Items filtered by date: Wednesday, 11 July 2018

የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታ የተጀመረው እአአ በ1971 ጋና አክራ ላይ ነው። ይህ በአስር ተሳታፊ ሀገራት የተጀመረ ውድድር፣ ከፍተኛ ትምህርትና ስፖርት በማስተሳሰር ጤናማ ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድ ዓይነተኛ ሚና የመጫወት ዓላማ አለው። ከስፖርታዊ ክዋኔው በተጓዳኝ አፍሪካውያን በአንድነት ተሰባስበው የእውቀት፣ የልምድ፣ የባህልና ሌሎች እሴቶቻቸውን እንዲለዋወጡ ማድረግንም ታሳቢ ያደርጋል።
ምንም እንኳ የጨዋታው ዓላማ ይህን መሰል አዎንታዊ ሚና ቢኖረውም የውድድሩ መርሃ ግብር ግን የአስፈፃሚና ባለድርሻ አካላት በቂ ትኩረትና የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን አልታደለም። በዚህም ምክንያት ወጥ ሆኖ መካሄድ አልሆነለትም። ውድድሩ ከጋናው መድረክ ከ3 ዓመት በኋላ በኬንያ ናይሮቢ ቢካሄድም ከዚያ በኋላ በነበረው ዓመታት ባልታወቀ ምክንያት ሳይካሄድ ቆይቶ በ2004 በናይጄሪያ ባውንቺ ድጋሚ መጀመር ችሏል። እአአ በ2016 በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የተካሄደ ሲሆን፤ ውድድሩ ብዙም ደማቅ ያልነበረና ዘጠኝ ተሳታፊ አገራት ብቻ ያሳተፈም ነበር።
ይህን መልክ የነበረው ውድድሩ የአዘጋጅነቱን ዕድል ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ እጅ በመቀበል መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለዘጠነኛው የአዘጋጅነቱን ኃላፊነት ስትረከብ የተሻለ የውድድር ዝግጅት እንደሚደረግና በነበረው ሽር ጉድ ውስጥም የነበረው ቀዝቃዛ መልክ ለመሻር ትኩረት እንደተሰጠ ከውድድሩ በፊት ሲገለጽም ቆይቷል።
የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታ ለዘጠነኛ ጊዜ ኢትዮጵያ እንድትረከብና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነቱን የመካሄዱ ዜና የተሰማው መስከረም 20 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር። የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ፌዴሬሽን ይሄን ውሳኔ ለመወሰኑ በተለየ መልኩ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የመሠረተ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ የመስራቱ ውጤት መሆኑ ተያይዞ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የመላ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታ ሲዘጋጅ የመጀመሪያ ጊዜ እንደመሆኑ ዝግጅቱም ይሄንኑ መሠረት ባደረገ መልኩ እንዲሆን ደፋ ቀና ብሏል። መቐለ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነቱን ከተቀበሉ በኋላ ባለፉት ወራት ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ሁለት የእግር ኳስ ሜዳዎችን ጨምሮ አራት ሜዳዎችን በማዘጋጀት የውድድሩን ዕለት ሲጠበቅ ቆይቷል። መሰናዶውን በአስፈላጊው ጊዜ በማጠናቀቅም በጉጉት ሲጠበቅ ለነበረው ዕለት አድርሷል። ደማቅ በሆነ መልኩ መስተንግዶውም በማሰናዳትም፤ ጨዋታው ሰኔ 24 ቀን በትግራይ ስታዲየም በይፋ በተጀመረበት ዕለትም ይህኑ አስመስክሯል።
የዘንድሮው የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታም መቀሌ ላይ ለስድስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል። በአስር የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በተካሄደው ውድድርም የአፍሪካ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በስፖርት ዘርፍ ያላቸውን እምቅ አቅም አሳይተውበታል። ውድድሩንም 980 ያህል ተሳታፊዎች ያደመቁት ሲሆን፤ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ጨምሮ ከአህጉር አፍሪካ18 አገራት የተውጣጡ 56 ዩኒቨርሲቲዎች አሳትፏል።
ውድድሩ ባሳለፍነው ዓርብ ዕለት በመቀለ ዩኒቨርሲቲ ዓዲ ሃቂ ጊቢ በሚገኘው ስታዲየም ተጠኗቋል፡፡ በቆይታው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ምን ዓይነት አሻራ አሳልፎ እንደተጠናቀቀ ለመዳሰስ ተሞክሯል። በዚህም ውድድር የተሳታፊ አገራት ቁጥርን በእጥፍ ጨምሮ የተካሄደው ውድድሩ ከባለፉት ዓመታት አንጻር ደማቅና ለየት ያለ እንደነበር ከተሳታፊዎች ተገልጿል።
የአዲግራት ዩኒቨርሲቲን ቮሊ ቦል ተጫዋች የሆነችው ሳምራዊት ሐዲስ የጨዋታው ታዳሚ ከሆኑት አንዷ ናት። ሳምራዊት «ውድድሩ ከስፖርቱ ባሻገር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ላይ ትልቅ ትርጉም ያለው ተግባር የታየበት መሆኑን ትናገራለች።
በውድድሩ አሸናፊ ተሸናፊ ከሚለው ትርጓሜ በላይ የእርስ በእርስ ትውውቅ የሚፈጥር መሆኑን የምትገልፀው ሳምራዊት፥ እኔም ሆንኩኝ ከእኔ ጋር የመጡ የቡድን አጋሮቼ የሚጋሩት የዘጠነኛው ሻምፒዮና ቆይታችን አዝናኝ፣ አስተማሪና አስደሳች እንደነበር ነው» ትላለች።
«ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ በመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታ ስሳተፍም በተመሳሳይ የመጀመሪያዬ ነው» ያለው የጋናው ዴኤቨሎፕመንት ስተዲ ዩኒቨርሲቲ የአጭር ርቀት ሩጫ ተወዳዳሪ ወጣት ዴሪክ ሳአኮሬ ደግሞ፤ ውድድሩ የነበረው ስፖርታዊ ፉክክር ጠንካራ የሚባል ነው ለማለት የሚያዳግት መሆኑን ይገልጻል።
ይሁንና ከውድድሩ በተጓዳኝ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ላይ ግን በጣም ጥሩ የነበረና በተለይ አፍሪካ የተለያዩ አገራት ስብስብ ብቻም ሳይሆን ማራኪ ባህላዊ አለባበሶች፣ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች፣ አይቼና ሰምቼ የማላውቃቸው የምግብ ዓይነቶች በተለይ በኢትዮጵያ መኖሩን ያወቁኩበት አጋጣሚ ነው ሲል ቆይታውን ይገልጸዋል።
በውድድሩ በአትሌቲክስ ረጅም ርቀት ዩኒቨርሲቲውን በመወከል በውድድሩ ሲሳተፍ የነበረው ከኡጋንዳ ዴጄ ዩኒቨርሲቲ ጄኮቭ ኦሆራጅ የዘንድሮው ውድድር ካለፉት ጊዜያት የተሻለ እንደነበር ይናገራል፡፡ በመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው ኦሆራጅ፣ ከሁለት ዓመት በፊት በጆሃንስበርግ የተካሄደውን ውድድር በቅርበት ለመመልከት ችሏል። በጊዜው የነበሩት ተሳታፊ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ጥቂት የሚባል እንደነበር ያስታውሳል።
ውድድሩ የከፍተኛ ተቋማት በቀለም ትምህርቱም ብቻ ውጤታማ መሆንን ከማሰብ አመለካከትና ልምድ እንድንወጣ የሚያደርግ መድረክ ነው። ተሳታፊዎቹም የአገራቸውን ስም እንዲያስጠሩ የማስቻል አቅሙ ከፍተኛ ነው ይላል።
ከዚህ ቀደም የነበረው ውድድር ለስፖርት መሠረተ ልማት የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን የሚያስታውሰው ኦሆራጅ፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት መሠረተ ልማት ላይ ትልቅ ሥራ መስራታቸውን የሚያበረታታና ለሌሎች አፍሪካ አገራት ጥሩ ተሞክሮ እንደሚሆን ነው ያስገነዘበው። በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን ያሳተፈው የመቀሌ የመላ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድርም ብርቱ ፉክክር የታየበትና ለተመልካችም አዝናኝ እንደነበር የሚገልጸው ተሳታፊው፤ ከስፖርቱ አኳያ በተለይ የኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ በእግር ኳሱም ሆነ በሌሎች ስፖርቶች ከነበሩት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጠንካራና ሆኖ መመልከቱን ያነሳል። ይሁንና እነዚህ መልካም ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ከጠቀሰው ውጪ ያሉት ተሳታፊ ዩኒቨርሲቲዎች በስፖርቱ በኩል ችግሮችና ክፍተቶች እንዳሉ ሃሳቡን ሰንዝሯል።
በአጠቃላይ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተመለከተው አገሪቱ አህጉራዊ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም እንዳላት መሆኑን የሚገልጸው ተሳታፊው፤ ውድድሩን በዚህ መልኩ ቀጣይ ለማድረግ የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌዴሬሽን ዩኒቨርሲቲዎች በስፋት እንዲሳተፍ የሚያደርግ ሥራ በቀጣይ መስራት ከቻለ ከዚህ በተሻለ መሆን ይችላል፤ ቀጣይ ውድድሩን የሚያዘጋጀው ዩኒቨርሲቲም ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮ በመውሰድ ልባዊ ትኩረትን የሰጠ ዝግጅት አድርጎ መቅረብ ይገባል ሲል ሃሳቡን ገገልጿል።
የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ማሉምቤቴ ራሌቴኤም ዘጠነኛው የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ከባለፉት የውድድር ጊዜያት በተሻለ መልኩ ደማቅና የተሳታፊውን ቁጥር ከፍ ብሎ የተከናወነ መሆኑን ይስማሙበታል።
በመቀሌ የተመለከቱት ውድድር ከጠበቁት በላይ መሆኑን የሚገልፁት ፕሬዚዳንቱ፤ «በመቀሌ በነበረን ቆይታም ኢትዮጵያ አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም እንዳላት ታዝበናል ነው ያሉት።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ ውድድሩ አፍሪካውያን በአንድነት ተሰባስበው የእውቀት፣ የልምድ፣ የባህልና ሌሎች እሴቶቻቸውን እንዲለዋወጡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ ማድረግ ችሏል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ አክባሪነትን የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌትነትን አስመስከሯል።
ውድድሩን እጅግ በጣም በተሳካ ሁኔታ ተጀምሮ ተጠናቋል የሚሉት ደግሞ፤ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህርና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ከሰቴ ለገሰ ናቸው።
እንደ ዶክተር ከሰቴ ገለፃ፤ ለዚህ ስኬት በመጀመሪያ ደረጃ በስፖርት መሠረተ ልማቱ በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ግቢዎች ውስጥ ስታዲየሞች ተገንብተዋል፡፡ በተጨማሪ በአንድ ሜዳ ላይ ሦስት የጨዋታ ዓይነቶችን ማስተናገድ የሚችሉ መወዳደሪያ ቦታዎች በአራቱም ዩኒቨርሲቲ ግቢዎች ተገንብተዋል። በቤት ውስጥ ለሚደረጉ ውድድሮችም ጂምናዚየሞች ተሰናድቷል። ይህም ውድድሩ ያለምንም የመለማመጃም ሆነ የመጫወቻ ችግር ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ አስችሎታል።፡
«በማንኛውም ዓለም አቀፍም ሆነ አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ የበጎ ፈቃደኞች ሚና ትልቅ ነው ያሉት ዶክተሩ፤ በዘንድሮው የመላ ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታውም የበጎ ፈቃደኞች ሚና እጅጉን የላቀ እንደነበር ነው የገለፁት።
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የበጎ ፈቃደኞችን አቅም ለመጠቀሙም በ15ኛው የዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ካስተናገደችው ደቡብ ኮሪያ የወሰደው ተሞክሮ እንደረዳው የሚያስረዱት ዶክተሩ፤ ዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ኮሪያ በጎ ፈቃደኞች ማኅበር ጋር ስምምነት በማድረግ ከዩኒቨርሲቲው ለተውጣጡ 600 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ እንዲሁም ከከተማው ነዋሪና ከቀይ መስቀል በማቀላቀል የተውጣጡ ወጣቶችን ሥልጠና እንዲሰጣቸው ማድረግ መቻሉንና ይህም ለውድድሩ ስኬት ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው ያስረዱት።
የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር በአገራችን መዘጋጀቱ በቀዳሚነት ተማሪው ያለውን ባህል ለሌሎች ማጋራትና የሌሎቹን ወደ ራሳቸው በማምጣት ልምድ መለዋወጥ ያስቻለ አጋጣሚን የፈጠረ መሆኑን የሚገልፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይ ኪዳነ ናቸው። ውድድሩም ከስፖርት ባሻገርም በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ያለውን የትምህርት ሒደት፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንዴት ናቸው? የኅብረተሰቡ አኗኗርና ባህል ምን ይመስላል? የሚለውን ያስመለከተ መድረክ መሆኑን ይናገራሉ።
በአጠቃላይ ከውድድሩ ስለ ተገኘውን ፋይዳ አቶ አባይ ሲገልፁት፤ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ላይ የሚገኙና ከተወዳዳሪዎቹ ጋር ወደ ውድድር መድረኩ የሚመጡ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች የሚደረገው ውይይት በሴሚናር፣ በጥናትና ምርምር፣ በኅብረተሰብ ጉዳይና በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ጉዳዮች እንዲመቻቹ አድርጓል፡፡ የቱሪስት መስህቦች እንዲጎበኙ በማድረግ በአገር ገጽታ ግንባታ ላይም ትልቅ ሚና ነበረው። በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ተተኪዎች ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ ላሉ ክለቦች ግብዓት የመሆን ዕድልን ይከፍታል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን አህጉራዊ ውድድሮችን የማዘጋጀት አቅም እንዳላት ነጸብራቅ ሰጥቷል ነው ያሉት።

ከ20 ዓመት በታች የቼስ ሻምፒዮና  አማራ ክልልና ድሬዳዋ ሻምፒዮና ሆኑ

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስተናጋጅነት ሲካሄድ በነበረው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ከ20 ዓመት በታች የአገር አቀፍ የቼስ ሻምፒዮና ትናንት ተጠናቀቀ። ከሰኔ 25 ጅምሮ ሲካሄድ በሰነበተው ሻምፒዮናው ፤በሴቶች የግል የበላይነት አማራ ክልል ሻምፒዮና ሆኗል። በተለያዩ የውድድር ዘርፎች ፉክክር ሲደረግበት በነበረው ውድድር የኢትዮጵያ ሻምፒዮና መቅደስ ሞገስ ከአማራ ክልል አንደኛ ስትወጣ፤ መርሀዊት ብርሃነ ከትግራይ እንዲሁም ረድኤት ሰጠኝ ከአማራ ክልል 2ኛና 3ኛ ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡
በወንዶች የግል የበላይነት ደግሞ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ማራኪ እንድርያስ ከድሬዳዋ አንደኛ ሲወጣ ፤ሮቤል ብርሃነ ከትግራይ እንዲሁም ሀብታሙ ባዮ ከኦሮሚያ 2ኛና 3ኛ ደረጃ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል፡፡በውድድሩ ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እና በአራት ክልሎች የተሳተፉ ሲሆን ፤ፉፁም ጨዋነት የተሞላበት እና ከፍተኛ ፉክክር የታየበት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዳንኤል ዘነበ 

Published in ስፖርት
Wednesday, 11 July 2018 16:57

የባህር ሞገዱን የተራመዱ

 

እያንዳንዱ ሙያ በራሱ ስነምግባርና ደንብ የተቃኘ ሲሆን፤ መልካም ፍሬ ይኖረዋል። በስሩ የሚገኙ ባለሙያዎችም ለተቀመጠው ህግና መመሪያ ተገዢ መሆን ሲችሉ ለበርካቶች አርአያ ይሆናሉ። ሁሌም በመልካም ስነምግባር የታነጸ ባለሙያ ደግሞ ስለትላንት የሚያወሳው ታሪክ ይኖራል። ሥራውን ለውጦ በሌላ ስፍራ ቢቀመጥ እንኳን ያለፈበት የህይወት መስመር የሚዘነጋ አይሆንም። የአዲስዘመኗ መልካምስራ አፈወርቅም ቀደም ሲል በመርከበኝነት ሙያ ያለፉና ዛሬም የትላንቱን ጊዜ በበጎ እያስታወሱ ትዝታቸውን ከሚያወጉ ባህረኞች ጋር ቆይታ አድርጋ ያካፈሏትን ተሞክሮ እንዲህ ታጋራናለች።

