Items filtered by date: Saturday, 07 July 2018

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አሰራርና ስነ ምግባር ለመወሰን ተሻሽሎ በወጣው በደንብ ቁጥር 58/2002 ዓ.ም ዓንቀፅ 26 ንኡስ ዓንቐፅ 1 መሰረት የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የበላይነት ለማክበር በት/ብ/ክ/መ ምክር ቤት የተላለፈ ውሳኔ (Resolution) ቁጥር 02/2010

የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን ባካሄደው መራራ ትግልና በከፈለው አኩሪ መስዋእት አምባገነኑን የደርግ ወታደራዊ ስርአት ከገረሰሰ በኋላ ቀጣይ አስተማማኝ ሰላምና ዋስትናው ያለው ዴሞክራሲ ለማስፈን፣ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለማረጋጋጥ፣ በእኩልነትና በዴሞክራሲያዊ ሕብረ-ብሄራዊ አንድነት ላይ የተመሰረት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገነባት በነበረውና ባለው ራዕይ ሕገ መንግስትና ሕገ መንግስታዊ ስርዓት እውን ለማድረግ የማይተካ አስተዋፅኦ ያበረከተና በማበርከት ላይ ያለ መሆኑን፤

የትግራይ ህዝብ በመሪ ድርጅቱ ህወሓት/ኢህወዴግ አመራርነት ባለፉት 27 የትግልና የድል አመታት ከሁሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን በካሄደው የሰላም፣ ዴሞክራሲና የልማት ትግል አማካይነት በጣም ሚያጓጓና አለም የመሰከረለትን ሁለንተናዊ ድሎችን በማመዝገብ ሀገራችን አንዥብቦባት ከነበረ የኋልዮሽ ጉዞና የመበታታን አደጋ በመታደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ህዝብ በመሆኑ፤

ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ጀምሮ በፌዴራልና በክልሎች በተለይም በመንግስት መዋቅር ስር እና መንግስትን በሚመሩ ድርጅቶች በተፈጠረው የውስጥ ችግር ምክንያ የተጀመሩ ዘርፈብዙ ስኬቶችና ድሎች እየተደናቀፉ በዋናነት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ እየወደቀ በመምጣቱ ኢህወዴግ እንደ ግንባርና የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ባደረጉት ጥልቅ ግምገማ ግልፅ የመፍትሄ አቕጣጫዎችን በማስቀመጥ ወደ እንቅስቃሴ የተገባ በመሆኑ፣

ኢህአዴግ እንደ ግንባር ሆነ እህት ድርጅቶች ከግምግማ ጎን ለጎን የተለዩ ችግሮች ከስር መሰረታቸው መንግለው ለመጣል ወደ ተጨበጭ እነቅስቃሴ በገቡበት ጊዜ ህገ መንግስታችንና ህገ መንግስታዊ ስርአታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ በአተሳሰብና በተግባር የሚገለጡ ችግሮ እየታዩ እና ከጊዜ ወደ ጊዜም እየተባባሱ መምጣታቸውን፤ 
ህገ መንግስታችንና ህገ መንግስታዊ ስርአታችን ላይ እየተፈፀሙ ካሉት ጥሰቶች ጥቂት ኣብነቶችን ለመግለፅ ያህል፡-
ሀ) የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እና ሃይማኖት እኩልነትና ወንድማማችነትን የሚወክል እና በህገ መንግስቱ እውቅና የተሰጠው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሰንደቅ ዓላማ በአደባባይ ጭምር ያህጋዊ ባልሆነ አኳኋን ሰንደቅ አላማዎች እየተውለበለቡ፣ ሰነደቅ ዓላማችንን እየተቀደደ፣ እየተጠረገ፣ እየተራከሰና እተየቃጠለ ማየት የእለት ተዕለት ተግባር እየሆነ መምጣቱ፤

ለ) የዜጎዎች ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ የመኖር፣ የመስራት እና ሃብት የማፍራት፣ ህገ መንግስታዊ መብታቸውንነና ነፀነታቸውን በአብዛኛው የአገራችን አከባቢዎች እየተጣሰ ብሔር ተኮር ጥቃት እየተፈፀመባቸውና እየተፈናቀሉ ማየት የእለተ ተዕለት ተግባር እየሆነ መምጣቱ፤

ሐ) ህገ መንግስታዊ ፌደራላዊ ስርቱን በሚቃረን አኳኋን የማንነት እና የአስተዳዳር ወሰን ጥያቄዎችን ምክንያት በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የሰው ህይወት ማጥፋት፣ አካል ማጉደልና ንብረትን ማውደም የዜጎች ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት አደጋ ላይ እየጣለው መሆኑን፤

መ) ይህ ሃገራዊ ችግር እንዳለ ሆኖ የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰላም፣ ዴሞከራስና ልማት የከፈለው ከባድ የህይወት መስዋእትነት በማይመጥን መልኩ ክብሩን መሰረት ያደረገ ጥቃቶች እየደረሱበት መሆኑ፣ መሬት የማስፋፋት ህልም መነሻ ያደረጉ እና በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠሩ ጠብ አጫሪ የሆኑ ሰልፎችና መፈክሮችና እየተካሄድ መጥተዋል፣ አሁንም እየተካሄዱ ነው፣

ሰ) በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ላይ ህዝብን ያላሳተፈ እና ዘላቂ ሰላም በማያረጋግጥ አኳኋን የአልጀርስ ስምምነት ግልፅነት በሌለው መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ህዝብ በራሱ ተሳትፎ የመወሰን ህገ መንግስታዊ መብቱን የሚጥስ ተግባር በመሆኑ፤

በኢፌዴደሪ ሕገ መንግስት ዓንቀፅ 50 ንኡስ ዓንቀፅ 3 መሰረት እንዲሁም የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ህገ መንግስት ዓንቀፅ 8 ንኡስ ዓንቀፅ 2 ምክር ቤት የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለትግራይ ህዝብ በመወከል የክልሉ ከፍተኛ የስልጣን አካል በመሆን እንደ የመንግስት አካል እና በኢፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት ዓንቀፅ 9 ንኡስ አንቀፅ 1፣ ዓንቀፅ 13 ንኡስ ዓንቀፅ 1፣ ዓንቀፅ 52 ንኡስ ዓንቀፅ 2/ሀ በድንጋጌዎች መሰረት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ህገ መንግስት የመጠበቅ፣ የማክበርን የማስከበርን ህገ መንስታዊ ግዴታ/ኃላፊነት ስላለው፤

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት በ5ኛ የስራ ዘመን 12ኛው መደበኛ ጉባኤው ውይይት ተደርጎባቸው እንዲወሰኑ 11 አጀንዳዎች ለማስፀደቅ በክብርት አፈ ጉባኤ ከቀረቡ ብኋላ በምክር ቤት አባላት የሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎችንና የህገ መንግስቱ የበላይነት የሚመለከት ተጨማሪ አጀንዳ በምክር ቤቱ ኣባላት በሞሽን ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት 12ኛ አጀንዳ ሆኖ እንዲያዝ በሙሉ ድምፅ ስለተደገፈ፤

በደንብ ቁጥር 58/2002 ዓ.ም መሰረት የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አሰራርና ስነ ምግባር ለመወሰን ተሻሽሎ በወጣ ደንብ ዓንቀፅ 26 ንኡስ ዓንቀፅ 1 መሰረት የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት የአገራች ወቅታዊ ሁኔታዎችን በሚገባ ከተወያየ በኋላ ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱትና ሌሎችን የህገ መንግስት ጥሰቶችን በጊዜው እንዲታሙ ካለው ፅኑ እምነት፣ ፍላጎት ከህገ መንግስታዊ ግዴታው በመነሳት የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት የበላይነትን ለማክበርና ለማስከበር የሚከተለው ውሳኔ (Resolution) አስተላልፏል፤

1.ሁለንተናዊ የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ፣ ሃገራችን ላለፉት 27 አመታት በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማት ግንባታ፣ በዘላቂ ሰላምና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጉዞ ላይ ያስመዘገበቻቸው አንፀባራቂ ድሎች የሚቀለብሱና የሚያፈርስ ሁኔታዎች መፈጠራቸው፣ በአጠቃላይ ሃገራችን በጣም በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች እና ከዚህ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚሆኑ አካላት የሃገርና የህዝብ ጠላቶች ብቻ መሆናቸው ተገንዝበን መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነታችንን አጠናኽረን ሃገራችንን ከውድቀትና ከመበታታን አደጋ ለመታደግ መረባረብ እንዳላብን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል፤

2.ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ህገ መንግስት የመጠበቅ፣ የማክበርና የማስከበር ሕገ መንግስታዊ ግዴታና ኃላፊነት አለዉ፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ህገ መንግስቱ የሚሻሻልበት ግልፅ የሆነ ሕገ መንግስታዊ አሰራር ባለበት ሀገር ውስጥ ከስርዓት ውጭ ሲኬድና ከላይ የተገለፁትንና ሌሎች የህገ መንግስት ጥሰቶት ሲፈፀሙ ዝም ብሎ ማየት ሃገር ወደ ከፋ ቀውስ ሊያስገባት የሚችል በመሆኑ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህጋዊ በሆነ መንገድ ጥፋቶችን በትረት በመኮነን ህገ መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

3.ሁሉም የዲሞክራሲ ተቋማት በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ የአገራችን ሚድያዎች ህግና ህገ መንግስታዊ ስርአቱንና የሕግ የበላይነትን ለማክባርና ለማስረከብ ያላቸው ኋላፊነትና ግዴታ በአግባቡ በመረዳት ኃላፊነታቸው እዲዋጡ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

4.የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከፌደራል መንግስትና ከክልል መንግስታት ጋር በመተባባር ቀደም ብሎ የጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት ይበልጥ አጠናክሮ በመቀጠል የህገ መንግስቱ የበላይነትና ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ኃላፊነቱ እንዲዋጣና ከተለያዩ የሃገራችን አከባቢዎች ተፈናቅለው የመጡ ወገኖችን ለማቋቋም በትጋት መስራት እንደዳለበት ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

5.የትግራይ ህዝብ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ በመሆን ባደረገው ትግልና በከፈለው መራራ መስዋእትነት እስካሁን ያረጋገጣቸው አንፀባራቂ ድሎችን ጠብቆ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለመላ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለው ትልቅ ክብርና ፍቅር አጠናክሮ በማስቀጠል የሚያጋጥሙት ማናቸውም እንቅፋቶችም በትእግስት እንዲፈታ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

6.የፌዴራል መንግስትና ሁሉም ክልሎች ግልፅ የሆነ ህገ መንግስታዊ ጥሰት በሚፈፅሙ ገለ ሰቦችንና አካላትን ወደ ሕግ በማቅረብ ሕገ መንግስታዊ ኃላፍነታቸውን እንዲወጡ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

7.በመጨረሻ አሁን እያጋጠሙን ያሉ ችግሮች ብፍጥነት በመፍታት በድህነትና ኋቀርነት ላይ የጀመርነው ትግል በማጠናከል አስተማማኝ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲና ዘላቂ ልማትን በማረጋጋጥ በህዝቦች ፍላጎት፣ እኩልነትና በመቻቻል ላይ የተመሰረተች ሃገር የመገንባት ራዕያችን ለማሳካት ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ እንዲረባረቡ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት
ሰኔ 29 ቀን 2010.ም
መቐለ

Published in የሀገር ውስጥ

የ1982 የዓለም ዋንጫ ለኤሽያዊቷ አገር ኩዌት የእግር ኳሷ ወርቃማ ዘመን ሆኖ ይታወሳል። የዓለም ዋንጫ በመጣ ቁጥር ግን ይህ የኩዌት ወርቃማ የእግር ኳስ ዘመን ሲታወስ አይታይም። እግር ኳስ በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች እየረቀቀ ሲመጣ፤ ኢንተርኔት ዓለምን ሲያቀራርብና ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭቶች እንደ ልብ እየሆኑ ሲመጡ እኤአ ከ1990ዎቹ ጀምሮ በዓለም ዋንጫ የታዩ ወርቃማ ብሔራዊ ቡድኖች፤ በርካታ ከዋክብቶችና አይረሴ አጋጣሚዎች አሁንም ድረስ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ ይታወሳሉ። ያም ሆኖ ከ1978 የዓለም ዋንጫ አስቀድሞ ከጣሊያንና አርጀንቲና ውጪ ያሉ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ ፓውሎ ሮሲና ማሪዮ ኮምፐስን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ትልቅ እውቅና ነበራቸው። ከዚህ የዓለም ዋንጫ በኋላም መረጃዎች እንደ ልብ በሌሉበት ዘመን የዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ለመጀመሪያ ጊዜ ለአርጀንቲና ተሰልፎ ቤልጂየምን እስከ ገጠመበት ጨዋታ በበርካታ የዓለማችን እግር ኳስ አፍቃሪዎች በቴሌቪዥን መስኮት የመመልከት እድላቸው ጠባብ ቢሆንም ስምና ዝናው ይታወቅ ነበር።

