Items filtered by date: Tuesday, 03 July 2018

አፍሪካውያን ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅርና ክብር እጅጉን የላቀና ከመዝናኛነቱም እልፎ ከዕለት ተዕለት ኑሯቸው ጋር የተቆራኘ ነው። አህጉሪቱም ከልጅነት ጀምሮ በየመንደሩ ባዶ እግራቸውን እግር ኳስ የሚጫወቱ፣ በልበ ሙሉነት ራሳቸውን ለኳስ ፍቅር አሳልፈው የሰጡ እና በድንቅ የእግር ኳስ ጥበብ የተካኑ ተጫዋቾችን ወልዳለች።እነዚህ ጥበበኞችም ከአህጉሪቱም ተሻግረው በታላላቅ ሊጎች ድንቅ የእግር ኳስ የጥበብ ልህቀታቸውንና ችሎታቸውን ማሳየትና ማስመስከር ችለዋል።
አፍሪካውያኑ ኮከቦች ምንም እንኳን በተለያዩ ታላላቅ ሊጎች አገራቸውንና ስማቸውን ከፍ አድርገው ማስጠራት ቢችሉም በአህጉር አቀፍ ውድድሮች በተለይ በታላቁ የዓለም ዋንጫ የሚያሳዩት አቋም ግን ብዙዎችን ግር የሚያሰኝ ነው።
በእርግጥ አፍሪካውያኑ ተጫዋች በዓለም ዋንጫው መድረክ መገኘት የሚያጎናፅፈውን ክብርና የሚሰጠውን የተለየ ስሜት ጠንቅቀው ያውቁታል። ከመገኘትም ባለፈ በመድረኩ አዲስ ታሪክ መስራት የሁሉም ምኞት ነው።ይሁንና ይህን ምኞታቸውን ዓለም ዋንጫው ከተጀመረ ዓመታትን ተሻግሮም ማሳካት አልቻሉም።
ብራዚላዊው ፔሌ አፍሪካ የፈረንጆቹ የሚሊኒየም መጀመሪያ ላይ የአፍሪካ ዋንጫን እንድምታነሳ ቢናገርም፤ሁለት አስርት ዓመታት ሊሆኑ ተቃርበውም አፍሪካ በታላቁ የእግር ኳስ መድረክ ዋንጫ ማንሳት አይደለም የውጤት ለውጥ ማድረግም እየተሳናት መጥቷል።
በእስካሁኑ የዓለም ዋንጫ ታሪክም አንድም የአህጉሪቱ ተወካይ ለግማሽ ፍፃሜ መድረስ አልቻለም።ሩብ ፍፃሜ መድረስ የቻሉትም ሶስት አገራት ብቻ ሲሆኑ እነርሱም ካሜሮን፣ ሴኔጋልና ጋና ናቸው። በ1990 በሮጀር ሚላ በሚመራው የካሜሮን ስብስብ እንዲሁም የእነ አልሃጂ እና ፓፓ ዲዩፍ ስብስብን የያዘችው ሴኔጋል ፈረንሳይን ሳይቀር በማሸነፍ በ2002 ለሩብ ፍፃሜ ደርሳ ነበር።
ከስምንት ዓመታት በፊት በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የዓለም ዋንጫ የምዕራብ አፍሪካዎቹ ጋናዎች ይህን ታሪክ ለመቀየር ከጫፍ ቢደርሱም እድል ግን ከእነርሱ ጋር አልሆነችም። ወቀሳው ለኡራጓዩ የፊት መስመር ተጫዋች ሉዊስ ሱዋሬዝና ለጋናው አሳሞህ ጊያን ይሁንና አህጉሪቱ ሩብ ፍፃሜውን ማለፍ አልቻለችም።አሳሞህ ጊያን ያመከናት ፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ ታሪክ ላለመቀየሩ ምክንያት ሆናለች።
እየተካሄደ ባለው 21ኛው የሩሲያ የአለም ዋንጫ በሶስት የሰሜንና በሁለት የምዕራብ አፍሪካ አገራት የተወከለችው አፍሪካ፣ የእግር ኳሱን የአሸናፊነት አቅጣጫ የመቀየር አቅም ያላቸው ተጫዋቾችን ይዛ ሞስኮ ብትደርስም የፈለገችውን ግን ማግኘት አልሆነላትም።
ከዓለም ዋንጫ መጀመር አስቀድሞ በርካታ ወገኖች በአለማችን ታላላቅ ሊጎች ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉና አገራቸውን ወክለው ወደ ሩሲያ ያቀኑ ኮከቦችን ዋቢ በማድረግ በዘንድሮው ፍልሚያ አፍሪካ የተሻለ ውጤት እንደሚኖራት ቢተማመኑም ሞስኮ ሰማይ ስር የሆነው ግን ከዚህ በታቃራኒው ሆኗል።
የዘንድሮው መድረክ አፍሪካውያን በዓለም ዋንጫው ታሪክ ያሳዩት በእጅጉ ደካማ አቋም መሆኑ ተነግሮለታል። ምክንያቱ ደግሞ አንድም ክለብ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አለመቻሉ ነው።
ከዚህ ቀደም ማለትም ከ1986 የሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ ወዲህ አህጉሪቱን ከወከሉ ብሄራዊ ቡድኖች ቢያነስ አንድ ክለብ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል።ይህ ውጤታቸው ደግሞ እኤአ 1998 የፈረንሳዩ የዓለም ዋንጫ የተሳታፊ አገራት ቁጥር ወደ 32 ፣ የአፍሪካ ተወካዮች ደግሞ አምስት ሳይሆን ሶስት አገራት ብቻ ሆነውም ያልተቋረጠ ነው።
ከዚህ በተቃራኒው አፍሪካውያኑ በዘንድሮው የሩሲያው መድረክ ያሳዩት የወረደ የእግር ኳስ ብቃት ከስፔኑ የዓለም ዋንጫ ማለትም ከሰላሳ ስድስት ዓመታት በኋላ ታይቶ የማይታወቅ አድርጎታል። በሩሲያ ምድር ከአስራ አምስት ጨዋታዎች አፍሪካውያኑ ውጤት ማምጣት የቻሉት በሶስቱ ብቻ ነው።በአስሩ ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። ግብፅ፣ሞሮኮ፣ ቱኒዚያና ናይጄሪያ የተሰናበቱትም ገና ከምድባቸው ነው። በተለይ በመድረኩ የተሻሉ ኮከቦችን የያዙት አገራት አንድም የረባ ጨዋታና ውጤት ሳይዙ መመለሳቸው አነጋግሯል።
በተለይ ሰባት ጊዜ የአፍሪካን ዋንጫ በማነሳት የአህጉሪቱን እግር ኳስ በበላይነት የተቆጣጠረችው ግብጽ በአሰልጣኝ ሄክተር ኮፐር መሪነት፣ በወጣትና ድንቅ ችሎታ ባለቤት በሆኑት በመሃመድ ሳላህ፣ ረመዳን ሳሆቢና በመሃመድ ኤልኔኒ ብቃት እየታገዘች በዓለም ዋንጫው መድረክ ብዙ ተዓምር እንደምታሳይ ብዙዎች እምነት ነበራቸው።ይሁንና ፈርኦኖቹ በሶስተኛው የዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸው የወረደ አቋም ከማሳየት ባለፈ ሶስቱንም ጨዋታ ተሸንፈዋል። የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በኡራጋይ1 ለ 0 ፣ በአዘጋጇ 3ለ1 እንዲሁም የመጨረሻ የምድብ ጨዋታቸውን በአልጄሪያ 2 ለ1 ተሸንፈዋል።
የፈርኦኖቹ ምትሃተኛ ኮከብ መሃመድ ሳላህ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የለመደውን ግብ ማስቆጠር በዓለም ዋንጫውም እንደሚችል ለዓለም ማሳየት አልሆነለትም። የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ በክለብ ያሳየውንም በብሔራዊ ቡድን መለያ መድገም አልቻለም። ግብፅም የካይሮን ትኬት ከመቁረጥ ባሻገር አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ሳትችል በዓለም ዋንጫው ያሳየችው አቋም ብዙዎችን አበሳጭቷል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በዓለም ዋንጫ የተሳተፈችው ሌላኛዋ የሰሜን አፍሪካ አገር ሞሮኮም በሩሲያ አልቀናትም።ከግብፅ የምትሻለው ከስፔን ጋር 2-2 በመለያየት አንድ ነጥብ ማግኘት በመቻሏ ብቻ ነው።እኤአ በ1998 የፈረንሳይ የዓለም ዋንጫ አንድ አሸንፋ፣ አንድ ተሸንፋና አንድ አቻ ወጥታ ከምድቧ ማለፍ ሳትችል የቀረችው ሞሮኮ፤ እኤአ በ1986 የሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ ላይ አስራ ስድስት ውስጥ መግባት ችላ የነበረች ቢሆንም፤በያኔዋ ምዕራብ ጀርመን አንድ ለባዶ ተሸንፋ ከውድድር ተሰናብታለች።
በ1978፣1998ና 2002 የዓለም ዋንጫዎች ላይ መሳተፍ የቻለችው ሌላኛዋ የሰሜን አፍሪካ አገር ቱኒዚያም ብትሆን፤ በሩሲያው የዓለም ዋንጫ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከምድብ ጨዋታዎች የዘለለ ተሳትፎ አልነበራትም።ፓናማን ከማሸነፏ በስተቀር ሁለቱንም ጨዋታዎች ተሸንፋለች።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ ሞስኮ አልተመቻትም። ናይጄሪያ፣ 1994፣1998ና 2014 ላይ ሦስት ጊዜ በዓለም ዋንጫ አስራ ስድስት ውስጥ መግባት ብትችልም የሩሲያ ተሳትፎዋ ግን ከምድብ ያለፈ አልሆነም። በሩሲያው መድረክ ጆን ኦቢ ሚካኤል፣ የአርሰናሉ አሌክስ ኢኦቢ፣ የቼልሲው ቪክተር ሞሰስ፣ የሌስተር ሲቲዎቹ ኬሌቺ ኢሄናቾ፣ አህመድ ሙሳ የመሳሰሉ ኮከቦችን ያጣመሩት ንስሮቹ፤የመጨረሻ የአርጀንቲና ጨዋታ እጣ ፈንታቸውን ወሰነው እንጂ ውጤታቸው ከሌሎች የተሻለ ሆኖ ታይቷል።
ወደ ዓለም ዋንጫውም ስታቀና የማጥቃቱን ኃላፊነት ለሴዱ ማኔ የመከላከል ተልዕኮውን ደግሞ ለኩሊባሊ የሰጠችው ሴኔጋል በአንፃሩ የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ማስተዛዘኛ ሆናለች። እኤአ 2002 ላይ ሩብ ፍፃሜ መድረስ የቻለችው ሴኔጋል፣አስደናቂ ጉዞ አድርጋ በቱርክ አንድ ለባዶ ተሸንፋ ከዚያ መድረክ መሰናበቷ ይታወሳል።
ከሁሉም የአፍሪካ ተወካዮች የተሻለ ውጤት ማምጣት የቻለች ሲሆን፤ ፖላንድን ስታሸንፍ ከጃፓን ጋር እኩል ተለያይታለች፤ በኮሎምቢያ ተሸንፋለች።
በመድረኩ አፍሪካን በመወከል የተሻለ ውጤት የነበራቸው ሴኔጋሎች በምድባቸው ከጃፓን እኩል አራት ነጥብ ተመሳሳይ ግብ ክፍያ ቢኖራቸውም፤ ከኤሲያዋ ተወካይ ጋር ባድረጉት ጨዋታ ሁለት ተጨማሪ ቢጫ ካርዶችን መመልከታቸውን ትከትሎ አሳዛኝ በሆነ መልኩ ሞስኮን ለመሰናበት ተገደዋል።።
ይህም ሴኔጋልን በዓለም ዋንጫው ታሪክ በቢጫ ካርድ ምክንያት ከውድድር የተሰናበተች የመጀመሪያዋ አገር አድርጓታል።በቀያዮቹ ሊቨርፑሎች ቤት ድንቅ ብቃት የሚያሳየውና በዓለም ዋንጫው መድረክ ይህን ችሎታውን እንደሚደግም የተጠበቀው ሳዲዮ ማኔም በአሳዛኝ ሁኔታ ሞስኮን ለመሰናበት ተገዷል።
ምንም እንኳን የሴኔጋል የሚያስቆጭ ቢሆንም፤ ሌሎቹ የአህጉሪቱ ተወካዮች በሞስኮ ሰማይ ስር ያሳዩት የወረደ አቋም ግን ብዙዎችን አናዷል። ለቀጣዩ ዓለም ዋንጫ ብዙ የቤት ስራ እንዳለባቸው ያሳሰቡም በርካታ ሆነዋል።
ከእነዚህ አንዱ በዓለም ዋንጫው መድረክ መጫወት የቻለው ኮትዲቯራዊው ዲዲየር ድሮግባ ቀዳሚው ሲሆን፤ የቀድሞው የቼልሲ ምልክት የአፍሪካውያኑን አቋም አስመልክቶ ለቢቢሲ አፍሪካውያን በሩሲያው የዓለም ዋንጫ የወረደ አቋም ማሳየታቸውን በማስረገጥ በእጅጉ ወደ ኋላ ተመልሰው መመልከቱን ጠቁሟል። አፍሪካውያን ምናልባትም አንድ ቀን በዓለም ዋንጫው መድረክ የሚናፈቁትን ውጤት እንደሚያመጡ እምነቱ እንዳልተሟ ጠጠ የገለጸው ድሮግባ፣ ከሌሎች አገራት በበለጠ ውጤታማ ለመሆን በተሻለ አወቃቀርና እቅድ ለታላቁ መድረክ መዘጋጀት እንዳለ ባቸው አስገንዝቧል፡፡ ይህም የወቅቱ ትክክለኛ ጥያቄ መሆኑን አመልክቷል።።
የሩሲያውን ውጤት ዋቢ በማድረግ በርካታ ወገኖች ሲናገሩ የተደመጡት ግን፤ በ2026 የዓለም ዋንጫ የተሳታፊ አገራት ቁጥር ሲጨምርና የአፍሪካ ተወካዮችም ከአምስት ወደ ዘጠኝ ከፍ ሲሉ ምናልባት አፍሪካ አማራጮቿን አስፍታ ውጤታማ ልትሆን ትችላለች» ብለዋል።
ሌሎች በአንፃሩ አፍሪካውያን ተጫዋቾች «ለክለብና ለብሄራዊ ቡድን የሚያሳዩት አቋም ወጥና ተመሳሳይ እስካልሆነ የዓለም ዋንጫውን ማንሳት ሲያምራቸው ይቀራል»ሲሉ ተናግረዋል።

