Items filtered by date: Sunday, 08 July 2018

ቀኑ ግንቦት 9 እኩለ ሌሊት ላይ ነበር። እንደወትሮው በሰላም ውሎ የሚያድረው የጃንሜዳ ግቢ ውስጥ እንግዳ ነገር ተከስቷል። ቀን ሲደክም የዋለ ሰውነት አረፍ በሚልበት እኩለ ሌሊት የተፈጠረው «ድንገቴ» የእሳት አደጋ ነበር። በግቢው ውስጥ ከሚገኙ ህንፃዎች አንዱ በሆነው የሰው ኃይል አስተዳደር የሥራ ክፍል የተነሳው አደጋ ቀስ በቀስ እየተዛመተ የህንፃው ክፍሎች ላይ ጉዳት ማድረስ ችሏል። 

በቃጠሎው ጉዳት ከደረሰባቸው ክፍሎች መካከል በማዕከሉ የሚገኘው የስፖርት ሙዚየም ተጠቃሽ ነው። ሙዚየሙ በተለያየ ዘመናት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ታሪካዊ ቅርሶች የያዘ ነበር። ለዝግጅት ክፍላችን መረጃ ያደረሱን አካላት በሙዚየሙ ውስጥ የሚገኙት ቅርሶች በቃጠሎው መውደማቸውን ይናገራሉ። ሆኖም ግን የጃንሜዳ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መኮንን ጤናው ሙዚየሙ ላይ ቃጠሎ ቢደርስም በውስጡ ያሉት ቅርሶች ግን ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ይናገራሉ።
የዝግጅት ክፍላችን በአካል በማዕከሉ ተገኝቶ ምልከታ ለማድረግ በአደረገው ጥረት ሥራ አስኪያጁን በቀጠሮው መሰረት ለማግኘት ተቸግሯል። አቶ መኮንን «ስብሰባ ላይ ነኝ፤ በግል ጉዳይ ከከተማ ውጭ ነኝ» በማለት የሚያስቀምጡት ምክንያት ሙዚየሙ ምን ዓይነት ጉዳት እንደደረሰበት በዝርዝር በአካል ተገኝቶ ለመመልከት እንዳይቻል እንቅፋት ሆኗል። ሙዚየሙ ተቆልፏል። ሌላ ይህን ጉዳይ ማስተባበር የሚችል ሰው በኃላፊው አልተወከለም። ሆኖም ግን በስልክ በሰጡን ምላሽ ስለቃጠሎው እና ስለደረሰው ጉዳት የሚከተለውን ነግረውናል።
«ከእሳት አደጋው ጋር ተያይዞ በቅርሶቹ ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም። መነሻው ምን እንደሆነ በትክክል መናገር አልችልም። ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ይገኛል» ያሉት ሥራአስኪያጁ ውጤቱ እንዳልደረሳቸው ይናገራሉ። በ ሙዚየሙ የፎቶ መዛግብት ከአጼ ኃይለስላሴ ጀምሮ እስከ ደርግ ዘመነ መንግሥት በተለያዩ ክፍለ ሀገሮች የተካሄዱ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮችን፣ የሽልማት አሰጣጥ እና መሰል ትዕይንቶችን እንደሚገኙም ገልፀዋል። እሳቱ የተነሳው በግቢ ውስጥ ከሚገኘው የሰው ኃይል ቢሮ እንደሆነም ማረጋገጫ ሰጥተዋል። የአስተዳደሩ እና የጸሐፊው ቢሮውን በማዳረስ ወደ ሙዚየሙ እና ፋይናንስ ሲሄድ እሳቱ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ይናገራሉ።
ቃጠሎው ከደረሰ በኋላ ምን ዓይነት እርምጃ ወሰዳችሁ ለሚለው ጥያቄ ሥራ አስኪያጁ በሰጡን ምላሽ «በመጀመሪያ ፖሊስ ምርመራውን ማድረግ ስለነበረበት በስፍራው እንቅስቃሴ ተከልክሎ ነበር» በማለት ፖሊስ በምርመራው የደረሰውን የጉዳት ዓይነት መዝግቧል በማለት ገልፀዋል። ከዚያም ሙዚየሙ ውስጥ ያሉትን ዕቃዎች ኮሚቴ በማቋቋም ቦታ መስጠታቸውን ይናገራሉ።
«በ ሙዚየሙ ውስጥ በብዛት ዋንጫዎች ይገኛሉ» የሚሉት ሥራ አስኪያጁ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድንን የሚያሳይ ምስል መኖሩን ገልፀዋል። በሸዋ ክፍለ አገር ይደረጉ የነበሩ የፖርት መረጃዎች፣ እንዲሁም የአፄ ኃይለስላሴ መቀመጫዎች መኖራቸውን ጠቁመው በእነርሱ ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ገልፀዋል። ሌሊት የደረሰው ቃጠሎ በብዛት የሙዚየሙ ጣራ ላይ መከሰቱንም ይናገራሉ። ኮርኒሱ እና እንጨቱ መቃጠሉንም አስረድተዋል። ጨረታ ወጥቶ ሙሉ ጥገና ከመካሄዱ በፊት ሙዚየሙ የባሰ ጉዳት እንዳይደርስበት ጣራ የማልበስ ሥራ እንደተሰራለት ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ከዚህ ቀደም በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶች ያሉበትን ሁኔታ ለመለየት ባደረገው ጥናት የጃን ሜዳ የስፖርት ሙዚየሙ አካትቶ ነበር። በጥናቱ ላይም ሙዚየሙ ውስጥ የሚገኙት ቅርሶች አቀማመጥ ለጉዳት የሚያጋልጥ መሆኑን የሚጠቁም መረጃዎችን ይፋ አድርጓል። የእሳት አደጋ ቢከሰት በቀላሉ ቅርሶቹ ጉዳት ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉም ጥቆማ ሰጥቶ ነበር። ስለዚህ ዝርዝር ጥናት ሥራ አስኪያጁ ያውቁ እንደነበር የዝግጅት ክፍላችን ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ጥናቱ ስለመደረጉ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልፀውልናል። በጥናቱ ቀድሞ በአስቀመጠው ግምት መሰረት አደጋው በሙዚየሙ ላይ ደርሷል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ተናግረዋል።
የዝግጅት ክፍላችን ጥናቱን ከሰራው የአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ በቀድሞው የሥራ ክፍሉ የቱሪዝም ማርኬቲንግ ጥናት ባለሙያ የሆነውን አቶ ፍፁም ፍቅሩ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር። የጥናቱን ዝርዝር ውጤቶች፣ ሙዚየሙ ለቅርስነት የሚያበቁ ታሪካዊ የስፖርት ቁሶችን በተመለከተ እንዲሁም በወቅቱ በስፍራው የነበሩትን አስጊ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ማብራሪያም ሰጥቶናል።
የመጀመሪያው የስፖርት ሙዚየሙ
የጃንሜዳ ስፖርት ሙዚየም በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ በጃንሜዳ የስፖርት ማዕከል ውስጥ ይገኛል፡፡ እንደሚታወቀው ጃንሜዳ በከተማዋ የሚገኝ ሰፊ ሜዳ ሲሆን፣ ለሃይማኖታዊ ሥርዓትና ለስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ በማገልገል ላይ ይገኛል። «ጃንሜዳ» የሚለው ስያሜ «ጃንሆይ ሜዳ» ከሚለው ስም የመጣ መሆኑን የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት በድሮ ጃንሆይ ሜዳ በአሁኑ ጃንሜዳ በሚባለው ስፍራ ድንኳን በማስተከል ፍርድ ይሰጡበት ነበር፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሥነሥርዓት የሚከበረው የጥምቀት በዓል በዚሁ በጃንሜዳ የሚከበር ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ብዙም የማይታወቅ የስፖርት ሙዚየም በውስጡ ይዞ ይገኛል፡፡

