Items filtered by date: Thursday, 05 July 2018

በክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ሀገሪቷን ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሏት ነው፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወሰን አካባቢዎች ተዳጋጋሚ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ ግጭቶቹ ለበርካቶች ህልፈትና የአካል ጉዳት ምክንያት ሆነዋል፤ እየሆኑም ይገኛሉ፡፡ በወሰን አካባቢዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬቸው ለመፈናቀል ተገደዋል፡፡ በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ተከትሎ በሚከሰቱ አለመረጋጋቶች በስፍራዎቹ የሚኖሩ ዜጎች በዝርፊያ ንብረታቸውን ሲያጡ ቆይተዋል፡፡ በክልሎች የአስተዳደር ወሰን አካባቢ የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ወሰን ያልተካለለባቸውን አካባቢዎች ለማካለል ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በቅርቡ በተካሄደው 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3 ኛ የስራ ዘመን 31ኛው መደበኛ ጉባኤ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የ2010 በጀት ዓመት የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቧል፡፡ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብትና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አፈጻጸም አስመልክቶ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን፤ ጥያቄ እና አስተያየቶች ከቀረቡባቸው ጉዳዮች መካከል በክልሎች መካከል የአስተዳደር ወሰን የማካለል ስራ ባለመጠናቀቁ የተፈጠሩ እና እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች አንዱ ነው፡፡ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችም በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴዎቹን ጥያቄ ያቀረቡት የምክር ቤቱ አባል አቶ ጸጋዬ ውዱ እንደተናገሩት፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተልዕኮ ላይ በግልጽ ከተቀመጡት ጉዳዮች አንዱ የግጭት አፈታት ሥርዓት በመዘርጋት የህዝቡን ሰላም ማስከበር ቢሆንም ባለፈው ዓመት ሆነ በዚህ ዓመት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሁከት እና ብጥብጥ ተነስቷል፡፡ የሁከት እና ብጥብጥ መነሻ የተለያየ ቢሆንም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አጽንኦት ተሰጥቶ በጊዜው ያልተፈቱ ጉዳዮች መካከል የአስተዳደር ወሰን ማካለል ቅድሚያውን ይይዛል፡፡
አንዳንዶቹ የአስተዳደር ወሰን ችግሮች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሁንታ አግኝተው ህዝበ ውሳኔ የተሰጠባቸው መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ጸጋዬ፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተግባራዊ ሳይሆኑ ዓመታትን ያስቆጠሩ በመሆናቸው ለሰው ህይወት እና ንብረት ውድመት መንስኤ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ አሁንም ያልተጠናቀቁ በርካታ የወሰን ማካለል ስራዎች መኖራቸውን በመጠቆም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እነዚህን ችግሮች በአፋጣኝ ለምን እንደማይፈታ እና በቀጣይ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማምጣት ምን እየተሰራ እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የአስተዳደር ወሰን የማካለል ስራ ባለመጠናቀቁ ተፈጥረዋል ያሏቸውን ችግሮችም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በአፋር እና በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን መካከል የወሰን ማካለል ስራ ባለመሰራቱ በየወቅቱ በሁለቱ ድንበር ላይ ግጭት እንደሚከሰት ጠቅሰዋል፡፡ የግጭቶቹ ምንጭ በዋናነት የግጦሽ መሬት እና የመሬት ወረራ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡ ይህ ግጭት ለረጅም ዘመናት የቆየ መሆኑን በመጠቆም ችግሩ እስካሁን መፈታት እንደነበረበት አንስተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት እንዳብራሩት ከሁለት ዓመት በላይ የቆየውን የዚህን የድንበር አካባቢ ችግር ከምንጩ ለማድረቅ ወሰን የማካለል ስራ ከመስራት ይልቅ እሳት የማጥፋት ስራ ብቻ እየተሰራ ቆይቷል፡፡ በየጊዜው በሚከሰተው ግጭት የሰው ህይወት እየጠፋ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ከምንጩ ለመፍታት ያደረገው ጥረት እምብዛም ነው፡፡ ጥረት ከማድረግ ይልቅ የአመራር ችግር ነው እየተባለ ቀን ቀንን፤ ወር ወርን እዲሁም ዓመት ዓመትን እየተካ ህዝቡ ለጉዳት እየተዳረገ ነው፡፡ የአመራሮች ችግር ካለባቸው ማንሳት እንደሚገባም ነው የቋሚ ኮሚቴው አባላት ያነሱት፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እርምጃዎቹ መጓተት በአዋሳኝ አካባቢዎች ላይ የሚገኘውን ህብረተሰብ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል፡፡ ባቲ አከባቢን በመወከል ፓርላማ እንደገቡ የገለጹት የምክር ቤቱ አባል እንደተናገሩት በአካባቢው በሚገኝ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ልጆች ትምህርታቸውን ካቆሙ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ መዘጋቱን የክልሉ መንግስትም ሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚያውቀው በመጥቀስ ችግሩን ለመቅረፍ ያደረጉት ጥረት ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡
ችግሩ እንዲፈታ ህዝቡ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው የተናገሩት እኝህ የፓርላማ አባል ችግሩ የሚፈታበትን ቀን በጉጉት እየተጠባበቀ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ክልሎች መንግስታት መካከል መልካም የሚባል ግንኙነት አለ፡፡ ይህ መልካም ግንኙነት በዚህ በወሰን ምክንያት ሳይሻክር እና የክልሎቹ ግንኙነት ሳይወሳሰብ ችግሩን መቋጨት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
ሌላኛው የቋሚ ኮሚቴ አባል እንዳብራሩት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በአፋር መካከል አንጻራዊ ሰላም አለ፡፡ ለዘመናት ወሰን አካባቢ ይከሰት የነበረው ችግር ለጊዜው ረግቧል፡፡ ሆኖም በአዋሳኝ አካባቢው ያለውን ችግር በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታት ማለቅ ያለባቸው፤ በአጭሩ ሊቋጩ የሚችሉ ጥቂት ስራዎች ይቀራሉ፡፡ ይህ የማይጠናቀቅ ከሆነ በአዋሳኝ አካባቢ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡
በአፋር እና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የታየውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ የወሰን ችግር በዘላቂነት የተፈታ አስመስሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሪፖርት ማድመቂያ አድርጎ እያቀረበ መሆኑን በመግለጽ ነገር ግን ችግሩ በዘላቂነት ሳይፈታ በተጋነነ መልኩ መቅረብ የለበትም ብለዋል፡፡ የሁለቱ ክልሎች ወሰን ችግር ዘላቂ መፍትሄ ላይ አልደረሰም የሚሉት የአካባቢው ተወካይ በስፍራው ዝርፊያ፣ ግጭት እና የዜጎች ሞት ባይከሰትም እንኳን ለአስተዳደራዊ ስራዎች አዳጋች ከመሆኑም በላይ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እየሆነ ነው፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጉዳዩን በጥብቅ ይዞት ሊፈታ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ መካከል የነበረውን የአስተዳደር ወሰን ችግር ለመፍታት ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት ህዝበ ውሳኔ የተካሄደ ቢሆንም፤ ጉዳዩ እየተንከባለለ 13 ዓመታት እንዳለፉ የተናገሩት የአካባቢው ተወካይ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካቶች ለህልፈት፣ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ለመፈናቀል ተዳርገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በርካቶች እየሞቱ ናቸው፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ከህዝበ ውሳኔ ጎን ለጎን በክልሎቹ መካከል ሊገነቡ የታሰቡ የጋራ ፕሮጀክቶችም የውሃ ሽታ ሆነው መቅረታቸው ችግሩን እያባባሰው እንደሆነ ነው ያብራሩት፡፡
ሌላኛው በወሰን ችግር ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እየተከሰተባቸው እንደሆነ ከተጠቀሱት አካባቢዎች መካከል በደቡብ ክልል የሰገን ህዝቦች አካባቢ እና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን፤ አፋር እና ትግራይ፤ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞኖች ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችን በአብዛኛው የአካባቢው ሽማግሌዎች እየፈቱት ቢሆንም ሳይውል ሳያድር ዳግም ግጭት እየተከሰተ ነው፡፡ የወሰን ችግሮች ባለመፈታታቸው ከወሰን በዘለለ የሌላ ችግር መንስኤ እየሆኑ ነው፡፡ ግጭቶቹ በሁለት ክልሎች በሚኖሩ ህዝቦች መካከል የሚከሰቱ እንደመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስካሁን ሊፈታው ይገባ እንደነበር አንስተዋል፡፡
የፌዴራል እና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ውለታው እንደተናገሩት፤ የየክልሎች የአስተዳደር ወሰኖች አለመካለል ለግጭቶች መንስኤ ሊሆን አይችልም፡፡ የወሰን ችግር የሌለባቸው አካባቢዎች ጭምር ግጭቶች መከሰታቸው የግጭቶቹ መንስኤ የወሰን አለመካለል ብቻ እንዳልሆነ ማሳያ ነው፡፡ ኦሮሚያ እና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎችን እንደአብነት በመጥቀስ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሙሉጌታ በክልሎቹ መካከል ያወዛግቡ ከነበሩ 48 መንደሮች ውስጥ አብዛኛው አካባቢዎች በሁለቱ ክልሎች ስምምነት ተካለዋል፡፡ ያልተካለሉት ስድስት መንደሮች ብቻ ናቸው፡፡ ለበርካቶች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት የሆነው ግጭት ግን ባልተካለሉ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በአብዛኛው አካባቢ ተከስቷል፡፡
በሀገሪቱ አብዛኞቹ አካባቢዎች ወሰን የማካለል ስራዎች ያልተከናወኑባቸው መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ወሰን አለመካለል የግጭቶች መንስኤ ቢሆን ሀገሪቱ በሙሉ ጦርነት ውስጥ ትገባ ነበር ብለዋል፡፡ የክልሎቹ ወሰኖች ተራሮች፣ ሸለቆዎች እና ወንዞች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ በአጠቃላይ ወሰን የግጭት መንስኤ አልነበረም፤ መሆንም አይገባውም ሲሉ አብራርተዋል፡፡
አቶ ሙሉጌታ እንዳብራሩት፤ በአንዳንድ ክልሎች ወሰን አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት የወሰን የማካለል ስራ ሲሰራ ግጭቱ ሲቆም ይስተዋላል፡፡ እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ላይ ወሰን ማካለል ግጭትን የሚያስቀር ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ጋምቤላ ክልሎች መካከል ቤሮ እና ዲማ የሚባል አከራካሪ ቦታ ላይ በሚከሰት ግጭት ሳቢያ ሰው ይሞት፤ ንብረት ይወድም ነበር፡፡ ወሰን የማካለል ስራ ሲሰራ ግን በአካባቢው የነበረው ግጭት ሙሉ በሙሉ ቆሟል፡፡ ስለዚህ ወሰን ማካለል ግጭት የሚያስቀር የሚመስልበት አጋጣሚ አለ፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ እኩይ ዓላማ ያላቸው አካላት ያልተካከሉ ወሰኖችን እንደ ግጭት ማባባሻ እየተጠቀሙበት ስለሆነ፤ ለእነዚህ በእኩይ ተግባር ለተሰማሩ አካላት ምክንያት ማሳጣት እና ክልሎች በይገባኛል እንዳይጨቃጨቁ ማካለል አስፈላጊ በመሆኑ ይህንኑ ማከናወን ተገቢ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የወሰን ማካለል ስራዎች በስፋት መከናወኑን የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ በመጀመሪያ ሁለቱ ክልሎች በስምምነት ወሰን የማካለል ስራዎች ሲሰራ እንደነበር በማንሳት ከክልሎች አቅም በላይ በሆነባቸው አካባቢዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እገዛ ሲያደርግ እንደነበር ነው ያነሱት፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ በቅድሚያ ችግሮቹ በክልሎች መፈታት አለባቸው፡፡ ክልሎቹ ከአቅማቸው በላይ ከሆነባቸው ለፌዴራል መንግስት ማሳወቅ አለባቸው፡፡ ክልሎች ሊስማሙ ባልቻሉባቸው የወሰን አካባቢዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሌሎች ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ጋር በመሆን አካባቢውን በማጥናት ከተጠናቀቀ በኋላ ገለልተኛ የሆነ አስተያየት ይሰጣል፡፡ ክልሎች አብዛኛውን ጊዜ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሰጡ ገለልተኛ አስተያየቶችን ተቀብለው ተግባራዊ በማድረግ የወሰን ችግሮችን ይፈታሉ፡፡
አከራካሪ የሆኑ የወሰን ጉዳዮችን ዘንድሮ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እንደነበር ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው እስከ መጋቢት ድረስ ሀገሪቷ ውስጥ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ይህንን ማከናወን እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ከነበረው አለመረጋጋት በተጨማሪ ቀደም ባሉ ጊዜያት በአጭር ጊዜ ውስጥ መጨረስ የነበረባቸውን ጉዳዮች ክልሎች ሲያንከባልሉ ቆይተዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ክልሎች ጉዳዩን ሲያዘገዩት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስተካክሉ ግፊት ያለመፍጠር ችግር እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በክልሎች ዳተኝነት ያልተካለሉ ወሰኖችን ለግጭቶች እንደአባባሽ ምክንያት ለሚጠቀሙ አካላት እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳብራሩት፤ የክልል መንግስታትን ግንኙነት የሚመለከት ፖሊሲ ባለመኖሩ ምክንያት ክልሎች ከክልሎች ጋር ተቀራርበው የመስራት ክፍተት ፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት የታቀዱ ስራዎች ተግባራዊ ሳይሆኑ ሲቀሩ የሚጠየቅ አካል አልነበረም፡፡ አሁን ይህን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህን ፖሊሲ የክልል ምክር ቤቶች እንዲወስዱ በማድረግ በክልል ምክር ቤቶች አማካኝነት ተጠያቂነትን ለማስፈን ስራ ይሰራል፡፡ ከፖሊሲው በተጨማሪም የፌዴራል መንግስቱ ከዚህ በፊት ከነበረው የተለሳለሰ አካሄድ ወጥቶ ጥፋተኛ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ እና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ካልቻለ ችግሩ ከዓመት ዓመት እየተንከባለለ ሊሄድ ይችላል፡፡
አሁን በሀገሪቱ ውስጥ የሚታየው ሰላምና መረጋጋት ከቀጠለ በ2011ዓ.ም የወሰን ማካላል ችግሮችን ለቅሞ ለመፍታት እቅድ ተይዟል፡፡ ስለሆነም ቅሬታ በማይነሳበት አግባብ ስራውን ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በወንድማማችነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመስርቶ እንዲካሄድ ግንዛቤን የማሳደግ ስራዎችም እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት፡፡
በወሰን ግጭቶች ምክንያት ትኩረታቸውን ግጭቶች ላይ በማድረግ ለሌላ ልማት ትኩረት እንዳይሰጡ እያደረጋቸው ስለሆነ ክልሎቹ ችግሩ በአፋጣኝ እንዲፈታ ይፈልጋሉ፤ ይህንን ተግባር ለማከናወን ከክልሎቹ ጋርም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ጉዳዩ ህዝቡ፣ ክልሎቹ እና የፌዴራል መንግስት የሚፈልገው እንደመሆኑ በ2011 በጀት አመት ያልቃል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከ2011 ሩብ ዓመት ጀምሮ የመጀመሪያው የዝግጅት ጊዜ ስለሚሆን ከጥቅምት ጀምሮ በሚሰራው ስራ እንዲቆዩ የተደረጉ ስራዎች እልባት ያገኛሉ፡፡ ወሰን የማካለል ስራ ለማከናወን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ የህዝበ ውሳኔ ውጤቶች፤ ከዚህ ቀደም የተሰሩ ጥናት ውጤቶች፤ በክልሎች መካከል የተደረሱ ስምምነቶች የማሰባሰብ ስራ መጠናቀቁን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡
አብዛኞቹ የወሰን አካባቢዎች የሚታወቁ እና ለመፍታትም ብዙም አዳጋች እንዳልሆነ የሚናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው በአንዳንድ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተደረጉ የጥናት ግኝቶች እንዳሉ በመግለጽ ክልሎቹ የጥናት ግኝቱን ተቀብለው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይሰራል ብለዋል፡፡ ከእነዚህ አካባቢዎች አንዱ ኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች ወሰን አካባቢ የማካለል ስራው ያልተጠናቀቀባቸው ስድስት መንደሮች ወሰናቸው የት እንደሆነ የጥናት ውጤት መኖሩን በመግለጽ ክልሎቹ በራሳቸው የማይፈቱት ከሆን የጥናት ውጤቱን ወስደው መተግበር እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡
የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ በበኩላቸው፤ የወሰን አካባቢ ችግሮች ከልማት ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሆናቸውን በማብራራት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ክልሎችን በልማት ማስተሳሰር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ከልማት ባሻገር ሙሰኞች የራሳቸውን የፖለቲካ ጥቅምን ለማስጠበቅ በአስተዳደር ወሰን አካባቢዎች ግጭቶች እንዲነሱ እንደሚያደርጉ በመግለጽ እነዚህን ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ ልማቱን የማስፋፋት ስራው በሁለቱ ክልሎች እና በፌዴራል መንግስት ድጋፍ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የክልሎቹ ወሰን የማካለል ስራው ከአቅማቸው በላይ እንደሆነባቸው እስኪያሳውቁ እና እሳት እስኪነሳ መጠበቅ እንደሌለበት በመግለጽ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚጠየቅበት ወቅት ይህን ምላሽ በተደጋጋሚ መስጠቱ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ካለ የፌዴራል መንግስት በአፋጣኝ መግባት እንዳለበት የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው የሰው ህይወት እየጠፋ የክልሎችን ይሁንታ መጠበቅ ተገቢነት የጎደለው ነው ብለዋል፡፡ የፌዴራል መንግስት ለክልሎች፣ ክልሎች ደግሞ ለዞኖች፣ ዞኖች ለወረዳዎች እየተው በዚያ መካከል ህብረተሰቡ ያልተገባ ዋጋ እየከፈለ መሆኑን የጠቀሰው ቋሚ ኮሚቴው፤ ይህ መሆን እንደሌለበት እና ጥናቶች ተደርገው ችግሮች በአፋጣኝ እየተፈቱ መሄድ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡
የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈቲያ የሱፍም፤ ወሰን ማካለል የግጭቶች መንስኤ እንዳይሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት ሊሰራ እንደሚገባ በመጥቀስ ለችግሩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