ታምራት ተስፋዬ

Published in ስፖርት
Tuesday, 03 July 2018 20:29

መለሎው ታዳጊ

ዓለማችን ከዚህ ቀደም አስገራሚና ያልተለመደ የሰዎች ገፅታ እና ተግባርን አስተዋውቃናለች። ለአብነትም አፈ-ሰፊው አንጎላዊ ፍራንሲስኮ ዶሚነጎ ጃኩይምን፣ ቀንዳሟን ወይዘሮ ቻይናዊቷን ዣንግ ሩይፋንግ፣ ብረት በሉን ፈረንሳዊ ሚቸል ሎቲቶ፣ ህንዳዊውን ፂመ-ረጅም ራም ሲንግ ቹዋሃን እንዲሁም ወገበ-ቀጭኗን ጀርመናዊ ሚሸል ኮብከን ማስታወስ ይቻላል።

አንድ ሰው ያለመጠን ሲረዝምም ሆነ ሲያጥር ስለማንነቱ መወራቱና መነጋገሪያ መሆኑ አይቀርም፡፡ አስገራሚ ቁመትን ፈልጋና አስፈልጋ ረጅሙን ቱርካዊ ሱልጣን ኮሰንና እንዲሁም አጭሯን ህንዳዊቷ ጂዮቲ አምጌ አሳይታናለች። ከሰሞኑ ደግሞ ሌላ መለሎም አለኝ ብላለች። ይህ ታዳጊ በአሁኑ ወቅት ዓለምን በማነጋገር ቀዳሚ ሆኗል።
ሬን ኪዩ ይባላል።ቻይናዊ ነው።እድሜው አስራ አንድ ሲሆን፣ የስድስተኛ ክፍል ተማሪም ነው። እርሱ ከትምህርት ቤቱም ሆነ ከክፍል ጓደኞቹ ልቆ ይታያል።በክፍል ውስጥ ከተማሪዎቹ ጋር የሚቀመጥበት ወንበርም በልዩ ሁኔታ የተሰራ ነው።
ታዳጊው በእውቀትም ባይሆን ከአስተማሪዎቹ ይበልጣል። አስተማሪዎችም እርሱን በሚመለከቱበት ወቅት የተሳሳተ ክፍል መገኘታቸውን በማመን ይቅርታ ጠይቀው ይወጣሉ።አንዳንዶቹ ደግሞ እርሱ የተሳሳተ ክፍል መገኘቱን በመናገር እንዲወጣ ይጠይቁታል።
ይህ ቻይናዊ ከትምህርት ቤቱና ከጓደኞቹ ብቻም ሳይሆን ከሌሎች የአገሩ እኩዮች በብዙ መልኩ ይለያል። ምክንያት ቢባል ደግሞ በቁመቱ ነው።አማካኝ በእርሱ እድሜ የሚገኙ ቻይናውያን ታዳጊዎች ቁመት አንድ ሜትር ከአርባ አምስት ሳንቲ ሜትር ሲሆን፣ የእርሱ ግን ሁለት ሜትር ከስድስት ሳንቲ ሜትር ይረዝማል።በዚህ ቁመቱም የዓለማችን ረጅሙ ልጅ በሚል ሪከርድ ለመስበር ከጫፍ ደርሷል።
ይህ ልዩነቱ ታዲያ የብዙዎችን ቀልብ እንዲገዛና እርሱም ታዋቂ እንዲሆን አድርጎታል። ብዙዎች መንገድ ላይ ሲያገኙት አብረውት ፎቶ ለመነሳት ያስችግሩታል። እርሱ በአንጻሩ ደግሞ እያደር በቁመቱ ላይ የሚያስተውለው ለውጥ ሰላም ይነሳው ጀመር። እንዲያማርርም ምክንያት ይሆነዋል። በተለይ የክፍል ጓደኞቹ ሲስቁበትና በዚህ እድሜው እንዴት ሙአለ ህፃናት ይማራል በሚል ብዙዎች ሲሳለቁበት ቁመቱን ይረግማል።
አሁን ላይ ግን ይህ ቁመቱ ምናልባት አንድ ቀን ከጉዳቱ ይልቅ እንደሚጠቅመው ማመን ጀምሯል። ቁመቱን ከመርገም ይልቅም ማወደስ ተያይዟል። በተሰጠው የቁመት ፀጋም በተለይ በዓለማችን የድንቃድንቅ መዝገብ «ጊነስ ቡክ ሪከርድስ» ላይ እንደሚያስመዘግብ ይተማመናል።ይህን ፍላጎቱን እውን ለማድረግና ስሙን በድንቃድንቆቹ ስብስብ ተርታ ለማሰለፍ ማመልከቻውንም ማስገባት ይፈልጋል።
ቤተሰቦቹም ቢሆኑ፤ የልጃቸው ቁመት ለየት ቢልባቸውም ‹‹ይህ ነገር የጤና አይመስልም›› በሚል ወደ ህክምና ተቋም እስከመውሰድ ደርሰዋል። የተደረገለት ምርመራ ግን ምንም የተለየ ውጤት አላስታወቀም። የልጁ አያት እንደሚናገሩት ታዲያ፤ ምናልባት መሰል ያልተለመደ ቁመት ከቤተሰቡ ሳይወርስ አልቀረም። በተለይ ከእናቱ።
የሬን ኪዩ እናት አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሜትር ትረዝማለች። ይህ የእናቲቱ ቁመትም ቢሆን በአገሬው ያልተለመደ ነው። አባትየውም ቢሆን ከእናቲቱ ጋር ተመሳሳይ ቁመትን ይጋራል።ይህም የኪም አስገራሚ ቁመት ከቤተሰቦቹ የወረሰው ስለመሆኑ እርግጥኛ ለመሆን ድፍረትን ሰጥቷል፡፡
ዓለማችን የድንቃድንቅ መዝገብ «ጊነስ ቡክ ሪከርድስ» ላይ የቁመተ መለሎ ታዳጊዎች ክብረ ወሰን የተያዘው እኤአ በ2015 ኬቬን ብራድፎርድ ነው።ብራድፎርድ በክብረ ወሰን ላይ ስሙን ማስፈር የቻለው ሁለት ሜትር ከአስራ አምስት ሳንቲ ሜትር በመርዘሙ ሲሆን፤በወቅቱ ግን እድሜው 16 ነበር።
እናም በአሁኑ ወቅት ሁለት ሜትር ከስድስት ሳንቲ ሜትር የሚረዝመው የ11ዓመቱ ቻይናዊ፤የዓለማችን ታዳጊው መለሎ የሚለውን ክብረ ወሰን የመቀዳጀት እድል ከሞላ ጎደል ሙሉ ሲሆን፤ አሁን ላይም ከዓለማችን መለሎ ልጆች ተርታ ስሙን አፅፏል። ዘገባው የኦዲቲ ሴንትራል ነው።

ታምራት ተስፋዬ

 

አስቀያሚዋ ውሻ ተሸለመች

ውድድሮች የሰው ልጆች እየተለማመዷቸው የመጡ ፍጻሜዎች ናቸው። ውድድር ከቀበሌ እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ በተለያዩ የውድድር መስኮች ይከናወናል። ስፖርታዊ ውድድር፣ የሙዚቃ ውድድር፣ የሞዴሊንግ ውድድር፣ የፉንጋዎች ውድድር ወዘተ እየተባለ ቁጥራቸው የሚያታክት የውድድር ዓይነቶች ይከናወናሉ፤ በመጨረሻም አሸናፊዎች ይሸለማሉ።

የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እንዳስነበቡት፤ ከሰሞኑ በተካሄደ እኤአ የ2018 የአስቀያሚ ውሻ ውድድር ከእንግሊዝ የተገኘች ውሻ አሸናፊ ሆናለች። ዣዣ የሚል መጠሪያ ስም ያላት ይህች ውሻ የ1ሺ500 ዶላር ሽልማትም ተበርክቶላታል። ሽልማቱም የውሻዋ ባለቤት ነዋሪነቱን በአሜሪካ ክፍለ ሀገር ሚኒሶታ ያደረገው ሜጋን ብሬናርድ ተረክቦታል ተብሏል። ዣዣ ለየት ባለውና ውጭ ላይ ተንጠልጥሎ በሚታየው ረዥም ምላስዋና ዘርዘር ብለው በሚታዩት ትልልቅ ጥርሶቿ ብዙዎችን ስታስገርም፤ ይህ አፈጣጠሯም የዘንድሮውን ውድድር እንድታሸንፍ የረዳት መሆኑ ተነግሯል።
ዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረችው ዣዣ፤ በአሜሪካ ካሊፎርንያ ግዛት ፔታሉማ ከተማ በተካሄደ 30ኛው የዓለም አስቀያሚ ውሻ ውድድር ነው አሸናፊ መሆን የቻለችው።

 

የትራምፕን ምስል ለእፅ ዝውውር

 

የታዋቂ ግለሰቦችን ምስል ለተለያዩ ምርትና አገልግሎቶች ማስተዋወቂያነት መጠቀም በዓለም የማስታወቂያ ስራ ግንባር ቀደም የማስታወቂያ ስልት መሆኑን ለመገመት አያዳግትም። ይህም ቢሆን ኩባንያዎችና ድርጅቶች ከታዋቂ ግለሰቦች በሚያደርጉት ስምምነትና በሰዎች ፈቃድ የሚፈጸም ነው። ታዲያ ከዚህ በተለየ መልኩ ወጣ ያለ ድርጊት ከወደ አሜሪካዋ ኢንድያና ክፍለ-ሃገር ተሰምቷል። የግዛቷ ፖሊስ ባውጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በአገሪቱ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምስል ተቀርጸው የተሰሩ የተከለከሉ እፆችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። የግዛቷ ፖሊስ ይህን በፕሬዚዳንቱ ምስል የተዘጋጀው ባለብርቱካናማ ቀለም የተከለከለ እጽን በማዘዋወር 129 ተጠርጣሪ አዘዋዋሪዎችን መያዙን ጠቁሟል። አዘዋዋሪዎቹ በዚህ እፅ ላይ አሜሪካን በድጋሚ ታላቅ ማድረግ የሚለውን የፕሬዚዳንቱን አባባል ማተሙን ነው የወሬው ምንጮች ያመለከቱት። አዘዋዋሪዎቹ ይህን ማድረግ የፈለጉት የእጽ ተጠቃሚዎችን ፍላጎት ለመጨመር ብሎም ገበያቸውን ለማሳደግ መሆኑም ተነግሯል። ፖሊስ እንደ ኮኬንና ሄሮይን የመሳሰሉ አደንዛዥ እፆችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም አስታውቋል።