የባህል እና ቱሪዝም ቢሮው ጥናት እንደሚያመ ለክተው የጃንሜዳ ስፖርት ሙዚየም ህንጻ መቼ እንደተገነባ በውል የሚታወቅ ነገር የለም። አሊያም ባግባቡ የተሰነደ መረጃ እና ስለ ጉዳዩ የሚያውቅ ባለሙያ አልተገኘም፡፡ የሙዚየሙ ህንጻ የሚገኘው በህንጻው አንደኛው ፎቅ ላይ ሲሆን፣ ቀሪው የህንጻ ክፍል የስፖርት ማዕከሉ ለተለያዩ ሥራዎች ይጠቀምበታል፡፡ የሙዚየሙ ህንጻ አሰራር ቆየት ያለ እና ዕድሜ ጠገብ መሆኑ ከህንጻው ዲዛይንና አሰራር በማየት መረዳት አያዳግትም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወደ ውስጡ ሊዘልቁ ሲል ፊት ለፊት የአፄ ኃይለስላሴ ምስል የተቀረጸበት መዳብ ይታያል ይህም ሙዚየሙ በንጉሱ ዘመነ መንግሥት እንደተመሰረተ ፍንጭ ይሰጣል፡፡
በ ሙዚየሙ ስላሉ ቅርሶች
በጃንሜዳ የስፖርት ሙዚየሙ ውስጥ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች መኖራቸውን ጥናቱ ያመለክታል። እርሳቸው እንደሚናገሩትም በሚውዜሙ ውስጥ የአፄ ኃይለስላሴ የግል መጠቀሚያ የነበሩ ለምሰሌ የቁም መስታወት ፣ አምፑል ፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ የስልክ ቀፎ እንዲሁም ካዝና ፤ የአሎሎ መወርወሪያ፣ የገበጣ መጫወቻ፣ የገና መጫወቻ፣ ከእንግሊዝ መንግሥት ለአፄ ኃይለስላሴ የተበረከተ ሻምላ፣ ከብርና ከነሃስ የተዘጋጁ ስጦታዎች፣ ከተለያዩ ሰዎች ለስፖርተኞቻችን የተበረከቱ ጋሻዎች፣ ሜዳሊያዎች ፣ ዋንጫዎች፣ የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ምስል ያረፈበት መዳብ የተሰራ ምስል፣ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ባደረገቻቸው ውድድሮች የተሰጡ አርማዎች ይገኛሉ።
የሙዚየሙን ውስጣዊ ክፍል በግምት 6 በ 4 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡም ምንም ዓይነት ክፍልፋይ የሌለው አንድ ሙሉ ወጥ ነው፡፡ የሙዚየሙ ግድግዳ እና ወለል በድንጋይ እና በሲሚንቶ የተሰራ ሲሆን ኮርኒሱ ነጭ ቀለም የተቀባና ከአቡጀዴ በቅርብ የተሰራ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ጥናት አድራጊው ህንፃው ቃጠሎ ደርሶበት ለጉዳት ከመጋለጡ በፊት የሙዚየሙን ኃላፊዎች ጠይቆ እንደተረዳው ከዚህ ቀደም ህንጻው ይህ ነው የተባለ ዕድሳት ተደርጎለት አያውቅም። ይህን ጥናት በሚያዘጋጅበት ወቅት በነበረው ምልከታ እንደተረዳው የህንጻው ኮርኒስ ያረጀ እና የፈራረሰ ሲሆን በኮርኒሱ በኩል የሚመጡ አቧራ በቅርሱ ላይ ጉዳት እያደረሱ እንደሚገኙ ነበር።
ጥናት አድራጊው አቶ ፍፁም የሚናገረው አጠቃላይ የሙዚየሙ አቀማመጥ እና አሰራር ሆነ ተብሎ ለሙዚየም እንዳልተሰራ ከዳሰሳው መረዳቱን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እሳት አደጋ ድንገት ቢከሰት የእሳት ማጥፊያ በሙዚየም ውስጥ አለመኖሩን ታዝቧል (ይህ ጥናት ከተሰራ ከጥር 2009ዓ.ም በኋላ በግንቦት 9 2010ዓ.ም የእሳት ቃጠሎ አደጋ መድረሱን ልብ ይሏል)። ከዚህ በተጨማሪም ባለሙያው ጥናቱን በሚያደርጉበት ወቅት የሙዚየሙ ህንጻ አገልግሎት መስጠት አቁሞ ተዘግቶ ነበር። አስፈላጊ ግብዓቶች እና የሰው ኃይል አሟልቶ ወደ ሥራ ለመግባት የሚደረገው እንቅስቃሴ በጣም ደካማ እንደነበርም ታዝቧል። አቶ ፍፁም «ለሙዚየሙ የተሰጠው ግምትም በሚያሳዝን መልኩ በጣም አነስተኛ ነው» በማለት ትኩረት እንደሚያሻው በጥናቱ ላይ አመላክቶ ነበር።
«ሙዚየሙ በራሱ የሚገኝበት ታሪካዊ እና ታዋቂ ሥፍራ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ የሆነ የፕሮሞሽን ሥራ ቢሰራ ተደራሽነቱ ከፍተኛ ይሆን ነበር» በማለት በጥናቱ ላይ ምክረ ሃሳብ የሚያስቀምጠው አቶ ፍፁም፤ ሙዚየሙ እራሱን በማስተዋወቅ በኩል ምንም የሰራው ሥራ አለመኖሩን ይናገራል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የጃንሜዳ ስፖርት ሙዚየም ህንጻ አሰራር በራሱ የራሱ የሆነ የኪነ ህንጻ አሻራ ያረፈበት ከመሆኑ አንጻር ለሙዚየሙ አገልግሎት ለመስጠት አመቺ እንደሚያደርገውም ሙያዊ አስተያየቱን አስፍሯል። ሙዚየሙ በራሱ የሚገኝበት ቦታ ለትራንስፖርት አመቺ ከመሆኑ አንጻር እንዲሁም በጃንሜዳ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለስፖርት እና ለሃይማኖታዊ ክብረ በዓሎች ቁጥሩ የበዛ የህብረተሰብ ክፍል ስለሚገኝ ሙዚየሙ እራሱን የማስተዋወቅ ሥራ ቢሰራ የስፖርት ሙዚየሙን እና የስፖርት ቱሪዝም ጽንሰ ሃሳብ ከማስተዋወቅ አንፃር ሰፊ ዕድሎች እንዳሉት ገልጿል። በአገራችን ብዙም ያልተለመደው የስፖርት ሙዚየሙ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም ይጠቁማል።