መላኩ ኤሮሴ

Published in ፖለቲካ

የጋሞ፣ የጎፋ፣ የዘይሴ ፣ የጌዲቾና የኦይዳ ብሄረሰቦችን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ ሌሎች የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ተወላጆች ተከባብረውና ተቻችለው በፍቅርና በሰላም ይኖሩበታል፡፡  የደቡቡ የጋሞ ጎፋ ዞን፡፡  በተለይም ደግሞ በተፈጥሮ ውበት በታደለችው  ድንቋ የዞኑ ከተማ አርባምንጭ የአባያና ጫሞ አስደናቂ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች  ፤ የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ፤ የአዞ እርባታ ጣቢያ፤ የአዞ ገበያንና በአካባቢው ታይተው የማይጠገቡ የዱር እንስሳት እና የተፈጥሮ ደኖችን  በአገሪቱ የቱሪዝም መዳረሻነት ጉልህ ስፍራ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ በዙኑ ካሉት ተፈጥሮ ሀብቶችና መስህቦች ክልሉ ብሎም አገሪቱ ምን ያህል ተጠቃሚ እየሆኑ ነው?  ስለዚህና እየተሰሩ ስላሉት የቱሪዝም ስራዎችን  የጋሞ ጎፋ ዞን ባህል ቱሪዝምና   የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ    ካምቦ ዴሮ  ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ እንደሚመለከተው አቅርበነዋል፡፡


አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ያሉትን የተፈጥሮ መስህቦች ለማስተዋወቅና ዞኑን የቱሪዝም መደረሻ ለማድረግ እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች ቢያብራሩልን?
አቶ ካምቦ፡- እንደሚታወቀው ዞኑ ከክልሉ በስፋትም ሆነ በቱሪዝም ሀብትም ቀዳሚ ስፈራ ይይዛል፡፡ በህዝብ ብዛትም ቢሆን ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚኖሩበት የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች መናኸሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም አምስቱ ነባር ብሄረሰቦች ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩበት ከመሆኑም ባሻገር የየራሳቸው ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ዞኑን ለቱሪዝም መዳረሻነት ተመራጭ አድርጎታል፡፡ ዞኑ ከእርሻ ተግባራት ጀምሮ እስከ የሽመና ጥበብ ድረስ የሚያከናውን የበለፀገ ባህል ያለው ህዝብ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ እንግዲህ ባለው ሀብት በተጨባጭ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በተለይም የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በክልል ደረጃና በገጠር መንገድ ፕሮጀክት የተወሰነ ስራ ተከናውኗል፡፡ በዋናነትም አርባ ምንጭ አየር ማረፊያ ለቱሪዝም መዳረሻነት ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ የግል ባለሀብቶችም ለቱሪስቱ ማረፊያ የሚሆኑ ሆቴሎችን፣ ሬስቶራንቶችና ሎጆችን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በአርባ ምንጭ ከተማ በአሁኑ ወቅት የተወሰኑ ስራዎች የሚቀራቸውና ዓለምአቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ከ10 በላይ ሆቴሎች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ ይሁንና ካለው እምቅ የቱሪዝም መስህብ አኳያ እየተሰራ ያለው ስራ አመርቂ ነው ብለን አንወስድም፡፡ በአገር ደረጃም ቢሆን የቱሪዝምን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም በፖሊሲ ደረጃ ተቀርፆ ወደተግባር የተገባው በቅርብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዞኑ ከቱሪዝም ዘርፍ በየአመቱ የሚያገኘው ገቢ ምን ያህል ነው?
አቶ ካምቡ፡- እንደሚታወቀው የቱሪዝም ገቢ ሰፊ ነው፡፡ ደግሞም አገሪቱም የቱሪዝም ገቢን የምትለካበት ሥርዓት በራሱ ገና ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህን ስል አንደኛ የቱሪዝም ገቢ የሚሰበሰበው በተወሰኑ ዘርፎች ላይ ብቻ በመሆኑ፤ ሁለትም አሁን ባለው ሁኔታ የቱሪዝም ገቢ መረጃ የሚሰበሰበው የዘርፉ ተዋናዮች ለመንግስት ከሚከፍሉት ግብር አንፃር ተሳቢ ተደርጎ በመሆኑ ትክክለኛውን ገቢ ለማወቅ አዳጋች ነው፡፡ አብዛኛው ባለሀብት ደግሞ እኛ በምንሰበስበው መረጃ ላይ ጥርጣሬ ስላለው እውነተኛውን ገቢ ላይነግረን ይችላል፡፡ እኛም ማስገደድ አንችልም፡፡ በዚህ መሰረት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከአልጋ ኪራይ ብቻ 47 ሚሊዮን ብር የተገኘ ሲሆን፤ ሌሎች አገል ግሎቶች ሲጨመሩ ገቢው ከእዚህም በላይ ሊልቅ እንደሚችል ይታመናል፡፡ በመሆኑም ይህንን ተሳቢ አድርገን በበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ከእነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ይገኛል ብለን እንጠብቃለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዳዲስ በለሀብቶችን ወደዘርፉ ለመጋበዝ የዞኑ አስተዳደር ምን ያህል ምቹ ሁኔታዎችን ዘርግቷል ማለት ይቻላል?
አቶ ካምቦ፡- የዞኑ አስተዳደር ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠርና በመደገፍ ረገድ የሚታማ አይደለም፡፡ እንደውም ከሚገባው በላይ አሰራሮችን በማቅለል መሬት በአጭር ጊዜ እንዲያገኙ በማድረግ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው ተብሎ የሚታመነው፡፡ እስካሁንም በዚህ ደረጃ ቅሬታ ቀርቦብን አያውቅም፡፡ ምንአልባት እንደችግር ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ባለሀብቱ ለኢንቨስትመንት የተሰጠውን መሬት ለተባለለት አላማ ያለማዋልና በተሰጠው የጊዜ ገደብ ግንባታ አጠናቆ ወደ ስራ ያለመግባት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አስተዳደሩ በሚፈልገው ፍጥነት ዞኑን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ትልቅ ማነቆ ሆኖበታል፡፡ በዚሁ ልክ ግን ከትላልቅ ከተሞች ባልተናነሰ ዓለምአቀፍ ደረጃ የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ያሉ ሆቴሎች ቁጥርም ቀላል አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግንባታ በማይጀምሩት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ምን ያህል አመርቂ ነው?
አቶ ካምቦ፡- እርምጃ እንወስዳለን፡፡ የምንወስደው ግን ጠቅልለን እናዳናስወጣቸው ስለምንፈራ ቀስ በቀስ እንዲማሩም ጭምር እያደረግን ነው፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ፍቃድ የቀማናቸው ባይኖሩም ያስጠነቀቅናቸው አሉ፡፡ ለአብነት ያህል እንኳ መጥቀስ ካስፈለገ በሆቴል ግንባታ ላይ ያሉ ስድስት ተቋማት በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገቡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ስለዚህ እዚህ ጋር መታሰብ ያለበት እንደዚህ አይነት ስራ ከፍተኛ መዋለንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ ቶሎ አልገነባችሁም ብለን ፍቃዳቸውን ብንቀማ ዞሮ ዞሮ የምንጎዳው ዘርፉን ነው፡፡ በመሆኑም በጥንቃቄ ማየት መፈተሽና መደገፍ ይገባል ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ ያሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ካምቦ፡- ያለው ችግር በጣም ሰፊ ነው፡፡ ከእኛ ስንነሳ በመጀመሪያ ደረጃ የእኔነት ስሜት ይዞ በቅንጅት ከመስራት አኳያ በሁሉም ደረጃ የሚታይ ክፍተት አለ፡፡ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ከማከናወን አኳያ ብዙ የሚቀረን ነገር አለ፡፡ በተለይም ያሉትን ሀብቶች በአግባቡ ጠብቆ ለመጪው ትውልድ የማቆየት ሃላፊነትን ተገንዝቦ እየተሰራ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዚሀ ደረጃ የተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አመርቂ ነው ብዬም አላስብም፡፡ ለዚህ በነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ በአሁኑ ወቅት እየታያ ያለውን ትልቅ ችግር በአብነት መጥቀስ እንችላለን፡፡ በፓርኩ ውስጥና አካባቢው ልቅ ግጦሽ በከፍተኛ መጠን ተስፋፍቷል፣ ደን ጭፍጨፋና ከሰል ማክሰል የመሳሰሉት ድርጊቶች የፓርኩን ህልውና አሳሳቢ ደረጃ አድርሰውታል፡፡
በሌላ በኩል ፓርኩ የውስጥ ለውስጥ የመሰረተ ልማት እጥረት አለበት፡፡ በውስጡ የሚሰሩ የመሰረተ ልማቶች ተጀምረው አይጨርሱም፡፡ በዚህ ምክንያት ቱሪስቱ በሚፈልገው መልኩ መጎብኘት አልቻለም፡፡ በተለይም በፓርኩ መሃል ላይ ያለው ድልድይ በማርጀቱና ጥገናም ያልተደረገለት በመሆኑ አንድ ቀን ጎብኚዎችን አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ስጋት አለብን፡፡ ይህንን ችግር ለሚመለከተው አካል አቤት ብንልም እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አላገኘንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፓርኩ አሁን ያለበት ስጋት ምን ያህል አሳሳቢ ነው? መታደግስ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድ ነው?
አቶ ካምቦ፡- ብዙዎቻቸን እንደም ናውቀው ይህ አንጋፋ ፓርክ የተቋቋመበት ዋና አላማ ብርቄዬውን የስዋይን ቆርኬ ለመጠበቅ ያስችል ዘንድ ነው፡፡ ይሁንና በፓርኩ ዙሪያ ባሉ ማህበረሰቦች እየደረሰበት ባለው የደን ምንጠራ፣ ልቅ ግጦሽና አደን ምክንያት ይህ ብርቅዬ እንስሳት የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበት ቆይቷል፡፡ በፓርኩ ላይ የሚደረገውን ወረራ ማስቆም ባለመቻሉ የክልሉ መንግስት የተረፉት ቆርኬዎች ወደ ማዜ ፓርክ በማሸጋገር እንዲጠበቁ አድርጓል፡፡ ይሁንና አሁንም ቢሆን በፓርኩ ውስጥ ያሉ እንደ የሜዳ አህያ የመሳሰሉት የዱር እንስሳት ከቤት እንስሳት ጋር ተዋህደው ለበሽታና ለአደጋ ተጋልጠዋል፡፡
ፓርኩ ከከተማዋ ጋር ተያይዞ የተመ ሰረተና ለከተማዋ ውበት ትልቅ ድርሻ ያለው እንደመሆኑ በኛ በኩል ከሰው ንክኪ የፀዳ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይሁንና ፓርኩ ሌሎች ዞኖችና ክልሎችን የሚያዋስን እንደመሆኑ በእኛ በኩል ብቻ የምናደርገው ጥበቃ ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ በተለይም ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ጋር በሚዋሰንበት በኩል ልቅ ግጦሽና ሰፈራ በመኖሩ ፓርኩንም ሆነ በውስጡ ያሉ እንስሳት እየጎዳ ነው የሚገኘው፡፡
ይህ ልቅ ግጦሽና ወረራ እንዲቆም በተለያየ ጊዜያት ለሚመለከታቸው አካላት አሳስበናል፡፡ ከደቡብ ክልል ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግስት ድረስ በአፋጣኝ ለችግሩ እልባት እንዲሰጠው ጥያቄያችን አቅርበናል፡፡ ይሁንና እስካሁን ድረስ ምንም አይነት አጥጋቢ ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም፡፡ በርግጥ የክልሉ መንግስት ባገኘው አጋጣሚና መድረክ ሁሉ መፍትሄ እንዲሰጠው ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን ከኦሮሚያ በኩል ይህንን ለማስፈፀም ያለው ዝግጁነትና እየተሰጠ ያለው ምላሽ ደካማ ነው፡፡
በሁለቱም ክልሎች ሊፈታ ባለመቻሉ ጉዳዩ ለፌዴራል መንግስት ቀርቦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቦታው ድረስ በመምጣት ጥናት ቢያደርግም እስካሁን ድረስ ይሄ ነው የሚባል መፍትሄ አልተሰጠውም፡፡ በአሁኑ ወቅት የፓርኩ ወሰን ባለመለየቱ፣ ወራሪዎቹም የታጠቁ በመሆናቸው ፓርኩንና እንስሳቱን ከአደጋ መጠበቅ አልተቻለም፡፡ ስለዚህ እንደ አጠቃላይ መናገር የሚቻለው የዚህ ፓርክ ህልውናው አደጋ ላይ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ችግር እስካሁን ድረስ ያለመታከት ለሚመለከተው አካል ሁሉ ብናመለክትም አድማጭ አጥተናል፡፡
እዚህ ጋር ማሳሰብ የምፈልገው ነገር ቢኖር ይህ ፓርክ የዚህ ክልል ሀብት ብቻ አይደለም፤ የአገሪቱ ሀብት ነው፡፡ እኛ ባልተወለድንበት ዘመን የነበረ ሀብት እኛ ተማርን፣ ፊደል ቆጥረን ብለን ልናጠፋው የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ይህንን ፓርክ ማጣት ማለት ይህንን ከተማ ከመስመር ማስወጣት ማለት ነው፡፡ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር መጋጨት ነው፡፡ ይሄ ፓርክ አደጋ ላይ ከወደቀ ደግሞ አባያና ጫሞ ሃይቆች የመድረቅ ስጋት ያንዣብብ ባቸዋል፡፡ ስለዚህ የሚሰማም የሚያዳምጥም መፍትሄ መስጠት የሚችል አካል ከአቅማችን በላይ መሆኑን ተገንዝቦ መፍትሄ እንዲሰጠው በልመናም ጭምር ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ!
አቶ ካምቦ፡- እኔም አመሰግናለሁ !

