Items filtered by date: Tuesday, 10 July 2018

ዘመናዊ ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት መዘውተር ከጀመረ ግማሽ ምዕተ ዓመትን አስቆጥሯል። ይሁንና በእነዚህ ዓመታት ተቋማዊ በሆነ መልኩ የስፖርት ሙያተኞችን አስተምሮ ከማስመረቅ ያለፈ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችን አሰልጥኖ ወደ ስፖርት ገበያ በማሰማራት በአገር፣ በአህጉርና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ውጤት በማስመዝገብ ራሳቸውና አገራቸውን መጥቀም የሚችሉ አትሌቶችን ማፍራት ሳይቻል ቆይቷል።

ነገር ግን ውጤታማና የማይነጥፍ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚቻለው፤ ተቋማዊ የስፖርት ማሰልጠኛ ተቋም በመገንባት ሳይንሳዊና ዘመናዊ ስልጠና በመስጠት መሆኑን በውል የተረዳው የአገሪቱ መንግሥት፤ ከሃያ ዘጠነኛው የቤጂንግ ኦሎምፒክ ማግስት በአሰላ ከተማና በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን አስገንብቷል።
በከፍተኛ በጀት ተገንብቶ በአስፈላጊው ግብዓት የተደራጀው የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚም ለሰልጣኞች፤ ስርዓተ ትምህርት በማዘጋጀት፣ አሰልጣኞችና የአስተዳደር ሰራተኞችን በማሟላት የሙሉ ጊዜ የስፖርት ስልጠና እና ሰልጣኞች መደበኛ ትምህርት በማስተማር የምግብ፣ የመኝታና የኪስ ገንዘብ በመክፈል ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ከመላ አገሪቱ ለተመለመሉ ታዳጊዎች ስልጠና ሲሰጡ ቆይቷል።
ይህ የስፖርት ልዕቀት አካዳሚም ለአገር፣ ለአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በአካልና በአዕምሮ የበቁ ወጣት ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት አንዱ ተልዕኮው ነው፤ እንዲሁም በተለያዩ የስፖርት መስኮች ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና የመስጠት በተጨማሪም ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ላይ የሚያካሂድም ነው፡፡ የሚገኙ ውጤቶችን ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽም ያደርጋል።
አካዳሚው በአካልና በአዕምሮ የበቁ ወጣት ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ረገድ ከዚህ ቀደም ስልጠና የሰጣቸው ሰልጣኞች መካከል 572 የሚሆኑትን ለክለባት አሸጋግሯል። 219 የሚሆኑትን ደግሞ ለብሄራዊ ቡድን አስመርጧል። አካዳሚው ብቃት ያላቸውን ስፖርተኞችን ለክለባትና ለብሄራዊ ቡድን ከማቅረብ በተጓዳኝ፤ በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የስልጠና ተቋማት እንዲገቡ በማድረግ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችን ማፍራት ችሏል።
አትሌቶችም ራሳቸውን ቤተሰባቸውንና አገራቸውን ከመጥቀም ባለፈ ስልጠና በሚሰጥባቸው ስፖርቶች በብሄራዊ ቡድን በመታቀፍ በአህጉር ዓቀፍ ሻምፒዮናዎች፣ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች፣ በአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ፣ በዓለም ሻምፒዮናዎች፣ በዓለም የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ አገሪቱ ተወዳድራ በማታውቅባቸው የውድድር መስኮች ጭምር በመሳተፍ አገራቸውን ከማስጠራት በላይ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።
አካዳሚው በእስካሁኑ ጉዞውም በአስር የስፖርት አይነቶች ስልጠና በመስጠት በየዓመቱ ሰልጣኞች ሲያስመርቅ የቆየ ሲሆን፣ ዘንድሮ በአካልና በአዕምሮ የበቁ ወጣት ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ተልዕኮው ውጤት ማሳያ የሆኑ 33 ሰልጣኞችን ከቀናት በፊት አስመርቋል። ተመራቂዎቹም በስምንት የስፖርት አይነቶች በአካዳሚው ለአራት ዓመታት ሲሰለጥኑ የቆዩ ናቸው።
ሃና ደረጄ ከዘንድሮው የአካዳሚው ተመራቂዎችና የተልዕኮ ስኬት ማሳያዎች አንዷ ናት። ከኢትዮ ሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ክልል የተገኘችው፣ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሴት ቦክሰኛዋ ሃና፤ አካዳሚውን የተቀላቀለችው 2007 ዓ.ም ነው።
ቦክሰኛዋ በአካዳሚው በስልጠና በቆየችባቸው አራት ዓመታት ባካሄደቻቸው ውድድሮችም የተለያዩ ውጤቶችን አምጥታለች። ያለፉትን ሦስቱን ዓመታት ትተን የዘንድሮውን ብንቃኝ እንኳን በኢትዮጵያ ቦክስ ሻምፒዮና ሁለት የወርቅና በሞሮኮ ካዛብላንካ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ቦክስ ሻምፒዮና ደግሞ በ 48 ኪሎ ግራም የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፍ ችላለች።
በአካዳሚ የነበራትን ቆይታ እጅግ አስደሳችና ውጤታማ ስትል የምትገልፀው ሃናም፤ በአካዳሚው በዋና አስልጣኝ ከድር ከማል እገዛ የምታገኘው ሳይንሳዊና ዘመናዊ ስልጠናም ለስኬቷ ዋነኛውን አስተዋፆኦ እንዳበረከተላትና እርሷም ሆነች ሌሎች ተመራቂዎች የአካዳሚው ተልዕኮ ስኬት ማሳያ መሆናቸውን ትናገራለች።
«ለቦክስ ስፖርት ጥልቅ ፍቅር አለኝ፤ ስፖርቱም አሁን ላይ የተሻለ እድገት እያሳየ ነው፡፡ እኔም በስፖርቱ አገሬን ማስጠራት ፅኑ እምነት አለኝ የምትለው ቦክሰኛዋ፤ በቆይታዋ በክህሎት፣ በእውቅትና በስነ ምግባር የቀሰመችውን ስልጠና በተገቢው ሁኔታ እንድምትጠቀም ነው ቃል የገባችው። ለቦክስ ስፖርት እድገትና በውጤታማነቱም የአገሪቱን ስም ይበልጥ ለማስጠራት ግን በተለይ ከለቦች የሴት ቦክሰኞችን መያዝ እንዳለባቸው ታስገነዝባለች።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚም ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ ሳይንሳዊና ዘመናዊ ስልጠና በመስጠት ልዩነት መፍጠር የሚችል ተቋም ለመሆን ተግቶ እንደሚሰራ የሚገልፁት ደግሞ፤ የአካዳሚው ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው ናቸው።
አቶ አንበሳው፣ ለተቋሙ ተልዕኮ ስኬት ማሳያ ተመራቂዎች ያስተላለፉት መልዕክትም፤ ተመራቂ ሰልጣኞችም በስልጠና ቆይታቸው በክህሎት፣ በእውቅትና በስነ ምግባር ቀስመው የወጡትን ስልጠና በተገቢው ሁኔታ እንዲጠቀሙ የሚያስገነዝብ ነው። ተመራቂዎች ባለፉት ዓመታት የሰለጠኑበትና የተማሩበትን ተቋም በማስተዋወቅ፣ ውጤት በማስመዝገብ፣ ተቋሙና መንግስት ያበረከቱላቸውን ውለታ እንዲከፍሉም የአደራ መልዕክታቸውን አሳልፈዋል።
የዘንድሮው ዓመት ተመራቂዎች ገና ከተቋሙ ሳይወጡ ሁሉም ከለብ ማግኘታቸውንና ያመላከቱት አቶ አንበሳው፣ ይሁንና ተመራቂዎች በክለብ ደረጃ ብቻ መወሰን እንደሌለባቸውና በአህጉርና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፕሮፌሽናል አትሌት ለመሆን መትጋት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።
«ስልጠና አይቆምም፤ ሁሌም እልህ አስጨራሽ ስልጠና ውድድር የማይለያዩ ጉዳዮች በመሆናቸው በተቋሙ ውስጥ ስታገኙት ከነበረው ስልጠና ባልተናነሰ መልኩ ስልጠናችሁን በምትሄዱበት ክለብ ሳታቆራርጡ ልትሰሩ ይገባል» ነው ያሉት። አካዳሚው ተተኪ ስፖርተኞች የማፍራትና ሚናውን በቀጣይም እንደሚያጠናክር ቃልም ገብተዋል።
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፈርህያ መሃመድ፣ ተመራቂዎች ከአካዳሚው ወጥተው ወደ ክለብና ዓለም ዓቀፍ ውድድር በሚሳተፉበት ወቅትም በአንድነት፣ በታማኝነትና በታታሪነት የአገራቸውን ስምና ሰንደቅ ዓላማ ክፍ እንዲያደርጉም ነው እምነታቸውን የገለጹት።

 ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚደረገው አጓጊ ጉዞ

የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑንና ወራጁን ለመለየት አንድ ጨዋታ ቀርቶታል። ሻምፒዮን ለመሆንና ላለመውረድ የሚደረገው ከፍተኛ ትንቅንቅ እጅግ አጓጊ ሆኗል።ቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ አባጅፋርም በሊጉ አናት ተቀምጠዋል።
ሁለቱ ክለቦች ተመሳሳይ 52 ነጥብ እና 19 ግብ ክፍያ ያላቸው ቢሆንም፤ በሊጉ ብዙ ጎል ባገባ በሚለው ህግ ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንደኛ፣ ጅማ አባጅፋር ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። ከሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ከሚወርዱ ሶስት ክለቦች መካከል ወልዲያ እግር ኳስ ክለብ ብቻ መውረዱን ሲያረጋግጥ ቀሪ ሁለት ክለቦች ገና አልታወቁም።
እንደ ፕሪሚየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ትንቅንቁ አጓጊ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ከፍተኛ ሊጉም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አዳዲስ ክለቦችን ለመቀላቀል ጥቂት ጨዋታዎች ይቀሩታል።ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ በሁለት ምድብ ተከፍለው 32 ክለቦች የሚያደርጉት ፉክክር አጓጊ ሆናል።

ባህር ዳር ከተማ የከፍተኛ ሊጉን -ሀ-ምድብ በመምራት ላይ ይገኛል


በከፍተኛ ሊጉም በሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታዎች ተካሂደዋል።በውጤቱም ባህርዳር ከተማ መሪነቱን ያሰፋበትን ድል አሳክቷል። በባህርዳር፣ ፍቃዱ ወርቁ ባስቆጠራት ግብ ደሴ ከተማን 1ለ0 አሸንፏል። በውጤቱም ከተከታዩ ሽረ እንዳስላሴ ያለውን ልዩነት ወደ 8 ከፍ ማድረግና በ23 ጨዋታዎች 51 ነጥብ በመያዝ የደረጃው አናት ላይ ተቀምጧል።
በ2011 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊጉን ይቀላቀላሉ ተብለው ከሚጠበቁ ክለቦች አንዱ የሆነው ባህርዳር ከተማ፣ ከዚህ በኋላ ፈታኝ ጨዋታዎች ቢኖሩበትም እያሳየ ያለው አስደናቂ ጉዞ ግን ይገታል ተብሎ አይጠበቅም።
አርባ ሶስት ነጥብና አስራ ሶስት ግቦችን ይዞ በሁለተኛነት የሚከተለው ሽረ እንደስላሴ፣ በአንፃሩ ፕሪሚየር ሊጉን የመቀላቀል እድል እያሰፋ መጥቷል።አርባ ሁለት ነጥብና አስራ ስድስት ግቦችን ይዞ በሦስተኛነት የሚከተለው አዲስ አበባ ከተማ ሲሆን፣ ከዚህ ምድብ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማደግ እድል ያለው ክለብ ነው።
ይህ በከፍተኛ ሊጉ ክለቦች መካከል ያለው ጠባብ የነጥብ ልዩነት ፕሪሚየር ሊጉን ለመቀላቀል በሚደረገው ፉክክር አጓጊ አድርጎታል። ክለቦቹ ተመሳሳይ ጨዋታ እንደ ማድረጋቸው መጠን ያላቸው የነጥብ ልዩነት ተቀራራቢ በመሆኑም በቀጣይ በሚደረጉ በየትኛውም ጨዋታዎች የደረጃ ለውጥ ማስከተላቸው እሙን ነው። በተለይ ቀጣዮቹ ጨዋታዎች ሽረ እንዳስላሴና አዲስ አበባ ከተማ ክለቦች ትልቅ ዋጋ ያላቸው ሆነዋል።
ባህርዳር ከተማ በአሸናፊነቱ የሚገፋ ከሆነና ሽረ እንዳስላሴም አዲስ አበባ ከተማም በአሸናፊነት የሚዘልቁ ከሆነ የውጤት ለውጥ ላይመጣ ይችላል። ይሁንና ሽረ እንደስላሴና አዲስ አበባ ከተማ ከዚህ ወዲያ የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በአሸናፊነት መቀጠል ከቻሉና ባህርዳር ከተማ ነጥቦችን የሚጥል ከሆነ ፉክክሩ የበለጠ ይጦዛል። ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚደረገውን ጉዞም እጅግ አጓጊ ያደርገዋል።
በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሰበታ ከተማም አርባ አንድ ነጥብና ሰባት ግቦች ይዞ ወደ ሊጉ ለመግባት የሚደረገውን ትንቅንቅ በቅርበት መከታተሉን ቀጥሏል።ሰበታ ከተማ የሚቀሩትን ጨዋታዎች እያሸነፈ ከሄደ ከላይ ያሉትን ክለቦች የነጥብ መጣል ተከትሎ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያደርገው ጉዞ የበለጠ ተስፋ እየዘራበት መሄድ ይችላል።
በዚህ ምድብ የካ ክፍለ ከተማና ሱሉልታ ከተማ ሃያ አንድ ነጥብ በመያዝ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አስራ አራትና አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ በመገኘት በወራጅ ቀጠና ላይ ተቀምጠዋል።ደሴ ከተማ ደግሞ በአስራ ስምንት ነጥብ በደረጃው ግርጌ በመቀመጥ ወደ አንደኛ ሊግ የመውረድ አደጋ ተጋርጦበታል።
የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ቢሆን እጅግ አጓጊ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።በዚህ ምድብ ልክ እንደ ፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ ፉክክር የከፍተኛ ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን እንዲሁም ፕሪሚየር ሊጉን ለመቀላቀል በርካታ ክለቦች በተጠጋጋ የነጥብ ልዩነት ፉክክሩን አጓጊ አድርገውታል።
በዚህ ምድብ ደቡብ ፖሊስ በአርባ አራት ነጥብና በሃያ ስድስት የግብ ልዩነት ይመራዋል።ደቡብ ፖሊስ ምድቡን በበላይነት መምራት ይቻል እንጂ፤የፕሪሚየር ሊጉን ትኬት ለመቁረጥ ብዙ ፈተናዎች ይጠብቁታል።
ጅማ አባቡና በአርባ አንድ ነጥብ ነጥብና አስራ ስምንት ግቦች ሁለተኛ ላይ በመሆን ደቡብ ፖሊስን ይከተላል።ባለፈው ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊግ አድጎ የወረደው አባ ቡናም ወደ ፕሪሚየር ሊግ የመመለስ ተስፋው ጎልበቷል።በተመሳሳይ አርባ አንድ ነጥብ የያዘው አስራ አንድ ግቦችን የያዘው ዲላ ከተማም ከእነዚህ ክለቦች እኩል ሊባል በሚችል ደረጃ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የማደግ እድል አለው።
በዚሁ ምድብ ድሬዳዋ ፖሊስ፣ሻሸመኔ ከተማ፣ መቂ ከተማና እንደየ ቅደም ተከተላቸው ሃያ፣ አስራ ዘጠኝ፣ አስራ ስምንት ነጥብ ይዘው ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ሆነዋል።
በከፍተኛ ሊግ የሁለቱ ምድብ ፉክክሮች ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማደግ በሚደረገው ፉክክር ሦስት ክለቦች የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የሚቀላቀሉ ይሆናል።ከሁለቱ ምድቦች አንደኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ክለቦች በቀጥታ ፕሪሚየር ሊጉን የሚቀላቀሉ ሲሆን፣ የከፍተኛ ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እርስበርስ የሚፋለሙም ይሆናል።
ከሁለቱ ምድቦች ሁለተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ክለቦች ደግሞ ለደረጃ በሚደረገው ፍልሚያ የሚለዩ ይሆናል።በዚህም ሶስተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ክለብ ፕሪሚየር ሊጉን ሲቀላቀል አራተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ቀጣዩን ዓመት እዚያው ከፍተኛ ሊግ ውስጥ ተፋላሚ ይሆናል።