የሙዚየሙን ህንጻ በተመለከተ እንደ ደካማ ጎን የሚጠቀሱትን ሲያነሳ ህንጻው «ለሙዚየሙ አገልግሎት ተብሎ አለመሰራቱ ላይ ትኩረት ያደርጋል። አንድ ሙዚየም ሊያሟላቸው የሚገባውን መሰረታዊ ነገሮች እንዳልያዘም ይታዘባል። ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ያሉት አመራሮች ስለ ህንጻው አሰራር እና ስለ ሙዚየም አመሰራረት አለማወቃቸው ጥናት አድራጊው ከታዘባቸው መካከል ነበር። ይህ ደግሞ ስለ ሙዚየሙ ህንጻ ታሪክ በዝርዝር ለማወቅ አዳጋች ሆኖበት እንደነበር ይናገራል። ከዚህ በተጨማሪ የሙዚየሙ ክፍል ጠባብ መሆኑ በውስጡ ያሉትን ቅርሶች በተደራጀ መልኩና አመቺ በሆነ አግባብ እንዳይቀመጡ ማድረጉን ይገልፃል። በቅርቡ በሙዚየም እና በሌሎች የአስተዳደር ህንፃዎች ላይ የእሳት ቃጠሎ ደርሷል። ቃጠሎው የተነሳበት ምክንያት ለማጣራት ፖሊስ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ የጃን ሜዳ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መኮንን ቢገልፁልንም ይህን መሰል ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ ቅድመ ጥንቃቄ ለመውሰድ በሚያስችል መልኩ ሙዚየም አለመደራጀቱ ለስፖርታዊ ቅርሶቹ የተሰጠው ግምት አነስተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
አቶ ፍፁም የጥናት ውጤቱን መሰረት በማድረግ «ሙዚየሙ ውስጥ በቂ የሆነ የአየር ዝውውር ካለመኖሩ አንጻር ከዚህ ጋር ተያይዞ ለሚመጡ ችግሮች በተገቢው መልኩ ሙያዊ እና ሳይንሳዊ የሆነ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ባለሙያ አለመኖሩ እንደ ድክመት ልንቆጥረው እንችላለን» ይላል። በሙዚየሙ ውስጥ በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ እና መተኪያ የሌላቸው የስፖርት ቅርሶች እንደመኖራቸው መጠን የቅርሶቹን ባህሪያት በባለሙያ በማስጠናትና ለቅርሶቹ ተስማሚ የሆኑ የመብራት ዲዛይን በመግጠም ቅርሶቹ ከጉዳት ስጋት ማውጣት አስፈላጊ መሆኑንም አስምሮበታል።
ይህን ማድረግ ከተቻለ ለስፖርት ሙዚየሙ የወደፊት ዕጣፈንታ እንዲሁም ለስፖርት ቱሪዝም ትውውቅ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ ያደርገዋል ይላል። ጥናት አድራጊው ከዓመት በፊት በዚህ መልኩ ምክረ ሀሳቡን ቢያስቀምጥም ሳይንሳዊውን ትዝብቱን ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የተንቀሳቀሰ አንድም አካል አለመኖሩን የሚያሳዩ መረጃዎች መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ ያክልም በሙዚየም ውስጥ የሚገኙ ቅርሶችን ከጉዳት አርቆ ለሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ተደራሽ ለማድረግ የተደረገው ጥረት አነስተኛ ነው። ይህ ደግሞ ያሳለፍነው ግንቦት 9 ላይ እስካሁን ባልተረጋገጠ ምክንያት የእሳት ቃጠሎ መነሳቱና በዚህም ሙዚየሙን ተጋላጭ አድርጎታል።
አቶ ፍፁም «ለሙዚየም ስብስቦች መጎዳት የሚጠቀሱ ብዙ ምክንያቶች ቢኖርም በሙዚየም ውስጥ የሚሰራ አንድ ባለሙያ ስለ ቅርሶች አሰባሰብ፣ አጠባበቅ፣ አያያዝ እና መሰል እውቀቶች ከሌለው ከማንም በላይ ዋናው የጥፋት መጀመሪያ እራሱ ባለሙያው ነው» በማለት በተመሳሳይ መልኩ ዳሰሳውን በሚያደርግበት ወቅት በጃንሜዳ ስፖርት ሙዚየም ውስጥ በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ አለመኖሩን መታዘቡን ገልጿል። ሙዚየሙን የተመለከተ መረጃ ከሚሰጥ መመሪያ አለመመልከቱንም ተናግሯል።
የስፖርት ሙዚየም ለስፖርት ቱሪዝም
አቶ ፍፁም የስፖርት ሙዚየም በማስመልከት በሰራው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ስፖርት ቱሪዝም ለአገር ያለው ፋይዳን ለማስቀመጥ ሞክሯል። ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረገው ቆይታም ለጥናቱ መነሻ የሚሆኑ ተሞክሮዎችን ማንሳቱን ገልፆ ፋይዳዎቹን አስረድቷል።
«በስፖርት ቱሪዝም ያደጉ የዓለም አገራት በአብዛኛው አውሮፓ የሚገኙ ናቸው» የሚለው አቶ ፍፁም ከዘርፉ የሚያገኙት ገቢ ትልልቅ የዓለም ውድድሮችን ማለትም የዓለም እግር ኳስ፣ የኦሎምፒክ ጨዋታ እንዲሁም መሰል ውድድሮችን ከማዘጋጀት ጋር ተያይዞ እንደመጣ ያስረዳል። ከነዚህም ውስጥ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሞናኮን እንደ ደረጃቸው የሚቀመጡ መሆኑን ይናገራል። መረጃውን የሚያስቀምጠው «ዎርልድ ትራቭል አዋርድ፣2015» ያወጣውን ደረጃ መሰረት በማድረግ ነው። በአፍሪካም ደቡብ አፍሪካ በቀዳሚነት እንደምትጠቀስ ገልፆ ሲሸልስ፣ ሞሪሺየስ፣ ሞሮኮ፣ ናሚቢያ፣ ኬንያ ተከታዮቹን ደረጃ እንደሚይዙ ይናገራል። እነዚህ አገራት የስፖርት ቱሪዝማቸው ዕድገት ያሳየው ያሏቸውን ታሪካዊ ቅርሶች እና ሙዚየም እንዲሁም የሚታወቁበትን የስፖርት ዓይነት በአግባቡ መጠበቅ እና ማሳደግ በመቻላቸው ነው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ስፖርቶች ውጪ በርካታ ቅርሶች እንዳሏትም ባለሙያው ይገልፃል።
«ስፖርት ቱሪዝም በብዙ አገራት ትኩረትን በመሳብ እና ፈጣን ዕድገትን በማስመዝገብ ላይ የሚገኝ የቱሪዝም ንኡስ ዘርፍ ነው» የሚለው አቶ ፍፁም አዲስ አበባ ለስፖርት ቱሪዝም ከፍተኛ እምቅ ሀብት ያላት ከተማ መሆኗንም ይናገራል፡፡ ከዋናዋናዎቹ መካከል አትሌቲክስ፣እግር ኳስ፣ብስክሌት ውድድር ፣እና ሌሎችንም ይጠቅሳል። በጥናት ውጤቱ ላይም ያረጋገጠው ይህንኑ ነው። ሌላው ከስፖርት ጋር በተያያዘ በመዲናችን አዲስ አበባ በጃንሜዳ የስፖርት ማዕከል ውስጥ የስፖርት ሙዚየም የሚገኝ መሆኑን እንደ ትልቅ ዕድል ሊቆጠር የሚገባው መሆኑን ያስገነዝባል። በሙዚየሙ ውስጥ በርካታ ታሪካዊ እና ዕድሜ ጠገብ ቅርሶች መኖራቸውን በመግቢያዎች ላይ በስፋት ለመዳሰስ ሞክረናል።

