Items filtered by date: Monday, 02 July 2018

ስለ ጅማ ከጥንት እስከ አሁን የማያውቁት ነገር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የሚወዱትን ስፖርትም ከእንግሊዛውያኑ እስከ ጅማ አባጅፋር ጠንቅቀው ያውቃሉ። የ«ጅማው ፔሌ» ቅጽል ስማቸው ሲሆን፤ በርካቶች ዘንድ በዚህ ስያሜ የሚታወቁት ሰው አቶ አብዱልከሪም አባገሮ ናቸው። ተወልደው ባደጉባት ጅማ ኳስ ከማንከባለል ባሻገር በተለያዩ ቡድኖች በተጫዋችነት፣ አሰልጣኝነትና ዳኝነት አልፈው አሁን የጅማ አባቡና እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ታላላቅ ወንድሞቻቸውን ተከትለው ሜዳ መዋላቸው ወደ እግር ኳስ ስፖርት እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ። ከእኩዮቻቸው ጋር በሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም የሚያሳዩት ብቃት ላይ የተመሰረተና የወቅቱን የእግር ኳስ ጠበብቶች ስም የመመረቅ ባህል ነበርና፤ ብላቴናው አብዱልከሪም ከጓደኞቻቸው በተለየ ከመሃል ሜዳ የሚያስቆጥሩት ግብና አጨዋወታ ቸው «ፔሌ» ለሚለው ስም መነሻ ሆናቸው። የ13ዓመት ታዳጊ ሳሉም በኳስ ጨዋታ ላይ አደጋ በማስተናገዳቸው ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ይሄዳሉ።
በህክምናው ያገኟቸው ባለሙያም ታዳጊው ለስፖርቱ ያላቸውን ፍቅር በመመልከት ስለ ብራዚላዊው የኳስ ንጉስ ፔሌ የሚተርክ፤ በአቶ ነጋ ወልደስላሴ የተተረጎመ መጽሃፍ ያበረክቱ ላቸዋል። መጽሃፉን ማንበባቸውም ይበልጥ እንደ ፔሌ የመሆን ህልማቸውን አንሮታል። በተለይ መጽሐፉ ከሚያትታቸው ጉዳዮች መካከል፤ አትጠጣ፣ አታጭስ፣ ባላጋራህን አክብር፣ ዳኛ አክብር፤ ውሳኔውንም በጸጋ ተቀበል፣ ተመልካች አክብር፣ ... የሚሉ ምክሮችን መተግበርም የዕለት ተዕለት ስራቸው ነበር። ይህም በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመናቸው አንድም ቢጫ ካርድ እንዳይመለከቱ አድርጓቸዋል። በጨዋታ ወቅት ግጭቶች መከሰታቸው ባይቀርም ሁሉንም በትዕግስት ያሳልፉት እንደነበርም ይጠቁማሉ።
ከፍተኛ 1፣ ቀይ ኮከብ፣ ጅማ ምርጥ ቡድን፣ ከፋ አውራጃ፣ የወሎ ምርጥ ቡድን እና ተስፋ ቡድን በእግር ኳስ ተጫዋችነት የተሰለፉባቸው ቡድኖች ናቸው። በወቅቱም ሙሉጌታ ከበደ፣ ሙሉጌታ ወልደየስ፣ ገብረመድህን ኃይሌ፣ ... ከመሳሰሉ አንጋፋ ተጫዋቾች ጋርም ተጫው ተዋል። የእግር ኳስ ተጫዋችነታቸውን ካቆሙ በኋላም በዳኝነት ስልጠና ደረጃ አንድና ሁለትን ወስደው ለጥቂት ጊዜ በዳኝነት ላይም ተሳትፈዋል። በአሰልጣኝነቱም በተመሳሳይ ሁለተኛ ደረጃ ስልጠና ወስደው፤ የከፋ ምርጥ ቡድን፣ ጅማ ከተማ፣ ከፍተኛ አንድ በዋና አሰልጣኝነት የክፍለ ሃገሩን ምርጥ ቡድን ደግሞ በምክትል አሰልጣኝነት ተሳታፊ ሆነዋል።
ጅማ እና ስፖርት የተዋወቁት ጣሊያን ኢትዮጵያን ለቃ ከወጣች በኃላ፤ በከተማዋ በብዛት ይኖሩ በነበሩት እንግሊዛዊያን መሆኑን ያወሳሉ። በወቅቱም ከእግር ኳስ ስፖርት ባሻገር፣ የብስክሌትና የቦክስ ስፖርትም የሚዘወተሩ ነበሩ። በተለይ የወታደር ተቋማት የስፖርት ቡድኖች ከሌሎች የውጪ ዜጎችና አረቦች ጋር ውድድሮች ይደረጉ የነበሩ ውድድሮች ተጠቃሽ ናቸው። የውሃ ዋና፣ ሰርከስ (ሰርከስ ጅማ)፣ መረብ ኳስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ እንዲሁም የሴቶች እግር ኳስ ጅማ ትታወቅበት የነበሩ ስፖርቶች ናቸው። በዚህም ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ተስፋዬን ጨምሮ በርካታ የስፖርት ባለሙያዎችንና ስፖርተኞች አፍርተዋል።
ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት የጅማ ስፖርት እንደ ሃገሪቷ እግር ኳስ «ወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ...» የሚባልለት ሁኔታ ላይ መድረሱን ይጠቁማሉ። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያነሱትም የከተማዋ ሁኔታ መዳከም ማሳየት ስፖርቱንም አብሮ እንዳዳከመው ነው። በዚህ ሁኔታ መቀጠሏ ሃዘን የፈጠረባቸው አንጋፋ ስፖርተኞችና የስፖርት ቤተሰቦችም ከአምስት ዓመት በፊት ስፖርቱን ለማነቃቃት ውጥን ይዘው ተነሱ።
በዚህም በ1948ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ እርሻ ኮሌጅ የተመሰረተውን የእግር ኳስ ቡድን፤ ጅማ በምትታወቅበት ቡና በመሰየም «ጅማ አባቡና» እንዲባል ተወስኖ ወደ ስራ ተገባ። በተከናወነው ተግባርም ክለቡ ወደ ከፍተኛ ሊግ ሊያድግ ቻለ፤ በጥንካሬው ቆይቶም የኢትዮጵያን ፕሪምየር ሊግ በ2009ዓ.ም ተቀላቀለ። ነገር ግን በውድድር ዓመቱ መጨረሻ አሳማኝ ባልሆኑ የተለያዩ ጉዳዮች ቡድኑ በድጋሚ ወደ ከፍተኛ ሊግ ሊወርድ ቻለ።
የክለቡ መውረድ አሳዛኝና የስፖርት ቤተሰቡን ልብ የሰበረ ቢሆንም በዚያው ዓመት ሃዘኑን ሊፈውስ የሚችለው መንትያው ክለብ ጅማ አባጅፋር ወደ ፕሪምየር ሊጉ አደገ። ክለቡ በመጀመሪያ ዓመት የሊግ ተሳትፎው ባልተለመደ መልኩ የተሻለ አቋም በማሳየትና አንጋፋዎቹን ክለቦች በመቀናቀን የዋንጫ ባለቤት ለመሆን በግስጋሴ ላይ የሚገኝ ክለብ ነው። የክለቡ ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ 17 ግቦችም ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፤ ይህም የጅማን እግር ኳስ ዳግም ሊቀሰቅስና ስፖርቱን ሊያሳድግ ምክንያት ሆኗል። የጅማው ፔሌም ጅማ አባቡና እና ጅማ አባጅፋር ብቻ በቂ ባለመሆናቸው አጋሮ አባቦቃን የመሰሉና በአካባቢው ብቃት ያላቸው በርካታ የፕሪምየር ሊግ ተካፋይ ክለቦች መምጣት አለባቸው ይላሉ። ይሁን እንጂ በየአካባቢውና በየትምህርት ቤቱ ፍላጎት ባላቸው ታዳጊና ወጣቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ አይደለም። በቀደመው ጊዜ በተለያዩ ስፖርቶች የትምህርት ቤቶች ውድድር የሚካሄዱ በመሆናቸው በርካታ ስፖርተኞችን ለማፍራት ተችሏል። አሁን ግን ይህ እየተደረገ አይደለም፤ ትምህርት ቤቶችም ቢሆኑ እንደቀድሞው ታዳጊዎች አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው ሜዳዎች የሏቸውም። ከዚህ ባለፈም ለስፖርቱ ግብዓት የሚሆኑ ትጥቆችና ኳሶችን ታዳጊዎቹ በራሳቸው አቅም ማሟላት አይችሉም፤ ድጋፍ የሚያደርግላቸውም የለም።
በጅማ በርካታ ስፖርተኞችን ያፈራው «ኪቶ ሜዳ»ን ጨምሮ በየአካባቢው በርካታ ሜዳዎች እንደነበሩ አቶ አብዱልከሪም ይጠቁማሉ። የወቅቱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በሜዳው በመደነቃቸው «ምነው መሃረብ ሆኖ ጠቅልዬ በወሰድኩት» እስከማለት እንደደረሱም ያስታውሳሉ። በሃገሪቷ ታዋቂ ከነበሩ ስታዲየሞች መካከል አንዱ በደርግ ጊዜ የተገነባው የከተማው ስታዲየም ነበር። አሁን ደግሞ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ገንብቷል።
አንጋፋው ሰው የጅማን ስፖርት ወደ ቀደመ ቦታው እንዲመለስ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ። ስፖርት የሚጀምረው ከቤት በመሆኑ፤ ህብረተሰቡ ልጁን በስፖርቱ ቢያሳትፍ፣ የአካባቢውን ታዳጊዎችም ቢያበረታታና በተቻለ መጠን ድጋፍ ቢሰጥ፣ በማዘውተሪያ ስፍራዎች በመገኘት አጋርነትን ቢያሳይ፣ በርካታ የስፖርት ባለሙያዎችን ለሃገሪቷ ማበርከት እንደሚቻልም እምነታቸው ነው። በመሆኑም ባለሃብቶችም ሆኑ አቅም ያላቸው ሰዎች ታዳጊዎቹን ከመደገፍ በተጓዳኝ ትውልዱን ካልተገቡ ቦታዎች እንዲርቁ በማድረግ ሚናቸውን ይጫወታሉ።

 

ሁለት አትሌቶች አበረታች መድኃኒት በመጠቀማቸው ተቀጡ 

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የጸረ-አበረታች መድኃኒቶች ተቆጣጣሪ ጽህፈት ቤት ሁለት አትሌቶችንና አንድ የመድኃኒት መደብር ማገዱን አስታወቀ። ጽህፈት ቤቱ ከስፖርት መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር በአበረታች መድኃኒት መቆጣጠርና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ላይ ውይይት አድርጓል።
አበረታች መድኃኒት የስፖርቱ ዓለም ስጋት ከሆነ ዋል አደር ብሏል። በተለይ ይህ ጉዳይ የሚያያዘው ከአትሌቲክስ ስፖርት ጋር በመሆኑም ኢትዮጵያን ጨምሮ በስፖርቱ ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸው ሀገራትን የሚያሳስብ ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጸረ-አበረታች መድኃኒቶች ተቆጣጣሪ ጽህፈት ቤትም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 መሰረት ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ እየሠራ ይገኛል።
ጽህፈት ቤቱ በሥራ አመራር ቦርዱ፣ ሰባት አባላት ባሉት የንኡሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም በጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎች ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። ከተግባራቱ መካከልም የትምህርትና ሥልጠና፣ ምርመራ የማድረግ እንዲሁም ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ጽህፈት ቤቱን ነጻ እና ከማንም ጣልቃ ገብነት የጸዳ አድርጎ በማቋቋም፣ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት፣ ግንዛቤ በማስጨበጥ እንዲሁም ለምርመራ የሚሆነውን ናሙና በመውሰድ ላይም የተሻለ ሥራ ማከናወኑን ከወራት በፊት አዲስ አበባ የመጣው የዓለም አቀፉ የጸረ-አበረታች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ እነዚህን ሥራዎች ከማጠናከር ጎን ለጎን ከአትሌቶች ናሙና በመውሰድና ቅጣት በማስተላለፍ ረገድ ጠንክራ መሥራት እንደሚገባት አሳስበው ነበር። በዚህም ጽህፈት ቤቱ እስካሁን 769 በሚሆኑ ስፖርተኞች ላይ ናሙና የወሰደ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ስድስት አትሌቶች እንዲሁም በአንድ የመድኃኒት መደብር ላይ ማጣራት አድርጎ ከሁለት እስከ አራት ዓመት የሚደርስ እገዳ ማስተላለፉ ይታወሳል። አሁንም ተጨማሪ ሁለት አትሌቶችና አንድ የመድኃኒት መደብር ህግ ጥሰው በመገኘታቸው ቅጣት አስተላልፎባቸዋል። አትሌት መቅደስ ፈቀደ ቸገን በቻይና በተካሄደ አይ ኤን በተባለ ውድድር ላይ የተሳተፈች ሲሆን፤ በተደረገላት ምርመራ አበረታች መድኃኒት ተጠቅማ መገኘቷ ተረጋግጧል። በዚህም እአአ ከኖቬምበር 16/2017 ጀምሮ የሁለት ዓመታት እገዳ ተጥሎባታል።
ሌላኛዋ አትሌት መሰረት ታዬ አሰፋ ደግሞ በደቡብ አፍሪካው የኬፕታውን ማራቶን ላይ የተሳተፈች ናት። አትሌቷ በምርመራው ላይ «ቴስቴስትሮን» የተባለ የተከለከለ መድኃኒት የወሰደች ሲሆን፤ በዚህም እአአ ከኖቬምበር 17/2017 ጀምሮ ለአራት ዓመታት በየትኛውም የአትሌቲክስ ውድድር ላይ ተሳታፊ አትሆንም።
አትሌት መሰረት የተከለከለውን መድኃኒት የገዛችበት ዮሃና መድኃኒት መደብርም፤ ያልተፈቀደ መድኃኒት ማስገባቱና መሸጡ ስለተረጋገጠበት ለሁለት ዓመታት አገልግሎት እንዳይሰጥ ተከልክ ሏል። ጽህፈት ቤቱ በመደብሩ ላይ ባደረገው ማጣራትም ተጨማሪ መድኃኒቶች የተገኘ ሲሆን፤ አትሌቷ የገዛችበት ደረሰኝም ተይዟል። በመሆኑም በኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ተነጥቋል።
ጽህፈት ቤቱ ከዚህ በኋላ በውድድር እና በድንገት አትሌቶቹ ያሉበት ድረስ በመሄድ ከሚደረገው ምርመራ በተጨማሪ በሚደርሰው ጥቆማ ላይ ተመስርቶ ልዩ ምርመራ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል። ከዚህ ባሻገር በግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው ላይ ህጻናትና ታዳጊዎች ጉዳዩን ከትምህርት ቤት ጀምሮ አውቀውት እንዲያድጉ ለማድረግ በትምህርት መርሃ ግብር ላይ ለማካተት እየተሠራም ነው። ከዚህ ባሻገር አቅም ያላቸው የስፖርት ማህበራት በአበረታች መድኃኒት ዙሪያ በራሳቸው ባለሙያ ታግዘው እንዲሠሩ ማድረጉን እንዲሁም የክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎችም የየራሳቸው የህክምናና የጸረ-አበረታች መድኃኒት መቆጣጠሪያ ቢሮ እንዲከፍቱ እያደረገም ነው።
ከዚህ ባሻገር ጽህፈት ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት ለባለ ድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ቢያዘጋጅም፤ ከአንድ ወቅት ጉዳይነት አለማለፉ በሚፈለገው ልክ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው እንዳልተሠራ ተጠቁሟል። በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ምሁራን እንደሚጠበቀው በጉዳዩ ላይ ከማስተማር ይልቅ ዝምታን መርጠዋል። በመገናኛ ብዙኃን በኩልም በስፋት የመሥራትና በየጊዜው በማንሳት በኩል ድክመት ታይቷል። ከዚህ በኋላም ባለሙያዎቹ በራሳቸው ምርመራ በማድረግና የተደበቁ ጉዳዮችንም ይፋ በማውጣት እንዲተባበሩ ተጠይቋል። መገናኛ ብዙኃኑ በተለይ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ለህብረተሰቡ ማድረስ እንዲችሉ በየወቅቱ መድረኮች ይዘጋጃሉም ተብሏል።

