Items filtered by date: Sunday, 01 July 2018

ዓለም ዋንጫ ደምቋል። ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ዓይኖቹን ወደ ሩሲያ ቀስሯል። የቻለ በግዙፎቹ የሩሲያ ስታዲየሞች ተገኝቶ ጨዋታዎቹን እየታደመ ይገኛል። ሌላው ደግሞ ከቴሌቪዥን ስክሪኖች ላይ ዓይኑን ሊነቅል አልቻለም። አፍሪካዊያኖቹ አልቀናቸውም። ከ1982 በኋላ አፍሪካን የወከሉ አገራት የመጀመሪያውን ዙር ማለፍ ሲሳናቸው የአሁኑ የመጀመሪያው ነው። ሴኔጋል እስከመጨረሻው ሰዓት ብትታገልም ለሌሎች ፍስሀን ይዞ የመጣው «ቫር» በገልባጩ ለሷ ሀዘንን ይዞ ከተፍ ብሏል። ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለው ከውድድር ውጪ ሆናለች። ገና በጠዋቱ ትሰናበታለች ተብላ ያልታሰበቸው ሻምፒዮናዋ ጀርመን በደቡብ ኮሪያ ሁለት ለዜሮ ቀምሳ አንገቷን አቀርቅራ ወደ አገሯ ተመልሳለች። ከምድቧ በጊዜ የተሰናበተችው ጀርመን ይህን ታሪክ ለመድገም 80 ዓመት ፈጅቶባታል። ለአዲሱ የጀርመን ትውልድ በጊዜ ከዓለም ዋንጫ መሰናበት እንግዳ ነገር ነው።

አርጀንቲና ዕድል አሁንም አልተለያትም ከጅምሩ እንዳትሰናበት የምትሀተኛው ሊዮኔል ሜሲ እና የተከላካዩ ማርኮስ ሮሆ የባከነ ግብ ታድጓታል። ዕድል ግን ቀዳሚዋ አዳኟ ነች። ፖርቹጋል እስከአሁን ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ እንደሆነላት ነው። የደጋፊዎች ውበት፣ ያልተጠበቁ ውጤቶች ሩሲያን ኳስ ኳስ እንድትሸት አድርጓታል። ዓለም አሁንም ወርቃማውን ዋንጫ በጉያዋ ከያዘችው ከዚህች አገር ዓይኑን አይነቅልም። ገና ብዙ ፈንጠዝያ፣ ብዙ አንገት የሚያስቀረቅሩ እና ግርምትን የሚጭሩ ትእይንቶችን እናስተውላለን። ምክንያቱም አሁን በሩሲያ ግዙፉ የዓለም ዋንጫ እየተካሄደ ነው።
እኛ ደግሞ በዛሬው የዕሁድ ገፃችን አሁን እየተካሄደ ስላለው ሳይሆን ስላለፈው፤ ስለውጤት ሳይሆን ግርምትን ተንኩሰው ስላለፉ ወቅቶች ከታሪክ ዶሴ ገልጠን ልናሳያችሁ ወደናል። ይህን ታሪክ የሠሩ አንዳንዶች አሁንም በሩሲያ ስታዲዮም ተገኝተው እግር ኳስ አቅላቸውን ስታስታቸው ተመልክተናል። ከዚህ ውስጥ አርጀንቲናዊው የቀድሞ ኮኮብ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ይገኝበታል። እግር ኳስ እና ያልተጠበቀ ውጤት እንዴት ፈንጠዝያና አቅልን እንደሚያስት ለማወቅ በናይጄሪያ እና አርጀንቲና ጨዋታ ላይ የታዩት የማራዶና ሁለት ጣቶች የታሪክ ምስክር ሆነው አልፈዋል። እኛ ደግሞ በዓለም ዋንጫው ላይ ወደኋላ መለስ ብለን እጆች እግር ሆነው ኳስን ወደመረብ የቀየሩበትን ታሪካዊ ጨዋታዎች እናስታውሳችሁ።
ብራዚል ከቼኮዝላቫኪያ
ጊዜው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 17 1962 ነው። የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ የሚደረግበት። ለፍልሚያው የደረሱት ደግሞ ብራዚል እና ቼኮዝላቪያ። ይህ ጨዋታ በብዙ የእግረ ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ በድራማ እንደተጠናቀቀ ተዘንግቷል። የድራማው ዋና ተዋናይ ደግሞ ብራዚላዊው ጃሌማ ሳንቶስ ነው። በግማሽ ጎኑ ፖርቹጋላዊ የሆነው ሳንቶስ በዚህ ጨዋታ የማይረሳ አሻራ ጥሎ አልፏል። ሳንቶስ ታሪክ የማይዘነጋውን ድርጊት የከወነው በእግሩ ሳይሆን በእጆቹ ነበር።
ጨዋታው እየተካሄደ ነው። ብራዚል ቺኮዝላቪያን 2ለ1 በሆነ ውጤት እየመራች ነበር። ቼኮዝላቪያ ደግሞ ዋንጫው እንዳያመልጣት ጠንክራ እያጠቃች ወደ ብራዚል የግብ ክልል በተደጋጋሚ ትደርሳለች። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 20 ደቂቃዎች ሲቀሩት አስገራሚ ጉዳይ ተከሰተ። በብራዚል የግብ ክልል ላይ ቼኮዝላቪያዎች እያጠቁ ነው። ሆኖም ግን ወደ ግብ መቀየር የምትችል ኳስ ሳንቶስ ሆን ብሎ በእጁ አስቀራት። አስገራሚው ነገር ደግሞ ዳኛው ፍፁም ቅጣት ምት መስጠት ሲገባው በቸልታ አለፈው። ብራዚሎች ሲፈነጥዙ። ቼኮዝላቪያዎች ግን ክፉኛ አዘኑ። ብራዚል አንድ ተጨማሪ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው 3ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቀቀ።
አርጀንቲና ከፖላንድ
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1978 የተካሄደውን የዓለም ዋንጫ አርጀንቲና እያስተናገደችው ነው። ቡድኗ ደግሞ በምድብ «ለ» ውስጥ ተደልድሏል። ጨዋታውን ከፖላንድ ጋር እያከናወነ ነበር። አርጀንቲናዊው ማሪዮ ኬምፔ በሁለተኛው አጋማሽ አገሩን መሪ የሚያደርግ ጎል አስቆጠረ። ጨዋታው ቀጥሏል። አርጀንቲና እየመራች ነው። ፖላንዶች እያጠቁ ነው። በክንፍ በኩል አንድ ኳስ ተሻገረ። ወደ ጎል እንደሚቀየር ምንም ጥርጥር አልነበረውም። ሆኖም ግን አገሩን መሪ ያደረገው አጥቂው ማሪዮ ልክ እንደግብ ጠባቂ ኳሷን በእጁ አጉኗት ግብ እንዳትሆን አደረጋት። ሁኔታው አስገራሚ ነበር። ዳኛው በዚህ ጊዜ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጠ። ሆኖም ፖላንዶች ማሪዮ በእጁ ስላዳናት ግብ የምትሆን ኳስ ሲያስቡ ፍፁም ቅጣት ምቱን ሳቱት። አስገራሚው ደግሞ ኬምፔ በድጋሚ ለአገሩ ግብ አስቆጥሮ ሁለት ለዜሮ እንዲጠናቀቅ እና ከምድቧ እንድታልፍ አደረጋት። ኧረ እንዲያውም ዋንጫውንም ያነሳችው እርሷው ናት።
አርጀንቲና ከእንግሊዝ (የእግዜር እጅ)
ያለ ምንም ጥርጥር በእጅ ተነክተው ወደ ግብነት ከተቆጠሩ ኳሶች ውስጥ ታዋቂዋ እና ዓለምን ያነጋገረች ነች። ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በእንግሊዝ ላይ በምትሀት ያስቆጠራት ጎል። ዳኛው ተሸውዷል። ማራዶና አጭበርብሯል። ሁለተኛው አጋማሸ ላይ የእግር ኳስ ባላንጣዎቹ 0ለ0 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን እያከናወኑ ነበር። ኳስ በአየር ላይ ሆና ማራዶናን እና የእንግሊዙን በረኛ ፒተር ሺልተንን አፋጣለች። በዚያ ቅፅበት ቆቁ ማራዶና ቅልጥፍናውን ተጠቅሞ ኳሷን በውጪኛው እጁ ወደ መረቡ ሰደዳት። በተደጋጋሚ በምስል ካልታየ በስተቀር በእጅ የተቆጠረ አይመስልም ነበር። ዳኛው ተጭበረበረ። እሱም እንግሊዞችን በጠራራ ፀሐይ አንድ ጎል ሰረቃቸው። በዚህ ጨዋታ ላይ ማራዶና ይሄን ብቻ ግን አልነበረም የሠራው። ቢያንስ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የእንግሊዝ ተጫዋቾችን ከመሀል ሜዳ ጀምሮ በመረፍረፍ «የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ጎል» ተብሎ የሚጠራውን ታሪከኛ ግብ አስቆጠረ። ማራዶና በሁሉም የሰውነቱ ክፍል ግብ እንደሚያስቆጥር አስመስክሮ እንግሊዝን እጅ ወደላይ አስባለ።
ከማራዶና ታሪካዊ የእጅ ጎሎች አልወጣንም። ይሄ ሰው ተአምረኛ ነው። ከቻለ በእጁ ካቃተው አጭበርብሮ በእጁ አገሩን ቀዳሚ ማድረግ ይፈልጋል። ጊዜው የ1986 የዓለም ዋንጫ ነው። አቆጣጠሩ እንደ አውሮፓውያን። የቀድሞዋ ዩ ኤስ ኤስ አር የአሁኗ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሩሲያ ከማራዶና አገር ጋር ተፋጣለች። ጨዋታው ቀጥሏል። ባዶ ለባዶ በሆነ ውጤት ላይ ናቸው። ሩሲያ በማጥቃት ላይ ትገኛለች። የአርጀንቲና የግብ ክልል ላይ ደርሰዋል። ኳስ ወደ ግብ ክልል ተመታ። አንድ ተጫዋች ግን ግጥም አድርጎ በእጁ መለሳት። ግብ ጠባቂው አይደለም። ይህ ተጫዋች ማራዶና ነው። ዩ ኤስ ኤስ አር መሪ መሆን የምትችልበት አጋጣሚ በዚህ ከሸፈ። በተቃራኒው አርጀንቲና ሁለት ግቦችን አስቆጥራ ጨዋታው ተጠናቀቀ። ራሺያ ከምድቧም ገና በጠዋቱ ተሰናበተች። ይሄ ክስተት ቅስም ሰባሪ ነበር። የወቅቱን ጨዋታ የዳኘው ኢንስትራክተር ሲዊዲናዊው ኤሪክ ፍሬድሪክሰን ነበር። የእውነትም ይህን ጨዋታ ሲያስቡ የእጅ ኳሷን ችላ ያላትን ሲዊዲናዊውን ዳኛ ራሺያዎች ሲረግሙ ይኖራሉ።
ፈረንሳይ ከአየርላንድ
ይሄ ጨዋታ አንድ ትዝታ ውስጥ ይከተናል። የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጥሎ ማለፍ ውድድር ነው። ጊዜው ደግሞ 2009። ፈረንሳይ ከአየርላንድ 1ለ1 ናቸው። ውጤቱ እስከ ዘጠናኛው ደቂቃ ድረስ ምንም ልዩነት አላመጣም። ሁሉም ነገር ሚዛኑን ጥብቆ እየተጓዘ ነው። አራተኛ ዳኛው ተጨማሪ ሰዓት አሳየ። ሆኖም በባከነ ሰዓት ከቅጣት ምት ለቲየሪ ሄነሪ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ወጪ ሊወጣ ሲል በእጁ አስቀርቶ በማቀበል ዊሊያም ጋላስ በግንባሩ ወደ ጎልነት እንዲቀይራት ዕድሉን አመቻችቷል። አየርላንድ 2ለ1 በሆነ እጅግ አሳዛኝ ውጤት ተሸንፋ ወጣች። ይሄ ጨዋታ እንዲደገም ለፊፋ በተደጋጋሚ ክስ ቢቀርብም ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
ጋና ከኡራጋይ
ጊዜው እ.አ.አ 2010 ነው። ኡራጋይ ከጋና አራት ውስጥ ለመግባት የሚያደርጉት ፍልሚያ ነበር። ሁለቱ ቡድኖች አንላቀቅም ብለው በባከነው ሰዓት እንዲሁም በተጨማሪው 30 ደቂቃ ድረስ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ቆይተዋል። ሆኖም ባለቀ ሰዓት ኦሳማ ጊያን ወደ ኡራጋይ የግብ ክልል የላካት ኳስ መስመሩን አለፈች ተብሎ አፍሪካውያን ለፈንጠዝያ ሲዘጋጁ ያልታሰቡት የአጥቂው ሊውስ ሱዋሬዝ እጆች ኳሳን ከግብነት አዳኗት። ለስፖርት አፍቃሪው በተለይ ደግሞ በታሪክ አራት ውስጥ ገብታ ለማታውቀው ጋና እጅጉን አብሻቂ እና ለግጭት የሚዳርግ ነበር። ዳኛው ፍፁም ቅጣት ምት ሰጠ። ይሄም ሌላ ተስፋ ቢሆንም በሚያስቆጭ ሁኔታ ኦሳማ ጊያን ዕድሉን አመከነው። ከማስቆጨት በዘለለ ቃል የጠፋለት አጋጣሚ ታሪክ በማይዘነጋው መልኩ ተመዘገበ። ሁለቱ ቡድኖች ወደ መለያ ምት ሄዱ። ኡራጋይ የበላይነቱን በመያዝ ወደ አራት ውስጥ ገባች። እጅግ አስገራሚ አጋጣሚ ነበር። ጋና ድል በሯ ላይ ደርሶ የተመለሰበት ጊዜ።
ኮሎምቢያ ከጃፓን «2018 ሩሲያ የዓለም ዋንጫ»
ታሪክ እራሱን እያደሰ እና አዳዲስ ክስተቶችን በዓለም ዋንጫው ላይ እየታየ፤ የሩሲያው ዓለም ዋንጫ ደረሰ። ሁሌም አዲስ ነገር የማያጣው አዝናኙ የዓለማችን እግር ኳስ በጃፓን እና በኮሎምቢያ ጨዋታ ላይ የማራዶናን ያህል ባይሳካም ለአገር ክብር ሲባል ኳስን በእጅ አፈፍ አድርጎ የመመለስ ሙከራን አሳየን። ጃፓን ኳሱን ይዛ ጫና በኮሎምቢያ ግብ ክልል እየፈጠረች ነው። በድንገት ወደ ግብ ክልል ኳስ ተመታ። ኮሎምቢያዊው ካርሎስ ሳንቼዝ አሻፈረኝ ብሎ ኳሷን ከግብ ለማዳን በእጁ ተከላከለ። ውጤቱ ግን ያማረ አልነበረም። እርሱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ ኮሎምቢያ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ ተቆጠረባት። ሺንጂ ካጋዋ ጃፓንን ቀዳሚ አደረጋት። የቀይ ካርድ ሰለባ የሆኑት ኮሎምቢያዎች በዩሃን ፈርናንዶ ከርቀት በተመታች ኳስ አንድ አቻ መሆን ቻሉ። ሆኖም ግን በቁጥር ብልጫ የነበራቸው ጃፓኖች በዩአያ ኦሳኮ የ73ተኛ ደቂቃ ግብ ኮሎምቢያን በመርታት የመጀመሪያውን 3 ነጥብ በሩሲያ ዓለም ዋንጫ ማሳካት ቻሉ።
ከላይ የጠቀስናቸው በእጅ ተነክተው ግብ የሆኑ ብሎም ከመግባት የዳኑ ታሪካዊ የእግር ኳስ ክስተቶች ናቸው። በጊዜው ለተሸናፊው ትልቅ ቁጭት ለአሸናፊው ደግሞ ያልተጠበቀ ድልን አምጥተዋል። ፈንጠዝያንና ቁጭትን የፈጠሩት እነዚህ ጊዜያት ካለፉ በኋላ የእግር ኳስ አፍቃሪው በቂም እና በድል አድራጊነት መንፈስ ሳይሆን በታሪክነታቸው ብቻ ሲያስታውሷቸው ይኖራሉ።

ዳግም ከበደ

 

Published in ስፖርት

እኔ እኮ ጥሎብኝ በየሄድኩበት አይኔ አያርፍም፡፡ አንድ ዕለት በአንድ ክፍለ ከተማ ውስጥ ተገኘሁና አንድ ነገር አየሁ(ለነገሩ እንዲታይ ነው ያስቀመጡት)፡፡ ‹‹እዚህ ቦታ ላይ ኮንዶም ያገኛሉ›› ይላል፡፡ ጽሑፉን ሳየው ፈገግ አሰኘኝ፡፡ ይኑረው አይኑረው ባላረጋግጥም ከአጠገቡ ኮረጆ ነገር አለ፡፡ ይሄ ኮረጆ የኮንዶም ማስቀመጫ ነው ማለት ነው፡፡ መቼም ጥያቄያችሁ ‹‹ታዲያ ምን አስገረመህ!›› ነው፡፡
አምናለሁ ይሄ ነገር በጣም አከራካሪ ነው፡፡ በመጀመሪያ ከተከራካሪዎቼ ወገን ያለውን ሀሳብ ስለማውቀው ልናገር(ስቼው አይደለም ለማለት ነው)፡፡ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው የጤና ነገር ነው፡፡ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ደግሞ ለወጣቱ ጠንቅ እንደነበር አያጠያይቅም፤ ለብዙ ዓመታት የተባለ ነው፡፡ ይህን አስከፊ በሽታ ለመከላከል ደግሞ ኮንዶም አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ኮንዶም በሽታን ብቻ ሳይሆን ያልተፈለገ እርግዝናንም ተከላካይ ነው፡፡ በዚህ በዚህ አገልግሎቱ ምንም ክርክር አይኖርም፡፡ ስለዚህ ኮንዶም መኖር አለበት፡፡
አሁን ወደ እኔ ሀሳብ ልመለስ፡፡ ይሄ እኮ ሥራ የሚሰራበት ክፍለ ከተማ እንጂ ጭፈራ ቤት አይደለም፤ መጠጥ ቤት አይደለም፤ ሆቴል አይደለም፤ ትልቅ ኃላፊነት መሸከም የሚችሉ ሰዎች ያሉበት ቦታ ላይ ‹‹ከዚህ ኮንዶም ይውሰዱ!›› ማለት ምን ማለት ነው? አልጋ ቤት አለ እንዴ እዚያ? እኔማ ፈገግ ያሰኘኝ ኮንዶሙን ብቻ ነው ወይስ ... አብረው ይሰጣሉ? ብዬ ነበር(መቼም ኮንዶም ሌላ አገልግሎት የለውም)፡፡ መቀመጡ አስፈላጊ ቢሆንም ቢያንስ ቦታ ቦታ አለው፡፡ በሆቴሎች አካባቢ፣ በአልጋ ቤቶች አካባቢ ነው መቀመጥ ያለበት፡፡ የመንግስት ተቋም ውስጥ ኮንዶም ማስቀመጥ እንደኔ እንደኔ ነውር ነው፡፡ እኮ ኮንዶም እንደ ዘይት በቀበሌ ሊከፋፈል? በነገራችን ላይ ‹‹ኮንዶም ውሰዱ›› ማለት እኮ ‹‹ወሲብ ፈጽሙ›› ማለት ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ቦታ ላይ ወሲብ ፈጽሙ ማለት ደግሞ ከትዳር ውጭ መማገጥን፣ ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸምን ማበረታታት ማለት ነው፡፡
የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ኮንዶም ማስቀመጥ እዚያው ተጠቀሙበት ማለት እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ የትም ሄደው ይጠቀሙ፤ ነገሩ ግን ወሲብ ፈጽሙ እያሉ ማዘዝ ነው፡፡ ‹‹ከትዳር ውጭ ወስልቱ›› ማለት አይደለም የሚለኝ ካለ ታዲያ ለባለትዳርማ ኮንዶም ምን ይሰራል? ባለትዳር ላልሆኑትስ ቢሆን መታቀብን ነው ማስተማር ወይስ ‹‹እዚህ ኮንዶም አለላችሁ›› እያሉ ሌላ ነገር ማሳሰብ?
እነዚህ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሥልጠና የሚሰጡ ሰዎች ላይም ከፍተኛ ቅሬታ አለኝ፡፡ እነርሱ ተከፍሏቸው የሚሰሩ ናቸው፡፡ የእነርሱ ሥራ ማለት የኮንዶም ተጠቃሚን ማብዛት ነው፡፡ እዚህ ላይ ነበር የሚያበሳጨኝ ትምህርት ሲሰጡ የሰማሁ፡፡ በአገራችን ውስጥ ያለው ባህል ኋላቀር እንደሆነ፣ ወሲብ ነውር መሆን እንደሌለበት ነው የሚሰበከው፡፡ ባህላችን ኋላቀር አይደለም፤ የሚያኮራና ጨዋነትን የሚያጎናጽፍ ባህል ነው ያለን፡፡ የማንም የውጭ አገር ልቅ ባህል ምሳሌ ሊሆነን አይችልም፡፡ ወሲብ ተፈጥሯዊ ቢሆንም በአደባባይ የምናወራበት ደግሞ አይደለም፡፡ ቃሉን እንኳን ለመጠቀም በሚከብድበት ባህል ውስጥ እንዲህ አድርጉ እያሉ ማስተማር ሥልጣኔ ሊሆን አይችልም፡፡
አስታውሳለሁ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ ስለዚህ ነገር ግንዛቤ ይሰጥ ነበር፡፡ ያኔ ሲያስተምሩን ኮንዶምን የመጨረሻው አማራጭ በማድረግ ነበር፡፡ የ‹‹መ›› ህጎች የሚባሉት ደረጃ ነበራቸው፡፡፡ የመጀመሪያው፣ ዋናውና አስተማማኙ መታቀብ፣ ሁለተኛው ማግባት፣ በትዳር መጽናትንና መተማመንን የሚጠይቀው መወሰን ሲሆኑ እነዚህ በማይቻሉበት አጋጣሚ ኮንዶም መጠቀም አማራጭ ይሆን ነበር፡፡ ይህም ተመራጭ ሳይሆን አማራጭ ነው፡፡ በኋላ ግን ሁሉንም አሸንፎ ትምህርቱ ሁሉ የኮንዶም አጠቃቀም ብቻ ሆነ፡፡ ስለዚህ መታቀብና መወሰን ዋጋ እያጡ ኮንዶም መጠቀም ዋና ጉዳይ ሆነ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የተዘጋጁ ሥልጠናዎችንና ስብሰባዎችን ተካፍዬ አውቃለሁ፤ ብዙ የታዘብኩት ነገርም አለ፡፡ አሰልጣኞቹ የሚያነሱት ቅሬታ ወጣቶች ኮንዶም ለመውሰድና ለመጠየቅ እንደሚያፍሩ ነው፡፡ ሲያብራሩም በቃ ማንም ወጣት ያለምንም ማፈር ኮንዶም መጠየቅ እንዳለበት ነው፡፡ ሴቷም ያለምንም ማፈር የኮንዶም አጠቃቀም መማር እንዳለባት ነው፡፡ የዝሙት ሥልጠና ነው እኮ የሚመስለው! ኮንዶም መጠየቅ የሚያፍር ወጣት፣ የኮንዶም አጠቃቀም ማሳየት የምታፍር ሴት ለእኔ ጨዋ እንጂ አላዋቂነት አይደለም፡፡ ኮንዶም መጠየቅ ማለት እኮ ‹‹ዝሙት ልሰራ ነው›› ማለት ነው፡፡ ከትዳር ውጭ፣ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ያው ዝሙት ነው፡፡ እኔ ኮንዶም መጠየቅን ወሲብ ሲያደርጉ ከመታየት አሳንሼ አላየውም፡፡ ይሄ ማለት ግን ኮንዶም መጠየቅን እያፈሩ ሌላ የብልግና ነገር መሥራት ማለት አይደለም፤ እንዲህ ከሆነማ የባሰ ባለጌነትና ትልቅ ነውር ነው፡፡
በዚህ በኮንዶም ትምህርት ላይ ሌላም የማይጥመኝ ነገር አለ፡፡ ከአንደኛ ክፍት ተማሪዎች ጀምሮ ነው ስለኮንዶም አጠቃቀም ትምህርት የሚሰጠው፡፡ እስኪ ለአንድ የአሥር ዓመት ልጅ ስለኮንዶም አጠቃቀም ማስተማር ምን ማለት ነው? እነዚህ ልጆች እኮ የተነገራቸውን ነገር ለማድረግ የሚጓጉ ናቸው፡፡ በዚያ ዕድሜያቸው ስለወሲብ የሚያስቡበት ጊዜ አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ማስተማር ግን ማሳሰብ ማለት ነው፡፡ እንኳን ለልጆች ለወጣቶች እንኳን ችግር አለው፡፡ በእርግጠኝነት በኮንዶም ትምህርት ሳያስቡት ወደ ወሲብ የገቡ ወጣቶች ይኖራሉ፡፡
ሌላው ደግሞ የሚያስቀኝ በትልልቅ መገናኛ ብዙኃን የሚነገረው የኮንዶም ማስታወቂያ ነው፡፡ ሰሞኑን እንኳን በአንድ ሬዲዮ ላይ የሰማሁት ሲገርመኝ ነበር፡፡ ማስታወቂያው የሚጀምረው ስለባልና ሚስቶች ፍቅርና መተማመን ነው፡፡ ስለትዳር ክቡርነት ሊያወራ ነው ብላችሁ ስትጠብቁ አንድ የኮንዶም አይነት ይጠራና ያስተዋውቃል፡፡ አንድ ደግሞ በቴሌቪዥን የሚተላለፍ ማስታወቂያ ነበር፡፡ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ሲያወሩ ይቆያሉ፡፡ ‹‹ናፈቅሽኝ፤ ናፈቅከኝ›› ይባባሉና ልክ ሲገናኙ ‹‹ያን ጊዜ….›› ይልና አንድ የኮንዶም አይነት ይጠራል፡፡ እንዴ! በቃ ሰው ከተገናኘ ለወሲብ ነው ማለት ነው? ማስታወቂያ ይሰራለት እንኳን ከተባለ መሰራት ያለበት በእንዲህ አይነት መንገድ አይደለም፡፡ አስከፊውንና ገዳይ የሆነውን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ለመከላከል በቃል መተረክ ብቻ በቂ ነው፡፡
እንዳልኳችሁ ይሄ ነገር አከራካሪ ነው፡፡ የኮንዶም ኩባንያዎች ቢሰሙኝ «በእንጀራችን ላይ መጣህ» ማለታቸው አይቀርም፡፡ የጤና ባለሙያዎችም «ይሄ እኮ የሰው ሕይወት ነው እንደሚሉ አስባለሁ፡፡ እያልኩ ያለሁት ግን ከትዳር ውጭ ያለኮንዶም በመጠቀም ወደባሰ ብልግና እንግባ አይደለም፡፡ ከትዳርና ከጋብቻ ውጭ ያለው የከፋ ነውር ሲሆን ኮንዶም በኪስ ይዞ መሄድም ለእኔ ነውር እንጂ ጀግንነት አይደለም፡፡ እንዲያውም አንድ ሰሞን ደግሞ የሚያስቀው ነገር ኮንዶም የያዘ ወጣት እንደጀግናም ተቆጥሮ ነበር፡፡ ጀግንነት ማለት በትዳር መጽናትና መተማመን እንጂ ኮንዶም ይዞ ዝሙት አዳሪ ማደን አይደለም፡፡ ይሄማ ስሜትን መቆጣጠር አለመቻል ነው፤ ይሄ ሽንፈት ነው፡፡
እነዚህ የኮንዶም ትምህርት የሚሰጡ ወጣቶችም ቢሰሙኝ ‹‹ኋላቀር ፋራ›› ብለው መሳደባቸው አይቀርም፡፡ አይ እንግዲህ እንከባበር! እንግዲያውስ ከጀመርኩት አይቀር ሌላም ልንገራችሁ፡፡ በእንዲህ አይነት ክበባት ውስጥ ያሉ ወጣቶች እንኳን ኤድስን ሊከላከሉ አንዱ መንስኤ ናቸው እየተባላችሁ ትታማላችሁ፡፡ ታዲያ ምን ይደረግ ሁሌም ስለኮንዶም ነው የምታወሩት!
በመጨረሻም በዚህ እንስማማ! በአስፈላጊነቱ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ዳሩ ግን ጊዜና ቦታ ይኑረው፡፡ በዚህ አካሄድ እኮ የሃይማኖት ቦታዎች ሁሉ ሊቀመጥ ነው፡፡ መታቀብና መተማመን ዋጋ እያጡ ነው፡፡ ትልቅ ኃላፊነት መሸከም የሚችሉ ሰዎች ባሉበት የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ‹‹ከዚህ ኮንዶም ይውሰዱ›› ማለት እንደኔ እምነት ዝሙትን ማበረታታት ነው!