ዳግም ከበደ

 

 

 

 

 

 

 

Published in ስፖርት
Sunday, 08 July 2018 22:56

የ97 ቀናት ሰበሮች

እንዴት ነው በቁጥር ርዕስ በድጋሚ ተገናኘን አይደል? ቆይ ግን ዘንድሮ 1 እና 0 ቁጥር አይለቁኝም እንዴ? ባለፈው ሰኔ 10 ቀን 10 10 10 ብያችሁ ነበር። ከሰሞኑ ደግሞ ምን ቢያጋጥመኝ መጥፎ ነው? አከራዬ 100 ብር ጨመሩብኝ። ነገሩን ስጠረጥር ያንን ጋዜጣ አንብበው ‹‹ይሄ ልጅ 0 መደርደር ከወደደ ለምን ቤት ኪራይ አልጨምርለትም›› ብለው መሰለኝ። የጻፍኩት እኔ አይደለሁም ብዬ እንኳን ድርቅ እንዳልል መታወቂያዬን ኮፒ አድርገው ይዘውታል። እናም የ 0 ሱስ ካለበት ብለው 100 ብር ጨመሩብኝ።
ወደዋናው ቁም ነገር እንግባ። (የእስካሁኑ ቀልድ ነበር ማለት ነው) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ ከሰሞኑ 100 ቀን ሊሆናቸው ነው። ዛሬ 97ኛ ቀኑ ላይ ስንገኝ የፊታችን ረቡዕ 100ኛ ቀን ይሆናቸዋል። ታዲያ በእነዚህ 100 ቀናት ውስጥ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሳይቀር በርካታ አስገራሚና አስደሳች ነገሮችን ስታሳይ ቆይታለች። የመገናኛ ብዙኃን ወሬ ሁሉ ‹‹ሰበር ዜና›› ሆኖ ነበር።
የቴሌቪዥን ጣቢያዎችማ ‹‹ሰበር ዜና›› የሚለውን ‹‹ስክሪን ሴቨር›› አድርገውት ነበር። ይሄን ጽሑፍ ስታነቡ ራሱ ሰበር ዜና ይኖር ይሆናል። ገና እስከ ረቡዕማ (100ኛ ቀኑ) ብዙ ሰበር ዜና ይኖራል። እንዲያውም አንድ ሰው ምን አለ መሰላችሁ? ‹‹ስልኬን ቻርጅ እስከማደርግ እንኳን ብዙ ሰበር ዜና ያልፈኛል›› ብሎ ነበር (ያው መቼም የማህበራዊ ድረ ገጾች ወሬ ቀድሟል)። አንዱ ደግሞ ‹‹ኧረ እባካችሁ መብራት አታጥፉብን ሰበር ዜና ያልፈናል›› ብሎ ነበር።
እንዲያው ከዚሁ ከሰበር ዜና ነገር ሳንወጣ ስለመገናኛ ብዙኃን ለውጥም ማንሳት ይቻላል (እኔ ራሱ ወደዋናው ጉዳይ ለመግባት ሰበር ወሬ በዛብኝ እኮ)። ስለመገናኛ ብዙኃን ካነሳን ደግሞ ቀድሞ የሚጠቀሰው አንጋፋው ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ቴሌቪዥን መሃል ላይ ኢቢሲ ተብሎ ስሙ ማምታታት ጀምሮ ነበር። ኢቢሲ የሚለው ቃል ሲለመድ አሁን ደግሞ እንደገና ኢቲቪ መባል ጀምሯል (እንግዲህ ይሄ በአዋጅ ይሁን አይሆን አላውቅም)። ያም ሆነ ይህ ኢቲቪ አሁን ‹‹ቃና ውስጤ ነው›› የሚለውን ፋሽን አዘግቶ ‹‹ኢቲቪ ውስጤ ነው›› ሆኗል።
እንዲያውም ባህርዳር ላይ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ‹‹ለውጥን ከኢቲቪ እንማር!›› የሚል መፈክር ነበር። ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ደግሞ ‹‹እባክህ ፈጣሪ ኑሮዬን እንደ ኢቲቪ ቀይርልኝ›› የሚል ተጽፎ አንብቤያለሁ። በፊት ኢቲቪ አሠልቺ ነው በሚባልበት ጊዜ የተማረሩ ሰዎች ደግሞ ግብር አይገባውም ብለው ያስቡ ነበር መሰለኝ፤ አሁን ግን ‹‹የኢቲቪ ግብር መክፈያ የት ነው?›› ያሉም ነበሩ፤ አሁን ይገባዋል እያሉ መሆኑ ነው ፡፡
እያወራን ያለነው ዶክተር ዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ወዲህ በአገሪቱ ስለታዩ ለውጦች ነው። የእርሳቸውን መመረጥ ተከትሎ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የነበሩ እስረኞች ተፈተዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ አንድ የሰማሁት ቀልድ ‹‹ይሄ ሰውዬ በዚህ ከቀጠለ ገና ህልምም ይፈታል›› የሚል ነበር። እንዲያውም ዶክተር ዓብይ የተመረጡት በዓብይ ጾም ውስጥ ስለነበር ከስማቸው ጋር አገጣጥመው ብዙ ያሉም ነበሩ።
የፋሲካ ሰሞን ደግሞ ከዶሮዎች ጋር ተያይዞ የተቀለደው ቀልድ አስቂኝ ነበር። በዶሮዎች ላይ ካርቱን ተሰርቶ ከዶክተር ዓብይ ንግግር እየተወሰደ ይጻፍባቸው ነበር። ‹‹እኛ ዶሮዎች ስንኖር ዶሮ ስንሞት ዶሮ ወጥ እንሆናለን›› ተብሎ ነበር። ከዶክተር ዓብይ መመረጥ በፊት በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ነበሩ። በተቃውሞ ሰልፎች ላይም የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱና በሌሎች አካባቢዎች የሚደርሱ ጥቃቶችንም የሚያወግዙ መፈክሮች ይያዙ ነበር።
ከዶክተር ዓብይ መመረጥ በኋላ ግጭቶች ሲቆሙ ነገሩ ወደ ቀልድ ተቀየረና የፋሲካ ሰሞን ለዶሮዎች ተሰጠ። ‹‹በየቤቱ የታሰሩ ዶሮዎች ይፈቱ!፣ የበጎች ደም የእኛም ደም ነው›› የሚል ካርቱን ሲሰራ ነበር። ቃላት በታዋቂ ሰዎችና በመሪዎች ሲነገሩ ትልቅ ዋጋ ይሰጣቸዋል። በመጥፎም ይሁን በደግ በመሪዎች የሚነገሩ ቃላት በአጭር ጊዜ ውስጥ እውቅና አግኝተው መግባቢያ ይሆናሉ። ለምሳሌ እንደዛሬው ‹‹መደመር›› የሚለው ቃል ማለት ነው። ይህ ቃል ከዶክተር ዓብይ መመረጥ ወዲህ ተጀምሮ አሁን ፋሽን ሆኗል። በየቀበሌው ብትሄዱ ‹‹ተደምረሃል›› ይባላል።
‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ›› የሚለውም እንዲሁ። እንዲያውም አንዱ ሲኖትራክ በአጠገቡ ሲያልፍ ምን አለ መሰላችሁ፤ ‹‹ውይ! ኢትዮጵያ አርጎኝ ነበር!›› ሞቼ ነበር ማለቱ ነው። አሁን ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተደጋገመ ያለው ‹‹የቀን ጅብ!›› የሚለው ቃል ነው። ይህ የሆነው በማህራዊ ድረ ገጾች ብቻ እንዳይመስላችሁ! በየቴሌቪዥኑ፣ በየሬዲዮውና በየጋዜጣው ጭምር ነው። በዚሁ ጋዜጣ ላይ እንኳን ‹‹የቀን ጅብ›› የሚለውን ቃል ለዚያውም ርዕስ ላይ ሁለት ጊዜ አይቼዋለሁ።
እንግዲህ በእያንዳንዱ ቃላት ላይ ቀልድ አይጠፋምና እዚህ ላይ ደግሞ ያሳቀኝ ‹‹ከሐረር ጅቦች የተሰጠ መግለጫ›› የሚል ጽሑፍ ያየሁ ዕለት ነበር። እንደሚታወቀው ሐረር ውስጥ ለማዳ ጅብ ስላለ ቀን ቀን ከሰዎች ጋር አብሮ የሚውል ነው። የጽሑፉ ይዘትም የቀን ጅብ የሚለው ቃል ‹‹እኛን አይወክልም›› የሚል ነበር።
ዶክተር ዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ቀን ጀምሮ አዳዲስ ነገሮች ጠፍተው አያውቁም። ገና እንደተመረጡ ሰሞን በየክልሎች እየሄዱ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረግ ጀመሩ፤ ከዚያም ከባለሀብቶች ጋር፣ ከዲያስፖራ ጋር፣ ከወጣቶች ጋር… እያለ በየዕለቱ ውሏቸው ይታወቅ ነበር። አንድ ዕለት ታዲያ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን አልጋ ወራሽን ራሳቸው መኪና እያሽከረከሩ መንገድ ሳይዘጋላቸው መሄዳቸው መነጋገሪያ ሆኖ ሰነባብቷል። በዚህ እየተገረምን ሳለን ደግሞ ሰኔ 16 በተካሄደው የድጋፍ ስልፍ ላይ በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ አስደንጋጭ ዜና ሰማን።
ታዲያ የዶክተር ዓብይ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ማወቅ የፈለገ ህዝብ አንድ ቀን እንኳን ሲጠፉ ‹‹የት ውለው ይሆን?›› ማለት ተጀምሯል። ይህ የዶክተር ዓብይ ውሎ ያሳሰበው አንዱ ደግሞ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹አብይ ከሚያመሽ ሚስቴ ውጭ ብታድር ይሻለኛል›› ለመሆኑ ኢትዮጵያ በእነዚህ 100 ቀናት ውስጥ ምን ነበረች? ብለን ብንዳስስ በብዙ ነገሮች ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ጆሮ ውስጥ ገብታ ከርማለች።
የኢትዮጵያና የኤርትራን ጉዳይ አንዱ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ነበር። ከብዙ ዓመታት በኋላ የኤርትራ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ውስጥ መጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የ2011 የእንቁጣጣሽ በዓል አስመራ ላይ ይከበራል ብለዋል። በቀይ ባህር ዳርቻ የእግር ጉዞ(ወክ) ይደረጋልም ንግግራቸው ነበር። ከኤርትራ የልዑካን ቡድን ጋርም እጅ ለእጅ ተያይዘው ‹‹ሰላም›› በሚለው የትዝታው ንጉሥ መሀሙድ አህመድ ዜማም ዶክተር ዓብይ ከእንግዶቻቸው ጋር አብረው አዚመዋል።
ኧረ ቆይ የዶክተር የኪነ ጥበብ ፍቅር ከተነሳስማ አንድ ነገር ሳልናገር ጽሑፌን አልቋጭም። መቼም በአንድ ተወዳጅ ፊልም ውስጥ በደራሲነት ተሳትፈው እንደነበር ‹‹አልሰማሁም›› የሚለኝ አይኖርም። እኔ እኝህ ሰውዬ ማዕረጋቸው በዛብኝ። ዶክተር፣ ደራሲ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር... ዓብይ አህመድ፤ እንዲያውም ወታደራዊ ሳይንስ ውስጥም አሉበት ነው የሚባለው። ዶክተር ዓብይ ለኪነ ጥበብም ያላቸውን ፍቅር አርቲስቶችን በጽሕፈት ቤታቸው ጠርተው በማወያየት አስመስክረዋል። በውይይቱ ላይ አይታችሁ ከሆነ የዘፋኞችንና የተዋናዮችን ስም እየጠሩ ሲያስተምሩ ነበር።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እያሉ የንባብ ለሕይወት ፕሮግራም ላይ ስለኪነጥበብ የተናገሩትን አልረሳውም። ‹‹ከሪያላይዜሽን ኢማጂኔሽን ይቀድማል ነበር ያሉት። አንድ ነገር ከመሰራቱ በፊት ማሰቡ ነው የሚቀድመው ማለታቸው ነው። ምሳሌ ሲሰጡም ‹‹ራይት ብራዘርስ›› የተባሉት ወንድማማቾች አውሮፕላንን ከመስራታቸው ከብዙ ዓመት በፊት የግሪክ ደራሲዎች ስለአውሮፕላን ጽፈው እንደነበር ነው።
እንግዲህ ዛሬ 97ኛ ቀናቸው ነው ብለናል። በእነዚህ ሦስት ቀናት ውስጥ ደግሞ ብዙ ሰበር ዜና ይኖራል፤ አሁንማ ፍርድ ቤቶችም እኮ ከሰበር ሰሚ ችሎት ወደ ሰበር ዜና መስጠት ተሸጋግረዋል። እስረኛ ተፈታ ነው፣ ክስ ተቋረጠ ነው፣ የሽብር ወንጀል ተቋረጠ ነው። በሉ እንግዲህ ሰበር ዜና በበዛበት ሰሞን ከዚህ በላይ ማውራት አንባቢ ማጣት ነውና ይብቃኝ። አገራችን ሰላም ትሁን!

እንዲህም ይበላል!

