Items filtered by date: Wednesday, 04 July 2018
Wednesday, 04 July 2018 20:26

የሳሎኑ ቀዝቃዛ ጦርነት

በሳሎኑ ተሰባስበው የቴሌቭዥን ፊልም እያዩ ካሉት መካከል አብዛኛዎቹ እየተሰደቱ ስለመሆኑ ገጽታቸው ይመሰክራል። ይህ ቤተሰብ እንደአሁኑ እረፍት ባገኘ ጊዜ በጋራ የሚያሰባሰበው እንዲህ አይነቱ የመዝናኛ ውሎ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንደኛው የቴሌቭዥን ጣቢያ የተጀመረው የቤተሰብ ፊልም ሁሉንም በአንድ እያገናኘ ሲያስቅና ሲያዝናና ማምሸቱ ተለምዷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዚህ ቤተሰብ መካከል የተለመደው የጋራ ጨዋታ እየደበዘዘ ነው ።ምሽት ደርሶ ሁሉም በተለመደው ስፍራ ሲቀመጥ የሚስተዋለው ጉራማይሌ ገጽታም ግልጽ የሆነ ልዩነት ስለመፈጠሩ ያመላክታል። ከሰሞኑ የቤቱ አባወራና የበኩር ልጅ የሆነው ወጣት መግባቢያቸው አንድ ሆኗል። ሁለቱም በእግር ኳሱ ቋንቋ ብቻ ያወራሉ ።
የኳስ ዜና ከመላው ዓለም ተነስቶ በቤተሰቡ መሀል ከገባ ወዲህ የጎራው ጦርነት ተጀምሯል። ጦርነቱ በሁለት ወገን የተከፈለ ልዩነት እንዳለው ግልጽ ነው። ይህን ውጊያ ለማሸነፍ አልያም ለመሸነፍ ግን ስልቱ ልክ እንደቀዝቃዛው ጦርነት ነው። ኩርፊያ፣ መነጫነጭና ንትርክ የበዛበት ታላቅ መቆራቆዝ።
ምሽት ደርሶ የቴሌቭዥን ስርጭት ሲጀምር እናት ትናንሽ ሴት ልጆችዋን ይዛ የተለመደውን ፊልም ለማየት ትሰየማለች። በዚህ ሰዓት ታዲያ ድስት ቢያርና በር ቢንኳኳ በአግባቡ ለአፍንጫና ለጆሮ የሚደርስ አይሆንም። ምን ቢጣሩና ቢጮሁም «አቤት» የሚል ላይኖር ይችላል። ይህ በሆነ ጊዜ ታዲያ የቤቱ አባወራ በእጅጉ ይቆጣሉ። በተለይ አውቀው ያጠፋሉ የሚሏቸውን ባለቤታቸውን።
የሰሞኑን አያድርገውና ሁሌም ቢሆን ይህ ፊልም ታይቶ እስኪያበቃ በእመቤቲቱና በአባወራው መሀል ጭቅጭቅ እንደነገሰ መቆየቱ ብርቅ አይሆንም። ባል ዜና እናዳምጥ፣ ወቅታዊ ጉዳዮችንም እንወቅ፣ በሚል ጥያቄ ያቀርባሉ። ይህ ፍላጎታቸው ግን ከጆሮ መለስ መፍትሄ አይኖረውም። ምንግዜም እንዳልሰማ ሆነው የሚያልፉት እማወራ ትናንሾቹን ልጆች አስተባብረው ለምን? ሲሉ ይደነፋሉ።ይሄኔ ሰውዬው አቅም አይኖራቸውም። በአብዛኛው ፍላጎት ተሸንፈው ሀሳባቸውን ይውጣሉ። ።
አባወራው ሁሌም ከነበሩበት በንዴት ተነስተው ወደ መኝታቸው ሲያመሩ አሮጌ ሬዲዮናቸውን እያንኮራኮሩ ነው። ምስጋና ለእሷ ይሁንና አብራቸው ያረጀችው የጥንት ስሪቷ ራዲዮ ከዚህም ከዚያም የቀራረመችውን ወሬ ለጆሯቸው ታደርሳቸዋለች። በማግስቱ ሁሉም ወደስራውና ወደትምህርት ቤት ሲበታተን የትናንቱ ጉዳይ በቤተሰቡ መሀል ‹‹ነበር›› ሆኖ ይረሳል። የማታው አለመግባባትና ኩርፊያም በባልና ሚስቱ መካከል እንዳልተፈጠረ ሆኖ ይተዋል። ምሽት ደርሶ ከተለመደው ቦታ ላይ ሲቀመጡ ግን የተለመደው ውዝግብና ‹‹የእኔ ይበልጥ የእኔ..›› ስሜት መጋጋሉ ይቀጥላል።
አንዳንዴ እመቤቲቱ የጓዳው ስራ ሲያሸንፋቸው ወደ ሳሎን ብቅ ሳይሉ ያሳልፋሉ። ይህን ግዜ አባት ልጆቻቸውን ለማሸነፍ ጉልበታቸው ይበረታና የሳሎኑን ቆይታ ተቆጣጥረውት ያመሻሉ። በዚህ ሰዓት ትናንሾቹ ልጆች ምን ቢያኮርፉና ቢንጫንጩ የእናታቸውን ያህል አቅም የላቸውምና በቀላሉ ይረታሉ። የእነሱ ቅያሜም ከተራ ማኩረፍና ዝምታ የዘለለ አይሆንም።
ሰሞኑን ደግሞ የቴሌቭዥኑ ሪሞት ኮንትሮል በአባወራው እጅ ገብቷል። እስከዛሬ ወይዘሮዋ ከልጆቻቸው ጋር የነበራቸው መደራጀትና ህብረትም በአንዲት ቃልና ማስጠንቀቂያ ድራሹ ሊጠፋ ግድ ብሏል። አሁን ወቅቱ ሀያ አንደኛው የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ የሚካሄድበት ነው። በዚህ እግር ኳስ ጨዋታም የዓለማችን ምርጥና ታዋቂ ተፋላሚዎች በየቤቱ ብቅ ብለዋል፡፡ እናም በቀላሉ ሪሞትን ለሌሎች አሳልፎ መስጠት ይከብዳል።
በዚህ ወቅት ለአባወራው ከእግር ኳስ ሌላ ወቅታዊ ጉዳይ የለም። ከታዋቂ ተጫዋቾች፣ ከጎል፣ ከቅጣትና ከምርጥ ጨዋታ ውጭም የሚያግባባና የሚያስማማ ቋንቋ ሊኖር አይችልም። አሁን በቤቱ ፊልምና ድራማ የሚሉት ጉዳይ ኮሽ እንዲል አልተፈቀደም። እንዲህ ሲሆን ደግሞ ሁሌም ምሽት በእግር ኳስ ድምጸት የሚዋጠው ሳሎን በእመቤቲቱና በልጆቻቸው ኩርፊያ መታጀቡ አልቀረም። ግን ምንም ማድረግ አይቻልም። አይደለም ኩርፊያና መነጫነጭ ለቅሶና ጩኸት ቢበረታ የአባወራው ውሳኔ ዝንፍ የሚል አልሆነም።
ይህ አቋም ደግሞ የእሳቸው ብቻ አይደለም ።የቤቱ የበኩር ልጅ ጎረምሳው ልጃቸውም ከጎናቸው ሆኖ ሲጮህና ሲደግፍ ማምሸቱ አዲስ አይደለም። ይህን ባዩ ጊዜ እመቤቲቱ የልጁ በጊዜ መሰብሰብ ያስደስታቸዋል። አንዳንዴ ደግሞ በትኩረት የሚከታተሏቸው እነዛ አጓጊ ፊልሞች እንደዋዛ እያለፏቸው መሆኑን ሲረዱ ልባቸው በንዴት ብግን ይላል።
በሰፊው ሳሎን ሁሌም ምሽት በደረሰ ቁጥር የቀዝቃዛው ጦርነት ፍልሚያ ይጀምራል፡፡ ጨዋታ ባለና ሰዓቱ በደረሰ ጊዜ ሪሞቱን የሙጥኝ የሚሉት አባት በዙሪያቸው የሚከቧቸውን ልጆች ለማባረር ቋንቋ አያሻቸውም። ፊታቸውን መለስ አድርገው አንዴ በግልምጫ ሲያነሷቸው ልጆቹ በቁማቸው ማዛጋት ይጀምራሉ። እማወራዋም ቢሆኑ እንደተለመደው ፊታቸውን ኮስተር አድርገው መነጫነጭ ያምራቸዋል። በሙከራቸው እንደማይዘልቁ ሲረዱ ግን ወደ ጓዳቸው ዘልቀው የቤታቸውን ጎዶሎ ሲከውኑ ያመሻሉ።
አንድ ቀን ምሽት ከሌላ አካባቢ ወደ ቤታቸው በእንግድነት ጎራ ያለ ዘመድ ቀዝቃዛውን ጦርነት በሌላ አቅጣጫ ለመምራት ሞክሯል፡፡ የቤተሰቡ ዘመድ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአርቲስቶች ጋር ያደረጉት ውይይት እየተላለፈ ነው፡፡ እሱን እንይ እንጂ! አሁን እኮ የአገር ውስጥ ወቅታዊ ጉዳዮችን ነው መመልከት የሚገባው›› በማለት የቴሌቭዥኑን ጣቢያ ለማስቀየር ጥረት አድርጓል፡፡
የምሽቱ እግር ኳስ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ እመቤቲቱ ሊያዩት የሚፈልጉት ፊልምና ድራማ አይኖርም። ይህን ሲረዱ ከልብ በሆነ ስሜት ያዝናሉ፡፡ ሳይወዱ በግድም የዚህን የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በእጅጉ ተመኝተው ቀን መቁጠር ይይዛሉ። እሳቸው ፈረንጅ ሲራገጥ ማየቱ ያበሳጫቸዋል፡፡ የእነሱ ፍልሚያና ትግልም ፈጽሞ ገብቷቸው አያውቅም። በፊልም የሚያውቋቸው ፈረንጆች ናቸው ለእሳቸው የሚጥሟቸው፤የሚገቧቸው፡፡
ሁሌም ቢሆን ምሽት ደርሶ ቤተሰቡ በቴሌቭዥኑ ዙሪያ ሲከብ የተለመደውን ፊልም እያስታወሱ መጎምጀት ይጀምራሉ።አንዳንዴ ደግሞ የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ሁለቱም ተቃናቃኞቻቸው ወደሳሎኑ ብቅ ላይሉ ይችላሉ። ይህን ጊዜ ደስታው ይደራል፤መከፋቱም ይረሳል።ወዲያውም የራሳቸውን ቡድን አጠናክረው ያቋረጡትን ፊልም ለማየት በቦታቸው ይሰየማሉ። ይህ ደስታቸው እምብዛም ሳይዘልቅ ግን አባት ከወንዱ ልጃቸው ጋር እየተጣደፉ ይገባሉ። ወዲያውም የቴሌቭዥኑን ሪሞት አንስተው ወደ እግር ኳሱ ዓለም ፈጥነው ይቀላቀላሉ።
ይህ ጦር ያላመዘዘ፤ ነገር ግን ውዝግብና መቀያየምን ያስከተለ ግብግብ ልክ እንደቀዝቃዛው ጦርነት የቤተሰቡ ሳሎን ከተቆጣጠረ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ቀድሞ ለምን? ሲባል በአሸናፊነት አቅጣጫ የሚቀየርበት የወይዘሮዋ ሪሞትም አሁን በሁለቱ ጉልበተኞች መዳፍ ላይ ወድቋል፡፡ ዛሬ ላይ በየምሽቱ በሳሎኑ የሚሰማው የዓለም ዋንጫና እግር ኳሱ ጨዋታ ብቻ ነው።
አሁንም በቤተሰቡ መሀል ቀን ቆጠራው ቀጥሏል። ሁለቱም ተቃናቃኝ ቡድኖች በየግላቸው ለጨዋታው መጠናቀቅ የቀሩ ጥቂት ቀናትን ያሰላሉ። አባትና ወንድ ልጃቸው በአንድ ወገን፣ እናትና ሴቶቹ ልጆችም በሌላ አቅጣጫ ሆነው አንድ ሁለት ሲሉ ይቆጥራሉ። የሁለቱም ቆጠራ ግን ዓላማና ግቡ ይለያያል። ወንዶቹ በአሸናፊና በተሸናፊ ቡድኖች ጉጉት ተወጥረዋል። ሴቶቹ ደግሞ ከጨዋታው ፍጻሜ ጀርባ ያሉትን ተወዳጅ የፊልም ቀናት እየናፈቁ ይቆጥራሉ። 1 2 3 4 ... በሰፊው የቤተሰብ ሳሎን ቀዝቃዛው ጦርነት ተፋፍሟል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

 

   የሳምንቱ ፎቶ ፍቅር ያሸንፋል!

 

ሁሌም ቢሆን ከጦርነት ይልቅ ሰላም፣ከጠብና ውዝግብም በላይ የፍቅርና መግባባት አሸናፊነት  ይጎላል።መልካም ልቦናና ጥሩ ስብዕና ያለው መሪ ደግሞ ከምንም  አስቀድሞ  የሀገሩንና የዜጎቹን ሰላም ውሎ ማደር አጥብቆ ይመኛል። ይህን ሰላማዊ መግባባት ለመፍጠር ደግሞ የጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ አዋሳኝ ድንበሮችና ዙሪያ ገባዎች ሁሉ በሰላምና መግባባት ሊተባበሩ ግድ ይላል። በቅርቡ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለአመታት ሻክሮ የቆየውን የኢትዮ- ኤርትራ ጉዳይ  በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል።ይህ ስኬት እውን መሆኑ ሲረጋገጥ ደግሞ ለሰላም የተዘረጉ እጆች አልታጠፉም።  በትህትና  ዝቅ ብሎ አክብሮትን ያሳየ ማንነትም ክብርና ሞገስን አልተነፈገም።ምንግዜም ፍቅር ሀያል ሆኖ ያሸንፋልና።