የትላንትናውን የህይወት መንገዱን ሲያስበው አሁን ለሚገኝበት መልካም ስብዕና መሰረት እንደሆነው ያምናል። በ1976 ዓ.ም በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለ እሱና ስድስት ጓደኞቹ ወደግሪክ አገር ተጓዙ። የዛኔ አገር ርቀው ባህር አቋርጠው የሄዱበት ዓላማ ታላቅ ኃላፊነትን የሚሻ፣ ማንነትንም የሚፈትን ሙያ ነበር። ከአራት ዓመታት በኋላ ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ አገራቸው ለታላቅ ተልዕኮ ትፈልጋቸዋለች።
ቺፍ ኢንጂነር አድማሱ ይታገሱ፤ ገና በአፍላነት ዕድሜው መርከበኛ ለመሆን ሲወስን የባህሩን ቆይታና አይቀሬዎቹን ስጋቶች አላጣቸውም። መቼም ቢሆን የባህር ላይ ነፍስ ከአስፈሪና ከአስደንጋጭ አጋጣሚዎች የራቀ እንደማይሆን ያውቃል። የመርከብ መስመጥና አደጋው፣ የማዕበሉ ወጀብና ግፊት፣ የአሳነባሪው ቁጣና የባህር ላይ ወንበዴዎች ክፋት ሁሉ አብረውት ይጓዛሉ።
መርከበኝነትን ሙያ አድርገው ሲቀበሉት ከእነዚህ እውነታዎች ጋር ተስማምቶ መጓዝ ግድ ይላል። አንዳንዴ በባህር ላይ ወራትን አልፈው ዓመታትን ሲሻገሩ ፣ ውስጣዊ ስሜት እንደውቅያኖስ አይረጋም። እንደ መርከብ እግርም በመልህቅ አይታሰርም። እንዲህ በሆነ ጊዜ ቤተሰብ በእጅጉ ይናፍቃል። የሀገርና የወገን ትዝታም ልክ እንደባህሩ ሽታ ውል እያለ ይፈታተናል።
መርከበኛው አድማሱ በግሪክ ቆይታውን አጠናቆ ሲመለስና ሙያውን አሀዱ ብሎ ሲጀምር ከእነዚህ ስሜቶች የራቀ አልነበረም። የዛኔ የመጀመሪያውን የሩቅ ምሥራቅ ጉዞ ያቀናባት «ነፃነት» የተባለችው መርከብ ነበረች። በዚህች መርከብ ተጉዞ ወደተነሳበት የአሰብ ወደብ ለመመለስም አራት ወር ተኩል ያህል እንደቆየ ያስታውሳል። በጉዞውም የጃፓን፣ የቻይና፣ የኮሪያ፣ የሲንጋፖር፣ የኬንያና ዳሬሰላም የባህር ወደቦችን አቋርጧል።
መርከበኞች በሚጓዙባቸው ሀገራት፤ በርካታ ስፍራዎችን የማየት ዕድሉ አላቸው። የሌሎች ባህልና ታሪክን ጨምሮ እንግዳ ሰዎችን ለማወቅም የቀረቡ ይሆናሉ። አድማሱና ጓደኞቹ ያዳበሩት ሙያዊ ስነምግባርና ጨዋነት ደግሞ ከብዙሃኑ ሲያስተዋውቃቸው ቆይቷል። የዚያኔው መርከበኛ በጉዞ ወቅት ሊያጋጥም በሚችል አደጋ የነበረውን አጋርነትና መተሳሰብ ዛሬም ድረስ አይዘነጋውም። በየመርከቡ የነበረው ወንድማማችነትና ፍቅርም በቋንቋና ባህል የሚለያየውን ባለሙያ አንድ አድርጎ የሚያሰባስብ ነበር።
ቺፍ ኢንጂነር አድማሱ ሙያዊ ግዴታውን በብርታት ሲወጣ እንደቆየ ያስታውሳል። ከሁሉም በላይ ግን የቤተሰቡ ናፍቆትና ትዝታ ይፈታተነው እንደነበር አይሸሽግም። የዚያኔ እንደአሁኑ የሞባይል ስልክ በሁሉም እጅ አልገባም። በቀላሉ የቤተሰብን ደህንነት ጠይቆ ለማወቅ ይቸግራል። ይህን ለማድረግ የሚኖረው አማራጭ መርከቡ በቆመበት የወደብ ከተማ የመስመር ስልክ አፈላልጎ መደወል ብቻ ይሆናል። በወቅቱ ለአገር ቤት ስልክ የሚጠየቀው ወጪ ከፍተኛነት ኪስን የሚጎዳና ኢኮኖሚን የሚያራቁት ነበር።
ሁሌም ቢሆን የባህርን ሞገድና ተፈታታኝነቱን መቋቋም ሙያዊ ግዴታ ነው። ይህ አይቀሬ ትግልም ለአንድ ባህረኛ በቀላሉ የሚረሳ አይሆንም። መርከበኛ አድማሱም ይህን ስሜት በዋዛ መልመድ እንደማይቻል ዛሬም ድረስ የሚመሰክረው ነው።
የባህር ላይ ሞገድ ድንገት ቢነሳ መርከበኛው ተጓዥ ሥራውን በአግባቡ ሊወጣ ግድ ይለዋል። ከተፈጥሯዊ ፈተናዎችና ከራሱ ስሜት ጋር እየታገለም ሙያውን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል። ቺፍ ኢንጂነር አድማሱ በሲንጋፖር ጉዞ የባህር ላይ ወንበዴዎችን ድንበር የማቋረጥ አጋጣሚን ጭምር እንደተጋፈጡ ያስታውሳል።
መርከብ በተበላሸ ጊዜም ዕረፍትና እንቅልፍ ይሉት ነገር አይታሰብም። ከሰማይ በታች በሰፊው የባህር ሜዳ ላይ የቆመው ግኡዝ አካል ነፍስ ዘርቶ እስኪንቀሳቀስ በትጋት መረባረብ ያስፈልጋል። ይህ ዓይነቱ ጉዳይ ሲነሳ ቺፍ አድማሱ በሙያው አጋጣሚ የደረሰበትን እውነት ዛሬም ድረስ ያስታውሳል።
በአንድ ወቅት እሱና የሥራ ባልደረቦቹ አዲስ መርከብ ከሮተርዳም ወደብ ይረከቡና ጉዟቸውን በሲዊዝ ካናል ወደአሰብ ወደብ ያደርጋሉ። መርከቧ ለጉዞ አዲስ እንደመሆኗ አብረዋት ካሉት ባህረኞች ጋር በቀላሉ አልተግባባችም። የሚስተዋልባት የቴክኒክ ችግርም እምብዛም የሚያራምዳት አልሆነም። የመርከቧ ያልተለመደ ባህርይ ለሁሉም መርከበኞች የእራስ ምታት ቢሆን ጤንነቷን ለመመለስ ትግሉ ተጀመረ። ዕረፍት አልባው ትንቅንቅም በስጋት ታጅቦ የአዕምሮና ጉልበት ዋጋን አስከፈለ።
ቺፍ አድማሱ ለአንድ ዓመት ያህል በባህር ላይ ትግል ከገጠመችው መርከብ ሌላ «በተአምር ተረፍኩበት» የሚለውን አይረሴ አደጋ መቼም ቢሆን አይረሳውም። ወቅቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተጀመረበት1990 ዓ.ም ነበር። በዚህ ጊዜ አሰብ ወደብ የቆመችውና እሱ የነበረባት መርከብ በከባድ መሳሪያ ትመታለች። በመርከቧ ላይ ያጋጠመው ጉዳት የላቀ መሆኑ በውስጧ የነበሩት ይተርፋሉ የሚባልበት አልነበረም። ቺፍ አድማሱና ባልደረቦቹ ግን ያለምንም ችግር በህይወት መኖራቸው ታወቀ። ለእሱ ይህ ተአምር አሁንም ድረስ በእጅጉ የሚያስገርመው ነውና ፈጣሪውን ደጋግሞ ያመሰግናል።
ቺፍ አድማሱ ከሦስት ጉልቻ በኋላ ተመልሶ ወደባህር መጓዝ ፈተና ሆኖበት ቆይቷል። ከትዳር አጋሩ ለመለየትም ስሜቱ ቀላል እንዳልነበረ ትዝ ይለዋል። አጋጣሚ ሆኖ ከጋብቻው በኋላ በመርከበኝነት ህይወት አለመዝለቁ የመለያየትን ሰቀቀንና ጭንቀት እንዳይደጋግመው አግዞታል።
ዛሬ ቺፍ ኢንጂነር አድማሱ የአራት ልጆች አባት ነው። በኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ተቋም በመምህርነት ሙያ እያገለገለ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በምህንድስና ሙያው በነበረው ታላቅ ተሳትፎ ከሀገራችን አስራአንድ መርከቦች መሀል የዘጠኙን ግንባታ በእሱ መሪነት አጠናቋል። ይህ መሆኑ ደግሞ በሙያው የሚኮራበት ተግባር ነውና ሁሌም ደስ ይለዋል።
ካፒቴን ጌትነት አባይ፤ አሁንም ቢሆን የባህር ላይ ቆይታውን የመርከብ ትዝታውንና የሥራ ላይ ፍቅሩን አይረሳም። ዛሬም የጥቁር ባህር ትዝታ፣ በዓይኑ ውል ይልበታል። የውቅያኖሱ ንፋስ፣ የማዕበሉ አረፋና ወጀብም ከጆሮው ሽው ይላል። ለእሱ ባህረኝነት ክቡር ሙያው ነው። ከዓመታት በኋላ ልክ እንደዛሬ የሚያስበው የህይወት ጥሪ።
ከዚህ ቀደም ያለፈበትን የመርከበኝነት ሙያ የሚያስታውሰው በተለየ ትዝታ ነው። እኤአ የመጀመሪያ ዲግሪውን በኒዮቲካል ሳይንስ ከህንድ አገር ከወሰደ በኋላ ሙያውን የጀመረው በተለማማጅ መሪ መኮንንነት ወደ ሀገሩ ተመልሶ ነበር። የዛኔ አድማስና አባይ ወንዝ የሚባሉ ሁለት መርከቦች ነበሩ። ካፒቴኑ መርከቦቹን ያወቃቸው በሙያው አጋጣሚ ነበርና ከእነሱ ጋር ለመዝለቅ የቀረበ ነበር።
የመጀመሪያው የባህር ጉዞ ከአሰብ ጂቡቲ ወደ ምጽዋ ቀጥሎም አውሮፓ ሆነ። በጀርመን የብሬመን ሀመን ወደብ ከነበረው ቆይታ በኋላም ወደ ሀምቡርግ፣ ሰሜን ኢንግላንድ፣ ሮተርዳምና ባርሴሎና አቀና። በባህር መንገዱ ሲመላለስ ሁሌም መድረሻው አሰብ ወደብ ነበር። ረጅሙን የባህር መስመር ያለማቋረጥ ሲጓዙ ለቀናት ውሃ ላይ መቆየት ይኖራል። በየሀገራቱ በሚገኙ ወደቦች ላይ አረፍ ብለውም የመልስ ጉዞን መጀመር የተለመደ ነው።
አንዳንዴ ወደቦችን አቋርጠው ሲሄዱ ከተሞችን በቅርበት ያገኛሉ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ነጋዴዎች መርከቡ ድረስ ዘልቀው እንዲጎበኟቸው የማድረግ አጋጣሚ ይኖረዋል። እነሱም ቢሆኑ በደረሱበት ከተማ ወርደው ገበያውን ተዘዋውሮ መመልከትን ለምደዋል። ካፒቴን ጌትነት በሠራው አጋጣሚ በርካታ የባህር መስመሮችን አልፏል። ጥቂት በማይባሉ ወደቦች አርፎም የብዙዎችን ባህልና ታሪክ ማወቅ ችሏል። አልፎ አልፎ ደግሞ ምንም ከተማና ወደብ ሳይገኝ ቀናትን የሚገፉበት ጊዜ እንደነበር አይዘነጋም። ከፒቴኑ ለዚህ የሚጠቀሰው አካባቢ ወደ ሩቅ ምሥራቅ የሚደረገውን አሰልቺ ጉዞ ነው። ከጂቡቲ ስሪላንካ፣ ሲንጋፖርና ማላካ የሚደረገው ማቋረጥም ምንም ዓይነት ከተማ የማይታይበት ጉዞ እንደሆነ ያስታውሳል። በተለማማጅ መኮንንነት የቆየው መርከበኛ ከእነዚህ ሁሉ የጉዞ ተሞክሮዎች በኋላ ሙያውን በተጨማሪ ስልጠናዎች አዳበረ። ጥንካሬው እውን ሆኖ ሲመሰከርም የሦስተኛ መሪ መኮንን ካፒቴን ማዕረግን አገኘ።
ባህር ማለት በባህርይው ቋሚ የሚባል አይደለም። ዛሬ ሰላማዊ ቢሆን ነገ ሊለወጥና ሊቆጣ ይችላል። ዝምታና እርጋታው ደፍርሶም በማዕበልና ወጀብ መታጀቡ የተለመደ ነው። ካፒቴን ጌትነትም በመርከበኝነት ህይወት የመጀመሪያው ጥንካሬ ከባህር እንቅስቃሴ ጋር መላመድ እንደሆነ ይናገራል። ከውሃ ጋር ጓደኛ እስኪሆኑ ስሜቱን መዋሀድ ግን ቀላል የሚባል አይሆንም።
ባህር ላይ ሲገኙ ማዞር፣ ማቅለሽለሽና በእጅጉ መረበሽ አይቀርም። አንዳንዴም ችግሩ ከዚህ ያለፈና የጠነከረ ሊሆን ይችላል። ይህ በሆነ ጊዜ ብዙዎች መርከበኝነት በቃን፤ እንደውም ይቅርብን ሊሉ ይችላሉ። ይህ ስሜት ውቅያኖስ ላይ ሲሆን ደግሞ በእጅጉ የበረታና የሚያስቸግር ይሆናል። ሆኖም ሙያውን ተዋህደው ከባህር ሲወዳጁ ድንገቴው አጋጣሚ የዘወትር ትዕይንት ሆኖ ይቀጥላል።
ካፒቴን ጌትነት ባለፈባቸው የባህር መስመሮች ከበርካታ ህዝቦች ጋር ተዋውቋል። ይህ አጋጣሚም ባህልና ልምዳቸው እሱ ከኖረበት ማንንት መራቁን አሳውቆታል። በተመሳሳይ በእነዚህ ስፍራዎች ያገኙት ባዕዳንም መልክና ቁመናው ያስገርማቸዋል። ጸጉሩን እየነኩና እየዳሰሱም በልዩነቱ ይገረማሉ። ጠቆር የሚሉ ባልንጀሮቹን ሲያስተውሉ ደግሞ የመልካቸው ቀለም እንደሚለቅ ገምተው በሙከራ ማረጋገጥን ይሻሉ።
የባህረኛ አለባበስ ዓለም አቀፍ ገጽታን የተላበሰ ነው። ካፒቴን ጌትነትም በሀገሩ ንግድ መርከብ ላይ በሚሠራበት ጊዜ ሰማያዊ ኮትና ሱሪ በነጭ ሸሚዝ ይለብስ ነበር። አለባበሱ እንደየደረጃና ማዕረጉ የሚለያይ ቢሆንም በባህር ጉዞ በተለይም በወደብ አቅራቢያ አለባበሱን የማሟላት ግዴታ እንደነበር ያስታውሳል። አሁን ላይ ግን በአንዳንድ ታላላቅ ድርጅቶች ላይ ይህ አሠራር እየቀረ መሆኑን አስተውሏል።
ካፒቴን ጌትነት ትዳር የመሰረተው ሁለተኛ መሪ መኮንን በሆነበት ጊዜ ነበር። ባህረኝነት ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ፈታኝ እንደሆነም ከህይወት ልምዱ አረጋግጧል። በተለይ የልጆች አስተዳደግንና ሙያዊ ግዴታዎቹን በአንድ ሚዛን ለማስቀመጥ እንደሚከብድ ያስተዋለው እውነታ ሆኗል። እንደሱ ዕምነትም የአንድ ባህረኛ ከባዱ እራስ ምታት ከቤተሰብ ተነጥሎ የሚያሳልፋቸው የብቸኝነት ጊዜያቶች ናቸው።
ዛሬ ላይ ካፒቴን ጌትነት ከባህር ላይ ውሎ አያድርም። ልክ እንደትላንቱም ወደሌሎች ሀገራት ለማቋረጥ በመርከብ ላይ አይገኝም። ይሁን እንጂ አሁንም ከሚወደው ሙያ አልራቀም። በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ውስጥ በመሥራት ላይ ይገኛል። በርካታ ጊዜውን በማሪታይን ባለስልጣን በማድረግም አስፈላጊውን ስልጠና እያበረከተ ነው። ትላንት ባለፈበት ጉዞ ያካበተውን ዕውቀት ለሌሎች ማበርከት ግድ ብሎታልና ለዚህ በመታደሉ ከልቡ ይደሰታል።
ሁለቱም መርከበኞች ትላንትን በሞገዱ ላይ ተራምደዋል። ባህር ወደቡን ተሻግረውም በማዕበል ወጀቡ ተፈትነዋል። ዛሬም ግን ያለፉበትን መንገድ የሚያወሱት ልክ እንደዛሬ ታሪክ በቅርበት ሆነው ነው። አሁንም ደማቁ የሙያ ማህተማቸው በውስጣቸው መፍዘዝ አልጀመረምና።