የዓለም ዋንጫን ወሳኝ ምዕራፍ ለመግለጥ

 

ሩሲያ ወደ ታላቁ የእግር ኳስ መድረክ ከጋበዘቻቸው 32 አገራት አሁን ላይ ግማሽ ያህሉን ወደየመጡበት ሸኝታለች። በጥቂት ቀናት ውስጥ ደግሞ ወደ ዓለም ዋንጫው ግማሽ ፍጻሜ በሚደረገው የሞት ሽረት ትግል አቅመ ቢስ ተሸናፊ የሆኑትን ሌሎች ተሰናባቾች ታሳውቃለች።
ዓለም ዋንጫውም በሞት ሽረት የጥሎ ማለፍ ወሳኝ የጨዋታ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። አገራትም ይህን ምዕራፍ ለመግለጥና ሞስኮን ላለመሰናበት ያላቸውን አቅም አሟጠው ለመታገል ዝግጁ ሆነዋል። ይህን ተከትሎም 16ቱን ከተቀላቀሉት ሀገራት መካከል የትኞቹ የጥሎ ማለፍ ጨዋታውን አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ያመራሉ የሚለውን የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።
በዛሬው መርሃ ግብርም በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎችም በሩሲያ የሚቆዩና የማይቆዩ ሁለት አገራት ይታወቃሉ። በዛሬው ጨዋታ ከየምድቦ ቻቸው አልፈው ጥሎ ማለፉን ከተቀላቀሉት ቡድኖች መካከል፤ የምድብ አምስት አንደኛን ከምድብ ስድስት ሁለተኛ እንዲሁም ከምድብ ሰባት አንደኛ ከምድብ ስምንት ሁለተኛ ጋር ያፋለማል። ወደ ዓለም ዋንጫው ግማሽ ፍጻሜ የሚደረገው የሞት ሽረት ትግልም ብራዚልን ከ ሜክሲኮ፤ ቤልጂየም ከጃፓን ያገናኛል። ቅድሚያ በሳማራ ስታዲየም የሚካሄደው ጨዋታም የደቡብ አሜሪካዎቹን ብራዚል እና ሜክሲኮን የሚያፋጥ ጠው ነው።


የዓለም ዋንጫውን ሻምፒዮን ጀርመን አንድ ለዜሮ በማሸነፍ የዓለም ዋንጫ የስኬት ጉዞዋን አሃዱ ያለችው ሜክሲኮ፤ይህን ጉዞዋን በጥሎ ማለፉ ለመደግም ከዓለም ዋንጫው ድምቀቶች ጋር ብርቱ ትንቅንቅ ታደርጋለች።
በዚህ ጨዋታ ለሜክሲኮዎች ወሳኝ የቤት ሥራ የሚሆነው በኔይማር ጁኒየርና በፊሊፔ ኩቲኒሆ እና በገብርኤል ጂሰስ የሚመራው የብራዚል የፊት መስመር ማቆም እንደሚሆን ታምኖበታል። ሜክሲኮዎች በሲውዲኑ ጨዋታ የሠሩትን የመከላከል ስህተት በቢጫ ለባሾቹ ጨዋታ የሚደግሙት ከሆነ ደግሞ ውጤቱ አስከፊ እንደሚሆንባቸው ጥርጥር አይኖረውም።
የዓለም ዋንጫ ጅማሮዋን ከሲውዘርላንድ ጋር አቻ በመለያየት በአስደንጋጭ ሁኔታ ብትጨምርም፤ ኮስታሪካና ሰርቪያን በማሸነፍ ደጋፊዎቿን ማረጋጋት የቻለችው ብራዚል፤ የሩሲያ ዓለም ዋንጫ አቋም ግን አሁንም ቢሆን ብዙዎችን አላስማማም። ይሁንና በየጨዋታው መሻሻል ማሳየቷን ዋቢ በማድረግ፤ ከሜክሲኮ ጋር የምታደርገውን ጨዋታ በብቃት እንደምታሸንፍ የሚገምቱም ብዙዎች ሆነዋል።
የደቡብ አሜሪካዎቹ ፍልሚያም በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ ከወዲሁ ተጠባቂ የሆነ ሲሆን፤ አገራቱም ጨዋታውን አሸንፈው ክብራቸውን ከፍ ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅትን አጠናቀዋል። ሜክሲኮዎች በጨዋታው ውጤት ለማግኘት በግብ አዳኟ ጃቪየር ሀርናንዴዝ ቺቻሪቶ እና በካርሎስ ቬላ ስትተማመን በድንቅ የእግር ኳስ ችሎታ በተካኑ ኮከቦች የተወከለችው ብራዚል በበኩሏ ለወርቃማው ልጇ ኔይማር ጁኔየር ዋናውን ኃላፊነቱን ሰጥታለች።
ሁለተኛውና በሩስቶቭ አሬና የሚካሄደው ሌላኛው ወሳኝ ጨዋታ ደግሞ፤ ቤልጂየም እና ከጃፓን መካከል የሚካሄደው ነው። የዚህ ጨዋታ ውጤትም አንዱ አጋር በሞስኮ እንደሚቆይ ዋስትና ይስጣል። ይህን ጨዋታ ሰፊ የማግባት እድሎችን በመፍጠር የማይታሙት የሮቤርቶ ማርቲኔዝ ልጆች፤ በቀላሉ ሊያሸንፉት እንደሚችሉ ከወዲሁ ተገምቷል።
የእስያ ተወካዮቹ በአንፃሩ በቀላሉ እጅ እንደማይሰጡና በሞስኮ የሚያቆያቸውን ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚፋለሙ«እመኑን» እያሉ ናቸው። ይሁንና በሮሜሎ ሉካኩና በኤዲን ሃዛርድ የሚመራውን የቤልጅየሞች የማጥቃት ጥምረትን ለጃፓኖች እጅጉን ከባድ እንደሚሆን ተገምቷል። የዓለም ዋንጫን ወሳኝ ምዕራፍ ለመግለጥ የዛሬው ዓለም ዋንጫ የሞት ሽረት ጥሎ ማለፍ ጨዋታም ለሁሉም መልስ ይሰጣል።

ብርሃን ፈይሳ

Published in ስፖርት
Monday, 02 July 2018 17:33

ወራፋየ ነው…

መቼም በዛሬ ጊዜ ያለ ወረፋ የሚገኘው አየር ብቻ ሆኗል። ጉድ እኮ ነው!! ለመብላት ወረፋ፣ ለመግዛት ወረፋ፣ ሥራ ለማግኘት ወረፋ፤ አሁንማ ፓርላማም ለመግባት በወረፋ ሆኗል አሉ። «ወረፋዬ ነው…» የሚባልበት ነገር በዛ'ኮ ጎበዝ፡፡ በምንሄድበት ቦታ ሁሉ ተሰልፈንም፣ ወረፋ ጠብቀንም የምንፈልገውን ማግኘት እንኳ አቅቶናል። በተለይ በታክሲና በሆስፒታሎች አካባቢ አገልግሎት ማግኘት ከባድ እየሆነ ነው። እንደውም «ወረፋዬ ነው…» በሚባልባቸው አካባቢዎች የታዘብኳቸውን ባካፍላችሁስ፤
በአሁን ወቅት አዲስ አበባ ላይ ታክሲ ከማግኘት የወደቀ መርፌ ማግኘት ቀላል ሆኗል። ሰሞኑን ታዲያ ለግል ጉዳዬ ስታዲየም አካባቢ ታክሲ በመጠበቅ ላይ እንዳለሁ ኃይለኛ ዝናብ መጣል ጀመረ። የዘንድሮ ዝናብ እንደ መንግስት መሥሪያ ቤት ፊርማ መውጫና መግቢያ ላይ መምጣት ግዴታ የሆነበት መስሎ የለ!? እናላችሁ ዝናቡን ለመከለል ገሚሱ ዣንጥላውን ዘረጋ የተወሰነው ሰው ደግሞ መጠለያ ወዳለበት ቦታ አመራ። እኔም ዣንጥላ የያዙት ጋር ተጠግቼ ታክሲ ጥበቃዬን ቀጠልኩ... የተወሰነ እንደቆየን ታክሲ መጣ። ይሄኔ ከየት መጡ ሳይባል፤ እንደው በቅጽበት ሰው ግልብጥ ብሎ ታክሲዋን ወረራት።
«ወረፋዬ ነው… ወረፋዬ ነው….» የሚሉ ድምጾች ከመሃል ይሰማሉ። የተሰለፍነውን ረግጠው አካባቢውን የትርምስ አደባባይ አስመሰሉት! ዝናቡ እየባሰ በመምጣቱ እኔም ሰልፌን ጥዬ ወደ አንድ ጥግ አመራሁ። ጭራሽ ራቅ ተብሎ ሲታይማ ጉድ ያሰኛል። ሰው መተራመሱን አላቆመም። ጭራሽ «ወረፋችን ነው፤ ዝናብ ለመጠለል ጥግ ይዘን ነው» የሚሉ በመብዛታቸው ታክሲው ሳይጭን ትቶ ሄደ።
እንደዚህ አይነት ክስተቶች ከመለመድም አልፈው «ወረፋዬ ነው…» የሚለው ቃል እንደ መብት ማስከበሪያ እና መሟገቻ ተቆጥሯል። እንደውም ሲመስለኝ፤ በጊዜ ሂደት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት መመሪያ ሲያወጣ «ወረፋዬ ነው…» ለምትለው አንድ አንቀፅ ማስቀመጡ አይቀሬ ነው።
መቼም በአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት ተቋማት ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በተለይ አንድ የነበረ ተቋም በኤጀንሲና በባለስልጣን አደረጃጀት እየተቆራረጠ በመውጣቱ የአዳዲስ መሥሪያ ቤቶች ቁጥር ከነባሩ በልጧል። በእነዚህ መሥሪያ ቤቶች የሴት ሠራተኞች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መታየቱም መንግስት ለሴቶች ምን ያክል ትኩረት መስጠቱን ያሳየናል። ጥናቱ ባይነግረንም የምናየው ነገር ነዋ!
ዋና ጉዳዬን ትቼ ወሬ አበዛሁ መሰል! … ቆይ ግን አስተውላችኋል? በመንግስት መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የመውለድ መጠን እየበዛ መጥቷል። አንዳንድ ቦታማ ቀጣይ አመት «ወረፋዬ ነው…» እየተባባሉ ቀን የሚያስይዙ አይታጡም።
የልጆቻቸውን የልደት ቀን ብንመለከት እንኳ ልዩነቱ የወራትና የቀናት ብቻ ነው እኮ! እንደውም ለወረፋ እንዲመች ነው መሰል መንግስት የወሊድ ፈቃዱን ከሶስት ወር ወደ አራት ወራት እንዲራዘም ያደረገው። ይህ ለመውለድ የሚያዝ ወረፋ መንግስት መሥሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን በየሰፈሩም የሚስተዋል ጉዳይ ነው። የወለደችውን ሴት ለማረስ እንዲመች ነው መሰለኝ በዓመት በመከፋፈል እየወለዱ ይገኛሉ።
ሌሊት ተነስቶ ወረፋ ከሚያዝባቸው ምክንያቶች አንዱ ሆስፒታል ቅድሚያ ለማግኘት መሆኑ አያጠያይቅም። ታዲያ እኔም አቅራቢያዬ ከሚገኘው ጤና ጣቢያ ቅድሚያ ለማግኘት 12፡00 ተነስቼ ወረፋ ይዤ አውቃለሁ። ሰዓቱ ደርሶ ከሠራተኞቹ ከክላሰር የተሠራች ወረፋ መያዣ ቁጥር ተሰጥቶኝ ቁጭ ብያለሁ። ካርድ ማውጣት ሲጀመር ወረፋ የሌላቸው ሰዎች መስተናገድ ጀመሩ። ግራ ተጋብቼ ምንድነው ጉዳዩ ስል ሰዎቹ ወረፋ ብለው ድንጋይ አስቀምጠው እንደነበር ተነገረኝ። ለካ ሆስፒታል ውስጥ ድንጋይም እንደ ወረፋ ይታያል…. እኔ መች አውቄ !!!
እናላችሁ «ወረፋዬ ነው» የሚባልበት ነገር እየበዛ መጥቷል። በየሄድንበት ቦታ «ወረፋ ጠብቁ፣ ወረፋችሁ አይደለም…» ምናምን ተብለንም የምናገኘው አገልግሎት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለነገሩ ተዉት! ወረፋ የመያዝ ባህላችን ለካ እራሱን የቻለ ትዝብት ነው። አብዛኛው ሰው ካልተጣበቀ የተሰለፈ የማይመስለውና ያለወረፋው መግባት እንደ ብልጠት የሚያይ ነው እኮ። ብቻ እናንተም «ወረፋዬ ነው» በሚለው የራሳችሁ ምልከታ እንዳላችሁ አምናለሁ፤ እኔ ግን በዚሁ ላብቃ!!