Published in መዝናኛ

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተካሄደው የድንበር ጦርነት ካበቃ 18 ዓመታት ተሻግሯል። በዚህም ሁለቱም አገራት በብዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ሰውተዋል፡፡ የጦርነቱ ዳፋ ደምን አፍሶ ብቻ አልቆመም፡፡ አገራቱ እርስ በእርስ በጠላትነት እንዲተያዩ አድርጎ ቆይቷል። ላለፉት ዓመታት አገራቱ ጥልና ቁርሿቸውን ረስተው ወደ ሠላም እንዲመጡ የተደረገው ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ለኤርትራ በተደጋጋሚ የሠላም ጥሪ ብታቀርብም በኤርትራ በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡
አሁን ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኤርትራ ያቀረቡት የሠላም ጥሪ በኤርትራ አቻቸው ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሠላም ጥሪውን እንደሚቀበሉ በማረጋገጥ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ ልከዋል፡፡ በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራው የልዑካን ቡድንም አዲስ አበባ በመምጣት ከዶክተር አብይና ከተለያዩ የኢትዮጵያ ባለ ስልጣናት ጋር በመወያየት ተመልሷል፡፡ የአገራቱ ግንኙነትም በአዲስ ምዕራፍ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ በቅርቡም የሁለቱ አገራት መሪዎች ተገናኝተው በጉዳዩ ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ አገራት ጉዞዋቸውን በአዲስ ምዕራፍ ሊጀምሩ ‹‹ ሀ»ብለዋል። የአገራቱ ህዝቦችም በተጀመረው የሠላም ሂደት ደስታቸውን በመግለፅ ያለፉትን ጊዜያት ለመርገም ተገደዋል። የትናንቱን የአብሮነት ጉዞ በማስታወስም ያሳለፉን የወዳጅነት ጊዜ ኋልዮሽ በመሄድ ይተርካሉ፡፡ በተለይም እ ኤ አ በ19 52 ኤርትራና ኢትዮጵያ አንድ አገር በመሆን ክፉና ደጉን አብረው ያሳለፉት አይረሳም፡፡ ይህ ዘመን ኤርትራ በኢትዮጵያ የስፖርት ሂደት ውስጥ የነበራትን አበርክቶ ማስታወስ ተገቢ ይሆናል፡፡
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት ኢትዮጵያና ኤርትራ እኤአ በ1953 እንደ አንድ አገር መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ የክለቦች ሻምፒዮና እንዲጀመር ምክንያት መሆኑም ይነገራል፡፡ በጊዜው ሦስት የኤርትራ ቡድኖች ከሸዋ ክፍለ ሀገር እና ከሐረር ጠቅላይ ግዛት ከተውጣጡ ቡድኖች ጋር ስምንት ክለቦች በመሆን የክለቦች ሻምፒዮና ተጀምሯል፡፡ ይህም እግር ኳሱ ወደ ፊት እንዲራመድ ረድቶታል፡፡ በዚህን ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 23 ሚሊዮን የኤርትራ ደግሞ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ነበር፡፡ በእግር ኳሱ ደግሞ ኤርትራ የተሻለ የሚባል ደረጃ ላይ እንደነበረች ለስፖርቱ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይነገራል።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በበሬሳ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በስፖርት ጋዜጠኝነት ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገለው ጋዜጠኛ ተሾመ ቀዲዳ «በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የኤርትራ ክለቦች አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው፡፡ በኤርትራ ክፍለሃገር የነበሩት ክለቦች ጠንካራ ስለነበሩ ለአገሪቱ ስፖርት ዕድገት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው» ይላል፡፡ በኢትዮጵያ የክለቦች ሻምፒዮና እንዲነቃቃና ትኩረት እንዲያገኝ የኤርትራ ክፍለሃገር ክለቦች ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። በሻምፒዮናው በተለያየ ጊዜ ከመሳተፋቸውም በላይ ሻምፒዮን በመሆንም ትልቅ ታሪክ ማስመዝገባቸውንም ያክላል፡፡
የኤርትራው ክለብ ሃማሴን በ1955 እና 1957 ለሁለት ጊዜ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ የሻምፒ ዮናነት ጉዞው ከኤርትራ ሳይወጣ በ1958 አካለ ጉዛይ የሚባለው የኤርትራ ክለብ ዋንጫውን አነሳ። ሌላኛው የኤርትራ ክለብ አስመራ ቴሌ፤ በ1959 ፣ 1969 እና 1970 ዓ.ም ሻምፕዮን በመሆን ለሦስት ጊዜያት ዋንጫውን ማንሳት ችሏል፡፡ ጂ ኤስ አስመራ በ1972 እና 1973 በተከታታይ ሻምፒዮና ለመሆን የቻሉ የአስመራ ክለቦች ናቸው፡፡ ቀይ ባህር እግር ኳስም ሌላው በሻምፒዮናነት ስሙ የሚጠቀስ የኤርትራ ክለብ መሆኑን አንጋፋው ጋዜጠኛ ተሾመ ያስታ ውሳል፡፡
ከጋዜጠኛ ተሾመ ማብራሪያ በተጨማሪ የኤርትራ ክፍለሃገር ክለቦች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የነበራቸውን ተጽእኖና ለእግር ኳሱ መነቃቃት ያበረከቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደሆነ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንና የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ደሳለኝ ገብረ ጊዮርጊስ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል፡፡ ደሳለኝ እንዳለው፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረችበት ጊዜ በኤርትራ ክፍለሃገር ውስጥ አዶሊስ በሚባል የቀበሌ ክለብ ውስጥ ይጫወት ነበር፡፡ በሂደትም በኢትዮጵያ የክለቦች ሻምፒዮና ጠንካራ ከሚባሉት አንዱ የሆነውን የኤርትራ ጫማ ክለብን ተቀላቀለ፡፡ ከክለቡ ጋር በነበረው ቆይታ አቅሙን ማዳበር ችሏል፡፡
በጊዜው ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ በኤርትራ ክፍለሃገር የነበሩ ጠንካራ ክለቦች ለብሄራዊ ቡድን በመሰለፍ ትልቅ ሚና የነበራቸው ተጫዋቾችን ማፍራት መቻላቸውን ደሳለኝ ያስታውሳል፡፡ ከኤርትራ ጫማ የወጡት እነ ጎደፋ ደባስ፣ ነጋሽ ተክሊት፣ ግዛቸው በርሄና ገብረ ሚካኤልን የመሳሰሉ አንጋፋ ተጫዋቾችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኤርትራ ጫማ ትልቅ ውጤት ያስመዘገቡ በርካታ ተጫዋቾች ያፈራ ክለብ መሆኑን የሚጠቁመው ደሳለኝ፤ እሱም የዚህ ክለብ ፍሬ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ብሏል፡፡
በ1924 ዓ.ም አካባቢ በኢትዮጵያ የሚኖሩ አርመናዊያን፣ ጣሊያናዊያን፣ እንግሊዛዊያን፣ ህንዶችና ግሪኮች እግር ኳስን እንዳስተዋወቁት ይተረካል። ክለቦችን በመመስረቱ ረገድም እነዚህ የውጪ ዜጎች ስማቸው ይጠቀሳል፡፡ በ1935 ዓ.ም የክለቦችን መመስረት ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በመውደቅና በመነሳት፣በመዳከምና በመጠናከር የተለያዩ ውጣውረዶችን አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
በእግር ኳሱ ጉዞ ውስጥ ሁለት ነገሮች ተንጸባርቀዋል። እግር ኳሱ ከውጤት ርቆ ሲወድቅ «ስታዲየሙ ይታረስ፤ ድንች ይዘራበት»የሚሉ ሃሳቦች እስከ መንፀባረቅ ተደርሷል፡፡ በዚህ ደረጃ እንዲቀበር የተፈረደበት እግር ኳስ ትናንት በአስደናቂ ከፍታ ላይ እንደነበር ይነገራል፡፡ የእግር ኳሱ ስኬት ሲነሳም ኤርትራውያን ስማቸው አብሮ ይነሳል፡፡ ኢትዮጵያ ከሦስተኛው እስከ 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በማድረግ በመካከል ለ30 ዓመታት ተሳትፎዋ ተገድቦ ቆይቷል፡፡ በእነዚህ የአፍሪካ ዋንጫ የተሳትፎ ታሪክ የኤርትራ ክፍለ ሀገር ተጫዋቾች የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡
ከዚህ በኋላ እአአ በ2013 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የቻለችው፡፡
ኢትዮጵያ ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ስታነሳ ከዚህ ድል ጀርባ በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ከነበሩት ተጫዋቾች የኤርትራ ክፍለሃገር ክለብ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ በዚህ የስኬት ታሪክ ውስጥ የቡድኑ መሪ የነበረው በኤርትራ የተወለደው ሉቺያኖ ቫሳሎ ስሙ ጎልቶ ይጠቀሳል፡፡
በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ እንደ ሉቺያኖ ቫሳሎ ሁሉ በርካታ የኤርትራ ተወላጆች ተሳትፎ አድርገዋል። ሉቺያኖ በእግር ኳሱ ህይወቱ ትልቁን መስመር ባስያዘው የኤርትራ የባቡር ድርጅት ክለብ በሆነው ሩፖ ስፖርቲቮ ፌሮቬሪ ውስጥ ነበር የሚጫወተው፡፡ በአሰልጣኝነት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ በማገልገል ከሚጠቀሱት መካከል ጸጋየ ባህረ ሌላው የአስመራ ፍሬ ነው፡፡ ጸጋየ የተጫዋችነት ጊዜውን ከጨረሰ በኋላ በኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ ይሰራ ነበር፡፡ በኋላም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በምክትል አሰልጣኝነት በመያዝ አገልግሏል፡፡
የኢትዮጵያ አካል የነበረችው ኤርትራ ካፈራቻቸው የስፖርት ባለሙያዎች መካከል ታሪክ የሚያስታ ውሳቸውን አቶ ተስፋዬ ገብረኪዳንን መዘንጋት አይቻልም፡፡ አቶ ተስፋዬ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በዳኝነት ሙያ አገልግለዋል። ኢትዮጵያን በመወከል የካፍ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆንም ሰርተዋል፡፡ አበርክቶዋቸው በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ አቶ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ዳኞች ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆንም ለስፖርቱ ዕድገት አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን አገልግለዋል፡፡
ከቀደሙት ዓመታት በኢትዮጵያ የስፖርት ጉዞ ውስጥ የኤርትራውያን ድርሻ ጉልህ ነበር፡፡ ኤርትራ እራሷን ችላ በህዝበ ውሳኔ ከኢትዮጵያ መነጠሏን ተከትሎ ሁለቱም ለየብቻቸው ለመጓዝ ተገደዋል፡፡ የስፖርቱ ታሪክም ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ ሁለቱ አገራት የየራሳቸውን ስፖርት ለማሳደግ ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ በአገራቱ መካከል በተፈጠረ ግጭት ሠላማዊ ግንኙነት ሳይፈጠር ለ18 ዓመታት ያህል ቆይቷል፡፡
በቅርቡ የተጀመረው የሠላም ሂደት ታዲያ በስፖርቱ ዘርፍም የተሻለ ግንኙነት እንደሚፈጥርም ጥርጥር የለውም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሠላም ጥሪ ተከትሎ አገራቱ ዳግም ታሪክ ለመጋራት መጀመራቸውን በብሄራዊ ቤተ መንግሥት እጅ ለእጅ በመያያዝ አብረው ዘምረዋል። አገራቱ የተናጠል መንገድን በመተው የአብሮነት ጉዞን መጀመራቸው ስፖርታዊ ግንኙነቱን ለማጠናከር ይረዳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ «...የእኛ አትሌቶች አስመራና ምጽዋ ላይ አብረው ለመሮጥ ተርበዋል...»እንዳሉት በስፖርት የአገራቱንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡
በቀደመው ዘመን ላይ የነበረው በስፖርት የመደመር ጉዞ አሁንም በአዲስ ምዕራፍ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደ ጠላት ሳይሆን በወዳጅነትና ወንድማማችነት ስሜት በስፖርት መድረክ ይሰለፋሉ፤ይፎካከራሉ፡፡ በእግር ኳስ ዘርፍም አገራቱ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ያደርጋሉ፡፡ በዲፕሎማሲ የተጀመረው ግንኙነት በስፖርቱ ሲጋዝ የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡ አይቀሬ ነው፡፡

 

መቀሌና አዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ሽንፈትን አስተናገዱ

 

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው ዘጠነኛው የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታ እንደቀጠለ ነው። በጨዋታው በአስር የስፖርት አይነቶች ከ18 አፍሪካ አገራት የተውጣጡ 57 ዩኒቨርሲቲዎች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
ባለፉት ሶስት ቀናት ቆይታ በእግር ኳስ በተደረገ ውድድር ከኢትዮጵያ የተወከሉት ዩኒቨርሲቲዎች ደካማ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡ ይህም የአገሪቱ የእግር ኳስ ድክመት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
በእግር ኳስ ስፖርት አምስት ቡድኖች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም ከኢትዮጵያ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ እና አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሲሆኑ፤ ጊኒ ኮናክራ ዩኒቨርሲቲ እና ዛንዚባር ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች አፍሪካ አገራት የተወከሉ ናቸው፡፡
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ ሁለተኛው ቀን ከታንዛኒያው ዛንዚባር ዩኒቨርሲቲ ጋር ተጋጥሟል፡፡ የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በበርካታ ደጋዎች ፊት ቢጫወትም መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በጨዋታ ተበልጦ 5 ለ 0 ተሸንፏል፡፡ የዛንዚባር ዩኒቨርሲቲ ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት ረገድ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴን አሳይቷል። ተጫዋቾቹ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲን የግብ ጠባቂ ድክመት በመረዳት ረጅም ኳስን በመጠቀም የፈጠሩት ጫና በመጀመሪያው አጋማሽ 4 ግቦችን ለማስቆጠር ረድቷቸዋል፡፡
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ከተጫዋቾቹ ጋር በአሰል ጣኝነት የቆየውን ባለሙያ በስተመጨረሻ በማሰናበት በቼዝ ስፖርት ባለሙያ እንዲተካ መደረጉ ሜዳ ላይ ቅንጅት የጎደለው እንቅስቃሴ እንዲታይ ምክንያት ሆኗል፡፡ ተናቦ ያለመጫወትና የልምድ ማነስም ተስተውሏል፡፡ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከጊኒ ኮናክራ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረገው ጨዋታም አራት ለባዶ ተሸንፏል፡፡
በእግር ኳሱ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁት እአአ 2018 መጨረሻ በቻይና በሚካሄደው የመላው ዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታ ላይ ይሳተፋሉ፡፡ የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጨዋታ እአአ ከ1975 ጀምሮ በጋና አክራ የተጀመረ ሲሆን፤ በየሁለት ዓመቱ እየተካሄደ ዘንድሮ ላይ ደርሷል፡፡ ሰኔ 24 የተጀመረው ውድድር ሰኔ 29 ቀን 2010 ዓ᎐ም ፍጻሜውን ያገኛል።

