Items filtered by date: Saturday, 09 June 2018
Saturday, 09 June 2018 17:25

ካለ ምርኩዝ ዝላይ!

አትሌቲክስን በዓለማችን በተለይም በምዕራባውያን ተወዳጅ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የሜዳ ተግባራትና የአጭር ርቀት ውድድሮች ናቸው። ውርወራና ዝላይ አይነታቸው የተለያየ ቢሆንም በአትሌቲክስ ታላላቅ ውድድሮችና ኦሊምፒክ ላይ ያላቸው ዋጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከአራቱ የዝላይ ውድድሮች ማለትም ከስሉስ ዝላይ፤ ከፍታ ዝላይና ርዝመት ዝላይ በተሻለ ቀልብ የመሳብ አቅም ያለው ምርኩዝ ዝላይ በዓለም ያለው ተወዳጅነትም ከፍተኛ ነው። 

ኢትዮጵያ አትሌቲክስ መለያዋና በዓለም የምትታወቅበት ስፖርት መሆኑ ብዙ ጊዜ ይነሳል። ይህን ግን በመቃወም ኢትዮጵያ በደፈናው የአትሌቲክስ አገር ናት በሚል ሳይሆን በረጅም ርቀት ንጉሥነቷ የሚስማሙ በርካታ ናቸው። በእርግጥም ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ኩራቷና መገለጫዋ የሆነው በረጅም ርቀት እንጂ በደፈናው በአትሌቲክስ ነው ለማለት ምሉዕ አይደለችም። ምክንያቱም በረጅም ርቀቶች ያላት ዝና እንዳለ ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመካከለኛ ርቀቶች ውጤታማ እየሆነች ከመምጣቷ በስተቀር በአጭር ርቀቶችና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች እዚህ ግባ የሚባል ታሪክ የላትም።
በሜዳ ተግባራትና አጭር ርቀቶች ኢትዮጵያ አቅም እንዳላት የሚናገሩ የስፖርቱ ባለሙያዎች ለነዚህ ስፖርቶች ትኩረት ተሰጥቶ እንዳልተሰራ ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣል። በዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በተከፈቱ አገር አቀፍ ፕሮጀክቶች ታዳጊና ወጣቶች ላይ በነዚህ ስፖርቶች የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ይታያል። ነገር ግን እነዚህ ፕሮጀክቶች እስካሁን ያፈሩት ፍሬ ካለመኖሩ በተጨማሪ ወደ ፊት ያላቸው ተስፋም ጥርጣሬን ይጭራል። እነዚህ በአገር አቀፍ ደረጃ ከታዳጊ አንስቶ በወጣትና በአዋቂዎች በሚካሄዱ የአትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች በአጭር ርቀትና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች የሚታዩ ችግሮች ማሳያዎች ናቸው።
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንደምናየው በተለይም በከፍታና በምርኩዝ ዝላይ አትሌቶች አስደናቂ የመተጣጠፍ (fleaxablity)ና የመገለባበጥ ወይንም ሰውነትን እንደፈለጉ የማዘዝ ክህሎት አላቸው። በነዚህ ውድድሮች በሚደረጉ ፉክክሮችም ጅምናስቲካዊ ክህሎትን አክለው ተመልካችን ሲስቡ እንመለከታለን። ወደኛ አገር ውድድሮች ስንመጣ ግን ከአዋቂዎቹ አንስቶ በታዳጊዎችም በወጣቶችም ላይ ይህን ነገር አንመለከትም። እንዲያውም አትሌቶቻችን ለመዝለል የሚያደርጉት ጥረት ከመሰረታዊ የቴክኒክ ስህተቶች በተጨማሪ ባልሆነ መንገድ ወድቀው ተሰበሩ ወይንም መውደቂያ ፍራሹን ስተው ጉዳት ደረሰባቸው የሚል ሥጋት ውስጥ የሚከቱ አይነት ናቸው። ይህን የሚመለከት አትሌቶቹ ክህሎቱ የላቸውም ወይስ እንደ አገር የነዚህ ስፖርቶች ተሰጥኦ የለንም? ብሎ መጠየቁ አይቀርም።
በቅርቡ ለስድስተኛ ጊዜ በአሰላ አረንጓዴው ስቴድየም በተካሄደው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ በምርኩዝ ዝላይ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው የአማራ ክልል አትሌት አበበ አይናለም ወደ ውድድር የመጣው ለስፖርቱ በሚያስፈልግ መሣሪያና ቁሳቁስ ልምምድ አድርጎ አይደለም። ለዝላይ የሚሆን ምርኩዝም ይሁን ፍራሽ ባለመኖሩ ከነጭራሹ ልምምድ ሳያደርግ በራሱ ጥረት ወደ ውድድር እንደመጣም ይናገራል።
በውድድሩ ብቁ የሆነ አሰልጣኝ ካለመኖሩ በተጨማሪ እሱ በሚሰለጥንበት ክለብም ይሁን በሌሎች ምርኩዝ ዝላይ እንደ ተጨማሪ ውድድር ከመታየት በዘለለ በዋናነት ስልጠና የሚሰጥበት አካል እንደሌለም ያብራራል። አበበ በሚወዳደርበት አማራ ክልል ለምርኩዝ ዝላይ ስልጠና የሚሆኑ ቁሶች የሚገኙት በባህርዳር ኢንተርናሽናል ስቴድየም ነው። እዚህ ስቴድየም እሱና የክለብ ጓደኞቹ ልምምድ ለመሥራት ቢፈቀድላቸውም የሚከፈላቸው ገንዘብ ባህርዳር ላይ እየኖሩ ለመሥራት አይፈቅድ ላቸውም። ስለዚህም ክለቡ ባለበት ሌላ ከተማ ለመኖር ይገደዳሉ። አሁንም በዚህ ውድድር ላይ ያላቸው ተስፋ በመሟጠጡ ወደ ሩጫ ለመግባት እንደተዘጋጁ ይናገራል።
በአሰላው ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው የኦሮሚያ ክልሉ አብዲሳ በዳሶም የአማራ ክልሉ አትሌት አበበ የገለፃቸው ችግሮች እነሱ አካባቢም መኖሩን በመግለፅ ሃሳቡን ይጋራል። አትሌት አብዲሳ አሰልጣኝና ክህሎቱ ቢኖርም መሣሪያ ባለመኖሩ ብቻ ከአቅም በታች ለመዝለልና ችሎታቸውን አውጥተው ለመጠቀም እንደሚቸገሩ ይናገራል። ነገ ግን መሣሪያው ተሟልቶ የተሻለ ነገር ይመጣል በማለት በተስፋ ይጠባበቃል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ በአሰላው የወጣቶች ቻምፒዮና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች የሚያረካ ነገር እንዳልተመለከቱ አልሸሸጉም። ሁሉም አካላት በመካከለኛና ረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ ትኩረት እንዳደረገ በመግለፅም ፌዴሬሽኑ እንዲያውም ዘንድሮ በተሻለ መልኩ ለሜዳ ተግባራት ውድድሮች ትኩረት ሰጥቶ ምርኩዝ ዝላይ የወጣቶች ቻምፒዮና ላይ እንዲካተት አደረገ እንጂ ከዚህ ቀደም ውድድርም እንደማይደረግ ያብራራሉ። ክልሎችና ክለቦች መሣሪያ ስለሌላቸውም ተዘጋጅተው ስለማይመጡ የሚሰጠው ትኩረት ትንሽ ቢሆንም አሁን እንደ ሙከራ ውድድር መጀመሩ ወደ ፊት ተጠናክሮ በተሻለ መንገድ ለመምጣት ያግዛልም ይላሉ።
ዝላይና ውርወራ ውድድሮች ላይ የሚታዩ መሰረታዊ የቴክኒክ ስህተቶች እንዲሁም ተስፋ የማይሰጡ ሁኔታዎች ከመለማመጃ መሣሪያ ዕጦት የተነሳ መሆኑ ሊያስማማ ይችላል። ምክንያቱም መሣሪያ በሌለበት ሁኔታ አትሌቶች ልምምድ ሳይሰሩ ውድድሮች ላይ ከየትም አምጥተው ተስፋ ሰጪ ነገር ሊያሳዩ አይችሉም። ይህ ግን የሚያስማማው በተለይም ለከፍታና ምርኩዝ ዝላይ ነው። ምክንያቱም ምርኩዝ ከሌለ ምርኩዝ ዝላይ ሊኖር አይችልም። ዘሎ ማረፊያ ፍራሽ በሌለበት ከፍታ ዝላይም አይኖርም። ይሁን እንጂ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ መሣሪያዎችን ወይንም ምንም አይነት መሣሪያ በማይጠይቁ የውርወራ (ዲስከስ፤ አሎሎ፤ ጦርና መዶሻ) የአጭር ርቀት ውድድሮች ላይ ተመሳሳይ አይነት የቴክኒክ ስህተቶች እንዴት ከጊዜ ወደ ጊዜ አይሻሻሉም?። ይህ ጥያቄ ዞሮ ዞሮ ጣታችንን ወደ አሰልጣኝና ስልጠና ሂደት ላይ እንድንቀስር ያደርጋል።
የቴክኒክ ዳይሬክተሩ አቶ ዱቤም በሜዳ ተግባራትና በአጭር ርቀት አሰልጣኞች ችሎታና አቅም ላይ እምነት እንደሌላቸው በመግለፅ ይህን ሃሳብ ያጠናክራሉ። እንኳን በክልልና ክለብ ደረጃ በብሔራዊ ደረጃም ብቁ የሰለጠነ ኃይል እንደሌለ ያስቀምጣሉ። እነዚህ ውድድሮች የቴክኒክ ውድድሮች እንደመሆናቸው ብዙ ልፋት እንደሚጠይቁ የሚናገሩት አቶ ዱቤ ከልምምድ መሣሪያዎችና ጅምናዚየም በተጨማሪ በነዚህ ስፖርቶች የሰለጠነ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ። ለዚህም ፌዴሬሽኑ እቅድ አውጥቶ የውጪ አሰልጣኝ እስከ መቅጠር ሙከራ ቢያደርግም በተለያዩ ምክንያቶች እንዳልተሳካ ያብራራሉ። ወደ ፊት ግን አጠናክሮ በመቀጠል በነዚህ ውድድሮች ላይ ለመሥራት የተጀመረው ጥረት እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
ከፍታና ምርኩዝ ዝላይ መሣሪያዎቹ የሚያስፈልጉ ቁሶች ውድ መሆናቸው ይነገራል። በብዙ ነገር ተደራጅቷል የሚባለው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እንኳን ይሄ መሣሪያ እንደሌለው ይታወቃል። አካዳሚው በአጭር ርቀት ትንሽም ቢሆን ተስፋ የሚሰጥ ሥራ እያከናወነ የሚገኝ ቢሆንም የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ላይ በአገር ደረጃ ለተለያዩ ክለቦች ስፖርተኞችን መመገብ እንጂ በትልቅ ደረጃ አገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ ብዙ ውስንነቶች እንዳሉበት አይካድም። በተለይም አሰላ በሚገኘው የአካዳሚው ካምፕ መሣሪያ በማይጠይቁት የሜዳ ተግባራትና የአጭር ርቀት ውድድሮች የተሻለ ነገር ማሳየት የሚችልበት መሰረተ ልማት እንዳለ ይታመናል። ይህንን በተገቢው መንገድ ተጠቅሞ በታላላቅ መድረኮች አገርን የሚወክሉ አትሌቶችን በብዛት ለማፍራት ግን አሰልጣኞቹንና የስልጠናውን ሂደት መፈተሽ ይገባዋል። አካዳሚው ብቻም ሳይሆን ሌሎች አገር አቀፍ ፕሮጀክቶችም ይህ ይመለከታቸዋል።

 

የዓለም ዋንጫ በቁጥሮች ሲገለፅ

 

ቁጥር አንድ ተወዳጁ የዓለማችን የስፖርት መድረክ፤ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የዓለም ህዝብ በጉጉት የሚጠብቀውና እኛም ኢትዮጵያውያን ክረምቱን የምናጋምስበት የአንድ ወር ቆይታ ለማድረግ ከፊታችን ይጠብቀናል። ስለዚህ ተወዳጅ መድረክ መገናኛ ብዙሃንም ብዙ እየተናገሩና እየፃፉ ይገኛሉ። የዓለም ዋንጫው ከቁጥሮች ጋር በተያያዘ ያለው እውነታና ስታስቲክስ እንደሚከተለው ይገለፃል።