መርድ ክፍሉ

Published in መዝናኛ

የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ስልጠና ዘርፉ ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ አስመልክቶ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ከመገናኛ ብዙኃንና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል፡፡ በዚህም እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችና ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት መስኮች ተዳስሰዋል፡፡ በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶች ሁሉም የሚያውቃቸውና ተደጋግመው የተነሱ ስለሆኑ ለዛሬው መከናወን ሲገባቸው ሳይከናወኑ በቀሩ ቀሪ የቤት ሥራዎችና በቀጣይ ሊሰሩ በታሰቡ አንኳር የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ትኩረታችን አድርገናል፡፡
በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ
የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተሳትፎን ማሳደግ፣ አግባብነቱንና ጥራቱን ማስጠበቅ፣ ዕድሜያቸው ለደረሱ ህጻናት ጥራቱን የጠበቀ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ማዳረስ ከአጠቃይ ትምህርት ዘርፉ ዓላማዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህን ዓላማዎች ከማሳካት አንጻር ብዙ ርቀት ቢኬድም አሁንም ድረስ ያልተሰሩ ቀሪ የቤት ሥራዎች መኖራቸውን በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት መሻሻል መርሐ ግብር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዮሐንስ ወጋሶ ይናገራሉ፡፡ እነዚህም ጉዳዮችም ከአጠቃላይ ትምህርት ጥራት አንጻር፣ ከትምህርት ተሳትፎ ፍትሐዊነትና ውስጣዊ ብቃት እንዲሁም የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት አኳያ የሚታዩ ናቸው፡፡
የሰለጠኑ የቅድመ መደበኛ መምህራን እጥረት፣ ከተቀመጠው የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ስታንዳርድ አንፃር አብዛኛው ትምህርት ቤት ከደረጃ በታች መሆን፣ የመምህራን የትምህርት ቤት አመራር የሙያ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደት በተፈለገው ፍጥነት አለመፈፀም፣ የተማሪዎች የትምህርት ውጤት በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን፣ የመፅሐፍት ህትመት አበረታች ቢሆንም በስርጭትና አጠቃቀም ዙሪያ ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸው አጠቃላይ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ ያልተሰሩ ቀሪ ሥራዎች ናቸው፡፡ የትምህርት ቴክኖሎጂን በአግባቡ ከመጠቀም አንፃር የመሰረተ ልማት፣ የክህሎት እና የአመለካከት ችግር መኖር፣ ከስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት አንፃር የሚፈለገውን ዉጤት አለማምጣትም የዘርፉ ተጨማሪ ተግዳሮቶች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
የትምህርት ተሳትፎ፣ ፍትሐዊነት እና ውስጣዊ ብቃት ከማሳደግ አኳያም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋንን በ2012 ዓ.ም 74 በመቶ ለማድረስና ዕቅዱን ለማሳካት የተጠናከረ ርብርብ እንዲሚጠይቅ የሚያሳይ አመላካች መኖሩ ተጠቁሟል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ (1-8) ያለው መጠን ማጠናቀቅ 54 በመቶ ብቻ መሆኑና አፈፃፀሙ ካለፉት ዓመታት አንፃር መሻሻል ያሳየ ቢሆንም የትምህርት ዘርፉን ውስጣዊ ብቃት እየተፈታተነው ያለ ተግዳሮት መሆኑ ተለይቷል፡፡
አብዛኛዎቹ ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸውን ህፃናት በተመለከተም በተለያዩ የአመለካከት ችግሮች ምክንያት ወደ ትምህርት ገበታ አለመምጣት እና ወደ ትምህርት ቤት ለመጡትም የትምህርት ተቋሞች ምቹ አለመሆን፣ በትምህርት ዘርፉ የሴት አመራሮች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆንም ተሳትፎን ከማሳደግ አኳያ ተግዳሮት ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም የአራቱን ልዩ/አፋር፣ ሱማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ/ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች የትምህርት እርከን አማካኝ የትምህርት ተሳትፎ ከአገር አቀፉ አማካኝ ጋር ለማመጣጠንና በተለይም የነባር ብሄረሰብ እና የአርብቶ አደር ህፃናትን የትምህርት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም አሁንም የሚፈለገዉ ደረጃ ላይ አለመድረሱ ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡
የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትን በተመለከተም ከላይ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያለው የጎልማሶች የትምህርት ቦርድና የቴክኒክ ኮሚቴ በተቀናጀ መንገድ ፕሮግራሙን አለመምራት፣ የመርሃ ግብሩ ከጎልማሶች የኑሮ ክህሎት ጋር አቀናጅቶ መስጠት ሲገባ በማንበብ መፃፍና ማስላት ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን፣ በየደረጃው ወቅታዊ እና ተአማኒነት ያለው መረጃ ፍሰት አለመኖሩ የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡
በመሆኑም በትምህርት ዘርፍ የተጠያቂነት ስርዓትን ማስፈን፣ የመምህራን ትምህርትና ስልጠና፣ የማስተማር ተግባር ውጤታማነትና የትምህርት አመራር ከምልመላ እስከ ስምሪት ያለውን አሰራር መከለስ፣ ትምህርት ቤቶችን ወደ ደረጃ ማስጠጋትና አገልግሎትን ማሻሻል፣ ቴክኖሎጂን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን አጠቃቀሙንም ማሻሻል በዚህ ዘርፍ ሊሰሩ የሚገባቸው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ የትምህርት እድል ያላገኙ የአርብቶ አደር ልጆችን ጨምሮ ለአካል ጉዳተኞችና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ልጆች ልዩ ትኩረት መስጠትና የጥራት ማረጋገጫ ፓኬጆችን ለትምህርቱ ዘርፍ ግብአት አድርጎ መጠቀምም በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፉ የታዩትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ
በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጽሁፍ ያቀረቡት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የአሰራር ውጤታማነት አስተባባሪ አቶ ኃይለሚካኤል አስራት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ተግዳሮቶች መካከል ኢንዱስትሪው ባለቤትነት በሚፈለገው ደረጃ አለመድረሱ፣ በሙያ ደረጃ ዝግጅት ክፍትት መኖሩ፣ በሙያ ብቃት ምዘና ተግባራት፣ በትብብር ስልጠና እንዲሁም በሙያ ብቃት ምዘና ላይ የሚስተዋል ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የተቋማት ተደራሽነት ችግር እንዲሁም የስልጠና ጥራት ማነስ ይገኙበታል፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት የሚያቀጭጭ የንግድ እንቅስቃሴ መኖሩ፣ ስለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የህብረተሰቡ ግንዛቤ አነስተኛ መሆንና የመረጃ አያያዝ በቴክኖሎጂ የታገዘ ያለመሆን ዘርፉን ካጋጠሙ ተግዳሮቶች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በተለያዩ ምድቦች ተከፍለው ተቀምጠዋል፡፡ የመጀመሪያው በሙያ ደረጃ ምደባና ብቃት ምዘና ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን በሙያ ደረጃ ምደባና ብቃት ምዘና የኢንዱስትሪውን ባለቤትን ለማረጋገጥ የሚሰራው የንቅናቄ ስራ ማጠናከር በቀጣይ ደግሞ ራሱን በቻለ የኢንዱስትሪ አደረጃጀት ስራው በባለቤትነት እንዲመራ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ በዚህም በሙያ ብቃት መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳብ የምላተ ህዝቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ ሙያዊ ብቃት የተረጋገጠ ዜጋ ለሁለንተናዊ ተወዳዳሪነት ያለውን ፋይዳ ማስገንዘብ፣ የሙያ ብቃት ምዘና ስርዓቱን ተዓማኒነት ማጎልበት፣ ሙያ ብቃት ምዘና ተደራሽነት ማስፋት እና ከኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ መታደግ የሚያስችሉ ሥራዎች የሚከናወኑ ይሆናል፡፡ በሙያ ብቃት ምዘና የኢንዱስትሪውን ተሳትፎና ባለቤትነት በማሳደግ ብቃት ያለውና ስነ ምግባር የተላበሱ መዛኞችን ማፍራት፤ እንዲሁም ጥራት ያላቸውና መስፈርቱን የሚያሟሉ ምዘና ማዕከላትን ማፍራትም በዘርፉ ቀጣይ ትኩረትን የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጡት የትኩረት አቅጣጫዎች የሰልጣኝ ልማትና የተቋማት አቅም ግንባታ የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በአነስተኛ ወጪ ተቋማትን በመገንባት ማስፋፋትና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የተቋማትን ቀጣይነት ያለው የፋይናንሲንግ ስርዓት መዘርጋት፣ አሰልጣኞችን በሚፈለገው ቁጥር፣ ዓይነትና ጥራት ማፍራት፣ የሴት አሰልጣኝ ተሳትፎ ማሳደግ በዚህኛው ምድብ ውስጥ የሚካተቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ የትብብር ስልጠና ሽፋንና ጥራት ማሻሻል፣ አጫጭር ስልጠና እና የአርሶ አደርና አርብቶ አደር ስልጠናዎችን ተደራሽነትና ጥራት ማሻሻል፣ የሴቶችንና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና እኩል ተጠቃሚነት ማሳደግ እንዲሁም ለታዳጊ ክልሎች ልዩ ድጋፍ መስጠትና አቅማቸውን ማሳደግ የትኩረት አቅጣጫው አካል ናቸው፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ስራዎች የሚመለከቱ ሥራዎች ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ሊሰሩ የታቀዱ የዚህ ዘርፍ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ አዋጪ የሆኑና ከውጭ ሀገር የሚገቡትን ለመተካት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራ፣ ከዩኒቨርስቲዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተሳስሮ መስራት፣ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ውጤታማነት እንዲረጋገጥ በአንቀሳቃሽ ደረጃ ብቃቱ በሙያ ብቃት ምዘና እንዲረጋገጥ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ እንዲሁም በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ገበያ ላይ በሚኖረው የምርትና አገልግሎት ተወዳዳሪነቱ ላይ ተግዳሮቶችን መለየትና መቅረፍ፣ የክትትል፣ የድጋፍና የግብረመልስ ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
የፋብሪኬሽንና የብየዳ ልህቀት ስራዎች በተመለከተም በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃታቸውን ያረጋገጡ የብየዳ ባለሙያዎችን በስፋት ለማፍራት ታቅዷል፡፡ ትራክተር የመስራት የሀገር ውስጥ አቅም ለመፍጠር የሚደረገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠልና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አቅም መገንባትም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡ ለዚህም የክትትልና ድጋፍ ስርዓቱን ማጠናከር፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን መቀመርና ማስፋት፣ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ማዘመንና በየደረጃው ተግባሩን የሚይዝ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ ሆኗል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ቀሪ ሥራዎችና ሊኖረው የሚገባው ቁመና
የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አማካሪ አቶ ይበልጣል አያሌው በበኩላቸው እንደሚገልጹት በሁሉም ዘርፎች የተጀመረውን ዕድገትና ልማት ማስቀጠል የሚችል የሰው ኃይል በማቅረብ የኢትዮጵያን ህዳሴ በአስተማማኝ መልኩ ማሳካት ወደ ሚቻልበት ደረጃ ላይ ማድረስ የሚገባ መሆኑ መግባባት ላይ ተደርሶበታል፡፡ ለዚህም በቂና ብቁ ምሩቃንን በማፍራት አገራዊ የማስፈፀም አቅምን ማሳደግ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ዋና የርብርብ ማዕከል ማድረግ ትኩረትን ይሻል፡፡
በዚህ ረገድ ወደ ኢንዱስትሪ መርና ወደ መካከለኛ ገቢ አገርነት ለመሸጋገር በሚደረገው ፈታኝ ሂደት ውስጥ ለሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች በቂ፣ ተወዳዳሪና ብቁ የሰው ኃይል በማቅረብ ምርታማነትን በማሳደግ ልማቱ በማይቆራረጥና በዘላቂነት እንዲያድግ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ዋና የርብርብ ማዕከል በማድረግና በሁሉም እርከን ትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የዚህ ዘርፍ ተዋናዮች ፋና ወጊ ሆነው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውም ተመላክቷል፡፡ ከዚህ አኳያ በቀጣይ የሚኖሩና የሚስፋፉ መሰረተ ልማቶች እየገዘፉና እየተወሳሰቡ መሄዳቸው ስለማይቀር የሚዘጋጀው የሰው ኃይል፣ የሚካሄደው ምርምርና የሚተላለፈው ወይም የሚፈልቀው ቴክኖሎጂ የዚህ ዘርፍ ልማት ጥራት ያለውና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን የሚያስችል ሥራ መሰራት የሚገባቸው ቀጣይ የቤት ሥራዎች ናቸው፡፡
ከየዕድገት ምዕራፉ ጋር የሚሄድ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ፣ አመለካከትና ስራ ባህል እንደዚሁም ተገቢ አመራር መስጠት የሚችል ኃይል ዝግጅት ስራ በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች በከፍተኛ ጥንቃቄ መፈፀም እንደሚገባውም ጽሁፍ አቅራቢው ይናገራሉ፡፡ በዚህ ረገድ በየዕድገቱ ምዕራፍ የሚከሰቱ የማህበራዊና የፖለቲካዊ ጉዳዮችን መስተጋብር ግንዛቤ እንዲጨበጥባቸውና ለሚከሰቱና ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮች በዕውቀትና በምርምር ላይ የተመሰረቱ ማብራሪያና መፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ የተቋማቱ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ይህም በጅምር ያለ ዲሞክራሲ የሚያጋጥመውን ችግር በጥልቀት በመረዳት መፍቻ የሚሆን ሳይንሳዊ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል የተሞክሮ ምንጭ ለመሆን የዘርፉ ተዋናዮችና ተቋማት በራሳቸውም ውስጠ ዲሞክራሲ ሊኖራቸው የሚገባ መሆኑን ያመላክታል፡፡
ከዚህ አኳያ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፉ ቀጣይ የቀጣይ ትኩረት መስኮች በሚከተሉት አንኳር ጉዳዮች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ይሆናሉ፡፡ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ በበርካታ ባለድርሻ አካላት መጠየቁ እንደተጠበቀ ሆኖ አገራችንን በማይናወጥ የልማት ጎዳና ለማስቀጠል የሚቻለው ብቁ ዜጋ እስካፈራን ብቻ መሆኑ መግባባት ሊፈጠርበትና የትኩረት ነጥብ ሆኖ ሊሰራበት እንደሚገባ ማስገንዘብና ለዚሁ ማዘጋጀት ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ብቁ ዜጋ ከማፍራት ጎን ለጎን የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች በሚያካሂዱት ምርምር ቴክኖሎጂ የማመንጨትና የመጠቀም አገራዊ አቅም የማሳደግ ተጨማሪ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለዚህም የሚካሄዱ ምርምሮች ጥራትና አግባብነታቸው እንዲጨምር ጥብቅ አመራርና ተገቢ ሃብት እንዲኖራቸው ማድረግ ያሻል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች በውስጣቸው መልካም አስተዳደርን በማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገል በዚህ ረገድ የልህቀት ማዕከል ማድረግም ግድ ይላል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ መሪዎች፣ መምህራንና ሌሎች ሰራተኞች በየተሰማሩበት ብቁ ትውልድ ለማፍራት የሚወጡት የተናጠልና የጋራ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ለተማሪዎቻቸው አርዓያና በሌላው ሕይወታቸውም ጭምር መማር የሚችል የመልካም ስብዕና ባለቤት እንዲሆኑ ማብቃት በቀጣይ ትኩረት የሚፈልግ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

