Items filtered by date: Friday, 06 July 2018

እግር ኳስንም ሆነ ሌሎች የስፖርት ዓይነቶችን ለማስፋፋት ዋናውና መነሻው በቂ ማዘውተሪያ ሥፍራ ነው፡፡ ያለ ማዘውተሪያ ሥፍራ ተተኪ ወጣቶችን ማፍራት አይቻልም፡፡ ብርቱ የሆኑና ዘመናዊነትን የተላበሱ ስፖርተኞችን ማግኘትም አዳጋች ነው፡፡ ስፖርቱን ለማሳደግ በአገር አቀፍ ደረጃ ተሰርተው ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ሜዳዎች መኖር አለባቸው፡፡
በአገሪቱ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እጥረት እንዳለ ሲዘከር የኖረ እውነታ ነው፡፡ የተሰሩ ስታዲየሞች እንኳን ከውድድር ባለፈ ወጣቶች ልምምድ እንዲያደ ርጉበትና በተለይ የእረፍት ጊዜያቸውን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲያሳልፉ የሚደረገው ትኩረት አናሳ ነው፡፡
ምንም እንኳን በአገሪቱ በርካታ ስታዲየሞች እየተገነቡ ቢሆንም ያሉትን የበርካታ ስፖርተኞች ፍላጎት ያማከለ ማዘውተሪያ ሥፍራ ስለመኖሩ ግን አጠያያቂ ነው፡፡ በከተሞች አካባቢ ያሉት የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ውስን ከመሆናቸው ባሻገር በተለይ በክረምት ወቅት ከሚጥለው ዝናብ አንጻር ብዙዎቹ ብልሽት ስለሚገጥማቸው ልምምድ አይደረግባቸውም፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ ማዘውተሪያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የችግሩ ግዝፈት ‹‹የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው›› አይነት ብሂል ባልተመቻቸ ሁኔታ በመስራት ብቃት ያለው ስፖርተኛ እንዳይወጣ ምክንያት ይሆናል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ትላልቅ ስታዲየሞች መሰራታቸው ጥሩ ቢሆንም አጠቃቀሙም ሊታሰብበት ይገባል፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከል የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ልማት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ እያደገ የመጣውን የከተማዋን የማዘውተሪያ ፍላጎት ለማሟላት ግንባታቸው እየተከናወነ ከሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል 738 ሚሊዮን ብር የተበጀተላቸው የአበበ ቢቂላ ስታዲየም፣ የአቃቂ ዞናል ስታዲየም እና የራስ ኃይሉ ውሃ ዋና መዋኛ ገንዳ ይጠቀሳሉ፡፡ የእነዚህ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ መዲናዋ አዲስ አበባ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ውድድሮችን እንድታስተናግድ ዕድል ይፈጥርላታል፡፡ ለመሆኑ የእነዚህ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የግንባታ ሂደታቸው ምን ይመስላል?
የአቃቂ ዞናል ስታዲየም ፕሮጀክት ግንባታ
በከተማዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ባለቤትነት፣ በአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ አማካሪነት በከተማዋ በተለያዩ ሥፍራዎች እየተገነቡ ካሉት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አንዱ የአቃቂ ዞናል ስታዲየም ነው፡፡ በ514 ሚሊዮን ብር በዛምራ ኮንስትራክሽን ፈጻሚነት በ2011ዓ.ም ሊጠናቀቅለት ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት የአቃቂ ዞናል ስታዲየም ፕሮጀክት ግንባታ ለመጀመር ከስምምነት ከተደረሰ2 ዓመት ሆኖታል፡፡ የግንባታ ሥራው ከተጀመረ ደግሞ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡
አስቸጋሪና ብዙ ልፋትን ይጠይቃል የሚባለው የስታዲየሙ የኮንክሪት ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ቀሪ ክፍሉን ጨርሶ ህብረተሰቡ እንዲገለገልበት ለማድረግ አምስት ወራት እንደሚወስድበትም የዛምራ ኮንስትራክሽን የአቃቂ ዞናል ስታዲያም ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አለምነህ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት፣ ስታዲየሙ ተመልካችን ከፀሐይና ዝናብ መከላከል እንዲችል ዙሪያውን ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍንና 30 ሜትር ርዝመት ያለው የጣራ ልባስ ይኖረዋል፡፡ ለዚህም የሚረዳና ጣራውን መያዝ የሚችሉ የብረት አምዶች ተተክለዋል፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ 25ሺህ ተመልካቾችና 120 የክብር እንግዶችን ማስተናገድ ይችላል፡፡ ከእንጨትና ብረት እየተሰራ ያለው ክቡር ትሪቡን ደግሞ ለመገናኛ ብዙኃን ዘጋቢዎች ተብሎ የተመቻቹ ክፍሎችም ይኖሩታል፡፡ ቀጥታ ሥርጭት የሚያስተላልፉ አራት ‹‹ኮሜንታተ ሮችን›› በአንድ ጊዜ ያስተናግዳል፡፡ ሁለት የምስል ቀረጻዎች የሚደረጉበት ክፍሎችም አሉት፡፡
በመጀመሪያ ጊዜ ይጠናቃቀል ተብሎ ከስምምነት የተደረሰው በ900 ቀናት ውስጥ የነበረ ቢሆንም፣ የህዝቡን ፍላጎት በፍጥነት ለማሟላት በፍጥነት መጨረስ አለበት በሚል በ540 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ከስምምነት ተደርሷል፡፡ የብረት እጥረትና የዋጋ ውድነት በፈጠረው አገራዊ ችግር ምክንያት በተወሰነ መልኩ ሥራዎችን አቀላጥፎ ለመስራት እንቅፋት መሆናቸውንም ነው አቶ አለምነህ የሚናገሩት፡፡ ግንባታው 44 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ወቅቱ ዝናብ የሚበዛበት በመሆኑ ቀሪውን 56 በመቶ ለመስራት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጥሯል ብለዋል፡፡ የብረት አምዶች፣ የጣራ ልባስ፣ ተፈጥሯዊ የሜዳ ንጣፍ ሥራዎች የሚጠብቁት ግንባታው፤ ሥራው በህዳር ወር 2011 ዓ.ም ተጠናቆ እንዲደርስ ቢታቀድም የዕቃ አቅርቦት መቆራረጡ ግን ፍጥነቱ ላይ ሊገድበው እንደ ሚችልም ገልጸዋል፡፡
ወንበሮችና ጣራውን የሚደግፈው ብረት እንዲሁም ጣራው ከውጭ የሚመጣ ነው፡፡ የሜዳው ግንባታ ሁሉንም የስፖርት ዓይነቶች ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፤ ለአትሌቲክሱ ውድድር እንዲያገለግልም ሙሉ የመሮጫ መም ይገጠምለታል፡፡ ስታዲየሙ ሲጠናቀቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ያስተናግዳል ተብሎ እንደሚጠበቀው ሁሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ የዳኝነት ሥርዓትን የሚሰጡ አሰራሮችን የሚይዝ መሳሪያና ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ግብዓቶች እንደሚኖሩትም ተገልጿል፡፡ የስፖርተኞች አልባሳት መቀየሪያ፣ ማሟሟቂያ ሥፍራ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ መታጠቢያና መጸዳጃ ክፍሎች፣ ካፍቴሪያዎችና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሱቆችም በዙሪያው ይኖራሉ፡፡
አቶ አለምነህ የስታዲየሙን ጥራት በተመለከተ በተቆጣጣሪ መሀንዲሶች አማካኝነት በየጊዜው እንደሚመዘንና ይህም ግንባታው የታለመለትን ግብ እንዲመታ ጥራቱን እየጠበቀ እንዲሰራ አግዞታል በማለት ከዓለም አቀፍ ይዘት ጋር አጣጥሞ ለመስራትም በዲዛይኑ ውስጥ የተካቱት በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ ግንባታ ዳይሬክተር አቶ አድሃኖም ገብረጻድቅ በበኩላቸው፤ ምንም እንኳን ፕሮጀክቱ ግዙፍ ቢሆንም በኮንስትራክሽን ጥራት አንጻር በሚደረገው ክትትል አማካኝነት እስካሁን ያለው ሂደት በጥራት ጉድለት ላይ ችግር አልታየም፡፡ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የታለመለትን ጊዜ መቀነሱም የጥራት ችግር እንደማያመጣና ይልቁንም ሰፊ ተነሳሽነት እንዲኖር ከመፍጠር አንጻር ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በየወቅቱ የሚገጥሙ ስጋቶችንም በመነጋገር ሥራዎች ከስር መሰረቱ እየፈጠኑ እንዲሄዱ እየተደረገ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ ከሆኑ ምክንያቶች በቀር የሥራው መጓተት እንደማይኖር እስካሁን ከተገኘው ልምድ አንጻር መቃኘታቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው እንደሚሉት፤ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ውድድሮችን ለማካሄድ በከተማዋ ውስጥ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች በተለይም የትላልቅ ስታዲየሞች ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ለእናቷ የሆነችው የአዲስ አበባ ስታዲየም ብዙ ውድድሮችን ከማስተናገዷ የተነሳ ብዙ ችግሮች ተስተውለዋል፡፡ ቀጣይ በሚኖሩ ውድድሮችና ለአገሪቷ ስፖርት ዕድገትም እየተሰራ ያለው የአቃቂ ዞናል ስታዲየም ፋይዳው ትልቅ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የስታዲየሙ መገንባት የአቃቂ አካባቢ ነዋሪዎች የብዙ ጊዜ ጥያቄ ነበር፡፡ በዘመናዊ መልኩ ወቅቱን እንዲዋጅ ተደርጎ እንዲሰራላቸውም ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ በፊት በነበረው መዋቅር ተደጋጋሚ ጨረታዎች ውድቅ እየሆኑ በመምጣታቸው እውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ነገር ግን ተግባሩን ወደ እውነታ በመቀየርና በቁርጠኝነት ለመስራት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አሁን ያለበትን ቁመና እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ቢሮው ከሚያስገነባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መካከልም እየፈጠነ ያለውም ይኸው ስታዲየም ነው፡፡ ግንባታው አጠቃላይ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ ይጠናቀቃልም ብለዋል፡፡
ለተገልጋዮች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አንጻርም ተጨማሪ የመሬት ይዞታዎችን የማካተት ሥራዎች እየተከናወኑም እንደሆነ አቶ ንጋቱ ተናግረዋል፡፡ በፊት የነበሩ የመኪና ማቆሚያ በቂ ባለመሆኑና 25ሺ ተመልካች የሚይዝ ስታዲየም በርካታ ሀይል ሊያስተናግድ ስለሚችል ተጨማሪ የማዘውተሪያ ስፍራም በዙሪያው እንደሚገነባ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በአካባቢው በመኖሪያ ቤት የተያዙ ቦታዎችን ለማስተር ፕላን ጽህፈት ቤት በማቅረብ የስታዲየሙ አካል እንዲሆኑ እየተሰራ ነው፡፡ እነዚህም የስታዲየሙ ተገልጋዮች ብዙ አማራጮችን እንደሚጠቀሙ አስገንዝበዋል፡፡
አቶ ንጋቱ የስታዲየሙ ዋና መግቢያ በር እየተሰራ ባለው የአቃቂ ዋና መንገድ በኩል በመሆኑ ለመግባት ምቹ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ለስታዲየሙ ግንባታ የሚበቃውን በጀት በማውጣት የከተማ አስተዳደሩ ለስፖርት አፍቃሪው ትኩረት በመስጠት ያለምንም ክፍተት እየሰራ ይገኛል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም ምንም የበጀት እጥረት እንዳላጋጠመ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም እየሆነ ያለው ግንባታው በወጣቶችና ስፖርት ቢሮም ሆነ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ቶሎ እንዲጠናቀቅ ጉጉት ከመኖሩ አንጻር ነው፡፡ የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመመለስ አኳያም ሁልጊዜ ክትትል የማይለየው ግንባታ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የስፖርት ልማት ከሌሎች ልማት ተነጥሎ የሚታይ አይደለም የሚሉት አቶ ንጋቱ የከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ከውጭ ምንዛሪና ከብረት እጥረት ጋ ተያይዞ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሌሎች ፕሮጀክቶች ባልተናነሰ መልኩ ትኩረት አድርጎ በመስራት ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡
ከዲዛይንና ሌሎች ችግሮች ጋር ተያይዘው የሚኖሩ ክፍተቶችንም ለመሙላት ወርሃዊ ግንኙነትና ሌሎች የውይይት ጊዜያቶች እንዳላቸው የተናገሩት የቢሮ ኃላፊው፤ ችግሮች እየተፈቱ እንዲሄዱ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ግንባታውን በማፋጠን ላይ እንደሚገኙና ግንባታው ያለበትን ደረጃ ማየት የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎችም መጎብኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በቀር በተያዘለት የጊዜ ግደብ እንደሚጠናቀቅና ከ2011ዓ.ም ግማሽ ዓመት በኋላ ለስፖርት ቤተሰቡ ክፍት እንደሚሆንም አስታውቀዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አቃቂ በርካታ ፋብሪካዎች ያለበት በታ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙ አምራች ዜጎች ይገኛሉ፡፡ ስለዚህም ስፖርታዊ ውድድሮች በዚህ ስፍራ መካሄዳቸው ኢንዱስት ሪውን የሚያነቃቃ ነው፡፡ የስታዲየሙ መገንባት የአካባቢው ህብረተሰብ ጥያቄ እንደመሆኑም ከማንም በፊት ቅድሚያ የሚያገኙ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የስታዲየሙ አገልግሎት ለአቃቂ ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚገለገሉበት፤ እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ የሚደረጉ የብሄራዊ ሊግና የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች የሚካሄዱበት ነው፡፡ በመሆኑም ተደራሽነቱ ለሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡
አቶ ንጋቱ የማዘውተሪያ ሥፍራ ችግር ለመፍታት በሂደት በከተማዋ ሌሎች አካባቢዎችም እንደሚገነቡና ከዚህም ውስጥ በንፋስ ስልክና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች መለስተኛ ስታዲየሞች ለመገንባት በእቅድ መያዛቸውን አስታውቀዋል፡፡ በከተማዋ ላይ ትላልቅ ስታዲየሞችን ከመገንባት ባሻገር በየወረዳዎችና በጋራ መኖሪያ ቤቶች በስፋት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በመገንባት ታዳጊዎችን የማፍራት ጉዳይም የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡ ስታዲየሞችን የመገንባት ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የግል ባለሃብቶችን ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አበበ ቢቂላ ስታዲየም
በ105 ሚሊዮን ብር ዕድሳት፣ ሙሉ የጣራ ልባስ ማኖር፣ ወንበር መግጠምና የመሮጫ መም መስራት አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ሥራ ሲሆን፤ በእድሳቱ 112 ጣሪያ ተሸካሚ ብረቶች ሲኖሩት ከነበረበት የገላጣነት ሁኔታው ሙሉ ለሙሉ በጣራ የሚሸፈን ይሆናል፡፡ የወንበር መግጠም ሥራ የሚሰራውም ጣራ የማልበስ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሆነ ከአስሪዎቹ መረዳት ተችሏል፡፡
የአበበ ቢቂላ ስታዲየም የእድሳት ግንባታ ሳይት ሱፐርቫይዘር አቶ ፍቃዱ አለሙ እንደሚሉት፤ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ዕድሳት ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት ጊዜ በላይ ዘግይቷል፡፡ የማሻሻያ ዲዛይን እንዲሁም የዕድሳት ግንባታ ግብዓቶች ከውጭ ስለሚመጡ ከትራንስፖርትና ወደብ ላይ በሚያጋጥሙ ምክንያቶች በተባለለት ጊዜ አልተጠናቀቀም፡፡ ዙሪያውን ሙሉ በሚገጠምለት የኤሌክትሪክ ሲስተም ዕድሳቱ ሲጠናቀቅ ደረጃውን የጠበቀ ይሆናል፡፡
ሜዳው የመሮጫ መም የሚገጠምለት ቢሆንም አሁን ላይ ያለው ዝናባማ የአየር ሁኔታ በሥራ ሂደቱ ላይ እንቅፋት እንደሆነ አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡ ስታዲየሙ ከ15 እስከ 16ሺህ ሰው የመያዝ አቅም እንዳለው የሚታወቅ ሲሆን፤ በፊት በነበረው አገልግሎቱ ወንበር የነበረው በጥላ ፎቅ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ እድሳት ግን ሙሉ ስታዲያሙ በሚይዘው የሰው ቁጥር ልክ ወንበር እንደሚገጠምለትም ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ በክቡር ትሪቡን በኩል ያለው ወንበር በልዩ መልክ ይገጠማል ብለዋል፡፡ ወንበሮቹ ከውጭ የሚገቡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥም 4ሺህ ወንበሮች ተገዝተው ገብተዋል፡፡ ግንባታው ተጠናቅቆ በ2011ዓ.ም መጀመሪያ ላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ጣራውን የሚሸከም አምድ በኤሌክትሪክ ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ብቻ ነው የሚመረተው፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም ከሚያስፈልገው 112 አምዶች ውስጥ ማምረት የተቻለው ወደ 45 የሚጠጉ ጣራ ተሸካሚ አምዶችን ብቻ ነው፡፡ ይህም በግንባታው ላይ መጓተትን እንደፈጠረ ገልጸው፤ ችግሩ የሚፈታ ከሆነ በተሻለ ፍጥነት ዕድሳቱ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡
እስካሁን ባለው የዕድሳትና ግንባታ ሂደቱ ዋናውን ህንጻ ጨምሮ በዙሪያው ያሉት 72ሱቆችና የመጸዳጃ ቤቶችና ከ90 በመቶ በላይ ዕድሳት ተደርጎላቸዋል፡፡
የራስ ሀይሉ ጅምናዚየም
የውሃ መዋኛ ገንዳ
ላለፉት ዓመታት ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ጋር ውል ተፈጽሞ እየተሰራ የሚገኝ ፕሮጀክት ሲሆን፤ ለበርካታ ጊዜ እየተጓተተ የመጣ ግንባታ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከዛሬ ነገ ያልቃል እየተባለ እልህ አስጨራሽ ትግል ተደርጎበት አሁን የማጠናቀቅ ምዕራፍ ላይ ተደርሷል፡፡ ግንባታው በከተማዋ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃም ትልቅ የሆነና አዲስ ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳ ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀና የተለያዩ አገራዊና አህጉራዊ ውድድሮችንም ማስተናገድ የሚችል ነው፡፡
ከስፔን አገር በተቀመረ ተሞክሮ እየተሰራ ያለው የውሃ መዋኛ ገንዳው፤ 48 የተመልካች መቀመጫዎችን ጨምሮ የህጻናት የመጫወቻ ቦታ፣ የዝላይ ቦታ፣ ሱቆችና ካፍቴሪያዎችም ይኖሩታል፡፡ አዲስ ግንባታ እንደመሆኑ መጠን ብዙ ጊዜ ቢጓተትም ሙሉ የግንባታ እቃዎች ተጠናቀው በመግባታቸው ለ2011ዓ.ም አገልግሎት እንደሚጀምርም ነው የቢሮው ኃላፊውና የሳይት ተቆጣጣሪዎች የገለጹት፡፡
ግንባታው የመጀመሪያ ደረጃ ሥራው ተጠናቅቋል፡፡ የተመልካች ወንበርም ተገጥሟል፡፡ በዙሪያው ያሉ ሱቆችም ተገንብተዋል፡፡ ቀሪዎቹን ሥራዎች በፍጥነት አከናውኖ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግም ልዩ ትኩረት እንደሚደረግበት ተገልጿል፡፡ ለአጠቃላይ ግንባታውም107 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡
ስታዲየሞች ትላልቅ ውድድሮች የሚካሄዱ ባቸው ብቻ ሳይሆኑ ተተኪዎች የሚፈሩበትና የሚዝናኑበት ከማድረግ በተጨማሪ በከተሞች አካባቢ የማዘውተሪያ ስፍራ ችግሮች ሊቀረፉ ይገባል፡፡ በቀጣይ የወጣቶች ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ችግር ለመቅረፍ በከተሞችና በገጠር በተለይም በፍጥነት እያደጉ ባሉ ከተሞች አካባቢ የማዘውተሪያ ሥፍራ እንዲኖራቸው በማድረግ ስፖርቱን በሁሉም ወቅቶች ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ በአገሪቱ ብቃት ያላቸው ስፖርተኞች የሚፈሩበት ውስን አካዳሚዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም፤ እነዚህ በቂ ባለመሆናቸው ሌሎች ተጨማሪ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በጥናት ተደግፈው ሊሰሩ ይገባል በማለት የዝግጅት ክፍላችን መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