«አርሼም አየሁት
ነግጄም አየሁት
እኔስ እግዚአብሔርን
በለቅሶ አገኘሁት!» የህዝብ ስነ ቃል ነው።
የምናወራው ጋና ውስጥ ስለሆነ አንድ አስገራሚ ነገር ነው። ዳሩ ግን ሮጠን ወደውጭ የመሄድ ሱስ አለብን እንጂ አገራችን ውስጥም ብዙ አስገራሚ ነገር አለ (ለዚያውም ከቅኔ ጋር)። በአገራችን አንድ ሰው ነበር። እርሻ ቢሞክር ውጤታማ አልሆን አለው፤ ግብርና ለእኔ አልተፈጠረም ብሎ ንግድ ሞከረ። በንግድም ውጤታማ አልሆነም። ሰውየው ተበሳጨ። አንድ የጎረቤት ለቅሶ ላይ ሙሾ አውራጅ ሆነ። ሰውየው ለቅሶኛውን ሁሉ አደበላለቀው አሉ። ከዚያ በኋላ ሰው በሞተ ቁጥር ለቅሶውን እንዲያደምቅ ይወስዱት ጀመር። ነገሩ ሲደጋገምበት ‹‹ለምን አላስከፍላቸውም›› ብሎ በክፍያ ማስለቀስ ጀመረ።
ሰዎች ግን እየከፈሉም ቢሆን መውሰዳቸውን አላቋረጡም። የዚህ ጊዜ «ለካ እንጀራዬ ንግድም ግብርናም ሳይሆን ሙሾ ማውረድ ነው» ብሎ ከላይ ለመግቢያ የተጠቀምነውን ቅኔ ተቀኘ። አሁን ወደ ጋና መሄድ እንችላለን። ሴትዮዋ አሚ ዶክሊ ይባላሉ። የእትዬ ዶክሊ እንጀራ እንደነገርኳችሁ ሰውዬ በለቅሶ ሆኗል። አይ ቢቢሲ! የኛን ሀገር ባለቅኔ አልቃሽ አልሰማው ይቺን ሴትዮ ግን ቃለ መጠይቅ አድርጎታል።
ሴትዮዋ ቀብረር ብለው ምን ቢሉ ጥሩ ነው? ‹‹አንዳንድ ሰዎች የቅርብ ዘመዳቸው እንኳን ሞቶ ማልቀስ አይችሉም፤ በእኛ አገር የቀብር ስነ ስርዓት ደግሞ ማልቀስ ባህላችን ነው። እነዚህ ማልቀስ የማይችሉ ሰዎች ለእኔ ረብጣ ብራቸውን ይከፍሉኛል፤ እኔም የሞተውን ዘመዳቸውን ስም እየጠራሁ እየዬውን ማስነካት ነው›› አሉ። ቆይ ግን እኔ ያልገባኝ ነገር፤ ለምሳሌ ከፍሎ የወሰዳት ሰው አጎቱ ሞቶበት ነው እንበል፤ ይቺ ‹‹ሴትዮ ወይኔ አጎቴ! ወይኔ አጎቴ ልትል ነው?» እሺ አለች እንበል፤ እሷን ያየ ሰው ያለቅሳል ወይስ ይስቃል?
ሴትዮዋ ባሏ እንደሞተባታም ለቢቢሲ ትናግራለች፤ እኔስ እንዲያው የባሏ መሞት ሆድ እየባሳት ይሆን? አቤት ይቺ ሴትዮ ባሏ የሞተባት ሴት ብትወስዳት እንዴት ታለቅስላት ነበር? ለነገሩ ለባል የማያለቅስ ስለማይኖር ማንም አይወስዳትም። ቢወስዷት ግን ለማልቀስ ምቹ ነው፤ ምክንያቱም የገዛትን ሰው ወክላ ስለሆነ የምታለቅሰው ‹‹ወይኔ ባሌ ወይኔ ባሌ!›› እያለች የራሷን ብሶት መወጣት ትችላለች።
የሴትዮዋ አስገራሚ ነገር መቼ ይሄ ብቻ ሆነና! እንድታለቅስ ይዟት የሚሄደው ሰው ከፈለገ ሴትዮዋ ጓደኞቿን ጨምራ ትሄዳለች። አብረዋት የሚሄዱት ሴቶች ሁሉም ባል የሌላቸው ናቸው (ሞቶባቸው ይሁን ስላላገቡ የተገለጸ ነገር የለም)። በነገራችን ላይ ዘገባው አያይዞ የነገረን ነገር በጋና ውስጥ የቀብር ስነ ሥርዓት ከፍተኛ ብክነት የሚጠይቅ ነው። እንግዲህ ለዚህ የዳረጋቸው በውክልና ማልቀስ የሚያስችል ባህል ቢኖራቸው ነው። አንድ የቀብር አስፈጻሚ ለሲ ኤን ኤን እንደተናገረው፤ አንድ የቀብር ስነ ሥርዓት ብቻ ከ15 ሺህ እስከ 20 ሺህ ዶላር ይወስዳል(ልብ በሉ ዶላር ነው የተባለው)።
እቴቴ ዶክሊ ሌላም ነገር ብለዋል። ‹‹እኔ ሥራዬ ይሄው ነው፤ ሰው ሲሞት ማልቀስ የማይችል ሰው ይደውልልኛል መሄድ ነው፤ እንዲያው ድንገት መንገድ ሄዶ ባይመቸው እንኳን ሰው ይልክብኛል›› እንግዲህ ለእቴቴ ዶክሊ በጠዋት ደውሎ ‹‹ስሚ ዛሬ እገሌ የሚባል ዘመድ ሞቶብኛልና አደራ እንደኔ ሆነሽ ዋይ ዋይ በይልኝ!›› ይላታል ማለት እኮ ነው። እኔ በዚህ ባህል ላይ ብዙ የማይገባኝ ነገር አለ። የሟች ቤተሰቦች ሴትዮዋ በውክልና እንደመጣች ያውቃሉ፤ ስለዚህ እሷ አለቀሰችልን ነው የሚሉት ወይስ ወካዩ?
ወካዩ በተወካይ አለቀሰ ማለት ለሟቹ አዝኗል ማለት ነው? መጀመሪያ እኮ ማልቀስ ስላልቻለ ነው ሰው የገዛው፤ ይሄ ሰው እኛ አገር ቢሆን እኮ ‹‹ከልብ ካዘኑ እምባ አይገድም›› በሚለው አባባል ይገደባል። እምባ ካጣ ከልብ አላዘነም ማለት ነው። ቅድም ስለአገራችን የነገርኳችሁ ሰውዬ ሙሾ አውራጅ እንጂ አልቃሽ እንዳይመስላችሁ ደግሞ።
መውጫችንንም እንደመግቢያችን ሁሉ በአገራችን ባህል ነው የምናደርገው። በአገራችን ውስጥ ለቅሶ በጣም የሚፈሩ ሰዎች አሉ። በባህላችን ደግሞ ለቅሶ አለመድረስ ነውር ነው። በተለይም በገጠር አካባቢ ሟቹ ብዙ ጊዜ ቢሆነው እንኳን ‹‹እርም ማውጣት›› የሚባል ነገር አለ። በዚሁ ባህል ውስጥ ታዲያ ሁሉም እንባ አውጥቶ ይወከወካል ማለት አይደለም። ድምጽ አውጥቶ ማንጎራጎርም የለቅሶው አይነት ነው።

 

 

ዋለልኝ አየለ

 