 ይበል ካሳ

Published in ማህበራዊ


ከተሜነት የአንድ አገር ልማት መለኪያ የማህበረሰብ እድገት ማሳያም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዓለማችን ላይ ከተሜነት በአማካይ 77 በመቶ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ከ20 በመቶ ያልዘለለ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን አሁን በኢትዮጵያ ከተሞች እየተስፋፉ፤ የከተሜዎችም (የከተማ ነዋሪዎችም) ቁጥር እየበረከተ መምጣቱ ይነገራል፡፡ ይህ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር መጨመር ደግሞ ከመንግስት የሚጠበቀው አገልግሎት አብሮ ማደግ ካልቻለ የመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ እንደሚሆንም ይገለጻል፡፡ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ባለው ከተሜነት ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ከተሞች እንደሆኑ ኃላፊዎች ይገልፃሉ፡፡
በአገር ልማትም ሆነ በማኅበረሰብ እድገት መለኪያነት የሚታዩ እነዚህ ከተሞች በመልካም አስተዳደር ችግር የሚታመሱ ከሆነ የሚፈለገው አገራዊ ለውጥ ሊመጣ፤ ማህበራዊ እድገትም ሊንጸባረቅ እንደማይችልም የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ እኛም ለዛሬው እትማችን በኦሮሚያ ክልል ያሉ ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ ከመልካም አስተዳደር አኳያ ምን ገጽታ አላቸው? የከተሞቹ መሰረታዊ ችግር ተብለው የተለዩ ነገሮችስ ምንድን ናቸው? ምንስ አቅጣጫ ተቀመጠላቸው? በሚሉና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የኦሮሚያ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የከተሞች የመልካም አስተዳደር ሲባል ምን ማለት ነው?
ዶክተር ቢቂላ፡- ለመልካም አስተዳደር ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ከተጋለጡት የአገራችን ክፍሎች መካከል አንዱ የከተማው ሴክተር ነው፡፡ የከተማው ሴክተር ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የሕዝብ ምልልስ እንዲሁም ሰፊ የአገልግሎት ፍላጎት ያለበት ነው፡፡ ህዝቡም ለመረጃዎች ቅርበት ያለው እንደመሆኑ የአገልግሎት ደረጃን ከፍ አድርጎ የሚያይ እና ከጎረቤት አገሮችም ሆነ ከሌሎች ከተሞች እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ከተሞችም ጭምር የሚያወዳድር ነው፡፡ በመሆኑም በከተሞች ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎት ተጠያቂነትን ያከበረ፣ ግልጽነት ያለበትና ቀልጣፋ የሆነ፤ ከጊዜ፣ ከጥራትና ከገንዘብ አንጻር የማያንገላታና በቅርበትም እንዲገኝ የሚፈልግ ነው፡፡
በመሆኑም ይሄ ተገንዝቦ የከተሞችን የመልካም አስተዳደር ማረጋገጥ ለህዝቦች ፍላጎት መሳካት ለከተሞችም እድገት ግብዓት የሚሰጥ ነው፡፡ በሌላ በኩል የከተማው ህዝብ በራሱ የመልካም አስተዳደር ችግሩ ከተፈታ ከተሞቻችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ መስተጋብር ማዕከል እንደመሆናቸው ለአገር ልማት ያለው ፋይዳ እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሰሞኑን የተካሄደው የክልሉ ከተሞች ፎረምም በከተሞች የመልካም አስተዳደርን ከማስፈን ጀምሮ በየደረጃው የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተናበበና በተሰናሰለ መልኩ ለመስራት የሚያስችል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኦሮሚያ ክልል ባሉ ከተሞች ያለ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ቢቂላ፡- ባለፉት ሶስት ዓመታት በከተሞቻችን አካባቢ የሚታዩ የሕዝብ ቁጣና እሮሮዎች በአብዛኛው ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ እነዚህ በመንግስት ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት በማግኘታቸው ምክንያት አንድ ሁለት ተብለው በከተሞች የሚንጸባረቁ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተለይተዋል፡፡ እነዚህ የከተሞች የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ከመሬት አስተዳደር፣ ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፣ በግዢ፣ ፋይናንስና በከተሞች አመራር አካባቢ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመሆናቸው ተለይተው እየተሰራባቸው ነው፡፡
ከእነዚህ ብዙዎቹ ችግሮች በአጭር ጊዜ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም የበጀትና የረዥም ጊዜ እቅድ የሚጠይቁ፤ በዋናነትም የህዝቡን ተሳትፎ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት ብዙዎቹ ተለይተው ከከተማው ሕዝብ ጋር ውይይት እየተደረገባቸው ነው፡፡ በዚህም መቼ፣ እንዴትና፣ በምን ሁኔታ እንደሚፈቱ መግባባት ላይ በመድረስ የሚፈቱ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ደግሞ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በዚህም በማለቅ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችንና በተለያየ ሁኔታ ተጠናቅቀው ለሕዝብ መድረስ ሲገባቸው ለሕዝብ ያልደረሱ ፕሮጀክቶችን በተመለከተም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ከ80 በመቶ በላይ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ቅድሚያ በመስጠትም ለከተማው ህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጋር በተያያዘም በፍጥነት አሰራሮቻችንን በማስተካከል፤ እንዲሁም ቢሮው አካባቢ በሚደረጉ ፈጣን ለውጦች በመጠቀም በከተሞች አካባቢ በተለይም በማዘጋጃ ቤት በኩል ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይሄን ለማድረግም በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ በሌሎች የተለዩ ችግሮች ዙሪያም በተመሳሳይ እንደየባህሪያቸው የአጭር ጊዜና የረዥም ጊዜ አቅጣጫ ተቀምጦ የህዝብን ብሶትና እሮሮ ለመመለስ የሚያስችሉ የመፍትሄ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአመራር ብቃት፣ የበጀትና የሰው ኃይል አጠቃቀም፣ እንዲሁም የሙያ ስነ-ምግባር ጉድለቶች በክልሉ ባሉ ከተሞች ከሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህ ችግሮች በክልሉ ከተሞች በምን ደረጃ የሚገለጹ ናቸው?
ዶክተር ቢቂላ፡- እንደ ክልል በዚህ ዓመት የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ከክልል ጀምሮ እስከ ከተማ ቀበሌዎች ድረስ ወርዶ ነው ጥናት ያደረገው፡፡ ጥናቱም ሰፊና ወደ አራት ሺህ ሰዎችን ያሳተፈ እና የዩኒቨርሲቲ ምሑራንን ጨምሮ 40 ያህል ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነው፡፡ በዚህ ጥናት ተለይተው ከወጡ ነገሮች አንዱ በከተሞች አካባቢ ያለው የሰው ኃይል አመራራችን ለከፍተኛ ብክነት የተጋለጠ መሆኑ ነው፡፡ በሙያው ዘርፍም በቀጥታ ህዝቡን ከሚያገለግል የሰው ኃይል (በቀጥታ ህዝብን ከሚያገለግሉ እንደ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎችና በከተማ አገልግሎት ላይ ካሉ ባለሙያዎች) ይልቅ በደጋፊ ሰራተኞች የተሞላ እና አንዳንድ ቦታዎችም አንድን ባለሙያ አራት ደጋፊዎች የሚደግፉበት አግባብ ታይቷል፡፡ በመሆኑም በዚህ መልኩ የባለሙያዎች ቁጥር ማነስና የደጋፊዎች ቁጥር መብዛት ሊስተካከል የሚገባው እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
ከዚህ ባለፈ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት ሲመዘኑም ሰዎች በዲፕሎማ፣ በዲግሪና በማስተርስ ደረጃ የትምህርት ማስረጃው እያላቸው፤ ነገር ግን በዛ ደረጃ የሚመጥን እውቀትና ክህሎት ኖሯቸው ሕዝቡን በቀጥታ የማገልገል፣ እንዲሁም የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ ተላብሰው ማገልገል ላይም ከፍተኛ ውስንነቶች ታይተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በቀላሉ ተገልጋዩን ቀርቦ 50 በመቶ መልካም ፊትና አቀራረብ በማሳየት ብቻ ሊመለሱ የሚችሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፤ በሰራተኞች የስነምግባር ችግር ምክንያት ይሄን ለማድረግ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በሰዓቱ በስራ ቦታ አለመገኘት፣ ተገልጋዮችን የማመናጨቅና አልፎም የተገልጋይን ኪስና እጅ የማየት አዝማሚያም ታይተዋል፡፡ ይህ ደግሞ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አንድ ሰው በከተሞች አገልግሎት ለማግኘት የሆነ ነገር ማቅረብ አለበት የሚል አመለካከት እያዳበረ መጥቷል፡፡ እዚህ ላይም በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑ ግንዛቤ ተይዟል፤ እየተሰራም ይገኛል፡፡
ከአመራሩ ጋር በተያያዘም በክልላችን ከክልል አመራር ጀምሮ እስከ ቀበሌ በሹመት ደረጃ የሚያገለግሉ 23ሺ አመራሮች አሉ፡፡ እነዚህ አመራሮች በተለያየ የትምህርትና ክህሎት ደረጃ የሚገኙ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት በተለይ እየጨመረ በመሄድ ላይ ያለውን የከተሞችን ህዝብ ፍላጎት ከማሟላት አንጻር አመራሩ በእውቀትም፣ በክህሎትም፣ በአመለካከትም ከፍ ብሎ የሚታይና በቅን ልቡና ይሄን ከፍ እያለ የመጣውን የአገልግሎት ፍላጎት ሊያገለግል የሚችል መሆን አለበት፡፡ ይሄንን ስንመለከት በዚህም ረገድ ከፍተኛ እጥረት ነው ያለው፡፡ በክልላችን 41 በመቶ የሚሆነው አመራር ዲፕሎማና ከዚያ በታች በሆነ የትምህርት ደረጃ አገልግሎት እየሰጠ እንደመሆኑም፣ ይሄን ማስተካከል አስፈላጊ ነው፡፡
ከትምህርት ደረጃ ባሻገርም አመራሩ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ኖሮትና አመራርነት ብቻውን እጅግ በጣም ትልቅ ክብር መሆኑን ተገንዝቦ ተገልጋዮችን ቀድሞ ችግሮቻቸውን ለይቶ በእቅድና ፖሊሲ በማስደገፍ ቅሬታ ከመነሳቱ በፊት ቀድሞ በማሰብ የከተማውን ህዝብ ቅሬታ ሊፈታ የሚችል አመራር እያዳበሩ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የአመራር ክህሎት ፕሮግራም በቢሯችን እየቀረጽን ነው፡፡ በየደረጃው እያገለገለ ያለው አመራር በእውቀትም በክህሎትም እየዳበረ እንዲመጣ ስለሚፈልግም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የክልሉን የአመራር ክህሎት በእውቀትም በአመለካከትም ለማዳበር እየተሰራ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው ጥናት የሚያሳየው በዚህ ዙሪያ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩንና በዚሁ ላይ መሰራት እንዳለበት ነው፡

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ከአመራር ሹመትና ምደባ፣ ከፋይናንስ አጠቃቀምና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በህግና መመሪያ ያለመጓዝ ችግር መኖሩ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያስ ያለው ችግር ምን ይመስላል?
ዶክተር ቢቂላ፡- እኛም ያየነው ትልቅ ችግር፣ በጥናቱም የተመላከተው ከዚሁ ከህግና አሰራር ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው፡፡ በክልሉ የምንሰራቸውን ስራዎች በሙሉ በህግ፣ በአሰራር፣ በመመሪያና ስርዓትን ተከትለን የማንሰራ ከሆነ እጅግ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄን በምንመለከትበት ጊዜ በክልላችን በከፍተኛ ሁኔታ በተለይም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ አሰራርን ተከትሎ ያለመስራት ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህን ክፍተቶች ፈጠን ብሎ ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡ በተለይ በታችኛው መዋቅር ወይም ወረዳዎች ላይ የሰው ኃይል ቅጥር፣ ምደባና ደረጃ እድገት ሲሰጥ የሕግና መመሪያ አሰራሮችን ካለመከተል ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸው ለአብነት ሊነሳ ይችላል፡፡ በዚህ መልኩ የሚገለጹ ሕግና አሰራርን የጣሱ አካሄዶች አሉ፡፡
እነዚህ ብቻም ሳይሆኑ በከተሞች አመራር ላይ የሚታዩ አንዳንድ ክፍተቶችና በከፍተኛ ጥንቃቄ አሰራርና መመሪያዎችን ተከትሎ መስራት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች መስተካከል እንዳለባቸው ነው ጥናቱ የሚያሳየው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች የግልጽነትና ተጠያቂነት ስርዓቱን በመሸርሸር የመልካም አስተዳደር ችግርን ይፈጥራሉ፡፡ የከተማውን ህዝብ የአገልግሎት ፍላጎትም የሚጎዱና ቅሬታን የሚያስነሱ በመሆናቸውም በፍጥነት የሚፈቱ ይሆናል፡፡ ለዚህ የሚሆን አሰራርም እየዘረጋን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በከተሞች ያለውን አገልግሎት ለማሳለጥ ሲባል የሚዘረጉ አደረጃጀቶችና መዋቅሮች ውጤታማነት ላይም የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በክልሉ የዚህ ችግር ገጽታ ምን ይመስላል?
ዶክተር ቢቂላ፡- በጥናቱ የተካተተው አንዱ ጉዳይ በከተሞች የምናዘጋጀው መዋቅሮች ህዝብን መሰረት አድርገው መሰራት አለባቸው የሚል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እስካሁን ያሉ የከተሞች አደረጃጀቶቻችን ሲታዩ፣ ህዝቡ ያለው ቀበሌ ውስጥ ነው፤ ችግሩም ያለው ቀበሌ ውስጥ ነው፤ ለችግሩ የሚሆን መፍትሄም ቀበሌ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ነገር ግን ቀበሌ ውስጥ ሕዝቡን በዛ ደረጃ ሊያገለግል የሚችል መዋቅር ባለመኖሩ ምክንያት ዜጎች ከቀበሌ ተነስተው እስከ ከፍለ ከተማ፣ እስከ ከተማ አስተዳደርና ከንቲባ ጽህፈት ቤት ድረስ አገልግሎት ፍለጋ የሚሄዱበት ሁኔታ ታይቷል፡፡
ከዚህ አኳያ በተለይ መሰረታዊ በሚባሉ አገልግሎቶች ተገልጋዮች በየቀኑ ከሚፈልጓቸው አገልግሎቶች አንጻር እነዚህ አገልግሎቶች ለህዝቡ ቀረብ እንዲሉና ወደ ቀበሌ መዋቅሩ ወደታች ወርደው ቢዋቀሩ የተሻለ ነው በሚል ጥናታችን አመላክቷል፡፡ በመሆኑም ወደፊት በምንዘረጋው አዲስ መዋቅር ውስጥ በተለይ ወሳኝ የሚባሉ አገልግሎቶችን በቀበሌ ደረጃ ለማደራጀት የምንሰራ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ባሉ ከተሞች በዚህ መልኩ የሚገለጹት ችግሮች በተለይ ከመልካም አስተዳደር አኳያ ያስከተሉት ችግር ምንድን ነው? ችግሮቹን ለማስወገድስ በምን መልኩ ለመስራት ታስቧል?
ዶክተር ቢቂላ፡- ክልሉ አቅም አለው፡፡ ሰፊ የሰው ሃብት አለ፤ ለም መሬት አለ፤ ይሄን ሊያስተባበር የሚችል መንግስትም አለ፡፡ ሆኖም እነዚህን እምቅ አቅሞች ለመጠቀም አልተቻለም፡፡ በአወቃቀርና በሰው ኃይል አጠቃቀምም ችግር ምክንያት ይሄን ሊያድግ፣ ሊለወጥና የሕዝብን ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል ከፍተኛ አቅም አቀናጅቶ መምራት ባለመቻላችን ምክንያት የሕዝብን ፍላጎት ከማሟላት አንጻር ውስንነቶች አሉብን፡፡ ስለዚህ አንዱ መዋቅራችንን ለሕዝብ በሚመጥን ደረጃ ወደ ሕዝብ አውርደን በማዋቀርና እዛ አካባቢ ያለውን ሃብት በማንቀሳቀስ፣ እንዲሁም ከሕዝቡ ጋር ሆነን ችግሩን ለመፍታትና መሰረታዊ አገልግሎቶቹን ወደ ሕዝብ ቀረብ ብለን ሕዝቡን በማደራጀት ችግሮቹን በመፍታት የሕዝብ ተጠቃሚነትን ከፍ ማድረግ ይቻላል የሚል አቅጣጫ ነው ጥናታችን ያሳየው፡፡ በዚሁ አግባብም እየሰራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በከተሞች የመልካም አስተዳደርን ከማስፈን አኳያ ማን በምን መልኩ መስራት አለበት በሚለው ዙሪያ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎ፤
ዶክተር ቢቂላ፡- ሰሞኑን የተከበረው የኦሮሚያ ከተሞች ፎረም መሪ ሃሳብ እንደሚያስረዳው የሕዝቦች ተጠቃሚነት የተረጋገጠባቸው ከተሞች ለህዳሴው ጉዞ ወሳኝ መሆናቸውን ነው፡፡ ከላይ የተገለጹት አብዛኞቹ ነገሮችም ከሕዝብ ተጠቃሚነት ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ለዚህም መዋቅርንና የሰው ሃብት አጠቃቀምን ማስተካከል ይጠይቃል፡፡ የመዋቅርና የሰው ሃብት አጠቃቀም መስተካከል ደግሞ የበጀትና የሃብት አጠቃቀምን ያስተካክላል፡፡ በመሆኑም የሰው ሃብቱን አቅም ከፍ ማድረግ፣ አመለካከቱንም በማጎልበት ቅን ልቡና ኖሮት ህዝብን እንዲያገለግል ማድረግ ይገባል፡፡
በሰራተኛውም በዚህ ላይ የሚሰራ፤ መዋቅሩ በጣም ውጤታማ በሆነ መንገድ ከላይ እስከታች የሚዘረጋና ብክነትን በሚቀንስ ሁኔታ ከተሰራ፤ በአመራሩና በሰራተኛው ደረጃም የተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋት የምንችልና ክትትል፤ ድጋፋችንም ጠንከር ብሎ የሚሰራ ከሆነ አሁን የሚታዩ የአገልግሎት ክፍተቶችን አስተካክሎ የህዝብ ተጠቃሚነት ብሎ በመሪ ሀሳቡ የተቀመጠውን ነገር ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በዚህ ላይ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮም ሆነ ከተሞቹ፣ ከከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ጋር ሆነን በቅንጅት የጋራ ፕሮጀክቶችን ቀርጸን የምንሰራ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፈቃደኛ ሆነው ለቃለ ምልልሱን ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ቢቂላ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