ዋለልኝ አየለ

 

ፍቅሩ ሲመጣ

 

«ማንነሽ!...ወዲህ በይው ድንቹን እኔ ልቆራርጠው» አሉ፤ የሻሽወርቅ። ለወትሮው ወዲያ ወዲህ ጎምለል እያሉ የሴቱን ሙያ ያብጠለጥሉ ነበር። «አሁን ጎመን የሚከተፈው እንዲህ ነው?» ይላሉ፤ የሚብሰው ደግሞ የፈረደባት ዐይናቸው ያረፈባት ሴት እስክትሸማቀቅ ድረስ ድምጻቸውን አጉልተው መናገራቸው ነው። ታድያ ግን «አከታተፉ እንዲህ ነው» ብለውኮ አያሳዩም።
በአካባቢያችን ያለው የሴት እድር በወጣት ኃይል የተተካ አይደለም። አሁን ድረስ ያሉት በየሻሽወርቅና በእትዬ አደላሽ እድሜ ያሉ እናቶችና መለስ ያሉ ወይዛዝርት ናቸው። እናቴ ይህን እያወቀች ቀሪ ተብላ በእድሩ እንዳትቀጣ ሰግታ ስትልከኝ ቅር ብሎኝ አያውቅም፤ የሻሸወርቅ ስለሚያ ዝናኑ። የሙያ ነገር ሲመጣ ግን...ከዐይና ቸው ያውጣኝ ማለት ነው።
ከየሻሽወርቅ ትዕዛዝ ከተል ብዬ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁና ተልጦ የተቀመጠ በርከት ያለ ድንች የያዘውን መዘፍዘፊያ አቀበልኳቸው። «ጎበዝ! አሁንማ በርትታችኋል፤ እንዲህ ቀልጠፍ ማለት ነው'ንጂ!» አሉና ለስለስ ባለ ፈገግታ ተመለከቱኝ። መልሼ ፈገግ አልኩ፤ ሙያ የማታውቂ ገልቱ አይበሉኝ እንጂ ሌላ ምንስ ቢሉኝ ምን ቸገረኝ።
«አሁንማ የእህትና ወንድሜ ልጆችም ካልመጣን ማለት ጀምረዋል። ብትተዋወ ቂያቸው እንደው ደስታዬ ነው። እዚህ መጥተውም ማጣፊያው እንዳያጥራ ቸው...» አሉኝ። እኔን ነው፤ እኔን የወጣቱ ትውልድ ተወካይ አድርገው የሚያስቡኝ፤ ለረጅም ዓመት አብረዋቸው የኖሩ የጎረቤቶቻቸው ልጅ።
«ኧረ ችግር የለውም የሻሽ...» አልኩኝ አስቀድሞ ከተነሳሁበት ቦታ ላይ እየተቀመጥኩ። «ለክረምቱ እረፍት ነው የሚመጡት?» አለች፤ እየሰማች መሆኑ ሳያስታውቅባት የቆየች፤ ከሰል አልያያዝ ብሏት ወዲያ ወዲህ ማንደጃውን የምትዟዟር ሴት። የሻሽወርቅ ቤት ለቡና እና ለሻይ የማትጠፋ፤ 'የሻሽወርቅን ከእናንተ የተሻለ በቅርበት አውቃቸዋለሁ' የምትል ሰው ናት።
የሻሽወርቅ ወደእርሷ ሳይዞሩ መልዕክታቸውን ወደእኔ መላኩን ቀጠሉ፤ «ሃሳባቸውስ እዚህ ጠቅለው ለመኖር ነው፤ እኔን 'አትመጪም ወይ' እያሉ ሲያደርቁኝ እንዳልኖሩ አሁን ካልመጣን ብለዋል። ከተማዋም መልኳ ሁሉ ተቀያይሮ ትጠፋቸዋለች ብዬ ነው የማስቸግርሽ» አሉኝ፤ አንዴ እኔን አንዴ ደግሞ በእጃቸው ይዘው ሊከታትፉ ያዘጋጁትን ድንች አገላብጠው እየተመለከቱ።
«ተመስገን! ለማይሞላ ኑሮ ከዛሬ ነገ አገራቸው መጣን እያሉ በሰው አገር እድሜ መጨረስ! መምጣታቸውስ ደግ ሆነ» አሉ፤ ዐይናቸውን አጥብበው በሰፌድ ላይ የተበተነ ድፍን ምስር እየለቀሙ ያሉት እትዬ አደላሽ። በሄዱበት የማይለይዋቸውን የወዳጃቸውን የእትዬ አደላሽን ቀልብ እንደያዙ የገባቸው የሻሽወርቅ ጨዋታውን ወደሰፊው የሴት እድርተኛ ጆሮ ላኩት።
«እንደው በቴሌቪዥን የሚያዩት ነገር አጓጊ ሆነባቸው መሰለኝ፤ ሰሞኑን ስንት ቀን ነው መሰላችሁ የምንሰማው እውነት ነው ወይ እያሉ የደወሉት። እኔም ታድያ ሰው መቼም በገዛ አገሩና በገዛ ወገኑ መቅናት የለበትም፤ እኔም ብሆን እነርሱ ጋር ቀን ነውና በሌሊት እየተደወለ እንቅልፌን ማጣት የለብኝም ብዬ ኑ አልኳቸው» አሉ ሥራውን ትተው ጓደኛቸውን እትዬ አደላሽን እየተመለከቱ።
«ጊዜው ተገላብጦ አይገርምም? ኑ ይሉን እንዳልነበር አሁን እኛ ሆንን ኑ የምንላቸው?» አለች፤ ከሴት እድር ቀዳሚ ተሰላፊ የሆነችው ሌላዋ ሴት። ይሄኔ የሻሽወርቅ ትክ ብለው አይዋት፤ «ጥሩ ተናገርሽ፤ ይሄ የሰፈር ሰው ስም እያነሱ ማብጠልጠል ብቻ የምታውቂ መስሎኝ ነበር።» አሉ፤ ደስ አላት። ጥሩ ተናገርሽ ከመባሏና የሰው ስም የምታብጠለጥል መሆኗ ከመጠቀሱ የትኛው የበለጠ ሊሰማት ይገባ ነበር ብዬ አሰብኩ። ጥሩ ሰው ሳትሆን አትቀርም።
«አሁንማ ባለጸጋ መሆናችን ሊመለስ ነው፤ ነዳጅ ልናወጣ አይደለ? መቼም በየት በኩል እንደሚደርሰኝ ባላውቅም እንደው ይህን ዜና ከሰማሁ በኋላ ልቤን ሞቅ ብሎታል» አለች፤ ዝም ብላ የቆየች፤ የሴት እድር አባላት ብዙ ጊዜ ስብሰባ የሚያደርጉበት ቤት ባለቤት የሆነችው ወይዘሮ። ብዙ የማትናገረዋን ይህቺን ደርባባ ሴት የሻሽወርቅ ነጥብ አግኝተውባት ስለማያውቁ ስለእርሷ ምንም አይናገሩም።
«እሱስ ልክ ብለሻል፤ የእኔ ልጆችስ አገራችን የባለሀብትን ደጅ ከመጥናት ወደ ባለሀብትነት ተቀየረች ብለው አይደለም ሊመጡ የጓጉት። እሱንስ ብለው ቢመጡ ምን አለበት? ተኝታችሁ መብላት ትጀምራላችሁ ያለ የለም። ደግሞ ሰው አገር የሄዱትስ ይህንኑ መሻሻል ፍለጋ አይደለምን?» አሉ ከተማሪው ላይ ስህተት እንዳገኘ መምህር አንገታቸውን ወደጎን ዘመም አድርገው በለዘብታ ሴቲቱን እየተመለከቱ።
«አይ! እሱስ የሚበልጥ ፍቅሩ ነው። ድሮም ነዳጅ መች ጠፋ! ስለነበር ነውኮ አሁን ወጣ ነው የተባለው። ፍቅሩ የሚበልጥ ይሄኔ ነው። ፍቅሩ ነውኮ ነዳጁን ያወጣው» አሉ እትዬ አደላሽ።
«ፍቅሩ ማን? ፍቅሩ የእኛ?» መኖሯ ሳያስታውቅ የቆየችው የወሬ እናት የሆነችው ሴት ድንገት ድምጿ ተሰማ። የሻሽወርቅ እንዳይናገሯቸው ፈርተው፤ ድምጻቸውን አጥፍተው ምንም አስተያየት ሳይሰጡ የቆዩ ሴቶች ሁሉ ሳቁ። ሁላችንም ሳቅን። «አሁን ፍቅሩ ስም ብቻ መስሎሽ ነው? ዋናው ተገኝቶ!» አሉና እትዬ አደላሽም አንገታቸውን ወደደረታቸው አስጠግተው ሳቃቸውን ቀጠሉ።
«ያልሰማ ጆሮ ከምን ያጣላል አሉ፤ አሁን ሥራሽን አርፈሽ አትሠሪም። በደረስሽበት የከረምሽ ለመምሰል ስትሞክሪ ችግር ትፈጥሪያለሽ» ሴቶቹ ሳቃቸውን ቶሎ አላቋረጡም።
«አሁን ቶሎ እንጨራርስና ለሰዎቹ እንድረስላ ቸው። መቼም የነሻሽወርቅ የሴት እድር ሆስፒታል የተኙትን እነዛን ምስኪን ልጆች ጠየቀ ተብሎ ጥሩንባ አይለፈፍም። ባይሆን ግን መቀላጠፍ የለብንም ማለት አይደለም። እንግዲህ አታሳፍሩኝ ቶሎ ቶሎ እንጠናቀቅ ባካችሁ፤ ዝናቡም ሳይመጣ» አሉ እትዬ አደላሽ፤ ትህትና እና ፍቅር በተሞላበት ንግግር።
«እውነቷን ነው አደልዬ፤ በሉ ገና የእኔ ቤተሰቦች ሲመጡም ሽር ጉድ ማለታችሁ አይቀርም። ማነሽ! ኧር ከሰል እንደዛ አይደለም የሚያያዘው። ሲሆን ነገረኛ ነበርሽና ቶሎ ይያያዝልሽ ነበር፤ ስትለግሚ ነው አይደለ..?» አሉ የየሻሽወርቅ ከሰል ወደምታያይዘው ሴት ፊታቸውን መለስ አድርገው።
ይሄኔ የወሬ እናት ቀበል ብላ ቀጠለች፤ «ነዳጁን ፍቅሩ ያመጣዋል አላለችም፤ አንድ ፊቱኑ ሲመጣ በሱ አንሠራም?» አለች። እየመረጠ የሚሰማ ሰው አያናድድም? ምን እያሰበች እንዲያ ቀልቧ ጠፍቶ፣ ስንስቅባት እንኳ ሳትባንን፤ ስትታማ ሳትሰማ፤ መልሳ እዛው መገኘቷ አሳቀን። ነገሩስ እውነቷን ነው፤ ነጃዱን ፍቅሩ ነው ያመጣው። የሴቱን እድር የበለጠ ሳቅ በሳቅ አድርጋ ሥራ አስፈታችን እንጂ።

ሊድያ ተስፋዬ

ማራኪ አንቀጾች

ፈጠነ ጥጋቡ፤ ዘገየ ትቶት እንደሄደ ነገር እያላመጠ ጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ አስናቀች ወደ ተኛችበት ተመልሶ «አስኒ፣ አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሞኝ ወደ ቢሮ መሄዴ ነው። ማታ እመለሳለሁ» ብሏት ወጣ። አስናቀች፣ በኩርፊያ ተንጠርብባ በጋቢዋ ተጠቀለለች። እርሱ በቀጥታ ወደ ፈለቀ ማመጫ ቤት ሄደ። እዚያ እንደደረሰም መኩሪያ የአጥሩን ካብ ተደግፎ ዋሽንት ሲጫወት አገኘው።
መኩሪያ፣ ፈጠነ ወደ እርሱ መምጣቱን እንደአየ ዋሽንት መጫወቱን አቁሞ፣ በአክብሮት አንገቱን ሰበር አድርጎ ሠላምታ አቀረበለት። ፈጠነም አጸፋውን ከመለሰ በኋላ ከፊቱ ቆመና «መቼም የዚህ ዋሽንት ሱስ ሳይገድልህ አይቀርም» አለው።
«አውደዋለሁ። ጊዜ ያማሻል፣ አሳብ ይከፍላል»
«ፈለቀ ማመጫ እያለልህ ምን ሐሳብ አለብህ?»
«አይ ነገሩን አልሁ'ይ አሳብስ የለብኝም»
«ፍቅር ይዞሃል መሰለኝ»
መኩሪያ አፍሮ ዐይኖቹን የሚያሳርፍበት ስፍራ አጥቶ አንዴ ወደ መሬት፣ አንዴ ወደ ሰማይ፣ አንዴ ፈጠነ ላይ፣ ደግሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ አራወጣቸው። የሚለው ቢያጣ «የምን ፍቅር?» አለ።
ፈጠነ ሳቀና «አይ የገበሬ ነገር፤ ግልጹን ስውር ማድረግ ትወዳላችሁ። የምን ፍቅር ልበልህ? የሴት ነዋ» አለው።
መኩሪያ በሸቀ፤ «ወንድን ተሴት ነው'ይ ፍቅር እሚይዘው ኋላ'ማ ተምን ይይዘዋል?» ብሎ አጸፋውን መለሰ።
«አየህ?፣ አንተንም የሴት ፍቅር እየወዘወዘህ ነው»
መኩሪያ ዝም አለ።
«በጓንጉል ልጅ ፍቅር መያዝህንና በእሷው የተነሳ ከዘገየ ጋር ቁርቋሶ መጀመርህን እማላ'ቅ መሰለህ?»
«ይኽን ሁሉ ምን ሊሆንህ አጠናኸው?»
«ለምን አጠናዋለሁ? ራሱ ዘገየ ነው የነገረኝ። ይልቅስ ተጠንቀቅ»
«ተምኑ ነው እምጠነቀቀው?» አለ መኩሪያ በመገረም።
ፈጠነ፣ የሳቁ በሚመስሉ ዐይኖቹ መኩሪያን አትኩሮ እያየው «ሞኝ አትሁን፤ 'ማጅር-ግንዱን ብዬ እደፋዋለሁ'፤ ብሎ እየዛተ ነው። ፊት ለፊት እንደማይገጥምህ አ'ቃለሁ፤ አድብቶ በማንኛውም ሁኔታ ሊያጠቃህ እንደሚችል ግን አልጠራጠርም። የፈለቀ ማመጫ ልጅ ባትሆን ኖሮ አልነግርህም ነበር። በል ከዋሽንትህ ጋር ደኅና ክረም» ብሎት ሄደ።
መኩሪያ፣ ፈጠነን ረጅም እርቀት በዐይኑ ሸኘው። የነገረው ሁሉ ከንክኖታል። «እውን ዘገየ ልብ አግኝቶ በ'ኔ ላይ እጁን ሊያነሳ? እማይመስል ነው» ብሎ አሰበ።...
ምንጭ፤ የበቀል ጥላ - ገስጥ ተጫኔ፡ 2010ዓ.ም

