Items filtered by date: Thursday, 12 July 2018

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የዓለም ስፖርት አፍቃሪያን ቀልብ ከሩሲያው ዓለም ዋንጫው ጋር ነጉዷል። በዚህም በዓለማችን የሚከናወኑ ሌሎች ታላላቅ የውድድር መድረኮች እየተሰጣቸው ያለው ትኩረት አነስተኛ ሆኗል። በአትሌቲክሱ ዓለም ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው የዓመቱ የዳይመንድ ሊግ ውድድር በዓለም ዋንጫው የተሸፈነ ትልቅ የውድድር መድረክ ነው። በአስራ አራት የዓለማችን የተለያዩ ከተሞች መዳረሻውን የሚያደርገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር የዓለም ዋንጫ ትኩረት ቢሻማውም ፉክክሩ በተለያዩ የዓለማችን ኮከብ አትሌቶች መካከል ጠንክሮ ቀጥሏል። በዚህም ዘጠነኛ የውድድሩ መዳረሻ ከተማ የሆነችው የሞሮኮዋ ራባት ነገ በተለይም በመካከለኛ ርቀት ከዋክብት አትሌቶችን የምታፋልምበት ውድድር ይጠበቃል።
በሴቶች አምስት ሺ ሜትር ውድድር ኬንያዊቷ የዓለም ቻምፒዮን ሔለን ኦቢሪንና ኢትዮጵያዊቷን ኮከብ ገንዘቤ ዲባባን ያፋጠጠው ውድድር ይጠበቃል። የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የክብረወሰን ባለቤትና በርቀቱ የኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ገንዘቤ ዲባባ ባለፈው የለንደን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ውጤታማ መሆን ቢሳናትም ዘንድሮ ከዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ጥምር የወርቅ ሜዳሊያ አንስቶ እስካሁን በተካሄዱት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ውጤታማ መሆን ችላለች።
ገንዘቤ ነገ ከኬንያዊቷ ጠንካራ አትሌት ሔለን ኦቢሪ ጋር በምትፎካከርበት የአምስት ሺ ሜትር ውድድር በርካታ ተፎካካሪዎች ቢኖሩባትም በርቀቱ ፈጣን ከሚባሉ አትሌቶች አንዷ ናት። እኤአ 2015 ላይ ያስመዘገበችው 14:15.41 ሰዓት በአምስት ሺ ሜትር ከዓለማችን አምስተኛዋ ፈጣን ሰዓት ያላት አትሌት ያደርጋታል።
በአምስት ሺ ሜትር ባለፈው ሪዮ ኦሊምፒክ ኬንያዊቷን ቪቪያን ቼሪዮትና አልማዝ አያናን ተከትላ የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለችው ሔለን ኦቢሪ በተመሳሳይ ከዓመት በፊት በለንደን የዓለም አትሌቲክሰ ቻምፒዮና አልማዝ አያናን አስከትላ በመግባት በአትሌቲክስ ህይወቷ ትልቅ ስኬት የነበረውን የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች። በርቀቱ ባለፈው ዓመት የሮጠችው 14:18.37 ፈጣን ሰዓቷ ሲሆን ይህም በዓለም በርቀቱ ስምንተኛዋ ፈጣን አትሌት ያደርጋታል።
ገንዘቤ ዲባባና ሔለን ኦቢሪ በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሲገናኙ የመጀመሪያቸው አይደለም። ሁለቱ ኮከቦች ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ርቀት ዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ የተገናኙት ባለፈው ዓመት ሮም ላይ ነበር። ገንዘቤ መጥፎ ሊባል የሚችል የውድድር ዘመን ባሳለፈችበት በዚያ ዓመት ሔለን ኦቢሪ ሮም ላይ በርቀቱ ከዓለም ስምንተኛ የዓለማችን ፈጣን ሰዓት ባለቤት ያደረጋትን ሰዓት አስመዝግባ ማሸነፍ ችላለች። ገንዘቤ እጅግ የወረደ አቋም ባሳየችበት በዚህ ውድድር ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል። ሔለን ኦቢሪ በዓለም ቻምፒዮና ወደ ስኬት ያንደረደራት ውድድርም ይሄው ነው።
ገንዘቤ ከመጥፎው የውድድር ዓመት ማግስት ወደ ድል ለመመለስ ብዙም ጊዜ አልፈጀባትም። በተለይም ባለፈው መጋቢት በርሚንግሃም ሲቲ በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአንድ ሺ አምስት መቶና በሦስት ሺ ሜትር ጥምር የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማሸነፏን ተከትሎ አሁን በጥሩ የአሸናፊነት መንፈስ ላይ ትገኛለች። ለዚህም በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች እያሳየች ያለው ድንቅ አቋም ምስክር ነው። ገንዘቤ የዳይመንድ ሊጉ ሦስተኛ መዳረሻ ከተማ በሆነችው ዩጂን ላይ በአምስት ሺ ሜትር ከሔለን ኦቢሪ ጋር ዳግም ተገናኝታ 14:26.89 በሆነ ሰዓት ማሸነፍ ችላለች። ኦቢሪ በበኩሏ ጠንካራ ፉክክር በማድረግ በአስር ሰከንድ ዘግይታ ሦስተኛ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች።
ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ኮከቦች የሚያደርጉት ፉክክር በአፍሪካዊቷ የዳይመንድ ሊግ መዳረሻ ከተማ ራባት አዲስ የውድድሩ ክብረወሰን ሊመዘገብበት እንደሚችል ከወዲሁ ግምት አግኝቷል። የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም የርቀቱ ፈርጥ የሆነችው አልማዝ አያና 2016 ላይ የራባትን የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰን 14:16.31 በሆነ ሰዓት የጨበጠች ሲሆን ይህም ሰዓት ከዓለም ፈጣን ሰዓቶች ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው።
በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ከሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናና በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ከሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ሌላ የአትሌቲክስ ውድድሮችን የምንመለከትበት አጋጣሚ ሰፊ አይደለም። ይህም በአገር ደረጃ ሲሆን ነው። በእግር ኳስና በሌሎች ስፖርቶች ፕሪሚየር ሊግ ወይንም በየሳምንቱ የሚከናወኑ ውድድሮች አይጠፉም። ወደ አትሌቲክሱ ስንመጣ ግን የዓለማችንን ስመ ጥር አትሌቶች ከማራቶን ውድድር ውጪ ያሉትን በግል ሲፋለሙ የምንመለከተው በዓመት በተወሰነ ወቅት ላይ በሚካሄደው በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ነው። ዳይመንድ ሊግ በፈረንጆቹ ከግንቦት መጀመሪያ አንስቶ በተለያዩ የዓለማችን አስራ አራት ከተሞች እሰከ መስከረም የሚከናወን የአትሌቲክስ ውድድር ነው። ይህ ውድድር በማራቶንና በጎዳና ላይ ውድድሮች የማናያቸውን አትሌቶች የምናይበት ሲሆን በመምና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ማለት ግን በጎዳና ላይ ውድድሮች ወይንም በአገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ የሚካፈሉ አትሌቶች አይወዳደሩበትም ማለት አይደለም።
የዳይመንድ ሊግ ውድድር እ.ኤ.አ ከ2010 ወዲህ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ ከዛ በፊት እ.ኤ.አ ከ1998 ጀምሮ ጎልደን ሊግ በመባል ነበር የሚካሄደው። ጎልደን ሊግ በአውሮፓ ከተሞች ብቻ የሚካሄድ ውድድር ነበር። ዳይመንድ ሊግ ከተካው ወዲህ ግን ከአውሮፓ ውጪ ውድድሩ ሌሎች አገሮችን አሳታፊ ሊያደርግ ችሏል። የአሜሪካ ሁለት ከተሞች ዩጂንና ኒውዮርክ፤ የቻይናዋ የንግድ ማዕከል ሻንጋይና የኳታሯ ዶሃ ከተማ ጎልደን ሊግ ወደ ዳይመንድ ሊግ ከተቀየረ ወዲህ ውድድሩን በየዓመቱ ማስተናገድ የጀመሩ ከተሞች ናቸው። ይሁን እንጂ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ተቀንሳ በምትኩ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ አገር ሞሮኮ በራባት ከተማ ውድድሩን ለማስተናገድ በቅታለች።
የኳታሯ ዶሃ የዓመቱን የመጀመሪያ የመክፈቻ ውድድር ግንቦት ወር ላይ ስታስተናግድ የቻይናዋ ሻንጋይ ከቀናት ልዩነት በኋላ ሁለተኛውን ውድድር ታስተናግዳለች። ከአስር ቀን በኋላ ደግሞ የጣሊያኗ መዲና ሮም የወሩን የመጨረሻ ውድድር ታዘጋጃለች። ሰኔና ሃምሌ ወር አራት አራት ውድድሮች በተለያዩ ከተሞች ይካሄዳሉ። በአሜሪካ ዩጂንና በሞሮኮ ራባት፤ የኖርዌይ ኦስሎና የስዊዘርላንዷ ሉዛን ሰኔ ላይ ውድድሮችን ያስተናግዳሉ። የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ፤ የእንግሊዟ በርሚንግሃም፤ ሞናኮ፤ ስቶክሆልም፤ ለንደን፤ ዙሪክና የቤልጂየሟ መዲና ብራሰልስ የዓመቱን የመጨረሻ ውድድሮች የሚያስተናግዱ ከተሞች ናቸው።
ለአንድ የውድድር ዓመት ከሃምሳ ሚሊየን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ይመደባል። ከእዚህ ገንዘብ ውስጥ ስምንት ሚሊየን ዶላር ያህሉ ለአትሌቶች ሽልማት የሚውል ነው። በእያንዳንዱ ውድድሮች አሸናፊ የሚሆነው አትሌት አርባ ሺ ዶላርና ልዩ ሽልማት ይበረከትለታል። የውድድር ዓመቱ አጠቃላይ አሸናፊ በሴትና በወንድ ለየግል «ዳይመንድ አትሌት» የተባለውን ሽልማት የሚወስድ ይሆናል።

ቦጋለ አበበ

 

ያለ በቂ ድጋፍ የሀገርን ስም ለማስጠራት የሚጥረው ስፖርት

 

በሀገሪቱ ትኩረት ካልተሰጣቸው የስፖርት አይነቶች አንዱ ቼስ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ቼስ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድም እንደ ስፖርት አይታይም፡፡ እውነታው ግን ወዲህ ነው-ቼስ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳጅ ከሆኑት ስፖርቶች ተጠቃሽ መሆኑ፡፡
ለስፖርቱ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ ሀገሪቱ አሁን በዓለም ዓቀፍ መድረክ ከታወቀችበት አትሌቲክስ ባልተናነሰ ሰንደቅ አላማዋን ከፍ የሚያደርግ ስፖርት እንደሆነ ፍንጮች ታይተዋል፡፡ በቅርቡ በጂቡቲ በተካሄደው በአፍሪካ የቼስ ፌዴሬሽን የተዘጋጀ የ2018 የዞን 4 ነጥብ 2 የአፍሪካ የግል ሻምፒዮና ላይ ያስመዘገበችው ውጤት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፉ በላይነህ እንደሚሉት፤ ስምንት ሀገራት በተሳተፉበት ኢትዮጵያ በአራት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች በተወከለችበት በዚህ ውድድር ሁለት የነሃስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች፡፡
የ2017ቱ የአፍሪካ የግል ሻምፒዮና በኢትዮጵያ በጅማ ከተማ ተካሂዶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰይፉ፤ኢትዮጵያ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት እንዳልቻለች ነበር ያብራሩት፡፡ ዘንድሮ በሁለቱም ጾታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የነሃስ ሜዳሊያ ማግኘት መቻሏ ትልቅ ስኬት መሆኑን በመግለጽ፤ ስፖርተኞቹ በዓለም ዓቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ ልምድ ማሳደጋቸው እና በሀገር ውስጥ በዓመት አንዴ ይደረግ የነበረው ውድድር ሶስቴ መካሄዱ ትልቅ እገዛ ማበርከቱን አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ሰይፉ ማብራሪያ፤ በስፖርቱ የሚገኘው ውጤት ከዕለት ዕለት መሻሻሎችን እያሳየ መምጣቱ ስፖርተኞች አቅማቸውን ማሳደጋቸውን ያሳያል፡፡ ተወዳዳሪዎቹም ለውድድሩ ቀደም ብለው መዘጋጀታቸው እና አቅማቸውን ለማሳደግ የግል ጥረት ማድረጋቸው ለውጤቱ መሻሻል እገዛ አድርጓል፡፡
በጅቡቲ በነበረው መድረክ የታየው ውጤት ለስፖርቱ እድገት ጠንክሮ ከተሰራ እና ስፖርተኞቹ በተደጋጋሚ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የመሳተፍ ዕድላቸው ቢሰፋ፤ እንዲሁም ሀገሪቷን ወክለው የሚወዳደሩ ስፖርተኞች ቁጥር ከፍ ቢል በቀጣይ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ የግል ሻምፒዮና ውድድር ወርቅ ያሸነፈ ሀገር የዓለም ዓቀፉ ቼስ ፌዴሬሽን ሻምፒዮና ላይ ቀጥታ ተሳታፊ እንደሚሆን የተናገሩት አቶ ሰይፉ፤ በአሁኑ ውድድር ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፍ ባለመቻሏ በዓለም ዓቀፍ የቼስ ፌዴሬሽን ሻምፒዮና ላይ መወዳደር ባትችልም እንኳን በቀጣይ የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ የዚህ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያብራሩት፡፡
እንደ አቶ ሰይፉ ማብራሪያ፤ ስፖርቱን ለማሳደግ ፌዴሬሽኑ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር ችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ከ31 ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ 66 የቼስ መምህራን ስልጠና ሰጥቷል፡፡ መምህራኑ በአካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስልጠናዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ የምስክር ወረቀትም ተሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህ መምህራን በአሁኑ ወቅት እስከ ከፍተኛ ኢንስትራክተርነት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በትምህርት ቤቶች ቼስ ስፖርትን እንዲያሰለጥኑ በቅርበት እየተሰራ ነው፡፡


ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ከ17 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር ላይ ቼስ እንዲካተት ጥረት ከማድረግ ጀምሮ በየክልሉ የቼስ ፕሮጀክቶች እየተሰራ ነው፡፡ አብዛኞቹ ክልሎች የቼስ ፕሮጀክቶች ባለቤት ሆነዋል፡፡ አሁንም ደግሞ በነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል ውድድር ለማድረግ ዝግጅት እየተከናወነ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ17 ዓመታት በታች የቼስ ውድድር በመጪው ነሃሴ ወር ይካሄዳል፡፡
በዩንቨርሲቲዎች መካከል ውድድር ለማድ ረግ ታቅዶ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ሰይፉ፤ በአገሪቱ አለመረጋጋት ስለነበር ውድድሩ መራዘሙን ነው ያብራሩት፡፡ የሰላሙ ሁኔታ በአስተማማኝ ደረጃ ሲሻሻል ይህ ውድድር እንደሚካሄድ ነው ያብራሩት፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ሀገር አቀፍ ሻምፒዮና ተብሎ በዓመት አንድ ውድድር ይካሄድ እንደነበር የገለጹት አቶ ሰይፉ አሁን በዓመት ሁለት ጊዜ ሁሉንም የሚያሳትፍ ( ኦፕን ቶርናሜንት) ይካሄዳል፡፡ ከዚያ ባሻገር አዲስ መድረኮችም በቅርቡ ተጀምረዋል፡፡ ታዳጊዎች ለብቻቸው የሚሳተፉበት ከ17 ዓመት በታች የውድድር እድል ተጀምሯል፡፡ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ከ20 ዓመት በታች ውድድር በድሬዳዋ ይካሄዳል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የክለቦች ሻምፒዮናም መጀመሩን ያብራሩት አቶ ሰይፉ፤ በዚህ ሻምፒዮና አምና አራት ክለቦች ተሳትፈውበት እንደነበር በመግለጽ፤ ዘንድሮ ከዚያ በላይ ክለቦች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የጠቆ ሙት፡፡
ፌዴሬሽኑ የትምህርት ቤቶች፣ የዩኒቨርሲ ቲዎች እና የግል ሻምፒዮኖችን ውድድር በየጊዜው እያካሄደ መሆኑን ያብራሩት አቶ ሰይፉ፤ እንደዚህ ውድድሮች በተካሄዱ ቁጥር ተጨዋቾች ሁል ጊዜ ስለ ስፖርቱ እንዲያስቡ ያደርጋል፡፡ ይህም አሁን እየመጣ ላለው የውጤት መሻሻል መልካም እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ሰይፉ ገለጻ፤ ከዚህ በተጨማሪ የዓለም አቀፍ ቼስ ፌዴሬሽን በሚሰጠው ደረጃ መሰረት ከፍተኛ አቅም ያላቸው ወይም ሬትድ ስፖርተኞች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ በዓለም ዓቀፍ መድረክ ያላት ደረጃም እየተሻሻለ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የፌዴሬሽኑ አቅም በጣም ውስን መሆኑ ስፖርቱ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ማድረጉን አቶ ሰይፉ ያነሳሉ፡፡ የፌዴሬሽኑ የፋይናንስ አቅም በጣም አነስተኛ መሆኑን እና መንግስትም በሚጠበቀው ደረጃ እገዛ እያደረገ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ በቅርቡ በጅቡቲ የተደረገው አህጉራዊ ውድድር ሀገር አቀፍ የስፖርተኞች ምልመላ ከተካሄደ በኋላ ተገቢው እገዛ ባለመደረጉ ሀገሪቷ ከውድድሩ ልትወጣ ደርሳ እንደነበር አንስተዋል፡፡
እንደ አቶ ሰይፉ ገለጻ፤ ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ሀገሪቱ በውድድሩ ሳትሳተፍ እንዳትቀር ጥረት በማድረግ ልኡካን ቡድኑ ወደ ጅቡቲ ሄዷል፡፡ የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን ስፖንሰር አድርጎ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት እንዲሳተፉ የተደረገ ሲሆን፤ የተቀሩት አራቱ ተወዳዳሪዎች በራሳቸው ሙሉ ወጪ ሀገራቸውን ወክለው ተሳትፈዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ድጋፍ ያደረገላቸውም ይሁን በራሳቸው ወጪ የተሳተፉ ተወዳዳሪዎች በአውሮፕላን መሄድ የነበረባቸው ሲሆን፤ በአቅም ማነስ በባቡር እስከ ጂቡቲ ሄደው እንዲወዳደሩ ተደርጓል፡፡
የተለያዩ ዘዴዎች በመጠቀም ባለሃብቶች በጅቡቲ ለሚደረገው ውድድር ገቢ ለማሰባሰብ ጥረቶች መደረጋቸውን ያመለከቱት አቶ ሰይፉ፤ ጥረቱ ግን ውጤት ሊያፈራ እንዳልቻለ ነው የተናገሩት፡፡
ተወዳዳሪዎቹ ከመንግስት ምንም ድጋፍ ሳይደረግላቸው ሀገርን የሚያኮራ ውጤት ይዘው መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ ሰይፉ፤ ሀገሪቱ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ስትገባ ከጥቂት የውድድር አይነቶች ቼስ አንዱ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ለስፖርቱ ትኩረት ቢሰጠው እና ብሄራዊ ቡድን በመንግስት ቢደጎም የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል በመጠቆም ጅቡቲ መሄድ የነበረባቸው አምስት ወንድ እና አምስት ሴት ስፖርተኞች ተሟልተው ቢሄዱ አሁን ከተመዘገበው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይቻል እንደነበር አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ሰይፉ ማብራሪያ፤ ፌዴሬሽኑ ከክልሎች ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር መልካም ነው፡፡ ለፕሮጀክትም ይሁን ለክለባት ማቋቋ ሚያም ለክልሎች የቴክኒክ እና የሙያ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለውድድር እና ለስልጠና የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ፌዴሬሽኑ ባለው አቅም በየዓመቱ ያከፋፍላል፡፡ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን በዳኝነት እና በአሰልጣኝነት ዙሪያ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
በሚደረገው ድጋፍ አንዳንድ ክልሎች ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳዩ ሲሆን፤ ሌሎች ክልሎች ደግሞ መልካም እንቅስቃሴ እያደረጉ አይደለም፡፡ እነዚህ ክልሎች ያለባቸውን ድክመቶች እንዲቀርፉ ፌዴሬሽኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

መላኩ ኤሮሴ

Published in ስፖርት

«እንደው ይህን የመሰለ ሰው...እስከዛሬ የት ነበር?» አሉ አንድ እናት፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አብቅቶ የሬዲዮን ፕሮግራሙ ዝግጅት አስተባባሪ ድምጽ ሲከተል፤ ዞር ዞር ብለን በፈገግታ ተመለከትናቸው። «ይኸው ራዲዮና እና ያንን ቴሌቭዥን ተከታታይ አድርጎኝ አረፈው» ብለው እየሳቁ ነጠላቸውን አራግፈው ከተቀመጡበት ተነሱ።
«እድሜዬን በሙሉ ስፈልግሽ ኖሬ
ጊዜው ደረሰና አገኘሁሽ ዛሬ» አለ ያ ዘፋኝ! መኪና ላይ ተኝቶ፤ ልክ ሴትየዋ በአጠገቤ እልፍ ሲሉ ሙዚቃው ብልጭ አለብኝ። ምርጥና በጣም አስፈላጊ ብሎም ተፈላጊ ሰው የት እየሄደ ነው ሲጠሩት ሳይሰማ ግን በድንገት ከች የሚለው? ምርጥ ነገሮች ብዙ ጊዜ ትንቢትን ይፈልጋሉ መሰለኝ፤ «ይመጣልና ታገሱ!» ተብሎ ካልተነገረለትና በተስፋ ካልተጠበቀ ዝም ብሎ አይከሰትም።
በሬዲዮን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ከሰማሁበት «ኑ ቡና ጠጡ» ሻይ እና ቡና ቤት ወጥቼ መንገድ ስጀምር ገራሚ የሆኑ ሰዎች እንዲህ በዘመናት መካከል እልፍ እልፍ እያሉ የሚታዩበት ምክንያት ምን እንደሆነ እያሰብኩ ነበር። አንድ ምርጥ ሰው ለመሥራት ስንት ዘመን ይፈጃል? ስንት ተላላዎችን አልፎ ነው አንድ ብልህ የሚወጣው? ከስንት ኪሎ ድንጋይ ውስጥ ነው አንድ ግራም ወርቅ የሚገኘው?
«በዛ በኩል ሂጂ...በዚህ ጋር አያስኬድሽም» የሚል ድምፅ ወደመጣሁበት መንገድ ፊቴን እንድመልስ አስገደደኝ። «ስለተቆፋፈረ...» አለኝ ተናጋሪው እንደማፈር እያደረገውና ጫማዬን እየተመለከተ፤ የተጋነነ ከፍታ ያለው ጫማ ያደረግኩ ስላልመሰለኝ በጥርጣሬ ጫማዬን ተመለከትኩ። ቢሆንም አጎንብሰው ደኅና የሚመስል የመንገድ ንጣፍ ድንጋይ ከሚፈነቅሉ ሰዎች መካከል የሆነው፤ የመንገድ ንጣፍ ሥራ ባለሙያ እንደሆነ ሁኔታው የነገረኝ ሰው ከእኔ የተሻለ መረጃ ስለሚኖረው ብዬ መንገዴን ቀየርኩ።
የተሻለ መንገድ መቼ ነው ተሠርቶ የሚያልቀው? አዲስ ሥራ እስኪፈጠር ድረስ ነው መሰል፤ ደንጊያ ሲያነጥፉ፤ መልሰው ሲነቅሉና ሲያፈርሱ...ደግሞ ሲሠሩ፤ መልሳችሁ አፍርሱ ሲባሉ፤ የሚሠራውን (ጠበቅ አድርጋችሁ አንብቧትማ!) የሚያውቁ ቢኖሩም፤ እነዚህ ባለሙያዎች ግን የሚሠሩት የተነገራቸው አይመስለኝም። የሠሩትን የሚያውቁት መንገዱ አልቆ ዳግም አይቆፈርም የሚባልበት ቀን ሲደርስ ነው።
ግን እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ እኛም ሁላችን የምንሠራውን የምናውቅ አይመስለኝም። «የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው...» ይል የለ ቅዱሱ መጽሐፍ ታሪክን ጠቅሶ? ለምሳሌ ሰውን እንደምንሠራ እናውቃለን? በእግራችን ስር ውር ውር የሚሉ ህጻናትን እየገነባንና እየሠራናቸው ያለነው እኛ እንደሆንን እናውቃለን? ዛሬ ከላያችን ላይ ሆነው ዘረፉን ሰረቁን የምንላቸውንስ የሠራቸው ማን ነውና?
እውነት! የምንሠራውንኮ አናውቅም። በመሰዳደብ እና በመጠላላት ውስጥ ምን ዓይነት መልካም ፍሬ ይጸድቃል? እንደውም ስታስቡት የጠቅላይ ሚኒስትራችንን በቀናነት የታሸ ብልህ መሪነት አይተን የምንደነቀው በዚህ ጊዜ እንዲህ ያለ ሰው ይኖራል ብለን ስለማናስብ ነውኮ! እንደዛ ዓይነት ሰው አልሠራንማ።
ግን ደግሞ በሌላም አቅጣጫ ማየት ይቻላል። ከተናቀ አፈር ውስጥ ወርቅ እንደሚወጣው በብዙ ፈተና ያለፉ ናቸው የበለጠውን ስኬት የሚያመጡት ወይም በብዙ ጠላት መካከል ነው ብርቱ ወታደር የሚገኘው። በጣም ጥላቻና ትክክል ያልሆነ ነገር በበዛበት ጊዜ ያንን ለማተካከል ያሰበ ሰው ድንገት ብቅ ይላል። ህሊናውን የሚሰማ፣ እውነትን የሚያዳምጥ።
የት ነበርክ? የት ነበርሽ? ብላችሁ ብትጠይቁ እነዚህ ሰዎች ሲሠሩ ነበር። እዚህ አረፍተ ነገር ላይ እንደው ተቸገሩና «ሲሠሩ» የምትለዋን ቃል አጥብቃችሁ አንብቡልኝ። አዎን! እነዚህ ሰዎች ሲሠሩ ነበር። ሠሪው ቤተሰብ ነው፣ ሠሪው ማኅበረሰብ ነው፣ ሠሪው ሕዝብ ነው። ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና ሕዝብ ታዲያ የሚሠሩትን አያውቁም። ግን ውጤታቸው በፊታቸው ይታያል። ወይ ወደ አዘቅት ይጨምራቸዋል አልያም አሁን እየሆነ እንዳለው ጤና አዳም ይሆናቸዋል።
ከዚህ በኋላ የምንሠራውን ማወቃችንን እንጃ፤ ግን በጎ ያልነውን ሁሉ ልንሠራ መርጠናል ብዬ አምናለሁ። ፍቅርን ማጠናከር፣ አንድነትን ማበረታት፣ እንደው አደባባይ ላይ ብቻ ሳይሆን በጓዳና በቤትም ውስጥ መተጋገዝ፤ በድምሩ መደመር የመሳሰሉትን ይዘን እንቀጥላለን። ቂምና ጥላቻ መወራረስ እዚህ ላይ አበቃ ማለት ነው። በዚህ የበለጠ ቀና ትውልድ፣ በፍቅርና በይቅርታ የሚያምን፣ የሚለፈፍለት ሳይሆን ትክክለኛውን ኢትዮጵያዊነትን የሚኖር ሰው ይመጣል።
በተጓዳኝ ዓይኑ የሚቀላም ይኖራል። «እሺ! ደግሞ ፍቅር ፍቅር ማለት ጀመራችሁ? ቆይ!» የሚል አይጠፋም። በቃ እንዲህ ነው! በጎ ያልነውን ብናደርግ እንኳ የምንሠራውን አናውቅም። ግን...እንደ ቱርክ ፊልም፤ ምን ችግርና ፈተናው ቢረዝም፣ አክተሮቹ ሁሉ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩ፣ ከአሁን አሁን አለቀ ቢባል፤ በጥቅሉ የመጣው ቢመጣ የሄደው ቢሄድ፤ አሸናፊው አሁን የያዝነው መንገድ ነው።
ልክ መንገዴን እንዳስቀየረኝ የመንገድ ዝርጋታ ሠራተኛ «እየሄዳችሁ ያላችሁበት መንገድ ከማንነታችሁ ከፍታ ጋር ስለማይሄድ መንገድ መቀየር ያስፈልጋል» ያለ መሪ ከች ብሏላ! ለልማትም ብለው ይሁን ለጥፋት፤ መንገዳችንን የሚቆፋፍሩ ካሉ...ድልድይ እንዴት እንደሚዘረጋም አይተናል።
ውይ! ብቻዬን ስሆን እንደ ፈላስፋ የሚያደርገኝ ይመስለኛል መሰል። ግን «እንደ ፈላስፋ አደረገኝ» ማለት ራሱ መልሶ ያሳፍረኛል። ለብቻ ሲሆኑ ግን ከቀኝ ጎን መማከር ነው ጥሩ፤ ይሄኔ ክፋትም ቢሆንኮ ስንቱን ክፉ ክፉ ነገር የማሰብ እድል አለኝ ማለት ነው? በቀኝ አውለኝ...ቀኙን አሳስበኝ ማለት ነው!
መንገድ ቀይሬ መንገዴን ከቀጠልኩ ቆየሁ። በምንም በኩል ሂድ፤ ትክክለኛው መንገድ ይሁን እንጂ መድረሻህ ጋር በትክክል ከደረስክ አልተሳሳትክም፤ የሚል አባባል ሰምቻለሁ ልበል? እያስፈራራ ያለውን ዝናብ ዘመን አመጣሿ ትንሿ ስስታም ጥላዬ እንደማታስጥለኝ ሳስታውስ ፈጠን እያልኩ መራመድ ጀመርኩ። ነገሩ ብዙም ሳልርቅ ነው የዘነበው፤ ከአንዱ ልብስ ቤት ዘልዬ ገባሁ። የምንሠራውን አናውቅምና በቦርሳ ለመያዝ ትመቻለች ብለን የያዝናት ትንሽዬ ጥላ ለራሳችንም እያነሰችን ነው መሰል። ሰላም!