ማህሌት አብዱል

Published in ኢኮኖሚ

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በቀጣዩ ወር አንድ ለአንድ በሚደረግ ስብሰባ ለመገናኘት ማቀዳቸውን ታዋቂው የአሜሪካ ጋዜጣ ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡ ይህ የትራምፕ እቅድ በአሜሪካና በሩሲያ መካከል የተፈጠረውን መካረር ቢያረግብም በኔቶ አጋሮች ውስጥ ውጥረቱን ያባብሰዋል ይላል ዘገባው፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕና ፕሬዚዳንት ፑቲን ቀደም ሲል በዓለም መሪዎች ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ሁለት ጊዜ ቢገናኙም፤ አሁኑ ይደረጋል የተባለው የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት በዓይነቱ የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባ ነው የሚሆነው፡፡ ስብሰባው የሚደረገው በተለይ በአሜሪካን ውስጥ በጣም አሳሳቢ ሁኔታዎች ባሉበት ወቅት ነው፡፡ ጉዳዩ ትኩረት የሚስበው በአሜሪካ የ«ሚድ ተርም» ምርጫ እንቅስቃሴ በስፋት በሚካሄድበና ሚስተር ትራምፕ ከሩሲያ ጋር በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ግንኙነት ነበራቸው፤ ራሽያ ጣልቃ ገብታለች የሚለውን ክስ የሚያጣራው ልዩ ምክር ቤቱ ምርመራውን በቀጠለበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ጋር ለመገናኘት ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳወ ቃቸውን የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ይገልጻሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በተለይም አደጋ ተደቅኖበት ከነበረው የአሜሪካና የሰሜን ኮርያ ፍጥጫ በኋላ ከሰሜን ኮርያው መሪ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን እንደ ዲፕሎማቲክ ድል አክብረውታል፡፡ በተጨባጭ ውጤት ደረጃ የተገኘው ጥቂት ቢሆንም፡፡
ሚስተር ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸው የሆኑትን ጆን አር ቦልተንን ወደ ሞስኮ የላኩ ሲሆን፤ እርሳቸውም ከፑቲን ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ሚስተር ቦልተን ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ከተወያዩ በኋላ ሁለቱ መሪዎች የሚያደርጉት ስብሰባ የትና መቼ እንደሚሆን በቅርቡ ይገለጻል ብለዋል፡፡ ሌሎች የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ሄሌሲንኪ ፊላንድ ከተማ የመጀመሪያዋ ዕጩ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ሚስተር ትራምፕ በኦቫል ኦፊስ ለሪፖርተሮች በሰጡት መግለጫ ከሩሲያና ቻይና እንዲሁም ከሁሉም ጋር መሆን በጣም ጥሩ ነገር ነው፤ ምናልባት በአውሮፓ ጉብኝቴ ከፑቲን ጋር ልንገናኝ እንችላለን ብለዋል፡፡
ሚስተር ትራምፕ የኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት) ስብሰባ ጉባኤን በብሩሰልስ ሐምሌ 11 እና 12 እንደሚሳተፉ ፕሮግራም ተይዟል፡፡ ቀጥሎም ብዙ የዘገየውን ጉብኝት በእንግሊዝ ያደርጋሉ፡፡ በአውሮፓ ጉዞአቸው ከሚስተር ፑቲን ጋር ይገናኛሉ የሚለው ግምት አይሏል፡፡
ይህን የመሰለው በከፍተኛ ደረጃ የሚደረግ ስብሰባ የሚያተኩረው በአሜሪካና ሩሲያ ግንኙነትና ተዛማጅነት ባላቸው ሁኔታዎች ላይ ሲሆን፤ የሶርያ ጉዳይና የጦር መሣሪያ ቁጥጥርንም እንደሚያካትት የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ሚስተር ትራምፕ ቀደም ሲል አጋሮቻቸው ከሆኑት ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳን ከመሳሰሉት ሀገራት ጋር በመጋጨታቸው ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር የሚያደርጉት ስብሰባ በአውሮፓ ሀገራ ዘንድ ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሯል፡፡
የአውሮፓ ባለሥልጣናት ይህ የትራምፕና የፑቲን ስብስባ የኔቶን ጉባኤ ጥላ ያጠላበታል ወይንም ዝቅ ያደርገዋል የሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ስብስቡ በቅርቡ በካናዳ ዋነኞቹ የኢንዱስትሪያል ፓወር የተባሉት በተገኙበት እንደተጠናቀቀው የግሩፕ 7 ስብሰባ እንደሆነው በቁጣና በምሬት ካበቃ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም ባይ ናቸው፡፡
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለኔቶ መግለጫ የሚሆን ጽሑፍ እያረቀቁ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ይህም በሕግ ላይ የተመረኮዘ ትዕዛዝን (rules based order) ጠቃሚነት መልሶ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን ሚስተር ትራምፕ ባለፈው ዓመት የኔቶ ዋና ጽሕፈት ቤት አዲሱ ቢሮ ሲመረቅ ባደረጉት ንግግር አንቀጽ 5 እንዳይጸድቅ የጋራ መከላከያ መርሕ የሚለውን ሰርዘውታል፡፡ አሁንም ተመሳሳይ ነገር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ባለሥልጣናቱ ይገልጻሉ፡፡
በምትኩ ሚስተር ትራምፕ በስብሰባው ላይ ሌሎች የኔቶ አባላት የሚደርስባቸውን የወታደራዊ ወጪዎች ተገቢ ድርሻ መሸፈን ባለመቻላቸው በኃይለ ቃል ተናግረዋል፡፡ በጣም በቅርቡም ከእነዚሁ ሀገራት ከጥቂቶቹ ጋር ንግድንና ስደተኞችን በተመለከተ ተጋጭተዋል፡፡ ከዩክሬን ጋር በተያያዘ ስላለው ውጥረት በሶርያ ጉዳይ እንዲሁም እና በ2016 ምርጫ ሩሲያ ጣልቃ ገብታለች በሚለው ክስ ግትር በሆነ አቋም ሚስተር ፑቲንን መውቀስን ተቃውመዋል፡፡
የሚስተር ፑቲን ረዳት የሆነው ዩሪ ኡሻኮቭ የትራምፕ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የሆኑት ሚስተር ቦልተን በአጭሩ የምርጫውን ጉዳይ በተመለከተ ለሩሲያ ባለሥልጣናት ማብራሪያ መስጠታቸው ገልጿል፡፡ ሚስተር ኡሻኮቭ ግልጽ በሆነ ሁኔታ የሩሲያ መንግሥት በአሜሪካው ምርጫ ሂደት ጣልቃ አልገባም፤አይገባምም ማለታቸውም ተጠቅሷል፡፡
በመጋቢት ወር ፕሬዚዳንት ፑቲን በሀገራቸው ሩሲያ በተደረገው የምርጫ ውድድር ዳግም በማሸነፋቸው እንኳን ደስ አለዎት ለማለት ሚስተር ትራምፕ ስልክ ከደወሉላቸው ጊዜ ጀምሮ ከሚስተር ፑቲን ጋር ለመሰብሰብ እቅድ ነበራቸው ተብሏል፡፡ ፑቲን ዳግም ያሸነፉበትን የሩሲያ ምርጫ በምዕራቡ ዓለም በስፋት እውነተኛ ያልሆነ ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ ሚስተር ትራምፕ ሚስተር ፑቲን ኋይት ሀውስን መጎብኘት ይችላሉ የሚል ሀሳብም ያነሳሉ፡፡ ይህም ከ2005 (እአአ) ጀምሮ የሩሲያ መሪ አድርጎት የማያውቀው ነው፡፡
አንዳንድ የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ይህን ዓይነቱን የትራምፕ ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡ የሚስተር ትራምፕ የፖለቲካ አጋሮች ሩሲያ በ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች፤ ከትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ጋር ይገናኛል በሚል እየተደረገ ያለውን ምርመራና ማጣራት መሠረት አድርገው ነው ሚስተር ትራምፕ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን አሜሪካንን መጎብኘት ይችላሉ የሚለውን ሃሳባቸውን የሚቃወሙት፡፡
የሚስተር ትራምፕና የሚስተር ፑቲን ስብሰባ ለሁለቱ ሰዎች ጥቂትና ቀላል የሆነ የዲፕሎማቲክ መሻሻል እርምጃዎችን ሊያስቆጥር ይችላል፡፡ ፕሬዚዳንቶቹ በጋራ መግለጫቸው አለፍ ያሉ ደረጃዎችን በማስመር ሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን እንዲያሻሽሉ በዓለም አቀፉ መድረክም ጥቂት የጋራ እርምጃ ለመውሰድ ሊስማሙ ይችላሉ ይላል ሚስተር ኡሻኮቭ፡፡
የክሬምሊን የውጭ ፖሊሲ አማካሪ የሆነው ሰርጌይ ካራጋኖቭ ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች አሁን እየተደረገ ባለው በሶርያ ጉዳይ ትብብራቸውን ሕጋዊ ሊያደርጉ እንዲሁም የስትራቴጂክ ጦር መሣሪያዎችን ስምምነት ሊያራዝሙ ወይንም ሊያሻሽሉ ይችላሉ ይላል፡፡
መሠረታዊ የሚባል የተለየ ለውጥ የለም የሚለው ሚስተር ካራጋኖቭ የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ በሀገራቱ መካከል ያሉትን ግንኙነቶች አሁን ካለው አደገኛ ከሆነ ሁኔታ በማላቀቅ በሰለጠነ መንገድ የማድረግ ሂደትን እንዲኖርም ያደርጋል ብሏል፡፡
ሚካኤል መክፋውል በሩሲያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩ ሲሆን ስለሌላው ወገን ያለውን የተዛባ መረዳት ለማስወገድ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ የሚደረገውን ስብሰባ እንደሚደግፉ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን ሚስተር ትራምፕ ለስብሰባው ተጨባጭ የሆኑ ግቦችን ይዘው ስለመምጣታቸው ይጠይቃሉ፡፡ ለምሳሌም ስለ ጦር መሣሪያዎች አዲስ ጅምር ስምምነትና ድርድርን በተመለከተ፡፡
ትራምፕ ከፑቲን ጋር ባላቸው ግንኙነት የማመንና የምሕረት ጉዳይ ውስጥ በመግባት የአሜሪካንን ብሔራዊ ጥቅም የማያስከብር ጉዳይ እንዳይፈጠር እሰጋለሁ ብለዋል፡፡ ማክፉኔል ትራምፕ ለኪም ጆንግ ኢል እንዳደረጉት ለፑቲንም ክምር ውደሳ ውስጥ ከገቡ ይሄ ለፑቲን ግዙፍ ድል ነው፡፡ ፑቲን የሚፈልገው ይሄንን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንግሊዝ ትራምፕ ያልተጠበቀ ስብሰባ ከፑቱን ጋር ለማድረግ በመወሰናቸው ክፉኛ መቆጣቷን ታዋቂው የእንግሊዝ ጋዜጣ ዘ ጋርድያን ዘግቧል፡፡ የእንግሊዝ ዲፕሎማቶች የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ከራሽያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር አውሮፓን ሊተዉ ይችላሉ የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡ ሰዎች የዶናልድ ትራምፕ ጥንካሬ ከተለመደው ውጪ ማሰባቸው ነው ይላሉ፡፡ ይሄ ትክክል አለመሆኑን ከአሜሪካን ፕሬዚዳንቶች ጋር ለበርካታ አስርት ዓመታት የሰሩ ቀደምት የእንግሊዝ ዲፕሎማት መናገራቸውን ዘ ጋርድያን በዘገባው አስፍሯል፡፡