የዓለም ዋንጫ አይረሴዎቹ ኮከቦች ሚካዔል ላውድሩፕ፤ ህሪስቶ ስቶቺኮቭ፤ ጂዮርጅ ሃጂና ሌሎችም የጀገኑበት ዘመን ሩቅ ቢሆንም የዓለም ዋንጫ በመጣ ቁጥር ሳይታወሱ የማይታለፉበት ታሪክ አኑረዋል። በተመሳሳይ በብሔራዊ ቡድን ደረጃም የ1966 የሰሜን ኮሪያ፤ በ1982 የአልጄሪያና በ1990 የካሜሩን ብሔራዊ ቡድኖች የሚዘነጉ አይደሉም። የኩዌት የ1982 ብሔራዊ ቡድንም ከነዚህ ብሔራዊ ቡድኖች እኩል የሚታወስ ነው።
የ1982 የስፔን የዓለም ዋንጫ የኤሽያን እግር ኳስ አንገት ቀና ያደረገ ድንቅ የብሔራዊ ቡድን ስብስብ ከኤሽያ አልፎ በመካከለኛው ምስራቅና የገልፍ አገራት እግር ኳስ ላይ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሮ ነበር። ይህ ከ1970 መጀመሪያ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ ትልቅ የእግር ኳስ አብዮት የፈጠረ የኩዌት ወርቃማ የእግር ኳስ ትውልድ ኤሽያ እስካሁንም መልሳ ያላየችው ስብስብ ይዞ ነበር።
ከ1976 እስከ 1978 በታሪካዊው ብራዚላዊ ማሪዮ ዛጋሎ እንዲሁም ከ1978 እስከ 1982 በሌላኛው ብራዚላዊ ካርሎስ አልቤርቶ ፔሬራ እየሰለጠነ ዓለምን ጉድ ያሰኘ የብሔራዊ ቡድን ስብስብ በድንቅ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች የተሞላም ነበር። ከግብ ጠባቂው አህመድ ታራቡልሲ አንስቶ እስከ አብዱላዚዝ አል አንባሪ፤ አህመድ አቡ ሐማድና ግብ አፈንፋኙ ጃሴም ያቆብ እንዲሁም አምበሉ ሳድ አል ሆቲና ፋሳል አል ዳክሂል ድረስ በከዋክብት የተሞላው የኩዌት ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ከእግር ኳስ በላይም ትልቅ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጽዕኖዎች ነበሩት። ይህ ስብስብ በዓለም እግር ኳስ ላይም በትልቅ ደረጃ ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ የመጀመሪያው የገልፍ አገራት ብሔራዊ ቡድን ሆኖ ይታወሳል።
የኩዌት ወርቃማ የእግር ኳስ ትውልድ በአንድ ጊዜ ተፈጥሮ በዓለም እግር ኳስ ላይ ድንገት ተፅዕኖ የፈጠረ ሳይሆን በሂደት እየተገነባ የመጣ ነው። ለዚህም በኤሽያና በገልፍ አገራት የእግር ኳስ ቻምፒዮና ሃያል የሆኑትን እንደ ኢራን አይነት አስደናቂ የቡድን ስብስብ ያላቸውን አገራት በሂደት አሸንፎ ዋንጫ በማንሳት ነው። ከዚህ በዘለለም ለ1980 የሞስኮ ኦሊምፒክ አልፎ እስከ ሩብ ፍፃሜ ድረስ በመጓዝ በርካቶችን አሳምኖ ነው ወደ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጣው።
በኤስያ አገራት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ኩዌት ኒውዘላንድ፤ ቻይናና ሳውዲ አረቢያ ከሚገኙበት ምድብ በፔሬራ አሰልጣኝነት እየተመራች በቀላሉ ወደ 1982 የዓለም ዋንጫ ማምራት ችላለች። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ግን ኩዌት በዓለም ዋንጫው ጠንካራ በሚባል ምድብ ውስጥ ተደለደለች። ይሁን እንጂ በቡድኑ ውስጥ የነበረው ጠንካራ ስነ ልቦና ጠንካራውን ምድብ አልፈው ወደ ጥሎ ማለፍ እንደሚገቡ ትልቅ ተስፋ የሰጠ ነበር።
«ግመሎቹ» በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው የኩዌት ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያቸው በሆነው የዓለም ዋንጫ በምድብ ድልድሉ ከሦስቱ አውሮፓውያን አገራት ቺኮስላቫኪያ፤ ፈረንሳይና እንግሊዝ ጋር ነበር የተደለደሉት። ይህ ምድብ ከቺኮስላቫኪያ በስተቀር ፈረንሳይና እንግሊዝ ያላቸው ትልቅ ስም ለግመሎቹ ስጋት ቢሆንም የፔሬራ ልጆች ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ትልቅ ተስፋን ሰንቀው ነበር። በተለይም በመጀመሪያው የቺኮስላቫኪያ ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ግምት የተሰጣቸው ቢሆንም ጨዋታው አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁ ያልተጠበቀ ነበር። ይሁን እንጂ ጠንካራዋ ፈረንሳይ በእንግሊዝ ሦስት ለአንድ መሸነፏን ተከትሎ ግመሎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋቸው እንደገና ነብስ ዘራበት።
ያም ሆኖ በሁለተኛው የምድብ ጨዋታ ሚሼል ፕላቲኒ፤ አሊያን ጊረስና ጄን ቲጋና ለፈረንሳይ ግቦችን አስቆጥረው ፈረንሳይ በቀላሉ መምራት ቢችሉም ግመሎቹ ወደ ጨዋታው ተመልሰው ወይ ለማሸነፍ ወይንም የአቻ ውጤት ይዘው ለመውጣት ተስፋ አልቆረጡም። በዚህም ፈረንሳይን ተጭነው በመጫወት በአብዱላህ አል ቦኑሺ የግንባር ኳስ ሦስት ለአንድ መሆን ቻሉ። ይህም ተነሳሽነታቸውን ጨምሮ ሌላ ግብ ለማስቆጠር ጥረት በሚያደርጉበት ሰዓት አንድ ተስፋ አስቆራጭ ክስተት ተፈጠረ። ይህም አለን ጊረስ ከጨዋታ ውጪ የሆነ ግብ ኩዌት ላይ አስቆጥሮ ዳኛው ይሽሩታል ተብሎ ሲጠበቅ ማፅደቃቸው ነበር።
ይህች ቅፅበት ግመሎቹን ተስፋ ከማስቆረጡም በላይ በወቅቱም የኩዌት ተጫዋቾች ውሳኔውን በመቃወም ጨዋታውን ሳይጨርሱ ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል። በወቅቱ የኩዌቱ ኤሚር ወንድምና የአገሪቱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የነበሩት ሼክ ፋሃድ አል አህመድ አል ጃበር አል ሳባህ ከክብር ወንበራቸው ተነስተው ወደ ሜዳ በመግባት በዳኛው ውሳኔ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ከተጫዋቾቹ ጋር የገለፁበት አጋጣሚ አይረሳም። በዚህም ዳኛው አሁንም ድረስ የዓለም ዋንጫ አስገራሚ ክስተት ተብሎ እንዲታወስ ያደረገውን አጋጣሚ ያፀደቁትን ግብ በመሻር ጨዋታው እንደገና እንዲጀመር ማድረጋቸው ነበር።
ያም ሆኖ ግን ግመሎቹ ወደ ጨዋታው ቢመለሱም ወደ ቀድሞው ተነሳሽነታቸው ሳይመለሱ ቀርተው ፈረንሳይ በመጨረሻ ሰዓት ሌላ ግብ አስቆጥራ አራት ለአንድ ማሸነፍ ቻለች። ከዚህም ቅፅበት በኋላ የኩዌት እግር ኳስ የተሰበረ ቅስም አሁንም ድረስ ሳይጠገን ደብዛው ሊጠፋ ችሏል።
የ1982 የስፔን የዓለም ዋንጫ ለኩዌት እግር ኳስ ወርቃማ ዘመን እንደመሆኑ መጠን ደብዛው የጠፋበት አጋጣሚም ሆኖ ይታወሳል። አብዛኞቹ የኩዌት ተጫዋቾች እድሜያቸው የገፋ እንደመሆኑ ከዚያ የዓለም ዋንጫ በኋላ ሌላ ተዓምር ሳያሳዩ ጫማቸውን ለመስቀል ተገደዋል። በእርግጥ የተወሰኑ ተጫዋቾች ከዚያም ወዲያ የተወሰኑ ዓመታትን ተጫውተዋል። እነዚህ ተጫዋቾች ከዓለም ዋንጫው በኋላ በገልፍ አገራት ቻምፒዮና እኤአ 1986ና 1990 ላይ ዋንጫ ማንሳት ቢችሉም ኩዌት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያን ለማለፍ የተቃረበችበት ወቅት እንኳን አልተከሰተም። ከዚህም በኋላ እኤአ በ1990 ኩዌት በኢራቅ የተወረረችበትና ቀጥሎም የገልፍ አገራት ጦርነት የተከሰተበት አጋጣሚ የአገሪቱን እግር ኳስ ከተነቃቃበት ወደ ገደል ገፍትሮታል። በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ብሔራዊ ቡድኑ በተደጋጋሚ በፊፋ እገዳ እየተጣለበትም ከድጡ ወደ ማጡ ሲገባ ታይቷል። የኩዌት እግር ኳስ አፍቃሪዎችም የወርቃማ ትውልዳቸው ከዋክብቶችን አል ዳክሂል፤ ያቆብ እንዲሁም አል አንባሪን በማስታወስ የዓለም ዋንጫ በመጣ ቁጥር ይደሰታሉ።

 

 አጣብቂኝ የበዛበት የፕሪሚየር ሊጉ መቋጫ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፍፁም በተጠጋጋ የነጥብ ልዩነት ወደ ዋንጫ የሚደረገው ጉዞ አሁንም አጓጊነቱ ቀጥሏል። ሃያ አንደኛው የዓለም ዋንጫና በአገራችን ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ የብዙዎች ቀልብ ማረፊያ ሆነ እንጂ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደ ዘንድሮው ዓመት ልብ አንጠልጣይ ሆኖ አያውቅም። ያም ሆኖ ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንት መርሃግብር ጨዋታዎች ብቻ የሚቀሩት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሳምንት ሳምንት የሚያስተናግዳቸው ክስተቶች፤ ለዋንጫ የሚደረገው ፉክክርና ላለመውረድ የሚደረገው ትንቅንቅ ለአፍታም ቢሆን ዞር ብለን እንድንመለከተው ያስገድዳል። በተለይም የሃያ ስምንተኛ ሳምንት ሰባት ጨዋታዎች ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ከተካሄዱ ወዲህ የተፈጠሩ የነጥብ ልዩነቶች ፉክክሩን ካለፉት ሳምንታት በላቀ አጓጊ ከማድረጋቸው ባሻገር ቀጣዮቹን መርሃግብሮች የበለጠ ተጠባቂ ማድረግ ችለዋል።
በቻምፒዮንነት ጉዞው አንገት ለአንገት ተናንቀው ያለፉትን በርካታ ሳምንታት ያሳለፉት ጅማ አባ ጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሃያ ስምንተኛው መርሃግብራቸው ተጋጣሚዎቻቸውን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፈው የደረጃ ሰንጠረዡን ቦታ ቢቀያየሩም አሁንም ዋንጫውን ማን እንደሚጨብት እርግጠኛ መሆን አያስችልም። ባሳለፍነው ሳምንት አርባ ስምንት ነጥቦችን ይዞ በአንድ የግብ ክፍያ ተከታዩን በልጦ ቀዳሚውን ደረጃ ይዞ ደደቢትን የገጠመው ጅማ አባ ጅፋር ሦስት ለዜሮ በሆነ ውጤት አሸንፎ የዋንጫ ጉዞውን ቢያጠናክርም ይህ ድሉ ዋንጫውን ለመሳም ወይንም ደረጃውን አስጠብቆ ለመጓዝ በቂ አልነበረም። በተመሳሳይ ነጥብ በአንድ ግብ ክፍያ ተበልጦ በቅርብ ርቀት ሲከተለው የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን አራት ለዜሮ በማሸነፍ በእኩል ሃምሳ አንድ ነጥብና አስራ ዘጠኝ ግብ መሪነቱን ሊረከብ ችሏል።
ሁለቱ ክለቦች በነጥብም በግብ ክፍያም እኩል መሆናቸውን ተከትሎ መሪውን ለመለየት ሌላ አማራጭ ማየት አስፈልጓል። ለዚህም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ አንቀፅ 2 ምዕራፍ 5 ተራ ቁጥር 6 መሰረት ክለቦች በነጥብም በግብ ክፍያም እኩል ከሆኑ የተሻለ ግብ ያስቆጠረው ቀዳሚ እንደሚሆን ይደነግጋል። በዛም መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰላሳ ስምንት ግቦችን ተጋጣሚዎቹ ላይ ሲያስቆጥር ጅማ አባ ጅፋር ሰላሳ አራት በማስቆጠሩ ፈረሰኞቹ የሊጉ መሪ መሆን ችለዋል። በተመሳሳይ ነጥብ እና ጎል ላይ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል።
በሃያ ዘጠነኛው ሳምንት ዛሬ በሚካሄዱ ጨዋታዎች የሁለቱ ክለቦች ትንቅንቅ ይለይለታል ወይንስ እስከ መጨረሻው ሰላሳኛ ሳምንት መርሃግብር ድረስ ይዘልቃል የሚለው ይታይበታል። ጅማ አባ ጅፋር ወደ ቦዲቲ አቅንቶ ላለመውረድ ትግል ላይ የሚገኘውን ወላይታ ድቻን ይገጥማል። ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ክለቦች እጅግ ወሳኝ መሆኑን ተከትሎ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሁለተኛውን ወራጅ ክለብ ልናይበት እንችላለን። ወላይታ ድቻ አሁንም ቁልቁል መውረዱን ቀጥሎበት በአስገራሚ ሁኔታ ከአምናው በባሰ መልኩ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል::
ወላይታ ድቻ ከሊጉ ላለመውረድ የዛሬውን ጨምሮ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ እና የሌሎችን ነጥብ መጣል የሚጠብቅ ይሆናል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለቻምፒዮንነት እየሮጠ የሚገኘውን ጅማ አባ ጅፋርን መግጠሙ ወልዲያ ከተማን ተከትሎ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛው ወራጅ ክለብ እንዳይሆን ያሰጋል። ይሁን እንጂ ወላይታ ድቻ በሜዳው ያለመሸነፍ ልምዱና ደጋፊዎቹን ተጠቅሞ ከመውረድ አደጋ ለመትረፍ ለቻምፒዮንነት ለሚሮጠው ጅማ አባ ጅፋር በሩን በቀላሉ ይከፍታል ተብሎ አይጠበቅም።
በተመሳሳይ ወደ አዳማ የሚያቀናው ሌላኛው የቻምፒዮንነት ሰፊ እድል ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃራዊነት ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል። እስከ ቅርብ ሳምንታት ድረስ የቻምፒዮንነት እድል የነበረውንና በአርባ ሦስት ነጥብ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን አዳማ ከተማን የሚገጥመው ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብና የነጥብ ልዩነቱን አስጠብቆ ቻምፒዮን ለመሆን የሚያደርገው ጥረት ተጠባቂ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን ከባድ ፈተና ቢቀረውም እንዳለፉት አራት ዓመታትም ቻምፒዮን የመሆን ጠንካራ ስነ ልቦናና ልምዱን ተጠቅሞ ቻምፒዮን እንደሚሆን በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች እምነታቸውን ሲገልፁ ይሰማሉ።
የሃያ ስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባለፈው ሰኞ ሲቀጥሉ ለዋንጫ ተፎካካሪነት ሰፊ እድል የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ውጤት ይጠበቅ ነበረ። ጥሩ ኳስ ለመጫወት አይደለም ለማየት በሚቀፍ መልኩ በዝናብ ምክንያት በጨቀየው የአዲስ አበባ ስታድየም ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና ከጨዋታው የሚፈልገውን ነጥብ ይዞ መውጣት ሳይችል ቀርቷል። በዚህም ከመሪዎቹ በአራት ነጥብ ዝቅ ብሎ በአርባ ሰባት ነጥብ ሦስተኛ ላይ ሊቀመጥ ችሏል። የመውረድ ስጋት ውስጥ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ነጥቡን ወደ ሰላሳ አንድ ከፍ በማድረግ ለጊዜውም ቢሆን ከወራጅ ቀጣናው ርቆ አስራ ሦስተኛ ላይ ሊቀመጥ ችሏል። ኢትዮጵያ ቡና በሰኞው እለት ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ባይችልም የቅዱስ ጊዮርጊስና ጅማ አባ ጅፋር ውጤት ላይ ተሞርኩዞ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች በማሸነፍ ቻምፒዮን የመሆን ጠባብ እድል አለው።
የፕሪምየር ሊጉ ሃያ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከትናንት በስቲያ በተከናወኑ ሁለት መርሃግብሮች ተጀምሯል። ደደቢት መውረዱን ካረጋገጠው ወልዲያ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ ሲዳማ ቡና መከላከያን በማሸነፍ ከመውረድ ስጋት ነፃ መውጣቱን ማረጋገጥ ችሏል። የአዲስ አበባ ስታዲየም ከሰሞኑ እየጣለ ባለው ዝናብ ሜዳው ለማጫወት ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት ወደ ሰበታ የተቀየረው የደደቢት እና የወልዲያ ጨዋታ ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል።
ጨዋታው በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይደረጋል ተብሎ ቢታሰብም ፌዴሬሽኑ ግን ዛሬ ማለዳ ለክለቦች 04:00 ላይ እንደሚደረግ ባሳወቀው መሠረት ተከናውኖ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ወልዲያ ከ8 ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሳይሸነፍ ሲወጣ ደደቢት ሙሉ ለሙሉ ከመውረድ ስጋት ነፃ መሆን ችሏል።
ይርጋለም ላይ በ9:00 ሲዳማ ቡናን ከመከላከያ ያገናኘው ጨዋታ በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህም ጨዋታው ለሲዳማ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ድል ሆኖ ክለቡ ለከርሞው በሊጉ መቆየቱን ያረጋገጠበትም ሆኗል። የሃያ ዘጠነኛ ሳምንት መርሃግብር ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ በሰላሳ ስምንት ነጥብ ስምንተኛ ላይ የሚገኘው ፋሲል ከተማ ለዋንጫ ተስፋ ያለውን ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳው ያስተናግዳል። በአርባ ስድስት ነጥብ አራተኛ ላይ የሚገኘው መቀሌ ከተማ በሰላሳ ሁለት ነጥብ አስራ ሁለተኛ ላይ የሚገኘውን ኤሌክትሪክን በሜዳው ይገጥማል። አስርና አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት እንዲሁም ብዙ የመውረድ ስጋት የሌለባቸው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ሐዋሳ ከተማም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሃያ ዘጠኝ ነጥብ ወልዲያን ተከትሎ ለመውረድ ጫፍ የደረሰው አርባ ምንጭ ከተማ አሁንም ሌላ አደጋ ተጋርጦበታል። ዛሬ በሰላሳ አንድ ነጥቦች ላለመውረድ እየታገለ ከሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ጋር ከሜዳው ውጪ ይፋለማል። ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ክለቦች እጅግ ወሳኝ እንደመሆኑ ሙሉ ነጥብ ያገኘ በቀጣይ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ የሚቆይበትን ትኬት ይቆርጣል። ተሸናፊውም የሌሎችን ክለቦች ውጤትና የቀሪውን አንድ ጨዋታ ድል ጠብቆ እጣ ፋንታውን ይወስናል።

ቦጋለ አበበ

 

 

Published in ስፖርት
Saturday, 07 July 2018 19:28

ዶክተሩ ምን ይስራ!