Published in መዝናኛ

ፀሐይ በምሥራቅ ወጥታ በምዕራብ ትጠልቃለች፤ ተፈጥሮዋንና ኡደቷን አትዘነጋም። ተፈጥሮውንና ማንነቱን እየዘነጋ ያለው የሰው ልጅ አስተሳሰብ ግን ከዚህ ተለይቷል። መልካም ስብእናውን በመርሳት ቂም ለመውለድ ከህሊና የሚያጣሉ እኩይ ተግባራትን ሲያከናውን ማየት እየተለመደ መጥቷል። ለዚህም ማሳያው አሁን ላይ በየአካባቢው የሚደረጉ ብሄር ተኮር ግጭቶች ናቸው። ኢትዮጵያዊነት ይህ እንዳልነበረ ግን ቀደምት ዘመናችን ያስተምሩናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬም ቢሆን አንደጥንቱ ኢትዮጵያዊነታችን እንዲጠነክር የእንደመር መርህን አንግበው ተነስተዋል። ኢትዮጵያዊ ማንነት የማይለወጥ፣ በደስታና በፍቅር የሚኖር አብሮነት፤ በጋራ መብላት፣ በጋራ መሥራት ያለበት ልዩ ስጦታ እንጂ መለያየት እንዳልሆነ በመስበክ ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያዊነት የሚለቅ ቀለም እንዳይደለም ይናገራሉ። የትኛውንም ችግር ለመፍታት ቀድሞ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን በሚገባ ስለሚያምኑም ከአገር ፍቅርና አይበገሬነት ተነሱ። የሀገር ውለታዋ ምን እንደሚመስል አስታውሱ። ነጋዴውን፣ ባለሀብቱን፣ ባለስልጣኑን፣ ማህበረሰቡ ተደምረው አንዲት የበለፀገች ኢትዮጵያን ልንፈጥር ይገባል፤ ሲሉ በመምክር ላይ ናቸው። በዚህም ንገረን፤ ምከረን፤ ዘክረን የሚሏቸው ተበራከቱ።
ባለተራዎቹ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ናቸው። አስቀድሞ መረጃው የተላለፈው ከማህበራዊ ድረ ገጽ/ፌስቡክ ነበር። በየአቅጣጫው ደውለን፣ ጉዳዩ እውነት ነው ወይ? የት ይከናወናል? ስንት ሰዓት እንገኝ? የሚለውን አጣራን። ቦታው ድረስ ለመዘገብ ብናቀናም ተፈላጊዎቹ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንጂ ዘጋቢዎች ባለመሆናቸው ተመለስን። ነገር ግን በመገናኛ ብዙሃን እንደሰማነው ከሆነ ውይይቱ ወይም ገለፃው ስኬታማ እንደነበር ለመረዳት ችለናል። የአገር ፍቅርና የአንድነት አስተሳሰቦችን በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ የሚያስችሉ ተግባራት ለመከወን የቤት ሥራ መውሰዳቸውን የኪነ- ጥበብ ሙያተኞች ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን የአገር አንድነትን እና አብሮነትን ለማጉላት ጥረት እያደረጉ ለሚገኙት የኪነ-ጥበብ ሰዎች ያላቸውን አክብሮት በውይይቱ ላይ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ለህዝብ እየቀረቡ ባሉት የፊልምና ቴአትር ሥራዎች ኢትዮጵያን ከመግለጽ አኳያ ክፍተት እንዳለባቸው በውይይቱ ተነስቷል። የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንደተናገሩትም በውይይቱ ላይ የተነሱ ሃሳቦች የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ለአገር ሰላምና ዕድገት መጫወት የሚጠበቅባቸውን ሚና ለማጎልበት የሚያግዙ ናቸው። ውይይቱ ስኬታማና የተነሱ ሃሳቦችም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተሰማሩበት ዘርፍ ያላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያጎለብቱ የሚያግዙ ነበሩ። የኪነ-ጥበብ ባለሙያው በማንኛውም አገራዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ዙሪያ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አጋዥ ሃሳቦችን ለማመንጨት አቅም ያላቸው መሆናቸው የተብራራበት ነበር።
ዘርፉ በተለይም ይቅርታንና ስነ-ምግባርን በተመለከተ የህብረተሰቡን አመለካከት ለመግራት ትልቅ መሳሪያ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩት መሰረት ሙያተኛው የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ያረጋገጠበትም ጭምር ነበር። በውይይቱ የኪነ-ጥበብ ሙያተኛው የአገራዊ አንድነትንና መደመርን የሚሰብኩ ሥራዎችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ አገሪቱን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የበኩላቸውን እንዲወጡ የቤት ሥራ የተሰጠበትም ነበር። ውይይቱ የኪነ-ጥበብ ዘርፉ «የኢትዮጵያዊነት» ትክክለኛ ገፅታና ስሜትን ከመግለጽ አኳያ ወደፊት በስፋት ሊሰሩ በሚገባቸው ቁም ነገሮች ላይ ትኩረት የተሰጠበትና ሙያተኛውም በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታዎች እንዲኖሩ ዕድል የፈጠረ ነበር።
በቦታው ላይ ከተገኙ ባለሙያዎች መካከል ገጣሚና ደራሲ አንዱአለም አባተ (የአጸደ ልጅ) አንዱ ሲሆን፤ ስለነበረው ገለጻ እንዲህ ሲል አጫውቶናል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ ጋር የነበረን ቆይታ እንደ ስልጠና የሚወሰድ አይደለም፤ ግን ትልቅ መልዕክት የያዘ ነበር። የኪነጥበብ ጉዳይ በመሪ ደረጃ ትኩረት ተችሮት መነጋገር መቻል ትልቅ ለውጥ ነው። በገለጻውም ብዙ ያልታዩ ክፍተቶች ተነስተዋል። በተለይ በአገሪቱ ላይ ከባድ ችግር የሆነው የዘርፉ ባለሙያዎች የእርስ በእርስ ሽኩቻ በሚገባ ታይቶ ራሱ ባለሙያው መፍትሄ ሊቸረው እንደሚገባ ተመላክቷል።
«ጥበብ በተለያዩ ጊዜያት ተጋድሎ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህም የድል አጥቢያ አርበኞች ሊነጥቋት ይችላሉ» የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በጣም የሚስብ ነበር። እርስ በእርስ መደጋገፍ ካለ የድል አርበኛ መሆን ይቻላል። እናም ራስን አይቶ ለሌሎች መቆም እንደሚያስፈልግና የድል አጥቢያ አርበኛ መሆን እንደማይገባ፤ ሁሉም በራሱ የመሮጫ መስመር (መም) ከመሄድ ተቆጥቦ ለሀገር በሚጠቅሙ የጋራ አስተሳሰቦች ላይ እንዲደመር የሚያስተምር ንግግራቸው ሁሉም ውስጥ የቀረ እንደነበር ይናገራል።
«ፍቅርን በቴአትር ማሳየት ብቻ ሳይሆን ፍቅርን በህይወት መኖርን መልመድ ይገባችኋል» ያሉትም በጣም የሚገርም እንደነበር የሚገልጸው ደራሲ አንዱአለም፤ አብዛኞቹ የዘርፉ ባለሙያዎች ለሌሎች ማሳየትን እንጂ መኖርን ባለመልመዳቸው የተነሳ ተከታዮች አርአያ የሚያደርጉት እነርሱን በመሆኑ እየጠፉ ናቸው። የሙያውን ስነምግባር በቅጡ አውቆ የመገዛት ባህል ባለመዳበሩ እንዲሁ ችግሮች እየተፈጠሩ መጥተዋል። ስለዚህም ይህን በመኖር መተርጎም ለሁሉም የተሰጠ የቤት ሥራ በመሆኑ መለወጥ ከተቻለ ጥሩ እንደሚሆን ይናገራል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ «እናንተ ሠርታችሁበት ቢሆን ኖሮ በአገሪቱ ላይ እየተከሰተ ያለው ብሄር ተኮር ግጭት ባልተፈጠረ ነበር» ያሉትም በአርአያነታችን ህብረተሰቡን መለወጥ ባለመቻላችን ነው ይላል።
እንደ ገጣሚና ደራሲ አንዱአለም በጉብኝቱ ላይ የታዘበውንም ጠቁሞናል፤ «ገለጻቸው የባለሙያን አቅም ያማከለና ችግሮችን በሚገባ ያሳየ ነው። ሆኖም በጉብኝቱ ላይ የታየው ክፍተት ግን ያሳዝናል። ቤተመንግስቱን ከነታሪኩ አንድ በአንድ እየጎበኙ ሳለ ከሚያደምጠው ይልቅ ፎቶ ለመነሳትና ማውራት የሚቀናው ብዙ ነበር። ይህ ደግሞ ለጉራ ተብሎ ወደቦታው ያመራው ባለሙያ እንዳለ ያመላክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ጥሪ እስከዛሬ ከነበረው ዞር በር፣ በዚህ አትለፍና ወዘተ የሚል ድምጽ የራቀ ነው። ቤተመንግስቱ የእናንተ ነው የሚል ስሜትም የተንጸባረቀበት ነበር። ታዲያ ያለን ጊዜ መጠቀም ሲገባ ወሬ መድራቱ ተገቢ አልነበረም»
በሥነ ጽሑፍና በቴአትሩ ዓለም የሌሎች አገራትን ተሞክሮ አይቶ መሥራት ላይ ክፍተት ያለ ሲሆን፤ አሁን የተሰጠው እድል መልካም ጅማሮ ነው። ክብር የሚገኘው በትህትና ውስጥ መሆኑን ያሳዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጥበብ ጋር መቆራኘት ለአገር ልዕልና ያለውን ትልቅ አስተዋጽኦ ተረድተው በአብሮነት ለመሥራት ትጉ ማለታቸውም ይበል ያሰኛል። ይሁንና ባለሙያው ጉዳዩን በስሜት እንጂ ከልቡ ካልተረዳው ችግሩ ችግር ሆኖ ይቀጥላል ብሎ እንደሚያምንም ይገልጻል። አሁን ላይ እየታየ እንዳለው ለውጥ፤ ዶክተር አብይን የመሰሉ በየደረጃው ያሉ አመራሮች እንደሚያስፈልጉና ዘርፉን ደጋፊና አዋቂም መኖር እንዳለበት ጠቁሟል።
«ኑ ለሰላም አብረን እንደመር፤ አገራችንን ካለችበት ችግር እናላቃት። እንደእናንተ አይነት መሪና መካሪ ያስፈልጋል» በመጀመሪያ የደረሰው መልዕክት እንደነበር የገለጸው ደግሞ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ ነው። እርሱ እንደሚለው፤ ጥሪው የስልጠና ሲሆን፤ የተገኘው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው። ምክርና የቀጣይ አቅጣጫ ጠቋሚ ሃሳቦች ተንጸባርቀውበታል። ባለሙያውም ያለበትን ክፍተት እንዲያይ አድርጎታል። የቤት ሥራን እንዲወስድና በተግባርም እንዲሳይ የሚያነሳሳ ነው። በተለይም ወጣቱ አገር ወዳድና ለአገሩ ተቆርቋሪ እንዲሆን የኪነ-ጥበብ ባለሙያው የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አደራ የሚሰጥ እንደነበር አስተውሏል። የቆዩትን አርአያ በመከተል የማይረሱ ስራዎችን ማበርከትም እንደሚገባ ተገልጾበታል።
እንደ አርቲስት ዳንኤል ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ለህዝቡ እየቀረቡ ባሉት የፊልምና ቴአትር ሥራዎች ዙሪያ ኢትዮጵያን ከመግለጽ አኳያ ችግር እንዳለ ተጠቁሟል። ስለዚህም የኪነ-ጥበብ ዘርፉ የኢትዮጵያዊነትን ትክክለኛ ገፅታና ስሜት ማሳየት አለበት። ለዚህ ችግሩ ደግሞ ሙያተኛው በነጻነት እንዲጽፍ፤ እንዲሰራና እንዲንቀሳቀስ አለመፈቀዱ ነበር። ነገር ግን አሁን ሁሉም በእጃችሁ እንደሆነ በማሰብ ልትሠሩ ይገባል መባሉ አስደሳች መልዕክት ነበር።
«ከባለሙያው በላይ ኪነጥበብን በሚገባ የሚያውቁ፤ ሥራዎች እንዴት እንደሚከናወኑ የተረዱና ባለሙያውን በሙያዊ ቋንቋ ማናገር የሚችሉ መሪ በማየቴ እጅግ ተደስቻለሁ» የሚለው አርቲስት ዳንኤል፤ ዶክተር አብይ የሁሉ ሙያ ባለቤትና ሁሉ የተሰጣቸው እንደሆኑ የተረዳው ክፍተታቸው ምን ላይ እንደነበረ በሙያው ቋንቋ ሲግባቡ ሲመለከት እንደነበር ያስረዳል። በተለይም ሰዎችን በፍቅር ለማሸነፍ የከወኑት ተግባር ከጎናቸው ላለመቆም የሚያስችል እንዳልነበረና ይበልጥ ተነሳስቶ መስራት እንደሚጠበቅ ባቸው በተግባር ያሳያቸው መሆኑን ይናገራል።
«ስንወጣም ቢሆን ሁላችንንም ጨብጠውና ስመው ለስራ እንድንነቃ አሳስበው ነው የወጡት። ከዚህ በላይ አንድ መሪ ምን ሊያደርግ ይችላል? እንደእኔ እምነት ማንም ይህንን የተመለከተ አካል ወደ ኋላ ይላል የሚል ግምት የለኝም። ስለዚህም ወደፊት ለመገስገስ ቆርጫለሁ» ብሎናል።
«ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ምሉዕ በኩልዬ ናቸው። ሁሉን ያውቃሉ፤ ይረዳሉ። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ በአንባቢነታቸው ነው ብዬ አምናለሁ» በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ደግሞ የደራሲያን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደለ ገድሌ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የአገር ፍቅርና አንድነት ከራስ ሰላም የሚመነጭ ነው። እናም እርሳቸው የሰላም መሪ በመሆን ከሁሉም ጋር ለመግባባት የኪነጥበብ ባለሙያውን በቤተ መንግስት ሰብስበዋል። ከዚያም የይቅርታ አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ ማስረፅ የሚቻለው በዚህ ዘርፍ መሆኑን አምነው አድርጉት ብለዋል። ቀጣዩ ሥራ የሚሆነው የባለሙያው ነው።
የኪነ-ጥበብ ባለሙያው በማንኛውም አገራዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ዙሪያ መፍትሄ ሊያመላክቱ የሚችሉ አጋዥ ሃሳቦችን ያመነጫል ብሎ ያመነና ጥናት አጥንቶ ለሙያው ባለቤቶች ስልጠና የሰጠ መሪ እስካሁን አልገጠመኝም የሚሉት ዶክተር ታደለ፤ ዶክተር አብይ የውጭው እድገት ከኪነጥበብ አኳያ ምን ይመስላል፣ የእኛስ አገር ነባራዊ ሁኔታ እንዴት ነው? ከሚለው ጀምሮ ብዙ ነገር ያስዳሰሰ ገለጻ ሰጥተዋል። በዚህም እይታን የሚያሰፋ፣ ዘርፉ በተለይም ይቅርታንና ስነ-ምግባርን በተመለከተ የህብረተሰቡን አመለካከት ለመግራት ትልቅ መሳሪያ መሆኑን ያሳየ ገለፃ እንደነበር።
ፍሬያማና ዘመን ተሻጋሪ ሥራ እንደሚያስፈልግ በገለጻቸው እንዳመላከቱ የሚገልጹት ዶክተር ታደለ አሁን ላይ ከሳምንት በላይ የሚቆዩ ጭብጦች ለማህበረሰቡ አይቀርቡም። ትውልድ ቀራጭነታቸውም እንዲሁ ጎልቶ የሚታይ አይደለም። ትውልድን በትውልድ የሚያስተሳስር መሆን አልቻሉም። በመሆኑም በተሰጠው ነጻነት ሥነ ጽሑፍም ሆነ ሌሎች የኪነጥበብ ሥራዎች ህዝብን ለማነሳሳትና አንድ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፤ መሥራት እንደሚያስፈልግም የተመከረበት ስለሆነ ባለሙያው ከዚህ በኋላ ጠንካራ ሥራ ይሠራል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።
«ለህዝብ መቆም፣ ህዝብን መውደድና ስነምግባር ያለውና ቅንነት የተሞላበት መሆን ቀዳሚው ተግባር ነው። ብር ተኮር ከሆነ ግን ይበልጥ ኪሳራው ይጎላል። እናም የተከበረውን ባህል በብልሃትና በጥበብ ለትውልዱ ማስተላለፍ ላይ በስፋት መሠራት እንዳለበት፤ ይህም የእያንዳንዱ የኪነጥበብ ባለሙያ የቤት ሥራ ነበር። የኪነ-ጥበብ ሙያተኛው መደመርን የሚሰብኩ ሥራዎችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ አገሪቱን ወደላቀ ደረጃ ማሻገር የሚል መልዕክትን የያዘ ነው። በኪነ-ጥበብ ሥራዎች የህዝቡን ችግር በማንሳት መፍትሄ እንዲመጣ ማስቻልና ያልታዩ ጉዳዮችን መዳሰስ ይገባል፡፡ በመሆኑ እኛም እንተግብረው» መልዕክታቸው ነው። ሰላም!

ጽጌረዳ ጫንያለው

 