ታምራት ተስፋዬ

 

 

Published in ስፖርት
Tuesday, 10 July 2018 16:41

የባቢሎን ግንብ አፍራሽ

«ሁለት ጉዳዮችን አትርሳ፤ የማይደርስ ነገር የለም፤ የማያልፍም እንዲሁ» ይህ ጥቅስ በሌላ ሰው ቤት ተሰቅሎ ስለመኖሩ እንጃ፤ እርሱ ግን በየዕለቱ ማለዳ ከእንቅልፉ ሲነቃ እንዲያየው ከራስጌው ትይዩ ከፍ አድርጎ ሰቅሎታል። በትምህርት ቤት ቆይታውም በመተኛ ክፍሉ ለጥፎት ዓመታት አልፈዋል።
ጥቅሱን ከዓመታት በፊት ነው የጻፈው። ከየት እንደሰማው ግን አያውቅም። «የማይደርስ ነገር የለም፤ የማያልፍም እንዲሁ።» የማይደርስ ማለት? ጊዜ ይወስዳል እንጂ የፈለጉት ሁሉ ይደርሳል ማለት ነው? ወይስ እኛ እየደረስንበት ግን በትህትና ይደርሳል እያልን እየጠበቅን ነው? ምን እየጠበቅሁ ነው? እስኪያልፍ? በቃ! ጥቅሱ ዛሬ አልገባህ አለው፤ እስከዛሬ እንደሚያበረታው አልሆነም።
ከእንቅልፉ በደንብ ነቅቷል፤ መሃሉ ከረገበው የሽቦ አልጋው ላይ ሰውነቱን አንጠራርቶ ተነሳና ለጥቅሱ ጎኑን ሰጠው። ከፊት ለፊቱ ካለው ባለ ሶስት እግር ወንበር ላይ የተቀመጠውን ጥቁር ጋዋን ተመለከተ። የዓመታት ድካሙ፣ ጥረቱ፣ እንቅልፍ ማጣቱ ታወሰው። ሲማር የኖረው ለማወቅ ነበር ወይስ ላለመውደቅ?
ውጪዋ በቆርቆሮ፣ ውስጧ በማዳበሪያ የተጌጠው የክፍሉ አንድያ በር ተንኳኳች፤ «ተስፉ? ተስፉ...አልነቃህም እንዴ?» እትዬ አደላሽ ናቸው። በትምህርት ዓመታት ቆይታው ሰበብ እንዳያበዛ እንቅፋት የሆኑበት ስለሚመስለው ለእርሳቸው ያለውን ስሜት ለይቶ አያውቀውም። ከቤተሰቤ ርቄ እንዳይል እንደእናቱ፣ አልባሽ አጉራሽ የለኝም እንዳይል እንደዘመድ ሆነውታል። የሚሰንፍበትን እድል ሁሉ ነጥቀውታል። የአደራ ልጄ ሲሉት ይሰማል፤ ሸክም የሆነባቸው መስሎ እንዳይሰማው የማያደርጉት ነገር እንደሌለም ሁሌ ያስተውላል።
«ተነስቻለሁ ማዘር...ደኅና አደሩ?» አለ፤ ወፈር ባለና ባልጠራ ድምጽ፡፡ «ይመስገን...ሄደህ ከተመራቂ ጋር አበባ ባትቀበልም መጥተህ ቁርስ ብላ...» አሉት። መነሳት ባይፈልግም «መጣሁ ...» አለ።
ከአልጋው የመንፏቀቅ ያህል ቀስ ብሎ ተነስቶ ቆመ። ባለ ሶስት እግር ወንበሩ ላይ የተቀመጠውን ጥቁሩን ጋዋን አንስቶ ተመለከተው፤ በልጅነቱ ምርቃቱ እንዴት ቢሆን እንደሚመኝ አስቦ አያውቅም ነበር። የሚያስበው ቤተሰቦቹን ስለሚያገኝበት መንገድ ነበር። ሲያድግ እናቱ ጋር የሚወስድ መንገድ የሚሠራ ኢንጅነር የመሆን ህልም ግን ነበረው። ኢንጅነር ሆኗል፤ ወደእናቱ የሚወስደውን መንገድ እንዴት መሥራት እንደሚችል ግን ያስተማረው አልነበረም።
የማይደርስ ነገር የለም፤ ግን አደራረስም ዓይነት አለው። ዝም ብሎ «ደረሰ» ማለት ብቻ ምን ዋጋ አለው። ውድ ጊዜ የተከፈለበት፣ ብዙ ዋጋ የወጣበት ከሆነ፤ ከ«ደረሰ» በላይ ቋንቋ ያስፈልገዋል። ተመርቄአለሁ...ምርቃቴ ዛሬ ነው፤ ግን ምን ጨመረ? አንዲት ከእናቴ ጋር የምታገናኝ መንገድ መዘርጋት እንኳ የሚያስችል ምን አገኘሁ? ግን በቃ ያልፋል፤ እንደቀላል ነገር ያልፋል።
ጥቁሩን የመመረቂያ ጋዋን መልሶ ካነሳበት ወንበር ላይ ወርውሮ አስቀመጠውና ትንሿን በሩን በእርጋታ ከፈታት፤ ከውጪ ያለው ብርሃን እኩለ ቀን ይመስላል። የአንድ ክፍል ቤቱ ጨለማ ውጪ ስላለው ብርሃን እንዳያስብ ጋርዶት ነበር? በሚከፈት አንድ በር ብቻ፤ ሙሉ ቤት በብርሃን ይሞላል? የፀሐይዋ ብርሃን ዓይኑን ሙሉ በሙሉ ሊያስገልጠው ባይችልም ተስፋን ሰጠው፤ ከምንም የሚገኝ ደስታን አገኘ።
«አንተ ልጅ! ተመርቄአለሁና አልታዘዝም ብለህ ነው? ና ስልህ ቶሎ የማትመጣው?» አሉ እትዬ አደላሽ ከቤታቸው በረንዳ ላይ አሻግረው ድርቡን እያዩ። ፈገግ አለ፤ ፀሐይዋ የሰጠችው ብርታት ሳይሆን አይቀርም ፈገግታው ለእርሳቸውም ተጋባ «ኧረ ማዘር ምን አገኘሁ ብዬ? ተጣጥቤ መጣሁ» ከበሩ አፍ ላይ የተቀመጠውን አፍንጫው የተሰበረ የውሃ ጆግ አንስቶ ወደቧንቧው አመራ።
**** **** ***** **** ****
እትዬ አደላሽ ተስፉ የሚያደርገውን በጥሞና ይመለከቱ ጀመር። ከነፍሳቸው ይወዱታል፤ ባህር ማዶ ሄደው ከተለይዋቸው ልጆቻቸው አብልጠው ያዝኑለታል። እናቱ ወዳጃቸው ስለነበረች? የልጅነት ዘመን ተድላውን ስለሚያስታውሱ? የእናቱን አደራ ስለተቀበሉ? ሰው ስለሆኑ? ብቻ የውስጡን ጥያቄ እንደማይመልሱትና ውስጣዊ እረፍት እንደማይሰጡት ቢያውቁም አንዳች እንዲጎድልበት አድርገው አያውቁም።
«አቤት ማዘር...» የበረንዳውን ሁለት ደረጃዎች ወጥቶ በሃሳብ ከተዋጡት እትዬ አደላሽ አጠገብ ተገኘ። ደነገጡ፤ «ታያለህ የአሮጊት ነገር? በሃሳብ ሄጃለሁኮ! አሃ! የት አለ ያ ጥቁሩ ካባህ የኔ ልጅ? ኧረ ተው ሥራ በማግኛህ ጊዜ አታስቀይመኝ። በል ሂድና ቶሎ ለብሰህ ና» አሉት። ይታዘዛቸዋል፤ እንደሚወዱት ያውቃላ! ቢያናድዱትም ይወዳቸዋል፤ ያለ እርሳቸውስ ማን አለው?
በሯ ያልተዘጋው ክፍሉ ውስጥ ዘው ብሎ ገብቶ ጋውኑን በፍጥነት አነሳውና ወጣ። ጋውኑን የመልበሱ ጥቅም አልታየውም፤ ግን ለእትዬ አደላሸ መታዘዙ ዋጋ እንዳለው ያምናል። ጋውኑን ታድያ እንደነገሩ ጣል አድርጎ እትዬ አደላሽ መኖሪያ ዋናው ቤት ዘው ብሎ ገባ። ባዶ ቤት አልጠበቀውም፤ «እንዴት ሆነልህ?...ጎሽ» እያሉ የሚያበረታቱት የአደላሽ ጎረቤቶች ቤቱን ሞልተውት ነበር።
እልል አሉ፣ አጨበጨቡ፣ ተቀባብለው ጉንጩን ሳሙት፣ እንባቸውን እየጠረጉ ፈጣሪን «ምን ይሳንሃል?» ብለው አመሰገኑ። ሁሉም ሲረጋጋ ነው ተስፉ ማሰብ የጀመረው። ደስ ብሎታል? ደንግጧል? ተነስቶ አመስግኖ መውጣት ፈልጓል? ተቀምጦ የጋገሩትን ዳቦ መቅመስ፣ ያቀረቡትን እህል መቃመስና ጨዋታቸውን መካፈል ፈልጓል? የተሰማውን ስሜት መለየት አልቻለም። «ከዚህ በላይ ምን ትጠይቃለህ?» አለችው ህሊናው፤ ይሄኑ በእርሱ ደስ ስላላቸው በዙሪያው ስላሉ ሰዎች ሲል ፈገግ አለ።
ተበላ...ተጠጣ...«መቼም ጠላታችሁ ወገቡ ስብር ይበልና ሰበር ወሬ በየሰዓቱ ነው የምንሰማ። እስቲ ማነሽ? ወሬውን ተይና ቲቪውን ብትከፍቺው» አሉ አንድ ተለቅ ያሉ የእትዬ አደላሽ የቅርብ ጓደኛና የዝግጅቱ እንግዳ። «አዎን! እውነት ነው። ይሄ ጎረምሳ ሄዶ ዝግጅቱን መሳተፍ ባይችልም ይመልከተው። እንደሚመረቅ ካወቀ በኋላኮ ያው መመረቂያ ካባውን ሊያመጣ አንዴ ነው የሄደ። እስቲ ጓደኞቹን ይመልከታቸው» አሉ እትዬ አደላሽ በዓይናቸው ተስፉን ገርመም እያደረጉ።
«አንቺን እንዳያስቸግር ብሎ እንጂ ቢሄድ የሚጠላ አይመስለኝም። አንቺ እንደሆነ ያው ተከትዬው ካልሄድኩ ነው የምትይ! አይደለም እንዴ ልጅ ተስፉ» አሉት አስቀድሞ የተናገሩት የእትዬ አደላሸ ጓደኛ። የተከፋበትን ስሜት ሁሉ የደበቀው ተስፉ ፈገግ አለ። «ማዘርዬማ ለእኔ ብለው ነውኮ! ያለእርሳቸው ማን አለኝ?» አለ።
ከየት እንደመጣ የማያውቀው እንባ ተናነቀው። ብሶቱ ሁሉ በዚህ ንግግሩ ቀዳዳ ሾልኮ ማምለጥ የፈለገ መሰለ። ሁሉም የጎረቤት እንግዳ ከንፈሩን መጠጠ። «ተው ይህን አንቱታና ማዘር ስልህ ይኸው ስንት ዘመን ሆነ? ተምረህ ጨርሰህ ተመረቅህ። እንዳይከፋህ ብዬ እንጂ በዚህች ማማሰያ አንጎራድድህ ነበር» አሉት ሳቅ ለመፍጠር ያህል፤ ይባስ እንባውን መቆጣጠር አቃተው፤ ተነስቶ ወጣ።
**** **** ** **** ****
«ተስፉ ...ና ቶሎ በል እባክህ» ከቤቱ በር አፍ ላይ ተክዞ የተቀመጠው ተስፉ የሰማው ድምጽ የሰላም ስላልመሰለው በፍጥነት ደረጃውን ወጥቶ አደላሽ አጠገብ ተገኘ። ማንም ምን ሳይነግረው በቴሌቭዥኑ ላይ ያረፈው ዓይኑ ግን የሆነውን ነገረው።
ሁለት ሰዎች ተያይዘው ይሳሳቃሉ፤ በሳቃቸው ውስጥ እንደህልም ትዝ የምትለውን እናቱን አየ፤ በሳቃቸው ውስጥ ማረፊያ ሲያገኝ ታወቀው፣ በሳቃቸው ውስጥ መመረቁ ትርጉም ሰጠው። እርሱ ያልሠራው መንገድ በሌላ ሰው ተሠርቶለት ሲያይ የእርሱ ታሪክ አልመስልህ አለው፤ ፊልም መሰለው።
በቤቱ ያለው ሰው ሁሉ ቲቪውን በጥሞና ይከታተላል። አደላሽ ግን ተሻግረው ሄዱ። እልል ከሚሉት የአስመራ እናቶች መካከል የተስፉን እናት የሚያገኙ መሰላቸው። ከዓመታት በፊት የኤርትራ ተወላጆች ከየቤቱ እንዲወጡና ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ሲታዘዝ፤ የተስፉ እናት ትገባበት ጨነቃት። እዛም ብትሄድ ለክፉ ቀን ብላ ያስቀመጠችው ነገር አልነበረም፤ ከዚህ ትታው የምትሄደው የበዛ ሀብት ኖሯት አይደለም። ልጇን ግን በእንግልት ውስጥ ማሳለፍን ፈራች፤ እንድትጨክን ተገደደች። ወደጎረቤቷ አደላሽ ተጠግታ ልጇን ሰጠች። «ልቤ ሁሌም ከዚህ ይሆናል» አለቻቸው።
ይህን ሲያስታውሱ እንባቸው በተሸበሸበ ቀይ ጉንጫቸው ላይ ከብለል ብሎ ወረደ። «ልጄ እንግዲህ መመረቅህ አሁን የበለጠ ዋጋ አለው። መንገዱን ታሰማምራለህ» አሉት በደስታ ሲቃ የያዘውን ተስፉን እያዩ። ተስፉ በክፍሉ ያለውን ጥቅስ እያሰበ ነበር፤ «የማይደርስ የለም ብለን አንጠብቅም፤ እንደርስበታለን እንጂ።» እርግጥም «በዚህ ጉዞ የማንደርስበት የለም፤ ይህም ሁሉ ቢሆን ደግሞ ያልፋል።»