እለቱ እሁድ ነው ያለሁት ደግሞ መሀል ከተማ ፒያሳ። አደባባዩ ፊት ለፊት ነጫጭ ድንኳኖች ተተክለዋል። ባዛር ተዘጋጅቶ ነው ይቺ ነገር አራት ኪሎና መገናኛም በየሦስት ወሩ የተለመደች ናት። እስቲ ዓይኔን ላድክም ብዬ ወደነሱ አመራሁ ጠጁ፣ ምግቡ ገና ከመግቢያው ላይ እውድ እያደረገ ይቀበላል ከዚህ ውጪ በገበያው ያለው አብዛኛው ምርት ግን የቆዳ ነው። ጫማ፣ ቀበቶ፣ ቦርሳ... ። ይሄ አይደንቅም ምክንያቱም በአፍሪካ በቀንድ ከብቶች ቁጥር ብዛት ቀዳሚ ስለሆንን። ወደ ውስጥ ዘለቅ ስል ከሙዚቃው ጋር ተደርቦ የሚረብሽ ድምፅ ደረሰኝ ማስታወቂያ መሆኑ ነው። «የራስ ድርቀትና የጸጉር መሳሳት ይከላከላል፤ የጸጉርን ቀለም ጠብቆ የማቆየት ኃይል አለው። ሽበት ያጠፋል፤ ጸጉር እንዳይነቃቀል፣ እንዳይሰባበር ያደርጋል... ።» በትንሿ ድንኳን በር ላይ የተቀመጠው የድምፅ ማጉያ ይለፈልፋል።
ጠጋ ብዬ ማየት ጀምርኩ ትንንሽ የቅባት ብልቃጦች ጠረጴዛውን ሞልተውታል። አንድ ራሰ በራ ጎልማሳ ጠጋ ብሎ እውስጥ የተቀመጠችውን ልጅ ማዋራት ጀመረ። እኔም አጠገባቸው ቆሜያለሁ። ጉዳዩ ሳይመለከተኝ አይቀርምና ጆሮ ሰጠሁ። «ይሄ ነገር እንዴት ነው?» መጀመሪያ ያቀረበው ጥያቄ ነበር። ልጅቱ አላስጨረሰችውም «ምርቱ የውጭ ነው። የወይራ ዘይት ነው። ምንም አልተቀላቀለበትም። በአውሮፓ ደረጃ የተዘጋጀ ነው። ደረጃውን የጠበቀ ነው። እንደ ሌሎቹ አይደለም፤ በቀን በቀን በደንብ እየታጠብክ ከተጠቀምከው ለውጡን በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ማየት ትችላለህ» ቀጠለች።
አፏ ሳይፎርሽ እጇም ሥራ ጀመረ አየኸው የኔን ጸጉር? መጠቀም ከጀመርኩ ሦስት ወር ሆኖኛል። በፊት እንደዚህ አያብረቀርቅም ነበር፤ እየተሰባበረም ያስቸግረኝ ነበር፤ ሳልተኮሰው እንዴት እንደሆነ ታየዋለህ? እጇ ጸጉሯን ያፍተለትል ይዟል። በቅባቱ መሆኑን ባላምንም ጸጉሯ ግን ያምራል .... እኔ ሰውየውን፤ ሰውየው እሷን ይመለከታል።
ቀጠለች ይሄኛው ይሄን ያህል ነው፣ ይሄኛው... የአምስት ዕቃዎችን ዋጋ ከአምስት ሰከንድ ባነሰ ነገረችው። አዳመጥከኩኝ። ሰውየው ምርጫ አልነበረውም እጁን ወደ ኪሱ ከቶ ድፍን መቶ ብር አወጣ መልስ ተሰጠው የቅባቷን ዕቃ እያገላበጠ እያየ ጉዞውን ቀጠለ።
እኔ በተራዬ ጥያቄ አቀረብኩ የእኔ ጥያቄ ግን እንድትንጣጣ በር አልከፈተላትም፤ ይልቁንም የሚያስከፋ ነበር ደረጃ መዳቢ ያቃችኋል?የመድኃኒት፣ የምግብና መጠጥ ቁጥጥር ባለሥልጣን ጎብኝቶታል?... የማውቃቸውን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ፈቃድ ሰጪ ጠቀስ ጠቀስ አደረኩ።
አፍጣ እያየቺኝ «ደረጃ መዳቢ ሳያውቀው የሚገባ ዕቃ እንዴት በይፋ ይሸጣል » ሌላ ጥያቄ እንዳቀርብ ዕድል አልሰጠቺኝም ከድንኳኑ ወጥታ ቆመች፤ ነገሩ ገብቶኛል ሂድልኝ ነው።
ዞር አልኩላት የጉድ ቀን አይመሽም ነጭ ዳማስ መኪና ከአቅሟ በላይ ሞንታርቦ ተሸክማ እዚያው ፒያሳ የተደረደሩት አውቶቡሶች መካከል ተሸጉጣ ትጮሀለች። «ሞሪንጋ» ለበርካታ ህመሞች ፈዋሹ መድኃኒት ለስኳር፣ ለኩላሊት፣ ውፍረት ለመቀነስ፣ ለፊት ጥራት.... የማላውቃቸውን በሽታዎች ሁሉ ይጠራል። ሥራ መፍታቴ ለምኔ እሱም ጋር ጠጋ አልኩ እንደ ሻይ ቅጠል በላስቲክና በካርቶን የታሸገውን ዱቄት ሳነሳ ሃምሳ ብር ነው አለኝ።
ግን የሚባለውን በሽታ ሁሉ ያድናል? የእኔ ጥያቄ ነበር።
«በሳይንስ የተረጋገጠ ነው። ሁሉም ሰው እየገዛው ነው ውሰድና ሞክረው። ሁለት፣ ሁለት የሻይ ማንኪያ በአንድ ብርጭቆ የፈላ ውሃ አድርገህ በቀን ሦሰት ጊዜ። የመጀመሪያ ቀን ግን ትንሽ ሊረብሽህና መፀዳጃ ቤት መመላለስ ሊያስፈልግህ ስለሚችል እቤት ስትውል ብትወሰድው ጥሩ ነው። ለሕፃናት አይሆንም በእርግዝና ወቅትም አይወሰድም» የሻጭ የህክምና መመሪያ መሆኑ ነው። ሞክረህ እየው ብሎ ምክር።
ግን ትክክለኛ ሞሪንጋ ነው? ጥያቄዬን ቀጠልኩ።
አትጠራጠር ውሰደውና ሞክረው ካርቶኑ ላይ ስልክ አለ። በማንኛውም ሰዓት ደውለህ ልታናግረን ትችላለህ።
ምንያህል ጊዜ መቆየት ይችላል ማለቴ «ኤክስፓየርድ ዴቱ»
አይ በጣም አታቆየው።
በጣም ስትል ሦስት... ቀን ሦስት ወር... ሦስት ዓመት... ።
በጥርጣሬ ማየት ጀመረ በቃ ሌላ ቀን የተጠቀመ ጠይቅና ትወስዳለህ።
ገብቶኛል ይሄም ዞር በልልኝ ማለቱ ነው። ከቦታው ተንቀሳቀስኩ።
ቀበና አካባቢ ያለአትክልት ቤት የገጠመኝን ነገር እያስታወስኩ ጉዞዬን ቀጠልኩ። ጭማቂ ቤቱ በጣም ያምራል ለመጀመሪያ ጊዜ የገባሁት ከሰው ጋር ነበር።
እኛ የቀረበልንን ተጠቅመን ወደ ማጠናቀቁ ስንደርስ ሁለት ቆነጃጅቶች ገቡ። ጓደኛዬ የኔንም ያህል ባይሆን በሴት አይጨክንም ከበሩ ጀምሮ ተቀብሎ በዓይኑ እየሸኘ አስቀመጣቸው። ከእሱ ዓይን የተቀበላቸው አስተናጋጅ ጠጋ ብሎ ትዕዛዝ ሊቀበል ሲያጎነብስ አንዷ አቡካዶ አዘዘች፤ አንደኛዋ ግን ለማዘዝ ግድግዳ ላይ በሚያምር መስታወት (ፍሬም) የተለጠፈውን ዶክተር ማማከር ነበረባት እናም ዓይኗን ግድግዳው ላይ ተክላ ቀረች።
ዓይኗ ያምራል። እናት ነገ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስብሰባ ስላለብኝ ዓይንሽን ብታውሽኚ ልላት አሰብኩ። ይሄን ውበቷን እያደነቀ ያለው ዓይኔ ዓይኗን ተከትሎ ግድግዳ ላይ ወደ ተለጠፈው ዶክተር አመራ። ዶክተሩ እኔንም ይመረምረኝና መድኃኒት ያዝልኝ ጀመር። እያንዳንዱ ፍራፍሬ ለየትኛው በሽታና የአካል ክፍላችን ጠቀሜታ እንዳለው ተዘርዝሯል። ይሄ ከመንገድ ላይ ነጋዴዎች በሁለት ነገሮች ይለያል። የመጀመሪያው ድምፅ አያሰማም ሁለተኛው ደግሞ የእያንዳንዱን ፍራፍሬ ፎቶ የያዘ ሲሆን ያልፈለገ አለማንበብ ይችላል። እነዚያን የመንገድ ላይ ማስታወቂያዎች ግን አላፊ አግዳሚው ሁሉ አለማስተዋል ትኩረት አለመስጠት ቢችልም የመስማት ግን ግዴታ አለበት።
የሚያመሳስላቸው ደግሞ ሁለቱም ላቦራቶሪ የማያስጠቅሙ ሲሆን በሽታውን ማወቅ የታማሚው ግዴታ ነው። የእነሱ ሥራ ለሁሉም በሽታ መድኃኒት ማቅረብ ነው። ሌሎችም አሉ ለማዲያት፣ ለፊት ጥራት የዝንጅብል ቫዝሊን፤ በበኩሌ ባዝሊን ከዝንጅብል መሰራቱን አላውቅም። የእሬት ሳሙናም አለ ፤ እሱ ፈንገስ፣ ቋቁቻ፣ ጭርት ከማጥፋት ባለፈ የማይፈልጉትንም ፍቅር እንደሚያስለቅቅ ሰምቻለሁ። ማስታው ቂያው ይቀጥላል ።...
እዚህ ውስጥ ያለውና ለእኔ የገባኝ ትልቁ ምስጢር ግን ፈውስ ይገኝባቸዋል ተብለው የሚጠቀሱት በሽታዎች በሙሉ እንኳን ገብተውባቸው በይሆናል ብዙኃኑን እንቅልፍ የሚነሱ አሳሳቢና አስጨናቂ ናቸው። በደንብ ሳስተውል ደግሞ የበሽታዎቹም መነሻ ምክንያቶች የተለያዩና በርካታ ከመሆናቸው ባሻገር ከመላምት በዘለለ በዚህ ይከሰታሉ አይባሉም። ብዙውን ጊዜም የአኗኗርና የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከል ለመቆጣጠር ዕድሉ እንዳለ የሚነገርላቸው ናቸው።
እንግዲህ ይግረማችሁ! እነዚህ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ምሁራንን ላስጨነቁ በሽታዎች ነው አዲስ አበባ በየመንገዱ በ50 ብር መድኃኒት የምታቀርበው። አዲስ አበባ ተአምራዊነቷ ይሄ ብቻ አይደለም። በየሜዳው የተበተኑ ያልተማሩ ደፋር ዶክተሮችም፣ ፋርማሲስቶችም አሏት። በጣም የሚገርሙኝ ግን ይሄን እያዩ ዝም የሚሉት የመንግሥት አካላት ናቸው። ለነገሩ ማን ያውቃል እነሱም ወይ ከነጋዴዎቹ አልያም ከተጠቃሚው ወገን ቢሆኑስ ? እኔ ግን በሌለኝ ሥልጣን ወዲያ ወዲህ ተናድፌ ግልምጫ አትርፌያለሁ። ቁንጥጫ ግን የለም!