ተወዳጁ የዓለም ዋንጫ ሊጀመር ስድስት ቀናት ይቀሩታል፤


21 – የ2018 የዓለም ዋንጫ ሲካሄድ ለሃያ አንደኛ ጊዜ ሲሆን አስተናጋጇ ሩሲያም ይህን ታላቅ ውድድር በማሰናዳት የመጀመሪያዋ ምስራቅ አውሮፓዊት አገር ሆናለች።
12 - ሩሲያ ይህን የዓለም ዋንጫ በአስራ አንድ የተለያዩ ከተሞቿ የምታስተናግድ ሲሆን አስራ ሁለት ስቴድየሞችን አሰናድታለች። ከነዚህ መካከልም አምስቱ አዲስ የተገነቡ ሲሆን ቀሪዎቹ እድሳት የተደረገላቸው ናቸው።
1930 -የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ የተካሄደው እ.ኤ.አ በ1930 ሲሆን አስተናጋጇም ደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ዩራጓይ ነበረች። ዩራጓይ ይህን ዋንጫ አርጀንቲናን አራት ለሁለት በሆነ ውጤት አሸንፋ ማንሳቷ ይታወቃል።
5 – ደቡብ አሜሪካዊቷ የእግር ኳስ አገር ብራዚል በዓለም ዋንጫ ታሪክ ስኬታማዋ ነች። ብራዚል እ.ኤ.አ 1958፤1962፤1970፤1994ና 2002 ላይ አምስት ጊዜ ቻምፒዮን በመሆን የሚስተካከላት አገር የለም።
32 – የዘንድሮው የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ሰላሳ ሁለት አገራትን የሚያፋልም ሲሆን እነዚህ አገራት በስምንት ምድቦች ተከፋፍለው የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን ጨምሮ ስልሳ አራት ፍልሚያዎችን ያስኮሞኩሙናል። የዓለም ዋንጫ በዚህ መልኩ መካሄድ የጀመረው እ.ኤ.አ ከ1998 ጀምሮ ሲሆን ወደ ፊት በ2026 የተሳታፊ አገራት ቁጥር አርባ ስምንት እንደሚሆን ፊፋ ማሳወቁ ይታወሳል።
209 – በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለት መቶ ዘጠኝ አገራት የተካፈሉ ሲሆን ይህም ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። ከነዚህ አገራትም ማጣሪያውን ማለፍ የቻሉት ሰላሳ ሁለት አገራት ናቸው ለዓለም ዋንጫው ቀርበው የምናያቸው።
3 – ብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉሥ ፔሌ ሦስት የዓለም ዋንጫዎችን በማንሳት ብቸኛው ተጫዋች ሲሆን እ.ኤ.አ 1958፤1962ና 1970 ላይ እነዚህን ዋንጫዎች ማንሳት ችሏል። ይህንንም ክብረወሰን እስካሁን የተጋራው አንድም የዓለማችን ኮከብ አልተገኘም።
8 – ላስሎ ኪስ ኤል ሳልቫዶር ላይ በስምንት ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር በዓለም ዋንጫ ታሪክ ፈጣን ሃትሪክ የሰራ ተጫዋች ሆኖ ይታወሳል።
5 – የሜክሲኮው ኮከብ አንቶኒ ካርቫሃል እ.ኤ.አ ከ1950-1966 ለብሔራዊ ቡድኑ ተሰልፎ የዓለም ዋንጫ ላይ የተጫወተ ሲሆን ጀርመናዊው ሉተር ማቲያስ እ.ኤ.አ ከ1982-1998 አምስት የዓለም ዋንጫዎች ላይ በመጫወት የሚስተካከላቸው የለም። በተለይም ሉተር ማቲያስ ሃያ አምስት የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን በመሰለፍ የሚስተካከለው የለም።
17 ዓመት ከ 41 ቀን – በዓለም ዋንጫ በዕድሜ ትንሹ ተጫዋች የታየው የሰሜን አየርላንዱ ኖርማን ዋይትሳይድ አስራ ሰባት ዓመት ከአርባ አንደኛ ቀኑ ላይ በመጫወት ነው። 43 ዓመት ከ 3 ቀን – በዓለም ዋንጫ ታሪክ በዕድሜ አንጋፋው ተጫዋች የተጫወተው ኮሎምቢያዊው ፋሪድ ሞንድራገን ሲሆን የዓለም ዋንጫን በአርባ ሦስት ዓመት ከሦስት ቀኑ መጫወት ችሏል።
42 ዓመት ከ 1ወር ከ8 ቀን – ካሜሩናዊው ታሪካዊ ኮከብ ተጫዋች ሮጀር ሚላ በአርባ ሁለት ዓመት ከአንድ ወር ከስምንት ቀኑ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ላይ ግብ በማስቆጠር አንጋፋው ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ይታወሳል።
16 – ጀርመናዊው ሚሮስላቭ ክሎስ በዓለም ዋንጫ አስራ ስድስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የሚስተካከለው የለም። ክሎስ ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን እነዚህን ግቦች ያስቆጠረው እ.ኤ.አ ከ2002 አንስቶ እስካለፈው የብራዚል 2014 የዓለም ዋንጫ ሲሆን ከብራዚሉ የዓለም ዋንጫ በፊት ይህ ክብረወሰን በሮናልዶ ሊውስ ናዛሪዮ ዴሊማ (ኤልፊኖሚኖ) የተያዘ እንደነበር ይታወሳል።
8 – እስካሁን በተካሄዱት ሃያ የዓለም ዋንጫዎች ቻምፒዮን መሆን የቻሉት ስምንት አገራት ብቻ ናቸው። ዩራጓይ፤ ጣሊያን፤ ብራዚል፤ እንግሊዝ፤ ጀርመን (ምዕራብ ጀርመንን ጨምሮ) አርጀንቲና፤ ፈረንሳይና ስፔን ናቸው።
13 – በአንድ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ እ.ኤ.አ ፈረንሳዊው ጀስት ፎንቴን እ.ኤ.አ 1958 ላይ አስራ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በአንድ ጨዋታ ብዙ ግብ የማስቆጠር ክብረወሰኑን ይይዛል።
1 – በዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ታሪክ አንድ ተጫዋች ብቻ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሃትሪክ መሥራት ችሏል። ይህም እ.ኤ.አ 1966 እንግሊዝ ምዕራብ ጀርመንን ረታ ብቸኛውን ዋንጫ ባነሳችበት ጨዋታ ሲሆን ግቦቹን ያስቆጠረውም ጊኦፍ ኸረስት ነበር።
1 - ጣሊያናዊው ቪቶሪዮ ፖዞ በአሰልጣኝነት ሁለት የዓለም ዋንጫ ክብሮችን በማንሳት ብቸኛውና የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል።
2 - በዓለም ዋንጫ ታሪክ በቀይ ካርድ ሁለት ጊዜ ከሜዳ የወጡ ተጫዋቾች ሁለት ናቸው። ካሜሩናዊው ታሪካዊ ተከላካይ ሪጎበርት ሶንግ የመጀመሪያው ሲሆን ፈረንሳዊው ኮከብ ዚነዲን ያዚድ ዚዳን ሌላኛው ተጫዋች ነው።
38 - በዘንድሮው የሩሲያ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን ሰላሳ ስምንት ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ተሸላሚ ይሆናል። እንደ አጠቃላይ ግን በዚህ የዓለም ዋንጫ አራት መቶ ሚሊየን ዶላር ለሽልማት ተዘጋጅቷል።
12 - ሩሲያ ይህን የዓለም ዋንጫ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ያወጣችው ገንዘብ አስራ ሁለት ቢሊየን ዶላር ይገመታል።

ቦጋለ አበበ

 

Published in ስፖርት
Saturday, 09 June 2018 17:23

ገዥዎችም ይገረፉ!

እስኪ ሳንወሻሽ ሕገ ወጥ ዕቃ ገዝተህ አታውቅም? አንችስ ቢሆን ገዝተሽ አታውቂም? ምነው ባለፈው መገናኛ ሱሪ ስታማርጭ አላየሁሽም? ካልተወሻሸንማ ብዙዎቻችን ሕገ ወጥ ዕቃ ገዝተን እናውቃለን፡፡ በነገራችን ላይ ደንብ አስከባሪዎች ላይ አንድ ቅሬታ አለኝ፡፡ ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ለመከላከል ልጆቹን እያራወጡ ሲገርፉ አይታችኋል አይደል? እንግዲህ ይሄ ደንባቸው ከሆነ ሻጮችን ብቻ ሳይሆን ገዥዎችንም ይግረፉ፡፡ ሁሉም የሚሰራው ለጥቅሙ ነው፤ ገዥዎች ለቅናሽ ዋጋ ብለው ሲገዙ ሻጮችም የሚሸጡት ግብር ሳይከፍሉ ለማትረፍ ነው፡፡ እናም ጥፋቱ የሻጮች ብቻ አይደለም፤ ስለዚህ የደንብ አስከባሪዎች ግርፋት ፍትሃዊ ስላልሆነ ሻጮችም ይገረፉ (ሰው እንዴት ግረፉኝ ብሎ ይለምናል?)

እኔማ እኮ ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ባለበት መንገድ ባለፍኩ ቁጥር ሊዠብጠኝ ነው እያልኩ ሰቅጥጥ እላለሁ (አያችሁ ገዥም መገረፍ እንዳለበት አምናለሁ ማለት ነው)፡፡ ቆይ ግን ከዚህ ሁሉ ሥጋት፤ ከህሊናም ወቀሳ ምናለ ህጋዊ ዕቃ ብገዛ? ያው መቼም ምክንያቱ ይገባችኋላ፤ ነገሮች ሁሉ ዋጋቸው ዕለት ከዕለት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ሻጮችም ለምን እንደዚህ ሆነ ሲባሉ ‹‹እኛም እኮ በውድ ነው የምናመጣው፤ በዚያ ላይ ግብር አለ፣ የቤት ኪራይ ውድ ነው›› የሚሉ ምክንያቶችን ይሰጣሉ፡፡ ልክ ናቸው ለእነርሱም ውድ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ጋርም እልህ እየተጋቡ ነው፡፡ ‹‹እኛ የቤት ኪራይ እየከፈልን፣ ግብር እየከፈልን፣ ጥራት ያለው ዕቃ እየሸጥን፣ ሰው ግን የሚገዛው ከጎዳና ላይ ነው›› እያሉም ይማረራሉ፡፡ እንግዲህ ይህን ችግር ማን ይፍታው? እስኪ አስቡት! አንድ ባለቡቲክ በቤት ኪራይና በግብር ተማሮ ሥራውን ተወው እንበል፡፡ በዚህ ሰው ሥራ ማቆም ተጎጂው ማነው? ተጎጂ ሰውየው ብቻ አይደለም፡፡ መንግሥት ተጎድቷል፤ ሕዝብ ተጎድቷል፡፡ ግብር ከፋይ የለም ማለት መንግሥት አቅም የለውም ማለት ነው፤ መንግሥት አቅም የለውም ማለት ደግሞ ህዝብ አቅም አጣ ማለት ነው፡፡ መቼም የሕገ ወጥ ነገር መጨረሻው ይሄው ነው፡፡
ኧረ ከዚህ በላይ የሚያንገበግበኝ አንድ ችግር ልንገራችሁ (ያው እንግዲህ በገዛ እጄ ያደረኩት ነው)፡፡ አንድ ቀን እንዲህ ሆነላችሁ (ጉዴን ላለመዘርዘር እንጂ አንድ ቀን ብቻ እኮ አይደለም)፡፡ ጨለማን ተገን አድርጌ ሱሪ ልገዛ ወጣሁ፡፡ ኧረ ምን ሱሪ ብቻ! እግረ መንገደንም ጫማ፣ ቀበቶ… በቃ ብዙ ነገር ገዛሁ፡፡ እንዲያው በቀላል በቀላል ዋጋ አገኘሁ ብየ እየሰበሰብኩ በፌስታል፡፡ ደግሞ እኮ ዕቃ ስገዛ ችግር አለብኝ፡፡ የገዛሁትን ልብስ እንኳን በልኬ መሆኑን የማየው ከቤት ገብቸ ነው፡፡ እንግዲህ ከህጋዊ ሱቅ ቢሆን ባይሆን ቀይርልኝ ተብሎ መለማመጥም ይቻል ነበር (መለማመጥ ያልኩት የተሸጠ ዕቃ ቀይሩኝ ማለት ነውር ስለሆነ ነው)፡፡
ከጎዳና ላይ ወደገዛኋቸው አልባሳት እንመለስ! ጥሩ ልብስ እንደገዛ ሰው ከቤት ገብቼ እስከምለካው ቸኮልኩ፡፡ አዲስ ልብስ እንደተገዛለት ሕፃን ልጅ በችኮላ ገብቼ መለባበስ ጀመርኳ፡፡ መጀመሪያ ሱሪውን ለበስኩ፡፡ መርዘምና ማጠር እኮ ችግር አልነበረውም፡፡ እጄን ከኪሱ ስከት የተገነጣጠለ ኪስ፡፡ ግደለም ዕቃዎችን በቦርሳ እይዛቸዋለሁ ብየ ተፅናናሁና ቁጭ ስል ስፌቱ ብትን! ግለደም አዲስ ስለሆነ ነው ይሰፋል አልኩና ወደጉልበቴ አካባቢ ሳይ የመጨረሻውን ቁርጤን ነገረኝ፡፡ ሱሪው ለፋሽን በሚመስል መልኩ ሌላ ተደራቢ ጨርቅ ነው በማስቲሽ የተጣበቀ፡፡ ለካ ንዴት ሲበዛ ያስቃል፤ በሥራዬ ተክ ብየ ሳቅኩ፡፡
እስኪ ደግሞ ጫማው ይሞከር! ጫማውን ለመጫመት ማሰሪያውን ፈታ ፈታ አድርጌ ወደ እግሬ ከተት ሳደርግ የጫማው የላይኛውና የታችኛው ክፍል ቀስ እያለ መለያየት ጀመረ፡፡ እንደምንም አጠለቅኩት፡፡ ስነሳ ሲላቀቅ፣ ስቀመጥ ሲላቀቅ፤ አይቼ ጨርሼ ሳወልቅ የጫማው የታችኛውና የላይኛው ገበር ተላቆ ጨረሰ! በቃ ምን ልበላችሁ የገዛሁት ዕቃ ሁሉ ክስረት ሆኖ ቀረ፡፡
ታዲያ ይሄ ችግር ለማን ይነገራል እንግዲህ? እነሱም መሸጡን አልተውትም፤ እኛም መግዛቱን አልተውነውም፤ ከደንብ አስከባሪዎች እያራወጡ መግረፍ የተሻለና መሰረታዊ ለውጥ መምጣት አለበት፡፡ በቃ ሁሉም ሰው ይህን ነገር መከላከል አለበት!
በነገራችን ላይ ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን በመከላከል የሰሞኑ ዝናብ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ እንዲያውም ስወቅሰው የነበረውን አሁን አመስግኘዋለሁ፡፡ ‹‹ገጠር ቢሆን ኖሮ የበልግ እርሻ ይሆን ነበር፤ ደግሞ አዲስ አበባ ምን ይሰራል!›› እያልኩ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ዝናብ ጠቀሜታው ሕገ ወጥ ንግድን ማስተጓጎል ነው፡፡ በእውነት የደንብ አስከባሪዎች ራሱ የዝናቡን ያህል መከላከል አልቻሉም፡፡ አሁን ሲዘረጉ ወዲያው ይዘንባል፤ ሲሠበስቡ ያባራል፤ አሁንም የለም ብለው ሲዘረጉ ድንገት ያወርደዋል፡፡ በዚህ ምርር ብለው አንዳንዶች ጠቅለው የሚገቡ ሁሉ አሉ፡፡
ኧረ ቆይ የሰሞኑ ዝናብስ ከዚህም በላይ ያስወራል፡፡ በእርግጥ ስለዝናቡ ብናወራም ከንግድ አንወጣም፡፡ የሰሞኑ ዝናብ ብዙ የማልፈልገውን ነገር አስገዝቶኛል፡፡ መንገድ ላይ እያለሁ ከጀመረ የግድ መጠለል አለብኝ፡፡ ለመጠለል ደግሞ የሆነ ቦታ መግባቴ ነው፡፡ እስኪ ጤናዬንም ኪሴንም በማይጎዳ መልኩ ይሁን ብየ ካፌ ውስጥ እገባለሁ፡፡ ሻይ ልጠጣ አስቤ የነበረው ወደ ማኪያቶ ያድጋል፡፡ እየጠጣሁ ደግሞ የሚበላ ነገር ማዘዝ ያምረኛል፤ ዳቦ አስቤ የነበረው ወደ ኬክና በርገር ያድጋል (ይቺ እንኳን ውሸት ናት!)፡፡
በዝናቡ ምክንያት ድንገት ዘልየ ቡቲክ ውስጥም ልገባ እችላለሁ፡፡ ቡቲክ ውስጥ ገባሁ ማለት እንግዲህ የሆነ ነገር ያምረኛል ማለት ነው፡፡ በተለይ የደመወዝ ሰሞን ከሆነማ ተውኝ! የሆነች ሱሪ ላይ ቀልቤ ካረፈ ያለ ዕቅድ ልገዛት እችላለሁ፡፡ አያችሁ አይደል የሰሞኑ ዝናብ የሰራውን ሥራ? እኔን በግድ ከቡቲክ ውስጥ ልብስ አስገዛ፤ ሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን ደግሞ አስተጓጎለ፡፡ ዝናቡማ የሆነ ምሥጢር ሳይኖረው አይቀርም፡፡
የሆነው ሆኖ ግን የደንብ አስከባሪዎች ምን ለውጥ አመጡ? እንደኔ እንደኔ ምንም ለውጥ አላመጡም፡፡ ከአዟሪዎች ጋር ድብብቆሽ ሲጫወቱ ነው የሚውሉት፡፡ አንዳንዴ እኮ ያስቃሉ (እንኳን ተመልካቹ አዟሪዎች ራሱ ይስቃሉ)፡፡ ደንብ አስከባሪዎችና አዟሪዎች እየተያዩና እየተሳሳቁም ይተላለፋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ‹‹መጣንላችሁ ተዘጋጁ›› የሚሉም ይመስላሉ፡፡ ከርቀት ሆነው ብትራቸውን ይቃጣሉ፤ አዟሪዎችም ሸራዋን ጠቅለል አድርገው መልሰው እዚያው ይዘረጉታል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ያሳዝኑኛል፡፡ የሆነ ልብስ ከአንድ ደንበኛ ጋር እየተከራከሩ ድንገት ደንብ አስከባሪዎች ሲመጡ ጥለውት ይሸሻሉ፡፡ ልብስ ገዥው ብቻውን ይቀራል፡፡ ያው እንግዲህ ካዘነለት ደንብ አስከባሪዎቹ ሲያልፉ ይሰጠዋል ማለት ነው፡፡ ይህኔ እኮ የማይገዛውን ነው ልጁን ጨምሮ የሚያስተጓጉለው፡፡ መቼም ሕገ ወጥ ነው ብሎ ይዞበት የሚሄድም ይኖራል እኮ፡፡ በእርግጥ ስርቆት በህጋዊ ቡቲክ ውስጥም ያለ ነው፤ ግን ቢሆንም እንደጎዳናው ምቹ አይሆንማ!
አሁን እንግዲህ የደንብ አስከባሪዎች ሥራ ሻጮች ላይ ብቻ ሳይሆን ገዥዎችም ላይ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ ሻጮችም ላይ ይሁን ገዥዎች ላይ ግን ለውጥ የሚመጣው በደንብ አስከባሪዎች አይደለም፡፡ የሚያደርሰውን ጉዳት ሁሉም ሰው መገንዘብ ሲችል ነው፡፡