 

Published in ማህበራዊ

ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት በ1967 ዓ.ም በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ጋር በመሆን ጭቆናን መቃወም ጀመሩ። ከመቃወም ያለፈ ግን ስለብሄራዊ ጭቆና ብዙም ግንዛቤ አልነበራቸውም። በወለጋ ክፍለ ሀገር ዕድገት በህብረት በዘመቱበት ወቅት ባላባቶች በጭሰኛው ላይ የሚያደርሱት ግፍ ሁኔታውን በደንብ እንዲረዱ አድርጓቸዋል። ያዩት ግፍና ጭቆና ለትግል አነሳሳቸው።
በወቅቱ የኢሀፓ አባል ቢሆኑም አባላቱን በደንብ ከሚያውቋቸው የህወሓት ታጋይ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው በ1968 ዓ.ም ወደ በረሃ ገቡ። ከትግሉ በኋላም ከ1983 እስከ 1986 ዓ.ም የአዲስ አበባና የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የጦር አዛዥ፣ ከ1986 እስከ 1993 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሆነው አገልግለዋል። በ1993 ዓ.ም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በኤርትራ ጉዳይና በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ከሰራዊቱ ተሰናብተዋል።
ከጦር አዛዥነታቸው ሲሰናበቱም በ48 ዓመታቸው ከመደበኛ ትምህርት ከተለዩ ከ30ዓመት በኋላ ትምህርታቸውን በመከታተል በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ በመቀጠልም በአሜሪካ በዓለም አቀፍና ህገ መንግስት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡ ወደ አገራቸው በመመለስም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል። የኢንስቲትዩት ኦፍ ፌዴራሊዝም ዳይሬክተር በመሆንም አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላምና ደህንነት ሶስተኛ ዲግሪያቸውን(ፒኤችዲ) እየተማሩ ሲሆን በተለያዩ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች በመፃፍም ይታወቃሉ፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሜጄር ጄኔራል አበበ ጋር ያረግነውን ቆይታ፤እነሆ!
አዲስ ዘመን፡- አሁን በአገሪቱ ላለው ለውጥ መንስዔው ምንድን ነው ይላሉ?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ እንጀምር። አገሪቱ በዓለም ምርጥ ህገ መንግስት ካላቸው አገራት ተርታ ትመደባለች። ይህን መሰረት አድርጋ ወደ ዴሞክራሲ እየተሻገረች ነው። ሽግግሩ ዴሞክራሲና ካፒታሊዝምን አጣምሮ የያዘ ስለሆነ ፈታኝ ነው። በሌሎች አገራት ሁለቱ በየተራ ነው ተግባራዊ የሆኑት። አገሪቱ ሽግግር እያደረገች ነው ሲባል ጠያቂ ህብረተሰብ እየተፈጠረ ነው።
ህገ መንግስቱ ከጸደቀ በኋላ ለሃያ አምስት ዓመት ሰላም አገኘን። ጥሩ የሚባልም ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት መጥቷል። ፖለቲካው ግን ወደ ኋላ ቀረ። ዴሞክራሲ ጠፋ፤ ፓርቲው የጠቅላይነት አባዜ ተጠናወተው። በፓርቲው ብቻ ሳይሆን ከታች እስከ ላይ ህዝብን ከማገልገል ይልቅ በህዝብ የሚገለገል መንግስት ተፈጠረ። የህዝብን መብት የማያውቅ መዋቅር ተፈጠረ። መንግስት በህዝቡ ላይ አመጸ። መንግስት ሲያምጽ በህገ መንግስት ላይ ያሉትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማፈን ጀመረ። ሰላማዊ ሰልፍ ተከለከለ፤ ሚዲያዎች በነጻነት አይዘግቡም፣ ፍትህ ጠፋ፤ በጥቅሉ ህገ መንግስቱን ተጻረሩ። መንግስት ሲያምጽ ህዝቡ በመንግስት ላይ የማመጽ ተፈጥሮአዊ መብት ስላለው ባለፉት ዓመታት ህዝቡ አመጸ። በተለያየ ደረጃ ቢሆንም የህዝቦች ጥያቄ ሆነ። ድንጋይ አልወረወሩም እንጂ፣ መጀመሪያ ይህ ጥያቄ የተነሳው ትግራይ ክልል ነበር። መሬታቸው ሲወሰድ ትክክል አይደለም ሲሉ የነበሩት ታሰሩ፡፡ በትግራይ ክልል ሰልፍ የሚፈቀደው ለኤርትራውያን ብቻ ነበር፤ ሻቢእያን ስለሚቃወሙ። በአጠቃላይ በሁሉም አካባቢ መንግስትና ህዝብ እየተራራቁ፣ አፈናው እየከፋ፣ ህዝብ ወደ አመጽ ገባ።
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ የተፈጠሩ ቀውሶች ምን ያህሉ ወደ መልካም አጋጣሚ ተቀይረዋል?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- በተለያዩ ጊዜያት ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጥበት መንገድ የተለያየ ነው። በ1993 ዓ.ም በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል ለተፈጠረው ችግር የተፈታበት መንገድ ከአሁኑ ይለያል፡፡ አሁን እንደ አገር አቅም ፈጥረናል። ህዝቡ የመብቱ ጠያቂ ሆኗል። በዚያን ጊዜ ‹‹አንጃ›› በማለት በጠላትነት ነበር የምንፈራረጀው። አሁን ቀውሱ የሚፈታበት መንገድ አግላይነትን በመተው ወደ አካታችነት ተቀይሯል፡፡ ማሰር ሳይሆን መፍታት፣ መገናኛ ብዙሃንን ከማፈን ይልቅ ነፃ ማድረግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሰቀሱ በሩ እየተከፈተ ነው። ህገ መንግስቱን በመተግበር ረገድ ችግር ነበር። አሁን ህገ መንግስቱን ተግባራዊ ለማድረግ ፍቅርና አንድነት በማምጣት ጥላቻን በማስወገድ ቀውሱን ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር እየተሰራ ነው። ከ1997 ዓ.ም በኋላ አፋኝ ህጎች ወጥተዋል። የታራሚዎችም አያያዝ ተገቢነት የሌለው ነበር። ከእነዚህ ችግሮች በመነሳት ችግር ቢኖርም አገሪቱ በለውጥ ውስጥ ናት።
በፌዴራል መንግስት ጅምር ቢሆንም ችግሮች ወደ መልካም አጋጣሚ እየተለወጡ ነው። ለአገሪቱ ችግር የሆነውና ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረነው አግላይ ፖለቲካ እየተፈታ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሟላ ሁኔታ እንዳይሳተፉ ይከለክል የነበረውን የመፍታት ጥሩ ጅምር አለ። ይህን በሁሉም ክልሎችና ቀበሌዎች ተግባራዊ ማድረግ ይገባል። በክልሎች ካሉ ገዥ ፓርቲዎች ውጭ የሚነገሩ ሃ፦ሳቦች እንደ ወንጀል መቆጠራቸው መቅረት አለባቸው።
‹‹ትምክህተኛና ጠባብ›› እያሉ ጠላት ከማድረግ ይልቅ የህብረተሰብ አስተሳሰብ ከሆነ ምክንያታዊ ውይይት በማድረግ መፍታት ይገባል። መከላከያ ሰራዊት የኢህአዴግ የመጨረሻ ምሽግ ነው ይላሉ። ይህ ጸረ ህገ መንግስት ነው። ብዝሃ ፓርቲ ስርዓት በምትከተል አገር መከላከያ ሰራዊት የአንድ ፓርቲ የመጨረሻ ምሽግ አይሆንም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሰራዊቱን በሰበሰቡበት ወቅት ‹‹የፓርቲ ተቀጥያዎች አይደላችሁም፡፡ ለሚመጣው መንግስት አገልጋይ ናችሁ›› ብለዋል። ይህ በጣም አስፈላጊ አቅጣጫ ነው። በዚህ ይቀጥላል አይቀጥልም የሚለውን በኋላ የምናየው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፈጠረውን ቀውስ ወደ መልካም አጋጣሚ እየቀሩት ነው። የተጀመረው ለውጥ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች እስከ ቀበሌ መውረድ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነባር ታጋዮችና ባለስልጣናትን ማሰናበታቸውና በአዲስ መተካታቸውን እንዴት አዩት?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- በእኔ እምነት አንዳንዶቹ ከአስር ዓመት፣ ሌሎቹ ከአምስትና ከሁለት ዓመት በፊት መሰናበት የነበረባቸው ናቸው። የእኛ ትውልድ በዘመኑ ብዙ ሰርቷል፤ አሁን ላለው ሁኔታ በአስተሳሰብ ኋላ ቀር በመሆኑ ከዴሞክራሲ ጋር አይሄድም። በተለይም በትጥቅ ትግል ያለፈ ወታደር ነው። በወታደራዊ ስራ ደግሞ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር የለም። በተለይም በብአዴንና በህውሓት ውስጥ ያሉ መሪዎች ይህ አስተሳሰብ የነበራቸው ናቸው። እንደ ትውልድ ይህ ትውልድ ከዴሞክራሲ ጋር የሚሄድ አይደለም። ይህ ትውልድ ደርግን ጥሏል። የተወሰነ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ለውጥ አምጥቷል። የዴሞክራሲ አስተሳሰብ ግን በውስጡ የለም።
በእኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ ሰልፍ እናድርግ ብለን ጓደኞቻችን ካላደረጉ አላደረጋችሁም ብለን እንደበድብ ነበር። ይህን ዓይነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ጠብመንጃ ተጨምሮበት ዴሞክራሲ ሊያመጣ አልቻለም። በመሆኑም የህውሓትና የብአዴን ሰዎች ጠብመንጃቸውን ለመከላከያ ቢያስረክቡም አስተሳሰባቸው ግን ወታደራዊ ነው። በመሆኑም አስተዳደራቸው ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው፤ አካታች አይሆኑም። በዚህ ላይ ከጥቂቶቹ በስተቀር አበዛኛዎቹ አልተማሩም። በድሮ አስተሳሰብ ነው ያሉት።
አገሪቱ በለውጥ ውስጥ በመሆንዋ በድሮ አስተሳሰብ ልትመራ አትችልም። ህዝቡ ስለመብቱ የሚሟገት ነው። ይህን የሚመልስ አመራር ያስፈልገዋል። የ‹‹ለማ›› ቡድን በጎልማሳና በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ የሚገኙና ለመማር ዝግጁ የሆኑ ናቸው። የድሮው ዘመን ከዚህ ጋር መሄድ አይችልም። የድሮው አመራር መወገድ ነበረበት። ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ጀምሬም በዚህ ጉዳይ ላይ ስጽፍ ነበር። በክብር ተሸኝቶ ወጣቱ ኃላፊነቱን ይያዝ። ወጣቱ አይሳሳትም እያልኩ አይደለም፡፡ ስለዴሞክራሲ ከድሮው አመራር የተሻለ ትንሽ እውቅት አለው። የተለያዩ ሃሳቦችን ማስተናገድ ይችላል፡፡ የእኛ ትውልድ የትጥቅ ትግል፤ የአሁኑ ደግሞ የዴሞክራሲ ትውልድ ነው። በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እርምጃ ትክክል ነው።
አዲስ ዘመን፦ በእርስዎ ሃሳብ የማይስማሙና በአዲሱ ትውልድ እምነት የሌላቸው ሰዎች አሉ። እንዲያውም አገርን አደጋ ላይ ይጥላል የሚሉ አሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ ሃሳብ ምንድን ነው?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ሁልጊዜም አንዱ ትውልድ ሌላውን ይንቃል። ለምሳሌ የእኔ ቤተሰብ የእኔን ትውልድ ይንቅ ነበር። አባቶች ስለድሮው ነው የሚያስቡት። ውጣቱ ደግሞ ስለወደፊቱ ነው የሚያስበው። ድሮ ግለሰባዊ ፍላጎት ብዙም አልነበረም። አሁን ስለሀብታም፣ ስለሰላምና ስለሌሎች ነገሮች ነው የሚታሰበው። የዛሬና የትናንት ኢትዮጵያዊነት መለኪያው እንኳ የተለያየ ነው። ድሮ ኢትዮጵያዊነት ነፃነት ነበር። አሁን መለኪያው እድገት ብልጽግ፣ ሀብታም መሆን፣ የዴሞክራሲ መኖርና ሌሎች መለኪያዎች ናቸው። የአሁኑ ትውልድ ለአሁኑ ኢትዮጵያዊነት ከድሮው በጣም የተሻለ ነው። የአሁኑ ትውልድ ስህተት አይፈጽምም ማለት ግን አይደለም። ከስህተቱ እየተማረ ግን ከድሮው ትውልድ የተሻለ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፡- በዶክተር አብይ የሚደረጉ ውሳኔዎች ከመርህ ውጪነው። በዚህ የተነሳም ኢህአዴግ ውስጥ መከፋፈል እንዳለ የሚያነሱ አሉ። የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ኢህአዴግ ቆሟል ወይም ወደ ኋላ እየሄደ ነው። ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን ስፖንሰር አደረገና አወጣው፤ ህገ መንግስቱን ግን ተጻረረ። አሁን ለህልውናው የሚሆን ቦታ የለውም። እራሱን ማደስ ነበረበት። ተሀድሶ፣ ጥልቅ ተሀድሶ አሉ ግን መታደስ አልቻሉም። ነባሮቹ መታደስ ሲያቅታቸው ይህን በማመን ስልጣናቸውን ማስተላለፍ ነበረባቸው። ግን የስልጣን ነገር ሆኖ አልለቀቁም፤ ስለዚህም ወደቁ። ኢህአዴግ የለም። የሌለው ግን እነሱ በመርህ አልባ እንደሚሉት ሳይሆን ህገ መንግስቱን የሚጻረሩ ፓርቲዎች በመሆናቸው ነው።
ኦህዴድ ነባሮቹን አሽቀንጥሮ በመጣል የለማ ቡድን አዲስ አመራር አመጣ። ብአዴንና ህወሓት ባሉበት ይንገዳገዳሉ። ደኢህዴን በመስራት ላይ ያለ ይመስላል። ኢህአዴግ የለም ስንል ጸረ ህገ መንግስት ሆኗል ማለታችን ነው። አራቱም ድርጅቶች ገምግመው ሀጢያት እንዳለባቸው የተናዘዙት ነው። ይህን ሲናዘዙ ግን አልገባቸውም። እንደዚያ ሀጢያተኛ ከሆኑ ሁሉም መቀየር ነበረባቸው። አሁን ህወሓትና ብአዴን ውስጥ በክልሎቻቸው ከእነሱ ሃሳብ ውጪ መናገር አይቻልም። ኦህዴድ ይሻላል፤ ግን ብዙ ይቀራል። ኢህአዴግ እራሱን ያድሳል ወይም ፈርሶ ሌላ ድርጅት ይፈጠራል። ይህ በየትም ዓለም የሚሆን ነው።
