Items filtered by date: Friday, 08 June 2018

የእነ እገሌ ቡድን ዓይኑ የታወረው፣
አርባ ኳስ ሰጥተነው አርባውንም ሳተው፡፡
እንዲህ ላትችሉን አትላወሱ፣
ዓይንን እንደ ንስር፤ እጅ እንዳንበሳ ከኛ ተዋሱ፡፡
እየተባለ ተሸናፊው ቡድን በሥነ ቃል ሲሸነቆጥ፤ በሌላ ጎራ ደግሞ ለጀብደኛውና አሸናፊው ቡድን ተከታዩ የሙገሳ ቃል ግጥም ይደረደርለታል፤ ይሽጎደጎድለታል በ‹‹ፋግ›› ጨዋታ፡፡
ጆሮው እንደቆቅ ዓይኑ እንደ ንስር፣
በአንዴ መትቶ ወንዝ የሚያሻግር፡፡
በረጅም ዱላ ቢቀረድዳት፣
ኳሲቱ ጠፋች የሄደችበት፡፡
በማለት አሸናፊው ቡድን ይወደሳል፡፡ ጨዋታው ደግሞ ሸካ፣ ፋግ ወይንም ሹካ ተብሎ ይጠራል፡፡
ሹካ በአብዛኛው በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ የትግራይ ክልል አክሱም አካባቢ እና በአጎራባች ቦታዎች ከሚዘወተሩ ባህላዊ የስፖርት ጨዋታዎች አንዱ ነው፡፡ ጨዋታው በተለምዶ ስሙ ከቦታ ቦታ ቢለያይም በጎንደርና አካባቢው ‹‹ፋግ›› ወይንም ‹‹ሹካ›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ በትግራይ አክሱምና አካባቢው ‹‹ሸካ›› በመባል ይታወቃል፡፡
አቶ አማረ ጥጋቡ ይባላሉ፡፡ የሰሜን ጎንደር ተወላጅና በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ናቸው፡፡ ይህንን ስፖርት ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያዘወትሩት እንደነበር አጫውተውናል፡፡ ይህ የባህል ስፖርት በብዙዎች ዘንድ ይታወቅና ስፖርታዊ ፋይዳውም ጎልቶ ይታይ ዘንድ የማስተዋወቅ ሥራውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ስፖርት እንደ አብዛኞቹ የባህል ስፖርት መቼና የት እንደተጀመረ ባይታወቅም፤ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣና አሁንም በተጠቀሱት አካባቢዎች እየተዘወተረ ያለ ነው የሚሉት አቶ አማረ፤ የሹካ ጨዋታ ከፍተኛ አካላዊ ጥንካሬንና ቅልጥፍናን የሚጠይቅ፣ በተፈጥሮው ጉልበትንና አቅምን ከሚፈትሹ ጨዋታዎች ውስጥ እንደሚመደብና ጨዋታው ያልተገደበ ክፍት የመጫወቻ ሜዳ እንደሚያስፈልገው ነው የሚናገሩት፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ይህ ጨዋታ በሁለት ቡድኖች መካከል የሚደረግ ፍልሚያ ሲሆን፤ ኳስን በዱላ በመምታትና በተቃራኒ ቡድን በኳስ ላለመመታት የሚደረግ ፉክክር ነው፡፡ ተከላካይ ቡድን ኳስን የሚቀልብና በቀለበው ኳስ ተቃራኒ ቡድን ለመምታት ሲሞክር አጥቂ ወይንም ኳስ የሚመታው ቡድን ደግሞ ኳስን በዱላ ላለመሳትና በቀላቢ ቡድን ላለመመታት ይጫወታል፡፡ በዚህ ጊዜ ኳስ ለውጥ የሚደረገው አጥቂ ቡድን ኳስ የመምታት እድሉን ሙሉ በሙሉ ከሳተ ወይንም ከመዝመቻና ከመነሻ ምልክቶች መካከል ባለው የሜዳ ክፍል በተቃራኒ ተጫዋች በኳስ ከተመታ ነው፡፡
የተጫዋቾች ቁጥር በእያንዳንዱ ቡድን ውስጥ ከ 3 እስከ 7 ተጫዋቾች እንዲሆኑ የሚመረጥ ቢሆንም፤ ይህ ነው የተባለ ውስን ቁጥር ግን የለውም፡፡ በሹካ ጨዋታ ውስጥ ማሸነፍ ማለት ለረጅም ሰዓት ወይንም ለተደጋጋሚ ጊዜ ኳስ የመቅለብ ብልሐትና ብቃት ያለው ቡድን መሆን አለበት፡፡
አጨዋወት
አቶ አማረ የአጨዋወት ስልቱንም ሲገልፁ፤ በመጀመሪያ ከሁሉም ተጫዋቾች ውስጥ ሁለት የቡድኑ መሪ ወይንም የቡድን አባት በመምረጥ ሁለት ቡድኖችን ይመሰረታሉ፡፡ ጨዋታውን ሁለቱ የቡድን አባቶች እጣ አውጥተው በሥራቸው ልጆቹን አቧድነው የቡድን አጋሮቻቸውን ያውቃሉ፡፡ ቡድን ከመሰረቱ በኋላ የመዝመቻ ቦታውን ተስማምተው በምልክት ይወስናሉ፡፡ ከዛ እጣ የደረሰው ቡድን አባት ኳስ በመምታት የቡድን አባላቱ ዘምተው እንዲመጡ ያደርጋል፡፡ ለእርሱ በተሰጠው አራት እድል ከቡድን አጋሮቹ አንድና ከዚያ በላይ ዘምተው ከመጡ ጨዋታው በነሱ በኩል ይቀጥላል፡፡ ካልሆነ ግን ለሌላኛው ቡድን ኳስ ተቀይሮ በዚህ መልኩ ጨዋታው ይካሄዳል፡፡
የጨዋታው ዋና ዋና ህጎች
አቶ አማረ፤ ‹‹ይህ የባህል ጨዋታ እንደሌሎች የስፖርት ዓይነት ጨዋታዎች ሁሉ የራሱ የሆኑ ህጎች አሉት፡፡›› ይላሉ፡፡ ጨዋታው የሚጀመረው በእጣ ሲሆን፤ እጣ የደረሰው ቡድን ኳስ በይ ወይንም አጥቂ ሲባል፤ ሌሎቹ ደግሞ ኳስ አብይ ወይንም ቀላቢ ይሆናሉ፡፡ ጨዋታው ሁለት የቡድን አባቶች ሲኖሩት ሌሎች የቡድን አባላትን በማቧደን ይመለምላሉ፡፡ ኳስ በዕጣ የደረሰው ቡድን ከተቃራኒ ቡድን የሚሰጠውን ኳስ በመምታት የሚጀምር ሲሆን፤ ቀሪ ባልደረቦቹ ግን ኳስ መምታት የሚችሉት ለቡድን አባቱ በተሰጠው አራት ኳስ የመምታት ዕድል በተቃራኒ ቡድን በኳስ ሳይመቱ ዘምተው ከመጡ ብቻ ነው፡፡ ኳስ የሚመታው የቡድን አባት በሁሉም ሙከራ አንድ ሰው ዘምቶ ሳይመጣ ከጨረሰ ኳስ ተቀይራ ለተቃራኒ ቡድን ይሰጣል፡፡ አንድ ተጫዋች ኳስ የመምታት የሙከራ ዕድሉ አራት ጊዜ ብቻ ሲሆን፤ ኳስ የሚመቱ አባላት ቡድን ከመዝመቻውና ከመነሻው መካከል ባለው ሜዳ መቆም አይፈቀድላቸውም፡፡
እስከ አንድ ሜትር ርዝመት ሊደርስ የሚችልና ውፍረቱ ከሁለት እስከ ሦስት ሳንቲ ሜትር የሚሆን ድቡልቡል በትር ወይንም ዱላ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም በግምት የሜዳ ቴኒስ ያክል መጠን ያላት ከጨርቅ፣ ከፀጉር፣ ከፕላስቲክ ወዘተ ሊሰራ የሚችል ለስላሳ፣ ለመወርወር ቀላልና በአንድ እጅ በቀላሉ ሊያዝ የሚችል ኳስ ያስፈልጋል፡፡ ኳሷ ስትመታ ጉዳት ልታደርስ የማትችል መሆን እንዳለባትም ነው አቶ አማረ የሚያብራሩት፡፡
በጨዋታው ወቅት ደልዳላና ክፍት ሰፊ የመጫወቻ ቦታ ይመረጣል፡፡ የመጫወቻ ቦታውም ኳስ መምቻው አካባቢ በግምት 10 ሜትር ስፋት ያለው ሆኖ ኳስ ወደሚመታበት አቅጣጫ እንደ ጎን ሶስት ወይም እንደ ውርወራ ስፖርት ሜዳዎች ቅርጽ ያለው ሲሆን ርዝመቱ ኳሷ እስከሄደችበት ድረስ ሲሆን፤ በሜትር አይወሰንም፡፡ በመነሻው በኳስ መቅለቢያው መስመር እና በመድረሻው ምልክት መካከል ያለው ርቀት በሁለት ቡድኖች ስምምነት የሚወሰን ሲሆን፤ በግምት ከ50 እስከ 60 ሜትር ሊረዝም ይችላል ይላሉ፡፡
ከአጥቂ ቡድን አንድ ተጫዋች የቡድን አጋራቸው ኳስ ሲመታ አንድ ወይም ከዚያ በላይ አባል በአንድ ጊዜ ዘምቶ መምጣት ይችላል፡፡ ብዙ ዘምተው የመጡ አባላት ካሉ የማጥቃት እድላቸው እየሰፋ ይሄዳል፡፡ አንድ ዘማች ፈጣን እና ቀልጣፋ ከሆነ በአንድ ኳስ ምት ከመዝመቻው ደርሶ መመለስ ይችላል፡፡
ማንኛውም የአጥቂ ቡድን አባላት በመዝመቻውና በመብያው ክልል መካከል በተቃራኒ ቡድን በኳስ ከተመታ የኳስ ለውጥ ይደረጋል፡፡ ኳስ የሚያበላ ቡድን ተጫዋች የተቃራኒን ቡድን አባል በመዝመቻ እና በመነሻ ነጥብ መካከል ያገኘውን ማንኛውንም ተጫዋች በኳስ የመምታት መብት አለው፡፡ ጨዋታውን ለመጫወት የሚያስፈልጉ የቡድን አባላት ብዛት ከሦስት እስከ ሰባት ቢሆን ይመረጣል፡፡
አቶ አማረ እንዳሉት፤ በዚህ ጨዋታ ላይ ይህ ነው የሚባል ነጥብ አያያዝ ባይኖርም ለተደጋጋሚ ሰዓት ኳስ ሲበላ የቆየ ቡድን እንደአሸናፊ ይቆጠራል፡፡ የኳስ ለውጥ የሚካሄደው አንደኛ የአጥቂ ቡድን የተሰጠውን ሙከራ ሁሉ ተጠቅሞ ኳስን ከሳተ ወይንም ሙከራውን እስኪጨርስ ከቡድን አባላት ዘምቶ የመጣ ሰው ከሌለ ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ ተቃራኒ ቡድን አባላት አልቻልናችሁም እድል ስጡን ብሎ ከጠየቀ ነው፡፡
የጨዋታው ጠቀሜታ
ስፖርት ለሰው ልጅ የሚሰጠውን በርካታ ጠቀሜታዎች በዚህ የባህል ስፖርት አማካኝነት ማግኘት እንደሚቻል የሚናገሩት አቶ አማረ፤ ይህ ጨዋታ ቀልጣፋና ፈጣን ሩጫን ስለሚጠይቅ ለተጫዋቾች የአካል ብቃታቸውን እንደሚያ ዳብርና ይህ ደግሞ እግረ መንገዱን የአተነፋፈስና የደም ዝውውር ስርዓትን ጤና ለማሻሻል ይረዳል፡፡ ከዚህ ባሻገር ጨዋታው ትኩረትን ስለሚጠይቅ የአዕምሮ ንቃትን ያዳብራል፡፡ ኳስ በሚመታ ሰዓት የግብረ መልስ ችሎታን ስለሚጠይቅ የእይታና የድርጊት ቅንጅታዊ አሰራርን ያዳብራል፡፡ በአጠቃላይ እንደማ ንኛውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የአካልና የአእምሮ ጤንነትን በመጠበቅና በማሻሻል ጤናማ እንድንሆን ያደርጋል፡፡
የተጫዋቾች ማህበራዊ መስተጋብር ምን ይመስላል
አቶ አማረ እንደገለጹት፤ ይህ ጨዋታ እንደማንኛውም የቡድን ጨዋታና ስፖርት ተሳታፊ ለሆኑ ስፖርተኞች ከጓደኞቻቸውና አብሮ አደጎቻቸው ጋር ማህበራዊ ግንኙነታ ቸውን ያዳብራል፡፡ በተጨማሪም የማሸነፍና መሸነፍ ባህሪን ተላብሰው በማደግ በሥነ ምግባራቸው ጥሩ እንዲሆኑ ከማድ ረጉም በላይ በራስ የመተማመን ክህሎታ ቸውን ያዳብሩ በታል፡፡ በአጠቃላይ የተስተካከለ ሁለንተናዊ እድገት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
የጨዋታው አሁናዊ ገፅታ
‹‹ቆየት ባሉት አመታት ልጆች እያለን ሰብል ተሰብስቦ በሚያበቃበትና በዓላትን ተንተርሰው በሚኖሩን ትርፍ ጊዜያቶች፣ ከብቶችን በምናግድበት ወቅት ፣ ጨዋታ ውን በብዛት እናዝወትር ነበር፡፡ ነገር ግን ከጊዜ ሂደት በኋላ ጨዋታው እየተቀዛቀዘ መጥቷል፡፡ ትኩረቱ ወደ ዘመናዊ ስፖርት ስላደላና የባህል ጨዋታ እንደ ኋላ ቀር ተደርጎ ስለሚታሰብ የዚህ ስፖርት አዝወታሪዎች ፊታቸውን ወደ እግር ኳሱ አዙረውታል፡፡›› በማለት አቶ አማረ ጨዋታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ስፖርቱ ዘመናዊ ከሚባሉ የስፖርት ዓይነቶች ባልተናነሰ ሁኔታ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ስለሚሰጥ መዘንጋት የለበትም፡፡ ጨዋታውን ሽልማት ለማግኘት ሳይሆን ጎበዝና ሰነፍን በመለየት የአቋም መለኪያ ማድረግ እንዲሁም ተዝናኖትን ለመፍጠር ነው፡፡ ከፍተኛ ፍጥነትንና አነጣጥሮ ኳስ መምታትን ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ግን ሰው ስለ ስፖርቱ ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ከነበረበት የተሻለ ተዘውታሪነት ቁልቁል እየተጓዘ ነው፡፡
ምክር
እንደ አቶ አማረ ገለጻ፤ የ‹‹ሹካ›› ባህላዊ ጨዋታ ሰርቶ መብላትን በምሳሌነት በውስጡ የያዘና በአስተማሪነቱ ትልቅ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ባህልን ከመጠበቅ አንፃር ስፖርቱ ትኩረት ይሻል፡፡ ማህበረሰቡን በአስተሳሰብ ከመለወጥ ጀምሮ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገቡ መፍትሄዎች በባህል ስፖርት ፌዴሬሽን በኩል መፈጸም አለባቸው፡፡ ከፍተኛ ንቅናቄ ተፈጥሮ እንዲህ አይነት ለመጥፋት የደረሱ የባህል ስፖርቶችን ግንዛቤ በመፍጠር መጠበቅ ይገባል፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ከ290 በላይ የሚሆኑ የባህል ስፖርቶች አገሪቷ ውስጥ አሉ፡፡ ነገር ግን ተመዝግበው እውቅናን ያገኙና አገር አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ላይ ለተሳትፎ የሚቀርቡት 11 ብቻ ናቸው፡፡ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን በየዓመቱ ሁለት የባህል ስፖርቶችን ለመመዝገብ እቅድ እንደያዘ ቢናገርም እነዚህን ሁሉ መዝግቦ ለመጨረስ ብዙ አመታን ስለሚፈጅ አሰራሩን መለወጥ ይኖርበታል፡፡ በተለይ አሁን ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየአካባቢው ተስፋፍተው ስላሉ በትብብር ቢሰራ ባህላዊ ጨዋታዎችን ከመጥፋት መታደግ ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ለአብነትም የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ሸዋ ውስጥ ያሉ የባህል ስፖርቶችን በመመዝገብ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹ሹካ›› ባህላዊ ጨዋታን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች እየተረሱ የሚመጡ የባህል ስፖርቶችን ሰብስቦ መሰነድ ብቻ ሳይሆን እየተተገበሩ እንዲቆዩ በማድረግና የተሳታፊን ቁጥር መጨመር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ተግባር ነባር የዚህ የባህል ስፖርት ከዋንኞችንም መጠቀም የግድ ይላል፡፡ የተሳታፊ ቁጥር መጨመሩ ጨዋታዎቹ አካላዊ እንቅስቃሴን ስለሚከተሉ ጤንነታቸውን የሚጠብቁ ዜጎች ቁጥርም እንዲበዛ ይሆናል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ብዙዎች ስፖርትን ከኢኮኖሚ ችግር ማምለጫነት ለመጠቀም ያስባሉ፡፡ በዚህ ዘመን በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ስፖርት የሚጠቅመው ገንዘብ ለማግኘት ነው የሚል ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ለጥቂት ስፖርተኞች ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ሽልማትን አስቦ የሚደረግ ስፖርታዊ ጉዞ አድካሚ ነው፡፡ ነገር ግን በለስ ከቀናው በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ማግኘትም ይቻላል፡፡ ፍላጎቱ የጤና ጥቅም ማስቀደም ላይ ማተኮር መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም ስፖርት የሚሰራ ሰው መጀመሪያ ጤናውን እየጠበቀ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ኪሳራ እንደሌለበት ማስገንዘብ ይገባል፡፡ በተለይ መገናኛ ብዙኃን እከሌ እከሌን አሸነፈ ብቻ ሳይሆን፤ የስፖርት መሰረታዊ ጥቅሞችንም በመዘገብ ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡ የባህል ስፖርት ዝንባሌውም የጠፋው ከስፖርቱ የሚገኘውን የጤና ጥቅም ካለመረዳት ነው፡፡ ከምንም በላይ የማንነት መገለጫና የአገር ክብር የሆኑ የራስን ባህላዊ ስፖርት መጠበቅ ታሪክ እንደመስራት ስለሚቆጠር በዚህ ልክ መረዳት ከሁሉም ባለ ድርሻ የሚጠበቅ ነው፡፡
ለባህል ውድድር ከቀረቡት ጥቂት ጨዋታዎች በተጨማሪ ሌሎችም ተካተው በውድድር ፌስቲቫሎች ውስጥ ሊካተቱ ይገባል፡፡ የባህል ስፖርቶች የሚካሄድ ባቸው የመወዳደሪያ ስፍራዎች ለዘመናዊ ስፖርት መወዳደሪያ የተዘጋጁ እንጂ ራሳቸውን ችለው ለባህል ስፖርት መወዳደሪያ የተሰሩ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ከመወዳደሪያ ስፍራ ጀምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን ከማግኘት አንጻር ውስንነት ስላለ ስፖርቶቹ እየተዳከሙ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህም ክዋኔዎች ላይም ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡ ስፖርቶቹ ከጠፉ በኋላ ከመፈለግ በቁመናቸው እያሉ መንከባከብ አቻ የሌለው አማራጭ ነው፡፡
ባህል ሲባል፤ ሙያዊ ጥበብ፣ ሙዚቃ ወይንም ማህበራዊ ልማዶች ብቻ አይደለም፡፡ በትርጉሙ ሠፊና ጥልቅ የሆነው የባህል እሳቤ በውስጡ አካቶ ከያዛቸው ጉዳዮች አንዱ የባህል ስፖርት ነው፡፡ በአገራችን ያሉት የባህል ስፖርቶች በተለያዩ ማህበራዊ ቡድኖች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የሚማማሩበት፣ የሚፈጥሩትና የሚለዋ ወጡት የባህሪና የእሣቤ መወራረስ የሚፈጥሩበት፣ የሚዝናኑበት አንዱን ከአንዱ በጉብዝና የሚለዩበት አይነተኛ ሚና አለው፡፡ ከዚህም ባሻገር ማህበረሰቦች በሚያከና ውኗቸው የባህል ስፖርት ጨዋታዎች የሥነምግባር መመሪያቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ የአምልኮ ሥርዓታቸውን፣ ሙያቸውን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራቸውን፣ የአለባበሣቸውን ሁኔታ፣ የምግብ አመራረታ ቸውንና አዘገጃጀታቸውን፣ የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት ሥርዓታቸውን ሁሉ ሊያንጸባርቁበት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› እንዲሉ ሳንቀደም የኛ የሆኑትን በመጠበቅም ሆነ ተንከባክቦ ለትውልድ በማስተላለፍ አሻራችን ማሳረፍ አለብን፡፡ የባህል ስፖርቶች ለዘመናዊ ስፖርት መሰረት ናቸውና ትኩረት ሊሰጣቸ ውም ይገባል፡፡ እነዚህ ባህላዊ ስፖርቶች የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከርም በላይ ለባህል እድገት እና መስፋፋት ከፍተኛ ትርጉም አላቸው፡፡
የባህል ስፖርቶችን ከጤና ለውጥና ሌሎች ፋይዳዎች ጋር በማስተሳሰር የተለያዩ የመስህብ ሀብት የሆኑና አደባባይ ያልወጡ ስፖርቶችን የማሳወቅ ተግባራት ሊከናወኑ ይገባል፡፡ የአገሪቷ ስፖርት ፖሊሲ ዋና የትኩረት አቅጣጫ ህዝባዊ መሰረት ያለው ስፖርት በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ በማስፋፋት እንደ ዘመናዊ የስፖርት ዓይነቶች ሁሉ ህብረተሰቡን በባህል ስፖርት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል የሚለው የዝግጅ ክፍላችን መልዕክት ነው፡፡