ዋለልኝ አየለ 

Published in መዝናኛ
Saturday, 09 June 2018 17:21

ከልመና ወደ ሽመና

እማሆይ ጻድቃን አርአያ ነጋ ጠባ ለልመና እጃቸውን ዘርግተው የእለት ጉርሳቸውን፣ የሌሊት ልብሳቸውን ያገኙ ነበር። በ2000 ዓ.ም የፍሬ ገዳም የሽመና ማህበር ተቋቁሞ አባል ከሆኑ በኋላ ግን ይሄ የህይወት መስመራቸው ሰርቶ ወደ መለወጥ ተቀይሯል። ዛሬ ለሚበሉት፣ ለሚጠጡትና ጋደም ብለው ጎናቸውን ለሚያሳርፉበት አያስቡም። ጠዋት ተነስተው ወደ ስራ መሄድ ብቻ ሳይሆን የኔ የሚሉትም ሙያ ባለቤት ሆነዋል።
ትናንት ከመንገድ ዳር ውሏቸውን ከአላፊ አግዳሚው ምጽዋት ይጠብቁ የነበሩት እማሆይ ጻድቃን ከዓመታት ጥረት በኋላ የእሳቸው የእጅ ፍሬና ላብ ሌሎችን ሲመግብ በማየታቸው እጅግ ተደስተዋል።
«እንኳን ሰልጥኜ የዛሬን ቀን ለማየት በቃሁ እንጂ ከዚህ በኋላ በምንም ተአምር ሙሉ አካሌን ይዤ ወደ ልመና አልገባም። ነገ ደግሞ የተሻለ ጊዜ እንደሚሆን እተማመናለሁ» ይላሉ እማሆይ ጻድቃን ለዓመታት ያሳለፉትን ጊዜ በምልሰት እያስታወሱ። «ሰው ከቸገረው መለመኑ አይቀርም ነገር ግን ሁሉም የሚለምነው አማራጭ አጥቶ ነው ማለት አይቻልም። አለማወቅ ረጅም ዘመን ተጋርዶብን ቆይቷል። አሁን ሁሉን ለማየትና ለማስተዋል እድሉን አግኝተናል። መጽሀፉም የሚለው 'የማይሰራ አይብላ' ነው ሰርቶ መብላት ታላቅ ደስታን የሚሰጥ ክብር ነው» ይላሉ።
«ፍሬ ገዳም በአለት ላይ የበቀለ እህል ነው» የሚሉት የማህበሩ ሊቀ መንበር ወይዘሪት ገነት ገብረ ስላሴ ናቸው። የማህበሩ መመስረት መስራት እየቻሉ መስራት ያልቻሉትን ምን ያህል እንደለወጠ ይናገራሉ። የማህበሩን አመሰራረትና ውጣ ውረድ የበዛበት ጉዞ እንዲህ ያስታውሳሉ።
«ማህበሩ በ2001 ዓ.ም በሁለት መቶ ብር መነሻ ስራውን ጀመረ። በወቅቱ ብሩ በቂ አልነበረም ግን ከበስተጀርባ ትልቅ አላማ ነበረን። አላማችን ደግሞ መስራት እየቻሉ የተቀመጡና ለስራና ለጥበብ የሚውሉ እጆቻቸውን ለልመና የሚዘረጉትን መታደግ ነው። ለግባችን መሳካትም ' ከልመና ወደ ሽመና ' የሚል መሪ ቃል ይዘን ረጅሙንና አሰልቺውን ጉዞ ጀመርነው። በአባልነት ያካተትናቸው ሁሉም ሴቶች ሲሆኑ አብዛኛዎቹ ደግሞ ዓለም በቃኝ ብለው የመነኮሱና በልመና የሚተዳደሩ፣ እድሜያቸውም ከወጣትነት ያለፉ ነበሩ» ሲሉ ያስታውሳሉ።
ወይዘሮ ገነት እንዳሉት አባላቱ ጥሪት ያልነበራቸው፣ የእለት ጉርሳቸውንም ከመፅዋች ጠባቂ የነበሩ፣ ለመስራት ጉልበት ቢኖራቸውም ሙያ ያልነበራቸው ናቸው። ግን ሁሉም እያንገሸገሻቸው ከኖሩበት ተመጽዋችነት ለመውጣት ቆራጥ አቋም ነበራቸው። ዛሬ የሚያቀላጥፉት የሽመና ስራ ያኔ ለእነሱ ፍጹም አዲስ ነገር ነው። ይሞክሩ የነበረውም ነጠላ ከመቋጨት የዘለለ አልነበረም። በማህበሩ ለሶስት ወራት የተሰጠውን ስልጠና አጠናቀው ስራ የጀመሩትም ቀላል በሚባለው የመነኮሳት ፎጣ ማምረት ነው። በወቅቱ ለአባላቱ በመንግስት በኩል የመነኮሳት ፎጣ ለማምረት የሚያስችል ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን በሴቶች ጉዳይ በኩል ደግሞ የማምረቻ ቦታ እንዲመ ቻችላቸው ተደርጓል።
ፍኖተ ብርሃን የህብረተሰብ እድገት በጎ አድራጎት ድርጅት የሚባል ምግባረ ሰናይ ድርጅት ደግሞ በነጻ የመሸጫ ቦታ አቅርቧል። እነዚህ እስካሁንም የዘለቁ የጅማሮ ድጋፎች አበረታች የነበሩ ቢሆንም የመነኮሳት ፎጣ በሚፈለገው ደረጃ በገበያው ተፈላጊ አልነበረም። ቀዳሚው የማህበሩ ፈተና የጀመረውም በዚህ ወቅት ነው።
አባላቱም ለምነው የእለት ጉርሳቸውን እንዳያገኙ፤ ስራ እየሰሩ ውለው ምርቱ በገበያ ተፈላጊ ባለመሆኑ ገቢ አላስገኘም። በዚህም የተነሳ ሲጀመር ሀያ ስምንት ከነበሩት የማህበሩ አባላት ሰርተን በማንለወጥበት ስራ ውስጥ ለምን እንቆያለን ብለው የተወሰኑት ወጡ። የቀሩትን አስራ ስድስቱን ይዘን አንድ ቤት ተከራይተን መኖር ጀመርን። በወቅቱ አንድም ፎጣ ሳይሸጥ ይውል ስለነበር ለእለት ጉርስ ከሚቀመስ ማጣት ጀምሮ በርካታ ፈተናዎችን አልፈናል። ነገር ግን በነዚህ ጊዜያት አላማችንን ይዘን ነገ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ ሁላችንም ተስፋ ሰንቀን እንደጋገፍ ነበር።ያኔ በ24 ሰአት አንዴ የምንበላት ምግብ ለሆዳችን ብቻ ሳይሆን ለተስፋችንም ስንቅ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሰናል።
ከረጅምዓመታት ልፋት በኋላ ህይወታችን እየተ ስተካከለ ኑሯችን እየዳበረ ሲመጣ ደግሞ ቃል በተገባባነው መሰረት ከኛ በባሰ የኑሮ ደረጃ የሚገኙትን ወደመርዳቱ ገብተናል። ዛሬ ከምናገኛት ጥቂት ትርፍ 16 ወላጅ አልባ ህጻናትንና ሰባት ረዳት የሌላቸው አዛውንቶችን እየረዳን እንገኛለን። ከነሱ በተጨማሪ በየዘርፉ ተቀጥረው የሚሰሩና የስራ እድል የተፈጠረላቸው አስራ ሁለት ተጠቃሚዎችም አሉ። ከእነዚህ መካከል በልመና፣ በስራ ፈትነትና አንዳንዶችም ተገቢ ባልሆነ ስራዎች የተሰማሩ ነበሩ። የስራ እድሉ የተፈጠረው ለአብዛኞዎቹ ተገቢው ስልጠና እየተሰጠ ሲሆን ጥቂቶች ደግሞ ቀድመው ከሽመና ስራ ጋር ልምድ የነበራቸው በመሆኑ በቀጥታ ማህበሩን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።
ዛሬም በልመና ስራ የተሰማሩ ስልጠናና ድጋፍ ቢሰጣቸው ራሳቸውን ለውጠው ለሌሎች የሚተርፉ እንዳሉ እናውቃለን። በመሆኑም የማምረቻ ቦታውን በማስፋፋት እንዲሁም ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እነዚህን ወገኖቻችንን የመታደግ ስራ ለመስራት ዕቅዱ አለን። እስካሁንም የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ በርካታ የተሞክሮ ልውውጦችን ስናደርግ ቆይተናል።
ማህበሩ በነበረው ስኬት ሁለት ዋንጫና ሁለት ሜዳልያ ለመሸለም በቅቷል። ሽልማቱ ብዙ ጥሪት ስላፈራን የተሰጠን ሳይሆን በሰፊው ስላሰብንና ያለንን አቅም በሙሉ ተጠቅመን ስለሰራን ነው። ከዚህም ውጪ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ሽልማቶችና ማበረታቻዎች አግኝተናል። በመንግስት በኩል አሁንም ድረስ በሀሳብም ፣በቁሳቁስም ድጋፍ ይደረግልናል። በኢግዚብሽንና ባዛር የገበያ ትስስር እንድናገኝ እንጋበዛለን። ውጤታችን ከምንጠብቀው አንጻር በቂ ነው ባንልም በደረስንበት ደረጃ ግን ደስተኞች ነን ይላሉ ወይዘሮ ገነት።
የፍሬ ገዳም የሽመና ማህበር የተጣለባቸውን አደራ የተወጡና በክልሉ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ለሌሎች አርአያ መሆን የሚችሉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የአክሱም ከተማ የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርዛፍ አበበ ናቸው። እንደ ኃላፊዋ ገለፃ ወደዚህ ስራ ተመልምለው ሲገቡ ይሄ እውቀት አላቸው የሚባሉ አልነበሩም። አሁን ግን በጥራትና በብዛት በማምረታቸው ብቻ ሳይሆን የገበያ ትስስርም የሚፈጥሩት በራሳቸው ጥረት ነው። ከጠባቂነት እየተላቀቁ ነው። በከተማዋ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሴቶች ቁጥር ብዙ ነው። በአንጻሩ ደግሞ ያለው በጀትና የቦታ አቅርቦት ውሱን ነው። በመሆኑም ቢሮው ዋና ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ሴቶቹ ባሉበት ደረጃ በቀላሉ ወደስራ እንዲገቡ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ ማስቻሉ ላይ ነው።
አንዳንዶቹ የመንግስትንም ሆነ የህብረተሰቡን እጅ የሚጠብቁት ሙሉ ለሙሉ መንገዱ ተዘግቶባቸው ሳይሆን በአካባቢያቸው ያለውንና ራሳቸውም ሊሰሩት የሚችሉትን የሚያመላክታቸው ባለመኖሩ ነው። የፍሬ ገዳም አባላት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። የአባላቱ ፅናት ከተደረገላቸው ድጋፍና ክትትል ጋር ተዳምሮ በቀላሉ ለሌሎች እስከ መትረፍ አብቅቷቸዋል ይላሉ።
ሃላፊዋ እንዳሉት ወደ ስራ የገቡት ሴቶች ዘላቂ ተጠቃሚ ለማድረግና ጥሪታቸውን እንዲያሳድጉ የዘወትር ክትትል ያደርጋል። አዳዲሶችን ወደ ስራ ለማስገባት ደግሞ ከምክርና ድጋፍ በተጨማሪ የስራ እድል ፈጠራና የብድር አመቻች ኮሚቴ ተቋቁሟል። አንዳንዴ ስራውም ፤ ስራ ፈላጊውም እያለ ሳይገናኙ የሚቀሩበት አጋጣሚ አለ። ስልጠና ወስደውም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ስራ ያልገቡም አሉ። እነዚህ ስራ ባለማግኘታቸው የሚያማርሩ ናቸው።
በመሆኑም ቢሮው በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰ ራው እነዚህን በማሰባሰብ ወደስራ ለማስገባት ይሆናል። በሌላ በኩል በቡድንም በግልም ሰርተው የተለወጡ አሉ ። በሁለቱም መንገድ ለሚመጡት ድጋፍ የሚደረግ ቢሆንም ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ስለሚመች የበለጠ ትኩረት የሚሰጠው ግን በማህበር ተደራጅተው ለሚመጡት ነው። በማህበር መደራጀታቸው ለብድር አገልግሎት ዋስትና ለመስጠት ለቦታ አቅርቦት እርስ በእርስ ተሞክሮና ልምድ ለመለዋወጥ የተሻለ እድል ይሰጣል ብለዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