አዲሱ ገረመው

Published in ስፖርት
Friday, 06 July 2018 16:44

ከመደመር ማግስት!

በዕለታዊ እንቅስቃሴዬ ከታክሲ ተለይቼ አላውቅም፡፡ እኔ ለታክሲ ታክሲም ለእኔ የተፈጠሩ እስኪመስለኝ ድረስ ወዳጅነታችን ጠንካራ ነው፡፡ አሁን ከፒያሳ ወደ ካሳንችስ እየተጓዝን ነው፡፡ ብቻ ታክሲው ትርፍ ጭኗል የሚለው አገላለጽ አይመጥነውም፡፡ በትንሹ 16 ሰው ሆነን በአንድ ታክሲ ተፋፍገናል፡፡ ለነገሩ መጠጋጋቱ የክረምቱን ብርድ ለተወሰኑ ደቂቃዎችም ቢሆን ያስታገሰልን ይመስላል፡፡ ረዳቱም ‹‹እናትዬ እዛ ጋ! ጠጋ በይ እስኪ ጊዜው የመደመር ነው›› እያለ ለሁለት ሰው በተፈቀደው ወንበር ሦስት ሰዎችን እየጫነ ነው፡፡ ታክሲው ከሞላ በኋላ እሪ በከንቱን አልፈን ወደ ቤተ መንግስት እየተቃረብን ነው፡፡
በዚህ መሃል አንዲት ሸንቃጣ ኮረዳ ‹‹ረዳት! አራት ኪሎ ስትደርስ ወራጅ አለ፡፡ እንዳታሳልፈኝ እሺ ባባ! አለችው ሙዚቃዊ ቃና በተላበሰ ድምጽ፡፡
ሹፌሩ አንገቱን 45 ዲግሪ ጠምዝዞ ‹‹አትቀልጂ እህቴ! አራት ኪሎ የሚወጣ እንጂ የሚወርድ የለም›› ሲል ሁላችንም ፈገግ አልን፡፡
ልጅቷ ቀልዱ አልጣማት ኖሮ! እንዴ ‹‹አይገርምህም ታወርደኛለህ እሺ!›› በማለት ንዴት የተሞላው ግን ቅንጡ አነጋገሯን አከለች፡፡
ሹፌሩም የዋዛ አልነበረም፡፡ አይ እንግዲህ መደመር ሲባል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አራት ኪሎ መገኘት ሳይሆን ለዚህ ቦታ የሚያበቃ ሥራ ላይ መጠመድ ነው ብሎት እርፍ፡፡ ‹‹መደመር›› ሰሞነኛ ቃል በመሆኗ ሁሉም ፈገግ ይበሉ እንጂ ልጅቷ ደስተኛ አልነበረችም፡፡ ብቻ ካሰበችው ቦታ ትንሽ እልፍ ብትልም ልጅቷ ወረደች፡፡ የመደመር እና የሁለቱ ልጆች እሰጣገባ ሳይደበዝዝ ከቤተ መንግስት ትንሽ አልፍ እንዳልን ገብርኤል ጫፍ ከሚባለው አካባቢ ስንደርስ ሞገደኛው ሹፌር ከትራፊክ ፖሊስ ጋር ተገጣጠመ፡፡
ትራፊኩ ትርፍ መጫኑን አይቶ ኖሮ ፖሊሳዊ ሠላምታ ከሰጠ በኋላ መንጃ ፈቃድህን ትሰጠኝ ሲለው ጠየቀው፡፡ ሹፌሩ መንጃ ፈቃዱን ከመስጠት ይልቅ ዘሎ ከታክሲ ወረደ፡፡ ለቡጢ የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ ከትራፊኩ ጋር ለረጅም ሰዓት ከተነጋገሩ በኋላ አንዲት ብጫቂ ወረቀት ይዞ እየተነጫነጨ ወደ መኪናው ተመለሰ፡፡
ከተሳፋሪዎቹ አንዱ ‹‹ቀጣህ እንዴ›› ብሎ ሹፌሩን ይጠይቀዋል፡፡ ረዳት ቀበል አድርጎት ‹‹አልቀጣውም፤ ነፃ የምክር አገልግሎት ነው የሰጠው›› ሲል ሹፌሩን በሃሳብ የማገዝ ዓይነትና ብስጭቱን እንደተጋራ ለማሳበቅ ሞከረ፡፡
ከነበርኩበት ታክሲ ወርጄ ጉዳዬን አጠናቅቄ አሁን ወደ ሌላ ታክሲ አመራሁ፡፡ ረዳቱ ፒያሳ ፒያሳ በአቋራጭ በአቋራጭ እያለ ይጠራል፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ነገር ታወሰኝ፡፡ ቅድም የነበረችው ልጅ አሁን ብትኖር ‹‹ለምን በአቋራጭ ትሄዳለህ?›› ብላ የምታፋጥጠው መሰለኝ፡፡ በእርግጥ ሹፌሩም የዋዛ አይሆንም፡፡ በቃ በአቋራጭ ነው የምሄደው ብሎ ለብሽሽቅ የሚዘጋጅ ነው የሚመስለኝ፡፡
ልጅቱም ‹‹እኮ! ለምን በአቋራጭ ቀጥታ በአራት ኪሎ አትሄድም›› ብላ ስታፋጥጠው በዓይነ ህሊናዬ አሰብኩት፡፡
‹‹ቆይ ግን አራት ኪሎ ምን ጥለሻል አንቺ ደግሞ ቀጥታ ብሎ አራት ኪሎ አለ እንዴ? በርካታ ውጣ ውረዶች ታልፈው ነው አራት ኪሎ ለመድረስ እሺ ሲስቱካ!›› ብሎ ሲመልስላት ተሳፋሪዎቹ በሞቅታ የሚያውካኩ ይመስለኛል፡፡
‹‹ኧረ ባክህ ! ተናግረህ ሞተሃል፤ ቆይ ግን እናንተ አቋራጭ ካልሆነ ሌላው ነገር አይታያችሁም አይደል?››
የእኔ አህት ‹‹ሁሉ ነገራችን በአቋራጭ ከሆነ እኮ ሰነባብቷል፡፡ ሃብት ለማከማቸት፣ ስልጣን ለመያዝ፣ ሥራ ለመያዝና ዝና ለማግኘት በአቋራጭ ኧረ ባክሽን ህልምም በአቋራጭ መሆኑ ይቀራል ብለሽ ነው?›› ብሎ ነገሩን ገታ በማድረግ ከእርሷ የሚሰነዘረውን አፀፋ የብሽቀት ቃል ለመስማት የታክሲውን ፍጥነት ቀዝቀዝ አድርጎ እየነዳ ነው፡፡
‹‹በቃ እሺ! ከአሁን በኋላ ባትናግረኝ ደስ ይለኛል፡፡ ግን ሰው ሁሉ ሲስቅልህ አራዳ የሆንክ እንዳይመስልህ›› ብላ የቆየውን ንግግር ገታ ለማድረግ እና ንዴቷን ለመቆጣጠር የምትዘጋጅ ይመስለኛል፡፡
ሹፌሩ ዝም ቢልም ‹‹ወያላው›› አጋርነቱን ለማሳየት ሲል፤ ‹‹የእኔ አህት ለምን ብቻሽን ብክንክን ትያለሽ? እንደ ሌላው መደመር አይበጅሽም ብሎ የተረጋጋ ስሜቷን ቀስቅሶ እንደ እብድ የሚያናግራት ይመስለኛል፡፡ መቼም የተሳፋሪዎቹ ማውካካት እንዲሁ በዓይነ ህሊናዬ ሳስበው ሳቅም፤ መሳቀቅም የሚፈጥርብኝ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ አሁን ፒያሳ ደርሻለሁ፡፡ ወደ ሰፈር ለመሄድ አሁንም ሌላ ታክሲ ላይ መገለባበጡን ሳልወድ በግድ የተላመድኩት የኑሮዬ ክፍል ሆኗል፡፡ ኑሮ እና ታክሲ ብወዳቸውም ብጠላቸውም ልለያቸው አልቻልኩም ወደሚለው ፍልስፍና እያመራሁ ነው፤ ከራሴ ዕለታዊ ኑሮ ጋር የታክሲን ቁርኝት እያየሁ ነው፡፡
ታክሲ ተሳፍሬ ሰፈር እንደደረስኩ አንዲት ስፋቷ ጠባብ፤ ደንበኞቿ የበዙ ግሮሰሪ አመራሁ፡፡ የምፈልገውን ነገር አዝዤ ከአንዱ ማዕዘን ላይ ተቀመጥኩኝ፡፡ ዓይኔን ወደ ባንኮኒው ጣል ሳደርግ አንድ ከሰማይ ስባሪ የማይተናነስ ወጣት ‹‹ከባለጌ ወንበር›› ብሎ ላይ ቁጭ ብሎ ባንኮኒውን እየደበደበ ያወራል፡፡ ሁኔታው በቤቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ትኩረቱን ወደ እርሱ እንዲያደርጉ የፈለገ ይመስላል፡፡ ትሰማለህ ና! ና! ቅዳ! ሰርቼ እንጂ ሰርቄ አይደለም፡፡ ደግሞ ና! ቅዳ፡፡ ነፃ ሰው ነኝ፡፡ ነፃ ሰው እኮ ነፃ ሆኖ ነው ይጠጣል፤ ነፃ ሆኖ ይወለዳል፤ ነፃ ሆኖ ይኖራል፤ ነፃ ሆኖ ያወራል… እያለ በሠካራም አንደበቱ ይቀባጥራል፡፡
በመጨረሻም አንድ የእርሱ መሰል ሲመጣ ሞቅ ያለ ሠላምታ ከተለዋወጡ በኋላ አጠገቡ ከነበረው ተመሳሳይ ወንበር ላይ ና! ና! እዚህ ተደመር ይለዋል፡፡ ከጓደኛውም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲያወሩ ቤቱን በአንድ እግር ሊያቆሙት አድርሰዋል፡፡ መደመር! መደመር! መደመር! የሚለውን ቃል ግን በሆነውም ባልሆነውም ሲጠቀሙ እየሰማሁ ነበር፡፡ የሚጠጡትን ነገርም ጨምሪ ለማለት ደምሪ ይሏታል አስተናጋጇን፡፡
ሰዓቱ እየመሸ ነው፡፡ አንዱ ሲወጣ ሌላው ሲገባ ቤቱ የመደመር እና የመቀነስ ህግን በአግባቡ እየተገበረ ነው፡፡ እኔ ለመቀነስ ስወስን ሌላ የሚደመር እንዳለም ተገነዘብኩኝ፡፡ ምሽቱ ቢገፋም የሚደመር ሰው ግን አልጠፋም፡፡ ለራሴ ይብላኝ እኔ ለተቀነስኩት እያልኩ ወደ ቤቴ አመራሁ፡፡ በእርግጥ እኔ ከማንም ጋር ሳልሆን ወደ ቤቴ መሄዴ መደመር ወይስ መቀነስ እያልኩ እራሴንም ስጠይቅ ነበር፡፡ ሁለቱ ወጣቶች አሁንም እዚያው ሆነው ተደማሪ እና ተቀናሽ የሚያሰሉ ይመስለኛል፡፡ ብቻ ከመደመር ማግስት አንዲት ቃል እንዲህ ዘርፈ ብዙ ትርጉም ሲሰጣት ማየቴ አግራሞት ፈጥሮብኛል፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