ዳንኤል ዘነበ 

Published in ስፖርት

ከወትሮው በተለየ በሰዎች አጀብ የተሞላው ግቢ ለአፍታ እንኳን ጭርታ አይታይበትም። ጠበብ ያለው መተላለፊያ ከወዲያ ወዲህ በሚሉ እንግዶች ተጨናንቋል። ሥራ የበዛባቸው የህክምና ባለሙያዎችም ወጪና ወራጁን በአግባቡ ተቀብለው ማስተናገዱን ተያይዘውታል። ዛሬ በዚህ ግቢ ዕረፍት ይሉት ነገር አይታሰብም። ሁሉም የመጣበትን ታላቅ ጉዳይ በአግባቡ ለመከወን ውድ ጊዜውን ሰጥቷል። አሁን ታላቅ ለሆነው ዓላማ ክቡር የሆነውን ስጦታ ለማበርከት እያንዳንዱ ተራው እስኪደርስ እየጠበቀ ነው። ብሔራዊ ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው ብሔራዊ የደም ባንክ ቅጥር ግቢ።
በእግራቸው ወደ ግቢው ከደረሱትና ጥቂት ከማይባሉት ባሻገር ከአውቶቡሶች እየወረዱ ወደ ውስጥ የሚዘልቁት በርከት ይላሉ። በማረፊያ ድንኳኖች ሆነው የሚለቀቁ ወንበሮችን የሚጠባበቁም ብዙዎች ናቸው። እያንዳንዳቸው በፊታቸው ላይ የበጎነት ምልክት ይነበባል። ሁሉም ዛሬን በዚህ ቦታ ታድመው ለዚህ ዕድል በመብቃታቸው መደሰታቸውን ብሩህ ገጽታቸው ይመሰክራል።
ተገቢውን ምክርና መረጃዎች ወስደው ደም ለመስጠት የሚጠብቁትን ተረኞች አልፌ በጀርባቸው ተንጋለው ደም ወደሚለግሱት በጎ ፈቃደኞች አማተርኩ። በተለያየ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ወጣቶች፣ ጎልማሳዎችና ሴቶች እይታዬን ማረኩት። ዓይኖቼ ከአንዱ ጥግ አረፍ ብላ ደም እየለገሰች ወደምትገኝ ወይዘሮ አነጣጠሩ። አጠገቧ መድረሴን እንዳየች በብሩህ ፈገግታ ተቀበለችኝ ።
ወይዘሮ ሙሉወርቅ ሽኩር በቦታው ለመገኘት ምክንያት የሆናት ከውስጥ የመነጨ የበጎነት ስሜት መሆኑን ትናገራለች ። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተደረገው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ በተፈጸመው የቦንብ ጥቃት የተጎዱ ወገኖቿ ህመም አሁንም ድረስ ይሰማታል። በዕለቱ በቦታው ለመገኘት ጽኑ ፍላጎት ቢኖራትም በሥራ ምክንያት አልተገኘችም። ይሁን እንጂ ካለችበት ሆና ከድጋፍ ያለመራቋን ታስታውሳለች። ልጆቿም በሰልፉ ታድመዋል፡፡
ከደማቁ ውሎ ጀርባ የሰማችው እኩይ ተግባር በእጅጉ አስደንግጧታል። ከምንም በላይ ግን የህዝቡ አንድነት፣ መተሳሰብና ጠንካራ ወኔ እሷም እንደዜግነቷ የምትጋራው ስሜት ነበር። ወይዘሮዋ ደም ለመስጠት አዲስ አይደለችም፡፡ በእሷ በጎነት የሌሎችን ህይወት መታደግ እንደሚቻል ጠንቅቃ ታውቃለች።
ከዚህ ቀደም የእናቶች ህይወት ሰበብ ሆኗት ለአምስት ጊዜ ደም ለግሳለች። እሷን ጨምሮ መላው ቤተሰቧ ደም የመስጠት ባህሉ እየጎለበተ መሆኑም ያኮራታል። በጥቃቱ ሳቢያ ጉዳት ላጋጠማቸው ወገኖች የእሷ ደም መድህን መሆኑ ከምንም በላይ እንደሚያስደስታት የምትናገረው በተለየ ስሜት ነው።
ወጣት ታሪኩ ተሰማ በሰኔ 16ቱ ህዝባዊ ሰልፍ አጋርና ተሳታፊ ከነበሩት መካከል አንዱ ነው። ገና ከማለዳው አንስቶ የደመቀው ሀገራዊ ስሜትና ወገናዊ ድጋፍም የተለየ እንደነበር ያስታውሳል። በዕለቱ የፍንዳታው ድምፅ ሲሰማ ርችት መስሏቸው «ይደገም» ሲሉ ከነበሩትም አንዱ ነው። ድምፁን የበዓሉ አካል አድርገው የወሰዱት በርካቶች ችግሩ እስኪታወቅ በዚህ ስሜት ውስጥ እንደቆዩ አይዘነጋውም።
ታሪኩ እውነታውን ዘግይቶ ሲረዳ ኀዘኑ በረታ፡፡ በወገኖቹ ላይ የተፈጸመው እኩይ ተግባርም በጣም አበሳጭቶታል፡፡ ይህን ስሜት በውስጡ ይዞ መቆየቱ ብቻ ያልበቃው ወጣት ታዲያ አጋርነቱን በተግባር ማሳየት እንዳለበት ወሰነ። ደሙን ቢለግስ የወገኑን ህይወት እንደሚታደግ ያውቃልና ያለማንም ጎትጓች ወደ ብሔራዊ ደም ባንክ አቀና፡፡ ደም መለገስ ሰብዓዊ ስሜት መሆኑንም በመረዳት በቀጣይም ደም በመለገስ የወገኑን ህይወት ለመታደግ ዝግጁ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት አስራ አምስት የሥራ ባልደረቦቹን አስተባብሮ ከስፍራው የደረሰው ወጣት ለዛሬ ያሰበው አልተሳካለትም። ከባልንጀሮቹ ቀድሞ ከመጀመሪያው ረድፍ ተሰለፈ። ሸሚዙን ወደ ላይ ሰብስቦም ክንዱን ለባለሙያዎች ዘረጋ። ባለሙያው የወጣቱን የዕለቱን የጤንነት አቋም ለማወቅ መመርመሪያቸውን አነሱና ደሙን ለኩ። ውጤቱ ራሱን አርአያ አድርጎ ሌሎችን ለማስከተል የነበረውን ዓላማ የሚያሳካ አልሆነም።
የደም ምርመራው ውጤት አንድ መቶ ሰባ በዘጠና ሆነ፡፡ ውጤቱ በጎ ፈቃደኛው ደም መስጠት የሚያስችል አይደለም፡፡ ይህን ያወቀው ወጣት በሰማው እውነት አልተደናገጠም። ትናንትና ከዚያ በፊት በነበሩት ዓመታት ለአስር ጊዜያት በለገሰው ደም ብዙዎችን እንደታደገ ያውቃል። የዛሬው እንዳሰበው ባይሆንም በእሱ መሪነት ሌሎችን ተክቷልና ደስተኛ ነው። ነገ ደግሞ ሌላ ቀን ነው፤ በሌላ ቀን ውስጥ ሌላ ህይወት ማትረፍና ደም መስጠት ይቻላል፡፡
አንድ መቶ ኪሎ ግራም የሚመዝነው የሃያ ሰባት ዓመቱ ፍልቅልቅ ወጣት ጌታነህ ከቀናት በኋላ ራሱን አረጋግቶና ጊዜ ወስዶ እንደሚመለስ እርግጠኛ ሆኗል። ይህን እንደሚያሳካ ሲያውቅ ደግሞ እንደልማዱ ሌሎችን አስተባብሮ በስፍራው እንደሚደርስ በማመን ነው። ለቀሪዎቹ ጊዜያት ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚጠብቁት ሲረዳም ዳግመኛ በውስጡ ያለው ነባር በጎነት ይቀጣጠላል።
የሰዎች አጀብ ከሚታይበት ሰፊ ድንኳን አካባቢ ደርሻለሁ። በዚህ ስፍራ አሁንም ተራቸውን ያለመታከት የሚጠብቁ በጎ ፈቃደኞች አሉ። የኪነጥበብ ባለሙያዎችና አንዳንድ ታዋቂ ሰዎችን አስተዋልኩ። ሳቅና ጨዋታ የደራበት ይህ አካባቢ በኮሜዲያን ቀልድ እየተዋዛ መሆኑ ቢገባኝ ጠጋ ብዬ ጥቂቶቹን ላዋያቸው ፈለግሁ።
ኮሜዲያን በረከት በቀለ /ፍልፍሉ/ ፈገግታ ባወዛው ገጽታው ከአጠገቤ ደርሷል። ዛሬ በቦታው የተገኘበት ዋና ዓላማ የሙያውን ፍሬ ለአድናቂዎቹ ለማቅረብ አይደለም። በአካባቢው በሳቅ የሚንከተከቱ ተመልካቾች የሉም። የተለመደው ቀልድና ጨዋታም እየፈሰሰ አይደለም። የእነ ፍልፍሉ ወቅታዊ ምክንያት ሌላ ድንቅ ዓላማን የያዘ ነው። ህይወትን ለማስቀጠል ክቡር የሆነውን ደም መለገስ፣ በበጎ ፈቃድ ስሜት በጎነትን የማስቀጠል ዓላማን የሰነቀ ነው።
ኮሜዲያን ፍልፍሉ ሰኔ 16ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በንጹሀን ወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን የቦምብ ጥቃት በእጅጉ ያወግዘዋል። ደም ለሚያስፈልጋቸው ህሙማን የራሱን ድርሻ ማበርከት እንደሚኖርበት ያምናል። ወደ ብሔራዊ የደም ባንክ ለመምጣት ምክንያት የሆነውም ይህ በውስጡ ያደረው ወገናዊ ስሜት መሆኑን ይናገራል።
ፍልፍሉን ጨምሮ ሌሎች የሙያ አጋሮቹ ወደ ስፍራው ለመምጣት ማንም አልገፋፋቸውም፡፡ በእነሱ አርአያነት ሌሎችን ለማስከተል የሚያደርጉት ጥረትም መልካም እንደሚሆን ያምናሉ። ይህ አጋጣሚ ደም ለመስጠት ምክንያት እንደሆናቸው የሚናገረው ኮሜዲያኑ በዚህ ብቻ ሳይቆም ወደፊትም ደም የመለገሱ ባህል ይቀጥላል ብሏል፡፡
ኮሜዲያን ደምሴ ፈቃዱ /ዋኖስ/ ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር ደም ለመለገስ በመምጣቱ ደስተኛ ነው። በቦምብ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ደም እንደሚያስፈልጋቸው ሲሰማም የበኩሉን ለማድረግ መዘግየት እንደማይኖርበት የወሰነው ወዲያውኑ ነበር። ይህን ጥሪ የሰሙ በርካቶችም በጎነትን ለማሳየት የመፍጠናቸው እውነታ እሱንና ጓደኞቹን ይበልጥ እንደገፋፋቸውም ይናገራል።
ደምሴ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ተሳታፊ እንደመሆኑ ድርጊቱን በሰማ ጊዜ ከልቡ አዝኗል። ከአደጋው በኋላ የበርካታ ወገኖችን መረባረብ ሲመለከት ደግሞ ለእሱ ኃይልና ብርታት ሆኖታል። በዚህ መነሻነት እሱና የኮሜዲያን ማህበሩ ከብሄራዊ የደም ባንክ ጋር በመነጋገር በየሶስት ወሩ ደም ለመለገስ መስማማታቸውን የሚናገረው በታላቅ ኩራት ነው። ይህም አጋጣሚ ለሌሎች አርአያ በመሆን በርካቶችን ከኋላ እንደሚያሰልፍ እርግጠኛ ነው፡፡
ኮሜዲያን ምትኩ ፈንቴ /ማይክርስቶስ/ ከሙያ አጋሮቹ ጋር ተወያይቶ ደም ለመለገስ ወደግቢው ዘልቋል። ለእሱ ይህ አጋጣሚ ለሦስተኛ ጊዜ ቢሆንም የአሁኑ ደግሞ ለተለየ ዓላማ የመሆኑ እውነታ በእጅጉ ያኮራዋል። ሁሌም ቢሆን በመሰል ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምላሽ ለመስጠት የፈጠነው የኮሜዲያን ማህበር ዛሬም አባላቱ ደም ለግሰው ህይወትን ማትረፍ በመቻላቸው መልካም ጅምር የሚያስብለው ይሆናል።
እንደ ኮሜዲያን ምትኩ ዕምነት ለወገን ደራሽ ሁሌም ወገን ነውና ይህ አጋጣሚ ሀገራዊ ስሜቱን በፍቅር ሊያቀጣጥለው ችሏል። ሁሌም ከወገን ጎን ለመሰለፍ ወደኋላ የማይሉት ጓደኞቹም ዛሬም ሆነ ነገ ለሚያከብራቸው ህዝብ ክብርን ለመስጠት ዝግጁ ናቸው። ከምንም በላይ ደግሞ ደምን ሰጥተው ህይወትን መመለስ መቻላቸው በበጎ አርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡
በሰኔ 16 ቀን 2018 በመስቀል አደባባይ ሠላማዊ ሰልፍ ላይ በቦምብ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚደረገው የደም ልገሳ ርብርብ አሁንም ድረስ ቀጥሏል። ህይወትን ለማዳን ደም የመለገሱ የበጎነት ተግባር በርካቶችን አሰልፏል፡፡ ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ የሆነው የደም ስጦታ ህይወትን ይታደጋልና ሁሉም ለዚህ በጎ ተግባር መሰለፍ ይኖርበታል፡፡ ደም በመለገስ ህይወትን ለማዳን መረባረብ ይገባል፡፡