Published in ፖለቲካ

ኢትዮጵያ ከቡና ግብይት ጋር በተያያዘ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት አዲስ የግብይት አደረጃጀትና አሰራር ተግባራዊ ማድረጓ ይታወሳል፡፡ ሆኖም አሰራሩ ችግሮች እንዳሉበት ይነገራል፡፡ በተለይም ቡና የአገሪቱን 30 ከመቶ በላይ የውጪ ገበያ የሚሸፍን ትልቅ የኢኮኖሚ መሰረት ቢሆንም ዘርፉ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ግን ከውጤት እየጋረደው ይገኛል፡፡ እኛም ለዛሬ በአዲሱ ሪፎርም ዙሪያ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
የአሰራሩ መነሻ
በባለስልጣኑ የግብይት ፈፃሚዎች ዕውቅናና ክትትል ቡድን መሪ አቶ አብደና ማሙዬ እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የግብይት ስርዓት በባህላዊ መንገድ የሚካሄድ፣ አብዛኛው አምራች ተጠቃሚ ያልነበረበት ደላሎች የሚበዙበት አሰራር ነበር፡፡ በዚህም ገንዘባቸው ረጅም ቀናት የሚጠባበቁበት እንዲሁም በደረቅ ቼክ መጭበርበርም የቅርብ ትውስታዎች ናቸው፡፡ ይህም ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ በገዢዎቹ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ችግሮቹን ለማቃለልም ከ10 ዓመት ወዲህ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ተጀምሯል፡፡
ሪፎርሙ ተግባራዊ የተደረገው 2009 ዓ/ም ሲሆን ሰራተኛው እንኳ ዕውቅና እንዳልነበረው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የገበያ ደህንነት የሥራ ሂደት ክትትል ቡድን መሪ አቶ ጌቱ የምሩ ይናገራሉ፡፡ የቡና ምርት ግብይት ላይ የተደረገው ጥናት ሁለንተናዊ የሆኑ ተዋናዮችን ያሳተፈና ያወያየ አልነበረም፡፡ በወቅቱ የነበረውን የመንግስትን ችግር በመመልከት ያጠኑት ጥናት በመሆኑም የተወሰኑ ላኪዎች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን፣ ንግድ ሚኒስቴር፣ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም፣ ግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር እንዲሁም የህብረት ስራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ በግብይት መስተጋብር ውስጥ ወሳኝ አካላት መሆናቸውን ቡድን መሪው ያብራራሉ፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት ይህን ከግንዛቤ በመክተት ላኪዎች ያቀረቡትን መነሻ ተቀብሎ ማጥናት፣ ማወያየት እና የተሟላ ለሪፎርም ግብዓት የሚሆኑ መነሻዎችን መያዝ ላይ ክፍተቶች ነበሩበት፡፡ ይህም የግብይት ተሃድሶው ውስንነት ማሳያ ነው፡፡
መሰረታዊ የመነሻ ክፍተት መኖሩም በግብይት ሰንሰለቱ ከአርሶ አደሩ ማሳ እስከ ላኪው ያለውን ሰንሰለት በመቁረጥ ውጤታማና አጭር ግብይት መፍጠር ንድፈ ሃሳቡ በርካቶችን ቢያስማማም በተግባር ያጋጠመው ግን ከታሰበው በተቃራኒው ሆኗል፡፡ ባለስልጣኑም የሪፎርሙን አፈፃፀም ለመገምገም ለሁለት ጊዜያት ወርዶ ውጤታማ እንዳልሆነ አረጋግጧል፡፡
የሚደረደረው ተሽከርካሪ መጠን ሲበዛ ንግድ ሚኒስቴር፣ የበላይ አካላትና ሪፎርሙን የሚከታተሉ የመንግስት አካላት በመነጋገር በቀጥታ መጋዘን እንዲገባ ተደረገ፡፡ ዓላማው ወጪን በመቆጠብ በዓለም ገበያ የአገሪቱ ላኪዎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል ቢሆንም በአፈፃፀሙ ግን በተቃራኒው ሆኗል፡፡ በዚህ ላይ በግለሰብ ደረጃ ላኪዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ቢኖርም አገሪቱ ግን ማግኘት የሚገባትን ገቢ ማግኘቷ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ይላሉ አቶ አብደና፡፡
በአሁኑ ወቅት
ገበያው በማዕከላዊ ገበያ 347 ወንበሮችን ያዘጋጀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ፍቃድ ወስደው እየሰሩ ያሉት 328 እንደሆኑ አቶ አብደና ያስረዳሉ፡፡ በዚህም 18 ተገበያይ አባል ሲኖረው 310 የሚሆኑት ደግሞ አገናኝ አባላት ለአቅራቢው፣ ለላኪውና ለዓለም ገበያ ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ባለስልጣኑ በ10 ዓመት ቆይታው መስተካከል ያለባቸው ውዝፍ ችግሮችን ለማቃለል ሪፎርም አካሂዷል፡፡ በዚህም የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ከአዲስ አበባ ውጪ በነቀምት፣ ሐዋሳና ጅማ ላይ ለማሳያነት እንዲጀምሩ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መሪነት በተደራጀ ኮሚቴ የተጠናው አዲስ አሰራር በአገር ደረጃ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመመልከት የተከናወነ ነው፡፡ ነገር ግን መፍትሔ ይሆናል በሚል መነሻ ቢጀመርም ችግሮችን ግን የተገነዘበ አለመሆኑ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ በሚያጋጥም ችግር እየታየ ነው፡፡ አዲሱ አሰራር ቀድሞ በቀጥታ ገብተው መገበያየት እንዳለባቸው ቅሬታ ያነሱ ለነበሩ አካላት ዕድል የሰጠ መሆኑን አቶ አብደና ያብራራሉ፡፡ በዚህም አባል ያልሆኑ ቀጥታ ተገበያይ በሚል በተከፈተው አዲስ የአባልነት መደብ 118 ተገበያዮች ደርሰዋል፡፡ ነገር ግን ይህም ቢሆን የራሱ የሆኑ ክፍተቶች እንዳሉት ታሳቢ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ዘመናዊ ግብይት ሲባል ግዴታ በመካከል ያሉት ድልድዮች አስፈላጊ መሆናቸውንም ይገልፃሉ፡፡ ምርታቸው አነስተኛ የሆኑ አርሶ አደሮች ወደ ማዕከላቱ ሲሄዱ የሚያወጧቸው ወጪዎች ኮሚሽን ከሚከፍለው በላይ ስለሚሆን ለእንግልት የሚዳርግ አሰራር ነው፡፡
ሪፎርሙ ከአስፈላጊነቱ እስከ ትግበራው ያለውን ሂደት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መምከር ላይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣንም ክፍተት እንደነበረበት አቶ ጌቱ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም አሰራሩ በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ 90 በተሽከርካሪ ላይ እንዳለ በሶስት ቀናት ውስጥ 10 በመቶ ደግሞ ወደ መጋዘን ገብቶ እንዲሸጥ ቢያስቀምጥም ይህ ሳይሳካ ቀርቶ ሁለት በመቶ ብቻ በተሽከርካሪ ላይ ሽያጭ ተደርጎበታል፡፡ በሌላ በኩል ለስራው የሚረዱ ጥብቅ ማቆያ ስፍራዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ወረቀት ላይ ቢቀርብም በቂ ዝግጅት ሳይደረግ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡
በአንድ ቀን በአንድ ማዕከል ከ600 በላይ ተሽከርካሪዎች እንደሚገበያዩ ታሳቢ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ይህ ግን ተግባራዊ ማድረግ አዳጋች ሆኗል፡፡ ለዚህም በቂ የሰው ሃይል፣ ቦታና ቀልጣፋ አሰራር አለመኖር ምክንያቶች ናቸው፡፡ በተያያዘ በግብይቱ ስነምህዳር ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት ላይም ውጤታማ አልነበሩም፡፡ ጎን ለጎንም ኬሻ ይመለሳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ሊመለስ አለመቻሉንም የቡድን መሪው በችግርነት ያነሳሉ፡፡ በሌላ በኩል የሪፎርሙ ትልቁ ትኩረቱ የነበረው ከአርሶ አደሩ አንስቶ ምርቱ ለውጪ ገበያ እስከሚቀርብበት ያለው ሂደት ቀንሶ ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ጥሪት ማሳደግ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በሂደቱ ማምረት ብቻ ሳይሆን የገበያ ሰንሰለቱ በአግባቡ በጠንካራ ስነምግባር መመራት ላይ ክፍተት እንዳለበት ይታያል፡፡ የተለያዩ አካላት ፍላጎት መጋጨትም እንደሚስተዋል ነው አቶ ጌቱ የሚገልፁት፡፡ ሪፎርሙ ገበያው በአግባቡ ተሳትፎበት በዘርፉ ብቃት ያላቸውን የባለሙያዎች አስተያየት መሰረት አድርጎ የተሰራ ባለመሆኑ ገበያው ላይ የተጣለበት እንጂ አምኖበት እንዳይሰራ አድርጎታል፡፡
በገበያው ታሪክ ውስጥ ክፍተት እየታየ መሆኑን የሚያነሱት የቡድን መሪው፤ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ላይ በጥናት ተመስርቶ ምን ችግር አለ? ምንስ ውጤት ይታያል? በሚል እንዲሁም የሌሎች ዓለም አገራት ተሞክሮ በጥልቀት የፈተሸ አለመሆኑን ማሳያዎችን በማንሳት ያስረዳሉ፡፡ ሪፎርሙ እንደመጣ ገበያው ስጋት ናቸው ያላቸውን ዘጠኝ ሀሳቦች በግልፅ አስቀምጦ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም ማሻሻያው በሚመለከታቸው አካላት የጋራ መግባባት የተፈጠረበት ባለመሆኑ የታቀደው ሊሳካ አልቻለም፡፡
አሰራሩ 90 በመቶ በተሽከርካሪ ላይ እንዲሸጥ ከማስቀመጡ ባሻገርም አንድ ተሸከርካሪ ሙሉ በሙሉ መሸጥ እንዳለበት አስፍሯል፡፡ ይህም አንዱን ጭነት በሙሉ ሳይጎድል አንድ ግለሰብ እንዲገዛ ስለሚያደርግ በኢኮኖሚ የተሻለ ገቢና የብድር አቅርቦት ያላቸውን ተጠቃሚ ሲያደርግ በሌላ በኩል አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ተሳታፊ አያደርግም፡፡ ይህም የተወሰኑ ግለሰቦች ኪሳቸው እንዲደልብ በማድረግ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍሉንም ያዛባዋል በሚል ቅሬታ እየፈጠረ መሆኑን ቡድን መሪው ያሳውቃሉ፡፡
በሌላ በኩል ባለቤትነትን መሰረት ያደረገ የግብይት ስርዓት መዘርጋቱ በችግር ሊነሳ ባይችልም ሁሉን አቀፍ የሆነ የግብይት መስተጋብር መኖሩን መገንዘብ ላይ ትልቅ ክፍተት ይታያል፡፡ ለአብነት 60 ከመቶ የሚደረገውን የጣዕም ምርመራና 40 ከመቶ የሚካሄደውን በጥሬ በሚደረገው ምርመራ የተሻለ ገቢ የሚያገኘው ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ያለው ነው፡፡
ለዚህም ምክንያቱ ላኪው አቅራቢውን እንደሚያውቀው በመግለፅ የተሰጠውን የጥራት ደረጃ እንደማያምንበት ያስቀምጣል፡፡ የተሻለ በሚል የተቀመጠውም ቡና ባለመግዛቱ ሳይሸጥ ይቀራል፡፡ ቤተሙከራ ውስጥ የሚሰሩትን ባለሙያዎችንም ተነሳሽነት የሚገድል ተግባር ከመሆኑ በተጨማሪም ለውጪ ገበያ የሚቀርበው ቡና በጥራቱ የተሻለው እንዳይሆን በማድረግ የአገሪቱ ገቢ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖር ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ጌቱ ገለፃ፤ ላኪዎች ገበያው ለምርቱ የሰጠው ደረጃ ተገቢነት ላይ ጥርጣሬ ካለባቸው በቡናና ሻይ ስር ያለ ሶስተኛ አካል ጋር ቅሬታ በማቅረብ ጥራቱ ከፍ እንዲል ማድረግ አልያም የተጋነነ ከሆነ ማስወረድ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የቀረበውን ከመግዛት ይልቅ አነስተኛ ደረጃውን መውሰድ አገሪቱ በዓለም በቡና ያላትን ደረጃ እንድትለቅ አሉታዊ አስተዋፅዖ ከሚያበረክቱ ምክንያቶች ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ሪፎርሙ ተግባራዊ በሆነበት በአንድ ዓመት ውስጥ የአሰራር ኪሳራ አድርሷል፡፡
ስጋቶች
አሰራሩ ላኪዎችን ፈላጭ ቆራጭ በማድረግ የጠቀመ በሌላ በኩል ደግሞ አቅራቢውን የበደለ እንደሆነም አቅራቢዎቹ በቅሬታ እንደሚያነሱ አቶ አብደና ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ በተያያዘም 15 ሺህ አቅራቢዎች ገብተው ይሳተፉ ማለት ዘመናዊ የግብይት ስርዓቱ የማይፈቅደውና ገበያው ማስተናገድ የማይችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሊያደርገው ይችላል፡፡
በመጀመሪያ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚፈለገው አርሶ አደሩ እንደሆነ የሚገልፁት አቶ አብደና ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ሲደረግ አገርም ተጠቃሚነቷ እንደሚረጋገጥ ዕሙን ነው፡፡ ነገር ግን ስራው ይህን ታሳቢ ያደረገ አለመሆኑ ችግሮችን የሚያባብሱና ግብይቱንም ወደኋላ የሚመልስ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ተስፋ የሚቆርጡበት ስርዓት ከሆነ ዘመናዊነቱን የኋሊት እንደሚወስደው አያጠራጥርም በማለት አቶ አብደና በአሰራሩ ላይ ያላቸውን ስጋት ይገልፃሉ፡፡
አቶ ጌቱ፤ ስራው በዚሁ ከቀጠለ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ከቡና ውጪ በሰሊጥ ላይ የነበረውን ተሞክሮ ለአብነት ያነሳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ሰሊጥ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ዘርፋቸውን እንደቀየሩም ያስታውሳሉ፡፡ ይህም የሚያመላክተው አርሶ አደሩ ተነሳሽነቱ እየወረደ እንዲሄድ እንደሚያደርገው ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ከመሆኑ በፊት ጥልቅ የሆነ ጥናት ማድረጉ ለሁሉም የሚበጅ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ይሆናል፡፡
መፍትሄ
አቶ ጌቱ አገሪቱ በዓለም ላይ ቡናን ለውጪ ገበያ የምታቀርብ አምስተኛዋ አገር እንደነበረች በማስታወስ የቡና ታሪክ የሌላቸው አገራት እየቀደሟት እንዳሉና ደረጃዋም ወደ ስድስተኛ ዝቅ ሊል እንደቻለ ይገልፃሉ፡፡ በቀጣይም ከስድስት ልትወርድበት የምትችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል በመግለፅ ምርታማነት ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ያመላክታሉ፡፡
እያንዳንዱ አካላት ሃሳባቸውን በመድረክ አንፀባርቀው መፍትሔ ላይ ለመድረስ በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ብሔራዊ ባንክ፣ ጉምሩክ እንዲሁም ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ስምምነቱ ላይ የሚሰሩ በመሆኑ አገሪቱ ምን ያክል ክፍተት እንደደረሰባት የመገምገምና መረጃ መስጠት ላይ ክፍተቶች እንደሚታዩም አቶ ጌቱ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ በመሆኑም በቀጣይ የስራ አፈፃፀም ሪፖርቶችም ሲቀርቡ ዕውነታነቱን ማረጋገጥ በሚቻልበት መንገድ መፈተሽ ይገባል ባይ ናቸው፡፡
ቀጣይ
በአዲሱ አሰራር ከዕውቀት ጋር ተያይዞ የሚጋጥሙ ችግሮች ካሉ ባለስልጣኑ በየጊዜው አቅምን ለማጎልበት የተለያዩ ትምህርትና ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ አቶ አብደና ይናገራሉ፡፡ አሰራሩም ያለበት ችግር ተገምግሞ ማሻሻያ እንደሚደረግበት ዕምነት አላቸው፡፡ በማሳያነት የተጀመረው የግብይት ስርዓቱም በቀጣይ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የማስፋት ስራ ይሰራል፡፡
ሁሉም አርሶ አደር ወደ ማዕከላቱ በመገኘት እንዲገበያይ መደረጉ ገበያው እንዲጨናነቅና መስተናገድ ከሚችለው አቅም በላይ ስለሚያደርገው በዚህ መሃል የሚከሰተው የምርት ብክነትም ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይህም ጥራቱና ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚሉት አቶ ጌቱ፤ አርሶ አደሩ ለምርቱ ተመጣጣኝ ክፍያ እንዳያገኝ በማድረግ የማምረት ተነሳሽነቱ እንዲቀንስና ለውጪ ገበያ የሚቀርበው ምርት እንዲያንስ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ኢኮኖሚ