ሳምንቱ በታሪክ

የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ 71ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ

ባለቅኔ፣ ደራሲና ገጣሚ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ያረፉት ከ71 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት (ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም) ነበር፡፡ 

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ከአባታቸው ቄስ ገበዝ ንጉሤ ወልደ ኢየሱስና ከእናታቸው ወይዘሮ ማዘንጊያ ወልደኄር በ1887 ዓ.ም. ጐጃም ውስጥ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም የቤተ ክህነት ትምህርት በሚገባ ተምረው አጠናቀዋል፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የአማርኛ፣ የግዕዝና የግብረ ገብ መምህር ሆነው እያስተማሩ ለብርሃንና ሰላም ጋዜጣ አጫጭር ጽሑፎችን ያቀርቡ ነበር፡፡
ወላድ ኢትዮጵያ፣ የኛማ ሀገር እና ድንግል አገሬ ሆይ የተሰኙትንና በሕዝብ ዘንድ በዋናነት የሚታወቁላቸውንና የሚወደዱላቸውን የመጀመሪያ የድርሰት ስራዎቻቸውን የፃፉትም በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ወደ ትያትር ስራ ለመግባት እንደገፋፋቸውም ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ በዚህም ‹‹ምስክር›› የተሰኘ የመጀመሪያ የትያትር ስራቸውን አበረከቱ፡፡
የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ በአምላክሽ ኃይል በንጉሥሽ›› የሚለውን የደረሱት ቀኝጌታ ዮፍታሔ፣ ስለአገር ፍቅርና ጀግንነት የሚያወሱ በርካታ ድራማዎችንና መዝሙሮችን የደረሱ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ‹‹አፋጀሽኝ››፣ ‹‹እለቄጥሩ›› ወይም ‹‹ጎበዝ ዐየን›› ይገኙበታል። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ከ1935 ዓ.ም እስከ ሕልፈታቸው ድረስ አገልግለዋል። ከዚህ በተጨማሪም፣ ተአምራዊው ዋሽንት፣ጥቅም ያለበት ጨዋታ፣ ሙሽሪት ሙሽራ፣ ያማረ ምላሽ፣የሆድ አምላኩ ቅጣት፣ ዳዲ ቱራ፣ የህዝብ ጸጸት፣ ሙሾ በከንቱ፣ አባት ንጉሳችን ጠረፍ ይጠብቅ፣ የደንቆሮዎች ቲያትር፣ ዓለም አታላይ፣ዕያዩ ማዘን፣ ንጉሡ እና ዘውዱ የተሰኙና ሌሎች የድርሰት ስራዎችን አበርክተዋል፡፡
በ19 ዓመታቸው የቀኝ ጌትነትን ማዕረግ ያገኙት እኒህ ታላቅ ሰው፣ የታሪክ መምህር፣ ዲፕሎማትና አርበኛም ነበሩ፡፡ ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም መደበኛ ስራቸውን ሲያከናውኑ ውለው በተኙበት አርፈው ተገኙ፡፡ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የምትታወቀው ‹‹አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› የተሰኘችው ስንኝ በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የድርሰት ስራ ውስጥ የምትገኝ ስሜት ቀስቃሽ ስንኝ ናት፡፡
በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ሕይወትና ስራዎች ላይ መጽሐፍ የፃፉት ደራሲ ዮሐንስ አድማሱ፣ ስለ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አጠቃላይ ማንነት ‹‹ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ብሔረ ነገዱ፣ አገረ ውላዱ፣ ጐጃም፤ ቅኔ የተቀኘበት፣ ድጓና ምስጢር የተማረበት፣ ደብረ ኤልያስ ነበር፡፡ ጠይም ረዥም፣ ጠጉረ ሉጫ፣ መልከ መልካም፣ ቀጭን-ዠርጋዳ ጣተ መልካም፣ ሽቅርቅር፣ ጥዩፍ፣ ኮከቡ ሚዛን ነፋስ ነበር›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡
የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አፅም ያረፈው በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነበር፡፡ ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም አፅማቸው ከአዲስ አበባ ፀሎተ ፍትሐት ተደርጎ፣ በርካታ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት መድረክ ‹‹አፋጀሽኝ›› የተሰኘው የትያትርና ሌሎች ስራዎቻቸውን የሚዘክር አጭር ትርኢት ቀርቦ ወደ ትውልድ ስፍራቸው ተሸኝቷል፡፡ በዚያም በርካታ ሰው በተገኘበት አፅማቸው በክብር አርፏል፡፡

አንተነህ ቸሬ

 