መልካምስራ አፈወርቅ

Published in ማህበራዊ

ህዝብ በርከት ያሉ ችግሮችን እያነሳ ጣቱን ወደ መንግሥት መቀሰር ከጀመረ ቆም ብሎ ማየቱ አገርን ከጥፋት የማዳን የመጀመሪያው የመፍትሔ እርምጃ ይሆናል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ታዲያ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው የተባሉ ጥያቄዎች ተነስተው የጋራ መድረኮችም እየተፈጠሩ ውይይት እንደተደረገባቸው የተለያዩ ለውጦችም እንደመጡ ይገለፃል፡፡ ይህንንም መሰረት ተደርጎ ጥልቅ ተሃድሶዎች መካሄዳቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታዎች ናቸው፡፡ እኛም ለዛሬ መንግሥት የለውጥ እርምጃ አድርጎ የወሰዳቸው መፍትሔዎች ምን ለውጥን አስገኙ? በሚል በተለይም በመልካም አስተዳደር ዘርፍ በችግር በተለዩት መሬት፣ ግንባታ ፈቃድና ደረቅ ቆሻሻ ላይ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ከተለያዩ አካላት ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ምን ተሰራ
አዳማ የክልሉ ትልቁ ከተማና ከግማሽ ሚሊዮን ነዋሪዎች በላይ በውስጡ እንዳቀፈ የከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጀንሲ የሪፎርም ሥራ ሂደት ተወካይ አቶ ጌቱ ኩምሳ ይገልፃሉ፡፡ ሁሌም ቢሆን ታዲያ ከተማ ባደገ ቁጥር መሬት በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ የማይተካ ስለሆነ በከተማው ያለው የመልማት ፍላጎት ሰፋ ያለ ነው፡፡ ኤጀንሲው በ2006 ዓ.ም ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ራሱን ችሎ የወጣ ሲሆን፤ ተቋሙን በሰው ኃይልና በግብዓት በማደራጀት ወደ ሥራ መገባቱን ያስታውሳሉ፡፡ በእነዚህ ዓመታትም ለህዝብና ለመንግሥት አገልግሎት የሚውሉ ለልማት የሚያስፈልጉ መሬቶች የማቅረብ፣ የማልማትና የማዘጋጀት ተግባር ሲከናወን ቆይቷል፡፡
በዘርፉ ለዓመታት የተንከባለሉ ሰፊ ውዝፍ ችግሮች እንደነበሩ የሚገልፁት አቶ ጌቱ፤ የጨረቃ ቤቶች፣ ካርታ ያልተሰጠባቸው ነባር ይዞታዎች መኖር እንዲሁም መልሶ ማልማት ሥራ እንደሚሰራ ያስረዳሉ፡፡ የጨረታ ቤቶቹ በ2005 ዓ.ም የሊዝ አዋጁ ከመውጣቱ አስቀድሞ የተገነቡትና ከፕላን ጋር የሚጣጣሙትን እንዲሁም ነባር ይዞታ ሆነው ካርታ የሌላቸውን የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙም ተደርጓል፡፡ ትልቁ ነገር ለህዝብና ለመንግሥት ተብሎ ከአርሶ አደሮች ላይ ከ1998 እስከ 2000 ዓ.ም በስፋት ለልማት ተወስዶባቸው ያልተቋቋሙ ብሎም ምትክ ያልተሰጣቸው ሰፋ ያሉ አርሶ አደሮች ነበሩ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታትም እነዚህን የመለየት ሥራ በከፍተኛ ትኩረት ሲሰሩ ከነበሩ ተግባራት ዋነኛው ነው፡፡
ቤት ለሌላቸው የመንግሥት ሠራተኞች መንግሥት ባወጣው አቅጣጫ መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ሌላው በትኩረት የተሰራ ተግባር ነው፡፡ በከተማው በማህበር ከተደራጁ ከ2 ሺህ 1 በላይ ነዋሪዎች መካከል 1 ሺህ 700 የቤት ርክክብ አድርገዋል፡፡ ከ2 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችም በ 1 መቶ 15 ማህበራት ተደራጅተው የማምረቻና መሸጫ ቦታ አዘጋጅቶ መስጠት ሌላው በቀዳሚነት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡
በተያያዘም ከኢትዮ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልል በተፈጠረ ግጭት ለተፈናቀሉ የመጀመሪያ ዙር 1 ሺህ 500 በሁለተኛ ዙር አምስት መቶ ተጨምሮ ቦታ ተዘጋጅቶ መልሶ የማቋቋም ተግባርም መከናወኑ በህብረተሰቡ በመልካም አስተዳደር የተለዩትን ችግሮች ለማቃለል የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አቶ ጌቱ ያመላክታሉ፡፡ የጨረቃ ቦታዎች መዝግቦ ለይቶ ማነው በህጉ መሰረት የሚገባው በሚል ከህዝብ ጋር የሚሰሩ ስፋት ያላቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ከተማው በዕድሜም የገፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሮቹም በርከት እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡
በልደታ ክፍለ ከተማ የጽዳት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዋለ እንደሚናገሩት፤ እያንዳንዱ ግለሰብ ከመኖሪያ ቤቱ እንዲሁም ተቋም ከሚያመነጨው ደረቅ ቆሻሻ በማህበራት እንዲሁም ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው አካላት በመሰብሰብ ያስወግዱታል፡፡ በየመንገዱም በክፍት ቦታዎች የሚመነጨው ቆሻሻ በመንግሥት ተቀጣሪ በሆኑ ፅዳት ሠራተኞች ይሰበሰባል፡፡ አገልግሎቱን ማዘመንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በርካታ መሻሻሎች ታይተውበታል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም አገልግሎቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየተሰራ ያለው ሥራ ውስንነቶች ይታዩበታል፡፡
ከሰው ኃይል በተጨማሪ የመንገድ ላይ ማፅጃ ማሽኖች በሥራው ላይ ውለዋል፡፡ ምንም እንኳ በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት ቢሰራም አሁንም በየቦታው ቆሻሻ የማዝረክረክ ችግሮች ሲፈጠሩ ይታያል፡፡ ይህም በአንድ በኩል ከግንዛቤ በሌላ በኩል በቸልተኝነት የሚፈጠር ነው፡፡ ይህንንም ለማስወገድ በተለያዩ ጊዜያት ግንዛቤ ማስጨበጫ ይሰጣል፡፡
ሥራውን ማዘመን እያንዳንዱ ሰው ከቤቱ የሚያወጣውን ቆሻሻ በአግባቡ ለይቶ ከማውጣት ይጀምራል፡፡ የእያንዳንዱ ድምር ውጤትም የአገሪቱን ገፅታ ለመገንባት የሚያስችል አቅም እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የህዝብ ተሳትፎ በሚያረጋግጥ መልኩ የባለቤትነት መንፈስ ለመፍጠር በወር አንዴ የፅዳት ዘመቻ ይደረጋል፡፡ በያገባኛል ስሜት በቅንጅት በመስራት ተጠናክሮ መሄድ እንዳለባቸው ታምኖ ይሰራል፡፡ ይህም ለሚነሱ ችግሮች ለውጥ ለማምጣት የጋራ ርብርብም እንደሚጠይቅ አቶ ተስፋዬ ይገልፃሉ፡፡
ዘርፉ ለብልሹ አሰራር ክፍት በመሆኑ ፈፃሚውን በስነምግባር የታነፀ እንዲሆንና በአቅምም የጎለበተ እንዲሆን ስልጠናዎች እንደሚሰጥ የሚናገሩት በጉለሌ ክፍለ ከተማ በመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አብዲሳ አሁንም ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉ የሚያመላክቱ ችግሮች መኖራቸውንም ይገልፃሉ፡፡
ግምገማዊ ስልጠና በስድስት ወርና በዓመት እንዲሁም አጠቃላይ ፈፃሚውንም አመራሩ የሚደግፍበት ሥርዓትን በመፍጠር ከጊዜ ወደ ጊዜ ለስርቆት በር የሚከፍቱ መንገዶችን የመስበር ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ አቶ ደሳለኝ እንደሚያስረዱት፤ ለዜጎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ብቁና በስነልቦና የተዘጋጀ ፈፃሚ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት የሚደረግበት መንገድ ስውር ነውና የማይታየውን ይህን ህዝብ የሚጎዳ ያልተገባ ድርጊት ለመከላከል እንቅስቃዎች ይደረጋሉ፡፡ ጎን ለጎንም አመራርና ፈፃሚዎችን ማጥራት ተደርጓል፡፡ በዚህም ዜጎች በተገቢው መንገድ አገልግሎት ላለማግኘታቸው ውጣ ውረዶችና እንግልቶች በመብዛታቸው በየደረጃው ተገምግመው ከህዝብ ጋር በመሆን ለማስተማሪያ በሚሆን ልክ የእርምት እርምጃ በከተማ ደረጃ መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡
በክፍለ ከተማው ብቻ 27 አመራርና ፈፃሚዎች ተጠያቂ መደረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ደሳለኝ በዚህ ችግሩ ተቀርፏል ማለት እንደማይቻልም ያብራራሉ፡፡ በመሆኑም የማስተካከያ እርምጃው ከአቅም ማሳደግ ሥራዎች ጎን ለጎን የሚቆም ሳይሆን በቋሚነት ሊሰራ የሚገባው ነው፡፡ ውሳኔውም በማስረጃ እየተደገፈ በህግ እንዲታይም የተደረጉ አሉ፡፡ ችግር የፈጠሩ አካላትም በድጋሚ በተመሳሳይ ተግባር ውስጥ ገብተው እንዳይገኙ ወደ ሌላ ተቋም እንዲዛወሩ መደረጉ የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ በተለያየ መንገድ ተጠያቂ ከማድረግ ባሻገር ይህም እየተሰራበትና ለውጥ ያመጣ ተግባር ነው፡፡
በሥራው ላይ በኃላፊነት ላይ ካለው አመራር ባልተናነሳ በዋናነት በተግባር ላይ ያለው ባለሙያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ችግሮች ለማቃለል የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ዕሙን ነው ያሉት ደግሞ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የከተሞች መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥዑመዝጊ በርኼ ናቸው፡፡ በመሆኑም ፈፃሚውን በአቅም መገንባትና ሳይሰራ ሲቀር ተጠያቂነትን ማስፈን ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ በትኩረት እየተሰራበት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ያመጡ ከተሞች ቢኖሩም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ያለው አፈፃፀም ግን የተለያየ በመሆኑ ወደ ተቀራራቢ ደረጃ ለማምጣትም የተሰራም ነው፡፡
ከተማ በየጊዜው የአሰራር ሥርዓቶችን እየዘረጉ አመለካከት እየቀየሩ የሚኬድበት እንጂ ባለበት የሚቆም አይደለም፡፡ እስካሁን ይነሱ የነበሩ ችግሮችን ለማቃለል መንግሥት ተገቢ ናቸው ያላቸውን የመፍትሔ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ይህም በቂ እንዳልሆነ አቶ ጥዑመዝጊ ያምናሉ፡፡ በመሆኑም የህዝቡን እርካታ ማግኘት እስኪቻል አሰራርን መፈተሽ ይገባል፡፡ በተያያዘ የተጠያቂነት ሥርዓቱም ተጠናክሮ መቀጠሉን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በእያንዳንዱ ተግባርም ህዝቡን ማሳተፍ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ መሆኑ ታምኖ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
እንደ አቶ ጥዑመዝጊ ገለፃ፤ አሰራሩ ለህዝቡ ግልፅና በደንብ ግንዛቤ እንዲጨበጥ ሲደረግ መብቱን ጠያቂ ተገልጋይ መፍጠር ይቻላል፡፡ በዚህ መሰረት በአንዳንድ ከተሞች ላይ ተገቢውን አገልግሎት ባለማግኘታቸው ጉዳያቸውን ህግ ድረስ የወሰዱ ተገልጋዮች እንዳሉ ታይቷል፡፡ ይህም በአንድም በሌላም በኩል የሚያሳየው ይህን መሰል ሞጋች ህብረተሰብ መፍጠር በራሱ በዘርፉ መንግሥት ሲያከናውን በቆያቸው ተግባራት ሳቢያ ሊመጣ የቻለ ትሩፋት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡
በአገሪቱ የሚገኙ በርካታ ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ያሉት ደግሞ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የከተማ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሒሩት ቢራሳ ናቸው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በተቀመጠው አሰራር አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻለ ህብረተሰቡ መጠየቅ መጀመሩ ታይቷል፡፡ በመሆኑም ማዘጋጃ ቤታዊ አሰራሮችን ዘመናዊ ለማድረግ ከህገመንግሥቱ ግዴታ አንፃር ዜጎችም ያላቸው መብት መጠቀም የሚችሉባቸው ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ መንግሥት የሚሰራቸውን ሥራዎች ግልፅነት የሰፈነበት አሰራር እንዲሆን በማድረግ የሚሰጡ አገልግሎቶች ለብልሹ አሰራር ያላቸው ተጋላጭነት በመቀነስ ህዝቡ ለወጪና ለእንግልት እንደዳረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡
ባለጉዳዩ አገልግሎት ለማግኘት ማሟላት ያለበትን በግልፅ እንዲያውቅ ከተደረገ አገልጋዩ በተጨማሪ ክፍያ ሳይሆን ግዴታው እንደሆነ አምኖ በተሰማራበት መስክ በአግባቡ እንዲሰራ እንደሚያስችለው ሚኒስትር ዴኤታዋ ያብራራሉ፡፡ ይህም ተገልጋዩ ፍትሃዊ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርገዋል፡፡ ለዚህም ለከተማ ልማት የወጡት ስታንዳርዶች ቅድሚያ የተሰጣቸው የህዝብ ሮሮ የበዛባቸው ዘርፎች ላይ ነው፡፡ በተለይም የስርቆት ትልቁ ምንጭ መሬት፣ የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ እንዲሁም ደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብ ላይ አሳሳቢ ችግሮች በመኖራቸው ለእነዚህ በጥልቅ ትኩረት እንዲሰራባቸው እየተደረገ ይገኛል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፃ፤ ስታንዳርዱን በ142 ከተሞች ላይ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረ ሲሆን፣ በጠንካራ ስነምግባር አስፈፃሚ አካል ወስዶ ህብረተሰቡን በዚህ ልክ ማገልገል ላይ ያለው ችግር ሲታይ ግን በቂ ግንዛቤ እንኳ እንዳልተፈጠረ ይታያል፡፡ በዚህም ህብረተሰቡ አገልግሎቱን ለማግኘት ገንዘብ ሲጠየቅ በአሰራሩ መሰረት መስተናገድ እንደሚገባው ትግል ማድረግ ላይና ይህን ተከትሎም ፈፃሚው ሊታገለው የሚችል ህብረተሰብ እንዳለ ተገንዝቦ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ላይ በጎ ጅምሮች ቢኖሩም ክፍተቶች ግን አላጡትም፡፡
የሚነሱ ችግሮች በጊዜ ሥራዎች ይሰሩበታል ተብሎ በተቀመጠላቸው ስታንዳርድ መሰረት ያለመስተናገድ ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው የቆዩ ችግሮች መሆናቸውን አቶ ጌቱ ይናገራሉ፡፡ ምልልሱ እንዲበረክትና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ይልቅ የህዝብ እንግልት እንዲተካ የሚያደርገው የተቆርቋሪነት ጉድለት እንዲሁም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር እንዳሉ ህዝቡም በተለያዩ መድረኮች ሲያነሳ ይደመጣል፡፡ ችግሮቹ በአንድ ጀምበር የተፈጠሩ እንዳልሆኑ ሁሉ በዚህ ፍጥነት ሊቃለሉም አይችሉም፡፡ የሚጠይቁት የሰው ኃይል እንዲሁም ገንዘብና ሌሎች አስፈላጊ ሥራዎች አቅምን ብሎም አፈፃፀምን የመፈታተን አቅም ያላቸው ናቸው፡፡
አቶ ጌቱ፤ ችግሮቹ ተጨባጭና ትክክለኛ መሆናቸውን አምነው ይህን ለማስተካከል ከህዝቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ይላሉ፡፡ በህዝቡ ተሳትፎም ባለፈው ዓመትና በዘንድሮ በጀት ዓመት በአመራርና በፈፃሚዎች ላይ ከኃላፊነት ከማንሳት ጀምሮ በየደረጃው ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃ ተወስዷል፡፡ ባለፈው ዓመት 14 ዘንድሮ ደግሞ አራት ሠራተኞች አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እየተደረገም ነው፡፡ በዚህም ህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ ሲሆን፣ ከፍተኛ አመራሩም ይህንን ችግር ለማቃለል መስራት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል፡፡
የደረቅ ቆሻሻ ዘርፍ ቀላል ለማይባል የሰው ኃይል የሥራ ዕድል በመፍጠር የመልካም አስተዳደር ችግር የሆነውን ሥራ አጥነት ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት አቶ ተስፋዬ ያስረዳሉ፡፡ ከሥራ ፈጠራው ውጪም ለምርምርና መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ አመቺ ኢኮኖሚ ሊደግፍ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ያክል ፈርጀ ብዙ ጥቅም ያለው ዘርፍ ችግሮች ሲገጥሙት ይስተዋላል፡፡ በተለያየ ምክንያት ከተማውን በሚፈለገው ስታንዳርድ ከሃይላንድና ፌስታል የፀዳ መንገድ ማድረግ አልተቻለም፡፡
በብዙ ሰዎች ዘንድ ያለው አስተሳሰብ በአገሪቱ ያሉ ከተሞችን ቀድሞ በነበሩበት ደረጃ ማሰብ ቢሆንም በተቃራኒው ከተሞች ከሚታሰበው በላይ በስፋት እያደጉ በመሆናቸው ችግሮችም የዚያኑ ልክ ሰፍቷል ይላሉ አቶ ጥዑመዝጊ፡፡ ከተማ ላይ የሚኖረው ህዝብ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው የሚሉት ኃላፊው በግልባጩ ደግሞ መሰረተ ልማት ላይ የመጡ ለውጦች ከህዝቡ ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝነት የጎደለው በመሆኑ የሚሰጠው አገልግሎት ላይ ጉድለቶች እንዲስተዋል ማድረጉን ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ለማስተካከል መንግሥት የቀየሳቸው በርካታ አሰራሮች ቢኖሩም ተገልጋዩ ግን በታቀደው ልክ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑ ይታያል፡፡
ኃላፊው እንደሚሉት፤ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ አገልግሎት ሲሰጥ በስታንዳርዱ መሰረት ተግባሩ በተቀመጠለት ሰዓት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህንንም ለህብረተሰቡ በማሳወቅ የማይሰራ ከሆነ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ላይ የሚነሱትን ችግሮች ማቃለል አይቻልም፡፡ ስታንዳርዶቹም የአገሪቱን የማስፈፀም አቅም ከግንዛቤ የከተቱ በመሆናቸው ለመስራት የሚያስቸግሩ አይደለም፡፡ ነገር ግን በዋናነት መቀየር ያለበት አመለካከት እንደሆነ የሚፈጠሩት ችግሮች ትልቅ ማሳያ ይሆናሉ፡፡
ተገልጋዩ ደመወዝ እንደሚከፍል በማወቅ ለአገልግሎቱ አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ሊስተናገድ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነና የሚቀሩ መሟላት ያለባቸው መረጃዎች ካሉም ይህንን በተገቢው ሁኔታ ማስረዳትና መሸኘት እንደሚኖርባቸው ቢታመንም በሥራ ላይ ያለው ዕውነታ ግን ከዚህ የተለየ እንደሆነም አቶ ጥዑመዝጊ አልሸሸጉም፡፡ በአሁኑ ወቅት ችግሮቹን እያገዘፈ ያለው ‹‹ይሆናል አይሆንም›› የሚል ምላሽ አለመሰጠቱም ነው፡፡ በመሆኑም ይህን መሰል ስህተት ከተፈጠረ በደብዳቤ ጭምር በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ይህንንም በማድረግ ከተቻለ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ላይ ያለውን ዝርክርክ አሰራር ያስተካክለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምን ለውጥ መጣ?
መንግሥት ከህዝቡ ሲነሱ የነበሩ በርካታ ችግሮችን ለማቃለል የለውጥ እርምጃ ናቸው ያላቸውን መፍትሔዎች ወስዷል፡፡ ከዚህ ቀደም ከህዝቡ ሲነሳ የነበረው ዋነኛ ጥያቄ መሬት ከአርሶ አደሩ ቢወሰድም ሳይለማ ለበርካታ ዓመታት ይቆያል፡፡ ይህም በአንድ በኩል አርሶ አደሩ በመሬቱ አርሶ እንዳይጠቀም ከማድረጉም በላይ ለልማት ተብሎ የተወሰደው መሬት ሳይለማ መቀመጡ መንግሥትን ለኪራይ ሰብሳቢነት አጋልጧል የሚል ጥያቄን ያስነሳ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ ትግልም ካሳ ተከፍሎ ያለ አግባብ እስከ 15 ዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ዓረም የወረሳቸው ከ 159 ሔክታር መሬት በላይ ወደ መንግሥት ሊመለስ ችሏል፡፡ ይህንንም በአሁኑ ወቅት እየተሰራ ላለው ልማት እየዋለ ነው፡፡
አርሶ አደሩ በአነስተኛ ካሳ መነሳቱ በህጉ ላይ በተቀመጠ መሰረት ምትክ መሬት መስጠትና ማቋቋም ጎን ለጎን ባለመሰራታቸው አርሶ አደሩና ቤተሰቡ መልሶ ችግር ላይ እንዲወድቅም አድርጎታል፡፡ ይህም ዕድገቱ እርሱን ያላማከለና ያላሳተፈ ከማጉረስ ወደ መጉረስ ያሸጋገረ ነው በሚል ከፍተኛ ችግር ነበር፡፡ ባለፉት ጊዜያትም አንዱ ለግጭት መነሻ ከነበሩ ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሹ ችግር ነው፡፡ በዚህም ከ 4 ሺህ ሰዎች በላይ ከነልጆቻቸው የማቋቋም ሥራ ተሰርቷል፡፡ ይህም ሙሉ ነው በሚባልበት ደረጃ ባይሆንም ጅማሮው ግን የተሻለ ነው፡፡
መጀመሪያ 500 ካሬ አርሶ አደሩና 200 ካሬ ደግሞ ዕድሜያቸው ለአካለ መጠን የደረሰ መኖሪያ የሌላቸው ከህዝቡ ጋር በመሆን ተጣርቶ ልጆችም ቦታ እንዲያገኙ ተሰርቷል፡፡
በመኖሪያ ቤት ደረጃ በሳምንት ሁለት ጊዜ እንዲሁም በትልልቅ ተቋማት በቀን አልያም በሳምንት የተወሰኑ ቀናት እንደ አስፈላጊነቱ አገልግሎቱ ተደራሽ እንደሚሆን አቶ ተስፋዬ ያስረዳሉ፡፡ አሰራሩም ቀድሞ ሰዎች በጀርባ ተሸክመው የሚሄዱበትን ኋላቀር አኗኗር ያስቀረ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከጋሪ እስከ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች እንዲሰማሩ በማድረግ ለውጡን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡ በተያያዘ አሰራሩ የነበረውን የተበታተነ የቆሻሻ አያያዝ በማስተካከልም ረገድ ያመጣው ለውጥ ከፍተኛ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በክፍለ ከተማው 72 የተለያዩ ቦታዎች ላይ የቆሻሻ ገንዳ ተቀምጦ ይሰበሰብ እንደነበር በማስታወስ በአሁኑ ወቅት ወደ ሰባት ቦታዎች ማድረስ መቻሉን እንደ አንድ ማሳያና ከተማዋን ከጊዜ ወደ ጊዜ ፅዱ ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተሰራው ሥራ በዘርፉ ይነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ማቃለሉን ይናገራሉ፡፡
ቀጣይ ተግባራት
የቀጣይ ዋና የትኩረት አቅጣጫ ሥራዎች ለማስፈፀም በተቀመጠላቸው ስታንዳርድ መሰረት መፈፀም መሆኑን አቶ ጌቱ ይገልፃሉ፡፡ ከዜጎች ጋር ስምምነት የተፈጠረበትን የዜጎች ስምምነት ቻርተር ሙሉ አድርጎ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሰራል፡፡ በዚህም አገልግሎቱንና መብቱን በገንዘብ የማይገዛ ጠያቂ ህብረተሰብ በአሁኑ ወቅት በተጀመረው መንገድ ተጠናክሮ መፈጠር አለበት፡፡ ባለሙያውም ከዚህ ጋር እኩል መራመድ የሚችልና አስተሳሰቡና ድርጊቱ የተለወጠ ህዝቡ የራሱ እንደሆነ አስቦ በተሟላ ስብዕና ማገልገል ክብር እንደሆነ አምኖ እንዲቀበል አመለካከት ቀረፃም ላይ ይሰራል፡፡
ባለሙያው ሥራውን ባለመስራቱ የሚወሰደው እርምጃ መቅረቱ ችግሩን እየፈጠረ እንዳለ አቶ ጥዑመዝጊ አልሸሸጉም፡፡ ይህም የሚያመላክተው አሰራሩ መፈተሽ እንዳለበት ነው፡፡ በዚህ ውስጥም በተመደበበት ብቁ ያልሆነና ችግር የፈጠረ አካልም ከሥራ የተነሳበት ምክንያት በአግባቡ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ እንደሆነ ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩን የፈጠረው ባለማወቅና ከግንዛቤ እጥረት ከሆነም ታይቶ ክፍተቱን የሚሞላ ስልጠና ይሰጣል፡፡
ህዝብ በአግባቡ ካልተስተናገደ ቀይ ካርድ ይሰጣል፡፡ እስካሁንም በዚህ ደረጃ እየተሰራ ባይሆንም ጠያቂ ማህበረሰብ ግን እየተፈጠረ መሆኑን አቶ ደሳለኝ ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ቀጣይ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ከልማዳዊ ወደ ዘመናዊ አሰራር በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣን ቀልጣፋ ምላሽ ህብረተሰቡ የሚያገኝበትን አሰራር መፍጠር ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ በማድረግ ዘርፉ የሚታወቅበትን ችግር ለማቃለል ያስችላል ይላሉ፡፡
በቀጣይም ችግሮቹን በዘላቂነት ለማቃለል ቁርጠኛ ሆኖ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች የሚሰጣቸው የሥራ ኃላፊነት እንደ ዕርስት የሚታይ ሳይሆን ከመስራት ጋር ተያይዞ ብቻ የሚቆይ መሆኑን መገንዘብም ይገባል፡፡ አፈፃፀም መሰረት ያደረገ በጀት ላይ ሊሰራም ይገባል፡፡ አገልግሎቱን መስጠት ካልቻለ በጀቱም ሊፈቀድለት እንደማይገባ ትግል መደረግ አለበት፡፡ እነዚህና መሰል ሥራዎችም የህዝቡን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትም ስታንዳርዱን ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ያሳያሉ፡፡ ይህም መረጋገጥ ከቻለ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዜጎች ቢሮ ድረስ መንገላታት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ሆነው በግል ተንቀሳቃሽ ስልካቸው አገልግሎትን ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሆነ አቶ ጥዑመዝጊ ያመላክታሉ፡፡
በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የከተማ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሒሩት ቢራሳ በበኩላቸው እንደሚገልፁት አለአግባብ ሲጉላሉ አልቅሰው ከመመለስ ይልቅ መንግሥት ከሚከፍላቸው ደመወዝ ውጪ በአቋራጭ መክበር የሚፈልጉ አካላትን ሊሸከም የማይችል ህብረተሰብ መፍጠር ይገባል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዋናነት የሚያስፈልገው የባለሙያ አስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ ከአስተዳደግ ጀምሮ ህብረተሰብን ማገልገል በመልካም ጎኖ ወስዶ በንፁህ ህሊና ከመስራት ይልቅ በተለይ መሬት ላይ በሥራ ኃላፊነትና በባለሙያነት የሚመደቡት ከህብረተሰቡ የወጡ አገልጋዮች ያልተገባ ጥቅምን እንዲሹ የሚያደርጋቸው ሰዎች ለስልጣን ያላቸው አተያይ መዛባት እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታዋ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ብልሹ አሰራሮችን ችግር ለማቃለል ህብረተሰቡም ሆነ መንግሥት ይህን መሰል ድርጊት ላይ የተሰማሩ አካላትን አንቅሮ ሊተፋቸው ይገባል ይላሉ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት በብልሹ አሰራር ውስጥ የሚገቡ አካላት መሸሸጊያቸው ራሱ ህብረተሰቡ በመሆኑ ሊታገላቸው ይገባል፡፡ በተመሳሳይ አገልግሎት ፈልጎ ሲሄድም ለእንግልት የሚዳርገውን አካል በተዘረጋው የቅሬታ አቀራረብ ሂደት መብቱን ለማስከበር እስከ መጨረሻው ድረስ ትግል ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ፖለቲካ