ሊድያ ተስፋዬ

Published in መዝናኛ
Thursday, 12 July 2018 17:08

ብርታትን በተግባር

አርባምንጭ ከተማ ሲቀላ በሚባል አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ ዕድሜው ለጨዋታ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የመኪና ፍቅር ያደረበት ሲሆን፤ በአካባቢያቸው ማንኛውም ተሽከርካሪ ባለፈ ቁጥር እየተከተሉ መሮጥ የቀን ተቀን ተግባራቸው ነበር፡፡ ወጣት ማንዴላ ገብረመድህንና ጓደኞቹ፡፡ በተለይም በጎረቤታቸው የሚኖር አንድ የፖሊስ ባልደረባ መኪና እስካሁን ድረስ አትዘነጋውም፡፡ ግለሰቡ ለህፃናቱ ፍቅር ስለነበረው መኪናው ላይ ሲወጡ ምንም አይላቸውም ነበር፡፡ እንዳውም ገና በለጋ ዕድሜያቸው መኪና መንዳትና ሲበላሽ እንዴት መጠገን እንደሚቻል ልምድ እንዲቀስሙ ያደርጋቸው እንደነበር ነው የሚገልፀው፡፡ እነርሱም በተራቸው መኪናውን በማጠብ ወሮታውን ይከፍሉ እንደነበረም ይገልፃል፡፡
«እንግዲህ ያኔ የጀመረው የመኪና እና የብረታ ብረት ፍቅሬ አድጎ ኮሌጅ ስገባም ቀዳሚ ያደረጉት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ነበር» የሚለው ወጣት ማንዴላ በኮሌጅ ቆይታውም የኦቶሞቲቭ ቴክኖሎጂን ጨምሮ ሌሎች መሰል ዘርፎች ላይ ሥልጠና መውሰዱን ይጠቅሳል፡፡ ውጤቱ ጥሩ በመሆኑም እዛው በመምህርነት ተቀጥሮ መሥራት ይጀምራል፡፡ ግን ተቀጥሮ መሥራቱ ስላላረካው አምስት ሺ ብር አጠራቅሞ ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ባቋቋመው ማህበር አማካኝነት የብረታ ብረት ሥራዎችን ማከናወን ጀመረ፡፡ በዚህም ለአካባቢው ህብረተሰብ ፈጠራ የታከለባቸው የብረታብረት ውጤቶችን በማቅረብ ተቀባይነትን ማፍራት ችሏል፡፡
ብዙም ሳይቆይ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተወዳድሮ በመግባት ረዳት ቴክኒሽያን ሆኖ ማገልገሉን ቀጠለ፡፡ ገና ከለጋነቱ ጀምሮ ተሽከርካሪን አወላልቆ መልሶ የመገጣጠም ልምዱ አድጎና ዳብሮ በአንድ ጎን በተቀጠረበት የሙያ መስክ በሌላ በኩል ደግሞ በምርምር ሥራው የመምህራኑን ቀልብ መግዛት ችሏል፡፡ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት የሚያስደስተው መሆኑን የሚገልፀው ወጣቱ በተለይም የዩኒቨርሲቲውም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ የቆየውን የዝንጀሮ ጥቃት መከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሠራ፤ ይኸውም የዝንጀሮ ወጥመድ ነበር፡፡

ወጣት ሰላማዊት ወልደሚካኤል፤


በዚህም ሥራው በዩኒቨርሲቲው ገንዘብና የነፃ ትምህርት ዕድል ተቸረው፡፡ በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜም በመካኒካል ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ተምሮ ሰሞኑን ለመመረቅ በቅቷል፡፡ አርባምንጭ ያፈራችው ይኸው ተመራማሪ ወጣት በመመረቂያ ሥራውም አዲስ ቴክኖሎጂን በማምጣት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዘንድ አንቱታን አግኝቷል፡፡ የራሱን 50ሺ ብር አውጥቶ የሞተር ሳይክል ሞተር በመጠቀም የሠራት ባለአራት እግር ተሽከርካሪ በምርቃቱ እለት በተመራቂ ቤተሰብና በመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ፊት አብራው ተመርቃለች፡፡
እንደወጣት ማንዴላ ገለፃ፤ በመመረቂያ ሥራው ያበረከታት ይህችው ተሽከርካሪ ከሌሎች የሚለያት አንድም ከሞተር ሳይክል ከተወሰደ ሞተር መሠራቷ ሲሆን፤ ሌሎች አካሏም በቀላል ዋጋ መገጣጠም መቻሏ ነው፡፡ አጠቃላይ ወጪዋም 70 ሺ ብር አይበልጥም፡፡ ይህም በአሁኑ ወቅት አንድ ባጃጅ ለመግዛት አገሪቱ ከምታወጣው 140ሺ ብር አኳያ ሲነፃፀር በግማሽ ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም የውጭ ምንዛሪን በመታደግ ረገድ የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡
ወደፊት በፋይናንስ የሚደግፈው ካገኘ ተሽከርካሪውን የበለጠ በማዘመን ለገበያ በስፋት ለማቅረብ አልሟል፡፡ በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የከተማዋ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ መጠነኛ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና ዩኒቨርሲቲው ለቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚመደብለት በጀት ባለመኖሩ የምርምር ሥራዎች ለህብረተሰቡ በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል መቸገሩን ያነሳል፡፡ በዚህም ምክንያት የምርምር ሥራዎች የሼልፍ ላይ አድማቂዎች እንዳይሆኑ ስጋት ያለ መሆኑን ጠቅሶ፤ የሚመለከታቸው አካላት ለእርሱ መሰል ወጣት ተመራማሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ነው የሚጠይቀው፡፡
ወጣት ማንዴላ ዋጋ ከፍሎ የሰራት ተሽከርካሪ እውን ሆና ማየቱ በራሱ ትልቅ የአዕምሮ እርካታ እንደፈጠረለት ያስረዳል፡፡ «ከኪሴ ያወጣሁት ወጪም ሆነ ሳልተኛ ያደርኩበት ጊዜ አሁን ላይ ምንም ትዝ አይለኝም፤ የእኔ ትልቁ ትርፍ ልክ እንደወላጅ ሁሉ አይኔን በአይኔ ማየቴ ነው» ሲል ይገልፃል፡፡ ለዚህ ያበቃውም ቁልፉ ምስጢር አስቀድሞ መክሊቱን ለይቶ ከግብ እንዲደርስ ያለመታከት መስራቱን ነው፡፡ በዚህም ካፒታሉን ከአምስት ሺ ተነስቶ አሁን ላይ 1ነጥብ 5ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም ያሉትን ሁለት ተሽከርካሪዎችና ማሽኖቹን ሳይጨምር እንደሆነ ነው የጠቀሰው፡፡
«በእርግጥ» ይላል ወጣቱ ስለ አላማ ፅናትና ግብን መምታት ሲናገር፡፡ «በእርግጥ ማንኛውም ወጣት ትልቅ ራዕይ ቢኖረውም ከጎኑ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አያጣም፤ በተለይ ራዕዩን ተረድቶ የሚደግፍ ማግኘት አዳጋች ሊሆንበት ይችላል» ይላል፡፡ ነገር ግን ችግሮችን ሁሉ በፅናት ማለፍ ከቻሉ የማይደረስበት ነገር እንደሌላ ያምናል፡፡ በመሆኑም ልክ እንደእርሱ ሁሉ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች የትዕግስት ፍሬ ጣፋጭ መሆንዋን ተገንዝበው የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮት በፅናት ሊጋፈጡት እንደሚገባ ነው የመከረው፡፡
ወጣት ሰላማዊት ወልደሚካኤልም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ካስመረቃቸው ተማሪዎች አንዷ ናት፡፡ ወጣቷ በተከታታይ ሦስት ዓመታት በትጋት በማጥናቷ 3ነጥብ 98 በማምጣት ከሁሉም ተማሪዎች በመላቅ የዓመቱን የወርቅ ሜዳሊያም ሆነ ዋንጫ ወስዳለች፡፡
ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሲዳማ ዞን ይርጋለም ከተማ ውስጥ ተወልዳ ማደጓን የምታስረዳው ወጣት ሰላማዊት ቤተሰቦቿ እንደአብዛኛው የገጠር ነዋሪ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አርሶአደሮች መሆናቸውን ትገልፃለች፡፡ «ቤተሰቦቼ ምንም እንኳ ቀለም የቀሰሙ ቢሆኑም ገፍተው ባለመማራቸው ምክንያት ኑራቸው ከእጅ ወደ አፍ የሚባል ዓይነት ነበር» ትላለች፡፡ ይህ ቁጭት ያሳደረባቸውም የሰላማዊት ቤተሰቦች ታዲያ አቅማቸውን ሁሉ አሟጠው ልጆቻቸውን ተግተው ያስተምራሉ፡፡ በተለይም አባቷ ልዩ ክትትልና ድጋፍ ያደርጉላት እንደነበር ትጠቅሳለች፡፡
ሴት ልጅ በመሆንዋ ምክንያት ብቻ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ በቤት ውስጥ የማይደርስባት መሆኑን የምትገልፀው ወጣት ሰላማዊት መላ ትኩረቷን ትምህርቷ ላይ ብቻ እንድታደርግም ይገፋፏት እንደነበር ታስረዳለች፡፡ « እነርሱ ተምረው ምንም ሳላላገኙ ያጡትን ነገር በእኔ የማየት ፍላጎት ስለነበራቸው ከትምህርት ቤት እንደመጣሁ ምንም ሥራ አልታዘዝም፤ ይልቁንም እንዳጠና ብቻ ነው የሚያስገድዱኝ» ትላለች፡፡ ይህም አወንታዊ ጫና በአንደኛ ደረጃም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ሰቃይ ተማሪ ሆና እንድትዘልቅ ትልቅ ሚና መጫወቱን ታስረዳለች፡፡ አሁን ለደረሰችበት ስኬትም የወላጆቿ ሚና ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ታምናለች፡፡
ወጣት ሰላማዊት እንደምትገልፀው፤ ምንም እንኳን የሁለተኛ ደረጃ እስከምታጠናቅቅ ድረስ ተሸላሚ ተማሪ ብትሆንም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ተፈትና ውጤቷ የጠበቀችውን ያህል ሆኖ አላገኘችውም፡፡ ይህም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ በፈለገችው የትምህርት ዘርፍ እንድትማር እንቅፋት ስለሆነባት በወቅቱ ልቧ ክፉኛ ተሰብሮ እንደነበር አትሸሽግም፡፡ «የግብርና ትምህርት ክፍል ሲደርሰኝ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ ነገር ግን ያለኝ አማራጭ ያገኘሁትን መውደድ ስለነበር የተመደብኩበትን የግብርና ትምህርት መስክ ለመውደድ ተገደድኩ» ትላለች፡፡
በትምህርት ክፍሉ ደግሞ «አግሪካልቸራል ቢዝነስ» ዘርፍ የተሻለ መስሎ ስለታያት ቀዳሚ ምርጫዋ አድርጋው ባለፉት ሦስት ዓመታት በትጋት በማጥናት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ «በዚህ ትምህርት ክፍል ከገባሁ በኋላ የፈራሁትን ያህል መጥፎ ሆኖ አላገኘሁትም፤ እንዳውም ትምህርቱን እየወደድኩት ሦስቱንም ዓመት በፍቅር ነበር የተማርኩት፡፡ በዚህም አመለካከቴ ሁሉ ተቀየረ» በማለት ትገልፃለች፡፡
የወጣቷ የመመረቂያ ሥራ ዋና መጠንጠኛ በአርባ ምንጭ ከተማ ዙሪያ ባሉ ቲማቲም አምራች ገበሬዎች ዙሪያ ሲሆን፤ በዋናነትም አርሶአደሮቹ በሚያመርቱት የቲማቲም ምርት ለምን ተገቢ ጥቅም እንዳላገኙና በገበያ ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ቁልፍ ተግዳሮቶች ምን እንደሆኑ ይዳስሳል፡፡ «በጥናቴ በዋናነት የለየሁት አንዱ ጉዳይ ከአርሶ አደሮች ይልቅ በገበያው ሰንሰለት ላይ ያሉ ደላሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ቲማቲም በባህሪው ቶሎ የሚበላሽ በመሆኑ ደላሎቹ ማሳው ድረስ መጥተው በሚያቀርቡላቸው የወረደ ሂሳብ ሳይደራደሩ የሚሸጡበት ሁኔታ መኖሩን አይቻለሁ» ትላለች፡፡
በሌላ በኩልም አካባቢው አብዛኛው ፍራፍሬ አምራች እንደመሆኑ ቲማቲምን እንደተደራቢ ሰብል በማየት ለምርቱ ጥራትና ብዛት እምብዛም ትኩረት እንደማይሰጡ ትገልፃለች፡፡ እንዲሁም ምንም እንኳ የአካባቢው ስነምህዳርና የአየር ፀባይ ምቹ ቢሆንም መሬቱ በተባይ የሚጠቃ በመሆኑ ምርትና ምርታማነቱን ይዞት መቆየቱን በጥናቷ ለማረጋገጥ ችላለች፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል በምን መልኩና እንዴት አርሶአደሮቹን ሊደግፍ እንደሚገባ ምክረሃሳቧን በመጠቆም ያከናወነችው ይኸው የመመረቂያ ሥራ በዩኒቨርሲቲ ምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘቱ ለሽልማት አሳጭቷል፡፡
የሰላማዊት የወደፊት ህልሟ በተለይም የገበሬ ልጅ እንደመሆንዋ የወላጆቿን የግብርና ሥራ ማዘመን ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የምታመርታቸው ምርቶች በገበያው ላይ ተወዳዳሪ ይሆኑ ዘንድ አዳዲስ አሰራሮችን ለመከተል አቅዳለች፡፡ በዚህም የእርሷንም ሆነ የቤተሰቦቿን ህይወት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ቆርጣ ተነስታለች፡፡ ለጋነቷም ሆነ ሴትነቷ ሳይበግራትም በአገሯ ኢኮኖሚ ላይ የበኩሏን ድርሻ ለመወጣትም ፅናትን ሰንቃ ይዛለች፡፡
ልክ እንደዚህ ሁለት ወጣቶች ሁሉ ሌሎች የአገሪቱ ወጣቶች ህልማቸውን ለማሳካት መትጋትና በአገራቸው ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ የየራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብርታትና ፅናትን መላበስ ይጠይቃል፡፡በተለይም የውስጣቸውን ጥሪና መክሊታቸውን በማዳመጥ መንግሥት ለወጣቶች ያመቻቸውን ልዩ ዕድል ሳያቅማሙ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ ወላጆች፣ ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎችም ቢሆኑ የነገ አገር ተረካቢ ትውልዶች መሆናቸውን ተገንዝበው የወጣቶችን ራዕይ ከግብ ለማድረስ ከጎናቸው መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