ሊድያ ተስፋዬ

Published in መዝናኛ

ፊልድ ኢፒዲሞሎጂ የበሽታ ወረርሽኝ እንዳይከሰት ለመቆጣጠርና ከተከሰተ በኋላም በቂ ምላሽ መስጠትን ዓላማ በማድረግ የተጀመረ የስልጠና ፕሮግራም ነው፡፡ ፕሮግራሙ የተጀመረው በአሜሪካ አትላንታ በሚገኘው የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል /CDC/ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአለም አቀፍ ደረጃ 65 የሚጠጉ ሃገራት የስልጠና ፕሮግራሙን እየሰጡ ሲሆን፣ስልጠናው በሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያም በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታን ለመቆጣጠር ሲባል ፕሮግራሙ አትላንታ /CDC/ በተደረገ ድጋፍ እ.ኤ.አ በ2009 እንደ ተጀመረ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በወቅቱ ስልጠናው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ መስጠት የተጀመረ ሲሆን፣በዚህም 15 የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ተመርቀው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2015 ወዲህ ግን ኢቦላን የመሳሰሉ ለሃገሪቱ ብሎም ለዓለም የሚያሰጉ በሽታዎች መከሰታቸውን ተከትሎ የሥልጠና ፕሮግራሙን በሃገሪቱ ባሉ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በማስፋፋት የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ሰልጣኞችን ቁጥር ወደ 504 ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም ስልጠናውን በመስጠት ሀገሪቱን በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስፍራ እንድትይዝ ያስችላታል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጤና ፅህፈት ቤት በጤና መኮንንነት የሚያገለግለው አቶ አንተነህ ጌታሁን የመጀመሪያውን የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ተከታትሎ ካጠናቀቀ በኋላ በቢሮ ደረጃ ብቻ ተገድበው ሲሰሩ የነበሩ ስራዎችን መስክ በማውጣትና ኅብረተሰቡ ዘንድ በመውረድ መስራት እንደሚቻል ተገንዝቧል፡፡እነዚህ ሥራዎች ፖሊሲ ለመቅረጽ ጭምር እንደሚያገለግሉ ተረድቷል፡፡
የኅብረተሰቡን የጤና ችግር በቅርበት ሆኖ የሚከታተል የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ የሚጠቅሰው አቶ አንተነህ፤ በተለይም በወረርሽኝ መልክ ሊከሰቱ በሚችሉ በሽታዎች ላይ የሚደረገው ቅኝትና የዳሰሳ ሥርዓት መጠናከር ይኖርበታል ይላል፡፡ በሽታው ከተከሰተም በኋላ በአፋጣኝ ምላሽ መስጠትና የማገገም ስራ መስራት እንዲቻል የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ይናገራል፡፡
እንደ አቶ አንተነህ ገለፃ፤ የበሽታ ቅኝት የሚጀምረው በአብዛኛው ከማኅበረሰቡ እንደመሆኑ መጠን የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ታች በመውረድ ማኅበረሰቡን ማገልገል ይኖርባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ወደማኅበረሰቡ ቀርቦ በመስራት ረገድ የሚስተዋሉ ድክመቶችን ማስወገድ ይገባል፡፡
በቢሮ ደረጃም የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ስራን በተመለከተ በአግባቡ አውቆ በመስራት በኩል የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ጠንካራ ተግባር ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ ኅብረተሰቡም የበሽታ ቅኝት ስራው ጥቅም ምን እንደሆነ ገና ያልተረዳ በመሆኑ ከጤና ተቋማት በመውጣት ማኅበረሰቡ ላይ ግንዛቤ መፍጠር፣የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስራ በአብዛኛው እንቅስቃሴ የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ በቂ ትራንስፖርት ሊመደብም ይገባል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው አቶ መዝገቡ የኋላ በትምህርት ቤት ቆይታው በዋናነት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ተብለው የሚጠቀሱ በሽታዎች እንዳይከሰቱ የሚያስችለውን እውቀት ጨብጧል፤በተለይ የበሽታ ቅኝት ስራዎችን በማካሄድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ እንዴት መከላከልና የኅብረተሰቡን ጤና መጠበቅ እንደሚቻል ፣በሽታዎችን በተመለከተ መረጃዎችን በመሰብሰብ መረጃዎቹ ውሳኔ እንዲያገኙ ለሚመለከተው አካል እንዲደርሱ ለማድረግ የሚያስችለውን ዕውቀት ቀስሟል፡፡
የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ትምህርት በአብዛኛው የሚሰጠው ማኅበረሰቡ ዘንድ በመዝለቅ በመስክ ቆይታ በመሆኑ በዚህ ሂደት የበሽታ ቅኝት ስራ ይካሄዳል፡፡ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በዋናነት መረጃዎችን ማሰባሰብን ይጠይቃል፡፡
ቀደም ሲል ፕሮግራሙ ተግባራዊ ሲሆን የቆየው በቢሮ ውስጥ ብቻ እንደነበር አስታውሶ፣‹‹በአሁኑ ወቅት መሬት ላይ በመውረድ ሥራዎች እየተሰሩ በመሆኑ ፕሮግራሙ በተለይ የኅብረተሰቡን ጤና አስቀድሞ እንዲጠበቅ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡›› ይላል፡፡
ከዚህ በፊት በአብዛኛው በሽታዎች ከተከሰቱ በኋላ ስራዎች ይሰሩ እንደነበር የሚጠቅሰው አቶ መዝገቡ፤ በአሁኑ ወቅት ግን በሽታዎች እንዳይከሰቱ ለማድረግ የሚያስችሉት የቅኝት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ለሃገሪቷ እንደ ዋና ስጋት ሊሆኑ በሚችሉ በሽታዎች ላይ ትኩረት በማድረግም የቅኝት ስራው የበለጠ መጠናከር እንደሚኖርበት ይጠቁማል፡፡
እንደ አቶ መዝገቡ ማብራሪያ፤ በቅኝት ሥርዓቱ በየጊዜው የሚገኙ መረጃዎች ጠቃሚ ግብአት ሊሆኑ ስለሚችሉ ለሚመለከተው አካል በማድረስ የመረጃ ሥርዓቱን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ይህም በሽታዎች እንዳይከሰቱ በእጅጉ ይረዳል፡፡ በሽታው ቢከሰትም ወዲያውኑ መቆጣጠር የሚቻልበትን ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሰው ሃብት ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ እንደሚገልፁት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላት ሃገር በመሆኗ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም ማቋቋም አስፈልጓል፡፡ ሌላው ፕሮግራሙ ያስፈለገበት ምክንያት በሃገሪቱ እ.ኤ.አ በ2009 የተከሰተው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ጠንካራ የበሽታ መከላከል አቅም መገንባትና መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ካላት የመልክአ ምድር አቀማመጥና የሕዝብ ብዛት አንፃር በርካታ በሽታዎች ሊያጋጥሟት ይችላሉ፡፡››ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በጎረቤት ሃገራት ጠንካራ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም አለመኖርም ትልቅ ስጋት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎችን በብዛትም በጥራትም መፍጠር ካልተቻለ ሀገሪቷ የበሽታ አደጋ ውስጥ ትገባለች ተብሎ እንደሚታሰብ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፣፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የሥልጠና ፕሮግራሙ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ ጅማ ፣ ሃሮማያ ፣ሃዋሳ ፣መቀሌ፣ጎንደርና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲስፋፋ ተደርጓል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ጌታቸው ገለጻ፤ በሀገሪቱ ያለው የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ቁጥር በቂ ባለመሆኑ ፣እ.ኤ.አ እስከ 2019 ባለሙያዎቹን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ባለሙያዎችን በማፍራት ሂደትም የጥራት ችግሮች መኖራቸው ታውቋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትም በርካታ ተግባሮችን ለማከናወን ተሞክሯል፡፡ የአገልግሎት ጥራትን በተመለከተ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች በትክክል ለቦታው የሚመጠኑ እንዲሆኑና በስራ ላይ እንዲሰማሩ ማህበር መፍጠር እንደሚገባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
‹‹የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ስራ የሚለካው በሽታ ከሌለ በመሆኑ በኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራሞች የተሰሩ ስራዎችን ለመዘርዘር ቁጥሮችን መጥቀስ አያስፈልግም›› የሚሉት ዶክተር ጌታቸው ፣ ለዚህም ምክንያቱ በሽታው እንዳይኖር ከተደረገ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያው ወይም የበሽታ ቅኝት ሥርዓቱ ጠንካራ ነው ማለት እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡ በሽታ ከተከሰተ ደግሞ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ስራ የሚለካው በሽታው የባሰ አደጋ ሳያስከትል መቆጣጠር በመቻሉ እንደሆነም ጠቀመው፣ችግሩ በሰፊው ከመጣ ደግሞ በሽታውን ለመከላከል ሙሉ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ጌታቸው ገለፃ፤በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች መሸጋገሪያቸውን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ማድረጋቸው ፣ሃገሪቷ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ፣ በጎረቤት ሃገራት ያለው የበሽታ ቅኝት ሥርዓት ደካማ መሆን፣ ኢትዮጵያ ታዳጊ ሃገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የጤና ሥርዓቷ ጠንካራ ባለመሆኑ ለአጣዳፊና ተላላፊ በሽታዎች የመጋለጥ እድሏ ሰፊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለአለም ስጋት የሆኑት የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት እንዲሁም ተላላፊ በሽታዎች በሀገሪቷ እስካሁን አለመከሰታቸው ጠንካራ የበሽታ ቅኝት ስርዓት መዘርጋቱን ያመለክታል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሰው ሃብት አስተዳደር ልማት ዳይሬክቶሬት የፊልድ ኢፒዲሞሎጂና የኅብረተሰብ ጤና ፕሮግራሞች አስተባባሪ ዶክተር ታጠቅ ቦጋለ በበኩላቸው እንደሚያብራሩት፤የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስልጠና ፕሮግራም በዋናነት ያስፈለገው በሃገሪቷ ያለውን የበሽታዎች ቅኝት ሥርዓት ለማሻሻል የላቀ ክህሎት ያላቸው የኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎችን በማሰልጠን በሃገሪቱ ወረርሽኞች፣የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ አፋጣኝ ርምጃ ለመውሰድ እንዲቻል ታስቦ ነው፡፡
ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ አነስተኛ የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች ቁጥር እንደነበራት የሚያስታውሱት አስተባባሪው፤ በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡ በቀጣይም ከሕዝቡ ብዛት ጋር የሚመጣጠን ባለሙያ ማሰልጠን ካልተቻለ ኢቦላን የመሳሰሉ በሽታዎች በሃገሪቱ ቢከሰቱ በቀላሉ ለመመከት አዳጋች እንደሚሆን ጠቁመው፣ ባለሙያዎቹን በጥራትም ሆነ በብዛት ማፍራት ከተቻለም በሽታዎቹ ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስቀድሞ መሆኑን ለማሳወቅና እንዳይመጡ ለመከላከል ብሎም ከተከሰቱም በኋላ ምላሽ ለመስጠትና ለመከላከል ያስችላል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
አስተባባሪው እንደሚሉት፤ፕሮግራሙ በሃገሪቱ የድርቅ አደጋ በተከሰተበት ወቅት ሰፊ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ከሃገር ውስጥም አልፎ በሴራሊዮንና ላይቤሪያ በተከሰተው የኢቦላ በሽታ ላይም ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ በቅርቡም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተከስቶ የነበረውን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ለማቆም የምላሽ ስራ ተከናውኖበታል፡፡ በዚህ ረገድ የስምንቱም ዩኒቨርሲቲዎች የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ሰልጣኞች በሃገር ደረጃ ለተደረገው ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሃገሪቱ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ዜጎችን ከማስተናገዷ አኳያ እስካሁን ኢቦላን በመሳሰሉ ከባድ ተላላፊ በሽታዎች አለመጠቃቷ ፕሮግራሙ ካመጣቸው ስኬቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን አስተባባሪው ጠቅሰው፤ ለዚህም ስኬት የኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች በተለይም በአየር መንገድ አካባቢ ጠንካራ የበሽታ ቅኝት ሥርዓት መዘርጋታቸው ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ይላሉ፡፡ በክልል ደረጃም ከዞን እስከ ወረዳ ድረስ ድንገተኛና አጣዳፊ የኅብረተሰብ በሽታዎችን ከመከላከል አንፃር የቅኝት ሥርዓቱ ከፍተኛ መሻሻሎችን ማምጣቱን ጠቅሰው፣ የበሽታዎች ቅኝት ሥርዓቱን አስቀድሞ ማጠናከር በመቻሉም በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች አስጊ የሆኑ በሽታዎች በሃገሪቱ እንዳይከሰቱ ማድረግ ማስቻሉን ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በፕሮግራሙ ተመራቂ የሆኑ ተማሪዎችም ከሃገራቸው በዘለለ ላይቤሪያና ሴራሊዮን በመሳሰሉ የአፍሪካ ሃገራት በመሄድ ድጋፍ በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ይጠቁማሉ፡፡
ተማሪዎቹ በአብዛኛው ማኅበረሰቡ ውስጥ በመግባትና በመስክ ላይ የሚሰሩበት ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰው፣ከዚህ አንጻር በሃገር ደረጃ ካሉት 72 የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ጣቢያዎች መኪናዎች ያሏቸው አርባዎቹ ብቻ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ይህ አንድ ተግዳሮት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ የአሜሪካ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተው፣ይህ ድጋፍ እየቀነሰ እንደሚሄድና መንግስት ለፕሮግራሙ ከሰጠው ትኩረት ጎን ለጎን የገንዘብም ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
የፊልድ ኢፒዲሞሎጂ ስራ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ በኢትዮጵያ በሚገባ ታይቷል፡፡ይህንን ከሀገሪቱ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ፖሊሲ አኳያ ውጤት እያስገኘ ያለ እንደ አህጉርም ተጠቃሽ ለመሆን የበቃ ፕሮግራም መንግስት በቀጥታ በመደገፍ የተሽከርካሪና እና የገንዘብ ችግሩን መፍታት ይኖርበታል፡፡ይህ ድጋፍ ተላላፊ በሽታዎች ተከስተው ከሚያስከፍሉት ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ሚዛን የሚደፋ መሆኑን በመረዳት መስራት ከመንግሥት በኩል ይጠበቃል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Published in ማህበራዊ
Tuesday, 10 July 2018 16:35