ራስወርቅ ሙሉጌታ 

Published in መዝናኛ
Saturday, 07 July 2018 19:26

ለሴቶች ጉልበት

ዓለማችን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ፤ የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ልዕልና በእጅጉ እንዲያድግ ያደረጉ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ በፖለቲካው፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች ለተገኙ ውጤቶች ከሚጠቀሱ ሰዎች መካከል ሴቶች ተጠቃሾቹ ናቸው።
«ሴቶች በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ ከወንዶች እኩል ተሳትፈው ውጤት ማስመዝገብ አይችሉም» የሚል አመለካከት ባለባት የአፍሪካ አገራት እንኳን ሴቶች ጠንክረው ሰርተው የአገር መሪ ሲሆኑ በኢኮኖሚው ከወንድ እኩል ሀብት ሲያፈሩ ታይተዋል፡፡ በሰሯቸው ሥራዎች አንቱ የተባሉ ሴቶች በዓለም ላይ ተስተውለዋል። በሥራቸው ራሳቸውን ረድተው አገራቸውን ጠቅመው ዝናን ከማትረፍ ባሻገር ከታች ለሚመጡ ሴቶች ተምሳሌት መሆን ችለዋል፡፡ በትምህርታቸው፣ በሰሩት ሥራ፣ በቁርጠኝነታቸው፣ በአመራር ብቃታቸው ... ለሌሎች አርአያ ከሆኑ የዓለማችን ታዋቂ ሴቶች መካከል አንዳንዶቹን በማንሳት ለዛሬው ለንባብ አብቅተናል።
በኢትዮጵያ በፖለቲካው ዘርፍ ከአገር ውስጥ አለፍው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታ ላይ በማገልገል ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ ሴቶች መካከል አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ አንዷ ናቸው፡፡ አምባሳደሯ በአዲስ አበባ ከተማ ተወልደው ያደጉ ሲሆን የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምርታቸውን በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡ በወቅቱም የውጭ ነፃ የትምህርት ዕድል በማሸነፍ ወደ ፈረንሳይ በመሄድ ትምርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
በዚህም ከፈረንሳዩ ሞንተፒሊር ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘት ቻሉ፡፡ በፈረንሳይ አገር ለዘጠኝ ዓመት ያህል ከኖሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ በመሆን አገራቸውን አገልግለዋል፡፡
አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩ ሲሆን፣ በጂቡቲና በሴኔጋል የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል፣ በአፍሪካ ኅብረት፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እንዲሁም በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፡፡
አምባሳደሯ ባላቸው ብቃት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን በአፍሪካ ህብረት ልዩ ተወካያቸው እና በአፍሪካ ህብረት የተመድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አድርገው ሾመዋቸዋል።
በዚህም መሠረት አምባሳደሯ የሥራ ጊዜያቸው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 23ቀን 2018 የሚያበቃውን አቶ ኃይሌ መንከሪዮስን የሚተኩ ይሆናል። በተሰጣቸው የኃላፊነት ቦታም በብቃት ሥራቸውን እንደሚወጡ ይታመናል። እኚህ ለሴቶች አርአያ መሆን የቻሉ ጠንከራ ኢትዮጵያዊት ናቸው።
አምባሳደር ሳህለወርቅ በመንግሥት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ በመሥራት ከአገራቸው አልፈው አፍሪካን የሚያኮራ ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ሴቶች በየትኛውም የሥራ መስክ ላይ ቢሰማሩ ከማንኛውም ሰው እኩል መሥራት እንደሚችል ያስመሰከሩ ናቸው፡፡
ሌላዋ ኢትዮጵያዊት በአማራ ክልል ወሎ ተወልደው ያደጉት ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ ናቸው። ወይዘሮ የትነበርሽ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡት ገና በልጅነታቸው ነበር፡፡ ይህም በአካባቢያቸው በስፋት ከሚካሄደው ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንዲያመልጡ አድርጓቸዋል፡፡ ወ/ሮ የትነበርሽ የመጀመሪያ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርታቸውን በሻሸመኔ የካቶሊክት ትምህርት ቤት እና በአዲስ አበባ ደግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡
ከዚያም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በሶሻል ዎርከ ሰርተዋል፡፡ ወ/ሮ የትነበርሽ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጸረ ኤድስ ንቅናቄ ውስጥ ከ2004- 2005 ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነበሩ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ማህበር እ.አ.አ በ2006 እንዲመሰረት አድርገዋል፡፡ በወቅቱም የማህበሩ ፕሬዚዳንት በመሆን በኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ በፀረ ኤድስ እንቅስቃሴ ውስጥ በተሳተፉበት ጊዜ አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ በዚህም እ.አ.አ በ2003 ከደቡብ አፍሪካ ለሴቶች የሚሰጥ አማኒታሬ የተሰኘ ሽልማትን መጎናጸፍ ችለዋል ፡፡
ከሃያ በላይ በሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በበጎ አድራጎት ሥራ እያገለገሉ የሚገኙት ልበብርሃኗ የትነበርሽ ከ2003-2007 የኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ማህበርን በሊቀመንበርነት መርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማጎልበቻ ልማት ማዕከልን ከመሠረቱ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን መካከልም አንዷ ናቸው፡፡
ማዕከሉም አካል ጉዳተኞች በተለያዩ የኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራሞች ውስጥ ተሳትፏቸው እንዲጨምር የሚያደርግ ነው፡፡ የትነበርሽ የአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች አምሳደር አባል በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ አካል ጉዳተኞችን የሚደግፍ ፕሮጀክት ላይ እየሠሩ ሲሆን እ.አ.አ 2007 ላይ የኖቬል ሽልማት ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ የትነበርሽ ሴት በእዚያ ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ተጨምሮባቸው እንኳን ከማንም በላይ በመስራት፣ በመምራት፣ እንዲሁም በተሳተፉባቸው በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ በመሆን በአርአያነታቸው በብዙዎች የሚነሱና የሚወደሱ ናቸው።
በአፍሪካ ላይቤሪያ በፖለቲካው ዘርፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ሴቶች መካከል የ78 ዓመት ባለጸጋ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ አንዷ ናት ፡፡ ሰርሊፍ በላይቤሪያ ሞንሮቪ እየተባለች በምትጠራ ሠፈር እ.አ.አ 1938 የተወለደች ሲሆን በአካውንቲንግ እና በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች፡፡ ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲም በሰው ሀብት አስተዳደር በዲግሪ መመረቅ ችላለች፡፡ ሰርሊፍ በአገሯ ላይቤሪያ በማንኛውም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፍ ላይ በመሳተፍ የምትታወቅ ሲሆን በአገሪቱ በፖለቲካ ውስጥም 30 ዓመት ያህል ተሳትፎ አድርጋለች፡፡ በፖለቲካ ቆራጥ አቋም ያላት ሴት ናት፡፡ በዚህም በአንድ ወቅት ላይ ለእስር ተዳርጋም ነበር፡፡
ላይቤሪያ በፕሬዚዳንት ዊሊያም ቶልበር በምትመራበት ወቅት ጆንሰን ሰርሊፍ በአገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስትር ዴኤታ ሆና አገልግላለች፡፡ እ.አ.አ 1980 የአገሪቱ የጦር አዛዡ ሳሙኤል ድያ ፕሬዚዳንት ቶልበርን ገድለው የሥልጣን መንበራቸውን ሲቆናጠጡ ሰርሊፍ ሥራዋን በመተው በኬንያ ናይሮቢ አድርጋ አሜሪካን ገባች፡፡ በአሜሪካ አገርም የአንድ ባንከ የበላይ አስተዳዳሪ በመሆን ሰርታለች፡፡
ኤለን ሰርሊፍ እ.አ.አ በ1989 ወደ አገሯ ተመልሳ በአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ብትሳተፍም ውጤታማ መሆን አልቻለችም፡፡ ከሽንፈቷ በኋላ ወደ ኮትዲቯር በስደት ለመሄድ ወስና ወደዚያው አቀናች፡፡ ሆኖም ግን ተስፋ ሳትቆርጥ ጠንክራ ከሠራች ፕሬዚዳንት የመሆን ህልሟን እውን እንደምታደርግ ጠንቅቃ የምታውቀው ሰርሊፍ ወደ አገሯ ተመልሳ እ.አ.አ 2005 ዩኒቲይ ፓርቲን ወክላ በፕሬዚዳንትነት ተወዳደረች፡፡ ውድድሩንም በማሸነፍ የላይብሪያ ብቸኛ ሴት ፕሬዚዳንት ለመሆን በቃች። በዚህም የአፍሪካ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ፕሬዚዳንት ለመሆን የበቃች ሲሆን ከአምስት ዓመት በኋላ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆናለች፡፡ በዚህም በርካቶች ዓላማዋን ለማሳካት የታገለች፣ ለፖለቲካ ተሳትፎ ጠንካራ አቋም ያላት ሴት ሲሉ ገልጸዋታል፡፡
ከድህነት በመነሳት የዓለም ቁጥር አንድ የቴሌቪዢን ሾ በማዘጋጀት ዝናን ያተረፈችው አሜሪካዊቷ ኦፕራ ዌልፌሪ ናት፡፡ ዌልፌሪ በችግር ውስጥ ተቆራምዳ ያደገች ሲሆን የመጀመሪያ ሥራዋን የጀመረችው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለች ነበር፡፡ በወቅቱም በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ በፍሪላንስ ጋዜጠኝነት መስራት ጀመረች፡፡ በዚያም ተወዳጅነትን ማትረፍ ቻለች፡፡ ይህን የተመለከቱት የሚዲያ ባለሙያዎች አካባቢያዊ በሚገኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ በዜና አንባቢነት እንድትሰራ አደረጓት፡፡ ይህም ለኦፕራ ስኬት የበለጠ መንገድ ጠረገላት፡፡ በመቀጠልም የራሷን ኦፕራ ዌልፌር ሾ ማዘጋጀት ጀመረች፡፡
በዚህም የሴትየዋ ስም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናኘ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷም በዚያው መጠን እየጨመረ መጣ፡፡ ዌልፌር ቴሌቪዥን ሾ የታዋቂ ደራሲያን መጽሐፍ መገምገምን ፣ የታሪክ ይዘት ያላቸው ፣ ጤናን የተመለከቱ ጉዳዮችን ማቅረብ ፣ ሥነልቦናን፣ መንፈሳዊ ጉዳዮችን የያዙ ፕሮግራሞች ያካተተ ነበር፡፡ በዚህም ብዙ ተመልካቾችን ማግኘት ችላለች፡፡ ሲ ኤን ኤን በአንድ ወቅት «በዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረች ያለች ሴት» ብሎ ሲጠራት ለሰዎች የምታደርገውን የበጎ ፍቃድ እንቅስቃሴዎች፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና በዓለም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የምታነሳቸውን ሃሳቦች በማድነቅ ነው፡፡
ኦፕራ በዓለም ላይ በኢኮኖሚ ሚሊየነር ከሆኑ ሴቶች መካከል ተመድባለች፡፡ በዚህም ከድህነት ተነስታ ጠንክራ በመስራት ለበርካታ የዓለማችን ሴቶች ተምሳሌት መሆን የቻለች ጥቁር አፍሪካዊ ሴት ናት፡፡
እንግዲህ ሴቶች ቀደም ባሉ ረጅም ዘመናት ጀምሮ ቁጥራቸው አነስ ቢልም በታሪክ በጀግንነት፣ በታዋቂነት ሲነሱና ሲጠቀሱ ቆይተዋል። የአገር መሪ እስከመሆን የደረሱ በአርአያነት የሚጠቀሱም አሉ። እነዚህ ሴቶች አሁንም በሥራ ላይ ላሉና ለአዲሱ ትውልድ ጉልበት ናቸው።