የሰኔ 30 ቀጠሮ

ሰኔ 30 ለተማሪዎች ወደ እረፍት ወራት መሸጋገሪያ ቀን ናት፤ ታድያ በዚህ እለት ከሚታወሱት ቀጠሮዎች መካከል የወላጆች ቀን አንዱ ነው። የተማሪ ወላጆች የልጆቻቸውን የውጤት ካርድ ይረከባሉ፤ በፊታቸውም ጎበዙ ተማሪ ይሸለማል። ወዲህ ደግሞ አስሩን የትምህርት ወራት ቂም ይዞ የኖረ ተማሪ ለመደባደብ ይቀጣጠራል፤ ሌላም ሌላም።
አጫጭር ስልጠና እና ትምህርቶችን ለመከታተልም ክረምቱን ቀጠሮ የሚይዝ ሰኔ 30 መሸጋገሪያው ናት። ወላጆች በተለይም እናቶች ልጆቻቸው በቤት ውስጥ ሥራ እንደሚያግዟቸው ተስፋ አድርገው ይጠብቃሉ። በተለይም ልጆችና ወጣቶች በየሃይማኖቱ ሃየማኖታዊ ትምህርትን በስፋት የሚያገኙት በክረምቱ ወቅት ነው፤ ከሰኔ 30 በኋላ።
ሌላም ቀጠሮ አለ፤ በትምህርት ወራት ከትምህርት ውጪ የሆኑ መጻሐፍትን እንዳያነቡ ይከለከሉ የነበሩ ልጆችም ለንባብ ፍቃድ እንደሚያገኙ የሚያረጋግጡበት እለት ነው። አሁን ከዘመኑ በ2010ኛው ዓመት ላይ በምንገኝበት ጊዜ፤ ይህቺ የጥቂት ተማሪዎች የነበረች ቀጠሮ አድጋ አገራዊ ሆናለች። ስለንባብ ንባብ እና ንባብ ብቻ የሚወራባት ዕለት።
የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ሰኔ ሰላሳ ቀን ብሔራዊ የንባብ ቀን ሆኖ እንዲከበር ለማድረግ እንቅስቃሴ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ማህበሩ ወደዛ ፓርላማውን እየጎተጎተ ወደዚህ ደግሞ ሕዝቡን እየቀሰቀሰ፤ ዕለቱንና ሰሞኑን አክብሮ ስለንባብ መልዕክቱን ያስተላልፋል።
«ሰኔ ሰላሳ ቀንን የመረጥነው ተማሪውም፣ መምህሩም፣ ካቢኔውና ፓርላማው እረፍት የሚያገኙበት ጊዜ ስለሆነ ነው። ወጣቱ በክረምት ሰሞን በአልባሌ ነገር እንዳይጠመድና በንባብ እንዲያሳልፍ ለማድረግ ምቹ ጊዜ ነው ብለን ስላመንን ነው።» ያሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙ ናቸው።
አንባቢ ትውልድን በመፍጠር ምን ይገኛል ያለን እንደሆነ ከአንባቢ ሰዎች የሚወጣውን ኃይል ያለው ሃሳብ እና ቃል መመልከት በቂ ነው። አቶ አበረ እንዳሉትም ያነበበ ትውልድ ምክንያታዊ ነው። ይህንንም ተከትሎ አሸናፊነት ይመጣል። ዘር፣ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ የኑሮ ደረጃ እያለ አይከፋፈልም፤ ንባቡ አዋቂ ስለሚያደርገው።
በእርግጥም በተለይ አሁን ባለንበት ጊዜ ላይ፤ መሪ አንባቢ ሲሆን ምን ያህል ተጽእኖ ፈጣሪ ሊሆን እንደሚችል ታዝበናል። የንባብ ጥቅም ከዚህ በላይ በተግባር ሊገለጥ አይችልም። ወደ ብሔራዊ የንባብ ቀን ጉዳይ ስንመለስ፤ ነገሩ የአንድ ቀን ጉዳይ ብቻ እንዳይደለ አቶ አበረ ነግረውናል።
ይልቁንም የንባብ ቀን በሚከበርበት ሰሞን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች፣ ዝነኛና ታዋቂ ሰዎች፣ በሙያ መስካቸውም ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ ሁሉ በየአካባቢያቸው እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን ስለንባብ የሚሰብኩበት ጊዜ ይሆናል። ይህ ታድያ ሰኔ 30ን ተከትለው የሚመጡትን የክረምት ቀናት በንባብ ለማሳለፍ የሚያስችል መነቃቃትና ፍላጎት በተማሪው፣ በወጣቱና በሠራተኛው ላይ መፍጠር የሚያስችል ነው።
የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ሰኔ 30ን የንባብ ቀን ሆኖ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር እየተንቀሳቀሰ ይሁን እንጂ እስከ አሁን በአዋጅ የፀደቀ ነገር የለም። 2005 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ሰኔ ሰላሳን አገራዊ የንባብ ቀን የማደርግ እንቅስቃሴ ዘንድሮ ስድስት ዓመት ሞልቶታል። ታድያ የሚመለከታቸው አካላት የማህበሩን «ቀጠሮው ይታወጅልን» ጥያቄ የት አደረሱት?
የንባብ ቀን አዋጅን ያዘገየው የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን አቶ አበረ ይናገራሉ። አንደኛው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያለው ያልተረጋጋ እና በየጊዜው የሚቀያየር አመራር ነው። አንዱ ጀምሮ ሲወጣ፣ ሌላው ሲረከብና ሲያዘገየው እስከዛሬ ቆይቷል። እሱም ብቻ ሳይሆን ፓርላማውም በቶሎ ግብረ መልስ አልሰጠም።
«በድምሩ ትኩረት ማጣት ነው፤ ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም» የሚሉት አቶ አበረ፤ እውነትም ደግሞ ሰኔ ሰላሳን አገራዊ የንባብ ቀን ለማድረግ ስድስት ዓመት ቢወስድም ጉዳዩ ከዚህ በኋላ ይቀየራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ይናገራሉ። ያም ባይሆንና ከዚህም በኋላ ምላሹ የሚዘገይ ቢሆን እንኳ እለቱንና ሰሞኑን ስለንባብ ከመወያየት፣ ከማስተማርና ከመቀስቀስ ማህበሩ እንደማይታቀብ ጠቁመዋል።
«የንባብ ቀን ሲባል አሁን ቀላል ይመስላል እንጂ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ፣ ወጣቱን ወደ ንባብ ሊያስጠጋ የሚችል ነው። ወጣቱ ከጫት እና ከአጉል ሱስ መታቀብ አለበት። ቃሚ ትውልድ ስሜታዊ ይሆናል እንጂ ልውጥ አያመጣም። ንባብን መርህ ያደረገ ዘመናዊ ትውልድ መፈጠር አለበት» ይላሉ አቶ አበረ።
ዘንድሮም ታድያ ይኸው የንባብ ቀን እንደማህበሩ ሃሳብ ከተሳካ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው። ማህበሩ በየጊዜው ከሚያካሂደው «ህያው የጥበብ ጉዞ» ጋር በማገናኘትም፤ የሰኔ ሰላሳን ቀጠሮ ከከተማ ውጪ ለማድረግ እቅድ ተይዟል። «ኢትዮጵያ ማለት አዲስ አበባ ብቻ ስላልሆነች፤ ከአዲስ አበባ ውጪ ያለው ወጣትም ደራሲውን ማወቅ አለበት፤ ደራሲውም ገጠሩን መመልከት አለበት። ያንን ዕድል ለመፍጠርና ለማስተሳሰር በማሰብ ነው ከከተማ ውጪ ለማድረግ ያሰብነው» ብለዋል።
እንደሚታወቀው ከዚህ ቀደም የነበረው ይህ ዝግጅት የመጻሕፍት ሽያጭና አውደርዕይ፣ እንዲሁም ጥናታዊ ወረቀቶች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች፣ የታላላቅ ደራስያን ልምድና ተሞክሮ መለዋወጫ መድረኮችና መሰል መርሃ ግብራትን ያካትት ነበር። ዘንድሮም በቀጠሮው እነዚህ መርሃ ግብራት አይዘነጉም።
በዚሁ አጋጣሚ አሁን የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ስላለበት ሁኔታ፣ በቅርቡ ስለሚጀመረው ስድስተኛ ዙር ስልጠና እንዲሁም ማህበሩ ወደፊትም ሊሠራ ስላሰባቸው ሥራዎች ሃሳባቸውን እንዲያጋሩን አቶ አበረን ጠይቀናል። የተወሰነውን እናካፍላችሁ፥
የማህበሩ አንዱ እቅድ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የሚያካሂዳቸው መድረኮችና ዝግጅቶች ናቸው። ከእነዚህ መካከል አንደኛው «ሥነ-ጽሑፍ ለአገራዊ መግባባት» በሚል መሪ ቃል በአገራችን አሁን በተጀመረው ለውጥ ላይ የሚያተኩር መድረክ ነው። ከፌዴራል እና አርብቶ አደር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርባሉ፣ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ይኖራሉ።
ማህበሩ በተለያዩ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ክፍለከተሞች ተመሳሳይ የመጻሕፍት አውደርዕይ ለማካሄድ እቅዶችን ይዟል። ይህም ባሳለፍነው ወር የተካሄደውን የመጻሕፍት ንባብና አውደርዕይ ተከትሎ የመጣ ነው። ሃያ ሰባት የመጻሕፍት አቅራቢዎች፣ አከፋፋዮችና አሳታሚዎች የተሳተፉበትና በርካታ ጎብኚዎችም የተገኙበት አውደርዕይና የመጻሕፍት ሽያጩ የተሳካ እንደነበር አቶ አበረ አስታውሰዋል።
ሌላው ደራስያን በአከፋፋዮች የሚደረስባቸውን ጫና ለመቀነስ፤ አንዱ ሌላውን ሳይበድል ሁለቱም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት እንዲመጣ ይሠራልም ተብሏል። በዚህ ረገድ የመጻሕፍት አሳታሚዎችና አከፋፋዮች ከማህበሩ ጎን እንደሚቆሙ እምነታቸው መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ነግረውናል።
የአፍሪካ ደራስያን ህብረት ጽሕፈት ቤትን ወደኢትዮጵያ ለማምጣት የተጀመረው እንቅስቃሴም እንደቀጠለ ነው። ምድረ ቀደምት የተባለች፣ የአፍሪካ መንግስታትም ማረፊያና መሰብሰቢያ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ የአፍሪካ ደራስያን መናኽሪያም ትሆን ዘንድ ማህበሩ እየሠራ ነው።
«ይህ የሚሆነው ዝምን ብለን ስለተመኘነው አይደለም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሰጠን 3ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ህንጻ ሠርተን፤ ቢሯችሁ ይህ ነውና ግቡ ማለት አለብን። ለዚህም ጠንክረን እየሠራን ነው» ያሉት አቶ አበረ። ከዚህ በተጓዳኝ ከውጭ ደራስያን ጋር ግንኙነት ለመመሥረት ጥሩ ጅምርና ውይይት እንዳለ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ከተለያዩ ማተሚያ ቤቶችና ድርጅቶች የሚሰጠው ድጋፍ አለ፤ ይህም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ገንዘብ በማህበሩ የተዘዋዋሪ ፈንድ ውስጥ ገብቶ ለአዳዲስና ወጣት የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ለመጻሕፍት ህትመት የሚውል ነው። ደራስያን ሥራቸውን ለማህበሩ ያስገቡና ማህበሩ ገምግሞና አወዳድሮ ለአንባቢ ቢደርሱ መልካም ነው ያላቸውን መርጦ ያሳትማል።
በዚህም መሰረት በዚህ ዓመት ለህትመት የገቡ ሶስት መጻሕፍት አሉ። ከነዛም መካከል አንደኛውና ከሰላሳ በላይ ደራስያንን የሕይወት ታሪክና ጉዞ የሚያስቃኝ መጽሐፍ ነው። ተወዳድረው ካለፉት መካከል ቀሪዎቹ ሁለት የግለሰብ ሥራዎችም በቅርቡ ለህትመት ይበቃሉ።
ሌላው ደግሞ ማኅበሩ በየዓመቱ የሚየካሂደው የሥነ ጽሑፍ ስልጠና ነው። የዘንድሮው የክረምት ስልጠና ዝግጅት ተጠናቋል። ታዋቂ የሥነ ጽሑፍ ምሁራን፣ ሃያሲያን፣ ደራሲያንም ወጣቱን ሊያሰለጥኑ ተዘጋጅተዋል። የኢትዮጵያን ድርሰት ማበረታታት እና ወጣት ደራስያንን ማፍራት ዓላማው የሆነው ማህበሩ፤ ይህም ወጣት ደራስያንን ለማፍራትና ከቀደሙት ልምድ እንዲወስዱ ለማድረግ ተመራጭ መንገድ ሆኖ ተገኝቷል። ማህበሩም ምን ላይ በስፋት መሥራት እንዳለበት የሚመለከትበትና የሚማርበት ነው ተብሏል።
ይህ ዓመታዊ የክረምት ስልጠና ታድያ ግቡ እንዲህ ሆኖ መቀጠል እንዳይደለ አቶ አበረ ነግረውናል። «እንደውም ዓላማው የሥነ ጽሑፍ ማሰልጠኛ ማዕከል መገንባት ነው። የተወሰነ ክፍሉን ወስደን ማሰልጠኛ ለማድረግ ሃሳብ አለን። ደራስያን ማሰልጠን ማፍለቅ አለብንና ነው» ብለዋል።
ይኸው ነው፤ ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ቢነሱም የተወሰነውን ጠቃቅሰናል። የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር በጠባብ ቢሮ ትልቅ ርዕይ ይዞ የሚገኝ ማህበር ነው። ስለንባብና አንባቢነት ከተነሳም የማህበሩን ስም አለመጥቀስ አይቻልም። ከማህበሩ እድሜ አንጻር አሁንም ገና ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸው ግልጽ ነው። ይህንንም ወደፊት የምንጠብቀው ለውጥ ይሆናል።
በዚህ እናብቃ! ሰኔ ሰላሳ አገራዊ የንባብ ቀን ሆኖ መከበሩ እንዳለ ሆኖ፤ አገርም ትኩረት መስጠቷን ያመላክት ዘንድ ከፓርላማውና ከሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሹን ሁሉም የሚጠብቀው ይሆናል። ስለንባብ በሚሰጥ ትኩረት ብዙ እናተርፋለን እንጂ ምንም አናጎድልም። እስከዛ ግን ማንበብ ማንበብ አሁንም ማንበብ ምክንያታዊ፣ አዋቂና መሪ ያደርጋልና እናንብብ፣ የሰኔ ሰላሳ ሰው ይበለን።

ሊድያ ተስፋዬ

የ«ባዮስፌር»  ሁለት ገፅታ

የዓለም ህዝብ ቁጥር እየበዛ በመጣበት ወቅት የተፈጥሮ ሀብትን የመመዝበሩ ጉዳይ የሰው ዘርንም እንዳያጠፋው አሳሳቢ ሆኗል። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) «ሰው እና ባዮስፌር» የተሰኘ ፕሮግራም በማዘጋጀት ለብዝሃ ህይወት መጠበቅ ቁልፍ ሚና ያላቸውን የዓለም አካባቢዎች በጥብቅነት እንዲቆዩ ጥረት እንደሚያደርገ ይገልፃል። የባዮስፌር ሪዘርቭ (ህይወተ ክልል ስፍራ) የሰው ልጅ ባህሉን እና አኗኗሩን በማይጎዳ መልኩ የተፈጥሮ ሀብትን እየተጠቀመ ለቀጣይ ትውልድ እንዲያስተላልፍ ዓላማ አድርጓል። በሰውና በተፈጥሮ መካከል ያለውን ትስስር ሚዛናዊ በማድረግ ባህል እና አኗኗርን በማይጎዳ መልኩ የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ማድረግ ላይ ያተኩራል።
እንደ ዩኔስኮ መረጃ ከሆነ፤ በአሁኑ ወቅት 669 ጥብቅ የባዮስፌር ቦታዎች በ120 አገራት ተመዝግበው ይገኛሉ። ምዝገባው የየአካባቢውን ህዝብ ባህልና ወግ በማይፃረር መልኩ የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል ስልቶችን ለመንደፍ ያግዛል። የየአገራቱንም የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ልምድ ለሌላው ለማጋራት ያስችላል። ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ደግሞ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ አምስት የባዮስፌር የዓለም ጥብቅ አካባቢዎች ተመዝግበዋል። የጣና እና አካባቢው፣ የያዩ ጥብቅ ደን፣ የከፋ ቡና እና ጥብቅ ደን፣ የሸካ ጥብቅ ደን እና የማጃንግ ጥብቅ ደኖች ዋነኞቹ ናቸው። ይሁንና የባዮስፌር ምዝገባው አስፈላጊነቱ ላይ ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎች ለየቅል የሆነ ሃሳባቸውን ሲያንጸባርቁ ይስተዋላል።
በአካባቢ እና የሰው ልጅ መስተጋብር ላይ በሰሜን አሜሪካ ጥናት የሚያደርጉት አቶ ሰለሞን ደስታ እንደሚገልፁት፤ ባዮስፌር የአየር፣ ውሃ እና ምድርን ስነ ምህዳር ውህድ የሆኑ አካላት ለሰው ልጆች ያላቸውን አስፈላጊነት በአጠቃላይ የሚያጠና ሳይንስ ነው። ዩኔስኮ ደግሞ አንድን ለሰው ህይወት አስፈላጊ ነው ተብሎ የታመነበትን ቦታ በጥብቅ የዓለም ሀብትነት በባዮስፌር ክልልነት ምዝገባ ያደርጋል። ይህም ልክ እንደ ልዩ ቅርሶች እንደሚደረገው ለአካባቢዎቹ ጥበቃ ለማድረግ ታስቦ ነው። ነገር ግን በባዮስፌርነት የተመዘገበ ቦታ ያላት አገር ስለቦታዎቹ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የምትቀበል በመሆኑ ለህጉ ተገዥ ትሆናለች። ኢትዮጵያም አምስት የተለያዩ ቦታዎችን በዓለም የባዮስፌር ክልልነት በማስመዝገቧ በተለየ መልኩ የአካባቢዎቹን ብዝሃ ህይወት አጠቃቀሟ ላይ ክትትል እንዲደረግ ይረዳል።
እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ፤ ጥብቅ ቦታዎች በባዮስፌርነት መመዝገባቸው ከባህል ልምዶች እና ኢኮኖሚያዊ አጠቃቀም አንፃር ለኢትዮጵያ አዋጭ አይደለም። ምክንያቱም አንድ ቦታ የዓለም ባዮስፌር አካል ተብሎ ከተመዘገበ ዩኔስኮ እና የዓለም አገራት ቦታው ላይ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ሥራዎች እንዳይካሄዱ የሚያግድ ሕግ አላቸው። የየአካባቢውን ማህበረሰብ ባህሉን እና ልምዱን የተመረኮዙ ሥራዎችን ለማከናወን በአካባቢው ጫካ ውስጥ ባህላዊ ንብ ማርባት ሥራ ቢያከናውን እክል ሊገጥመው ይችላል። ማህበረሰቡ የተፈጥሮ ሀብቱን ተጠቅሞ ሌሎችም ክንውኖች ሊያደርግ ቢሞክር ብዝሃ ህይወቱን መጉዳት እና አለመጉዳቱ በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እስኪጣራ ድረስ ሊታገድ ይችላል። በዋናነት ደግሞ ኢትዮጵያ በባዮስፌር የተመዘገቡ ጥብቅ ደኖች ውስጥ ይሁን ጣና ሐይቅ ላይ የተለየ ማዕድን ወይም ሀብት ብታገኝ ያንን ሀብት አውጥታ እንዳትጠቀም ክልከላ ይደረግባታል። የውጭ አካላትም መገናኛ ብዙሃኑ በእጃቸው ስለሆነ ኢትዮጵያ በባዮስፌር የተመዘገቡ ቦታዎችን እያወደመች ነው በሚል ሰበብ ውግዘትን ሊያስከትሉብን ይችላሉ።
የባዮስፌርን ምዝገባን ተከትሎ የሚደረጉ ክልከላዎችን ተጽዕኖ የተረዱ በርካታ የዓለም አገራት የተለያዩ የተፈጥሮ ቦታዎቻቸው በባዮስፌር እንዳይመዘገብ አድርገዋል። ምክንያቱም ወደፊት ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እራሳቸውን ከክልከላ ነፃ እያደረጉ ነው። በኢትዮጵያ ግን እንደ ጥሩ ነገር ተቆጥሮ በውጭ አገራት እና በሕግ ቁጥጥር ውስጥ የተፈጥሮ ሀብቶችች እንዲገቡ መደረጉ አግባብ አይደለም። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በባዮስፌር ያስመዘገበቻቸው ለዓለም የአየር ንበረት በጎ አስተዋጽኦ አላቸው የሚባሉ ቦታዎች ጉዳት ሲደርስባቸው ዩኒስኮም ሆነ ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ኃላፊነት ያለቸው የዓለም አገራት ምንም ያደረጉት ድጋፍ የለም። ለአብነት የጣና ሐይቅ በእንቦጭ አረም ሲወረር አዲስ አበባ ቢሮውን ከፍቶ የሚሰራው የዩኒስኮ ተቋም በተለይም ስለባዮስፌር ያገባኛል ብሎ እንደመንቀሳቀሱ ለሐይቁ ያደረገው ድጋፍ የለም። በመሆኑም ለኢትዮጵያ የጥብቅ ቦታዎቹ ምዝገባው ፋይዳ እንደሌለው አቶ ሰለሞን ይናገራሉ።

በዩኔስኮ የተመዘገቡ ጥብቅ ቦታዎች


«ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ቦታዎችን በባዮስፌር የዓለም ጥብቅ ቦታነት ማስመዝገቧ ጥቅም ያስገኛል ተብሎ አይጠበቅም» የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ አስመዝግባ ያስቀመጠቻቸው ቦታዎች ላይ ወደፊት የተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ለማግኘት ያላት ዕድል በዩኔስኮ እጅ እንዲወድቅ ያደርጋል። ስለዚህም በኢትዮጵያ ተጨማሪ ቦታዎች በባዮስፌር ጥብቅ ክልል ምዝገባ ውስጥ እንዳይገቡ መከላከል ያስፈልጋል። ተጨማሪ ቦታዎችን በባዮስፌር የዩኒስኮ የተፈጥሮ ሀብት ውስጥ ማስመዝገብ የሚቀጥል ከሆነ ግን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቶቿ ወደፊት ልትጠቀም የምትችለውን ያህል እንዳትጠቀም ልጓም የማስቀመጥ ያህል እንደሚቆጠር ይናገራሉ። በቀጣዩ ትውልድ ላይ የሚያደርሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ ከፍተኛ በመሆኑ አገርን ይጎዳልና ካሁኑ ሊታሰብበት እንደሚገባም ያሳስባሉ።
የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የማይንቀሳቀስ ቅርስ ልማት ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ፀሐይ እሸቴ እንደሚገልፁት፤ የዩኔስኮ የአንድ አካባቢ ባዮስፌር ምዝገባ ሰው እና አካባቢ ባላቸው ግንኙነት ውስጥ የሰው ልጅ ያላአግባብ የብዝሃ ህይወት ምዝበራ በማካሄድ ብዝሃ ህይወት እንዳይጎዳ የሚጠብቅ ሥራን ለማከናወን ያለመ ነው። ምዝገባው የመሬትን፣ የአየር እና አካባቢያዊ ሁኔታን በማጥናት በዓለም ላይ ያሉ ለሰው ልጅ ህይወት አስፈላጊ የሆኑ ቦታዎችን ለመጠበቅ ልዩ ትኩረት ያደርጋል እንጂ የሰው ልጅ ከባህሉ እና ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ ላይ ጋሬጣ እንዲጥልበት አያደርግም።
በተለይ ከዓለም የአየር ንብረት መጨመር ጋር ተያይዞ የሰው ልጅ ህይወት አደጋ ላይ እየወደቀ ባለበት ወቅት ይህን የሰው ልጅ ዘር ከመጥፋት ለመታደግ ደግሞ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የስነ ምህዳር ሀብት ያላቸው ቦታዎች እንዲጠበቁ ዓለም አቀፍ ሕግ ወጥቷል። ከኢትዮጵያም እንደ ጣና እና ሸካ ደን የመሳሰሉ ቦታዎች እንዲጠበቁ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክት ተቀርፆ በዩኔስኮ አማካኝነት ተመዝግቦ ለሰው ልጅ ህይወት መቀጠል አስፈላጊ ከሆኑ ቦታዎች መካከል ተመድበው ዓለም አቀፍ ጥበቃ እየተደረገላቸው ይገኛሉ።
ወይዘሮ ፀሐይ እንደሚሉት፤ «ኢትዮጵያ ጥብቅ ቦታዎቹን በማስመዝገባ ወደፊት ለሚገኝ ሀብት ተጠቃሚ አትሆንም» የሚለው ሥጋት መሰረት የለውም። ምክንያቱም የዚህ አይነቱ ሥጋት ቦታዎቹ ላይ ያለውን ስነ ምህዳር እስካልጎዳ ድረስ ሀብቱን አውጥታ አትጠቀምም የሚል መከራከሪያ አያስነሳም። ዋናው ጉዳይ የአካባቢዎቹን ተፈጥሮአዊ ባህሪ እንዳይጠፋ እና ለሰው ልጆች ያለውን ጥቅም ማስቀጠል በመሆኑ ማዕድንም ሆነ ሌላ የተፈጥሮ ሀብት አውጥቶ መጠቀም የሚከለክል ሕግ የለም። ነገር ግን ኢትዮጵያም ከቦታው የምታገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ስትወስድ ለቦታውም እንክብካቤ አስፈላጊው ጥበቃ በተጓዳኝ እንዲደረግ ደግሞ ዩኔስኮም ክትትል ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም ወደፊት ኢትዮጵያ ጥብቅ ቦታዎቹ ላይ የተፈጥሮ ሀብቶቿን ለመጠቀም እክል ይገጥማታል ብሎ መደምደም አያስፈልግም።
እንደ ወይዘሮ ፀሐይ ገለፃ፤ እንደ አሜሪካ፣ ቻይና እና የአውሮፓ አገራት በባዮስፌር ያስመዘገቧቸው አካባቢዎች አሏቸው። እንደየ አስፈላጊነቱም በጥብቅ ቦታዎቻቸው ላይ መሥራት የሚፈልጉት ነገር ሲኖር ስነ ምህዳሩን ለሰው ልጅ በማይጎዳ መልኩ እየተጠቀሙ እየሰሩበት ይገኛሉ። የባዮስፌር ምዝገባ መደረጉ ጉዳት እንጂ ጥቅም እንደሌለው ብቻ ማሰብ አይገባም። ነገር ግን ዓለም አንድ መንደር እየሆነች በመጣችበት ወቅት ስለ ኢትዮጵያ ጥብቅ የባዮስፌር አካባቢዎች የሌላው ዓለም ህዝቦችም እንደሚያገባቸው ማሰብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የአማዞን ደን ኦክስጂን ለሰው ልጆች ህይወት ጥቅም እንዳለው ሁሉ የኢትዮጵያ ጥብቅ ቦታዎች እና ሐይቆች በተመሳሳይ ለሌላው ዓለም ህዝብ ንፁህ አየር እንዲያገኙ ይረዳል።
እንደ ጣና ሃይቅ ያሉ በባዮስፌር የተመዘገቡ ሐይቆች በእንቦጭ አረም ሲወረር እና ጥብቅ ደኖች ጉዳት ሲደርስባቸው ምንም ድጋፍ ከዩኒስኮ አልተደረገም በሚል ምክንያት ባዮስፌር አያስፈልግም ማለት እንደማይገባም ይናገራሉ። ኢትዮጵያ በእራሷ ቦታዎች ጉዳት ሲደርስባቸው አስፈላጊውን መረጃ አሟልታ እና አካሄዱን ተከትላ ጥያቄዎችን ለዩኔስኮ አቅርባለች ወይ? የሚለውን መፈተሽ ይገባልም ይላሉ። ጥያቄው በተደራጀ ሁኔታ ቢቀርብ ቦታዎቹ ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉበት ሁኔታ አለ፤ በደፈናው ባዮስፌር ለኢትዮጵያ አይጠቅምም ብሎ መደምደም ግን ተገቢነት የሌለው መሆኑንም ያስረዳሉ።
አንድ አገር ገንዘብ እና ዕውቀት ከሌላ አካል ስትጠይቅ አስፈላጊውን መንገድ እና አካሄድ መከተል አለባት። ጥብቅ ቦታዎቹ ላይ ጉዳት ሲደርስም የመከላከል ሥራውን የጋራ አድርጋ መውሰድ ይኖርባታል። ነገር ግን በቦታዎቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር የሚያውቀው በአካባቢው ያለው ሰው ወይም ቦታው ያለበት አገር ሆኖ ሳለ ስለችግሩ ለዩኔስኮ በተገቢው አካሄድ ሳያስረዳ ቆይቶ ይህንን አላደረገም መባሉ ትክክል እንዳይደለም ይገልፃሉ። ድጋፍ ማግኘት የሚቻለው ተገቢውን ጥያቄ መመለስ ሲቻል ነው እንጂ በደፈናው ምዝገባው አልጠቀመንም የሚል ድምዳሜ መስጠት እንደማያስፈልግም ነው የሚያስገነዝቡት።
እንደ ወይዘሮ ፀሐይ ከሆነ፤ የባዮስፌር ጥበቃ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ አካባቢዎች ዕውቅና በመስጠት ዓለም አቀፍ ጥበቃ እንዲያገኙ የሚረዳ አሠራር ነው። በመሆኑም አስፈላጊነቱ የማያጠራጥር በመሆኑ የተመዘገቡ ጥብቅ ቦታዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው የተደራጀ ጥያቄ እና ሰነድ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ባዮስፌር አያስፈልግም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ በርን ዝግ እንደማድረግ ስለሚቆጠር ጥብቅ አካባቢዎች ተገቢው ጥበቃ እንዳይደረ ግላቸው እክል መፍጠር ይሆናል። በዚህም ለሰው ልጅ ተስማሚ የሆነ አየር በማጣት ተጎጂ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ሕዝቦች ጭምር ናቸው። እናም ምልከታው ይስተካከል።

