልና መኪናው የማከራየት ስራ ልስራ ብሎ የሚመለከተውን አካል ሲጠይቅ መኪናው ጥቆማ ስላለበት ከቀረጥ በተጨማሪ 25 በመቶ ቅጣት መከፈል አለበት ተብሎ ድርጅቱም መንግስትም ሳይጠቀም አመት ከስድስት ወር ታግዶ የቆመ መኪና እንዳለ አቶ ብስራት ይገልፃሉ፡፡
አገሪቱ ውስጥ የነበረው የጸጥታ ችግር ዘርፉን ጎድቶታል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቱሪስቶች ወደ አገር እንዳይመጡ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ አዋጁ መነሳቱም መንግስትንም ህዝብንም ይጠቅማል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመነሳቱ የውጭ ዜጎች ደፍረው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ያደርጋል፡፡
የቴድ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ሙሉጌታ በማስጎብኘት ስራ ላይ 20 ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣበትና ተስፋ የተጣለበት ዘርፍ ነበር ይላሉ፡፡ ሆኖም የመጀመሪያው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ የቱሪዝም ስራው ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም ማሽቆልቆሉን ያስታውሳሉ፡፡ በጊዜው የቱሪስቶች እንቅስቃሴ የተገደበ ስለነበር ጉብኝታቸውን አቋርጠው እስከመመለስ የተደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡ ከመጀመሪያው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኋላ የነበረው የቱሪዝም ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ይበልጥ ስራውን እንዳዳከመው ያስረዳሉ፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱ በዘርፉ ላይ ለውጥ ያመጣል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አሁን ያለው ሁኔታ የኢትዮጵያን ገጽታ ሙሉ ለሙሉ እየቀየሩ ያሉ ነገሮች እየተፈጠሩ ስለሆነና ከስራ አጋሮቻቸው ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች ላይ ተስፋ የሰጠ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ በቱሪዝም ብቻ ሳይሆን በኢንቨስት መንቱም ላይ የተሻለ ለውጥ እንደሚያመጣ ያምናሉ፡፡
አስቀድሞ አገልግሎት ለማግኘት የሚመዘገቡ ቱሪስቶች ቁጥር መረጋጋት ከሰፈነ ወዲህ እየጨመረ መጥቷል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ ደግሞ ስራውን ወደነበረበት ሙሉ ለሙሉ ይመልሰዋል፡፡ አሁን ያለው የአገሪቱ ሁኔታ በተረጋጋ ሁኔታ ቢቀጥል የቱሪዝም እድገቱ ወደ ተሻለ የገበያ ስርዓት ውስጥ ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ቱሪዝም ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አመንጪ በመሆኑ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ በጎ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
የቱሪዝም ስራ በተወሰኑ ዘርፎች ብቻ የሚሸፈን አይደለም፡፡ ዘርፉ አገርን ማስተዋወቅ ስለሆነ ለቱሪዝም ትልቁና ዋናው ምሰሶ የአካባቢና የአገር ጸጥታና ሰላም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜያት የምትታወቅበት የሰላም ሁኔታዋ ወዳልተጠበቀ ሁኔታ መለወጡ ችግር ፈጥሮ ነበር፡፡ በአገሪቱ እየተፈጠረ ያለውን የፖለቲካ ለውጥ በሁሉም ዘርፍ በጋራ በመሆን ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡
በተለያዩ አገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶች ከሙያቸው አንጻር ብዙ የሚቀራቸው ስራዎች አሉ፡፡ በተለያየ አገራት በሚዘጋጁ መድረኮች የቱሪዝም ዘርፉን ማስተዋወቁ ላይ ብዙም ተሳትፎ የላቸውም፡፡ በየኤምባሲዎች ውስጥ ባለሙያዎችን መመደብና አካባቢያዊ የቱሪዝም ስራዎች እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ቱሪዝሙን ማስተዋወቅና ስራውን የጋራ በማድረግ ላይ ብዙ የሚቀሩ ስራዎች አሉ፡፡ የቱሪዝም ድርጅትም ዋነኛ ስራው ይህ ቢሆንም በሚገባ እየሰራ አይደለም፡፡ በዚህም ቅሬታ ይሰማኛል፡፡ ድርጅቱ የተቋቋመው የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማሳደግ ነበር፡፡ ነገር ግን በተሰራው ስራ ለውጥ ሊመጣ አልቻለም፡፡ በኃላፊነት ላይ የተመደቡት ሰዎች በራሳቸው እንጂ በአገሪቱ ቱሪዝም ላይ ሰርተዋል ተብሎ አይታመንም፡፡
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ብዙ ውስብስብ ችግሮችና ትልቅ ተፅዕኖ ያለበት ዘርፍ ነው፡፡ መንግስት የቱሪዝም መስፋፋት አላማ ሲያደርግ የዘርፉ ተዋናዮች ችግራቸው ምንድነው? ተብሎ መፍትሄዎች ቢተገበሩ መልካም ነው፡፡ በመንግስት በኩል ለዘርፉ የተሰጡ በርካታ እድሎች ቢኖሩም እድሎቹ ውስን ናቸው፡፡ ዘርፉን በትክክልና በሚያስፈልገው ያህል አያሳድገውም፡፡ ቀጣይነት ሊኖራቸውና ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ቱሪዝም እንደ የወጪ ንግድ ዘርፎች የውጭ ምንዛሪ አመንጪ እስከሆነ ድረስ ዜሮ ታክስ መሆን አለበት፡፡ መንግስት የዜሮ ታክስ ጥያቄን በቀላሉ ባያየው መልካም ነው፡፡ የአስጎብኚ ዘርፍ ላይ ያሉ ድርጅቶች የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንዲያመጡ የሚያስችሏቸው ሁኔታዎች እንዲሟሉ እድሎች ሊሰጡ ይገባል፡፡ ከታክስ ነጻ እንዲሆኑ የተጠየቁ ተጨማሪ እቃዎችን በሟሟላት ቱሪዝሙን የበለጠ ማሳደግ ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ብዙ ሆቴሎችና ሎጆች ተከፍተዋል፤ ቱሪዝሙ ላይ ሊያሰሩ የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን የግድ ዜሮ ታክስና ከታክስ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት ይገባል፡፡