Published in ማህበራዊ

ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ያጋጠመውን የዳቦ ስንዴ ዱቄት እጥረት ለመፍታት መንግስት እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ገበያን የማረጋጋት ኃላፊነት ያነገበውና በንግድ ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ከብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የስንዴ ክምችት የዳቦ ስንዴ በመውሰድ የተፈጠረውን እጥረት ለመቅረፍ ለዱቄት አምራቾች በዝቅተኛ ዋጋ ለማቅረብ ተገዷል፡፡
በዚህም የተከሰተውን የዳቦ እጥረት ችግር በመጠኑ ለማስታገስ ቢቻልም አሁንም የዳቦ አቅርቦት ቤቶች አልተቀረፈም፡፡ ወረፋው አልቀረም፡፡ የዳቦ መጠን መቀነሱን ሸማቾች ይናገራሉ፡፡ ችግሩ በአዲስ አበባ በስፋት ይስተዋላል፡፡ በክልል ከተሞችም መሰል ችግሮች መከሰታቸውን ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡
የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ መሰረት መንግስቱ በአዳማ ከተማ በተለምዶ ዮሐንስ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ ዳቦ የቤተሰባቸው የእለት ተእለት ምግብ ነው፡፡ ከሚያዝያ ወር ወዲህ ዳቦ ማግኘት አዳጋች ሆኖ መቆየቱን ያነሳሉ፡፡ በብዙ ልፋት ከተማዋ ውስጥ ዳቦ ቢገኝ እንኳን ለማግኘት ረጅም ወረፋ መጠበቅ ግድ ነው፡፡ የዳቦ መጠን መቀነሱን ያወሱት ወይዘሮ መሰረት ከሁለት ወራት ወዲህ ያጋጠመው የዳቦ እጥረት በኑሯቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን ያነሳሉ፡፡ ዳቦ ለማግኘት ሰዓታት ወረፋ ከመጠበቅ ጀምሮ ከሌሊቱ 10 ሰዓት የዳቦ ወረፋ ለመያዝ የወጡበት ቀን እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ወረፋ መጠበቁ የሰለቻቸው ወይዘሮ መሰረት ለተወሰኑ ጊዜያት ከዳቦ ቤቶች የሚገዛውን ዳቦ በመተው ስንዴ ገዝተው አስፈጭተው ራሳቸው ዳቦ እየደፉ ሲጠቀሙ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ሳምንት በዳቦ ቤቶች አካባቢ የሰልፉ ወረፋ ስለቀነሰ ዳቦ ቤት ለመግዛት የመጡ ሲሆን ሆኖም የዳቦው መጠን መቀነሱን ተናግረዋል፡፡
የዳቦ ዱቄትና ዳቦ በማምረት የታወቀው የሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ የአዳማ ቅርንጫፍ ስራ አሥኪያጅ አቶ ፍስኃ ነጋ ከዚህ ቀደም ለዳቦ ዱቄት የሚሆን ስንዴ ከመንግስት በዝቅተኛ ዋጋ ይቀርብ የነበረ ሲሆን ድርጅቱም ለሸማቹ ዳቦ በዝቅተኛ ዋጋ ሲያቀርብ ኖሯል፡፡ ከሚያዚያ 2010 ዓ.ም ወዲህ የዳቦ ስንዴ እጥረት በማጋጠሙ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ዳቦና ዱቄት ለማምረት አለመቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ ከአዳማ ውጭ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የፋብሪካው ቅርንጫፎችም የአቅማቸውን ያህል እያመረቱ አይደለም፡፡
ከመንግስት እየቀረበ የነበረው የስንዴ ኮታ ከሁለት ወራት ወዲህ ቀንሶአል፡፡ ስንዴ በጊዜ እየቀረበ አለመሆኑን ያነሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በቀን እስከ 450 ኩንታል የዳቦ ዱቄት የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት በቀን 300 ኩንታል ብቻ ለማምረት ተገዷል፡፡ ማምረት ከነበረበት 150 ኩንታል ቀንሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ድርጅቱ ለዳቦ ፈላጊው ሕብረተሰብ በበቂ ደረጃ ማቅረብ አልቻለም፡፡ ሕዝቡ ከሌሊቱ 9፡00 ጀምሮ ወረፋ የሚጠብቅበት ጊዜ መኖሩንም ይናገራሉ፡፡
አቶ ፍስኃ እንደሚያብራሩት፤ አንዳንድ ወቅት ለፋብሪካው መቅረብ ካለበት ድርሻ ከግማሽ በታች የሚቀርብ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ በጣም ዘግይቶ መቅረቡ ሸማቾች በዳቦ እጥረት እንዲቸገሩ ከማድረጉም በላይ ፋብሪካው ስራ ሳይሰሩ ለሰራተኞቹ ደሞዝ እየከፈለ አስፈላጊ ላልሆነ ወጪ ተዳርጓል፡፡ የሚቀርበውን ውስን ስንዴ እየቆጠበ ምርቱ እንዳይቋረጥ እስካሁን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ መልኩ የስንዴ አቅርቦት ችግር የሚቀጥል ከሆነ ፋብሪካው ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ምርቱን ያቆማል፡፡
ኃላፊው በግንቦት ወር የቀረበውን ጥቂት ስንዴ በቁጠባ በመጠቀም እስካሁን ድረስ ፋብሪካው ዱቄትና ዳቦ እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡በአንድ ጊዜ አልቆ ድርጅቱ እንዳይዘጋ በጥንቃቄ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ፋብሪካው በሙሉ ኃይሉ እየሰራ ባለመሆኑ ትርፋማነቱ ላይ የራሱን አሻራ አሳርፎአል፡፡
በስንዴ እጥረቱ ምክንያት እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት ለመንግስት ሪፖርት ማድረጋቸውን ለንግድ ሚኒስቴር ተደጋጋሚ ደብዳቤ መጻፉን ጭምር ገልጸዋል፡፡ የሚቀርበው ስንዴ በቂ አለመሆኑን በጊዜ እየቀረበ እንዳልሆነ ለንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የአዳማ ቅርንጫፍና ለዋናው የአዲስ አበባ ቢሮ አመልክተዋል፡፡
መንግስት የስንዴ አቅርቦት ችግርን ከፈታ ፋብሪካው መብራት ቢቋረጥ እንኳን ጄኔሬተር በመጠቀም 24 ሰዓት በመስራት ከዚህ ቀደም ለሸማቹ ዳቦ ለማቅረብ ያደርግ የነበረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በስንዴ አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች የሚቀረፉ ከሆነ ድርጅቱ ቅርንጫፎችን የማስፋፋት እቅድ እንዳለው ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በቢሾፍቱ የሚገኘው አዋሽ ዱቄትና ብስኩት ፋብሪካ ተወካይ አቶ ደሳለኝ በቀለ በበኩላቸው፤ ፋብሪካቸው ለንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ቅድመ ክፍያ የፈጸመ ቢሆንም ኮርፖሬሽኑ የስንዴ እጥረት ስላለበት ስንዴን ማቅረብ አለመቻሉን ያነሳሉ፡፡ ከግንቦት ወር እስከ ሰኔ ማብቂያ አንድ መኪና ብቻ ስንዴ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ስንዴ በወቅቱ ባለመቅረቡ በቢሾፍቱ ነዋሪ ብሎም በፋብሪካው ላይ አደጋ ተደቅኗል፡፡ በከተማዋ በርካታ የዳቦ ዱቄት የሚፈልጉ ዳቦ ቤቶችና ሸማቾች አሉ፡፡ ፋብሪካው በዳቦ እጥረት ሳቢያ ፍላጎታቸውን ማሟላት አልቻለም ብለዋል፡፡
ኃላፊው በስንዴ እጥረት ምክንያት በግንቦት ወር ለፋብሪካው መቅረብ ከነበረበት ኮታ አንድ አራተኛ ብቻ እንደቀረበ ይናገራሉ፡፡ ከሰኔ ወር ጀምሮ ምንም ሊቀርብ አልቻለም፡፡ ለአንድ ወር ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ስራውን አቁሟል፡፡ ሆኖም ያለስራ ያለምርት ለሰራተኞች ደሞዝ ይከፍላል፡፡ በዚህም ፋብሪካው ለጉዳት እየተዳረገ መሆኑን አቶ ደሳለኝ ይገልጻሉ፡፡
በቅርቡ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ከጅቡቲ ካስመጣው ስንዴ ውስጥ 400 ኩንታል የደረሳቸው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ደሳለኝ፤ ፋብሪካቸው ይህን ስንዴ ፈጭቶ ዳቦና ዱቄት ለሸማቹ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም አቅርቦቱና ስርጭቱ ባለመመጣጠኑ የተነሳ የከተማዋን ፍላጎት እንደማያሟላ ይገልጻሉ፡፡ በከተማዋ ያሉት ሌሎች ዱቄት አምራች ፋብሪካዎች በስንዴ እጥረት ሳቢያ ዱቄትና ዳቦ ማምረት ማቆማቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በወላይታ ሶዶ የአወል ሸረፈዲን ዱቄት ፋብሪካ የምርትና ቴክኒክ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ እንዳሻው ኃይሌ በበኩላቸው ከጅቡቲ የሚመጣውን ስንዴ በመጠባበቅ በአዳማ ከተማ ከ50 ቀን በላይ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ ወላይታ ሶዶ ደርሰው እንዳይመለሱ ከዛሬ ነገ ወረፋ ደርሶ ስንዴ እወስዳለሁ በሚል ተስፋ በመጠባበቅ ራሳቸውንና ፋብሪካውን አስፈላጊ ላልሆነ ወጪ እየዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ስራ ማቆሙን የሚናገሩት አቶ እንደሻው ስንዴ ከዛሬ ነገ ይመጣል በሚል ተስፋ ለሠራተኞቹ ደሞዝ እየከፈለ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሆሳዕና ከተማ የሚገኘው የሀዲያ ሊቻ ዱቄት ፋብሪካ ተወካይ አቶ ተስፋዬ ሱለንቆ፤ ፋብሪካው በሆሳእና ከተማ ላሉት ዳቦ ቤቶች ዱቄት ከመሸጥ ባሻገር በዞኑ ለሚገኙ ወረዳዎችም የዳቦ ስንዴ ያቀርባል፡፡ከቅርብ ወራት ወዲህ በተከሰተው የስንዴ እጥረት የተነሳ ፋብሪካው የሚጠበቅበትን ማምረት አልቻለም፡፡ከግንቦት ወር ወዲህ አንዴ ብቻ ከመንግስት ስንዴ እንደወሰዱ ይናገራሉ፡፡ ከግንቦት 12/2010 ጀምሮ ከሆሳእና አዳማ ከተማ በመመላለስ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡በግንቦት ወር ለፋብሪካው በቂ ኮታ አልወሰዱም፡፡የሰኔ ወር ኮታ በተባለበት ቀን አዳማ ሊደርስ ባለመቻሉ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሀዲያ ዞን ስንዴ በስፋት ይመረትበታል፡፡ከፍተኛ የስንዴ ክምችት አለ፡፡መንግስት ከሚያቀርበው ዋጋ ጋር ከፍተኛ ልዩነት ስላለው የአካባቢውን ስንዴ ገዝቶ ለመጠቀም አልተቻለም፡፡የአካባቢው ስንዴ መቶ ኪሎ 1400 እየተሸጠ መንግስት የሚያቀርበው ግን 500 ብር ነው የሚሸጠው፡፡
በንግድ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንደሚሉት በተያዘው በጀት ዓመት የትራንስፖርት፣ የአውራጅ፣ የጫኝ፣የማሸግና ሌሎች ወጪዎችን መንግስት ሸፍኖ ለስንዴ ዱቄት አምራች ፋብሪካዎች ሰባት ነጥብ 12 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማቅረብ አቅዶ ነበር፡፡ ከሰባት ነጥብ 12 ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ አራት ሚሊዮኑን ከውጭ የማስገባት እቅድ ነበረው፡፡ ከውጭ የሚገባው የአራት ሚሊዮን ኩንታል የግዢ ሂደት እስከ ታሕሳስ ማለቅ ነበረበት፡፡ አራት ሚሊየን ኩንታል የዳቦ ስንዴ ተገዝቶ እንዲገባ የፌዴራል ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ለፌዴራል ግዥ ኤጀንሲ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ስፔስፊኬሽንና ጨረታ ወጥቶ የግዢ ሂደት ላይ በነበረበት ሁኔታ ላይ ተጫራቾች ማሟላት ያለባቸውን መስፈርት ማሟላት ባለመቻላቸው ሁለት ጊዜ ጨረታው ውድቅ ተደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት መግባት የነበረበት ስንዴ ሀገር ቤት ሳይገባ ቀርቷል፡፡ እስከ መጋቢት ድረስ ስንዴ ሀገር ቤት ባለመግባቱ የተነሳ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ የስንዴ አቅርቦት እጥረት ተከስቷል፡፡ በዚያም ምክንያት የዳቦ እጥረት መከሰቱን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
አቶ ወንድሙ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የእህል ክምችት ስንዴ በመውሰድ ለዱቄት አምራቾች እንዲቀርብ መደረጉን ይናገራሉ፡፡ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በሚደረገው ጉዞ ላይ በተፈጠረው የትራንስፖርት መጓተት ምክንያት ለፋብሪካዎች በወቅቱ ለማቅረብ አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ከውጭ የገዛው አራት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ ሀገር ቤት በመግባት ላይ ይገኛል፡፡ ከአራት ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ ሁለት ሚሊዮን ተገዝቶ በአሁኑ ወቅት ሀገር ውስጥ ገብቶአል፡፡ ከዚህ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ጭነቶች ከጅቡቲ ኢትዮጵያ ገብተው በየአካባቢው ለሚገኙ ዱቄት አምራች ፋብሪካዎች በመከፋፈል ላይ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ዙር ለሚገባው ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ደግሞ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊ ተለይቶ ውል መፈጸሙን ነው ያብራሩት፡፡
ወቅቱ የመኸር ወቅት ስለሆነ ከፍተኛ ማዳበሪያ ከውጭ የሚገባበት ነው፡፡ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓጓዝ ማዳበሪያ ቅድሚያ እንዲሰጠው በመወሰኑ የተነሳ ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የትራንስፖርት ችግር መፈጠሩን አንስተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ማዳበሪያ የማጓጓዝ ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን፤ከአሁን በኋላ ስንዴን የማጓጓዙ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ፤ በዚህም መሰረት የዱቄት አምራቾችንና የዳቦ ሸማቹን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ በቅርቡ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት መልስ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃ እጥረትን አስመልከቶ በሰጡት ምላሽ ስንዴን ጨምሮ በተለያዩ የፍጆታ እቃዎች ላይ ለሚስተዋለው እጥረት ምክንያቱ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ለዚህም ስንዴን የመሳሰሉ የምግብ ምርቶች በሀገር በብዛት ማምረት እንደሚያስፈልግ ነው ያብራሩት፡፡ የዜጎችን የመግዛት አቅም ማሳደግ እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