የመንግሥት ግዥ ግልጽ፣ ቀልጣፋ ፍትሀዊ ለማድረግ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ተቋቁሟል፡፡ ተቋሙ የመንግሥትን ሀብት በተሻለ ቁጠባና ውጤታማነትን በተከተለ መልኩ ለመጠቀም እንዲቻል የመሥራት ኃላፊነት አለበት፡፡ ከፍተኛ ሀብት የሚፈስበት የመንግሥት ግዥ በጥቅል የሚከናወንበትን አሰራር በመዘርጋት ይንቀሳቀሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የንብረት አወጋገድ ሥርዓቱን ባለው መንገድ ለማቀላጠፍ ይሠራል፡፡
ተቋሙ ከፍተኛ ኃላፊነትን ተረክቦ ቢቋቋምም በአተገባበሩ ላይ በርካታ ችግሮች መኖራቸው እየተነገረ ነው፡፡ በተቋሙ አማካኝነት ግዥ የሚከናወንላቸው እና ንብረት የሚወገድላቸው የመንግሥት ተቋማት በአገልግሎቱና በአቅራቢዎቹ ላይ የተለያዩ ቅሬታዎችን ያቀርባሉ። አገልግሎቱ በበኩሉ በመንግሥት ተቋማትና አቅራቢዎች ላይ ህጸጾች መኖራቸውን ይናገራል፡፡ አቅራቢዎቹ ደግሞ ችግሩ ያለው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በአገልግሎቱ ላይ እንደሆነ ነው የሚጠቁሙት፡፡
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንደሚሉት፤ አቅራቢዎች በገቡት ውል መሰረት ዕቃዎችን በሚፈለገው መጠን፣ ጥራትና ጊዜ አያቀርቡም ይላሉ። የጥራት ደረጃውን ያልጠበቀ፣ አንዳንዴም የማይሠራ ዕቃ በማቅረብ የማጭበርበር ድርጊት ለመፈጸም ይሞከራል፡፡ ይህን ሲያደርጉ የተያዙ ድርጅቶችም አሉ፡፡ የዚህ ዓይነት ከፍተኛ የሥነ ምግባር ችግር የሚታይባቸውን አቅራቢዎች በመቆጣጠርና አካሄዱን በማስተካከል ረገድ አገልግሎቱ ክፍተት አለበት፡፡
ከአቅራቢዎቹ የሚነሳው ቅሬታ ደግሞ ይህን ይመስላል፡፡ የገበያ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ሲጨምር በተገባው ውል መሰረት የዋጋ ማስተካከያ አይደረግም። ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቢኖርም ችግሩ አልተፈታም፡፡ ተቋማት ዕቃዎችን ከተረከቡ በኋላ በውሉ መሰረት ክፍያ ከመፈፀም ይልቅ ደጅ ያስጠናሉ፡፡ የሚቀርቡላቸውን ዕቃዎች ያለመረከብ ችግርም በስፋት አለ፡፡ በዚህም የተነሳ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና አገልግሎቱ ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ግዥ የሚፈጸምላቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በርካታ ችግሮች ይመዛል። ችግሩ ፍላጎትን ከማሳወቅ ይጀምራል ይላል፡፡ መሥሪያ ቤቶች ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ ቶሎ ምላሽ አይሰጡም፡፡ ይህ ችግር ደረጃ ቢለያይ ነው እንጂ በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይታያል። ባሳወቁት ፍላጎት መሰረት ዕቃ ከተገዛላቸው በኋላ አይረከቡም፡፡ እነዚህና መሰል የመሥሪያ ቤቶቹ ችግሮች በአሰራሩ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን በአፅንኦት ይናገራል፡፡
አገልግሎቱ በአቅራቢዎቹ በኩል የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውንም ይጠቁማል፡፡ ሁሉም ባይሆኑም በርካታ አቅራቢዎች በውላቸው መሰረት ያለማቅረብ፣ የሥነ ምግባር ሌሎች ችግሮች አሉ ይላል፡፡ በዚህም የተነሳ አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አቅራቢዎች መኖራቸውን ያስረዳሉ፡፡ እናም ችግሩ በሁለቱም ወገን የሚንፀባረቅ ነው፡፡
ይህን ከአንዱ ወደ ሌላው ለሚወረወረው ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት አገልግሎቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡ የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋምን ወክለው የመጡ ባለሙያ በተቋማቸው ስቴፕለር፣ የደንብ ልብስ፣ የጽዳት ዕቃና ሌሎች በርካታ ዕቃዎች አለመቅረባቸውን ተናግ ረዋል፡፡ እነዚህን ጥቃቅን እቃዎች ጨምሮ ሌሎች ለሥራ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች በወቅቱ ካልቀረቡ ተገቢውን አገልግሎት ለህዝብ ለመስጠት ያስቸግራል ይላሉ። ግብዓቶቹ አለመሟላታቸው ለመል ካም አስተዳደር ችግር መንስዔ እንደሆኑባቸው ነው የተናገሩት፡፡
የግዥ ሥርዓቱን ለማስተካከል የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶ መቅረብ አለበት። ይህ ካልሆነ ለህዝብ በሚሰጡ አገልግሎት ላይ የበጀት አጠቃቀም ችግር ይፈጥራል። አንዳንድ ዕቃዎች ላይ የአገልግሎቱ ውል ተሻሽሎ ዋጋ ካልተስተካከለ ዕቃ የማያቀርቡ ድርጅቶች መኖራቸውን አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡
የወሎ ዩኒቨርሲቲን የወከሉት ባለሙያ በበኩላቸው የሚቀርቡት እቃዎች የጥራት ችግር እንዳለባቸው ነው ያስረዱት። ዕቃዎቹ በሚፈለገው ጊዜ አይቀርቡም፡፡ ይህም የዩኒቨርሲቲዎቹን እንቅስቃሴ አስቸጋሪ አድርጎታል። ችግሩ እንዲስተካከል ቢጠየቅም መፍትሔ አልተገኘም፡፡ የመኪና መለዋወጫዎች በማዕቀፍ ግዥ ገብቶ እንዲከናወን ዩኒቨርሲቲው ቢጠይቅም አልተካተተም፡፡ የሚወገዱ ዕቃዎች ግምትና ገዥዎች የሚያቀርቡት ዋጋ ባለመጣጣም ሳይወገዱ የቀሩ ዕቃዎች በርካታ ናቸው፡፡ ይህን ለማሳለጥ ወጥ የሆነ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ነው የተመለከተው፡፡
የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ተወካይም፤ በአቅራቢዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት አነስተኛ መሆን አቅራቢዎቹ በወቅቱ እንዳያቀርቡ ክፍተት ፈጥሯል ይላሉ፡፡ አሰራሩ የተቀላጠፈ አለመሆኑ በመንግሥት ከፍተኛ ኪሳራና የሥራ መስተጓጎል እያደረሰ ነው፡፡ በመሆኑም በአቅራቢዎች ላይ የሚጣለው የተጠያቂነት ደረጃ ከፍተኛ መሆን አለበት። የመንግሥት ተቋማት ፍላጎታቸውን ለይተው በወቅቱ በመስጠት፤ ዕቃውን በውሉ መሰረት መግዛቱን አረጋግጦ በመረከብ፤ ለአቅራቢዎቹ ቶሎ ክፍያ በመፈፀም ረገድ ክፍተት እንዳለ ተወካዩ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ኬሚካሎችና መሰል ንብረቶችን የሚያስወግድ ተቋም ባለመኖሩ ባለቤት ሊበጅለት ይገባል ብለዋል።
ከቶነር አሰምብሊ የመጡት አቶ ሰለሞን አለሙ፤ አንዳንድ ጊዜ ቶሎ ያለማቅረብ ክፍተት መኖሩን ይናገራሉ፡፡ የመዘግየቱ ዋናው ምክንያት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ የአገሪቱ የሎጀስቲክስ ሥርዓት በጣም ኋላ ቀር መሆን የአቅርቦት መዘግየት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዘለቄታዊ መፍትሄ ካላገኘ ችግሩ ይቀጥላል። ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የገበያ ጥናት በማይደረግባቸው ዕቃዎች ላይ የዋጋ ማስተካከያ አለማድረጉ ሌላው ችግር ነው፡፡ ዋጋ ሲጨምር ማስተካከያ ስለማይደረግ በአቅራቢዎቹ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ስለሚያደርስ የማይቀርቡ ዕቃዎች መኖራቸውን አቶ ሰለሞን ይጠቁማሉ፡፡ መንግሥት ይህን ማስተካከያ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት፡፡
አገልግሎቱ በገባው የጥራት ውል መሰረት የቀረበን ዕቃ የማይረከቡ አንዳንድ ተቋማት መኖራቸውን አቶ ሰለሞን ይገልፃሉ፡፡ ለመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተገባው ውል መሰረት ዕቃ ሲያቀርቡ ዩኒቨርሲቲው ሊረከባቸው እንዳልቻለ በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡ ችግሩን ለአገልግሎቱ ቢያሳውቁም መፍትሄ ሊሰጣቸው አልቻለም፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታት የመንግሥት ኃላፊነት በመሆኑም በተዘረጋው አሰራር የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረት የአቅራቢዎች ራስ ምታት መሆኑ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው፡፡ የሃይ ላይት ድርጅት ተወካይ አቶ ቢኒያም መንበሩ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንቅፋት እንደሆነባቸው ነው የሚናገሩት፡፡ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ረጅም ጊዜ ፈጅቶ ምላሽ ስለሚያገኝ ዕቃውን በተባለው ጊዜ ለመንግሥት ተቋማት ለማቅረብ አላስቻላቸውም። የዋጋ ማስተካከያ የተደረገባቸው ዕቃዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ አሁንም ዋጋቸው ያልተስተካከሉ ዕቃዎችን ለማቅረብ መቸገራቸውን ነው ያስረዱት፡፡ አንዳንድ ጊዜ አገልግሎቱ ማስተካከያ አድርጎ ተቋማት ማስተካከያ የማያደርጉበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቁመው፤ ለእነዚህም መንግሥት ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ይላሉ፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ፤ ተቋሙ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚያስፈ ልጋቸውን ሁሉንም ግዥዎች አይፈጽምም። የመኪና መቀያየሪያና ሌሎች ግዥዎች ተቋማት እራሳቸው ያከናውናሉ፡፡ ‹‹የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚጠቀሙባቸውን ሁሉንም ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ የመግዛት ደረጃ ላይ አልደረስንም። የተመረጡትን እንገዛላቸዋለን፤ ሌሎችን ተቋማቱ ራሳቸው ይገዛሉ፡፡ በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብዙ ሥራ ስለሚያከናውኑ በእራሳቸው በርካታ ግዥዎችን ያከናውናሉ። አገልግሎቱ የሚገዛላቸው ፓኬጆችን (ጥቅል ግዥዎችን) ነው›› ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ የግዥ ህጉ ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍል አይፈቅድም። አቅራቢዎች ከዋጋ ግሽበት በፊትም ሆነ በኋላ በዋጋው ላይ ልዩነት የለውም። የዋጋ ለውጥ የሚኖረው ማዕከላዊ ስታትስቲክስ በየሶስት ወሩ በሚያወጣው የዋጋ መረጃ ላይ ተመስርቶ ብቻ ማስተካከያ ሲደረግ ነው። መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ከፍና ዝቅ ባደረገ ቁጥር ዋጋ አይጨምርም። በመንግሥት በኩል የውጭ ምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ አቅራቢዎቹ ዋጋ ላለመለወጥ ተስማምተዋል። ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በሰጠን የዋጋ መረጃ መሰረት በበርካታዎቹ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያት በአንዳንድ ዕቃዎች ላይ የማስተካከያ ዋጋ ሳይደረግ በመቆየቱ የአቅርቦት ችግር እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
የተወሰኑ አቅራቢዎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደማይወጡ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በእነዚህ ላይ የውል ማስከበሪያቸው እንዲወረስና እንዳያቀርቡ መደረጉንና ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውም መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በኋላም በውሉ መሰረት የማይሄዱ አቅራቢዎች ላይ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለፁት። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከንብረት አወጋገድ፣ በወቅቱ ፍላጎታቸውን ካለማሳወቅ፣ በተገባው ውል መሰረት ካለመረከብ እና በወቅቱ ለወሰዱት ዕቃ ክፍያ ካለመፈፀም ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉባቸው አቶ ይገዙ ተናግረዋል፡፡ ችግሩ እንዲፈታ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አሳውቀዋል፡፡ በዚህም የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተከናውኗል፡፡
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የአገልግሎት አቅራቢ ተቋማትና የግዥ ሂደቱን የሚመራው አገልግሎቱ ክፍተቶች አሉባቸው፡፡ አንደኛው በሌላኛው ላይ ጣቱን ቢጠቁምም ድርሻው ይለያይ ይሆን እንጂ ሁሉም ክፍተት አለባቸው፡፡ በዚህ ሂደት ደግሞ ሥራዎች እየተጓተቱ የመንግሥት ሀብት ለብክነት ይዳረጋል፡፡ ይህን ለማሳለጥ የተዘረጋው ሥርዓትም ውጤታማ መሆን ያቅተዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም የቤት ሥራውን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል፡፡