አቡበከር ሳውማሀሮስ በየቀኑ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎችና ህዝባዊ ንግግሮች እስኪጠናቀቅ የእጅ ስልኩ በተደጋጋሚ መጥራቱን አያቆምም፡፡ የሰላሳ ስምንት ዓመት ወጣቱ የኢጣሊያ ዜግነት ያለው ኮትዲቯራዊ አቡበከር በሚሰራበት ድርጅት ውስጥ የሠራተኛ ማህበር መስራችና መሪ ነው፡፡ በተጨማሪም በጣሊያን ለሚኖሩ ስደተኞች ተከራካሪና ህዝብ በተሰበሰበበት ንግግር በማድረግ በስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ያወግዛል፡፡
በተያዘው ወር መጀመሪያ በጣሊያን በተደረገው ምርጫ “ፋይቭ ስታር” እና “ዘ ሊግ” በጥምረት መንግሥት ለመመስረት ያደረጉት ጥረት ባለመግባባት ከተጠናቀቀ በኋላ በደቡባዊ ካላብራ የ 29 ዓመት ሶማሊያዊ በሽጉጥ ተመትቶ ህይወቱ አልፏል፡፡ ከዚህ በኋላ ሳውማሆሮ ለሟቹ ፍትህ ያስፈልጋል በሚል ቅስቀሳ ማድረግ ጀመረ፡፡ እንዲሁም ለሟቹ ሚስትና ልጆች ገቢ እያሰባሰበ ይረዳል፡፡ የ43 ዓመቱ ኢጣሊያዊው አንቶኒዮ ፖነቶሪሮ በሳስኮ ግድያ ተጠርጥሮ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል፡፡
ሶማሊያዊው ሟች ሳስኮ ተከታታይ የሥራ ቀናቶቹ ቁርጥራጭ ብረቶችን በመሰብሰብ ወደ ሚኖርበት ፈርድናዶ አፓርታማ በመውሰድ ለሌሎች ስደተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ነበር፡፡ በሻኒንቲ ከተማ ከሦስት ሺ የማያንስ ከማሊ፣ ከሴኔጋል፣ ከጋምቢያ፣ ከጊኒ እና ከአይቮሪኮስት የመጡ ስደተኞች ይሰሩባታል፡፡ ስደተኞቹ
የሚኖሩበት ሁኔታ በጣም አሰቃቂ ከመሆን ባለፈ ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈላቸው ሲሆን በቀን ሦስት ዩሮ ብቻ ያገኛሉ፡፡ የአካባቢው ማፍያዎች ‹‹ ናድራህጋታ›› ምርቶችን በተለያየ መንገድ የሚቆጣጠሩ ሲሆን ምርቱን የሚወስዱ ድርጅቶች ግን ግዥ የሚፈፅሙት በዝቅተኛ ዋጋ ነው፡፡
እአአ 2010 ላይ ስደተኛ የጉልበት ሠራተኞች የሚኖሩበት ሁኔታ አስከፊ በመሆኑ ምክንያት በሥራ ላይ ያሉ ሦስት ሠራተኞች ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ባደረጉት ተቃውሞ በመሳሪያ በማስፈራራት ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ተደርጎ ነበር፡፡ በተጨማሪም ከሚኖሩበት አካባቢ ወደ መቶ የሚሆኑ ስደተኞች ከሚኖሩበት አካባቢ በዘረኝነት እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አንድ የፖለቲካ አመራር ሲገልፀው፤ በአካባቢው ነጮች ብቻ መኖር አለባቸው በሚል ብዙ ስደተኞች ተባረዋል፡፡ በቅርቡ አዲሱ መንግሥት ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የሊጉ አንዱ ባለስልጣን የሆነው ማቲዮ ሳልቫኒ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስደተኞችን ሲረዱ በዘር ላይ ማተኮር እንዳለበትና እርዳታ መደረግ ያለበት በካምፕ ውስጥ ለሚኖሩ ለሮማ ተወላጆች መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በስደተኞች ላይ እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ጥሰት እንደቀጠለ ነው፡፡ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ሰኔ 11 ላይ የታጠቁ ቡድኖች ስደተኞች ላይ ጥቃት ፈፅመዋል፡፡ በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት የጣሊያን መገናኛ ብዙሀን የሆነው አንሳ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ የ22 ዓመት የማሊ ዜግነት ያለው ወጣት በሽጉጥ ተመትቶ የህክምና እርዳታ እየተደረገለት ይገኛል፡፡
አልጀዚራ ከ አቡበከር ሳውማሆሮ ጋር ስለ ሶማሊያዊው ሳስኮ ጉዳይ ቃለመጠይቅ አድርጓል፡፡ በቃለ መጠይቁም ስለ ሳስኮ እና በጣሊያን ስደተኞች እያደረጉት ስላለው እንቅስቃሴ ሰፋ ያለ መረጃ ሰጥቷል፡፡ ሳስኮ በሶማሌ እያለ አርሶ አደር የነበረ ሲሆን በሶማሌ ባጋጠመው የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ወደተለያዩ አገራት ከተሰደዱ 143 ሚሊዮን ሰዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በአየር ንብረት መዛባት ከሚያውቀውና ከኖረበት አገር ከወጣ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ጣሊያን ካላብራ መጣ፡፡ በዛም የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ማህበራዊ መብቶች እንዲከበሩ ትግል ማድረግ ጀመረ፡፡
በመስሪያ ቦታው እንደሌሎቹ ሠራተኞች እሱም የሚጠበቅበትን ሥራ ያከናውናል፡፡ በድርጅቱ ሠራተኞች ትክክለኛ የሥራ ሰዓታቸው ስድስት ሰዓት ተኩል ነው፡፡ ከዛ ውጪ ያለው የሥራ ሰዓት ግን በትርፍ ሰዓት ክፍያ ታሳቢ ይደረግላቸዋል፡፡ ከሳስኮ ግድያ ሰዓታት በኋላ ዘራፊዎች እንደገደሉት የአካባቢው ባለስልጣናት ማስወራት ጀመሩ፡፡ ነገሩ አስነዋሪና ኢሰብዓዊ የሆነ በመሆኑ በአካባቢው የሚገኙት ስደተኞች ጉዳዩን መቀበል አልቻሉም ነበር፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ምክንያቶች ጉዳዩን ለማድበስበስ የአካባቢው ባለስልጣናት የሚጠቀሙበት ዘዴ በመሆኑ ነው፡፡ ስደተኞቹ ተሰባስበው ለመገናኛ ብዙሀን ስለጉዳዩ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ የአካባቢው የፖሊስ ምክትል አዛዥ የካስኮን ግድያ የወንጀል ምርመራ እንዲደረግበት መመሪያ ሰጠ፡፡
የዘረኝነት ጥቃት በጣሊያን አሁን የተጀመረ ሳይሆን ቀደም ብሎ በተለያዩ የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ምክንያት እና በዓለም የለውጥ ሂደቶች የመጣ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሠራተኞች ላይ እየተፈፀመ ያለው የጉልበት ብዝበዛ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ስደተኞቹ ይዘው በሚመጡት ባህል ምክንያት ጥቃት የሚደርስባቸው ሲሆን የአካባቢው መንግሥት ጉዳዩን የመደገፍና አንዳንዴ የመቃወም ሁኔታዎች ያሳያል፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች መሪዎቹ እንደሚከተሉት አስተሳሰብ የሚለያይ ሲሆን አብዛኛዎቹ በቅኝ ግዛት ዘመን ያለውን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ናቸው፡፡
በየአካባቢው ስደተኛ ሆነው መጥተው ጋዜጠኛ፣ ዘፋኝ፣ ነጋዴ እንዲሁም ተማሪ የሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህን ሁኔታ የአፍሪካ ስደተኞች እንደ ጥሩ ጎን በማንሳት ለመብታቸው እየታገሉ ይገኛሉ፡፡ የአፍሪካ ስደተኞች ለአምስት ሚሊዮን ድሀ ህዝቦች የማህበራዊ ፍትህ ለማስጠበቅ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ ትግል ማድረግ ለስደተኞቹና በመጠለያ ለሚገኙ ሰዎች ጥቅም የሌለው በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ ለሁሉም ሰዎች እኩል የሆነ ነገር እንዲመጣ ህብረት ተፈጥሯል፡፡
የስደተኞቹ ፍላጎትና ጥያቄ በአካባቢው የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮችን እያስደነገጠ ይገኛል፡፡ ለዚህም የስደተኞቹ እንቅስቃሴ መቆም አለበት የሚል አመለካከት ይዘዋል፡፡ ነገር ግን የስደተኞቹ ባህል በህግ ፊት እውቅና ካገኘ የአካባቢው ፖለቲከኞች ላይ እንቅፋት መፍጠሩ አይቀርም፡፡ አስፈላጊው ለውጥ እስኪመጣ ድረስ ስደተኞቹ የያዙትን አቋም አይለቁም፡፡
በጣሊያን በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ያሉት የአፍሪካ ስደተኞች ወደ ትክክለኛ ህይወት መምጣት ይፈልጋሉ፡፡ በተለይ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል መታየት፣ ዘረኝነትና ፆታዊ ጥቃቶች እንዲቆምላቸው ይፈልጋሉ፡፡ የጣሊያን ዜጎች በሁሉም ጉዳዮች ላይ ከስደተኞቹ ጎን ናቸው፡፡ ስደተኞቹ መብታቸው እንዲከበር በሚያደርጉት ሰልፍ ላይ በመሳተፍ ከእነሱ እኩል መብት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡
የአገሪቱ የስደተኞች ህግ ላይ ለስደተኞች የተቀመጡ ክልከላዎች አሉ፡፡ በህጉ ላይ ከተለያዩ አገራት የመጡ ስደተኞች እምነት ሊጣልባቸው እንደማይገባ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ሁኔታ በሁሉም የአውሮፓ አገራት ላይ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል፡፡ አገራቱ የሚከተሉት ስደተኞችን የማሰቃየት ፖሊሲ ምንም አይነት ለውጥ የሚያመጣ አይደለም፡፡ በአሁን ወቅት በየአገሩ ያለው ስደተኛ መብቱን ለማስከበር በየአደባባዩ እየጮኸ ይገኛል፡፡
የጣሊያን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ስደተኞች ለሚሰሩበት ትልቁ የአትክልት ማምረቻ ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት እንዲሰራ ተደርጓል፡፡ እዚህ ግዛት ላይ ተመርጠው የሚመጡ ሰዎች በሚያደርጉት ያልተገባ ነገር አካባቢው እየወደቀ ነው፡፡ በምርጫ ወቅቶች ዘረኝነት የሚደግፉ ሰዎች ተሳታፊ ቢሆኑም የምርጫው ሁኔታና የአካባቢው ነዋሪ በተለያዩ መንገዶች እንዲቆሙ አድርጓቸዋል፡፡ በምርጫው የተሳተፉት የጣሊያን ዜጎች ሁሉም እኩል የሆነ አስተሳሰብ የላቸውም፡፡ በዚህም የስደተኛ ተወካዮች በአካባቢው በስደተኛ ጉዳይ ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ በምርጫ የተሳተፉትን አጠቃላይ ሰዎች አነጋግረዋል፡፡
በጣሊያን ጥምር መንግሥት ለመመስረት የተደረገው ጥረት ስኬታማ አለመሆኑን ተከትሎ አጠቃላይ ምርጫ በድጋሚ እስከሚካሄድ ድረስ በሀገሪቱ የባለአደራ መንግሥት ሊቋቋም እንደሚችል ተገልጿል። የጥምር መንግስት ለመመስረት ለሦስት ጊዜያት የተካሄደው ድርድር ውጤታማ አለመሆኑን ተከትሎ የባለአደራ መንግሥት እንዲቋቋም ይደረጋል፡፡ በጣሊያን ፖለቲካ ተፅዕኖ ያላቸው “ፋይቭ ስታር” እና “ዘ ሊግ” የተሰኙት ፓርቲዎች በቀጣይ ወር አዲስ አጠቃላይ ምርጫ እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳለቸው አስታውቀዋል።
ፓርቲዎቹ የራሳቸውን አቋም ማራመድ እንደሚችሉ የገለፁት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የባለአደራው መንግሥት ስልጣን እንዲኖረው እና አጠቃላይ ምርጫ በሀምሌ ወር እንዲካሄድ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። በፕሬዚዳንቱ በኩል የፖሊሲ አርቃቂዎች በባለአደራ መንግሥቱ እንደሚሾሙ ተነግሯል።
እነዚህ ባለሙያዎችም ሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን የፈረንጆቹን በ2019 የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳይከሰት በማድረግ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። በዚሁ ዓመት መንግሥት የሚሰበስበው የግብር መጠን ከፍ ለማድረግ የተያዘውን እቅድ ተግባራዊ ያደርጋሉም ተብሏል። ባለአደራ መንግሥቱ እስከ ፈረንጆቹ 2019 ሀገሪቱን ያስተዳድራል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። ሆኖም ፋይቭ ስታር እና ዘ ሊግ የተሰኙት ፓርቲዎች ለዚህ እርምጃ ድጋፍ ሲያደርጉ አልታዩም ተብሏል።