አዲሱ ገረመው

Published in ስፖርት

እድሜ ይስጠኝና ያለፈውን ለማውጋት ያብቃኝ እያልኩ እመኘው የነበረው ወቅት ደረሰ መሰለኝ ገና ከእንጭጭ እድሜዬ ሳልወጣ በትዝታ እቆዝም ጀምሬያለሁ፡፡ ግና የሚስቆዝመኝ ነገር በ70ኛዎቹና በ80ዎቹ የእድሜ ክልል ካሉ ሰዎች ጋር የሚያመሳስለኝ አይደለም፡፡ በእዚህ እድሜማ በርካቶች እንደሚያጋጥማቸው እንኳን የልጅነት ትዝታዎች ሊታወሱ ቀርተው ዛሬ የሰሩት ነገ አልበጅ እያለ የአብራክ ክፋይ እንኳ ሲዘነጋ ይታየል፡፡ እኔ ግን ማምሻም እድሜ ነች እንዲሉ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ሳይሆን ከሁለት አመታት በፊት የነበረውን ትውስታዬን ማውጋት በመቻሌ ነው እድሜ ይስጠኝ ያልኩት፡፡ ምስጋና ለፈጣሪ ቀጥሎም ለራሴ ይሁንና፡፡ መቼስ ከራስ በላይ ነፋስ አይደል ብሂሉ፡፡
እርግጥ ነው ሰው ኖሮ ሲያረጅ ትዝታ ይውጠዋል የሚለውን የአገሬን ብሂል አውቃለሁ፡፡ ምናልባት ሰው ሲያረጅ ሰውነቱ የሚዝለው ያለፈውን በማስታወስ እየደከመው ይሆን? ይመስለኛል፡፡ ብሂሉ ግን ለእኔ አይሰራም፤ አሊያም የአገልግሎት ዘመኑ አልፎበታል፡፡ ምክንያቱም እኔ ሳላረጅ ትዝታ ውስጥ መግባቴና በትዝታ ቁዘማ ሰውነቴ ዝለት ስላላጋጠመው ምስክርነቱ በቂ ይመስልኛል፡፡ እስኪ በትዝታ ፈረስ ወደኋላ ተመልሼ ከሶስት አመታት በፊት የነበረውን የዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ጥቂት ላስታውሳችሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲ አይደለም፤ ብዙ ልብንና ስሜትን የሚኮረኩሩ አሳዛኛና አስደሳች ትዝታዎች አይጠፉም፡፡
በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ የትዝታ ሽውታ ውስጥ ብዙ እያነበቡ ትንሽ ውጤት የሚያገኙ ተማሪዎች አንጀቴን ይበሉት ነበር፡፡ በቀን 18 ሰዓት ቢያነቡም የት እንደሚተንባቸው ባላውቅም ከሁሉም ያነሰ ውጤት ሲያመጡ እታዘብ ነበር፡፡ እንግዲህ እነዚህ ተማሪዎች ከሌሎች ልዩ የሚያደርጋቸው አንዳች ተአምር ካልተፈጠረ በቀር ቤተ መጽሐፍ ከመግባት የሚያግዳቸው ነገር አለመኖሩ ነው፡፡ ቤተ መጽሐፉ ዝግ ቢሆን እንኳን ሀኪም እንደ መድኃኒት ያዘዘላቸው ይመስል በሩ አጠገብ ሆነው ያነባሉ፡፡ እንዴውም እነርሱን ስመለከት ምናለ ተንቀሳቃሽ ቤተ መጽሀፍ ቢሰራላቸው፤ ሲፈልጉ ይዘውት የሚሄዱ ሲያሻቸው መጥተው የሚያንቀላፉበት እል ነበር፡፡ ገራሚው ነገር ጥብቅ ጓደኛቸው ቢሆንም ጠብ የሚል ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ሲያመጡ አይስተዋሉም፡፡ ታዲያ መተኛ ቢያደርጉት እንጂ የሚያጠና ሰው እንዴት ጥሩ ውጤት አያመጣም፡፡ ምን አለፋችሁ ሁልጊዜ ከቤተ መጽሐፍት አትጠፉም ብሎ አስተያየት ለሰጣቸው ሰው ‹‹በቤቴ ምን አገባህ›› የሚሉ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ቤተ መጽሐፍት ከሚያዘወትሩት ውስን የጤና ተማሪዎች መካከል በፓራሲታሞል ምስል የተሰራ የጆሮ ጌጥ የምታንጠለጥል ተማሪ የግቢያችን ልዩ መነጋገሪያ ነበረች፡፡
በሌላ መልኩ መጥፎ ትዝታ ሆኖ አእምሮዬ ውስጥ የተከተበው ደግሞ የተለያዩ ሴት ተማሪዎችን በውጤት የሚሸምቱ መምህራን ብልግና ነው፡፡ በጣም ያበሳጩኛል፡፡ ሀይማኖት ውስጥ መዋዠቅም ሌላው የወረርሽኝ ትውስታ ነው፡፡ አንዴ መነኩሴ አንዴ ምንትሴ የሆኑ የማይጨበጡ ሰዎችን ማለቴ ነው፡፡ ተማሪ ሲተኛ ጠብቀው የእንስሳት ድምፅ እያወጡ የሚረብሹ ልጆች እንዴት ያበግኑኝ እንደነበር፣ በቴሌቪዥን ቻናል አለመስማማት ማለትም ቀይረው ቀይረው የሚለው ድምፅ፤ የአለባበስ ሽግግር፣ የስም ቅያሪ ስንቱ ስም ተቀይሯል መሰላችሁ፡፡ ስምን መላክ ያወጣዋል እንዲሉ በየአመቱ ተመክሮ አድሮ ቃሪያ ለሆነ ተማሪ ማሙሽ ብለው ወላጆቹ ትክክለኛ ገላጫ ስም አውጥተውለት ወደ ግቢ ከመጣ በኋላ ማሙሸት እያሉ ጭራስ ራሱን ከእሸት ጋር የሚያነጻጽር አብግን ተማሪም ነበር፡፡
እየተገደዱ ሰልፍ መውጣት፣ እየተገደዱ መሰብሰብ፤ ሁሉም ነገር እብደት ነበር እኮ፡፡ የካፌ ግርግሩማ አይነገርም፡፡ ምናለ ምግቡም እንደዛው አስደሳች በሆነ ኖሮ፡፡ እኔ በነበርኩበት ግቢ በሳምንት ሶስት ቀን ስጋ ይበላል፡፡ ተረፈ ስጋ ብለው ይቀለኛል፡፡ በሬው ራሱ በምን እንደሚጋይ አይታወቅም ከስኳር ያነሰ ደቃቅ ቅንጥብጣቢ፡፡ ብቻ ተመስገን ማለት ይበጃል አትክልትም በሳምንት ሁለቴ እንበላለን፡፡ ዳሩ አትክልቱ ቃሪያ ብቻ ነበር እንጂ፡፡
ወይኔ ብዙ ጊዜ ካፌ ውስጥ ስንመገብ ከሚ ያስደነግጠንና ከበላን በኋላ በድንጋጤ የበላነው ከሆዳችን የሚጠፋበት አጋጣሚን የሚፈጥሩ ተምዘግዛጊ ወዳቂዎች እንዴት ይረሱኛል፡፡ እነዚህ ተምዘግዛጊ ወዳቂዎች እኮ በአንድ እጃቸው የተፈቀደላቸውን ምግብ በሌላ እጃቸው ማወራረጃ ሻይ ይዘው ቦታ ለመያዝ ሲሽቀዳደሙ የያዙትንም ወደ አፋቸው ሳይሉት መሬት ክዳቸው የሚወድቁት ናቸው፡፡ መቼስ አዳራሹ ለማንሸራተት ማን ብሎት ወዳቂዎቹ ጥቂት አልነበሩም፡፡ ይህስ ይሆን መሬት ይክዳል፤ አዕምሮ ሲክድ ነው የሚያሳዝነው አንብቦ እንዳላነበቡ መሆን አያድርስ አይደል፡፡
የምግብ ሰልፍ ላይ የካፌ አስተባባሪዎችን ካልቾ ከምግቡ አስቀድመው የሚቀምሱት፤ የድጌው አይነትስ ብትሉ አንድ ጊዜ በልቶ የማይጠግብ ተማሪ ሺምንተሸ ነው እኮ፡፡ ምልክት የተደረገበትን ቦታ ፍቀው ድጋሜ ምልክት ያስደርጋሉ፡፡ ሌላው ደግሞ በግ ተራ ነው፡፡ እዚህ ያለው የጾታዊ ንግግር ብዛቱ ምኑ ቅጡ፤ ከሁሉም መጥፎ ነገሮች ዘረኝነትን ሳስበው በቃ መፈጠሬን እጠላለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከብሄር በታችም የጠበበ ዘረኝነት ነበር፡፡ ደግሞ ለእረፍት የመኪናዎች ማስታወቂያ ላይ ሁሉም ከተሞች ውቢቷ ሲባሉ ግራ ነው የሚገ ባው፡፡ በእረፍት ወቅቶች የተማሪ መግቢያና መውጫ ጊዜያት ለመቼውም አይዘነጉኝም!...
አንዱ የዶርማችን ሀብታም ፍቅር ጠልፎት ‹‹ጭንቀቴን የሚጨነቅልኝ ሰው ቢኖር አንድ ሺህ ብር እሰጠው ነበር፡፡›› አለን ከእለታት በአንዱ ቀን፡፡ እኔ ደሀ ሆዬ እውነቱን መሰለኝና ‹‹መልካም መጨነቅ ጀምሬአለሁ አንድ ሺህ ብር ወዲህ በለው›› አልኩት፡፡ ሀብታሙ የልብስ አራዳም ‹‹እሱማ የመጀመሪያው ጭንቀትህ ነው፡፡›› አለኝና ድህነቴን የበለጠ ተሳለቀበት፡፡ ይህ ደግሞ ሀበታምና ድሀ ሆኖ በአንድ ዶርም ውስጥ ማደር በራሱ የሚያስከትለውን ትልቅ የሞራል ተጽእኖ ያሳየኝ ነበር፡፡
ትምህርቱ ያማረረው አንዱ ቦዘኔ ደግሞ ስልችት አለውና በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አሟሟት ለመፈጸም ወሰነ፡፡ (ሳያማክረን ማለት ነው) ምነው ቢያማክራችሁ ኖሮ ትፈቅዱለት ነበር? ትሉኝ ይሆናል እኮ፡፡ ኧረ ምን በወጣንና! መቼም በሞት አይቀለድም፡፡ እናም የመጨረሻው ደረጃ ሊደርስ ሲል ጓደኛችን እክፍሉ ሲገባ ሟች የገመድ ሸምቆቆ ወገቡ ላይ እንደታሰረ ቆሞ አገኘውና ‹‹ምን እያደረግክ ነው? ብሎ ጠየቀ፡፡ ለመሞት የሚታገለውም ‹‹ህይወቴን ላጠፋ ነው ብሎ መለሰለት፡፡›› ‹‹ታዲያ ገመዱ ወገብህ ላይ ምን ይሰራል? ብሎ ቢጠይቅ፤ ‹‹ታዲያ አንገቴ ላይማ አድርጌው ትንፋሽ ከለከለኝ እኮ›› ብሎ መመለሱ የቅርብ ትዝታ ነው፡፡
እኔ በተማርኩበት ዩኒቨርሲቲ ሀብታሞች ወፍራሞች ነበሩ፡፡ በዚያ ላይ ጠባያቸውም ጥሩ ነው፡፡ አንዱን ወፍራም ጓደኛዬን ‹‹ወፍራሞች ስትባሉ ለምንድነው ጠባየ መልካም የሆናችሁት?›› ስለው፤ ‹‹መደባደብም ሆነ ሮጦ ማምለጥ ስለማንችል ነዋ›› ያለኝ ጊዜም አይዘነጋኝም፡፡
በአንድ መኝታ ክፍል አብረውን ከሚኖሩ ሁለት ተማሪዎች መካከል አንዱ ልብሱን እያመሰቃቀለ ቁምሳጥኑን ፈተሸና ዞር ብሎ ጓደኛውን ‹‹ሸሚዜን የት አደረግከው›› ብሎ ጮኸበት፡፡ ‹‹ላውንደሪ ልኬዋለሁ፡፡›› አለው ሌላው ጓደኛችን፡፡ ‹‹ የፈጣሪ ያለህ እጅጌው ላይ የኢትዮጵያ ታሪክ እንዳለ ተጽፎበት ነበር እኮ፡፡›› አለው በድንጋጤ፡፡ ለካስ በንጋታው ፈተና ስለነበር አጤሬራ ይዞበት ኖሯል፡፡ በነገራችን ላይ የኩራጅ ስልቶችን አንገት የሚያስደፋውና ጥልቅ የሆነ ስልት ያለበት አጤሬራ ዘመን ተሻጋሪ እየሆነ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ መምህራን ፈተና በሚፈትኑበት ወቅት አጤሬራ አውጥቶ መስራት ያልቻለው አንዱ ተማሪ የመፈተኛ ወረቀቱን ባዶ በማግኘቱ ‹‹ምንድነው?›› ብሎ ቢጠይቀው ‹‹ዝምታ በራሱ ጥሩ መልስ ነው ብዬ ነው›› ብሎ መመለሱንም አስታውሳለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የእረፍት ቀናቶች በጣም አጭር ስለሚሆኑ ‹‹ሜድ ኢን ቻይና›› የሚል ተቀጽላም ይሰጣቸዋል፡፡