አጎናፍር ገዛኽኝ

Published in ኢኮኖሚ

ባለፈው እሁድ ምሽት በደስታ የሰከረችው ሜክሲኮ ሰኞን አልደገመችውም፡፡ በሜክሲኮ ሰማይ ስር በአንድ ቀን ልዩነት ሁለት የተደበላለቁ የተቃርኖ ስሜቶች ተስተውለዋል፡፡ እሁድ የአዲሱን ፕሬዚዳንት ማሸነፍ ተከትሎ ደስታቸውን የገለፁት ሜክሲኮያውያን የሰኞው የዓለም ዋንጫ ሽንፈት ደስታቸውን አደብዝዞታል፡፡ ዜጎቿ መሪያቸውን በመምረጥ በደስታ የመፈንጠዛቸው ስሜት ሳይበርድ የሩስያው መርዶ ፈገግታቸውን አደብዝዞታል፡፡ ሜክሲኮን በዓለም ዋንጫ ድል ለማቀዳጀት ወደ ሩስያ ያመራው ብሔራዊ ቡድናቸው ከትናንት በስትያ በብራዚል ተሸንፎ ከውድድር ውጭ ሆኗል፡፡

የሜክሲኮ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ሚስተር አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ ኦብራዶ ታዲያ ሜክሲኮ በዓለም ዋንጫ ውድድር ያጣችውን ድል በኢኮኖሚው ለማካካስ ቆርጠው የተነሱ ይመስላል፡፡ በምርጫው 53 በመቶ ድምፅ በማግኘት ያሸነፉት የ64 ዓመቱ የግራ ዘመም ፓርቲ ተወካይ የአገራቸውን ኢኮኖሚ ማሳደግን ዋናው ተግባራቸው አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ መናገራቸውን ሲ ኤን ኤን አስነብቧል፡፡ በዚህም ‹‹የሜክሲኮን ኢኮኖሚያዊ አቅም በማፈርጠም ከሌሎች አገራት ጥገኝነት አላቅቃታለሁ›› ሲሉ ተደምጧል፡፡ በሜክሲኮ የምርጫ ታሪክ 88 ሚሊዮን ህዝብ በመራጭነት በተሳተፈበት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለአሸናፊነት የበቁት ሚስተር ሎፔዝ አብራዶ በብዙዎች ዘንድ ለአሸናፊነት የተሰጠውን ግምት ያሳካ ሂደት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
የተመራጩ ፕሬዚዳንት ደጋፊዎች በሜክሲኮ ዞካሎ አደባባይ በመገኘት ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ ወደ መንበረ ሥልጣኑ የመጡት ተመራጩ ፕሬዚዳንት ‹‹የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተግዳሮት የሆነውን ሙስናን ማጥፋት ሌላው ትልቅ ትኩረት የሰጡት ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ሀብታምና ደሃ ሳይባል ፤ሁሉም ሜክሲኮያውያን ድምፃቸው እንዲሰማ እናደርጋለን›› በማለትም ለሁሉም መብት መከበርና መረጋገጥ እንደሚሰሩ መናገራቸውን የዘገበው ደግሞ ኒውዮርክ ታይምስ ነው፡፡ በዚህም ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸውና በሚከተሉት ሃይማኖት ልዩነት ሳይፈጠርባቸው በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ዕውን ይሆናል ብለዋል፡፡
ከምርጫ ቅስቀሳው ጊዜ ጀምሮ ድህነትን በማጥፋት የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ እንደሚሰሩ ሲናገሩ የነበሩት ሚስተር ሎፔዝ ኦብራዶ አሁን ያሉትን በተግባር የሚያሳዩበት ጊዜ ላይ ደርሰዋል፡፡ በአገሪቱ ለሚስተዋለው ግጭት መንስዔ የሆነውን ሙስናና ድህነትን ለመዋጋት ብርቱ ጥረት እንደሚያርጉም ነው የተናገሩት፡፡ በሙስና ላይ ጥናት በሚያደርገው ዓለም ዓቀፉ ትራንስፓረንሲ ተቋም ሪፖርት መሰረት ሙስና ከሚፈፀምባቸው 180 አገራት መካከል ሜክሲኮ በ135 ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እናም ይህን አሳፋሪ ታሪክ ለመቀየር ቆርጠው መነሳታቸውን ነው ተመራጩ ፕሬዚዳንቱ የገለፁት፡፡
አዳዲስ የሙስና ስልቶች ከሚቀመሩባቸው የዓለም አገራት ሜክሲኮ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርቷ እስከ አስር በመቶ የሚሆነውን ሀብት በሙስና እንደምታጣ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከሙስናው በተጨማሪ አደንዛዥ ዕፅ የሜክሲኮ ትልቁ ራስ ምታት ነው፡፡ የአደንዛዥ እፅ ዝውውር ከሚካሄድባቸውና ሰፊ መረብ ከተዘረጋባቸው አገራት ሜክሲኮ ዋነኛዋ ነች፡፡ ይህም ዜጎቿ ለተለያዩ ወንጀሎች እንዲጋለጡ እያደረገ ነው፡፡ በአሜሪካ በአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች በዜጎች ላይ ይፈፀማል ከሚባለው ከ50 በመቶ በላይ ወንጀል በሜክሲኮ ይፈፀማል፡፡ በዚህም ቀመር መሰረት ከአስር ሺ ሜክሲኮያውያን በአንዱ ላይ የወንጀል ጥቃት ይፈፀማል፡፡
በርካታ ወንጀሎች በሚፈፀሙባት ሜክሲኮ ዜጎቿ የስጋት ኑሮን ለመግፋት የተገደዱበት አጋጣሚ መኖሩን የዘርፉ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ይህን መሰናክል ለማስወገድ በመንግስት በኩል የተወሰደው እርምጃ ምንም መፍትሔ አለማምጣቱም ነው የሚነገረው፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የፕሬዚዳንት ኤንሪክ ፔና ኒቶ አስተዳደር በዚህ በኩል ለውጥ ባለማምጣቱ ክፉኛ ይተቻል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ችግሩን ለመከላከልና ለማስቆም የአሜሪካንን ድጋፍ ከመጠየቅ በተጨማሪ በርካታ ፖሊሶችን አሰማርታለች፡፡ ውጤቱ ግን የታሰበውን ለውጥ አላመጣም፡፡ እንዲያውም ፖሊሶቹ ከወንጀለኞቹ ጋር በገንዘብ በመደራደር ቁጥጥሩን አላልተውታል የሚሉ ድምፆች ጎልተው ይደመጣሉ፡፡ ይህም የወንጀል ድርጊቱ ከመቀነስ ይልቅ ወደ መጨመር፤ወንጀለኞቹም ከመፍራት ይልቅ ወደ መደፋፈር ገብተዋል እየተባለ ነው፡፡
በሜክሲኮ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንጀሎች ቢፈፀሙባትም በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ የሚቀርቡት ግን በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ መረጃዎች እንደሚመለክቱት ከሃያ ሺ ወንጀሎች ወደ ህግ የሚቀርበው አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህም የችግሩ ስፋት ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል፡፡ ወንጀለኞቹ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር በተደራጁት ወንጀለኞችና ግብረ አበሮቻቸው በቀላሉ ይከሽፋል፡፡ አሁን በተጠናቀቀው ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ ከነበሩ ዕጩዎችም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ላይ ከፍተኛ እርምጃ እንደሚወስዱ በመናገራቸው ብቻ ሰባት ዕጩዎች ተገድለዋል፡፡ ከንቲባዎችና በተለያዩ የመንግስት ኃላፊነት ላይ የነበሩ ኃላፊዎች የወንጀለኞቹ ሰለባ ሆነዋል፡፡
እነዚህና መሰል በርካታ ችግሮች የተበተቧትን ሜክሲኮን ነው እንግዲህ አዲሱ ፕሬዚዳንት እአአ በመጭው ታህሳስ አንድ ቀን 2018 ቃለ መሃለ በመፈፀም የሚረከቡት፡፡ ፕሬዚዳንቱ ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ተግዳሮቶቹም በርካታና ውስብስብ ናቸው፡፡ እአአ በ2015 በሜክሲኮ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ኢርሊ ዋይኔ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሜክሲኮ ድክመት ሆኖ የቆየውን ሙስናን በመዋጋት በኩል ተመራጩ ፕሬዚዳንት ቁርጠኛ አቋም ቢኖራቸውም ፈተናው ከባድ ነው፡፡ ሚስተር ሎፔዝ ኦብራዶ የሜክሲኮን ችግር ለመፍታት የሚያደርጉት ትግል በብዙ ጋሬጣዎች የተከበበ በመሆኑ ጥረቱን ለማሳካት ይከብዳቸዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን የገቡትን ቃል ለመፈፀም የሚያደርጉት ጥረት አጋዥ ካገኘ ሊሳካ ይችላል፡፡
በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑትና በሜክሲኮ ታሪክ ዙሪያ ጥናት ያካሄዱት ፕሮፌሰር ፓብሎ ፒካቶ፤ ሚስተር ሎፔዝ ኦብራዶ ለለውጥ ቁርጠኛ አቋም ቢኖራቸውም ዕቅዳቸው በጥንቃቄ የተቃኘ አይደለም ብለዋል፡፡ በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና ለመቆጣጠርና ቢሮክራሲውን ለመሰባበር ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ጠቁመዋል፡፡ በአገሪቱ ለውጥ ለማምጣት የሰነቁትን ራዕይ ዕውን ለማድረግ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሟቸው ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ሚስተር ሎፔዝ የሜክሲኮ መንግሥት የሰሜን አሜሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ለመከለስ የያዘውን ዕቅድ እንደሚያከብሩ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ አሜሪካም በ1994 የተደረሰው የንግድ ስምምነት እንዲሻሻል ፍላጎት አላት፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር በግንብ ለማጠር ማንፀባረቃቸው ከሜክሲኮ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያሻክር በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ የ64 ዓመቱ ሚስተር ሎፔዝ ኦብራዶ ታዲያ ከአሜሪካ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተመራጩ ፕሬዚዳንት በቲዊተር ገፃቸው ላይ የ‹‹እንኳን ደስ አልዎት››መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር አብሮ ለመስራት ጠንካራ ፍላጎት እንዳላትም ነው የገለፁት፡፡
ሜክሲኮያውያን አዲሱ መሪያቸው በምርጫ ቅስቀሳና ድህር ምርጫ ንግግራቸው የገቡትን ቃል በተግባር እንደሚያሳዩ ተስፋ አድርገዋል፡፡ በተለይም ሙስናን የመከላከልና የመግታት ዘመቻው ጠንካራ ሥርዓት ተበጅቶለት ሊወገድ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ በሙስና ምህዋር የምትናጠውን ሜክሲኮን ከሙሰኞችና ከሀብት ብክነት መታደግ ይቻላል ብለዋል፡፡ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን የመታገሉ እርምጃውም መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ግጭትን የሚያስነሱ ተግባራት እንዲቆሙም አዲሱ ፕሬዚዳንት በትኩረት እንዲንቀሳቀሱ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ የሜክሲኮ ዜጎች ተናግረዋል፡፡
የሜክሲኮ ዜጎች ከዓለም ዋንጫ ውድድር በመሰናበታቸው የተጫናቸው የኃዘን ድባብ በሚስተር ሎፔዝ ኦብራዶ የለውጥ ጉዞ ከላያቸው ላይ እንደሚገፈፍ ተስፋ አድርገዋል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና የአገሪቱን ዕድገት የሚያፋጥኑ ተግባራትን ያከናውናሉ ብለው እየጠበቁ ነው፡፡ ሚስተር ሎፔዝ ደግሞ በበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተተበተበችውን ሜክሲኮን ከስድስት ወራት በኋላ በመረከብ የፕሬዚዳንትነት ጉዞውን ለመጀመር ተዘጋጅተዋል፡፡ ጉዞው ታዲያ በጣም ከባድና ፈታኝ እንደሚሆን ብዙዎች እየተናገሩ ነው፡፡