መላኩ ኤሮሴ

Published in ኢኮኖሚ

ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ባህሬንና ግብጽ እ.አ.አ ሰኔ 5 ቀን 2017 አንድ አቋም በመያዝ «ኳታር አሸባሪዎችን ትደግፋለች፤ ለቀጣናውም ስጋት ነች» በሚል ሰበብ የዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ መወሰናቸው ይታወሳል፡፡ በአየር፣ በየብስና በባህር የሚደረገው ግንኙነትም ይብቃን ብለዋል፡፡ ይህ ውሳኔ ወትሮም ባለመረጋጋት ለሚታወቀው ቀጣና ተጨማሪ የውዝግብ ምክንያት ሆኗል፡፡ ለሁለት ጎራ ከፍለው የሚወዛገቡት አገራት እያደር በየፊናቸው አቋማቸውን የሚደግፉላቸውን ከጎናቸው ለማሰለፍ በርካታ ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ የምስራቅ አፍሪካዋ ሶማሊያ በዚህ ረገድ በሁለቱ ጎራዎች የምትፈተን አገር ስትሆን፤ ጉዳዩ ጫና እያሳደረባት እንደሚገኝና አንድነቷን ለማስመለስ የምታደርገውን ጥረት አደጋ የሚጋረጥበት ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡
ዩሮ ገልፍ ኢንፎርሜሽን ሴንተር የተባለው ድረ ገጽ ከሰሞኑ እንደዘገበው፤ ለዓመታት መረጋጋት የተሳናት ሶማሊያ በሁለቱ ጎራ የተሰለፉት አገራት የእነርሱን መንገድ እንድትከተል የሚራኮቱባት ሥፍራ ሆናለች፡፡ ዘገባው እንደሚያብራራው፤ በምስራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲክስ ቁልፍ ሚና የምትጫወተውን ሶማሊያ የገልፍ አገራቱ የየራሳቸው ደጋፊ ለማድረግ ቢሞክሩም፣ ሞቃዲሾ እስካሁን ይፋዊ በሆነ መልኩ ገለልተኝነትን መርጣለች፡፡
ሶማሊያ በይፋ የገለልተኝነት አቋም ብታራምድም፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ (በቅጽል ስማቸው ፎርማጆ) ከኳታር ወገን መቆማቸውን የተለያዩ ማስረጃዎች በማጣቀስ ድረ ገጹ ይተነትናል፡፡ በብዙ አገራት እውቅና ያልተሰጣቸው ሶማሌ ላንድና ፑንት ላንድ በበኩላቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሳዑዲ አረቢያና በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በዋናነት ከሚመራው ጎራ መሰለፋቸውን ያትታል፡፡
በአገራቱ መካከል ቀውሱ እንደተፈጠረ ሶማሊያ ከኳታር ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥ ግፊት ለማድረግ ሳዑዲ አረቢያ የ80 ሚሊዮን ዶላር ስጦታ አቅርባላታለች የሚለው ከዓመት በፊት የተሰራጨ መረጃ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ግን በወቅቱ ገለልተኛ መሆንን መርጠዋል፡፡
ይሁንና ፎርማጆ በአገሪቱ ለሚያካሂዱት ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ዘመቻ ከኳታር የገንዘብ ድጋፍ መቀበላቸውና ቀደም ሲል የአልጀዚራ ቴሌቪዥን ባልደረባ የነበረውንና ከዶሃ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚገመተውን ፉአድ ያሲንን በኤታማጆር ሹምነት ከጎናቸው ማሰለፋቸው ገለልተኛ ስለመሆናቸው ጥርጣሬ የሚያስነሳ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በይፋ ባይገለጸም ጉዳዮቹ የሳዑዲ አረቢያንና የዩናይትድ አረብ ኢምሬትስን ጎራ ገለል በማድረግ ከኳታር መወገናቸውን ያሣያል አስብሏል፡፡
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ፎርማጆ ከኳታር ወገን መሆናቸውን የሚያሳዩ ሌሎች መረጃዎች መኖራቸውን ዩሮ ገልፍ ኢንፎርሜሽን ሴንተር የተለያዩ መረጃዎችን በማቅረብ ያስረዳል፡፡ ፎርማጆ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኳታር ሁለት ጊዜ ያቀኑ ሲሆን፤ ከወዲያኛው ጎራ ወደ የተሰለፈችው የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ግን አንድም ጊዜ አልሄዱም፡፡ ኳታር በበኩሏ ከአገሪቱ ጋር የፈጠረችውን መልካም ግንኙነት በመጠቀም ጎረቤቶቿ በነፈጓት የአየር ክልል ምትክ ሶማሊያን እንደ መልካም አጋጣሚ መገልገል ችላለች ይላል ዘገባው፡፡
በሳዑዲ አረቢያና በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ የሚመራው ጎራ ሶማሊያ ከኳታር ጋር ግንኙነትዋን እንድታቋርጥ ሙከራ አድርጎ ያለ ውጤት ከቀረ በኋላ ሞቃዲሾ በተለይ ከአቡዳቢ ጋር ያላት ግንኙነት ተቀዛቅዟል፡፡ በሶማሊያ አካባቢ ያላትን መሰረት ማጣት ያልፈለገችው ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስም፤ ኳታር ከማዕከላዊ መንግሥት የፈጠረችውን ወዳጅነት ሚዛን ይጠብቅልኛል በማለት ከሶማሌ ላንድ እና ከፑንት ላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር መርጣለች፡፡
ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ አላማዋን ለማሳካት በሶማሌ ላንድ በርበራ ወደብ ላይ ለየመንና ለኤደን ባህረ ሰላጤ ቅርብ በሆነ ስትራቴጂክ ሥፍራ ላይ ወታደራዊ ቤዝ መገንባት ጀምራለች፡፡ ይህን ተከትሎ ሞቃዲሾ እንደ ግዛትዋ በምትቆጥረው ሶማሌ ላንድ የተጀመረው ወታደራዊ ቤዝ ግንባታ ‹‹አገራዊ አንድነቴ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ስለመጣሱ ማሳያ ነው›› በማለት ተቃውሞ አቅርባለች፡፡
ሶማሊያ ሉአላዊነቴ በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ እየተጣሰ ነው የሚል ክስ ብታቀርብም፤ ኳታር በበኩሏ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ከሶማሌ ላንድና ከፑንት ላንድ ጋር በመቀራረብ ስትራቴጂክ ሥፍራዎችን ለመቆጣጠር ገንዘብ እየረጨች ነው፤ የእነርሱ ድጋፍ ይቅርባችሁ በማለት ቅስቀሳ እንደምታደርግ ይነገራል፡፡ ይሁንና እራሷ ኳታር በሶማሌ ላንድ ከምትገነባው ወታደራዊ ቤዝ ውጭ የደህንነት ጉዳይ ግድ ይለኛል በሚል ሰበብ በጅቡቲና በኤርትራ ጦሯን ለማስፈር በመሞከር ትከሰሳለች፡፡
በምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር መሰረቷን በማስፋት የራሷ ጥቅም ለማስጠበቅ ጥረት በማድረግ ላይ ያለችው ሌላዋ አገር ውግንናዋና ከኳታር ጋር ማድረጓ የሚነገርላት ቱርክ ናት፡፡ ቱርክ በአካባቢው ሰብዓዊ እርዳታና ኢኮኖሚያው ትስስርን መሰረት ያደረገ ግንኙነት መመስረት ፍላጎቷ መሆኑን ብታሳይም፤ እ አ አ በ2017 በሶማሊያ ከአገሯ ውጭ ትልቅ የተባለውን ወታደራዊ ቤዝ ይፋ አድርጋለች፡፡
ጎራ የለዩት አገራት በዚህ መልኩ ተጽዕኗቸውን በሶማሊያ ለማሳረፍ ሲረባረቡ ቆይተው፤ አሁን ሞቃዲሾ አሰላለፏን እንድትለይ የተለየ መንገድ መከተል መጀመራቸውን አልጀዚራ በአለፈው ሳምንት በድረ ገጹ ባሰፈረው ዘገባ አትቷል፡፡ እንደ ዘገባው ሳዑዲ አረቢያና በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ለሶማሊያ ያደርጉት የነበረውን የበጀት ድጋፍ አቋርጠዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ተገቢ አይደለም የሚል ውግዘት እየገጠመው ነው፡፡ መቀመጫውን በቤልጂየም ብራሰልሰ ከተማ ያደረገው የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው የአቋም መግለጫው፤ ሁለቱ አገሮች ሶማሊያ በገልፍ አገራት ውዝግብ ገለልተኛ አቋም በማራመዷ ያደርጉት የነበረውን የበጀት ድጋፍ ማቋረጣቸው የሚወገዝ ተግባር ነው፡፡
‹‹በሁለቱ ጎራዎች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የሶማሊያ መንግሥት ገለልተኛ አቋም ስታራምድ ቆይታለች፡፡ ይሁንና ሳዑዲ አረቢያና ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ለአገሪቱ ያደርጉ የነበረውን መደበኛ የበጀት ድጋፍ አቋርጠዋል›› የሚለው የምክር ቤቱ መግለጫ ይህም በሂደት አገሪቱ ለፀጥታ ኃይሉ የምትከፍለውን ደመወዝ በተመለከተ አቅሟ እየተፈተነ አሸባሪዎች እንዲያገግሙ በር ይከፍታል፡፡
ዩሮ ገልፍ ኢንፎርሜሽን ሴንተር ድረ ገጽ እንዳሰፈረው የገልፍ አገራት በምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር የሚያደርጉት ሽኩቻ ለአገሪቱ መከፋፈል ወሳኝ አስተዋጽኦ ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን አካባቢውን በውጥረት የተሞላ ማድረጉ አይቀርም፡፡
ሶማሊያ በቅድሚያ የውስጥ ፖለቲካዊ ውዝቧን ማብረድና አገራዊ አንድነቷን ለማጠናከር በቂ እርምጃዎች መውሰድ አለባት፡፡ አገሪቱ ይህን ካደረገች ከአሸባሪዎችና ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር የሚደረገው ፍልሚያ ቀላል ነው፡፡ የአገሪቱ መንግሥት ከአልሸባብ የበለጠ ለህብረተሰቡ ዋጋ እንዳለው ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ይሁንና ፖለቲካዊ ሽኩቻ፣ ሙስና መሰረታዊ አገልግሎ ለማቅረብ አለመቻሉ እምነት እንዲታጣበት አድርጓል፡፡ ሶማሊያ በተለያዩ ጎራ በፈጠሩት የገልፍ አገራት የመከፋፈል አደጋ ቢጋረጥባትም ውስጣዊ መረጋጋቷን ካረጋገጠች ለቀጣናው ብሎም ለአህጉሩ ዕድገት ጥሩ ዕድል ይሆናል፡፡
የገልፍ አገራቱ በምስራቅ አፍሪካ የሚያደርጉት ፉክክርም የራሳቸውን ጥቅም ማስጠበቅን ያለመ ቢሆንም፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሌሎች የቀጣናውን ሉአላዊ አገራት መንካቱ እንደማይቀር ይታመናል፡፡ በዚህ ሂደት ኢትዮጵያም በዙሪያው የሚደረገውን እንቅስቃሴ በንቃትና በጥንቃቄ እንድትመለከት ይመክራል፡፡

ዳንኤል በቀለ

Published in ዓለም አቀፍ
Thursday, 12 July 2018 17:04

እናመሰግናለን !

ገንዘብ ለሰጠ ገንዘብ ይመለሳል፤ ከሀብቱ ላካፈለም ቆይተው ካፈሩት ሀብት መልሰው ይሰጡታል። አንዳንዴ ግን ከምስጋና ውጪ ምንም ሊሰጠው የሚችል ስጦታ፣ ሊውሉለት የሚችሉት ውለታ የሚታጣለት ሰው ይመጣል። ይሄኔም አንድ ቃል ብቻ ሁሉን የሚሸከም ይመስለናል፤ እናመሰግናለን !
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አሕመድ ገና ከመግቢያቸው ማመስገን መሰልጠን መሆኑን አሳይተውናልና፤ እኛም እናመሰግናቸዋለን። በአካል ስላሳዩን፣ በመንፈስም ስላስገኙልን ከፍታ እናመሰግናለን። ላስጨበጡን ተስፋ፣ ለሰጡን መፅናናት እናመሰግናለን። እውን ስላደረጉት ህልማችን እናመሰግናለን፣ ከመደመር ስለደመሩን፣ ከመከፋፈል ስላተረፉን እናመሰግናለን። አገር የሚያህል ፍቅርን ስላየንባቸው፣ ከወንድም ከእህቶቻችን ስላገናኙን፣ ለመርከቢቱም መዳን ምክንያት ስለሆኑ እናመሰግናለን!
እርሳቸው፣ ከጎናቸው የነበሩና ያሉ አመራሮችን ሁሉ እናመሰግናለን፤ እነዚህ የእኛ አሸናፊዎች ናቸው። እንደምን ቢባል፤ እኛ ልናደርግ ያልቻልነውን አድርገዋል፣ ከከፋ ጥፋትም አትርፈውናል። በእኚህ ሰው ብዙ የኖሩ ህልሞቻችን እውን እየሆኑ ነው። ተዓምር እንዳየ ሰው የሚሆነውን በመደነቅ እናያለን፤ ህልምና እውነታችን ደስ በሚል መልኩ ተቀላቅለዋል።
«ወይ ጉድ!»
ማለት ብቻ ተርፎናል። በዚህ መካከል ከእኛ የሚጠበቀውን አብሮ መቆምና ያንንም በሥራ መግለጽ ሊዘነጋ እንደማይገባ ግን ልብ ይሏል! ታድያ ወደነገሬ ስገባ በሃሳባችን የሚመላለስ፤ ከአሸናፊዎቻችን አንደበት ባይወጣም እኛ ግን ተገልጦ ያገኘነው ብዙ ምክር አለ፤ ስለዛም ሁሉ እናመሰግናለን። እንዲህ ነው፤
አንድ ሰው እልፍ ሊያክል እንደሚችል አሳይተውናልና እናመሰግናለን
ሳውቅና ስሰማ «እስቲ ብቻሽን ምን ታመጪያለሽ? ለብቻ መጮህ ምን ዋጋ አለው?» የሚለው ቃል ተለምዷል፤ ታምኖበታልም። አንድ ሰው ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ስለማይመስለን ችላ ያልነው ስንት ነገር አለ? «እኔ ብናገር ባልናገር! እኔ ብል ባልል! እኔ ብሄድ ብቀር!...» ወዘተረፈ እንላለን፤ ግን አንድ ሰው ዋጋ አለው፤ አንድ ሰው ለውጥ ያመጣል።
አንድ ሰው ነኝና ለውጥ አላመጣም አትበል። አንድ ሰው ነኝና አጃቢ ከሌለኝ ሰው አይሰማኝም አትበል። አጃቢ ሃሳብህን ተከትሎ ይመጣል። አገር የሚያክል ሃሳብ ከያዝክ ብቻህን አይደለህም። እያንዳንዱ የምትሟገትለት ሰው በአንተ ውስጥ አለ። ስለዚህ አስተዋይ ከሆንክ፤ አንተ እንደምታስበው አንድ ሰው አይደለህም። አንድ ሰው እልፍ ሲያክል እያየህ?
በጊዜ ላይ መሰልጠን እንደሚቻል አሳይተውናልና እናመሰግናለን
«አሁን መቼ ልጨርሰው ነው? ጊዜው ይበቃኝ ይሆን? ሃያ ምናምን ዓመት ምን አላት? ይህን ለመሆን ሃምሳ ዓመትም የሚበቃ አይመስለኝም…» ወዘተ ሲባል ሰምተን፤ እኛም ብለን እናውቃለን። ጊዜ መንገደኛ ነዋ! በዘመን ጥሪ እንከፋፍለው እንጂ ጊዜ እንደ ወራጅ ውሃ ፈሰስ እያለ ይሄዳል።
ለካ አጭር የሚባል ጊዜ የለም፤ ጊዜ አያንስም። ምን ያህል ተጠቅመናል ነው ጥያቄው። ጊዜን ስታከብረው ያከብርሀል። ለምሳሌ ሦስት ወር አገር ይሠራበታል፤ በሦስት ወር ታሪክ ይገለበጣል፤ በሦስት ወር የሰርተፍኬት ስልጠና ብቻ ይመስለናል የሚያልቀው? ሰው ኅብረትና አንድነትን ይማራል። በጊዜ ውስጥ ታሪክ አይቀየርም፤ ታሪክማ እንዳለ እየተመዘገበ ነው የሚያልፈው። አዲስ ምዕራፍ ግን ይከፈታል። አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ደግሞ አሁን ያለችው እስትንፋስህ በቂ ናት፤ ብዙ ዘመን አያስፈልግም።
ጊዜ አለህ፤ ጊዜው መኖሩ ብቻ ሳይሆን በቂ ነው። ስትሠራና ትልልቅ ህልም ሲኖርህ ጊዜን ትበልጠዋለህ። ከሰዎች አእምሮ በላይ የምትሆነው ጊዜህን ስትጠቀም ነው። የምትፈልገው ለውጥ አውቀህ ካላዘገየኸው በቀር ረጅም ጊዜን ለመጠበቅ አይታገስም። ሦስት ወር ለአንተ ወይም ለሁላችን ለእኛ ምን ያህል ናት? ትንሽ? እንግዲያው በሦስት ወር አገር ተቀይሯል፣ መልክ ታይቷል፣ ዳመና ተገፍፎ የተስፋ መሰረት ተጥሏል።
በፍቅር የማይቻል ነገር እንደሌለ አስታውሰውናልና እናመሰግናለን
«በምን አቅሜ» ብዙዎቻችን እንላለን። የሰው ልጅ በራሱ ሳይሆን በተላበሳቸው ጸጋዎች ምክንያት ትልቅ አቅም አለው። ወላጆቻቸው በፍቺ ተለያይተው፣ እህትና ወንድም በጥቅም ተባልተው፣ ጎረቤታሞች በነገር ተጣልተው...ሁሉም ነገር የተዘጋ ዶሴ መስሎ የተቀመጠበት ቤት በርካታ ነው። ተመልካችም በፍርሃት አልያም በግዴለሽነት ዝም ብሎ ቆይቶ ይሆናል።
ሰው ያደረገውና መልሶ ሊለውጠው የማይችል ነገር የለም። የተዘጋውን ሁሉ በፍቅር መክፈት ይቻላል። የሰው ልጅ ከተላበሰውና ትልቅ አቅም ከሚሰጠው ጸጋ ፍቅር ኃያሉ ነው። ፍቅር የደነደነ የሚመስልን ልብ ያራራል፣ የጨነቀውን ያለዝባል፣ አገርን አንድ አድርጎ የተዘጋን በር ያስከፍታል።
እናም ‹‹ፍቅር የለም›› አትበል። መኖሩ ምን እንደሚመስል ካወቅህ በአቅምህ ፍቅርን አሳይ። ሁሉም አምርሮ ቢጠላላ ወይም ግዴለሽ ቢሆን አልያም ቢፈራ፤ አንተ ግን እንደምትችል እመን። በዚህ ጊዜ በፍቅር የማይቻል ነገር የለም ብሎ አለማመን እንዴት ይቻላል?
አሸናፊነት ምን እንደሆነ አሳይተውናልና እናመሰግናለን
«ሲያበሳጩ» ብለህ ተናደህ የምትተወው ነገር ብዙ ነው። ሃሳባቸውና ድርጊታቸው ልክ እንዳይደለ ስታውቅ፣ አንድ ሰው ነኝና የሚሰማኝ አይኖርም ብለህ ተስፋ ስትቆርጥ ሁሉን ትተህ ትቀመጣለህ። ትቃወማለህ፣ በተቃራኒ ወገን ትቆማለህ፣ የገዛ ወዳጆችህ ቢሆኑ እንኳ ሃሳባቸው ካልጣመህ ትርቃቸዋለህ። በተቃራኒ ወገን ትቆምና ትሟገታለህ።
ብልህ ስትሆን ደስ ያላለህን ጉዳይ ተቃዋሚ ሳይሆን ቀያሪ ትሆናለህ። አስተሳሰባቸው ጠምሟል ያልካቸውን በርቀት ሆነህ በጥላቻ አታያቸውም፤ ትቀርብና የምትፈልገውን እናም መሆን ያለበትን፣ የዘነጉትን ቀለም ታስይዛቸዋለህ። ማሸነፍ የሚቻለው ከላይ ስለሆኑ አይደለም፤ አንድ አባት እንዳወሱት፤ ሙሴ የተገኘው ከፈርኦን ቤት ነው። ወሳኙ ያለህበት ቦታ አይደለም፣ እንዲኖርህ የመረጥከው አስተሳሰብ ነው።
እውነተኛ አሸናፊዎች ደግሞ በድላቸውና በዋንጫቸው ብቻ ሳይሆን እንዲሁ የሚያስተላልፉት ብዙ መልዕክት አለ። ውስጠ ወይራ እንደምንለው ንግግር ወይም ሀሳብ ውጤታቸው ብዙ ምክር ያዘለ ነው። የደረሱበት ብቻ ሳይሆን የሄዱበት መንገድም ያስተምራል። ጉዳዩ አስተውሎ መመልከትን ብቻ ይጠይቃል።
እነዚህ አሸናፊዎች የምናውቀውን እውነት ገለባብጠው ሌላ እውነት ሹክ ይሉናል። እጅ እንደሌላቸው ዓይናችን እያየ ስዕል ይስላሉ፣ እንጨትን ከሚስማር አዋድደው በእግራቸው ወንበር ይሠራሉ። ዓይናማ ባይሆኑም ለዓይናሞችም መብት ተሟግተው ይረታሉ፤ ልጆች ቢሆኑም ከአዋቂ ይልቃሉ።
ሁላችንንም ባለስልጣን ስላደረጉን እናመሰግናለን
ሰው አንድ አመልካች ጣቱን ወደሌላ ሰው ሲቀስር ሦስቱ ወደራሱ ነው የሚያመለክተው ይባላል። ቀላል ነገር አይደለም ለካ! ገልብጣችሁ እዩት። እንኳን በሀሜት በፍቅርም ቢሆን አንዷ ጣታችን ወደ ሌላ ስታመለክት፤ ሦስቱ የቀሩ ጣቶች በፍቅር ነው ወደ እኛ የሚያመለክቱት።
ስማችን አልተጠራም፣ በክብር እንግድነት አንጋበዝም፣ በዘነጡ መኪናዎች ተሳፍረን በአጀብ አንንቀሳቀስም፣ ከገበታው ቀድመን አናነሳም፣ በተቀመጥንበት መድረክ «ክብርት...ክቡር» አንባልም። ግን አንድ ሰው የሚያመጣውን ለውጥ አይተን፣ ጊዜ በቀመሩ ውስጥ ተዋናይ እንጂ እንቅፋት ሊሆን እንደማይችል ተረድተን፣ ሁላችን ባለስልጣን ነን/ሆነናል።
ስልጣን የሰጡን በአደራ ነው። አደራቸው ቀላል ነው፤ መደመር ብቻ። ሰው እንዴት ተዋደድ፣ አንድነትን አስቀድም፣ ፍቅርን አስበልጥ፣ ይቅርታን እወቅበት ሲባል ይከብደዋል? አገርህን በቀና ልቦና፣ በእኔነት መንፈስ አገልግል ሲባል ፊቱን ያጠቁራል? በፍፁም! የሰጡን አደራ ከተሸከሙት ያነሰ ነው። ከባዱን ሸክማችንን ተሸክመው፣ የማንደፈረውን ደፍረው አሳይተውናልና ቀላሉን ነገር ማድረግ ደግሞ ሊከብደን አይገባም።
ፈጣሪ የሰውን ልጅ ሲፈጥር ፍቅሩን የገለጠው ሁሉን አሟልቶ ሰጥቶ ነው፤ ለምሳሌ ገነት የተባለ ውብ ስፍራ ከነሙሉ ክብሩና ውበቱ ለመጀመሪያው ሰው ተሰጥቶት ነበር። ከሰው ደግሞ የተጠበቀው አንድ ነገር ብቻ ነበር፤ በተራው ለፈጣሪው አክብሮት እና ፍቅሩን እንዲገልጽ አንዲት ትዕዛዝን ማክበር ብቻ፤ አንዲት ቅጠልን አለመንካት፤ ያውም የሞት ፍሬ በመሆኗ።
«ወይ አዳም!» የምንልበት ዘመን አልፎ አሁን «ወይ እኔ» ላይ ደርሰን የለ? የምንፈልገው ሁሉ ከሆነልን ዘንዳ አመስግነን የሚፈለግብንን ልናደርግ ይገባል። ፍቅርን ማጠንከር፣ አንድ ሰው ነን ብለን ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን እውነትን ይዘን መሟገት፣ መሸሽ ሳይሆን መጋፈጥ፣ ይህንንም ሁሉ በፍቅር ማድረግ። የእነዚህ ድምር የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ከሌሎች የምንጠብቅ ሳይሆን እኛው የምንሠራት ያደርገናል። ይህን መንገድ ያስጀመሩንን ግን...አሁንም እናመሰግናለን። ሰላም!