አዲሱ ገረመው

 

ሳምንቱ በታሪክ

 

የወጋየሁ ንጋቱ 74ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ
ተወዳጁን ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› የተረከው ዝነኛውና ተወዳጁ ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ የተወለደው ከዛሬ 74 ዓመታት በፊት (ግንቦት 28 ቀን 1936 ዓ.ም) ነበር፡፡
ወጋየሁ ከአባቱ ከአቶ ንጋቱ ብዙነህና ከእናቱ ከወ/ሮ አምሳለ በየነ ግንቦት 28 ቀን 1936 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለደ፡፡ ወጋየሁ እናቱና አባቱ ጋብቻ ከፈጸሙ በኋላ ልጅ ሳይወልዱ ቆይተው ስለነበር በስለት ያገኙት ልጅ እንደነበር ይነገራል፡፡ (‹‹ፍቅር እስከመቃብር›› ልብ ወለድ ላይ ያለው በዛብህም የስለት ልጅ መሆኑን ልብ በሉ)
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው በስዊድን ሚሲዮን ት/ቤት ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ነው፡፡ በት/ቤት ቆይታውም በርካታ ድራማዎችንና ሌሎች ኪነ-ጥበብ ስራዎችን እንደሰራና በት/ቤቱ ማኅበረሰብ ዘንድም ተወዳጅ እንደነበረ ታሪኩ ያስረዳል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በወቅቱ ‹‹ኪነ ጥበባዊ ትያትር›› ይባል ወደነበረው የአሁኑ ‹‹የባህል ማዕከል›› ገብቶ ከጓደኞቹ ከነአባተ መኩሪያ እና ደበበ እሸቱ ጋር እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ፡፡ የትወና፣ የዝግጅትና የፅህፈተ-ተውኔትን መሠረታዊ እውቀት ተምሮ ‹‹ሮሜዮና ጁሌት››፣ ‹‹ጠልፎ በኪሴ››፣ ‹‹የከርሞ ሰው››፣ ‹‹መድሃኒት ቀምሰዋል››፣ ‹‹ዳንዴው ጨቡዴ››፣ ‹‹የዋርካው ሥር ምኞት›› እና ‹‹ላቀችና ድስቷ›› በተባሉ የትርጉምና ወጥ ተውኔቶች ላይ አብይ ሚናዎችን ይዞ በመጫወቱ ተደናቂ ሆነ፡፡
በ1959 ዓ.ም. ከደበበ እሸቱ ጋር ወደ ሀንጋሪ ቡዳፔስት ተልኮ የሥነ-ተውኔት ሙያን ለሁለት ዓመታት አጥንቶ ተመለሰ፡፡ ከሀንጋሪ እንደተመለሰም በሬዲዮና በቴሌቪዥን አጫጭር ተውኔቶችን ማቅረብ ቀጠለ፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመልካች እንግዳ የሆኑ ‹‹አስማተኛው››፣ ‹‹ቁንጫ››፣ ‹‹ባሉን››፣ ‹‹ቀለም ቀቢው››፣ ‹‹የተዘጋ በር›› እና ሌሎች ተውኔቶችን እያቀረበ ተደናቂነትን አተረፈ።
ወደ ሐገር ፍቅር ትያትር ቤት ከተዛወረ በኋላም የትያትር ክፍሉ ኃላፊ፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይና እንዲሁም በሙያው ለመስራት የሚፈልጉ ወጣቶችን በማስተማር ሁለገብ አገልግሎት ሰጠ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ተዛወረና በመዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢነትና በዜና አንባቢነት ሲሰራ ቆየ፡፡ ብሔራዊ ትያትር ከገባ በኋላም ‹‹የበጋ ሌሊት ራዕይ››፣ ‹‹ትግላችን››፣ ‹‹ደመ መራራ››፣ ‹‹ደማችን››፣ ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››፣ ‹‹ሞረሽ››፣ ‹‹አፅም በየገፁ››፣ ‹‹ፀረ-ኰሎኒያሊስት››፣ ‹‹እናት ዓለም ጠኑ››፣ ‹‹የአዛውንቶች ክበብ››፣ ‹‹ዋናው ተቆጣጣሪ››፣ ‹‹ፍርዱን ለእናንተ››፣ ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት››፣ ‹‹ክራር ሲከር››፣ ‹‹ሀምሌት››፣ ‹‹ሊየር ነጋሲ››፣ ‹‹የድል አጥቢያ አርበኛ››፣_‹‹ዘርዓይ ደረስ››፣ ‹‹ገሞራው››፣ ‹‹አሉላ አባነጋ›› እና ‹‹እናት ነሽ›› በተሰኙ ስራዎች ላይ አብይ ሚናዎች እየወከለ ተጫውቷል፡፡
ወጋየሁ ከተውኔት አዘጋጅነቱና ተዋናይነቱ በተጨማሪ በመጽሐፍት ትረካዎቹ ይታወቃል፡፡ በተለይ ደግሞ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ የፃፉትን ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር››ን የተረከበት መንገድ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ለዚህም ደራሲው ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁም ‹‹ፍቅር እስከመቃብርን እኔ ጻፍኩት፤ ወጋየሁ ነፍስ ዘራበት፤ እኔ ከፃፍኩት ይልቅ አንተ በህዝቡ አዕምሮ የሳልከው ይበልጣል›› በማለት ለወጋየሁ የትረካ ብቃት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› በተጨማሪ የብርሃኑ ዘሪሁን ሶስት መፅሐፍት (ማዕበል የአብዮት ዋዜማ፣ ማዕበል የአብዮት መባቻ እና ማዕበል የአብዮት ማግስት) እንዲሁም የገበየሁ አየለ ‹‹ጣምራ ጦር›› ከተደራሲያን አዕምሮ የማይጠፉ ናቸው፡፡
ሰአሊ እሸቱ ጥሩነህ ‹‹መላ አካሉ ቋንቋው›› በሚል ርዕስ የወጋየሁ የሰውነት፣ የቁመት፣ የፊት፣ ቅርጽ ሁኔታ ላይ ጠለቅ ያለ ሂሳዊ ጽሁፍ አቅርበዋል። ታዋቂው ሀያሲ ስዩም ወልዴም ‹‹ገጸ ብዙ ጠቢብ›› ብሎ የወጋየሁን ሁለገብ የተዋናይነት ብቃት አብራርቶ ጽፈዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀይማኖት ዓለሙ ወጋየሁ ለመድረክ የተፈጠረ መሆኑን መስክረዋል። አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በበኩሉ ወጋየሁ ከእርሱ በኋላ ለሚመጡ ተዋናዮች እውቀቱን ለማካፈል ፍጹም የማይሳሳ እነደነበር ተናግሯል።
ወጋየሁ በ1966 ዓ.ም እንደፀረ-አብዮተኛ ተቆጥሮ ለጥቂት ጊዜያት ታስሮ ተፈትቷል፡፡ በ1977 ዓ.ም. ከባህል ሚኒስቴር ሠራተኞች መካከል ‹‹ምሥጉን ሠራተኛ›› ተብሎ ተሸልሟል፡፡ ወጋየሁ ወደመጨረሻው የህይወት ዘመኑ በግልፅ አውጥቶ በማይናገራቸው ጉዳዮች ይበሳጭ እንደነበርና አብዝቶ የመጠጣት ችግርም አጋጥሞት እንደነበር ይነገራል።_ በመጨረሻም ኅዳር 6 ቀን 1982 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡

አንተነህ ቸሬ

 