ኢህአዴግን አሁን ዶክተር አብይ የያዘው መንገድ ሊለውጠው ይችላል። የሚሆነውም አዲስ ኢህአዴግ ነው። የፓርቲው የምርጫ ስርዓትና ውሳኔ የሚያስተላልፍበት መንገድ የድሮ ነው። ዶክተር አብይ ከበፊቱ በተለየ ወደ ስልጣን ለመምጣት ከምርጫ በፊት ለመመረጥ ሲሰሩ ነበር። ከተመረጡ በኋላም ሰብስበው የሚወስኑት በእሳቸው ስልጣን ስር የሆነውን ስራቸውን መወሰን ጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ መንግስት እንደ መንግስት፣ ፓርቲም እንደ ፓርቲ ሁሉም በተሰጣቸው ኃላፊነት መስራት አለባቸው። ስራ አስፈፃሚዎቹ ስራ ስለሌላቸው እየተሰበሰቡ መወሰን የለባቸውም። የኤርትራ ጉዳይም መወሰን የነበረበት በካቢኔው ነበር። የተወሰነው ግን በስራ አስፈፃሚው ነው። ይህ ጸረ ህገ መንግስት ነው። በህወሓት የሚቀርበው ቅሬታ ብቻቸውን ወሰኑ የሚል ነው። ማን በምን ይወሰናል የሚለው በህገ መንግስቱ የተቀመጠው መታየት አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጣቸው ስልጠና ላይ መወሰን ያለባቸው እሳቸው ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብም የሚጠይቀው እሳቸውን ስለሆነ። ፓርቲው እንዲወሰንለት የሚፈልገው ነገር ካለ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሳመን አለበት።
ፓርቲውና መንግስት መለየት አለበት። ፓርቲው የገመገመው መንግስት እንደገመገመው ይቆጠራል። በፓርቲው የሚያደርገውን ግምገማ የሚጠይቅ አካል አልነበረም። መጠየቅ የተጀመረው አሁን ነው። በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ተፈናቅሎ አመራሮች አልተጠየቁም። ከስብሰባ ወደ ስብሰባ ብቻ ነበር የሚሸጋገሩት። አጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓቱ የተበላሸ ነበር። አብዛኛዎቹ ኃላፊዎች ህገ መንግስቱን፣ የፌዴራል ስርዓቱንና ሰብዓዊ መብትን አያውቁትም። ህገ መንግስቱን ትተው በእራሳቸው ሲመሩ ነበር። በፓርቲው ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ አልነበረም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ማስተካከል ጀምረዋል።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት አገራት ያደረጉትን ጉብኝትና በኤር ትራ ላይ በተደረሰው ውሳኔ ዙሪያ አስተያየ ትዎን ቢገልፁልን?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤትና በመካከ ለኛው ምስራቅ ያደረ ጓቸው ጉብኝቶች ከፍተኛ ውጤት የተገኘባቸው ናቸው። በአጭር ጊዜ ውስጥም ለውጥ መጥቷል። የኢትዮጵያና የኤር ትራ ግንኙነት ግን በዚያ መልክ መሄድ አልነበ ረበትም። የተወሰነ ዝግጅትና ከህዝቡ ጋር ውይይት ያስ ፈልግ ነበር። ችግሩ የተፈጠረው የአልጀርስ ስምምነት ሲፈረም ነው። ይህ ስምምነት መፈረም አልነበረበትም። በእኔ እምነት ይህ ስምምነት ተቀዶ አዲስ ስምምነት መደረግ አለበት። የሚደረገው ስምምነትም የኢትዮጵያን የባህር በርና የህዝብ አሰፋፈር በሚያስጠብቅ መልኩ መካሄድ አለበት።
የአልጀርስ ስምምነት ተወረን ከወራሪ ጋር እኩል አድርጎናል። አሸንፈንም እንደተሸናፊ ነው የሆነው። የኢትዮጵያን መብት ያላስጠበቀና በኤርትራ መንግስት የተጣሰ ነው። በፓርላማው የአልጀርስ ስምምነት ይሁንታ አገኘ እንጂ አልጸደቀም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ለፓርላማው ያቀረቧቸው አምስት ነጥቦች በምክር ቤቱ አልተሰረዘም። ይህ በፓርላማው ሳይነሳ መወሰኑ ትክክል አይደለም። መወሰን ያለበት ምክር ቤቱ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ሁለቱን አገራት ለማቀራረብ የሚሰራው ስራ በጣም ጥሩ ነው። ኤምባሲ እንዲከፈት፣ የአየር በረራ እንዲጀመር መሰራቱ የሚደገፍ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤርትራን ወደ ኢትዮጵያ የቀላቀላት ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት ነው። አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ይዘን የባህር በር የማያረጋግጥ ከሆነ ተገቢነት የለውም።
አዲስ ዘመን ፡- በውጭ አገር ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የቀረበውን ጥሪ እንዴት ይመለከቱታል?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ለቀውስ የዳረገን የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ ነው። ጠንካራዎቹ ተቃዋሚዎች በውጭ አገር ነው ያሉት። የፖለቲካ ምህዳሩ ከዚህ በላይ እንዲሰፋ መሰራት አለበት። እስካሁን የተወሰዱት እርምጃ በጣም ጥሩ ናቸው። ጅምሩን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ነገር ግን የሚወስኑት ውሳኔ ሁሉም ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት። የህዝብ መብት መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ህዝቡን ሲያሰቃዩ የነበሩ ሰዎች መጠየቅ አለባቸው። በጓደኝነት ዝም ተብሎ መኬድ የለበትም። የሚጠየቀው ስላጠፋ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትምህርት መሆን ስላለበት ነው። ተጠያቂነቱም እስከ ወረዳና ቀበሌ መውረድ አለበት። አንዳንዱ ቦታ ላይም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መደመር እየተባለ መቀነስን የሚያመላክቱ ጉዳዮች ስላሉ እሳቸውም አቋም መያዝ አለባቸው። አንዳንዶች እንደ ህወሓት ያሉ ለውጥን የሚቃወሙት በግትርነት ነው። እንደ ብአዴን ያሉት ደግሞ ለውጡ ውስጥ ሆነው ጸረ ለውጥ ሁኔታዎችን በማንሳት ነው። ከዚህ መጠንቀቅ ይገባል። ለውጡ ቢፈለግም ባይፈለግም የግድ ነው።
አዲስ ዘመን ፡-ታራሚዎች በተለቀቁበት መንገድ ዙሪያስ ምን ይላሉ?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ድርጅቶቹ ባደረጉት ግምገማ ፍትህ አልነበረም ብለዋል። ስለዚህ አብዛኛው ሰው አላግባብ ነው የታሰረው ማለት ነው። ከዚህ አኳያ አብዛኛው ሰው መፈታት ነበረበት። እነዚህ ሰዎች ሲፈቱ የተወሰኑ ወንጀለኞች መውጣታቸው አይቀርም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስር ወንጀለኞችን ከማሰር አንድ መቶ ተጠርጣሪዎችን ለቆ ሲጣራ ወንጀለኞቹን ማሰር ይገባል ያሉት ለዚህ ነው። ከፍትህ አኳያ ሲታይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዱት እርምጃ ትክክል ነው። ታራሚዎቹን በመልቀቅ ሂደት ስህተቶች ሊኖሩ ይችላል። አንዳንድ ሰው ለውጡን ለመቃወም ስህተቱን ያጎላዋል። መሆን ያለበት ግን ስህተት ቢኖርም በሂደት ቀስ ብሎ ማረም ይቻላል። በሙስና ያልሆነ ዶክመንት ተቀላቅሎ የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን እኔ አውቃለሁ። በጥቅሉ በሂደት እየታረሙ መሄድ የሚገባቸው ቢኖርም ውሳኔው ትክክል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዷቸውን እርምጃ እንዴት አገኙዋቸው?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ፍትህ አልነበረም ካልን ሰብዓዊ መብት አልተከበረም ማለታችን ነው። እንዳልነበረም እናውቃለን። ይህ እንዳይቀጥል ያጠፉ ሰዎች መጠየቅ አለባቸው። ህብረተሰቡ ገና መብቱን አላወቀም። በህብረተሰቡ ውስጥ ዴሞክራሲያዊነትና የህግ የበላይነት ገና አልዳበረም። የህብረተሰቡ ግንዛቤ አድጎ መብቱን እስከሚያስከብር ድረስ ይህ ነገር ወደፊትም ይገጥመናል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊነታቸውን አልተወጡም። ከዚህ በኋላ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- የምህረት አዋጁን ለማጸደቅ በሂደት ላይ ነው። አሳሪ የተባሉ ህጎችን ለማሻሻልና ወይም ለመሰረዝ የባለሙያዎች ኮሚቴ ተቋቁሟል። በዚህ ዙሪያስ ምን ይላሉ?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- የምህረት አዋጁ መውጣቱ ዘግይቷል ካልሆነ በቀር ተገቢነት ያለው እርምጃ ነው። ታራሚዎች ከመለቀቃቸው በፊት መውጣት ነበረበት። ሌሎቹ ህጎቹም አንዳንዶቹ ሊሻሩና ሊስተካከሉ የሚገባቸው ናቸው። የተቀሩትንም ከህገ መንግስቱ ጋር በማጣጣም ማስተካከል ይገባል። የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ ሆነው መስተካከል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ግጭቶች መንስዔው ምንድን ነው? መፍትሄያቸውስ ?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- አሁን እየተነሱ ያሉ ግጭቶችን ተፈጥሯዊ አድርጌ ነው የማየው። ይህ የማይቀር ነው። ማድረግ የምንችለው መቀነስ ብቻ ነው። የግጭቱ መንስዔ አፈናው ነው። ታፍኖ ሲከፈት እንዲህ አይነት ነገር ይገጥማል። በውይይት እየተፈታ መጥቶ ቢሆን ኖሮ በዚህ ደረጃ አይሆንም ነበር። ለምሳሌ የትግራይ የበላይነት አለ ይባላል። ውይይት አልተደረገም። ውይይት ቢደረግ ችግሩ እንደዚህ አይሆንም ነበር። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያዊነት በሚል ብሄር ብሄረሰብ የሚባለው መታፈን እየተጀመረ ነው። ይህ ትክክል አይደለም።
ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ሲሰፋ ሁሉም እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ ሁኔታ እስኪስተካከል የታፈነው ሲለቀቅ ወደ ግራና ቀኝ ይሄዳል። ማፈን እስካለ ድረስ ይህ ችግር ይቀጥላል፤ ተፈጥሯዊ ነው። ማፈን ሰው እንሰሳ እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው። እንስሳ ሲለቀቅ እንደሚናከሰው ሰውም ነፃ ሲሆን እስከሚሰክን እንደዚያ ነው። አሁን የተጀመረው ጥረት ከቀጠለ እየቀዘቀዘ ይሄዳል። የህግ የበላይነት እየተረጋገጠ ከሄደ ችግሩ ይፈታል። በደቡብ ክልል እንደተወሰደው እርምጃው ከቀጠለ ችግሩ ይፈታል። አሁን የተጀመረው ካልቀጠለ ግን እንደሶሪያ ወደ መፍረስ ነው የምንሄደው።
አዲስ ዘመን፡- ሰላማዊ ሰልፎች ሲካሄዱ በተንጸባረቁት አስተሳሰቦችና በተያዙት ሰንደቅ ዓላማዎች ላይ ያለዎትን ሃሳብ ቢገልፁልን?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ይህ ባይንጸባረቅ ነበር የሚገርመኝ። በአማራ ክልል ህገ መንግስታዊ ያልሆነ፣ በኦሮሚያ የኦነግን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ወጥተዋል። ይህ ማለትም በአሁኑ ሰንደቅ ዓላማ ተጨቁነናል የሚል ህብረተሰብ ተፈጥሯል ማለት ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ ስራውን አልሰራም ማለት ነው።
ጭቆና ካለ ምልክቶቹ ይወጣሉ። በሰላማዊ ሰልፎቹ ሁሉም ቆሻሻ ነገር ወጥቷል። መውጣቱ ጥሩ ነው። የትግራይ ብሄርን መስደብ ይታያል። ይህ እንደመር እየተባለ መቀነስ ነው። ይህም ቢሆን ውይይት ከተካሄደ ችግሩ እየተፈታ ይሄዳል። ጠንካራ የሆነው የአማራና የትግራይ ህዝብ ግንኙነት እየተጠናከረ ይሄዳል። በወሬ እየተጋነነ ችግር እየተፈታ ይሄዳል። ይህ መሆኑ የሚገርም አይደለም። ውይይትና መቀራረብ ሲፈጠር ችግሮቹ እየተፈቱ፤ ትክክል ያልሆኑት እየተስተካከሉ፤ መቻቻል እየተፈጠረ ይሄዳል። ሂደቱ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የሚታዩት ለውጦች በተሻለ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ከማን ምን ይጠበቃል?
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- ሁልጊዜም ህዝቡ ተመልካች ከሆነ ለውጥ አይመጣም። ከሶስት ዓመት በፊት ጀምሮ ህዝብ እምቢ አለ። ህዝቡ እምቢ ማለቱን መቀጠል አለበት። እምቢ ሲል ግን ድንጋይ በመወርወርና ጥይት በመተኮስ መሆን የለበትም። አሁን ያለው ሁኔታ ከቀጠለ ድንጋይ መወርወር፣ ጥይት መተኮስም አያስፈልግም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ህገ መንግስቱን በማክበር የህዝቡን ነፃነት ማክበሩን መቀጠለ አለበት።ምሁራን አገሪቱ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እስከምትደርስ ዝም ማለታቸው በታሪክ የሚያስወቅሳቸው በመሆኑ የተከፈተውን ቀዳዳ ተከትለው መስራት አለባቸው። የሃይማኖት አባቶች መጀመሪያ እራሳቸው ውስጥ ያለውን ጥላቻ በማስቀረት ፍቅርን መስበክ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተጀመረው እስከ ቀበሌ መውረድ አለበት። ትክክል ያልሆነ ስራ ሲሰራ ህዝቡ እምቢ በማለት ህገ መንግስታዊ መብቱን ማስከበር አለበት። ተቋማትም ይህን ማክበር አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ቃለ ምልልስ በጣም አመሰግናለሁ።
ሜጄር ጄኔራል አበበ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አጎናፍር ገዛኸኝ