ሰብስቤ ኃይሉ

Published in ማህበራዊ

በአገራችን በተግባር ላይ ከዋሉ ህጎች መካከል በተለይ የፀረ ሽብር፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት እንዲሁም የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ በተደጋጋሚ ጊዜ በአገር ውስጥ እና በውጪውም ጭምር ቅሬታ እና ትችት ይሰነዘርባቸዋል። በመሆኑም በህጎቹ ዙሪያ ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? የሚለውን ጥናት የሚያጠና የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ በቅርቡ ተቋቁሟል። አማካሪ ጉባኤው 13 አባላት ያሉት ሲሆን ይህን የአማካሪ ጉባኤ በማቋቋም ስራ ላይ ከሚሳተፉት መካከል ዶክተር ሙሉጌታ መንግስት አንዱ ናቸው።
ዶክተር ሙሉጌታ ቀደም ሲልም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ዙሪያ የፍትህ እና የህግ ዘርፉ ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከእርሳቸው ጋር በነበረን ቆይታ የአማካሪ ጉባኤው መቋቋም አስፈላጊነት እና ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለመጠይቅ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ እንደ ችግር ለሚነሱ ህጎች የማሻሻያ ሃሳብ የሚያቀርብ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባኤ ተቋቁሟል፡፡ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባኤ ሲባል ምን ማለት ነው? ለምንስ አስፈለገ?
ዶክተር ሙሉጌታ፦ የህግና ፍትህ አማካሪ ጉባዔ መንግስትን የማማከር ስራ የሚሰራ ነው፡፡13 አባላት ያሉት ሲሆን፤ የተመረጡትም በጉዳዩ ዙሪያ ባላቸው የትምህርት ዝግጅት፣ የስራ ልምድ፣ የተለያዩ ትውልዶችንና የስራ መስኮችን ይወክላሉ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ናቸው፡፡ በርካታ ባለሙያዎች ተመርጠው በመመዘኛዎች መሰረት ተለይተዋል፡፡ የተመረጡት ባለሙያዎች በዘርፉ የምርምር ስራ የሚሰሩ፣ የጥብቅና ሙያ ላይ የተሰማሩ፣ በዳኝነትና በዐቃቤ ህግነት ስራ ያገለገሉ ናቸው፡፡ ወጣቶች፣ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙና ረጅም እድሜ ያላቸው እንዲሁም ህግና ፍትህን ከስነ ጾታ አኳይ በመመልከት ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች ተካትተውበታል፡፡ በተቻለ መጠንም ለማመጣጠን ተሞክሯል፡፡
የጉባኤው ዋና ተልእኮ የአገሪቱን የህግና ፍትህ ስርዓትን ማሻሻል ነው፡፡ እንዲሁም ሲተገበሩ ከነበሩ የለውጥ ስራዎች በመማር የህግና የፍትህ ስርዓቱ ወደማያቋርጥ የለውጥ አዙሪት ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦችን ለመንግስት ማቅረብ ነው፡፡ ጉባኤው ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ እንደመሆኑ ባለሙያዎቹ ጥናታቸውን መሰረት አድርገው ምክራቸውን ለእርሳቸው ያቀርባሉ፡፡
ምክር ከመስጠት ባሻገር መንግስት ምክሩን ተቀብሎ ሲተገብር አተገባበሩን በመገምገም ተከታትለው የማስተካከያ ሃሳቦችና ሙያዊ ድጋፎችን ይሰጣሉ፡፡ የጉባኤ አባላቱ የሚሰሩት ተከፍሏቸው አይደለም፡፡ ‹‹ለአገራችን አስተዋጽኦ እናደርጋለን›› ብለው ፍቃደኝነታቸውን የገለጹ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሙሉ ጊዜውን መስዋዕት አድርጎ ጉባኤውን የሚያግዝ ጽህፈት ቤት አለ፡፡ ጽህፈት ቤቱ እየተደራጀ ይገኛል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ይካተቱበትና ጉባኤው በሚሰጠው ሥራ መሰረት ጥናት ይከናወናል፡፡
አዲስ ዘመን፦ ጉባኤው ለቀጣይ ሊሰራቸው ያቀዳቸው የስራ መርሃ ግብሮች ምን ምን ናቸው?
ዶክተር ሙሉጌታ ፦ የሶስት ዓመታት የስራ መርሃ ግብር አለው፡፡ ጉባኤው ለቀጣይ ሊሰራቸው ያቀዳቸው የስራ መርሃ ግብሮች ስምንት ንኡሶችን ይዟል፡፡ በቀዳሚነት ያስቀመጠው የስራ ዕቅድ ህግ የማመንጨትና የማውጣት ስርዓቱን ማሻሻል ነው፡፡ ወይም የህግ ማመንጨትና ማውጣት ስርዓቱን ለማዘመን የሚያስችሉ የለውጥ ሃሳቦችን ለመንግስት ማቅረብ ነው፡፡_ይህ ስራ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወጣ አዋጅ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጣ ደንብ፣ በተለያዩ የአስተዳደር ተቋማት ባልተማከለ ሁኔታ የሚወጡ መመሪያዎች አሉ፡፡ ህግ፣ አዋጅ ፣ደንብና መመሪያዎች የሚወጡበትን ስርዓት በማጥናት ያለባቸው ችግሮች፣ ህጎቹ ጥራታቸውን ያልጠበቁ የሆኑት ለምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ መርምሮ የማስተካከያ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
በሁለተኛነት የተቀመጠው የህግ ማሻሻያ ንዑስ ፕሮግራም ከመጀመሪያው ንዑስ መርሃ ግብር ጋር የሚቀራረብ ነው፡፡ የሚለየው የመጀመሪያው ንዑስ መርሃ ግብር ስርዓቱን የሚያሻሽል ሲሆን፤ ይህ ደግሞ የተመረጡ ህጎችን ወስዶ ያሻሽላል፡፡ በእርግጥ ስርዓቱ ሲሻሻል የህጎቹም ጥራት አብሮ ይሻሻላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ግን ያ ረጅም ጊዜ ይወስዳል ፡፡ እስከዛው ጊዜ የማይሰጣቸው ተብለው የተለዩ ህጎች አሉ፡፡ እነዚህን ህጎች የማሻሻል ሃሳብ ያቀርባል፡፡
ሶስተኛው ንዑስ መርሃ ግብር የዳኝነት ስርዓቱ ማሻሻያ ነው፡፡ በአገራችን የዳኝነት ስርዓት ሲባል ሁለት ተቋማትን ይመለከታል፡፡ በአንድ በኩል ፍርድ ቤቶች ሲሆኑ ሌላው በከፊል የዳኝነት ስልጣን የተሰጣቸው አስተዳደራዊ ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ያሉበትን ሁኔታ አጥንቶ የበለጠ ህዝብን አገልጋይ፣ ውጤታማና ፍትሃዊ ሊሆኑ የሚችሉበትን ሁኔታ መርምሮ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
አራተኛው ንዑስ መርሃ ግብር የወንጀል ፍትህ ስርዓቱን የሚመለከተው ነው፡፡ በወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ ሶስት ዋና ተቋማት አሉ፡፡ ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ ዐቃቤ ህግና ማረሚያ ቤቶች፤ በእነዚህ ተቋማት ጥናት በማካሄድ ያሉባቸውን ችግሮች ለይቶ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችላቸውን የመፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
የፍትሃብሄር ህግና በአስተዳደር ተቋማት የህግ ማስከበር ስርዓቱን ማስተካከል ሌላው ተግባር ነው፡፡ ለምሳሌ ፍትሃብሄር የሚባለው የግለሰቦች ሙግት፣ ውል፣ ንብረት ሊሆን ይችላል። የሚሟገቱት ግለሰቦች ናቸው፡፡ የሚሟገቱትም ፍርድ ቤት ሄደው ነው፡፡ እዚህ ላይ የመንግስት ሚና ውስን ነው፡፡ የመንግስት ሚና በዋናነት የመረጃ እና የመዝገብ ስርዓትን ማደራጀት ነው፡፡ ለምሳሌ የንብረት፣ የተሽከርካሪ ባለቤትነት፣ የመሬት ባለይዞታ ፣ የውልና ሰነዶች ምዝገባ ስርዓቶች ማጠናከር ነው፡፡ ስርአቶቹ ትስስራቸው የጠበቀ፣ ዋስትናቸው የተረጋገጠ እና ተደራሽ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ንብረት መመዝገቡ ብቻ ሳይሆን አንድ ዜጋ ውል መፈጸም ቢፈልግ እና መረጃ ቢያስፈልገው የመረጃ ስርዓቱ ተደራሽ መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ዙሪያ ችግሮችን የማስተካከል ስራ ነው የሚሰራው፡፡
ህጎች የሚከበሩት በአብዛኛው በፖሊስ ሳይሆን በአስተዳደር ተቋማት ነው፡፡ ለምሳሌ የአካባቢ ጥበቃ ህጎች የሚጠበቁት በአስተዳደር ተቋማት ሲሆን፤ የአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር በየአካባቢዎቹ እየሄደ የሚያደርገው የቁጥጥር ስራ አለ፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን የሚያደርገው የቁጥጥር ስርዓትም አለ፡፡ ብዙ የአስተዳደር ተቋማት በሚያደርጉት የቁጥጥርና የክትትል ስርአት ነው ህጎቹ የሚከበሩት፡፡ ነገር ግን ይህ የክትትል ስርዓት እየተከናወነ ያለው ባልተማከለ መንገድ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ አጥንቶ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ _አምስተኛው ንዑስ መርሃ ግብር ሆኖ ተቀምጧል፡፡
ስድስተኛው የዴሞክራሲ ተቋማትን ይመለከታል፡፡ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ማለት ነው፡፡ በሰባተኛነት የተቀመጠው ንዑስ መርሃ ግብር ደግሞ የህግና ተያያዥ አገልግሎቶች የሚባሉት ናቸው፡፡ አቅም ለሌላቸው ሰዎች የሚሰጥ ነጻ የህግ አገልግሎት ሲሆን፤ በእነዚህ ውስጥ ነጻ ምክር፣ ነጻ ጥብቅና እና የመሳሰሉትን ይመለከታል፡፡ ጠበቆች የፍትህ ስርዓቱ አንድ አካል በመሆናቸው የፍትህ ስርዓቱን ማሻሻል የሚቻለው የእነርሱን ሁኔታ በማሻሻል እንደመሆኑ ጠበቆችንም ይመለከታል፡፡ በመጨረሻም የህግና ስልጠና ተያያዥ ትምህርት ይታያል፡፡ ፖሊሶችና የማረሚያ ቤት ባለሙያዎች እንዴት እንደሚሰለጥኑ ይመረምራል፡፡ በጥቅሉ ሁሉን አቀፍ መርሃ ግብር አቅፏል፡፡
እንዲህ ሆኖ የተቀረጸው ከዚህ በፊት ከነበሩ የለውጥ ስራዎች ትምህርት በመውሰድ ነው፡፡ የፍትህና የህግ ስርዓቱ እርስ በእርሱ የተቆራኘ፣ በብዙ ተዋንያን እና በብዙ ግንኙነቶች የተዋቀረ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች፣ ማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ፣ ዐቃቤ ህግ፣ጠበቆች፣ ህግ አውጪው፣ ህግ አስፈጻሚው አካል አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ የፍትህና የህግ ስርዓቱ አካል ናቸው፡፡ በመሆኑም አንዱን ነጥሎ በመሄድ ችግሩን መፍታት አይቻልም፡፡ እርስ በእርሱ ተመጋጋቢ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ እይታና ምልከታ ሊኖር ይገባል፡፡ በመቀጠል በቅደም ተከተል ስርዓት በማስያዝ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም አማካሪ ጉባኤው ከላይ የተዘረዘሩትን ስምንት ንዑስ ፕሮግራሞች በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
አዲስ ዘመን፤ የሚሻሻሉት የትኞቹ ህጎች ናቸው? እንዴትስ ተመረጡ ? ስራዎቹን ለማጠናቀቅ ሶስት ዓመት አልበዛም ?
ዶክተር ሙሉጌታ፤ እስካሁን አራት የሚደርሱ ህጎች ተለይተዋል፡፡እነዚህም የፀረ ሽብር ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት እንዲሁም የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጆችና ጠበቆችን የሚመለከተው የህግ ማእቀፍ ናቸው፡፡ እነዚህን በአጭር ጊዜ ለማሻሻል እቅድ አለ፡፡ ወደፊትም በምክክር መድረኮች፣ በጥናቶች የሚለዩ ጊዜ የማይሰጣቸው ተብለው የተለዮ ህጎች አሉ፡፡ እነርሱንም ወደ ማሻሻሻል ሊገባ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ሁሉም ስራዎች ለማለቅ ሶስት ዓመታት ይፈጅባቸዋል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በሁለተኛነት የተጠቀሰው የህግ ማሻሻያ ንዑስ መርሃ ግብር የተመረጡ ጊዜ የማይሰጣቸው የህግ ማሻሻል ስራዎች ከሶስት እስከ ስድስት ወራት ማጠናቀቅ አለብን፡፡
አዲስ ዘመን ፦ የሰንደቅ ዓላማ ጥያቄና የጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ጊዜ ገደብን በሚመለከት የህገ መንግስት ማሻሻልን አይጠይቅም? የህገ መንግስት ማሻሻያ በሌለበት አንዳንድ አከራካሪ ህጎችን ለመለወጥ የሚደረገው ጥረትስ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል?
ዶክተር ሙሉጌታ፦ በስምንቱ ንዑስ መርሃ ግብሮች ውስጥ ህገ መንግስት ማሻሻል የሚል የለም፡፡ ዋናው ስራው የህግና ፍትህ ስርዓት አቤቱታ የሚነሳባቸውን ህጎችና የህግ አወጣጥ ስርዓቱን ማሻሻል ነው፡፡ ከህገ መንግስቱ ወረድ ያሉ ህጎችና ተቋማትን ማሻሻልና የማጠናከር ስራ ይሆናል፡፡ ጉባኤው በቀጥታ ህገ መንግስትን የማሻሻል ስልጣን አልተሰጠውም፡፡ ግን ህገ መንግስቱም የኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት አንድ አካል በመሆኑ ጉባኤው ስራውን በደንብ ሲጀምር፣ ከህዝብ ጋር እየተወያየ፣ ጥናቶችን እየሰበሰበ የሚያየው ነው የሚሆነው፡፡ እስካሁን በተለያዩ ሁኔታዎች በተደረጉ ጥናቶች በዋና ችግርነት ህገ መንግስቱ አልተነሳም፡፡ በዋናነት የተነሱ ጥናቶች ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ መብቶችን ለመተግበር የሚያስችል ተቋማዊ አሰራር አለመኖር ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ስራ ለመስራት ህገ መንግስቱን ማሻሻል አያስፈልግም፡፡
በእርግጥ ህጎቹ የሚወጡት ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው ነው፡፡ ህግ የሚወጣው ህገ መንግስቱ ውስጥ የተቀመጡ መርሆዎች፣ መብቶችንና ድንጋጌዎችን የበለጠ ለመዘርዘር ተብሎ ነው፡፡ ህግ ማውጣት የሰው ስራ ስለሆነ ስህተቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ በአፈጻጸምም ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ህጉ ሲቀረጽ ስህተት ተሰርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ህጉ ሲተገበር በአፈጻጸም ሂደት ችግሮች ታይተው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ህጎቹ የሚሻሻሉት ከልምድ በመነሳት ነው፡፡
የተመረጡት ህጎች ለምሳሌ የጸረ ሽብር ህጉ ዓላማ፣ ይዘቱ፣ በአፈጻጸም ያጋጠሙ ችግሮች ይታይሉ፡፡ መሻሻል አለበት ወይ? ይህን ጥያቄ ጉባኤው በመጀመሪያ መመለስ አለበት፡፡ በአፈጻጸም ሂደት የተገኙ መረጃዎችን፣ ልምዶችንና ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ይህ አዋጅ ሊሻሻል የሚገባው ከሆነ እንዴት መሻሻል እንዳለበት ጥናት አድርጎ ምላሽ ይሰጣል፡፡ የአማካሪ ጉባኤው አባላት ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ ነው የሚፈለገው፡፡ ሙያቸውንና ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው እንዲተገብሩ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱ መመሪያቸው ነው የሚሆነው፡፡ ህገ መንግስቱ ውስጥ የህግ የበላይነት የሚል መርህ አለ፡፡ የህግ የበላይነት መርህ የዚህ ስራ መመሪያ ነው፡፡ ስለዴሞክራሲ ስርዓት፣ ስለህዝብ ተሳትፎ፣ ስለሰብአዊ መብት፣ ፍትህ ስለማግኘት፣ ስለእኩልነት መብት ያወራል፤ እነዚህ ነገሮች ለዚህ ስራ መሰረት ናቸው እንጂ እነርሱን ለማሻሻል አልታሰበም፡፡
አዲስ ዘመን፦ አሁን እንደሚሉኝ ከሆነ እንዲሻሻሉ የተለዩ ህጎችን ለመቀየር ይጠናል እንጂ ውሳኔ ላይ አልተደረሰም፡፡ ታዲያ ይሻሻላሉ የተባሉት እንዴት ተመረጡ?
ዶክተር ሙሉጌታ፦ ጥሩ ጥያቄ ነው። ውሳኔ የሚወሰነው ጥናትን መሰረት አድርገው ነው፡፡ ህጎቹ የተመረጡበት ምክንያት በተደጋጋሚ በተለያዩ የውይይት መድረኮች እና በተሰሩ ጥናቶች ችግር እንዳለባቸውና መቀየር እንደሚገባቸው ስለሚነሳ ነው፡፡ አንዳንዴ ከአፈጻጸም ጋር ተያይዞ፣ አንዳንዴ ህጎቹ ለአስፈጻሚው አካል ሰፊ ወይም ያልተገደበ ስልጣን የሚሰጡ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ ይህ ሁኔታ ‹‹ለብልሹ አሰራር ያጋልጣቸዋል›› የሚል አቤቱታም ይቀርባል፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ከአላማውና ከይዘቱ ጋር ተያይዞ አቤቱታ ይቀርባል፡፡ አቤቱታ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካላት የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶችም አሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረኮች በእነዚህ ህጎች በተለይም የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ እንዲሁም የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጆች በተደጋጋሚ ትወቀስበታለች፡፡ ህጎቹ ከወጡ የተወሰኑ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በመሆኑም መሻሻል አለባቸው ወይ? መሻሻል ካለባቸው እንዴት ይሻሻሉ? የሚለው ባለሙያዎችንና ህዝብን በማሳተፍ ጥናት በማካሄድ ይወሰናል፡፡
እዚህ ላይ ሶስት የአሳታፊ ስርዓቶችን እንከተላለን፡፡ ለምሳሌ የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅን አስመልክቶ ጥናት ይካሄዳል፡፡ ለጥናቱ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎች የሚሰበሰቡት ከባለድርሻ አካላት ነው፡፡ ህጉን ከሚያስፈጽሙ፣ በህጉ ከሚገዙ ከሚዲያና ከአስፈጻሚ አካላት መረጃ ይሰበሰባል፡፡ በቃለ መጠይቅ፣ እስካሁን ባለድርሻዎቹ የሰሯቸውን ጥናቶች በግብአትነት በመጠቀምና የተለያዩ የምክክር መድረኮችን በማካሄድ ሊሆን ይችላል፡፡
ሁለተኛው የተሳትፎ መንገድ ባለሙያዎቹ ረቂቁን ሲያዘጋጁ በጉባኤው ድረ ገጽ ላይ የሚለቀቅ በመሆኑ ማንኛውም ዜጋ አስተያየት እንዲሰጥበት ይደረጋል፡፡ ከባለድርሻዎች ጋር የሚዘጋጀው የምክክር መድረኮች ሶስተኛው የአሳታፊነት መንገዱ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ በፍትህ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ ብዙ ስራዎች እንደተሰሩ ይታወቃል፡፡ በትግበራው ምን ውጤት ተገኝቶ ነው አሁን ወደ ሌላ አሰራር እንዲገባ ያስገደደው?
ዶክተር ሙሉጌታ፦ ህገ መንግስቱ ከወጣ ጀምሮ በፍትህ ስርዓቱ ህጎችን ከማጣጣም ጀምሮ ብዙ የማሻሻያ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ህገ መንግስቱ አንድም የፌዴራል የአገር አወቃቀርን አምጥቷል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን አሀዳዊ የአገር አወቃቀር ጋር ማጣጣም ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቶችንም በዚህ መንገድ ማደራጀት፣ ህጎችን ማሻሻል ለምሳሌ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉን፣ የቤተሰብ አዋጅ፣ የፍርድ ቤት አዋጅን የማሻሻል ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው አንድ የህግ ትምህርት ቤት ብቻ ነበር፡፡ የህግ ትምህርት ቤቶች መስፋፋትም አንዱ የለውጥ አካል ነው፡፡ ይህ የህግ ማሻሻያ አካል ነው፡፡
በአንድ ወቅት የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር በነበረበት ጊዜ ሁሉን አቀፍ የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ መርሃ ግብር ተነድፎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ሲፈርስ ወደሚመለከታቸው አካላት ተዘዋውሯል፡፡ ወደ ፍርድ ቤት፣ ፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴር፣ በቀድሞው አጠራር ፍትህ ሚኒስቴር ተዘዋውረው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው፡፡ በፍርድ ቤቶች ቢ ፒ አር፣ ቢ ኤስ ሲ የለውጥ ስራዎች ሲተገበሩ ነበር፡፡ የዳኞችና የችሎቶች ቁጥር መብዛት፣ የዳኞችና የዐቃቤ ህግ ስልጠና ማዕከል መቋቋም ሌላው የተሰሩ የለውጥ ስራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ለውጦች ተደርገውም አሁንም ህዝቡ በተለያዩ መድረኮች ስለ ፍትህ ስርዓቱ ያማርራል፡፡ ስለአገልግሎት ጥራቱ መጓደልና ስለብልሹ አሰራሩ ይነሳል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ የለውጥ ስራዎች እየተሰሩ ችግሩ ያልተቀረፈበት ሁኔታ ጥያቄ ይነሳል፡፡
በአንድ በኩል የለውጥ ስራዎቹ ሲቀረጹ በአቀራረጽ የዲዛይን ወይም የንድፍ ችግር ነበረባቸው፡፡ የፍትህ ስርዓቱን ጸባይ ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ የመንግስት የህዝብ አስተዳደር ስራ በሙሉ የህግ አስተዳደር ስራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ፍርድ ቤቶች፣ ዐቃቤ ህግ፣ ማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ጠበቆች፣ የህግ ትምህርት ቤቶችና የህግ ምርምር የሚሰሩ፣ ህግ አውጪ ከአዋጅ እስከ መመሪያ ብዙ አካላቶች አሉበት፡፡ እነዚህ ተነጣጥለው የሚሰሩ አይደሉም፡፡ በመሆኑም የለውጥ ስራ ሲታቀድ ይህንን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ባተገባበርም ሰፊ ችግር አለ፡፡ ያዝ ለቀቅ አሊያም የዘመቻ አይነት ስራ ይታያል፡፡
ዘመቻ ህዝብን ማነቃነቁ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ችግር ሰፊ ነው፡፡ ግን በተወሰነ ጊዜ ተተግብሮ የሚፈጸም አሰራር አለ፡፡ እንደ ቋሚ የመንግስት ስራ አይታይም፡፡ የዘመቻ ስራ በመከተል ለምሳሌ ቢ ፒ አር ተተግብሮ እሱ ተቋማዊ ቅርጽ ሳይይዝ ሌላ አዲስ ነገር ይተገበራል፡፡ ይህንን ትተን አዲሱን አንጠልጥለን የመሮጥ ስራ ሲሰራ ነው የቆየው፡፡ ቢ ፒ አር በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ለውጥ ማምጣቱ በግምገማ ተረጋግጧል፡፡ ይህ የለውጥ ስራ በአንድ ተቋም ለውጥ ስላመጣ ፍርድ ቤት አይተገበርም፡፡ ከየተቋማት ባህሪ ጋር መታየት አለበት፡፡ ፍርድ ቤት ያለው ችግር አንዱ ይህ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ ሳያምኑበት ነው ይተገብሩት የነበረው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ያለው አመራር ባልተለወጠበት፣ በቀድሞ ቅኝት ውስጥ ያለውን አመራር ይዞ በዘርፉ እንዴት ለውጥ ማምጣት ይቻላል?
ዶክተር ሙሉጌታ ፦ይህ በተለያዩ ንዑስ ዘርፎች ውስጥ የሚዳሰስ ነው የሚሆነው፡፡ ዞሮ ዞሮ አማካሪ ጉባኤው በሚያደርገው ጥናትና ግምገማ ላይ ተመስርቶ በሚያቀርበው ውሳኔ ላይ የሚመሰረት ይሆናል፡፡ ይህንን አስቀድሞ መተንበይ አይቻልም፡፡ የሚያቀርባቸው ምክረ ሃሳቦች ተቋማዊ መሆን አለባቸው፡፡ ጉባኤው የሚያመነጫቸው የለውጥ ሃሳቦች ተቋማዊ፣ ስር የሰደደና የማይቀለበስ መሆን ይኖርበታል፡፡ ያዝ ለቀቅ አሰራር መቀየር አለባቸው፡፡ ግለሰብ ወይም አንድ አመራር ወሳኝ ነው፡፡ ግን አንድ አመራር ብቻውን አይወስንም፡፡ ተቋማዊ አሰራሩ ነው የሚወስነው፡፡ ስራው በአንድ ሰው ላይ የሚንጠለጠል መሆን የለበትም፡፡ ተቋማዊ አሰራሩ የሚገለጸው በህግ በመሆኑ ዝርዝር ሆኖ አመራሩንም ሰራተኛውንም የሚመራ የህግ ማዕቀፍ ሊኖር ይገባል፡፡ በእኔ እምነት አመራር ስለተለወጠ ሳይሆን ዋናው ነገር ተቋማዊ አሰራሩን ማጠናከር ላይ ማተኮር ነው የሚገባው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ከህግና ፍትህ አማካሪ ጉባኤው ምን ውጤት ይጠበቃል ?
ዶክተር ሙሉጌታ ፦ በአጠቃላይ በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ መርሆዎች መሰረት ያደረገ የህግና የፍትህ ስርዓት እየገነባን እንድንሄድ የሚያደርግ ስራ መስራት ይጠበቃል፡፡ የተጠናከረ የህግ የበላይነት፣ የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብት በተግባር መዋል አለበት፡፡ ህገ መንግስቱን ያከበረ፣ የሕዝብ አገልጋይ፣ ሰብአዊ መብትን ያከበረ፣ ፈጣን፣ ውጤታማ፣ ፍትሃዊና አዋጭ የፍትህና የህግ ስርዓት ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡
የሚወጡ ህጎች ጥራታቸውን የጠበቁ፣ግልጽና ዝርዝር እንዲሆኑ ለማስቻል ይሰራል፡፡ ለአስፈጻሚው አካል የሚሰጡት ፈቃደ ስልጣን ምክንያታዊ የሆነ፤ ለፈቃደ ስልጣን የቁጥጥር ስርዓት የተዘረጋለት፤ ውጤታቸው በየወቅቱ እየተገመገመ የሚፈተሽበት ስርዓት የተዘረጋበት መሆን አለበት፡፡ ስርዓቱ ራሱን እያሻሻለ የህጎች ጥራት የሚሄድበት ስርዓት መፍጠር ይጠበቃል፡፡ ዜጎች በፍርድ ቤቶች በአጭር ጊዜ ጉዳያቸውን የሚጨርሱበት፣ ዳኝነት የሚጠናከርበት ስርዓት፣ ተጠያቂነት፣ ተደራሽነት፣ ግልጽነት የሚባሉት የህገ መንግስት መርሆዎች የሚከበሩበት እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ የሚፈለገው ለማስቀመጥ የህግና ፍትህ ስርዓቱ የህዝብ አገልጋይ፣ በህዝብ የታመነ፣ ውጤታማና እየተጠናከረ የሚሄድ የህግና ፍትህ ስርዓት መዘርጋት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ፦ ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ!
ዶክተር ሙሉጌታ ፦ እኔም አመሰግናለሁ!