Published in መዝናኛ

አንድን ሀገር ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተፈላጊና ሳቢ ከሚያደርጉት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ መኖር አንዱ ነው፡፡ ምቹ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፍ ሲኖር ባለሃብቶች የተሰጣቸውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ምቹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ቢኖሩም እነርሱን ሊያስተገብር የሚችል አሰራር ካልሰፈነ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ በተለይም ከተንዛዛ አሰራርና ውጣ ውረድ (ቢሮክራሲ) የተላቀቀ ፈጣንና ቀልጣፋ የአሰራር ሥርዓት ካልተፈጠረ ባለሃብቶች በቀላሉ በመግባት ህልማቸውን እውን ለማድረግ ከመቸገራቸው ባሻገር ሀገሪቱ ከኢንቨስትመንቱ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ ያደርጋል፡፡
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለማልማት ፍላጎት ያላቸው በርካታ ባለሃብቶች ከሚያሰሙት እሮሮ መካከል በአሰልች አሰራሮች ምክንያት እንዲመላለሱ መገደድ፣ በቀላሉ ጉዳያቸው አለመፈጸምና ጉዳይ ለማስፈጸም እጅ መንሻ በተለያዩ አማራጮች መጠየቃቸው ባለሃብቶችን ቀርቦ ያነጋገረ ሰው ሊያደምጣቸው የሚችሉ ችግሮች ናቸው፡፡
በዚህ ረገድ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከኢሚግ ሬሽንና ከአየር መንገድ ጋር በመቀናጀት ኢንቨስተሮች ኤሌክትሮኒክስ ቪዛ የሚያገኙበትን አሰራር ቢዘረጋም ወደ ሀገሪቱ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ተጨማሪ ሊጠናቀቁ የሚችሉ ሥራዎችን ስለማያካትት በዘርፉ ዕድገት ላይ እንቅፋት መፍጠሩ አያጠያይቅም፡፡
ሌላው ተግዳሮት ፈቃድ ሰጪው አካል ለቀረበለት ማመልከቻ ቶሎ መልስ ካልሰጠበት፣ ግለጸኝነት የሚጎድለው ከሆነ እና ሰፊ የሆነ ፈቃደ- ስልጣን የሚስተዋል ከሆነ ለሌላ ብልሹ አሰራር ያጋልጣል፡፡ ይህም ባለ ጉዳዩ አቋራጭ መንገድ ለመጠቀም ስለሚገደድ ፈቃድ ለማግኘት መደለያ እና ማግባቢያ ገንዘብ ለጉዳይ አስፈጻሚያቸው ወይም ወኪሎች እንዲከፍሉ ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ ይህን ኢንቨስትመንቱን ከማቀጨጩ ባሻገር በሀገር ዕድገት ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖም ከባድ ይሆናል፡፡
በኢንቨስትመንት ዘርፉ ያሉትን ችግሮች የተረዱት የቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት አምስት ተማሪዎች ኢንቨስተሮች ካሉበት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሳያስፈልጋቸው አጠቃላይ የሥራ እቅዳቸውን ዝርዝርና ሌሎች አስፈላጊ መስፈርቶችን በማሟላት ምዝገባ ማድረግ የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ (ሶፍት ዌር) መስራት ችለዋል፡፡ ተማሪዎቹ አስተዳደራዊ ችግር ለማስቀረት በማሰብ በተለይም ለውጭ ኢንቨስተሮች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመውሰድ የሚያደርጉዋቸውን ውጣ ውረዶች ለመቀነስ በማሰብና ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መተግበሪያውን እንደፈጠሩት ያስረዳሉ፡፡
«በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪነት ችግር ሊፈታ የሚችል መተግበሪያ (ሶፍትዌር) መስራት ቀርቶ ኮምፒዩተር መክፈትና መዝጋት እንደ ትልቅ ይታይ ነበር፡፡ በልዩ ሁኔታ ትምህርቱን ስንጀምረው መተግበሪያ እንሰራለን የሚል እምነት አልነበረንም፡፡ ሆኖም የአደጉ ሀገር ተማሪዎች እንደሚሰሩት እኛም ችግር ፈች የሆነ መተግበሪያ መስራት ችለናል፡፡ ችግሮችን እንደ ዕድል ተጠቅመን መስራታችን ትልቅ ውጤት ነው፡፡» ሲሉም ይናገራሉ፡፡
በቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ረቂቅ ታደሰ «ኢትዮ-ኢንቨስት የሚል መተግበሪያ ለመስራት ያነሳሳን በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል በማሰብ ነው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ባጠናነው ጥናት መሰረት ብዙ ወጪዎችን አውጥተው፣ ጊዜያቸውን አባክነው ወደ ሀገሪቱ ከመጡ በኋላ ኢንቨስተሮችን ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል የሥራ እቅዳቸውን ለማቅረብ ወደ ባለስልጣኑ መመላለስ አንዱ ነው፡፡ ይህን ችግር በምን መልኩ መታደግ አለብን የሚለውን ተመካክረው ባሉበት ቦታ ሆነው ምዝገባ እንዲያካሂዱ፣ የሥራ እቅዳቸውን እንዲያቀርቡና ተቀባይነቱ ተረጋግጦ እንዲመጡ ለማድረግ በቀላሉ ሞባይል መተግበሪያው መስራት ይቻላል ወደሚል ሃሳብ በመድረስ መስራት ችለናል» ትላለች፡፡
እንደ ታዳጊ ሀገር በኢንቨስትመንት ዘርፍ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች አንድ በአንድ ይፈቱ ቢባል ረጅም ጊዜ ከመውሰዱ ባሻገር አሰልቺም ይሆናል፡፡ ዘርፉ በግለሰቦች ይሁንታ ላይ ጭምር የተመሰረተና ወደ ባለስልጣኑ የሚሄዱ ሰዎች ገንዘብ ያላቸው እንደመሆኑ ለሙስናም የተጋለጠ ነው የምትለው ተማሪ ረቂቅ፤ ሁሉንም ችግሮች በተናጠል ለመፍታት ጊዜ ከመውሰዱ ባሻገር አሰልቺም ስለሚሆን ችግሩን በዘመናዊና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከሰዎች ንክኪ ነጻ በሆነ አሰራር መፍታት ተገቢ ነው፡፡ ሙስናን ከመቀነስ አኳያ ሰዎች ባለሃብቶችን በአካል እንዳያገኙ ስለሚያደርግ በተወሰነ ደረጃ ያግዛል፡፡ እንዲሁም የባለስልጣኑን ሥራ የሚያቀላጥፍ ነው ስትል ታስረዳለች፡፡
እንደ ተማሪ ረቂቅ ገለጻ፤ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በመሄድ ባጠናነው ጥናት በርካታ ኢንቨስተሮች አጠቃላይ መረጃ ሳይኖራቸው የሚመጡበት ሁኔታ አለ፡፡ በአንድ ዘርፍ ለመሰማራት ከመጡም አማካሪዎችን ሳይቀበሉ የመጡበትን ዘርፍ ብቻ የመፈለግና ከአዋጭነት አኳያ የማይመዝኑበት ሁኔታ መኖሩን ተረድተናል፡፡ ያነጋገርናቸው ኢንቨስተሮች ደግሞ የሞባይል መተግበሪያ ቢሰራላቸው ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀልላቸው የገለጹበት ሁኔታም አለ፡፡ መተግበሪያውን አጠናቅቀን የምንገኝ በመሆኑ ቀሪው ከኢንቨስተሮችና ባለስልጣኑ ጋር መደራደርና ወደ ሥራ ማስገባት ነው፡፡
ተማሪ ረቂቅ እንደምትለው፤ የሞባይል መተ ግበሪያው ሦስት የአጠቃቀም መንገዶች አሉት፡፡ መጀመሪያ አጠቃላይ ስለ ኢንቨስትመንት ባለስልጣን ያለውን አሰራር፣ ምን መስፈርቶችን መሟላት እንደሚገባው ተገቢ መረጃ እንዲያገኝ በማድረግ በመተግበሪያው ላይ የራሱ የሆነ መጠቀሚያ (ዩዘር) በመክፈት ቀጥታ ለኢንቨስትመንት ባለስልጣኑ የሚፈልገውን በመላክ ባለበት ቦታ ጉዳዩን ማስጨረስ ይችላል፡፡ በኢንቨስትመንት ባለስልጣን ያሉ አማካሪዎች ደግሞ በቀጥታ መስመር (ኦንላይን) አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርጉለት ይሆናል፡፡ አጠቃላይ ማሰማራት ስለሚፈልግበት ዘርፍና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያሉ አማራጮችን፣ ጠቀሜታቸውንና አዋጭነታቸውን ተገቢውን የምክር አገልግሎት መስጠት እንዲችሉም ያደርጋል፡፡ በዚህም አማካኝነት ኢንቨስተሩ መሬት እስኪሰጠው ድረስ ያለውን ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ፣ መሬት ከተዘጋጀለት በኋላ እንዲመጣ ማድረግ ያስችላል፡፡
ለተማሪዎቹ ድጋፍ ሲያደርግላቸው የነበረው በሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የኢንፎርሜሽን ሳይንስ ተማሪ ሳሙኤል በሽር፤ ኢትዮ ኢንቨስትመንት የሚለውን መተግበሪያ ካሰቡ በኋላ በዋናነት ኢንቨስተሮች ወደ ሀገሪቱ ሲመጡ የሚገጥማቸውን ችግር ማጥናት ነበር፡፡ ችግሮቹ በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል ብዙ ጊዜ አንድ ኢንቨስተር አጠቃላይ የኢንቨስትመንት መረጃዎችን የሚያገኘው ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን የሚያባክኑበት ሁኔታ ሲፈጥር ይስተዋላል፡፡ ይህን ችግር ለመቀነስ አንድ ኢንቨስተር ወደ ኢትዮጵያ ሳይመጣ አጠቃላይ በሀገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት መረጃዎችን በሞባይሉ በማግኘት የሚፈልገውን ዘርፍ ባለበት ቦታ እንዲወስንና ካለ ውጣ ውረድ እንዲመዘገብ ያስችላል ሲል ያብራራል፡፡
ተማሪ ሜላት ደቻሳ በበኩሏ፤ በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ተማሪዎች ኮምፒዩተር ሳይንስ መማር የሚጀምሩት ዘግይተውና ሁለተኛ ደረጃ ላይ በመሆኑ አዕምሯቸውን እንዳይጠቀሙ እየሆኑ ነው፡፡ በአደጉ ሀገሮች ዜጎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገቡ የህብረተሰቡን ችግር በማጥናት ችግር ፈች ቴክኖሎጂ ሲፈጥሩ ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ወደ እኛ ሀገር መምጣት አለበት፡፡ ከቴክኖሎጂ ጋር መተዋወቅ ያለብን ከልጅነት ጀምሮ መሆን አለበት ትላለች፡፡
እንደ ተማሪ ሜላት ገለጻ፤ ተማሪዎች የልጅነት አዕምሯቸውን በመጠቀም ችግር ፈች ፈጠራ ሊሰሩ ዘንድ ሊበረታቱ ያስፈልጋል፡፡ የኮምፒዩተር ትምህርት ከታች ክፍል ጀምሮ የሚሰጥበት ሁኔታ ቢመቻችና ህጻናት ከቴክኖሎጂ ጋር ጥብቅ ትስስር ፈጥረው ቢያድጉ አዲስ ነገር ለመፍጠር ይረዳቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተማሪዎች እየተሰሩ የሚገኙ መተግበሪያዎች ማሳያ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲ ካልተገባ መተግበሪያ (ሶፍትዌር) መሥራት አይታሰብም ነበር፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የሚካሄድ የንግድ ልውውጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንደመሆኑ ይህን ወደ ሀገሪቱ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ቴክኖሎጂን መጠቀም ወደ ግዴታ እየሄደ ያለበት ሁኔታ ይስተዋላል፤ ይህም ከታች ክፍል ጀምሮ በልጆች ላይ መስራት እንደሚገባ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው «በአሁኑ ወቅት የሀገራት ሀብት በቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ላይ ሲወሰን እየተስተዋለ ነው፡፡ ምንም ያህል ሃብት ቢኖር ቴክኖሎጂን ማሳደግና በቴክኖሎጂ መደገፍ ካልተቻለ የሚፈለገውን ዕድገት ማምጣት አያስችልም፡፡ በሀገሪቱ ያለውን ኢንቨስትመንት ከማገዝ አኳያ የልጆች ሥራ አበረታች በመሆኑ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚጠቀሙበት ሰርቨር ፈቅዶላቸዋል» በማለት ሚኒስቴሩ ለቴክኖሎጂ የሚሰጠውን ድጋፍ አረጋግጠዋል፡፡
ተማሪዎቹ ‹‹ሰርቨር እናገኛለን ብለን ባንጠብቅም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሰርቨር እንድንጠቀም ውሳኔ መስጠቱ የበለጠ እንድንሰራና እንድንበረታታ አድርጎናል፡፡ ሰርቨሩ የሚያስፈልግበት ምክንያት መረጃዎች የሚቀመጡት በዳታቤዝ በመሆኑና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለማደስ (አፕዴት) ለማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ሊፈቀድ ችሏል፡፡ ኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ ሥራውን ለማቅለል ጥረት እያደረግን በመሆኑ ሊያበረታታን ይገባል፡፡ ኢንቨስተሮች ሞባይል መተግበሪያውን እንዲጠቀሙ እንዲያስተባብርና ከእኛ ጋር እንዲሰራ እንፈልጋለን» ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ዑመር እንድሪስ