Published in መዝናኛ

«ጥበብ ሥራዋን ብትሠራ ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥላቻ ነግሶ ሰው የራሱን ወገን ለመብላት ባልተዘጋጀ ነበር። ጥበብ ሚናዋን ብትጫወት ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ሀብት ይዛ ባልተቸገረች። ጥበብ በባህሪዋ ግን የሚፈጥራትን ብቻ ሳይሆን አውቆ የሚጠቀምባትን ሕዝብ ትፈልጋለች። ሁሉ ችግር የእናንተ አይደለም» በማለት ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ።
ዶክተር ዓብይ ከአንደበተ ርዕቱነታቸው በተጓዳኝ አዕምሮ ያለው የሰው ልጅ በመነጋገር መግባባትና ለውጥ ማምጣት እንደሚችል በአጭር ጊዜ በተግባር ማሳየት የቻሉ ናቸው። ታዲያ በዚህ ሂደት በቤታቸው፣ በቢሯቸው ጋብዘው ሃሳባቸውን ካካፈሏቸው መካከል የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተጠቃሽ ናቸው። ይህ የሆነው ሰኔ 20 ቀን 2010ዓ.ም ሲሆን፤ ያደረጉትን ገለጻም አንዳች እንኳ ችላ ሊባል የሚቻል ንግግር ባይኖረውም፤ ለጋዜጣው በሚመች መልኩ የተወሰነውን ክፍል አለፍ አለፍ ብለን ቃል በቃል ልናካፍላችሁ ወደድን።
ውይይቱ ለምን አስፈለገ?
ጥበብን ማድነቅ፣ ጥበብን መጠቀም ያልቻለ ሕዝብ አልሰለጠነም፣ አላደገም፣ አልተቀየረም፤ እኛም እንደዚሁ ነን። አሁን ያለውን ትውልድ የፈጠረው የባለፈው ጥበብ ነው፤ ይህኛው ትውልድ ደግሞ ቀጣዩን እንዳይገድል እንድናስተውል ነው ውይይቱ ያስፈለገው።
ጥበብ ምንድን ነው?
ጥበብ ረቂቅ ሰብዓዊ ስሜቶች በትዕምርት የሚቀርፁበት ፈጠራ ነው። ረቂቅ ስሜት መቅረጽና ማስተጋባት የሚቻለውም በጥበብ ብቻ ነው። ሰዎች፣ ማኅበረሰብ ስለዓለም ያላቸውን ውበታዊ ግንዛቤ የሚገልጽ ክዋኔ ጥበብ ነው። ዓለም ከጥበብ ውጪ ውበቷ አይታይም። የዓለምን ጥበብ አውቀን፣ ተገንዝበን በደስትና በፍስሀ እንድንኖር የሚያስችለን ደግሞ ጥበብን መገልገል መቻል ብቻ ነው።
የሰው ልጅን ደመነፍስ እውን የሚያደርግ ኪን (ክዋኔ) የሚፈልቀው ከጥበብ ነው። በደመነፍሳችን የምንገነዘባቸው ግን መግለጽ የማንችላቸው ስሜቶች በጣም በርካታ ናቸው። የሚያስደነግጡን ግን ለምን እንደደነገጥን መናገር የማንችላቸው፤ እነሱን ሁሉ መግለጥ የሚችል ብቃት አለው።
በሌላው እሳቤ ደግሞ ጥበብ ምናባዊ አካልን ፈጥሮ ሰው በቀላሉ እንዲያይ፣ እንዲዳስስ፣ እንዲጨብጥ ማድረግ የሚያስችል ብቃት አለው። አንድ አርቲስት በአምስት ደቂቃ ማስለቀስ ወይም ማሳቅ ይችላል፤ እኛ ግን እንደምታውቁት በአንድ ሰዓት ለማስጨብጨብ መከራችንን እናያለን።
ጥበብ እንዴት ይጠቅማል?
ሥነጥበብ ስንል የማኅበረሰብ ስሜት፣ ፍላጎት፣ ቁጭት፣ ሀዘን ደስታ የሚገለጽበት መሣሪያ ነው። ይህን መሣሪያ መጠቀም የቻለ ማኅበረሰብ ከደስታ ወደላቀ ፍስሀ ይሸጋገራል፤ መጠቀም ያልቻለ ደግሞ ደስታ በእጁ እያለ ወደኀዘን ሊገባ ይችላል። ይህን መጠቀም ለአገራት በጣም ጠቃሚ ነው። በቸገረው ጊዜ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌላውም ዓለም ጥበብን ተጠቅሟል። ሲቸግረው ኪነት እያለ ይጠራል፤ ሲደላው ይረሳል። እስኪያሸንፍ ኪነት ትልቅ ተቋም ነው፤ ካሸነፈ በኋላ ይዘነጋል። ጥበብ ግን በቀጣይነት የሚያስፈልግ ሀብት ነው። ይህን ሀብት መመንዘር አለብን የሚል አጠቃላይ ግንዛቤ የለም።
የሰው ልጅ ውስጣዊ ስሜት መግለጫ ምልክት የምናይበት ቀላሉ መንገድ ጥበብ ነው። ሰው ካልተኮረኮረ አይስቅም፤ ግን አንድ ሰው መድረክ ላይ ቆሞ ሺዎችን ማሳቅ ይችላል። ያን ስሜት መቀስቀስ የሚያስችል፤ ጣትን ሰድዶ የመኮርኮር ያህል ብቃት ያለው ቋንቋ ማፍለቅ የሚችል ጥበብ ብቻ ነው። ይህንን በነቢብ (intuition) የሚገለጹ፤ ሰው በቀላሉ የሚያያቸው፣ የሚገነዘባቸውን እውነታዎች የዘነጋ የትኛውም ማኅበረሰብ አይሻገርም።
እናንተ (የኪነጥበብ ባለሙያዎች) በተፈጥሮ፣ በእውቀት፣ በልምድ ያገኛችሁትን ሀብት ደምረን ለኢትዮጵያ አጠቃላይ ዕድገት መጠቀም የማንችል ከሆነ፤ ጥሩ የምንገዳደል መሆን እንችላለን፤ ግን አብረን ማደግ አንችልም። ጥበብ ሚናዋን ስትጫወት ብቻ ነው ማኅበረሰብ የሚቀየረው። ተስፋ መታየት የሚጀምረው ጥበብ በተለያየ መንገድ ሥራዋን ስትሠራ ነው።
የጥበብ ዓለማት
ጥበብ በሁለት ተከፍሎ ይታያል፤ የተፈጥሮ ዓለም እና ማኅበራዊ ዓለም። ይህ እሳቤ ከጥበብ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ብቻ ሳይሆን መገንዘብን የሚጠይቅ እሳቤ ነው። የተፈጥሮ ዓለም የሚባለው የሰው ልጅ በተፈጥሮ ያገኘው፣ ሲወለድ የተቀበለው፤ የለመደው፤ አብሮት የሚኖር ከባቢ ነው። ይህንን አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔር ጥበብ ይሉታል፤ ራሱ እዛ ውስጥ ጥበብ ስላለ።
ማኅበራዊ ዓለም ግን የሰው ልጅ አብሮ ሲኖር ከጎረቤቱ፣ ከከባቢው እየተማረ፣ ሃሳብ እየተጋራ አብሮ በመኖር በዘመናት ፍልስፍናው እያሻሻለው ወይም እያጠፋው የሚሄደው ዓለም ነው። ብዙ ጊዜ ጥበብ የሁለተኛው ዓለም ውጤት ናት ይባላል። ነገር ግን የዚህ ውጤት የሆነች ጥበብ የተፈጥሮን ዓለም እንድናይ ታግዛለች ብለው ያስባሉ።
በሁለቱ ዓለም ውስጥ የሚታየው ጥበብ በማኅበራዊ ዓለም ተፈጥሮ፤ ተፈጥሮአዊ ዓለምንም ግልጥ አድርጎ የሚያሳይ ነው። የጥበብን ያህል ተፈጥሮአዊ ዓለምን ሊያሳይ የሚችል አቅም ያለው ነገር የለም፤ የምናቀው ተራራ፣ ዛፍ፣ መስክ በጥበብ ዓይን ሲታይ የተለየ ውበት ስለሚሰጥ።
ጥበብና ፍልስፍና
በሁለቱ ዓለም ውስጥ ያለው ፍልስፍና ሲታይ በተለይም አርስቶትል እንደሚለው፤ «ሥነጥበብ ጎደሎ የሆነችው ዓለም ሙሉ መስላ እንድትታይ ታስችላለች» ዓለም ሙሉ ሆና አታውቅም፤ እሱን ሙሉ እያደረገ የሚያሳየው ጥበብ ነው። በችግር ጊዜ ፍስኃ ሊመጣ እንደሚችልና መሻገር እንደሚቻል የሚያሳየው ጥበብ ነው፤ በረሃብ ጊዜ እንደሚያልፍ፣ እንደሚዘንብ፣ ምርት ማግኘት እንደሚቻል የሚያመላክተው ጥበብ ነው።
ትላንትና ከጥበብ ውጪ የለችም። ብዙ ሰው ታሪክን ከጥበብ ውጪ ማሰብ የሚቻል ይመስለዋል፤ ግን አይቻልም። ካልተሳለ፣ ካልተጻፈ ታሪክ የለም። በአፈ ታሪክ የለም ወይ ትሉ ይሆናል። በአፈታሪክ የሚጀምር ማንኛውም ነገር መጨረሻ ላይ ፍጹም ተቀይሮ ታገኙታላችሁ። ራሱን ይዞ አይወርድም። የተጻፈና የተሳለ ነገር ሲሆን ነው መሰረቱን ሳይቀይር ሊሄድ የሚችለው። ጥበብ ናት ታሪክ፣ ጥበብ ናት ትላንትና። ነገን የምታመላክትም ጥበብ ናት። የጎደለውን ዓለም ሙሉ የምታደርግም ጥበብ ናት ብሎ ማመን ያስፈልጋል።
ሌላው ፍልስፍና የሰው ልጅ የሥነጥበብ ባለቤት መሆኑ የንቃተ ህሊና ዕድገት ማሳያ ነው። ስሜትን የመረዳት አቅም በዋናነት የሚታወቀው በጥበብ ነው። ይህም ማልቀስና መሳቅ ሊሆን ይችላል፤ ከጥበብ ውጪ ያንን ስሜት መቀስቀስ የሚችል ብቃት ያለው ነገር የለም።