ሊድያ ተስፋዬ

Published in አጀንዳ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ 100 ኛ ቀናቸውን ትናንት አስቆጥረዋል፡፡ እርሳቸው ወደ ስልጣን የመጡት በአገሪቱ ለሦስት ዓመታት አንዴ ጠንከር አንዴ ላላ እያለ የዘለቀው የሠላም መደፍረስ ከፍተኛ አደጋ በደቀነበት ወቅት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ የምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አስተማማኝ ሠላም የሚታይበት አይደለም፡፡ ሶማሊያ ለዓመታት የአሸባሪዎች መናኸርያ ከመሆኗም ባሻገር ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የላትም፡፡ ደቡብ ሱዳን በእርስ በርስ ግጭት የምትታመስ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባደረገችው ደም አፋሳሽ የድንበር ግጭት ምክንያት ሞት አልባ ጦርነት ላይ ነበረች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አጭር በሚባል ጊዜ አገሪቱን የመበታተን ጫፍ ላይ አድርሰዋት የቆዩ የተጠራቀሙ ችግሮች እንዲፈቱ እንዲሁም፤ ህዝብን ለምሬት የዳረጉ ብሶቶች እንዲቀንሱ በቁርጠኛ አመራራቸው ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ተስፋ ሰጪው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወደ ኋላ እንዳይመለስ የሚያግዙ አቅጣጫዎችን ጠቁመዋል፤ ተግብረዋል፡፡ በመልካም አንደበታቸው ለመላው ህዝብ ተስፋንና ብሩህ ዘመናትን አመላክተዋል፡፡ በይቅር ባይነት የሚሻር መጥፎ ጠባሳ መኖሩን አስተምረዋል፡፡ የእስከዛሬው ቆይታቸውም በደማቅ ስኬት የታጀበ ሲሆን፤ ቀጣይ የቤት ሥራዎች መኖራቸው አይካድም፡፡
ኢትዮጵያ ከፊት የሚጠብቃት ወሳኝ የቤት ሥራ ለመወጣት የውስጥ ሠላሟን ማረጋገጥና ከቀጣናዊ መረጋጋት የሚገኘውን ትሩፋት ለማጣጣም ይቻል ዘንድ የድርሻዋን ማበርከት አለባት፡፡
በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመቶ ቀናት ጉዟቸው ሠላም ርቋት የነበረችውን አገር ለማረጋጋት ያደረጉት አድካሚ ጥረት ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ በጅግጅጋ፣ አምቦ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ባሌ፣ ደንቢዶሎ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ወልቂጤና አፋር ከተሞች የሠላም መልእክት አንግበው ኅብረተሰቡን አወያይተዋል፡፡ችግሩን አዳምጠው ስለ መፍትሄው መክረዋል፡፡
በተደረገው ጥረት አሁን በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች አንጻራዊ ሠላም ቢሰፍንም፤ በተለያዩ ስፍራዎች ብሄርን መሰረት አድርገው የሚታዩ ግጭቶች ሙሉ ለሙሉ አልቆሙም፡፡ የተጀመረው ለውጥ ሙሉ እርካታን ያጎናጽፍ ዘንድ ችግሮችን ከምንጫቸው በመፈተሽ መፍትሄ መስጠት ይገባል፡፡ በተለይ በየክልሉ ለውጡ ያልተዋጠላቸው በስርዓቱ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ሲያጋብሱ የነበሩ አመራሮች ወንበራቸው ሳይነቀነቅ ለመዝለቅ ግጭትን እንደ እድሜ ማሰንበቻ ስልት ሊጠቀሙበት ስለሚችል ምርቱን ከግርዱ መለየት ያስፈልጋል፡፡
ላለፉት ዓመታት ዜጎች ለውጥ ያስፈልጋል በሚል መንፈስ በተለያየ መንገድ ሀሳባቸውን ሲገልጹና ሲታገሉ የቆዩት የእነርሱ መብት ተከብሮ የሌሎች እንዲጣስ አይደለም፡፡ ስለሆነም በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም ይሰፍን ዘንድ የዞረ ድምር አለ በሚል የተሳሳተ ስሌት ለብቀላ መነሳቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መደመር በሚል ጽንሰ ሀሳብ ያለመታከት ካስተላለፉት መልእክት በተቃራኒ መቆም ነው፡፡ መደመር ያለ ዘር ልዩነት በአንድ ላይ በመቆም የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያ ህዳሴ እውን ማድረግ ነውና በየስፍራው የሚንጸባረቀው የልዩነት ግንብ ሊፈርስ ይገባል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በቅርብም በሩቅም ከሚገኙ የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አጋር ወደ ሆኑ አገሮች አቅንተው በጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ግብጽ፣ ሶማሊያ፣ ዩጋንዳና ኤርትራ ከመካከለኛው ምስራቅ ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያና ዩናይትድ ዓረብ ኢሜሬቶችን ጎብኝተዋል። በተለይ ከኤርትራ ጋር የሞት አልባ ጦርነት ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመዝጋት የወሰዱት ቁርጠኛ አቋም ለዓመታት ተራርቀው የኖሩትን ህዝቦች ለማቀራረብ፣ መልካም ጉርብትና የሚያስገኘውን ትሩፋት ለመቋደስ የሚያስችል በመሆኑ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ነው፡፡
ከጎረቤትና ከስትራቴጂክ አጋር አገሮች ጋር የሚካሄደው ጠንካራ ግንኙነት ጠቀሜታው የበዛ ነው፡፡ በወደብና በየብስ የሚደረገው ግንኙነት የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያሳድጋል፡፡ በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች በጋራ ለማደግና ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡ ከምንም በላይ አገሪቱ ሰላሟ የተረጋገጠ እንዲሆን በጸጥታ ረገድ የሚያበረክተው ሚና ጉልህ በመሆኑ በተጀመረው ልክ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችው የህዳሴ ጉዞ መድረሻው ሩቅ በመሆኑ ከምንም በላይ ከውስጥ የሚመነጭ ሠላም ለአካባቢ ይተርፋልና መላው ኅብረተሰብ ሠላሙን በማስጠበቅ፤ ከጎረቤት አገራት ጋር በጋራ ለማደግ ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን ያበርክት፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ ካሏት ባለ አራት ኮኮብ ሙሉ ጄኔራሎች አንዱ ናቸው፡፡ ትውልዳቸው በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ወረዳ ኩየራ አካባቢ ሻሻ ቀበሌ ጥር 27 ቀን 1957 ዓ.ም፡፡ የደርግን ሥርዓት ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል ተሳትፈዋል፡፡ ከትጥቅ ትግሉ በኋላ የብርጌድ፣ የሬጅመንት፣ የኮር እንዲሁም የማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ፤ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ፤ የተባበሩት መንግሥታት የአብዬ ግዛት ግዳጅ የኃይል አዛዥ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በሰላም ማስከበር ዋና መምሪያ ኃላፊነትም ያገለገሉ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የኦፕሬሽን ኃላፊ በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ጄኔራል ብርሃኑ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ የማስተርስ ዲግሪ ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ የተቀበሉ ሲሆን፤ በሰላምና ደህንነትም ማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአገራዊና ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከጄኔራል ብርሃኑ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ ይላል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ መለኪያው ብዙ ነው፡፡ አንደኛው የዘመናዊ ሠራዊት መለኪያ ሠራዊቱ ዓላማውን እንዲያውቅ፣ ለምን እንደተደራጀና እንደሠለጠነ እንዲገነዘብ ተደርጎ ሲገነባ ነው፡፡ ሁለተኛው የዘመናዊነት መገለጫ በወታደራዊ ሳይንስ ጥበብና ዶክትሪን በቂ እውቀት ያለው ሆኖ መገኘት ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በወታደራዊ ባሕል ዙሪያ በቂ እውቀት መጨበጡ ይታያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሰራሮችን፣ መመሪያዎችንና ደንቦችን ማወቅ ግዴታ ነው፡፡ ደንቦችንና መመሪያዎችን ተከትሎ በሥነ ሥርዓት የሚሠራ፤ ተልዕኮውን ጠንቅቆ የሚያውቅ በከፍተኛ ወታደራዊ ዲስፕሊን የታረቀ ሠራዊት መሆን አለበት፡፡ በሚገባ የተደራጁ ብቁ የሥልጠና ተቋማት ያሉት፤ ሠራዊቱም በዚህ ሂደት ያለፈ መሆን አለበት ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታውን ቀድሞ ከነበረው ሠራዊት ጋር ሲያነፃፅሩት እንዴት ያዩታል ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- ማነፃፀር አይቻልም፡፡ ያን ጊዜ ሠራዊቱ የተደራጀበት ዓላማ፣ ተልዕኮና ወቅቱም ለየት ይላል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ሥርዓት አብዛኛው የሠራዊቱ አካል በብሔራዊ ውትድርና እና በሚሊሺያ መልክ ነው የተመለመለው፡፡ መደበኛ ሠራዊቱ ጥቂት ነው፡፡ መኮንኖቹ በሙሉ የመደበኛ ሠራዊት አባል ናቸው፡፡ በአገሪቱ የምሥራቅ አካባቢ ያጋጠመው ጦርነት እንዲሁም የእርስ በእርስ ጦርነት በስፋት ስለነበር የሰው ኃይል በብዛት አስፈላጊም ስለነበር መደበኛ ያልሆነው ኃይል ይበዛል፡፡ ኦፊሰሮቹን ከወሰድን በደርግ ጊዜም ከደርግ በፊትም በሀገር ውስጥም በውጭም የተማሩ በብዛት ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዲስ በተዋቀረው የመከላከያ ሠራዊት ቀድሞ የነበሩት ፕሮፌሽናል የሆኑ መኮንኖች ተካተው ነበር፡፡ አሁንስ እውቀታቸውን ለመጠቀም የመመለሱ ሀሳብ የለም ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- አስፈላጊ በሆነ ቦታም አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ወደፈትም አስፈላጊ በሚሆኑበት ቦታ እንጠቀማለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሌሎች ሀገራት ነፃ ሁነው በተለያየ የሙያ ዘርፍ የሚሠሩ አማካሪዎች በውትድርናው፣ በዲፕሎማሲውና በሌሎችም መስኮች ለመንግሥት ብዙ ይጠቅማሉ፡፡ በዚህ ረገድ የቀደሙትን ባለሙያዎች የመጠቀም ሀሳቡ አለ ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- አሁን ያለው መከላከያ 1985 እስከ 1989 ዓ.ም አካባቢ የነበረው አይነት አይደለም፡፡ አሁን ካዴት የሚያስተምርበት ተቋም አለው፡፡ ስታፍ ኮሌጅ የሚባል አለው፤ ድሮ የነበሩ ቢሆኑም እኛ ስንገባ ፈርሰው ነበር፡፡ በዓይነቱ አዲስ የሆነ የጦር ኮሌጅ (ዋር ኮሌጅ) እየመሰረትን ነው፡፡ ዋር ኮሌጅ ማለት ጦርነትን፣ ፖለቲካን ኢኮኖሚን አጣምሮ በስትራቴጂክ ደረጃ ጥናት የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡
ይህ ለሚሊተሪው ብቻ አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ አመራሩንም ያቅፋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እዚህ ደረጃ ደርሰናል፡፡ በሚገባ የተደራጀ ስታፍ ኮሌጅ፤ በሚገባ የተደራጀ የካዴት ኮሌጅ አለን፡፡ በሚገባ የተደራጀ የጦር ኮሌጅ እያቋቋምን ነው፡፡ ሁለተኛ ተቋሙ የራሱ ሪሰርች ኤንድ ዴቨሎፕመንት ሴንተር አለው፡፡ዶክትሪን የሚያጠና ስትራቴጂ የሚያጠና፤ ቴክኖሎጂ የሚያጠና፤ የዘመኑን ጦርነት የሚያጠና አካል አለ፡፡ የራሳችንን ሙያው፣ እውቀቱና ልምዱ ያላቸውን ሰዎች እንጠቀማለን፡፡ አስፈላጊ ሁኖ ሲገኝ ከውጭም እናመጣለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሠራዊቱ የሰላም ማስከበር ግዳጁን በምን መልኩ እየተወጣ ነው ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ አገራት የሰላም ማስከበር ግዳጁን በጣም በሚያኮራ ደረጃ ነው እየፈጸመ የሚገኘው፡፡ ዝግጁነቱ፣ ብቃቱና ተልእኮውን የመወጣት አቅሙ በተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት የተመሰከረለት ነው፡፡ በየትኛውም የግዳጅ ቀጣና ተመራጭ የሆነው የሰላም አስከባሪ ኃይል የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በሠራዊቱ ተጠቃሚነት ረገድ ያለው ሁኔታ እስከምን ድረስ ነው ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- በግዳጅ ስምሪቱ ውስጥ የሠራዊቱን ተጠቃሚነት በተመለከተ በተቋሙ አሰራር መሰረት የሚፈጸም ነው፡፡ ሠራዊታችን በደመወዝና በጡረታ ብቻ የሚሰናበት ሠራዊት አይደለም፡፡ ግዳጅ ላይ ተሰማርቶ እየተሳተፈ ከዚያ ግዳጅ የሚገኘውን ገቢ በተወሰነው ልክ እያገኘ እራሱን የሚደጉምበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለምሳሌም ያህል ኦብዘርቨሮች፣ ስታፍ ኦፊሰሮችና አመራሮች አሉን፡፡እነዚህ የተባበሩት መንግሥታት የሚከፍላቸው ደመወዝ ከእኛ ሀገር ለየት ያለ ስለሆነ ጥሩ የሚባል ነው ብለን እናስባለን፡፡ አገልግሎት የሚሰጡት ለአንድ ዓመት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ኃይል ስላለን በተቻለ መጠን ሁሉም እንዲዳረሳቸው ለማድረግ ነው፡፡ በሌሎች ሀገሮች ሲታይ አንድ ሰው ሦስትና አራት ጊዜ የሚላክበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እኛ ጋ ግን ሁሉም ዕድሉን እንዲያገኝ ነው ስንሠራ የቆየነው፤ እየሠራንም ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በሀገራችን ፖለቲካዊ ቀውስ አጋጥሞ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ በአንዳንድ አገሮች እንደሚታየው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አልተካሄደም፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- ቀደም ሲል እንደገለጽኩት መከላከያ ኃይሉ ፕሮፌሽናል ነው፡፡ ይህ ከሆነ ከሠራዊቱ መገለጫዎች አንዱ የተሰለፈበትን ዓላማ ጠንቅቆ ማወቅ ነው፡፡ ይሄ ሠራዊት የተደራጀው ሕገ መንግሥቱን እንጂ፤ ፓርቲ ለመጠበቅ አይደለም፡፡ በግልጽ በሕገ መንግሥቱ በሰፈረው መሰረት ሠራዊቱ የማንም ፓርቲ ወገንተኛ እንዲሆን አይፈቀድም፡፡ ለማንኛውም ፓርቲ ወግኖ ሀሳብ አይሰጥም፡፡ ይሄ ሠራዊቱ የተደራጀበት መሰረታዊ ዓላማ ነው፡፡ ይሄን ስናይ ሠራዊታችን ሕገመንግሥቱን ነው የሚጠብቀው፡፡
ሕገ መንግሥቱን ማንም ማፍረስ አይችልም፡፡ ሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ሌላ ተቃዋሚ ኃይል ሕገ መንግሥቱን ማፍረስ አይችልም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ግን ተመርጦ ጉድለት አለው፣ መታረም፣ መለወጥና መጨመር አለበት የሚለውን ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊወስን ይችላል፡፡
ሠራዊታችን የሕገ መንግሥት ጠባቂ ነው ሲባል ግልጽ ነው፡፡ ሕገ መንግስቱን ጠባቂ የሆነ ሠራዊት መፈንቅለ መንግስት አያደርግም፡፡ ሀሳቡም ራሱ ነውር ነው፡፡ ምክንያቱም ሕገመንግሥቱ ያስቀመጣቸው መርሆዎች አሉ፡፡ እነዛ መርሆዎች ሥራ ላይ መዋል አለባቸው፡፡ ሠራዊቱ ሀገሩንና ሕዝቡን ጠባቂ ነው እንጂ ፖለቲካዊ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገባም፡፡ እንደዚህ አይነት መርህ የለውም፡፡