በሪሁ ብርሃነ

 

Published in መዝናኛ

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ወቅት የመድኃኒት አጠቃቀም ችግር በስፋት ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ጉዳቶች ይደርሳሉ። በኢትዮጵያም ቢሆን የመድኃኒት አጠቃቀም በአብዛኛው ትክክለኛ ሥርዓትን ያልተከተለና ጤናማ አለመሆኑንና በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ጉዳቶች እንደሚደርሱ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ናቸው የሚሏቸውም ከባለሙያው የመድኃኒት ማዘዝ አንስቶ እስከ መድኃኒት ዕድላና ተጠቃሚው እንደሚዘልቅ ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን ለመሆኑ አግባብነት ያለው የመድኃኒት አጠቃቀም ችግር መንስኤ እና መፍትሄ ምን ይሆን ሲል በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩ. ኤስ. ኤ. አይ. ዲ) ድጋፍ የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን አማካሪ ከሆኑት አቶ ወንዴ አለሙ ጋር ያካሄድነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን:- አግባብነት ያለው የመድኃኒት አጠቃቀም ሲባል ምን ማለት ነው?
አቶ ወንዴ:- አግባብነት ያለው የመድኃኒት አጠቃቀም ማለት ትከክለኛውን መድኃኒት በትክክለኛ ጊዜ እና መጠን መወሰድ ማለት ነው። ይህንንም ለመተግበር የሦስት አካላት ጥምረት በእጅጉ ያስፈልጋል። እነርሱም አንደኛው አካል መድኃኒት የሚያዘው ሲሆን፣ ሁለተኛው መድኃኒት የሚያድለው ሦስተኛው ደግሞ መድኃኒት የሚጠቀመው ናቸው።
መድኃኒት የሚያዘውን ስንመለከት፤ አንድ ባለሙያ አግባቡን በጠበቀ መልኩ መድኃኒት ለማዘዝ የሚከተላቸው ደረጃዎች አሉ። በቀዳሚነት ትክክለኛ ምርመራ በማድረግ የበሽተኛውን ህመም ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። ቀጥሎም መድኃኒት ያስፈልገዋል አያስፈልገውም የሚለውን መለየት ግድ ይለዋል። መድኃኒት እንደሚያስፈልገው ሲረጋገጥ ደግሞ ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት የትኛው ነው የሚለውን ይወስናል። ከዚያም መድኃኒቱን ያዛል።
አዲስ ዘመን:- አግባብ ያልሆነ የመድኃኒት ትዕዛዝ እንዴት ሊከሰት ይችላል፤ መገለጫውስ ምንድን ነው?
አቶ ወንዴ:- ይህ ምርመራው በትክክል በሽታውን ማግኘት ሳይችል አሊያም ምርመራው በአግባቡ ሳይከናወን ወይም ሁለቱም ሳይሆን ሲቀር የሚከሰት ነው። መገለጫው ደግሞ ቅጥ ያጣ የመድኃኒት ትዕዛዝ ነው። ይህም ከሚያስፈልገው በላይ አሊያም በታች መድኃኒት በማዘዝ ይገልፃል። ሌላው ለማንኛውም ህመም መድኃኒት ማዘዝና በተለይም መድኃኒት ለማያስፈልጋቸው ቀላል ህመሞች ሁሉ መድኃኒት ማዘዝን ይጨምራል።
አዲስ ዘመን:-አሁን መልስ ማግኘት ያልቻለው ጥያቄ መድኃኒት የማዘዝ ሥልጣን የማነው የሚለው ነው፤ እርስዎ መድኃኒት ማዘዝ ያለበት ማነው ይላሉ?
አቶ ወንዴ:- በአሁኑ ወቅት እንደሚስተዋለው፤ እስፔሻሊስቶች፣ የጤና መኮንኖች፣ ነርሶች፣ አንዳንድ ጊዜ ሆስፒታል ውስጥ የቆዩ የፅዳት ሠራተኞችና አስታማሚዎች ጭምር መድኃኒት ሲያዙ ይስተዋላል። ይህም መድኃኒት የማዘዝ ሥልጣን ያለው ማነው የሚለውን በመለየት ረገድ ወጥነት የጎደለው ሁኔታ እንዳለ ያመለክታል። በየደረጃው በስፔሻሊስት፣ በጤና መኮንን እና በነርስ ስለሚታዘዘው መድኃኒት ይህ ነው በሚል የተቀመጠ ወጥ መመሪያም የለም።
አዲስ ዘመን:- አግባብነት ያለው የመድኃኒት እደላስ እንዴት ይገለፃል?
አቶ ወንዴ:- አግባብነት ያለው የመድኃኒት እደላ ማለት በታዘዘው አሊያም በህመምተኛው ጥያቄ መሠረት በአግባቡ መድኃኒቱን ማደል ነው። ጥሩ የመድኃኒት እደላም የራሱ መገለጫ አለው። በዚህም ስለ መድኃኒቱ በቂ መረጃ መስጠት ከሁሉ ቀዳሚው ነው።
እኛ መድኃኒት የምንለው ኬሚካል ሲደመር መረጃ ነው። መድኃኒት ያለመረጃ ብቻውን ኬሚካል ይሆናል። መድኃኒት መድኃኒት እንዲሆን መረጃ ያስፈልገዋል። እነዚህ መረጃዎችም የቃልና የጽሑፍ መሆን አለባቸው። ለታማሚው መድኃኒት በሚታደልበት ጊዜ አንድ የመድኃኒት አዳይ ስለ አወሳሰዱ የቃል ወይም የጽሑፍ መረጃ መስጠት አለበት።
በቃል የተያዘ ይረሳል የተፃፈ ይወረሳል እንደሚባለው ታማሚው በቃል የተነገረው ቢረሳ የጽሑፉን ስለሚመለከት በሁለቱም መንገድ መረጃው መሰጠት ይኖርበታል። መረጃውም ህመምተኛው በሚገባው ቋንቋ የተዘጋጀ መሆን አለበት። ይህ በጣም ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል። ይህ ካልሆነ አግባብነቱን ያልጠበቀ የመድኃኒት እድላ ይከሰታል።
አዲስ ዘመን:- በአሁኑ ወቅት ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒቶች ለተጠቃሚዎች እየቀረቡ መሆናቸው ይነገራል፤ በዚህ ላይስ ምን ይላሉ?
አቶ ወንዴ:- አንድ መድኃኒት በሦስት መንገዶች ለተጠቃሚው ይሰጣል። በመጀመሪያ ደረጃ ለቀላል የጤና እከሎች መድኃኒት ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል። ይሁንና ሁለተኛና ሦስተኛው ፈፅሞ ያለሐኪም ትዕዛዝ ለታማሚው አይሰጡም፤ በተለይ በሦስተኛ ደረጃ የሚታዩት የግድ በሐኪም ትዕዛዝ የሚሰጡና ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ናቸው። እነዚህ መድኃኒቶች የሚያዙትም በፋርማሲስት ሲሆን፣ የሚታደሉትም በከፍተኛ ባለሙያዎች ብቻ ነው።
ይሁንና በከፍተኛ ጥንቃቄ መታዘዝና መያዝ ያለባቸው መድኃኒቶች ያለ ሐኪም ማዘዣ ሲሸጡ ይስተዋላል። በተለይ ፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ያለሐኪም ማዘዣ እንደማይሸጡ እየታወቀ በአንዳንድ ቦታዎች በሰዎች ጥያቄ ብቻ እየተሸጡ ናቸው። ይህ ፈፅሞ መታረም ያለበትና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው።
አዲስ ዘመን:-የመድሃኒት አቀማመጥና አያያዝ ያለበት ደረጃስ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ወንዴ:- አግባብነቱን ያልተከተለ የመድኃኒት እድላ ከሚገለጽባቸው መካከል አንዱ የመድኃኒት አያያዝና አቀማመጥ ችግር ነው። አንዳንድ መድኃኒቶች ከፀባያቸው አንፃር በአግባቡ መቀመጥ አለባቸው። በርካታ ታማሚዎች መድኃኒት ከወሰዱ በኋላ የሚያስቀምጡበት ቦታና ሁኔታ እጅጉን የተሳሳተና ለፀሐይና ለሙቀት የተጋለጠ ነው። በርካታ የሚሆኑት ደግሞ መድኃኒቶችን ለረጅም ጊዜ ያስቀምጣሉ።
መድኃኒቶች በመሸጫ ተቋማት በአግባቡ ተለይተው መደርደር ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም አንዳንድ መድኃኒቶች አስተሻሸጋቸው ስለሚመሳሰል የአንዱን ለአንዱ አገላብጦ መስጠትን ያስከትላል። ይሁንና በመድኃኒት አያያዝና አቀማመጥ ችግር ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳቶች ይደርሳሉ።
አዲስ ዘመን:- በታማሚዎች ዘንድ የሚስተዋል አግባብነቱን ያልተከተለ የመድኃኒት አጠቃቀም ምን ይሆን?
አቶ ወንዴ:- መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በአሁኑ ወቅት ሃምሳ በመቶ የሚሆኑት ታማሚዎች መድኃኒታቸውን በአግባቡ አይውስዱም። የታዘዘላቸውን መድኃኒት የሚጀምሩ እንጂ የሚጨረሱ፤ እንዲሁም በታዘዘላቸው ሰዓት፣ ጊዜና መጠን መሠረት የሚወስዱት ጥቂቶች ናቸው። በታማሚዎች መካከል መድኃኒቶችን መዋዋስም ሌላኛው ችግር ነው። እስኪሻል ብቻ መውሰድም ይስተዋላል። መድኃኒት አምራች አገራትን የማማራጥ የሕንድ አሊያም የጀርመን ይሻላል የሚል እሳቤም አለ።
ባለሙያው ከሚያዘው ይልቅ የራሳችን የመድኃኒት ምርጫ ካልሆነ ብሎ መሟገት አሊያም ይህን ብታዝለኝ የሚል ጥያቄ ማቅረብም ይስተዋላል። ለእያንዳንዱ ህመም መድኃኒት መፈልግም ሌላው ዋነኛ ችግር ነው።
አዲስ ዘመን:- ታማሚዎች አግባብነት ያለው የመድኃኒት አጠቃቀም እንዳይኖራቸው የሚያደርጉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ወንዴ:- አንደኛው የበሽታው ሁኔታ ነው። ይህ ማለት በበሽታው ሁኔታ ምክንያት ከባለሙያው የታዘዘላቸው መድኃኒት ለረጅም ጊዜ የሚወሰድ ከሆነ መድኃኒቱን በመውስድ ይሰላቻሉ። ምክንያቱም የታዘዘላቸው መድኃኒት በአጭር ጊዜ እንዲያድናቸው እንጂ ረጅም ጊዜ መውሰድ አይፈልጉም። ሌላኛው የሚወስዱት መድኃኒት ለውጥ ካመጣላቸው ሳይጨረሱ ወዲያውኑ እንዲያቋርጡ ምክንያት ይሆናቸዋል።
ሌላው ከእምነት አንፃር በተለይ በፆም ወቅት መድኃኒቶችን ከመውሰድ የሚቆጠቡ አሉ። ከዚህ በተጨማሪ መድኃኒቱ አቅማቸውን ያገነዘበ ካልሆነ፤ የጎንዮሽ ጉዳት ካለው፤ እንዲሁም መድኃኒቱን የሚወስዱበት ጊዜ ማጣት አግባቡን የጠበቀ የመድኃኒት አጠቃቀም እንዳይኖራቸው ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
አዲስ ዘመን:- አግባብነትን ያልጠበቀ የመድኃኒት አጠቃቀምን ለማስወገድ ምን ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ይላሉ?
አቶ ወንዴ:- በቀዳሚነት ታማሚው በመድኃኒት ዙሪያ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት መድፈን ያስፈልጋል። በተለይ ህሙማን ስለታዘዘላቸው መድኃኒት በቂ መረጃ የሚያገኙ ከሆነ አግባብነት ያለው የመድኃኒት አጠቃቀምን ማጎልበት ይቻላል። በተለይ ለረጅም ጊዜ በሚወሰዱና መቋረጥ በሌለባቸው መድኃኒቶች ላይ ከባህልና እምነት ጋር ተያይዞ አግባብነት ያለው የመድኃኒት አጠቃቀም እንዳይስተጓጎል የቤተ እምነት አባቶችም የማስተማር ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።
በሥራ ቦታዎች ላይ ህመመተኞች መድኃኒታቸውን በአግባቡ እንዲወስዱ በቂ እረፍት መስጠትም የግድ ይላል። ባለሙያውም በአግባቡ ምርመራ ማካሄድና ለታማሚው ፍቅርና እንክብካቤ ማሳየት አለበት። መድኃኒቶችን የማዘዝ ሥልጣን ያለውን ባለሙያ መለየትም ይገባል።
መድኃኒቶች በአግባቡ ስለመታዘዛቸው፤ ስለመያዛቸው ለተጠቃሚ ስለመቅረባቸው በቂ ቁጥጥር ማድረግ በተለይ በሐኪም ትዕዛዝ መሸጥ ያለባቸው መድኃኒቶች በባለሙያ ትዕዛዝ ብቻ እየተሸጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በአንዳንድ ቦታዎች የሚስተዋለውና በተለይ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ያለ ባለሙያ ማዘዣ መሸጥ መቆም አለበት። በመድኃኒት ማስታወቂያዎች ላይም በቂ ቁጥጥር ማድረግም ይገባል።
አዲስ ዘመን:- ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡
አቶ ወንዴ:- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ታምራት ተስፋዬ