የፕራይድ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መሀመድ ሁሴን ደግሞ የቱሪስቱ ፍሰት የቀነሰው ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ሳይሆን ካለፈው ሶስት ዓመታት ጀምሮ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በድጋሚ መታወጁ ደግሞ ባልተረጋጋ አገር ለመምጣትና ለመጎብኘት የሚደፍር ቱሪስት እንዳይኖር ስለሚያደርግ ለቱሪዝም ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በአገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት የቱሪዝም ዘርፉ ችግር ስለደረሰበት አብዛኞዎቹ አስጎብኚ ድርጅቶችን ከመደበኛ አሰራር ውጭ እንዳደረጋቸው ይጠቁማሉ፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገር ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት በይፋ የሚያረጋግጥ እና መነሳቱ ደግሞ ሰላማዊ ሁኔታ መፈጠሩን የሚያሳይ በመሆኑ በአንድ ጊዜ ቱሪዝሙ ወደነበረበት ባይመለስም በሂደት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር እንደሚያደርግ ተስፋ እንዳላቸው አቶ መሀመድ ይገልፃሉ፡፡ ዲፕሎማ ቶችም በቀጣይ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲኖር እንደሚሰራ ከነበረው በተሻለ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ያመለክታሉ፡፡ በመንግስት የተመደቡ በመሆናቸው የማስተዋወቁን ስራ ለመስራት በይበልጥ እድሉና ተዓማኒነት ስላላቸው ጠንክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያመለክታሉ፡፡ የመንግስት ዲፕሎማሲ ስራ የውጭ ኢንቨስትመ ንትና ቱሪስቶችን ወደ አገር ውስጥ በመሳብ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው፤ ከዲፕሎማቶች ከዚህ በኋላ የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡
‹‹ቤት ሲሰሩት ነው እንጂ ሲፈርስ አይቸግርም›› እንደሚባለው የነበረው ጊዜ እንደሚለወጥ ማስተዋወቁ ብዙ መስራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ አዋጁ በተነሳበት ቀን የቱሪስቶች ምርጫ ላይ የሚፈጥረው መልካም ሁኔታ ቢኖርም ቱሪዝሙን ወደ ነበረበት ለመመለስ ግን አዋጁን ማንሳት ብቻ በቂ አይደለም›› በማለት መንግስትም ከፍተኛ የማስተዋወቅ ስራ መስራት እንዳለበት አመላ ክተዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የቱሪዝም ዘርፉን እንዳቀዛቀዘው በመጀመሪያው አዋጅ የታየ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም ዘጠኝ መቶ አስር ሺ ደርሶ የነበረው የጎብኚ ቁጥር በ 2009 ዓ.ም ስምንት መቶ 86 ሺ ወርዷል፡፡ በ2010 ዓ.ም በዘጠኝ ወር የመጣው ቱሪስት ከሰባት መቶ ሺ አልበለጠም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ሰላም ያለመኖርና ከህግ በላይ የሆነ ችግር እንዳለ ስለሚያሳይ ቱሪስቶችም አስጊ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ እስኪያውቁ ድረስ ቁጥሩ መቀነሱ አይቀርም፡፡ አንድ አገር በህግ የምትተዳደርበት ስርዓት እያላት ከህግ በላይ ችግር ማጋጠሙን የሚያመላክት በመሆኑ ቱሪስቶችን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መኖሩ በጎ አይደለም፡፡ የቱሪስት ፍሰቱም ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ በሶስት ዓመት ከአንድ ነጥብ ሁለት አምስት ሚሊዮን ቱሪስት ለማምጣት በታቀደበት ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ መታወጁ የራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ ጥሩ የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሰላምና ጸጥታ ችግር ተፈቷል የሚል አንድምታ ስለሚኖረው ለሚቀጥሉት ዓመታት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲያንሰራራ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ቱሪዝሙ ከነበረበት ሁኔታ እንዲያገግም ያደርገዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን በመነሳቱ ዋስትና ሳይሆን የሰላም ሁኔታው አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ የዜጎች ደህንነት አደጋ ውስጥ እስካልገባ ድረስ ቱሪስቶችን ወደ አገር ማምጣቱ ከባድ አይሆንም፡፡
የመጀመሪያው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳ በኋላ ስራዎችን በፍጥነት ለመስራትና ቀንሶ የነበረውን ገቢ መልሶ ለማግኘት በሚኒስቴሩ በኩል የተሰሩ ስራዎች በቂ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ የመጀመሪያው አዋጅ ከተነሳ በኋላ ሐምሌ 2009 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደሮችን በመሰብሰብ ሚኒስቴሩ ያቀደውን አንድ ነጥብ ሁለት አምስት ሚሊዮን ቱሪስት ለማምጣት በተመደቡበት አገር እንዲሰሩ እቅድ እስከማከፋፈል የደረሰ ጥረት ተደርጓል፡፡ የተለየ የማስተዋወቅ ስራ ለመስራት የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መስፋፋት አለባቸው፡፡ ጥሩ ስራ በመሰራቱ ነው ባለው ችግር ውስጥ ቢሆን ዘንድሮ የቱሪስት ቁጥሩ እንዳይቋረጥ የተደረገው፡፡ እንደውም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የቱሪስት ቁጥር ጨምሯል፡፡ ለቀጣይም አስጎብኚ ድርጅቶች በተለያዩ አገራት በመሄድ የቱሪስት ጉብኝቶች ትስስር እንዲፈጥሩ እየተሰራ ነው፡፡ በተሰሩ ስራዎችም ውጤት መጥቷል፡፡
እንደ አገር በሚፈለገው መጠን የማስተዋወቅ ስራ ይቀረናል፡፡ ከሆቴል ኢንዱስትሪና ከቱሪስት መዳረሻ ልማት እኩል ቅድሚያ ተሰጥቶት የማስተዋወቁ ስራ አይሰራም፡፡ ለውጭ ሚዲያዎች ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ከማስተዋወቅ በአገር ውስጥ ሚዲያና በዲፕሎማቶች ማስተዋወቁ እንዲሰራ ቢደረግ ይሻላል፡፡ የአገር ሰላም ዋነኛ የቱሪዝም መሰረት በመሆኑ የአገርን ሰላም ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡

ሰላማዊት ንጉሴ

Published in ኢኮኖሚ

ጊዜው እ.አ.አ ከ1927 እስከ 1949 ነበር፡፡ በኮምንታንግ ፓርቲ በሚመራው መንግሥትና በተቃዋሚው ኮሚኒስት ፓርቲ መካከል በተለይም በመጨረሻዎቹ አራት ዓመታት በተከሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት የኮሚኒስት ፓርቲ አሸናፊ ይሆናል፡፡ ይሄን ተከትሎ ቻይና እና ታይዋን ሁለት ሀገራት ሆኑ፡፡ ከዋናዋ ቻይና የተባረረው ኮምንታንግ ፓርት በደቡብ ምሥራቅ ቻይና በሚገኝ የታይዋን ደሴት የራሱን ግዛት መስርቶ አካባቢውን መምራት ጀመረ፡፡
ሆኖም ይህ የኮሚንታንግ ፓርቲ አካሄድ ዋናዋን ቻይና በሚመራው በኮሚኒስት ፓርቲ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይልቁኑም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የታይዋንን ሉዓላዊነት እውቅና ላለመስጠትና የዋናዋ ቻይና አካል እንደሆነች ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እውቅና እንዲሰጥ የተለያዩ ጫናዎችን እያሳደረ ቆይቷል፡፡
ሀገራት ከታይዋን ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲያቋርጡም የቤጂንግ መንግሥት ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ሲያሳድር መቆየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተለይም በፍጥነት እያደገ የመጣውን የቻይና ኢኮኖሚ ተከትሎ ቻይና በሀገራት ላይ እያሳደረች ያለው ጫና እየበረታ መጥቷል፡፡ በዚህም ሀገራት ለታይፔ መንግሥት እውቅና ከመስጠት እየተቆጠቡ መጥተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ለታይዋን እውቅና ሰጥተው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መስርተው የነበሩ ሀገራት ሳይቀሩ ኤምባሲያቸውን በመዝጋት ደሴቲቱን እውቅና እየነፈጉ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡም የምዕራብ አፍሪካዋ ሀገር ቡርኪነፋሶ ከታይዋን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ መወሰኗ ለብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ቡርኪናፋሶ የቻይናን ፍላጎት ለማርካት ስትል ከታይዋን ጋር ያላትን ግንኙነት በማቋረጥ ሁለተኛዋ ሀገር ሆናለች፡፡ በቻይና መንግሥት ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው ይህ የአፍሪካዊቷ ሀገር ውሳኔ ዶምኒካ ሪፓብሊክ የተሰኘችው የካሪቢያን ደሴቷ ሀገር ከታይዋን ጋር የነበራት ግንኙነት በማቋረጥ ከቤጂንግ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የወሰነችውን ውሳኔ ተከትሎ የተከሰተ ነው፡፡
ራስ ገዝ እና ዴሞክራሲያዊት የሚትባለው በደቡብ ምሥራቃዊ የቻይና የባህር ጠረፍ የምትገኘውን ታይዋን ቻይና የራሷ ግዛት አካል አድርጋ የምትቆጥር ሲሆን፤ ለታይዋን እውቅና ከሚሰጥ ከየትኛውም ሀገር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደማታደርግ ስታሳውቅ ብዙ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከታይፔ ጋር ግንኙነት ያላቸው 18 ሀገራት ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በፓስፊክ እና ካሪቢያን ደሴቶች የሚገኙ በጣም ትናንሽና ድሃ ሀገራት ናቸው፡፡ የቡርኪናፋሶን ውሳኔ ተከትሎ የታይዋን ፕሬዚዳንት ታይ ኢንግዌን ቻይና ኢኮኖሚያዊ አቅሟን በመጠቀም በታይዋን ላይ ጫና እያሳደረች ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡
ከቡርኪናፋሶ ውሳኔ በኋላ ለጋዜጠኞች ያልተለመደና በጠንካራ ቃላት የተሞላ መግለጫ የሰጡት የታይዋን ፕሬዚዳንት ቻይናን አስጠንቅቀዋል፡፡ ‹‹የቻይና ባህሪይ ከሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት የሚጎዳ ብሎም የቻይናን መልካም ስም የሚያጠለሽ ነው፡፡ ሀገራት ከታይዋን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ቻይና እያሳደረች ያለው ጫና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ስለ ቻይና ጥሩ አመለካከት እንዲኖረው አያደርግም›› ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ አክለውም ‹‹ቻይና ሀገራት ከታይዋን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ በማድረግ ታይዋን ላይ እያሳደረች ያለው ጫና ታይዋን ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት አይጎዳም፤ ይልቁኑ ሀገራት ከታይዋን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የሚያደርግ ነው፡፡ በመሆኑም ታይዋያን የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለቻይና አሳልፈው አይሰጡም›› ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡
የታይዋን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፍ ዉ ሀገራቸው ከቦርኪናፋሶ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ፕሮጀክቶችን እንደምታቋርጥና ከዚህ ቀደም ለቡርኪናፋሶ የምትሰጣቸውን የብድር እና ዕርዳታ ድጋፎች እንደምታቋርጥ አስታውቀዋል፡፡ በኤምባሲው ውስጥ የሚገኙ ዲፕሎማቲክ ስታፍ እና ቴክኒክ ልዑካንን በሙሉ ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር እንደምታስወጣም አብራርተዋል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ቡርኪናፋሶ ያሳለፈችውን ውሳኔ እንደሚያበረታቱም የቻይናው የዜና ወኪል ሽኑዋ ዘግቧል፡፡ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ‹‹ቡርኪናፋሶ የአንድ ቻይና መርህ በመቀበል የቻይና አፍሪካ ወዳጅነት ትብብር አካል ለመሆን የወሰነችውን ውሳኔ ቻይና ታበረታታለች›› ብለዋል፡፡