 

Published in ፖለቲካ

በአንድ ወቅት በጅማና አካባቢው በሚኖሩና በርከት በሚሉ እናቶች ላይ አንድ ጥናት ማካሄድ አስፈላጊ ሆነ። ይህ ጥናት በእናቶች የጡት ወተት ውስጥ ያለውን ይዘት ማወቅና ውጤቱን በህክምና ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነበር። የውጤቱ ምላሽ ግን ጥናቱን ለሚያካሂዱት አካላት ከማስገረም አልፎ አስደንጋጭ የሚባል ሆነ። የእናቶቹ የጡት ወተት የሚያስረዳው «ዲዲቲ» በተባለውና ወባን ለማጥፋት በሚታወቀው የጸረ ተባይ መድሀኒት ጥርቅም የተሞላ መሆኑን ነበር።
ይህም ብቻ አይደለም፤ የመድሀኒቱ ይዘት ሰዎች በሚጠጡት ውሃ ውስጥ ለመገኘት ቅርብ መሆኑ ተረጋገጠ። በአካባቢው በሚበቅለው የጫት ተክል ላይም ጸረ ተባይ መድሀኒቱ መኖሩ ታወቀ። በተመሳሳይ በአንዳንድ ሰዎች ጸጉር ላይ በተደረገው ጥናትም በእያንዳንዱ የጸጉር ቅንጣት ውስጥ የዲዲቲን መድሀኒቲ ጥርቅም በቀላሉ ተገኘ።
«ዲዲቲ» የሚል ስያሜ ያለውና ከዓመታት በፊት ለወባ ትንኝ ማጥፊያ ይውል የነበረው መድሀኒት የአገልግሎት ጊዜውን ካጠናቀቀ ዓመታት መቆጠራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ የፀረ ተባይ ይዘት ያለው የርጭት መድሀኒት ሀገራችንን ጨምሮ በበርካታ ስፍራዎች ገዳይ ናቸው የሚባሉትን የወባ ትንኞች በማጥፋት ባለውለታ እንደነበረም ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ይህ መድሀኒት በሙያው በሰለጠኑና ልምድና ችሎታው ባለቸው አካላት አማካኝነት የወባ ትንኞች ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ እንዲደርስ ይደረግ እንደነበርም ይታወቃል።
መድሀኒቱ ጥቅም ላይ እንዳይውል ከተከለከለ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ የመድሀኒት ይዘትም በየትኛውም ስፍራ ርጭት የማካሄዱ ልማድ ፍጹም የተረሳና የማይሞከር ነው። እውነታው ይህ ይሁን እንጂ ዲዲቲን አሁንም ድረስ የሚፈልጉትና ለዘርፈ ብዙ ግልጋሎት የሚሹት ወገኖች ጥቂቶች አልሆኑም። ዱቄት መሰሉ መድሀኒት ዛሬም ከአርሶ አደሩ ጓዳና ከሰፊው የእርሻ ማሳው መሀል የራቀ አለመሆኑ የብዙዎች ምስጢር አይደለም። በተለይ በጅማና አካባቢው።
በዚህ ስፍራ የሚኖሩ አርሶ አደሮች በጓሯቸው የበቀለው የጫት ተክል ከተለመደው ልምላሜ ጨምሮ ምርታማ እንዲሆንላቸው የመጀመሪያ መፍትሔ ያደረጉት ዲዲቲን መጠቀም ነው። በአካባቢው ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች በየትኛውም ጊዜና ቦታ በህገወጥ መንገድ የሚያገኙትን ይህን መድሀኒት በጋዝ በጥብጠው በጫቱ ቅጠል ላይ ሲያሹት ልምላሜው እንደሚጨምርላቸው ያምናሉ። ይህ ልማዳቸውም ለዓመታት አብሯቸው የዘለቀና እስከአሁንም እንደ አማራጭ የሚጠቀሙበት ሆኗል።
የጥናት ውጤቱ እንደሚጠቁመው አሁንም ድረስ በገጠሩ አካባቢ ዲዲቲን እንደ ጸረ ሰብል መድሀኒት በመቀበል ጥቅም ላይ ማዋሉ የተለመደ ነው። በእነዚህ ስፍራዎች ማንኛውም የእህል ዘር እንደነቀዝ መሰል ተባዮች እንዳይጎዳ በሚልም በዲዲቲ አሽቶና ለውሶ የማስቀመጡ እውነታ አዲስ የሚባል አይደለም። ይህ ለዓመታት እንደባህል የዘለቀው ጉዞ ግን በህብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ስጋት እንዲያንዣብብ አድርጓል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ጤና አጠባበቅ ትምህርት ክፍል የአካባቢ ብክለት ተማራማሪው ተባባሪ ፕሮፌሰር አርጋው አምበሉ እንደሚሉት፤ ደግሞ በዚህ ዓይነቱ የአጠቃቀም ልማድ የሚመጣው ችግር የሰዎችን ጤንንት በእጅጉ የሚጎዳ ሆኖ ተገኝቷል። ዲዲቲ መሰሉን የተባይ ማጥፊያ ለሰው ልጆች ምግብነት ከሚውሉ ግብአቶች ጋር የማዛመዱ ልማድ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሰዎች ጤንነታቸው እንዲታወክና በርካቶች ለብክለት እንዲጋለጡ የሚያደርግ ነው።
‹‹የዲዲቲ ንጥረ ነገር በባህርይው ለረጅም ጊዜ የማይጠፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እየቆየ የሚያስከትለው ጉዳትም ከፍተኛ ነው›› የሚሉት ፕሮፌሰር አርጋው በተለይ በጅማ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ይህን መርዛማ ኬሚካል በህገወጥ መንገድ በማስገባት በሚሸጡ ሰዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ግድ እንደሚል ይናገራሉ።
ፕሮፌሰሩ ከጥናት ውጤቱ በመነሳት በተለይ በእናት ጡት ውተት ውስጥ የተገኘውን የዲዲቲ ክምችትን አደገኝነት እንደምሳሌ ያነሱታል። ‹‹እናት ለልጇ በየጊዜው የምታጠባው የጡት ወተት ከዚህ መርዛማ የኬሚካል ክምችት የጸዳ አለመሆኑ፣ የትውልዱን ጤንነት ከብክለት የሚያርቀው አይሆንም ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ›› የጊዜው ህብረተሰቡ የሚጠቀመው የመጠጥ ውሃና በነቀዝ የማይጠቃው የጤፍ ሰብልም እንዲሁ።
እንደ ፕሮፌሰሩ ዕምነት በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን እየታየ ካለው ተጨባጭ ለውጥ ጋር ተዳምሮ የሚስተዋለው አካባቢያዊ ብክለት አሳሳቢ የሚባል ነው። አብዛኛው የህብረተሰባችን ተለምዶ አካባቢውን ከበከለ በኋላ መልሶ የማፅዳት ዕርምጃው የፈጠነ አለመሆኑ ችግሩ እንዲስፋፋና በርካቶችም ለበርካታ የጤና እክሎች እንዲዳረጉ እያስገደደ ነው።
ይህን አሳሳቢችግር መፍትሔ ለማሰጠት ህብረተሰቡን ጨምሮ ኢንቨስተሩ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍና የፖሊሲ አውጪ አካላት ጉዞ የሚናበብ ሊሆን ይገባል። የአካባቢን ብክለት በአግባቡ ለመቆጣጠር በአንድ ወገን ትከሻ ላይ ብቻ የሚተው ኃላፊነት ያለመሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰር አርጋው እያንዳንዱ ዜጋ ሊያስብበትና እንደግዴታ ሊወጣው የሚገባ ማህበራዊ ድርሻ ስለመሆኑም አጽንኦት ይሰጡታል።
አካባቢን በብክለት ከሚያውኩ ይዘቶች መሀል ከኢንዱስትሪው አካባቢ በስፋት የሚለቀቁ ውጋጆች ዋንኞቹ ናቸው። እንደ ፕላስቲክና መሰል የኢንዱስትሪ ውጤቶችም በቆሻሻ መልክ ሲወገዱ የሚኖራቸው የኬሚካል ውህድ በጤንነት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ ነው። እነዚህን ጎጂ የሚባሉ ንጥረ ነገሮች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ማስወገድ ካልተቻለም ህብረተሰቡን ለብክለትና ጉዳት የመዳረጉ ሂደት በስፋት የሚቀጥል ይሆናል። በሀገራችን ከሚገኙ በርካታ ፋብሪካዎች ተሞክሮ ለማወቅ እንደሚቻለው ድርጅቶቹ ሥራ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ስለፍሳሽ ማስወገጃዎች ትኩረት ያለመስጠታቸው ልማድ ነው።
ፋብሪካዎቹ ወደሥራ ከተሰማሩ በኋላ ውጋጅን ለማስወገድ የሚከተሉት ተገቢ ያልሆነ አካሄድም የአካባቢው ነዋሪ የብክለት ሰለባ እንዲሆንና ስለጤንነቱ አፋጣኝ መፍትሔ እንዳያገኝ ያደርጉታል። የአብዛኞቹ ቆሻሻ ማስወገጃዎች ከቆሻሻው ባህርይ ጋር የማይዛመዱ መሆናቸውም የችግሩን ስፋት የሚያጎሉት ይሆናል። በከተማ ማዘጋጃ ቤቶች አካባቢ የሚስተ ዋለው ቆሻሻን በአግባቡ ያለማስወገድና ተገቢውን ግንዛቤ ያለመስጠት ቸልተኝነትም ለብዙሀኑ ነዋሪ የብክለት ችግር መነሻ እየሆነ ነው።
በአሁኑ ጊዜ በታላላቅ ሀይቆች አካባቢ የዚሁ ስጋት ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው። በእነዚህ ስፍራዎች ለምግብነት የሚፈለጉ ዓሳዎች ሳይቀሩ ሞተው የሚገኙበት ልማድ ተበራክቷል። ይሁን እንጂ ለዚህ አሳሳቢ ጉዳይ በወቅቱ ትኩረት ሰጥተን ችግሩን መታደግ ከሞከርን እያንዣበበ ካለው ስጋት በአግባቡ መከላከል እንደሚቻል ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።
ከቱሪዝም ዕድገትና መስፋፋት ጋር ተያይዞ በአሁኑ ጊዜ በሀይቅ ዳርቻዎች ዙሪያ የሚገነቡ ሆቴሎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። ከግንባታዎቹ ጎን ለጎንም አካባቢዎቹ ዘላቂ በሚባሉ ውጋጆች እየተበከሉ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ይቻላል። ከውስጥ የሚለቀቀውን ቆሻሻ በአግባቡ ተቀብሎ የሚያጣራ ቴክኖሎጂ ያለመኖሩም ውሃው ከተለመደው ቀለም ተቀይሮ ተፈጥሯዊ ያልሆነ አረንጓዴነትን እንዲላበስ ስለማድረጉ ማስተዋል ይቻላል።
ይህም እውነታ በርካታ ሀይቆችን ጨምሮ የሃዋሳ፣ ባህርዳርና ቢሸፍቱ ሀይቆቻችንን እንዳናጣ ስጋት ላይ የሚጥለን ይሆናል። በእንዲህ ዓይነቱ ተሞክሮም ቀደም ሲል በኬንያ ይታወቁ የነበሩ በርካታ ሀይቆች በአያያዝ ጉድለት የተነሳ ሙሉ ለሙሉ ስለመድረቃቸው ፕሮፌሰር አርጋው በምሳሌነት ያነሳሉ።
በሀገሪቱ አብዛኞቹ ከተሞች በየስፍራው የሚጣለው ቆሻሻ መድረሻው እንደ መነሻው አይታወቅም፡፡ በዘፈቀደ በየስፍራው የመወገዱ ልማድም በከፍተኛ ደረጃ አካባቢን ለብክለት እየዳረገ ይገኛል። ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀ የቆሻሻ ማስወገጃ ያለመኖሩም የመንግሥትን ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅ ይሆናል።
የአካባቢ መበከል ውጤት በአሁኑ ጊዜ የዓለማችን ከፍተኛ የጤና ስጋት እየሆነ ለሚገኘው የካንሰር ህመም ጭምር ምክንያት ስለመሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ። ሰዎች ከሚተነፍሱት አየር፣ ከሚመገቡትና ከሚጠጡት ውሃ ጋር ወደሰውነታቸው የሚያስገቡት በካይ ንጥረ ነገር ጤንነታቸውን እያወከው እንደሚገኝም ተረጋግ ጧል። የኩላሊት መድከምና የጉበት መጎዳትን ጨምሮ ከልጅ እስከ አዋቂ የሚጠቁበት የተለያዩ የካንሰር ህመሞች ከዚሁ የአካባቢ ብክለት ጋር የተያያዘ ውጤት እንዳላቸው በጥናት መረጋገጡን ፕሮፌሰር አርጋው ይናገራሉ።
በሀገራችን በአካባቢ ብክለት ላይ ተመስርቶ የተቀረጹ ህጎች ስለ መኖራቸው አይካድም። ይሁን እንጂ እነዚህ ህጎች በተግባር ካልተተረጎሙ አሉ መባላቸው ብቻውን መፍትሔ ሊሆን አይችልም። እንደ ፕሮፌሰር አርጋው ዕምነትም የህግ አስገዳጅነቱ ደካማ የመሆኑ እውነታ በኢንዱስትሪው ዓለም የሚገኙ አንዳንድ ባለሀብቶች በዘፈቀደ እንዲጓዙ ጭምር በር ከፍቷል።
ፕሮፌሰር አምበሉ ደጋግመው አጽንኦት የሚሰጡት ሌላው ጉዳይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማነስ ነው። ህብረተሰቡ ቆሻሻን ከቤቱ ማስወገዱ ብቻ ራሱን መልሶ የሚጎዳው አይመስለውም። ይህ ውጋጅ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ወደውስጣዊ አካል የመድረስ አጋጣሚው ሰፊ የሚባል ነው። ማንኛውም ሰው ቆሻሻ በአግባቡ ያለመወገዱ አጋጣሚ ለመላው ቤተሰቡ ጠንቅ ሊሆን እንደሚችል ሊረዳው ይገባል።
እንደሳቸው እሳቤም ንጹህ የሆነ አካባቢ ምንጊዜም ቢሆን አትራፊ የሚባል ነው። ለቱሪስቶች መስህብ ቢሆንም ምርታማነትን ቢያስፋፋና ለንጹህ መጠጥ ውሃ ማደሪያ መሆን ቢቸል ጠቀሜታው ለሁሉም ይሆናል። ከብክለት የጸዳ አካባቢ መጪውን ትውልድ ጭምር ከአደገኛ የጤና ስጋት ጠብቆ ለማሸጋገር የሚኖረው ፋይዳ ቀላል አይሆንም። ይህን እውን ለማድረግ ግን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነትና ድርሻን በአግባቡ የመወጣት ግዴታ ሊኖር ይገባል።