Published in ማህበራዊ

የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)ን ከመሰረቱት አንጋፋ ፖለቲከኞች_ አንዱ ናቸው፡፡ ፓርቲውን ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት፣ በዋና ፀሐፊነትና በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል። ከሦስት ዓመት በፊት ከፓርቲው ቢለቁም በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን ከመስጠት፤ አገራዊ በሆኑ የውይይት መድረኮች ላይ ከመሳተፍ አልተቆጠቡም አቶ ሙሼ ሰሙ። አሁን ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያም ቃለምልልስ አድርገናል። መልካም ንባብ!
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በእርሶ ዕይታ ምን ይመስላል?
አቶ ሙሼ፡- የፖለቲካ ሁኔታው ሽግግር ላይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ገና የተጀመረ በመሰራት ላይ ያለ የፖለቲካ ሂደት ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ሂደት የተፈጠረው በሕዝቡ ነው። ሕዝቡ በተለያየ ጊዜ ውስጥ ሲከማቹበት የነበሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶቹ ከሚሸከመው በላይ ስለሆነበት መንግሥት የአቅጣጫ ለውጥ እንዲያመጣ በአመፅ መልክ ጠይቋል፡፡ መንግሥትም ይህንን በተለመደው መልኩ ሰላማዊ ሰልፎችንና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን በማዳከምና ከጨዋታ ውጪ ማድረግ የማይችልበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ በራሱ ለውጥ እንዲኖር አስገድዷል፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ድርጅታዊ ለውጥ እያካሄደ ነው፡፡ ድርጅታዊ ለውጡ ደግሞ እስከዛሬ ካየነው ለውጥ በይዘቱም ሆነ በባህሪው የተለየ ነው፡፡ ለውጡ ገና ጅምር ነው፡፡ ውጤቱ ደግሞ ወደ ፊት ይታያል፡፡ መዘንጋት የሌለበት ሕዝቡ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ያስገደደው መሆኑን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን በጅምር ደረጃ ያሉት ለውጦች እንዴት አዩአቸው?
አቶ ሙሼ፡- እስከ አሁን የሚታየው በጽሑፍ የቀረበ ቃልኪዳን ብቻ ነው፡፡ በተግባር የታየው የእስረኞች መፈታት ነው፡፡ ከኢህአዴግ አስቸጋሪ ባህሪ አኳያ ሲገመገም ቃል መገባቱ ብዙም የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የኢህአዴግ ታሪክ ወደ ኋላ ሲታይ ቃል የገባውን የማስፈፀም ብቃትም፣ አቅምም ሆነ ተነሳሽነት እንዲሁም ቁርጠኝነት ኖሮት አያውቅም፡፡ አሁን ግን እየተገቡ ያሉ ቃሎች እንዲፈፀሙ ያለው ፍላጎት መልካም ነው፡፡ ሌላው ተወደደም ተጠላ ኢትዮጵያ ላይ አንዣቦ የነበረው አስከፊ አለመረጋጋት፣ የደም መፋሰስና የዕልቂት ስጋት መብረዱ አንድ እርምጃ ወደፊት መባሉን ያሳያል፡፡
በተግባር የታየውም የእስረኞች መፈታት እንደትልቅ ለውጥ መቁጠር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የብዙ ነገሮች መሠረት ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ የሕዝቦችን አንድነት ለማምጣት ቂም፣ በቀልና ቁርሾን መርሳት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ መሠረትን መከተል ደግሞ የግድ ይላል፡፡ እንደየጥፋቱ ደረጃ፣ ሚዛንና ዓይነት ሰዎችን ይቅር ብሎ ማህበረሰቡን እንደገና እንዲያገለግሉ ዕድል መስጠት ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ በአጠቃላይ ስንመለከት ጉዳዮችን በቀናነት የማየት መንፈስ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ የሁሉ ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ነው ማለት አይቻልም፡፡
በኢህአዴግ በኩል ብዙ ለውጦች እንደሚኖሩ በመገለፅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለውጦቹ በንባብ በየስብሰባዎቹ እየተነገሩ ናቸው፤ በፖሊሲ ደረጃ ተካተው በአዋጅ በመመሪያ በደንቡ መሠረት ሲወጡ አልታዩም፡፡ ስለዚህ መተማመን የሚቻለው የተባለውን ለማስፈፀም አዋጅ ሲወጣ፤ ደንብ ሲሆኑና ወደ ተግባር ሲገባ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሕገመንግሥቱ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብን መገንባት ይገባል ተብሎ ቢቀመጥም፤ በተግባር ልዩነት ሰፊውን ድርሻ ወስዶ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር አንድነትን መስበክና በቃልም ቢሆን ብዙ ተግባራት እንደሚፈፀሙ መናገር ቀላል ነው?
አቶ ሙሼ፡- ከላይ እንደገለፅኩት ነው፡፡ ኢህአዴግ በተለምዶ የመጣበትን አብዮት ለመቀልበስ ሲፈልግ ቃል መግባት ተፈጥሯዊ መለያው ነው፡፡ ይህንን ላለፉት 27 ዓመታት አብረነው ስንኖር አይተነዋል፡፡ ነገሮች ከተረጋጉና ሁሉም ወደ የሥራውና ወደ ዕለት ተዕለት ሕይወቱ ካመራ በኋላ ወደ ነበረበት ይመለሳል፡፡ ኢህአዴግ የመጣው ይህንን ባህሪውን አድሶና ለለውጥ ተዘጋጅቶ ነው ከተባለ፤ ዕድል መሰጠቱ ትክክል ነው፡፡ በነበረ ታሪክ መውቀስና መክሰስ በቂ አይደለም፡፡ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ተነስቶ ቃል እየተገቡ ያሉት ነገሮች ሁሉ ወደ ተግባር ይሸጋገራሉ ብሎ ተስፋ ማድረግ ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱም ቃል እየተገቡ ያሉት ጉዳዮች በሦስትና በጥቂት ቀናት ውስጥ ዕውን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሂደትን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ ካለችበት ውስብስብ ችግር ኢኮኖሚውም ሆነ ፖለቲካዊ እንዲሁም ማህበራዊ ቀውስ ለማውጣት በጣም ብዙ ጉልበት ጊዜና ገንዘብ የሚጠይቅ ነው፡፡ መጀመሪያ ይህንን ለመለወጥ ፍላጎት መኖሩ በራሱ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ቃል ብቻ በቂ አይደለም የሚያስብለው አንዳንዴ ቃል የተገቡት ነገሮች ወደ ፖለቲካ ሊመነዘሩ የሚችሉ አይደሉም፡፡ መተባበር፣ መቻቻል፣ ቅድሚያ መስጠት፣ መፋቀር የሚባሉት ነገሮች ወደ መሬት ወርደው ለመተግበርና የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ ጊዜ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ የመግባቢያ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በሥራ ሊመነዘሩ አይችሉም፡፡ የሰውን ኑሮ ሊያሻሽሉና የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ዕውን ሊያደርጉለት አይችሉም፡፡ ዋናው ነገር እነዚህ በሕግ መረጋገጥ አለባቸው፡፡ በቃል የሚነገሩ ነገሮች ሕግ ስለማይሆኑ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ እነዚህ ነገሮች የሌላውንም ፍላጎት ይጠይቃሉ፡፡ ኢህአዴግ ይህን በማለቱ ብቻ ሌላው ሰው ይህን ይፈልጋል ማለት አይደለም፡፡
ሰሞኑን እንደተደረገው ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫን ማስቀመጥ ግን ተግባራዊ እርምጃ ነው፡፡ የአሁኑ ቃል ይለያል ከተባለ ሕጎች መመሪያዎችና ደንቦች እየፀደቁለት ወደ ተግባር መገባት ሲቻል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ምስቅልቅል ውስጥ በገባች ቁጥር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብሰባ ይጠራሉ፡፡ ድርድር ይደረጋል፤ ነገር ግን ድርድሮቹ የትም አልደረሱም፡፡ አሁን ለውጥ ካለ ሕጎችንም መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የፀረ ሽብር ሕጉ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ እንቅፋት ነበር፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የፕሬስ ሕጉም ሌሎችም ችግር የሆኑ ሕጎች በመለወጥ ቁርጠኝት መኖሩን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ጊዜው አጭር ነው፡፡ ለልጆቹ ዳቦ ማብላት የማይችል አባወራም ሆነ እማወራ ምን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አይታወቅም፡፡ ሥራ በጉጉት የሚጠብቀው በሚሊዮን የሚቆጠር ወጣት ነገ ከነገወዲያ ዝምብሎ ያያል ብሎ ማመን አይቻልም፡፡ አስቸኳይ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ የተወሰነ ጊዜ ማቆየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በፍጥነት ወደ ተግባር ገብቶ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ ችግሩ የሁሉም ችግር ይሆናል፡፡ ጉዳዩ ከኢህአዴግም አልፎ የመላው ሕዝብ ይሆናል፡፡ የሚፈጠረው ምስቅልቅል ለሁሉም ይተርፋል፡፡ ይህን በመወቃቀስ ብቻ መወጣትም አይቻልም፡፡
ስለዚህ በቀናነት መጀመሩና የሚታየው ተነሳሽነት ጥሩ መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ቀናነት፣ በጎነትና መቻቻል ወደ መሬት መውረድ አለባቸው፡፡ ተቋማት ላይ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መውጣት አለባቸው፡፡ ምህራኖች በጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ በሩን መክፈት፤ መድረኮችም በስፋት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ይሄ በጣም ከባድና ትልቅ ሥራ ቢሆንም ምርጫ የለም፡፡ አንዳንዴ ቃል የሚገባው ነገር እውነት የሚቻል ነው ወይ? የሚለውም ያጠያይቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ ተቃዋሚዎች ለድርድር የሚጋበዙት አገር ውስጥ ያሉት ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ውጪ ላሉትም በራችን ክፍት ነው እየተባሉ ነው፡፡ ለምሳሌ በነሌንጮ ለታ የሚመራው ኦዴግ ለድርድር ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል፡፡ ይሄ ምን ያሳያል?
አቶ ሙሼ፡-ለሁሉም ፓርቲዎች ጥሪ መቅረቡን አላውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለውን ለውጥ አገር ውስጥ ገብተን ብንጠቀምበት ያዋጣናል ብሎ በማሰብ ወደ አገር የገቡ አሉ፡፡ ነገር ግን እያንዳንዳቸው ፓርቲዎች የራሳቸው ሚዛን አላቸው፡፡ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ የሚያዩበት ዓይን ይለያያል፡፡ ከፓርቲው አስተሳሰብ፣ ከተፈጥሮ፣ ከተነሳበት ዓላማ ከሚያራምደው ፖለቲካ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ይጠቅመኛል፤ አገር ውስጥ ለመግባትም በር ይከፍትልኛል ብሎ ሊገባ ይችላል፡፡አገር ውስጥ ከገባ በኋላም ፓርቲውን ሕጋዊ አድርጎ ምርጫው ሲቃረብ ይወስናል፡፡
ሌሎችም በዚህ መልኩ ራሳቸውን ገምግመው የሚመጡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እየተወያዩም ያሉ ይኖራሉ፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከነበረበት የትግል ስልት ወጥቶ ወደ ሌላ የትግል ስልት የሚገባው ቁጭ ብሎ በጉዳዩ ላይ ውይይት አካሂዶ ነው፡፡ ስለዚህ ኦዴግም አሁን ያለውን ሁኔታ ገምግሞ በሰላማዊ መንገድ አገር ውስጥ ገብቼ የፖለቲካ ሥራ ብሰራ ውጤታማ እሆናለሁ ብሎ ወይም የዚህ ለውጥ አካል መሆን እንዳለበት ስላመነ ወደ አገሩ መጥቷል፡፡ በዚህም ለውጡ የበለጠ እየጠነከረ እና ሥር እየሰደደ ይሄዳል ብዬ አስባለሁ፡፡ የገቡት ሰዎች መደላድል ከተፈጠረላቸው ሌሎቹም ፓርቲዎች እምነት እያሳደሩ የጀመሩትን መንገድ ትተው የሚመጡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ስለዚህ አሁን ሥራ መሰራት አለበት፡፡ ይሄ ጅማሮ ነው፡፡
ደፍረው የመጡ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ቅስቀሳ ማድረግ እንዲችሉ መድረኩን ማስፋት፣ ዕድሉን መሥጠት፣ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ ሃሳባቸውን እንዲገልፁ ከሕዝቡ ጋር እንዲገናኙ በሩ ከተከፈተ ሌሎቹም ተማምነው ዋስትና አግኝተው ይመጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለሁሉም በጎ ነው፡፡ ማንም ሆነ ማን በጥይት የሚመጣ ለውጥ ዘለቄታዊ ለውጥ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ውጭ ስላሉ ተቃዋሚዎች ሲገልጹ በአሸባሪነት የተፈረጁት የነግንቦት ሰባት ክስ መቋረጥና የሌሎችም እስረኞች በይቅርታ መለቀቅን አስመልክቶ ሃሳብዎ ምንድን ነው?
አቶ ሙሼ፡- ለእኔ መጀመሪያም የፖለቲካ እስረኞች የተያዙበትና የታሰሩበት ሁኔታ ከመርህ አኳያ ትክክል ነው ብዬ ሰለማላምን እርምጃው በጎ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር ሕግና ሥርዓት አለው፡፡ የተለቀቁት በሕጉ መሠረት ነው ከተባለ በሕጉ መሠረት ስለመፈታታቸው መታወቅ አለበት፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ውዥንብር አለ፡፡