ቤጂንግ እና ታይፔ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ተጠቃሚ ለመሆን እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን ለማግኘት በሚያደርጉት ሽኩቻ የረጅም ዘመናት ባላንጣዎች ሆነው ኖረዋል፡፡ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የቻይናን ኢኮኖሚ ተከትሎ ግን የረጅም ዘመኑ የታይፔ እና የቤጂንግ ፉክክር በቻይና አሸናፊነት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡
አሁን በቡርኪናፋሶ የተወሰነው ዓይነት ታይዋንን ያስደነገጠው ውሳኔ ከዚህ ቀደም በፓናማ ተወስኖ ነበር፡፡ ይህም ፓናማ ለታይፔ ትሰጥ የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ እውቅና ወደ ቤጂንግ አዙራ ነበር፡፡ በታይዋን ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጥና ከተቀሩት የታይዋን ወዳጆች አንዷ የሆነችው ቫቲካን ግንኙነቷን ልታቋርጥ ትችላለች የሚሉ ግምቶች እየተሰነዘሩ ናቸው፡፡
ዋሽንግተን ከቤጂንግ ጋር ይፋዊ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ቢሆንም ከታይዋን ጋር ይፋዊ ያልሆነ ግንኙነት አላት፤ ለደሴቷ ሀገር የተለያዩ ወታደራዊ ድጋፍም ትሰጣለች፡፡
የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ አምራች ኢንዱስትሪዎች የጦር መርከቦችን ለታይዋን እንዲሸጡ ፈቃድ መስጠቱና የታይዋን ከፍተኛ ባለሥልጣናት አሜሪካን እንዲጎበኙ በአጸፋው የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደሴቷን ሀገር ታይዋንን እንዲጎበኙ መፍቀዷ ቤጂንግን ክፉኛ አስቆጥቷታል፡፡
በተያዘው ወር ቻይና የውጭ ሀገራት አየር መንገዶች በድረገጾቻቸው ላይ ታይዋንን ከሌሎቹ የቻይና ግዛቶች የተለየ አድርገው እንዳያሰፍሩ ቻይና ማስጠንቀቋን ተከትሎ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በቅርቡ የቻይና ሲቪል አቪዬሽንና የተወሰኑ የአሜሪካ አየር መንገዶችን ጨምሮ 30 አየር መንገዶች ታይዋን፣ ሆንግ ኮንግ እና ማካው የቻይና ግዛት እንዳልሆኑ በሚያስመስል መልኩ ያሰፈሩትን መረጃ እንዲያነሱ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ የነጩ ቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት በበኩላቸው ቻይና ማስጠንቀቋ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁሟል፡፡
የቻይና መገናኛ ብዙሃን ከሰሞኑ እንደዘገቡት ከሆነ በቅርቡ አንድ ሙጂ የተሰኘ የጃፓን ልብስ ሰፊ ድርጅት በማሸጊያው ላይ ታይዋንን እንደ አንድ ሉዓላዊ ሀገር በሚያሳይ ሁኔታ በታይዋን የተመረተ መሆኑን የሚያመላክት ጽሑፍ አስፍሯል፡፡ ምርቱን ወደ ቻይና ሻንጋይ ግዛት በማስገባታቸው 200 ሺ ዩዋን በግዛቷ ባለሥልጣናት ተቀጥቷል፡፡
የታይዋን ፕሬዚዳንት ‹‹ቡርኪናፋሶ ከሀገራቸው ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ መወሰኗን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ቻይና በዲፕሎማሲ ዘርፍ ታይዋንን ለማፈን እየወሰደች ያለው ውሳኔ ሀገሪቷ በራስ መተማመን እንደሌላት ማሳያ ነው›› ሲሉ አብጠልጥለዋል፡፡

መላኩ ኤሮሴ

Published in ዓለም አቀፍ
Thursday, 07 June 2018 16:22

ሀገር በሥራ ላይ ነች

ሀገር በሥራ ላይ መሆኗን ለማረጋገጥ በወርሃ ግንቦት ወር ውስጥ ብቻ የተከናወኑትን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ማንሳት ይቻላል። ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሎች ያደረጉት ጉብኝትና ምክክር ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለመፍጠር የተሠራ ታላቅ ሥራ ነበር። ከአገራት ጋር ያለንን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠንከር የሚያስችሉ ጉብኝቶች ከሱዳን፣ ከኬንያና ከሳኡዲ አረቢያ ጋር ተደርጓል።
በሦስቱ አገራት ጋር በተደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ታስረው የነበሩ ከ35 ሺ በላይ የሆኑ ዜጐቻችን ተፈተው ለአገራቸው በቅተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማይንድ ሴት ኮንሰልት በተባለ ተቋም አማካይነት በሚሌኒየም አዳራሽ (ግንቦት 11) በተዘጋጀ የአዲስ አስተሳሰብ ማራመጃ መድረክ ላይ ተገኝተው «አዲሱን ተውልድ በአሮጌ አስተሳሰብ መምራት አይቻልም» የሚል መሠረት ያለው ንግግር አድርገዋል።
8ኛውን ዙር ሀገር አቀፍ የፍትህ ሳምንት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ተጐብኝቶ ስለፍትህ ጉዳይ ያለን ግንዛቤ የተሻለ እንዲሆን አግዟል።«ስለ አባይ እሮጣለሁ» በሚል መሪ መልእክት የተዘጋጀው የህዳሴ ግድባችን የብሔራዊ አንድነታችን መገለጫ መሆኑ ይበልጥ ግንዛቤ ያገኘበት መላው ህዝብ በተለይ ወጣቱ «እንዳጋመስነው እንጨርሰዋለን» በሚል ቁርጠኝነት ቦንድ በመግዛትም ሆነ በሌላ ማንኛውም ሁኔታ ለአባይ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገባውን ቃል በተግባር ያሳየበት ታላቅ ብሔራዊ ክንውን በዚህ ወር ተካሂዷል። በአዲስ አበባ ብቻ ከ90 ሺ በላይ ህዝብ በሩጫው ተሳትፏል።
ምንም እንኳን በግድቡ ዙሪያ ብዙ ቢሰራም እንደ ሀገር ግዙፍ ፕሮጀክት ልናውቃቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም፡፡ ለምሳሌ ከስያሜው ብንነሳ የግድቡ ትክክለኛ መጠሪያ በቅጡ መታወቅ አለበት። ገሚሶቹ «የህዳሴ ግድብ» ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ‹‹የአባይ ግድብ›› ይሉታል። «ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ» ብሎ የሚጠራው ብዙ ሰው አላጋጠመኝም፡፡ ይህን ስም ማስረጽ ተገቢ ይመስለኛ። ሌላው ግድቡ የሚገኝበትን ቦታ የሚመለከት ነው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ ከጉባ ከተማ 30 ኬሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝም በደንብ ሊታወቅ ይገባል። ሌላው ወደ ግድቡ ስፍራ ለመድረስ የምንሄደው በየት በኩል ነው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህንንም አብዛኛው ዜጋ አያውቀውም። ግድቡ የሚገኘው በሰሜን ምዕራብ ደብረማርቆስና ቻግኒ ከተሞችን በማቋረጥ 750 ኪሎ ሜትር ላይ ወይም ከአዲስ አበባ በምዕራብ ነቀምትና አሶሳ ከተሞችን በማቋረጥ 850 ኪሎ ሜትር ላይ መሆኑን የሚናገሩ ብዙ ሰዎች የሉም። ጉዳዩን ለግንዛቤ ያህል አነሳሁት እንጂ ህዝቡ « ግድቡ የእኔ ነው፤ አሻራዩን አኑሬያለሁ ... ወዘተ» የሚለው መንፈሱ ጽኑ ነው።