መልካምስራ አፈወርቅ

Published in ኢኮኖሚ

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከድንበር ጋር ተያይዞ እ አ አ ከ1998 እስከ 2000 የዘለቀው ጦርነት ከ70ሺ በላይ የሁለቱን አገራትን ዜጎች ህይወት ቀጥፏል። ጦርነቱ ቆሞም በሁለቱ ሀገሮች መካከል ላለፉት 17 ዓመታት ሰላምም ጦርነትም ሳይኖር ቆይቷል። በኢትዮጵያ በኩል በተለያየ ጊዜ ችግሩን ለመፍታት ፍላጎቱና ዝግጁነቱ ቢኖርም፣ ችግሩ መፍትሄ ሳያገኝ ሁለት አስርት አመታትን ዘልቋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኤርትራ ጋር ከስምምነት ለመድረስ አስመራ ድርስ ሄደው ለመወያያት ዝግጁ መሆናቸውን ስልጣን በያዙበት ወቅት ቢያረጋግጡም ፣ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምኞት ሳይሳካ እሳቸውን ስልጣኑን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡም የኢትዮ-ኤርትራ ችግርን መፍታት አጀንዳቸው አድርገውታል። በአጭር ጊዜ ውስጥም ለውጥ መምጣት ጀምሯል። የአልጀርሱን ስምምነት ያለቅድመ ሁኔታ በመቀበልም ለኤርትራው ፕሬዚዳንት የሰላም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህ ጥሪያቸውም በፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኩል ተቀባይነት አግኝቶ በቅድሚያ የኤርትራ ልኡካን ቡድን ወደ ኢትዮጽያ በመምጣት በሁለቱ ሀገሮች መካከል አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ መከፈቱን ያበሰረ ጉብኝት አርጎ ወደ ሀገሩ መመለሱ ይታወቃል፡፡
ይህ የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ሰሞኑን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአስመራ ጉብኝት የሰላምና የልማት ስምምነት በማድረግ መቋጫውን አግኝቷል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ይህ ስምምነት የሰሞኑ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አበይት ዜና ሆኗል፡፡
ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል ድረ ገጽ ኢትዮጵያና ኤርትራ በመሪዎች ደረጃ ያደረጉትን የሰላምና የልማት ስምምነት ከረጅም ዓመታት የጠለሸ ግንኙነት በኋላ የተደረገ ታሪካዊ ስምምነት ሲል በአግራሞት ዘግቧል።
በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ የደም መፋሰስ የተከሰተበትን ይህ ጦርነት የአገራቱ መሪዎች መቋጫ አበጁለት ሲል ዋሽንግተን ታይምስም ዘግቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስልጣን በያዙ በመጀመሪያ ወር ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ቃል መግባታቸውን ዘገባው አስታውሶ ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃላቸውን ፈጸሙ ሲል ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስመራ ሲደርሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ወጥተው የተሰማቸውን ደስታ በሲቃ ጭምር ሲገልጹ መታየታቸውን ጠቅሶ፣ይህም የኤርትራውያን የሰላም ፍላጎት ምን ያህል ጠንከራ መሆኑ ለመረዳት አያዳግትም ሲል ገልጿል፡፡ ሁለቱ አገራት በንግድ፣ በትራንስፖርትና በቴሌኮሚኒኬሽን እና በዲፕሎማሲ ያደረጉት ስምምነትም ወዳጅነታቸውን የሚያጠናክር መሆኑንም ዘግቧል።
ኤርትራ ነጻነቷን ለማግኘት የረጅም ጊዜ ጦርነት ማድርጓን ያስታወሰው ዘገባው፣ ከነፃነት በኋላ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ውዝግብ የተነሳው የሁለት ዓመታት ደም አፋሳሽ ጦርነት በሁለቱም አገራት በኩል የበርካታ ዜጎችን ህይወት መቅጠፉን ጠቅሷል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ አገራቱ ጦርነቱን ለማቆም የአልጀርሱን ስምምነት ቢያደርጉም ችግሩ ሊፈታ እንዳልቻለም ዘግቧል፡፡
ዘገባው እንዳመለከተው፤ ባለፈው ሚያዝያ ወር ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፓርቲያቸው ስራ አስፈፃሚ የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመቀበል የአገራቱን ሰላም ለማረጋገጥ ወስኗል። የሰላም ስምምነቱንም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚደግፈው ቢሆንም ፣አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎች ግን “ስምምነቱ መሬታችንና ማህበረሰባችንን ወደ ኤርትራ ቆርሶ የሚወስድ በመሆኑ ዳግም ሊታይ ይገባል” በማለት ሲቃወሙት ታይቷል።
ሁለቱ አገራትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ስምምነቱን ደግፈውታል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ እንደሚገኙና ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማእቀብ እንዲነሳ ጥሪ ማቅረቧን ድረ ገጹ አትቷል፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ በመካከላቸው የነበረውን ግጭት ለማቆም በይፋ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው በተለይ ቀጠናው በዓለም የሚታወቅበትን የአለመረጋጋትና የሰላም ዕጦት ለማስቀረት እንደሚጠቅም የዘገበው ደግሞ የዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ድረገጽ ነው። እንደ ድረ ገጹ ዘገባ ፤ ስምምነቱ በቀይ ባህር በኩል በየመን ላለው የእርስ በእርስ ጦርነትም መፍትሄ ይዞ እንደሚመጣ አመላክቷል።
ኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች የጦርነት ጊዜ አብቅቶ የሰላምና ወዳጅነት አዲስ ምዕራፍ መጀመራቸው በቀጣናው የሚታየውን የጦርነት ስጋት ለማስወገድ እንደሚጠቅምም አስታውቋል። ይህንን ተከትሎ ግብጽ የአገራቱ ስምምነት እንደምትደግፍና መልካም እርምጃም መሆኑን ገልጻለች፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስመራ ድረስ በመሄድ ከፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የአገራቱን ደህንነትና መረጋጋት የሚያረጋግጥ አዲስ የሰላምና የወዳጅነት ምዕራፍ መጀመራቸውን የገለጹት የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአፍሪካ በጦርነት ለሚታመሱ ለሁሉም አገራት አርአያ እንደሚሆንም አንስተዋል። አገራቸው ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ያላት ግንኙነት የበለጠ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ፤ኢትዮጵያና ኤርትራ በአገራቱ መካከል ለሃያ ዓመታት የቆየውን ጥላቻና ጦርነት በፍቅርና ወዳጅነት መቀየራቸው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን ትብብርና መረጋጋት የሚያጠናክር ታሪካዊና ቆራጥነት የተሞላበት ለውጥ ነው ብሎታል፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ ዘላቂ ወዳጅነት ይመሰርቱ ይሆን በሚለው የአልጀዚራ ዘገባ ደግሞ አገራቱ በመሪዎች ደረጃ የተደረገው ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ በታሪክ ማህደር ሊሰነድ የሚገባ የመጀመሪያ ክስተት ነው ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአስመራ ያደረጉትን ጉብኝትም ታሪካዊ ብሎታል፡፡
አገራቱ መራራ ጦርነትን ያሳለፉበትና የሃያ ዓመታት የድንበር ግጭትን ዶክተር አብይ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ከኤርትራ ጋር ሰላም ለመመስረት ያደረጉት ጥረት በኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተቀባይነት አግኝቶ ፍሬያማ መሆኑን ያብራራል።
የሮይተርስ ድረ ገጽ በበኩሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ መዲና አስመራ በረራውን እንደሚጀምር አስታውቆ የአየር መንገዱ በረራ መጀመር የአገራቱን መልካም ግንኙነት ያጠናከራል፤ የቀጠናውን ሰላም ለማረጋገጥ ከፍተኛ አሰተዋጾ ይኖረዋል። አየር መንገዱ በቢ787 አውሮፕላን ከሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በረራ እንደሚጀምር የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ተናግረዋል።
የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት ለአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም መላው አፍሪካ የተስፋ ብርሃን ነው ያሉት የሩሲያው ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ አገራቱ በወሰዱት መልካም የሰላም እርምጃ የበረራና የስልክ ግንኙነታቸውን ለመጀመር መዘጋጀታቸው ለሁለት አስርት ዓመታት የነበራቸውን ጥላቻና ጦርነት ማስቀረት የሚያስችል ተምሳሌት ነው ብለዋል።
በሁለቱም አገራት መካከል የነበረው አለመስማማት ቀጣናው የተቃውሞ ማእከል አድርጎ አቆይቶታል። ኢትዮጵያና የሶማሊያ መንግስት ኤርትራ አሸባሪውን ቡድን ትደግፍ ነበር ሲልም ቢቢሲ ዘግቧል።
የሰላም ስምምነቱ ዋንጫ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንደሚገባ የገለጸው ዘገባው ወደ መሪነት ከመጡ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ፣ ፖለቲካዊ እስረኞች እንዲለቀቁ እንዲሁም በመንግስት እጅ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች በከፊልና በሙሉ ለግል ባለሃብቶች እንዲዘዋወሩ ማድረጋቸውንና ለሃያ ዓመታት የዘለቀውን የአገራቱን ግጭት ወደ ሰላምና ወዳጅነት እንዲሻገር ማድረጋቸውን ያትታል።

በሪሁ ፍትዊ

Published in ዓለም አቀፍ
Wednesday, 11 July 2018 16:44

ውኃና ዘይት

ሰውዬው እጅግ በጣም ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ስጋ ወዳድ የሚሉት ዓይነት ነው። መውደድ ቢባልስ እንዲህ በቀላሉ ነው እንዴ? ከቁርጥ ከጥብሱ፣ ከቅቅል ከዝልዝሉ ያለ እንደሆን አያያዝና አጎራረሱን ያውቅበታል። ቢላዋውም ቢሆን በእሱ እጅ ሲሆን ውበት አለው። አዋዜውን ከሚጥሚጣው፣ ሰናፍጩን ከአረቄው አዋህዶ ግባ በሞቴ ባለ ጊዜ ተመልካቹን ሁሉ ያስጎመጃል። እናንተዬ እውነት እላችኋለሁ፣ አሁን እንኳን አቆራረጡና አያያዙ ትውስ ሲለኝ አፌ በምራቅ ይሞላል። እውነቴን እኮ ነው! አይ እኔ...?
ወዳጆቼ! ሰውዬው እኮ የስጋ ዓይነቶችን ለይቶ የሚያውቃቸው ልክ እንደዘር ማንዘሩ ነው። ሽንጡን ከታላቅ ታናሹ፣ ጎድኑን ከፍሪምባው ጮማውን ከቀዩ እያለም ሌሎችን ለመለየት ጠያቂ አያሻውም። ለእሱ ልዩ የሚባሉት እነዚህ ምርጦቹ ከእጁ በገቡ ጊዜ ታዲያ ለወሬ ጊዜ የለውም። በዚህ ሰዓት ሞቅ ያለ ሰላምታና በዓይን ሰው ፍለጋ የሚባል አይኖርም። የአምሮቱን ለመወጣት አንዴ ካቀረቀረ ልክ እንደ ሰዓት ሰሪ ነው። ሌሎችን ይመለከታል ማለት ዘበት ይሆናል።
የሚገርመው ይህ ሰው ድንገት ስጋ ካማረውና በዓይኑ ውል ካለበት ከየትም አምጥቶ ቢሆን የአምሮቱን ማድረሱ ግድ ይለዋል። ይህ ካልሆነ ግን ውሎው ሁሉ ተረብሾ፣ ዕንቅልፍና ሰላም ይነሳዋል። ልማዱ እንደቀረበት ሱሰኛም ሲያዛጋና ሲያማርር ይውላል። ደግነቱ እንደ አንበሳ በየቀኑ ስጋ አያምረውም። ለእሱ እንደው ደርሶ አምጣ፣ አምጣ የሚለው የተለየ ጊዜ አለ። የዚያኔ ታዲያ በስጋ ቤቶች ጎርደድ ብሎ ከአንዱ ጎራ ማለት ብቻ ነው። በቃ!
አንዳንዴ ደግሞ ስጋ በልኩ ባማረው ጊዜ ጥቂት ጓደኞቹን አስተባብሮ ወደለመደበት ስፍራ ጎራ ይላል። የዚያኔ ጨዋታ በጋራ፤ ሂሳብ በግል ስለሚሆን የትኛውን ላስቀድም የቱስ ይቅርብኝ? ሲል አይጨነቅም። ባልንጀሮቹ ያዘዙትን ተጋርቶ ብስሉን ከጥሬ ማለት ይችልበታል። ችግር የሚሆነው ግን ኪሱ በሳሳበት ወቅት ልማዱ ውል ካለበት ነው።
እንዲህ በሆነ ጊዜ ይህን ሰው አለማየት ይሻላል። የኪሱ አቅም ከፍላጎቱ አይደራረስምና ጭንቅ፣ ጥብብ ይለዋል። በስጋ ቤቶች ማለፍና አሻግሮ ማየት ጭምር ያሳቅቀዋል። በደህና ቀን ያስለመደው ሰፊ ሆዱን እያማረረም ራሱን ደጋግሞ ይረግማል። ይህ ስሜቱ ያለመፍትሄ ቀናትን ከተሻገረ ደግሞ ከህመም ባልተናነሰ ችግር ውስጥ ሊወድቅ ይችላል። የጾም ወቅት ሆኖ በርካታ ስጋ ቤቶች በሚዘጉበት ጊዜ ደግሞ ራሱን በራሱ ሸንግሎ ነገሮችን ለመርሳት ይሞክራል። በዚያን ወቅት ለዓይኑና ለሆዱ የሚፈትነው ብዙ እይታ አይኖርምና እንደምንም ለመቻል የሚያደርገው ሙከራ ሊሳካለት ይችላል።
እነዚህ የጾም ወራት ሊጠናቀቁ ጊዜያት ሲቀራቸው ግን አንድ ሁለት እያለ ቀሪዎቹን ቀናት በጣቱ ያሰላል። እንዲህ ሲሆን ደግሞ ባዶ የከረመው ሆዱ በጨኸት ይተራመሳል፣ አፉ በምራቅ ተሞልቶም ገጽታው በወዝ ይፈካል። ተናፋቂው ቀን ሲጠባለት ያለፋቸውን ጊዜያት እያሰበ ከስጋው መንደር ይከራርማል። አዕምሮውን በደስታ ያረካል።
በዚህ ሰው የሕይወት ልምድ ለነገ ብሎ ገንዘብ መያዝ፣ ለቁም ነገር ሲባልም ዕቁብና ቁጠባ መግባት የሚባል ጉዳይ አይታወቅም። ዛሬን ብቻ መኖር፣ አሁንን ብቻ በልቶ ጠጥቶ መደሰት እንጂ ስለነገ ጭንቅ፣ ጥብብ ማለትን አይሞክረውም። ስለነገ አስበው ስለ ተነገወዲያም ጭምር የሚጨነቁ ሲያጋጥሙት ደግሞ ይገረማል፤ ይናደዳልም። ለምን? ካሉትም የሚመልሰው አያጣም። ይህን ጉዳይ ለማብራራት የሚመዛቸው አሳማኝ ምሳሌዎችና ጥቅሶች የበረከቱ ይሆናሉ።
ወዳጆቼ ይህ ሰው ዛሬ እንደ ትናንቱ አይደለም። እንዲያ የሚወደው ሆዱ እጅግ ከሚወደው የስጋ አምሮት ሊራራቅ ፈተና ላይ ወድቋል። ከሆዱ ሌላ ዘመድ የለውም የሚባልለት ጎልማሳ አሁን በትዳር ተይዞ ከጎጆው ታድሟል። የእኔ ብቻ የሚለው የለምና ያለውን ለሌሎች ሊያካፍል ግድ ብሎታል። አሁን ስጋ የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ሲካፈል ብቻ ነው። በሕይወት መንገዱ ለነገ ይሉትን ቁምነገር እንደነውር ሲቆጥር ነበርና ድንገት ልማዱ ውል ሲልበት ሮጦ የሚሄድበት አቅም አይኖረውም።
አንዳንዴ ታዲያ ይህ መጠን ያለፈው ስጋ ወዳድነቱ ሲፈታተነው አንዳንዶች የሚሉትን አማራጭ ያስብና ለመሞከር ይዳዳዋል። ጉዳዩን መለስ ብሎ ሲያጤነው ግን የሚባለው ሁሉ ቀልድ መሆኑ ይገባዋል። ይህኔ ከልቡ ይናደዳል። መላና መፍትሄ ነው ብለው ያመጡት መለኞችንም በሃሳቡ እየፈለገ ከልቡ ይረግማቸዋል።
ወዳጆቼ! ይህን የሰው አንበሳ ምን እንዳበሳጨው ታውቃላችሁ? ንፍሮና አሹቅ፣ ቆሎና ቅቅል የሚሆነው ባቄላ እንደዋዛ ቦታ አግኝቶ ስጋን ይተካል መባሉ እኮ ነው። አጅሬ ታዲያ ይህን በሰማ ጊዜ የተባለውን በቀላሉ ያመነ እንዳይመስላችሁ። እውነት ግን ለእሱ ይህን እንዴት መቀበል ይቻለዋል? አንዴ በሚዛን ሌላ ጊዜ ደግሞ በሰሀንና በጣሳ እየተሰፈረ የትም የሚሸጠው ባቄላ እንዴት ሆኖ ነው ያን ብርንዶ ሊተካለት የሚችለው? በየትኛው መስፈርትስ ነው? ጮማውን ከጥሬ፣ ታናሹን ከታላቁ ሲያገላብጥ የኖረ ሰው ባቄላ ስጋን ይተካል ሲሉት የሚቀበለው?
አያ ሆዬ! ይህን ደጋግመው እየነገሩ ሊያሳምኑት የሞከሩ ባልንጀሮቹን ጠምዶ ከያዛቸው ሰንብቷል። የእነሱን በምሳሌ ማስረዳትና ስጋን ባቄላ ይተካዋል ብሎ ምክር በአምሮቱ እንደመቀለድም ወስዶታል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ በጽኑ ፍላጎቱ እያፌዙ እንደሆነ ገምቶ ድርጊታቸውን ከንቀትና ከስድብ ቆጥሯል። እነሱ ባቄላን ከስጋ ሚዛን አስቀምጠው አሹቁን እንደጥብስ እያሰቡ፣ የንፍሮ ውሃ እንደ በግ መረቅ ነው ሲሉት ለምን አይናደድ?
ትናንት እንፋሎቱ እያወደው፣ ሽታው ቅመሙ እየናፈቀው ያቀላጠፈው ቅቅል፣ ቀድሞ በስል ቢላዋው እየመተረ በአዋዜ በሰናፍጩ የሰለቀጠው ጥሬ ስጋ፣ እንደምን ብሎ ነው በጥሬ ባቄላ ሊተካ የሚችለው? ወይ ጉድ እናንተዬ! ጉዳዩ እውነትነት ቢኖረው እንኳን ለእሱ መሰል ስጋ አፍቃሪ ማሳመኑ ቀላል አይሆንም። ውስጠት ሌላ ውጤት ሌላ!
አንዳንዴ ወዳጃችን ከዚህ ምሬቱ መለስ ብሎ ከስጋ ናፍቆቱ ሊርቅ ሲሞክር ይህን ልክ ያጣ ፍላጎቱን ገደብ ሊያበጅለት ይወስናል። ግን እንዳሰበው ሆኖ ሃሳቡ በቀላሉ አይሰበሰብም። ድንገት ቀድሞ በሚያውቃቸው የስጋ ደንበኞቹ ደጃፍ እግሩ በጣለው ጊዜም ትናንትን በትዝታ እያሰበ በቀድሞው ማንነቱ ራሱን ሊሸነግል ይሞክራል።
አሁን ድግስና በአላት ካልሆኑ በቀር ከስጋ ጋር በጽኑ መፈላለግን እርም ካለ ቆይቷል። ዛሬም ግን ባቄላ ስጋን ይተካዋል ይሉትን ምሳሌ ፈጽሞ አያምንበትም። ሁሌም ቢሆን ባቄላን ከተወዳጁ ስጋ ጋር በፍጹም አያወዳድረውም። ለእሱ ይህ እውነት ልክ እንደዘይትና ውሃ ነው። መቼውንም ወደውስጡ የማይዘልቅ፣ ከስሜቱ የማይዋሀድ እንቆቅልሽ። ሁሌም ላይና ታች ሆኖ የሚንሳፈፍ እርስ በርሱ የማይስማማ ውሃና ዘይት።