ጌትነት ተስፋማርያም

የባህል ማዕከላት- ስኬት አልባ ጉዞ

የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል አዲስ ምዕራፍ ሊጀምር የተዘጋጀ ይመስላል፤ እንደሚሳካለትም ተስፋ በማድረግ እንጀምራለን። ይህም ማዕከሉ አዲስ መሪ ወይም አመራር ከማግኘቱ ጋር ይገናኛል። ማዕከሉ አንድ ሁለት ተብለው የማይቆጠሩ በርካታ ችግሮች ያሉበትና ብዙዎችም በየጊዜው ቅሬታ የሚያነሱበት ነው። ይህም ችግር ከላይ የመጣ ይሁን ከታች የወጣ፤ በብቁ አመራር ሊለወጥ እንደሚችል ያለንበት ጊዜም ምስክር ይሆነናልና ተስፋችንን የበለጠ እናጠነክራለን።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ ከሳምንት በፊት የባህል ማዕከላት ጉባኤ በሻሸመኔ ከተማ የተካሄደው። ይህም አራተኛው መድረክ የኦሮሚያ ባህል ማዕከል አዘጋጅቶት የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል በአስተባባሪነት የተሳተፈበት ነው። እኛም ጉዳዩን ለመዘገብ ከአዲስ አበባ 241 ኪሎሜትር ርቀት፤ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ የተገኘነው ዕኩለ ቀን ከገፋ በኋላ ነው፤ ሰኔ 10 ቀን 2010ዓ.ም።
የባህል ማዕከላት ጉባኤ መካሄዱ በባህል ማዕከላት መካከል የልምድ ልውውጡ እንዲኖርና ሥራቸውን ለማቀላጠፍ ይረዳቸው ዘንድ ነው። ዓላማውም ቃል በቃል በባህል ማዕከላት መካከል የተሞክሮና የልምድ ልውውጥ በማድረግ፤ ማዕከላቱን በማጠናከርና በጋራ ትብብር የሚተጋገዙበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አቅማቸውን እንዲገነቡና ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ ማገዝ ነው።
በዚህ ላይ የባህል ማዕከላት በዋናነት የባህል እሴቶች የሚበለጽጉበት ብሎም ለእይታና ለአገልግሎት የማቅረብ ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት መሆናቸው ሊነሳ ይገባል። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገጽ ላይ የባህል ማዕከል ራዕይ ተብሎ የተቀመጠው «የባህል እሴቶች መግለጫዎች በልጽገው፣ ተዋውቀውና ለአገልግሎት በቅተው ለአገር ልማት ውለው ማየት» የሚል ነው።
ታድያ የባህል ማዕከላትን በአግባቡ መጠቀም ባህልን ከማቆየትና ለተረካቢው ትውልድ ከማስረከብ አንፃር ትልቅ ሚና አለው። ከዛም በተጓዳኝ ጥናትና ምርምር በሁሉም ዘርፍ አስፈላጊ በሆነበት በዚህ ጊዜ ባህሎች በጊዜ ሂደት ኋላቀር እንዳይባሉና በየዘመኑ ሕዝብን ማገልገል እንዲችሉ ለማድረግ ጥናትና ምርምር የሚደረገው በእነዚህ ማዕከላት ውስጥ ነው። ይህም ማለት ማዕከሉ አገር በቀል ዕውቀትን ለማሳደግ፣ ለማስተዋወቅና ለመጠቀም ከፍተኛ ድርሻ የአለው ነው።
ታድያ ይህን የሚያክል አገራዊ ሥራ ያለባቸው ተቋማት በዕውኑ ምን እየሠሩ ነው? ልክ ሻሸመኔ ላይ እንዳገናኘውና ከዚህ ቀደም በተለያዩ ክልል ከተሞች ላይ የተካሄደው ጉባኤ ወይም ዓመታዊ የጋራ መድረክስ ምን ውጤት ተገኘበት?
የባህል ማዕከላት እንቅስቃሴ
የባህል ማዕከላት በመላው አገሪቱ ስማቸው መጠራትና መታወቅ ከጀመሩ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። ስያሜው ይለያይና በአዳራሽ ይወሰን እንጂ ተቀራራቢ ዓላማ ያለው ተቋምን ለመገንባት በደርግ ዘመነ መንግሥትም ጥረት ይደረግ ነበር። አሁን ላይ ያለውን እንቅስቃሴ ስንቃኝ ባህል ማዕከላት ስም፣ ቦታ እና ኃላፊነት ይዘው በመሥራት ላይ ናቸው። ይሁንና ከግንባታ እንዲሁም ከውስጣዊ መዋቅር ስንጀምር በባህል ማዕከላት መካከል ጉራማይሌ መሆን ይስተዋላል። በክልሎችም መካከል ልዩነቶች ጎልተው ይታያሉ።
አንዳንድ ባህል ማዕከላት በአዳራሽና በኪነጥበብ ሥራ ላይ ትኩረት አድረገው ሲሠሩ የተቀሩት ደግሞ የጥናት ማዕከልና ቤተመጻሕፍትንም በግንባታው ውስጥ ያካትታሉ። በአንፃሩ አንዳንድ ክልሎች ግንባታ ጨርሰው ሥራ ውስጥ የገቡ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የመሰረት ድንጋይ ጥለው የተቀመጡ አሉ። ይህ በክልሎች የሚታይ ችግር ታድያ ወደታችም በዞን እና በከተማ ደረጃም ማዕከላት እንዳይስፋፉና እንዳይጠናከሩ እንቅፋት ሲሆን ይታያል። በዕኩል እርምጃ የማይሄዱ በተለያዩ ቦታ ያሉ ተመሳሳይ ተቋማትን ማስተናገድ ደግሞ አይቻልም። ይህም በዘርፉ ላይ ለውጥ ይምጣ የሚል ብርቱ ኃይል ቢመጣ እንኳ በአንድነት ሊያስኬዳቸው እንደማይችል ያመላክታል።
ማዕከላቱ የሚጠበቅባቸውን እንዳይሠሩ የሚያደርገው አንዱና ትልቁ ችግር ይኸው ነው፤ ወጥ የሆነ አደረጃጀትና አሠራር አለመኖሩ። ይህም ብሔራዊ የባህል ማዕከል እንዲሁም ከላይ ሆኖ የሚከታተለው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቸል ለማለት ዕድል የሰጣቸው ይመስላል። ስለዚህ ከባህል ማዕከላት የሚፈለገው የመጀመሪያ ውጤት ወጥ የሆነ አደረጃጀትን መዘርጋት ነው። በይበልጥ ደግሞ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ጉዳዩ ይመለከተዋል።
አቶ ጠይብ አባፎጊ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው። እንደርሳቸው ገለፃ፤ የባህል ማዕከላት አስፈላጊነት አንዳች አያጠራጥርም። በተለይም ብዙ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ፀጋ በታደለች አገር ላይ በባህልና ቱሪዝም ላይ መሥራት ዓይንን ሳያሹ የሚቀበሉት ጉዳይ ነው። ጭስ አልባ ኢንደስትሪ ከሚባለው ቱሪዝም ለመጠቀምም ተመራጭ መንገድ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ካላት ሀብት አንፃር የተጠቀመችው ቢጠና ገና ጅምር ነው ይላሉ። የባህል ማዕከላትንም በሚመለከት ተቋማቱ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው በብዛት የሚታየውን ጅምር ማጠናከር ይገባል፤ እኛም በጥብቅ እንከታተላለን ብለዋል።
«ብሔራዊ የባህል ማዕከል ተጠናክሮ እና አድጎ ሥራውን በአግባቡ ከሠራ ሌሎች በክልል እና በዞን ያሉት የማይጠናከሩበት ሁኔታ የለም። ወጥ በሆነ መልክ ባህል ማዕከላትን ማጠናከር እንዲቻል በዋናነት ብሔራዊ የባህል ማዕከሉ መጠናከር አለበት፤ ለዛም የተጀመረ ሥራ አለ፤ እሱንም እየተከታተልን ነው።» ብለዋል፤ አቶ ጠይብ አባፎጊ።
ክልሎች ለባህል ማዕከላት የሰጡት ትኩረት በቂ አይደለም። ከዚህ ጋር አያይዘው አቶ ጠይብ እንደጠቀሱት፤ ምንም እንኳ ብዙ በጅምር ላይ ያሉና ብዙም ያልተንቀሳቀሱ ማዕከላት ቢኖሩም፤ ጅምሩን ማበረታታት የበለጠ ለማጠናከር ስለሚረዳ ሁሉም ባለበት ደረጃ ሊበረታታ ይገባል።
የአመራር ቁርጠኝነት የለም፣ በየጊዜው የሚደረጉ የአደረጃጀት ለውጦችም ሥራውን አጓተውታል የሚሉት አቶ መሀመድ አምቢሶ፤ በደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ የባህል፣ የታሪክና የቅርስ ጥናትና ልማት ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። በደቡብ ክልል የባህል ማዕከላት እንቅስቃሴ ሲታይ ዞኖች ጋር የተሻለ ጥንካሬ ይታያል። ለምሳሌ በክልሉ ጋሞ ጎፋ ዞን ግንባታው 90 በመቶ ደርሷል የተባለ የባህል ማዕከል ግንባታ ተከናውኗል። የጋሞ፣ ጎፋ፣ ኦይዳ፣ ዛይሴ እና ጊዲቾ ብሔረሰቦችን መልክ እንዲያሳይ ታስቦ በዞን ደረጃ የተሠራው ይህ የባህል ማዕከል በደቡበ ክልል፤ በዞን ደረጃ የሚሞካሽ ማዕከል ነው። ከዛም ባሻገር በክልሉ በተለያዩ ዞኖች የባህል ማዕከላት እንቅስቃሴ እና ወደባህል ማዕከልነት የሚደርስ አካሄድ ይታያል።
በክልል ደረጃ የባህል ማዕከል ለመገንባት የተጣለ የመሰረት ድንጋይ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ ፀሐይና ዝናብ ሲፈራረቅበት ቆይቷል። «አምሳ ስድስት ብሔር ብሔረሰቦች ወካይ የባህል ማዕከል ለማሠራት የዲዛይን ሥራ ትኩረት ይፈልጋል። ለዛ ነው ሰፊ ጊዜ የወሰደው።» የሚል አመክንዩ የቀረበ ቢሆንም፤ የአመራር ቁርጠኝነት አለመኖር ለችግሩ መንስኤ ቅርብ ይመስላል። አቶ መሀመድ እንዳሉትም፤ ሰነዶች ተዘጋጅተው ቢቀርቡም የክልሉ መንግሥት ፈቃድ እስኪሰጥ፣ አመራሮችም ወስነው ወደ ሥራ እንዲገባ ትዕዛዝ እስኪያስተላልፉና አደረጃጀትም ነጋ ጠባ መቀያየር እስኪተው ድረስ የባህል ማዕከል ግንባታ የሚታሰብ አይሆንም።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አሁንም ልምድ ከመቅሰምና ተሞክሮን ከመቀመር አልቦዘነም። በዚህ ላይ ወጥ የሆነ አደረጃጀት አለመኖ መፍትሄ ካላገኘ በቀር በየስፍራው የተቀመጠው የመሰረት ድንጋይ ድንጋይ ሆኖ ይቀራል። ይህ በቅርብ ለማግኘት የተሳካልን መረጃ ሆነ እንጂ በሌሎችም ክልሎች እንዲሁም በዞንና ከተሞች በተመሳሳይ ሁኔታ የባህል ማዕከላት ሥራ ተጓቷል። ይመለከታቸዋል ተብለው በክብር እንግድነት የመሰረት ድንጋይ የሚጥለው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች የሚያውቋቸው ተጥለው፤ በዛውም ተረስተው እንዳይቀሩ የሚያሰጉ በርካታ ጅምር የባህል ማዕከላት መኖራቸውም ግልጽ ነው።
ይህን ያዝ አድርገን ግንባታቸውን ጨርሰው በሥራ ላይ ናቸው የሚባሉ የባህል ማዕከላትም ችግር ሳያጣቸው ቀርቶ አይደለም። ለምሳሌ የኦሮሞ የባህል ማዕከል፤ በራሱ ሊፈታው ከሚችለው ውስጣዊ ችግር ባሻገር የሰው ኃይል እጥረት አለበት። በአሁኑ ሰዓት ሊኖር ከሚገባው ባለሙያ ውስጥ 46 በመቶ ብቻ ይዞ ነው እየሠራ የሚገኘው።
ይህ ጉዳይ ባህል ማዕከሉ በፈለገው መንገድ ተደራሽ እንዳይሆን ያደርገዋል። የኦሮሞ የባህል ማዕከል ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ገመቹ ዳዲ እንዳሉት፤ ከማኅበረሰቡ ለበለጠ ጥናትና ግምገማ የሚቀርቡ መጻሐፍትን በብቃት ሳይሆን በሰው ኃይል እጥረት ምክንያት ለማየት እንደተቸገሩ ይናገራሉ። ውጤትን ፍለጋ እየተንቀሳቀሰ ያለ ተቋም በቅድሚያ ችግሮቹን ነጥሎ ማውጣትን ያስቀድማል። ለዛም ነው በእነዚህ ችግሮች ላይ ትኩረት የተደረገው። ከዛ ባሻገር ግን የባህል ማዕከላትን የጋራ መድረክ ከመፍጠር ጀምሮ ጥሩ የሚባሉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው አይካድም። ግን ውጤትን ካላስገኘ ዋጋው ምኑ ጋር ነው?
የባህል ማዕከላት የጋራ መድረክ ቅኝት
የባህል ማዕከላት የጋራ መድረክ መከፈቱ ያለጥርጥር አስመስጋኝ ጉዳይ ነው። በሚገባ መጠቀም ከተቻለም በዘርፉ ችግራቸውን በጋራ ይጥላሉ፤ ድልን በጋራ ይጎናጸፋሉ፤ ለአገርም ጥቅም ይሰጣሉ። እንደሃምሳ ሎሚ፤ በመተጋገዝ የሚቀሉና የሚፈቱ ችግሮች መኖራቸው አይቀርምና። ታድያ በተጨባጭ ያለውን ሁኔታ ስንቃኝ የባህል ማዕከላት ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ ያካሄዷቸውና ያለፉት ሦስት ጉባኤያት እንዲህ ነበሩ ተብሎ በሻሸመኔው አራተኛ ጉባኤ ላይ የቀረበውን ሪፖርት እንታዘባለን። በዛም የባህል ማዕከላት አሁንም ውጤትን ፍለጋ ላይ መሆናቸውን እናያለን። ዘገባው እንዲህ ነው፤
የመጀመሪያው መድረክ በሐረር ከተማ የተዘጋጀ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ በወልቂጤ የተካሄደ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ዓመት በ2009 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ ተከናውኗል። ታድያ በሁሉም ጉባኤያት ላይ የሚነሳው አንዱ ጥያቄ ወጥ የሆነ አደረጃጀት ወይም ደረጃ /Standard/ እንዲኖር ነው። ይህም የባህል ማዕከላት ግንባታ ሂደት ምን መምሰል አለበት ከሚለው ጀምሮ ውስጣዊ አደረጃጀትና ሥራን የሚመለከት ነው። ከውጫዊ ገጽታ አንፃር ብናይ እንኳ አንዳንዶቹ አዳራሽ ብቻ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ የጥናት ማዕከል፣ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት እንዲሁም ሙዝየም ይዘው ይገኛሉ።
ከዚህ ባሻገር በባህል ማዕከላት መካከል ትስስርና አብሮ መሥራት በጉባኤው ላይ በየዓመቱ የሚነሳ ጉዳይ ነው። የዚህን ውጤት ብንፈልግ ለዓመታዊ ጉባኤውና ሌሎች የሚያገናኙ መድረኮች ካልተፈጠሩ በቀር በጋራ መሥራትና መናበብ አይታይም። «ባለፈው የወሰድከውና ያደነቅከውን ልምድ ምን አደረስከው? የተረከብከውን ፈፀምክ ወይ?» ብሎ መጠያየቅና መደጋገፍ አይስተዋልም። ይልቁንም የጉባኤው ተሳታፊዎች ቁጥር መብዛት ጋር ተያይዞ፤ ጉባኤው በሚካሄድበት ከተማና አካባቢ የሚደርግ ጉብኝት የማይረሳና ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል።
በጉባኤያቱ ላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሳተፉና እነርሱም በበኩላቸው የባህል ማዕከላት እንዲኖራቸው መቀስቀሱ ሊበረታታና ሊጠናከር የሚገባ ጉዳይ ነው። በተጓዳኝ በጋራ መድረኩ ላይ ጥናታዊ ወረቀቶች መቅረባቸው የሚበረታታ ሆኖ ለሚቀርቡ ጥናታዊ ወረቀቶች ይዘትና ብቃት ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ይህም በዘንድሮው ፍፁም ትኩረት የተነፈገው ጉዳይ ይመስላል።
እናብቃ! ብሔራዊ የባህል ማዕከል አዲስ አመራር ከማግኘቱ ጋር በተገናኘ እነዚህ ችግሮች የመጨረሻ ሊሆኑ እንደሚችሉና ማዕከሉ ከሚነስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በጋራ ሊፈታቸው የሚችለውን ችግር ለማየት እንደሚንቀሳቀስ ተስፋ እናደርጋለን። ይህም ከራሱ ሥራና ኃላፊነት በተጓዳኝ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ለሁሉም አረአያ በመሆን በኩል ድርሻ ስላለው ነው። ውጤት ፍለጋው የተሳካ ይሁን እያልን፤ የተነሱት ችግሮችም «የችግር ዳርቻ» እንዲሆኑ እንመኛለን።

ሊድያ ተስፋዬ

   በጡሩምባ የተገፉ ዓመታት

 