«የላቀ ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለላቀ አገራዊ ስኬት» በሚል መሪ መልእክት የግንቦት 20 በዓል ለ27ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡ በብዙ መስዋዕትነት በተገኘ ድል የተመዘገቡትን የልማትና የዴሞክራሲያዊ ፍሬዎችን መካድ ወይም አሳንሶ ማየት አይቻልም። ሌላው ቀርቶ «ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር» ከሚል አውዳሚ መፈክር ተላቀን «ሁሉም ነገር ወደ ፀረ ድህነትና ትግል» ወደሚል ልማታዊ መሪ መልእክት መሸጋገራችን በራሱ ትልቅ ውጤት ነው። በዚህም መሰረት በሁሉም ክልሎች ገጠርና ከተሞች ልማት ያልተሰራበት አካባቢ የለም መብራት፣ ውሃ፣ ቴሌ፣ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ተሰርተዋል።
ለወጣቶችና ለሴቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በብዙ ተደክሟል። ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ፋብሪካዎችና ታላላቅ ዘመናዊ አውራ መንገዶች ተዘርግተዋል። በአየር መንገድ አገልግሎታችን የላቅ እድገት አስመዝግበናል። በሴቶች አብራሪዎች፣ ቴክኒሺያኖችና መስተንግዶ ባለሙያዎች ቡድን የተቀናጀው በረራ ረጃጅም የአየር ጉዞዎችን ማድረግ ተችሏል። ይህን ሁሉ መካድ እንዴት ይቻላል? በሌላ በኩልም የመኖሪያ ቤቶች ችግርን ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። የከተሞችን በተለይ አዲስ አበባን በአለም የከተማነት ደረጃ ለማዘመን የተሰራው ሥራ በዓይን የሚታይ ነው። እነኝህ ሁሉ በግንቦት 20 ድል ላይ የተመሠረቱ ተጨባጭ ውጤቶች ናቸው።
እንደ እውነቱ ከሆነ ግንቦት 20 ታላቅ ቀን ነው፤ ሊከበርም ይገባል። አከባበሩ ግን ብሔራዊ አንድነትን፣ ህዝባዊ መግባባትን፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋትና የፌዴራል ስርዓቱን በማስጠበቅ ብሩህ ተስፋን በሚፈጥር መልኩ ማድረግ አለብን። እነኝህንም ለማድረግ ሀገር እየሠራች ነው። የኑሮ ውድነት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የንግድ ሂደቱ ስርዓት አለመያዝ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች ... የመሳሰሉት ችግሮች በተለያዩ ደረጃ ቢኖሩም መንግሥትና ህዝብ በጋራ እየሰሩ ለማስወገድ እየተጉ ነው። ሀገር እንደ ሀገር እየተንቀሳቀች ነው፤ የቆመ ነገር የለም። ሁሉም መስመሩን ይዞ እንዲቀጥል እየተሰራ ነው።
ያሳለፍነው የግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሁለተኛ የሥራ ወር (መጋቢት 24 -ግንቦት 24) የተጠናቀቀበትና ሦስተኛ ወራቸውን የያዙበት ነው። ከተመረጡ ጊዜ ጀምሮ ባሳለፉት ሁለት ወራት ከፍተኛ ውጤት ያስገኙ ሥራዎችን አከናውነዋል። ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ቅድሚያ በመስጠት ከህዝቡ ጋር መክረዋል። ለሀገሪቱ የወደፊት ጉዞ መንገዱ እየተመቻቸ ነው። የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና ብሔራዊ ተሳትፎን ለማረጋገጥ በውጭ ሆነው ሲታገሉ ከነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ጋር ፊትለፊት በመነጋገር እየሰሩ ነው። ህዝቡም ከጐናቸው እንደሚቆም በየአጋጣሚው ድጋፉን ገልጿል። ከሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋርም እየተካሄደ ያለው ድርድርም ቀጥሏል። ቀደም ሲል ከድርድሩ በራሳቸው አቋም ወጥተው የነበሩ በመንግሥት በኩል ያለውን የዴሞክራሲ ምህዳር የማስፋት አቅጣጫ ተስፋ ሰጪ ሆኖ ስላገኙት ወደ ድርድሩ ገብተዋል። ይህን አቋም ሁሉም ይደግፈዋል፡፡ በተከናወኑት ስራዎች ሀገራዊ መግባባት እየታየ፤ የአንድነት መንፈስ እያስተጋባ ሲሆን ለዚህም ሀገር እየሰራች ትገኛለች።
በግንቦት ወር የተከናወኑ ሥራዎች በሙሉ በተሟላ ሰላም ውስጥ የተካሄዱ ናቸው። የህዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ያለምንም ስጋት በሰላም እየቀጠለ ነው። በክልሎቻችን መካከልም የተረጋጋ ሰላም አለ። የኢኮኖሚያዊ ልማትና ንግድ በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ናቸው። ሰላም ለሰው ልጅ ሁሉ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። የአገራችን አንድነትና ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ዜጋ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ግዴታ አለበት።
በዚሁ ወር አጽንኦት ከተሰጣቸው በርካታ ጉዳዮች አንዱ የፌዴራል ስርዓቱን የተመለከተ ነው፡፡ ይህን ስርዓት እንደ ጐጂ አድርጐ የማየት የተንሸዋረረ አመለካከትን ለማስተካከል ብዙ ተሰርቷል። ፌዴራሊዝም ማለት ያልተማከለ የመንግሥት አስተዳደር ስርዓት ሲሆን፤ በብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል የነበሩ በኃይል ላይ የተመሰረቱ ግንኙነቶችንና ጭቆና አስወግዷል። በህዝቦች መካከል ችግሮችን የሚፈታና አንድነትን የሚያጠናክር ስርዓት ነው፡፡