ህይወት የተራበች ከተማ

ከተማዋ በሚያስፈራ ዝምታ ውስጥ ትገኛለች፡፡በጦርነቱ የፈራረሱ መኖሪያ ቤቶቿና የንግድ ማዕከላቷ በአውራ ጎዳናዋ ግራና ቀኝ ይታያሉ፡፤ተሽከርካሪ እንደልብ ይመላለስበት የነበረው የተንጣለለው አስፋልት መንገዷ የከተማዋ ልጆች መጫወቻ ሆኗል፡፡
ከተማን በከተማነት ለመጥራት ቢያንስ በከተማው የትራንስፖርት እና የንግድ እንቅስቃሴ የግድ ያስፈልጋሉ፡፡እልፍ እያለ ሲሄድ ደግሞ ከተማዋን አቋርጠው የሚያልፉ ተሽከርካሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የዛላንበሳ ከተማ ግን ይህን ሁሉ ከተቀማች ሁለት አስርት ዓመታት እንደ ዋዛ ተቆጥረዋል፡፡ ከተማዋ ከድንበር ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከ1990 እስከ 1992 ድረስ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ እንዳልነበረች ሆናለች፡፡
እንደሚታወቀው ኤርትራ 30 ዓመታትን የዘለቀ ጦርነት ከኢትዮጵያ ጋር በማድረግ በ1983 ዓ.ም ነጻነቷን የተቀዳጀች ሀገር ብትሆንም ፣ በዚህ ጦርነት ሳቢያ በሁለቱም ሀገሮች ድንበር አካባቢ ያሉ ህዝቦች ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር ከድንበር ጋር በተያያዘ እኤአ ጦርነት ውስጥ መቆየቷ ይታወሳል፡፡በጦርነቱም በዚህ ዘመን በዓለም መራራ የተባለውን ጦርነት አካሂደዋል፡፡ ጦርነቱን አንዳንድ መረጃዎች በሁለቱም ወገን 100 ሺ ሰዎች ያለቁበት እየተባለ የሚገለጽ ሲሆን ፣ብዙዎች ይህን አሀዝ 70 ሺ ሰዎች የተሰውበት ሲሉ ይገልጹታል፡፡
በሁለቱ ሀገሮች መካከል ለተቀሰቀው ጦርነት እልባት ለመስጠት የተባበሩት መንግስታት፣የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተሳተፉበት ስምምነት በአልጀርስ መደረሱም ይታወቃል፡፡ ስምምነቱም ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት እንደሆነች የሚነገርላት ባድሜ ለኤርትራ እንደምትገባ መወሰኑን የኢትዮጵያ መንግስት ቢቀበልም ስምምነቱ ሳይተገበር በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡በዚህ የተነሳም በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ፍጥጫ ጦርነትም ሰላምም የሌለበት እየተባለ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱም ሀገሮች ዜጎች ህይወት ክፉኛ ተጎድቷል ፡፡
ዛላምበሳም ጦርነቱ ከተካሄደባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ መሆኗ ይታወቃል፡፡ጦርነቱ ቆሞም የዛላምበሳ ከተማና ሌሎች ከኤርትራ ጋር የሚዋሰኑ አካባቢዎች ከዛሬ ነገ ጦርነት ሊያገረሽ ይችላል በሚል ስጋት ከልማት እንቅስቃሴ ውጪ ሆነው ቆይተዋል ፡፡
ህይወት የተራበችዋ የዛላምበሳ ከተማም የዛሬን አያድርገውና ከ20 ዓመት በፊት እንደ መሰሎቿ ከተሞች ሞቅ ደመቅ ያለች ፣የንግድ ልውውጥ የደራባት ፣ነዋሪዎቿ ነግደው ያተረፉባት፣ ቤተሰብ መስርተው በደስታ በተድላ የኖሩባት፣ የዳሩባት፣ የኳሉባት ነበረች። በዚያ አስከፊ ጦርነት ምክንያት ክፉኛ ወድማለች፡፡
ከኦራል እና የመሳሰሉት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ከአዲግራት ከሚመጡ አንድ ወይም ሁለት የትራንስፖርት መኪኖች ውጪ አይታ እንደማታውቅ ነዋሪዎቿ በምሬት ይገልጻሉ፡፡
ለሌላ ስራ በአካባቢው ብንገኝም የዛላምበሳ ከተማን እንድንጎበኝ የተመቻቸልንን የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የያዙት ሁለት መኪኖች በከተማዋ ሲደርሱም የከተማዋ ነዋሪዎች በተዘበራረቀ ስሜት ውስጥ ሆነው ተመለከቷቸው፡፡ ይህ ስሜታቸው አንድ ነገር ይጠቁማል፡፡ እርሱም በተስፋ የሚጠብቁት የኢትዮጵያና ኤርትራ የእርቅና የሰላም ማዕድ ነው።
ነዋሪዎቿ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ለሁለት አስርት ዓመታት የቆዩባት ዛላንበሳ ዛሬ ነፍስ የሚዘራላት ተስፋ ከወደ አዲስ አበባ እና አስመራ እየጠበቀች ትገኛለች፡፡በዚህ ዜና ነዋሪዎቿ በከፍተኛ ደስታ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ወደ ኤርትራ ምድር ገብተው ለመነገድ ከኤርትራ የሚመጡ ነጋዴዎችንም ለማስተናገድ ጓጉተዋል፡፡ይህንንም አፋቸው ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ስሜታቸውም ይናገራል፡፡ፊታቸው ላይም ቁልጭ ብሎ ይነበባል፡፡
የኤርትራዋ ሰንዓፌና አዲግራት ለዛላንበሳ እኩል ርቀት ያላቸው የድንበር ከተሞች ናቸው ፡፡ ሰንዓፌ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች ለማወቅ ባንችልም ዛላንበሳ ግን ክፉኛ በእርግጥም ተጎድታለች። ይህንንም ማንም ሳይነገር በከተማ የሚስተዋለው ፍራሽ ብቻ ያረጋግጣል፡፤ ሴቶች ፣ህጻናትና አዛውንቶች በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያሉባት አሳዛኝ ከተማ ለመሆን ተዳርጋለች።
አማርኛ አቀላጥፈው የሚናገሩት የዛላንበሳ ነዋሪዎች ችግሩን ቁልጭ አርገው ስለሚያስረዱም ስሜታቸውን ለመጋራት ዕድል ፈጥሯል፡፡ከህፃን እስከ አዋቂ ያሉት የህብረተሰብ ክፍሎች ስለከተማዋ በቁጭት ይናገራሉ፡፡
‹‹ዛላንበሳ እንደ ቀድሞው ወደ ንግድ ልውውጥ ብትመለስ ህይወት ትዘራ ነበር›› የሚሉት የአካባቢው አዛውንቶች፣በዚህም ልጆቻቸውንም ከስደት እና በስደት ምክንያት ከሚደርስ ሞትና እንግልት መታደግ እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡
ወይዘሮ ኤልሳ በርኸ ተወልደው ያደጉት በዛላንበሳ ከተማ ነው፤ እድሜያቸው ብዙ አሳይቷቸዋል፤ ተድረዋል ፤ወልደዋል ፤ከብደዋል፡፡ እንደ ዛሬው ሳይሆን በከተማዋ ታዋቂ ሱቅ ነበራቸው፡፡ በአካባቢውም ባለሀብት አስከ መሆን ደርሰው ነበር ፡፡
ከአራት ልጆቻቸው ጋር በደስታ ይኖሩ እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ ኤልሳ፣ ከተማዋ የድንበር ከተማ እንደመሆኗ ንግዳቸውም የጦፈ ፣ ኑሯቸውም ያማረና የሰመረ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ዛሬ ያ ሁሉ አዱኛ እንደሌለ ሲገልጹም በፊታቸው ላይ የሚነበበው ስሜትና አንደበታቸው የችግሩን ግዘፈት ይመሰክራል።
«ነግጄ የማተርፍ ብዙ ደንበኞች ያፈራሁ፤ ልጆቼን ከማንም በላይ የማሳድግና የማስተማር፣ በሴትነቴ አንቱ የተባልኩ እመቤት ነበርኩ።በዚያች በተረገመች የጦርነት መጀመሪያ ቀን ሁሉም ነገር እንደ ጉም በነነ››የሚሉት ወይዘሮ ኤልሳ፣ ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ህጻን ልጃቸውን በአንሶላ አዝለው ቅሌን ጨርቄን ሳይሉ ሀብታቸውን ሜዳ ላይ በትነው ሌሎች ልጆቻቸውን አስቀድመው ነፍሳቸውን ለማትረፍ አዲግራት መግባታቸውን በሀዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ያስታውሳሉ።
ወይዘሮ ኤልሳ እርሳቸውን መሰል የከተማዋ ነዋሪዎች ከተጠለሉባት አዲግራት ከተማ እያሉም የአስረኛ ክፍል ተማሪው ልጃቸው «አምቢኝ ለአገሬ ለዳር ድምበሬ» ብሎ ጦሩን ተቀላቅሎ በግዳጅ ላይ እያለም ይሰዋል፡፡
«ጦርነቱ ልጄን አሳጥቶኛል ንብረትም የለኝም፤ የሚሆን መስሎንም ብዙ መስዋዕትነት ከፈልን ፤እኔ ብቻ አይደለሁም፤ እህቴም ልጇን አጥታለች፤ ሌላውም ዜጋ እንዲሁ ግን ምንም አልጠቀመንም፤ አሁን አብሮን ያለው ልጆቻችንን እያሰብን በሀዘን መቆራመድ ብቻ ፣ በችግርና ረሀብ መጠበስ ብቻ ነው» ብለው ይገልጻሉ።
‹‹ጦርነት ክፉ ነው፤ ሰላም ካለ ይበላል ይጠጣል አገርም ታድጋለች፤ እኛም ከአሁን በኋላ የሞቱትን በማሰብ ከመኖር ቀሪውን ቤተሰባችን ይዘን በሰላም መኖር የሁልጊዜ ምኞታችን ነው ፤ እንደ ድሮ ነግደን መኖር ደግሞ ህልማችን ነው፤ የተጀመረውን የሰላም አካሄድም በጉጉት እየጠበቀን ነው ››ይላሉ ።
«የሁለታችን ጸብ (ኢትዮ-ኤርትራ ለማለት ነው) መሆን ያልነበረበት ነው፤ ሁለታችንም የተጋባንና የተዋለድን የአንድ አገር ሰዎች ነበርን፤ በታሪክ አጋጣሚ ለእዚህ ተዳርገናል ›› ያሉት ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ በርሄ ገብረዮሀንስ ፣ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየወሰዱ ባሉት የሰላም እርምጃ በእጅጉ መደሰታቸውን ይናገራሉ፡፡
እድሜና ችግር የተጫኗቸው እኚህ አዛውንት በአስመራ የሚገኙትን እህት ወንድሞቻቸውን ለማየት ናፍቀዋል፤ ከተማቸው ዛላምበሳም እንደ ቀድሞው ሞቅ ደመቅ ብላ ለልጆቿ ተስፋ ሰጪ እንድትሆን ይመኛሉ፤እነዚህን ሳያዩ ባይሞቱ እንደሚመርጡም እንባ እየተናነቃቸው ይናገራሉ፡፡
« በእኛ ስም የሚነግዱ ብዙዎች እንዳሉ እናውቃለን፤ እኛ ግን እነሱ እንደሚሉት በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ የምንኖር አይደለንም ፤ ጦርነት ያጎሳቆለን ሀብት ንብረታችንን እንዳለ ያጣን አሁን ደግሞ በስደት ምክንያት ልጆቻችንን ለባህር እየገበርን ያለን አሳዛኝ ሰዎች ነን» በማለት አንገታቸውን ወደ መሬት አቀርቅረው ተናግረዋል።
ዛላንበሳ ቀድሞ ጦርነቱ ሳይነሳ ብታይዋት ኖሮ እጅግ ደማቅ ብዙ ስራና ንግድ ያለባት ከተማ ነበረች ያሉት አቶ በርሄ፤ አሁን በጦርነቱ የፈራረሰ ቤቷን፣ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎቿን ይዛ ህይወት እየተራበች የምትኖር ከተማ መሆኗን ይገልጻሉ።
አቶ በርሄ እንደሚናገሩት፤ በዛላንበሳ ከተማ ወጣቶች ሥራ የላቸውም፤ አዛውንቶች የሚውሉበት፣ የሚጫወቱበት፣የሚመክሩበት የተጣላ የሚያስታርቁበት ሁኔታም የለም። መንግሥት በቤተሰብ የሚያድላቸውን 5 ኪሎ የእርዳታ እህል እየጠበቁ እሱን እየተመገቡ አለፍ ሲልም ተሳክቶለት ባህር አቋርጦ ወደ ተለያዩ የዓረብ አገራት የሄደ ልጅ የሚልከውን እርጥባን እንዲሁም አዲስ አበባና መቀሌ ላይ ያሉ ዘመዶቻቸው የሚልኩለትን እየጠበቁ መኖር የግድ ሆኖ ቆይቷል።
«ወጣቱ ምንም ሥራ የለውም፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ከቤተሰቡ ጋር ተፋጥጦ መሞትን አይፈልግም እናም ያለችውን ይዞ በባህር ወደ ተለያዩ አገሮች ለመሄድ ጥረት ያደርጋል፤ በዚህም የተነሳ ብዙ ልጆቻችን አልቀውብናል» ይላሉ።