Published in ማህበራዊ

የኢትዮጵያና የኤርትራ ወደ ሰላም ሂደት መመለስ ጉዳይ አጀንዳ መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ሰምምነት ሙሉ በሙሉ እንደምትተገብር በመግለጽ ለኤርትራ መንግሥት ያቀረበችው የሰላም ጥሪ ከኤርትራው መንግሥትም ፈጣን ምላሽ አገኝቶ ኤርትራ የልዑካን ቡድኗን ከ20 ዓመት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ልካለች፡፡
ይህ የኢትዮጵያና ኢርትራ መሪዎች ለሰላም የሰጡት ትኩረት ለኢትዮጵያውያኑም ሆነ ወንድም ለሆነው የኤርትራ ህዝብ በእጅጉ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንም ትልቅ አጀንዳ አድርገውት የዜና መከፈቻቸው ፣የፊት ገጽ ማድመቂያቸው ዋና ርዕሰ ጉዳያቸው አድርገውታል፡፡ ጉዳዩ አሁንም ድረስ መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መረጃ የማዳረሱን ሥራ የተያያዙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ካደረጉት ንግግር አንስቶ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ አንድነት፣ ፍቅርና መደመር አጥብቀው መናገር የጀመሩት ለኢትዮጵ ያውያን ብቻ አልነበረም፡፡ አገር ተሻጋሪ ንግግራቸው መደመጥ የጀመረው በዚሁ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት እንደመሆኑ ከጎረቤት አገሮች ጋር አብሮ በመሥራት ለማደግ በትኩረት እንደሚሠራም በመግለጽ ነው፡፡
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የደረሰችበትን የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቷን ይፋ ካደረገበት ቀን አንስቶ ደግሞ የኤርትራና ኢትዮጵያ ጉዳይ የእነዚህ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዋና አጀንዳ መሆኑ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሀገሪቱን የ2010 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት እንዲሁም ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፤ ኢህአዴግ የአልጀርሱ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር ውሳኔ ላይ የደረሰው ውሳኔው የምክር ቤቱም ስለሆነ ነው፡፡
ለኤርትራ የሰላም ጥሪ መቅረቡም ለአገሪቱና ለአካባቢው ዘለቂ ጥቅም ለማምጣት ታስቦ እንጂ ሌላ የተደበቀ አጀንዳ ኖሮ አይደለም፡፡ ውሳኔው የተላለፈው ለማስመሰል ወይም ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ሳይሆን የሁለቱ አገሮች መከራና ችግር እንዲያበቃ ማድረግን በማለም ነው፡፡
በሁለቱ ሀገሮች መካከል መሆን የማይገባው እጅግ የከፋ ጦርነት መካሄዱንና ከፍተኛ ዋጋ መከፈሉትንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ጉዳቱ በሀብትም በንብረትም በምንም ድርድርና በምንም ስምምነት የማይመለስ ነው ብለዋል፡፡ ይህን ዋጋ እያስታመምን ለበርካታ ዓመታት ኖረናል፡፡ ጉዳዩ አሁንም እንቀጥል ወይም አንቀጥል ነው፡፡ ምርጫው የኛ ነው፡፡ ችግሩ መፈታት አለበት፡፡ ኤርትራውያኑም ሆኑ ኢትዮጵያ ውያኑ እየተሰቃዩ ነው፡፡ ይህን ግን አዲስ አበባ ያለ ሰው አይገነዘበውም፡፡ ድንበር አካባቢ ያሉ ሰዎች ግን መከራቸውን እያዩ ነው›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የዘረጉት የሰላም እጅና ቅንነት የተሞላበት የሰላም ጥሪ ምላሽ በኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኩል ተቀባይነት ያገኝ ይሆን የሚል ጥያቁ ከፕሬዚዳንቱ ባህሪ በመነጨ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ አሥመራ ወዲያውኑ ምላሽ አለመስጠቷም ከዚሁ ከፕሬዚዳንቱ ባህሪ የመነጨ ነው እንዲባል አድርጎ ቆይቷል፡፡
ይሁንና ፕሬዚዳንቱ እንዳለፉት ጊዜያት ሳይሆን ሀገሪቱ የሰማእታት ቀንን ባከበረችበት ዕለት ለሰላም ጥሪው ምላሽ መስጠታቸውን ወደ ኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን እንደሚልኩ ይፋ በማድረግ አረጋግጠዋል፡፡ ይህም የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑን ትኩረት ያገኘ ታላቅ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል፡፡
አብዛኛዎቹ ዓለም አቀፉ መገኛኛ ብዙኃን ገና ከጅምሩ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ሽፋን እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡ በርካታ የሚሆኑትም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ጥቁር መጋረጃ ስለመገፈፈፉም ነው በተለያየ አቀራረብ የዘገቡት፡፡
በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኦስማን ሳለህ እንዲሁም ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ባላቸው አቶ የማነ ገብርአብ የተመራው ይህ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ከቦሌ አንስቶ እስክ ቤተመንግሥት ያለው መንገድ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሰንደቅ ዓለማዎች እንዲያሸበርቅ ተደርጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፕሮቶኮል ባልተለመደ ሁኔታ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራውን ልዑክ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝው ተቀብለውታል፡፡ የልዑካን ቡድኑ በብሄራዊ ቤተመንግሥት የእራት ግብዣ የተደረገለት ሲሆን፣ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገኝቶም ጉብኝት አድርጓል፡፡
አልጂዚራ በዘገባው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የሰላም ጥሪ ተከትሎ የኤርትራው ልዑክ ወደ አደስ አበባ በሚገባበት ወቅት የአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች በኤርትራና በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሽብርቆ እንደነበር በመጥቀስ፣ በበርካታ ባነሮችም ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ጽሑፍ የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ በሆነው በአማርኛና የኤርትራ አንዱ ቋንቋ በሆነው በትግርኛ ተጽፎ እንደነበር አትቷል፡፡ የሁለቱን አገሮች ቅርርብ የወንድማማቾች ግንኙነት ሲልም አስቀምጦታል፡፡ ሁለቱ የምሥራቅ አፍሪካ ጎረቤት አገሮች ረጅምና ውስብስብ ታሪክ እንዳላቸውም በዘገባው ተመልክቷል፡፡
ኤርትራ እኤአ በ1993 ነፃነቷን ከማግኘቷ አስቀድሞ የኢትዮጵያ አንድ አካል መሆኗን ያስታወሰው የአልጀዚራ ዘገባ ከነፃነት በኋላ በነበሩት የመጀመሪያ ዓመታት ሁለቱ አገሮች በግንኙነታቸው ደስተኞች መሆናቸውን ያስታውሳል፡፡
ዘገባው የድንበር ጦርነቱ እኤአ በ1998 ከፈነዳ በኋላ ግን ይህ የግንኙነት ምዕራፍ እየተቀየረ መጥቶ ፈጽሞ መቋረጡን እና በርካታ ቤተሰቦችም ለመለያየት መዳረጋቸውን አስታውሶ፣ ይህ ምዕራፍ ባለፈው ወር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለኤርትራ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን ዘግቧል፡፡ የሰላም ጥሪውን አልጂዚራ የፖለቲካ ተንታኙን አቶ አበበ አይነቴን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የሁለቱ አገሮች ተቀራርቦ መነጋገር ጠቃሚ ነው፡፡ ውይይቱ ውጤታማ ከሆነም የሰላም እጦቱም ሆነ ኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎችን ትረዳለች ብሎ መወቃቀሱ አይኖርም፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ በኋላ ወደ አሥመራ መጓዝ እንደሚጀምር የገለጸው የአልጂዚራ ዘገባ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በምጽዋ ወደብ አካባቢ ሽር ማለት የናፈቀው ኢትዮጵያዊ ወደስፍራው ማቅናት እንደሚችል ለኤርትራው የልዑክ ቡድን የእራት ግብዣ ባደረጉበት ወቅት መናገራቸውን አስረድቷል፡፡
የኤርትራ ሸቀጥ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ያላትን የኢትዮጵያን ገበያ ይፈልጋል፤ ኢትዮጵያም ለጎረቤቷ ኤርትራ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ትችላለች ሲል መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገውን የምጣኔ ሀብት ባለሙያውን እዮብ ተስፋዬን ጠቅሶ አልጂዚራ አብራርተዋል፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው፤ የሁለቱ አገሮች መስማማት አለመቻል ቤተሰብን ያራራቀና በኀዘንም ሆነ በደስታ እንዳይደራረሱ ያደረገ ነው፡፡ በሁለቱ አገሮች ሰላም ባለመኖሩ የተነሳ በአባቱ ቀብር ላይ መገኘት ያልቻለ መሆኑን አዲስ አበባ የሚገኘው ጋዜጠኛ ዮናስ አብረሃም ለአልጂዚራ መናገሩም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ ጋዜጠኛ ዮናስ ቤተሰቡንም ለሃያ ዓመታት አለማየቱን የጠቀሰ ሲሆን፣ ከቤተሰቡ የተለያየውም ጦርነቱ በፈነዳበት ወቅት መሆኑን ይናገራል፡፡ እሱ ኢትዮጵያዊ፣ ቤተሰቡ ደግሞ ኤርትዊ መሆኑን ነው ለአልጂዚራ ያስረዳው፡፡ ጋዜጠኛ ዮናስ ኢትዮጵያዊ ቢሆንም ስለኤርትራውያን በጥልቀት ያስባል። በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም ከተፈጠረ ከሃያ ዓመት በኋላ ቤተሰቦቹን የሚያይበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ተናግሯል፡፡
የብሉምበርግ ዘገባ ኢትዮጵያ አየር መንገዷ በመጪው አዲስ ዓመት መስከረም ወር ላይ ወደ አሥመራ ጉዞ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሶ ፣ አየር መንገዱ ወደ አሥመራ በረራ ካቆመ ሁለት አስርት ዓመታትን ማስቆጠሩን ያብራራል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መጀመር እንደሚፈልጉ ዘግቦ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኤርትራው የልዑክ ቡድን የእራት ግብዣ ባደረጉበት ውቅት አየር መንገዱ በረራ ስለሚጀምር ከወዲሁ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት መናገራቸውን ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያምም ለዚህ ጉዳይ አየር መንገዱ ዝግጁ መሆኑን ማረጋገ ጣቸውንም ብሉምበርግ በዘገባው አብራርቷል፡፡