Published in መዝናኛ
Friday, 06 July 2018 16:41

«ማዚ» የወተት ማለቢያ

ወተት እንደዛሬ ሰፊ ገበያ ስላልነበረውና ምርቱም አነስተኛ በመሆኑ ለወተት ማለቢያ የሚሆን ዕቃ ማዘጋጀት ላይ የሚጨነቅ አልነበረም።በጣሳ፣በፕላስቲክ፣ በሳህን በማንኛውም ዕቃ ነው የሚታለበው።በማንኛውም እቃ የሚደረገው የወተት አለባ ንፅህናውን ለመጠበቅ አመቺ አለመሆኑና እንደሚባክንም ይነገራል።የወተት ላሞች የሚሰጡት ምርትም ከፍ ካለ በቀን ከሁለት ሊትር የበለጠ አይሆንም። መጠኑ አነስተኛ መሆኑም የተሻለ የወተት ማለቢያ ላለማዘጋጀት ሌላው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።የወተት ማለቢያ አስፈላጊነት በገበያ ግምት ውስጥ ባለመግባቱ ለሽያጭ የሚቀርብ አልነበረም።የፈጠራ ባለሙያዎችም ፊታቸውን ወደዚህ ባለማዞራቸው የወተት ማለቢያ ዕቃ ከተለመደው የተለየ ሊሆን አልቻለም።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወተት ከቤት ውስጥ ከራስ ፍጆታ አልፎ ገበያ ላይ መዋል ቢጀምርም በተለመደው የወተት ማለቢያ ዕቃ ታልቦ ነው ወደ ገበያ የሚወጣው።ከአርሶ አደሩ እየሰበሰቡ ወተት በማቀነባበር ለተጠቃሚው የሚያቀርቡ ድርጅቶች እየተስፋፉ ባለበትና የወተት ልማቱንም ለማሳደግ እንቅስቃሴ በሚደረግበት በዚህ ወቅት በተለመደው የወተት ማለቢያ በመጠቀም ገበያ ላይ ማውጣት አይታሰብም።ተወዳዳሪም መሆን አይቻልም። ድርጅቶቹ የሚሰበሰበው ወተት በመጠንም በጥራትም ከፍ ያለ እንዲሆን ይፈልጋሉ።
አሁን ባለው አሰራር አርሶአደሩ ምን ያህል ሊትር ወተት እንዳለበ የሚያውቅበት መንገድ ባለመኖሩ የሚረከበው ድርጅት ለክቶ በሚነግረው ብቻ ነው መጠኑን የሚያረጋግጠው።ይሄ ደግሞ እርግጠኛ ለመሆን አያስችለውም።በዋጋም ለመደራደር ከፍተኛ ችግር እንደሆነ ነው የሚገለጸው።እንዲህ ያለው አሰራር በአርሶአደሩና በተረካቢው መካከል አለመግባባት እየፈጠረ መቀጠል እንደሌለበት ይታመናል። የወተት አለባው በቴክኖሎጂ አለመታገዙ በምርት ጥራትና የአቅርቦት መጠን ላይ ተፅዕኖ እንዳለው በሥራው ላይ የተሰማሩት ይገልፃሉ።
በወተት አቅራቢውና በተቀባዩ መካከል ያለውን የግብይት ክፍተት የሚፈታ ካለፈው ዓመት ጀምሮ «ማዚ» የወተት ማለቢያ በተወሰኑ አካባቢዎች ተሰራጭቶ ጥቂት አርሶ አደሮች እጅ ገብቷል።ማዚ አፉ ሰፊ በመሆኑ፣ማጥለያ ስላለውና በዕቃው የታለበውን ወተት በቀላሉ ለማጓጓዝ የሚያግዝ በመሆኑ ሦስት በአንድ ተብሏል።አፉ ሰፊ መሆኑ በደንብ በማጠብ የዕቃውን ንፅህና ለመጠበቅ ያስችላል።በወተት አለባ ወቅት የሚያገለግል ማጥለያም አብሮ ስላለው ማጥለያው ከላሟ የሚረግፈውን ፀጉር፣ላሟ ጤናማ ካልሆነች ወተቱ ላይ ደም ወይም ሌላ አይነት ቀለም ከታየ በቀላሉ ለመለየት፣ከአካባቢው ወደ ወተቱ ሊገባ የሚችል አቧራ ወይም ሌላ ቆሻሻን ለመከላከል ከፍተኛ ጥቅም አለው።ማዚ የመጠን ልኬትም ስላለው ወተት አምራቹ የወተት መጠኑንና ገበያ ላይ አውጥቶ የሚያገኘውን ገቢም አስቀድሞ ለማወቅ ያስችለዋል ።
ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ማዚ የወተት ማለቢያ ግሎባል ጉድስ በተባለ የአሜሪካን ኩባንያ ነው ዲዛይን የተደረገው።ይህ ፈጠራ በመጀመሪያ ጥቅም ላይ የዋለው በኬንያ ሀገር ሲሆን፣ማዚ የሚባለው ስያሜ የተሰጠው በዛው በኬንያ ነው።ማዚ በስዋህሊኛ ወተት ማለት እንደሆነም ማለቢያው በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረገው ኤስ ኤን ቪ የኔዘርላንድ ልማት ድርጅት አስታውቋል።
በድርጅቱ የግሉ ዘርፍ አማካሪና የዕድገት ወተት ልማት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ማህሌት ዮሐንስ እንደገለፁት፣ ማለቢያው ለኢትዮጵያ ወተት አምራቾች ምቹ ሆኖ በሀገር ውስጥ በሚገኝ የፕላስቲክ አምራች ድርጅት ተመርቶ ለሙከራ ለተወሰኑ የወተት አምራች አካባቢዎች መሰራጨቱን አመልክተዋል። ቴክኖሎጂው የወተት ምርት ጥራትን ለመጠበቅ ከማስቻሉ በተጨማሪ መጠን ለማወቅም የሚረዳ መሆኑ በወተት አምራቹ በኩል ተፈላጊ እንዲሆን እንዳስቻለ ባሰራጩት ማለቢያ መረዳት መቻላቸውን አስታውቀዋል።
ወይዘሮ ማህሌት፣ማዚ የሚለው የወተት ማለቢያ ቴክኖሎጂ በኬንያ ላይ በመሞከሩ ከነስያሜው በኢትዮጵያ ቢተገበርም የወተት ማለቢያና ማጓጓዣ እንደሚባል ገልፀዋል።እስካሁንም ወደ አንድ መቶሺ ማዚ የወተት ማለቢያ በነፃ ለአርሶአደሩ በድርጅቱ ማሰራጨቱን አመልክተዋል።ሰሞኑን በተከናወነው ቴክኖሎጂውን ይፋ የማድረግ ሥነሥርዓት ላይ እንደተገለፀው፣ ድርጅቱ እስከዛሬ ያሰራጨው ዩኒቨርሳል የተባለ የግል ፕላስቲክ ፋብሪካ እንዲያመርት በማድረግ ሲሆን፣የተጠቃሚውን ፍላጎት ለማሟላት ከዚህ በኋላ ከቴክኖሎጂ ባለመብቱ ግሎባል ጉድስ ጋር በመነጋገር ፋብሪካው ፈቃድ አግኝቶ እንዲያመርት ውል በመፈራረም በስፋት አምርቶ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርብበትን መንገድ እየተመቻቸ ነው።
በይፋ ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት በእንስሳትና አሳ ሀብት ሚኒስቴር የወተት ሀብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ተካ እንደገለፁት፣ የወተት ጥራትን ለመጠበቅ ከሚያግዙት አንዱ የወተት ማለቢያ ዕቃ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ ነው።እስከዛሬ በሀገሪቷ ወተት ከቤት ፍጆታ ያለፈ ባለመሆኑ ለማለቢያ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል።
እንደ አቶ ታሪኩ ማብራሪያ ወተት በሚታለብበት ወቅት፣ የታለበው ወተት ደግሞ ወደሌላ ዕቃ ሲገለበጥና ሲጓጓዝ በቀላሉ የሚበከል በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል።እንደ ማዚ ያለ የወተት ማለቢያ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ መዋሉ የወተት ብክለትን ለመቀነስም ጥቅም አለው።ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግም ይረዳል ብለዋል።ወተት ገበያ ላይ በማዋል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ፍላጎት እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት ዘመናዊ የወተት ማለቢያ መጠቀሙ ወቅታዊ እንደሆነም ገልፀዋል።
ወተትን ገበያ ላይ በማዋል ኑሮአቸውን የለወጡ ሰዎች ቢኖሩም ከዚህም በላይ ሲሰራና የወተት ምርቱም ሲጨምር ቴክኖሎጂውም በማዚ የወተት ማለቢያ ብቻ እንደማያበቃም አመልክተዋል። በብክለት የጤና ስጋትን ለመቀነስም ሆነ ለአያያዝ ምቹ የሆነ ማለቢያ መኖሩ አስፈላጊነት አጠያያቂ እንዳልሆነ በወተት ማቀነባበር ላይ የተሰማሩትም ይገልፃሉ።በተለይ የወተት መጠኑ አለመታወቁ ብዙ ጊዜ ከአምራቾች ጋር አለመግባባትን እንደሚፈጥርም በይፋ ሥነሥርዓቱ ላይ የነበሩት ወተት አቀነባባሪዎች ተናግረዋል።

ለምለም መንግስቱ

Published in ማህበራዊ

ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶች ባለቤትና የበርካታ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫዎች መሆኗ አገሪቱ እያስመዘገበችው ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ጋር ሲደመር፣ አገሪቱ ለሥራ፣ ለጉብኝትና ለሌሎች ጉዳዮች ወደ ድንበሯ ለሚገቡ የውጭ አገራት ዜጎች ቀልጣፋና አስተማማኝ የቪዛ አገልግሎት መስጠት ከቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎቿ መካከል አንዱ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
ታዲያ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥትም ለሥራ፣ ለጉብኝትና ለሌሎች ጉዳዮች ወደ አገሪቱ የሚመጡ የውጭ አገራት ዜጎች ቀልጣፋ የቪዛ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ አሠራሮችን ሲተገብር ቆይቷል፡፡ ከነዚህ አሠራሮች መካከል አንዱ የ«ኦንላይን ቪዛ (Online Visa/ኢ-ቪዛ)» ሥርዓት አንዱ ነው፡፡ ይህን አሠራር ተግባራዊ በማድረግም ከባለፈው ግንቦት ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱን ለ37 አገራት ዜጎች መስጠት ተጀምሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና ሀገሪቱን ለቱሪስቶችና ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ ከግንቦት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ አገልግሎቱን ለሁሉም የውጭ አገራት ዜጎች መስጠት ተጀምሯል፡፡ ይህ የኢ-ቪዛ አገልግሎት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለሙያዎች የተሠራ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዲጂታል ዳይሬክተር አቶ ምህረተአብ ተክላይ፣ አገልግሎቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሚፈልጉ ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው በኤሌክትሮኒክ መንገድ ቪዛ ማግኘት የሚችሉበት አሠራር ነው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ይህ አገልግሎት የአገልግሎት ፈላጊውን ግለሰብ ማስረጃዎችን ተመልክቶ፣ አገልግሎት ጠያቂውም ክፍያውን ከፍሎ መረጃው ወደኢሚግሬሽን ተልኮ ቪዛውን ከኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት በኢ-ሜይል አማካኝነት የሚያገኝበት አሠራር ነው፡፡ ይህም የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ፈጣን፣ ቀላልና አስተማማኝ የሆነ አገልግሎት እንዲገኙ ያስችላቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎቱ በኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት የመረጃ ቋት የመረጃ አቅርቦት እንዲሁም የአገልግሎቱ ጠያቂዎች ዝርዝር መረጃዎች ምልከታ ላይ ተመስርቶ ስለሚከናወን ለፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች አስተማማኝ ምላሽ የሚሰጥ አሠራር ነው፡፡
የአገልግሎቱን ፋይዳዎች በተመለከተ ሲገልጹም፣ «አገልግሎቱ ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ ለቱሪዝም መጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ለአብነት ያህል ሩዋንዳ አገልግሎቱን መስጠት እንደጀመረች የቱሪስት ፍሰቷ ከ22 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ቢኖሯትም ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ (ጥቅም) አነስተኛ ነው፡፡ የዚህ አሠራር ሥርዓት መጀመር የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶችንም ቁጥር ይጨምራል» ይላሉ፡፡
አቶ ምህረተአብ እንደሚናገሩት፣ የኢ-ቪዛ አገልግሎት አንድ አገልግሎቱን ጠያቂ ግለሰብ በሦስት ሰዓታት ውስጥ ቪዛ ማግኘት ያስችላል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ቀንና ሌሊት በሦስት ፈረቃዎች አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው፡፡
አገልግሎቱ ሰፊ ዝግጅት የተደረገበት ሥራ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ችግሮች ቢፈጠሩ የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መምሪያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን የጋራ ግብረ ኃይል አቋቁመዋል፡፡ ይህም ከቴክኖሎጂ ሽግግርና አገልግሎቱን በራስ አቅም ከመስጠት አንፃር ትልቅ እምርታና ለውጥ ነው፡፡
አሁን እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት የበለጠ ተደራሽና ውጤታማ ለማድረግ በቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎች እንዳሉ አቶ ምህረተአብ ይገልፃሉ፡፡ ከነዚህ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከልም አገልግሎቱ ዓለም ላይ ብዙ ተናጋሪ ባላቸው በሰባት ቋንቋዎች እንዲሰጥ፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ለማግኘት የሚከፍሉትን ክፍያ በየአገራቸው የክፍያ ሥርዓት መክፈል እንዲችሉና አሁን በኢ-ሜይል ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እንዲሰጥም የማድረግ ተግባራትም ዋናዎቹ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡
የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ገብረዮሐንስ ተክሉ የኢ-ቪዛ አገልግሎት አገሪቱ በዘርፉ ያቀደችውን ለውጥ ለማሳካት ከሚያስችሉ አሠራሮች መካከል አንዱ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ይህ አሠራር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ አገራት ዜጎች ቀልጣፋ የቪዛ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ አገሪቱ ከዓለም ጋር የሚኖራትን ትስስር የበለጠ ጠንካራ ያደርገዋል፡፡ ይህም ለጎብኚዎችና ለባለሀብቶችም አገሪቱን ለመጎብኘትና መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጠንካራ መተማመኛ ይሆንላቸዋል፡፡
አገሪቱ በፍጥነት እያደጉ የመጡትን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በኢሚግሬሽንና በዜግነት ጉዳዮች ላይም በመጠቀምና ለውጭ አገራት ዜጎች እንቅስቃሴ ምቹ በመሆን ተወዳዳሪ መሆን ስላለባት አገልግሎቱን መስጠት እንደጀመረችም ያስረዳሉ፡፡
ይህን የአሠራር ሥርዓት ከግብ ለማድረስ ባለድርሻ አካላት ብርቱ ጥረት እንዳደረጉ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ «የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የተጠቃሚዎችን ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥበው ይህ አሠራር እውን እንዲሆን ከ20 ወራት በላይ ደክመውበታል» ይላሉ፡፡ በቀጣይም አገልግሎቱ በየጊዜው በሚደረጉለት ማሻሻያዎች የውጭ አገራት ዜጎች የተሻለና ለወቅቱ የሚመጥን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሠራም ይጠቁማሉ፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው፣ የኢ-ቪዛ ሥርዓቱ የቱሪስት ፍሰቱን እንደሚጨምረው ይገልፃሉ፡፡ ሚኒስትሯ እንደሚሉት፣ አገልግሎቱ መንግሥት አገሪቱ ከመላው ዓለም ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር የወሰዳቸው እርምጃዎች አካል ነው፡፡ የቱሪስት ፍሰቱን እንዲጨምር በማድረግም «ምድረ ቀደምት (Land of Origins)» የሚባለው የአገሪቱ የቱሪዝም መታወቂያም በብዙዎች ዘንድ እውቅና እንዲያገኝ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል፡፡
የምጣኔ ሀብትና ፖለቲካ ጉዳዮች ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ብርሁተስፋ የኢ-ቪዛ አገልግሎት ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፣ በቅርቡ ይፋ የሆነውና ለሁሉም አገራት ዜጎች ክፍት የሆነው የኢ-ቪዛ አገልግሎት የ«ቪዛ» አሰጣጥ ሥርዓቱን ቀልጣፋ በማድረግ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምርና በርከት ያሉ ባለሀብቶች ወደአገሪቱ መጥተው በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ያደርጋል፡፡
ያደጉት አገራት ብቻ ሳይሆኑ የአፍሪካ አገራትም በዚሁ ሥርዓት መጠቀም ከጀመሩ ብዙ ዓመታት እንደተቆጠሩ የሚያወሱት ባለሙያው፣ እርምጃው ኢትዮጵያ ለውጭ ጎብኚዎችና ባለሀብቶች የበለጠ ክፍት ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝም ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎቱ የቪዛ አሰጣጥ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የኤምባሲዎችን ሥራ እንደሚያቃ ልልም ያብራራሉ፡፡
ከዚህም ባለፈ የኢ-ቪዛ ሥርዓቱ ለቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስሮችም ፋይዳ እንዳለው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይገልፃሉ፡፡ እንደርሳቸው ገለፃ፣ አገልግሎቱ የአፍሪካ ኅብረት የወሰነውን የአፍሪካውያንን ነፃ እንቅስቃሴ ውሳኔ ለማስፈጸም የሚያስችል እርምጃም ነው፡፡ ኅብረቱ አፍሪካውያን በአህጉሪቱ ውስጥ አንድ ወጥ በሆነ ፓስፖርት እንዲዘዋወሩ የሚያስችል መርሃ ግብር ከዚህ ቀደም ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ የኢ-ቪዛ ሥርዓት ደግሞ ቪዛ በቀላሉ ለማግኘት ስለሚያስችል ኢትዮጵያ የኅብረቱ ውሳኔ ተፈፃሚ እንዲሆን የራሷን አስተዋፅዖ እንድታበረክት የሚያስችላት አሠራር ነው፡፡
«የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የማቃለል ጉዳይም የአገልግሎቱ ሌላኛው ፋይዳ ነው፡፡ የኢ-ቪዛ አገልግሎት የቱሪስቶችን ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲያድግ ያደርጋል፡፡ በዚህም ምንም እንኳ አገሪቱ ለገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ብቻውን መፍትሄ መሆን ባይችልም የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል» ይላሉ፡፡