ሌላው ነጥብ የእኛ ሠራዊት መፈንቅለ መንግሥት ቢያደርግ አደገኛ ነው፡፡ መፈንቅለ መንግሥት ማድረግ በሠራዊቱ የግንባታ አቅጣጫዎች ላይ ክልክል ነው፡፡ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይሄንን ጥሶ መፈንቅለ መንግሥት አደርጋለሁ ብሎ የሚሞክር ኃይል ካለና ቢሞክር ራሱ ነው የሚጠፋው፡፡ ሠራዊቱ በዚህ የተገነባ ነው፡፡ ስለዚህ የማይታሰብ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- በተለያዩ ክልሎች ግጭት ሲፈጠር ሠራዊቱ በመንግሥት ሲጠየቅ ጣልቃ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የነበረው የሠራዊቱ ሚና እንዴት ይታያል ? አንዳንድ ጊዜ ኃይል አብዝቶ ይጠቀማል የሚሉ አስተያየቶች በስፋት ይሰማሉ፤ ይሄንን እንዴት ነው የሚያዩት ?
ጄኔራል ብርሃኑ ፡- እውነት ነው፡፡ እንደዛ እየሠራን ነው ሀገሪቱን ያቆየነው፡፡ ችግር በተፈጠረበት ሁሉ እየገባን እያገዝን ፖለቲከኛው የፖለቲካ ሥራውን ሰርቶ ከዛ ውስጥ እንድንወጣ ፋታ እንዲያገኝ ስናደርግ የነበረው፡፡ በዚህ አፈጻጸም ላይ አንዳንድ ቅሬታዎች አሉ፡፡ የበዛ ኃይል(ኤክሰስ ፎርስ )ተጠቅሟል የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ ኤክሰስ ፎርስ (የበዛ ኃይል) የሚለውን መተርጎም ማብራራት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኤክሰስ ፎርስ (የበዛ ኃይል) የሚለው እንዴት ነው የሚገለጸው ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- የራሱ መለኪያዎች አሉት፡፡ የሆነ ሰው ተነስቶ ኤክሰስ ፎርስ ተጠቅመዋል በሚል በማህበራዊ ድረ ገጽ ይጽፋል፡፡ አንዳንድ የዳበረ ዴሞክራሲ ያላቸው ሀገሮችም «ይሄን ያህል ሰው ሞተ» በማለት የበዛ ኃይል ጥቅም ላይ መዋሉን ይናገራሉ፡፡ እዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት አለ ወይ ? የሚለው አንዱ መነሳት ያለበት ነጥብ ነው፡፡
መጤን ያለበት ግን ጉዳት መቀነስ እየተቻለ ጉዳት የበዛበት አጋጣሚ የለም ማለቴ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዝም ብሎ ከሁኔታዎች ገፊነት የተነሳ ከቁጥጥር ውጪ የሚሆን ነገር አለ፡፡ ሠራዊቱ የሕግ ተገዢነትን (ሩል ኦፍ ኢንጌጅመንት) መመሪያን በኪሱ ይዞ ነው የሚሄደው፡፡ በጥብቅ ያከብረዋል፡፡
ሠራዊቱ ወደ ግዳጅ ከተሰማራ በኋላ እያንዳንዱን ወታደር በርቀት መቆጣጠሪያ (በሪሞት ኮንትሮል) ሳይሆን በአሰራርና በመመሪያ ነው የምትመራው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቀላሉ ሊቆጣጠረው የሚችል ነገር እያለ የሚጠፉ ነገሮች አሉ፡፡ በሁኔታዎች ገዢነት የሚፈጠር ነው፡፡ ተገቢ እንዳልሆነ እናምናለን፡፡ ዳግም በሌላ ግዳጅ አፈጻጸም ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ የመቆጣጠር የመከታተል ተጠያቂነትን የማስፈኑ ሥራ የቅርብ ኃላፊዎች ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በድንበር አካባቢ በሚከሰት ግጭት መከላከያ ፈጥኖ ምላሽ አይሰጠም የሚል ወቀሳ ይሰማል፡፡ ሰሞኑን በተለይ በጎንደር ጠረፍ አካባቢ የሱዳኖች ዘልቆ መግባትን በተመለከተ ጉዳዩ ተነስቷል፤ ይሄን እንዴት ያዩታል ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- እንዴት መሰለህ ይሄ ሁኔታ የቆየ ነው፡፡ አንደኛ እስከዛሬ የድንበር ማካለል አልተደረገም፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬዎች የሚያርሱት መሬት አለ፡፡ የሱዳን ገበሬዎች የሚያርሱት መሬት አለ፡፡ ተቀላቅለው ነው የሚኖሩት፡፡ ኬንያ ለምሳሌ ቦረና አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ቦረና አለ፡፡ እዛ ጋ መልካሙ ነገር ድንበሩ ይታወቃል፡፡ በሱዳንና በእኛ በኩል ያለው ድንበር በግልጽ ተሰምሮ አልተካለለም፡፡ ሰው ግን አብሮ ይኖራል፡፡ ሱዳኖች ለኢትዮጵያ ገበሬ መሬት ያከራያሉ፡፡ ሱዳኖቹም ኢትዮጵያውያኖቹም እዛው አብረው የኖሩ ናቸው፡፡ ልክ እንደሌላው ቦታ ሁሉ አንዱ መሬት ያለው ነው፡፡ አንዱ መሬት የሌለው ነው፡፡
የእኛ ወገኖችም ሚሊሺያ አላቸው፡፡ ሱዳኖቹም ሚሊሺያ አላቸው፡፡ በእርሻ መሬት ነው የሚጣሉት፡፡ በሚጣሉበት ጊዜ ሚሊሺያዎቹ ይታኮሳሉ፡፡ ሚሊሺያዎቹ በሚታኮሱበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ የሱዳን ሚሊሺያዎች ጥቃት የደረሰባቸው ሲመስላቸው የሱዳን ወታደሮች ታዘው ሳይሆን በራሳቸው ተነሳሽነት ይደረባሉ፡፡ እኛም እንደዛ ሲሆን ለወገናችን እንደረባለን፡፡ በተረፈ የእኛ መደበኛ ሠራዊት ከሱዳን ሚሊሺያ ጋር የሱዳን መደበኛ ሠራዊትም ከኢትዮጵያ ሚሊሺያ ጋር የሚዋጋበት ምክንያት የለም፡፡ ይሄን ሁለታችንም ማድረግ የለብንም፡፡ አይደረግምም፡፡
አዲስ ዘመን ፡- የኢትዮጵያና የሱዳን መከላከያ ኃላፊዎች ችግሮቹን ለመፍታት ብዙ ጊዜ ሲወያዩ ነበር፡፡ መፍትሄው ምንድነው ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- አዎን እንወያያለን፡፡ ገበሬዎቹ ይረሱ፡፡ ድንበር የመለየቱ ጉዳይ በሁለቱ መንግሥታት በሕግ አግባብ ይጨረስ ነው ሁልጊዜ የምንለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን የእኛ መከላከያ አልገባም ነው የሚሉኝ? ግጭቱን ማን አስቆመው፤ ሱዳኖቹን ማን መለሳቸው ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- አሁን መጨረሻ ላይ የሆነው አንዳንድ የመደበኛ ሠራዊት አካል የሆኑ ሰዎች መሳተፋቸውን ስላየን ገብተን አቁሙ አልናቸው፡፡ ይሄ ሕገወጥ ነው፡፡ ከስምምነት ውጪ ነው፡፡ አርሶ አደሮቹን ማስታረቅ ነው እንጂ ወደእዚህ ግጭት መግባት የለብንም ነው ያልነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው አሉባልታ ነው፡፡ ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡ የሱዳን መደበኛ ሠራዊት ወደ ውጊያ አልገባም፡፡ ቢገባ ደግሞ አርሶ አደሩና ሚሊሺያው ሊያስቆመው አይችልም፡፡ ድንበሩ አካባቢ መቃኘት ሳይሆን ኃይል አለን፡፡ ያ የተወሰነ ኃይል አካባቢውን እየተቆጣጠረ እዚያ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለበላይ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ ሁለቱ ሀገራት ይነጋገራሉ፡፡ በውይይት የሚፈታውን ይፈታሉ፡፡ መስተካከል ያለበት ካለም ለማስተካከል ይረዳል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሀገር ደረጃ ለሁሉም ተቃዋሚ የሰላም ጥሪ ተደርጎአል፡፡ ከሰላም ጥሪው በኋላ የኦነግ ክንፍ በወለጋ አካባቢ መሳሪያ ይዞ ለመንቀሳቀስ መሞከሩ ይነገራል፤ ምን ያህል እውነት ነው ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- የታጠቀ የኦነግ ኃይል ገብቶ እንደዚህ አደረገ የሚለውን በተመለከተ፤ ኦነግ በሚወራለት ደረጃ አይደለም ያለው፡፡ ትርጉም ያለው ኃይል የለውም፡፡ ሰላም ማደፍረስ የሚችሉ የታጠቁ አነስተኛ ሰዎች ግን አሉት፤ ትናንሽ ኃይሎች፡፡ አሁን ለምሳሌ በምዕራብ ወለጋ በኩል በጣም ጥቂት የኦነግ ታጣቂዎች ገቡ፡፡ ከገቡ በኋላ ሰው በገንዘብ ገዙ፡፡ ከህብረተሰባችን መካከል ሥራ የሌለው ቶሎ ይመለመላል፡፡ አነሳስተው ይመለምሉታል፡፡ የገባው ኃይል ላይ ተጨማሪ ያደርጉታል፡፡ ከዛ በኋላ መንገድ መዝጋት ሰው መግደል ይጀምራሉ፡፡ ያለው እውነት ይሄ ነው፡፡ የተወሰኑ ከአንድ የመቶ የማይበልጡ ሰዎች ገቡ፡፡ ሰዎችን መለመሉ 190 ደረሱ፡፡ እነዚህ ደግሞ በቀበሌዎችና በወረዳዎች ተበተኑ፡፡ ሲበተኑ ደግሞ አራት አምስት ሆነው ነው፡፡ በዚያ አካባቢ የተባበራቸውን ሰው እየጨመሩ እያስተባበሩ ቀጣናውን የማወክና የማስፋት ሥራ ነው የሠሩት፡፡
የተደረገው ትክክለኛ ያልሆነ ሥራ ሲሆን፣ የሚወገዝ መወገድም ያለበት ነው፡፡ ጊዜው ለዚህ ዓይነቱ ድርጊት አይመችም፡፡ የሚታይ ሀገራዊ ለውጥ እየመጣ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየለፋና እየደከመ ይገኛል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ ያለው ተቀባይነት ከጫፍ ጫፍ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ዓለምም እያወራለት ነው ያለው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ተወካይ ነኝ ብለህ ጫካ ቆይተህ ምንም ውጤት ሳታመጣ ስትቀር፤ ሕዝቡ ታግሎ ባመጣው ለውጥና ውጤት ባለቤት ለመሆን መሞከር ነውር ነው፡፡
አሁን ሕዝቡ እያገለላቸው ነው፡፡ እኛ የታገልነው ለእዚህ አይደለም፡፡ ግቡ ተብላችሁ ሰላም ከሰፈነ በኋላ ምንድነው የምትፈልጉት እያላቸው ነው፡፡ ይሄ የሁለት ሳምንት ግርግር ነው፡፡ እንኳን ዛሬ ድሮ 30 ሺ ተዋጊ ኃይል ይዞ የአልሠራውን ሥራ በአንዴ መጥቶ ለመሥራት መሞከር ምን ማለት ነው፡፡ ትርጉም የለውም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው ሰላም አፋርና ትግራይ ያለው ሠራዊታችን አሁን ባለበት ይቆያል ወይንስ የማንቀሳቀስ ሁኔታ ይኖራል ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- ይሄ የመንግሥት ውሳኔ ነው፡፡ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ተነጋግሮ ሠራዊት እናርቅ ካለ እናርቃለን፡፡ ባለበት ይቆይ ካለ ባለበት ይቆያል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሠራዊቱ የብሔር ብሔረሰብ ተዋጽኦ ተመጣጣኝ አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች ይሰሙ ነበር፤ ይሄንን እንዴት ያዩታል ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- መስመራዊ መኮንንና ከዛ በታች ያለው የብሔር ተዋጽኦ የተጠበቀ ነው፡፡ የተመጣጠነ ነው፡፡ ችግር የለም፡፡ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የብሔር ተዋጽኦውን በተመለከተ ችግር አለ፡፡ ብዙ ጊዜ ተመጣጥኖአል ተብሎ ሲገለጽ ነበር፤ አልተመጣጠነም፡፡ የግድ ለማመጣጠን ሪፎርም መካሄድ አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ፡- አሁን ይሄ እየተሠራ ነወይ ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- እየተሠራ ነው፡፡ በየደረጃው ይሠራል፡፡
አዲስ ዘመን ፡- እስከታች ይወርዳል ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- በታችኛውማ ደረጃ ምንም ችግር የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከየት ጀምሮ ነው አለመመጣጠኑ ጎልቶ የሚታየው ?
ጄኔራል ብርሃኑ ፡- ከክፍለ ጦር በላይ ያለመመጣጠን አለ፡፡ ይሄ ማለት ግን ተሳትፎ የለም ማለት አይደለም፡፡ ተሳትፎ አለ፡፡ መመጣጠኑ የሀገሪቱን ገጽታ በሚያሳይ ልክ አይደለም፡፡ ይሄ መሠራት መስተካከል አለበት፡፡ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን የሚመስል ሠራዊት ነው መገንባት ያለበት፡፡ ከታች ብዙ ኃይል እየመጣ ነው፡፡ በዛ መልክ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ እላይ ያለው የማመጣጠን ሥራ ዘግይቶአል፡፡ ችግሩ የተለያየ የራሱ ምክንያቶች አሉት፡፡ አንደኛው ከሌላው መምጣት ያለበትን ኃይል በበቂ ያለማዘጋጀት ነው፡፡፡እያንዳንዱ ለማመጣጠን መቀነስን ነው የሚያስበው፡፡ ሳትቀንስ ግን ማመጣጠን ትችላለህ፡፡ ሳትቀንስ የማመጣጠን ሥራ በደንብ ሠርተናል ማለት አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሠራዊቱ ታማኝነቱ ለሀገሪቷና ለሕዝቧ ሁኖ ያለ ተጽእኖና እንዲቀጥል፤ በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ጠንካራ ግንዛቤ እንዲፈጠር የሚሰራ ስራ አለ ?
ጄኔራል ብርሃኑ ፡- አሁን ሕገ መንግሥቱን ስለሸረሸርነው ነው እንጂ ሕገ መንግሥቱ እኮ ስለ ኢትዮጵያ ነው የሚያወራው፡፡ ሠራዊታችን የሚያወራው ስለ ኢትዮጵያና ስለ ሕገመንግሥቱ ነው፡፡ቋንቋውም ይሄ ነው፡፡ ይህንን በአዋጆች፣ በደንቦችና በመመሪያዎች ወደ መሬት ማውረድ ያለበት ፖለቲካዊ አመራሩ መሆን ነበረበት፡፡ ፖለቲካዊ አመራሩ ደግሞ ይሄን በደንብ እየመራው አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ነው ኢሕአዴግ ችግር ውስጥ የገባው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ኢትዮጵያን እጠብቃለሁ እንጂ የሆነ ፓርቲ እጠብቃለሁ አይልም፡፡ ሠራዊቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መኖር እንዳለበትና የፖለቲካ ሥልጣን ሽግግር በምርጫ መሆን እንዳለበት ያምናል፡፡ የሀገሪቱ ሉዓላዊነት እንዳይደፈር ይሠራል፡፡ ለዚህ ነው የዓላማ ብዥታ ችግር ሠራዊቱ የለበትም ያልኩህ፡፡
ሕገመንግሥቱ በተጻፈበት መንገድ ፖለቲካዊ አመራሩ ሰርቶአል ወይ የሚለው ነው ጥያቄ እያስነሳ ያለው፡፡ አልሠራችሁም ብሎ ሕዝቡ አመጸ፡፡ የፖለቲካ አመራሩ ሕዝቡ እያነሳ ያለው ጥያቄና ተቃውሞ እውነት መሆኑን አምኖ ተቀበለ፡፡ የእኔ ችግር ነው አለ፡፡ አሁን ችግሩን የማስተካከል ሥራ ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ሠራዊቱ ይሄንን መደገፍ አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመከላከያ ስር የሚገኙ የተለያዩ የልማት ተቋሞች ለአገሪቱ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል ?
ጄኔራል ብርሃኑ ፡- የመከላከያው ኢንዱስትሪ እና ሌሎች የመንግሥት ኢንዱስትሪዎች የነበሩት በአንድ ዕዝ ስር ሆነው በሜቴክ እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡ የመከላከያን ፍላጎት እንዲያሟላ እንዲሁም አጠቃላይ የሀገሪቱን ኢንዱስትሪ እንዲመራ ተብሎ ነበር የተቋቋመው፡፡ ለሲቪልና ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ምርቶችን ሲያመርቱ ነበር፡፡ የእንደነዚህ አይነት ተቋማት ዕድገት ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ባሳለፍነው ጊዜ መጠን ተራምደናል ወይ የሚለውን መገምገም አለብን፡፡ ጅምሩ ጥሩ ነበር፡፡ በመሀል ትንሽ ተቋሙ ላይ ያለመርካት ሁኔታ በተለያዩ ኃይሎችም ነበር፡፡ ቢሆንም አሁን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ብዙ ዓመታት አገልግለው ጡረታ ሳያገኙ የተሰናበቱ በከፋ ችግር ላይ ያሉ የቀድሞው ሠራዊት አባላት በመላው ሀገሪቱ አሉ፡፡ ጡረታ ሲጠይቁ የግል ማህደራችሁ የለም አልተገኘም ነው መልሱ፡፡ ምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያና ጡረታ ሚኒስቴር በመመላለስ የኖሩም አሉ፡፡ ወታደሮች፣ የበታች ሹሞችና መኮንኖች የነበሩ በተለያየ ክስ የጡረታ መብታቸውን ለረዥም ዓመታት የተነፈጉ ዜጎችም አሉ፡፡ ይህ ችግር እንዴት ይፈታል ?
ጄኔራል ብርሃኑ፡- የጡረታ መብታቸው እንዲከበር እየተሠራ ነው፡፡ ጡረታቸው ሳይከበር የወጡ ሰዎች በጥፋት የተከሰሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ በአለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአንዳንዶች ማዕረጋቸው በክብር እንዲመለስ ጡረታቸውም እንዲከበር ካስደረጉ በኋላ በዚሁ መነሻነት በእነሱ ብቻ ሳይቆም ጡረታቸው ሳይከበር የተሰናበቱ የቀድሞው የሠራዊት አባላት በሙሉ ማሕደራቸው ተፈልጎ ታውቀውና ተለይተው መከላከያ ሚኒስቴር ውሳኔ ሰጥቶ ጡረታቸው እንዲከበር እየሠራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን!
ጄኔራል ብርሃኑ ፡- እኔም አመሰግናለሁ !