ሌሊት ወጥተው ምሽት በመግባት ይታወቃሉ። ጡርንባ በመንፋትና በቤት ሰራተኝነት ዓመታትን አሳልፈዋል። ካገኙ ቀምሰው ካጡ ደግሞ ተኮራምተው ማደር ለእሳችው ብርቅ አይደለም። በመስራት መለወጥን ያምናሉና ማንኛውንም እንጀራ የሚያስገኝ ስራን አይንቁም። በተለይ የጉልበት ሥራን። ጡርምባ መንፋትና የእድር ሥራዎችንም በመስራት ልጆቻቸውን አሳድገዋል። ሲያምጡና ሲወልዱ ማንንም ጠርተው አያወቁም። እትብቱን ራሳቸው ቆርጠው እራሳቸው ይቀብራሉ።
ይህ ከመሆኑ በፊት ግን እጅግ በሚያስገርም የህይወት መስመር አልፈዋል። ዛሬም ድረስ እንደታሪክ የሚያወሱት አስደናቂው የህይወት ጉዟቸው ደግሞ በእርሳቸው ማንነት ውስጥ ተቀብሮ የሚቀር ብቻ አልሆነም። ለሚሰሙት ሁሉ አፍ የሚያሲዝና ልብ የሚነካ እውነት አለው። እኔ ስለጠንካራዋ ወይዘሮ ማንነት በሰማሁ ጊዜ በእጅጉ ተደምሚያለሁ። ይህ ግርምታዬ ግን በእኔ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አልፈለግሁምና የዛሬ የህይወት እንዲህ ናት እንግዳዬ አደረኳቸው። የእርሳቸውን የኑሮ ውጣውረድና ጠመዝማዛውን የህይወት መንገድ ላስቃኛችሁ ወደድኩ። ወይዘሮ ሙሉ ዋሴ ይባላሉ። ተከተሉኝ።
የልጅነት ጊዜ
ትውልዳቸው ደቡብ ጎንደር ልዩ ስሙ ስማዳ አርጋሚካኤል ነው። እድሜያቸውን በቅጡ አያውቁትም። ከጭውውታችን ግን ለመረዳት እንደሚቻለው ስልሳዎቹን ያለፉ ይመስላል። የወይዘሮ ሙሉ አባት በአካባቢው አሉ የተባሉ ጠንካራ ገበሬና የተጣላን አስታራቂ ሽማግሌ ናቸው። እናታቸው ደግሞ የተመሰገኑ የቤት እመቤት። በእነ ወይዘሮ ሙሉ ቤት ሁሉም በእኩል ደረጃ ያርሳል፣ ያጭዳል፣ ይቆፍራል። ሁሉን የሚከውነው በደስታና በፍላጎት ነበር። በቤተሰቡ መሀል ከሳቅ ጨዋታ ሌላ ጭንቀትና ጥላቻ የለም። እናም ወይዘሮ ሙሉ አይረሴውን የልጅነት ጊዜ ያሳለፉት በተለየ ደስታ ተሞልተው ነው። የዛኔ እንደማናቸውም የመንደሩ ልጆች በሚወዷቸው ጨዋታዎች ዘለዋል፣ በሜዳ በመስኩ ቦርቀዋል። ማርና ወተቱም ሳይጎድልባቸው አድገዋል።
አንድ ቀን ግን ይህንን ሁሉ ታሪክ በነበር የሚያስቀር አጋጣሚ ተፈጠረ። ሞት ቤታቸውን በድንገት አንኳኳ። አዲስ እንግዳን ሲጠብቅ የነበረ ቤተሰብ እማወራውን በወሊድ ምክንያት ተነጠቀ። ደስታ ነግሶበት የነበረው ጎጆ ሀዘንና ለቅሶ ውሎ አደረበት። ሰንበት ሲል ደግሞ በቤቱ ሰላም ጠፋ፤ እርስ በእርስ መነታረክና መጨቃጨቁም በረታ። ጥቂት ቆይቶ አባት ሌላ ሚስት አገቡ። ይህ ውሳኔም የቤቱን ልጆች ሁሉ ለስደትና እንክርት ዳረጋቸው። ወይዘሮ ሙሉም ነጋዴዎችን ተከትለው ከአካባቢው ራቁ። እምብዛም ያልጠነከረው የልጅነት ጉልበታቸው ግን ርቀው እንዳይጓዙ ስለሚገድባቸው በቀላሉ ተይዘው ወደዚያው ቤተሰቡ ለመመለስ ይገደዱ ነበር። አንድ ቀን ግን ከልብ ወስነው ጠንክረው ተጓዙ። እስቴ ወደተባለ አገር አቅንተውም ህይወትን በዛው ቀጠሉ።
የጉልበት ሥራ
«ለእኔ ሥራዬ እንደ ልጄ ነበር። በመጀመሪያ ይህንን ሥራዬን ልጄ ያደረኩት እስቴ ስገባ ነው። ሁለት ዓመት ባልጠነከረ ጉልበቴ ለቤትና ለሆዴ መሙያ ስል ያልሰራሁት አልነበረም። በተለይም ከቤተሰብ ለመሸሽ በነበረኝ ፍላጎት ብዙ ጫና አሳድሮብኛል» የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ እስቴ እያሉ ያጭዱ፣ ያርሱና ነዶ ይጭኑ እንደነበር አይረሱትም። ከዚያ ወጥተው ባህርዳር ሲገቡም ጣና ሀይቅ ሁሉ ነገራቸው ሆኖላቸው ነበር።
በዛ ስፍራ ዓሳ አጥምዶ በቀላል ዋጋ መሸጥን ተማሩ። ጥቂት ገንዘብ ሲይዙም ከዓሳው ሽያጭ ጋር ጠላ እየጠመቁ በርካታ ደንበኞችን አፈሩ። ቀጥለውም ቀለል ያለች ምግብ ቤት ከፈቱ። የዛኔ ሀብት ቋሚ የሚሆነው በወርቅና ብር ተለውጦ ሲቀመጥ ነበርና እርሳቸውም ገንዘባቸውን እንደዘመኑ ልማድ ለውጠው በአግባቡ አኖሩት። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አንድ ሀሳብ በአዕምሯቸው ተከሰተ። ብዙ ወደሚነገርላት አዲስ አበባ መግባት ተመኙ።
ከድጡ ወደ ማጡ
ባህርዳርን ተሰናብተው አባይን ሲሻገሩ አንዲት ሴት ብርታት ጥንካሬያቸውን አይታ ለአዲስ አበባ እንደሚመጥኑና እርሷም እንደልጇ ልትንከባከባቸው ቃል መግባቷን ያስታውሳሉ። በተለይም የሴትዬዋ ኑሮዋ በብቸኝነት መሆኑ ያሰቡትን ለማሳካት እንደሚረዳቸው አምነዋል። በስፍራው ሲደርሱ ግን የጠበቃቸው ተቃራኒ ሆነ። ብቻዬን ነኝ ያለችው ሴት ዋሽታቸዋለች። የምትኖረው ከእናቷ ጋር በመሆኑ እርሳቸውን መንከባከብ ግዴታ ተጣለባቸው። ሌሎችን ቀጥረው ሲያሰሩ የቆዩት ወይዘሮ ሙሉ ተቀጣሪ ሆኑ። የወር ደመወዝ የሌላቸው ተቀጣሪ።
እየተደበደቡና የቁጣ ናዳ እየወረደባቸው የሚገዙ አሽከር ሆኑ። እናቲቱ በየጊዜው የሚደግሱት አያጡም። ሰንበቴና ሌላም ጉዳዮቻቸው ይበረክታሉ። ወይዘሮ ሙሉም ከአቅማቸው በላይ እየሰሩ ለድግሱ የሚሆነውን ሁሉ ያዘጋጃሉ። በጉልበታቸው ሰርቶ ማደሩ ባያስከፋቸውም ድብደባውን ግን መቋቋም አልቻሉም። ውሃ ቀጠነ ተብለው ይሰደባሉ፤ ሮጠው የሚሄዱበትና የሚያውቃቸው ሰው ስለሌለ ውርጅብኙን በጸጋ ከመቀበል ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም። አንድቀን ደግሞ በድንገት መባረርን የሚያስከትል ጥፋት አጠፋሽ ተባሉ።
የሰሩት ሥራ «እሰይ» ሊያስብላቸው ቢችልም ውሳኔው ግን ከቤት መባረር ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የሚያስገርም ነው። የተቦካው ሊጥ ሊቆመጥጥ በመሆኑ ጋግረው በመጠበቃቸው ድርጊታቸው እንደነውር ተቆጠረ። እስከዛን ቀን ድረስ ሴትዬዋ ካልመጡ መጋገርም ሆነ ሊጡን መንካት አይፈቀድላቸውም ነበር። አሁን ህግ ተላልፈዋል። ይህም ድርጊት እናትና ልጁን አስቆጥቷል። በምላሹ የዱላ ውርጂብኝ ያስተናገዱት ሙሉ መጨረሻቸው ከቤት በመባረር ተቋጭቷል።


የሰው አገር ሰው የሆኑት ሙሉ ከቤት ተባረዋል። ማደሪያ ጥግና ማኩረፊያ ዘመድ ግን የላቸውም። የት ይደሩ፤ የሚያውቋቸው ጎረቤቶች እንኳን እንዳታስጠጓት የሚል ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል። መንገድ ከማደርና ጎዳና ላይ ከመውደቅ ሌላ ምርጫ አጥተዋል። በስንት ጥረት ያጠራቀሙትን ወርቅና ብር በሳጥን ይዘው ከአንዱ አንዱ በረንዳ እየተዘዋወሩ ቀናትን አሳለፉ። አንድ ቀን ግን ከባድ ፈተና ገጠማቸው። በእግራቸው እየተዘዋወሩና ደላላ እየፈለጉ ሳለ ከአንድ ሰው ጋር ተገናኙ። ሰውዬው ደላላ እደሆነና ሥራ እንደሚያስቀጥራቸው ነግሯቸዋል።
ደላላው በያዟት ሳጥን ላይ አይኑ ስላረፈ መቀማትን ፈልጓልና ስራ እንዳገኘላቸው ነግሮ እስኪመሽ ያስጠብቃቸዋል። በመጨረሻም አንድ ጓደኛውን ጠርቶ የማታለያ ሃሳብ እንዲያቀርብ ያደርገዋል። ጓደኛ ተብዬውም ገና እንደደረሰ « ዛሬ ገብረኤል ስለሆነ ብርድልብስ እየተሰጠ ነው ለምን ሄደህ አትቀበልም፤ አንቺስ ምን ትሰሪያለሽ ሄደሽ ተቀበይ» ሲል ያሳምናቸዋል። ደላላው ግን « መጀመሪያ ሁለታችሁ ተቀበሉ እኔ እዚህ ልጠብቃችሁ» ሲል ይመልሳል።
ይህ ዘዴ ያልገባቸው ወይዘሮ ሙሉም «እኔ የማርፍበት እንጂ ገንዘብ መቼ አጣሁ ብርም ሆነ ወርቅ አለኝ። ስለዚህም የትም መሄድ አልፈልግም» ይላሉ። ይህን ያወቀው ደላላም ይበልጥ ራሱን ዝግጁ ማድረግ ጀመረ። ሳጥኗንም ያለምክንያት እንዳልተያዘች አረጋገጠ። እስኪመሽም እሳቸውን ማዘናጋቱን ተያያዘው። ሁለቱ ባልንጀሮች ማንሾካሾክ ሲያበዙ ሊገሏቸውና ያላቸውን ንብረት ሊነጥቋቸው እንዳሰቡ የተረዱት ሙሉ «ከገንዘቡ ህይወቴ ይበልጣል» ሲሉ አመኑ። ጥቂት አስበውም «በል ጠብቅልኝ ደርሼ ልምጣ» በማለት ሳጥናቸውን አስረክበው ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደፊት ገሰገሱ። ራቅ ብለውም ኡኡታውን አቀለጡት። ሰሚ ቢያገኙም ንብረታቸውን አላስመለሱም።
ከዚህ በኋላ ቀድሞ ይወዷቸው ወደነበረ የአካባቢው ሴት አምርተው በእንግድነት ተቀመጡ። ጎረቤትዬዋ ጥሩ ሴት ነበሩና ሁለት ሦስት ቀን ከቤት እንዳይወጡና እንዳይታዩ አድርገው አስቀመጧቸው። ከቀናት በኋላም ዋስ ሆነው በዘመድ ቤት አስቀጠሯቸው።
ሌላኛው የስቃይ ቤት
ፈተናን እጣ ክፍላቸው ያደረጉት ወይዘሮ ሙሉ 40 ዓመታትን የሰሩበት ቤት የገቡት ከዚህ በኋላ ነበር። የሰው ልጅ ምን ያህል እራስወዳድ እንደሆነ የተገነዘቡት በዚህ ቤት ሳሉ እንደነበር አይዘነጉትም። ምክንያቱም 40ዓመታትን ሲያሳልፉ ሆዳቸውን እንዲሞሉ ከማድረግ ውጪ ምንም አይነት ክፍያ አይሰጣቸውም። ይባስ ብሎ ያሏቸውን ሁለት ልጆች ብቻቸውን ከእናት በላይ ሆነው አሳድገዋል። የሽንት ጨርቅ ያጥባሉ፣ እንጀራ ይጋግራሉ፤ ቤት እየጠረጉ ልጅ ይጠብቃሉ፤ ከባድ የሚባል ሥራ የሚሰጣቸው ለእርሳቸው ብቻ ነበር። በተለይም በወንዶች አቅም የሚሰሩ እንደ እንጨት ፈለጣ፣ ሸክም፣ በሙቀጫ የሚከወኑና ጉልበትን የሚፈትኑ ሥራዎች የእርሳቸው ግዴታዎች ብቻ ናቸው።
በዚህ ቤት ደከመኝ ልረፍ ማለት አይቻልም፤ ልጁን ለደቂቃ እዩልኝ ብሎ ትቶ መውጣትም እንዲሁ ክልክል ነው። የተሰጠን ሥራ በተሰጠው ሰዓት አለማጠናቀቅም ያስጠይቃል። ከዚህ ቢወጡ ደግሞ የትም መሄድ አይችሉም። ሌላ ቦታ የሚያስቀጥር ሰውን አያውቁም። እናም አማራጫቸው ፈተናውን መቻል ብቻ ነበር። በመጨረሻ ግን አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ። አሰሪዎቻቸው አገር ለቀው ሌላ ቦታ ተጓዙ። አብረሽን ካልሄድን ቢሏቸውም እርሳቸው ስቃዩዋን ቀምሰዋታልና ከአዲስ አበባ መውጣት እንደማይፈልጉ ገልጸው ነጻነታቸውን አወጁ።
ከዚህ በኋላ በሰው ቤት መቀጠርን እርግፍ አድርገው ተው። ይህን ሲወስኑ ግን ማደሪያም ሆነ መኖሪያ አልነበራቸውም። አማራጭ እንደሌላቸው የተረዱት ወይዘሮ ሙሉ ዋስ ሆና ወደ አስቀጠረቻቸው ጎረቤት ሄደው ከመቅጠሩ ይልቅ በራሳቸው መስራት እንደሚፈልጉ አጫወቷት። እርሷም ትክክለኛ ምርጫ እንደመረጡና ከጎናቸው እንደምትቆም ነገረቻቸው። ብርታት ያገኙትም ወይዘሮ ሙሉም አንድ ክፍል ቤት ተከራይተው እንጨት ለቅሞ በመሸጥ ራሳቸውን ማኖር ጀመሩ።
ለራስ ራስ መኖር
ትንሿ ጎጆ ለእርሳቸው ሰላማዊ እረፍት ማግኛ ናት። ቀን ሙሉ በእንጦጦ ማርያም ጫካ እንጨት ለቅመውና ዳገቱን ወጥተው ወርደው ለሽያጭ ያቀርባሉ። ከዚያ ሲመለሱ ደግሞ እንጀራ በመጋገርና ልብስ በማጠብ ተመላላሽ ሥራ ይሰራሉ። ማምሻቸውንም ቆሎና ዳቧቸውን አዘጋጅተው መንገድ ዳር ለመሸጥ ይወጣሉ። «በሆዴ መደራደር አላውቅም» የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ ጦማቸውን ማደር አይወዱም። ድካም እንኳን ቢጥላቸው ጥቂት አረፍ ብለው ይመገባሉ። በተለይ አጥሚት ይወዳሉ፤ ከስንዴ ዳቦ ሌላ ግን የፈረንጅ ዳቦ ምርጫቸው ሆኖ አያውቅም። እንጀራን ከምንም በላይ ይመርጡታል። ከወጥ ደግሞ ለሽሮ ያለቸው ፍቅር የበረታ ነው።
ወይዘሮ ሙሉ «የሚሰራ ሰው ከምግብ ራሱን ማግለል የለበትም። ምክንያቱም የሚሰራው ለመብላትና ራስን ለማኖር ነው። በእጅጉ መልፋት፣ መስራትና ራስን መለወጥ ያስፈልጋል። በዚያው ልክ ደግሞ ለሚለፋ አካል እንክብካቤ ማድረግም ይገባል» የሚል እምነት አላቸው። ይህ በመሆኑም ጠንካራና ጉልበተኛ ሰራተኛ መሆን ችለዋል። ይህን ጥንካሬ ይዘው የተጓዙት ሴት አንድ ቀን አዲስ የህይወት ምዕራፍ መገለጡን ተረዱ። ከእርሳቸው ውጭ ሌላ ምግብን የሚሻ ሆድ ተጨምሯል። የመጀመሪያ ልጃቸውን አርግዘዋል። የዛኔ የሆነውን ሁሉ ዛሬ ላይም ያስታውሱታል።
አንድ ቀን አሰሪያቸው በሌሊት ተነስተው ለህክምና ወረፋ እንዲይዙላቸው ያዟቸዋል። እርሳቸውም እንጀራቸው ነውና ማንም እንዳይቀድመኝ በማለት ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ሰልፍ ለመያዝ ይወጣሉ። በስፍራው ሲደርሱ ግን ማንም በአካባቢው አልነበረም። ሆስፒታሉ ጥበቃ የሚደረግለት በወታደሮች ነውና ተረኛው ወታደር በዚህ ሰዓት ሰልፍ ለመያዝ ማን እንደመጣ ለመመልከት ወደ እርሳቸው ይጠጋል። «ለምን በዚህ ሰዓት መጣሽ ከ12 ሰዓት በፊት እኮ ሰልፍ አይጀመርም። አዲስ ነሽ?» ሲልም ይጠይቃቸዋል። እርሳቸውም እንዳይመታቸውና እንዳያባርራቸው በመስጋት ተሰልፈው እንደማያውቁና ለሌላ ሰው ወረፋ ለመያዝ እንደመጡ ይነግሩታል።
«ሰዓት እስኪደርስ ነይ እዚህ ብርድ እንዳይመታሽ የሚለበስ ልስጥሽና ተቀመጭ» ብሎ ይጋብዛቸዋል። ጥቂት ቆይቶ መብራት ሲበራና ሲተያዩ ጎረቤታማቾችና የአንድ አካባቢ ልጆች መሆናቸውን አወቁ። ወታደሩ በፊትም ያስባቸው ኖሮ አጋጣሚውን ለመጠቀም ሞከረ። የሰልፍ ሰዓት እስኪደርስም አብረው አሳለፉ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ለመጀመሪያ ልጃቸው መጸነስ ምክንያት ሆነ። የልጃቸው አባት እየተዘዋወረ ስለሚሰራ ይህንን ሳያውቅ ከአዲስ አበባ ወጣ። ይህኔ በራሳቸው መቆም ያልቻሉትን ወይዘሮ ሙሉ ተጨማሪ እዳ ተጫነባቸው። አርግዘው እንጨት ይሸከማሉ፣ ልብስ ያጥባሉ፣ ለድግስ እንጀራ፣ ወጥ፣ ጠላ በማዘጋጀትም ለመጪዋ ልጃቸው ጥሪት ያስቀምጡ ነበር።
ማስወርድ የሚባለው ነገር በወቅቱ አይታወቅም። ላድርገውም ቢሉ ይህንን ማድረግ የሚያስችል ገንዘብ የላቸውም። ስለዚህ ከአሁን አሁን እወልዳለሁ እያሉ በስራ ተጠምደው ቆዩ። በእርግጥ ሁለቱንም ልጆቻቸውን ሲወልዱም ሆነ ሲያረግዙ የአጋጣሚ ጉዳይ ነበር። በዚያው ልክ ማንንም መጥራትና ማስቸገር አይፈልጉም። እስከሚወልዱባት ጊዜና ሰዓት ድረስ በሥራ ተወጥረው ያሳልፋሉ። «እንኳን ማርያም ማረችሽ» የሚል ጠያቂና በወጉ የሚያርስ ዘመድ እንደሌላቸው ስለሚረዱም በማግስቱ ተነስተው ወደ ሥራቸው ይገባሉ።
ልጆች ያሳደገች ጡርምባ
ወይዘሮ ሙሉ ከ30 ዓመታት በላይ ሌሊት ተነስተው ጡርምባ በመንፋት ገንዘብ ያገኙ ነበር። ወተት የማያውቁትን ልጆቻቸውን ለማሳደግና ጡታቸውን በሚገባ ለማጥባት ጡርንባቸው ባለውለታቸው መሆኗን ይናገራሉ። ለስራቸው ትልቅ ክብር እንዳላቸው የሚያስረዱት ወይዘሮ ሙሉ፤ ልጃቸውን በአንቀልባቸው አዝለው ሰዓታቸውን ጠብቀው ሰርተዋል
ይህን ሲያስታውሱ በአንድ ወቅት የሆነውን አጋጣሚ ፈጽሞ አይዘነጉትም። የዛኔ ሌሊት 10፡00 ሰዓት ላይ ሁለተኛ ልጃቸውን ወልደው የእንግዴ ልጁን ለመቅበር ጓሯቸው እየቆፈሩ ነበር። ድንገት ግን «እከሌ ሞቷል ጡሩምባ ንፊ» የሚል መልዕክት ደረሳቸው። እንዲህም አሉ «የእኔም ሞት፣ የሞተውም ሞት ነው። እኔ ካለፈፍኩለት ደግሞ መሞቱን ሰምቶ ቀብሩን የሚፈጽምለት አይኖርም። ስለዚህም አደርገዋለሁ።» እንዳሉት ሆነና የተወለደውን ህጻን በሌላኛዋ ልጅ አስጠብቀው ለመለፈፍ ወጡ።
«ጡርምባዬ የልጆቼ እራት ናት፤ ጡርምባዬ የልጆቼ ህልውና ናት፤ ጡርንባዬ እንጀራዬ ናት»የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ የጡርምባ ሥራ በየቀኑ የሚያገኙበት ሥራ እንዳይደለ ይናገራሉ። ይህ ስራ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ሊመጣ ይችላል። አልፎ አልፎ ግን በተከታታይ በዛ ያለ ሰው ይሞታልና ገቢ አይታጣበትም። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ኑሮዬን የምደጉመው ጡርምባዬ በፈጠረችልኝ ተዛማጅ ሥራ ነው። ለምሳሌ ለአርባና ሰማንያ ሙት ዓመት መታሰቢያ ቀን ጠላ መጥመቅ፤ እንጀራ መጋገርና ወጥ መስራት» ይላሉ።
የሆነው ሆኖ ግን ከብቸኝነት ኑሮ ወደ ልጆች ማሳደግ ሲሸጋገሩ ብዙ ወጪዎች ነበረባቸው። ስለዚህም ኪራይ ለመክፈል ይቸገራሉ። ግድ የራሳቸው ቤት ማግኘት አለባቸው። ይህ ጉጉታቸው ደግሞ ጫካና የተወረሰ ቦታን እንዲያጸዱ አስገድዷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በወቅቱ በመንግስት ብዙ ቦታዎች ተወርሰዋል። ስለዚህም እየፈረሱ ሜዳ የሆኑ ቦታዎች ነበሩ። ይህንን የተረዱት ወይዘሮ ሙሉም ሽታና ቆሻሻን ሳይጸየፉ አንገት ማስገቢያ ቦታ ፍለጋ ማጽዳት ጀመሩ።
አፍንጮ በር በሚባለው አካባቢም ነዋሪዎች ቆሻሻ መድፊያ ያደረጉትን ሥፍራ ሌሊት እየተነሱ ለዓመታት አጸዱ። መጨረሻ ላይ ግን ቦታው መጸዳጃ ቤት ነበረበትና ፈንድቶ አካባቢውን አጥለቀለቀው። በዚህም ተይዘው ማረሚያ ቤት ገቡ። በጉዳዩ በተደጋጋሚ እየተከሰሱ ለእስር ተዳርገዋል። ይሁንና ለቅሶ ሲመጣ ለፋፊ ስለሚጠፋ የእድር ዳኛ ያስፈታቸው ነበር።
«በየጊዜው ቀበሌውን ብጠይቅም ምላሽ አልሰጥ አለኝ። ስለዚህም የማይፈለገውን ቦታ አጽድቼ አንገቴን ለማስገባት ይህንን አደረግሁ» የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ ጎጆ ለመቀለስ ገንዘብ ከፍለው መጸዳጃ ቤቱን አስመጥጠው ካስተካከሉት በኋላ ቦታውን ፈላጊ በዛበት «ልጆቻችን የት ይጫወቱ፣ እገሌ ፈልጎታልና ልቀቂ» የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ። ሆኖም አልበገር ባይነታቸው አይሎ ልጃቸውን እየያዙ በሳጠራ በከለሉት ቦታ ላይ ብርድ እየቆጋቸው ሳምንታትን አሳልፈዋል፤ ሽንት እየተለቀቀባቸው ቆይተዋል። ግን አጋር የሌለው ሆኑና ነገሩ ቆይቶ ቦታቸው ተወሰደ። ይህን ጊዜ አዘኑ፣ አምርረውም አለቀሱ።
መቼም የድሃ ለቅሶ ጠብ አይልምና ልፋታቸው ከንቱ ሆኖ ሳይቀር ከዓመታት በኋላ በድንገት ተጠሩ። ቦታውንም አስረከቧቸው። እርሳቸውም እንደወንድ ጭቃ አቡክተው፤ እንጨት ለቅመውና መሬቱን ደልድለው ቤታቸውን ሰሩ። ቆርቆሮ መቱ፤ ጭቃ ለጠፉ። ነገር ግን እንዲህ የለፉበት ቤት ብዙ ጊዜ አላቆያቸውም። በልማት ተነሺ ተብለው ዳግመኛ ወደ ኪራይ ቤት ተመለሱ። በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ አብዛኞቹ ተነሺዎች በክፍያ የሚታሙ አልነበሩምና ኮንዶሚኒም እንደሚሰጣቸው ቃል ተገባላቸው። «እርሷ መክፈል አትችልም። ስለዚህም እንዴት ከእኛ ጋር መካተት ትችላለች» የሚለው ስጋት የብዙዎች ዘንድ ነበር። ሆኖም እየሰራሽ ክፈይ ተብለው በግንፍሌ አካባቢ በተሰራው የጋራ መኖሪያ ቤት አካባቢ የቀን ሰራተኛ እንዲሆኑ ተደረጉ።
በሥራ የማይታሙት ወይዘሮ ሙሉም ወገባቸውን ታጥቀው ዓመታትን በትጋት አስቆጠሩ። ቃል የተገባላቸውን ቤት ግን ማግኘት አልቻሉም። እርሳቸው እንደሚሉትም፤ ያንቺ ነው የተባለው ባለአንድ መኝታ ቤት ቆይቶ ስለመሸጡ ሰሙ። ቤት የለሽምም ተባሉ። ያቋረጡት ክፍያ ሳይኖር ተስፋ ያደረጉት ቤት ግን አልነበረም። ለምን እንደተወሰደ ለመጠየቅ ያልረገጡት ቦታ አልነበረም። ምላሽ ግን አልተገኘም ።
ደጅ የጠኑባቸው አካላት መጨረሻ ላይ ጭቅጭቃቸው ሲበረታባቸው ከጋራ መኖሪያ ቤቶቹ መሀል ስቱዲዮ እንዲሰጣቸው ፈቀዱ። «በልፋቴ ልጆቼ የሚወድቁበት ቤት በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ፤ ለእለት እንጀራዬ ደግሞ ጡርምባዬ አለችልኝ» የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ የመጀመሪያ ልጃቸው አረብ አገር በመሄዷ ብቻቸውን ለአንደኛው ልጃቸው ህይወት ደክመዋል። ሆኖም ይህም ልጅ ዛሬ ላይ ስቃያቸው እንደሆነባቸው ያስረዳሉ።
«ገንዘብና ወገን የሌለው ሰው ሁልጊዜም ቢሆን ይህ ይገጥመዋል። አሁን እንኳን እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ማቅቄ ያስተማርኩት ልጅ በምን መልኩ እንደሆነ ባልታወቀበት ሁኔታ ውጤት መጥቶለት ተቀብሎ ቤት ሳይመለስ ዛፍ ስር ወድቆ በስንት ፍለጋ ተገኘ።» የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ፤ ለዓመታት ሳይናገር ችግሩን በውስጡ ይዞ ቆይቷል። በስንት ትግል ጸበል እያመጡ ከጠመቁት በኋላ አሁንም ከእርሳቸው ጋር ብቻ መነጋገር ጀምሮላቸዋል። ይሁንና ዛሬም ቢሆን ከማንም ጋር መገናኘትና ማውራት እንደማይፈልግ ይናገራሉ። ማሳከም እንዳለባቸው ቢረዱም «በምኔ ልታደገው፤ እጄን አጣጥፌ ተቀምጫለሁም» ይላሉ የልጃቸው ሀዘን ከውስጣቸው ሆኖ እያብከነከናቸው እንደሆነ ለመግለጽ።
ልጅ ስለ እናቷ
«እናቴ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ሰው መምህርት ናት። በሥራ ወደኋላ አትልም። ሁሌም ቢሆን በመስራት መለወጥ ይኖራል ብላ ታምናለች። ሌት ተቀን መልፋትንና መስራትን ከእርሷ ተምሪያለሁ። ይሁንና ከእጅ ወደአፍ ብቻ ነው ኑሯችን።» የምትለው ልጃቸው አስቴር ምትኩ፤ አጋዥ ቢኖር መለወጥም አብሮ ይመጣል። ማንም ስለሌላቸው ግን በእነርሱ ልፋት ብቻ መለወጥ እንዳልቻሉ ትናገራለች። በዚሁ ችግራቸው ላይ ደግሞ ወንድሟን እንኳን ማሳከም አቅቷቸዋል።
እናቷን ለማገዝ ብላ በስደት ሰው አገር ቆይታለች። ግን ያተረፈችው ምንም አልነበረም። አሁን እዚህ መጥታ ተደራጅታ ገና ሰሞኑን ኮብል እስቶን ላይ ለመስራት እየጣረች ነው። ከተሳካላት ወንድሟን እንደምታሳክም ካልሆነላት ግን እያየችው እንደምታዝን ነው የገለጸችው። «ሌሎች ሊማሩ የሚገባው የእናት ውለተዋ በቀላል ተነግሮ የሚያልቅ አለመሆኑን ነው። እኛን የምትመግበው ከጥሩንባ በምታገኛት 25 ብር ሲሆን፤ ከምግብ ሌላ ማሳከም የምትችልበት እንኳን እንደሌላት ብትረዳም ፊቷን ሳታጠቁር በደስታ በርቱልኝ ትላለች። ስለዚህም ለእናታችን ፍቅርና ክብር እንስጥ» መልዕክቷ ነው።
ከሆድ የቀረው ገጠመኝ
እናት ልጇን እያየች መቼም ቢሆን መቅበር እንደማትችል ማንም ይረዳል። ይሁንና እርሳቸው ግን ይህንን አድርገውታል። አሁን ባሉት ልጆች መካከል የወለዷትን ልጅ እንዲህ ተጠናክረው እድር ባልገቡበት ወቅት አጧት። ስለዚህም የሚቀብሩበት ቤተክርስቲያን የለም። ሁሉም ጋር ቢጠይቁ የሰበካ የከፈሉበትን ተጠየቁ። በዚያው ልክ ለቦታውም ሆነ ለማስቆፈሪያ የሚከፍሉት ገንዘብ የላቸውም። የልጅ አስከሬን ደግሞ ማደር የለበትም። ስለዚህ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ተጋቡ። በመጨረሻ ግን አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። ወደ ቀጨኔ መድሃኒአለም ሄደው ጥበቃውን አካፋና ዶማ ለመኑ። ወደ ጓሮ ዞሩ። ብዙ ክፍያ በማይጠየቅበት ቦታ ላይ እራሳቸው በመቆፈር ልጃቸውን አልቅሰው ቀበሩ። የተቀበሉትን እቃ መልሰውም ምንም እንዳልተፈጠረ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። «ሰው በሌለበት ብቻ አልቅሶ የራስን ልጅ ቆፍሮ መቅበር ምን ያህል እንደሚያሳምም የወለደ ይየው» ይላሉ።
ወይዘሮ ሙሉ እድሜያቸውን በሙሉ እጃቸውን ለልመና ሳይዘረጉ በጉልበታቸው ኑረዋል። ከሞት በኋሃላ ለመረዳዳት የሚፈጥኑትን እድሮች ለ30ዓመታት አገልግለዋል። እድሜ እየተጫጫናቸው ቢመጣም አሁንም ከህይወት ጋር ለመጋፈጥ እንደበረቱ ናቸው። ይሁን እንጂ ልጃቸውን ከህመም ለመታደግ ጉልበታቸው ብቻውን አላገዛቸውም። ልጃቸውን ለማሳከም የሚያግዛቸው ይፍለጋሉ። ቀሪ የህይወት ዘመናቸውን የተሻለ ለማድርግም አለሁልሽ የሚላቸው ካለ በዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ሊያገኛቸው ይችላል።ሰላም!