መርድ ክፍሉ

Published in ዓለም አቀፍ

በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂ ዕድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበትና ዓለምንም የተቆጣጠረበት አቅም መፍጠሩ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ እያንዳንዱ አገር የለውጡ አንድ አካል በመሆን በከፍተኛ ፍጥነት የሚጓዝበት ሁኔታ መኖሩ እሙን ነው፡፡ ከዚሁ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ተያይዞም ኣለም ወደ አንድ መንደርነት የተለወጠችበት ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ በዚህ የተነሳም በዚህ ዘመን አንድ አገር ለብቻው ከሌሎች አገራት ተነጥሎ ሊኖር የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚሁ ልክም በአገራት መካከል የሚደረገው ፉክክር እያደገ መጥቷል፡፡
ኢትዮጵያም የዚሁ የለውጥ ሂደት አካል ናት፡፡ በዚህ ሂደት ተወዳዳሪ ለመሆንም ዘርፈብዙ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ በ2017ዓ.ም ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር የመሆን ራዕይ በመቅረፅም ለተግባራዊነቱ እየተጋች ትገኛለች፡፡ ይህ ራዕይ እውን እንዲሆን ደግሞ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አመራሮችና ተቋማትም የየራሳቸውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል አገራችን በለውጥ ሂደት ላይ የምትገኝ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ እንዳይሳካ የሚያደርጉ በርካታ ችግሮች እንዳሉም ይታወቃል፡፡
ለምሳሌ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተለያዩ የፀጥታ ችግሮች እንደነበሩ የምናስታውሰው ነው፡፡ ለሠላም መደፍረሱ ዋነኛ ምክንያቶችም ተብለው ከተገመገሙ ችግሮች ውስጥ አንዱ ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ አገራችን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በልማቱ መስክ ያስመዘገበችውን ለውጥ ያክል በመልካም አስተዳደር ላይ ማስመዝገብ አለመቻሏ በተደጋጋሚ ይገለፃል፡፡ ይህ ደግሞ የሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት እየተባባሰ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አስፈፃሚዎችም እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት የሚፈታ አሠራርና አደረጃጀት ፈጥሮ ችግሩን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጣ ቆይቷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ በተለይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ይፈታሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸውና ብዙ ሲወራላቸው የነበሩት የለውጥ መሳሪያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በ2000 ዓ.ም በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች በተለይ በአዲስ አበባ በሚገኙ መንግሥታዊ ተቋማት ተግባራዊ የተደረገው መሠረታዊ አሰራር ሂደት ለውጥ ጥናትና በ2002 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ተግባራዊ የሆነው ሚዛናዊ ሥራ አመራርና ውጤት ተኮር ምዘና ስርዓት ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
እነዚህ የለውጥ መሳሪያዎች አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የበለፀጉ አገራት የሚሠራባቸው የለውጥ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ መሳሪያዎቹ ወደ አገራችን ሲተገበሩም የነዚህ አገራትን ተሞክሮ በመውሰድ ጥናት ተደርጎ እንደሆነ የሚታወስ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን እነዚህ የለውጥ መሳሪያዎች ከወጣባቸው ወጪና ከፈሰሰባቸው ጉልበትና እውቀት አንፃር ምን ያህል ለውጥ አምጥተዋል የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ በጥናት ሊፈተሽ ይገባል፡፡ በኔ እይታ ግን አተገባበሩን በተመለከተ የታዘብኳቸውን ለማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡
መሠረታዊ አሰራር ሂደት ለውጥ ጥናቱ ተግባራዊ ሲደረግ በቅድሚያ የነበረውን አሮጌ አስተሳሰብ እንድናወልቅና አዲስ አስተሳሰብ እንድንለብስ የሚያስችል የአእምሮ ግንባታ ሥራ ላይ ያተኮረ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ ወቅት በተለይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የወጡ አዳዲስ ሠራተኞችን በመንግሥት ተቋማት ላይ በማሰማራት የቆየውን ሲቪል ሰርቫንት በአዲስ ሃይል ለመተካት የሦስት ወራት ስልጠና ተሰጥቷቸው በየተቋማቱ መሰማራታቸውም ይታወሳል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም የተለያዩ ወጪዎች ተደርገው ቀደም ሲል የነበሩ ቢሮዎች አደረጃጀት እንዲስተካከል ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ በዚህ ጊዜም የቢሮዎች የውስጥ አካፋዮች እንዲፈርሱ ተደርጓል፡፡ አዳዲስ ህንጻዎችም ተገንብተዋል፡፡ ነባር መመሪያዎችም እንዲሻሩ ተደርጎ በአዲሱ የቢፒአር አሠራር ተተክተዋል፡፡ በበርካታ ተቋማትም ልምድ የሌላቸው ወጣቶች የአመራርነት ሚናውን እንዲወስዱ በማድረግ መመሪያዎች እንደልብ እንዲጣሱ ተደርጓል፡፡
በዚህ ወቅት ቢፒአር ስም የተጣሱ አንዳንድ መመሪያዎችና አሰራሮች በፈጠሩት የአሰራር ክፍተት እስካሁን ድረስ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚነሳባቸው ተቋማት አሉ፡፡ በተለይ ከመሬትና መሬት ነክ አሰራሮች ጋር፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ፣ ከቤቶች ወዘተ አንፃር የተፈጠሩ ክፍተቶች ለዘመናት ሲሰራባቸው የነበሩ አሰራሮችን በመጣሳቸው አዲሶቹ አሰራሮች ለሙስናና ብልሹ አሰራር በር ከፍተው የሄዱበት ሁኔታ ጉልህ ነው፡፡
ሌላው ጉዳይ ደግሞ ከራዕይ፣ተልዕኮና እሴቶች ጋር የተያዘ ነው፡፡ በየተቋማቱ ከተቀረፁና በየቦርዱ ላይ ከተለጠፉ መረጃዎች መካከል ራዕይ፣ ተልዕኮዎችና እሴቶች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ለአንድ ተቋም ወሳኝና የየተቋሙን ሠራተኞችና አመራሮች ለስራ የሚያነሳሱ በመሆናቸው መኖራቸው እንደችግር የሚታይ አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ነገር ግን ችግሩ የሚታየው የእነዚህ እቅዶች ቀረጻና ትግበራ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
በአብዛኞቹ ተቋማት ራዕይና ተልዕኮዎች የቀረፁት ታስቦባቸውና የተቋሙንና የአገሪቷን አቅም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አይደለም፡፡ በተለይ የሚዛናዊ ሥራ አመራርና ውጤት ተኮር ምዘና ስርዓት ሲተገበር ሥራው ወደ መሬት ሊወርድ የማይችልባቸው ተጨባጭ ችግሮች መኖራቸው እየታወቀ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” በሚል ብሂል ተግባራዊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
ለምሳሌ በዚህ አሰራር እያንዳንዱ ፈጻሚ በሚሰራው ሥራ ልክ እንዲበረታታ የሚያደርግና በማይሰራው ላይም ተጠያቂነት የሚስከትል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት ሰዎች በሚሰሩበት ልክ እንዲጠቀሙ ማድረግ የዚህ የለውጥ መሳሪያ አንዱና ዋነኛው መገለጫው ነው፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ሥራው የሚመዘንበት ሁኔታም እንዲሁ በቴክኖሎጂ መታገዝ ያለበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አውቶሜሽን ቢኤስሲ ከሚመዘንባቸው መንገዶችም አንዱ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን ይህ የለውጥ መሳሪያ ሲተገበር በአንድ በኩል ግልፅነት ሳይፈጠርበትና ሥራውን በትክክል የሚሰራው አካል ሳይረዳው ተግባራዊ በመደረጉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በየተቋማቱ ያለው ተጨባጭ ሁኔታና አጠቃላይ የማስፈፀም ብቃት ምን ላይ ይገኛል በሚል በቂ ጥናት ሳይደረግበት በሁሉም የመንግሥት ተቋማት መተግበሩ የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጣ ትልቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ የተነሳ ይህ አሰራር በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ለይስሙላ ብቻ ሲሰራ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን ይህ የለውጥ መሳሪያ ምን ለውጥ አስገኘ፣ በተጨባጭ ስራውስ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል የሚል ጥያቄ ቢቀርብ መልስ ሊሰጥ የሚችል አመራርም ሆነ ፈጻሚ ማግኘት ይከብዳል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም አንዱ አስቂኝ ጉዳይ ከራዕይ አቀራረፅ ጋር ያለው ችግር ነው፡፡ በዚህ የለውጥ ሥራ ውስጥ አንዱ የተቋማት ፋሽን ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶቻቻውን በጉልህ አስፅፎ በር ላይ መለጠፍ ነው፡፡ ነገር ግን ስንቶቻችን ራዕዮቻችንን በትክክል ቀርፀናቸዋል? ምን ያህሎቻችንስ እነዚህን መለስ ብለን እናያቸዋለን? ስንቶቻችንስ ተግባራዊ እንደሚሆኑ እናምንባቸዋለን?
በአንዳንድ ተቋማት በር ላይ ተለጥፎ የምናገኘው ራዕይ ደግሞ እውን እነዚህ ተቋማት ምን እንደፃፉ በትክክል ያውቁታል? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ተቋማት “በ2012 ከአፍሪካ አምስት ምርጥ----አንዱ እንሆናለን“፣ “በ2012 ከአፍሪካ አስር ምርጥ---“ ወዘተ የሚል ማነፃፀሪያዎችን የያዙ መሆናቸውን ስንመለከት እነዚያ የምናነፃፅራቸው ተቋማት ባሉበት ቆመው እየጠበቁ ይሆን የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ምንም አይነት ተጫባጭነት የሌላቸውና የሥራ ተነሳሽነትንም የሚፈጥሩ አይደሉም፡፡
በዚህ አጋጣሚ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠው ራዕይ በ2017 ኢትዮጵያን ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ እንዲኖራት ማድረግ መሆኑን ስንመለከት ይህ አገራዊ ራዕይ ምን ያህል ተጨባጭ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ተቋማት ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ መቀመጣቸው ሲታይ የጋራ መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው እንደሆነ ማየት አያዳግትም፡፡
ከላይ እንደገለፅኩት አሁን ባለው ሁኔታ የአገራችን ተቋማት በየጊዜው የሚፈርሱና መልሰው የሚጠገኑ ሳይሆኑ አገሪቷን ወደፊት ሊያስኬድ የሚችል ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ለውጥ ማድረግ የሚያሥችሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የያዝነውን ሥራ አጠናክረን በማስቀጠል ወደፊት መራመድ ከሁሉም የመንግሥት ተቋማት ይጠበቃል፡፡ አሁን አሁን ግን በአገራችን መንግሥታዊ ተቋማትን በየጊዜው በአዲስ መልኩ ማደራጀትና መለዋወጥ ባህል ሆኗል፡፡ አንድ ተቋም ቀደም ሲል ሲሰራበት የነበረው አሰራር እና አደረጃጀት ውጤታማነቱ ሳይፈተሽና የለውጡ አስፈላጊነት ሳይመዘን አዲስ አደረጃጀት ይፈጠራል፡፡ በዚህ ሂደት ሠራተኛው አጠቃላይ ትኩረት በዚህ ላይ እንዲያተኩር ይደረጋል፡፤ በዚህ ሂደትም ገና ስኬታማነቱ ሳይለካ በሚዲያ አማካይነት ስኬታማ መሆኑ ይገለፃል፡፡ በዚህ ሂደት ለጥቂት ጊዜ ተቋሙ ሪፎርም ማድረጉ እየተነገረ ሠራተኛውና አመራሩ በዚህ ተጠምዶ ይቆያል፡፡
ትንሽ ቆይቶ ደግሞ በተቋም ውስጥ የሠራተኛ ችግሮች ሲፈጠሩና ህብረተሰቡም አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቅሬታ ሲያነሳ አዲስ የመዋቅር ለውጥ ይመጣል፡፡ ይህም ለጥቂት ጊዜ የሠራተኛውንና የተገልጋዩን ኅብረተሰብ ቀልብ ገዝቶ ይቆያል፡፡ በችግሮች ላይ አዳዲስ ችግሮችን እየደረብን እየሄድን እንደሆነ የሚገነዘብ ግን ብዙም አይስተዋልም፡፡
ከላይ ያነሳኋቸው የቢፒአር፣ የቢኤስሲ፣ የካይዘን ወዘተ አሠራሮችም በአገራችን አንድ ሰሞን ፋሽን የነበሩ፣ ነገር ግን ያመጡት ለውጥ ምን እንደሆነ በግልጽ ያልተለካ የዘመኑ መሳሪያዎች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በዚህ የለውጥ ወቅት የሚቀመጡት አንዳንድ እቅዶች ደግሞ ታስቦባቸው ሳይሆን በግብታዊነት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ራዕዮቻችንን ማየት በቂ ነው፡፡ አብዛኞቹ ራዕዮች ራሳቸውን ከአፍሪካ አምስት ምርጥ አቻዎቻቸው ጋር በማወዳደር የተሻሉ ለመሆን መታቀዳቸው መነሻቸው ከምን የመነጨ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በዚህ የተነሳም በአንዳንድ ተቋማት እነዚህ ራዕዮች ለሠራተኛው የሞራል ስንቅ ከመሆን ይልቅ መሳለቂያ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው፡፡
በአገራችን ለህዝብ ቃል የምንገባባቸው ጉዳዮች ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ አብዛኖቹ ራዕዮች ሊደረስባቸው የሚችሉ አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን የተቀመጡበት የፉክክር መንፈስም ተገቢነት የሚጎድለው ይመስለኛል፡፡ ከአፍሪካ አምስት ተቋማት አንዱ ለመሆን ሲታቀድ እነዚያ አገራት ቆመው የማይጠብቁ መሆናቸውን ታሳቢ ማድረግ ይገባል፡፡ ነገር ግን እቅዱ ይቀመጥና ቢደረስበትም ባይደረስበትም ልሞክረው ከሆነ ዘላቂ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ቆይቶ የመልካም አስተዳደር ችግር ስለሚሆን ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ውቤ ከልደታ