መንፈስን የመረዳት አቅም የሚባለው ዋናው አምልኮ ነው፤ በሁሉም ሃይማኖት። ዜማ ባይኖር ማነው ቀን ሙሉ ቤተክርስቲያን የሚቀመጠው? ስንት ሰዓት ነው ስብከት የምትሰሙት፤ ስንት ሰዓትስ ነው በዝማሬ መቆየት የምትችሉት? በዛም ውስጥ ከፍተኛ ሚና አለው። ብዙ ቁርኝነት የለውም የሚባለው አካልን ከመረዳት አቅም ጋር ነው፤ ግን ከዚህም ጋር በጣም ቁርኝነት አለው። ከሙዚቃ ጋር ነው የእኛ አካል ረጅም ሰዓት በንቃት መሥራት የሚችለው።
ፈጠራ ሥራ በጥበብ
አሁን ላይ የምንመጻደቅበት ፈጠራ ሁሉ የጥበብ ውጤት ነው። ሳይንስ የጥበብ ውጤት ነው፤ የምንበርበት ሂሊኮፕተርና የምንጋደልበት ክላሽም የጥበብ ውጤት ነው። ንድፉ ካልተሠራ አይገነባምና ህንጻም የጥበብ ውጤት ነው።
የፈጠራ ባለሙያ ዜማ ሲደርስ፣ ግጥም ሲጽፍ ወይም ቴአትር ሲሠራ፤ አስቀድሞ በጭንቅላቱ ጨርሶታል የሚሠራውን። መከራውን የሚያየው በጭንቅላቱ ያየውን ሰዎች እንዲያዩለት ነው፤ በምናቡ ያልሠራውን ነገር ማሳየት አይችልም። የፈጠራ ሰዎች ማለት የፈጠሩትን ለሰዎች ለማሳየት የሚተጉ ማለት ነው። እነርሱ ያውቁታል።
ለምሳሌ የፊልም ዳይሬክተሮች «አልመ ጣልኝም» ይላሉ። አዕምሯቸው ውስጥ ያልመጣ ላቸው ንጽጽር አለ ማለት ነው። በደንብ መናገርና ማስቀመጥ ይቸገሩ ይሆናል እንጂ፤ ሲመጣና ሳይመጣ ሲቀር ያውቁታል፤ እውነተኛ ዳይሬክተር ሲሆኑ ማለት ነው፤ አሁን አሁን እየተቀላቀለ ስለሆነ። በየትኛውም መስክ ያሉ የፈጠራ ሰዎች የሚሠሩትን ነገር በጭንቅላታቸው ያውቁታል።
የጥበብ ብያኔዎች
ሁለት እሳቤዎች አሉ፤ አንዱ ሥነጥበብ ለማኅበረሰብ ግንባታ መዋል የሚገባት ናት። በራሷ መቆም ያለባት ሳይሆን ፖለቲካን ወይም ውጊያ ካለ በኪነት ለማንቃት፤ ለማስተማር፤ በጥቅሉ ማኅበረሰብ ለመገንባት የቆመች አንድ ምሰሶ ናት ብለው የሚያስቡ አሉ። በአንጻሩ በፍጹም፤ ጥበብ ራሷን የቻለች፤ ውበት ያላት፤ በራሷም ግብ ያላት፤ ግቧን ለማሳካት በምታደርገው ሂደት ውስጥ ማኅበረሰብ የምታግዝ ናት ይላሉ።
በሁለቱም አግባብ ብናይ፤ በኪነጥበብ የሚገኝ ደስታ ለሥነፍጥረት የመጨረሻው ፍስኃ እንደመሆኑ መጠን፤ ጥበባቱ በቀላሉ የሚገኙ አይደሉም። አንድ ዘፈን እንዲሁ በዋዛ ግጥምጥም ተደርጎ ቢወጣ፤ በማግስቱ ይዘፈን ይሆናል፤ ከሳምንት፣ ከዓመትና አሥር ዓመት በኋላ ግን የለም። ጥበብ መድከምን ትፈልጋለች፤ ሳይደከም በግርግር ለዛሬ እንጨርሰዋለን ግን አይዘልቅም። ለምን? የድካም ፍሬ የሆነው ጥበብ እናንተ በሌላችሁበት ለብዙዎች ደስታ እና ኀዘን ቀስቃሽም ጭምር ነው።
ጥበብ ስሜትን መግለጫ ነው ስንል፤ ለምሳሌ ተናግረን መግለጽ የማንችለውን በስዕል እናያለን። አንድ ስዕል አይተን ሰፋ ያለ ጽንሰ ሃሳብ እንድንገነዘብ የሚያደርገን ጥበብ ስዕል ብቻ ነው። አንድን ስዕል በጽሑፍ መግለጽ ካስፈለገ፤ አስር ገጽ ሊወስድ ይችላል። ይህን በጽሑፍ መገንዘብ ካስፈለገም አሥራ አምስት ደቂቃ ማንበብን ይጠይቃል። አንድ ደቂቃ ብቻ አይቶ ያንን ስሜት መፍጠር ያስቸግራል።
በአሁኑ ጊዜ የጥበብ ድርሻዋ ምን ይሁን?
አሁን ያለው ሁኔታ የዘመኑ ሰው ከለመድነው ሁኔታ የወጣ ነው። የሰው ተፈጥሮአዊ ባህሪ ሰውን ውሃ ሲወስደው ዘሎ ገብቶ ማዳን ነው፤ አሁን ግን ባህሪያችን እንዴት እየሰመጠ እንዳለ ቀርጸን ለሰው ማስተላለፍ ነው። አሁን ያለው ትውልድ ሰው በቦንብ ቆስሎ ድረሱልኝ ሲል እሱን ከመርዳት ይልቅ ቆሞ ለፌስቡክ ይቀርጻል። ጭንቀቱ እንዴት እንደሚዘግበው እንጂ እንዴት እንደሚያድነው አይደለም። ይህ ነገር መቀየር አለበት።
ኢትዮጵያ በጥላቻ፣ በመገዳደል፣ በዘረኝነት፣ በሃይማኖት...ቅርጫ በቅርጫ ስትሆን እንዴት እየጠፋች እንዳለች መዘመር፤ አጠፋፉን ላልሰማ ማሰማት ሳይሆን፤ ከአጠፋፉ እንዴት ይወጣል የሚለውን ማመላከት ነው የጥበብ ሥራዋ። እየተቃጠለ ያለን ቤት ተቃጥሏል ብሎ ፎቶ አንስቶ ማሳየት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሥራ አይደለም። የእናንተ ሥራ ቤቱ ሲቃጠል ውሃ እዛ ጋር አለ፤ አምጥተህ ብታፈስበት ሊጠፋ ይችላል ማለት ነው። ምክንያቱም ያልታየ ማየት ነው የእናንተ ብቃት፤ ማንኛውም ሰው ማየት የማይችለውን ነገር ማየትና ማሳየትም ጭምር ስለሆነ።
ጥበብ ሥራዋ ችግር ሲታይ በሆነ ቀዳዳ ሊወጣ እንደሚችል ፍንጣቂ ብርሃን መስጠትና ማመላከት ነው። ኢትዮጵያ ከምንጊዜም በላይ ይህ ጉልበት ያስፈልጋታል። ሰዎች አጥፍተው፣ ጎድተው፣ አክስረው እንኳ የጸጸት ልብ የላቸውም፤ ተጨማሪ ነገር ነው የሚያስቡት። ይህ የሰዎቹ ችግር ብቻ ሳይሆን የእናንተ (የኪነጥበብ ባለሙያዎች) ችግር ነው።
የፍቅርን እና የይቅርታን እንዲሁም የማስተዋልን ጉልበት፤ ምንም ወረቀት ብንሰበስብ መሞት እንደማይቀር ካላስተማርን፤ የእኛ ውጤት ነው መጨረሻ ላይ በሆነ መንገድ ቀበሌ ሊቀመንበርና ፖሊስ የሚሆነው። በየጊዜው በሥራችን ውስጥ ያንን ነገር ማስጨበጥ ያስፈልጋል። ሠርተናል ትሉ ይሆናል፤ የእናንተ ሥራ የሚለካው በፍሬ ነው። በማሰባችሁ፣ በመጻፋችሁ ሳይሆን በፍሬው ነው መታየት ያለበት።
ለምሳሌ የጥቁር አሜሪካን የባርነት ዘመን ብናስብ እንደሚታወቀው በተስፋ ሙዚቃዎቻቸው ብዙ ሥራን ሠርተዋል። እዚህ ላይ አንድ አከራካሪ ጉዳይ አለ፤ በቆየው የአሜሪካ የአገዛዝ ስርዓት ውስጥ በጣም የተጎዳ የሚባል ማኅበረሰብ ጥቁር እና አይሁድ ነው። ሁለቱም ተገርፈዋል፣ ተጨቁነዋል፣ ታስረዋል፣ እንዳይሠሩና ሀብት እንዳያደረጁ ሆነዋል። ልዩነቱ መብት መከበር ሲጀምር የአይሁድ ዘፈኑ፣ ግጥሙ፣ ፊልሙ፣ ድራማው ወደፊት ሆነ። በዛም እንዴት ዓለምን መቆጣጠር እንደሚችል ያስባል።
ጥቁር ደግሞ ዛሬ ላይ ቆሞ 'ትላንትና ገረፉህ፣ ገደሉህ፣ እንዲህ አደረጉህ' ይላል። አሁን ያለው ትውልድ ትላንት ውስጥ እንዲኖር አደረገው። ሃምሳ ዓመት ባልሞላ ጊዜ አይሁዳውያን ሀብታምና ኃያል ሆኑ፤ ጥቁር ደግሞ ነጻ ደሃ ሆነ። የእኛ ሥራ ትውልድን ወደኋላ መውሰድ አይደለም፤ ያንን ቆሻሻ ጊዜ ለትውልድ አሳይቶ ወደፊት መውሰድ ነው። ያንን እያሰብን በዛ እየቆሰልን እንድንኖር ከተፈለገ ይቻላል፤ ግን አንሻገርም። ስሜት በቀላሉ እየቆሰቆሱ መዝለቅ ብቻ ሳይሆን ማሻገር የሚያስችል ብቃት በጥበብ ውስጥ ስላለ፤ እሱን ማውጣት ያስፈልጋል።
ሥነጥበብ ጭንቀቷ ትውልድም ጭምር ነው። ዛሬ ብቻ አይደለም፤ አንድ መገንዘብ ያለባችሁ ነገር፤ በተለይ ወጣት አርቲስቶች አሁን የምትሠሩት ሥራ አሁን ላለው ትውልድ ምንም ነው። እናንተን ለመስማት ጊዜ የሚያባክን አይኖርም። ለምሳሌ እኔ እና በእኔ እድሜ ያሉ ሰዎች ዘፋኝ ሲባሉ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ኬኔዲ መንገሻ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ ይላሉ። ትንሽ ከፍ ያሉት ደግሞ እነጥላሁን ገሠሠን፣ እነዓለማየሁ እሸቴን ይጠራሉ፤ የሚያገናኝ ነገር ስላለ። አሁን ያሉት ደግሞ ወደፊት ቴዲ እና ጎሳዬ ይላሉ።