ዘላለም ግዛው

Published in ፖለቲካ

የአራተኛው ዙር የህዝብና ቤት ቆጠራ በቀጣዩ አመት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዋናው ቆጠራ በተመረጡ 234 የጥናት ቦታዎች ከሰኔ 11 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም በገጠር፤ ከሰኔ 10 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 በከተማ ቤት ለቤት የሙከራ ቆጠራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡
የማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የቆጠራውን መረጃ ለመሰብሰብ መጠይቆችና የአሰራር መመሪያዎች በአምስት የተለያዩ ቋንቋዎች ተርጉሞ ለስራ ያዘጋጀ ሲሆን፤ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን (ታብሌት ) በማዘጋጀት የቆጠራውን ቅድመ ትግበራ ሙከራ አከናውኗል፡፡
የሙከራ ቆጠራው ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በገጠር 161 ሩቅና አስቸጋሪ እንዲሁም በከተማ 73 በድምሩ 234 የጥናት ቦታዎች ሲያከናውን ቆይታል፡፡ በተመረጡ የስደተኛ ጣቢያዎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና ሴተኛ አዳሪዎች እንዲሁም አርብቶና አርሶ አደሮችንም በማካተት መልኩ ነው የተከናወነው፡፡
ትግበራው ወደ ዋናው ቆጠራ ከመገባቱ አስቀድሞ ለቆጠራው የተዘጋጁ አሰራሮች አደረጃጀቶችና ግብአቶች፣ የቴክኖሎጂ እቃዎች፣ የጥራት መቆጣጠሪያ ስርዓቶች፣ መረጃ ማስተላለፊያና መቀበያ ማዕከላትን በመፈተሽ ዝግጁ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡
በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነትና መረጃ ስርጭት ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ በሙከራ ትግበራው ስለተገኘው ውጤት ሲገልጹ፤ ስራው በዋናነት የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ይፈልጋል፡፡ ኔት ወርክ ባለበት አካባቢ በሙሉ በተሳካ ሁኔታ መረጃ ወደ ማዕከል እየገባ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ዋናውን ቆጠራ ለማከናወን የታሰበው ቴክኖሎጂ መረጃን ከመስክ ወደ ማከማቻ ማዕከል የማስተላለፍ ሁኔታ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል ፡፡
እንደ አቶ ሳፊ ገለጻ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል በሌለባቸው አካባቢዎች ፓወር ባንኮችና ሶላር ፓኔል ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሙሉ ብርሃን የማይገኝበት አካባቢ መሳሪያውን በጸሃይ ብርሃን ለመሙላት የመጓተት ሁኔታ ታይቷል፡፡ ህዝቡ ለስራው ተሳትፎ ያደረገ ቢሆንም፤ ከግንዛቤ እጥረት አንጻር አንዳንድ አካባቢዎች የታዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህን ከዋናው ቆጠራ በፊት የሚስተካከሉ ይሆናል፡፡
ለሙከራ ቆጠራው ከተመረጡ አካባቢዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ አዋሾ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 01 አንዱ ነው፡፡ ከአዳማ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ቢሮ ለህዝብና ቤቶች ቆጠራ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ የቅድመ ስራ የሙከራ ቆጠራ ስታከናውን ያገኘኋት ከድጃ አማን እንደምትለው፤ ለናሙና ከተመረጠው አካባቢ ቤት ለቤት በመገኘት አንድ ቤት ውስጥ የሚገኙ የአንድ ቤተሰብ አባላት በሙሉ መረጃ ይሰበስባል፡፡ ስራው ላይ ያገጠመ አስቸጋሪ ሁኔታ የለም፡፡
ጥያቄው በርካታ ቢሆንም ህብረተሰቡ በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎን መረጃ በመስጠት ተሳትፏል፡፡ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች በጥያቄው መብዛት የመሰላቸት ሁኔታ አሳይተ ዋል፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ መረጃው የሚሰበሰበው ለህብረተ ሰብ ጥቅም መሆኑን በማስረዳት ትብብር እንዲያደርጉ በማበረታታት እና ሲገነዘቡም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መረጃ በመስጠት ይተባበራሉ፡፡
አንድ ቤተሰብ ስለኢኮኖሚ ሁኔታው፣ ስለትምህርትና ሌሎችም ጥያቄዎች ይቀርቡለ ታል፡፡ የተጠያቂውን ሁኔታ መሰረት በማድረግ መግባባት በሚችሉበት ቋንቋ ጥያቄው ይቀርባል፤ የምትለው ከድጃ ለቆጠራው ጥቅም ላይ የዋለው ቴክኖሎጂም በተለያዩ ቋንቋዎች በመዘጋጀቱ ለህብረተሰቡ አመቺና ቀላል ነው፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ የተለያየ ብዛት ያላቸው እንደመሆኑ እንዲሁም ሁሉም የቤተሰብ አባል ስለሚጠየቅ በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖረው ቆይታ የቤተሰብ ብዛትን መሰረት ያደርጋል፡፡ የቤተሰብ ብዛት ያለበት ቤት ከ40 እስከ 50 ደቂቃ በአማካኝ ሊፈጅ እንደሚችል በመጠቆም በቀን ከ16 እስከ 20 ቤተሰብ በቆጠራው ስትሸፍን እንደነበረም ትናገራለች፡፡
«ለቆጠራው ጥቅም ላይ የዋለው ቴክኖሎጂ ቀድሞ ልምምድን ይፈልጋል፡፡ ከመሳሪያው ጋር ለተግባባ ሰው አጠቃቀሙ ቀላል ነው፡፡ በመሳሪያው አጠቃቀም ዙሪያ ቀድሜ ስልጠና በመውሰዴ እስካሁን በስራው ላይ ምንም ነገር አልቸገረኝም፡፡ በቆጠራው ላይ በመሳተፌ ለኔ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ የህብረተሰቡን የአኗኗር ሁኔታ ባግባቡ ለማወቅ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ደረጃውን ለመረዳት አስችሎኛል፡፡ ከህብረተሰብ ጋር እንዴት መግባባት እንደሚቻል ጥሩ ልምድ ሆኖኛል» ትላለች ከድጃ፡፡
የሶስት ልጆት እናት የሆኑት ወይዘሮ በዳቱ ቡሊ በሻሸመኔ ከተማ አዋሾ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 01 ነዋሪ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል መምህርት የነበሩ ሲሆን አሁን የቤት እመቤት ሆነው ልጆቻቸውን በማሳደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በቆጠራው መረጃ ሲሰጡ ያገኘኋቸው ወይዘሮዋ፤ የቤተሰብ ሁኔታን፣ የኢኮኖሚ ደረጃቸውንና የተጠየቁትን ሌሎች መረጃዎችን በሙሉ ያለችግር ምላሽ በመስጠት ተባባሪ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡
ከዚህ በፊትም ስለቆጠራው መረጃ ስለነበራቸው ምንም እንዳልተቸገሩ ይናገራሉ፡፡ ቆጠራው የህዝብ ብዛት ምን ያህል መሆኑን ለመገንዘብ ስለሚረዳ ትክክለኛ መረጃ መስጠት ተገቢ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ህዝቡ ይህንን እንዲገነዘብ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ፡፡ ባለሙያዋ ተግባብታ መረጃ ለመሰብሰብ የምትችል መሆንዋን የሚመሰክሩት ወይዘሮ በዳቱ፤ ህብረተሰቡ ጥቅሙን ተገንዝቦ መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግም መክረዋል፡፡
በምግብ ቤት ስራ ላይ የተሰማሩትና የሁለት ልጆች እናት ወይዘሮ አስናቀች አጎናፍር ባለቤታቸው በሞት ስለተለዩአቸው በምግብ ቤታቸው የቀጠሯቸውን ሶስት ሰራተኞችን የማስተዳድሩ ኃላፊነት እንዲሁም ልጆቸቸውን የማሳደጉ ስራ የተጣለው በእርሳቸው ትከሻ ላይ ነው፡፡ አብረዋቸው የሚኖሩ የቤተሰብ ብዛት ምን ያህል እንደሆነ የተጠየቁትን መረጃ ተገቢ ምላሽ እንደሰጡ ይናገራሉ፡፡ ይህ አይነት መረጃ የህዝቦች ብዛት ምን ያህል እንደደረሱ እንዲሁም ምን እንደሚያስፈልጋቸው ለማወቅ ይረዳል፡፡
በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የአዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅና የአራተኛው ዙር ህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን የኦሮሚያ ክልል ጸሃፊ አቶ ሼኮ ጉሩ፤ ለአራተኛ ዙር ህዝብና ቤት ቆጠራ የተለያዩ ዝግጅቶች ሲሰሩ ቆይተዋል ፡፡ ከእነዚህ መካከልም አገሪቱን በቆጠራ ካርታ የመሸንሸን የካርታ ዝግጅት ስራው ምን ያህል የሰው ሃይል፣ መጓጓዣና የተለያዩ አስፈላጊ አቅርቦቶች ለመመደብ የሚሰሩ ስራዎችን ለማወቅ የሚያስችል ሲሆን ትግበራው መጠናቀቁንም ይናገራሉ፡፡
እስካሁን ሁለቴ የሙከራ ቆጠራ ተካሂዷል፡፡ ዛሬ የተጠናቀቀው የሶስተኛ ዙር የሙከራ ቆጠራ ነው፡፡ የሙከራ ቆጠራው ዋና ዓላማ በዋና ቆጠራው ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች በቅድሚያ በመለየት ለማስተካከል ታስቦ ነው፡፡ በዚህ መነሻነትም የቆጣሪ ባለሙያዎችና ተቆጣጣሪዎች ስልጠና ወስደው በናሙናነት በተመረጡ አካባቢዎች በመዘዋወር መረጃ ሰብስበዋል ሲሉም አቶ ሼኮ ይናገራሉ፡፡
የኦሮሚያ ክልል በ53 ሺ የቆጠራ ቦታ ተከፋፍሏል፡፡ በተጨማሪም ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን በቆጠራው ለማካተት አሁን የሰፈሩባቸውን አካባቢዎች መሰረት በማድረግ ዝርዝር ተወስዶ ይሰራል፡፡ በሙከራ ቆጠራው ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት ተባባሪ ነበረ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በሚከናወነው በዋናው ቆጠራ ወቅትም ይህ ተባባሪነት እንደሚደገም እንጠብቃለን፡፡
ቆጠራው በየአስር ዓመቱ የሚከናወን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በየመሃሉ የመረጃ አሰባሰብ ስራ በናሙና የሚከናወን በመሆኑ ለመረጃ አጥጋቢ አይደለም፡፡ በዚህ መካከል የሚያገለግል ሌላ መረጃ አይገኝም፡፡ በመሆኑም ተመራማሪዎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የመንግስት ፖሊሲ አውጪዎች በሙሉ ለአስር ዓመት የሚጠቀሙት በቀጣይ የሚገኘውን መረጃ መሰረት አድርገው ነው፡፡ በመሆኑም ህዝቡ ተባባሪ ሊሆን ይገባል፡፡
ከመጀመሪያው ህዝብና ቤት ቆጠራ ጀምሮ ተሳትፌያለሁ፡፡ ከዚህ በፊት መረጃ ይሰበሰብ የነበረው በወረቀት በመሆኑም ቆጠራውን ለማከናወን ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ለማጓጓዝም የትራንስፖርት ችግር ያጋጥማል። አሁን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ በመዋሉ ካርታው በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ ተሰርቷል፡፡ ቆጠራውም የሚከናወነው በቴክኖሊጂ በታገዘ በታብሌት በመሆኑም ጊዜን ይቆጥባል፣የመረጃ ጥራትን ይጠብቃል፣ በአጭር ጊዜ መረጃውን ሰብስቦ ለህዝብ ይፋ ለማድረግም ያመቻል፡፡
በመጀመሪያው ቆጠራ 23 ሺ ኪሎ ሜትር መንገድ የሚደረገው ጉዞ በበቅሎና በፈረስ ነበር፡፡ ድልድዮች ባለመኖራቸው ለመሻገርም አስቸጋሪ ነበር፡፡ በሁለተኛው ቆጠራ መንገዶች እየተሻሻሉ ሄደዋል፡፡ በአሁን ሰዓት 100 ሺ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የመንገድ መሰረተ ልማት በመኖሩ የቆጠራው ስራ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡
በመጀመሪያው ዙር ህዝብና ቤት ቆጠራ የቆጠራ ባለሙያዎቹ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል የሚገኙም ተሳትፈውበት ነበር፡፡ በአሁኑ ግን በርካታ የተማረ የሰው ሃይል በመኖሩ በቆጠራው የሚሳተፉት ከዲፕሎማ በላይ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ናቸው፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የትምህርት፣ የከተሞች ፣ የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነት ለስራው መልካም አጋጣሚ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡በመሆኑም ህብረተሰቡ የቆጠራውን ጥቅም እየተረዳ በመሆኑ ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡
የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይም የተሰበሰበውን መረጃ ተቆጣጣሪዎች አረጋግጠው ይልካሉ፡፡ መስክ ላይ በመሆን በኔት ወርክ የሚላከው መረጃም ወደ ሰርቨር ገብቶ ይከማቻል፡፡በፊት መረጃ የተሰራበት ወረቀት በተሽከርካሪ ተጭኖ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ይጓጓዝ ነበር፡፡ መረጃው ይፋ ይሆን የነበረውም በአራት ዓመታት፣ በሶስት እና ከዛም ተሻሽሎ በሁለት ዓመት ነበረ፡፡ በቀጣዩ ዓመት የሚከናወነው አራተኛው ዙር ህዝብና ቤት ቆጠራ በአንድ ዓመት ለህብረተሰቡ ይፋ እንዲሆን ታሳቢ ተደርጓል፡፡
ለማንኛውም ዓይነት ዕቅድ፣ ህብረተሰቡን ወደ እድገት ለመምራት ጥቅም ላይ የሚውለው የዚህ የቆጠራ ውጤት በመሆኑ ሁሉም ለስራው ድጋፍ ሰጪ ሆኖ ትግበራውን ለማሳካት ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ዘላለም ግዛው 