ወ/ሮ ኤልሣ በርኸ፣ ወ/ሮ ምህረት ታደሰ፣ ወ/ሮ በላይነሽ አለም (ከግራ ወደቀኝ)


የዛላንበሳ ነዋሪዎች 20 ዓመታት በከፍተኛ ስቃይ አሳልፈናል፤ በከተማዋ ምንም ዓይነት ልማት የለም፤ ወጣቱም አዛውንቱም ህጻናቱ ሳይቀሩ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ናቸው፤ድንበሩ ከተከፈተ እና ሰላም ከተገኘ ነግደን እንኖራለን፤ ህይወታችንም በእጅጉ ይለወጣል በማለትም የሰላሙ አስፈላጊነት አጠያያቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ኑሮ ያጎሳቆላቸው አቶ ገብረህይወት ሀዱሽም ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡« እኛ እኮ ሰው እንደሚያስበው ደልቶን የምንኖር አይደለንም፤ በጦርነት ስቃያችንን ያየን ከዚያም በኋላ ሰላምም ጦርነትም ሳይሆን እንዲሁ በስጋት ሰውነታችንን የጨረስን ሰዎች ነን ሲሉ ያብራራሉ።
‹‹በቤተሰብ 5 ኪሎ እህል በወር እየተረዱ መኖር እኮ ከሞት ያልተሻለ አሰቃቂ ህይወት ነው፤ እኛስ እያረጀን ነው ፤ወጣት ልጆቻችን ግን ተስፋ እየቆረጡ ቁጭ ብለን ከምንሞት የባህር አሳ ይብላን እያሉ እየሄዱ እያለቁብን ነው።››ያሉት አቶ ገብረህይወት፣ ይህንን እያየን እንዴት ነው ሰላም የማንፈልግ ሲሉም ይጠይቃሉ።
ሰላም ካለ ንጹህ አየር ይተነፈሳል፣ ከተማችን እንደ ቀድሞው ትሞቃለች፣ ትደምቃለች ፤እንነግዳለን፤ አስመራ ሄደን ከዘመዶቻችንን ጋር የልባችንን ተጫውተን ውለን አድረን ካሻንም ከርመን እንመጣለን፤ ይህንን የማይናፍቅ የዛላምበሳ ነዋሪ የለም፤ቃል ወደ ተግባር የሚለወጥበትን ቀን ናፍቆናል ይላሉ።
‹‹እኛ ሰላም አንጠላም ግን እየተካሄደ ያለውን የሰላም አካሄድ ቀርቦ የነገረን የመንግስት የሥራ ኃላፊም የለም፤ በአሉባልታ የምንሰማውን ይዘን ነው የምናወራው፤ ያሉት አቶ ገብረህይወት፣የክልሉ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ሊያወያያቸው፣ስሜታቸውን ሊረዳ እና ተግባራዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባ እንደነበርም ይጠቁማሉ። ‹‹ይህንን ማድረግ የሚሳነው ከሆነ ደግሞ እኛን የሁለቱን አገር ዜጎች ያገናኙን በግማሽ ቀን ችግራችንን ፈተን እናሳያቸዋለን›› በማለት ያስገነዝባሉ።
የሰባተኛ ከፍል ተማሪው ናትናኤል አንገዞም የመገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎቹን ቡድን ሲያይ ችግሩ ሁሉ በአንድ ቀን የተቀረፈ ይመስል በእጅጉ ተደሰተ፡፡የመጀመሪያ ጥያቄውም « ድንበሩ ተከፈተ እንዴ?» የሚል ነበር።
እንዳልተከፈተ ስንነግረው ግን በእጅጉ አዘነ ፤«መቼ ነው የሚከፈተው እኛስ አስመራ የምንሄደው መቼ ነው?» በማለትም ጥያቄውን ያከታትለው ጀመር። ሌሎች የእድሜ እኩዮቹም ጥያቄያቸው መቼ ነው ችግራችን ተፈትቶ ሰላም የምናገኘው ? ከተማችን እንደ ሌሎች ከተሞች የምትሆነው? የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ።
ናትናኤል «ሰላም ይሁንና ድንበሩ ይከፈት፤ እኛም አስመራ እንሂድ ፤እነሱም ይምጡ። በሰላም በፍቅር እንኑር» በማለትም በልጅ አንደበቱ ተማጽኗል።
ወይዘሮ ምህረት ታደሰ ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናት ናት። ከጦርነቱ በፊት በንግድ ሥራ ትተዳደር ነበር ፡፡ከጦርነቱ በኋላ ይህ ሁሉ የለም፡፡በከንቱ ከመቀመጥ በሚል አነስተኛ የመጠጥ ግሮሰሪ ከፍታ እንደምትሰራ ገልጻ፣በቀዘቀዘ ከተማ ላይ ውጤታማ መሆን እጅግ አስቸጋሪ ብሎም ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ትናገራለች፡፡።
ሰላም ከሆነ ሰርተው እንደሚቀየሩ ፣እርዳታ ጠባቂ እንደማይሆኑ ፣ልጆቻቸውም ትልቅ ተስፋ እንደሚሰንቁ ትናገራለች፡፤ ሰላም ካልወረደና ድንበሩ የማይከፈት ከሆነ ግን እንደዚህ ባለው ሁኔታ ምን ያህል ጊዜ እንደምንኖር ለመገመት ይከብዳል ስትልም አስከፊነቱን ትናገራለች።
‹‹ስፌት እንዳንሰፋ ማን ይገዛናል፤ ፈትለን ሸማ እንዳንሸጥ የሚመላለስ ትራንስፖርት የሚመጣም ሰው የለም፤ ማን ይገዛል ? በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ለ20 ዓመታት መኖር ከከባድም በላይ ከባድ ነው ስትል በምሬት ትገልጻለች፡፡
ወይዘሮ በላይነሽ አለም ግማሽ ኤርትራዊ ግማሽ ኢትዮጵያዊ ናት። በሁለታችን መካከል የተካሄደው ጦርነት እኮ በቤተሰብ መካከል የተደረገ እጅግ በጣም አስከፊ ጦርነት ነው ትላለች፡፡ ጦርነቱና መዘዙ እስከ አሁን ድረስም ማብቃት እንዳልቻለ ጠቅሳ፣ በዚህ ከቀጠለ ደግሞ ይህንን መጥፎ ገጽታ የልጅ ልጆቻችን ሊወርሱት እኮ ነው ስትል ስጋቷን ትጠቁማለች፡፡
ወይዘሮ በላይነሽ እንዳለችው፤ ጦርነቱ ያስከተለውን መዘዝ ለልጆች ማውረስ የታሪክም ተወቃሽነት ያመጣል፡፡ በተለይም በመንግስት የስልጣን ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ቆም ብለው ቢያስቡበት መልካም ነው፡፡ አሁን የተጀመረውን የሰላም ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል እልባት ማበጀት ያስፈልጋል ።
‹‹ልጆቻችንና ወንድሞቻችን ከመላው የአገሪቱ ከፍል ሳይበሉ ሳይጠጡ ሳይወልዱ ተምረው ሰው የደረሰበት ሳይደርሱ ድንበር ተደፈረ ስለተባሉ ብቻ ሆ ብለው ወጥተው አፈር ሆነው ቀርተዋል፤ ይህ በጣም የሚያሳዝንና ልብ የሚነካ ጉዳይ ነው›› ያለችው ወይዘሮ በላይነሽ፣ የሞቱትን እያሰብን እኛም እየተቸገርን መኖሩ ምንድነው ፋይዳው ?ስትል ትጠይቃለች፡፡ የሞቱት ሞተዋል ነፍሳቸው በአፀደ ገነት ይኑር፤ እኛ መኖር ስላለብን ይቅር ተባብለንና ሰላም አውርደን መቀጠል አለብን ። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በዚህ ጊዜ ብቻ ነው በመሆኑም ሀሳቡ በተግባር ተቀይሮ ማየት እንፈልጋለን ›› ትላለች ፡፡
ይህ የድንበር ግጭት የዛላምበሳ ነዋሪን ብቻ ዋጋ ያስከፈለ አይደለም የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ‹‹ከመላው አገሪቱ ክፍል የመጡ ወጣቶች በዚህ ቦታ ላይ ወድቀዋል፤ አካላቸውን አጥተዋል ፤እንደ አገርም ብዙ ቀውስ ተከስቷል።››ሲሉ ያብራራሉ፡፡
‹‹ሀዘኑ የዛላምበሳ እናት ብቻ አይደለም፤ የመላው ኢትዮጵያውያን እናት ጭምር እንጂ፤ በመሆኑም የሞቱት ልጆቻችንና ወንድሞቻችን እንደማይመለሱ ካመንን ለምን ይቅር መባባል ያቅተናል?››ስትል ትጠይቃለች፡፡በእርግጠኝነት ይቅር እንባባላለን ግን ጠንክሮ ይቅር እንዲባል የሚያደርግ ሰው ግን አጥተን ቆይተናል ስትል አስታውሳ፣ አሁን የሚሰማውን ተስፋ እንኳን ቀረብ ብሎ የሚነግረንና የሚያስረዳን የመንግስት ሹመኛ አላገኘንም ትላለች።
አዎ የህዝቡ ስሜት ከቃልም በላይ ነው፤ የሰላም ጥማቱን ለመግለጽ ከባድ ነው። ምክንያቱ ደግሞ 20 ዓመታትን የሰላም አየር ሳይተነፍሱ ምንም የተስፋ ጭላንጭልን ማየት ሳይችሉ የመኖር ከብደትን ከነዋሪው በላይ ማን ይረዳዋል።
የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሁለቱን ሀገሮች የድንበር ጉዳይ እልባት ለመስጠት የተደረሰበት የአልጀርሱ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር በቅርቡ መወሰኑ የከተማዋን እና የሌሎች በድንበር አካባቢ የሚገኙ አካባቢዎችን የሃያ ዓመት ጥያቄ ይመልሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣኑን በጨበጡበት እለት ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማውረድ እንደሚሰራ ባረጋገጡት መሰረት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያሳለፈውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ለኤርትራ መንግስት የሰላም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ይህን ጥሪ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የልኡካን ቡድናቸውን መላካቸውም ይታወቃል፡፡ የልኡካን ቡድኑ ጉብኝት የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ወደ አዲስ ምእራፍ ያሸጋገረ ሆኗል፡፤
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ላለፉት ሁለት ቀናት በኤርትራ ጉብኝት አድርገዋል፡፤ በጉብኝታቸውም የኤርትራ ህዝብና መንግሥት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተወያይተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ሀገሮቹ ለሀያ ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ እንዲጀምር፣የአሰብና ምጽዋ ወደቦች ለኢትዮጵያ ክፍት እንዲሆኑ፣የሁለቱም ሀገሮች ዜጎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ እንዲሁም ቀሪዎቹን ጉዳዮች በሂደት ለመመልከት ከሚያስችሉ መግባባቶች ላይ ደርሰዋል፡፡
የዛላምበሳ ከተማ ነዋሪዎች ጥያቄም በእዚህ ምላሽ አግኝቷል፡፡ነዋሪዎቹ እንዳሉት ያለፈውን ትተው ከወንድም የኤርትራ ህዝብ ጋር እንደቀድሞው የሚኖሩበትን ሁኔታ በመጠቀም ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለማልማት መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ሌሎች በሁለቱ ሀገሮች ድንበር አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችም የሀያ ዓመታት ጥያቄ ተመልሷል፡፡
የኢትዮ ኤርትራ የሠላም ስምምነት ፍሬ ሲያፈራ ግን በእርግጠኝነት ዛላንበሳ በሳምንት ውስጥ ህይወት ትዘራለች ። እንዲህ ጭብጥ ኩርምት ያሉት ነዋሪዎቿም የሰርቶ መለወጥ ህልማቸው እውን ይሆናል። ወጣቶች ከስደት ከስደትም ባህር ገብቶ ከመሞት ይድናሉ ይህ ግን እውን መሆን የሚችለው ሁሉም ለሰላም ጥሪው ቀናይ ሲሆን ብቻ ነው።