አንተነህ ቸሬ

Published in ፖለቲካ

በኢትዮጵያ ለባለሀብቱ በተፈጠረው ምቹ ዕድል ተጠቅመው በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ከተሰማሩት መካከል አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አንዱ ሲሆን፤ በዘርፉ በሀገሪቷ ግዙፍ ከሚባሉት ኢንዱስትሪዎች መካከልም ተጠቃሽ ነው። ቁጥሩ ስድስት ሺ የሚሆን የሰው ኃይል ይዞ ላለፉት 22ዓመታት በሥራው ላይ የቆየው አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አሁን ከሚገኝበት ደረጃ የላቀ ሆኖ ለመገኘት እየሠራ መሆኑን የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅና ተጠሪ ተወካይ አቶ ተክለማርያም ተስፉ ይገልጻሉ።
ከመንግሥት ወደግል የዞረው ጥቁር አባይ ጫማ ፋብሪካም ከመንግሥት በግዥ የወሰደውን አንድ ፋብሪካ ወደ ሦስት አድርሶ የማምረት አቅሙን በማሳደግና የሰው ኃይሉንም ከሶስት መቶ ወደ ስምንት መቶ ከፍ በማድረግ ፋብሪካው በመንግሥት ይዞታ ስር ሆኖ ይሠራ ከነበረበት በተሻለ ማምረት የሚችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ መደረጉን የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ተክሉ ያስረዳሉ። ፋብሪካዎቹ ሀገሪቷ ከቀረጥ ነፃና ሌሎችንም ማበረታቻዎች በማመቻቸት ባለሀብቶችን ለመሳብ በምታደርገው ጥረት እንዲህ ውጤታማ የሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ መቻሏ ማሳያዎች ናቸው።
ሀገሪቷ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለመሸጋገር ብሎም በ2025ዓ.ም. መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመሳብ እንቅስቃሴዋን ቀጥላለች። በቅርቡም በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎችና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሙሉ በሙሉና በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደግል እንዲዘዋወሩ በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይፋ መሆኑ ይታወሳል።
ጥሪው የሀገር ውስጥንም የውጭ ባለሀብቶችንም የሚያሳትፍ ቢሆንም የሀገር ውስጥ ቅድሚያ የሚያገኙበት እድል መኖሩ ይነገራል። ይህን ጥሪ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዴት ያዩታል? ዝግጁነታቸውስ ምን ይመስላል? የሚለውን በግሉ ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱት መካከል አንዳንዶቹን አነጋግረናቸዋል። የአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅና ተጠሪ ተወካይ አቶ ተክለማርያም ተስፉ የሀገር ውስጥ ባለሀብት የአክሲዮን ሽያጩ ተሳታፊ ይሆናል ብሎ ለማሰብ ያዳግታል ይላሉ። እንደ አቶ ተክለማርያም ማብራሪያ መንግሥት ኢንዱስትሪው እንዲስፋፋ ፍላጎት ቢኖረውም ድጋፉ አነስተኛ ነው። አክሲዮን ሊገዙ የሚችሉ ባለሀብቶችን አልፈጠረም። የተጠናከረ አቅም ያለው ባለሀብት ቢኖርም በጣም አነስተኛ ነው። አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ላለፉት 22ዓመታት በሥራው ውስጥ የቆየው ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ነው። ከመንግሥት ያገኘው በቂ የሆነ ድጋፍ የለም። ለምርቱ የሚሆን የጥጥ ግብአት በጊዜ፣ በመጠንና በጥራት ማግኘት ትልቁ ፈተና ነበር። ችግሩ በመንግሥት ቢታወቅም እስከዛሬ አልተፈታም። ከውጭ የሚገባው ጥሬ ዕቃም በወቅቱ ባለመግባቱ በማምረት ሂደቱ ላይ ከፍተኛ መጓተት እየፈጠረበት ይገኛል። ከፋብሪካው ወደተጠቃሚው ምርቱን ለማጓጓዝም የማጓጓዣ ትራንስፖርት አቅራቢው የሚጠይቀው ዋጋ የተጋነነና ውድ ነው። ሀገሪቷ ውስጥ የደረቅ ጭነት ታሪፍ አለመውጣት አገልግሎት ሰጭው የፈለገውን ዋጋ እንዲጠይቅ መንገድ ከፍቷል።
«በአሁኑ ጊዜ ተጠቃሚው ገበያ ውስጥ የቻይና ምርት ከእኛ ምርት በዋጋ በተሻለ ያገኛል»ያሉት አቶ ተክለማርያም የቻይና ፋብሪካዎች ከኢትዮጵያ በተሻለ ድጋፍ ስለሚደረግላቸው ምርታቸውን ለተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ መቻላቸውን በንፅፅር ይገልጻሉ። የተለያዩ ተግዳሮቶችን አልፎ ሁለት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የውስጥ አቅሙን በማጠናከርና ውጫዊ ችግሮችንም ተጋፍጦ ለመቀጠል የሚያስችለውን እቅድ ነድፎ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል እየሠራ መሆኑን ነው ሥራ አስኪያጁ ያስረዱት። መንግሥት ድርጅቶችን ለአከሲዮን ከማቅረቡ በፊት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን አቅም መፈተሽና አቅማቸውን የመገንባት ሥራ በቅድሚያ ማከናወን እንደነበረበትም ተናግረዋል። በተለይም የጨርቃጨርቅ ዘርፉ ብዙ የሰው ኃይል በመያዝ ቀዳሚ መሆኑ ግምት ውስጥ መግባት እንደነበረበትም ገልጸዋል።
ተወዳዳሪነት ለፋብሪካቸው ስጋት አለመሆኑን የገለጹት የጥቁር አባይ ጫማ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ተክሉ ተቋማቸውን የሚያሰጋ ነገር ባይኖርም እንደሀገር ግን መታየት እንዳለበት ያምናሉ። እርሳቸው እንዳሉት የውጭ ባለሀብቶች በሁለት መንገድ ድጋፍ ያገኛሉ። ከሀገራቸው መንግሥትና ከኢትዮጵያ መንግሥት። ከሁለት በኩል ድጋፍ ከሚያገኙ ባለሀብቶች ጋር ተወዳዳሪ መሆን ብዙ የሀገር ውስጥ ባለሀብትን ይፈትናል። በሀገር ውስጥ ባለሀብት ሊሠሩ የሚገባቸው ዘርፎች ላይ የውጭ ባለሀብቶችን የመጋበዝ ሁኔታም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በቴክኖሎጂ ሽግግር ስም የሚደረገው ጥሪም ሊታሰብበት ይገባል። ቴክኖሎጂው መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑ ሳይረጋገጥ ባለሀብቱ እንዲመጣ ከተደረገ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን መጠንቀቅ ይገባል።
አቶ አበበ እንዳሉት ሀገር ውስጥ ሊስተካከሉ የሚገቡ ብዙ ነገሮች አሉ። የግብአት አቅርቦት፣ ከባንክ ጋር ያለው አሰራር፣ የኢንቨስትመንት አዋጁን መተግበር፣ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓቱን ማጠናከር፣ በፍትሃዊነት አገልግሎት መስጠት ጥቂቶቹ ይጠቀሳሉ። ነገሮችን በጥንቃቄ ማየት ከተቻለ ለአክሲዮን የቀረቡትን ኩባንያዎች የሀገር ውስጥ ባለሀብት ለመግዛት የማይችልበት ምክንያት እንደሌለ ያስረዳሉ።
«መንግሥት የሀገሪቷን ባለሀብት አቅም ፈትሾና ድርጅቶቹም በግል ስር ሆነው ቢንቀሳቀሱ ለቁጥጥር፣ ለልማትና ለእድገት ፈጣን መንገድ ይሆናል ብሎ ቀድሞ አስቦበት ነው ውሳኔ ላይ የደረሰው»ያሉት የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበርና የኢትዮጵያ በንግዱ የተሰማሩ ሴቶች ማህበራት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ ወቅታዊና ጥሩ የሆነ ውሳኔ እንደሆነ ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በአክሲዮን ሽያጩ ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሚሆንም ያምናሉ። የውጭ ባለሀብቶች ቢሳተፉ ጥቅሙ ብዙ እንደሆነም ይገልፃሉ። የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ሀገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ ችግርን ለመፍታት እንዲሁም ያላቸውን እውቀትና የሚጠቀሙበትን የሥራ ማቀላጠፊያ ቴክኖሎጂ ይዘው ስለሚመጡ ከእነርሱ የሚገኘው ተሞክሮ ጥቅሙ ከፍተኛ እንደሚሆን ያስረዳሉ። የቴክኖሎጂ ሽግግሩ የሀገር ፍላጎትን አሟልቶ ምርትና አገልግሎትን ለውጭ ሀገር ገበያ ለመላክ፣ በሚገኘው ገቢም የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ እንዲሁም ሌሎች ሀገራት የደረሱበት የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚኖረው ሚና ቀላል እንደማይሆን ይናገራሉ። እርምጃው ሴት ባለሀብቶችንም እንደሚያነቃቃና እንደ ሚያበረታታም ገልጸዋል።
እንደ ወይዘሮ እንግዳዬ ማብራሪያ በውሳኔውና በእነርሱ በኩል ማድረግ ስላለባቸው ዝግጅትም ተወያይተዋል። በአሁኑ ጊዜ በመኖሪያ ቤትና በተለያየ የግንባታ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ የማህበሩ አባላት ቢኖሩም አብዛኞቹ በአነስተኛ የንግድ ሥራ ውስጥ ናቸው። ከአነስተኛ ንግድ ውስጥ ለመውጣት በጋራ አቅም የሚፈጠሩበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ይገኛሉ። ጠንካራ አቅም ለመፍጠር ቁጠባ ጀምረዋል። የቁጠባ ባህላቸውን ማዳበር ከቻሉ በቀረቡት የአክሲዮን ሽያጭ ላይ በቀላሉ ለመሳተፍ ያስችላቸዋል። በዚህ ረገድ መልካም ጅምር ቢኖርም በጋራ ቁጠባን ባህል ማድረግና ተቀናጀቶ ለመሥራት ያለው ፍላጎት ገና እንደሆነና በዚህ ላይ ማህበሩ እየሠራ ይገኛል። የአስተሳሰብ ለውጥ ላይም መሠራት እንዳለበት ማህበሩ ያምናል። ዓለም ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለመራመድ በገንዘብ አቅም መፍጠር ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብ ለውጥም ዝግጁ ሆኖ መገኘት እንደሚገባ ወይዘሮ እንግዳዬ ተናግረዋል።
አስፈላጊውን ነገር ለማሟላት ዝግጁነቱ ካለ የውጭ ወይም ከፍተኛ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች በሀገር ውስጥ ለሚገኙ ባለሀብቶች ስጋት የሚሆኑበት ምክንያት እንደማይኖር የሚናገሩት ወይዘሮ እንግዳዬ አብላጫው ድርሻ የመንግሥት መሆኑ በሥራ ሂደት ችግር ቢያጋጥም ቶሎ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚያስችልም ገልጸዋል። ከስጋት ተላቅቆ ለሀገር የሚበጀው ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የምጣኔ ሀብት አማካሪው ዶክተር በየነ ታደሰ እንዳሉት በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችና በተለያዩ አካላት በተለያየ መድረክ ሲነሳ የቆየ ጉዳይ በመሆኑ ውሳኔው ትክክለኛና ተስፋ ሰጭ ነው። ወደተግባር ሲገባ ግን የኢኮኖሚ የበላይነቱ በውጭ ሀገር ዜጎች እንዳይያዝ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በዚምባቡዌና ኬንያ ውስጥ የታየው የውጭ ሀገር ዜጎች የኢኮኖሚ የበላይነት ዜጎችን በባርነት ቀንበር ውስጥ እንደጣላቸውና ችግር ያስከተለ መሆኑ አይዘነጋም። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማበረታታት መልካም ቢሆንም በሙስና የሚጠረጠሩ ባለሀብቶች ሁኔታም በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል፡፡
በአክሲዮን ሽያጩ አፈፃፀም ላይ መንግሥት የክትትልና ቁጥጥር ሥራውንም አብሮ ካላጠናከረ ባለሀብቶች ገንዘብ ስላላቸው ብቻ፣ የሀገር ሀብት ለተሻለ አገልግሎት እንዲውል ካልተደረገና ለመንግሥት የሚገባውንም ጥቅም ማስገኘት ካልቻሉ ጉዳቱ ያመዝናል። ከዚህ ቀደም ወደግል የተላለፉ ሰፋፊ እርሻዎች፣ ሆቴል ቤቶችና የተለያዩ ድርጅቶች ቀደም ሲል ከነበራቸው አገልግሎት የተሻሉ አለመሆናቸውን ለአብነት በመጠቆም፣ በሁሉም አቅጣጫ ጥቅም በሚያስገኝ መልኩ ካልተቃኘ ወደግል ማስተላለፉ ብቻውን ግብ አይሆንም፡፡ የሠራተኞችን ጥቅም በማስከበር በተለይም በደመወዝ ክፍያ ችግሮች መኖራቸውንና በዚህ ረገድም ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ተሞክሮዎች ያሳያሉ።፡፡
አሁን በአክሲዮን ለመሸጥ ውሳኔ ያገኙት ድርጅቶች መንግሥት ከዚህ ቀደም አቅም ያለው ባለሀብት የለም፣ ፈቃደኝነትም የለም፣ ትላልቅ ድርጅቶች ለመንግሥት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ በመሆናቸው ለግሉ አይሰጡም የሚሉ ምላሾችን በመስጠት የቆዩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ለምለም መንግሥቱ