ፅጌረዳ ጫንያለው

Published in ማህበራዊ

«ጎጃም ያረሰውን ፣ ለጎንደር ካልሸጠ፣
ጎንደር ያረሰውን ለጎጃም ካልሸጠ፣
የሸዋ አባት ልጁን ለትግሬ ካልሰጠ፣
የሐረር ነጋዴ ወለጋ ካልሸጠ፣
ፍቅር ወዴት ወዴት ፣ ወዴት ዘመም ዘመም፣
ሀገርም አለችኝ ሀገር የኔ ህመም።
ስሩ እንዳይበጠስ መቋጠሪያው ደሙ
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው ቀለሙ...»
ይህ የአንድ ምሁር ዲስኩር አይደለም፤ ይህ የአንድ ሃይማኖት አባት የትንቢት ቃልም አይደለም፤ ይህ የአንድ የፖለቲካ ምሁር የትንታኔ ትንበያ አይደለም፤ይህ የአንዲት የጥበብ ሰው ከ20 ዓመት በፊት የተቀነቀነ ዜማ ለበስ ቅኔ ወይም ትንቢት ነው። የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፡፡
ማንኛውም ሙያ የራሱ ዓላማና ግብ እንዳለው አይካድም፡፡ ኪነጥበብ ግን የማትገባበትና የማትዳስሰው፣ የማታነቃቃው፣ የማታጀግነው፣ የማትደግፈውና የማትገስጸው የሙያ ዓይነት የለም። የአንድን ማህበረሰብ ወይም ሕዝብ ሁለንተናዊ ሰላም፣ እድገት፣ ብልጽግና፣ ደህንነትና ህልውናን ለማሳደግ፣ ለመጠበቅና ለመንከባከብ የተጣለበት ኃላፊነት ከሌላው ሙያ ሁሉ የከበደ ስለመሆኑ እማኝ መጥቀስ አያስፈልግም። ምክንያቱም የኖርንበት፣ የምንኖርበትና ያስተዋልነው እውነት ነውና፡፡
የኪነጥበብ ጉልበት የሚለካው የማህበረሰቡን ሁኔታ ተረድቶ ከማህበረሰቡ ደስታና ብሶት ጋር የሚያብር ሲሆን ነው። አብሮም ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን ሲተነብይም ጭምር ነው። ጥበብ ማህበረሰባዊ ናት የምንለውም ከማህበረሰቡ ተፈጥራ ለማህበረሰቡ በማገልገሏ ነው።
ኪነጥበብ የሕዝብ ከሕዝብ ለሕዝብ የተፈጠረች ናት፡፡ ይህም ማለት ኪነጥበብ ሁልጊዜ የሕዝብ መብትና ጥቅም፣ የሐቅ ተሟጋችና ጠበቃ ናት። የተፈጠረችበት ዓላማና ግብ ሕዝብን ማገልገል ለእውነት መሟገት ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ወይም እኩል የብስለት ደረጃ፣ የማሰብ አቅም፣ የማገናዘብ ችሎታ፣ የሀገር ፍቅርና የተቆርቋሪነት ስሜት አለው ማለት አይቻልም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ በመሆኑም ሁሉንም የሚያግባባው የኪነጥበብ ሚና ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት ከፊት የምትቆም መሆኗን ነው።
ሀገራችን አሁን ከገጠማት ብሄር ተኮር ጥላቻና መጠላለፍ ለመውጣት የሁሉንም ዜጋ ርብርብ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ርብርብ የዳር ተመልካች ወይም ገለልተኛ የሚባል ዜጋ ወይም ሙያ ሊኖር አይችልም፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር የግማሽ ቀን ቆይታ ማድረጋቸው ሚናቸውን ተረድተው አሁን ባለው የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ በሙያቸው ተደማሪ እንዲሆኑ ለማነሳሳት ነው።
በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዲህ ብለው ነበር «ማንም ሰው መርጦ ወይም ፈልጎ ከየትኛውም ብሄር አልተወለደም፤ ነገር ግን መርጠንና ፈልገን ልናደርገው የምንችለው ነገር ቢኖር መልካም ሰው መሆንና መልካም ነገር ማውረስ ነው» በርግጥም ማናችንም ብንሆን መርጠን፣ ወደንና ፈቅደን የተቀበልነው ብሄር የለም። ሁላችንም በአንዲት በኢትዮጵያ ጥላ ስር የተሰባሰብን አንድ ህዝቦች ነን። ይህን እውነት በመረዳት በሙያችን ተጠቅመን ማህበረሰባዊ ኃላፊነትን መወጣት ጊዜው የሚጠብቀው የህሊና ግዴታ ነው።
በመሆኑም እርስ በርሳችን ሊያናጩንና ሊያጋጩን የሚፈልጉ አካላት ካሉ «ተድምረናል አንሰማችሁም» ልንላቸው ይገባል። እኛ ከአባቶቻችን የተረከበንው የሙስሊም፣ የክርስቲያን፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌ፣ የትግሬ...የምትባል ሀገር ሳይሆን የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሀገር የሆነችውን ኢትዮጵያን ነው። የተረከብናትን አንዲት ኢትዮጵያን ለተረካቢዎቻችን አንድነቷን ጠብቀን ሀብቷን አበልጽገን ልናስረክባቸው ይገባል። በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሳ አስተሳሰብ አንድነቷ የተናጋ ሀገር ልናወርሳቸው አይገባም። የኪነጥበብ ባለሙያዎችም የዚህ ሀገራዊ ኃላፊነትን በጥበብ ስራዎቻቸው በመታገዝ ህብረተሰቡን ለአንድነት ማነሳሳት ይጠበቅባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን የሰላም፣ የፍቅር የይቅርታና የመደመር ጉዞ ጅማሮ ላይ ናት። በእንቅስቃሴያችን፣ ከድህነት ለመውጣት ለምናደርገው የመደመርና የአብሮነት ባህላችንን የምናጠናክርበት፣ ሁሉን አቀፍ ጥረት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ የእርስ በእርስ ትስስርን፣ የሀገር ፍቅር ስሜት በዜጎች ላይ እንዲሰርጽ ለማድረግ የምንተጋበት ጊዜ ነው። ከኪነጥበብ ባለሙያዎችም በመንግስት እየተደረገ ያለውን ጥሪ በሙያችን በማገዝ ተስፋ አመላካችና አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ ይጠበቃል፡፡
ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የአገር ፍቅርና የአንድነት አስተሳሰቦችን በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ የሚያስችሉ ተግባራት ለመከወን የተቀበላችሁትን የቤት ሥራ በተግባር ግለጹት። ለአገር ሰላምና ዕድገት መጫወት የሚጠበቅባችሁን ሚና ለማጎልበት በርቱ። በማንኛውም አገራዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ዙሪያ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አጋዥ ሃሳቦችን ለማመንጨት ያላችሁን አቅም ተጠቀሙበት። ዘርፉ በተለይም ይቅርታንና ስነ-ምግባርን በተመለከተ የህብረተሰቡን አመለካከት ለመግራት ትልቅ መሳሪያ ነውና የድርሻችሁን ልትወጡም ይገባል።
የአገራዊ አንድነትንና መደመርን የሚሰብኩ ሥራዎችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ አገሪቱን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ፍጠኑ። የኢትዮጵያዊነት ትክክለኛ ገፅታና ስሜትን ከመግለጽ አኳያ ወደፊት በስፋት ሊሰሩ በሚገባቸው ቁም ነገሮች ላይ ትኩረት ስጡ። የህዝቡን ችግር በማንሳት መፍትሄ እንዲመጣና ያልታዩ ጉዳዮችን በመዳሰስ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ለመጀመር ስንቃችሁ አድርጉ። በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶች ለማረጋጋት የመደመርና የፍቅርን ፋይዳም አቀንቅኑ። የጥበብን አቅምም አሳዩ፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የዓለም ባንክ በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንዳመለከተው ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2018 ወይም በ2010 እና 2011 ዓ.ም 9ነጥብ 6 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ታስመዝግባለች ብሏል። ይሁን እንጂ አገሪቱ እድገቷን የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮች ስለተደቀኑባት የተተነበየው እድገት ሊሳካ እንደማይችል ስጋት አለ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ገለጻ፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የነበሩ አለመረጋጋቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥረዋል። የኢኮኖሚ እድገቱንም ወደ አንድ አሃዝ አውርደውታል። በ2008ዓ.ም በተከሰተው ኤልኒኖ ሳቢያም የግብርናው ዘርፍ የስልተ ምርት ሥርዓቱ ስር-ነቀል ለውጥ ውስጥ እንዳይገባ ሆኗል። ይህ ደግሞ እስከ 2010ዓ.ም ድረስ የዕድገት ምጣኔው ከአየር ሁኔታው ጋር እንዲዋዥቅ አድርጎታል።
የውጭ ንግድ ሁኔታውም ሲታይ በ2010 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የካፒታል መጠን በ7ነጥብ7 ቢሊዮን ዝቅ ብሏል። በዚህም አገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ዕዳ ጫና ውስጥ ገብታለች። ይህ ደግሞ ገንዘቡን በአግባቡ ጥቅም ላይ አውሎ ወደ ተጨማሪ ካፒታል እና ትርፍ በመቀየር ዕዳን መክፈል እንዳይቻል አድርጓል፤ የውጭ ዕዳን የመክፈል አቅም እንዲቀንስም ምክንያት ሆኗል። ስለሆነም በእነዚህ ምክንያቶች የኢኮኖሚ እድገቱን ሊፈትኑት እንደሚችል መግለፃቸው ይታወሳል።
የኢፌዴሪ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበጀት ዙሪያ ከሕዝብ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፤ አገሪቱ እስካሁን ባላት እንቅስቃሴ የተሻለና ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡ አገራት ተርታ ተመድባለች። ሆኖም ከዚህ በኋላ ይህንን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አስቀጥላ ለመጓዝ ከባድ ችግሮች እንዳጋጠሟት አስታውሰው፤ ለዚህም አራት ምክንያቶችን ጠቅሰዋል። የኢኮኖሚው አወቃቀር ችግር፣ የውጭ ንግድ፣ የታክስ ገቢና የሥራ ዕድል ፈጠራ ናቸው።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የኢኮኖሚ እድገቱ አወቃቀር ችግር አምራች ኢንዱስትሪውና ግብርናው ሳይሆን ኢኮኖሚውን እየደገፈ ያለው የአገልግሎት ዘርፉና ኮንስትራክሽን መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ቀጣይነቱ ላይ ችግር ፈጥሯል። ተወዳዳሪነት ላይም ክፍተት ይፈጥራል። ለአብነት በ2009 ዓ.ም አገሪቱ በፈጣን እድገት ውስጥ ስትገባ 65 በመቶውን የሸፈነው የአገልግሎት ዘርፉና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ነበር። በዚህም ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪዎች እንዳይፈጠሩ፤ ግብርናውም አገልግሎቱን ደጓሚ ብቻ እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል። ይህ ደግሞ አገሪቱ ያሰበችውን የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት እንዳትችል አድርጓታል ይላሉ።
የውጭ ንግድ ችግር ሌላው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገቱን የተፈታተነውና በቀጣይም ችግሩን ሊያባብሰው የሚችል እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አብርሃም፤ ዘርፉ በ2010 በጀት ዓመት 3ቢሊዮን ዶላር ብቻ የተገኘበት ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ከኢኮኖሚው ያነሰ ገቢና የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲያጋጥም ያደረገ እንደነበር ያስረዳሉ። የኢኮኖሚው እድገት ላለፉት ስድስት ዓመታትም ብዙ እድገት ሳያሳይ ባለበት እንዲቀጥል ያደረገው ይኸው የውጭ ንግድ ውጤታማ አለመሆን እንደሆነ ይገልጻሉ።
እንደ ዶክተር አብርሃም ገለጻ፤ የመንግሥት የታክስ ገቢ ዝቅተኛነትና የሥራ ዕድል ፈጠራው አነስተኛ መሆንም የኢኮኖሚውን ፈጣን እድገት ከሚገቱ መካከል ናቸው። በ2010 ዓ.ም 200 ቢሊዮን ብር ከታክስ ይሰበሰባል ቢባልም ከ150 ቢሊዮን ብር በላይ እንደማይሰበሰብ ታምኖበታል። ይህ ደግሞ አገሪቱ በ2011ዓ.ም ተጨማሪ 60 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ካልቻለች ፈጣን የኢኮኖሚ እድገቷን ማስቀጠል አትችልም። እድገቱን ተከትሎ ፍላጎቶች ቢሰፉም በርካታ የሥራ ዕድል የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ከሥራው ጋር መገናኘት አልቻሉም። ስለዚህም አገሪቱ የተባለውን የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ብዙ መሰናክሎች አሉባት።
የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ረዳኢ ገብሬ በበኩላቸው፤ አገሪቱ በፈጣን እድገት ውስጥ እየተጓዘች ነው ቢባልም በተጋረጡባት በርካታ ችግሮች ምክንያት ከዓመት ዓመት እድገቷ ቀንሷል። በተለይም ተወዳዳሪ የሆነ አምራች ኢንዱስትሪ በአገር ደረጃ አለመፈጠራቸው፣ በሕግና ፖሊሲው የሚመራና ክትትል የሚያደርግ አካል አለመኖሩ እንዲሁም አፈጻጸሞች በተገቢው ሰዓት ታይተው ምላሽ አለመሰጠታቸው የኢኮኖሚውን እድገት ፈተና ውስጥ ከከተቱት ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ይናገራሉ።
እንደ አቶ ረዳኢ ገለጻ፤ ትልቁ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያሳድግ የሚችለው የታክስ ገቢ ነው። ሆኖም ታክስ በትክክለኛው መንገድ የሚከፍለው ሰው አነስተኛ ሆኗል። ለዚህም መንስኤው ለመደራደር በሚል ሰበብ ያለ አግባብ ግብር ተቆልሎ መሰጠቱ ነው። ይህ ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግርን በመፍጠሩ የተነሳ አገሪቱ ተገቢውን ግብር እንዳትሰበስብ አድርጓታል። ሌላው እድገቱን የሚፈትነው ጉዳይ የግዢ ሁኔታው ሲሆን፤ አላስፈላጊ ግዥ በተለይም በመንግሥት መስሪያቤቶች የሰፋ በመሆኑ ከፍተኛ ገንዘብ ለብክነት እየተዳረገ ይገኛል። ይህም ለኢኮኖሚ እድገቱ ማነቆ ይሆናል።
የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተነ ያለው ሌላው ምክንያት፤ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች አገሪቱን በምን መልኩ ይደጉማታል የሚለው ባለመታየቱ የተነሳ እንደሆነና በተለይም በኮንትሮባንድ የሚገቡ ዕቃዎች የአገሪቱን ገበያ ማራከሳቸው መሆኑን የሚገልጹት አቶ ረዳኢ፤ መደበኛ ሠራተኞችና ላኪዎች እንዲሁም የአገር ውስጥ ነጋዴዎች በሕገወጥ ነጋዴዎች ምክንያት ተገቢውን ግብር መክፈል አልቻሉም። የውጪ ምንዛሬን ለማግኘት የሚሄዱበት መስመርም የሳሳ ነው። በዚህም ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት የተፈለገበት ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ያደርጋል ይላሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ አቶ አብርሃም ስዩም በበኩላቸው፤ ከውጪ የሚመጡ ባለሀብቶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር አናሳ መሆንና አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን በስፋት አለመደገፉ እድገቱን ከሚጎዱት መካከል እንደሆኑ ይናገራሉ። በተለይም በኢንቨስትመንት ሰበብ ምርቱ አገሪቱ ውስጥ እያለ ጥራት የለውም በሚል ሰበብ ዶላርን ከአገሪቱ እየወሰዱ ከራሳቸው አገርና ፋብሪካ ጥሬ ዕቃ በማምጣት የሚሰሩ ድርጅቶች አሉ። ይህ ደግሞ አገሪቱን በውጭ ምንዛሬ እጥረት ኢንቨስተሮችን እንዳታበረታታ አድርጓታል። የራሷን ሀብት እንዳትጠቀምም መሰናክል ፈጥሯል። በዚህም የተፈለገውን የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ፈተና እንደሚሆን ያስረዳሉ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አየለ ነገሬ እንዳሉት፤ በመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ነፃ ቀረጥ የገባው 260 ቢሊዮን ብር ነው። ሆኖም በዚያ ልክ ግብር መሰብሰቡ አጠያያቂ ነው። ይህ ደግሞ ከቀረጥ የሚገባውን የውጭ ምንዛሬ ያሳጣል። በዚህም አገሪቱ የፈለገችው የኢኮኖሚ እድገት ላይ ልትደርስ አትችልም።
«አምራች ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ ካልሆነና ግብርናው በፍጥነት ማደግ ካልቻለ የ2008ቱ ዓይነት ድርቅ በአገሪቱ ላይ መከሰቱ አይቀሬ ነው» የሚሉት ዶክተር አብርሃም፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ኢንቨስተሮችን የሚያጓጓና ኢኮኖሚውን በቀላሉ የሚያሳድግ ሆኖ ቆይቷል። በዚህም አገሪቱ ለ15 ዓመታት በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ተጉዛለች። ይሁንና እስካሁን የኢኮኖሚውን ፈጣን እድገት በመደጎም እድገቱ እንዳይገታና እንዲቀጥል ሲደረግ ቆይቷል። ከዚህ በኋላ ግን የሚደጎምም ሆነ የሚቀነስ በጀት ስለሌለ ኢኮኖሚውን የሚያግዘውና እድገቱን የሚያስቀጥል በጀት እንደማይኖር ይገልጻሉ።
በጀት ከሌለ ለሠራተኛም ሆነ ለልማት ሥራዎች የሚውል ገንዘብ መቀነሱ አይቀርም። ይህንን ለመሸፈን ደግሞ ብድር ይከሰታል። በዚህም ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ያለችው አገር ወደ ከፋ የዕዳ ጫና ውስጥ ትገባለች። አገሪቱም ሙሉ ለሙሉ እራሷን በኢኮኖሚው መደገፍ ይሳናታል። በየጊዜው የኢኮኖሚ እድገቱ እያሽቆለቆለ ይሄድና የኑሮ ውድነቱ ይባባሳል። የመግዛት አቅምም ይዳከማል። ዜጎች የሥራ ዕድል አያገኙም።