በእርግጥ በሀገራችን ህዝቦች በየአካባቢው ለከብቶች ግጦሽና ውሃ ፍለጋ ሲንቀሳቀሱ በመሬት ይገባኛል ሲቆራቆሱ መኖራቸው ይታወቃል። ሁሉም የህዝብ ግጭቶችና አለመግባባቶች የየራሳቸው መንስኤ አላቸው። የግጭቶች መንስኤ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ አይደለም። በተለያዩ ክልሎች ወይም በአንድ ክልል በራሱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ግጭቶች ደግሞ በአገር ሽማግሌዎች፣ በአባ ገዳዎች፣ በሃይማኖት አባቶችና በመንግሥት ተሳትፎ በቂ ግንዛቤ በማስጨበጥ በባህላዊና በኢትዮጵያዊ የእርቅ አሰራር ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው። በጭራሽ ጠመንጃ ማንሳት ሳያስፈልግ መፍታት ይቻላል። ይህ የፌዴራሊዝም ስርዓት በህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት የተገኘ የግንቦት 20 ድል ውጤት ነው። ችግሩ በአብዛኛው ስለፌዴራ ሊዝም ካለን የግንዛቤ ማነስ እንዲሁም በልዩነት ውስጥ ብሔራዊ አንድነትን ማምጣት እንዳይቻል ሆን ብለው አዛብተው በሚሰብኩ ሰዎች በኩል የሚቀርብ የተጣመመ አቀራረብ ነው። ይህን ሁኔታ ለማስተካከለ ሀገር በሥራ ላይ ነች በጊዜ ሂደትም ፌዴራሊዝም ተገቢ ስፍራውን ይቀዳጃል።
ሀገር በሥራ ላይ ነች ሲባል መንገዱ አልጋ በአልጋ ሆኗል ማለታችን አይደለም። በዚህ ጽሁፍ በጠቀስናቸው በሌሎችም የሀገር ሥራዎች ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን እንገነዘባለን። ችግራችን የፖሊሲ ችግር አይደለም ወይም አላሰራ የሚል የፖሊሲ እንቅፋት በአብዛኛው የለብንም። ችግራችን በከፊል የአፈፃፀም ሲሆን በአብዛኛው ግን የአሠራር ችግር ነው።
ፖሊሲ ቢኖርም ባይኖርም የአፈፃፀም መመሪያ ቢወርድም ባይወርድም መሠራት ያለባቸውንና የሌለባቸውን ጉዳዮች በሚመለከት የምንፈጥረው የአሰራር አካሄድ ማረም ይቻላል። ለምሳሌ ሠራተኞች ከመስሪያ ቤቶቻቸው የውሎ አበል ሳይወስዱ እንደወሰዱ ተደርጐ ሂሣቡ የሚያዝበት ሁኔታ አለ። ለአንድ የሥራ ኃላፊ የሚመደብለት መኪና እዚያው መስሪያ ቤት ውስጥ እስካለ ድረስ የሚጠቀምበት እንጂ መስሪያ ቤቱን ከለቀቀ በኋላ መኪናውን እንደራሱ የግል ንብረት ይዞ የሚሄድበት የህግ አግባብ የለም፡፡ ይህ አይነት አሠራር ህገወጥ ብቻ ሳይሆን ፀያፍ መሆኑን ደመነፍሳችን ይነግረናል፡፡ ይህን ለማረም ፖሊሲ ወይም መመሪያ ሳይሆን የሚያስፈልገን ህሊና ነው በዚህ መንፈስ ብንንቀሳቀስ በሥራ ላይ ያለችው ሀገራችን ለሁላችንም ሞልቶ የሚተርፍ የእድገት ደረጃ ይኖራታል። ተስፋ አንቁረጥ! ሀገር በሥራ ላይ ነች።

ግርማ ለማ

Published in አጀንዳ

ከአምስት ዓመት የኢጣሊያን ወረራ በኋላ የኢትዮጵያ ነፃነት መመለሱን ተከትሎ ንጉሠ ነገሥቱ ዙፋናቸውን ተረከቡ። በወቅቱ ካከናወኗቸው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ተግባራት ቀዳሚው የመገናኛ ብዙኃንን ማደራጀትና ማቋቋም ነበር። በዚህም መሠረት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም በይፋ ሥራውን ጀመረ።
የጋዜጣው ስያሜ አፄ ኃይለሥላሴ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ወደሀገራቸው የተመለሱ ቀን «ይህ አዲስ ዘመን ነው» ካሉት ንግግር ላይ የተወሰደ ነው። «የሰማይ መላእክት የምድር ሠራዊት ሊያስቡትና ሊያውቁት ይቻላቸው ባልነበረ በዚህ በዛሬው ቀን ቸር እግዚአብሔር በመካከላችሁ ለመገኘት ስላበቃኝ በሰው አፍ የሚነገር ምስጋና የሚበቃ አይደለም። ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁ ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው፣ ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚሁ በአዲሱ ዘመን ሁላችንም መፈጸም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል» በማለት ባደረጉት ንግግር አዲስ ዘመን ጋዜጣም ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ ዘመን ማብሰሪያና የነጻነት አብሳሪ ጋዜጣ ሆኖ ስራውን ጀምሯል።
«ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነቱን ሥራ ይሠራ ዘንድ የተመሠረተ ነው። ይህ ጋዜጣ የፕሮፖጋንዳ ጋዜጣ ሳይሆን እውነትን፣ አገልግሎትን፣ ረዳትነትን መሰረት አድርጐ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ በአዲስ ሥራ ተመርቶ እንዲረዳ የቆመ ነው። አገልግሎት ስንል የኢትዮጵያን ነፃነት ሲመለስ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው፤ የነበራቸውን ጥቅም ሁሉ አስወግደው፤ ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ሲሉ የሰው አቅም ሊሸከመው የማይችለውን ድካም ተቀብለው፤ ማናቸውም ሰው ሊያደርገው ያልቻለውን በኢትዮጵያ ሕይወት ውስጥ እስከ ዛሬ ያልታየውን ሥራ ከፍፃሜ ላደረሱ ለንጉሠ ነገሥታችንና ላቆሙት መንግሥት የሚያገለግል እንዲሆን ነው» በማለት በዋነኝነት የተቋቋመበትን ዓላማ «የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጀመር» በሚል ርዕስ ባስነበበው ርእሰ አንቀጹ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በርካታ የሥነጽሑፍ ሰዎችን አፍርቷል፤ ደምቀው እንዲታዩም አድርጓል። በርካታ የሥነጽሑፍ ሰዎችም አዲስ ዘመንን ባለ ግርማ ሞገስ፤ ተወዳጅና ተነባቢ አድርገውታል። መረጃ ሰጥተውበታል፤ እውቀት ተቀብለውበታል። እንደ ጳውሎስ ኞኞ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ በዓሉ ግርማን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ የብዕር ግርማ ሞገሶች የጻፉበት ጋዜጣ ነው።
ጋዜጣው ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት የሚጠበቅበትን የመረጃ ሰጭነት ሚና በብቃት ተወጥቷል። ከዚህ ባለፈም ለሀገራችን ሥነጽሑፍ እድገት ያበረከተው አስተዋጽኦም በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ጋዜጣው ከመረጃ ሰጪነቱ ባሻገር የታሪክ ማጣቀሻ ድርሳን ሆኖ አገልግሏል። በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በስነፅሁፋዊ ስራዎች ላይ የበርካታ ጥናታዊ ፅሁፎች መነሻና ማጣቀሻ በመሆን አገልግሏል፤ አሁንም በማገልገል ላይ ነው። በተለይም በሚሌኒየሙ መግቢያ ላይ ለኢትዮጵያ ስነጽሁፍ እድገት ባደረገው አስተዋፅኦ ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ግንባር ቀደም ተሸላሚ መሆኑ ለአብነት ተጠቃሽ ነው።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ የአዲስ ዘመን ትንሳኤ አብሳሪ ነውና አሁንም ብዙ ብስራት ይጠብቀዋል። ሠዎች በያዘው ቁም ነገር መርጠውና ፈልገውት የሚገዙት፤ ተሻምተው የሚያነቡት ጋዜጣ መሆን ይጠበቅበታል። ብቸኛው የዕለት ጋዜጣ በመሆኑም በየዕለቱ በጉጉት የሚጠበቅ ጋዜጣ ሊሆን ይገባል። የኢትዮጵያን ስኬትና ገመና እስከ ጓዳ ጎድጓዳው ድረስ ዘልቆ እየፈተሸ አዳዲስ እና ትኩስ መረጃዎችን የሚመግብ እንዲሆን ከአመራሩ ጀምሮ የ77ኛ ዓመት ልደቱን ማብሰሪያ ሻማ የለኮስን ሰራተኞች ሁሉ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።