እፀገነት አክሊሉ

ሙስና መጠኑ ይለያይ እንጂ በየትኛውም ዓለም ይታያል፡፡ እያደጉ ባሉ የአፍሪካ አገራት ያለው ሙስና ግን መጠኑ ሰፊ ነው። በእነዚህ አገራትም ሙስና እጅግ ከመስፋፋቱ ባሻገር የሚፈጸምበት መንገድም እጅጉን ረቀቅ ወደ ማለት ተሸጋግሯል። በዚህም ምክንያት በየዓመቱ በሁሉም የአፍሪካ አገራት በሚባል ደረጃ እጅግ ከፍተኛ የሚሆን ገንዘብ በሙስና ይመዘበራል። አህጉሪቱም ለእነዚህ ሀገሮች ባለሥልጣናት እና ግብረ አበሮቻቸው ብቻ የፍስሃ ምድር ሆናለች ።
በየዓመቱ በየሀገራቱ ያለውን የሙስና መጠን ደረጃ የሚዘረዝር መረጃ ይፋ የሚያደርገው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ተቋም፣ በአህጉሪቱ መጠነ ሰፊ የገንዘብ ምዝበራ እንደሚካሄድ ሲጠቁም ቆይቷል። በቅርቡ የወጡ መረጃዎችም አህጉሪቱ በየዓመቱ 50 ቢሊዮን ዶላር በሙስና እንደምትመዘበር አመላክተዋል።
ከዓለማችን ደሃ አገራት ግንባር ቀደም ላይ የተቀመጠችው አፍሪካዊቷ ማላዊም ሙስና ከተንሰራፋባቸው አገራት በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም፣ የአገሪቱ ሰላሳ በመቶ የህዝብ ሀብት በሙስና ይዘረፋል። የመንግሥት ባለሥልጣናትም ዋነኛዎቹ የዝርፊያው ተዋናዮች ሆነው ይጠቀሳሉ።
በተለይ ከአራት ዓመት በፊት በዚህች ወደብ አልባዋ አገር የተንሰራፋው ሙስና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆይስ ባንዳ እና ከሰባ በላይ ባለሥልጣናት ስም በመቶ ሚሊዮኖች ከሚቆጠር የሀገሪቱ ገንዘብ ምዝበራ ጋር የተቆራኘና በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ እስክመሆን የደረሰም ነበር። ሙስናው በርካታ የአገሪቱ ዜጎች አደባባይ እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል።
በአገሪቱ ከሰሞኑ የተሰማው የሙስና ቅሌት ዜና ደግሞ ብዙዎችን ያስገረመና ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር የተመሳሰለ ሆኗል። ዜናው የአገሪቱን የወቅቱ ፕሬዚዳንት ፒተር ሙታሪካን ስም ከተግባሩ ጋር በማቆራኘቱም ይበልጥ አነጋጋሪ ሆኗል። የሙስና ቅሌቱ ለአገሪቱ የፖሊስ ኃይል የምግብ አቅርቦት በሚል ከወጣ ጨረታ ጋር ተያይዞ የተፈጸመ ነው ተብሏል።
የሙስና ቅሌት የሚመረምረውን የአገሪቱ የፀረ ሙስና ቢሮ ዋቢ በማድረግ መገናኛ ብዙኃኑ እንዳስነበቡት፤ ባለቤትነቱ የዛማር ካሪም የሆነና ፒነር ኢንቨስትመንት የተባለ ድርጅት ከሦስት ዓመት በፊት ለማላዊ ፖሊስ አገልግሎት ተቋም ምግብ ለማቅረብ ውል ይፈራረማል። የውሉ አጠቃላይ ዋጋም 2ነጥብ3 ቢሊዮን የአገሪቱ ገንዘብ ይተመናል። ስምምነቱም በፋይናንስ ዳይሬክተሩ ቦትማንና በድርጅቱ ባለቤት ዛማር ካሪም መካከል የተፈጸመ ሲሆን፤ በተጭበረበረ ፊርማ በተቀመረ ውል የታሰረ ነው፡፡ይሁንና የአቅርቦቱ ዋጋ ተመን ቀደም ሲል ከነበረው 2ነጥብ3 ቢሊዮን ወደ ሁለት ነጥብ ስምንት ከፍ እንዲል ይደረጋል።
ከቆይታዎች በኋላ የአቅራቢ ድርጅቱ ባለቤት 145 ሚሊዮን የአገሪቱ ገንዘብ አሊያም ሁለት መቶ ሺ ዶላር አገሪቱን በማስተዳደር ላይ በሚገኘው ዴሞክራሲያዊ እድገት ፓርቲ በእንግሊዝኛው ምህፃረ ቃል ዲፒፒ የሂሳብ ቁጥር እንዲገባ ይደረጋል።
የፓርቲው የባንክ ሂሳብ የሚንቀሳቀሰው በፕሬዚዳንቱ መሆኑን ዋቢ በማድረግ በርካታ ወገኖች በስምምነቱ ላይ በተፈፀመ ሻጥር ፕሬዚዳንቱና ፓርቲያቸው የሙስና ፅዋ እንዲጎነጩ ሳይደረግ አልቀረም የሚል ጥርጣሬ እንዳደረባቸው እየገለጹ ናቸው፡፡ ጆይስ ባንዳን በመተካት እ ኤ ኤ በ2014 ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ሙታሪካም ከሙስናው ቅሌት ጋር ተፋጠዋል።
ይሁንና ፕሬዚዳንቱም ሆኑ የድርጅቱ ባለቤት በዚህ የሙስና ተግባር ውስጥ እጃቸው እንደሌለ በመግለጽ ከደሙ ንፁህ ነኝ እያሉ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ሙታሪካ ውንጀላውን በቀጣዩ ምርጫ ለሚያደርጉት ዘመቻ ስማቸውን ለማጥፋት ሆን ተብሎ የተሸረበ ሴራ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ። «የግል ጥቅምን የማሳደድ ሰው አይደለሁም፤ ከወርሃዊ ደመወዜ 40በመቶውን ብቻ ነው የምቀበለው፤ ቀሪው ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ አድርጌያለሁ» ሲሉም ተደምጠዋል።
ወቅቱ ምርጫ ለማካሄድ የተቃረበበት መሆኑን በመጥቀስም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአገሪቱን ህዝብ አመኔታ ለማግኘት ያቀዱት ሴራ ነው ማለታቸውን ሮይተርስ አስነብቧል። የድርጅቱ ባለቤትም ቢሆን ኮንትራቱን ያገኙት በህጋዊ መንገድ መሆኑን በማስረዳት አንድም ወንጀል አለመፈፀማቸውን እየተናገሩ ናቸው ።
የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ በበላቸው ፕሬዚዳንቱን ፖለቲካዊ ጥቅምን ለማግኘትና የፓርቲውንና የፕሬዚዳንቱን ስም ለማጥፋት የተጠነሰሰ ሴራ ነው ብሎውታል። የፓርቲው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ለገቢ ማሰባሰቢያ ተግባር የተከፈተ መሆኑንም ተናግረዋል።
አንዳንዶች በአንፃሩ «በእርግጥ ይህ የሂሳብ ቁጥር የተከፈተው ከሦስት ዓመት በፊት ነው፤ ፓርቲው ከተለያዩ አካላት እርዳታ የሚቀበለው በዚህ ሂሳብ ቁጥር አማካይነት ነው፤ ይሁንና የአገሪቱ ህግ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ከህዝብም ሆነ ከግል ኩባንያ እርዳታ መቀበል እንደሌለበት ያስቀምጣል፤ ይህ ለገቢ ማሰባሰቢያ ነው የተባለ የሂሳብ ቁጥርም ህግን የጣሰና ለዝርፊያ እንዲመች የተቀመረ ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።
ሙስናውን ያጋለጠው የአገሪቱ ፀረ ሙስና ቢሮም ወንጀሉን በመመርመር ላይ መሆኑና ሙሉ መረጃውን ለማውጣት እንደሚቸገር አስታውቌል። ይሁንና የአገሪቱ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የትኛው ህግ እንደ ተሻረ ለመግለጽ አልፈቀደም። በፓርቲውና በግለሰቡ መካከል ያለውን ግንኙነትም ይፋ አላደረገም። በፕሬዚዳንቱና በሌሎች ተዋናዮች መካከል ስላለው ግንኙነትም ምንም አልተነፈሰም። የሙስናው ቅሌት ዜና ግን መላ ማላዊያንን በእጅጉ አስቆጥቷል።
በፕሬዚዳንቱ ላይ ከፍተኛ ትችትና ተቃውሞ እየተሰነዘረባቸው ይገኛል። ፕሬዚዳንቱ ተግባሩን ስለመፈፀማቸው እርግጠኛ መሆናቸውን በመግለጽ በርካታ ወገኖች ፕሬዚዳንቱ እምነታቸውን አጉድለዋልና ከሥልጣናቸው ባስቸኳይ ይልቀቁ የሚል ጥያቄም እያቀረቡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡እነዚህ ወገኖች ይህንንም በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ፕሬዚዳንቱ እንዲፈፅሙ ቀነ ቀጥሮ በመስጠት ይህ ካልሆነ ለተቃውሞ አደባባይ ከመውጣት የሚያግዳቸው አንድም ኃይል እንደማይኖር እያሳወቁ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
አንዳንድ የሲቪል ማህበራትም ፕሬዚዳንቱ የጉዞ ማዕቀብ እንዲጣልባቸው እስከመጠየቅ ደርሰዋል። አገራትም ይህን በማድረግ ለሙስና ምንም አይነት ቦታ እንደሌላቸው አቋማቸውን ማሳየት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲው የኤም ሲፒ መሪ ላዛሩስ ቻክዋራም፤ የፕሬዚዳንቱ አስተዳደር በሙስና መቆሸሹን ደጋግመው ሲገልፁ እንደነበር በማስታወስ፤ ተግባሩ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳይቀር እንደሚፈፀም ማወቅ ከተቻለ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን እንዲያስረክቡ በማድረግ በአስቸኳይ ምርጫ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።
በርካታ ወገኖች የፀረ ሙስና ቢሮው ሙሉ መረጃውን ለመስጠት ያልፈለገው በጫና ሳይሆን የአገሪቱ መንግሥት ተባባሪ በመሆኑ ነው ሲሉ ወንጅለውታል። የጸረ ሙስና ቢሮው በጉዳዩ ላይ የሚያደርገውን ትብብር ለማገዝ እንደሚሠሩ ማረጋገጣቸውን ሮይተርስ አስነብቧል።
ማላዊ 24 በዘገባው፤‹‹ፕሬዚዳንቱ ነፃ ነኝ ካሉ ፀረ ሙስና ቢሮው ደግሞ የሙስና ፍንጭ እንዳለ ካመላከተ በግልፅ መረዳት እንደሚቻለው ከሁለት አንዱ ትክክል መሆናቸውን ነው።›› ሲል ገልጾ፣ ከሁለት አንዳቸው ራሳቸውን ነፃ ማድረግ የግድ እንደሚላቸውም ጠቁሟል።
ፕሬዚዳንቱና የሙስና ቅሌት አገሪቱ በቀጣዩ ዓመት በምታካሂደው ምርጫ ላይ ጫና ማሳደር ጀምሯል። የሙስናው ቅሌት በርካታ ወገኖች ከወዲሁ ለፕሬዚዳንቱ ጀርባቸውን እንዲሰጡ አድርጓቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ ከወዲሁ ከመፍረድ እውነታውን መጠበቅ ምርጫቸው አድርገዋል።
ፕሬዚዳንቱ ከወዲሁ ስማቸውን በማጥራት ውንጀላው ሐሰተኛ መሆኑን እስካላረጋገጡ የብዙዎችን እምነት እንደሚያጡ የሚጠቁሙም በርካታ ሆነዋል። ይህ ካልሆነና በሙስና የጎደፈ ስማቸውን ይዘው በምርጫው የሚፎካከሩ ከሆነ ውጤቱ አሉታዊ እንደሚሆንም እየጠቆሙ ይገኛሉ፡፡ራሳቸውን ነፃ ማድረግ ከቻሉ የአብዛኛውን ህዝብ አመኔታ እንደሚያገኙም ተመላክቷል።
ስድስት ተወዳዳሪዎች ለመፋለም ስማቸውን ባስመዘገቡበት በዚህ ምርጫ የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ጆሴ ባንዳ የፕሬዚዳንቱ ዋነኛ ተፎካካሪ መሆናቸው ታውቋል። ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትና ስማቸው ከሙስና ጋር መዛመዱን ተከትሎ ከወራት በፊት በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከሥልጣን ያገለሉት ሳወሊስ ቺሊማ በምርጫው ትንቅንቅ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