ወንድወሰን መኮንን

Published in ዓለም አቀፍ
Thursday, 05 July 2018 22:04

የቀን ጅቦች የትም አሉ

በየዕለቱ በፍጥነት የሚለዋወጠው የፖለቲካችን ሁኔታ በመሰረታዊ ለውጦች እየታጀበ ይገኛል፡፡ ለመጣው ለውጥና ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም እንዲሁም ለተፈጠረውም ሀገራዊ መግባባት የኢሕአዴግ ጥልቅ ተሀድሶ የድርሻውን አበርክቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድም የመሪነት ሚናውን በብቃት በመወጣት ከጎረቤት አገራት ጋር ሰላም ለመፍጠር ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር፤ ለጉብኝት ሲሄዱ በተለያየ ምክንያት ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲፈቱ ማድረጋቸው ለዜጎች የተሰጠውን ክብር ያመላከተ ነው፡፡
በውጭ ሀገራት በፖለቲካ ስደት የሚገኙ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች የጠብመንጃ ትግል ውስጥ የነበሩትንም ጨምሮ ወደሀገራቸው ገብተው በሰላም እንዲኖሩ፣ እንዲሠሩና ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲያራምዱ እንዲሁም አላማቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያራምዱ የተመቻቸው ዕድል የኢህአዴግ የተሀድሶ ውጤት ነው፡፡ በውጭ የሚገኙ የተለያዩ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ተቃዋሚ ሚዲያዎች ወደሀገራቸው ገብተው እንዲሠሩ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ይህም በሀገራችን የሰለጠነ ዴሞክራሲያው ባሕል እንዲያብብና እንዲገነባ ኢሕአዴግ በጥልቅ ገምግሞ በወሰነው ውሳኔ መሰረት የተከናወነ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በመሪነት በቆዩባቸው አጭር ጊዜያት በሀገር ውስጥ የሚጠቀሱ ለውጦችን ያስከተሉ፤ ሰላምና መረጋጋትን ያመጡ፤ ኢትዮጵያዊ መተሳሰብ መከባበርና አንድነትን ያጎለብቱ ሥራዎች ሠርተዋል፡፡ ሕዝቡም የመከፋፈልንና የመበታተን ስጋትን ሙሉ በሙሉ አውግዞ በመደመር የለውጡን ሂደት ለማስቀጠል በአንድነት ጸንቶ ቆሟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠል በርካታ ሕዝብ በራሱ ተነሳሽነት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም አደባባይ ወጥቶ ለመሪው ያለውን ድጋፍና አድናቆት ገልጿል፡፡ በዚያው ስነስርዓት ላይ የቦንብ አደጋ ለማድረስ በጥናትና እቅድ ተቀነባብሮ የነበረው ሴራ በዜጎች ርብርብና መስዋእትነት ከሽፏል፡፡ ብዙዎች በቦምብ ፍንዳታው ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የተወጠነ መሆኑን ሕዝቡ በሚገባ ተረድቶታል፡፡
ድርጊቱ በምርመራ እየተጣራ ሲሆን፤ ተጠርጣሪ ግለሰቦች ለአደጋው መፈጸም ክፍተት ፈጥረዋል የተባሉ የፖሊስ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየት ጀምሯል፡፡ በየትኛው መልኩ ቢሆን የተጀመረውን ሕዝባዊ ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ማቆምም ሆነ መግታት አይቻልም፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ የሚያደረጉት ተመሳሳይ ታላላቅ ሕዝባዊ ሰልፎች በባሕርዳር የተደረገውን በሺዎች ያሳተፈ ግዙፍ ሕዝባዊ ሰልፎች ጨምሮ በክልሉ ውስጥም በሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድም ለሕዝቡ ያላቸውን አክብሮትና ድጋፍ አስተላልፈዋል፡፡ የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ እየተራወጡ ያሉት ኃይሎች ዛሬም ከሴራቸው አልታቀቡም፡፡ ሕዝቡ ነቅቶ እንዲጠብቅና እንዲከላከል መንግሥት ጥሪ አስተላልፏል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ፀጉረ ልውጥ ሰዎች ሰርገው በመግባት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሩጫ ላይ መሆናቸው ስለታወቀ መላው ዜጋ እንግዳ ሰዎችን በአካባቢው ሲያይ ነቅቶ እንዲከታተል ጉዳዩንም ለጸጥታ አካላት ፈጥኖ እንዲያሳውቅ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን፤ ይህን አገራዊ ግዴታ መወጣት ለውጡን ለማስቀጠል ጉልህ ሚና ያበረክታል፡፡
በአገሪቱ ትርምስ የመፍጠር ሴራና ደባ የሚከናወነው በሀብት ዘረፋና በሙስና ተሰማርቶ የነበረውና ተጠያቂነት ይመጣብኛል ባለው አካል እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚያ በፊት ሀገር ላተራምስ፤ ሕዝቡንም በጎሳ በሃይማኖት እርስ በእርስ በማጋጨት በአራቱም ማእዘናት እሳት በመለኮስ ሀገሪቱን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ መክተት አለብኝ ብሎ የወሰነ አካል ርዝራዥ አሁንም እንደሚኖር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እነዚህን ትርምሱ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች የቀን ጅቦች ያሏቸው ሲሆን፤ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተሰገሰጉ የተፈጠሩበትንና የተወለዱበትን ሕዝብ የማይወክሉ ናቸው፡፡ በተለይ ድርጅታቸውና መንግሥት ለሕዝብ እንዲሠሩ የሰጣቸውን የኃላፊነት ወንበር በመጠቀም በዘረፋ ውስጥ ተሰማርተው የኖሩ ሕገወጥ ሀብት ያካባቱ ሰዎች የኢሕአዴግ አባል ድርጅት በሆኑት ብአዴን፣ኦሕዴድ፣ ደኢህዴንና ሕውሐት ውስጥ የነበሩ ግለሰቦችን ያካተተ ነው፡፡ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጀምሮ በየደረጃው እስከ ዝቅተኛው ኃላፊነት ድረስ በመረብ የተሳሰረውን በቡድን የደራጀ ኃይል ይመለከታል፡፡
ለዚህ ነው የቀን ጅቦቹ ሕዝብን አይወክሉም፤ በግለሰቦች ወንጀልና ጥፋት ሕዝብ ስሙ ሊነሳ በጅምላ ሊወነጀል አይገባም የምንለው፡፡ የቀን ጅቦች በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ አሉ፡፡ የተፈጥሮው ጅብ በሁሉም ክልሎች እንዳለ ሁሉ፤ በዘራፊነትና በበልቶ አይጠግቤነት የሚታወቁት የቀን ጅቦችም በሁሉም ክልል ይገኛሉ፡፡ ይህ በውል ሊታወቅ ጥንቃቄ ሊደረግበትም የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
በጅምላ መወንጀል በስሜታዊነት ጥላቻ ውስጥ በመዘፈቅ መኮነን ሊቆም ይገባዋል፡፡ ለሀገር የለፉ የደከሙ ዛሬ ለተደረሰበት ልማትና ዕድገት ሳይታክቱ የሠሩ ሰዎችን ማመስገን ድካማቸውን መሬት አለመጣል ጥፋተኞችን እንደግለሰብነታቸው በተጨባጭ ማስረጃ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት መንግሥት በጥንቃቄ እየሠራ ይገኛል፡፡
በጥላቻ ስሜት ተዘፍቀው በየሶሾል ሚዲያው የከፋ የስም ማጥፋትና የዘር ጥላቻ የሚረጩ ግለሰቦች ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና ጥፋት እንዲከሰት ለማድረግ በመሮጥ የመደመርን፣ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የሰላምና የይቅርታ መንፈስ የሀገራዊ መቻቻልን መልካም ጅምር ከማደፍረስ ቢታቀቡ ይመረጣል፡፡ የመደመር መንፈስ ጥላቻን በቀልን ጥፋትን የሀሰት ውንጀላን በጎሳና በዘር ላይ የሚደረግ ዘመቻና ማነሳሳትን አያስተናግድም፡፡ አይቀበልም፡፡
ከጥንትም ሆነ ከቅርቡ አስከፊ ታሪካችን በጠላትነትና በጥላቻ ከመተያየት፣ ከመጠፋፋት፣ ከመባላላት፣ ከመናቆር፣ ከመገዳደል ወጥተንና ተላቀን በፍቅር፣ በሰላም፣ በይቅርታ ተደምረን ሀገራችንን በአዲስ መንፈስ በጋራ እንለውጣት፣ እንገንባት፣ ተሳስበን፣ ተዋደን፣ ተከባብረን እናሳድጋት በሰላም እንኑር ነው የመደመር መንፈስ መርሕ፡፡ ዛሬም ጥላቻን መከፋፈልን የዘረኝነትና የጎጠኝነት እኩይ በሽታን የሚያራምዱ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና ለማጣላት የሚንቀሳቀሱ የሀሰት ፈጠራ ወሬ የሚነዙ ከሰላምና ከአብሮነት ይልቅ በቀል አግተው ለጥፋት የሚያሴሩት ሁሉ ከመደመር ሂደት ውጪ ናቸው፡፡
የአለፈውን ሁሉ እንርሳ በአዲስ መንፈስ እንነሳ ማለት ቂም እያሰላን ቁስሉን እያከክን መቆዘም አይደለም፡፡ በመደመር መንፈስ ታድመን ወደፊት ሀገራዊ ተስፋን ሰንቀን ነገን ብሩህ አድርገን ማየትና ለዚህም መሥራት መረባረብ መትጋት ማለት ነው፡፡ ኋላቀር ከሆነ ትውልድና ሀገርን ከገደለ አስተሳሰብ በመላቀቅ ወደፊት መትመም ነው መደመር፡፡ መልሶ ጨለማ ውስጥ ከሚከት አስከፊ አስተሳሰብ መፅዳትም ነው፡፡ መደመርን የሚያደናቀፍ ከመደመር የሚቀንስ የመደመርም እንቅፋት የሆነ እሳቤ እስከወዲያኛው እንደ አረም ተነቅሎ ሊጠፋ ይገባል፡፡
የዜጎች ዴሞክራሲዊ መብቶች እንዲከበሩ የፖለቲካ ምሕዳሩ እንዲሰፋ ኢሕአዴግ እየሠራ ያለው የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ነው፡፡ ይህን በየደረጃው ለመከወን ሕግና ስርዓት የግድ መከበር አለበት፡፡ የለውጡ ሂደት ወደፊት እንዲራመድ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲሸጋገር የሚያደርገው ሕዝብ ነው፡፡ በየሰፈሩ በየመንደሩ በሥራ ቦታ በአደባባዮች በየትኛውም ቦታ ሕግና ስርዓት ሲከበር ለውጡ መሬት የሚረግጠው፡፡
በስፋት የጥበቃዎች መላላት፣ ጸጥታ አስከባሪዎች ሕገወጥ ድርጊት ዘረፋና የመሳሰለውን እያዩ እንዳላዩ ማለፍ፣ የነጣቂዎችና የማጅራት መቺዎች መበራከት፣ በአንዳንድ ቦታዎች ዘረፋ ማካሄድ በስፋት እየታየ ሲሆን፤ መንግሥት የዜጎቹን ሕይወትና ንብረት የመጠበቅ ግዴታና ኃላፊነቱን እንደማይወጣ ተደርጎ እንዲታይ ሆን ተብሎ እየተሠራ ያለውን አሻጥር ሕዝብ ተረድቶ እርስበእርሱ በመተባበር በየአካባቢው ጥበቃውን ማጠናከር፣ ወንጀለኞችንም አድኖ ለሕግ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ የቀን ጅቦቹ አንዱ ሴራ ይኸው ነውና ሕዝቡ ሊያከሽፈው ይገባል፡፡ የለውጡ ሂደት ጠባቂና ከግብ አድራሹ ሕዝብ ነው፡፡ ኢሕእዴግ የጀመረውን የስኬት ጉዞ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