መልካምሥራ አፈወርቅ

«በለሷን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል»
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጋር ከአሥመራ ወጣ ብሎ በሚገኝ «ድርፎ» በተሰኘ ሥፍራ ተዝናንተዋል። ሁለቱ መሪዎች በእራት ግብዣ ላይ አብሮ ለመሥራት መስማማታቸውን፣ አዲስ የወዳጅነት ምዕራፍ መከፈቱን የሚያበስሩ ንግግሮችን አሰምተዋል። ታዳሚውም በተደጋጋሚ የሁለቱን መሪዎች ንግግሮችን በጭብጨባ ሲያጅብ ነበር። በድርፎ አፋፍ በተገናኙበት አጋጣሚ ፍሬን ሲያጣጥሙ ታይተዋል።ከበለሱ ፍሬ ጣዕም በላይ አሻግሮ ለተመለከተው ደግሞ፤ትናንት በቁርሾና በጥላቻ ተዘግቶ የነበረው የጥላቻ መጋረጃ መቀደዱን የሚያስረዳ ነው።ይህም የጽናትና የትግስትን ቆይታ በእጅጉ ያመላክታል።ታዲያ ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ« በለሷን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል» የሚለውን መልካም ምሳሌ እንድናስታውስ ያደርገናል።

የሳምንቱ ፎቶ

 

Published in መዝናኛ

የመደመር ዕሳቤን ይዞ አዲስ ምዕራፍ የገለፀው የለውጥ ጉዞ እንደተጋጋለ ቀጥሏል፡፡ ጊዜውም ተፈጥሮአዊ ዑደቱን ጠብቆ እየተጓዘ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ፋና ወጊ ሊባል በሚችል ደረጃ የአገሪቱ ርዕሰ መንግስት ለተተኪው ሥልጣንን በሠላማዊ መንገድ ያስረከበበት ሂደት ታይቷል፡፡ ለቀደመው መሪ ክብርና ምስጋና የተሞላው ደማቅ ሽኝትም ተደርጓል፡፡ ለብዙዎች ምሳሌ የሆነው የሥልጣን ሽግግር ተከናውኖ አንድ ሁለት…እያለ የቀጠለው ጉዞ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ የመቶ ቀናት ሻማውን ለኩሷል፡፡
ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መንበረ ሥልጣኑን የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሠላም ለማረጋገጥ ህዝቡ በአንድነት እንዲቆም ያደረጉት ጥረት ፍሬ አፍርቷል፡፡ ኃላፊነቱን እንደተረከቡ ሠላምን ማረጋገጥ ቀዳሚው ሥራቸው በማድረግ ከህዝቡ ጋር በመምከራቸውና በመወያየታቸው ደፍርሶ የነበረው የሠላም አየር ሊጠራ ችሏል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተዘጋጁት ህዝባዊ የምክክር መድረኮች የመደመር ዕሳቤውን ለፍሬ አብቅተዋል፡፡ ህዝቡ ለሠላሙ ዘብ ለመቆም ቁርጠኝነቱን በተለያዩ መንገዶች አሳይቷል፡፡ የመደመር ጥረቱ ብዙ ማገዶ ሳይፈጅ በህዝቡ ዘንድ አንድነትን የተላበሰ መነሳሳት ፈጥሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ለኤርትራ መንግስት ‹‹የጥሉ ግድግዳ ይፍረስ›› ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ለ18 ዓመታት እንደ ጠላት በሚተያዩት ኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሠላም እንዲወርድ ቁርጠኝነትን የተላበሰ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ መድረኮች የኤርትራ መንግስት የሠላም ጥሪውን እንዲቀበል ከማሳሰብ አልቦዘኑም፡፡ ጥረቱም ታዲያ ፍሬ አልባ አልሆነም፡፡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት የሠላም ጥሪውን በመቀበል ልዑካኑን ወደ አዲስ አበባ ልከዋል፡፡ ይህ ደግሞ በደም ለተሳሰሩት ኢትጵያውያንን ኤርትራውያን ትልቅ የምስራች ነበር፡፡ በአንድነት ተጉዘው በመካከል ከመለያየት አልፈው በጠላትነት እስከመፈራረጅ የደረሱት አገራት የሠላም ሂደቱን መጀመራቸው በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም ትልቅ ቦታ አሰጥቷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሠላም ወዳድነት ጥረት አንፀባርቋል፡፡
ባለፈው እሁድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኤርትራ በማምራት ከኤርትራው አቻቸው ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተዋል፡፡ እጅግ ደማቅ አቀባበል በተደረገበት ጉብኝት ሁለቱን አገራት የሚለየው ግንብ በድልድይ ተተክቷል፡፡ የኤርትራውያን ከፍተኛ ደስታ በተንፀባረቀበት ጉብኝት የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት በተግባር ዕውን መሆኑ በተለያዩ ስምምነቶች ተበስሯል፡፡ የአገራቱ ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩ በአገራቱ መሪዎች በይፋ ታውጇል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤትና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጅቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳ ፣በግብፅ፣በሶማሊያ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባደረጉት ጉብኝት በርካታ ትሩፋቶች ተገኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተጋረጡባት በርካታ ችግሮች ተላቃ በጋራ ጥቅም ላይ ወደ ተመሠረተ ብልጽግና ለመሸጋገር ጽኑ አቋም እንዳላት ለዓለም አሳይታበታለች፡፡ ለቀጣናው ሠላም መስፈንና የምጣኔ ሀብት ትስስር መጎልበት ያላትን ቁርጠኝነት አንፀባርቃለች፡፡ ከአገራቱ ጋር የመተማመን መንፈስ ለመፍጠር ረድቷታል፡፡ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብርን በተሻለ ደረጃ ለማስቀጠል የሚረዳ መሰረት ለመጣል ረድቷል፡፡
ከ90 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ወጭና ገቢ ንግድን ከምታስተናግደው ጅቡቲ ጋር ወደብን በጋራ ለማልማት የተደረሰው ስምምነት የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ ፖርት ሱዳንን በጋራ ከማልማት በተጨማሪ ሱዳንና ኢትዮጵያን በባቡር መሰረት ልማት ለማስተሳሰርም ከስምምነት ተደርሷል፡፡ በኬንያና በሌሎች አገራትም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገው ውይይትና ስምምነት የዲፕሎማሲው ጥረት ውጤት ነው፡፡ በየአገራቱ መካከል ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚረዱ ተግባራትን ለማከናወን ቁርጠኛ አቋም ተይዟል፡፡
በዲፕሎማሲ ጉዞው ከአገራቱ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በሚረዱ ጉዳዮች ዙርያ በመምከር የተለያዩ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ተፈራርመዋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በየአገራቱ በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው መሬት ለማብቃት ረድቷል፡፡ በዚህ በኩል የተገኘው ውጤት ከየትኛውም በላይ አመርቂና ያልተጠበቀ ነበር፡፡ እርምጃው መንግስት ለዜጎቹ ያለውን ተቆርቋሪነትና አሳቢነት በተጨባጭ ያሳየ ሆኖ አልፏል፡፡ በሳዑዲ አረቢያ ለ13 ዓመታት ያህል የአልጋ ቁራኛ የነበረው ብላቴና ተገቢውን ካሳ አግኝቶ በቤተሰቡ ፍቃድ ወደ አገሩ ተመልሶ ህክምናውን እንዲከታተል መደረጉም ሌላው ሰብአዊነትን ያስቀደመው ጉብኝት ውጤት ነው፡፡ በየአገራቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መብታቸው እንዲከበር ጠንካራ መግባባትና መተማመን ተፈጥሯል፡፡
የለውጥ ጉዞው በስኬት እንዲታጀብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለካቢኔ አባላትና ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ለመከላከያ ጄኔራሎችና ከፍተኛ አመራሮችም ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህሉ እንዲጠናክር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያለመታከት አሳስበዋል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚረዱ እርምጃዎችም ተወስደዋል፡፡ ለዚህም የትጥቅ ትግልን አማራጭ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሠላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ተዘግተው የነበሩ መገናኛ ብዙኃንና ጦማርያንም ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲያንሸራሽሩ ተፈቅዷል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሲባል መንግስት ልቡን ለይቅርታ ክፍት አድርጓል፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ወንጀሎች የተከሰሱና የተፈረደባቸው ፖለቲከኞች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የተለያዩ ሰዎች የይቅርታ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ከእስር ተለቀዋል፤ እየተለቀቁም ይገኛል፡፡ የይቅርታው ልብ በዚህ ብቻ የሚቆም አልሆነም፡፡ በመከላከያ ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩና በተለያየ ምክንያት ማዕረጋቸው ተገፎ የነበሩ አባላት ሙሉ ማዕረጋቸው ተመልሶ በክብር በጡረታ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡ በመከላከያና በደህንነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ከፍተኛ አመራሮችን በክብር ሸኝቶ በአዲስ አመራር የመተካት ሥራም ተከናውኗል፡፡ በመንግስት ተቋማት ውስጥም የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የሚረዱ ማሻሻያዎች (ሪፎርም) እየተደረጉ ነው፡፡
የይቅርታና የመቻቻልን አስፈላጊነት በአፅንዖት የሚናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተኮራረፉ አካላትም ዕርቀ ሠላም እንዲያወርዱ ከማሳሰብና ከማወያየት አላረፉም፡፡ ‹‹የውጭውና የአገር ውስጥ›› በሚል ለበርካታ ዓመታት ተራርቀው የቆዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሶች ሠላም እንዲያወርዱ ጥረቱን ገፍተውበታል፡፡ በተያዘው ሐምሌ ወር በአሜሪካ በሚያደርጉት ጉብኝትም አንዱ አጀንዳ ይሄው ጉዳይ ነው፡፡ ሲኖዶሶቹ ችግሮቻቸውን በውይይት በመፍታት ወደ አንድ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአወልያ ትምህርት ቤት አስተዳደርን መነሻው በማድረግ በሙስሊሞች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እንዲፈታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመለከታቸውን አካላት በተናጠልና በአንድነት አወያይተዋል፡፡ በመሆኑም በሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴና በኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ፅህፈት ቤት መካከል የቆየው አለመግባባት እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፡፡
የመደመሩ የለውጥ ጉዞው በጥበብ ሲታገዝ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅኑ እምነት አላቸው፡፡ ጥበብ ኃያል ነው፡፡ በጥበብ ችግር ይፈታል፤ መፍትሔ ይቀመጣል፤ ትምህርት ይተላለፋል፡፡ ጥበብ የሚፈለገውን መልዕክት ማራኪና ሳቢ በሆነ መንገድና ቋንቋ ስለሚቀርብ የበርካቶችን ቀልብ የመሳብ አቅም አለው፡፡ በበርካቶች የሚወደደውን መንገድ በመጠቀም የሠላም፣ የልማትና የአንድነት ጉዞውን የሚያጠናክሩ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ከተቻለ የተራራ ያህል የከበደውን ችግር ማቃለል ይቻላል፡፡ ስለሆነም በተለያዩ ዘርፎች ለተሰማሩ አርቲስቶች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሰርተዋል፡፡ አርቲስቶቹ የያዙትን ትልቅ መሳርያ በመጠቀም ለህዝባቸውና አገራቸው የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፤ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን ለማብረድና ዳግም እንዳይነሱ የተሄደበት ጎዳናም በመልካም ውጤት ታጅቧል፡፡ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተፈጠረውን ግጭትና ሁከት ለማብረድና ለማስወገድ ከህዝቡ ጋር ያደረጉት ውይይትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ግጭቱን ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ኃላፊነቱን ለአካባቢው ሽማግሌዎችና ወጣቶች በማስረከብ የተደረገው ጥረት ፍሬ አፍርቷል፡፡ ወጣቶችም ላጠፉት ጥፋት የአካባቢውን ማህበረሰብ ይቅርታ በመጠየቅ በአኩሪ አገራዊ ዕሴት ለሠላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይተዋል፡፡
ወጣቶች ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር በማዘመን በዕውቀትና ክህሎት በልፅገው አቅማቸውን አዳብረው የሚፈልጉት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የልህቀት አስተሳሰቦችና የሥራ ፈጠራ ዕሳቤዎችን ተንትነው አስረድተዋል፡፡ በተለይም በሚሊኒየም አዳራሽ ከ25ሺ በላይ ወጣቶች በተሳተፉበት የልህቀት ማስረፅ መድረክ ላይ ወጣቶች በወሳኙ የሥራ ዕድሜያቸው በቁርጠኝነት ከተንቀሳቀሱ ያሰቡትን ከዳር ለማድረስ ምንም እንደማያግዳቸው በምሳሌዎች በማስደገፍ አስረድተዋል፡፡ የለውጡ ዋናው ሞተር ወጣቱ ኃይል መሆኑን በአፅንዖት አሳስበዋል፡፡ ከየዩኒቨርሲቲዎቹ በከፍተኛ ውጤት ለሚመረቁ ወጣቶች በመንግስት የውጭ የትምህርት ዕድል እንደሚመቻች ቃል ተግብቷል፡፡
ሁሉም የለውጡ ተዋናይና ተጠቃሚ ነውና ከባለሀብቶችና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋርም ውይይት ተደርጓል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን ለህዝብ በማቅረብ ለህዝባቸውና ለአገራቸው ልማትና ዕድገት እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎችም ለአገራቸው ልማት እንዲተጉ በተደጋጋሚ መልዕክት ተላልፏል፡፡ በተያዘው ወርም በአሜሪካ ከሚገኙ ዳያስፖራዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡
ሠላምን ለማደፍረስና አንድነትን ለማላላት የሚጥሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጥብቅ መልዕክት በተደጋጋሚ ቀርቧል፡፡ በየደረጃው የሚገኝ አመራርም የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ጎትጉተዋል፡፡ ኃላፊነቱን ያልተወጣውም በራሱ ጊዜ ሥልጣኑን እንዲለቅ አማራጭ ቀርቦለታል፡፡ በዚህም ኃላፊነታቸውን የለቀቁ አመራሮችን ለማየት ተችሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና መንግስታቸው እያስመዘገቡት ያለውን ውጤት በማድነቅም ህዝቡ አድናቆቱን ችሯል፡፡ በተናጠል ከሚገለፀው በተጨማሪ ህዝቡ‹‹ ለውጥን እንደግፍ፤ ዲሞክራሲን እናበርታ›› በሚል መሪ ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማመስገን የድጋፍ ሠልፍ አድርጓል፡፡ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተጀመረው ሠልፍ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችም ተካሂዷል፡፡ በዚህም ከመንግስት ጎን በመቆም የሚጠበቅበትን ለመወጣት ቃል ገብቷል፡፡ ህዝቡ ሠላም እንዲረጋገጥ፣ ልማቱ እንዲፋጠን፣ ዲሞክራሲ እንዲጎለብትና አንድነቱ እንዲጠናከር በሠላማዊ ሰልፍ ያሳየው ቁርጠኝነትም በመንግስት ‹‹ምስጋና ይገባሃል›› ተብሏል፡፡ በሠላማዊ ሠልፍ ያሳየውን ድጋፍ በሥራ እንዲለውጠውም ጥሪ ቀርቦለታል፤ የአደራ መልዕክትም ተላልፎለታል፡፡
የአገራችን የዓመታት ችግሮች የሚቀረፉትና ወደተሻለ ደረጃ የሚሸጋገሩት በቀና መንፈስ የለውጥ ኃይል ሆኖ መስራትና መደመር ብቻ ሲቻል ነው። የሁሉም ችግሮች መፍትሄ ከአንድ አካል ብቻ እንደማይገኝ እሙን ነው፡፡ ለለውጥ ከተተጋ በ100 ቀናት እልፍ ሥራዎችን ማከናወን፤ ረጅም ርቀት መጓዝ እንደሚቻል ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የዜጎች ኑሮ ተለውጦ የአገር ዕድገትና ብልጽግና የሚመጣው ኢትዮጵያውያን ክንዳቸውን አስተባብረው በአንድነት ተደምረው ሲተጉ ነው፡፡ በ100 ቀናት እርምጃ ይህን ያህል መጓዝ ከተቻለ በዓመታት ብዙ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ታዲያ የጉዞው ፍጥነት ሊጨምር እንጂ ሊቀንስ አይገባውም፡፡
_