ዳንኤል ንጉሤ

 

Published in ዓለም አቀፍ

«ጨለማ ክፍል ውስጥ ለብቻዬ አሰሩኝ፡፡ ይህም ሳይበቃቸው ክብሬን በሚነካ መልኩ አሰቃዩኝ፣ ደበደቡኝ፡፡ በደረሰብኝ ድብደባና ስቃይ ለማይድን ከባድ የአካል ጉዳት ተዳርጌአለሁ…» ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከተሰሙ የታራሚዎች የሰቆቃ ድምፆች አንዱ ነው፡፡ ይህን መሰሉን ዘግናኝ ድርጊት መስማት በእውነት ያማል፡፡ በዜጎች ላይ የሚፈፀም ስቃይና እንግልት ያናድዳል፣ ያሳዝናል፡፡ ለፅሁፌ መግቢያ ከተጠቀምኩት አስተያየት ውጪ በርካታ የማረሚያ ቤት በደሎች በተለያዩ የህዝብና የግል መገናኛ ብዙኃን ተሰራጭተዋል፡፡
ከአንዳንዶቹ ታራሚዎች የተሰማው ዘግናኝ ድርጊት በኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተፈጸመው? የሚል ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም፡፡ በታራሚዎቹ አንደበትና አካላዊ ማስረጃ የሚቀርበው ዘግናኝ ድርጊት ማረሚያ ቤቶቹ ወደ ህገ ወጥ ድርጊት መፈጸሚያ ማዕከላት የተቀየሩ አስመስሏቸዋል፡፡ ሁሉም ህጎች ታራሚዎች ሰብዓዊ መብታቸው መከበርና መጠበቅ እንዳለበት ይደነግጋሉ፡፡ ማንኛውም ዓይነት በደልና ስቃይ ሊፈጸምባቸው እንደማይገባም ያስገነዝባሉ፡፡ ከዚህ ውጪ የተንቀሳቀሰ አካልም በፈፀመው ድርጊት በህግ እንደሚጠየቅ አበክረው ያስጠነቅቃሉ፡፡
እ.አ.አ በ1991 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጡት መሰረታዊ የታራሚዎች አያያዝ መመሪያና ደንብ ታራሚዎች ተገቢው ክብር እንዲሰጣቸውና ሰብዓዊ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ በታራሚዎች ላይ የቁም ስቅልና ሌሎች የጭካኔና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን መፈጸም ክልክል መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ታራሚዎችን የሚያዋርዱ አያያዞችና ቅጣቶችን መፈፀምም ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ደንግገዋል፡፡ እነዚህ በክልከላ የተቀመጡ ድርጊቶች በታራሚዎች ላይ እንዳይፈፀሙ በሚመለ ከታቸው አካላት ተገቢው ከለላና ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህንና ሌሎች በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የተዘጋጁ ዓለም አቀፍ ሰነዶችን ተቀብላ አፅድቃለች፡፡ ህጎቹ፤ደንቦቹና መመሪያዎቹ ቢኖሩም ታዲያ በተግባር የሚታየው በተቃራኒው ሆኗል፡፡ ታራሚዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተገፏል፡፡ ክብራቸውን የሚነካ ድርጊት ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ሰሞኑን በዝዋይ ተሃድሶ ማዕከልና በቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ቅኝት በማድረግ ከቀረቡት ዘገባዎች ለመረዳት እንደተቻለው ታራሚዎች ጥፍራቸው ተነቅሏል፤ ከፍተኛ ድብደባና ስቃይ ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም ለከባድ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በተደጋጋሚ በተፈፀመባቸው ድብደባ ለማይድን የአካል ጉዳት የተዳረጉም አሉ፡፡ ይህን መሰሉ በደል በዜጋ ላይ ተፈፅሞ ማየትና መስማት እውነት በጣም ያማል፣ያሳዝናል፡፡
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀፅ 21 በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ቅኝት ባደረጉባቸው ማረሚያ ቤቶች የታየው እውነታ ከህገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ነው፡፡ በታራሚዎቹ ህገ መንግሥታዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞባቸው ለስቃይና ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ህገ መንግሥታዊ መብታቸው በማረሚያ ቤቶቹ አስተዳደሮች ሊከበርላቸው አልቻለም፡፡ በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ወደ ማረሚያ ቤት ከመሄዳቸው በፊትም የማያውቁት ቦታ እየተወሰዱ ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ እንደደረሰባቸው ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ ይህ እንግዲህ ድርጊቱ ምን ያህል ከህጉ የተጣረሰ መሆኑን በግልፅ ያሳያል፡፡ በህግ ቁጥጥር ስር ያለን ዜጋ የፍትህ አካል የሆነ ግለሰብ በፈለገው ጊዜና ቦታ ህገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽምበት ከሆነ ፍትህ አስከባሪነቱ ምኑ ላይ ነው?
አንድ ታራሚ በፍርድ ቤት የተላለፈበትን ውሳኔ አጠናቆ እስኪወጣ ድረስ ሰብዓዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮላቸው ተምረው፣ በፈጸሙት ህገ ወጥ ድርጊት ተፀፅተው፣ የባህርይ ለውጥ አምጥተው፣ የበደሉትን ህዝብ ለመካስ ዝግጁ የሚሆኑበት ስፍራ እንጂ የስቃይ ቦታ ሊሆኑ እንደማይገባ የአገሪቱና ሌሎች ዓለም አቀፍ ህጎችም ደንግገዋል፡፡ ይፈፀማሉ የሚባሉት ህገ ወጥ ድርጊቶች ታዲያ ማረሚያ ቤቶቹ ከተልዕኮአቸው በተቃራኒ ተሰልፈው የመታረሚያ ሳይሆን የመሰቃያ ማዕከላት አስመስሏቸዋል፡፡
ማረሚያ ቤቶች ለታራሚዎች ምቹ አለመሆን ሌላው በታራሚዎቹ የሚንጸባረቅ ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ብዙ ሰው እንዲታሰር መደረጉ ቆይታቸውን በተፋፈገና በተጨናነቀ መልኩ ለማሳለፍ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህን መሰሉ አያያዝ ታራሚዎች በተጨናነቀ መልኩ ከማሳለፍ ባለፈ ለተለያዩ ተባዮች መፈልፈል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ታራሚውን ለተጨማሪ ችግር በመዳረግ በተባይ የሚተላለፉ በሽታዎችን እንዲቀባበል አድርጎታል፡፡ በዚህም የተነሳ የጤና መቃወስ ያጋጥመዋል፤ ጉንፋንን ለመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ እንዲጠቃ ያደርጉታል፡፡ መፀዳጃ ቤቶች በሚፈለገው መጠንና ጥራት አለመኖራቸው ታራሚዎች በተፈጥሮ እንዲቀጡ ያደርጋል የሚል የብሶት ድምፅ በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ በማንነት የማዋረድና የማሸማቀቅ እርምጃም ሌላው ቁም ስቅል መሆኑ ነው የሚገለፀው፡፡
ጨለማና ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ በማስተኛት ታራሚዎችን የማሰቃየትና የማንገላታት ህገ ወጥ ድርጊት ይፈጸማል፡፡ በዚህም የተነሳ ማረሚያ ቤቶች ቁም ስቅል የሚፈጸምባቸው የስቃይ ቤቶች ናቸው ሲሉ ታራሚዎች ይገልፃሉ፡፡ ታራሚው የማረሚያ ቤቱን ቆይታ አጠናቆ ሲወጣ ሠርቶ መለወጥን ሳይሆን አካሉ ሳይጎድል የሚወጣበትን አጋጣሚ ነው የሚያስበው፡፡ «ስወጣ ይህን እሠራለሁ» ሳይሆን «አካሌ ሳይጎድል እወጣ ይሆን?» የሚለው እንደሚያስጨንቀው ተናግረዋል፡፡
በታራሚው ላይ ድብደባና ስቃይ በማካሄድ በውሸት በራሱ ላይ እንዲመሰክር ማድረግም ሌላው በማረሚያ ቤቶች የሚፈፀም ህገ ወጥ ድርጊት ነው፡፡ ይህ በህጉ በጣም የተከለከለ ቢሆንም የማረሚያ ቤቶቹ ኃላፊዎችና አባላት እንደልባቸው ይተገብሩታል፡፡ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት «የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት የለውም» ቢልም ድንጋጌው በተግባር ተሽሮ በአንዳንድ ታራሚዎች ላይ ተፈፅሟል፡፡
ታራሚዎች ከቤተሰባቸው፤ ከሐኪሞቻቸው፣ ከሃይማኖት አባታቸውና ከጠበቃቸው ጋር የመገናኘት ህገ መንግሥታዊ መብት አላቸው፡፡ ይህም ቢሆን ታዲያ በማረሚያ ቤቶቹ ከወረቀት ወደ መሬት መውረድ አልቻለም፡፡ ታራሚዎች እንኳን ቤተሰባቸውን ሊያገኙ፤ ያሉበትንም ቦታ ለማሳወቅ ትልቅ ችግር ሆኖባቸዋል፡፡ በህጉ ከተፈቀደላቸው አካል ጋር የመገናኘት ዕድሉ በማረሚያ ቤቶቹ ኃላፊዎች መልካም ፈቃድ ላይ የወደቀ ነው፡፡ በማረሚያ ቤቶች ከህግ በላይ የሚፈራውና ሥልጣን ያለው የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ነው፡፡ ይህ አሰራር ባለበት ቦታ ህግን መጥቀስ ዋጋ የለውም፡፡
የታመሙ ታራሚዎች ተገቢውን ህክምና ማግኘት መብታቸው ቢሆንም ይህን ዕድል ማግኘት ከባድ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በከባድ ህመም የሚሰቃይ ታራሚ ህክምና ሳያገኝ በአስቸጋሪው የማረሚያ ቤት ቆይታ መራራ ስቃይን ለማሳለፍ የሚገደድበት እውነታም ተንፀባርቋል፡፡ ታክመው መዳን እየቻሉ በህክምና እጦት ለአካል ጉዳትና ዘላቂ ህመም የተዳረጉ አሉ፡፡ እነዚህ በህግ ከለላ ስር ያሉ ዜጎች መብታቸው ተገፎ ለስቃይና ጉዳት መዳረጋቸው የችግሩን አስከፊነት ከማሳየቱም ባሻገር ጥቁር ጥላን ጥሎ ያልፋል፡፡
ታራሚዎች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የሚደርስባቸውን በደል ቢያሳውቁም መፍትሔ አያገኙም፡፡ አንዳንዴ ማረሚያ ቤቱ ያሉበትን ክፍተቶች እንዲያስተካክል ከመንገር ያለፈ ውሳኔ አያሳልፉም፡፡ ማረሚያ ቤቶች በበኩላቸው ድርጊቱ ከእውነታ የራቀ መሆኑን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ሰሞኑን የተስተዋለውም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የአንዱ ማረሚያ ቤት ኃላፊ በታራሚዎቹ የሚነሳው ቅሬታ ውሸት መሆኑን ለማስተባበል ሞክረዋል፡፡ ታራሚዎቹ የደረሰባቸውን አካላዊ ጉዳት እያሳዩ ድርጊቱን መካድ ግን ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም የታራሚዎቹን አስተያየት እውነታነት አረጋግጧል፡፡ በታራሚዎቹ የቀረበው ቅሬታ ለኮሚሽኑ አዲስ አለመሆኑን በማረጋገጥ ይህንንም ለባለፉት ሁለት ዓመታት ሲሠራ መቆየቱን አስታውቋል፡፡ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመንግሥት ነው የሚፈፀም፡፡ ኮሚሽኑ መንስዔውንና ችግሩን የሚያባብሱ ጉዳዮችን ለሚመለከታቸው አካላት በወቅቱ ቢያሳውቅም ምላሽ አላገኘም፡፡ በ2010 ዓ.ም ለምክር ቤቶች፣ ለማረሚያ ቤቶችና ለክልል መንግሥታት ቢያሳውቅም ምላሽ አላገኘም፡፡ የክልል መንግሥታትም ዝምታን በመምረጥ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥበዋል፡፡
«ተጠያቂነት እንዲሰፍን ቢሰራም በችግሩ ውስጥ እጃቸው ያሉ አካላት አልተጠየቁም፡፡ ኢ-ሰብዓዊነት እንዲጠፋ እየሠራን ነው፡፡ ጥቃት እያደረሱ ያሉ ግለሰቦች በህግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ህገ መንግሥቱ ኢ-ሰብዓዊ አያያዝን ይከለክላል፡፡ አመራሮች መጠየቅ አለባቸው» ያለው ኮሚሽኑ፣ የህግ የበላይነት ያልተከበረበትና ተጠያቂነት የሌለበት ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ እንደማይሆን አስገንዝቧል፡፡
ታራሚዎች ችግር እንዳለ፣ ህገ መንግሥታዊ መብታቸው እየተጣሰ፣ በደልና ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን እየጮሁ የሚመለከተው አካል ዝምታን መምረጡ ለምን ይሆን? የታራሚዎቹን አያያዝ በመፈተሽና በመገምገም ህፀፆቹን ነቅሶ ያወጣው የኮሚሽኑ ሪፖርትስ ለምን ምላሽ ተነፈገው? የህዝብ እንደራሴ የሆነው ምክር ቤት ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ አለማድረጉስ ለምን? ያስብላል፡፡ የክልል መንግሥታት ዝምታም ምነው? ማስባሉ አይቀርም፡፡
ለእነዚህ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ይህን አለማድረግ ዜጎች ማረሚያ ቤትን ሲያስቡ የስቃይና የመከራ ቦታ አድርገው እንዲስሉ ያደርጋል፡፡ ማረሚያ ቤት የገባ ሰው በሙሉ ጤንነት ፍርዱን ጨርሶ ይወጣል የሚለው እሳቤ እንዲሸረሸር ያደርጋል፡፡ የአገሪቱ ማረሚያ ቤቶች በበርካታ ችግሮች የተተበተቡ፣ የዜጎች ህገ መንግሥታዊ መብቶች በግለሰቦች የሚጣስበት፣ የስቃይና የመከራ ማዕከላት ተደርገው ይሳላሉ፡፡ ህብረተሰቡ ለማረሚያ ቤቶች ያለው አመለካከት በጣሙን እንዲወርድ ያደርጋል፡፡
በህግ ቁጥጥር ስር ያሉ ታራሚዎችን ህገ መንግሥታዊ መብት መግፈፍ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ ይህን መሰሉን ህገ ወጥ ድርጊት የፈፀሙ አካላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ማረሚያ ቤቶቹን ለታራሚዎች ምቹ የማድረግ ሥራውም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ የማረሚያ ቤቶችን አሰራርና የታራሚዎችን አያያዝ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ማረሚያ ቤቶች ዜጎች ታርመውና ተምረው፣ በፈፀሙት ህገ ወጥ ድርጊት ተፀፅተውና የባህርይ ለውጥ አምጥተው የሚወጡበት ተቋም እንጂ የስቃይና የሰቆቃ ቦታ ሊሆኑ አይገባም፡፡