Published in ኢኮኖሚ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከኢራን ነዳጅ እንዳይገዙ ጥሪ ማቅረባቸውና ለተፈፃሚነቱም ግፊት ማድረጋቸው ልዕለ ኃያላኗ አሜሪካ እና ኢራን የነበራቸውን አለመግባባት ከድጡ ወደ ማጡ ወስዶታል፡፡
ይህን ተከትሎም ኢራን የነዳጅ ምርት ሽያጯን በግል ኩባንያዎች በኩል በማከናወን የአሜሪካን የነዳጅ ማዕቀብ ጥሪ እንደምታከሽፍ አስታውቃለች፡፡ የአሜሪካ የማዕቀብ ሙከራም አደገኛ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቃለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢራን የነዳጅ ላኪ አገራት ድርጅት አባላት የነዳጅ አቅርቦትን በጋራ ለመጨመር የገቡትን ስምምነት እንዲያከብሩና አባል አገራቱ ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡትንና ወደ ሌሎች አገራት የሚልኩትን የነዳጅ ምርት እንዲጨምሩ ጥሪ አቅርባለች፡፡
የኢራን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሃኒ ለስራ ጉብኝት ከሄዱበት ኦስትሪያ ቬይና ሆነው በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹አሜሪካውያን የኢራንን የነዳጅ ምርት ዜሮ ስለማድረግ ያስባሉ፤ ነገር ግን ይህ ሃሳባቸው ምን ዓይነት ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል አላሰቡበትም፡፡ ይህ ሙከራ አደገኛ ውጤት ስለሚያስከትል ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል›› ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ ኢራን የነዳጅ ምርቷን ለዓለም ገበያ እንዳታቀርብ የምትገደድ ከሆነ ለቀጣናው አገራት የምታቀርበውን ምርቷን ልታቆም እንደምትችልና ያን ጊዜ ለሚፈጠረው የዋጋ ንረትም ኃላፊነት እንደማትወስድ ፕሬዚዳንቱ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ሜጀር ጀኔራል ቃሲም ሱሌማን የተባሉ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ነባር አመራርም ከፕሬዚዳንቱ መግለጫ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ የኢራን የነዳጅ ምርት በአሜሪካ ማዕቀብ የሚጣልበት ከሆነ አገራቸው ለቀጣናው የምታቀርበውን ምርት እንደምታቋርጥ ገልፀዋል፡፡ ለዚህ እርምጃ ትግበራም በግላቸው ዝግጁ እንደሆኑ የዘብ አመራሩ ተናግረዋል፡፡
የአብዮታዊ ዘቡን የውጭ ጉዳዮች የሚቆጣጠረው ‹‹ቁድ›› የተባለው ኃይል አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጀኔራል ቃሲም ሱሌማን፣ ‹‹ፕሬዚዳንት ሮሐኒ ይህን መሰል ጠቃሚና ጊዜውን የጠበቀ ሃሳብ መስጠታቸውን በጣም አደንቃለሁ፡፡ የእስላማዊ ሪፐብሊኩን ጥቅም የሚያስጠብቅ ማንኛውንም ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ›› በማለት እስላማዊ ሪፐብሊክ የዜና ድርጅት ለተባለው የኢራን ብሔራዊ የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ ከ2015ቱ የኢራን ኑክሌር ስምምነት ከወጣች በኋላ የኢራንን ምጣኔ ሀብት ለማሽመድመድ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው፡፡ ከነዚህም እርምጃዎች መካከል ከቀጣዩ ኅዳር ወር ጀምሮ ከኢራን ነዳጅ የሚገዙ አገራት ከኢራን መግዛታቸውን እንዲያቆሙ አልያም ነዳጅ ከኢራን መግዛታቸውን ካላቆሙ አሜሪካ ከባድ የቅጣት እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች፡፡
ለዚህ የአሜሪካ ዛቻም ምላሽ የሰጡት የኢራን ባለስልጣናት ዋነኛ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር የሆነውን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ እንደሚዘጉ ተናግረው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ የማዕቀብ ሙከራ የነዳጅ ዋጋን በማናር የራሷን ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ ባለስልጣናቱ ገልጸዋል፡፡
ለኢራን ባለስልጣናት ማስጠንቀቂያ ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ ቃል አቀባይ ካፒቴን ቢል አርባን፣ የባህረ ሰላጤው የባህር ላይ መስመሮች ለንግድ እንቅስቃሴ ክፍት እንደሚሆኑና መስመሮቹን ለመዝጋት የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ዋጋ እንደሚያስከፍል ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሜሪካና የቀጣናው አጋሮቿ ዓለም አቀፍ ሕጎች ባስቀመጧቸው ድንጋጌዎች መሰረት በባህር መስመሮቹ ላይ የንግድ እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እንዲከናወኑ አስፈላጊውን እገዛና ጥበቃ ያደርጋሉ›› ብለዋል፡፡
ከፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሐኒ መግለጫ ቀደም ብሎ ለአሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ሃሳባቸውን ያካፈሉት ቃል አቀባዩ፣ አሜሪካ ሕጋዊ የባህር ላይ እንቅስቃሴዎች ያለምንም መስተጓጎል እንዲከናወኑ ኃላፊነቷን ትወጣለች ብለዋል፡፡
አሜሪካ ነዳጅ ከኢራን የሚገዙ አገራት ከመጪው ኅዳር ጀምሮ ከኢራን መግዛታቸውን እንዲያቆሙና መግዛታቸውን ካላቆሙ ግን በሁሉም አገራት ላይ እርምጃ እንደምትወስድ የሰጠችው ማስጠንቀቂያ ደግሞ የኢራንን ብዙ የነዳጅ ምርት ከሚገዛው የአውሮፓ ኅብረት ጋር ያፋጥጣታል፡፡ በስደተኞች ጉዳይና በቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ጫና ውስጥ ያለው የአውሮፓ ኅብረትም አሜሪካ በኢራን የነዳጅ ምርቶች ላይ የጣለችውን ማዕቀብ እንድትሰርዝ ጠይቋል፡፡
ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ቬይና ውስጥ የተገኙት የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሐኒ፣ በ2015ቱ የኢራን ኑክሌር ስምምነት ውስጥ የቆዩት አገራት የኢራንን ጥቅም እንደማይጎዱ ተጨባጭ ዋስትናና ማረጋገጫ ከሰጡ በስምምነቱ ውስጥ እንደምትቆይ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢራን የአሁኑንም የአሜሪካን የማዕቀብ ሙከራ ከዚህ ቀደም እንደተጣሉባት ማዕቀቦች ሁሉ ትቋቋመዋለች፤ የአሜሪካ ድርጊት የወረራ ወንጀል ነው›› ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ሩስያ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይና ቻይና እ.ኤ.አ በ2015 የተፈረመውንና ባለፈው ግንቦት ወር አሜሪካ ጥላው የወጣችውን የኢራን የኑክሌር ስምምነት እንደሚያከብሩ በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡ የእነዚህ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ስምምነቱ ተጠብቆ ስለሚቀጥልበት ሁኔታ ከኢራን ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ለዛሬ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን እ.ኤ.አ በ2015 በኢራንና በስድስቱ የዓለማችን ኃያላን አገራት (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩስያ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ) መካከል ከተፈረመው የኢራን የኑክሌር ስምምነት አስወጣታለሁ እያሉ ሲዝቱ ቆይተው ባለፈው ግንቦት ወር ከስምምነቱ እንዳስወጧት የሚታወስ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 በኢራንና በስድስቱ የዓለማችን ኃያላን አገራት (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩስያ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ) መካከል የተፈረመውን የኢራን የኑክሌር ስምምነት ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታዋን እንድታቆምና በምላሹም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአሜሪካ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ይደነግጋል፡፡ ኢራን ስምምነቱን የማታከብር ከሆነም ቀደም ባሉት ጊዜያት ከተጣሉባት ማዕቀቦች የከፋ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተፅዕኖ ያላቸው ማዕቀቦች እንደሚጣሉባት፤ ከዚያም አልፎ ጉዳዩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንደሚቀርብ በስምምነቱ ውስጥ ከተካተቱት ድንጋጌዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡
ከስምምነቱ መፈረም በኋላም ኢራን የስምምነቱን ድንጋጌዎች ተቀብላ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ በናታንዝ እና ፎርዶ ጣቢያዎች የሚገኙ ግብዓቶች እንዲወገዱ ተደረጉ፤ በብዙ ቶን የሚቆጠር ዩራኒየም ወደ ሩስያ እንዲወሰድ ተደረገ፡፡ ከዚህ ባሻገርም፣ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ተቆጣጠሪ ድርጅት ባለሙያዎች የኢራንን የኑክሌር መሳሪያ ግንባታ በየጣቢያዎቹ ተገኝተው መታዘብ ችለዋል፡፡
ስምምነቱ ሲፈረም አሜሪካን ሲያስተዳድሩ የነበሩት የወቅቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስምምነቱ እንደትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ተቆጥሮላቸዋል፡፡ ኦባማን ተክተው ወደ ነጩ ቤት የመጡት ቢሊየነሩ ዶናልድ ትራምፕ ግን ስምምነቱን መቀበል ይቅርና ስለስምምነቱ መስማት አይፈልጉም፡፡ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹የምንጊዜውም መጥፎው ስምምነት›› እያሉ የሚያብጠለጥሉትን ይህን ስምምነት እንደሚሰርዙት ያስታወቁት ገና በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ነበር፡፡
ትራምፕ ስምምነቱ ኢራንን ለተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ከኑክሌር ማበልጸግ ተግባሯ የሚገታ እንጂ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ባሊስቲክ ሚሳይሎችን ከማምረት የሚያግዳት አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ እንዲያውም ስምምነቱ ኢራን በውጭ አገራት ባንኮች ያላትንና እንዳይንቀሳቀስ ታግዶባት የነበረውን 100 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንዲለቀቅላት ስላደረገ ኢራን ገንዘቡን ሽብርተኞችን ለመደገፍ፣ የጦር መሳሪያ ለመግዛት እንዲሁም አክራሪነትን ለማስፋፋት ተጠቅማበታለች ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራን የኑክሌር ስምምነትን የማይቀበሉባቸው ምክንያቶች ብዙ እንደሆኑ በተንታኞች ዘንድ ይገለፃል፡፡ ሰውየው የአሜሪካ ጠንካራ አጋርና ወዳጅ የሆነችውን እስራኤልን ለማጥፋት እቅድ አላት የምትባለው ኢራን የኑክሌር መሳሪያ ታጥቃ ማየት አይፈልጉም፡፡ የልጃቸው ኢቫንካ ትራምፕ ባለቤት የሆኑት አይሁዳዊው ጃሬድ ኩሽነር የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ መሆን ደግሞ ሰውየው ለኢራን ያላቸውን ጥላቻ ይባብሰዋል ብለው የሚናገሩ አካላትም አሉ፡፡ ትራምፕ ለእስልምና ያላቸው ‹‹የጥላቻ አመለካከት›› እስላማዊቷን ሪፐብሊክ (ኢራንን) ለመጥላት ምክንያት ሳይሆናቸው አይቀርምም ተብሏል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ከ1978/79 እስላማዊው የኢራን አብዮት በኋላ ሆድና ጀርባ ከመሆን አልፈው የጦር መሳሪያ ለመማዘዝ የሚቃጡት አሜሪካና ኢራን ቁርሿቸው ከግለሰባዊ ስሜት የዘለለና አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ነው፡፡
የስምምነቱ ፈራሚ የሆኑ የአውሮፓ አገራት (ብሪታኒያ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ) ግን ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንዳትሆን ለማድረግ ስምምነቱን አክብሮ ከመቀጠል የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ደጋግመው ገልፀዋል፡፡
ትራምፕ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከኢራን ነዳጅ እንዳይገዙ ጥሪ ያቀረቡትና ግፊት ያደረጉትም የኢራንን ምጣኔ ሀብት በማሽመድመድ ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታዋ ለመግታት በማሰብ እንደሆነ ይነገራል፡፡