ጋዜጣው ለበርካታ ጊዜያት ያጋጠሙትን ውጣ ውረዶች አልፎ ለዚህ መድረሱም አይካድም። በመሆኑም በቀጣይም የሚያጋጥሙትን መሰናክሎች በማለፍ ይዘቱን የሚያሻሽሉ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የህዝብ ድምፅ መሆኑን ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስመሰክራል፡፡ ጠንካራ ስራ ለማቅረብ የሚደፍሩ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሁም ለስራቸው ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሚሰማቸው ጋዜጠኞች መፍለቂያ ይሆናል። ብቃትና ታላላቅ ሰብዕና ያላቸው አምደኞች እንደቀደመው ዘመን ዛሬም አዲስ ዘመን ላይ እንዲፅፉና እንዲሳተፉም ይጋብዛል፤ያበረታታል።
አንባቢ የሚመርጣቸውና በጉጉት የሚያነባቸው አምዶችን ለመክፈትም ይተጋል። የተለያዩ ድምፆች በሚዛናዊነት የሚስተናገዱበት ጋዜጣ ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሰራል። አሁን እየሠሩ ያሉ ባለሙያዎችም ይህን ለማድረግ ብቃቱ እንዳላቸው በማመን ዘመኑ የሚጠይቀውን እውቀትና ክህሎት እንዲላበሱ ለማድረግም ኃላፊነቱን ይወጣል። የአዲስ ዘመን ለአዲስ ዘመን ማብሰሪያነት ተቋቁሟልና ወደፊትም የኢትዮጵን ህዳሴ ለማብሰር፤ የላቀ ብሄራዊ መግባባትና ለዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ለላቀ አገራዊ ስኬት በርትቶ ይሰራል። ከዘመኑ ጋር እየዘመነ ዛሬ የ77ኛ ዓመት የምስረታ ሻማውን ሲለኩስም ለኢትዮጵያ ህዳሴ የሚተጋ ብእር የጨበጠ መሆኑን በማስታወስ ነው።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አራት ኪሎን ሰንጥቆ ፒያሳ የሚዘልቀው ጎዳና በተሽከርካሪ ተጨናንቋል፡፡ ገና ከረፋዱ አላፊ አግዳሚው በዝቷል፡፡ ለትርምሱ ቦታ ያልሰጡ አንድ አዛውንት ከፕላስቲኩ መቀመጫ ተደላድለው በገለጡት «ኒውስ ዊክ» መፅሔት ላይ አተኩረዋል፡፡ ከካፍቴሪያው በረንዳ ያዘዙትን የጀበና ቡና«ፉ…ት» እያሉ ከመነፅራቸው ባሻገር በሩሲያው ረቂቅ የሚኒቴሪ ታሪክ ተመስጠዋል፡፡ በየመሃሉ በአግራሞት ፈገግ የሚሉት አቶ አዲስ እንግዳ፤ የዕድሜያቸውን አጋማሽ የሰጡለት የጋዜጠኝነት ሙያ ዛሬም ከንባብ አቆራኝቷቸዋል፡፡

ጎምቱው ጋዜጠኛ ከ73 ዓመት በፊት ይህቺን ዓለም ሲቀላቀሉ አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የምስረታውን አራተኛ ዓመት ሻማ ለኩሷል፡፡ በ1933 ዓ.ም ተመስርቶ ዛሬ 77 ዓመት የደፈነው ጋዜጣው በየዘመኑ የተከሰቱ በርካታ ፀሐፍትን ለዘርፉ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡ ከበዓሉ ግርማ እስከ ብርሐኑ ዘሪሁን፣ ከጳውሎስ ኞኞ እስከ አንተነህ ይግዛው የተቡ ብዕረኞችን የሥነፅሑፍ ሀ…ሁ… አስቆጥሮ በልብ-ወለድ ሥራዎች አግንኗቸዋል፡፡ የቀደሙት አልፈው መጪ ብዕረኞች እንዲተጉ አድርጓል፡፡
ከንባብ ተመስጧቸው ነቅተው በትዝታ ወደትናንት የተሻገሩት አቶ አዲስ፤ ከተጠቀሱት ደራሲያን መካከል ደቀመዝሙሩ ለነበሩት በዓሉ ግርማ የላቀ ግምት አላቸው፡፡ በጋለ የሥነፅሑፍ ስሜታቸው ላይ የማይጠፋ የብዕር ፍም በማንደድ ዳናውን ተከትለው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል፡፡ «ጋዜጠኝነት የጀመርኩት በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ በተርጓሚነት ነበር፤ ከዚያም በዓሉ ግርማ አዲስ ዘመን የተሻለ ተርጓሚ ይፈልጋል በማለት በ1964 ዓ.ም ወደ ፕሬስ አስመጣኝ» የሚሉት አቶ አዲስ፤ ከተቀጠሩባት ዕለት ጀምሮ ከትርጉም ሥራ ጎን ለጎን በዜና ክፍል እየሠሩ እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት ዘልቀዋል፡፡
አቶ አዲስ፤ ከጡረታ በኋላ ያለውን የፍሪላንስ ቅጥር ጨምሮ በአጠቃላይ 45 ዓመት በአዲስ ዘመን ጋዜጠኝነት አገልግለዋል፡፡ «ጋዜጣውን እንደራሴ ንብረትና ሀብቴ ነው የምቆጥረው፤ ሌላ ነገር ስለማላውቅ ራሴንም ከአዲስ ዘመን ለይቼ አላየውም» ይላሉ፡፡ በወቅቱ በየዕለቱ የሚታተመውን ጋዜጣ በጥቂት ባለሙያዎች መዘጋጀቱ በሥራቸው ላይ የነበረውን ጫና አብዝቶታል፡፡ በዚህም የግል ወይም የማህበራዊ ኑሮ እስከመዘንጋት ቢያደርስም በሙያው ፍቅር ተለክፈዋልና ጫናው ቢበዛም ፍላጎታቸው ሁሌም ሙሉ ነበር፡፡

በተለያዩ ዘመናት ጋዜጣው ላይ አሻራቸውን ካኖሩ በኋላ ወደተለያዩ መስኮች የተሳቡ በርካታ ናቸው፡፡ ከ1980 ዓ.ም እስከ 1988 ዓ.ም ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አጋረደች ጀማነህ ይጠቀሳሉ፡፡ «አዲስ ዘመን ጀማሪ ሆኜ ስቀጠር የሥነጽሑፍ የትምህርት ማስረጃዬን እንጂ የጋዜጠኝነት ሙያን ይዤ አልገባሁም» የሚሉት ዶክተር አጋረደች፤ ጋዜጣው የተግባር ትምህርት ቤት ሆኗቸዋል፡፡ ለእርሳቸው የሙያ ጉዞም እንደ አቶ አዲስ እንግዳ፣ አቶ ግርማ ቦጋለ እና አቶ ዋካ ይርሳው ትልቅ ስፍራ አላቸው፡፡
«አዲስ ዘመን ጋዜጣ የታላላቅ ባለሙያዎች መፍለቂያ ነው» የሚሉት ዶክተር አጋረደች፤ ለእርሳቸው የዛሬ ማንነት የትናንት ልምዳቸው ብዙ አበርክቷል፡፡ ለመምህርነት ሕይወታቸው ከፅንሰሃሳብ እውቀት ባሻገር የአገሪቱን የጋዜጠኝነት ዓለም ወደመሬት ወርደው እንዲረዱ ትልቅ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በየትኛውም ብዙኃን መገናኛ ውስጥ የተሟላ ጋዜጠኛ ለመሆንም እንደ አዲስ ዘመን ባሉ ዕለታዊ ጋዜጦች ላይ መሥራት የላቀ አስተዋፅኦ አለው ይላሉ፡፡
የትውልድ ቅብብሎሹ ቀጥሏል፡፡ የበዓሉ ተከታይ የነበሩት አቶ አዲስ እንግዳ በተራቸው ለበርካታ ወጣቶች አርአያ ሆነዋል፡፡ ዓመታት ተሻግረው ባገኙት ዕድል ብዕራቸውን ካሳረፉ ወጣት ጋዜጠኞች መካከል አንዷ የነበረችው ቆንጂት ተሾመ፤ በልጅነቷ ጋዜጣውን ፈልጋ ስታነብ አድጋለች፡፡ አቶ አዲስና ሌሎች ብዕረኞችም ለነገ የጋዜጠኝነት ህልሟ መሠረት ጥለዋል፡፡