ታምራት ተስፋዬ

Published in ዓለም አቀፍ

በሀገራችን በዚህ ዓመት በፖለቲካው መስክ እየታዩ የሚገኙት ለውጦች ያለፈውንም መለስ ብለን በጥቂቱ እንድንቃኝ ጭምር የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ የንጉሡ አገዛዝ ወድቆ የደርግ ሥርዓት እንደተተካ እንዲሁም የደርግ ሥርዓት ተገርስሶ የኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን እንደተቆጣጠረ ሀገሪቱ የተለያዩ አመለካከቶችን ያራመዱ በርካታ ፓርቲዎችን ለአፍታም ቢሆን አይታለች፡፡ እነዚህም ለለውጦቹ እንደ ማጣፈጫነት አገለገሉ እንጂ የህዝብ ፍላጎት የሆነውን ዴሞክራሲ ለማምጣት ሳይታደሉ ቀርተዋል፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሆኑላቸው እየቀሩ የህዘብ ሥልጣን በብልጣ ብልጦችና አምባገነኖች እየተያዘ አባሎቻቸው በአሳዛኝ ሁኔታ እየተገደሉ፣ ለእስር እና ለስደት እየተዳረጉ ፓርቲዎቹም እንደ ጉም በነው ቀርተዋል፡፤
ከ1983 ወዲህ ያለውን ብንመለከት እንኳ የእነዚህ ፓርቲዎች መሪዎችና አባሎቻቸው ለእስር፣ ለስደት ተዳርገዋል፡፤ ህፃናት ሳይቀሩ ዶክተር እና ፕሮፌሰር መሆን እንዲጠሉ ያደረገ ክስተትም ታይቷል፡፡ የአንዳንዶቹ መሪዎች ምሁራን እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ አሁን ወቅቱ ጥሩ ነውና መናገር ይቻላል። መንግሥት እነዚህ ፓርቲዎች በህዝብ ዘንድ ትንሽ ተሰሚነት ባገኙ ጊዜ ይህቺ ጥሬ ካደረች አትቆረጠምም በሚል የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ ሲያሳድዳቸው ሲያስራቸው ሲያሰቃያቸው በዓይነ ቁራኛ ሲከታተላቸው ቆይቷል፡፡
ከእነዚህ ፓርቲዎች አመራሮች መካከል ጥቂት የማይባሉት ምሁራን ነበሩ፡፡ እነዚህ ምሁራን በሚከተሉት አመለካከት ሳቢያ ለእስር እየተዳረጉ ፍርድ ቤት ይመላለሱም እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህም በመገናኛ ብዙኃን ይገለጽ ነበር፡፤ ያኔ እንደ ዛሬው አማራጭ መገናኛ ብዙኃን አልነበሩምና ትንሹም ትልቁም አንድ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ብቻ ይከታተል ነበር እና ህፃናትም እኩል ተሰላፊ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፤
የምሁራኑን መታሰር እንዲሁም ፍርድ ቤት መመላለስ የተከታተሉ ህጻናት ‹‹አሉ›› የተባለውን ልነገራችሁ ነው። አባት ይሁን እናት እንጃ ልጃቸው በትምህርቱ ጥሩ ውጤት በማምጣቱ ተደስተው ለማበረታት ‹‹ጎበዝ የእኔ ልጅ አንተ ፕሮፌሰር ትሆናለሀ››ሲሉ አድናቆታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይህን የሰማው ተማሪ ከመበረታታት ይልቅ ምን ቢል ጥሩ ነው ‹‹እምቢ፤ አልፈልግም፤ ለመታሰር ነው ›› የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ ይህም በወቅቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ላይ ይደርስ የነበረው አፈና፣ እንግልት፣ እስርና ስደት በህፃናት ላይ ሳይቀር ምን ያህል ከፍተኛ ጫና አሳድሮ እንደነበር ያመለክታል፡፡
የፖለቲካ እንቅስቃሴው ከዓመታት እስር ቆይታቸው በኋላ የእስር ጊዜያቸውን አጠናቅቀው ሲፈቱ ተከታዮቻቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን ይቀጥላሉ ብለው ሲጠብቁ በወህኒ ቤት ምን አስነክተዋቸው ይሆን በሚያሰኝ መልኩ ሀገራቸውን ጥለው የወጡ ፖለቲከኞችም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች ከሀገር መውጣታቸው ላያስደንቅ ይችላል፡፡ የሚያስደንቀው ግን በውጭ ሀገር እየኖሩ ፖለቲካ ባለፈበት ሳያልፉ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡እነዚህ ‹‹የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ነው፤ ለመታ ቢሻን ጋኒ›› እንደተባለው ሁለተኛ ፖለቲካ ባለፈበት ታልፉና አልተባሉም ማለት ይከብዳል። ከእስር ሲለቀቁ በፖለቲካ ላይሳተፉ ፈርመው ነው ብሎ ለመገመትም ያስደፍራል፡፡ይህን ፈረመው ከሆነም ፊርማው ባህር ማዶ ድረስ መዝለቁም የሚያነጋግር ነው፡፡
እነዚህ መሪዎቹ ናቸው፡፡ ተከታዮቻቸው በተለይ በምርጫ 97 እና ማግስቱ በአደባባይ በጥይት ተገድለዋል፤በጸጥታ ሀይሎች ተቀጥቅጠዋል፤በደዴሳ ፣ በሸዋ ሮቢት ፣ በዝዋይ ፣እና በሌሎች የተለያዩ ወህኒ ቢቶች ማቀዋል፡፤እነሱ ብቻ አይደሉም ጋዜጣ ያነባሉ፤ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ይደግፋሉ፣ ገዥውን ፓርቲ ተቃውመዋል የተባሉ ዜጎችም ያላዩት ችግር እንደሌለ ይታወቃል፡፡ የሞተ ተጎዳ ነው የተባለው። ያልሞቱት አዲስ አመለካከት መጣና ተፈቱ። እነዚያ ወጣቶች ግን ደመ ከልብ ሆነው ቀሩ፡፤
ሀገሪቱ አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ወጣ ያለና የገዥውን ፓርቲ የሚቃወም ሆኖ ከተገኘ ወይም የሚቃወም ከመሰለ ከጎኑ ሌላ የገዥውን ፓርቲ የሚደግፍ እንዲያበቅል እየተደረገ ከሥራ ውጪ ሲደረግባት የቆየች፣ አንዳንዶች ኢህአዴግ ሠራሽ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም አሉ ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ እያደጉ አይከስሙ አይነት ፓርቲዎች ለሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ምንም ሳይፈይዱ በሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ ለማለት ያህል እንዲንቀሳቀሱ ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች አሁን ነፃነታቸውን አውጀው መንቀሳቀስ ቢጀምሩ ይበጃል፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና መንሰራፋትን፣ ሥራ አጥነትን እና የፖለቲካ ምህዳር መጥበብን ምክንያት ያደረጉ ተቃውሞዎች፤ ሁከቶችና ግጭቶችን ተከትሎ ባለፉት ሦስት ወራት ሀገሪቱ አዳዲስ ክስተቶችን ማስተናገድ ጀምራለች፡፡
በሀገሪቱ ስር እየሰደደ የመጣውን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና እንዲሁም ወጣቱ የሥራ ዕድል ያለህ እያለ ያቀረበውን ጥያቄ ለመፍታት ኢህአዴግ የተለያዩ አቅጣጫዎችንና ውሳኔዎችን ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ የግንባሩ ሊቃነመናብርትም ባልተለመደ መልኩ በጋራ ግምገማውን አስመልክቶ መግለጫ መስጠታቸውም ይታወቃል። ይህም ፓርቲው ዘንድ ውጥረት እንደነበረ ያመለከተም ነው፡፡
ከሁሉም ከሁሉም ግን የሀገሪቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የችግሩ የመፍትሄ አካል ለመሆን በመወሰን ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ መወሰናቸው የሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አዲስ መልክ እንዲይዝ በር ከፍቷል፡፡ በሀገሪቱ አንድ መሪ ሥልጣን በገዛ ፈቃዱ ሲለቅም ይህ የመጀመሪያው እንደመሆኑ ኢትዮጵያንም ወግ ደረሳት አሰኝቷል፡፡ ግዙፍ ችግር የፈጠሩ፣ ሲፈጠር የተመለከቱ ለ27 ዓመታት ፓርቲዬ እስከ አመነብኝ ድረስ ፍንክች ያባ ቢለዋ ልጅ እያሉ ሥልጣናቸውን ማውረስ እስከሚቀራቸው ድረስ የፈለጉትን ሲያደርጉበት በኖሩባት ሀገር ይህ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ በእርግጥም አዲስ ክስተት ነው። ዋናው ነገር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን መልቀቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ የሚያደርግ ሥርዓት ማበጀት ላይም ጭምር ነውና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡
የእርሳቸውን ከሥልጣን የመውረድ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎም የኢህአዴግ ምክር ቢት አዲስ ሊቀመንበር ይመርጣል፡፡ ይህ ከፍተኛ ፍልሚያ እንደተካሄደበት የሚነገርለት ምርጫም የኦህዴድ ሊቀመንበር የሆኑትን ዶክተር አብይ አህመድን የግንባሩ ሊቀመንበር አርጎ ሲመርጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴው ይበልጥ እየለየለት ወደ አዲስ ምእራፍ እየተሸጋገረ መጣ፡፡
የግንባሩ ሊቀመንበር የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ይታወቃልና ብዙዎች ዶክተር አብይ ሊቀመንበር ከሆኑባት ሰዓት አንስቶ የፖለቲካው አየር መቀየሩን በእርግጠኛነት እስከ መናገር ደርሰዋል። ዶክተር አብይም በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው በተባለ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መጡ፡፡ ይህ በራሱ ለሀገሪቱ እና ለዜጎቿም ሲናፈቅ የኖረ አዲስ ክስተት ነበርና ህዝቡ አድናቆቱን ገልጾለታል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢህአዴግን ፖሊሲ የሚያራምዱ እንደመሆናቸው ብዙም ለውጥ ያመጣሉ ብለው ባይገምትም በወቅቱ የነበረውን ለውጥ ግን በአድናቆት ሳይመለከቱት አላለፉም፡፡ የለውጡ ተጠናክሮ መቀጠል ይህን ጥርጣሬ እንደሚያስወገደው ይታመናል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን መምጣት ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ቀደም ሲል የጀመረውን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመነጋገር፣ ጅማሮ በማስፋት የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት እና በክስ ላይ የሚገኙትንም ክሳቸው እንዲቋረጥ እያደረጉ በመልቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይበልጥ አስፍተውታል፡፡ በዚህም በርካታ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላትና ሌሎች ከእስር ተፈትተዋል፤ በክስ ላይ የሚገኙትም እንዲሁ ክሳቸው እየተቋረጠ ተለቀዋል፡፡ እርምጃው በእርግጥም አንዱ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፊያ መንገድ መሆን ችሏል፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ቁርጠኝነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ ሀገር ሆነው በትጥቅ ትግልም ሆነ በተለያየ መንገድ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ አመለካከታቸውን እንዲያራምዱ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ይገኛሉ፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም እነዚህን ወገኖች አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ከመቀበል ባለፈም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው እየተቀበሉ አነጋግረ ዋቸዋል፡፡ ይህ የልብ የሆነ አቀባበል በኢትዮጵያን ዘንድ ስለፖለቲካ ማሰብ እንዲያንሰራራ የሚያደርግም ነው፡፡
በሚያራምዱት የፖለቲካ አቋም የተነሳ እስራትና ስቃይ የደረሰባቸው አልፎም ተርፎ ሞት የተፈረደ ባቸውና ከእስር እንፈታለን ብለው ጨርሰው ባልገመቱበት ሁኔታ ከእስር ተለቀው ከቤተሰባቸው እንዲቀላቀሉ ብቻም ሳይሆን የፖለቲካ አመለካከታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያራምዱ የሚያስችል ሁኔታም የተፈጠረላቸው በመሆኑ እንዳለፉት የፖለቲካ መሪዎች ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ የማይሉበት ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የተለያየ አመለካከት የሚያራ ምዱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ይገኛሉ። እነዚህ ፓርቲዎች ገና ምርጫ ቦርድ እየቀረቡ አልተመዘገቡምና ይህን ያህል ናቸው ማለት ባይቻልም በርካታ ስለመሆናቸው የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥትን ማሳደድ ፈርተው በድንበር በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እያደረጉ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው በዚያው በመከተማቸው ሳቢያ ሀገሪቱ ስትጎዳ ቆይታለች፡፡ የነበሩባቸው ሀገሮች መንግሥታት ኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያስተናግድ ሥርዓት የላትም እያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ለጋሽ ሀገሮች በሀገሪቱ ላይ ጫና እንዲደረግ ተጽእኖ ሲፈጥሩ ቆይተዋል፤ ዜጎች ወደ ሀገራቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ በባንክ በኩል እንዳይላክ በማድረግ ሀገሪቱ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እንድትፈታ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ይህ ተጽእኖ የድንጋይ ላይ መቀመጫ እና የእናት ሞት እያደር ይሰማል እንዲሉ እነዚህ ወገኖች ይህን በማድረጋቸው ሀገር ቀስ በቀስ ትጎዳለች። በሀገራችን የተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተከሰተው አንድም በእዚህ አይነቱ መንገድ ነው፡፡ ይህን የሚያቀሉ ካሉ ጤንነቱ ያጠራጥራል፡፡
የመንግሥት እርምጃ በሽብርተኝነት የፈረጃቸውን ኦነግን፣ ግንቦት ሰባትንና ኦብነግን ከአሸባሪነት መዝገብ እስከ መሰረዝ ደርሷል፡፡ ይህን እርምጃ ለመውሰድም መንግሥት የምህረት አዋጅ በአስቸኳይ በማዘጋጀት አስፈላጊው ሁሉ በሚመለከታቸው አካላት እንዲደረግበት በማድረግ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ አድርጓል፡፡ ይህም ገና ወደ ሀገራቸው ያልገቡና መንግሥት ወደ ሀገራችሁ ገብታችሁ በሰላማዊ መንገድ ታገሉ እያለ የሚያቀርበው ጥሪ በህግ ማዕቀፍ እንዲደገፍ ለሚፈልጉ ፓርቲዎች ዋስትና በመሆኑም በቅርብ ጊዜ ውስጥም ሌሎች ፓርቲዎች ወደ ሀገራቸው እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ሥልጣን ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ እንደማይያዝ የሚያደርግ አሰራር እንደሚዘረጋ ተናግረዋል፡፡ ይህም መንግሥታት አምባገነን እንዳይሆኑ ከማድረጉም በላይ የሚችሉ ሰዎች ሥልጣኑን እንዲይዙትና ሀገራቸውን እንዲለውጡ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የሚጠቁሙት፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግሥት እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት እንዲሁም እየወሰደ ያለው እርምጃ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የዴሞክራሲ ተቋማት ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትን አሰራር ለመዘርጋቱ ሥራ ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን፣ በፍትህ ሥርዓቱ፣ በምርጫ ቦርድ ላይ በትኩረት በመሥራት በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ለውጡ ወደ ኋላ እንዳይመለስ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው እውነተኛ ሆኖ እንዲቀጥል ያስችላል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችም መንግሥት የፈጠረውን የፖለቲካ ምህዳር ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ለመጠቀም መዘጋጀት፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ በመድረስ በሠለጠነ አግባብ አመለካከታቸውን ማራመድ ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓቱ ግብዓት የሚሆኑት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ይገኛሉ። በሀገሪቱ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ የሚታየውን ይህን የአመለካከት ብዝሃነት በጸጋነት በማየት ሀገሪቱ በጽኑ ለምትፈልገው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዋል ከሁሉም ይጠበቃል፡፡

ዘካርያስ

 

Published in አጀንዳ
Tuesday, 10 July 2018 16:33

ኦሮማይ!