Published in ማህበራዊ

"ኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው" በሚል ርዕስ ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም አንድ አስተያየት አዘል መጣጥፍ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ማስነበቤ ይታወሳል፡፡ በርካታ አንባቢያን አዎንታዊ አስተያየቶችን በመስጠት ሰፋ አድርጌ እንዳቀርብ ስላበረታቱኝ ቀጣይ ጽሑፍ አዘጋጀሁ፡፡
ስለ ኢትዮጵያዊነት ኃይልነት፣ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ክቡርነት፣ ስለ ኢትዮጵያችን ድንቅ ሀገርነት ብዙ ተብሏል፤ ብዙም ተጽፏል፡፡ በታሪክ ፀኃፊዎች መነጽር ወደፊትም በርካታ መልካምና አስተማሪ ጭብጦችን ለእኛም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ ሊጽፉ እንደሚችሉም እርግጠኛ ነኝ፡፡
ስለ ኢትዮጵያዊነት ውበት፣ ስለ ኢትዮጵያ ቀደምት የታሪክ ባለቤትነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ብዝኃነት በሀገር ውስጥ ሆነን ብዙም ላይሰማን፣ ትርጉም ላንሰጥ እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀገር ማለት የደም ስርን ዋኝቶና አጥንትን ሰርስሮ የሚገባ ኃያል የፍቅር ማዕበል ነው፡፡ የህይወት ስንቅ ነው፡፡
ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ፈልገንም ሆነ ሳንፈልግ በፖለቲካ አመለካከት ሳቢያ ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ "ሁኔታዎች" ሲከሰቱ አንዳንዶቻችን በፍጥነት ለሁላችንም በማይጠቅም ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ወደዚያ ሜዳ የሚያደርሱ አስገዳጅ ምክንያቶች ቢኖሩም ሀገራዊ ሁኔታው ሰላማችንና ልማታችንን የሚያደናቅፍ እንዳይሆን ሰከን ብሎ ማሰቡ ያስፈልጋል፡፡ ነገ ልንደርስ ያሰብንበት የጋራ ግብ ዋጋው ትልቅ መሆኑን እንዘነጋለን፡፡ ግቡም ሁሉንም ዜጋ የሚጠቅም መሆኑን እንረሳለን፡፡
ሀገር የመውደድ ስሜት ከሌሎች አመለካከቶች ሁሉ ይለያል፡፡ ሀገራዊ ስሜት ከፖለቲካዊ ስሜት የገዘፈ ነው፡፡ በፖለቲካዊ አመለካከቶች ዙሪያ ልዩነቶች መኖራቸው ምን ጊዜም አይቀሬ ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነት የሌለው ሀገርና ህዝብ መውጫና መግቢያ የሌለው የረጋ ውኃ ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶች ወደተካረረ የእርስ በርስ ግጭቶች ከመድረሳቸው በፊት እልህ አስጨራሽ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶች መደረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ውይይቶች ሲካሄዱ የይስሙላ ሳይሆኑ ልባዊና በሀገራዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባትን የሚፈጥር ኃይል ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ እየተሻሻለ የሚሄድ ጉዞ ሳይሆን እየተሸራረፈ የሚደናቀፍ መንገድ ይሆናል፡፡
ስልጣን የያዘው ኃይልም ሆነ ለስልጣን ትግል የሚያደርጉ አካላት ሀገር የጋራ መሆኑን በሚገባ መገንዘባቸው የጋራ ጠቀሜታ አለው፡፡ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማመንም አለባቸው፡፡ ማመን ብቻ ሳይሆን ወደ መሬት ማውረድ አለባቸው፡፡ ስልጣን የያዘው አካል በስልጣን ዘመኑ ህዝብ የሚወደውና ህዝባዊ ከበሬታ የሚያገኝበትን ልማት ከሰራ በህዝብ ዘንድ በባለውለታነቱ ዘወትር እንደተወደሰ ይኖራል፡፡ ታሪካዊ ኃላፊነቱን በታሪካዊ ወቅት ሳይጫወት ዘመኑ ካለፈበት ደግሞ የታሪክ ተወቃሽ ይሆናል፡፡ ታሪካዊ ተወቃሽ እንዳይሆን የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍና ምክር የሚፈልግ እንጂ ስልጣንን መጠቀሚያ አድርጎ ዛፍ ላይ የተንጠለጠለና የማይወርድ የሚመስል መሆን አይጠበቅበትም፡፡
ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት ለህዝቡ የገቡትን ቃል ማክበር አለባቸው፡፡ ማክበር ባይችሉ ደግሞ ምክንያቱ ለህዝብ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ማለት በአጭሩ ይህ ነው፡፡ ያለፉ ስርዓቶች ደካማ ጎኖች እንደ ከበሮ እያስጮሁና ያለአግባብ ስልጣን ላይ ያለውን አካል እንደ እንቧይ ካብ እየካብን መኖር (መካብ በሚገባን ቦታ መካብ እንዳለ ሆኖ) ይቅርብን፡፡ ካቡ በፈረሰ ጊዜ የራሱ ጉዳይ ማለት ይመጣል፡፡ የራሱ ጉዳይ ማለት ብቻ ሳይሆን አብሮ መናድም አለና፡፡
እንደ ሌሎች ሀገሮች ሁሉ በሀገራችንም በርካታ መንግስታትና የመንግስታት መሪዎች ስልጣን ላይ ወጥተዋል፡፡ እነዚህ መንግስታትም ሆኑ መሪዎች በዘመናቸው የየራሳቸው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ አሻራዎች አሏቸው፡፡ ብዙዎቻችን ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ አሻራዎችን አግዝፈን በማየት ገንቢ ላልሆኑ ትችቶች ብሎም መበቃቀል ወደሚያደርሱ ድርጊቶች ቶሎ እንጋበዛለን፡፡ የሁሉንም ሀገር መሪዎች የአመራር ዘመን ስንመለከት ከላይ ከተጠቀሱት ድርጊቶች በአንዱ ወይም በሁለቱ ታጅበው ያለፉና ያሉም እንዳሉ በተጨባጭ እንገነዘባለን፡፡ አንድ ታሪካዊ ክንዋኔ አልፎ ሁለተኛው ቦታውን ሲረከብ ሰላማዊ መሆኑን ብዙዎች የሚደግፉት ሲሆን፣ ከሰላማዊ መንገድ ውጪ የሚመጡ ለውጦች ሁሉ ውጤታቸው ይብዛም ይነስ ጉዳት አላቸውና ጠንቀቅ ያሻል፡፡ አስከፊና አስነዋሪ የታሪክ ጠባሳ ጥለው ያልፉና የሚቀጥለውን ትውልድ እርስ በርስ ያነታርካሉ፣ ያቆስላሉ፣ ያፋጃሉ፡፡ እንደ ተላላፊ በሽታ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ ቀብረው ይሄዳሉ፡፡ አብሮ እየኖረ ያለውንና ወደፊትም አብሮ የሚኖረውን ህዝብና የሁሉም እናት የሆነችውን ወርቃማ ሀገር ለትርምስ ያበቃሉ፡፡
ስለ ኢትዮጵያችን ከጥንት ጀምሮ ይነገሩ ከነበሩና ከተጻፉ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ጥቂቶቹን ብቻ ለግንዛቤ ብናነሳ ሀገራችን የምትታወቀው በምስራቅ አፍሪካ የውኃ ፏፏቴነት፣ የዳቦ ቅርጫትነት፣ ለጥቁሮችና በቅኝ ግዛት ስር ሲማቅቁ ለነበሩ የዓለም ህዝቦች የአሸናፊነትና የአይበገሬነት አርአያ፣ ከቅኝ ተገዥነትና ከባርነት ለመላቀቅ መራር ትግል ለሚያደርጉ ጭቁን ህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት ያስከፈለ ድጋፍ ሆናለች፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሳትነካ ሊነካኩ የመጡባትን የዘመናት ጠላቶች አምበርክካና አሳፍራ የመለሰች ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር መሆን ነው፡፡ የጦረኝነትን ታሪክ ሳንረሳ ማለት ነው፡፡ ይህ የጦረኝነት ታሪክ ወደ ድህነት ውጊያ ሜዳ በዘላቂነትና በአስተማማኝነት መቀየር አለበት፡፡
ስለ ኢትዮጵያችን በውጭ ሀገር ድርሳናትና ቋንቋዎች የተሰጡ ትርጉሞችን በአጭሩ ስንመለከትም "ፊታቸው የተቃጠሉ ህዝቦች የሚኖሩባት ሀገር (ራሺያዎች፣ ግሪኮችም ይህንኑ ትርጉም ይጋራሉ)፣ ሐሐሐሀሐሀሀሀሀበበበሐሀበሻ (ዐረቦች)፣ ኤይቶጵያ (ግሪኮች)፣ አብሲኒያ (አብሲኒያ የሚለው ስያሜ መነሻው የት እንደሆነ አይታወቅም/አከራካሪ ነው የሚሉ ጸሀፊዎች እንዳሉ ሆኖ አንዳንዶቹ ትርጉሙን ድብልቅ ህዝቦች የሚኖሩባት ሀገር ይላሉ)፣ አትያብ (በዐረብኛ ቅመሞች፣ሽቶዎች እንደ ማለት ነው)፣ በተራራ ላይ የሚኖሩ ህዝቦች የሚሉ ትርጉሞች እንዳሉ ሆኖ ለማንኛውም ግን አጠራሩ ከዓረብ ባህረ ሰላጤ እስከ አፍሪካ ቀንድ ድረስ ያሉ አከባቢዎችን የሚያካልል እንደነበረ እንገነዘባለን፡፡ ዓረቦቹ እንዳሉት በእርግጥም ቅመሞችና ሽቶዎች ነን፡፡
እነዚህን መንደርደሪያዎች ለክፍል ሁለት ጽሑፌ የተጠቀምኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ከተሰጡት ትርጉሞች መካከል በአንዱ በተለይም ጥቁር ህዝቦች የሚኖሩበት ወይም ፊታቸው የተቃጠሉ ህዝቦች የሚኖሩባት ሀገር በሚለው ላይ አጭር "ማብራሪያ" መስጠት ፈልጌ ነው፡፡ አንባቢዎቼ ፊታቸው የተቃጠሉ ህዝቦች ማለት ጥቁሮች የሚኖሩበት ለማለት እንደሆነ ቢታወቅም ይህ ትርጉም በተሰጠበት ዘመን በአፍሪካ ወይም በሌላ ዓለም ጥቁር ህዝቦች ስለመኖራቸው የሚያውቁ ነጮች ወይም ሌሎች ህዝቦች መኖራቸውን ጥርጣሬ ኣሳደረብኝ፡፡ ጥቁር ውበት ነው፣ ይህ ውበትና ቁንጅና ደግሞ የእኛ የኢትዮጵያውያን መለያ መሆኑ ከማንም ከምንም በላይ እኛኑ ኢትዮጵያውያንን ያኮራናል፣ ያስደስተናል፣ እያኮራንና እያስደሰተንም እንኖራለን፡፡
ከላይ የተገለጹት ሀገሮች በየቋንቋቸው ወይም በስነልሳኖቻቸው ህዝባችንን ወይም ሀገራችንን ጥቁሮች ወይም ፊታቸው የተቃጠለ ህዝቦች የሚኖሩበት ሀገር ያሉት ያለ ምክንያት አይመስለኝም፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ይጋራሉ ብዬ በማስበው እይታዬ ኢትዮጵያውያን በእርግጥም ጥቁሮች ነን፡፡ ያውም የውበት ህብረ ቀለም ያለን ህዝቦች፡፡ በዚህም ጥቁርነታችን እንኮራለን፡፡ እንመካለንም፡፡ ለዚህ ትርጉም ያነሳሳቸው የሚመስለኝ እኛ ኢትዮጵያውን ስንታወቅ ሌሎች ጥቁር ህዝቦች አይታወቁም ነበር ማለት አያስችለንም ይሆን? እኛ ከውጭው ዓለም ጋር ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ስንመሠርት ሌሎቹ ጥቁሮች በቅኝ ግዛት ስር ስለነበሩ ይህ ይፋዊ ግንኙነት አልነበራቸውም፡፡ ዛሬም ቢሆን የኛን ያህል የዚህ ዓይነቱ ግንኙነት የሌላቸው አሉ፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያዊነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ አፍሪካዊና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ማዕከል ሆና መቆየቷ ነው፡፡ ለአፍሪካ አንድነትና ነጻነት በኢትዮጵያዊነት ስሜት በቁርጠኝነት በመስራታችን ነው፡፡ ነገም ወደፊትም ኢትዮጵያዊ ባህላችንን የጠበቀ መስተንግዷችንና ዲፕሎማሲያዊ ጥረታችንን አጠናክረን ከቀጠልን ይህ ከኒውዮርክና ጄኔቫ ቀጥሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሶስተኛ እንደሆነ የሚጠቀሰው አገልግሎታችን ክብሩን እንደጠበቀ ይዘልቃል፡፡ ለማንኛውም ግን ኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው ወደሚለው ርዕሴ እንዲመለስ ይፈቀድልኝ፡፡
እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚመስለኝን አስተያየት ሳቀርብ ከብዙዎቹ ኢትየጵውያን የተለየ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ኖሮኝ ባይሆንም ወይም ስለሌሎቹ መናገር ግዴታ ባይሆንብኝም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንድን አስተሳስብ አጉልቶ አንዱን አሳንሶ ለማሳየት ብሎም ለማደብዘዝ ለዓመታት ሲሰሩ የነበሩ አስተሳሰቦችን ትተን ለሀገራችን ልዕልናና ከፍታ ስንል ወደ አንድ የሰገነት ጫፍ ማድረስ የጋራ ግዴታችን ይመስለኛል፡፡
ወደ ሰገነት ጫፍ ማድረስ ይገባል ሲባል ወደ ጫፍ በማድረሱ ሂደት በኢትዮጵያችን ምንም ዓይነት የሚዳሰሱ ተግባራት አልተሰሩም የሚል ጨለምተኛ አስተሳሰብ የለብኝም፡፡ ወደፊትም አይኖርብኝም፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ መሰንዘር መነሻ የሆኑኝ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህን አስተሳሰቦች ደግሞ በእኔ አዕምሮ አግዝፌ አሳይቼ በሌሎች ይህንኑ ለማራገፍ አይደለም፡፡ ይህንን የሚለው በተለያዩ አከባቢዎች ስሜታዊ መገለጫዎች እየተንጸባረቁ የሚታዩበትን ሁኔታ ስለማስተውል ነው፡፡ እንደ ቀድሞው ሁሉ ኢትዮጵያዊነት ኃይል ሆኖ መቀጠል አለበት እላለሁ፡፡ የማይስማማ አስተሳሰብ ካለም እንወያይ፡፡
ዶ/ር አብይ ሁልጊዜ ስማቸውን ሲያወድሱ የምሰማቸው የህንዳውያን አባት ማህተመ ጋንዲ፤ ከተናገሯቸው አብነቶች አንዱ "አንድ ዓይን ከጠፋ ሌላውን ዓይን ማጥፋት ብቻ መላው ዓለምን እውር ያደርጋል" የሚለው አባባላቸው ነው፡፡ ማህተመ ጋንዲ አክለውም " ከበቀል/ቅጣት ይልቅ ይቅርታ መደራረግ ሰዋዊነት ነው" ይላሉ፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግም "ለፍቅር ጥንካሬ" በሚለው ጽሁፉ ይቅርታ የመደራረግን አስፈላጊነትን አጉልቶ ሲያሳይ " ይቅርታ መደራረግ ወደ አዲስ መሻሻልና አዲስ ጅማሮ ያበቃል፣ ይቅር መባባል የአንድ ወቅት ተግባር ሳይሆን የዘወትር ባህል ሊሆን ይገባል" ብሏል፡፡ ታዋቂው የደቡብ አፍሪካ ጳጳስ ዴዝመንድ ቱቱ በበኩላቸው እ.አ.አ በ1999 ለህዝባቸው ባደረጉት ንግግር "ያለ ይቅርታ መደራረግ ይቅርታ የለም" ብለዋል፡፡
ይቅርታ መደራረግ ራስን (መንግስት ቢሆን) ነጻ ለማውጣትም ሆነ ከአዕምሮ እስረኝነት ለማውጣት ፍቱን መዲኃኒት ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለሌሎች የዓለም ህዝቦች ሞዴል የሆነችው ከማንዴላ እስር መፈታት በኋላ ከአምስት መቶ ዓመታት በላይ ሲያስሩ፣ ሲገድሉ፣ ሲጨቁኑና ሌሎችን ሰብዓዊ ጥሰቶች ሲፈጽሙባቸው ለነበሩ ነጮች ልባዊ ይቅርታ በማድረግ ነው፡፡ በወቅቱ የማንዴላን የይቅርታ አስተሳሰብ የተቀበሉት ጥቁሮች ብቻ አልነበሩም፡፡ አስተሳሰቡን የተቀበሉት ጥቁሮችም ሆኑ ነጮች ዝናና ክብር አግኝተዋል፡፡ ጥቁሮቹ ነጮቹን እንበቀል ካሉ ሁለቱም ወገኖች መጨረሻቸው ወዴት እንደሚያደርስ በደንብ ተወያይተዋል፡፡ ተማምነዋል፡፡ በዚህም ቅሬታዎችንና ቂም በቀሎችን በመተው ወንድማማችነትና ሰብዓዊነትን ማስታረቅ ችለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቁሮች የተሟላ የኢኮኖሚ የበላይነት ባይኖራቸውም የፖለቲካ የበላይነት አላቸው፡፡ የፖለቲካ የበላይነት ብቻውን መፍትሄ ባይሆንም "በስልጣናቸው" ለሀገራዊ ጉዳይ እጅ የመጠምዘዝ አቅም አግኝተዋል፡፡ እነሆ በሰላምና በመቻቻል እየኖሩ ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውን ከጥንት ጀምሮ ከሚያለያየን ይልቅ የሚያመሳስለን፣ ከጠላትነት ይልቅ ቤተሰባዊነትና ወዳጅነት፣ ከስጋት ይልቅ አብሮነታችን፣ በዚህም ሆነ በዚያ የሚያከባብረንና የሚያዋድደን ታሪክ እንጂ በጠላትነት የምንፈራረጅበት ታሪክ የለንም፡፡ እነዚህ መልካም ባህሎችና የመልካም ህዝቦች እሴቶች ጎልተው መውጣት አለባቸው፡፡ የኛን መልካም ነገራችንን ለሌላው የዓለም ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለልጅና ለልጅ ልጆቻችን ካላሳየን ማን ሊመጣልን ነው፡፡
ሀገራችን የበለጠ ተሰሚነት ያላትና ያደገች እንድትሆን እያንዳንዳችን ኃላፊነት አለብን፡፡ የተበታተነች ሀገርና የተበታተንን ህዝቦች እንዳንሆን ነቅተን ዘብ መቆም አለብን፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻልን የዛሬው ዓለም ሰላም እንደ ብርጭቆ ተሰባሪ መሆኑን ለራሳችን ስንል ማወቅ አለብን፡፡ ይህንን ማድረግ በአንድ በኩል ሀገሩን የሚወድና የሚጠብቅ ትውልድ መፍጠር ሲሆን በሌላ በኩል አንድነታችን በቀላሉ የማይናወጥ ህዝብ መሆናችንን ለዓለም በተለይም ደግሞ ከጥንት ጀምሮ የኛን መውደቅ ለሚመኙ ወገኖች ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የሀገሩን ታሪክ የሚያውቅና የሚንከባከብ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡
ሀገራችን የጀመረችው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስለ ጦር ጀግንነት አያወራም፡፡ አንገታችንን እያስደፋ ያለውን ድህነት እንድንዋጋ ለመላ ህዝባችን ሀገራዊ ጥሪ ተደርጎልናል፡፡ እርስ በርስ አሸናፊና ተሸናፊ በመባባል ከምንሸነጋገል የልማት አርበኛ ለመሆን እንሽቀዳደም፡፡ እያስመዘገብን ያለው ውጤት ለዚህ የሚያበቃን ስለመሆኑ እርግጠኛ እንሁን፡፡ ከዚህ የበለጠ ማደግ የሚያስችል አቅም እየፈጠርን ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የምንችለው በጉልበት ስንመካ ሳይሆን በአዕምሮ እያሰብንና ቴክኖሎጂ እየተጠቀምን ስንሰራ ነው፡፡ ድሮም ቢሆን የሀብት ድህነት እንጂ የአዕምሮ ድህነት እንዳልነበረብን እናውቅ የለ? የሀብት ድህነትን ጠንክረን በመስራት ልንሻገር እንችላለን፡፡ የተሻለ ለመማርና በተሻለ ቦታ ለመስራት በውጭ ሀገራት ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያውያን ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ስንገነዘብ ሀገራችንን ወደ ቀድሞ ገናና ክብሯ መመለስ አያስችለንም? ያንን ድንቅ ክብርና ሞገስ ያቆዩልን በሁሉም ኢትዮጵያ የነበሩ ጀግና አባቶቻችን ናቸው፡፡ በተናጥል የሚወደስና አንሶ የሚታይ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ይህ ሀቅ መሆኑን አንዱን አሳንሰው ሌላውን ደግሞ ላቅ አድርገው የሚያዩ አካላት መገንዘብ አለባቸው፡፡ ሰላም ለኛም ለሀገራችንም ይሁን፡፡