ሰዎቹ የተፈቱት ኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል የሁለቱ ኃይሎች ሽኩቻ ውጤት ነው፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ ማን አቅም እንዳለው ለማሳየት የሚያደርገው ጥረት ውጤት ነው ብሎ የሚያምን አለ፡፡ እነዚህን ሰዎች በመፍታት በሕዝቡ ዘንድ ይሁንታን ለማግኘት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ሕዝቡን ከሌሎች ተቃዋሚዎች ነጥሎ ለመውሰድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው የሚሉም መኖራቸው መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ የዕርቅ የመቻቻል ውጤት ነው ብሎ ለማረጋገጥ የፖለቲካ ሥራ መሰራት አለበት፡፡ በአግባቡ መረጃ ለሕዝቡ ሊደርሰው ይገባል፡፡
ሌላው የቅደም ተከተል ችግሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ክሳቸው የተቋረጡ ሰዎች የተከሰሱት በግለሰብነታቸው አይደለም፡፡ በፓርላማው አሸባሪ የተባለ ድርጅት አባል በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ በቅድሚያ ፓርላማው እነዛ ድርጅቶች አሸባሪ አለመሆናቸውን ማፅደቅ ነበረበት፡፡ ሥራ አስፈፃሚው መጀመሪያ ፓርላማው እንዲወስን ሳያደርግ ይህንን ውሳኔ መወሰኑ የሚጣረስ ነው፡፡ አለቃውና አዛዡ መለየት አለበት፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት ፓርላማው ነው፡፡ ፓርላማው አሸባሪ ያላቸው ድርጅቶች አሸባሪ አለመሆናቸው መጀመሪያ በፓርላማው ሳይፋቅ በፓርቲው ሲሳተፉ የነበሩ እስረኞች መፈታታቸው ከፓርላማው የሥልጣን ሂደት ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ድርጅቶችን የሚመሩት ሰዎች ነፃ ወጥተው ድርጅቱ አሸባሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ሥራ አስፈፃሚው ይህን ማድረግ አይችልም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ብዙ የአፈፃፀም ችግሮች አሉ፡፡ የይቅርታ ሂደቱ ግን በትክክል ተከናውኖ ሊሆን ይችላል፡፡
ለማንኛውም መንፈሱን በጥሩ መልኩ መውሰድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ አካሄድን ተከትሎ መፈፀሙ ሰዎች ላይ እምነት ያሳድራል፡፡ ዛሬ ሕጋዊ የሆነውን መንገድ ትቶ የሚፈፀም ተግባር ካለ ሰዎች ሌሎች ሕጎች ስላለመጣሳቸው ዋስትና የላቸውም፡፡ ዛሬ ሕጋዊ የሆነውን መንገድ ለበጎም ቢሆን ሲጣስ ነገ ደግሞ ለክፉ ተብሎም ሕጎች ሊጣሱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ሁሉንም የሚያስተሳስር ከፍቅርና ከአንድነትም ባሻገር የሕግ የበላይነት ያከባብራል፡፡
ኢህአዴግን ስንታገል የነበረው ሕግ እንዲያከብር ነው፡፡ ሌላው ሁለተኛ ነገር ነው፡፡ ሕግ ማክበር ማለት የሰዎች ሰብአዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሌሎችም መብቶች መከበር ማለት ነው፡፡ ለሕግ የበላይነት ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው በጎ ነገር ነው፡፡ ሲፈቱ ሕግን ማዕከል አድርጎ መንቀሳቀስ መተማመንን፤ ዕውቅና መስጠትን ያዳብራል፡፡ መንግሥት ሕግን ሲያከብር ሌሎች ሰዎችም ሕግን ለማክበር ድፍረት ይኖራቸዋል፡፡ ሕጋዊ መሠረት ተይዞ ከተለቀቁም ሕዝቡ ይወቅ፡፡ ይህንንም የሰራው አካል አካሄዱን የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ በውክልና የተሰጠውን ሥልጣን ሲጠቀም በሕግ መሠረት መሥራቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡
በተለይ ከሙስና ጋር ተያይዞ የተፈቱ ሰዎችን ጉዳይ ብዙዎች ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ ከወር እስከ ወር ከማያደርሰው ደመወዙ፣ ከጉሮሮው ላይ ነጥቆ ግብር የከፈለው ኅብረተሰብ የግብሩን ገንዘብ የበሉ ሰዎች ሲለቀቁ አሳማኝ ምክንያት መቅረብ አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ኅብረተሰቡ ተመልሰው ኅዝቡን እንዲጠቅሙ ማለት በቂ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህ ሌሎችም እንዲዘርፉ የሚያበረታታ ነው፡፡ ሰዎች እንዲህ አድርገው ከተፈቱ እኛም እንፈታለን የሚል ሃሳብን ሊፈጥር ይችላል፡፡
ፖለቲካ የአንድ ድርጅት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የአጠቃላይ የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ያንን በሚመጥን መልኩ መቅረብ አለበት፡፡ ሥራው ይሰራ ነገር ግን ስለሥራው በቂ ማብራሪያ፣ ትንታኔና ምክንያት ይሰጥ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ማንኛውም ተግባር ሲከናወን ሕግን መሠረት አድርጎ መንገዱንም ለሕዝብ አሳውቆ መሆን አለበት እያሉ ነው?
አቶ ሙሼ፡- አዎ! ሕዝቡን ማሳወቅ ማለት ፓርላማውን ማሳወቅ ማለት ነው፡፡ ፓርላማው የሕዝብን ውክልና የያዘ ነው፡፡ ፓርላማው መሠረታዊ ስትራቴጂካዊ ለውጦች ሲካሄዱ በቂ ግንዛቤ ሊኖረው እና ሕዝቡን እንዲያስተምር ይጠበቃል፡፡ የሁልጊዜ የኢህአዴግ ችግር ይሄ ነው፡፡ ኢህአዴግ ሌሎችን ረስቶ ጋሪና ፈረሱን ይዞ ይገሰግሳል፡፡ አሁንም የራሱን ብቻ ይዞ መንገዱን እየጠራረገ መሄድ ይፈልጋል፡፡ እንደዚያ ሊሆን አይገባም፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ክልሎች እያነጋገሩ ነው፡፡ ነገር ግን እዚያ ላይ የሚቀርቡት ነገሮች የተጠቃለሉ ናቸው፡፡ ይህችን አገር በአንድነት ስለማቆየት ነው፡፡ በእርግጥ በአጠቃላይ ከሕዝቡ ጋር መወያየት ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለሙያዎችን እንዲወያዩበት ማስቻል ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኤርትራን አስመልክቶ የሰጠውን የውሳኔ ሃሳብ እንዴት ተመለከቱት?
አቶ ሙሼ፡- ኤርትራን በሚመለከት የተወሰደው አቋም ይደገፋል። ዕድሜ ልክ ሰላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ መፍትሔ የሌለው ችግር ይዞ ኢኮኖሚውን በሚያላሽቅ መልኩ ተንጠልጥሎ መኖር ተገቢ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ በመረጠው መድረክ በፍርድ ቤት ሂደት ተሸንፏል፡፡ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚያስተናግድበትን መንገድ መፈለጉ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ መራዘም አልነበረበትም፡፡
ባድመንም ሆነ በአካባቢው ያሉ መሬቶችን አስመልክቶ የተካሄደው ጦርነትና ያስከፈለው መስዋትነት በጣም ያሳዝናል፡፡ ነገር ግን ስህተትን በስህተት መፍታት ተገቢ አይደለም፡፡ ከጦርነቱ በፊት በሕጋዊ መንገድ ሄዶ መፍታቱ ይሻል ነበር፡፡ ያ አለመሆኑ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ነገር ግን ዋጋ አስከፍሏል በሚል ደግሞ ዕድሜ ልክ በጦርነት መኖር አይገባም፡፡ ከዚህ ታሪክ ተላቆ መውጣት ያስፈልጋል፡፡
ሰው አይመስለውም እንጂ በዚያ አካባቢ ያለው የጦርነት መንፈስ ኢኮኖሚውን በብዙ መንገድ ይጎዳል፡፡ የኢንሹራንሱ ዋጋ ይጨምራል፤ ቱሪስቶች ለመምጣት ያላቸው ፍላጎት ይቀንሳል፤ በሚፈለገው መጠን አካባቢው አያድግም፤ ኢትዮጵያ መጠቀም የሚገባትን የባህር በር ማግኘት አልቻለችም፤ በሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት የለም፤ የንግድ ትስስሩ ተቋርጧል፤ አንዱ አገር ለሌላው አገር ሊያቀርበው የሚችለው ሀብት፣ የሰው ሀይል፣ ገንዘብ፣ ቁሳቁስና የተፈጥሮ ሀብት እንዳይኖር ሆኗል፡፡ ስደተኞችን ማስተናገዱም ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ ምስቅልቅሉ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ ታሪክ መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ኤርትራን አስመልክቶ እንደዚህ ዓይነት ቁርጠኛ አቋም መውሰድ ነበረበት፡፡ ስለዚህ የአሁኑ ውሳኔ ትክክል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኤርትራ ጋር የሚኖረው ግንኙነት አሁን በተያዘው አቅጣጫ መሆን አለበት ማለት ነው?
አቶ ሙሼ፡- አዎ! ይህ እኮ የኢህአዴግና የሻዕቢያ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች ጠባቸውን በፈለጉበት መንገድ ይሞካከሩ፡፡ ነገር ግን ሕዝቦች ዕድሜ ልካቸውን የነርሱ ጥላቻ ምርኮኛ መሆን የለባቸውም፡፡ በእኔ እምነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ መጠንከር አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሌሎች የቅርብ ጎረቤት አገሮች ጋር ያለው ግንኙነትስ?
አቶ ሙሼ፡- ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረቱና መደላድሉ በተለያየ ምክንያት የተጎዳ ነው፡፡ ከማንም በላይ የሚቀርቡ ጎረቤቶቻችንን ማቅረብ የግድ ነው፡፡ ከአሜሪካና ከቻይና ጋር የሚኖር ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከጎረቤት አገራት ጋር ያለው ግንኙነት መልካምነት በዜጎች ላይ ያለው በጎ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ መሰራት አለበት፡፡ እነርሱን ተሻግረን ሄደን ከሌሎች አገሮች ጋር የምንፈጥረው ግንኙነት መቼም አመርቂ አይደለም፡፡
የቅርብ ጎረቤቶች ለሰላማችንም ሆነ ለዕድገታችን እንዲሁም ለሕዝብ ግንኙነቱ ለልምድም ሆነ ለባህል ልውውጡ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ በጎና ቀና ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ከአሜሪካና ከሌሎችም አገሮች ጋር ግንኙነት ሳይኖረን ቀድሞ ግንኙነት የነበረን ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ነው፡፡ ብዙ ባህል ተዋርሰናል፤ ብዙ ልምድ ተለዋውጠናል፤ ተዋልደናል፡፡ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያው ያኖችም በእነዚህ የጎረቤት አገሮች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ግንኙነቱን ለማጠናከር በዚህ መልኩ መሄዱ ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም የአለመረጋጋቱን አጋጣሚ ተጠቅመው ቁርሿቸውን መወጣት የሚፈልጉ አገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ያ መሆን እንደማይገባው ለእነዚህ መንግሥታት በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መግለፅ ትክክል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀጣዩ የ2012 ዓ.ም አገራዊ ምርጫን አስመልክቶ ምን ይታይዎታል?
አቶ ሙሼ፡- እስከ አሁን የነበረው ውይይት የሚቋጨው በ2012ቱ ምርጫ ነው፡፡ በተግባር የሚተረጎሙት በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችን እንደዕድል ማየት፣ ኢትዮጵያን እንደ አንድ አገር ማየት፣ ለተቃዋሚዎች መድረክ መስጠት የተባሉት ነገሮች በሙሉ የሚተገበሩት በዚያ ወቅት ነው፡፡ አንድ ተማሪ ዓመቱን ሙሉ አጥንቶ የሚፈተነው በዓመቱ መጨረሻ እንደመሆኑ መጠን ኢህአዴግም የሚፈተነው በምርጫው ወቅት ነው፡፡ ይህ ምርጫ ለኢትዮጵያ አንደኛውና ዋነኛው መፍትሄ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ዜጎችን ለመጠበቅ የተቋቋሙ ነገር ግን አፈና በማካሄድ ላይ ያሉ ተቋማት እጃቸውን ሰብስበው ወደ ትክክለኛ ሥራቸው ይመለሱ፡፡ ፖሊስ ሥራው ወንጀለኛና ሌባን ማደን ነው፡፡ ፖለቲካ ውስጥ እጁን አያስገባ፡፡ መከላከያም ደህንነቱም ከፖለቲካ ጉዳይ ራሳቸውን መነጠል አለባቸው፡፡ ዜጎች የፈለጉትን አማራጭ የመስማት፤ የፈለጉትን ሰምተው የፈለጉትን የመምረጥ መብት አላቸው፡፡ ይህንን በቅድሚያ በእምነት ደረጃ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ለእዚህ እንቅፋት የሆኑ ከፖሊስ፣ ከደህንነትና ከመከላከያም ውጪ የእንባ ጠባቂ፣ የሰብአዊ መብት፣ የወረዳ የቀበሌ መዋቅሮች የምርጫ ሂደቱን የሚያሰናክሉ፣ ምርጫው በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዳይካሄድ በወገንተኝት የሚሰሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ጨምሮ መገናኛ ብዙኃን በሙሉ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ሁሉንም ፓርቲ እኩል ካስተናገዱ ሕዝቡም ቢሆን ለመምረጥ አይቸገርም፤ ፓርቲዎቹም የሚችሉትን አድርገው ስለተሸነፉ አይከፉም፡፡ ሌላ አገር እንደሚካሄደው ሁሉ ተጨባብጦ መለያየት ይቻላል፡፡ ምርጫው ሲጠናቀቅም ውጤቱን ተቀብለን አገሪቷን በጋራ ለመገንባት የምንነሳበት ሊሆን ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሙሼ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ምህረት ሞገስ