መሐመድ አማን 

Published in አጀንዳ

በኢትዮጵያ የለውጥ አየር እየነፈሰ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲተያይ በሁከት ይናጡ በነበሩ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ ወጥቶ ለመግባት ችግር የሆነባቸው ስፍራዎች ዛሬ ተረጋግተው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ገብተዋል፡፡ መንገዶች፣ ንግድ ቤቶችና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በየሰበቡ አይዘጉም፡፡
የለውጡ መሪ በመሆንም ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ወደ መንበሩ ከመጡ ወዲህ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ለ17 ቀናት ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች የራሳቸውን ጥበብና ክህሎት በማከል እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ በዚህም በአገሪቱ የተጠራቀሙ ብሶቶችን የፈጠሩ እክሎችን ጭምር እየፈቱ ነው፡፡ ይቅርታና ፍቅር የማይሽሯቸው ጠባሳዎች እንደሌሉ፤ መደመር አገሪቱ ከተዘፈቀችበት አረንቋ የሚያወጣ ብቸኛ አማራጭ መሆኑን በተደጋጋሚ በመናገር ጽኑ የህዝብ ተቀባይነትና ፍቅር አፍርተዋል፡፡
ለውጡ የአብዛኛው ህብረተሰብ ፍላጎት መገለጫ ቢሆንም፤ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ካለው የበረታ ምኞትም በመላው አገሪቱ አደባባይ በመውጣት በተቸረው የምስጋና መርሐ ግብር ተግባራዊ ምላሽ ቢያገኝም፤ በተለያዩ አካላት የሚረጩ መርዘኛ የፍረጃ ዝንባሌዎች ግልጽ ስጋት እንደሚደቅኑ ደግሞ ሊታወቅ ይገባል፡፡
በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት ተከስተው በነበሩ ችግሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰቦች፣ ተቋማትና አካላት ይኖራሉ፡፡ ሁሉም በተሳሳተ የአልጠግብ ባይነት ስሜት እራሳቸውንና በዙሪያቸው የሚገኙ ጥቂት ሰዎችን ተጠቃሚ አድርገው ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና የወጡበትን ማህበረተሰብ ይወክላሉ ማለት ግን አይደለም፡፡ ለእዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ‹‹ለውጥን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበርታ›› በሚል መርህ ለድጋፍ ሰልፍ ለወጣው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ‹‹ግለሰቦችን ከህዝብ እንለይ፤ እሾኩን ከጽጌረዳ እንነጥል፤ ዓይጥ በበላ ዳዋ አይመታ፤ በአንድ ጠማማ ዛፍ ምክንያት ደኑ አይለቅ፤ ከይቅርታ የተሻለ ማሸነፊያ መንገድ አለመኖሩን በየዕለቱ አንዘንጋ›› በማለት መልዕክት ያስተላለፉት፡፡
በእርግጥም በጥቂቶች ጥፋት ሌሎችን ባልተጨበጠ ምክንያት መፈረጁ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ አዝማሚያ ያጠፋን ብቻ በመለየት በእኩይ ተግባሩ ለመጠየቅ የሚስችለው አካሄድ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳደር ጅምር የለውጥ እንቅስቃሴውን ይገታዋል፡፡ አጥፊዎችን በቅጡ ሣይለይ የሚንጸባረቅ ጥላቻ እያደረ በሰዎች አዕምሮ የሚፈጥረው መጥፎ ስሜት ወደ ብቀላ ማምራቱ አይቀርም፡፡ ይህም በአንድ ጠማማ ዛፍ ምክንያት ደኑን ማጥፋት ነው እንደተባለው፤ በጥቂት እኩይ ሰዎች የተነሳ ብዙ ንጹሐንን ባልተገባ ፍረጃ ከማጥቃት ዝንባሌ ጋር ተመሳሳይ ነውና አጽንኦት ተሰጥቶት ሊገታ ይገባል፡፡
ማህበራዊ ሚዲያዎች ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ተቀጣጥሎ ለነበረው የለውጥ ፍላጎት አዎንታዊ ሚና የመጫወታቸውን ያህል፤ ባልተጨበጠ መረጃና በተሳሳተ የትግል ስልት ልጆቻችን ከጉያችን እንዲነጠሉ አሉታዊ ሚና የተጫወቱ አልነበሩም ማለት አይቻልም፡፡ እያንሰራራ የነበረው ኢኮኖሚያችንም ወደ መቀመቅ እንዲወርድ ተግተው የሠሩም ነበሩ፡፡ በህዝቦች መካለል ጥላቻና ጥርጣሬ እንዲሰፍን ሙከራ ማድረጋቸውም የሚዘነጋ ተግባር አይደለም፡፡
ዛሬ ያለፈውን ቁርሾ ትተን በይቅርታ ታክመን በአዲስ መንፈስ አገራችንን በጋራ እንገንባ ብለን በተነሳንበት ወቅትም ባልተጨበጠ መረጃ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፤ መተላለቅን የሚጋብዙ መልዕክቶች መታየታቸው አልቀረም፡፡ ይህ ለአዲሱ ምዕራፍ የማይመጥን የማሕበራዊ ሚድያ ዘመቻ በቃህ ሊባል ይገባዋል፡፡ ህብረተሰቡም የለውጡን አቅጣጫ ለማስቀየር የተጀመረ አዲስ መላ መሆኑን በመንቃት አትኩሮት መንፈግ ፣ ወይም አፍራሽነቱን የሚቃወም ምላሽ መስጠት አለበት፡፡
በአገሪቱ ቀደም ሲል በነበሩ ችግሮች እንዲሁም በቅርቡ ከተፈጠሩ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ አፍራሽ ሚና የተጫወቱ፣አሁንም በዚህ ተግባር የዘለቁ መኖራቸው አይካድም፡፡ የህግ የበላይነት የአንድ አገር ህልውና በመሆኑ በተጨባጭ መረጃ ችግር የፈጠሩ የሚጠየቁበት ስርዓት ተጠናክሮ መቀጠሉን ሁሉም ሰላም ወዳድ ዜጋ ይፈልገዋል፡፡ ለእዚህም ትብብሩና አንድነቱ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቅርቡ ምክር ቤት ቀርበው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት እንደቀድሞው በጥርጣሬ ይዞ ለማጣራት ከመሞከር ተጨባጭ ማስረጃ በማሰባሰብ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

በየደረጃው የሚገኘው የህዝብ ግንኙነት መዋቅር ትክክለኛና ፈጣን መረጃዎችን ከመስጠት አንፃር አሁንም ውስንነቶች ያሉበት መሆኑን በቅርቡ በቢሾፍቱ ከተማ ለህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ ችግሩ የሚመነጨው ባለሙያዎቹ ከተመለመሉበት መንገድና ከሚሰጣቸው ተልዕኮ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