ሠላም ዘአማን

Published in አጀንዳ
Wednesday, 04 July 2018 19:45

ድጋፍን በውጤታማ ተግባር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ላስመዘገቡት አመርቂ ውጤት ዕውቅና ለመስጠትና ምስጋና ለማቅረብ የተለያዩ ሠላማዊ የድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ «ለውጥን እንደግፍ፤ ዴሞክራሲን እናበርታ» በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የድጋፍ ሰልፍ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተካሂዷል፡፡
ለተሠሩት ሥራዎች ዕውቅና መስጠት ተገቢም ወቅታዊም ነው፡፡ ለለውጡ አራማጆችም አቅምን ከመፍጠሩም በላይ ህዝቡ ከጎናቸው የመሰለፉ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ የህዝቡን ፍላጎት ለማረጋገጥ ተግተው መሥራት እንዳለባቸው ትልቅ ኃላፊነትን ማስረከብ መሆኑም አይካድም፡፡ በሰልፎቹ ላይ እንደተንጸባረቀውም የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የበኩሉን ለመወጣት ተዘጋጅቷል፡፡ የለውጥ ሂደቱ ግለቱን ጨምሮ እንዲጓዝ ህዝቡ በየመድረኮቹ ቃል ገብቷል፡፡ ልማትና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ የበኩሉን እንደሚወጣ አንፀባርቋል፡፡
የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዳይጓተት፤ ዘላቂ ሠላምን የማረጋገጥ ሂደቱ እንዳይደናቀፍ ብርቱ ትግል ለማድረግ በአዲስ መንፈስ ተነሳስቷል፡፡ ይህን የሠላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ጉዞ ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን በተባበረ ክንድ ለመታገል ወኔውን ሰንቋል፡፡ በአዲስ ምዕራፍ የተጀመረው ለውጥ ለአፍታም ሳይቀዛቀዝ እንዲቀጥል ህዝቡ ወገቡን ታጥቋል፡፡ ይህንን እውነታም በየሰልፎቹ አንፀባርቋል፡፡
የታሰበውን ከግብ ለማድረስ፣ የታቀደውን ወደ መሬት ለማውረድ፣ የተጀመረውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደ ሰልፉ ሁሉ ተግባራዊ ሥራው ላይ በንቃት መሳተፍ ይገባል፡፡ በህዝባዊ መድረኮቹ ላይ የተገቡትን ቃል ወደ መሬት ማውረድ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም በየተሰማራበት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ በየመድረኮቹ እንደተባለውም የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡ የታለመው እውን ይሆናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና መንግሥታቸውን የመደገፉ ፍላጎትና ተነሳሽነት በተግባር መተርጎም ይኖርበታል፡፡ ዘላቂ ሠላምን የማረጋገጥ፣ ልማትን የማፋጠን፣ ዴሞክራሲን የመገንባትና ድህነትን የማሸነፍ ወኔው በተግባር ሊታይ ግድ ይላል፡፡ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ ህዝቡ የገባውን ቃል ወደ መሬት ማውረድ ይጠበቅበታል፡፡ ቃል በተግባር ተተርጉሞ ውጤት ማስመዝገብ አለበት፡፡ በአንደበት የተገለጸው ‹‹ከጎንህ ነን›› የድጋፍና የአንድነት ድምፅ ፍሬ ማፍራት ይኖርበታል፡፡
ሁሉም በተሰማራበት መስክ የታሰበው ውጤት እውን እንዲሆን አቅሙ በፈቀደ መጠን መንቀሳቀስና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ደግሞ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚተው አይደለም ሁሉንም ለውጥ ፈላጊ ይመለከታል፡፡ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ህዝብን ከጎኑ በማሰለፍ ለልማትና ሠላም ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ መሰለፍ አለበት፡፡ ዜጎች ጎራ ለይተው የሚጣሉበትን ዕድል ማጥፋት፤ በመልካም አስተዳደር እጦት ከዜጎች የሚነሳውን ቅሬታ መፍታትና ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡ በተደጋጋሚ እንደተባለው ሥልጣን ህዝብን ማገልገያ እንጂ መገልገያ አለመሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት ጠንክሮ መሥራትና ማሠራት ይኖርበታል፡፡
በተለይም በህዝቦች መካከል መቃቃርና ጥላቻን የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በመመርመርና በመፈተሽ ለመፍትሔ መሥራት ይኖርበታል፡፡ በተለይም የብሔር መልክ የያዙ ግጭቶች ዳግም እንዳይፈጠሩ መሥራት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች በህገ መንግሥቱ የተረጋገጠላቸውን በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውሮ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብትን ማስከበር ተገቢም፤ ወቅታዊም፣ ግዴታም ነው፡፡
ሰሞኑን ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች የታየው ዓይነት ግጭት ዳግመኛ እንዳይከሰት መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ዘመኑ ያለፈባቸው የግጭትና የሁከት አስተሳሰቦችን ድባቅ መምታት ይገባል፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚቆጠሩበት ያፈጀና ኢ-ህገ መንግሥታዊ አስተሳሰብ መወገድ ይኖርበታል፡፡ በዚህ የተነሳ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የመፈናቀል አደጋ ማስቆም ተገቢ ነው፡፡ አንዱ መጤ ሌላው፣ ነባር ተደርጎ በዜጎች መካከል የሚፈፀም የመከፋፈል ህገ ወጥ ድርጊት ሊገታ ግድ ይለዋል፡፡ ለዚህ እውን መሆን ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሁከትና ብጥብጥ ጎዳና የሚንቀሳቀሱ አካላትን መታገልና ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡
የመንግሥት ሠራተኛው የተረከበውን ኃላፊነት በጥራት፣ በፍጥነት፣ በታታሪነትና በታማኝነት በመወጣት የህዝብ አገልጋይነቱን በተግባር ማስመስከር ይኖርበታል፡፡ ዳያስፖራውና የግል ባለሀብቱም ለህዝብና አገር ልማትና ዕድገት የሚበጁ ተግባራትን በማከናወን የለውጡን ጉዞ ማፋጠን ይኖርበታል፡፡ ከትናንት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ መትጋትና መረባረብ ግድ ይላል፡፡
ይህን ማድረግ ከተቻለ የሚፈለገው ውጤት የማይመጣበት አንዳች ምክንያት አይኖርም፡፡ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ሰልፍ ላይ በተፈጠረ ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች ደም ለመለገስ የተደረገው ዓይነት ርብርብ በሥራ ላይ ከተንፀባረቀ ከሚፈለገው ከፍታ ለመድረስ አያዳግትም፡፡ የተባበረው የአንድነት ክንድ ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን በማጎልበት ለልማትና ለሠላም ዘብ መቆም አለበት፡፡ ሠላም ሲረጋገጥ፣ ልማት ሲፋጠን፣ ዴሞክራሲ ሲጎለብት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ የሚፈለገው ውጤት በተጨባጭ ይታያል፡፡ ለዚህ ስኬት እውን መሆን ታዲያ በድጋፍ ሰልፉ የታየው ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎትና መነሳሳት በእያንዳንዱ ሥራ ላይ መመንዘር አለበት፡፡ በየህዝባዊ ሰልፎቹ የተፈጠረው መነቃቃት በተግባር መለወጥና በውጤት መታጀብ አለበት፡፡

 

 

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በኢትዮጵያ ያለው የማዕድን ሀብት በቅጡ ታውቆ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ሀብቱን በጥናት ለይቶ ወደ ጥቅም ለመቀየር መንግሥት አዲስ ስልት ነድፎ ወደ ሥራ መግባት እንደሚጠበቅበትም ያነሳሉ። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬሚካልና ባዮ ምህንድስና ትምህርት ቤት ዲንና የማዕድን አመራር ምሁር ዶክተር አቡበከር ይማም እንደሚሉት፤ በአገሪቱ ካለው የማዕድን ሀብት የሚታወቀው ጥቂቱ ብቻ ነው። ወጥቶ ጥቅም ላይ የዋለው ኢምንት ነው። በአጠቃላይ በአገሪቱ ምን ዓይነት እና ምን ያህል ማዕድን እንዳለ አይታወቅም። ያለውን ሀብት አውቆ ወደ ጥቅም ለመቀየር ትኩረት በመስጠት አዲስ ስልት ነድፎ ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል።
የኢኮኖሚ ምሁሩ አቶ ካህሳይ ገብረየሱስ፤ መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ ያስቀመጠው ፖሊሲ ከሌሎች ዘርፎች ጋር የማይጣጣም ነው። አገሪቱን ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለማሸጋገር አቅዶ ለማዕድን የተሰጠው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለማዕድን ዘርፍ ትኩረት ነፍጎ ኢንዱስትሪን ማሰብ ምን ተይዞ ጉዞ ነው። የግሉ ዘርፍ በማይገባባቸው ወሳኝ ዘርፎች መንግሥት የማያለማቸው ከሆነ ከልማታዊ መንግሥት ባህሪ ጋር የሚጋጭ ነው።
አቶ ካህሳይ እንደሚሉት፤ መንግሥት በአገሪቱ ያሉትን ማዕድናት ለማውጣትና ለመጠቀም አዲስ ስልት መንደፍ አለበት። በአገሪቱ ያሉትን ማዕድናት በዓይነትና በብዛት ፈልጎ መለየት ይጠበቅበታል። ለአልሚዎችም ያልተንዛዛ ቢሮክራሲ መዘርጋት፣ ከሙስና የጸዳ የፍቃድ፣ የቁጥጥር፣ የማበረታቻና ሌሎች አገልግሎት ሊሰጥ ይገባል። ከግል ባለሃብቶች ጋራ በመቀናጀት ለኢንዱስትሪያላይዜሽን ሽግግር ወሳኝ የሆኑ እንደ ብረት፣ ፖታሽ፣ ኮፐርና ሌሎች ማዕድናት አውጥቶ ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆን ያስፈልገዋል።
የማዕድን አለኝታ ቦታዎች ናቸው ተብለው ለተለዩ ቦታዎች የሚሰጠው ፍቃድ በትክክል ያልተጠና በመሆኑ ምን ያህል ክምችት እንዳለ አይታወቅም። በዚህ የተነሳ አንዳንድ ባለሃብቶች ወደ ልማት ከመግባታቸው በፊት ዝርዝር ጥናት እያደረጉ ነው። ይህን ሁኔታ ዓለም አቀፍም ሆኑ አገር በቀል ድርጅቶች አይፈልጉትም። በርካታ ድርጅቶችም ፍቃድ ወስደው ከ10 ዓመታት በላይ ሳያለሙ ቦታውን ይዘው የተቀመጡት ለዚህ ነው። አጥንቶ ለአልሚዎች የማስተላለፍ የፌዴራል መንግሥት ነው። የመንግሥት ተነሳሽነት ባለመኖሩ ሀብቱ አልታወቀም ታውቆም የሚወጣው በህጋዊ መንገድ ህዝብና አገር አልጠቀመም።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር አቡበከር እንደሚያብራሩት፤ የማዕድናት ክምችቱንና ዓይነቱን ለማወቅና ወደ ልማት ለመቀየር በየጊዜው ማጥናትና መመርመር ቢገባውም መንግሥት ይህን አላደረገም። ይህ ባለመደረጉ ወደ ጥቅም መቀየር አልተቻለም። እ.አ.አ በ2017 ዓ.ም በእንግሊዝ የወጣ ሪፖርት እንዳመለከተው በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካን ያህል የወርቅ ክምች መኖሩ ተገልጿል። በአገሪቱ ከወርቅ በተጨማሪ ታንታለም፣ ሊቲየም፣ ፖታሽ፣ ብረት፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ነዳጅ፣ የከበሩ ማዕድናትና ሌሎችም በርካታ ማዕድናት እንዳሉ ቢታወቅም፤ መንግሥት አጥንቶ ለማልማት ዝግጁ ባለማድረጉና ባለማስተዋወቁ ወደ ጥቅም መቀየር አልተቻለም።
መንግሥት ይህን ሀብት ወደ ጥቅም ለመቀየር በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ በጥልቀት ማጥናትና ምርምር ማድረግ አለበት። ዘመናዊ የመመርመሪያ መሳሪያዎችም መጠቀም ይገባል። አንዳንዶቹ ማዕድናት ወደ ውጭ ተልከው የሚመረመሩ በመሆኑ ዓይነቱና የክምችት መጠኑ ሲታወቅ ለውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ስለሚጋብዝ የአገሪቱን የቤተ ሙከራ አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ያብራራሉ።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመሬት ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ካሳ አማረ፤ በበኩላቸው የማዕድን ዓይነት፣ ብዛት እና የኬሚካል ይዘታቸውን የሚያሳይ ጥናትና ምርምር ተደርጎ ካርታ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ያለው የማዕድን ዓይነትና ብዛትን የሚያሳየው ካርታ የተሰራው በተወሰኑ ቦታዎች ነው፤ ጥራትም የሌላቸው ናቸው። የተወሰኑ ማዕድናት ለማውጣት ወሳኝ የሆነው የኬሚካል ካርታዎች ጥናት በጥቂት ቦታዎች ካልሆነ በስተቀረ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መስራት አልቻለም። በመሆኑም መንግሥት ፍለጋ ማካሄድና የአልኝታ ቦታዎች ማጥናት አለበት ይላሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር አቡበከር፤ ማዕድናቱን የግል ባለሃብቱ እንዲያለማ ዕድል መስጠቱ ጥሩ ቢሆንም የተንዛዛ ቢሮክራሲን ማስወገድ ይገባል፡፡ ማበረታቻ በመስጠትም ትኩረቱን ማሳደግ ተገቢ ነው። የግሉ ባለሃብት ደፍሮ የማይገባባቸው እንደ ፖታሽና ብረት ያሉ ለግብርናውና ለኮንስትራክሽኑ የጀርባ አጥንት የሆኑ ማዕድናትን መንግሥት ማልማት አለበት። ከኢትዮጵያ የወጡ ማዕድናት ሌሎች አገራት ትንሽ እሴት በመጨመር በአራት እጥፍ ይሸጣሉ። የሚለሙ ማዕድናት እሴት በመጨመር ያለቀለት ምርት ለገበያ ለማቅረብም አስቀድሞ ስልታዊ ሥርዓት መዘርጋት አለበት። ማዕድናት የሚወጡበትን አካባቢ ማህበረሰብ የተወሰነ ባለድርሻ ማድረግ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥና በአካባቢ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚያግዝ በመሆኑ ስልት ነድፎ ተግባራዊ ማድረግም እንደሚገባ ይናገራሉ።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ካሳ በኩላቸው፤ የማዕድን አለኝታ ቦታዎችን መለየት፣ ለባለሃብቶች ማስተዋወቅ፣ የተንዛዛ ቢሮክራሲን ማስቀረት፣ አልሚዎች ተቀናጅተው እንዲሰሩ አሰራር መዘርጋት፣ የመንግሥት ተቋማትን ዘርፉን በአግባቡ እንዲመሩ በሚያስችል መልኩ እንደገና በማዋቀር ማዕድናትን ለመጠቀም የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጦ ወደሥራ መግባት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
የኢኮኖሚ ምሁሩ አቶ ካህሳይ፤ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር አልሚዎችን ከመቀበልና ፍቃድ ከመስጠት ያለፈ ሚና ሊኖረው ይገባል። በኢትዮጵያ የተቀናጀና የተደራጀ ዕድገትና ልማት ለማምጣት በአገሪቱ ሁሉንም ዘርፍ የሚያጠና ሁሉን አቀፍ ጥናትና ምርምር በማድረግ መረጃ በመሰነድ ለመንግሥትና ለባለሃብቶች መረጃ የሚያቀርብ ስልታዊ የጥናትና ምርምር ማዕከል በማቋቋም ሁሉም ዘርፎች በተቀናጀ ጥናት እንዲካሄዱ ማድረግ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በ2009 ዓ.ም ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በተለያዩ የማዕድን ዓይነቶች 174 የአለኝታ ቦታዎች ተለይተዋል። በተወሰኑት የአለኝታ ቦታዎች እየለሙ ነው።
የማዕድን ሀብቱን በአግባቡ በመለየት ጥቅም ላይ ማዋል ካልተቻለ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሽግግር በግብአት እጥረት ስለሚፈተን ግቡን ለማሳካት ፈተና ያጋጥማል፡፡ ከውጭ የሚገባው የተለያየ ማዕድን ወጪን በማናር አገሪቱ የገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት በቀላሉ እንዳይፈታ ያደርጋል፡፡ ሀብቱን አሟጦ ጥቅም ላይ ማዋል ካልተቻለ የውጭ ጥገኛ በማድረግ በአገሪቱ የልማት ፖሊሲ ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል፡፡ 

ዜና ትንታኔ
አጎናፍር ገዛኸኝ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።