አንተነህ ቸሬ

Published in ዓለም አቀፍ

እኛ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዘመናት ነዳጅ ባላቸው አገራት እድገትና ብልፅግና ስንቀና ኖረናል፡፡ እነርሱ በኢኮኖሚ በልፅገውና ዜጎቻቸው የተንደላቀቀ ኑሮ ሲመሩ ማየታችንና ማድመጣችን እንድንቆጭ አድርጎናል፡፡ እነዚህ በነዳጅ ምርት የበለፀጉ አገራት ኢኮኖሚያቸውን በነዳጅ ሽያጭ ላይ የተመሰረተ ቢያደርጉም ውሎ አድሮ የዓለም ዋጋ ማሻቀብና መውረድ ሲፈታተናቸውና የገነቡትን ኢኮኖሚ አደጋ ውስጥ ሲጥለው ይታያል፡፡
ለምሳሌም ቀደም ሲል ያሽቆለቆለው የነዳጅ ዋጋ እ.ኤ.አ. 2015 በርካታ የዓለም ነዳጅ አምራች አገሮች ዋጋው ከወደቀበት ይነሳል የሚል ተስፋ ቢፈነጥቅላቸውም በቀጣዩ ዓመት ተስፋ ያለው አልሆነም፡፡ ይልቁንም ከዚህ ቀደም የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 115 ዶላር ደርሶ እንደነበረው ብዙም ሳይቆይ ተመልሶ ዝቅ እንደሚልና እስከ 2020 ድረስ ወይም ከዚያም ለበለጠ ጊዜ በጣም እንደሚያሽቆለቁል በተለያዩ ጊዜያት የታዩት የዋጋ መለዋወጦች ያስረዳሉ፡፡
በዚህ የነዳጅ ዋጋ መውረድ ምክንያት ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሩሲያ፣ ቬንዙዌላና ናይጄሪያ ምንም እንኳ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ የነዳጅ ሀብት ያላቸው አገሮችም ቢሆኑም የዋጋ መውረዱ ችግር ተጠቂ ሲሆኑ ታይቷል፡፡
ነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጫቸውን የነዳጅ ገቢ በመሆኑ የዋጋ መውረድ የበጀት ጉድለትን እያስከተለባቸው ቢሆንም ሳዑዲ አረቢያ ግን ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በወሰደቻቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ከነዳጅ ጥገኝነት የመላቀቅ ስራን በመስራት ላይ ትገኛለች።
በነዳጅ የወደፊት እጣ ፈንታ ብዙም ያልተማመነችው ሳዑዲ ኢኮኖሚዋን ቀስ በቀስ ከነዳጅ ጥገኝነት ለማላቀቅ ረዘም ያለ እቅድ ነድፋ መሥራት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህም የሳዑዲ ባለሀብቶች ከራሳቸው አገር ጀምሮ በተለያዩ አገራት ሰፊ የኢንቨስትመንት ስራን በማከናወን ላይ ናቸው። ይህ ስራ በመስራታቸው የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ መውረድም ለሳዑዲ ኢኮኖሚ ፈተና አልሆነም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ለነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት ፈተና ቢሆንም ለሸማች አገራት ግን አጋጣሚው መልካም ሆኖላቸዋል፡፡
በሌላም በኩል በርካታ አገራት ነዳጅ እንዲኖራቸው ቢመኙም ከዓለም አቀፉ የአየር ሙቀት መጨመር ጋር በተያያዘ ነዳጅን በሌሎች አማራጭ የኢነርጂ ምንጮች ለመተካት በአንዳንድ አገራት እየተደረገ ያለው ጥረት በተለይም በአውሮፓና በአሜሪካ በኤሌክትሪክ፣ በባትሪና በሶላር የሚሰሩ ቁሶች መመረታቸው ለነዳጅ አምራች አገራት ስጋትን ፈጥሮባቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የነዳጅ ምርት ባለቤት እየሆኑ ያሉ ሀገራት ቁጥር እየጨመረ መሄድ የዓለም የነዳጅ ላኪ አገራት ድርጅት የወደፊቱ ገበያ ላይ ስጋት ፈጥሯል።
ለምሳሌ አሜሪካ በከፍተኛ ደረጃ አላት ከሚባለው የነዳጅ ክምችት ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መጠቀም መጀመሯ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለነዳጅ ዋጋ መውረድ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። በዚሁ የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ኢኮኖሚያቸው ክፉኛ እየተጎዱ ካሉት አገራት መካከል አንዷ ሩስያ ስትሆን ለአለም አቀፉ ነዳጅ መውደቅም አሜሪካንን ተጠያቂ አድርጋለች።
የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር የሚችለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ኢኮኖሚ መሻሻል ሲያሳይና የነዳጅ ፍላጐት ሲጨምር ብቻ መሆኑም ብዙ አገራትን ያስማማ ጉዳይ ሆኖ መዝለቁ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ዘይት አሳሽ ኩባንያዎች ከዚህ ቀደም የተሣካ ውጤት ያለማግኘታቸው ምክንያቱ በውል ባይታወቅም በምሥራቅ ኢትዮጵያ ለ7 ዓመታት በ 42 ሺ ካሬ ኪሎሜትር ቦታ አሰሳና ቁፋሮ ለማካሄድና ለ 25 ዓመታት የሚገኘውን ሃብት ለመካፈል ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል 4 ትሪሊዮን ኩብ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ከምችት እንዳላት ቢገለፅም እስካሁን አውጥታ ጥቅም ላይ ያዋለችው ተመሳሳይ የተፈጥሮ ሀብት የለም። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ነዳጅ ዘይት ለማግኘት ያለው ተስፋ የሚያማልል ነው፡፡
በአገራችን ባለፉት ሰባ ዓመታት በኦጋዴን አካባቢ ሲካሄድ የቆየው የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ውጤታማ ሆኖ በፖሊጂሲኤል ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት የቻይና ኩባንያ አማካኝነት ሂላላ በተባለው ሥፍራ የተገኘውን ድፍድፍ ነዳጅ የሙከራ ምርት ማውጣት ሥራ ተጀምሯል፡፡ በዚህ ታላቅ የዜና ብስራት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ እንደተናገሩት ከጋዝ የወጪ ንግድ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ገልጸው፤ስራ አጥነትን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍና ዘላቂ እድገትን ለማምጣት ይረዳል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሃብት አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የነበረው ልዩነት ይህን ሃብት በአግባቡ እንዳንጠቀም አድርጎ መቆየቱን ፣ የተገኘውን የተፈጥሮ ሃብት በእኩልነትና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በጋራ መጠቀም እንደሚገባ፣ የተፈጥሮ ሃብትን መቀራመት ትልቁ የአፍሪካውያን ችግር መሆኑን ፣አሁን የተገኘውን ሃብትም በሰላማዊ መንገድና በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ፣ የተገኘው ድፍድፍ ነዳጅም አዳዲስ ሃብቶችን ለማምጣት እንደሚያግዝና በቀጣይም የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገኘው ሃብት ለብጥብጥ ሳይሆን ለጋራ ተጠቃሚነት እንዲውል ጥሪ አቅርበው ህብረተሰቡም ከሃብቱ ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በርግጥም በድህነት ተሳስቦ ይኖር የነበረ ህብረተሰብ ሀብት ሲገኝ ወደ ብጥብጥ የሚያመራ ከሆነ ምነው ሀብቱ ባልተገኘ የሚያስብል ሊሆን ይችላል፡፡ በአገራችን የተገኘው ድፍድፍ ነዳጅም አዳዲስ ሃብቶችን ለማምጣት የሚያግዝ ፣ልማታችን እንዲፋጠን የገንዘብ እጥረትን በመቅረፍ ለበርካታ ታላላቅ ፋብሪካዎች መገንቢያ የሚውል ገቢ የሚያስገኝ ፣ ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብአት የሚሆኑ የማዳበሪያና የፀረ ተባይ መከላከያ መግዣና አገሪቱ በመሰረተ ልማት በማህበራዊና በኢኮኖሚ መስክ ላቀደቻቸው ታላላቅ ዕቅዶች ማሳኪያ ደጋፊ እንደሚሆን አያጠራጥርም ፡፡
የአገራችን ኢኮኖሚ መሰረቱን ያደረገው በግብርና ውጤቶች ላይ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ይህንን የኢኮኖሚ ዋልታ ኋላ ቀር በሆነ አሰራር በአዝጋሚ ሁኔታ ለበርካታ ዓመታት ይዘን መጓዛችን በድህነት ውስጥ እንድንቆይ አስገድዶናል፡፡ ባለፉት ጥቂት የሚባሉ ዓመታት ግን ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ዘመናዊ የአስተራረስ ዘይቤን በመላበስ፣ ምርጥ ዘርን በመጠቀም፣ የግብርና ኤክስቴንሽን አሰራርን በመከተል፣የምርት አሰባሰብን በማሻሻል መላ አገሪቱን ሊመግብ የሚችልና ለአደጋ ጊዜ የመጠባበቂያ ክምችት ለመያዝ ያስቻለ ስራ ተከናውኗል፡፡
ይህንን የአገሪቱን የኢኮኖሚ መሰረት ሳንለቅ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው የገቢ ምንጭ ማግኘታችን ለሕዝባችን ታላቅ የምስራች ይዞ የመጣ ቢሆንም ባለን ላይ የሚጨመር ፣ መሰረተ ልማታችንን የሚያሳድግ፣ ለመገንባት ላቀድናቸው ፕሮጀክቶች ደጋፊ የሚሆን ፣ አምራች ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችሉ ተቋማትን መገንባት የሚያስችል፣ የጤና ተቋማቶቻችንን የሚያሰፋና የሚያሳድግ፣ ሥራ አጥ ለሆኑ ወገኖቻችን የሥራ ዕድል የሚፈጥር ወዘተ... መሆኑን በማመን ተስፋ ሰንቀን ይህ ትንሹ የድፍድፍ ነዳጅ ምርት በስፋት ወጥቶና ተመርቶ ለአገር ውስጥ ፍጆታና ለዓለም ገበያ ቀርቦ የምናይበትን ወቅት መናፈቅ ይኖርብናል፡፡
በአገራችን የተገኘው ድፍድፍ ነዳጅ መጠን አዋጭ መሆኑ ሲረጋግጥ፣ የነዳጅ ልማት ዝርዝር ተሰርቶ ወደ ምርት የሚገባበት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የምርቱ መጠን የሚታወቅ አይደለም፡፡ ለአገር ውስጥም ሆነ ለዓለም ገበያ ሽያጭ ለማቅረብ የድፍድፍ ነዳጁ ክምችት መጠን መታወቅ ይኖርበታል፡፡ አዋጭነቱ በጥናት ሲረጋገጥ ነው ወደ ልማትና ሽያጭ ምርት መግባት የሚቻለው፡፡ ይህ ደግሞ ጊዜ እንደሚወስድ ሊታሰብ ይገባል፡፡
በካሉብ፣ በሂላላና በገናሌ ለመልማት ከተዘጋጁ መሬቶች በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ያልተገኘ አዲስ የተፈጥሮ የጋዝ ክምችት ዶሃር በተባለ ሥፍራ እንደተገኘም ታውቋል፡፡ዶሃር የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ከሦስት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ በላይ ይገመታል፡፡ ይህ ሥፍራ በካሉብና በሂላላ መካከል የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ የሚለማ ይሆናል፡፡ ትዕግስት ያለውና ጠንክሮ የሰራ የድካሙን አያጣምና መላ ኢትዮጵያውያን ለወደፊቱ ዕድገታቸው በጋራ መስራትን፣ መቻቻልን፣ ባለን ላይ መጨመርን በማሰብ ለአገሪቱ ልማት መትጋታቸው ለራሳቸው ልማትና ዕድገት አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ይህ ሳይሆን ቀርቶ በቅርቡ ባሉ ጎረቤቶቻችን እንደምናስተውለው የነዳጅ መኖር ለግጭትና ለስንፍና የሚዳርገን ከሆነ ከተጠቃሚ ነታችን ይልቅ ነዳጅ አናዳጃችን እንጂ ጠቃሚያችን የመሆኑ ነገር ያከትማል፡፡
አገራችን አሁን ያለችበት የኢኮኖሚ እድገት ፈጣንና ወደፊትም በዚሁ እንደሚቀጥል ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ የተገኘው ተስፋ ፈንጣቂ የነዳጅ ምርት ደግሞ ለኢኮኖሚ እድገቱ እንደ አንድ ተጨማሪ አቅም እንጂ ብቻውን የሚሸከመው አለመሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ የያዝነውን ለቅቀን ተስፋችንን በነዳጅ ብቻ አድርገን እድገት የምንጠብቅበት ሁኔታ ውስጥ የሚከትተን አይሆንም፡፡

 አያሌው ንጉሴ

 

 