በሪፖርተር ጋዜጣ የፖለቲካ ጉዳዮች አዘጋጅ አቶ ዮሐንስ አንበርብር እንደሚናገሩት፤ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች በየተቋሙ የሚመደቡበት ዋነኛ ምክንያት የመረጃ ነፃነት አዋጁ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውልና መረጃ በማዕከል ለማስተላለፍ እንዲረዳ በማሰብ ነው፡፡ ይሁንና በአንዳንድ የመንግስት ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ለዘርፉ ያላቸው ቅርበት ሳይጠናና አግባብነት ያለው የትምህርት ዝግጅት እንዳላቸው ሳይፈተሽ ተመድበዋል፡፡ ይልቁንም ለፖለቲካው ታማኝና የስርዓቱ አቀንቃኝ መሆናቸውን ብቻ ታሳቢ በማድረግ በቦታው ተቀምጠዋል፡፡ ይህም አብዛኞቹ ባለሙያዎች ውግንናቸው ለህዝብ ሳይሆን ለፖለቲካው ወይም ለተመደቡለት ተቋምና ኃላፊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በዚህም ምክንያት ጥቂት የማይባሉት ባለሙያዎች በወቅቱና በአግባቡ መረጃ አያስተላልፉም፡፡ «በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መጠመድ፣ መረጃ መስጠት ማለት የመንግስትን እንከን ማጋለጥ የሚመስላቸው በመኖራቸው መልካም መልካሙን ብቻ የመናገር አባዜ የተጠናወታቸው ናቸው» ይላሉ፡፡ የሚሰጡትም አብዛኛው መረጃ ከእውነታው የራቀ፣ የተጋነነና የተዛባ በመሆኑ የህዝብን አመኔታ ያሳጣቸው መሆኑን አቶ ዮሐንስ ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ከራሳቸውና ከሚሰሩበት ተቋም ባሻገር ህዝብ በመንግስት ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረውና ቅሬታ እንዲፈጠርበት አድርጓል ባይ ናቸው፡፡
ለዚህም አብነት አድርገው የሚጠቅሱት ጠፋ ስለተባለው ኮንዶሚኒየም ህንፃ ጉዳይ ሲሆን፤ ቦታው ለግንባታ አመቺ ባለመሆኑ ምክንያት ግንባታ ባለመከናወኑ የህንፃዎቹ ቁጥር ሊያንስ መቻሉ ቢታወቅም ይህንን መረጃ በጊዜው ተከታትሎ ለህዝብ ማስተላለፍ ባለመቻሉ አሁንም ድረስ ህዝቡ በግንባታውም ሆነ በእጣ ማስተላለፉ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት አድርጓል፡፡
የህዝብ ግንኙነት ዋነኛ ሚና በተቋም ወይም በመንግስትና በመገናኛ ብዙሃን መካከል ድልድይ ሆኖ ማገልገል ቢሆንም አንዳንዶቹ ይህንን ሚናቸውን የዘነጉ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ «እነርሱ የተመደቡበት ኃላፊነት መንግስትና ተቋማቸውን ማስተዋወቅና ገፅታ መገንባት ብቻ አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡ በእኔ እምነት ግን እነዚህ ሰዎች የመንግስትንም ችግር የማጋለጥ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ችግሩን አጋለጡ ማለት ተቋሙ እንዲስተካከል አገዙት ማለትም ጭምር ነው» ይላሉ፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ከበላይ አመራሮች ሊደርስባቸው የሚችለውን ተፅእኖ መቋቋም የሚጠበቅባቸው መሆኑን በማስረዳት፡፡
በሌላ በኩልም ስለተቋማቸው እንኳ በቂ እውቀት የሌላቸው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች መኖራቸውን አቶ ዮሐንስ ይጠቅሳሉ፡፡« የየትኛውም ተቋም የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የማኔጅመንት አባል ይሆናል ተብሎ ቢታመንም በገዛ ተቋማቸው ላይ እየተፈፀመ ስላለው ጉዳይ ተገቢ መረጃ የላቸውም። ከእነሱ ቀድሞም መረጃው ጋዜጠኛው ጋር የሚደርስበት ሁኔታም አለ» ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹም የራሳቸውን ሚና ያለምንም አጥጋቢ መረጃ ማጉላት ስለሚፈልጉም የሚመለከተውን ባለሙያ ለማገናኘት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይህም ከመገናኛ ብዙሃን ጋር የሻከረ ግንኙነት እንዲኖራቸው ያደረጋቸው መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ውስጥ የህዝብ ግንኙነትና የማስታወቂያ ክፍል መምህርና አስተባባሪ አቶ መስፍን ቦጋለ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የህዝብ ግንኙነት ስራ ራሱን የቻለ የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ ሙያ በመሆኑ ደግሞ የራሱ ስነምግባርና ኃላፊነትን ጠብቆ መስራት ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ በአገሪቱ በቀደሙት ዓመታት በሙያ ደረጃ ስልጠና የማይሰጥ በመሆኑና መናገር የሚችል ሁሉ ይህንን ስራ ይሰራል የሚል አስተሳሰብ በመስረፁ ሙያው የተንጋደደ አካሄድን እንዲከተል አድርጎታል፡፡
በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግስት በየተቋሙ የመደባቸው ባለሙያዎች የፖለቲካ ተልዕኮ ብቻ ይዘው ስለሚሰለፉ ለስርዓቱ ታማኝነታቸውን የሚያረጋግጡት የፕሮፖጋንዳ ወሬዎችን በማሰራጨት እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉትም በአስተሳሰብ ከማሸነፍ ይልቅ በኃይል የራሳቸውን አላማ ለማስፈፀም የሚሞክሩት የተዛባ መረጃ በመስጠትም ጭምር እንደሆነ ነው አቶ መስፍን የሚያመለክቱት፡፡
የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በህዝብና በመንግስት መካከል ለተፈጠረው ቁርሾ የጎላሚ ሚና እንደነበራቸው አቶ ዮሐንስ አበክረው ይናገራሉ፡፡ ይህ ሲሆንም ተጠያቂነት ያለው አሰራር ባለመዘርጋቱ ችግሩ መባባሱን ነው የሚናገሩት፡፡ «በተቋምም ሆነ በአገር ደረጃ ለጠፋው ነገርና ለሀብት ብክነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ባጠፉት ልክ ደግሞ የሚጠይቃቸው አሰራር ያለመዘርጋቱ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል» ሲሉ ይገልፃሉ፡፡ ይህም ድምር ውጤቱ ሚናቸው የተዛባ እንዲሆን አድርጎታልም ባይ ናቸው፡፡
እንደ አቶ ዮሐንስ ማብራሪያ፤ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎቹ በመንግስትና በህዝብ መካከል ጥሩ ድልድይ መሆን የሚችሉት ፖለቲካን ሳይሆን ሙያውን በአግባቡ ጠንቅቀው የተገነዘቡ ሲሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ በዘርፉ ስርነቀል የሆነ ለውጥ ማምጣትን ይጠይቃል፡፡ በተለይም ያለውን አመለካከት መለወጥ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ትክክለኛና ተጨባጭ መረጃ በወቅቱ እንዲያስተላልፉም ተጠያቂነት ያለው አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በሹመኞች የሚደርስባቸውን ጫና ለመከላከል ደግሞ ቀጥታ ተጠሪነታቸው ለመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሊሆን ይገባል፡፡
የህዝብ ግንኙነት ሙያ በዘፈቀደ ማንም የሚዳክርበት አይደለም የሚሉት አቶ መስፍን በመንግስትና በህዝብ ወይም በተቋምና በህዝብ መካከል ድልድይ ሆኖ ከማገልገልም በላይ የላቀ ኃላፊነት ያለበት የተከበረ ሙያ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ መንግስትም ሆነ ተቋማት የተቋቋሙበትን አላማ እንዲሁም በገቡት ቃል መሰረት ካልሰሩ የማጋለጥም ጭምር ድርብ ኃላፊነት እንዳለበት በመጥቀስ፡፡ በአገሪቱ ያሉ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች እውነተኛውን መረጃ ማስተላለፍ ቢችሉ ኖሮ ህዝቡ በመንግስት ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ የመፍትሄ አካል በመሆን ከመንግስት ጎን ይሰለፍ እንደነበር ነው የሚያነሱት፡፡
መምህሩ የህዝብ ግንኙነት ስራ ወደ አንድ ጎን ያዘነበለ ሊሆን አይገባም፡፡ ግንኙነቱም የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ መረጃው ሲሰጥም ልክ እንደመድኃኒት ሁሉ እንደየበሽታው ታይቶና ዲፕሎማሲያዊ መንገድን በተከተለ መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ መሆን ባለመቻሉ ነው ሚናቸው በአወንታዊ መንገድ መጠቀስ ያልቻለው ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ዋቢ አድርገው የሚጠቅሱት ላለፉት 27 ዓመታት በኃይል መረጃዎችን በህዝብ ላይ ለመጫን ቢሞከርም የነቃና ተሳታፊ ማህበረሰብ መፍጠር አለመቻሉን ሲሆን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ያለውን ችግር አፍረጥርጦ በማውጣት ለማረም ዝግጁ የሆነ አመራር በመምጣቱ ህዝቡ ምንም ሳያቅማማ ከጎኑ ለመቆም መወሰኑን ነው፡፡
እንደ አቶ መስፍን ማብራሪያ፤ በአገሪቱ የህዝብ ግንኙነት ስራ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት ካስፈለገ ባለሙያዎቹ የሙያውን ስነምግባር በሚጠይቀው መልኩ ሃቀኛ፣ ታዓማኒና ሚዛናዊ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በክህሎት የታገዘ እውቀት ማካበት ያሻል፡፡ በትምህርት ቤት ከሚገኘው እውቀትና ክህሎት ባሻገርም የሰለጠኑትን አገራት ተሞክሮ መቅሰም ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም በየተቋሙ የሚመደቡትም ባለሙያዎች ይህንን መስፈርት ያሟሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ አሁን ያሉትም ቢሆን ከፕሮፖጋንዳና ከጠበቃነት ሚናቸው ሊወጡ ይገባል፡፡ ይህ ሲሆንም ነው መንግስትም ሆነ ተቋማት የህዝብን ልብ ማሸነፍና ለአላማ በአንድ ድምፅ ማሰለፍ የሚችሉት፡፡
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው የመረጃ ነፃነት አዋጁ በተጨባጭ ተግባራዊ ይሆን ዘንዳ እንዲሁም መረጃ በማዕከል ደረጃ መስጠት ያስችል ዘንድ በ2000 ዓ.ም ከክልሎች በወረዳ በተለያየ አመራርነት ላይ የነበሩና በተለያየ የትምህርት ዘርፍ የተመረቁ ከ600 በላይ የሚሆኑ ባለሙያዎች በሶስት ወራት በፖሊሲና በህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሰልጥነው በ2001 ዓ.ም በህዝብ ግንኙነት ባለሙያነትና በኃላፊነት በመንግስት ተቋማትና በመገናኛ ብዙኃን ላይ እንዲመደቡ ተደርጓል፡፡
የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አስተሳሰብና አሰራር ስርነቀል በሆነ መልኩ መለወጥ ካልተቻለ በተለይም በአሁኑ ወቅት ለአገር አንድነት ለለውጥ የተዘጋጀውን ህዝብ መንፈስ በማቀዝቀዝ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ብሎም በመንግስት ላይ ያለው ጥርጣሬ ያይላል፡፡ በሃሳብ ደረጃ መግባባትና ለለውጥ መስራት እንቅፋት ይገጥመዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን የመረጃ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው ተአማኒ ዘገባ ለማቅረብ ይቸገራሉ፡፡ ሚናቸውን ለመወጣት እክል ያጋጥማቸዋል፡፡ ይህም በህዝብና በመንግስት መካከል መራራቅ ይፈጥራል፡፡

ዜና ትንታኔ
ማህሌት አብዱል

 

Published in የሀገር ውስጥ

- ለ27 ዓመታት ተለያይቶ የነበረው  ሲኖዶስ ዕርቀ ሰላም ሊያወርድ ነው

አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሐምሌ ወር ወደ አሜሪካ በማቅናት ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚመክሩና ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያና የአሜሪካ በሚል ተለያይቶ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ዕርቀ ሰላም ሊያወርድ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡ 

ሐምሌ 21 እና 22 ቀን 2010 ዓ.ም በአሜሪካ ዋሽንግተንና ሎስአንጀለስ ‹‹ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ›› በሚል መሪ ሃሳብ የሚደረገውንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚገኙበትን ህዝባዊ ጉባዔ በተመለከተ ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ በመግለጫው ከጉባኤው ጎን ለጎን ዕርቀ ሰላሙን አስመልክቶ መድረክ እንደሚኖር ተመልክቷል፡፡
የኮሚቴው የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ አባል አቶ ብርሃን ተድላ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በአገራቸው ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተሳትፎ ዙሪያ ይወያያሉ፡፡ በቅድሚያ ግን በአሜሪካ የሚገኙትን የቅዱስ ሲኖዶስ ሰብሳቢ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስንና መቀመጫውን በእዚያ ያደረገውን የሲኖዶስ አባላት ያነጋግራሉ፡፡
ዕርቀ ሰላሙን የሚያደርግ ራሱን የቻለ አብይ ኮሚቴ መኖሩን ያመለከቱት አቶ ብርሃን፤ ጽህፈት ቤቱን በቤልጂየም ያደረገው ኮሚቴው የሚመራው በመላዕከ ህይወት ሀረገወይን ብርሃኑ እንደሆነና 23 የኮሚቴ አባላትንም እንደያዘ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው ቅርንጫፉም በልዑል ራስ መንገሻ ስዩም የሚመራ ሲሆን፤ ሰባት አባላት ይዟል፡፡
በሲኖዶሶቹ መካከል ዕርቅ መፈጸሙ ለአገር ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሚሆንና በይቅርታ ተምሳሌትነቱም እንደሚጠቀስ አቶ ብርሃን ገልፀዋል፡፡ ኮሚቴው በሁለቱም አገራት ያሉ ሲኖዶሶች እርቅ እንዲፈጽሙ ከዚህ ቀደምም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅት ትኩረት በመስጠት ከልዑካኑ ጋር የሚሄዱ ሶስት ብፁዓን አባቶች መወከላቸውን ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ በአሜሪካ ሶስት አባቶች የተመደቡ ሲሆን 30 በሚደርሱ አደራዳሪ ኮሚቴ አባላትም በመመራት በዋሽንግተን ዲሲ ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም ድርድሩ ይጀመራል፡፡
ዕርቀ ሰላሙን የሚያካሂደው ኮሚቴም እንደዚህ ቀደሙ በተለያዩ ምክንያቶች እንዳይሰናከል ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉና ለስኬቱም ቅድመ ዝግጅቶች ላለፉት ስድስት ወራት ሲሰራ መቆየቱን የኮሚቴው አባል አስታውቀዋል፡፡ ዕርቀ ሰላሙም የተሳካ እንዲሆን ህዝቡ በፀሎት እንዲደግፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- በጉጂና ጌድዮ ዞን ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ ስምንት መቶ ሺ ዜጎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡ 

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሣ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ለዜጎቹ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በተለይ ለእናቶችና ለሕፃናት የሚያስፈልገው አልሚ ምግብ፤ ለአዋቂዎችም የበቆሎ ዱቄትና ዘይት የሚቀርብ ሲሆን፤ ብርድ ልብስና ፍራሾችም ተሰራጭተዋል፡፡


እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፤ እስከ ቅርብ ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን ከአካባቢዎቹ የተፈናቀሉት ዜጎች እስከ 500 ሺ መሆናቸው ይገለጽ ነበር፤ ግጭቱ እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም አልፎ አልፎ በሁለቱም ወገን አካባቢ አነስተኛ ችግሮች ስለሚታዩና ወደ ፊት ግጭቶች ይኖራሉ በሚል የሚሰጉ ሰዎች ቀዬአቸውን እየለቀቁ በመምጣታቸው የተፈናቃዮች ቁጥር ስምንት መቶ ሺ ደርሷል፡፡ አብዛኛዎቹ ከምዕራብ ጉጂ ዞን የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ዜጎቹ በሁለት ስፍራ ተጠልለዋል፡፡


አቶ ምትኩ ለዜጎቹ ከሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ባሻገር፣ በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም እንዲቻል ግጭት የማስቆምና ዘላቂ ሰላም የማስፈን እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች የሚከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ሥራዎቹን ለማሳለጥ የሚያስችል አደረጃጀት ተፈጥሮ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ ወደ ትግበራ የገባ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በብሔራዊው ኮሚቴ ስር የተቋቋመ ስቲሪንግ ኮሚቴም እንዳለ ጠቅሰው፤ ሌሎች ባለድርሻ ተቋማትን የሚካትት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በተመሳሳይ ከክልል እስከ ወረዳ መዋቅር የተዘረጋ ሲሆን፤ በቅንጅት በመሥራት ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስና የድጋፍ ሥራው ይሠራል፡፡


በተፈጠረው ግጭት ንብረታቸው የጠፋ ዜጎችን በተመለከተ ዝርዝር ጥናት እንደሚሠራና የመልሶ ማቋቋሙ አካል እንደሚሆን የጠቀሱት አቶ ምትኩ፤ በፌዴራልና በክልል ያለውን ሀብት በማሰባሰብ በቅድሚ ለሰብዓዊ ድጋፍ ትኩረት መሠጠቱን አመልክተዋል፡፡ የውጭ አጋር አካላት በሙሉ አቅማቸው በድጋፉ ባይሳተፉም ጥረቶች በመደረጋቸው በቀጣይ በትብብር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡


አዋሳ ከተማ ተከስቶ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን በተመለከተ ድጋፍ እየተሰጠ እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በተለይ የክልሉ መንግሥት የአደጋ መከላከል መዋቅር በጉዳዩ ዙሪያ ተገቢውን ሥራ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡


የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የዴኢህዴን ሊቀመንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ሰሞኑን ከተጠቀሱት ስፍራዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመጠለያ ስፍራ ተገኝተው መጎብኘታቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በወቅቱ መንግሥትና ህዝብ ከተፈናቀሉ ወገኖች ጎን መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናችውን እንደተገነዘቡ በመግለጽ ‹‹በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እያደረጉ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ብለዋል፡፡


‹‹ተፈናቃዮች በአጭር ቀናት ውስጥ ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የደቡብ ክልል መንግሥት ከኦሮሚያ ክልልና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው›› ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ ህዝብ በህዝብ ላይ ይህን ችግር እንደማይፈጥር አመልክተው ፤ በህዝብ ስም የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ተገቢ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ወንድወሰን መኮንን

 

Published in የሀገር ውስጥ

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ግቢ ውስጥ ግንባታው ባልተጠናቀቀ ህንፃ የታችኛው ወለል ባለችው አነስተኛ አዳራሽ ውስጥ ህዝበ ሙስሊሙ በጋራ ተሰባስቧል፡፡ መቀመጫ ወንበር ያላገኙ ጥቂት የማይባሉ ተሳታፊዎች እዚህም እዚያም ቆመዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ኡለማ፣ፈትዋና ዳዕዋ ምክር ቤት ጋር በመቀናጀት በተዘጋጀው የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት ጉባኤ ላይ ለመታደም ነበር፡፡

በጉባኤው ታዋቂ ኡለማዎች ፣ወጣቶች ፣ሴቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣የመንግስት ተወካዮች፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣የመስኪድ ኢማሞችና የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመጡት ሼህ አሊ መሃመድ ከጉባኤው ተሳታፊዎች አንዱ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት፤ ጉባኤው ህዝበ ሙስሊሙ በሰላምና በፍቅር ጉዳይ ላይ በአንድነት እንዲሰለፉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ለዚህ አንድነትና ሀገራዊ መግባባት ትልቁን ሚና የወሰዱት ደግሞ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ አንድ ሲሆን አንድነታቸው ለሀገር ሰላምና ልማት ብሎም ለዓለምም መትረፍ ይችላል፡፡
በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የመጣውን ሀገራዊ መግባባት፣አንድነትና ፍቅርን ለማስቀጠል ታች ድረስ በመውረድ ማስተማር እንደሚገባ ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ረገድም የሃይማኖት አባቶችና ኡለማዎች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያመለክታሉ፡፡ ህዝቡም ይህን የመጣውን የፍቅርና የአንድነት ስሜት በመረዳት ለጋራ አንድነት በትብብር ሊሰራ ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ የእርዳታና ልማት ምክትል የዘርፍ ኃላፊ ሃጂ መሃሙድ ኡመር በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ ወቅቱ የሰላምና የፍቅር በመሆኑ ቁርዓንም የሚሰብከው አንድነትን እስከሆነ ድረስ ህዝበ ሙስሊሙም የተጀመረውን የአንድነት ጉዞ ለማጠናከር በጋራ ተሰባስቧል፡፡ በዚህ ረገድ ከአሁን ቀደም በህዝበ ሙስሊሙ መካከል የነበረውን ፍረጃና ቁርሾ በማስቀረት ሙስሊሙ በአንድነትና በፍቅር እንዲቀጥል ጉባኤው ትልቅ እገዛ ይኖረዋል፡፡
በሀገሪቱ የተጀመረውን የፍቅር፣የሰላምና የአንድነት ሂደት ለማስቀጠል ተከታታይነት ያላቸው በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚጠይቅ ይናገራሉ፡፡ ተከታታይነት ያላቸው ውይይቶች ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተው፤ «በየመስኪዱ ሰላምና ፍቅር እንዲሰበክ መደረግ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ ህዝበ ሙስሊሙ በሙሉ አሁን ላይ ለመጣው ለውጥና አንድነት በነቂስ ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል» ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሃመድ አሚን በበኩላቸው፤ አዲሱ የሀገሪቱ አመራር በመላው ሀገሪቱ የመግባባት፣ የመዋደድና የትብብር መንፈስ እንዲፈጠር ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የዚህ መንፈስ ዋነኛ ተዋንያን የሃይማኖት አባቶች በመሆናቸው ሀገራዊና ሃይማኖታዊ ግዴታ እንዳለባቸው በመገንዘብ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
አዲሶቹ አመራሮች በሀገሪቱ ላይ አንዣቦ የነበረው የሰላም እጦትና ስጋት ተገፎ የአንድነት፣የፍቅርና የመተባበር ጮራ እንዲፈነጥቅ በማድረጋቸው ዜጎች በነቂስ ወጥተው ምስጋና ማቅረባቸውንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸው፤ ምክር ቤቱ ይህን የህዝቡን የነቃ ተሳትፎ እንደሚደግፍ ያመለክታሉ፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና አብረዋቸው በትጋት እየሰሩ ላሉ ሁሉ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
ህዝቡን በመልካም ስነ ምግባር በማነፅ መልካም ዜጋ የመፍጠር ኃላፊነት በዋነኝነት በሃይማኖት አባቶችና በኡላማዎች ትከሻ ላይ ያረፈ በመሆኑ ይህንኑ ኃላፊነት ከእስካሁኑ በላቀ መልኩ እንዲወጡና በተለይም የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት የመመለሱንና የማጠናከሩን ተግባር እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡ በተለይም ዜጎች በዘር፣ በጎሳና በሃይማኖት ሳይከፋፈሉ በአንድነት ለሀገር ልማት ይተጉ ዘንድ ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፀሃፊ ሼህ አልፈዲል አሊ በበኩላቸው፤ በስራ ላይ ያለው የሙስሊም አመራር ቀደም ሲል የነበሩ የተቋሙን ችግሮች በመቅረፍ የሙስሊሙን ወንድማማችነትና አንድነት በማጠናከር የህዝበ ሙስሊሙን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባው ይገልፃሉ፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ እየታየ ያለውን ሰላምና ብሄራዊ መግባባት ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር ለመደገፍ ጉባኤው አስፈላጊ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
ጉባኤውን ከሌላው ጊዜ የሚለየውም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንዲሆኑ በመደረጉ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡ ተሳታፊዎቹ በተለይ ጠቅላይ ምክር ቤቱን ከማገዝ አንፃር የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንደሚወጡና ለተቋሙ ችግሮች የመፍትሄ አካል እንደሚሆኑም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

ዜና ሐተታ
አስናቀ ፀጋዬ

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ ፡- የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በህግ ታራሚዎች ላይ የሚፈጸሙ ችግሮችን ለመፍታትና ህገመንግስቱን ለማስከበር የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አመራሮችን ከኃላፊነት ማንሳቱን አስታወቀ፡፡

የፌዴራል አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የማረሚያ ቤት አስተዳደር ህገ መንግስታዊ ግዴታውን በተገቢው ሁኔታ መወጣት ባለመቻሉ ከማረም፣ ከማነፅ እንዲሁም ሰብአዊ መብቶችን ከማስከበር አኳያ ክፍተት በመኖሩ አመራሮቹ ከኃላፊነት ተነስተዋል፡፡
አቃቤ ህጉ እንዳሉት፤ አዲስ የተመደቡት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አመራሮች ዋና ትኩረቱ በዜጎች የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታትና በህገ መንግስቱ የሰፈሩትን የሰብአዊ መብቶችና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ህጎች ባከበረ መልኩ መፈፀም ነው፡፡ ከዚህ በፊት ህግ የጣሱ አካላት ማጣራት እየተደረገባቸው ወደ ፍትህ ይቀርባሉ፡፡
መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር እና አራት ምክትል ዳይሬክተሮች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተሹመዋል። በዚህ መሰረት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት አቶ ጀማል አብሶ ናቸው። ረዳት ኮሚሽነር ያረጋል አደመ በአስተዳደሩ የፋይናንስና የሰው ሀብት ልማት ዘርፍ፤ ኮማንደር ሙላት አለሙ የጥበቃ እና የደህንነት ዘርፍ፤ ኮማንደር ደስታ አስመላሽ የተሃድሶ ልማት ዘርፍ እንዲሁም ኮማንደር ወንድሙ ጫማ የመሰረታዊ ፍላጐት ዘርፍን በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት እንዲያስተዳድሩ ተሰይመዋል፡፡
የፌዴራል ማረሚያ ቤት አስተዳደር በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ታራሚዎችን ተቀብሎ መጠበቅ፣ ለታራሚዎች የተሃድሶ አገልግሎት መስጠት፣ የአስተሳሰብና የስነምግባር ለውጥ እንዲያመጡ እንዲሁም የህግ ታራሚዎች ህግ አክባሪ ሰላማዊና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

Published in የሀገር ውስጥ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።