ሠላም ዘአማን

Published in አጀንዳ

በሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ወደ ሥልጣን በመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ኃላፊነቱን ከተረከበ 100 ቀናትን አስቆጥሯል፡፡ በሩብ ዓመት ጉዞ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
በተለይም ሠላምን ለማረጋገጥ፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር በተከናወኑት ተግባራት የታዩት ለውጦች ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶች ተወግደው አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት በመፈጠሩ ችግሩን ለማረጋጋት ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቷል፡፡
ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የለውጥ ጉዞውን በይቅርታና በመቻቻል ለማስጓዝ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወሰነው መሰረት በተለያዩ ወንጀሎች የተከሰሱና የተፈረደባቸው ዜጎች በይቅርታ እና ክስ በማቋረጥ ከእስር ተፈትተዋል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግስት ቆርጦ በመነሳቱ ከአገር ውጭ የሚንቀሳቀሱና በሽብርተኝነት ጭምር የተፈረጁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሠላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ያቀረበው ጥሪም በጎ ምላሽ አግኝቷል፡፡ የእንደራሴዎች ምክር ቤትም በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶችን ፍረጃ በመሰረዝ ለህዝባቸውና ለአገራቸው ጥቅም በሠላማዊ ጎዳና እንዲራመዱ አደራ አስረክቧቸዋል፡፡
ለባለፉት 18 ዓመታት በቁርሾ ውስጥ የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን በአዲስ ምዕራፍ የማስቀጠሉ ጥረት በመልካም ፍሬ መታጀቡ የዲፕሎማሲው ስኬት ማሳያ ነው፡፡ በጎረቤትና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ሰብአዊነትና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ያደረገው ጉብኝትም በየአገራቱ የታሰሩ ዜጎችን ማስፈታት ችሏል፤ የሁለትዮሽ ግንኙነትን አጠናክሯል፤ የተለያዩ ድጋፎችንና ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ረድቷል፡፡
የተጀመረውን ለውጥ ለማሳለጥ መከላከያና ደህንነትን ጨምሮ በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የአመራር ለውጥና የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ከሰብአዊ መብት ጥሰትና ከታራሚዎች አያያዝ ጋር በተያያዘም ችግር ያለባቸውን አካላትን ከኃላፊነት የማንሳትና የማስተካከያ እርምጃዎችን የመውሰድ ተግባር ተፈፅሟል፡፡ የምህረት አዋጅ ረቂቅን ከማዘጋጀት ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሥልጣን ዕድሜ የሚገድቡ፣ የፀረ ሽብር ህጉንና ሌሎች በጥናት ላይ የተመሰረቱ የህግ ማሻሻያዎች የማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በመንግስት እጅ ሥር የነበሩ እንደ ኢትዮ-ቴሌኮምና አየር መንገድ የመሳሰሉ ትላልቅ ተቋማት መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ ወደ ግል የማዛወር ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደ አንድ ምንጭ የሚቆጠረውና በአገሪቱ ታሪክ ፋና ወጊ የሆነውን ነዳጅም በሙከራ ደረጃ ማምረት ተጀምሯል፡፡
ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ በ100 ቀናት ብዙ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ቀድሞ የተጀመሩ ልማቶችም ለፍሬ በቅተዋል፡፡ በእነዚህ ቀናት ለለውጥ ጉዞው መደላድል የፈጠሩ መሰረቶች ተጥለዋል፡፡ ይህን መደላድል በመጠቀም የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ መትጋት ይገባል፡፡ ሥራው ተጀመረ እንጂ የታሰበው ላይ አልተደረሰም፡፡ ከተመዘገበው ይልቅ የሚቀረው፣ ከተደመረው ይልቅ ያልተደመረው ሥራ ይበዛልና ጉዞው በፍጥነት መቀጠል አለበት፡፡ በመቶ ቀናት የለውጥና የፍላጎት እርምጃ ሲለካ ቀጣዩን ጉዞ ማሳካት ከባድ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯልና፡፡
አሁን ጊዜው የስራ ነው፤ ተግባራዊ ሥራ እውን የሚሆንበት፡፡ ቃል ወደ ተግባር የሚተረጎምበት፣ ሠላማዊ ድጋፍ በተጨባጭ ውጤት የሚለካበት ጊዜ ነው፡፡ ችግሮችን በማስወገዱና መልካሙን በማጠናከሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተግባራዊ ተሳትፎ መታየት አለበት፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ የ100 ቀናቱ ስኬቶች በቀጣይም በመልካም ፍሬ መታጀባቸው አይቀርም፡፡ ህዝብና አገር በመሪ ይወከላሉና የመሪ ስኬት የአገርና የህዝብ ስኬት ነው፡፡ ለአገር ስኬት ደግሞ የሁሉም ዜጋ ጥረትና ተሳትፎ ወሳኝም፤ ግዴታም ነው፡፡
አገሪቱን በአዲስ ምዕራፍ ለለውጥና ለውጤት ለማብቃት የሚደረገው ጥረት አልጋ በአልጋ እንደማይሆን ግልፅ ነው፡፡ የለውጥ ትግል ከፍተኛ ጥረት፣ ብዙ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ግጭትም የዚሁ ተግዳሮት አንዱ መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የሠላምና የለውጥ እንቅፋቶች ጉዞውን እንዳያደናቅፉት መትጋት ይገባል፡፡ የጥፋት ዘበኞችን ከልማት ጎዳናው እንዲወገዱ ብርቱ ትግልና ርብርብ ያስፈልጋል፡፡
ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ የሚያስፈልገው አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ዕውን እንዲሆን ሁሉም ከበቀልና ከጥላቻ ነፃ ሆኖ በአንድነት መቆምና መደመር አለበት፡፡ በመደመር የአንድነትና የህብረት ዕሳቤ የተጀመረው ጉዞ በብሔር፣ በእምነት፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ልዩነቶች ሳንካ እንዳይገጥመው መትጋት ተገቢ ነው፡፡
የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩባት፤ የዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጡባት፣ ዘላቂ ልማትና ዕድገት ዕውን የሆኑባት አገር ተገንብታ ለማየት ርብርቡ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ለውጡ ፍሬ እንዲያፈራ ዓላማና ግቡ ዕውን እንዲሆን ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ግድ ይላል፡፡ ለዚህ የሚጠቅመውን ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት ደግሞ ትልቁ የቤት ሥራ ነው፡፡ እንደ አገር ጠንካራ ሥርዓት ከተዘረጋ ህዝብን ለቅሬታ የሚዳርጉ ቀዳዳዎች ይደፈናሉ፤ የግጭትና የሁከት ምንጮች ይወገዳሉ፡፡ ሠላም፣ዲሞክራሲና ልማትን የማፋጠኑ እርምጃ ሥርዓቱን ተከትሎ ይቀጥላል፡፡
መንግስትና ህዝብ ተባብረውና ተናበው ሲጓዙ ችግሮች ይወገዳሉ፤ አመርቂ ውጤቶች ይመዘገባሉ፤ ለውጦች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን እውን ለማድረግ እከሌ ከእከሌ ሳይባል ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ ለውጤት መትጋት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን በ100 ቀናት የታየው ተስፋ ሰጭ ስኬት አድማሱን እያሰፋ፣ጉልበቱን እያበረታ፤ውጤታማነቱን እያጎለበተ በቀጣዮቹ ወራትና ዓመታት መደጋገሙ አይቀሬ ነው፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ ቅርሶች በመንግሥታትና በግለሰቦች ተዘርፈው በተለያዩ አገራት ይገኛሉ። እነዚህን ቅርሶች የተደራጀ አሠራር በመዘርጋት ማስመለስ ይገባል፡፡
በቅርስ ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማድረግ የሚታወቁት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ቅርሶቹን ለማስመለስ ያገባናል የሚሉ ግለሰቦች፣ ምሁራን፣ ከቅርስ ጋር የሚሠሩ ድርጅቶች፣ መንግሥት፣ የቅርስ ባለቤቶች እና የተለያዩ አካላት የሚሳተፉበት ሕዝባዊ ተቋም ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት በብዙ አገሮች የዚህ አይነት ሕዝባዊ ተቋማት ቅርሶችን ለማስመለስ አስችለዋል። ኢትዮጵያም ይህን መንገድ ብትከተል በመንግሥታት ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች ዕጅ ያሉ ቅርሶች ለማስመለስ ያስችላል። በዚህ መልኩ ተደራጅቶ መሥራት ከታቻለ ቅርሶችን ይዘው የሚገኙ አገራትንም ሆነ ግለሰቦችን ለማሳመንና ጫና ለማድረግ ያስችላል፤ ዓለም አቅፍ ሕግና ዲፕሎማሲ ለመጠቀምም አቅም ይፈጥራል፡፡
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ አብርሃም ኪሮስም የዲያቆን ዳንኤልን ሀሳብ ይጋራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ከሠሩ ቅርሶችን ለማስመለስ ይቻላል። በተለይም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤምባሲዎች፣ ቆንስላዎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቀናጅተው ቅርሶችን ለማስመለስ መታተር አለባቸው። የቅርስ ባለቤቶች የሆኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ በዚህ ላይ የሚሰሩ ማህበራትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ከሰሩ ቅርሶችን ለማስመለስ እንደሚቻል ይናገራሉ።
የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃ ቁጥጥርና ደረጃ ምደባ ባለሙያ አቶ አበራ ኢንጭሎ፤ የዓለም የባህል፣ የሳይንስና የትምህርት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1970 የአንድ አገር ቅርስ  ወደሌላ እንዳይወሰድና እንዳይዘዋወር ስምምንት ቢደረገም ከዚህ ስምምንት በፊት የተወሰዱ ቅርሶችን በሕግ ለማስመለስ አስቸጋሪ መሆኑን ያመላክታሉ።
ባለሙያው እንደሚሉት ቅርሶቹን ማስመለስ የሚቻለው በዲፕሎማሲና በድርድር ብቻ ነው። ይህን ለማድረግም በመጀመሪያ በተለያዩ አገራት ያሉንን ቅርሶች ማጥናት ያስፈልጋል። እስካሁን ግን መንግሥት ይህን ለማድረግ የሰራው ሥራ የለም። በመሆኑም ከግለሰቦችና ከድርጅቶች በላይ መንግሥት ዋና ተዋናይ በመሆን ከማጥናት እስከ ማስመለስ መሥራት አለበት። ቅርስ በማስመለስ እስካሁን ምንም ያልሰሩት የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግንባር ቀደም ሆነው ቅርሶቻችን ተዘርፍው ከሚገኙበት አገራት ለማስመለስ መደራደር አለባቸው። ከመንግሥት ጎንም በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትና ሁሉም ዜጎች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በተለይም መገናኛ ብዙሃን ጫና ማድረግ አለባቸው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂና የቅርስ ትምህርት ክፍል መምህር ተክሌ ሀጎስ በበኩላቸው፤ ቅርሶችን ለማስመለስ ያሉበትን ቦታ መለየትና አዋጭ የሆነ የዲፕሎማሲ ስልት በመንደፍ መሠራት አለበት። የዓለም የባህል፣ የሳይንስና ትምህርት ድርጅትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንም የሥራው አጋር ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለማጥናትም ሆነ ለማስመለስ ሁሉም ዜጋና ድርጅቶች ባለቤትና ተዋናይ መሆን አለባቸው። መንግሥትም የአንባሳውን ድርሻ ስለሚወስድ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ነገር ግን እስካሁን አብሮ የመሥራት ችግር ስላለ በቀጣይ በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን በአፅንኦት ይናገራሉ።
የወጡትን ቅርሶች ማስመለስ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት የቅርስ ሽያጭ በሰፊው ይታያል የሚሉት መምህር ተክሌ ለዚህ ዋነኛው መንስኤ ደግሞ ከመንግሥት አመራር እስክ ሕብረተሰቡ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ነው ይላሉ። እንደ እሳቸው ገለፃ፤ በአገራችን ያሉት ቅርሶች ዓለም አቅፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ አልተመዘገቡም። አገር አቅፍ የመረጃ ሥርዓት አልተዘረጋም። ይህ ባለመሆኑ ሲሰረቁ በሕግ ለማስመለስና ከአገር እንዳይወጡ ለመከላከል አልተቻለም። ቀደም ሲል ለወጡት ቅርሶች ብቻ ሳይሆን አሁን ከዕጃችን እያመለጡ ያሉትን ቅርሶቻችንንም ትኩረት መስጠት ይገባል።
ዲያቆን ዳንኤል፤ ከውጭ ያሉትን ማስመጣት ብቻ ሳይሆን ከተመለሱ በኋላ የትና እነዴት ነው የሚቀመጠው የሚለው አንገብጋቢ መሆኑን ያብራራሉ። ቅርሶችን ለማስመለስ ብቻ ሳይሆን ያሉትንና የሚመጡትም ዳግም እንዳይሰረቁ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው። አምጥተን ድጋሚ የሚወጡ ከሆነ ታጥቦ ጭቃ ነው። የቅርስ ጉዳይ የሁሉም ዜጋ በመሆኑ በማስመለስና በመጠበቅ ግዴታና ኃላፊነት አለበት። መንግሥትም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ይላሉ።
አቶ አብርሃም በበኩላቸው እንደሚሉት፣ ቅርስ ከማስመለስ ጎን ለጎን ስለቅርስ ለህዝቡ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል። የተዘረፉብንን ቅርስ ብናመጣም ተመልስው መሄዳቸው አይቀረም። መንግሥትም ዜጎች ለቅርስ ያላቸው ግንዛቤ እንዲያድግ ማስተማር አለበት። ለቅርሶቻችን ማስቀመጫና ማሳያ ሙዜየሞችም ለመገንባት ትኩረት መደረግ አለበት። ዜጎችንም ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድርግ ያስፈልጋል። ለዘራፊዎች ሸጠው ከሚያገኙት በላይ ቅርሶቹ በአገራቸው መኖሩ ተጠቃሚ እንዲያደርጋቸው መሥራት እንዳለበት ይመክራሉ።
አቶ አበራ በበኩላቸው በአገር ውስጥ ያለው ቅንጅት ዝቅተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለፃ በክልሎች በትንሽ ገንዘብ ቅርሶችን አሳልፈው እየሸጡ ነው። ቅርስን ከአገር የሚያወጣ ከፍተኛ የሆነ የደላላ ሰንሰለት አለ። ተዘርፈው በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እየወጡ ነው ያሉት። ይህን ማስቆም ይገባል። ቅርሶቻችን ለማስመለስ እስካሁን መንግሥትም ሆነ ዜጎች ተደራጅተው አልሰሩም። ከዚህ በኋላ መንግሥት በመደበኛነት ቅርስ የማስመለስ ሥራውን ከዜጎች ጋር በመተባበር መሥራት ይጠበቅበታል።
ከኢትዮጵያ ተዘርፍው በሌላ አገራት ያሉ ቅርሶች ከ50 በላይ በሚሆኑ አገራት እንደሚገኙና ቁጥራቸውም ከ15ሺ በላይ እንደሚሆኑ ዲያቆን ዳንኤል ይጠቅሳሉ። አቶ አብርሃም ኪሮስ በበኩላቸው የተዘረፉ ቅርሶቻችን ከ30 እስከ 40ሺ እንደሚደርሱ ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ መገለጫ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ቅርሶች በተለያዩ አገራት መገኘታቸው ገሃድ ነው። እነዚህ ቅርሶች የሳይንስ፣ የዕምነት፣ የፖለቲካ፣ የጦርነት፣ የኪነጥበብ፣ የፍልስፍና፣ የህክምና ሌሎች መገለጫዎቻችን ናቸው። በመሆኑም እነዚህ ቅርሶች በሚፈለገው መጠን ካለተመለሱ አገራችን በቀጣይ በተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ለምታከናውናቸው ሥራዎች ተገቢውን መረጃ እንዳታገኝ ያደርጋል፡፡ የቀደመውን ታሪካችንንም ቀስ በቀስ እንድናጣ በማድረግ ታሪኮቻችን እየተረሱ እንዲመጡ ያደርጋል፡፡

ዜና ትንታኔ
አጎናፍር ገዛኸኝ

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።