‹‹ከክቡር ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ዛሬ ባደረግነው ስብሰባ አየር መንገዶቻችን እና ወደቦቻችን ሥራ እንዲጀምሩ፣ ህዝቦቻችን እንዲቀያየሩ ፣ኤምባሲዎቻችን እንዲከፈቱ ፣እኛም በሳምንቱ መጨረሻ እየመጣን በሁለተኛ ሀገራችን አስመራ ከቤተሰቦቻችን ጋር እንድንዝናና፣ ኤርትራውያን ኢትዮጵያ እየመጡ ቤተሰቦቻቸውን እንዲጠይቁ፣ የቀረውን ትናንሽ አጀንዳ በፍቅር ግንቡን አፍርሰን ድልድይ እየሰራን እንደምንጨርሰው ተስማምተናል፤ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ድንበር የለም ፤ምክንያቱም በፍቅር ድንበሩ ፈርሷል›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለሃያ ዓመታት የዘለቀው ፍጥጫ ማብቃቱን ይፋ አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት ሁለት ቀናት በኤርትራ አስመራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከትናንት በስቲያ በተዘጋጀላቸው የእራት ግብዣ ላይ እንደገለጹት፤ሁለቱ ሀገሮች ለኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጉዳይ መፍትሄ አስቀምጠዋል፤ ከእንግዲህ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንን ከመንቀሳቀስ የሚገድብ ድንበርም ሆነ እገዳ አይኖርም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለክብራቸው በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ያበሰሩትን ይህን ዜና የሀገሮቹ ህዝቦች ሲናፍቁት የኖሩት ነበርናም በአዳራሹ የተገኙት ባለስልጣናት በጭብጨባ ተቀብለውታል፡፡ዜናውን በተለያየ መንገድ የተከታተሉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንም ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተቀበላቸው ሲሆን፣ህዝቡም በዋና ዋና መንገዶች ላይ በመውጣት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለውን ክብር ገልጿል፡፡ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች የመከሩ ሲሆን፣ ስምምነትም ተፈራርመዋል፡፡ይህ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገው ደማቅ አቀባበል የሁለቱን ሀገሮች ህዝቦች ትስስር የተገለጸበትም በመሆኑ ለቀጣዩ ትስስር ጠንካራ መሰረት ይሆናል፡፤
ሁለቱ ሀገሮች በትናንቱ እለትም የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡በስምምነቱ መሰረትም በትራንስፖርት አገልግሎት እንደገና ይተሳሰራሉ፤አየር መንገዶቻቸው እና ወደቦች ሥራ ይጀምራሉ፤የስልክ አገልግሎትም ጀምሯል።እነዚህ ለሁለቱ ሀገሮች ትስስር ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶች በአስቸኳይ ሥራ ላይ እንዲውሉም ይደረጋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለቱ ሀገሮች መካከል የዘለቀው ይህ ውዝግብ እንዲያበቃ ይዞት የተነሳው አቋም በአፋጣኝ ወደ ተግባር የተተረጎመበት በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በመንግሥታቸው ላይ ያላቸው አመኔታ የበለጠ እንዲጠናከር ያደርጋል፡፡
ሁለቱ ሀገሮች የደረሱባቸው ስምምነቶች በኢትዮጵያውያን ዘንድ የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር የተላለፈው ውሳኔ ድንበር አስምሮ የሚያበቃ መሆን የለበትም፡፡ ሁለቱን ሀገሮች የሚያስተሳስሯቸውን የተለያዩ ጉዳዮችንም የሚመለከት መሆን አለበት እያሉ ሲሰጡ ለነበረው አስተያየቶችም በቂ ምላሽ የሰጠ ሆኗልና እንኳ ደስ አለን ልንለው የሚገባ ነው፡፡የሁለቱ አገሮች ለ20 ዓመታት የዘለቀው የጥላቻ ግንብ ማብቃቱን ያበሰረ ነው፡፡ በትግርኛ ጥላቻ ‹‹ኦሮማይ›› (አበቃ፤ተፈጸመ) ፡፡
በስምምነቱ መሰረት በድንበር አካባቢ የሚኖሩት የሁለቱም ሀገሮች ዜጎች ድንበሩ ሳያግዳቸው መንቀሳቀስ ይችላሉ። ይህም በሰላም እጦቱ ሳቢያ ለተጎዱት ለእነዚህ አካባቢዎች ህዝቦች ስብራታቸውን የሚጠገን ታላቅ የምስራች ነው፡፡ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን እንደ ቀድሞ አንዳቸው ወደ አንዳቸው በመሄድ የሚጠያየቁበት የተለያዩ ቤተሰቦች የሚገናኙበት በመሆኑም የህዝቦቹ አንድነት እንዲጠናከር በር ይከፍታል፡፡
ሀገሮቹ በጠላትነት በመፈራረጅ አንዱ አንዱን ለመመከት የሚያደርጉትን የጦር ኃይል ግንባታ ከአሁን በኋላ ኦሮማይ፡፡ተቀናቃኝ ኃይሎችን የመደገፍ አባዜም ኦሮማይ፡፡ በዜጎቻቸው ይደርስ የነበረውን ሞት፣ጉዳት እንዲሁም በሀገሮቻቸው ሀብት ላይ ይደርስ የነበረውን ውድመት ከአሁን በኋላ ላይመለስ ኦሮማይ፡፡
ዓለም ኢኮኖሚያዊ ውህደት እያደረገ ባለበት በዚህ ዘመን ይህን ውህደት በስኬታማ ሁኔታ መፈጸም የሚያስችል በቂ አቅም ያላቸው እነዚህ ሀገሮች ይህን አቅም ተጠቅመው ከመበልጸግ ይልቅ ያላቸውን ሀብት በሚቀማ ጦርነት እና የጦርነት ፍጥጫ ውስጥ ቆይተዋል፡፡ሁለቱ ሀገሮች አሁን የደረሱበት ስምምነት ወደቦችን ፣ አየር መንገዶችንና የስልክ አገልግሎትን ለማስጀመር የሚያስችል በመሆኑም ይህን እምቅ አቅማቸውን በመጠቀም ለብልጽግና እንዲተጉ ያስችላል፡፡
ስምምነቱ ያ የመከራ ዘመን ተቀይሯል የሚያሰኝ ነው፡፡በእርግጥም ዘመን ተቀይሯል ። ሁለቱም ሀገሮች ስላለፈው ከማውራት ወጥተው ስለወደፊት እያሰቡ በጦርነት እና በድህነት የተጎዱ ዜጎቻቸውን ለመታደግ መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም በቅድሚያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲያገግም ማድረግ ይገባል፡፡በሚቀጥለው አዲስ ዓመት እንደሚካሄድ የሚጠበቀው ጉብኝትም ለዚህ ፋይዳው ከፍተኛ ነውና በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡
የጦርነት ታሪክ ተዘግቷል፤ኦሮማይ ! ታላቅ ደንቃራ ከመንገዳቸው ላይ ተነስቷል እናም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት ግንቡን እያፈረሱ ወደ ልማት የሚያሸጋግራቸውን ድልድይ ለመገንባት በትኩረት ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡
ስምምነቱ ለቀጣናው ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡አፍሪካ በንግድ ለመተሳሰር እየሰራች በዚህ ወቅት የኢትዮጵያና ኤርትራ ውዝግብ መፍትሄ ማግኘቱ ለአህጉሪቱ የንግድ ግንኙነት ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋልና በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተደረሱትን ስምምነቶች መሬት ላይ እንዲወርዱ በትኩረት መስራት ቀጣዩ አብይ ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡ ኦሮማይ ጥላቻ፣ኦሮማይ ግጭት፡፡ በፍቅርና በይቅርታ ተተክተዋል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና ኤርትራ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነታቸውን ወደ መደበኛነት መመለስ የሚያስችል የሰላምና የልማት ስምምነት ፈፀሙ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ባካሄዱት የሁለት ቀናት ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሁለቱ አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት በሚቀጥልበት መንገድ ላይ መክረዋል።
ከውይይቱ በኋላም፤ የሁለቱ አገራት መሪዎች በተለያዩ መስኮች ተባብሮ ለመሥራት ለሰላምና ልማት ከስምምነት ደርሰዋል። አገራቱም በመካከላቸው የነበረው ጦርነት በይፋ ማብቃቱን በማስታወቅ፤ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች ተባብረው ለመሥራትና በዲፕሎማሲ፣ በፀጥታ፣ በንግድ፣ በትራንስፖርት እንዲሁም በቴሌኮሙዩኒኬሽን መስኮች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
አገራቱ በስምምነቱ የጦርነት በርን በመዝጋት በልማት ለመተባበር፣ ቀጣናዊ ሰላምን በማስፈን እድገትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ወደብ መጠቀምን ጨምሮ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመጀመር የተስማሙ ሲሆን፣ በአዲስ አበባና አስመራ ኤምባሲዎቻቸውንም ለመክፈት ስምምነት ፈፅመዋል።
ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የስልክ አገልግሎት ለማስጀመር እንዲሁም የሁለቱ አገራት አየር መንገዶች ወደ አገራቱ መደበኛ በረራ እንዲያካሂዱና የአልጀርሱም ስምምነት ሆነ የድንበር ስምምነቶች ገቢራዊ እንዲሆኑ ከመስማማት ደርሰዋል።
የሁለቱ አገራት ዳግም ግንኙነት አስመልክቶም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ፣ «በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ድንበር በፍቅር ፈርሷል» ብለዋል።ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም ጥሪና አጋርነትን በእጅጉ አድንቀዋል። ሁለቱ መሪዎች አገራቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገራቸውን አብስረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሁለት አስርተ ዓመታት በኋላ ታሪካዊ የተባለለትን ጉብኝት በማድረግ አስመራ ሲገቡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኤርትራውያን ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ይታወሳል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ በኤርትራ የነበራቸውን ቆይታ በማጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አሸኛኘት አድርገውላቸዋል፡፡ 

ታምራት ተስፋዬ 

 

Published in የሀገር ውስጥ
Tuesday, 10 July 2018 16:29

እጅ ወደላይ ያሰኘ ፍቅር

«ሚሳኤል፣ ታንክ፣ ክላሽንኮቭ…. የሰውን አካል መማረክ ይችላል፤ የሰውን ልብ ግን መማረክ አይቻለውም፡፡ የሰውን ልብ መማረክ የሚችለው፣ ብዙ ወጪ የማያስፈልገው ፣ ራሽያ አሊያም ቻይና መሄድ የማይጠይቀው በተፈጥሮ የተሰጠን ፍቅር ነው፡፡ በአስመራ ያየነውም ፍቅር ለእኛ ስንቅ ነው» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአስመራ የተደረገላቸውን አቀባበል አድንቀዋል፡፡

የልብ መዝገብን አንደበት ይተርከዋል እንዲሉ ከትናንት በስቲያ በአስመራ ብሄራዊ ቤተ መንግሥት በአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ህዝቡ ደግሞ በአስመራ ጎዳናዎች ያደረገላቸውን አቀባበል ከልብ የተደረገ ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ዶክተር አብይ፣ በረሃ ገብተው ነፍጥ አንግበው የሚዋጉትን፣ በተለያየ ምክንያት በእስር ቤት የተጣሉትን እንዲሁም ውሃ በማይቋጥር ሰበብ ተለያይተው ፍቅር የተራቡትን ድልድይም መሰላልም በመሆን ላከናወኑት የማይረሳ ተግባር ኢትዮጵያውያኑ አንስተው አይረኩም፡፡ በጥይት ሳይሆን በፍቅር ቃላት ማርከው የኢትዮጵያውያንን ልብ በማሸፈት እጅ ወደላይ ያስባሉት እኚህ መሪ፣ ከትናንት በስቲያም በአስመራ ተመሳሳይ ታሪክ ደግመዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች እውነተኛ ፍቅር በአደባባይ ተገልጧል፡፡ የአስመራ ጎዳና በፍቅር ከመድመቅም በላይ የናፍቆት እንባም ሲረጭበት ተስተውሏል፡፡
በአስመራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገውን የአቀባበል ትዕይንት በተመለከተ ያነጋገርናቸው የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችም እንደተናገሩት፤ ኤርትራውያን ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ፍቅርና ክብር በአደባባይ አይተዋል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም ያደረጉት ሥራ ከቃላት በላይ ሆኖ አግኝተውታል፡፡
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫኔ ከበደ ፤ ‹‹በአፍሪካ ምድር ያልታየ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም ይላሉ፡፡ ‹‹ እለቱ የኤርትራ ህዝብ በነጻነት ስሜቱን የገለጸበት ነው፡፡ ሁለቱ ህዝቦች አንድ ናቸው፡፡ ወቅታዊ ሁኔታዎች ቢለያያቸውም የእነርሱ ፈቃድ እንዳልሆነ በእለቱ ማረጋገጥ ተቸሏል›› በማለት በአስመራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገውን አቀባበል ገልጸውታል። አቀባበሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሆንም ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸውን ክብር፣ ፍላጎትና አንድነት በእጅጉ የሚያሳይ ገጽታ ነበረው ይላሉ፡፡
‹‹የህዝቡ ሁኔታ ልብን የሚነካ ነው፡፡ ወደፊት በጋራ በመሥራት ማደግ ይቻላል፡፡ ትልቅ ተስፋም አለ፡፡ በኢኮኖሚም መተሳሰር ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያም ወደብ መጠቀም ከቻለች ነጻ የንግድ እንቅስቃሴ ከተደረገ በአንድነት ማደግ ይቻላል›› ይላሉ፡፡
የተጀመረው የሰላም እንቅስቃሴ እንዳይደናቀፍ ጠንከር ያለ የዲፕሎማሲ ሥራ መሠራት እንደሚያስፈልግ ዶክተር ጫኔ ጠቁመው፤ የሁለቱ አገሮች ስምምነትም የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ማድረግም ተገቢ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡
የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ በበኩላቸው፤ ሁለቱ አገሮች አንድ አይነት ባህልና ቋንቋ ያላቸው፣ በደም የተሳሰሩ ወንድማማቾች ህዝቦች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በፖለቲካ ምክንያት በተደረጉ ጦርነቶች ልብን የሚሰብር እልቂት የተፈጸመበት ጊዜ ብናሳልፍም ልብን የሚያቀልጥ ፍቅርን በትናንት በስቲያው እለት ማየት ችለናል›› በማለትም አቀባበሉን ያደንቃሉ፡፡
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትራችን ቆራጥና ደፋር መሆናቸው የጥላቻን ግንብ ማፍረስ አስችሏቸዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች በፍቅርም እንዲገናኙ ማድረግ ችለዋል፡፡ የጥላቻው ግንብ ፈርሶ የፍቅር ድልድይ እንዲተካ ያደረጉት አስተዋጽኦ ታላቅ ነው›› ሲሉም ገልጸውታል፡፡
እንደ አቶ አየለ ገለጻ፤ እለቱ በኢት ዮጵያውያንም ሆነ በኤርትራውያን ልብ ውስጥ ታላቅ ቀን ሆኖ የሚዘከር ነው፡፡ ታሪክነቱ ለሁለቱ አገሮች ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ቀንድ ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ለሰላም ትልቅ መሰረት የሚጥል ከመሆኑም በተጨማሪ ለኢኮኖሚውም ታላቅ በረከት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሁለቱም አገሮች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የሚናገሩት አቶ አየለ፣ ስደተኝነትን እንደሚያስቀርም ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ክስተት የዓለም መገናኛ ብዙኃን ሁሉ ትልቅ ስፍራ ሰጥተው ሲቀባበሉ መዋላቸውም ታላቅ ጉዳይ መሆኑን እንደሚያመለክት ይናገራሉ፡፡
የመላ ኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ንቅናቄ ፕሬዚዳንት ልጅ መስፍን ሽፈራው፤ በቀጣይ ለሚሠራው ሥራ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ አሁን እየታየ ያለው ሰላም ጅምር ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱም በጣም ደስተኛ ሆነው አይተናቸዋል፡፡ ኤርትራውያን ለሰላም የታመቀ ውስጣዊ ፍላጎት እንደነበራቸው ያስታውቃል፡፡
‹‹አቀባበሉ የወንድምነትና የቤተሰባዊነት ነው፡፡ የአስመራ ጎዳና በፍቅር ደምቆ ሲታይም እውን እነዚህ ሰዎች ሃያ ዓመት ሙሉ በጠላትነት ተፈራርጀው የቆዩ ናቸው የሚያስብል ነው›› ይላሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፣ የኤርትራን የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ‹ደርቤ እንድሠራ ተፈቅዶልኛል› ያሉትም ኤርትራ በአካባቢው አገሮችና በዓለም አቀፉ መድረክ ያለው ተጽዕኖና ጫና እንዲነሳላት ለማገዝ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንኳን ወንድም ለሆነው ህዝብ ቀርቶ በጉርብትናም ስም ሊደረግ የሚችል ነውና መልካም ነው የሚል እምነት አለኝ›› ብለዋል፡፡
አጎራባች በሆኑት በትግራይና በአፋር አካባቢ ያለው ሁኔታም ማንንም ቅር በማያሰኝ መልኩ ሊፈታ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ጅምሩንም አድንቀዋል፡፡ በቀጣይ እንደጎረቤት ሳይሆን እንደ ወንድምና እህት መቀራረቡ ለኢኮኖሚው እድገቱም ሆነ ለቀጣናው ሰላም ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹የዶክተር አብይ አካሄድ እንደ ተቃዋሚ ምንም እንድንናገር እድል የሚሰጥ ሆኖ አልተገኘም፡፡ እንዲያውም አጀንዳችንን ሁሉ ነው እየወሰዱት እየሠሩ ያሉት፡፡ ያልሠሩት ምን ይሆን የሚያስብል ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት፡፡ በዚህ አይነት አካሄዳቸው ምናልባት ወደፊት ድርድርም ላያስፈልግ ሁሉ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ተፎካካሪና ተቀናቃኝ መሆንም የግድ ላያስፈልግ ይችላልና›› በማለት አስተያየታቸውን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን የተደረገው እንቅስቃሴም ፍሬ አፍርቶ በሁለቱ አገር መሪዎች መካከል የስምምነት ፊርማ መካሄዱም ታውቋል፡፡ 

ዜና ሐተታ
አስቴር ኤልያስ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።