ከወልደ አማኑኤል ጉድሶ (ሀዋሳ)

Published in ፖለቲካ

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ፕሮግራም የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች አጠቃላይ አፈፃፀም ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ሰሞኑን ከከተማዋ የተውጣጡ ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎችና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአቃቂ ቃሊቲ፣ቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኙትን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅትም በየሳይቶቹ ያሉ ቤቶች የግንባታ ሂደት፣ ፈታኝ ጉዳዮችና ተስፋ ሰጪ አሰራሮች ተቃኝቷል፡፡እንዲሁም ለግንባታው መጓተት ምክንያት በሆኑት ላይ የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት የተገለፁ አንኳር ነጥቦች እነሆ!
የግንባታዎቹ ሂደት
የአቃቂ ቃሊቲ ቤቶች ግንባታ ቅርንጫፍ ጽህፈት ሥራ አስኪያጅ አቶ ንጉሴ ፀጋዬ እንደገለፁት፤ ግንባታው በ2006 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የተጀመረው እና በአቃቂ ክፍለ ከተማ ስር የሚገኘው ኮዬ ፈጬ ሳይት አንዱ ሲሆን ሰባት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በስሩ ይገኛሉ፡፡ግንባታውም በ960 ሄክታር ላይ በመገንባት ላይ ሲሆን፤20/80 ግንባታዎችንም ያካተተ ነው፡፡ ግንባታው በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እየተገነባ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 50ሺ110 ቤቶች የሚገነቡበት ሥፍራ ነው፡፡ በሳይቱ ፓኬጅ ‹‹ኤ›› ያሉ የ20/80 ቤቶች ግንባታው በአማካይ 86 ከመቶ የደረሱ ሲሆን፤ ‹‹ቢ›› ደግሞ 70ነጥብ5 ከመቶ ደርሷል፡፡
ቦሌ አራብሳ
የየካ ክፍለከተማ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መለሰ ተገኘ እንደሚሉት፤ በሳይቱ እየተገነቡ ካሉ ቤቶች የካ፣ ቦሌ፣ ቂርቆስ፤ ልደታ እና ፕሮጀክት 13 የተባሉ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን ያካተተ ሲሆን፤ አማካይ የግንባታው ሂደት 93 ከመቶ ደርሷል፡፡ በዚህ አካባቢም ግንባታው የ20/80 እና 10/90 ቤቶችን ግንባታን አጣምሮ የያዘ ነው፡፡
ቦሌ አያት 40/60
አቶ የኑስ መሐመድ የቦሌ አያት የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፤ የ40/60/ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ሶስት ቅርንጫፍ እንዳሉት ይጠቁማሉ፡፤ ይሁንና በዚህ ሳይት ላይ 265 ህንጻዎች እየተገነቡ ነው፡፡ ግንባታቸውም ከጥቅምት 2007 ዓ.ም የተጀመሩ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሳይቶች የሚገነቡ ቤቶች የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃና የአደጋ ጊዜ መውጫ ቴክኖሎጂ፣ ሊፍቶች ይገጠምላቸዋል፡፡
ስኬቶች
በበርካታ ሳይቶች ላይ ከፍተኛ ሆነ የገበያ ትስስር እና የስራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ለአብነትም በአቃቂ ቃሊቲ ስር በሚገኘው ኮዬ ፈጬ ሳይት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 132 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሯል፡፡ ለ24ሺ ዜጎች በተፈጠረው የሥራ ዕድል በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በቦሌ አራብሳ አካባቢ 141 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር የተፈጠረ ሲሆን፤ እስከ ሚያዚያ 2010 ዓ.ም ድረስ 12ሺ654 ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ 40/60 የጋራ መኖሪያ ከሚገነቡባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው፤ ቦሌ አያት አካባቢም የ744 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር የተፈጠረ ሲሆን በሥራ ዕድል ፈጠራ ደግሞ 477 ማህበራት በሳይቱ ላይ በመስራት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡በእነዚህ ሳይቶች ቀደም ካሉት በተለየ መልኩ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያው በአንድ ስፍራ ተጠራቅሞ በድጋሚ አገልግሎት የሚሰጥበት አሰራር ተግባራዊ ሆኗል፡፡
የጋራ ችግሮች
በበርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይቶች አካባቢ ላይ የጋራ ችግር እንደሚስተዋሉ ተገልጿል፡፡በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ስር የሚገኘው ኮዬ ፈጬ፣ ቦሌ አራብሳም ሆነ 40/60 ቤቶች ግንባታ በሚከ ናወንባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የየሳይቱ የሥራ ኃላፊዎቹ ችግሮቹን አመላክተዋል፡፡
በአቃቂ ክፍለ ከተማ ስር የሚገኘው ኮዬ ፈጬ ሳይት ግንባታ ሲጀመር የተሟላ መሠረተ ልማት አለመኖር፣ የዲዛይን ችግር፤ የባለሙያ እጥረት፣ የአፈር ምርመራ አለመደረጉ፣ ግብዓት አለመሟላቱ፣ አካባቢው በሩቅ ሥፍራ ላይ በመሆኑ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የሚሰሩ ማህበራትንና የጉልበት ሠራተኞችን አለማግኘት ፣ የገንዘብ እጥረት ፈታኝ ጉዳዮች ማጋጠማቸው ተብራርቷል፡፡ የተቋራጮች የአቅም ውስንነት፣ የዋጋ በየጊዜው መለዋወጥ፣ የሥራ ተቋራጮች መግዛት ያለባቸውን ግብዓት በወቅቱ አለመግዛት ለግንባታው እንቅፋት መሆናቸው ተመልክቷል፡፡በአማካሪ በኩል ደግሞ የአቅም ውስንነት፤ ክትትል አለማድረግና ፈጣን ውሳኔ አለመስጠት፣ በመስፈርቱ መሠረት በትክክል ሰርቶ አለማስረከብ በሰፊው መስተዋላቸውንና በቡድን ተደራጅቶ ስርቆት መፈፀምም ፈታኝ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በቦሌ አራብሳ ሳይትም ለግንባታ የሚሆን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት፤ የተቋራጮች የዋጋ ክለሳ መዘግየት፣ የውሃ እጥረት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ጥገና በየጊዜው አለመከናወን እና ለስራ አስቸጋሪ መሆን፣ በቡድንና በተደራጀ መንገድ የተደራጀ ዝርፊያ ማካሄድ፣ በሳይቱ ላይ በብዛት የሚሳተፉና በጥራት የሚሰሩ ማህበራት እጥረት መኖር በሳይቱ ላይ በዋናነት የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው፡፡
40/60 ግንባታ በሚከናወንበት ቦሌ አያት ሳይትም፤ ቤቶቹን ለማስረከብ ከተያዘው መርሐግብር አኳያ እንደሚዘገይ ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ግንባታዎቹ በጥራትም ሆነ በመጠን ከፍተኛ ጥንቃቄ እና መዕዋለ ንዋይ የሚወጣባቸው በመሆናቸው ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ሳይት በዚህ ዓመት መንገድ ግንባታ እስከ ሚያዚያ 2010 ዓ.ም ይጀመራል ቢባልም እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ለግንባታው የሚሆን አርማታ ብረት አቅርቦትም በከፍተኛ ደረጃ ችግር እንዳለ አስገንዝበዋል፡፡
የ40/60 ቤቶች ግንባታ ሥራዎች አብዛኛው የገንዘብ አቅርቦትና ፍሰት ከባንክ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ፈጣን አገልግሎትና ምላሽ አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡ አብዛኛው የግንባታ ግብዓት ከውጭ አገር የሚገባ በመሆኑ ለግዥ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትና ተያያዥ ሂደቶች ላይ ችግር መኖራቸው ተብራርቷል፡፡ ፕሮጀክቶችን ማስተዳደርና መምራትም ደካማ እንደሆነ ነው የተገለፀው፡፡
የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ
በየሳይቱ የሚነሱ ችግሮች እንደየባህሪቸውና ሥራው ሁኔታ የሚለያዩ ቢሆን የጋራ መፍትሄ እንደሚያስፈልጋቸው ነው ኃላፊዎቹ የሚናገሩት፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ እንደሚሉት፤ በየሳይቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል የተቀናጀ አሰራር መተግበር ያስፈልጋል፡፡በመሆኑም ሁሉም አካላት እየተወያዩ መፍትሄ የሚያበጁበት መንገድ ተመቻችቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም የችግሩን ስፋት በመገንዘቡ ከችግር ባለፈ ወደ መፍትሄ የሚያመሩና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በሚያስችሉ አሰራሮች ላይ አተኩሯል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ብቻውን የማያስተካክላቸውንም ከሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት ጋር በመመካከር እልባት እንደሚያበጅ አረጋግጠዋል፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው፤ ችግሮቹን መለየት መፍትሄውን ለማምጣት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ባይ ናቸው፡፡ ግንባታዎቹ ከተጀመሩ የቆዩ ቢሆንም፤ አሁን ያሉበት ደረጃ ተስፋ ሰጪ በመሆኑ የተጓደሉ አሰራሮችን ማስተካከልና ወደ ተሻለ አቅጣጫ ማምራት እንደሚቻል አረጋግጠዋል፡፡
«ችግሮቹ በተለያዩ አካላት መፍትሄ ያገኛሉ» የሚሉት ሚኒስትሩ፤ ተቋማትን ከማቀናጀት አኳያ ሚኒስቴሩ መሥራት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ችግሮቹ እየተፈጠሩ ያሉት ከማን ጉድለት በምን ምክንያት እንደሆነ በሰፊው ተገምግሞ መፍትሄ መስጠቱ ግድ ይላል፡፡ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታትም ከሚመለከተው አካል ጋር መስራቱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ በርካታ ሥራዎች በከተማ አስተዳደሩ የሚከናወኑ ቢሆንም፤ ሚኒስቴሩ የአቅም ክፍተት ወይንም አስፈላጊ እገዛ ሲኖር በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