ወንድወሰን መኮንን 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞችና የሠራተኛ ማህበሩ ባንኩ የተገበረው አዲስ የመዋቅር ለውጥና የሰው ኃይል ምደባው ባልተጨበጠ መስፈርት ተመስርቶ የተፈጸመ፣ አመራሩ የሚፈልጋቸውን ሰዎች ብቻ ተጠቃሚ ያደረገ በመሆኑ ትግበራው እንዲቆም እንዲሁም ተገቢ ማስተካከያ እንዲደረግበት ጠየቁ፡፡ ከማህበሩ አመራርና ከሠራተኞች የተነሳው ቅሬታ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ባንኩ አስታውቋል፡፡

በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት የሰው ኃይል ማኔጅመንት ቅጥርና ምልመላ ሠራተኛ አቶ ኤልያስ የኔሁን ገዳሙ፤ የመዋቅር ለውጡ የባንኩ የሰው ኃይል አስተዳደር ከየክፍሉ አስተዳደሮች ጋር በመተባበር ተጨባጭ ባልሆነ መስፈርት የሚፈልጓቸውን ሰዎች ብቻ ተጠቃሚ ያደረጉበት ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡
የ‹‹አመለካከት›› ግምገማ አንድ መስፈርት ሆኖ መቀመጡ እንደ ክፍተት ተጠቅመውበታል ያሉት አቶ ኤልያስ፤ ሰዎችን ሆን ብሎ ለመጥቀምና ለማጥቃት ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ «ሁሉም ሠራተኞች እኩል የመወዳደር መብት ሊሰጣቸው ሲገባ በአመለካከት በተደረገው ግምገማ ከፍና ዝቅ መደረጋችን ተገቢ አይደለም» ብለዋል፡፡
በተቋሙ በቆየሁባቸው ጊዜያቶች የደረጃ ዕድገት የሚከናወነው በቅርበትና በመተዋወቅ ላይ ተመስርቶ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ አመራሩ በዕድገት ውድድር ሰሞንም ምክንያቶችን በመፈለግ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን በማሳደር ለደረጃው የማይመጥኑ ሰዎች እንዲያድጉ ሲያደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ ሠራተኛ ማህበሩ ጠንካራ ሆኖ የሠራተኞችን ድምጽ በማሰማት ለውጥ ለማምጣት ባለመቻሉ ሠራተኛው አንገቱን እንዲደፋ ችግሮች እንዲባባሱ ማድረጉንም አክለዋል፡፡
ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አለ ይባላል እንጂ ተዋቅሮ በይፋ አለመታወቁን አቶ ኤሊያስ ጠቁመው፤ ጠንካራ የሰው ኃይል አስተዳደር እንዲፈጠር መንግሥት ገለልተኛ አካል አቋቁሞ በአዲሱ የባንኩ የበላይ ኃላፊ በመመራት ሂደቱ መፈተሸ አለበት ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ይህ ካልሆነ አገሪቱን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚጎዳ፣ የሠራተኛውን የሥራ ተነሳሽነት እንደሚገድልና ታሪካዊ ስህተት ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
በባንኩ የዛግዌ ቅርንጫፍ ሄድ ዌይተር አቶ ከድር አሰፋ በበኩላቸው «የመዋቅር ለውጡ የደረጃና የደመወዝ ማስተካከያ ያስገኛል ብለን ብንጠብቅም አብዛኞቻችንን በነበርንበት ቦታ እንድንቀጥል አድርጓል» ብለዋል፡፡ የመዋቅር ድልድል የነጥብ አሰጣጥ የሚከናወነው ከቅርብ አለቃ በሚሰጥ ምስክርነት መሆኑም ክፍተት መፍጠሩን አክለዋል፡፡
«ለምመጥነው ደረጃ፤ የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት እያለኝ ሳይሰጠኝ ቀርቷል፡፡ ይህ እንደክፍል አልታየም ብዬ እንዳላስብ የታየላቸው ሰዎች አሉ» ያሉት አቶ ከድር፤ አሰራሩ ፍትሃዊነት የጎደለው የቅሬታ ምንጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለቦታው የሚመጥን ብቃት እያለኝ ምስክርነት በቅርብ አለቃዬ ባለመቅረቡ የሚገባኝን ቦታ አላገኘሁ ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ከድር ማብራሪያ፤ ሰሞኑን እየተተገበረ በሚገኘው አዲሱ የመዋቅር ለውጥ የደረጃ ዕድገት የሌለው መሆኑ ደግሞ በአብዛኞቹ ሠራተኞች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡ በዚህም ሠራተኞች ተቆጥተውና አኩርፈው ይገኛሉ፡፡ አስተዳደራዊ በደል የሚፈጥሩት ጫና ለሠራተኞች መሰደድ በር የሚከፍት በመሆኑም አሰራሮችን ፈትሾ ዜጎች እኩል የሚታዩበት ፍትሃዊ ውሳኔ ሊሰጠው ይገባል፡፡

አቶ ከድር አሰፋ፤


ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ የደመወዝ ማስተካከያ ሳይደረግ ለረጅም ዓመታት እንደቆየ አቶ ከድር አንስተው፤ ተስፋ ያደረጉት የመዋቅር ለውጥ ተጠቃሚ ያላደረጋቸው መሆኑ ከፍተኛ ኀዘን እንደፈጠረባቸው ጠቁመዋል፡፡ አድሎአዊ አሰራሩ ሲጨመርበት ደግሞ የሠራተኛውን የሥራ ተነሳሽነት እንደሚገድልም አስረድተዋል፡፡ «ስለሆነም ባንኩ አሰራሩን ፈትሾ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ሊያደርገን ይገባል» ብለዋል፡፡
የባንኩ የሠራተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሃይማኖት ለማ፤ ሠራተኛው በጉጉት የሚጠብቀው የደመወዝ ማስተካከያ ምላሽ እንዳላገኘ ጠቁመዋል፡፡ አመራሩ ለሠራተኞችና ለሠራተኛ አመራሩ የሚሰጠው ትኩረት በመቀነሱም ማህበሩ በተደጋጋሚ ጠያቂ እንጂ የሚደራደር አካል ባለመሆኑ ማህበሩን ማዳከሙንም ገልጸዋል፡፡
ቅሬታዎቹ በርካታ መሆናቸውን የሚገልፁት አቶ ሃይማኖት፤ ሠራተኛው ያነሳው የደመወዝ ማስተካከያው ጥያቄ ሊመለስለት እንደሚገባ፣ ከአዲሱ መዋቅር ጋር ተያይዞ የሚነሳው ቅሬታም እንደ አዲስ መታየት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ አዲሱ የደመወዝ ስኬል ተፈጻሚ ባልሆነበትና ከአዲሱ መዋቅር ጋር ተያይዞ ከሠራተኞች የሚነሱት ቅሬዎች ምላሽ ሳያገኙ የመዋቅሩ ትግበራ ሊቆም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ካልሆነ ማህበሩ ህገ መንግሥቱ በሚፈቅድለት መሰረት ማንኛውንም እርምጃዎች የሚወስድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ህብረት ስምምነቱ ላይ የዕድገት መስፈርቶች መቀመጣቸውን ያነሱት አቶ ሃይማኖት፤ መስፈርቶቹ የሚጣሱበት ሁኔታ በስፋት እንዳለም አንስተዋል፡፡ ዕድገት በሚኖርበት ጊዜ መስፈርቶቹ አለመተግበራቸውን፣ ተግባሩም የቅሬታ ምንጭ መሆኑንና ማህበሩ ይህንንም በተለያዩ አጋጣሚዎች ማንጸባረቁን ጠቁመዋል፡፡ ባንኩን ለማሳደግ የሚተገበሩ የተለያዩ አሰራሮች ሠራተኛውን ባማከለ መንገድ ሊከናወኑ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡
የባንኩ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ በልሁ ታከለ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አዲስ መዋቅር መተግበር ያስፈለገው ባንኩ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የሚመጥን አሰራር ለመፍጠር ታሰቢ ተደርጎ ነው፡፡ መዋቅሩ ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቶ ባሸነፈው የጀርመን ኩባንያ የተሰራ ሲሆን፤ መስፈርት ወጥቶ ሠራተኞች በመመዘኛው እየተለኩ ምደባው እንዲከናወን ተደርጓል፡፡ በእያንዳንዱ ምደባ የሠራተኛ ማህበሩ የተሳተፈ ሲሆን፣ ዕድገት የተሰጠውም ማህበሩ በሚያውቃቸውና ባመነባቸው መለኪያዎች ብቻ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ከማህበሩ አመራርና ከሠራተኞች የተነሳውን ቅሬታ ተቀባይነት የለውም፡፡
ከዕድገትና ከአዲሱ መዋቅር ጋር ተያይዞ የሚነሳው ቅሬታ ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች ባላቸው ግላዊ አመለካከት የመነጨ መሆኑን ጠቁመው፤ ‹‹በአሰራሩም ሁሉንም ሰው ተመሳሳይ ቦታ ማስቀመጥ አንችልም፣ ሁሉንም ሠራተኞችም ማስደሰት አይቻልም፣ የሁሉም ሠራተኞች አፈጻጸምም ተመሳሳይ አይሆንም›› ብለዋል፡፡
ይሁንና የሠራተኛ የደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ የደመወዝ ማሻሻያ እቅድ በማዘጋጀት ለሚመለከተው አካል የውሳኔ ሃሳብ ተልኮ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑንም አቶ በልሁ አስረድተዋል፡፡ ከአመዳደብ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ቅሬታ የሠራተኛ ማህበሩ ተሳትፎበት መጠናቀቁን ጠቁመው፤ «ቅሬታ ያላቸው አካላት የተዘረጋው የቅሬታ ማቅረቢያ ስርዓት በመከተል ማቅረብ ይችላሉ» ብለዋል፡፡
የጋዜጣው ሪፖርተር በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ 12 የባንኩ ቅርንጫፎች ባደረገው ምልከታ በትግበራው ሠራተኞች ቅሬታ እንዳላቸው ለመታዘብ ችሏል፡፡  

ዘላለም ግዛው

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።