ትንታኔ
ጽጌረዳ ጫንያለው

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እያመጧቸው ያሉ ለውጦችን ለመደገፍ «ተደምረናል ኢትዮጵያዊነት ያኮራናል» በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል። 

በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደ ተገለጸው፤ ከዚህ በፊት በክልሉ በሚገኙ 13 ከተሞች የድጋፍ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን፤ ከትናንት ጀምሮም ሰልፉ እንደቀጠለ ነው። በክልሉ 20 ከተሞች ላይ ሰላማዊ ሰልፎቹ የተደረጉ ሲሆን፤ ትናንት በነበረው ሰልፍ ደብረ ብርሃን፣ ወልድያ፣ ሀይቅና ሰቆጣ ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም ሰላማዊ በሆነና ፍቅርና መተሳሰብ በመላበሰ ሁኔታ መጠናቀቁ ተዘግቧል።
በሰልፉ ወቅት ከተነሱ መፈክሮች መካከል «ሕዝባዊ ሰልፎች ያለ ዘርና ሃይማኖት ልዩነት የጋራ አንድነታችንን ለዓለም የምናሳይበት መልካም አጋጣሚ ናቸው»፣ «በሰው ልጆች እኩልነት ማመንና ክፋትን መፀየፍ የኢትዮጵያዊ አሸናፊነት መለያ ነው»፣ «ይህንን የለወጥ አመራር እና የይቅርታ አመራር በፍፁም ሀገር ወዳድነት እና በትህትና እንደግፋለን»፣ «የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመደመር የይቅርታ እና የለውጥ አመራርን በልብ ሙሉነት እንደግፋለን»፣ «በዘረኝነት መቃብር ላይ አትዮጵያዊነት ለዘለዓለም በፅኑ መሠረት ይተከላል» ፣ «ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የበኩላችንን እንወጣለን»፣ «ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት እናወግዛለን»፣ «ተደምረናል ኢትዮጵያዊነት ያምርብናል» የሚሉት ይገኙበታል።
ተመሳሳይ ሰላማዊ ሰልፍ በባህርዳርና ሌሎች የክልሉ ከተሞች ዛሬ የሚቀጥል ይሆናል። ሰልፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እያመጧቸው ያሉ ለውጦችን የመደገፍና ምስጋና የማቅረብ ሥራ የሚከናወንበት ሲሆን፤ ከምስጋናው ባሻገር ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በንፁሃን ወገኖች ላይ የተፈፀመውን የቦንብ ጥቃት የሚያወግዝ ነው። 

ጽጌረዳ ጫንያለው

 

Published in የሀገር ውስጥ

- ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን እያስመረቁ ነው

አዲስ አበባ፡- በ2010 የትምህርት ዘመን በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ መርሃ ግብሮች 170ሺ 578 ተማሪዎች የሚመረቁ ሲሆን፤ ከተመራቂዎቹ መካከል 116 ሺ 128 በመደበኛ፣ 54 ሺ 450 ደግሞ መደበኛ ባልሆኑ መርሃ ግብሮች የተማሩ ናቸው። በሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን በማስመረቅ ላይ ይገኛሉ። 

የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በአራተኛ ዙር የምረቃ መርሀ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ 1ሺ634 ተማሪዎችን እና በሁለተኛ ዲግሪ 67 ተማሪዎችን በድምሩ 1ሺ701 ተማሪዎችን ትናንትና አስመርቋል። ከእነዚህም ውስጥ 404ቱ ወይም 23 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው።
በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በእለቱ እንደተናገሩት፤ ተመራቂዎች ቀሪውን የህይወት ዘመናቸውን ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገርን መጥቀም በሚያስችሉ ስራዎች ላይ መሰማራት አለባቸው ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኑርልኝ ተፈራ በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ 21 የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ክፍሎች የማዕረግ ተመራቂዎች የሁለተኛ ዲግሪ ነጻ የትምህርት እድል እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም በየትምህርት ክፍሉ ለሚገኙ ለ21 ሴቶች እና በምርምር ስራ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ሶስት ተመራቂዎች ከዘንድሮ ዓመት ጀምሮ የሁለተኛ ዲግሪ ነጻ ትምህርት እድል እንደሚቀርብላቸው ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በማታና በተከታታይ መርሃ ግብር ከዲፕሎማ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1ሺ462 ወንድ እና 1ሺ727 ሴት በድምሩ 3ሺ189 ተማሪዎችን አስመርቋል። በትናንትናው እለት በኮከብ አዳራሽ በተካሄደው የምርቃት ስነስርዓት ላይ፤ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና፤ ተመራቂ ተማሪዎቹ በአገሪቱ እየታየ ባለው የለውጥ ጉዞ ውስጥ እንዲጓዙ፤ አገራቸውንም በማገልገል ከለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
የማዕረግ ተሸላሚዎች የዋንጫ እና ሜዳልያ ሽልማት ከክብር እንግዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው የተቀበሉ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ነጥብ ላመጡ ተማሪዎችም ነጻ የትምህርት እድል ተሰጥቷል።
የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 6ሺ950 ተማሪዎች ትናንትና እና ዛሬ አስመርቋል። በትናንትናው ዕለት 4ሺ465 ተማሪዎች የተመረቁ ሲሆን፤ 400 ተማሪዎቹ የድህረ ምርቃ ተመራቂ ናቸው። ዩኒቨርሲቲው በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ በአካባቢው የአንደኛ ደረጃ መምህሩና ከትራፊክ ደህንነት ጋር በተያያዘ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በመስራት ለሚታወቁት መምህር አብርሃም ሙሉነህ ነፃ የትምህርት እድልና የምስክር ወረቀት ሸልሟል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ በተለያዩ የትምህርት መስኮች 5ሺ965 ተማሪዎችን አስመርቋል። 5ሺ537 ተመራቂዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪና 428 በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን፤ ከተመራቂዎቹ መካከል 33 በመቶ ሴቶች ናቸው። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ተማሪዎች ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር በማዋሀድ ለአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተጨማሪ የጅማ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ2ሺ100 በላይ ተማሪዎቹን አስመርቋል። ከእነዚህም ውስጥ 1 ሺ 556 በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 620 በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም 4 ተማሪዎችን በሶስተኛ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው።
የባርዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 11 ሺ ተማሪዎቹን አስመርቋል። በተጨማሪም ወባን በአማራ ክልል እንዲጠፋ ፀረ ወባ ማህበር መስርተው ሁነኛ ለውጥ ላመጡት ለአቶ አበረ ምህረቴ እና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የምህድስና ዘርፍ ተመራማሪ ለሆኑት ለፕሮፌሰር ታምስቲን ሆርስ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል።
በተያያዘ ዜና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 8ሺ600 ተማሪዎችን አሰመርቋል። ከዚህ ውስጥ 9 በዶክትሬት፤ 1ሺ469 በሁለተኛ ዲግሪ እና 1ሺ45 በሶስተኛ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን ከተመራቂዎቹ መካከል 23 በመቶ ሴቶች ናቸው።
የድሬዳዋ እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎችም በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎቻቸውን አስመርቀዋል። ጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲም ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በ67 ፕሮግራሞች አስመርቋል። በቀጣይ ሳምንት ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በቀንና በማታ ያስተማሯቸው ተማሪዎችን እንደሚያስመርቁ ይጠበቃል።
በተያያዘ ዜና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በትናንትናው ዕለት በማስተርስ ዲግሪ፣ በመደበኛ፣ በማታ ተከታታይ ዲግሪ፣ በማታ ተከታታይ ዲፕሎማ ፣ በግዕዝ ቋንቋ እና በርቀት ትምህርት ዲፕሎማ ያስተማራቸውን 603 ደቀመዛሙርት አስመርቋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በምርቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የኮሌጁ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ ጢሞቴዎስ በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የስነ መለኮት ትምህርት ከዚህ በፊት በውጭ አገር ቋንቋ ይሰጥ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ትምህርት የተሰጠው በግዕዝና በአማርኛ ነው፡፡ የኮሌጅ መርሀ ግብርም በየጊዜው እያደገ መጥቷል፡፡ ኮሌጁ የራሱ ህንጻም አስገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡ ኮሌጁ በማስተርስ ዲግሪ 6፣ በመደበኛ ዲግሪ 33፣ የማታ ዲግሪ 82፣ የማታ ዲፕሎማ 96፣ የማታ የግዕዝ ዲፕሎማ 17፣ የክህነት ዲፕሎማ 270፣ የርቀት ዲፕሎማ 56 እና የሰርተፍኬት 43 በድምሩ 603 ደቀመዛሙርት ተመርቀዋል፡፡ 

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

 

Published in የሀገር ውስጥ

መርካቶ አንዋር መስጊድ ጀርባ ወትሮ በማር እና ቅቤ፣ በአማሩ የቤት ዕቃዎች፣ በኤሌክትሮኒክስ እና አልባሳት የተሞላ የደራ የገበያ ስፍራ እንደነበር በስፍራው የተዘዋወረ ሁሉ ያውቀዋል። ገበያ አዋቂ ነጋዴዎቿ ደግሞ አማላይ የዋጋ ጥሪ እያቀረቡ «ይሄ ይሻልዎታል» በሚለው ማግባቢያቸው ይታወቃሉ። ጀምበር ወጥታ ብታዘቀዝቅም የአካባቢው ገበያ ምሽቱንም ጨምሮ እንደደራ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ይዘልቃል። ዙሪያቸውን በብረት ላሜራ የተገነቡት ሱቆች ተጠጋግተው የተሰሩ ቢሆኑም በመብራት አሽቆጥቁጠው ለሽያጭ የቀረቡ ምርቶችን ጎላ ጎላ አድርገው ለገበያተኛው ሲያሳዩ ውበታቸውና ድምቀታቸው ሸማቹን ይበልጥ ይስባሉ። 

የቀኑ ወከባ ለምሽቱ ፀጥታ ቦታውን ለቆ ተሸኝቷል። በፀጥታውና በጨለማው መሀል አንድ አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ። እንደወትሮዋ በዕቃ ግብይት እና በሰዎች ግርግር ስትዋከብ የዋለችው የገበያ ሰፈር ረቡዕ ሰኔ20/2010 አመሻሽ ላይ እንዳልነበረች ሆነች።
ሌሊቱ ሲጋመስ ንብረት የሚበላ፣ ገንዘብ የሚያጠፋ ነበልባል በሱቆቿ መሃል ይንቀለቀል ጀመር። ነበልባሉ ክፉኛ የጎዳቸው ሱቆች እንዳልነበሩ ሆነው ተቃጠሉ። ዛሬ በቦታው የተገኘ ሰው የቆየ ገጽታዋ ከል ለብሶ፤ የነበረው እንዳልነበረ ሆኖ አመድ ሆኖ ይመለከታል። በአንዋር መስጂድ ከሴቶች በር አንስቶ የቅቤ መሸጫ ሱቆች፣ አባያ፣ ሂጃብና ሌሎች ኢስላማዊ አልባሳት መሸጫዎች እንዲሁም በተለምዶ «ጎንደር በረንዳ» በሚባለው ሰፈር ያሉ ሱቆች ላይ እሳቱ ጉዳት አድርሷል። ሙሉ በሙሉ ከመደሙት 158አካባቢ ሱቆቹ ባሻገር የመስጊዱ የሴቶች በር መግቢያ ቅጥር ውስጥ የሚገኙ የስብከት (ዳዕዋ) አገልግሎት የሚሰጡ የመንፈሳዊ ትምህርት መማሪያ ክፍሎች ጣሪያቸው እንደነደደ በእሳት ማጥፋቱ ላይ ተሳትፎ ያደረጉት የዐይን እማኞች ተናግረዋል።
የሱቆቿ ብረቶች ተገነጣጥለው፤ የእሳት ወላፈን ለብልቧቸው ጥላሸት መልበሳቸውን ላየ ልቡ በኀዘን ይሰበራል። በሱቆቹ ውስጥ የተቀመጡ ውድ ዕቃዎች የገዢዎችን ልብ ሲማርኩ እንዳልነበር አሁን ላይ እዚህም እዚያም ደርቀው እና ከሰል ሆነው ወድቀዋል።
የአካባቢው ነዋሪ አቶ ነስሩ ጀማል እሳቱ እኩለ ሌሊት ሲነሳ በቦታው ላይ ተገኝቶ ነበር። በሱቆቹ አቅራቢያ ያለው ሰው በፍጥነት ንብረቱን ለማዳን ሲሯሯጥ አስተውሏል። የአካባቢው ነዋሪም የነጋዴው ንብረት የእኔም ነው በሚል ስሜት እሳቱን ወደ አንዋር መስጊድ እንዳይዛመት በማጥፋት ይረባረብ እንደነበር ያስታውሳል። ምክንያቱ ባልታወቀ መነሾ የተጀመረው እሳት ግን ከአልባሳት ምርቶች አንስቶ እስከ ኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ ከገቢና ወጪ ደረሰኝ እስከ ሒሳብ ማስያ መሣሪያዎች፣ ከንብረት መደርደሪያ እስከ መሬት ምንጣፍ ድረስ ያሉትን በሙሉ እያቃለጠ ወደ አመድነት እንደቀየረው ተመልክቷል።
በአካባቢው ሰዎች እሳት የማጥፋቱ እንደተጀመረ አንዳንዶች ወደ አዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ስልኮችን መደወላቸውን አቶ ነስሩ ያስታውሳል። «ከወዲያኛው የስልክ መስመር የድምጽ ምላሽ ያገኙት ደዋዮች እሳቱ የተነሳበትን አካባቢ በመጥቀስ በአፋጣኝ እርዳታ እንዲደረግላቸው ተማፀኑ። ከአፍታ ቆይታ በኋላም በአስገምጋሚ ድምጾቻቸው ታጅበው የእሳት አደጋ መከላከያ መኪናዎች ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ በቦታው ደረሱ። ከዚህ በኋላ ግን የእሳት አደጋ ሠራተኞቹ እና ኅብረተሰቡ መግባባት አልቻሉም» በማለት በወቅቱ የነበረውን ሂደት ይናገራል። እሳት ለማጥፋት የመጡት ሰዎች እሳቱን ቆመው ከማየት ውጪ አፋጣኝ መፍትሄ አለመውሰዳቸውን ታዝቧል።
እሳት በዓይን ብቻ አይጠፋምና ንብረቱ እየወደመበት ያለው ነጋዴ ደግሞ ለምን ሥራቸውን እንደማይጀምሩ ሲጠየቁ እሳቱን ከማጥፋት ይልቅ ቅድመ ክፍያ መጠየቃቸው እንዳሳዘነው ተናግሯል። በሌሊት የተሰበሰበው ሰው መኪናቸው ላይ ሆነው የሚመለከቱትን ሠራተኞች ግን ከዚህ በላይ ሊታገሳቸው ባለመፈለጉ በድንጋይ እና ባገኘው ነገር እያስፈራራ እሳቱን የማያጠፉ ከሆነ ወደመጡበት እንዲሄዱ ኃይል በተቀላቀለበት ስሜት ጥያቄውን ቢያቀርበም ሠራተኞቹ ፈጣን ምላሽ ባለመስጠታቸው ጉዳቱ እየሰፋ እንደሄደ ተናግሯል።
ከብዙ ጉትጎታና ቦታው ላይ ከደረሱ ከሰዓታት በኋላ የእሳት ማጥፋት ሥራው ላይ መሳተፍ ቢጀምሩም በርካታ ሱቆች ከነሙሉ ንብረታቸው ወድመዋል። እሳቱ ወደ አንዋር መስጊድ ከመዛመቱ በፊት ማጥፋት ተችሏል። የእሳት አደጋ ሠራተኞች ቸልተኝነት ግን ሊተርፉ የሚችሉ ንብረቶች እንዳይድኑ በማድረጉ ነጋዴዎች እና የአካባቢውን ኅብረተሰቡ ማሳዘኑን በቁጭት ይናገራል።
ወይዘሮ ዘይነባ አሊ መርካቶ በተለምዶ «ጎንደር በረንዳ» በሚባለው አካባቢ የኤሌክትሮኒክስ ሱቅ ያላቸው ናቸው። የእሳት አደጋው መከሰቱን እንደሰሙ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በአካባቢው መድረሳቸውን ይናገራሉ። በወቅቱ በሱቆቹ ውስጥ ያሉት ንብረቶች በፍጥነት ሊቀጣጠሉ የሚችሉ በመሆኑ በርካታ ባለሱቆች እና ሠራተኞች ንብረቶቻቸውን እያሸሹ ነበር። በዚህ ወቅት ግን ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ንብረት የሚዘርፉ ሌቦችም እንደነበሩ አስተውለዋል።
ባለሱቆች ንብረታቸውን ለማትረፍ በአካባቢ በነበሩት የእሳት አደጋ ሠራተኞች መኪናቸው ድረስ በመሄድ እሳቱን እንዲያጠፉ ሲጠይቁ «በመጀመሪያ ብር ክፈሉን» የሚል መልስ መሰጠቱ እንዳሳዘናቸው የሚያስረዱት ወይዘሮ ዘይነባ፤ ሠራተኞቹ ይህን ማለታቸው አሳፋሪ እና ከእነርሱ የማይጠበቅ ቢሆንም እሳቱን ካጠፉ በኋላ ቢጠይቁ እንኳን ሊረዳቸው የሚችል ሰው ነበር። በዚህም ምክንያት በርካታ ሱቆች ላይ ጉዳት መድረሱ እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ግን ይህን ወቀሳ አይቀበሉትም፤ ተቋሙ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ተኩል ላይ የእሳት አደጋ የድረሱልኝ ጥሪውን ተቀብሏል። ወዲያውኑ መኪናዎች ወደመርካቶ ተልከው ወደ እሳት ማጥፋት ሥራው መግባታቸውን ይገልጻሉ። በአጠቃላይም 15 የእሳት አደጋ ማጥፊያ መኪናዎች፣ ሦስት አምቡላንሶች እና 112 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተሰማርተው ነበር። ነገር ግን ሠራተኞች «አስር ሺ ብር ካልተከፈለን አንሰራም» አሉ የተባለው ከእውነት የራቀ እና ማስረጃ የሌለው መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ሐሜታው በፊትም ሲባል የነበረ እና የገንዘብ መጠኑም ሳይቀየር የቀረበ ነው። ነገርግን ይህ ዓይነቱ አስተያየት በእሳትና በጭስ እየታፈኑ ንብረት እና የሰው ሕይወት ለማዳን የሚሰማሩ ሠራተኞችን ሞራል እየገደለ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ በሱቆቹ የነበሩት ምርቶች በባህሪያቸው ተቀጣጣይነት ያላቸው በመሆኑ ውድመት ደረሰ እንጂ ሠራተኞቹ የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት ተወጥተዋል። ሥራው በቡድን የሚከናወን እና ፖሊስ እና ሕዝብ ፊት የሚሰራ በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት የገንዘብ ጥያቄ ያስነሳ ሠራተኛ ገጥሟቸው እንደማያውቅ አስታውሰው፤ ይልቁንም ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ የሕዝብን ንብረት የሚያድኑ ሠራተኞች እንዳሏቸው ይናገራሉ።
«አደጋው ተዛምቶ አንዋር መስጊድ እና ሌሎች ተቋማት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ የተቻለውም ይህን በማድረጋቸው ነው» የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ እጅን በእሳት አደጋ ሠራተኞች ላይ ብቻ ከመቀሰር ይልቅ ለአደጋው መነሻ ምክንያት የሚሆኑ ተቀጣጣይ ነገሮችን አደጋ እንዳያስከትሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል በማለት የቀረበውን ቅሬታ አስተባብለዋል።
ባለፉት ጊዜያት መርካቶ ሸራ ተራ እና ሌሎች አካባቢዎች ሲቃጠሉ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በወቅቱ አይደርሱም የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ሲቀርብ እንደነበር ይታወሳል። የጣይቱ ሆቴል በተቃጠለበት ወቅት የእሳት አደጋ መኪኖች በቃጠሎ ቦታዎች ላይ ደርሰው በሚከፈላቸው ገንዘብ ላይ ሲደራደሩ እሳቱ እየተባባሰ መጥቷል የሚል ቅሬታ ከኅብረተሰቡ ይቀርብ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ዜና ሐተታ
ጌትነት ተስፋማርያም

 

Published in የሀገር ውስጥ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።