ብሎምበርግ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች በቅርቡ እንደሚነጋገሩም የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በሁለቱ አገሮች ጦርነት ሳቢያ አንድ መቶ ሺ ያህል ሰዎች ማለቃቸውን አስታውሶ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት መጀመርን ማድነቁን አስረድቷል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ የእንግሊዝኛው አገልግሎት በበኩሉ፤ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የኤርትራን ልዑካን ቡድን መቀበላቸውን አስታውቋል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረገው የሰላም ሂደት መጀመር በተለይ ተጨንቆ ለቆየው የኤርትራ ህዝብ ትልቅ የምሥራች ነው ሲል ዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ከባድሜ ጋር ተያይዞ የተካሄደው ጦርነት እንዲቆም የአልጀርሱ ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑ ስምምነት መፈረሙን ያስታወሰው ዘገባው፣ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ እነዚህ አንድ ዓይነት ባህል፣ ቋንቋ እንዲሁም ቅርስ ጭምር የሚጋሩ አገሮች አንዱ አንዱን በጠላትነት በመፈረጅ ሁለት አስርት ዓመታት ማስቆጠራቸውን አብራርቷል፡፡
የአትላንቲክ ምክር ቤት የአፍሪካ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር በሮነዊያን ብሩቶን በቅርቡ ከኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥት ኃላፊዎች እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መነጋገሩን የሚያመለክተው የቪኦኤ ዘገባ ፣ግለሰቡ ሰላም የማስፈን ሥራ በተለያዩ ነገሮች ላይ እንደሚመሰረት መናገሩን አመልክቷል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው አለመግባባት ከድንበር ጋር የተያያዘ ነው ብሎ እንደማይምን ይጠቁማል፡፡ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ሰላም ለማስፈን ከድንበር በዘለለ ባሉ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ መሥራትን እንደሚጠይቅ መናገሩን የቪኦኤ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ቢቢሲም በዘገባው፤ የኢትዮጵያዊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራ ጋር ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅሶ፣ የኤርትራ ልዑክም ከሃያ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን ዘግቧል፡፡ በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳለህ የተመራው ልዑክ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቀይ ምንጣፍ እና በአበባ ጉንጉን አቀባበል በተደረገለት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ‹‹እኛ በአሁኑ ወቅት የሰላም በራችንን ከፍተናል›› ሲሉ መግለጻቸውን ሌሎች የዜና ምንጮችን በመጥቀስ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በቢሲ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩትን ጠቅሶ እንደ ዘገበው የኤርትራ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ ጉብኝት ለኢትዮጵያና ኤርትራ ብሩህ ተስፋን ይፈነጥቃል፡፡
ኑሮውን በኬንያ ያደረገ አንድ ኤርትራዊ የኤርትራን ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ መገኘቱ በራሱ ታላቅ ነገር ሲል መናገሩን በቢሲ ዘግቧል፡፡ ‹‹የተሰማኝን መቆጣጠር አልቻልኩም፤ በህይወት እያለሁ የሰላም ሂደቱ ሲጀመር መመልከቴ ለእኔ ታላቅ ነገር ነው›› ያለው ኤርትራዊው ዲያቆን ዳንኤል ባህለቢ፣ በሁለቱም ሀገሮች ዘንድ አያሌ ችግሮች አሉ፤የሰላሙ ችግር ከተፈታ ግን ሁላችንም እናተርፋለን ›› ሲል መናገሩን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።
ከጦርነቱ በኋላ ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደብ መጠቀም አልቻለችም ያለው የቢቢሲ ዘገባ፣ በዚህ የተነሳም ሌላ አማራጮች መፈለግ እንደነበረባት አብራርቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከምትልካቸውና ከምታስ ገባቸው ዕቃዎች 95 በመቶ የሚሆኑት የሚተላፉት በጅቡቲ ወደብ በኩል መሆኑንም ዘገባው የጠቆመው፡፡
የኤም ኤስ ኤን ኒውስ ድረ ገጽ፤ አዲስ አበባ ለኤርትራ ልዑካን ቡድን ደማቅ አቀባበል ማድረጓን ጠቅሶ፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከድንበርም የሚሻገር ነው ብሏል፡፡ የሁለቱ ሀገሮች ወደ ሰላም ሂደት መመለስ ለሀገሮቹ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጠቃሚ ይሆናል ሲሉ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ መግለጻቸውን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ዋሽግተን ፖስትን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙኃንም የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ሊገናኙ እንደሆነ ዘግበዋል፡፡ በዘገባቸው እንዳመለከቱትም፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወንድማማች አገሮች ናቸው፡፡ የእነርሱ ሰላም መሆን ሁለቱን ሀገሮች ብቻ ተጠቃሚ አያደርግም፡፡ ጥቅሙ በቀጣናው አገሮች ሰላም ለማስፈን ለሚደረገው ሂደት ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ያደረገውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ የኤርትራው ልዑክ ኢትዮጵያን መጎብኘቱ ለአገራቱ ሰላም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ሲል የሰላም ሂደቱ መጀመሩነት አድንቋል፡፡ በተለይም አገራቱ እያደረጉት ያለው ጉዞ ከራሳቸው አልፎ ለቀጣናውም ሰላም ሚናው የጎላ እንደሆነም አስታውቋል፡፡ አገራቱ የጀመሩት የሰላም ጉዞ የሚደግፍ መሆኑን አስረድቷል፡፡
በተመሳሳይም የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በሁለቱ አገሮች መካከል የተጀመረውን የሰላም ሂደት በአድናቆት ተመልከቶታል፡፡ ለሰላም ጥረቱም ድጋፍ እንደሚ ያደርግ አረጋግጧል፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ምንም እንኳ የአንድ አገር ዜጎች ሆነው የቆዩ ቢሆንም፤ በ1985 በተደረገው የህዝብ ውሳኔ ኤርትራ ነፃ መውጣቷን ማረጋገጧን ተከትሎ አገሪቱ ሉዓላዊ አገር መሆን ችላለች፡፡ ብዙም ሳይቆይ በ1990ዎቹ አካባቢ በድንበር ይገባኛል ጥያቄ የተነሳ እነዚህ ወንድማማች አገሮች አንዱ በሌላው ላይ ቃታ ወደመሳሳበ አመሩ፡፡ በዚህም አስከፊ ጦርነት ሳቢያ ከአንድ መቶ ሺ በላይ ሰዎች ለህልፈት ተዳረጉ፡፡ ምንም እንኳ ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተደመደመ ቢሆንም በአልጀርስ ስምምነት መሰረት ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት የሆነችው ባድሜ ለኤርትራ እንድትሆን ተወሰነ፡፡
ኤርትራ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን በማስጠለል ፣በሶማሊያ አልሸባብን በማስታጠቅ፣ ቱሪስቶችን አፍኖ በመውስድ ሳቢያ በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ጋር ስትናቆር ፣ኢትዮጵያም ለእነዚህ ድርጊቶች አጸፋ ያላችውን ወታደራዊ ዕርምጃ ስትወስድ ቆይታለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በሶማሊያ ለአልሸባብ ስታደርግ በቆየችሰው ድጋፍ ሳቢያ በኤርትራ ላይ በተደጋጋሚ ማዕቀብ ሲጥል ቆይቷል፤ እነዚህና በሀገሪቱ ያለው የውስጥ ጉዳይ ህዝቡን ለስደትና እንግልት ዳርጎት ቆይቷል፡፡
በሁለቱም አገሮች መካከል የባህል፣ ቋንቋ እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች ተመሳሳይ መሆን አንዱ ከሌላው በአገር ቢለያይም በስነ ልቦና ግን መተሳሰቡና መፈላለጉ እንዳለ አይካድም፡፡ ይህንን መፈላለግ ታዲያ መንበረ ስልጣናቸውን ከያዙ ገና ሦስት ወር እንኳ በቅጡ ባልሞላቸው ኢትዮጵያውያን የፍቅር ተምሳሌት አድርጎ በወሰዳቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካይነት በቀረበው የሰላም ጥሪ እየጎለበት መምጣት ጀምሯል፡፡
የሰላም ሂደቱ የሁለቱም አገሮች ዜጎች ግንኙነት እንዲያንሰራራ በር እየከፈተ ነው፡፡ አንዳቸው ወደሌላኛቸው በመሄድ ናፈፍቆታቸውን ለመወጣት ጉጉት እንዳደረባቸውም በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቃል እንደተገባውም በቀጣዩ አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤርትራ ሰማይ ላይ የሚቀዝፍ ይሆናል፡፡ ይህም ተነፋፍቀው የቆዩ የሁለቱ አገር ዜጎች እንደሚገናኙ በጉገት እንዲጠበቅ አድጎታል፡፡
የሁለቱ አገሮች ሰላም መሆን በኢኮኖሚውም ለመተሳሰር የሚያስችል በመሆኑ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ በአገር ቤት የተጀመረው የመደመር ቅኝት ወንድም ወደሆነውም የኤርትራ ህዝብ መዝለቁንም ሰሞኑን በወጡ ዘገባዎች ማስታዋል ተችሏል፡፡ ፍቅርና ሰላምን አንግቦ ለመደመር የሚያኮበኩበውም አውሮፕላን የሚነሳው መቼ ነው በሚል እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ለኤርትራ የሰላም ጥሪ ማቅረብ መጀመሯ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራም አስችሏታል፡፡