Published in ፖለቲካ
Saturday, 09 June 2018 17:17

ቱሪዝምን ለሥራ ዕድል

ሥራ መፍጠር ከበጀት፣ ስልጠናና ከቁሳቁስ አቅርቦት በተጨማሪ አዲስ ሃሳብንና አቅጣጫን ይዞ መገኘትን ይጠይቃል። አንዳንዶች በአካባቢያቸው ያለውን ሀብት በቅጡ ባለመገንዘባቸው ሩቅ ሳይሄዱ ሊያገኙት የሚችሉትን ተጠቃሚነት ሳያዩት ይኖራሉ። የብዙዎች የፈጠራ ሥራ ምርት አቅርቦትም ሆነ አገልግሎት ሰጪነት ተደራሽ የሚያደርገው በአቅራቢያቸው ለሚገኘው ማህበረሰብ ብቻ ነው። የሀገራችን የቱሪዝም ሀብትም ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መሆን እየቻለ ሳይነካ የተቀመጠ ዘርፍ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
«ቱሪዝምና ጠቀሜታዎቹ ሲታሰቡ በብዙዎች አዕምሮ የሚመጣው ከጉብኝት ከሆቴልና ከትራንስፖርት አገልግሎት የሚገኘው ተጠቃሚነት ብቻ ነው። እነዚህ እንዳሉ ሆኖ ያልነካናቸው ነገርግን ለበርካቶች የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ የማይዳሰሱ ሀብቶች አሉን» ይላሉ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ዳይሬክተር ዶክተር ስምዖን ዘካሪያስ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በሀገራችን ከሚዳሰሱት የቱሪዝም መዳረሻዎች በተጨማሪ አብዛኛው ጎብኚ ሊያያቸውና ሊሰማቸው የሚፈልጋቸው እንደ ሠርግ ስነ ስርዓት ያሉ በርካታ ባህላዊ ክንዋኔዎች አሉ። እነዚህን ክንዋኔዎች ለማየት የሚመጣ ጎብኚ እንደ ሁኔታው ረጀም ርቀት መጓዝ አልያም እነዛ ክንዋኔዎች የሚካሄዱበትን ወቅት መጠበቅ የግድ ይለዋል። ነገርግን የተመረጡ ሊታዩ የሚገባቸውን ባህላዊ ክንዋኔዎች ከሌሎቹ ቅርሶች ጋር በቅርበት በቋሚነት በማካሄድ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ማራዘምና በመስኩ መሰማራት ለሚፈልጉ የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል።
እንዲህ ዓይነት ዝግጅት በሌሎች በርካታ ሀገራት የተለመደና ውጤታማ የሆነ የቱሪስት መስህብ ነው። በኢትዮጵያ ግን እስከአሁን በዚህ መልኩ የተጀመሩ ሥራዎች የሉም። በቅርብ ጊዜ የዚህ ዓይነት ባህል የማስተዋወቅ ፕሮፖዛል ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ያቀረቡ ተማሪዎች እንዳሉ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ ፕሮፖዛሉ ተቀባይነት አግኝቶ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነም ይገልጻሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለመደው አሠራር የተለያዩ ጌጣጌጦችን የሚያመርቱትንም በአቅምም በተደራሽነትም እያስፋፉ የሥራ መስክ ፈጠራ ማድረግ ይቻላል የሚሉት ዳይሬክተሩ በቅርጻ ቅርጽ በሥዕልና ሌሎች የስነ ጥበብ ዘርፎች የተሠሩት ሥራዎች በቂ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። በርካታ ልንገልጻቸውና ልናሳያቸው የሚገቡን ታሪኮች አሉ። በቅርፃ ቅርጽ ሥራ የተሻለ እየተሠራ ቢሆንም ፈጠራ ታክሎበት ያልታዩ ሀብቶችን ሲያስተዋውቁ አይታይም። በመሆኑም በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩትን ማጠናከር ከተቻለ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በማስፋፋት ብቻ ሳይሆን የማይዳሰሱ ባህሎችንና ተንቀሳቃሽ ባህላዊ ቁሳቁሶችን በማቅረብ የቱሪስት መስህብ ማድረግ እንደሚቻል ይናገራሉ።
የአክሱም ከተማ የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍጹምብርሃን በበኩላቸው ወጣቱ ትውልድ የሥራ ዕድል ባለማግኘቱ ለተለያዩ ሱሶች ተጋላጭ መሆኑን ይናገራሉ። በአንጻሩ የቱሪዝሙ ዘርፍ በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያስችል እምቅ አቅም አለው። እንደ አክሱም ከተማ የተጀማመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ከዚህም በላይ በርካታ ሥራዎች ለማከናወን የሚያስችሉ ዕድሎች አሉ። በትንሹ ከሀገር ውስጥ ብቻ ለጽዮን ማርያም በዓል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ ወደ ከተማዋ ይመጣሉ። እነዚህ የእምነት ተጓዦች ደግሞ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የተለያዩ ጌጣጌጦችና አልባሳትን ይገዛሉ። በከተማዋ ከድንጋይ ከሸክላና ሌሎች ቁሳቁሶች እየተፈለፈሉ የሚሠሩ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውና ሌሎችም ጌጣጌጦች አሉ። እነዚህ ጌጣጌጦች የተለየ ማሽን ወይንም ወጪ የሚጠይቁ ሳይሆኑ የአካባቢው ነዋሪ በልምድ የሚሠራቸው ነገር ግን ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ናቸው። በመሆኑም ምርቶቹን በማዘመን ደረጃቸው የበለጠ እንዲስተካከልና በዓይነትም እንዲጨምሩ በማድረግ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያለውን ገበያ በስፋት እንዲጠቀሙ ማድረግ እንደሚጠበቅ ይጠቁማሉ።
የማይዳሰሱ ሀብቶችን ለቱሪዝም አገልግሎት በማዋሉ በኩል የተጀመረ ሥራ ባይኖርም በቁሳቁስ አቅርቦት በኩል በተያዘው በጀት ዓመት የተጀመሩና ውጤት ያስመዘገቡ ሥራዎች መኖራቸውን ኃላፊው ይገልጻሉ። በመስከረም ወር መጀመሪያ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት ሥራና የገቢ ምንጭ ያልነበራቸው 40 ሴቶች በስፌት ሥራ ሰልጥነዉ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። እነዚህ አምራቾች የገበያ እጥረት እንዳይገጥማቸውም በቀጥታ ወደ ውጪ ከሚልኩ ድርጅቶች ጋር በየወሩ የ30 ሺ ብር የሦስት ዓመት ቋሚ የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው ናቸው። ስምምነቱ የተሻለ ምርት ባቀረቡ ቁጥር እየጨመረ የሚመጣ ነው። ከነዚህ በተጨማሪ አስር ሥራ አጦች ከድንጋይ ለሚሠሩ የቅርፃ ቅርጽ ሥራዎች ስልጠና የወሰዱ ሲሆን፤ ተመሳሳይ የአስር ሺ ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል።
የተደራጁት ወጣቶች ምንም ያልነበራቸው በመሆኑ ስልጠና ከሰጠቸው አካል የቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን፤ የማምረቻ ቦታ የቱሪዝም ቢሮ ከሚያስተ ዳድረው ሕንፃ በጊዜያዊነት እንዲያገኙ ተደርጓል። በስፌት ሥራ የተሰማሩትን ሲዳ የሚባል ግብረ ሰናይ ፕሮጀክት ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ ያሠለጠናቸው ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በመጀመሪያ 50 ሴቶች ስልጠና ወስደው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተደረገ ስምምነት እስከአሁንም እየሠሩ ይገኛሉ።
«በመመረቂያችን ወቅት ያመረትነውን ልከን በስምምነቱ መሰረት በመሸጡ አርባ ሺ ብር የመጀመሪያ ዙር ክፍያችንን ተቀብለን ተከፋፍለናል» ያሉን ደግሞ በስፌት ሥራ ስልጠና ወስደው በሥራ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ጌጤ ምላሹ ናቸው። ወይዘሮ ጌጤ እንደተናገሩት የተሰጣቸው ስልጠና በቂ ነው። በቂ እውቀት መጨበጥና ያንኑ በተግባር ማስመስከር ችለዋል። የምርቶቻቸው ተቀባዮች ዲዛይን ሲልኩላቸው በዚያ መሰረት እያመረቱ ያቀርባሉ።
«እኔ ከዚህ ቀደም የምሠራው ነገር አልነበረኝም። የኔ የምለውም ገቢ የለኝም። አሁን ግን ጥሩ ቅርስ አስይዘውኛል፤ እንደየአቅማችንም ቁጠባ ጀምረናል። ባለፈው የላክነው እንደ መጀመሪያው በወቅቱ ገንዘቡ ሳይገባልን በመቆየቱ ይቆማል የሚል ስጋት ገጥሞን ነበር። አሁን ግን ከተቀባዮቹም ጋር ተነጋግረን ሁሉም ነገር እንደተስተካከለና እስከ ሦስት ዓመት በውሉ መሰረት ሁሌም ምርታችንን እንደሚወስዱልን ቃል ገብተውልናል። ሥራው ከመጣልንና ብሩም በየወቅቱ ከተከፈለን ብዙ ለመሥራት መኪናም ለመግዛት ሃሳብ አለን» ይላሉ ወይዘሮ ጌጤ።
የአክሱም ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወልደገብርኤል ተወልደ በተያዘው ዓመት በቋሚነት ለ1ሺ717 እንዲሁም በጊዜያዊነት 1ሺ565 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ያስታውሳሉ። ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ ለጥቂቶች የጌጣጌጥና የመገልገያ ቁሳቁስ እንዲያመርቱ ሁኔታዎች ከማመቻቸቱ በስተቀር ሌሎች ሥራዎች አለመሠራታቸውን ይናገራሉ።
ኃላፊው ለቀጣይ የተያዙትን እቅዶችም አስመልክተው እንደተናገሩት በግብርና፣ በንግድ፣ በአገልግሎት አቅርቦት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በባህላዊ የስፌት ሥራና ባልትና በጥቃቅንና አነስተኛ የሚደራጁ እንዲሳተፉ እየተሠራ ያለ ሥራ አለ።
ለቀጣይ ግን የቱሪዝሙን ፍሰት ተከትሎ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ጎብኚ የሚሆኑ ምርቶችን በማቅረቡ በኩል በስፋት ትኩረት ሰጥተን የምንሠራ ይሆናል። በዚህም አሁን በእንቅስቃሴ ላይ ከሚገኙት የስጦታ ዕቃና በቅርጻ ቅርጽ በተጨማሪ የቦታ፣ ስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ በማመቻቸት በዚሁ ዘርፍ በተለያዩ መስኮች ወጣቶችን በማሰባሰብ እንደ የፍላጎታቸው ከቱሪዝሙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚሠራ ሥራ ይኖራል። በአሁኑ ወቅት በብረታ ብረትና በቆዳ ውጤቶች ሥራ የተሰማሩ ዓድዋና ውቅሮ ስልጠና እየወሰዱ ነው። እነዚህንም አጠናክሮ ምርቶቻቸውን በጥራትና በብዛት በማሳደግ እንዲሁም ምርቶቹ ጎብኚዎችን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ በማድረግ አምራቾች ከቱሪዝሙ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ 

Published in ኢኮኖሚ

በርካታ አፍሪካውያን በእርስበርስ ግጭት፤ በፖለቲካ እንዲሁም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወደ ሌሎች አገራት ይሰደዳሉ። የአፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ተከትሎም የአውሮፓ ህብረትና የዓለም አቀፉ ስደተኞች ተቋም ባለፉት ዓመታት መፍትሄ ያሉትን ልዩ ልዩ ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ሞክረዋል። የአውሮፓ ህብረት ስደተኞችን ለማስቆምና ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን እንዳያንሰራሩ ለማድረግ በርካታ እቅዶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይፋ ቢያደርግም ወቀሳዎች እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ላይ መሰንዘሩ አልቀረም።
በሁለት ፅንፎች ላይ የቆመው የአውሮፓ ህብረት የስደተኞች ስትራቴጂ በአንድ በኩል የሊቢያ የባህር ጠባቂዎችን ማሰልጠንና ስደተኞች ባህሩን ከማቋረጣቸው በፊት አግዶ ወደ ሊቢያ መመለስ ላይ ያተኩራል። በሌላ በኩል ደግሞ ከባህሩ ውጪ አታካች በሆነ መልኩ የህገወጥ አዘዋዋሪዎችን ስራ ፈታኝ ለማድረግ በሚል ለዚህ ስራ የሚውሉ ጀልባዎችን የሚያቃጥሉና ከአገልግሎት ውጪ የሚያደርጉ ሃይሎችን መድበዋል። ይህም ህብረቱን በጉልህ ያስነቀፈ ተግባር ሆኗል። ምክንያቱም በሜድትራኒያን ባህር የጀልባዎቹ መቃጠል ከሞት ቁጥር መጨመር ጋር የተዛመደ መሆኑ ነው።
ተንታኞች እንደሚያስረዱት ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ይህንን እርምጃ ተከትሎ ባህሩን ሊቋቋም ይችላል ተብሎ የማይገመት፤ ቢቃጠልም የማይጎዱበትን ርካሽ ጀልባ መጠቀም ከጀመሩ ሰንብተዋል። ራሳቸው ስደተኞቹ እንደሚገልፁት ደግሞ የባህር ሃይል ጠባቂዎች ተብለው በህብረቱ የተደገፉና የሰለጠኑት አካላት ጨዋታውን ቀይረውታል። ስደተኞቹን ወደ መጡበት ለመመለስ በሚል ህብረቱ ተከፋይ አድርጓቸዋል ፤ እነሱ ደግሞ ባሉበት ሆነው ለህገወጥ አዘዋዋሪዎቹ የይለፍ ፍቃድ ለመስጠት በገንዘብ መደራደራቸው የአደባባይ ምስጢር እየሆነ መጥቷል።
በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ ነው የሚባለው ህገ ወጥ ስደተኞችን ለመግታት ህግ የለሽ፤ መሪ አልባ እየተባለች ወዳለችው ሊቢያ ባስገዳጅነት መመለስ በራሱ ከሰብዓዊነት አኳያ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ በሰብዓዊ ተሟጋቾች መነሳቱ አልቀረም። ይህ ውዝግብ በተለይም በሊቢያ የባህር ሃይል ጠባቂዎች ላይ የተነሳ ዓለም ትኩረት እንዲሰጠው ግፊት እየተደረገ ቢሆንም ጣሊያንና የአውሮፓ ህብረት ግን ትኩረት ያደረጉት ለህይወት አድንና ለበጎ አድራጎት በተሰማሩ አካላት ላይ ነው።
ህገ ወጥ ስደቱን ለመቆጣጠር ትብብር የተጠየቁት የእርዳታ ተቋማትና በህይወት አድን ስራው ላይ የተሰማሩት እንደሚሉት ከሆነም ከባህሩ የከተሙት በወጣው ትዕዛዝ መሰረት ለቁጥጥር የተነሳውን ሃሳብ ሊያስከብሩ ሳይሆን እንደ ጤና ባለሙያ የሞት ሽረት ትግልን አልፈው በህይወት መቆየት ለቻሉ ሊደርሱ፤ የህይወት አድን ስራንም በቃላቸው መሰረት ሊፈፅሙ ነው። ይህም ውሳኔያቸው ደግሞ ብዙሃኑን ከውሳኔ አውጪው ጋር ያቃቃረ ስለመሆኑ ይነገራል።
በዚህ ሁሉ ውስብስብና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም እንኳን አፍሪካውያን ስደተኞች በቀጣይ ዓመታትም ቁጥራቸው ከፍ ሊል እንደሚችል ኒውስ ዊክ ሰሞኑን ያወጣው ዘገባ ያመለክታል። የአውሮፓ ኮሚሽንን ጥናት መሰረት አድርጎ የወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው ከዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘም በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ የአፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር በእጥፍ ሊጨምር ይችላል።
የጥናቱ ሪፖርት ቀደም ባሉት ጊዜያትና አሁን ላይ ያለውን የአፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ፊት ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል ትንበያውን ያስቀምጣል። በዚህም መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች የትውልድ ስፍራቸውን ለቀው ወደተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚሰደዱ አፍሪካውያን ቁጥር አሁን ላይ በዓመት አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ደርሷል። ይህ ቁጥር እኤአ በ2050 ከሁለት ነጥብ ስምንት እስከ ሦስት ነጥብ አምስት ከፍ ሊል እንደሚችልም ያመለክታል።
ወደ ፊት በስደት የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ይሰደዳሉ ተብለው ከሚታሰቡት አፍሪካውያን መካከል ግማሹ እዚያው አፍሪካ ውስጥ የሚሰደዱ እንደሆኑ ሪፖርቱ ያሳያል። ምዕራብ አፍሪካውያን ባህር አቋርጠው ወደ ሌሎች አህጎራች በመሰደድ ረገድ ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አርባ በመቶ ያህሉ ወደ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካና ምዕራብ ኤሽያ አገራት የመሰደድ እድላቸው ሰፊ ይሆናል። አሜሪካና ካናዳ ግን የእነዚህ ስደተኞች በቀዳሚነት የሚመረጡ መዳረሻዎች እንደማይሆኑ ሪፖርቱ አፅኖት ሰጥቶ ያስቀምጣል።
ከአፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ከባድ የአየር ንብረት ለውጥ ትልቁ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ሊቢያ የስደተኞቹ ዋነኛ መሸጋገሪያ አገር መሆኗ እንደሚቀጥል ያስቀምጣል። የአየር ንብረት ለውጥ ቀደም ባሉት ዓመታትም በዓለም የስደተኞች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ትልቅ ምክንያት እንደነበር ይታወቃል። እኤአ በ2011 በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሶሪያ የገጠማት ድርቅ ማህበራዊ ቀውስ አስከትሎ በአገሪቱ ለተፈጠረው ትልቅ አለመረጋጋት ምክንያት እስከመሆን ደርሷል።
አፍሪካ በቀጣይ ዓመታት ከፍተኛ ሙቀት ልታስተናግድ የምትችልበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ስጋት አለ። ይህም በርካታ አፍሪካውያን ከመኖሪያ መንደራቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር ለፖለቲካ አለመረጋጋትና ለትልቅ ግጭት ሊዳርግ እንደሚችል ያሰጋል። በግለሰብ ደረጃ የምግብና የውሃ ፍላጎትን ለማሟላት እንዲሁም ለም መሬት ለማግኘት በሚደረግ ጥረት ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ።
የአሜሪካ የአየር ንብረትና የጤና ተቋም እንደገለፀው የአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካውያን ብቻም ሳይሆን የዓለም ስጋት ነው። በተለይም በመካከለኛው አሜሪካ አገራት ጓቲማላ፤ ሆንዱራስና ኤል ሳልቫዶር በመሳሰሉት አገራት ሊከሰት የሚችለው የምግብ እጥረት የየአገራቱን ነዋሪዎች ከቤታቸው አፈናቅሎ ለስደት ሊዳርግ ይችላል።
ከአየር ንብረት ለውጥ በተጨማሪ የአፍሪካውያንን የስደተኞች ቁጥር ከፍ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ የተቀመጠው ከህዝብ ቁጥር ጋር በተያያዘ ነው። ከሌሎች ዓለማት በተለየ በአፍሪካ በአማካኝ ከእያንዳንዷ እናት የሚወለዱ ህፃናት ቁጥር መቀነስ ላይ መሰረታዊ ሊባል የሚችል ለውጥ አለመታየቱ እንደ አንድ ምክንያት ተቀምጧል። በዚህ ላይ የሚሞቱ ህፃናት ቁጥር ከመቀነሱ ጋር ተያይዞም የአፍሪካውያን የህዝብ ቁጥር በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል ሪፖርቱ ያመለክታል። እኤአ 2017ላይ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ይገመት የነበረው የአፍሪካ የህዝብ ቁጥር እኤአ 2050 ላይ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።
በሌላ መልኩ የአፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ የሚቀመጠው ከኢንቨስትመንት ጋር የተቆራኘ ነው። በአፍሪካ ኢንቨስትመንት በጨመረ ቁጥር በርካታ አፍሪካውያን የተሻለ ገቢና ህይወት ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰባል። በዚህም ከነበሩበት የትውልድ ስፍራቸው የተሻለ ብለው ወደሚያስቡት አካባቢ ሊፈልሱ ይችላሉ የሚል ግምት ተቀምጧል። ለዚህም በሌሎች አገራት ከሚኖሩ አፍሪካውያን ስደተኞች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የተማሩ መሆናቸውን ያስቀምጣል።
እኤአ ከ1960 ወዲህ የአፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር በሂደት እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። 1960ዎቹ ላይ ከትውልድ ስፍራቸው ለቀው በስደት ሌሎች አገራት የሚኖሩ አፍሪካውያን ቁጥር ስምንት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ነበር። እስካለፈው 2017 ግን ይህ ቁጥር ሰላሳ ስድስት ነጥብ ሦስት ማሻቀቡን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ቦጋለ አበበ