Published in ኢኮኖሚ

ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ባህሬን ከኳታር ጋር ያላቸውን ግኙነት አቋርጠው ልዩ ልዩ ማዕቀቦችን ከጣሉባት ድፍን አንድ ዓመት ተቆጠረ፡፡ እ.አ.አ ሰኔ 5 ቀን 2017 በአረብ ባህረ ሰላጤ ቀጠና ኃያል ናት የምትባለውን ሳዑዲ አረቢያንጨምሮ ግብፅ፣ ባህሬንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ‹‹ኳታር አሸባሪዎችን እየደገፈች ነው›› የሚል ክስ አቅርበው ከአገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋረጡ፡፡ ሊቢያ፣ የመንና ማልዲቭስም የነሳዑዲ አረቢያን ፈለግ ተከተሉ፡፡
ልዕለ ኃያላኗን አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገራት ሁለቱን ወገኖች ለማስማማት ያደረጓቸው ጥረቶች ይህ ነው የሚባል የረባ ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተዋል፡፡ ኳታርም ሆነች እነ ሳዑዲ አረቢያ አባል በሆኑበት የባህረ ሰላጤው የትብብር ካውንስል (Gulf Cooperation Council) በኩልም የተደረጉት ጥረቶች አልተሳኩም፡፡ እነሳዑዲ አረቢያ ከኳታር ጋር ለመደራደር ያቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎችም በኳታር በኩል ተቀባይነት ማግኘት ሳይችሉ ቀርተው የሁለቱ ወገኖች ፖለቲካዊ ሽኩቻና ፍጥጫ ያለምንም መፍትሄ ለአንድ ዓመት ዘልቋል፡፡
ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል በተለይ የአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያና ዶሃ ውስጥ የሚገኘው የቱርክ ወታደራዊ ሰፈር እንዲዘጉ እንዲሁም ኳታር ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥ የሚጠይቁት መደራደሪያዎች ለኳታር መንግሥት ፈፅሞ የማይዋጡ ነበሩ፡፡
ሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿ ኳታርን ለአሸባሪዎች ድጋፍ ታደርጋለች ብለው ሲወቅሷት ነገሩ ‹‹አመድ በዱቄት ይስቃል›› እንደሚባለው መሆኑን የተናገሩ ወገኖች ብዙ ነበሩ፡፡ እነዚህ ወገኖች እነሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው የበርካታ ግለሰቦችና ተቋማት መቀመጫ ሆነው ሳለ በኳታር ላይ እንዲህ ዓይነቱን ክስ ማቅረባቸው ከጀርባው ሌላ የተቀነባበረ ሴራ እንዳለ ሲገልፁ ነበር፡፡ ኳታር በቀጣናው የሳዑዲ አረቢያ ዋነኛ ባላንጣ ከሆነችው ከኢራን ጋር ያላት የጠበቀ ግንኙነት ሳዑዲ አረቢያን እንዳስቀየማትና ብሔራዊ ደህንነትን ከሽብርተኝነትና አክራሪነት ለመጠበቅ በሚል ሰበብ ኳታርን መበቀል ትፈልግ እንደነበርም ለሴራው ማስረጃ አድርገው ያቀርባሉ፡፡
ሽኩቻው ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉትም የፖለቲካ ተንታኞች ደጋግመው ተናግረዋል፤ጽፈዋል፡፡ ከነዚህ ምክንያቶች መካከል አንዱ ኳታር የምትከተለው የፖለቲካ ስርዓት ከሌሎቹ የባህረ ሰላጤው አገራት ጋር በብዙ መልኩ የተለየ መሆኑ ነው፡፡ ሁለቱን ወገኖች ለማደራደር ተደጋጋሚ ጥረቶችን ያደረገችውን ኩዌትን ጨምሮ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ባህሬንና በፍጹም ዘውዳዊ አገዛዝ ስር የሚተዳደሩ ሲሆኑ ኳታር በበኩሏ ላላ ያለ አስተዳደር ትከተላለች፡፡ ይህም እነሳዑዲ አረቢያ የኳታርን የአስተዳደር ስርዓት ያዩ ዜጎቻችን በመንግሥታት ላይ አመፅና ሁከት ለመፍጠር ያነሳሳቸዋል የሚል ፍራቻ አላቸው፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሁለቱ ወገኖች አለመግባባት የከፋ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የገመተው መንግሥታቱ ከኳታር ጋር ያላቸውን ፖለቲካዊ ግንኙነት ከማቋረጣቸውም በተጨማሪ በየአገሮቻቸው የሚገኙ የኳታር ዜጎች አገሮቹን ለቀው እንዲወጡ የጊዜ ገደብ ባስቀመጡበት ወቅት ነው፡፡
በአሜሪካና በአውሮፓ ኅብረት በኩል ከተደረጉት ጥረቶች በተጨማሪ ኳታርም ሆነች እነ ሳዑዲ አረቢያ አባል በሆኑበት የባህረ ሰላጤው የትብብር ካውንስል እንኳ ሁለቱን ወገኖች ለማስማማት ያደረገው ጥረት ሊሳካ አልቻለም፡፡
ታዲያ አገራቱ ወደዚህ ፖለቲካዊ ሽኩቻ ውስጥ ገብተው እንዲህ ረዘም ላለ ጊዜ ይቆያሉ ብለው የገመቱት ወገኖች በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡ በዶሃ ኢንስቲትዩት የግጭትና ሰብዓዊ ጉዳዮች ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ሱልጣን ባራካት፣ የባህረሰላጤው ቀውስ እልባት ሳያገኝ ለአንድ ዓመት ያህል ይቆያል ተብሎ የታሰበ እንዳልነበር ይገልፃሉ፡፡ ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ ኳታር ከነሳዑዲ አረቢያ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ አግኝቶ አገራቱ ቀድሞ ወደነበራቸው ግንኙነት ይመለሳሉ የሚል ተስፋ ነበራት፡፡ ይሁን እንጂ ሳምንታትና ወራት እያለፉ ሲሄዱ ኳታር ከጎረቤቶቿ ተነጥላ ብቻዋን እንዳለች ተገንዝባለች፡፡
እንዲያም ሆኖ ኳታር አጋጣሚውን እንደመልካም እድል ልትጠቀምበትም ሞክራለች፡፡ አገሪቱ በተጣሉባት ምጣኔ ሀብታዊ ማዕቀቦች ምክንያት ያጋጠማትን ችግር በምግብ ምርቶች ራሷን ለመቻል፣ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከርና ለአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ጥንካሬ የሚሰጡ የፋይናንስ ፖለሲዎችን በመቅረፅ ምጣኔ ሀብታዊ መረጋጋትን ለመፍጠር ሞክራለች፡፡
ኳታር ከነሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላት ግንኙነት እንደተቋረጠ ወዲያውኑ ከየመን ዘመቻ ራሷን ማግለል መቻሏ አስደስቷታል፡፡ ወትሮውንም ቢሆን እነሳዑዲ አረቢያን ለማስደሰት እንጂ አምናበት ካልገባችበት ዘመቻ ውስጥ መውጣቷ ዘመቻው ሊያደርስባት ከሚችለው የምጣኔ ሀብት ቀውስ አድኗታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በየመናውያን ላይ በፈፀሙት አሰቃቂ እልቂት ምክንያት ከደረሰባቸው ውግዘትም አምልጣለች፡፡ በአጠቃላይ ኳታር ከየመን ዘመቻ መውጣቷ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እንደትልቅ ፖለቲካዊ ስኬት ተቆጥሮላታል፡፡
ነፃና ከዘመናዊው የፖለቲካ ስርአት ጋር የተጣጣመ ነው የሚባልለት የኳታር የውጭ ግንኙነት ፖለሲም እነሳዑዲ በዓለም አቀፍ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲተቹ፣ ኳታር ደግሞ እንድትመሰገን አድርጓታል፡፡ የአገራቱ ሰብዓዊ መብት አያያዝና ጥበቃም ለነሳዑዲ ወቀሳ ለኳታር ደግሞ ሙገሳ ያተረፉ ናቸው፡፡ በእርግጥ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ኳታርም ከዓለም አቀፍ የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች ወቀሳዎች እንደሚቀርቡባት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ኳታር በባህረ ሰላጤው ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት እነሳዑዲ ከተወገዙበት የእየሩሳሌም ጉዳይ ከወቀሳ ድናለች፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም ሲያዛውሩ ድጋፋቸውን የገለፁት ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከሌሎች የአረብና የሙስሊም አገራት ከባድ ተቃውሞና ትችት ደርሶባቸዋል፡፡ በእርግጥ ሳዑዲ አረቢያ የትራምፕን ውሳኔ የደገፈችው የእስራኤል ዋነኛ ጠላት የሆነችውን ኢራንን ለማናደድና ከእስራኤል ጋር በማበር ለማስፈራራትም ጭምር ነው፡፡ በአጠቃላይ ኳታር በየመንና በእየሩሳሌም ጉዳይ ላይ የወሰደችው አቋም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ምስጋናንና ተቀባይነትን አስገኝቶላታል፡፡
ሌላው ኳታርን ተቀባይነት ያስገኘላት ጉዳይ በኢራን የኑክሌር ስምምነት ላይ የያዘችው አቋም ነው፡፡ አወዛጋቢው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን እ.አ.አ በ2015 በኢራንና በስድስቱ ኃያላን አገሮች (አሜሪካ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ) መካከል ከተፈረመው የኢራን የኑክሌር ስምምነት ማስወጣታቸውን ተከትሎ ኳታር ለፕሬዚደንቱ ውሳኔ ድጋፍ አለመስጠቷ ከፕሬዚደንቱ ውሳኔ በተቃራኒ ከተሰለፉት የአውሮፓ ኃያላንና ቻይና ድጋፍ አግኝታለች፡፡ በሌላ በኩል ለፕሬዚደንቱ ውሳኔ ድጋፍ የሰጡት ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ልክ እንደ የመንና ኢየሩሳሌም ጉዳይ ሁሉ ሌላ ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈት ደርሶባቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኳታር አንድ ዓመት ያስቆጠረውን የባህረ ሰላጤውን ቀውስ ወደመልካም አጋጣሚዎች በመቀየር ለመጠቀም መሞከሯና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በወሰደቻቸው አቋሞች ምክንያት ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን ብታገኝም ቀውሱ በቀጣይ ጊዜያት የሚፈጥርባት ተፅዕኖ ቀላል ይሆናል ተብሎ እንደማይጠበቅ ሱልጣን ባራካት ያስረዳሉ፡፡ በዚህም አገሪቱ ለረጅም ጊዜያት የሚያራምዷትን ስትራቴጂዎች መቀየስ አለባት ይላሉ፡፡ ባራካት እንደሚሉት ፕሬዚደንት ትራምፕ ከምርጫ ጋር ተያይዞ እየተካደባቸው ያለው ምርመራ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን የሚታሙበት የሙስና ቅሌት በአቡ ዳቢና በሪያድ መካከል እየታየ የመጣው ክፍተት አሜሪካ፣ እስራኤል ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያላቸውን ጥምረት ሊያዳክሙት ይችላሉ፡፡
የሳዑዲ አረቢያው አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን ሳዑዲ አረቢያን የተሻለችና ዘመናዊ ለማድረግ እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ መናገራቸው ኳታር እየተጓዘችበት ወዳለው የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ስርዓት መግባታቸው እንደማይቀር አመላካች ነው እየተባለም ይነገራል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ለኳታር ትልቅ ዋጋ ያላቸው ድሎች እንደሚሆኑ መገመት ቀላል ነው፡፡
ያለምንም መፍትሄ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የባህረ ሰላጤው ቀውስ የሚኖረው ቀጣይ ሁኔታና ለመተንበይ አስቸጋሪ በሆነው የመካከለኛው ምስራቅና የአረቡ ዓለም ፖለቲካ ውስጥ የሚኖረው ተፅዕኖ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