አስቴር ኤልያስ

Published in ፖለቲካ

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ለደን የሚሰጠው ቦታ እምብዛም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ደን ለማልማት የተለየ ጥረት ሲደረግም አይስተዋልም፡፡ ብቻ ለክፉ ቀን ይሆነኛል በሚል አስተሳሰብ፣ ባለው ትርፍ ቦታ እንደዋዛ የሚተከለው ችግኝ በአልሞት ባይ ተጋዳይነቱ መብቀል ቢጀምርም ተገቢ የሆነ ትኩረት ሲደረግለት አይስተዋልም፡፡ አሁን አሁን ግን ይህ ዓይነቱ ሂደት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለውጥ እያሳየ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ በአገር ደረጃም የተለያዩ መርሐ ግብሮች ተነድፈው ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ይሁንና ይህም አጥጋቢ አለመሆኑና ዛሬም ድረስ ተገቢ የሆነ ትኩረት ለደን አለመሰጠቱ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ በደን ልማት ዘርፍ ያደረገቻቸውን ዓለም-አቀፍ ስምምነቶች፣ አገራዊ እቅዶቿንና ስትራቴጂዎቿን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመፈጸም በዛፍ ዘር ጥራት ላይ አተኩራ መሥራት እንደሚገባትም የመስኩ ምሁራን ያስገነዝባሉ።
ዶክተር ይጋርዱ መብራህቱ በኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት የዛፍ ዘር ቴክኖሎጂ ማስተባበርያ ዳይሬክተር፣ ደን ኢኮኖሚዊ፣ አካባቢያዊና ማሕበራዊ ጥቅም እንደሚያበረክት ያመለክታሉ፡፡ የዛፍ ችግኝን ለማግኘት የዛፍ ዘር ቁልፉ ግብአት መሆኑን በመጥቀስ፤ የደን ልማት ጥራት ባለው ዘር ካልተካሄደ ለድካምና ኪሳራ እንደሚዳርግም ነው የሚናገሩት።
እንደ ዶክተር ይጋርዱ ማብራሪያ፤ የዛፍ ዘር ጥራት ሦስት መመዘኛዎች አሉት። የዘረ-መል ጥራት፣አካላዊ ጥራት ወይም ንጻት እንዲሁም የብቅለት አቅም ናቸው። ጥራት ያለው የዛፍ ዘርን ለማግኘት በዘር ምንጩ ወይም እናት ዛፍ መረጣ ጥንቃቄ በማድረግ እናት ዛፏን መምረጥና የዛፍ ዘርን መሰብሰብ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ የብዝሃነት ኢንስቲትዩት የደንና ግጦሽ መሬት፣ እፅዋት ብዝሃ-ህይወት ዳይሬክተር ዶክተር ደቤሳ ለሜሳ፣ የዛፍ ዘር የዘረ መል ጥራት ውስጣዊ ጥራቱና እምቅ የመብቀል አቅምን የሚያመለክት መሆኑን ይናገራሉ። የአንድ ዛፍ በሽታንና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም፣ ከአካባቢ ጋር የመላመድና የመብቀል ችሎታ በዘሩ የዘረ-መል ጥራት ላይ ይመሠረታል። የዛፍ ዘር የዘረ-መል ጥራት የሚገኘው ደግሞ ከምንጩ ወይም ከእናት ዛፍ በመሆኑ ጥራት ያለው ዘር የማግኘት ሂደት የሚጀመረው ከጫካ ወይም ከእናት ዛፍ መረጣ ነው በማለትም የዶክተር ይጋራዱን ሃሳብ ያጠናክራሉ። በእናት ዛፍ ዙርያ ያሉ የእናት ዛፍ ማሕበረሰብም በእናት ዛፏ የዘረ-መል ጥራት ቀጥተኛ ተፅእኖ እንደሚኖራቸው ይጠቁማሉ።
ዶክተር ደቤሳ «የዘረ-መል ጥራት ብቻውን በቂ አይደለም። ዘር ከሚለቀምበት ቦታ እስከ ችግኝ ጣብያ ድረስ ያለው አያያዝ በጥራቱ ላይ ትልቅ ድርሻ ይጫወታል። ዘር ሲለቀም በሙያዊ ክህሎት የተደገፈ ተገቢ አያያዝ፣የእናት ዛፍና የቅርንጫፎች አመራረጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ዘር በቀላሉ ለብልሽት ሊጋለጥ የሚችል በመሆኑ በማጣራት ሂደትም ጥንቃቄን ይሻል» ይላሉ።
ዶክተሩ እንደሚገልጹት፤ ከዚህ ቀደም የደን ባለሙያዎች እጥረት የዛፍ ዘር በቀን ሠራተኛ ተሰብስቦ ችግኝ ጣቢያ እንዲገባ ይደረግ ነበር። ይህም ጥራቱ ዝቅተኛ ዘር እንዲሰራጭና ችግኝ ሆኖ እንዲተከል ምክንያት ሆኗል። አሁን ግን የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እያወጡ ዘርፉን እየተቀላቀሉ በመምጣታቸው ችግሩ እየቀነሰ መጥቷል።
ዶክተር ይጋርዱ በበኩላቸው፤ ከአቅርቦቱ መጨመር ጎን ለጎን ጥራትን ለመቆጣጠር ስርዓት መዘርጋት፣ ሕጎችን ማውጣትና ግንዛቤ መፍጠር ይገባል። ዘር አቅራቢዎችና ሸማቾችን የዛፍ ዘር ጥራት ምን ማለት እንደሆነ ማስተማርና ማስገንዘብ የሚያስፈልግ መሆኑን ይናገራሉ።
ዶክተሯ እንደሚናገሩት፤ጥራት ያለው የዛፍ ዘርን ለማግኘት ዘር አቅራቢዎች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ይህም በእናት ዛፍ አመራረጣ ቸው፣ለማሰባሰብና ለማጣራት በሚጠቀሙበት ዘዴ እንዲሁም የእርጥበት መጠኑን አጠባበቅ ሁኔታ ያካትታል። በተጨማሪም የዘር አከመቻቸት፣ የክምችት ቆይታና የማከማቻ ቦታው የዘሩን የብቅለት አቅምን ይወስናሉ። ጥራት ያለው የዛፍ ዘር ለማግኘት የእርጥበት መጠን፣የአካላዊ ጥራትና የብቅለት ደረጃ በማውጣት መለካትና ማሰራጨት ያስፈልጋል። ኢንስቲትዩቱ ይህን ታሳቢ በማድረግም የ50 ዝርያዎች ደረጃዎችን አውጥቷል።
እርሳቸው እንደሚያስረዱት፤ዘርን እንደ ገቢ ማግኛ ከመጠቀም ባለፈ ዘር አቅራቢዎች ዘር ምን ማለት ነው? እንዴት ይሰበሰባል? የሚለውንና እንዴትስ መከማቸት እንዳለበት በውል ሊያውቁ ይገባል። ዘር አቅቢዎች የወጡትን የዛፍ ዘር የጥራት መመዘኛ መሥፈርቶችን ተንተርሰው ዘር እንዲያመርቱ አቅራቢዎቹን በማሰልጠንና ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ አቅማቸውን መገንባትም ያስፈልጋል።
«በአሁን ወቅት መደበኛ ያልሆኑ የዛፍ ዘር አቅራቢዎች ያለፍተሻ የዛፍ ዘርን እንደማንኛውም ሸቀጥ ይሸጣሉ፤ዘር ህይወት ያለው ነገር በመሆኑ በከፍተኛ ሙቀት ህይወቱን ያጣል፤በዘር ውስጥ የሚገኘው መብቀል የሚቸለው አካልም ሊጎዳ ይችላል። ይህን ለመከላከልም የዛፍ ዘር ስርዓትን መፈተሽ፣የአመራረት ሂደቱን መከታተልና ቁጥጥር ማድረግም ያሻል» ባይ ናቸው።
ዶክተሯ እንዳሉት፤ የጥራቱ ጉዳይ የዛፍ ዘር መጠን ዕድገት ያስመዘገበው ዕድገት ያህል አላመጣም፤ ከፍተኛ ሥራም ይጠይቃል፡፡ ከቁጥጥርና የአቅም ግንባታ ባሻገር የወጣውን ዛፍ ዘር ጥራት መለኪያ ደረጃ ሥራ ላይ ለማዋል የእፅዋት ዘር አዋጅን በአገር ደረጃ ማፀደቅና ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።
ዶክተር ይጋርዱ እንደሚያመለክቱት፤ የጥራት ፍተሻ በማካሄድ አንድ ዘር የእርጥበት መጠኑ፣ አካላዊ ጥራትና የብቅለት መጠን በላቦራቶሪ መፈተሽ አለበት። ተፍትሾ የማይበቅል መሆኑ ከተረጋገጠ እንዳይሰራጭ ማድረግ ይቻላል። የግል ዘር አቅራቢዎች አቅማቸው ውሱን በመሆኑ ላቦራቶሪና ዘር ማከማቻ ቀዝቃዛ መጋዘን ለማግኘት ይቸገራሉ። ይህን ለመቅረፍም የግል ዘር አቅራቢዎች ከመደበኛ ዘር አቅራቢዎች ድጋፍ የሚያገኙበት መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል። የጋራ ማዕከላዊ የፍትሻ ቦታ በማመቻቸትም ድጋፍ መሥጠት ይገባል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በአገሪቱ ጥራቱ የተፈተሸ የዛፍ ዘር ማቅረብ የተጀመረው በ1970ዎቹ በቀድሞው የደን ምርምር ማዕከል ነው፡፡ በ1980ዎቹ ደግሞ በመጠኑ ትልቅ የሆነና በተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሐግብር ድጋፍ ብሄራዊ የዛፍ ዘር መርሐግብር መተግበር ተጀመረ። መርሐግብሩ ጥራት ያለው የዛፍ ዘር አቅርቦትን አሻሽሏል። በመርሐግብሩ 370 ሄክታር መሬት ያካለሉ የዛፍ ዘር ምንጮችን ማቋቋም ተችሏል። በወቅቱ አገሪቷ በዓመት ስምንት ቶን ዘር ይቀርብ የነበረ ሲሆን፣የዛፍ ዘር የማምረት አቅሙ አድጎ በመንግሥት፣በግል ኢንተርፕራይዞችና በአርሶ አደር የዛፍ ዘር አቅራቢዎች በዓመት 100ቶን የዛፍ ዘር ይሰበሰባል።
እንደ ዶክተር ይጋርዱ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ የደን ልማትን ማእከል ያደረጉ የደን ዘርፍ አገራዊና ዓለምአቀፋዊ እቅዶች አሏት። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ስትራቴጂን ጨምሮ የአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ፣ተሻሽሎ የወጣው የደን ልማት፣ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅና ሌሎች ስትራቴጂዎች፣የሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳ መርሐግብር፣የደን ዕጽዋት ብዝሃነት ጥበቃ ስምምነቶችና በረሃማነትን የመከላከል ስምምነት እንዲሁም 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የተራቆተ መሬት በደን ለመሸፈን ቃል-የገባችበት የኒውዮርክ ስምምነት ይጠቀሳሉ።
«ጥራት ያለው የዛፍ ዘር መጠቀም ያልተጣመመ፣ጠንካራ፣በሽታዎችንና ተባዮችን የሚቋቋም እንዲሁም ከአካባቢው ጋር ተላምዶ ቶሎ የሚጸድቅ ችግኝ ይገኛል፤ በዚህም የደን ልማቱን ውጤታማ ያደርገዋል» በማለት የሚናገሩት ዶክተር ደቤሳ፣ በአንጻሩ ጥራታቸው ዝቅተኛ የሆኑ የዛፍ ዘሮች መጠቀም በሽታንና ተባዮችን የማይቋቋሙ ሲተከሉ የመጽደቅ እድላቸው ከአምሳ በመቶ በታች የሆኑ ችግኞችን በማስገኘት የደን ልማቱ እንዲወድቅም ምክንያት እንደሚሆን ያብራራሉ።
እንደ ዶክተር ይጋርዱ ማብራሪያ፤የደን መመናመን የደን ውጤት ምርቶች ከውጭ ለማስገባት ስለሚያስገድድ አገርን ለከፍትኛ የውጭ ምንዛሬ ይዳርጋል። ለዚህም ጥራት ያለቸው የዛፍ ዘሮች በማሰራጨት የደን ልማቱን ውጤታማ ማድረግ ያስፈልጋል። በአገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች በረሃማነት እየተስፋፋ ይገኛል። ጥራት ያለው ችግኝ በመጠቀም በደን ካልተሸፈኑ ውሃ ወደ መሬት የመስረግ አቅሙ አናሳ ስለሚሆን ውሃ እጥረትም ሊያጋጥም ይችላል። ጥራቱ ዝቅተኛ የሆነ የዛፍ ዘር በመሰብሰብ፣ በችግኝ ጣብያ ቆይታ እንዲሁም በተከላ ወቅት በሚኖረው ድካምና ውጪ ዋጋ ከማስከፈል ያለፈ ፋይዳ የለዉም። አገሪቱ ያቀደቻቸውና የፈረመቻቸው አገራዊ እቅዶችና ዓለም-አቀፋዊ ስምምነቶችን በተግባር ለመተርጎም የሚደረገውን ጥረትም ያስተጓጉላል።