Published in ዓለም አቀፍ

«እንጣቆ» ነው ከአፏ የምታወጣው ቃል። ከጎኗ ላለችው ሴት በምታወራው ወሬ መካከል «እንጣቆ ነው እሱ» እያለች ትናገራለች። ይህን የቃል መደጋገም የሰማ አንድ ወጣት «እንጣቆ» ምንድነው? አማርኛ ነው? ሲል ጠየቃት ተናገሪዋን ወጣት። ይህን የተጠየቀችው ወጣት እንዴት እስከዛሬ አልሰማም ወይ ደግሞ ወሬዬን እያዳመጠ ነበር ለካ በሚመስል ይሆን እንጃ ብቻ ከት... ከት ብላ ሳቀች። ጎንበስ ቀና እያለች። ቀጠለ «እውነቴን ነው፤ እንጣቆ ምንድነው?» አለ በድጋሚ። ሳቋን ገታ አድርጋ ታብራራ ገባች። «እንጣቆ ! እንጣቆማ ሰብል ውስጥ እየበቀለ አርሶ አደሩን የሚያሰቃይ አረም ነው። ክፉ አረም!» አለች። እሷም መጥፎ ያለችውን ሰው ነው በዚህ ቃል የምትገልጸው። ለሰዎች መልካም የማያስብ፣ ምቀኛ ፣ ተንኮለኛ፣ የሰዎችን እድገት ሳይሆን ውድቀት የሚመኝ ...።
ልክ አሁን ኢኮኖሚው ውስጥ ገብቶ ዋጋ በቀን በቀን እየጨመረ፤ የህዝቡን የመኖር ህልውና እንደሚፈታተን አይነት አረም ማለት ነው? በኢኮኖሚው ውስጥ የተሰገሰገ አረም እንደማለት ብሎ ፈገግ አለ። የእሱ አሳሳቅ ግን እንደ እሷ አይደለም። ማሽላ ሲያር... አይነት እንጂ። የታክሲው ውስጥ ጭውውት እንደቀጠለ ሁሉም የጋራ ባደረገው ጉዳይ የሆድ የሆዱን ሳይገልጥ መድረሻችን ሾላ ገበያ ወረድን።
የሾላ ገበያ ሁልጊዜም ሞቅ ደመቅ እንዳለች ትውላለች። ሰው ቀነስ ብሏል ከተባለ ያው በዕለተ ሰንበት ብቻ ነው። ሌላው ቀናቶች በዛም አነሰ በሰው ውጣ ውረድ ይጨናነቃል። እኛም ደብለቅ ብለን ገበያተኛ ተብለናል።
የሰሞኑ ዝናብ ደግሞ አካባቢውን አጨቅይ ቶታል ፤ጭቃውን ለመሸሽ የተሻለ መንገድ በመፈለግ መተላለፊያ ላይ ያለው ግፊያው የዛኑ ያክል ሆኗል። ማን ፈርቶት ገዥና ሻጭ በየቀኑ የተለመደ የግብይት ሥርዓታቸውን ተከትለው ያከናውናሉ። የመንገድ ዳር ንግዱ፣ የልብስ ፣ ጫማ፣ የአትክልት፣ ቅመማ ቅመም ፣የሱቅ በደረቴ ...ብቻ ሁሉም አይነት አለ። የእኔ ጉዳይ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ ሚጥሚጣ በጆንያ ሞልተው ‹‹ምን፣ እንስጥሽ›› ከሚሉት መደዳ ነበር።
ወይዘሮ ስህን በላይ ዘንቢላቸውን አንጠልጥለው ጥራጥሬ በሚሸጥባቸው መደብር አጠገብ ቆም ብለው እህሎቹን በእጃቸው ዘገን እያደረጉ ዋጋ ይጠይቃሉ። የዘገኑት ወደ ጆንያው መልሰው ሌላውን አይነት ዘገን አድርገው ደግሞ ይጠይቃሉ፤ ብቻ በተለያዩ ጆንያ ውስጥ ያሉትን ጥራጥሬዎች ምስር ፣ የተከካ ሽሮ፣ አጃ ሌላም ሌላም ጠይቀው በዋጋው ባለመርካታቸው ይሁን ወይም ሌላ ቦታ ቅናሽ ባገኝ ብለው በአቧራ የተበላቸውን እጃቸውን ጆንያው ላይ ጠረግ ጠረግ አድርገው ወደ ቀጣዩ መደብር አመሩ። እዛም በተመሳሳይ የዋጋ ጥያቄ ላይ ናቸው። ቆም አሉ ግራ በገባው አይነት ስሜት ያስባሉ።
ጠጋ ብዬ ግራ የተጋቡ ይመስላሉ? አልኳቸው «በጣም እንጂ በጣም... አሉ»። እንቺም እንደኔው ግራ ቢገባሽ እየዞርሽ ነው በሚል አይነት አስተያየታቸው። ሁለታችንም ለምንገዛው እቃ ለመያዣ በእጃችን ያንጠለጠልነው የማዳበሪያ ዘንቢል አመሳስሎናል። እናም የልብ የልባችንን ለማውራት አልተቸገርንም። «ኧረ የዘንድሮ ባሰ፣ ኑሮው ምን እየሆነ ነው» ሲሉ ጨዋታቸውን ቀጠሉ። «እያንዳንዱ እህልም ሆነ ሸቀጣ ሸቀጥ ወደ ላይ እንጂ ወደታች አይወርድም። ገበያ ላይ ለአይን የጠፋ ነገር የለም ፤ ገበያው ሙሉ ነው። እግዜር ምርት አልነፈገን ኧረ ለመሆኑ ምኑ ነው እንዲህ የሚያደርገው?» ብለው የመፍትሄ ሀሳብ ከእኔ የሚያገኙ በሚመስል ሀሳባቸውን በጥያቄ መልክ አቀረቡ።
በዚህም አላበቁም። ይገርምሻል ብለው ቀጠሉ። «ባለፈው 55 ብር የገዛሁት ምስር ክክ አሁም 68 ብር ይባላል። ሽሮውም ይኸው ነው ። ድሮ ደሀ የሚመገበው ሽሮ ነበር። አሁን እኮ ሽሮ መግዛት አልቻለም። ሌላውን ተይው» ብለው ግራ ያጋባቸውን ነገር ደግመው አነሱት።
በአጠገቧ ቆመን የምንወያየውን ያደመጠች የእህል ነጋዴም «እኛም ግራ ግብት ብሎናል። ዛሬ ያመጣነው አለቀ ብለን ነገ ልናመጣ እህል በረንዳ ስንሄድ ዋጋ ጨምሮ ይጠብቃል። ትተን አንመጣ ነገር ጨምረን እንገዛለን። አሁን በጣም በሚገርም ሁኔታ ትርፋችን ሳይቀር ቀንሷል። ግን ነጋዴ መቼም ቢሆን የሚያምነው ስለሌለ ነው እንጂ የምንሸጠው በአነስተኛ ትርፍ ነው። ትርፋችንን ብንከምር ገዥ እናጣለን። ለእኛም የግብር ወቅት አይደል የሚጠብቀን» ስትል እሷም የሚያስጨንቃትን ወርወር አድርጋ የጭውውታችን አካል ሆነች። ነጋዴው ከደሙ ንፁህ ነው። የኑሮ ውድነቱ ምንጭ ነጋዴ አይደልም የሚል ስሜት አላት።
ግን እኮ እያንዳንዱ ነጋዴ ገዝም ሻጭ ነው። የእህል ነጋዴው ሸቀጣ ሸቀጦችን ይገዛል። የኮንስትራክሽን እቃዎችን ሌላም ሌላም የሚያስፈልገውን ገዝቶ የሚጠቀም ነው። የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴውም ተመሳሳይ ገዢና ተጠቃሚ ነው። የኑሮ መስመሩ ይለያይ እንጂ ከአንድ ከሸማችነት ክብ አይወጣም።
አሁን ያለው የሀገራችን አዲስ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከብዙዎች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ድጋፍ ያገኘ ነው። የእስረኞች መፈታት ለአንድነትና ለእርቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ ፣ ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት ከመደርደሪያ እንዲወርዱ መሰላል ቆሟል። ሰብአዊነት እንደ ህፃን ልጅ ድክ ድክ ማለት ጀምሯል። ይሄ ትንሽ ጅማሮ ከአገር ውስጥ ዜጋው ጀምሮ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ጆሮ ያሰጠ ፤የውጭ መንግስትታንም አይን የሳበ መሆኑ ሀቅ ነው።
ኢህአዴግ ባለፉት ጊዜያት ባደረገው የ17 ቀናት የግምገማ ውጤቱ አንዱ ካስቀመጠው ውሳኔ መካከል የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች እስረኞችን መፍታት የሚል ነው። ይሄ በድርጅቱ ቃል የተገባ ድርጊት በተግባር ታይቷል። በእስር የነበሩ ግለሰቦች ተፈተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለዋል። በሃሳብ ልዩነት የጎሪጥ ከመተያየት ይልቅ ተቀራርቦ መወያየት መፍትሄ መሆኑ የታመነበት ወቅት ላይ ደርሰናል።
አገራችን በአንድነቷ ተከብራ፣ ሰላሟ ተጠብቆ፣ ዜጎች እንደ ልባቸው ወጥተው እንዲገቡና ሰርተው እንዲያፈሩ የታሰበው የይቅርታ፣ የውይይት እና በጋራ ጉዳዮቻችን በጋራ፣ በአንድነት ለመስራት ተቀራርበን እንመካከር የመንግስት ጥሪም በጎ ምላሽ እያስገኘ ይገኛል። የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) አመራሮች ወደ አገር ቤት ገብተው ለመወያየት ያደረጉት ጥረት የዚሁ አንዱ ውጤት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአስተዳደር ዘመናቸው በተከተሉት አዲስ የፖለቲካ አካሄድ በአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ከጎረቤት አገራትም ጭምር በመንቀሳቀስ በሰሩት የዲፕሎማሲ ስራ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዜጎቻችንን ከእስር አስለቅቀው ለእናት አገራቸው ምድር አብቅተዋል። ይሄ ከአንድ ለዜጋው ከሚያስብ መሪ የሚጠበቅ ነው። እንዲሁም በሳውዲ አረቢያ ሆስፒታል በህክምና ስህተት ለ12 ዓመታት የአልጋ ቁራኛ የሆነውን ታዳጊ ጎብኝተውና በችግሩ ዙሪያ ከአገሪቱ መንግስታት ጋር በመወያየት መፍትሄ የሚያገኝበትን መስመር አስይዘዋል። ሌሎች ሰብአዊ የሆኑ ተግባራትን እየታዩ ጭምር ነው። ይሄ ከአንድ መሪ የሚጠበቅ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው።
ነገር ግን የሰው ልጅ ዴሞክራሲያዊ መብቴ አልተከበረም ፤ሰብአዊ መብቴም ተነፍጓል ማለት የሚችለው ሆዱ ሞልቶ ከሆድ በላይ ማሰብ ፣መመራመር፣ መስራትና መናገር ሲችል መሆኑ መታሰብ አለበት። አሁን ባለው ሁኔታ ህዝቡ ምን እንሁን ወደማለት እየተሸጋገረ ነው። 1ብር ከ50 ሳንቲም የሚሸጥ ዳቦ ዛሬ 3 ብር ደርሷል። እሱም ከተገኘ። ዋጋ አልጨመርንም ባሉ ዳቦ መጋገሪያዎች ደግሞ የዳቦ መጠን ወደ ኪኒንነት ተለውጧል። የጥራቱ ነገር ሳይነገር ማለት ነው። እዚህ ላይ እያንዳንዱ መሰረታዊ የሚባለው የሰው ልጅ የየዕለት ምግብ ከቀን ወደ ቀን የዋጋ ለውጥ እያስከተለ ነው። ይሄንን የኑሮ ውድነት ተከትሎም ቤት አከራይቶ አዳሪዎች የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ ላይ ናቸው። ምክንያቱም እነሱም የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም በእጃቸው በያዙት ሀብት ላይ ያለ ከልካይ የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ ይችላሉ።
አሁን አይን ሸፍኖ እስኪከፈት ያለው የዋጋ ጭማሪ መነሻው ምንድነው ብሎ መፈተሽም ያስፈልጋል። አሁን ኢኮኖሚውን እያመሰ ያለው ‹‹እንጣቆ›› በወቅቱ ካልተነቀ ህዝቡ ለቅሬታና ለብሶት መንቀሳቀሱ አይቀሬ ነው። ምክንያቱም ምንም ተሰራ ምን የሰው ልጅ ሰርቶ ገንዘብ ማግኘት፤ በገንዘቡ መግዛትና ህይወቱን መቀየር ካልቻለ ፖለቲካም እንበለው ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት ብቻውን ትርጉም አይኖረውም። ስለዚህ ሁሉንም በልክ በልኩ በመያዝ፣ በማስተዳደርና በመምራት የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት መጣር ያስፈልጋል። የኢኮኖሚ ዕድገቱ በህዝቡ ኪስ የሚታይ፣ ተመዝሮ የሚገዛ ፤ተቆርሶ የሚበላ መሆን ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ አሁን በኢኮኖሚ ውስጥ እየታየ ያለውን ‹‹እንጣቆ›› ለመንቀል መንግስት መስራት አለበት ።