«ፕሬስ ከመቀጠሬ በፊት ሐረር ከተማ አማራጭ የዕትመት ውጤቶች ባለመኖራቸው በተለይም የሰንበት ጋዜጣን እከታተል ነበር» የምትለው ቆንጂት፤ በ1999 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ እንደወጣች ፕሬስ በመቀጠር ለዓመታት አብሯት የኖረ ህልሟን እውን አድርጋለች፡፡ ዕድሉን ካገኘች በኋላም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደ ፀሐፊ ብቻ ሳይሆን እንደ ተማሪም ሆና በመሥራቷ ብቃቷን አጎልብታለች፡፡
ጋዜጣው ካፈራቸው ወጣት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የነበረውና በአሁኑ ወቅት በፌዴራል አቃቤ ሕግ የሚያገለግለው አብርሃም አያሌው፤ ከጀማሪ ሪፖርተርነት ጀምሮ እስከ ረዳት አዘጋጅነት ለስድስት ዓመታት ቆይቷል፡፡ «የተማርኩት ሕግ በመሆኑ ስለጋዜጠኝነት ሃ…ሁ የቆጠርኩት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ነው» የሚለው አብርሃም፤ በተለይም በሕግ ትምህርት መነሻነት የፓርላማ ውሎዎችና የምርመራ ጋዜጠኝነትን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርጓል፡፡ በዚህም የተለያዩ የምርመራ ዘገባ ውጤቶች መመልከቱን ይጠቅሳል፡፡
«በጋዜጠኝነት ሁሉንም ሙያ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ይበልጥ ደግሞ በአንድ ጉዳይ ጥልቅ እውቀት ማካበት በዘገባዎች ላይ ጥንካሬን ይጨምራል» የሚለው አብርሃም፤ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከአጀንዳ መቅረፅ በተጓዳኝ የተደበቁ ብልሹ አሠራሮችን ለማጋለጥ መሣሪያ ይሆናል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣም በአንድ ወቅት ጀምሮት አሁን የተቀዛቀዘው የምርመራ ዘገባ በርካታ የሕግ ጥሰቶችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፈልፈል ችሏል፡፡ ከራሱ ተሞክሮ በመነሳትም በአንድ ወቅት በአዋሽ ባንክ ተፈፅሞ የነበረን የአሠራር ጥሰት ተከትሎ በተሠራ የምርመራ ዘገባ በርካታ ስህተቶች ተገኝተው ማረሚያ ተደርጎባቸዋል፡፡
የትውልዶች ቅብብሎሹ አሁንም ቀጥሏል፡፡ በጋዜጠኝነት የቅርቡን ትውልድ የሚወክለው ዋለልኝ አየለ፤ ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ጋዜጣውን ሲያነብ ቆይቷል፡፡ ተራው ደርሶ መፃፍ ከጀመረ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል፡፡ እንደሌሎቹ ጋዜጠኞች በአቶ አዲስ እንግዳ የሚዘጋጀውን ዓለም አቀፍ ዜናዎች ሲያነብ ኖሯል፡፡ «አዲስ ዘመን ተቀጥሬ እሠራለሁ ብዬ አላስብም ነበር» የሚለው ዋለልኝ፤ በሁለት ዓመት ውስጥ የሥነፅሑፍ አቅሙን ከሙያ ሥነምግባር ጋር አጣምሮ ማግኘቱን ይናገራል፡፡ በቀጣይም ጋዜጣው ላይ ከጋዜጠኞች ልዩ ተሰጥኦና ፍላጎት ጋር የሚጣጣም አሠራር ቢዘረጋ የተሻለ ነገር መሥራት ይቻላል ይላል፡፡
የብዙዎች የሙያ አባት የሆኑት አቶ አዲስ «በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሠራ አንድ ጋዜጠኛ ሙያውን መውደድና ማክበር አለበት» ሲሉ ወጣት ጋዜጠኞችን ይመክራሉ፡፡ ከጠንካራ ሥነ-ምግባር በተጨማሪ ባለሙያው ሁሌም በቡድን ሥራና በውይይት የሚያምን መሆን ይገባዋል፡፡ ካለፉት ጊዜያቶች አንፃር ለጋዜጠኝነት ሙያ አሁን ብዙ መልካም ዕድሎች አሉ፤ ጋዜጠኞች በተለያዩ መንገዶች ብቃታቸውን ማሻሻል ከቻሉ ዘርፉን ለማሳደግ ምቹ መድረክ ተፈጥሮላቸዋል ይላሉ፡፡
የእርሳቸውን ሃሳብ የሚጋራው አብርሃም አያሌው በበኩሉ፤ አሁን በአገሪቱ የተከፈተው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ለሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ተልዕኮ ተፈፃሚነት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ ጋዜጣው ከዚህ ቀደም ትኩረት ሰጥቶ ሲሸፍናቸው የቆዩ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር፣ የሰብአዊ መብት፣ የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል፣ የዜጎች ሕገወጥ ፍልሰት እንዲሁም የወጣቶች ሥራ አጥነት አጀንዳዎች ዙሪያ ሞጋች ዘገባዎችን መሥራት ይገባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ለውጡም ይሄን ማስተናገድ የሚችል በመሆኑ ከፊት ቀድሞ መገኘት የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት መሆን አለበት፡፡
የትናንቱ ፀሐፊ ዛሬ የጋዜጣው አንባቢ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት «አሁን ጋዜጣው ላይ መሻሻሎች ቢኖሩም ዘገባዎችን ተከታትሎ ያመጡትን ውጤት መሸፈን ላይ ክፍተት ያለ ይመስለኛል» የሚለው አብርሃም፤ የትኛውም የመልካም አስተዳደር መጓደል ከተዘገበ በኋላ በኅብረተሰቡ ሕይወት ላይ ያሳደረው አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይ ለጋዜጠኞች በራስ መተማመን የሚዲያ ተቋሙ መሪዎች ብቃት ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
«ጋዜጠኛው ሁሌም ሙያዊ ነፃነት ሊኖረው ይገባል» የምትለው ቆንጂት፤ ለዚህ ደግሞ የሚዲያ ተቋማት አመራሮች የዘርፉ ሙያተኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጋዜጠኞች የሕዝብ አገልጋይነት ባሕሪ መላበስ፣ ከዘመኑ ጋር ለመራመድ በማህበራዊ ድረገጽ የጋዜጣውን ተደራሽነት ማጠናከር፣ የቡድን ሥራ ማስረፅ፣ ጥራት ያለው ሥራ ለማከናወን ጫናዎችን መቀነስ እንደሚገባ ትገልጻለች፡፡
ከቀድሞ ባልደረቦች ውስጥ በዋናነት የተንፀባረቀው የጋራ ጉዳይ የዘገባዎች ጥራት ነው፡፡ ለዘገባዎች ጥራት ደግሞ የባለሙያዎች በቁጥርም ሆነ በአቅም የተሻለ መሆን ይገባዋል፡፡ ተቋሙ ለዚህ ክፍተቶቹ ትኩረት ሰጥቶ መፍታት ከቻለ ለ77 ዓመታት የውጣ ውረድ ቅብብሎሽን አስቀጥሎ ነገን በተሻለ ከፍታ ላይ የማኖሩ ጥረት መሳካቱ አይቀርም፡፡

 

ዜና ሐተታ
ብሩክ በርሄ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።