በሪሁ ብርሃነ

Published in ኢኮኖሚ

በአውሮፓ ህብረትና በብሪታኒያ መካከል ለአራት አስርት ዓመታት የዘለቀው የአንድነት ትስስር ገመድ ከሁለት ዓመት በፊት በይፋ ተበጥሷል። ‹‹ከአብሮነት ይልቅ ፍቺ ይሻለኛል›› የሚል ጥያቄን በይፋ ያቀረበችው ብሪታኒያም፣ የፈለገችውንም ለማስፈፀም ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች።
የሁለቱ ወገኖች መለያየት ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶም ታዲያ ህብረቱና አገሪቷ ስለሚፈፅሙት ፍቺና ቀጣይ ግንኙነታቸው በርካታ አስተያየቶች ከተለያዩ ወገኖች ተሰምተዋል። በተለይ ‹‹ብሪታኒያ የሌለችበት የአውሮፓ ህብረትና የአገሪቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?›› በሚል ብዙ ተብሏል።
ቀናት ባለፉ ቁጥር እያደር አነጋጋሪነቱ በሚጨምረው የሁለቱ ወገኖች የፍቺ ድርድር ሂደት ምክንያትም በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑ ሙሉ ትኩረታቸውን ለጉዳዩ በመስጠት በመዘገብ ላይ ይገኛሉ፤ እያንዳንዷን ጉዳይ ለአንባቢ፣ አድማጭና ተመልካቾቻቸውም በማድረስ ተግባር ተጠምደዋል።
እንደ መገናኛ ብዙሃኑ ዘገባም፤ አሁን ላይ የሁለቱ ወገኖች የመለያየትና የአብሮነት ጉዳይ ይበልጥ ጦዟል። የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሪሳ ሜይም የህዝባቸውን ፍላጎት ለማስፈፀም የሚያስችል ቃታቸውን ይበልጥ ስበዋል። ይህን ተከትሎም አንዳንዶች የአገሪቱን ቁርጠኝነት ሲያደነቁ ሌሎች ደግሞ እጅጉን በመኮነን ተጠምደዋል። ገሚሶቹ በአንፃሩ ከዛሬና ትናንት ይልቅ ነገ ፍቺው የሚያስከትለውን ለመመለክት እጅጉን ናፍቀዋል።
አሁን ላይ ግን የሁለቱን ወገኖች ፍቺ ሁለት አይነት መልክ ማሳየትና የተለያየ ፅንፍ ያነገቡ አስተያየቶችን ማስተናገድ ጀምሯል። የአገሪቱን መቆየት የሚደገፉ አካላት ያሉትን ያህል በመውጣቷ ተጠቃሚ እንደምትሆን የሚያስረዱም ተበራክተዋል። ህብረቱን መልቀቅ ቀላል የሚባል አለመሆኑን በመወትወት ላይ የሚገኙትም ቁጥራቸው ከወትሮው ይልቅ በርክቷል።
እነዚህ ወገኖችም ፍቺ ሲታሰብ ለአብነት ህብረቱ ላለፉት ዓመታት ያፀደቃቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ህግና ደንቦች እንዲሁም የኢኮኖሚና ሌሎችም ትስስር መለወጥንና መቀየርን የግድ ይላል፤ ይህ ደግሞ የፍቺው ሂደት እጅግ ከባድና ውስብስብ ያደርገዋል፤በድርድሩ በሁለቱም ወገን የሚቀርቡ ፍላጎቶችን ማስታረቅም ከባድ የቤት ስራ እንደሚሆን ይነገራል፡፡
በእርግጥም አገሪቱና ህብረቱ የፍቺውን ድርድር ከጀመሩ ወዲህ በሁለቱም በኩል የየቅል ፍላጎት እጅጉን ተንፀባርቆባቸዋል። አንዳንዶቹ ልዩነቶች ደግሞ ግትር አቋም የሚንፀባረቅባቸውን ለማስታረቅ የማይመቹ ሆነው ታይተዋል። በተለይ የአንድ ገበያ ትስስራቸውን የማስቀጠሉ ድርድር እጅጉን ከባድ ልዩነቶች የታየበት ሆኗል።
ህብረቱ፣ ‹‹አቋሜ›› በሚለው መሰረት አባል አገር መሆንና ተባባሪ መሆን እጅጉን ልዩነት አለው። ቀጣናዊ ሰላም ለማረጋገጥና አንድ የገበያ ትስስስር ለመፍጠር ከመፋታት ይልቅ የጋራ አንድነት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ህብረቱ ያምናል። ይሁን እንጂ ከህብረቱ ተገልሎ ቀደም ሲል እንደነበረው በንግድና ሌሎችም መስኮች በአንድነት መስራት አይዋጥለትም።
በተለይ የህብረቱ አባል ሳይሆኑ ‹‹የአንድ ገበያ ተጠቃሚ እሆናለሁ›› የሚል ሃሳብ ‹‹ጊዜው ያለፈበትና የተሳሳተ ነው›› የሚል አቋም አለው። ብሪታኒያ የሰዎችን ነጻ ዝውውር መብት በገደበችበት ሁኔታ ከህብረቱ አባል አገራት ጋር የምታደርገው የንግድ ግንኙነት እክል እንደሚገጥመው ያስገነዝባል።
ብሪታኒያና ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሪሳ ሜይ በአንፃሩ ፍቺው ቢፈፀምም፤ ከአባል አገራቱ መንግስታት ጋር በተናጠል እንዲሁም ከአውሮፓ ህብረት ጋር የሚኖራት የንግድ ግንኙነት ይቆረጣል የሚል እምነት የላቸውም። በተለይ የአንድ ገበያ ተጠቃሚነታቸውን የማስቀጠልና በሰላምና ፀጥታ ጥበቃ ረገድ ትስስር እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ለዚህ ግን ህብረቱ የያዘውን ግትር አቋም እንዲለውጥ ፍላጎት አላቸው። እናም በሁለቱ ወገኖች ድርድር የሚቀርቡ አንዳንድ እቅድና ፍላጎቶች ከመቀራረብ ይልቅ ለመራራቅ የተጠጉ ናቸው።
በፍቺው ሂደት ዙሪያ ከሰሞኑ የሚወጡ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችም፤ ምንም እንኳን በሁለቱ ወገኖች መካከል ቀደም ሲል የነበሩ አንዳንድ ልዩነቶችን እያጠበቡ ቢመጡም፤ አሁንም ቢሆን ሰፊ ልዩነቶችና ከባድ ፈተናዎች መልስ አለማግኘታቸውን የሚያትቱ ሆነዋል። ለዘ ኢንዲፔንደንት የሚፅፈው ጆን ስቶን፤ ከሰሞኑ በቤልጄየም ብራሰል ከተካሄደው የ27ቱ አባል አገራት የመሪዎች የጋራ ስብሰባ፤ የፍቺ ሂደት አንድም መሻሻል እንዳላሳየ መገምገሙን አስነብቧል።
በእርግጥም በጉባኤው ላይ የአውሮፓ ህብረት ዋና ተደራዳሪ ሚስተር ሚሼል ባርቬር፤ ምንም እንኳን አንዳንድ ልዩነቶችን ማጥበብ ቢቻልም፤ አሁንም ቢሆን ግዙፍ ልዩነቶች አሉን ብለዋል። ይፋዊ የፍቺ ቀጠሮው የሚታወቅበት ቀን እየተቃረበ በመሆኑ የብሪታኒያ መንግስት የፍቺውን ሂደት ለማሳለጥ የሚያግዙ እቅዶችንና ፍላጎቶቹን ማቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል።
ይህን የሚጋሩት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ማካኤል ሮዝም፤ ብሪታኒያ ከህብረቱ ስትነጠል በቀጣይ ስለምትፈልጋቸው ፍላጎቶችና ጥቅሞች ግልፅ፣ ምክንያታዊ፤ አሳማኝ እንዲሁም ውጤታማ የሆነ እስትራቴጂን በድርድሩ ጠረጴዛ ላይ ማቅረብ ግድ እንዳለባት አስገንዝበዋል።
የአሾሽየትድ ፕሬስ ጂያን ላውለስም፤ ከፍቺው ስር የተደቀኑ ፈተናዎችን በሚዳስስው ትንታኔው፤ አገሪቱና ህብረቱ አሁን ላይ መግባባት ያልቻሉበት አብይ ጉዳይ የሰላምና ፀጥታ ጥበቃ መሆኑን አስነብባል። እንደፀሃፊው ከሆነም፤ ህብረቱ ብሪታኒያ ፍቺውን ከማፋጠን ይዛው የምትመጣቸው እቅዶችና ፍላጎቶች የራሷን ጥቅም የሚያስጠበቁ መሆናቸውን ያምናል። ብሪታኒያ በበኩሏ፤ በድርድሩ ሂደት በተለይ በፀጥታው ረገድ ህብረቱ የሚያንፀባርቀው ግትር አቋም ምቾት አልሰጣትም።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ፣ በአንፃሩ አገራቸው ቀጣናዊ ሰላም በማረጋገጥና በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑንና ይህንንም በቀጣይ ማጠናከር እንደምትፈልግ ይገልፃሉ። በተለይ በጋራ ፀጥታ ጥበቃው ከአውሮፓው የፖሊስ ኤጀንሲ ከ«ዩሮፖል»መውጣትን አይፈልጉም።
ይሁንና አስተዋጽኦ በአንዳንድ አካላት አደጋ ውስጥ ማግባቱን ያስረዳሉ። ምክንያት የሚሉትም፤ ለድርድር የሚቀመጡ ሰዎች አገራቸው ሚናዋን እንዳትቀጥል በተለይ ሽብርተኝነት በመከላከል ረገድ እንቅፋት መሆናቸውን ነው። እናም ህብረቱ ይህን ግትር አቋም በመተው ሁኔታዎችን በማገናዘብ 500 ሚሊዮን ዜጎችን ከጥቃት መጠበቅ እንዳለበት ነው የሚያስገነዝቡት። ከሁሉ ቀድሞ ለሰላምና ፀጥታው ጥበቃ አጋርነት ትኩረት እንዲሰጥም ነው የተጠየቀው።
ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስተሯ፣ ይህን ሃሳባቸውን በአባል አገራቱ መሪዎቹ ፊት ቆመው አስረግጠው ቢናገሩም፤ የውስጥ የቤት ስራቸውን አለመወጣታቸው ግን በአደባባይ ይታያል። ምክንያቱ ደግሞ ፓርቲያቸው አባላቱ መካከል ፍቺው ሲፈፀም ‹‹አገሪቱ በምን መልኩ በፀጥታና ጥበቃው ረገድ ልትሳተፍ ትችላለች? እንዲሁም አጋርነቷስ እንዴት ሊሆን ይገባል?›› በሚለው ላይ የየቅል እንጂ የጋራ አቋም መያዝ አለመቻላቸው ሆኗል።
አሁን ላይ በህብረቱና በአገሪቱ የፍቺ ድርድር ፊት ከተደቀኑ ፈተናዎች ሌላኛው የድንበር ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል። ይህም በሁለቱ አየርላንዶች መካከል ያለው ድንበር ጉዳይ ነው። በእርግጥ ይህ የድንበር ጥያቄ ድርድሩ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ምንም አይነት ምላሽ ማግኘት አልቻለም። ድንበሩ ይከለል የሚለው ጥያቄ ሲነሳም ኃላፊነቱን ለመውሰድ የሚፈልግ አለመኖሩ በግልፅ ይታያል።
ብሪታኒያም ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ፤ ‹‹በእኔ በኩል እንዳታስቡት›› የሚልና አሉታዊ ነው። አየርላንድም ቢሆን በጠቅላይ ሚኒስትሯ ሊዮ ቫርድካር አስረግጣ እንድምትናገረው፤ ይህን ማድረግ ፍላጎት እንደሌላት ነው።
በተለይ የህብረቱ አባል አገራት የአየርላንድ ድንበር ጉዳይ አፋጣኝ መልስ እንዲያገኝ ፍላጎት አላቸው። እናም ይህ ፍላጎታቸው የሚፈፀምበትን ሂደት ከብሪታኒያ ይጠብቃሉ። የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍላጎትም ድርድር እንዲፋጣን ነው። ብሪታኒያ በአንፃሩ አንድም እርምጃ እግሯን ማንሳት አልቻለችም። ይህ ደግሞ ለብዙዎች አልተዋጠላቸውም።
እነዚህ ፈተናዎች መልስ ማግኘት ባልቻሉበት በአሁን ወቅት ሁለቱ ወገኖች ያስቀመጡት ይፋዊ የፍቺ ቀነ ቀጠሮ እጅጉን ተቃርቧል። ከዚህ አንፃሩ በርካቶች ፍቺው እየተንቀረፈፈ መሆኑን ተስማምተውበታል። ለዚህ ምክንያት የሚሉትን ሲያስቀምጡም፤ ብሪታኒያ መንግስት መካከል ያለው የእርስ በእርስ የልዩነት አቋም መሆኑን ነው።
ይህ ደግሞ ለአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዣን ክሎድ ድ ጄንከር ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም። ሰውየውም ቢሆን የፍቺው ጥያቄ አንድም የረባ መሻሻል አለማሳየቱን ይስማሙበታል። ይሁንና ፍቺውን በታቀደለት የጊዜ ቀጠሮ ለመፈፀም ከሁሉ ቀድሞ ብሪታኒያ የውስጥ ልዩነቷን ማስወገድና የጠራ አቋሟን ማሳወቅ እንዳለባት ነው ያስገነዘቡት።
አነጋጋሪው የሁለቱ ወገኖች የፍቺ ሂደትና ከፊቱ የሚደቀኑ ፈተናዎች ግን በተለይ ከህብረቱ ጋር ሆድና ጀርባ ለመሆን አቅደው ለነበሩ አገራት ህብረቱን መልቀቅ እንዲሁ ቀላል አለመሆኑን ማስተማሩም ተመላክቷል። በአሁን ወቅትም የብሪታኒያን ፈለግ የመከተል ፍላጎት እንዳላቸው የሚነገርላቸው አገራት ሳይቀር ከውሳኔ በፊት የፍቺውን ሂደት በሰከነ መልኩ መከታተልና ከህብረቱ መለያየት የሚያስከትለውን ጫና ማጤን ምርጫቸው አድርገዋል።
ብሪታኒያ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት ያስቀመጠችው የጊዜ ገደብ እ.ኤ.አ.መጋቢት 30 ቀን 2019 ይጠናቀቃል። አገሪቱ ከህብረቱ ለመነጠል የጀመረችው ሂደት ሁለት ዓመታትን ብቻ ይወስዳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከታቀደው ጊዜ በላይ ይፈጃል እየተባለ ነው፡፡

ታምራት ተስፋዬ

Published in ዓለም አቀፍ
Tuesday, 03 July 2018 20:15

የመረጃ አጥሮቹ

የመገናኛ ብዙኃንና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችን ያገናኘ አንድ መድረክ በቅርቡ በቢሾፍቱ ተካሂዶ ነበር፡፡ መድረኩን አስመልክቶ በቴሌቪዥን በተላለፈ ዘገባ እንደተመለከትኩት፤ መረጃ መስጠት የሚጠበቅባቸው ነገር ግን በመረጃ ከልካይነታቸው የሚታወቁት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና የመረጃ ያለህ የሚሉት የመገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎችም በመድረኩ ተገናኝተዋል፡፡ 