Published in አጀንዳ

‹‹የሐሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም። ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርህ ላይ ተመሥርተን መግባባት ስንችል የሐሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል። በሐሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሄ ይገኛል። በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ፤ ስንደመር እንጠነክራለን፤ አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም፤ አገር ይገነባል፡፡ የእኔ ሐሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብን ያፈርሳል፤ ያለችን ኢትዮጵያ ነች፤ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ አገራዊ አንድነት ይበልጣል፤ አንድነት ማለት ግን አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፤ አንድነታችን ልዩነቶቻችንን ያቀፈ ብዝኃነታችንን በኅብረ ብሔራዊነት ያደመቀ መሆን አለበት፡፡›› በማለት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ስሜት የሚኮረኩር ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ባደረጉት የሰላም ጥሪ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪውን ተቀብለው ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ይገኛሉ፡፡
ጥሪውን በመቀበል ወደ አገር ቤት የተመለሱት ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ራሳቸውን በመገንጠል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ፣ በብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹ ሲመራ የነበረ የኦሮሞ አንድነትና ነፃነት ግንባር (ኦአነግ) ፣ በብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋና አባ ነጋ ጃራ የሚመራው የተባበረው ኦሮሞ ነፃነት ግንባርና ሞረሽ ለወገኔ የሚባል ድርጅት በአሜሪካ በመመሥረት እቅስቃሴ ላይ የነበሩት አቶ ተክሌ የሻው ሲሆኑ፤ በቀጣይም በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት እንደሚመለሱ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በፓርላማ የመጀመሪያ ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ትጥቅ ትግልና ሰውን በመግደል ሥልጣን መያዝ ኋላ ቀር እንደሆነ፣ የትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲታገሉ ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡ ይህንን ጥሪ መሰረት በማድረግ አርበኞች ግንቦት 7 ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን ተግባራዊ የሚያደርጉና የሕዝቦች ደኅንነት የተጠበቀ ከሆነ የትጥቅ ትግሉን በመተው ወደ አገር ውስጥ ለመግባት ዝግጁ መሆኑን በመግለፅ በቀጣይም ምንም ዓይነት የትጥቅ ትግል ከማድረግ መቆጠቡን አስታውቋል፡፡
እነዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት ገብተው በሰላማዊ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱበት አግባብ ግን ብዙዎችን የሚያነጋግር ነው፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ሰላማዊ ትግልን በመተው የትጥቅ ትግል ያዋጣናል ብለው ጫካ ገብተናል በማለት ጦርነት አውጀው የነበሩ መሆናቸው ስለሚታወቅ የአሁኑን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የሰላማዊ ትግሉ ተካፋይ ለመሆን በዕውነት ተዋጊ ኃይል ካላቸው ይህ ኃይላቸው ምን ሊሆን እንደሚገባ አስቀድሞ መፍትሄ ሊሰጡት ይገባል፡፡
በቀጣይም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው በፖለቲካ ድርጅትነት ዕውቅና ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ፓርቲዎቹ ከአገር ርቀው በመኖራቸው በሰላማዊ የትግል መድረክ ተሳትፈው ለአገሪቱ ሕዝብ ያበረከቱት አስተዋፅኦ በውል የሚታወቅ ባለመሆኑ በአሁኑ ወቅት አገሪቱን እያስተዳደረ ካለው ገዢ ፓርቲ የተሻለ የሚሉትንና በተጨባጭ በተግባር ሊውል የሚችል ተግባራዊ ዕቅድና የፖለቲካ ፕሮግራም በግልፅ የሚያሳውቁበትን መድረክ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ እነርሱም ለህዝቡና ለአገር ይጠቅማል ያሉትን የተጨበጠና በተግባር የሚውል ሃሳብ በማቅረብ ሕዝቡን የሚያሳምን እንቅስቃሴ በማድረግ እስከዛሬ በውጭ አገራት ኖረው የቀሰሙትን በጎ ልምድና ጠቃሚ አሰራር ተግባራዊ የሚሆንበትን አግባብ ማሳየት ልምድ ካላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አዲስ አበባ፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 34ተኛ መደበኛ ስብሰባ በ2003 ዓ.ም በአሸባሪነት የፈረጃቸው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) እና ግንቦት ሰባት ከሽብርተኝነት ስያሜ እንዲሰረዙ ወሰነ፡፡

ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ቀደም ሲል በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶች ስያሜያቸው ተነስቶ በሠላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እንዲያስችላቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 25 ንዑስ አንቀፅ (2) መሰረት በመንግሥት የቀረበለትን መነሻ በማድረግ ደርጅቶቹ ከሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ከሽብርተኝነት ስያሜ እንዲወጣ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡
የፌዴራል ዋና አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ለምክር ቤቱ አባላት የአዋጁን መነሳት ፋይዳ ዝርዝር ሁኔታ እንዲያስረዱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 25 መሰረት ድርጅቶችን የመፈረጅም ሆነ ፍረጃውን የመሻር መብት አለው፡፡ በዚህም መሠረት መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ አዋጁ እንዲሻርና የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጎለበት ጥረት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በአሸባሪነት የተፈረጁት እነዚህ ድርጅቶች ወደ አገሪቱ ውስጥ ገብተው በሠላም እንዲንቀሳቀሱ በመጀመሪያ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለበት ከግምት ውስጥ ያስገባ በመሆኑ፤ ስያሜውን ማንሳት አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል ያሉት ዋና አቃቤ ህግ፤በሠላማዊ ሂደት የማይታገሉና የህዝብና የመንግሥት ጥቅም የሚፃረሩ ከሆነ በህግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚሆኑም አብራርተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የወንጀል ድርጊት ውስጥ ለተሳተፉ ሰዎች ምህረት ለመስጠት በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን፤ ጉዳዩን በዝርዝር ለማየት ያመች ዘንድ ለህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡
የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 እንደሚለው፤ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም የአይዶሎጂ ዓላማን ማራመድ በማሰብ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር፣ ሕብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት፣ የሃገሪቱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ፣ ህገ መንግሥታዊ ኢኮኖሚያዊ ወይንም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት ወይንም ለማፍረስ ሲል በሰው ሕይወት፣ አካል፣ ንብረት፣ ነፃነት ላይ ጉዳት ያደረሰ፣ ድርጊቱን የደገፈ፣ ያበረታታ፣ ወይንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፈ ሰው አሊያም ድርጅት እንደ ወንጀሉ ክብደት እስከ ሞት የሚያደርስ ቅጣት እንደሚያስከትል የተቀመጠ ነው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የወንጀል ህግ አንቀፅ 486 መሰረት፤ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያምፅ በማሰብ በመንግሥት፣ በህዝብ ባለስልጣኖች ወይንም በሥራቸው ላይ የሀሰት ወሬዎችንና ሐሜታዎችን በማውራት ህዝብን ማነሳሳት የተከለከለና የሚያስቀጣ መሆኑም ተደንግጓል፡፡ 

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 

Published in የሀገር ውስጥ

ከ2011 መደበኛና ካፒታል በጀት ውስጥ ከፍተኛው ለትምህርት ተመድቧል፡፡ ይህም በአገሪቱ ቀጣይነት ያለውና ጠንካራ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት የሚኖረው ሚና የጎላ ነው፡፡

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ እንደሚሉት፤ ምንም እንኳን ሁሉም የማይናቅ ሚና ቢኖራቸውም፤ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ በአንድ አገር ትምህርት፣ ጤናና ግብርና ላይ የሚመደበው በጀት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ታሪክ የመቀየር ብቃት አለው፡፡
ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ አጠቃላይ አገር ላይ ኢንቨስት እንደማድረግ ይቆጠራል፡፡ ትምህርት የሌለን ነገር ወደ ማኖር የሚያመጣ፤ ጨለማን ወደ ብርሃን የሚቀየር ነው፡፡ ትምህርት ሲታሰብ ምርታማነት፤ እውቀት እና አመለካከትም አብረው ታሳቢ ይደረጋሉ፡፡ ለአብነትም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋሉ የሥርዓተ አልበኝነት ችግሮች በትምህርት ላይ ከዳር ዳር በጥልቀት ባለመሠራቱ የመጡ ናቸው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ላይ በሚገባ ቢሰራ፣ የአገሪቱ ታሪክ በአግባቡ ቢዳሰስና ምርምር ቢደረግበት ኖሮ ይህ ሁሉ አስነዋሪ ድርጊት ባልተከሰተ ነበር ይላሉ፡፡ ከስሜት የፀዳና ምክንያታዊ ወጣት ለማፍራትም አበርክቶው በቀላሉ የሚለካ እንዳልሆነ ነው የሚያብራሩት፡፡
ዶክተር ጴጥሮስ በርካታ አገራት ከፍተኛ በጀት በትምህርት ላይ በማዋላቸው ስልጣኔ ማማ ላይ ስለመድረሳቸው በአብነት ያስረዳሉ፡፡ ሉግዘንበርግ ምርምር ላይ በማተኮሯ ከስፔስ ሳይንስ በዓመት ከ180 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታገኛለች፡፡ ምርምር ሲደረግ በምጣኔ ሃብት ለመበልጸግ፣ የመደራደር አቅም የማሳደግ እና ሌላም ተፅዕኖ ለመፍጠር ፈርጣማ ያደርጋል፡፡ ፊላንድ የምትባለው አገርም ከ60 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ አኳያ ስትታይ ድሃ አገር የነበረች ቢሆንም፤ ትምህርት ላይ በሰጡት ትኩረት ድህነት ዛሬ ታሪክ ሆኗል፡፡
መንግስት ለትምህርት እየበጀተ ያለው ገንዘብም በጥቂት ጊዜ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት በእጅጉ የሚያሳድገው ነው፤የሚሉት ደግሞ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት አቶ ሲራጅ ናቸው፡፡
አሁን ያለውን ምጣኔ ሃብት የመሰረተ ልማትን ከማሳደግ የላቀ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡ በአገሪቱ በብዛት የተማረ ሰው ሲኖር በርካታ መንገዶች ይገነባሉ፡፡ መንገዶች በተገነቡ ቁጥር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚገናኙበት ሲሆን፤ በዚያው ልክ ከፍተኛ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት ነው፡፡ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ይኖራል፡፡ ፋይዳውም በአጭር ጊዜ ብቻ ተመንዝሮ የሚያልቅ ሳይሆን፤ በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ትኩረት ሲያደርጉ ሌሎች የልማትና የዕድገት ሥራዎችንም በሰፊው ይዞ ይመጣል፡፡ በርካታ የጤና ባለሙያዎች ያፈራች አገር በቀጣይ በዘርፉ የሚጋጥማትን ችግር በቀላሉ ለመመከት ያግዛታል፡፡ በመስኩም ኢንቨስትመንቱን የሚያስፋፋ ማህበረሰብም እንዲፈጠር መልካም አጋጣሚዎችን እንዲኖሩ ያደርጋል በማለት ሰፊ ማብራሪያ ይሰጣሉ አቶ ሲራጅ፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ አሰፋሽ ተካልኝ፤ የአንድ አገር ዕድገት የሚለካው በሰው ልማት ነው፡፡ ምጣኔ ሃብቱን የሚሸከም ትውልድ መፍጠር ማለት ደግሞ ድህነትን ለማጥፋትና ተወዳዳሪ አገር ለመሆን እጅግ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት 26 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው፡፡ ይህ በርካታ የአፍሪካ አገራት ካላቸው ህዝብ በእጅጉ የሚበልጥ ነው ይላሉ፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ ትምህርት በገበያ ላይ ተሸጦ የሚሰላ ትርፍ ያለው ሳይሆን፤ ትውልድ ላይ የሚገነባና ትርፉ ሁሌም የማይከስም እንደሆነም ያብራራሉ፡፡ ምጣኔ ሃብቱ የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ማቅረብ የትምህርት ዘርፍ ትልቁ ሥራው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚያከናውኑ ዜጎች ማፍራት ተችሏል፡፡ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የአገሪቱን ዘላቂ ዕድገት ለማስቀጠል የታለመ ነው፡፡ ይህም አገሪቱን በእጅጉ የሚለውጣት ይሆናል፡፡ በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት አኳያ እንድትሰለፍ የሚኖረው አስተዋፅኦ ትልቅ ነው፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም ተከስተ በበኩላቸው፤ የ2011 በጀት አመዳደብ ለዘላቂ ልማት፣ በምጣኔ ሃብት ትራንስፎርሜሽንና በድህንነት ተኮር ክፍለ ኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት ላይ ያመዘነ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ከዚህም በላይ የብሄራዊ ክልላዊ መንግስታት ለሚያካሂዷቸው አጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚያስፈልገውን የወጪ ፍላጎት ለመሸፈን እንዲያስችላቸውም ለዘርፉ ከፍተኛ የበጀት መመደቡን ይጠቁማሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚመያለክቱት፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለድህነት ተኮር ልማቶች ከፍተኛ በጀት ሲመደብ ቆይቷል፡፡ በ2011 ከተያዘው 346 ቢሊዮን ብር ውስጥ 66 ከመቶ ለዘርፉ የሚውል ነው፡፡ በ2010 በጀት ከተመደበው 320 ቢሊዮን ብር ውስጥም ከፍተኛ ድርሻ ያለው ትምህርትን ጨምሮ ድህነት ተኮር ጉዳዮችን ያማከለ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት ለዘርፉ እየተመደበ ያለው ገንዘብ ቀጣይነት ያለውና በጠንካራ መሰረት ላይ የተመሰረተ ምጣኔ ሃብት ለመመስረት ጥልቅ መሰረት የሚጥል ነው፡፡ ይህም አገሪቱ በስልጣኔ ማማ ላይ እንድትቀመጥ ያስችላታል፡፡ ኢትዮጵያም በሁሉም መስክ ተወዳዳሪ፣ አምራችና ጤናማ ዜጋ እንዲኖራት ከተፈለገም ከድህነት ለመላቀቅ በሚያስችሉ ዘርፎች በተለይም በሰው ሀብት ማልማት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት መመደብዋ የሚፈለገውን ዕድገት ያስገኝላታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በተሻለ የዕድገት መንገድ ላይ በመሆኗ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምስክርነት እያገኘች ነው፡፡ አገሪቱን የሚረከበው ዜጋ የተማረ ሲሆንም በመሰረታዊነት አገሪቱን የሚለውጥ አካሄድና ትክክለኛ መሰረት ለመጣል የሚያስችለውን አቅም ያገኛል፡፡ይህ ሂደት በትምህርት የተገራ አዕምሮና በአመክንዮ የሚያምን ትውልድ ለመፍጠርም ዋነኛ መንገድ ይሆናል፡፡ 

ዜና ትንታኔ
ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።