  አዶኒስ (ከ ሲኤም ሲ) 

Published in አጀንዳ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፉት ሁለት ወራት ወደ ተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ የአገር ውስጥ ሰላምንና የህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር ከህብረተሰቡ ጋር ሰፊ ውይይት አድርገዋል። ችግሮች ሁሉ በውይይት፣ በእርቅና በይቅርታ እንዲፈቱና የአገር አንድነትንና ልማትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባም ሲያሳስቡ ከርመዋል።
ከዚህ አለፍ ብለው ወደ ጎረቤት አገሮች በማቅናትም ኢትዮጵያ በጋራ ለመልማት የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራርመዋል። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ጤናማና የተጠናከረ እንዲሆንም ተንቀሳቅሰዋል። በየአገራቱ የታሰሩ ዜጎቻችን እንዲፈቱና ወደ እናት አገራቸው በሰላም እንዲገቡ አድርገዋል። ሌሎች ሰብአዊ የሆኑ ስራዎችም ሰርተዋል። በአጠቃላይ የተገኙት ውጤቶች አስደሳች ነበሩ።
የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ መቋጫ እንዲያገኝ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሜቴ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ለመቀበል መወሰኑን አስታውቋል። ላለፉት 20 ዓመታት ያለ ዘላቂ መፍትሄ ተንጠልጥሎ የቆየው የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ መቋጨቱ የሚያስገኘውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት የተንጸባረቀው አቋም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው የለውጥ ሂደት አንድ አካል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይሄ ውሳኔ በዋነኛነት ተጠቃሚ የሚያደርገው የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ነው።
የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ መቀበል ለኢትዮጵያ እድገትና ለሕዝቦች ተጠቃሚነት ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ አንድ ሀገር ላይ ሰላም ከደፈረሰ ምንም አይነት የልማትና የእድገት ዕቅዶችን ማቀድና ማሳካት አይቻልም፡፡ ስለዚህ በህዝቡ መካከል ሰላም እንዲሰፍን ፤ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረውና የቆየ ታሪካዊና ቤተሰባዊ ትስስር እንዲጠናከር የውሳኔ ሃሳቡን ወደ ተግባር እንዲለወጥ ቀዳሚውን ድርሻ ኢትዮጵያ ወስዳለች።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው ጦርነት በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሽ ፤ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺ የሰው ሕይወት የጠፋበት ነው፡፡ ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ መኖሪያ አፈናቅሏል፡፡ ቤተሰቦችን አለያይቷል፣ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎችም በዕለት ከዕለት ህይወታቸው ተረጋግተው እንዳይኖሩ ፤ ለነገ አቅደው እንዳይሰሩና ለቀጣይ አመታትም ራዕይ እንዳይኖራቸው አድርጓል። ሁሌም ሰግተው እንዲኖሩ የስነልቦና ጫና አሳድሮባቸዋል። በአጠቃላይ ባለፉት 20 ዓመታት በሁለቱም ወንድማማች ሀገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ላለፉት ሃያ ዓመታት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት አላመጡም፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ሀገራት መካከል እውነተኛ ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ አስፈልጓል፡፡
ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና ለአካባቢያዊ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት እንደ አንድ ዘላቂ መፍትሔ የሚወሰደው የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት ነው፡፡ ይሄ ባለመሆኑ በርካታ ለሁለቱም አገሮች የሚበጁ እንዲሁም ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው እድሎች አምልጠዋል፡፡
በመሆኑም በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ሰላም ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይህም ውሳኔ ተገቢና ትክክልም ነው። ለሁለቱ አገሮች ያለውንም ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት ከኤርትራ መንግስትም በጎ ምላሽ ሊሠጠው ይገባል፡፡
አንድ አይነት ቋንቋ የሚናገሩ በባህልና በጋብቻ የተሳሰሩ ህዝቦች ተለያይተውና በጠላትነት ተፈርጀው እስከመቼ ይኖራሉ የሚለው የብዙዎች ጥያቄም ነበር። የሁለቱ አገራት ህዝብም ጭንቀት ነበር። ስለዚህ ለህዝብ ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ሲባል ለስምምነቱ ተገዢ መሆን ይገባል። እዚህ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው እርምጃ ተገቢ እና ለህዝቦች ሰላም ቅድሚያ የሰጠ ነው። ውሳኔውን በቅንነት ተቀብሎ ለተግባራዊነቱ ዝግጁ መሆን ጥቅሙ ለሁለቱም አገሮች ህዝቦች ነው።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግሥት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሀብቶች እንዲተላለፍ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ይሄ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ምን ጥቅም አለው?
የፖለቲካ ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ እንደሚናገሩት፤ ኩባንያዎቹ ወደ ግል መዘዋወራቸው የመልካም አስተዳደር፣ የሙስና እና የካፒታል ችግር በማቃለል በኩል ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ የመንግሥት ንብረት ሊዘረፍ ይችላል፡፡ የግል ሲሆን ግን ንብረቱ በአግባቡ ይጠበቃል፤ ስለዚህ ሌብነት ይቀንሳል፡፡
የግል ዘርፉ ለራሱ ሲል አገልግሎት አሰጣጡን የሚያሻሽል በመሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈተና አይሆንም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት ከፍተኛ ካፒታል የሚያገኝ በመሆኑ ያጋጠመውን የፋይናንስ እጥረት ይቃልላል በማለት የሥራ አስፈፃሚው ውሳኔ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ያብራራሉ፡፡
ከዩኒቨርሲቲውና ከኮሌጆች ወጣቶች እየተመረቁ ሥራ በሚያጡበት አገር የግል ዘርፉ በመጣ ማግስት ይህ ችግር ይሻሻላል፡፡ የሥራ ዕድልና ካፒታል ይኖራል፡፡ ይህም ከኢኮኖሚ ዕድገት ባሻገር ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን አስተዋፅኦ ይኖረዋል ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የባህር ትራንስፖርት በተወሰነ መልኩም ቢሆን በአክሲዮን ሲሸጡ ገቢው ቀላል እንደማይሆን ይናገራሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህ የመንግሥት ድርጅቶች ለመንግሥት ትርፍ እያስገኙ ነው ቢባልም ትርፋቸው ለአገሪቷ ብዙም ጠቃሚ እንዳልነበር ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይጠቅሳሉ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊ ሆነው በናይጄሪያ ሲሠሩ ያዩቱን በተመክሮ ያነሳሉ። በናይጀሪያ መንግሥት ተይዞ የነበረው ቴሌኮም ወደ ግል ሲዘዋወር አራት ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ በመምጣታቸው አገሪቱ ታገኝ የነበረውን ገንዘብ በአንድ ዓመት ውስጥ በአሥር እጥፍ ማደጉን ተናግረዋል፡፡ አሁን ናይጄሪያ ከግል ቴሌኮም ኦፕሬተሮች ብቻ በዓመት ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታገኛለች። በኢትዮጵያ ግን የውጪዎች ሲመጡ ይዘርፉናል በሚል ስጋት ለማይሠራ ስልክና ኢንተርኔት ከቻይና ተበድራ የምታገኘው ገቢ የአገሪቷን ወጪ በመደገፍ በኩል ያለው አስተዋፅኦ ዝቅተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
የግል ዘርፍ ሲባል ኢትዮጵያን ብቻ ማየት አይገባም፡፡ በሉዓላዊነት ዘመን የግል ዘርፍ አገርም ድንበርም የሌለው ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ ማንኛውም ባለሀብት መጥቶ ጥሩ ቦታ ላይ ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖችን በብድር ቢገዛም ዕዳውን እየከፈለ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን በዓለም የአክሲዮን ሽያጭ ላይ በለንደን እና በኒዮርክ ስቶክ ኤክስቼንጅ እንዲሁም በኢንሺያል ፐብሊክ ኤክስቼንጅ የተወሰነው ድርሻ ቢሸጥ አገሪቷ ብዙ ገንዘብ ልታገኝ ትችላለች ብለዋል፡፡
እንደዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ ኩባንያዎቹ ወደ ግል መዘዋወራቸው ምንም ዓይነት ጉዳት አይኖረውም፡፡ ሆኖም ግን ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይመጣ ወደ ግል ሲዘዋወር አካሄዱ በሙስና እንዳይጨማለቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ እስከ አሁን በጥቂቱ እንደታየው ሁሉ 40 ኩባያን ለአንድ ድርጅት መሸጥ ትክክለኛ አካሄድ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ፡፡
የቁጥጥር ሥርዓቱ ሲካሄድ ሰዎች መመደብ ያለባቸው በፖለቲካ አዝማሚያ ሳይሆን በችሎታና በብቃታቸው መሆን አለበት፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረጃ ቁርጠኝነት ያላቸው ሰዎች ተመድበው ከተቆጣጠሩት ውጤታማነቱ አያጠራጥርም ብለዋል፡፡
ህንድ፣ ጀርመንም ሆነች እንግሊዝ ልማታዊ የነበሩ ቢሆኑም ኩባንያዎቹን ወደ ግል በማዛወራቸው ዜጎቻቸው አልተጎዱም፡፡ ነገር ግን አሁን ለአገር ውስጥ ባለሀብት እንሽጠው የሚለው አካሄድ በወረዳ ላይ ከመሬት ጋር ተያይዞ እንደሚታየው ዓይነት ዘግናኝ ሙስና መፈፀሚያ መንገድ ሊሆን ይችላል። ይሄ ደግሞ አገሪቷን የማይጠቅም መሆኑን ያሳስባሉ፡፡
እንደዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለፃ፤ መንግሥት ፋይናንሱንም ወደ ግል ማዘዋወር አለበት፡፡ በዳያስፖራ ገንዘብና ወደ ውጭ ከሚላከ ዕቃ ላይ በሚገኘው ጥቂት ገንዘብ እንዲሁም በዕርዳታ ገቢ ብቻ ብዙ መሥራት አይቻልም፡፡ ይህ ከሆነ አገሪቷ ከሚጠበቀው በላይ ታድጋለች፡፡ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ እንዳይሳካ ያሰረው የካፒታል እጥረት ትልቅ መፍትሔ ያገኛል፤ ወጣቱ ሥራ ያገኛል፤ ሰላምና መረጋጋት ይሰፍናል፡፡ ለዚህ በየክልሉ ያሉ ኃላፊዎች ብቃትና በንፁህ ልቦና መሥራት ወሳኝነት አለው፡፡ በመጨረሻም አገሪቷ ከልመናና ብድር ወጥታ የህዝቡ ኑሮ እንደሚሻሻል አያጠያይቅም ብለዋል፡፡
ኢኮኖሚስቱ አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ የመንግሥት ትልልቅ ኩባያዎች ትልቁን ድርሻቸውን መንግሥት ይዞ የተወሰነውን ለመሸጥ መወሰኑ ተገቢ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ መብራት ኃይልም ሆነ፣ ቴሌ የአገሪቷን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የሚያቀላጥፉ ቢሆኑም እንዲተላለፉ መታሰቡ ተገቢነት ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ዝውውሩ አግባብ ባለው መልኩ በተጠና መንገድ መሆን አለበት ይላሉ፡፡
‹‹በእርግጥ መንግሥት ከኢኮኖሚው ቢወጣ ጥሩ ነው፡፡ የሞባይል ካርድ እና መብራት እየቸበቸበ አይኖርም፡፡ ዕርምጃው ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን በተዘዋዋሪ አደጋ እንዳይኖረው እሰጋለሁ›› ይላሉ፡፡
ኢህአዴግ በእጅ አዙር በልማት ድርጅቶቹ አማካኝነት እነዚህን ትላልቅ ኩባንያዎች ሊገዛ አስቦ ከሆነ አደገኛ አካሄድ መሆኑን አቶ ሙሼ ይገልጻሉ። አሁን ላይ አቅሙ ያለው እነጥረት፣ ኤፈርት፣ ጉና አካባቢ በመሆኑ እነሱ እጃቸውን የሚያስገቡ ከሆነ ዕቅዱ ከድጡ ወደ ማጡ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ፖለቲካውም ኢኮኖሚውም በአንድ አካል ከተያዘ ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ ስለዚህ አካሄዱ ጥንቃቄ የተሞላው የታሰበው የኢኮኖሚ ለውጥ የሚያመጣ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
እንደ ኢኮኖሚስቱ ማብራሪያ፤ መግዛት ያለባቸው ዜጎች ብቻ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ዳያስፖራው በልዩ ሁኔታ ሊፈቀድለት ይችላል፡፡ በቅድሚያ ግን ፓርላማውም ሆነ ሙህራን በዚህ ጉዳይ ሊወያዩበት ይገባል። የተደረገ ጥናትም ካሉ በግልጽነት ህዝቡ ሊረዳው ይገባል ብለዋል፡፡
ከ20 ዓመት በፊት ጀምሮ ሲሰጥ የነበረው ምክንያት መንግሥት የውጭ ኩባንያዎች ላይ ቁጥጥር ለማካሄድ ችሎታ የለውም፡፡ የግል ዘርፉ የኢኮኖሚ አቅም የዳበረ አይደለም ሲባልም ዓመታት አልፈዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ኩባንያዎቹ ወደ ግል ሳይዘዋወሩ ዘግይተዋል፡፡ በሌላ በኩል አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርን የሚከተል መንግሥት በመሆኑ ሁሉንም ሥራ ይሥራው የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ነገር ታጥቷል፡፡
የመንግሥት ትልልቅ ድርጅቶችን በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ ግል ማዘዋወሩ ትልቅ ተስፋን አጭሯል፡፡ በሌሎች ዓለሞች እንደተለመደው የተሻለ አገልግሎትና የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ፣ የውጭ ምንዛሬውን እጥረት ለማቃለል እና የአገሪቷን ዕድገት በተሻለ መልኩ ወደፊት ለማስቀጠል እንዲሁም ከዕርዳታና ብድር ለመላቀቅ ዋነኛ መፍትሔ ነው፡፡ ይሄን የታሰበውን ዓላማ ለማሳካት ግን አካሄዱ የተጠናና ጥንቃቄ የተሞላው መሆን አለበት። አካሄድ ላይ ስህተት ከተፈጠረ ዕቅዱ ከድጡ ወደ ማጡ ይሆናል። 

ምህረት ሞገስ
ዜና ትንታኔ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።