Published in ኢኮኖሚ

ዚምባቡዌ በታሪኳ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ትገኛለች። አገሪቱ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ቀን አንስቶ ባለፉት ሰላሳ ሰባት ዓመታት የመሯት አዛውንቱ ሮበርት ሙጋቤ የሌሉበትን ምርጫ በማድረግ ወደ ዴሞክራሲ ጎዳና እያመራች ትገኛለች። በአገሪቱ ህገ መንግስት መሰረትም የፕሬዚዳንትና የሁለቱን ምክር ቤቶች ምርጫ ለማከናወን ሽርጉዷን ከወዲሁ ጀምራለች።
የወቅቱ የተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በነሐሴ ወር አጋማሽ የቆይታ ጊዜያቸው ሳይጠናቀቅ አገሪቱ ምርጫውን የምታከናውን ይሆናል። የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ማናንጋዋም ይህንን ቀደም ብለው ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በነበራቸው ቆይታ ማሳወቃቸው ይታወሳል። በዚህም የተነሳ አገሪቱ ሐምሌ ላይ የምታካሂደው ምርጫ ከፍተኛ ትንቅንቅ እየታየበት እንደሚገኝ ተዘግቧል።
ባሳለፍነው 2017 በዘጠና አራት ዓመታቸው እንኳን የስልጣን ጥማታቸው ያልቆረጠላቸው ሮበርት ሙጋቤን በመፈንቅለ መንግስት አንስቶ ወደ ስልጣን የመጣው የአገሪቱ መንግስት በርካታ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በቀጣዩ ወር የሚደረገውን ምርጫ ከማስተካከል ጀምሮም ከድሃው ማህበረሰብ ተዘርፎ ከአገር የወጣውን የአገሪቱን ሀብት በማስመለስ ስራም ተጠምዶ ይገኛል። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ከዚምባቡዌ ህዝብ በባለስልጣኖች የተዘረፈ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በአውሮፓ ባንኮች ተሸሽጎ ይገኛል። የማናንጋዋ መንግስትም ስምንት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ዶላር ያህል እስካሁን ተመላሽ ማድረጉ ታውቋል። ከዚህ ቀደም በተጨባጭ ማስረጃዎች በማስደገፍ በሙጋቤ ዘመን ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ የነበሩ ባለስልጣኖች ከአገር ያሸሹትን ገንዘብ እንዲመልሱ የሦስት ወር ቀነ ገደብ ማስቀመጡ ይታወሳል። ይህም ለፕሬዚዳንት ማናንጋዋ ከፍተኛ አድናቆትን ያስገኘላቸው ሲሆን በቀጣይም በአገሪቱ ሙስናን ለማስቆም ተጨማሪ ስራ መስራት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
የሰባ አምስት ዓመቱ ማናንጋዋ የካቢኔ አባላቶቻቸው ሀብታቸውን የሚያሳውቁበት የተለየ የፀረ ሙስና ፍርድ ቤት ያቋቋሙ ሲሆን ያስቀመጡት ቀነ ገደብ እስኪጠናቀቅ ቀሪውን የተዘረፈ ገንዘብ ያላስረከቡ ባለስልጣኖች ወደ ወህኒ ቤት እንደሚወረወሩ አስጠንቅቀዋል። ፕሬዚዳንት ማናንጋዋ በጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ ሰፊ የፀረ ሙስና ትግል ከማድረጋቸው ባሻገር አገሪቱ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ ሃያ ሦስት ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩ እጩዎች እንዲሁም አንድ መቶ ሃያ ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊመዘገቡ ችለዋል።
ከአገሪቱ የስልጣን ለውጥ ጋር ተያይዞ ስሙ የማይጠፋው የአገሪቱ መከላከያ ሃይል ለምርጫው ስጋት እንደሆነ ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል። የቀድሞ የአገሪቱ መሪ የሮበርት ሙጋቤ ባለቤት ግሬስ ሙጋቤም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስማቸው እየተነሳ ይገኛል። ባለፈው ሰኔ አስራ ስድስት ቀን ስለ ምርጫው ማብራሪያ ለመስጠት በርካታ ዜጎች በተሰበሰቡበት መድረክ ላይ በደረሰው የቦንብ አደጋ የሁለት ዜጎች ህይወት የጠፋበትና ሃምሳ ያህሉ የቆሰሉበት አጋጣሚ የሚታወስ ነው። ለዚህም አደጋ በዋናነት እጃቸው እንዳለበት የተጠቀሱት የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ሲሆኑ ክስተቱ በውጭ ሃይሎች ጭምር ምርመራ እየተደረገበት ነው።
ግሬስ ሙጋቤ ባለቤታቸውን ተክተው ወደ ስልጣን ለመምጣት እንደሚፈልጉ በርካታ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ። ለዚህም በመጪው ወር መጨረሻ የሚካሄደውን ምርጫ እንደ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ማሰባቸው እየተነገረ ይገኛል። ከዚህ ቀደም እንደነበረው ተሞክሮም የአገሪቱ መከላከያ ሃይል ከግሬስ ሙጋቤ ጋር በገንዘብ ተደልሎ አንድ ነገር እንዳይፈጥር ስጋት ሆኗል።
አልጄዚራ የአገሪቱን ጋዜጣ ጠቅሶ ከሁለት ቀናት በፊት እንዳስነበበው የአገሪቱ መከላከያ ኮማንደር ይሄው ስጋት እንዳለ በማሰብ ለሰራዊቱ አባላት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ባለፈው ሳምንት የማናንጋዋ መንግስትን በመቃወም ከዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ራሳቸውን ያገለሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በግሬስ ሙጋቤ እየተመሩ አዲስ ፓርቲ ማቋቋማቸው ተሰምቷል። ይህም ምርጫውን ሚዛን ከማሳጣት ባለፈ የወታደራዊ ሃይሉ ሃላፊዎች የማናንጋዋ የቅርብ ወዳጅ በመሆናቸው የወቅቱን መሪ ጥቅም ለማስጠበቅ ይንቀሳቀሳሉ የሚል ስጋት ፈጥሯል። በሙጋቤ አመራር ወቅት በወታደራዊ ሃይሉ ስር የነበሩ መኮንኖች አሁን በማናንጋዋ አስተዳደር በካቢኔ ደረጃ መሾማቸውም ይታወሳል።
ከአንድ ወር በታች በቀረው ምርጫ የቱንም ያህል ስጋቶች ቢያንዣብቡም ከአምስት ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸው ታውቋል። ባሳለፍነው ወር የአገሪቱ ዋነኛ ተፎካካሪ ፓርቲ የሆነው ሙቭመንት ፎር ዴሞክራቲክ ቼንጅ ውስጥ የቀድሞ ከፍተኛ የፓርቲው አባላት በመጀመሪያው ምርጫ ከፓርቲው ውክልና እንዳላገኙ ይታወሳል። በምርጫው የፓርቲው ቁልፍ ሰው የሆኑትና የወቅቱ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኤልያስ ሙዲትሪ ውክልናው ከተነፈጋቸው መካከል አንዱ ናቸው። በምርጫው ዋነኛው የገዢው ፓርቲ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ኤም ዲሲ በአንጋፋዎቹ የፖለቲካ ሰዎች ሳይሆን በወጣቶች እንደሚተካ የአልጄዚራ ዘገባ ያመለክታል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሙዲትሪ ይህ ያልተዋጠላቸው ሲሆን እሳቸውን ከምርጫው ለማግለል ወይንም ከፖለቲካ ለማራቅ የተወጠነ ሴራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገሪቱ ገዢው ፓርቲ ዛኑ ፒ ኤፍ በበኩሉ አንጋፋው ሮበርት ሙጋቤ ባይኖሩም የሚያሰጋው ነገር እንደሌለ በመግለፅ ላይ ነው። በዚህም የዘጠና አራት ዓመቱ አዛውንት ሮበርት ሙጋቤ በሌሉበት ምርጫውን ማሸነፍ እንደሚችል እየተናገረ ነው።
ባለፈው የፈረንጆች 2017 ዓ.ም በሙጋቤ አስተዳደር ዙሪያ ወንጀለኞች ተከማችተዋል በሚል የአገሪቱ ጦር ጣልቃ ገብቶ አንጋፋውን መሪ ለሰላሳ ሰባት ዓመታት ከመሩበት ዙፋን እንዲነሱ ማድረጉ ይታወሳል። ሮበርት ሙጋቤ በጦሩ ግፊት ከሐራሬው ቤተመንግስት ቢወጡም አሁንም ድረስ የደጋፊያቸው ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ይነገራል። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ዛኑ ፒ ኤፍ ቀጣዩን ምርጫ ከሙጋቤ ውጪ እንዴት ማሸነፍ ይቻለዋል? የሚሉ በርካታ ናቸው።
የሙጋቤ ድጋፍ እንደተቸረው የሚነገረውና በቀድሞው የአገሪቱ ብርጋዴር አንብሩሲ ሙቲንሂር የተመሰረተው ኒው ፓትሪዮቲክ ፍሮንት ፓርቲ በምርጫው ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። ሙቲንሂር ከቀድሞ ፓርቲያቸው ዛኑ ፒ ኤፍ ሙጋቤ ከስልጣን ሲወገዱ ተቃውመው የለቀቁ ሰው ናቸው። በዚህም ሙጋቤ አሁን ላይ ድጋፋቸውን ሊሰጧቸው ችለዋል። ይህም ሙቲንሂር በዚምባቡዌ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው አድርጓቸዋል። እኤአ በ1970ዎቹ በአገሪቱ የነጮችን የበላይነት ለመግታት በተደረገው ትግልም የነበራቸው አስተዋፅኦ ተቀባይነታቸውን ያጎላዋል። ይህ ፓርቲ ወደ ስልጣን ይመጣል ተብሎ ባይጠበቅም ዛኑ ፒ ኤፍ በከተሞች አካባቢ በሚያገኘው ድምፅ ይፈታተነዋል ተብሎ ተገምቷል።
ምርጫው በገዢው ፓርቲ ዛኑ ፒ ኤፍና በኤም ዲሲ መካከል ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት መሆኑን በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ከወዲሁ ግምታቸውን እያስቀመጡ ይገኛሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ከምርጫው ጋር እየተነሳ የሚገኘው ዝቅጠት ውስጥ ያለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ነው። ዚምባቡዌ በሙስና ምክንያት በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደምትመዘበር መረጃዎች ያሳያሉ። ይህን ችግር መቅረፍም የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ዋነኛ ድምፅ የማግኛ ዘዴ እንደሚሆን ተነግሯል።
የሙስና ወንጀል የሚፈጽሙት የመንግስት ባለስልጣናትና የፖሊስ አባላት መሆናቸውን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም ሪፖርት ማመላከቱ ይታወቃል።
በሙጋቤ አስተዳደር ዘመን ፊት ተነስቶ የነበረው የአውሮፓ ህብረት ከአስራ ስድስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጫውን ለመታዘብ ልዑካን እንደሚልክ መገለፁም ይታወሳል። የአውሮፓ ህብረትና የዚምባቡዌ መንግስትም ምርጫውን በመታዘብ ዙሪያ ባለፈው ወር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወቃል። በወቅቱም የአውሮፓ ህብረት ከዚምባቡዌ መንግስት በቀረበለት ጥሪ መሰረት ምርጫውን እንደሚታዘብ የህብረቱ የዚምባቡዌ ልዑክ መሪ ፊሊፕ አንዲ ተናግረዋል። የአውሮፓ ህብረት ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ግልፅ ምርጫ ለማካሄድ እንደሚያግዝም ገልፀዋል።

ቦጋለ አበበ  

Published in ዓለም አቀፍ
Saturday, 07 July 2018 19:11

«ይደገም... ይደገም... »