Published in አጀንዳ

አገራችን ላለፉት ሦስት ዓመታት ለሰላም መደፍረስና ብጥብጥ ተዳርጋ ቆይታለች፡፡ በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌና በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ችግሩ የከፋ መልክ ይዞ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም መንግሥት የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ከአንድም ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የተደረገው ሙከራም የዚሁ አካል ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ቅድሚያ በመስጠት የጀመሩት ዋነኛ ሥራ በመደፍረስ ላይ የነበረውን ሰላም የማጥራት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመገኘት ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በነዚህ ጊዜያትም ትኩረት ሰጥተው ካስተላለፏቸው መልዕክቶች ውስጥ የአገራችንን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ፍቅር፣ አንድነትና ተስፋ ሊኖረን ይገባል የሚለው ዋነኛው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩ ጎልቶ በተከሰተባቸው አካባቢዎችም በመገኘት ሰላምን ለማስፈን ያደረጉት ጥረት በህዝቡ ዘንድ በጎ ምላሽን ያስገኘ እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ ይህ ግን በራሱ በቂ ባለመሆኑ በእነዚህ አካባቢዎችም ሆነ በመላ አገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት፣ የሰብዓዊ ነጻነትን ማረጋገጥ፣ ብዙኃኑን የሚያስማማ አሰራርና አደረጃጀት መፍጠር፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ማጠናከርና በየቦታው የሚፈጠሩ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን እሴት መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ ጊዜን የሚፈልግ ሰፊ ሥራ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዚህ የተነሳ ባለፉት ሶስት ወራት ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ቢከናወኑም አሁንም ቢሆን አልፎ አልፎ በሚፈነዱ ግጭቶች የሰው ህይወት እስከመጥፋት እየደረሰ ነው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሰላም፣ ስለአንድነትና ስለመደመር ዋነኛ አጀንዳ አድርገው በሚሠሩበትና ይህ ሃሳባቸውም በመላ ኢትዮጵያውያን ተቀባይነትን ባገኘበት በዚህ ወቅት ከዚህ በተቃረነ መልኩ ግጭቶች መከሰታቸው ከፊት ለፊታችን የሚጠብቀን ብዙ ሥራ መኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሥራ አጋሮቻቸው እያከናወኗቸው በሚገኙ የአንድነትና የመደመር ተግባራት የታዩ ለውጦችን በመደገፍ በመስቀል አደባባይ በተደረገው ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተፈፀመው የቦምብ ጥቃትም ሰላምን ለማደፍረስ የተደረግ ሙከራ ነው፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ ክልል በሀዋሳ፣ በጌዲኦ እና በወልቂጤ፣ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን፣ በአማራ ክልል ባቲ አካባቢ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የተከሰቱ ግጭቶችና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች አስጊና አገርን የሚበታትኑ ድርጊቶች በመሆናቸው መታረም አለባቸው፡፡
በአንድ በኩል ደፍርሶ የነበረው የአገራችን ሰላም እየተጠገነ ሲሄድ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን በማይፈልጉ ኃይሎች የሰላም መደፍረስ ጥረት ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ አገርን ወደብጥብጥና ወደማያባራ የእርስ በርስ ግጭት የሚከት ተግባር ነው፡፡ ስለሆነም መቆም አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ህዝቡ ዋነኛ የሰላም ባለቤት በመሆኑ በንቃት ሰላሙን መጠበቅ ይገባዋል፡፡
የዘረኝነት አስተሳሰቦች የሚያስከትሉት በሽታ አደገኛና የማይሽር ቁስል መሆኑን ታውቆ ለሰላም መሥራት ይገባል፡፡ ቁስሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲሽርና አገራችን ዘላቂ ሰላም እንድታገኝም ማንኛውንም የሁከት መንገድ መቃወም፣ ችግሮች ሲፈጠሩ በድርድርና በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረግ፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን ማስቀደም፣ ለአገሪቱ፣ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህሎች ተገቢውን ክብር መስጠት እያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ውጭ ግን ግጭት መተማመንን የሚያጠፋ፣ ለሌሎች በጎ ማሰብን የሚያስቀርና ለውጥና እድገት እንዳይኖር በማድረግ በድህነት ውስጥ እየማቀቅን እንድንኖር የሚያደርግ በመሆኑ ከዚህ በሽታ ለመላቀቅ ሰላምን መሻት ግድ ነው፡፡
በተለይ ሰሞኑን ያየናቸው የሰላምና የልማት ተስፋዎች የአገራችን መፃኢ ጊዜ በብሩህ ተስፋ የተሞላ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው የሰላም መንገድ ለቀጣናው ሰላም አስተማማኝነት ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ሥራ የጀመረው ድፍድፍ የነዳጅ ዘይትም የልማታችንን እድገት የሚያፋጥን ነው፡፡ ሌሎች የጀመርናቸው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሥራዎችም ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ተስፋ እያየለ ሄዷል፡፡ እነዚህና ሌሎች ተስፋዎቻችን ግን በጥላቻና በእርስ በርስ ግጭት እንዳይሰናከሉ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
ስለዚህ የሰላም እሴቶችን ለመገንባት እያንዳንዳችን ቅን አስተሳሰብን ልናዳብር ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በየደረጃው ያለው የመንግሥት አካልና ግለሰቦችም ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ በህዝቦች መካከል የሚኖሩ ግንኙነቶችም ሁከት አልባ እንዲሆኑ ማድረግ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ውጪ በማንኛውም አጋጣሚ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በውይይትና ከዚያም ሲያልፍ ለዘመናት በቆየው ኢትዮጵያዊ የሽምግልና ባህላችን መፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ጠቃሚ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ድህነት፣ ኋላቀርነትና ጉስቁልና ይብቃን! አዲስ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት እሴቶችን አዳብረን የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን እናድርግ! ለዚህ ደግሞ ብቸኛው መንገድ ሰላም በመሆኑ ሁላችንም ይህንን መንገድ ተከትለን አስተውለን እንራመድ፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

ባሕር ዳር፡- መንግሥት ህዝቡ ለሚያነሳው ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና ለመታረም ዝግጁ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የአጋሮቻቸውን አመራር ለመደገፍና ለማመስገን በትናንትናው ዕለት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም «ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ» በሚል መሪ ሃሳብ የከተማውና በዙሪያው ከሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች የተገኙ ነዋሪዎች፣ የክልሉና የፌዴራል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትና አመራሮች የተሳተፉበት የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመድረኩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ ህዝቡ የመንግሥትን እያንዳንዱ እርምጃ በንቃት በመከታተል አካሄዱ ከዴሞክራሲ ያፈነገጠና የዜጎችን መብት የሚጋፋ ሆኖ በታየ ጊዜ ሁሉ ሊታገል ይገባል፡፡ ለዚህም መንግሥት ህዝቡን እንደሚያደምጥና ለህዝብ ጥያቄም ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ባለፉት ዓመታት በአገር ደረጃ ለለውጥ መነሻ የሆኑ ሥራዎች የተመዘገቡ ቢሆንም ከሚጠበቀው ለውጥ አኳያ የተሰራው ሥራ አጥጋቢ አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅትም ህዝቡ ለመንግሥት እየሰጠ ያለው ድጋፍና ምስጋና ችግሮች በመወገዳቸው ሳይሆን የጅምር አያያዙ ዕምነት አሳድሮበት ነው፡፡ በየደረጃው ያሉ መሪዎችም ለውጡን በሚጠበቀው ከፍታ ለማስቀጠል ካለፈው ጉድለት በመማርና ቃል በማደስ ህዝቡን ለመካስ ዝግጁ ናቸው፡፡ ህዝቡም ባልተሸበበ አዕምሮ በነፃነትና በኃላፊነት መንፈስ ድጋፍና ተቃውሞውን የመግለፅ ባህሉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ቀጣዩን ጊዜ የተሻለና ክልሉንና አገሪቱን ተመራጭና ተወዳጅ የሰላምና የልማት ምድር ለማድረግ ትግል መደረጉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ኃይልም ቀጣይ አለት እንደሚያንቀጠቅጥና ድህነትን እንደሚንድ አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የጥምረቱ ኃይልም መሰናክሎችን ደምስሶ እንቅፋቶችንም አፍርሶ ድህነትና ኋላቀርነትን ታሪክ እንደሚያደርግ አያጠራጥርም ያሉት አቶ ደመቀ፤ መድረኩ ለምስጋና ብቻ ሳይሆን ለውጡን ከዳር ለማድረስ ለመታረምና ለማገልገል ቃል የሚገባበት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፖለቲካ አስተሳሰብ የተለያየ አመለካከት የሚያራምዱ አካላት መኖራቸውን በመግለፅም መሰረታዊው ጉዳይ ሁሉም ለአገሪቱ ጥቅም የተሰማራ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ የለውጥ ፋና ወጊ የሆነው ወጣቱ ኃይልና ህዝቡም በምክንያታዊነት በጋራ ለአገራዊ ለውጥ ርብርብ ማድረግ ይገባዋል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፤ በልዩነት ላይ ጊዜ ማባከንን ወደ ጎን በመተው አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች በመተሳሰር ድጋፍ መደረጉ ለቀጣይ የለውጥ ጉዞ የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ አገሪቱ ከዓመታት የሰላም ዕጦት በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመውጣት አንፃራዊ ሰላም የሰፈነባትና ህዝቦቿ አንድ መሆን ጀምረዋል፡፡ የነበሩ አለመረጋጋቶችም በሰላምና በፍቅር ተተክተዋል፡፡ ይህም የትናንቱን ገናና ታሪክና የነገውን ታላቅ ተስፋ ማስተሳሰሪያና ማረጋገጫ ማህተም ነው፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታየው የለውጥ ተስፋ ዕውን እንዲሆን የክልሉ ህዝብ በግሉና ተደራጅቶ ያደረገው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን በማወደስ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከወደቀችበት ዳግም እየተነሳች እንጂ መራመድ እንዳልቻለችም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ያለው አንድነት በማይናወጥ መሰረት ላይ በማነፅ የዚህን ዘመንና የመጪውን ትውልድ ዕድል ተስፋ እንዲበቅልበት ማድረግ ካልተቻለ በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ መገኘቱ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ የአንድነቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በጋራ መሻገርን የሚጠይቁ በርካታ ወንዞችና ሰበርባራ መንገዶች ከፊት ለፊት በመኖራቸው ይህንን መሰናክል የሚያሳልፍ ስንቅን ማንገብ እንደሚገባም አስገን ዝበዋል፡፡ ረጅሙን የፍቅርና የአንድነት ጉዞም ከአጠገብ ካሉ ቤተሰቦች ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝና በመተሳሰብ መጀመር እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የክልሉ ወጣቶችም አፍላ ጉልበታቸውን ከዕውቀትና አስተዋይነት ጋር አላብሰው እርምጃቸውን ሁሉ በማስተዋልና በጥበብ እንዲሁም ስሜትን በመተው በምክንያታዊነት አንድነቱና ተስፋው እንዳይጨናገፍ ለመታደግ እንዲረባረቡ አቶ ገዱ አሳስበዋል፡፡ በተመሳሳይ የሃይማኖት አባቶች በአገሪቱ አብሮ የመኖር እሴት ላይ ተግተው እንዲያስተምሩና በአገር ውስጥና በውጭ የክልሉን ህዝብ በልማትና በዴሞክራሲ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ችግሮችን ተራርቆ መፍታት የማይቻል መሆኑን በመገንዘብ ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር ለመደገፍና ለማመስገን በአዲስ አበባ የተጀመረው ህዝባዊ ሰልፍ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡ በአማራ ክልልም 20 የሚደርሱ ከተሞች ላይ የድጋፍ ሰልፍ ሲደረግ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።