አንተነህ ቸሬ

Published in ዓለም አቀፍ

ሰውየው የሰፈሬ ነዋሪ ነው፡፡ አዘውትሮ መጠጥ የሚጠጣ በመሆኑ በሰከረ መንፈስ ያሻውን የመናገር ድፍረት አለው፡፡ አንድ እርምጃ ወደፊት ተራምዶ ሦስት እርምጃ ወደጎን ይንደረደርና ሚዛኑን ጠብቆ ለመቆም እየሞከረ፣ አላፊ አግዳሚውን በደበዘዙ አይኖቹ አተኩሮ እያየና አመልካች ጣቱን እያወዛወዘ « እያንዳንድሽ ሙስና ፈፅሟል ብለሽ የጠቆምሽ፣ የመሰከርሽና ይታሰር ብለሽ የደነፋሽ ሁሉ ጉድሽ ፈላ!» በማለት ያስፈራራል፡፡
ሰካራም የልቡን ይናገራል እንዲሉ ሆኖ እንጂ ሰው ምን ቢሰክር እውነቱን አይስትም፡፡ « ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል!» የሚለው ብሂልም ለዚህ ጥሩ መግለጫ ይሆናል፡፡
ይህ በመጠጥ ሃይል የልቡን የሚናገረው ሰው ንግግሩ ከሰከረ ሰው የመነጨ ይሁን እንጂ ያነሳው ርዕሰ ጉዳይ የአብዛኛው ኅብረተሰብ ለመሆኑ ማን ይጠራጠራል?
ለሙስና ብያኔ ከመስጠት ይልቅ «ብልሹ አስተሳሰብ ነው!» ብዬ ባልፈው እመርጣለሁ፡፡ ስለዚህም የሙስና ድርጊት የብልሹ አስተሳሰብ የመጨረሻ ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ድርጊቱ በስልጣን መባለግ፣ ለሦስተኛ ወገን ያላግባብ ጥቅም መስጠት፣ ያለ ላብ መበልፀግን መፈለግ ወዘተ... የመሳሰሉትን ሊያካትት ይችላል፡፡
ሙሰኞችን በህግ ቁጥጥር ሥር ማዋል የመቆጣጠሪያ መንገዱ ትንሹ ተግባር እንጂ ሙስናን ለማስወገድ ዘራፊዎችን ማስወገድ አማራጭ መፍትሄ አይደለም፡፡
የሙስና ምንጭ የሆነውን ብልሹ አስተሳሰብ መዋጋት የመጀመሪያው መፍትሄ ሲሆን፤ብልሹ አስተሳሰብን በጤናማ አስተሳሰብ መቀየር ማለት ሙስናን መዋጋት ማለት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ሙስና ፈፃሚዎችን ባጠፉት ጥፋት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ በፍርድ ሂደት ውሳኔ በማሰጠት ወደ ማረሚያ ቤት ማስገባት የመጨረሻው አማራጭ ይሆናል፡፡
የአገራችንን የፀረ ሙስና ሕግ ስንመለከት በሙስና የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የዋስትና መብት እንኳ የሚከለክል ሆኖ ሳለ አንዳንዶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ተይዘው በዋስትና ይለቀቃሉ፤ አንዳንዶች ዋስትና ተከልክለው ፍርዳቸው እየተጓተተ በእስር ይንገላታሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ዘርፈው ባገኙት ገንዘብ በተቀናጣ ህይወት ካለ ተጠያቂነት ሲንደላቀቁ፣ ልጆቻቸው ውድ ክፍያ የሚከፈልበት ትምህርት ቤት ሲማሩ፣ ለትንሽ ህክምና ውጭ አገር ሲመላለሱ መታየታቸው ለዚህ ሁሉ መንደላቀቅ ምንጩ ያልታወቀው የገቢ ምንጭ መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡
በተለይ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸውና በተለያዩ ጊዜያት ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል ተብሎ ለሕዝብ ተገልጾ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩና አሁን የተፈቱ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ሌሎች ግለሰቦችን በተመለከተ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡
እነዚህ ግለሰቦች ታክስ እንዳይሰበሰብ በማድረግ በመንግሥት የገቢ ምንጮች ላይ ጉዳት በማድረስ ፣አንድ ድርጅት መክፈል የነበረበትን በርካታ ሚሊዮን ብር ግብር እንዲከፍል ሲወሰን የጠቋሚ ክፍያ ከገቢው ላይ ተቀንሶ ለግለሰቦች ያላግባብ እንዲከፈል ሰዎችን በማደራጀት፣ ቃለ ጉባዔ በማዘጋጀትና ጠቋሚ ያልሆኑ ሰዎች በጠቋሚነት እንዲመዘገቡ በማድረግ፣ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ከብዙ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ንብረትና ገንዘብ በማፍራት፣ አራጣ በማበደር ወንጀል ተጠርጥረው ማስረጃ የቀረበባቸውን ግለሰብ እያወቁ ለሕግ አሳልፎ ባለመስጠት፣በርካታ ሆቴሎች ከቀረጥ ነፃ የገቡ የሆቴል ዕቃዎችን ከታለመለት ዓላማ ውጪ እየተገለገሉበት መሆኑ መረጃ የደረሳቸው ቢሆንም ባላቸው ስውር የጥቅም ግንኙነት ክስ እንዳይመሠረትባቸው በማድረግ፣ ከቀረጥ ነፃ የገባ ሲሚንቶ ለሦስተኛ ወገን ሲሸጥ ዝም በማለትና ሲከሰሱም ክሳቸው እንዲቋረጥ ማድረጋቸው፣መወረስ የሚገባቸውን መኪኖች እንዳይወረሱ በማድረጋቸው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ የክስ መዝገቦች በማደራጀት ክስ ማቅረቡ ለህዝቡ ተነግሯል፡፡ በክሱ ሂደትም ከሰነድ ማስረጃዎች በተጨማሪ እማኝ የሆኑ የሰው ምስክሮች ለደህንነታችን እንሰጋለን ባሉበት ሁኔታ መቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ዛሬ ለእነዚህ ግለሰቦች የተደረገላቸው ይቅርታ ግን የተደከመበትን የማጣራት ሂደትንና የተፈፀመውን ወንጀል ያጋለጡ ወገኖችን ዋጋ ያጣ ይመስላል፡፡ የአጣሪ ፖሊሶችና የዓቃቤ ሕግ ድካም፣ የዳኞች የፋይልና መረጃ የማጣራት ልፋት፣ የእማኞች የምስክርነት ቃል ከንቱ ቀርቷል፡፡ መንግሥት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የታሰሩትን፣ ጦርነት በማወጅና ብጥብጥና ሁከት በማነሳሳት በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን እንዲሁም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ክሳቸውን እያቋረጠ በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡ ይህ ለሠላምና ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ሲባል ይበል የሚያሰኝና የሚበረታታ ተግባር በመሆኑ ሁሉም ይደግፈዋል፡፡
ይሁን እንጂ የአገርን ልማት ያደናቀፉ፣ የህዝብ የኑሮ ደረጃ አሳዛኝ በሆነበት ወቅት ከህዝብ ጉሮሮ እየነጠቁ እነርሱና ቤተሰባቸውን ያንደላቀቁ አልጠግብ ባይ ናቸው ተብለው በሙስና የተጠረጠሩት ተገቢውን ፍርድ ማግኘት ሲገባቸው፣ ለሌሎች ማስተማሪያ የሚሆን ቅጣት ሊሰጣቸው ሲገባ ክሳቸውን አቋርጦ ማሰናበት« ሙስና የአገሪቱና የሥርዓቱ አደጋ ነው፣ ሙስናን የሚሸከም ማሕበረሰብ መፍጠር የለብንም፣ሙስና ቀይ መስመር» ነው ብሎ በአደባባይ ይናገር ከነበረ መንግሥት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ከዚህ በኋላስ መንግሥት በነፃ የሚያሰናብታቸውን የሙሰና ተጠርጣሪዎችን እያየ ሙስና ለመፈጸም የማይደፍር እንዲሁም ሙሰኛን ለማጋለጥ የሚነሳሳው የትኛው የኅብረተሰብ ክፍል ነው? በነፃ መሰናበት ካለስ ሌላው ላለመዝረፍና ለዘረፋ ላለመተባበር ምን የሚከለክለው ይኖራል?
ሕግ አውጪ፣ ተርጓሚና አስፈፃሚ፣የሲቪል ማህበረሰብና መገናኛ ብዙሃንን የመሳሰሉት የፀረ ሙስና ትግሉ ተዋናዮች ቢሆኑም በተለይ ሙስና ለመፈፀማቸው በቂ ማስረጃ ተገኝቶባቸው ለፍርድ ሂደት ቀርበው ሳሉ ክሳቸውን ማቋረጥና ማሰናበት ተገቢ ነው ብሎ ማሰብ ለጥቂቶች ቀላል ቢሆንም ጉዳት ለደረሰበት የኅብረተሰብ ክፍል ግን ከፍተኛ የሞራል ጉዳት ያደርሳል፡፡ይህ አካሄድ የኢትዮጵያ የፀረ-ሙስና ትግል አደረጃጀትና ተግባር ድቡሽት ላይ እንደተገነባ ቤት ተመስሎ ይታያል፡፡
በኢትዮጵያ ሙስናን ለመዋጋት ለሚደረገው ትግል ከአስተሳሰብ ቀጥሎ ብቸኛው አማራጭ የአሰራር ሥርዓት በመሆኑ ይህንን ሥርዓት ማዛባት ጉዳቱ የሁሉም ነው፡፡
ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት የሙስናውን ከባድነት ሲገልፁ« አንድ እጃችን ተይዞ በአንድ እጃችን ነው እየሠራን ያለነው!» ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ዛሬ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ከባድ ወንጀል ስናስተውልና የህግ ተጠያቂነቱም ሲቋረጥ ለሙስና መፈፀም በተቃራኒው ለቆሙና የጸረ ሙስና ትግሉ ደጋፊ አካላት ተስፋ አስቆራጭ ወቅት ላይ የደረስን ይመስላል፡፡በፅሁፌ መግቢያ ያነሳሁት በመጠጥ ሃይል የልቡን እንደተናገረው ሰው« እያንዳንድሽ ሙስና ፈፅሟል ብለሽ የጠቆምሽ፣ የመሰከርሽና ይታሰር ብለሽ የደነፋሽ ሁሉ ጉድሽ ፈላ!»የት ይሆን መግቢያሽ?

አያሌው ንጉሤ

ደብዳቤዎች

ይድረስ ለአዲስ ዘመን

 

ሌብነት በይቅርታ አይታለፍም

 

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ አቶ ብርሃነ ፀጋዬ ቅዳሜ ግንቦት 18/2010 ዓ.ም በፅህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በሽብር ወንጀል ተከሰው የነበሩ 137 ግለሰቦች እንዲሁም በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ አቶ መላኩ ፈንታ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ አቶ አለማየሁ ጉጆ እና አቶ ዘይድ ወልደገብርኤልን ጨምሮ የሙስና ክሳቸው አንዲቋረጥ መደረጉን ማስታወቃቸው ይታወሳል። እንደሚታወቀው በሽብር ተግባር ወንጀል ተከሳሾችም ሆኑ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እንዲሁም ጋዜጠኞች ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ ሁኔታ መታሰራቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመጨረሻዎቹ የስልጣን ሳምንታት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በይቅርታ ከእስር እየተፈቱ መሆናቸውን እያየን ነው፡፡
በፖለቲካ ልዩነቶች የታሰሩትን በመፍታት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ለሀገራችን ዕድገትና ለዴሞክራሲ ግንባታ እጅግ ጠቀሜታ ስላለው በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ብቻ የተለያዩ ተፅዕኖ ተደርጎባቸው የታሰሩ፣ወደ ተለያየ ውጪ ሀገራት የተሰደዱ፣ በሀገር ውስጥ ያኮረፉ ሁሉ በይቅርታ ክሳቸው መቋረጡና ነፃ መሆናቸው መንግሥት ባመቻቸው የፖለቲካ ምህዳር መስፋት አጋጣሚን በመጠቀም ለሀገር ግንባታና ለዴሞክራሲ ስኬት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ሲናገሩ በመስማታችን በጣም ተደስተናል፡፡ ይቅርታ መደረጉም ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር ስለሆነች የጥቅምም ሆነ የጉዳት ሸክምን ኢትዮጵያዊ በእኩል መጋራት አለበትና፣ ከፍቅርና ከይቅርታ የሚበልጥ ማሰሪያ ስለሌለ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉትን በይቅርታ መልቀቁ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በእርግጥም ሙስና ፈፅመው ከሆነ የተመዘበረውን ሀብት ሳይመልሱና ተገቢውን ቅጣት ሳያገኙ በይቅርታ መለቀቅ የለባቸውም፡፡ የይቅርታ መስፈርቱ ለህዝብ ሲገለፅ ዝርዝር ማብራሪያ ሊኖር ይገባል እንጂ በደፈና በይቅርታ ተለቀቁ። መባሉ ህዝብን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከትና መንግሥትንም በህዝብ ዘንድ አመኔታ የሚያሳጣ ስለሆነ የሙሰኞችን የክስ ሂደት ለማቋረጥ መስፈርቱ ምን እንደሆነ ግልፅ ይደረግ፡፡
በወቅቱ ተመዘበሩ ተብሎ በዓይነትና በአሃዝ የተጠቀሰው የሀብት መጠን የፈጠራ ወሬ እና መሰረተ ቢስ ከሆነ፣ ተወንጅለው የነበረው ለፖለቲካ ፍጆታ ወይም በቂም በቀልና በጥቅም ግጭት ከሆነም ግልፅ ይደረግ፡፡ አለበለዚያ የመዘበሩት የህዝብ ሀብት ይመለስ፡፡ ሌሎችም የመዘበሩ ካሉ ማስረጃ እየተሰበሰበ እንዲመለስ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ቀደም ሲል የመንግሥትንና የሕዝብን ገንዘብ የሰረቁ ጎምቱ ባለስልጣናት ተጠያቂ የማይሆኑ ከሆነ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙት የሕዝብን ሀብት እደማይዘርፉ ምን ዋስትና አለ? በየጊዜው በየተቋማቱ የሚታየው እና ዋና ኦዲተር በሚያቀርበው የኦዲት ግኝት መሰረት ያለ አግባብ የሚባክነውን የመንግሥትና የህዝብ ገንዘብ በተመለከተ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ሳይጠየቅ ነገ ሀገርን የሚረከቡ ወጣቶች ከዚህ ምን ተምረው ይጠንቀቁ? ስም የተመዘበረ ሀብት በይቅርታ ብቻ ሳይመለስ የሚቀር ከሆነ ህዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ የማጣቱ ጉዳይ የሚቀጥል ይመስለኛልና ይታሰብበት፡፡ ሌብነት በይቅርታ አይታ ለፍምና!
አለሙ ዳንጌሶ ዋዬ
ከሀዋሳ

Published in አጀንዳ

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማክሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. በአወጣው መግለጫ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሠላም እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኢህአዴግ በመግለጫው ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተውን ጦርነት‹‹በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ሕይወት ሊጠፋ ችሏል፡፡ ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢና የመኖሪያ ቀዬ አፈናቅሏል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረገው ጦርነት ቤተሰቦችን አፍርሷል፡፡ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎችን ያለመረጋጋትና የሥጋት ሥነ ልቦና ሰለባ አድርጓቸዋል፤›› በማለት የገለጸው ሲሆን፣ «በድምሩ ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱም አገሮች ሕዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል›› በማለት የጦርነቱን አስከፊነት አብራርቷል፡፡
በዚህ ምክንያትም በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ አገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ መንግሥት የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሠራ መሆኑን ለመግለጽ እንደሚፈልግም በግልፅ አስቀምጧል፡፡
‹‹የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሠላም ጥሪውን ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሠላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት እንዲሠራ እንጠይቃለን›› በማለት ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ይሁን እንጂ እስካሁን በኤርትራ በኩል ምንም አይነት ምላሽ አልተደመጠም፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 18 ዓመታት በሁለቱ አገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሠላም የሌለበት ሁኔታ አሳልፈዋል፡፡
ቀደም ሲል በኤርትራ በኩል የነበረው አቋም በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ይተግበር፣ኢትዮጵያም ሠራዊቷን ከባድመ ታውጣ የሚል ነው ፡፡ በአሁኑ በኢትዮጵያ በኩል ለሁለቱ አገሮች ሠላም ሲባል በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተደረሰው ውሳኔ ቀና እርምጃ ነው፡፡እስካሁን የኤርትራ ምላሽ አለመደመጡ የኤርትራ መንግሥት ለሠላም ያለው አቋም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የወሰደችው እርምጃ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ይህ ግን በኤርትራ ለአለው ሃይል የማይታመን ነው፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ መንግሥት በሃገር ውስጥ ያለውን ችግር ውጫዊ መልክ ለማስያዝ የሚጠቀመው አንዱ ሰበብ መሸፈኛ ይህ የአልጀርሱ ስምምነት አልተከበረም የሚል ነው፡፡የአሁኑ የኢህአዴግ ውሳኔ ለሁለቱም ህዝቦችና ለክፍለ አህጉሩ ጠቃሚ ቢሆንም የኤርትራው ስርዓት እስካሁን በመጣበት መንገድ መቀጠል አያስችለውም፡ የሠላም ሃሳቡ አለመቀበሉም የትም አያደርሰውም፡፡ስለሆነም ጥሪውን ተቀብሎ ለሁለቱ ህዝቦች ዘላቂ ሠላም መስራት ይጠበቅበታል፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ ባለፉት ዓመታት ሠላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ መቀጠላቸው በቀጣናው ውስጥ በጦርነት የሚጠባበቁ አገራት ሆነው ቆይተዋል። የኤርትራ መንግሥት ከአሸባሪዎች ጋር በማበርና የውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች በማገዝ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ችግር እንዲፈጠር አድርጓል።የአሁኑ የሠላም ጥሪ ይህን ችግር በመፍታት ሁለቱ ሃገሮችና ህዝቦች በጋራ ማደግ የሚችሉበት አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ ለተግባራዊነቱ መስራት ይገባል፡፡ለዚህ ደግሞ የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ጭምር ለሠላም ጥሪው ስኬት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባዋል፡፡
ቀደም ሲል ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነቷን ተጠቅማ በኤርትራ ላይ ባደረገችው ተጽዕኖ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እንድትገለል አድርጋለች። በዚህም ኤርትራ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ሽያጭና በሌሎች ድርጊቶቿ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብና በቀጣናው አገራት ተአማኒነትን እንድታጣ አድርጓታል።
ከዚህ ሁሉ ውጥረትና ውዝግብ በኋላ ኢትዮጵያ የወሰደችው ለሁለቱ ህዝቦችና ለቀጣናው የሚበጅ የሠላም እርምጃ በይበልጥ ለሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ታላቅ የምስራች መሆኑን በመገንዘብ ኤርትራ የቀረበላትን የሠላም ጥያቄ ለራሷ ዜጎችና አገር ከድህነት ለመላቀቅ ስትል አፋጣኝ ምላሽ እንድትሰጥ መላው የዓለም ህብረተሰብ ግፊት ሊያደርግ ይገባል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጀኔራል ሰአረ መኮንንን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አድርገው ሾሙ። የቀድሞ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሳሞራ የኑስ በብሔራዊ ቤተመንግሥት በተከናወነ ልዩ ስነ ስርዓት ከፍተኛ የኒሻን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።