በአንድ አባወራ ቤት ነው። ሴት፣ ወንድ፣ ወጣት አዋቂ ሁሉም ተሰብስበዋል። በሳሎኑ በርከት ያሉ ሰዎች እንዳሉ ከሚሰማው ድምጽ ለመገመት አይከብድም። በየመሀሉ ደግሞ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ይደመጣል። እኔ መቼም ኳስ ለማየት ብዬ ጊዜ አላጠፋም። ወይ ደግሞ የኳስ ፍቅሩ የለኝም ብል ይሻላል። አሁን ደግሞ የዓለም ዋንጫ እየተካሄደ ያለበት ወቅት በመሆኑ ሁሉም ሰው ፊቱን ወደ ቴሌቪዥን መስኮት መልሷል። የሰዎቹ ሰብሰብ ማለት ከዚህ የሚያልፍ እንደማይሆን ገምቻለሁ። ገባ ብዬ ሰላም ብላቸው «ሰላምታ የእግዜር ምሳና እራት አይደል» ብዬ ለሰላምታ ወደ ሳሎኑ ዘለቅኩ።
በቴሌቪዥኑ ላይ የሚታየው የገመትኩት የእግር ኳስ ሳይሆን በባህርዳር ከተማ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ትዕይንት ነው። ይሄ ፕሮግራም ጠዋት በቀጥታ ስርጭት የተላለፈ ቢሆንም በድጋሚ የሚቀርበውን ፕሮግራም ሁሉም በተመስጦ ያደምጣሉ። ኳስ የሚተላለፍበት ሰዓት እስኪደርስ ይሆን?
ብዙ ጊዜ ከምሰማቸው አስተያየቶች ተነስቼ ግን አንድ ነገር እንዳስብ አደረገኝ። መሪዎች ሲናገሩ ከአንዳንዶች በስተቀር በአብዛኛው (ጥናት ላይ የተመሰረተ ባይሆንም) ይሄንን ፖለቲካችሁን የሚሉ ሁሉ ዛሬ ኳስ ጨዋታ ተመልካች እስኪመስሉ ድረስ ከቴሌቪዥኑ ፊት ለፊት መፋጠጣቸው አስደነቀኝ።
«ቃል ይተክላል - ቃል ይነቅላል፡፡ ቃል ጉልበት አለው፡፡ ትውልድ ይፈጥራል - ትውልድ ያጠፋል፡፡
ፍቅር ያናኛል - ጥላቻን ይዘራል፡፡ በቃል ውስጥ ብዙ መማር ብቻ ሳይሆን ሀገር መስራትም ይቻላል - ኢትዮጵያ የተሰራችውም የፈረሰችውም በቃል ስለሆነ፡፡ ቃል ካልወጣ በአዕምሮ ቢብሰለሰል ብቻውን ሃሳቡ የሚታወቅ ሊሆን አይችልም» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተናገሩት አእምሮዬ ላይ ደወለ። ለካንስ ሕዝብ የተራበው ፍቅርና አንድነት የሚሰብክ ቃል የሚተነፍስ መሪ ነው ስል ለራሴው ምላሽ ቸርኩት። የእነሱን ስሜት ባላውቅም።
ግን እኮ ይሄንን መስበክ ያለባቸው የሃይማኖት አባቶች አይደሉ? የሃይማኖት አባቶች በየእምነታቸውና በየእምነት ተቋሞቻቸው የሀገርን አንድነት፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ይቅር ባይነትን ...መስበክ አለባቸው። የየሃይማኖቶች አስተምህሮትም ይሄንን ያዛል። ግን ሕዝብ በበቂ ሁኔታ ስለፍቅር አልተነገረውም፣ ስለ አንድነት አልተሰበከም፣ ስለ ሰላም አልተዘመረለትም። ይሄ ቢሆን ኖሮ ዛሬ እንደ አዲስ ከመሪያችን ስለ አገር አንድነት፣ ስለ ፍቅር... ተሰበከ ተብሎ የገዘፈው አድናቆት ባልተቸረ። አንድ የሃይማኖት አባት ያሉትን እዚህ ላይ ባስታውስ ይገባል። «ዶክተር አብይ የሰራልን እኛ የሃይማኖት አባቶች መስራት ያለብንን ሥራ ነው» በማለት ሲጸጸቱና ተግባሩን ሲያደንቁ ሰምቻለሁ። አዎ! ለሰላም ሁሉም ሰው ቢነጋገር፣ ቢወያይ ጥሩ ነው። በሃይማኖት አባቶች፣ በጎሳ መሪዎች፣ በአገር ሽማግሌዎች፣ በታዋቂ ሰዎች...ሲሆን ደግሞ ተሰሚነቱ ከፍ ይላል። የአሁኑም ውጤት የዚሁ መነሻ ይመስለኛል።
አሁንም በጥሞና የተመልካቹን ስሜት እያየሁ ነው። በየንግግሮቹ መካከል ያጨበጭባሉ። እርስ በራስ ጎን ለጎን በጉዳዩ ላይ ይወያያሉ። ትክክል በሚሉት ላይ ይስማማሉ። ይሄማ አይሆንም የሚል ሃሳብ የሚያነሳም አልጠፋም። አንዳንዶቹ ለማስረዳት ይሞክራሉ፤ ሌላው ደግሞ «አንተ ገና ነህ በፖለቲካው አልበሰልክም» ሲሉ በጥሞና ማዳመጥና ማወቅ እንደሚቀረው ይገልፃሉ። በንግግሮቹ የሚተላለፉ መልዕክቶች ሰምና ወርቅ አላቸው?
ግን የእስካሁኑ መሪዎቹ (ንግግሩን ያደረጉትን የክልሉን ፕሬዚዳንትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን) የት ነበሩ?። አሁን ይሄንን ሁሉ ንሰሐ የሚገቡት?ይጠይቃሉ። ሌላው ደግሞ «በቃ ተጸጽተዋል፣ ከሰሩት ስህተት ተምረዋል። ደግሞ አጋዥ አገኙ፣ አሁን ስላለፈው ሳይሆን ወደፊት እንዳይሆን በምንፈልገው ላይ ማተኮር ነው። ጊዜው የይቅርታ ነው!» ሲል ይመልሳል። ብቻ የሁሉንም አስተያየት ስመለከት ሀገሪቱ በለውጥ ላይ መሆኗን፣ ይቅርታ፣ አንድነት ቦታ ማግኘታቸውን ያመለክታል። በያገባኛል መንፈስ ሁሉም ለአገር አንድነት መነሳሳቱን መገንዘብ ይቻላል።
በባህርዳር በተካሄደው «ዴሞክራሲን እናጎልብት ለውጡን እናበረታታ» ሰላማዊ ሰልፍ ላይ አንድ የታዘብኩት ነገር ነበርና አሁንም በድጋሜ እንዳስታውሰው አድርጎኛል። ይሄ ቃል «ይደገም...ይደገም...» የሚለው ነው። በቴሌቪዥን መስኮት የሚከታተለውም ይሄንን ድምጽ ማውጣት እና ማሰማት ባይችልም ፊት ለፊቱ የሚያደምጠውን አድምጦ ስሜቱን በጭብጨባ ገልጿል። በወቅቱ ጆሬዬን ማመን አልቻልኩም። ከአካባቢው ከሚሰማው ተጨማሪ ድምጽ ጋር ታክሎ የሰማሁት ነገር ትክክል ለመሆኑ በደንብ ለማጣራት ሳስብ ንግግር አድራጊው የክልሉ ፕሬዚዳንት ያቋረጡትን ለመቀጠል «እደግመዋለሁ» ሲሉ ያ ለጆሬዬ ያጠራጠረው ቃል ትክክል መሆኑን አረጋገጥኩ። የማየው፣ የምሰማውና የማደምጠው ነገሮችን በጥሞና እንድከታተል ደግሞም መለስ ብዬ ያለፉትን አስታወስኩ።
በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች የማያቸው ጽሑፎችም እንዲሁ እንዳስታውስ አድርጎኛል። በተለይ «ኢቲቪን አንመለከትም። የሚያቀርቡት ዘገባ የተዛባ ነው፣... የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን ላለማየት ቻናል የሚቀይሩ፣ ዝጉልኝ» የሚሉም አጋጥመውኝ ያውቃሉ። አሁን ደግሞ ወረትም ይሁን እውነት በደንብ ባልገባኝ ሁኔታ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን መከታተል ትልቅ ጉዳያቸው ሆኗል። ከዚያም አልፎ የመንግሥት ባለሥልጣናት ንግግር ሲያደርጉ «ይደገም...ይደገም...» ብሎ እስከማስደገም ከተደረሰ እውነትም ለመግባባት፣ ለፍቅር አንድ እርምጃ ጀምረናል ማለት ነው።
ግን እኮ ይሄ እውነት ሌላ ከጀርባው እንዳይኖረው አድርጎ ማሰብም ይገባል። «ይደገም!» የሚባሉት ሃሳቦች አንድነትን የሚያጠነክሩ፣ ፍቅርን የሚጨምሩ፣ ይቅር ባይነትን የሚሰብኩ ናቸው? ወይንስ ሌላ? ይሄ መታየት አለበት። ሊጤን ይገባዋል። የጠላቴ ጠላት... የምንል ከሆነ አሁንም ይቅር ባይነቱ የይስሙላ ይሆናል። አንድ ብሔር ላይ እጅ የምንጠቁም ከሆነ ስህተት ነው። እንዲደገም የምንፈልገው ቁስል ቀስቃሽ፣ በቀል አነሳሽ ከሆነ ጠያፍ ነው። አሁን የተነሳንበትን የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነትንና የመደመር አዲስ ተስፋ የሚያጨልም ነው።
አንድ ሆነን አገራችንን ወደ ዕድገት ጎዳና እንምራ፣ ሰላማችንን እንጠብቅ፣ እናረጋግጥ፣ ቂም በቀል እንዳይኖር እያልን እንደሆነ በፈጣሪም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነው። በሕዝቡም የሚኖረው ተቀባይነት የሰፋ ይሆናል።
በአገራችን ሥርዓት በተቀያየረ ቁጥር፣ የሥልጣንና የባለሥልጣን መለዋወጥ በተካሄደ ቁጥር የምናነሳቸው የተሰሩትን መልካም ነገሮች ሳይሆን የከፋውን ብቻ ነው። ያገኘናቸውን ጥሩ ነገሮች ሳይሆን ያጣናቸውን ብቻ ነው። ያለፉትን አንኳሶ መጪውን አወድሶ መቀጠል የተለመደ ጥሩ ያልሆነ ባህሪ ነው። እንኳንስ አገርን በሚያክል ግዙፍ ነገር ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳን ሁሉንም እኩል ማርካት አይቻልም። ሁሉም የቤተሰብ አባላት ተመሳሳይ ባህሪ የላቸውም። የሁሉም ፍላጎትና አስተሳሰብ አንድ ሊሆን አይችልም። ከአንድ መልካም ቤተሰብ መካከል ለጎዳና ተዳዳሪነት የሚዳረግ ይፈጠራል። ወይ ደግሞ ሌባ ይወጣል። ከውጪ ብቻ ሳይሆን ከቤቱ ከቤተሰቡ የሚሰርቅ። አገር ሲሆን ደግሞ ይሄን በእጅጉ አስፍቶ ማየትን ይጠይቃል።
ከአንድ ብሔር በመጥፎ ተግባሩ የተጠረጠረ ወይም የተያዘ ሰው ካለ ይሄ መጥፎ ተግባር የዚያ ብሔር መገለጫ ተደርጎ መወሰድ የለበት። ይሄ ሲባል ግን አጥፊ አይጠየቅ፣ ጥፋት አይነሳ ለማለት አይደለም። ሁሉም አግባብ ይኑረው። ጥፋቱ የጅምላ አይደረግ፤ ምክንያቱም በየትኛውም ብሔር ሙሰኛ፣ ተለጣፊ፣ ወቅትን ጠባቂ እና ለግል ጥቅም የሚሯሯጥ ነበር። አሁንም አለ፡፡ ወደፊትም ይኖራል። ይሄ የሁሉም ባይሆንም የጥቂት ሰዎች ባህሪ ነው። በአቋራጭ ለመበልጸግ መሯሯጥ የነበረ ነው። አሁንም ለዚህ የተዘጋጀ አይኖሩም ብሎ መደምደም አይቻልም። አይደመደምም።
ነገር ግን ትልቁ መሆን ያለበት ካለፈው ጥፋትና ስህተት መማር ነው። እንዳይደገም መስራት ነው። አንድ ሆኖ ተደምሮ ወደፊት ለመገስገስ መጣጣር ነው። የተሳሳቱ መንገዶችን ማስተካከል ደግሞ ጊዜው የሚፈልገው ነው። አንድ እንሁን የሚያለያዩንን እናጥብብ፤ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያን ለአስተዳደር ያመች ዘንድ በክልል የከፋፈለውን የፌዴራል ሥርዓት ሕገ መንግሥት እስከማሻሻል እንሂድ በሚባልበት ወቅት ሌላው እንዲሸማቀቅ የሚያደርጉ መጥፎ ቃላቶችን መንዛት የምናስበውን አንድነት፣ ሰላም፣ ፍቅር እና መተሳሰብ ሳይሆን ልዩነትን የሚያሰፋ ይሆናል።
አሁንም በለውጥ ሂደቱ ሁሉም ሰው ለውጡን ይደግፋል፤ በለውጥ እርምጃ እኩል ይሰለፋል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ለውጥ የሚጉረብጠው፣ እዚህም እዚያም ሰላም እንዲደፈርስ የሚሰራ የሚያልም አይኖርም ብሎ ማቀንቀን የዋህነት ነው። ከምንም በላይ ግን ፍቅርና አንድነት አሸናፊ መሆኑን ሁሉም መረዳት አለበት። ይሄ የምናስበው ብቻ ሳይሆን ካሰብነውም በላይ የሆነች አገር መፍጠር የሚያስችለን ይሆናል። ለዚህ ግን ፍቅር፣ አንድነት፣ ሰላም፣ ይቅር ባይነት ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል። ይደገም... ይደገም...ለፍቅር ይሁን። ለአንድነታችን ይሁን! በይቅርባይነት መንፈስ እንየው።

አዶኒስ (ከሲኤምሲ)

Published in አጀንዳ

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2011 በጀት ዓመት 346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት ትናንት አጽድቋል። ከዚህም አጠቃላይ በጀቱ 64 በመቶ የሚሆነው ለድህነት ተኮር የልማት ሥራዎች የተመደበ ሲሆን ከበጀቱ 55 በመቶ የሚሆነው ለካፒታል በጀት የተያዘ ነው፡፡ ከአጠቃይ በጀቱ 45 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለመንግሥት ሥራ ማስኬጃ መደበኛ በጀት የሚውል ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳስረዱት ከፍተኛው በጀት የተመደበው ድህነት ቅነሳ ላይ ነው። ድህነት ቅነሳ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የተደረገው ሁሉም ዜጋ የሀገሪቱን ሀብት እኩል ተጠቃሚና ተካፋይ የመሆን መብት ስላለውና ይሄንንም ለማረጋገጥ ነው። ይሄንን መብቱን ለመጠቀም ደግሞ ትልቁ በጀት ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለመንገድ፣ ለውሃ እና ለመሳሰሉት ሁሉንም ተደራሽ ለሚያደርጉ የመሠረተ ልማት ጉዳዮች እንዲውል ተደርጓል።
የአፍሪካ አገራት በአማካይ ድህነት ቅነሳ ለሆኑ ተግባራት የሚመድቡት በጀት40 በመቶ ሲሆን ከሰሃራ በታች ያሉት አፍሪካ አገራት ደግሞ 35 በመቶ ነው። ኢትዮጵያ አሁን ለዘርፉ የመደበችው የበጀቷን 64 በመቶ ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ የተሻለ ነው። ይሄ የሚያሳየው ዜጎችን እኩል ተጠቃሚ በሚያደርጉና የዜጎች መብት በሆኑ ዘርፎች ላይ መንግሥት የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ በጀቱም ትልቅ መሆኑን ነው።
ለ2011 በጀት ዓመት የጸደቀው ይሄ በጀት ከ2010 በጀት ዓመት ከነበረው 320 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ 26ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ነው። በበጀት ዓመቱ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ተግቶ መስራት እንጂ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደማይኖሩም ተረጋግጧል። ይህ የሆነው ደግሞ አሁን በግንባታ ያሉ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ በመሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መጀመር አዋጭ ባለመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም በዋናነት በድህነት ቅነሳ ላይ ያተኮረውን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል ውጤታማ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡
ከበጀቱ 39.1 በመቶ ለክልሎች ድጋፍ የሚውል ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የታዳጊ ክልሎችን ልዩ ፍላጎት ለመሙላት የሚያስችል ተጨማሪ ግማሽ ቢሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል። ይህም ያለውን ሀብት በማሸጋሸግ የተቀራረበ ዕድገት እንዲመጣ እንዲሁም ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት ፍላጎት ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ያለመ ነው።
ሀገሪቱ ያላትን የኢኮኖሚ አቅም ያገናዘበ ትልቅ በጀት ነው ያጸደቀችው። ዋናውና ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ግን ይሄን በጀት በተገቢው መንገድ ለታለመለት አገልግሎት ማዋሉ ላይ ነው። በጀቱ ሳይባክን በትክክል ለታለመለት አላማ ማዋል ይገባል። እያንዳንዱ ሠራተኛና ኃላፊ በኃላፊነት ስሜት በጀቱ ለታለመለት ዓላማ መዋሉንም ጎን ለጎን መከታተል አለበት።
እያንዳንዱ በጀት በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ከሁሉም በፊት በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች፣ አመራሮች፣ ሚኒስትሮችና ኮሚሽነሮች ሠራተኞቻቸውን ሰብስበው በጀቱ ለምን እንደተመደበና በምን አግባብ ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት ግልጽ በሆነ መልኩ ማስረዳት፤ ሁሉም በባለቤትነት መንፈስ ኃላፊነት እንዲሰማው ማድረግ ይገባል።
«ጠብታ ውሃ ጋን ይሞላል» የሚለው የአበው ምሳሌያዊ አነጋገር እዚህ ላይ ማንሳት ይገባል። እያንዳንዱ ሠራተኛ የተመደበለትን በጀት በአግባቡ ለተገቢው ሥራ ማዋል ከቻለ፣ በአግባቡ ሥራ ላይ የማይውል ከሆነም ለምን ብሎ መጠየቅ እና በባለቤትነት ስሜት መስራት ከተቻለ የምንጠብቀውንና የምንሻውን ዕድገትና ልማት ማምጣት የሚያዳግት አይሆንም። ለዚህ ደግሞ ግልጽ ውይይት ማድረግ ከሁሉም በላይ ወሳኝ ነው።
የተመደበውን በጀት በአግባቡ መጠቀም፣ ወጪ ለመቀነስ ጥረት ማድረግ፣ ወሳኝ ላልሆኑ ሥራዎች የሚደረግን የውጭ አገር ጉዞ መቀነስ፣ አላግባብ የሚባክን የመንግሥት ተቋማት ነዳጅን መቆጣጠር፣ በስልክ፣ በመብራት እና ውሃ የሚወጣ ወጪን መቆጣጠር፣ በውሎ አበል፣ በግዢና በሌሎችም ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሀብት ብክነትን የሚያስከትል አለመሆኑን መከታተልና መቆጣጠር ወሳኝ ነው።
በጀቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል መንግሥትና ሕዝብ በተለይ ደግሞ በኃላፊነት ቦታ ያሉ አስፈጻሚዎች ከሌብነት በጸዳ መልኩ ሥራቸውን ሊሰሩና ሊመሩ ይገባል፡፡ በሌብነት የሚሳተፉ ከሆነ ግን ድህነት ለመቀነስ የሚደረገው የመንግሥትና የሕዝብ ጥረት በማደናቀፋቸው ፈጣን የሆነ የሕግ ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡ ምክንያቱም የሕዝብንና የሀገርን ድህነት ለመቀነስ ታሳቢ ተደርጎ የጸደቀ በጀት ለታለመለት አላማ ማዋል ይገባልና፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።