በመድረኩ ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተገኙ ሲሆን፣ ኃላፊዎቹ ከሚኒስትሩ ጋር የተዋወቁበት መድረክም ጭምር ነው ስል ገመትኩ፡፡ የሕዝብ ግንኙነት እና የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎቹ የሆድ የሆዳቸውን ያነሳሉ ብዬም ጠብቄያለሁ፤ አንስተውም ሊሆን ይችላል፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆኖብኝ ነው መድረ ኩን መጥቀሴ፡፡ ወደ ጉዳዩ ልግባ፡፡ ሁሌም ከመረጃ ጋር በተያያዘ ባለሙያዎቻቸው የሚቸገሩት የእነዚህ ተቋማት ኃላፊዎች ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ መድረኮች ሲገናኙ የኖሩ እንደመሆናቸው የመገናኛ ብዙኃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጁ ችግራቸውን ፈትቶላቸው ይሆን የሚል ጥያቄ ለማንሳት የማያስደፍር ተግዳሮት እንዳለባቸው በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የሚነሱ አስተያየቶች ያመለክታሉ፡፡
እነዚህ ተቋማት ሁሌም እንደተፈላለጉና እንደተካሰሱ ናቸው፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር የሚኖራቸው የሥራ ግንኙነት ሰፊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መገናኛ ብዙኃኑ መረጃ ፈላጊ እነሱ መረጃ ሰጪና ሌሎች የተቋሞቻቸው ኃላፊዎች እንዲሰጡ አመቻቾች መሆናቸው ነው። ተቋማቱ የመሥሪያ ቤታቸውን የሥራ እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ እንዲያውቅ ለማድረግ መረጃዎቹን ለመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ለሌሎች ደንበኞች መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም መረጃ በሚገባ አቀናጅተውና አሰናድተው የማስተላለፍ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
የሕዝብ ግንኙነቶች የቆየም ሆነ ትኩስ መረጃ ሲጠየቁ ፈጥነው እንዲሰጡ የሚያ ስችላቸውም መረጃን አደራጅቶ ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ ይህ ሥራው የሚጠይቀው ቢሆንም በአንዳንድ ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ዘንድ የሚስተዋለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ በሥራ አጋጣሚ ከማውቃቸው በርካታ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች መካከል ለሥራቸው ታማኝ የሆኑ ጥቂት ቢኖሩም፣ ብዙኃኑ እምቢተኞች ወይም አጥሮች ሆነዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞቻቸው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አጥር ሆኑብን፣ ለትንታኔ የሚሆን ጠንከር ያለ መረጃ አይሰ ጡንም፡፡ ገብስ ገብሱን (መረጃ ማቅለሌ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ) እንኳ ሊሰጡን ፈጽሞ ፍላጎት አያሳዩም እየተባለ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ እውቀቱ ያለውን ባለሙያ አገናኙን ሲባሉ «እኔ የማንን ጎፈሬ አበጥራለሁ» በሚል ስሜት ከእኔ በላይ ላሳር ይላሉ፤ ካልተነተንን እስከ ማለትም ደርሰዋል ይባላል፡፡
ልብ በሉልኝ ስለሆነው ነው የምገል ጽላችሁ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ጉዳዩ የሚመለከተው ባለሙያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊውን አስፈቅዱ እንጂ በእኔ በኩል ችግር የለም እያሉም ጭምር ነው መረጃ የሚከለ ክሉት፡፡ በእነሱ እምቢተኝነት የተነሳም ስንት «ባላንስ» ማድረግ የሚፈልጉ ሥራዎች መክነዋል፡፡ ቀድመው ይዘዋቸው ሊወጡ የሚችሉ የመገናኛ ብዙኃን በዚህ የውድድር ዘመን ተቀድመዋል፤ በዚህ ሥራቸው የሕዝብ ግንኙነት ሳይሆን የሕዝብ ማራራቅ ቢባሉ ይቀላል፡፡
በአንድ በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ላይ በመከረ መድረክ ላይ እንደሰማሁት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎቹና ኃላፊዎቹ መረጃ መስጠት የማይፈልጉበት ምክንያት መረጃውን መገናኛ ብዙኃኑ በተገቢው መንገድ ስለማ ይጠቀሙበት ነው ይላሉ፡፡ እነዚህኞቹ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ይህን ድርጊታ ቸውን በደግ ይወስዱታል፡፡ መረጃ ሰጥቶ ከመጠየቅ አለመስጠት ይሻላል ወደሚል መደምደሚያ የደረሱ ናቸው፡፡
ተቋማት ለመረጃ ያላቸው ግምት አነስተኛ መሆኑን በመጥቀስ መረጃዎቹ የሚገኙበት ቦታ መረጃ ለማጠናከር እና ለማደራጀት አመቺ አይደሉም ሲሉም ይገልጻሉ፤ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጁን ከማስፈጸም አንጻር ተጠሪነት ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም መሆኑ ያልተመቻቸው እንዳሉም አስተውያለሁ፡፡
ይህ ሁሉ አስተያየት የሚሰጠው እንግዲህ አዋጁ ከወጣ ከአስር ዓመት በኋላ ነው፡፡ አሁን አዋጁ ምን አስገኘ ምንስ ቀረው ተብሎ መገምገም መሻሻል ካለበትም ማሻሻል ሲገባ በአዋጁ ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ችግሩ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ላይ ብቻ እንዳልሆነ ቢያመለክትም፤ ክፍሉ በቀደመው መንገድም ቢሆን መረጃ ማድረስ አለመቻሉ በትኩረት ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡
«የማይተማመኑ ጓደኛሞች በየወንዙ ይማማላሉ»እንደሚባለው እነዚህ ሁለት አካላት በመረጃ ዙሪያ ያለውን ችግር በመፍታት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ሁሌም ቢነጋገሩም ሁሌም እንደ አዲስ ከመነጋገር አልዳኑም፡፡
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎቹና ባለሙያዎቹ የመገናኛ ብዙኃንን ይመርጣሉ፡፡ ዛሬ በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እያሉም በርካታ ጋዜጠኞች ተሰብስበው እያለ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ አልመጣም ይላሉ፤ እነዚህ ቴሌቪዥን ናፋቂዎች ካሜራ ከሌለ መገናኛ ብዙኃን የለም ብለው የሚያስቡ ናቸው፡፡
መገናኛ ብዙኃን በፈለጉት ጉዳይ ላይ በቂ እውቀት ያለው የመስሪያ ቤቱ ባለሙያ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኖ እያለ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ካልፈቀደ በስተቀር መረጃ መስጠት አይፈቀድለትም፡፡ የበርካታ መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ይህን አቋም ሲያራምዱ ይስተዋላል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እና ባለሙያው ከእነዚህ ኃላፊዎች መረጃ ተቀብለው ማስተላለፍ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡ በዚህ መረጃ አማካኝነትም ሕዝብ ፊት ይቀርባሉ፡፡
ከኃላፊዎች መረጃ ሲጠየቁም በቅድሚያ ጥያቄዎቹ እንዲላኩላቸው የሚፈልጉ አሉ፡፡ ይህ ችግር ባይኖረውም ጋዜጠኛው ፊት ለፊት በሚኖር ቃለ ምልልስ ሊያነሳቸው የሚችል ጥያቄዎችን ለመመለስ አይፈልጉም፡፡ አንዳንዴ እነዚህ መሀል መሀል ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ወሳኝ የሚሆኑበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ መለስ ስጥ ከዚህ መለስ አትስጥ የሚሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች እንዳሉም ጋዜጠኞች ይጠቁማሉ፡፡
ጥያቄዎቹን ላኩ ብለው የውሃ ሽታ ሆነው የሚቀሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም አሉ፡፡ ምነው ሲባሉ መስሪያ ቤቱ በጉዳዩ ላይ በቅርቡ ጋዜጣዊ መግለጫ ስለሚሰጥ እናሳውቃችኋለን የሚል መልስ ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የሚገናኙባቸው የራሳቸው መድረክ የሌላቸው ናቸው፡፡ እናም በመገናኛ ብዙኃኑ ጥያቄዎች ላይ ተመስርተው ጋዜጣዊ መግለጫ በማዘጋጀት ሰራን ይላሉ፡፡ እነዚህ የመረጃ ትኩስነት የማይገባቸው ሊባሉ ይገባል፡፡
ሁሌ ስብሰባ፣ ግምገማ፣ መስክ ማለት የሚቀናቸው በእርግጥም ሥራቸውም ይህ የሆነ የሚመስል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም አሉ፡፡ መረጃ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሥራቸው የሆነ እነዚህ አካላት መስሪያ ቤታቸው ስትሄዱ ሁሌም ሲጣደፉ ነው የምታገኟቸው፡፡
ወደ መረጃ የሚያደርሱ ድልድይ መሆን ሲገባቸው የመረጃ አጥር በሆኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሳቢያ የበርካታ የመገናኛ ብዙኃንን እቅዶች አጨናግፈዋል፡፡ ሕዝብ ዘንድ መድረስ የነበረበት መረጃ ከንቱ ቀርቷል፡፡
ይህ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ለአንዳንዱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ምቾትን ያጎናጸፈ ይመስላል። የተቋማቸው መረጃ ሕዝብ ዘንድ ባለመድረሱ ተደላድለው እንዲቀመጡ አድር ጓቸዋል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ እንዲቀየርና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ያደርጉም ነበር፡፡
አንዳንድ ተቋማት ደግሞ በራሳቸው እቅድ በዓመት ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ ይህ በአንድ በኩል ትክክል ቢሆንም፣ በየጊዜው ከሚፈጠር ወቅታዊ ጉዳይ ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ ጋዜጠኞች ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ መስጠትን የሚከለክል መሆን የለበትም፡፡ የእነሱ ድርጊት ግን ለምን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠን ዕለት አለመጣችሁም ነበር በማለት ድክመቱን ወደ መገናኛ ብዙኃን ያዞራሉ፡፡
አሁን አሁን ደግሞ የመጣው አዲሱ አሠራር ሚኒሰትሩ፣ ሚኒስትር ዴኤታው፣ ዳይሬክተሩ፣ ወዘተ፣ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ቢሆኑም እንኳን የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን ማስፈቀድ የግድ ሆኗል፡፡ ይህም የግድ በእነሱ በኩል ማለፍ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህ አካሄድ አገሪቱን እየመራ ያለው የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ነው እንዴ ያሰኛል።
ጋዜጠኛውም፣ ሚኒስትሩም፣ ሚኒስትር ዴኤታውም፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊውም ባለሙያውም ለአገር እድገት መረጋገጥ የየራሳቸው የቤት ሥራና ኃላፊነት አለባቸው። ሚኒስትሩ የሰራውን በራሱ አንደበት አልያም ረዳቶቹ በሆኑት ዳይሬክተሮችና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ማሳወቅ ጋዜጠኛውም ያገኘውን መረጃ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለኅብረተሰቡ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ ሲችሉም ነው እጅ ለእጅ ተያይዘው ማደግ የሚችሉት ። አንዱ ፈላጊ ሌላው ገፍታሪ ሊሆን አይገባም፡፡
እዚህ ላይ ግን ምንም ቢሮክራሲ ሳያበዙ የተቋማቸውን ስኬትም ጉድለትም በድፍረትና በራስ መተማመን የሚገልጹ ብሎም የመፍትሔው አካል የሚሆኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ለመረጃ ዝግ የሆኑ እንዳሉ ሁሉ ሌት ተቀን ሥራቸውን ሰርተው ስልክ ደውለው ለመገናኛ ብዙኃን ተደራሽ የሆኑ የሕዝብ ግንኙነት እንዳሉ መጥቀስም ይገባል፡፡ ችግሩ አለመብዛታቸው ላይ ነው፡፡ እነዚህን ለማብዛት የሰራን ሰርተሀል ያልሰራንም አጉድለሃል፤ አስተካክል ማለት ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ተያይዞ ማደግ ይቻላል።
ይህንን ትልቅ የሥራ ዘርፍና ኃላፊነት ተሸክሞ አለመስራት ብሎም ሥራቸው ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ያለመፍፈቀድ ኃላፊነትን ካለመወጣት በተጨማሪ ራስን መኮፈስም ይሆናል፡፡ በመስሪያ ቤቱ ኤክስፐርት ሊተነተን የሚገባን ጉዳይ እኔ አተነትናለሁ ብሎ መነሳት ከንቱ መኮፈስ አይደለም አይባልም፡፡ ከዚህ አንጻር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ጋዜጠኞችን ከኤክስፐርቶችና ኃላፊዎች ጋር በማገናኘት ሕዝብ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኝ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአንድ ወቅት እንዳሉት መደባበቅ አያስፈልግም፡፡ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል፤ መረጃውን ተንተርሶ የሚገኝ ግብረመልስን በመጠቀም መስራት ይገባል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የተቋማት ኃላፊዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቋም ሊጋሩት ይገባል፡፡ በመሠረቱ የመረጃ ትንሽና ትልቅ የለውም፡፡ ነገር ግን ወቅታዊ እና ወቅታዊ ያልሆነውን ምስጢራዊና ምስጢራዊ ያልሆነውን ለይቶ በማደራጀት ለመገናኛ ብዙኃን በመስጠት ለሕዝብ እንዲደርስ ማድረግ በማድረግ ግብረ መልስ መሰብሰብም ይገባቸዋል፡፡

እፀገነት አክሊሉ

 

 

 

Published in አጀንዳ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።