ጥበብ አንድ ትውልድ የሚሻገር ነገር መሆኑን እና መሻገር ሲሳነው እንደሚረሳ ማወቅ ያስፈልጋል። ለዚህ ነው በፓተንት ራይት ውስጥ ከሆነ ጊዜ በኋላ ጥበብ የህዝብ ነው የሚባለው። ከሆነ ጊዜ በኋላ ዳኛው ሕዝብ ነው፤ የትኛው ነው የሚዘልቀው፤ የትኛው ነው የሚረግፈው የሚለውን የሠራው ሰው አይወስንም። ያ ሃሳብ ሕዝብ ውስጥ ገብቶ ትውልድ መሻገር ከቻለ ያኔ ነው ያ እውቀትና ጥበብ የትውልድ ሀብት የሚባለው።
ጥበብ ወዲያው ሞጭለፍ ማድረግ አይደለም። ሙዚቃዬ አርባ ሺህ እና ሃያ ሺህ አወጣ አይደለም። ጥበብ ዛሬ ባወጣው ዋጋ አይለካም። እንደሱ ቢሆን ኖሮ እነጥላሁን ገሠሠን ማን ማድነቅ ይችላል፤ እነርሱ ምን አላቸው? ምንም የላቸውም። አሁን ያለው የጥበብ ብልሽት አንዱ እንደ ስግብግቡ ውሻ ነው። ስግብግብ ውሻ ጉዳይ አግኝቶ ስጋ ይዞ ወደ ውሃ ጋር ሄደ ይባላል። በውሃ ውስጥም ስጋ የያዘ ውሻ ያያል። ይህንን ሲያይ ሌላ ውሻ መስሎት፤ እርሱን ለማስደንገጥ ሲጨህ የያዘው ስጋ ውሃ ውስጥ ይገባል። ያን ስጋ ለማዳን እሱም ውሃ ውስጥ ገባ።
አሁን እንትና ስንት ብር ሸጠ፣ ስንት አወጣ ከሆነ ጥበብ ትሞታለች። ምክንያቱም ገበያው እንደ ሁኔታው ይወሰናል። አንዳንዴ በጣም ልዩ የሆነ ሥራ ሰው በጊዜው ሳይገነዘበው ቀርቶ ሳይገዛ ይቀራል። ግን በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ሥራው ላይዘነጋ ይችላል። ጥበብ በገንዘብ አትለካም፤ አንዳንዱ ዘመድ ያለው በጣም ሊደመጥ ይችላል፤ ዘመድ የሌለው ላይደመጥ ይችላል። እንደ እኛ አገር ሲሆን አብዛኛው ሚዲያ የእኛ ስለሆነ፤ ለእኛ የማትመቹ ከሆነ አትደመጡም ማለት ነው። በዚህ ውስጥ አደገኛው ነገር የእናንተ መመዘኛ የእንትና ዘፈን ስንቴ ተደመጠ የሆነ እንደሆነ ነው። ይህ መመዘኛ መሆን አይችልም። መመዘኛችሁ መሆን ያለበት 'ሥራዬ ትውልድ ይሻገራል ወይ?' የሚለው ነው።
ሌላው የሥነጥበብ ምሥጢር የአንድ ማኅበረሰብ ድምር የታሪክ ክምችት የሚገኝበት ነው። ለምሳሌ ስድስት ኪሎ የሚገኘውን የሰማዕታት ሃውልት አይተን ጣልያን የሚባል ወራሪ መጥቶ፤ በአንድ ቀን በአንድ ጀንበር ይህን ያህል ሰው ጨፈጨፈ የሚለውን ብዙ አርቲክል የሚወጣውን ነገር በአንድ ሃውልት እናሳያለን። ይህ ጥበብ ነው፤ ይህ ይሻገራል። አሁን ተሻግሮ ደርሷል ወደፊትም ይሻገራል።
ሌላው ጥበብ ፍትህን፣ ነጻነትን፣ እኩልነትን እና ማህበራዊ ክስተቶችን ማሳያ ነው። ስንበደል ስለፍትህ ይጮሃል፤ ስንጨቆን ነጻነት ይላል፤ መብት ሲጓደልና በእኩል ዓይን መታየት ሲጓደል ደግሞ ስለእኩልነት ያነሳል። በታሪክ ውስጥ የጥበብ ሥራ ይህ ነው።
የጥበብ ችግር ምንድን ነው?
የጥበብ ችግር ሙያተኞች ቁጭ ብለው የሙያቸውን ልክ ለማንበብና ለማወቅ ስለማይጥሩ፣ መሪዎቻቸው ትልቅ ሀብት መሆኑን ስለማይገነዘቡ፣ የዳኝነት ስህተት ይፈጠርና ጥበብ ቆስቁሶ፣ አታግሎ ካሸነፈ በኋላ የድል አጥቢያ አርበኞች ይቀሙትና ጥበብ ይዘነጋል። የአፍሪካ ከባርነት ነጻ የመውጣት እንቅስቃሴ ከጥበብ ውጪ አይታሰብም። አፍሪካ ነጻ የወጣችው በክላሽና አመጽ ባስነሱ ሰዎች ብቻ አይደለም። እነሱን ያነቃ፣ ያስታጠቀ፣ ሞራላቸውን የገነባ ጥበብ ነው። ግን በጥይት ተሸንፏል።
ጥበብ ተዘነግቷል፤ የተዘነጋውን ጥበብ ማውጣትና ቆፍሮ ማሳየት የሱ ሥራ መሆኑን፤ መንግሥትም አያስብም፣ አርቲስቱም አያስብም። በመሃል እንቁ ስጦታ ከሰረ ማለት ነው። ነዳጅ እንፈልጋለን ከነዳጅ የማያንሰው ሀብት ግን ትኩረት አልተሰጠውም። ወርቅ እንፈልጋለን በእጃችን ያለው ግን ቦታ አላገኘም። ይህን መቀየር ያስፈልጋል። መቀየር የሚያስፈልገውም ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምጽ መሆን የሚችል ስለሆነ ነው።
ብዙ መሪ የሚባል ሰው ኮርቶ ይደብቃችሁ ይሆናል እንጂ የጥበብ ውጤት ነው። ሳያነብ፣ ሳይሰማ፣ ስዕል ሳያይ መሪ መሆን አይቻልም። ምክንያቱም ጥበብ ያለው እዛ ውስጥ ነው። በጉዞ ውስጥ ያንን እየተማረ ነው አንድ ቀን መሪ የሚሆነው። ግን ሲፈጠር መሪ የሆነ ስለሚመስለው የብዙዎችን የጭንቅላት እውቀት ውጤት ይዘነጋዋል።
አባባሎችም አሉ፤ ኢትዮጵያ «ያልጠረጠረ ተመነጠረ»፤ «ብቅ ብቅ ያለ ዘንጋዳ ለወፍ ወይ ለወንጭፍ ነው»፤ ዝቅ በል፣ አጎንብስ፣ ተገዛ ነው ባህላችን። አሜሪካውያን ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ነው አባባላቸው። «ድምጽ የማያሰማ ቸርኬ ግሪስ አይቀባም» ይላሉ። ግሪስ መቀባት ከፈለግህ መጀመሪያ መጮህ አለብህ። ይህ እሳቤ ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ነጻ ማኅበረሰብ የተፈጠረው ግን በዚህ ነው።
«ምንም አያግደን፤ ሰማዩ ነው ዳርቻችን» ይላሉ፤ እኛ «አልበር እንዳሞራ» እንላለን። ግጥም እንዲሳካ ብለን እንደቀላል የምናስገባው ነገር ትውልድ ውስጥ የተቀጨና ቀና ማለት የማይችል ይፈጥራል። ምን ዓይነት ቋንቋ እንጠቀማለን። ያነሳሳል ወይ? ያሻግራል ወይ? የሚለውን ጉዳይ በጣም ማሰብ ያስፈልጋል። ልጆችም ላይ የጥበብ ሚና ምንም የሚነገር አይደለም። ልጆች በሂሳብና በፊዚክስ ጥሩ ውጤት ማምጣት የሚችሉት ጥበብ ውስጥ የሚሳተፉ ከሆነ ነው።
ሌላው፤ አንዳንድ ሰው ቢሮው ውስጥ ብዙ ወረቀት ሲያከማች በጣም የተዋከበና ብዙ የሠራ ይመስለዋል። ግን አይደለም። ከብዙ ወረቀት ይልቅ አንድ መንፈስን የሚያነሳሳ ስዕል ፊት ለፊቱ ቢያስቀምጥ፤ ሠርቶ ቀና ሲል ጉልበት ያገኛል። ቢሮ እንዲሁም ቤት ውስጥ ስዕል ማስቀመጥ፤ በየጊዜው ኮርኳሪ ማስቀመጥ ማለት ነው።
ከያንያኑን ስንታዘብ?
ማኅበረሰብ ለመለወጥ እንደ ጥበብ ብቃት ያለው ነገር የለም። ነገር ግን ሚና መቀየር ላይ ሥራ አልሠራችሁም። ለምሳሌ መሠረት መብራቴን የሚያደንቅ አንድ ሺህ አንድ ተማሪ አለ፤ መሠረት አንድ ቀን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄዳ የተወሰነ ደቂቃ ስለራሷ ጥረትና ስኬት ብታወራ፣ ከተማሪዎቹ መካከል ነገ ማን እንደሚነግስ ወይም የኪነጥበብ ባለሙያዎች ኃላፊ ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም። ጊዜአችሁን አታባክኑ። ማብላትና ማልበስ አትችሉ ይሆናል ገንዘብ የላችሁም፤ ግን በማይጠገብ ቋንቋችሁ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ማስተማር፤ ስንፍና እንጂ የሚከለክላችሁ ነገር የለም። ያንን በማድረግ ግን የምትፈጥሩት አቅም ሊነገር አይችልም። ዛሬ አንድ ቦታ ትንሽ ነገር አድርጋችሁ ከሆነ ከዓመት በኋላ የሆነ ዘመን ትርጉም አለው።
ከያኒ ማን ነው?
ከያኒ (አርቲስት) ሁለት ዓይነት ነው፤ መደበኛ ያልሆነ አለ፤ ስም አልባ ነው። ይህ በሰርግ፣ በቀብር፣ እናቶች ልጅ ሲያጠቡ፣ ሲያዝሉ፣ ሲያበሉ፣ ሰዎች በደቦ ሥራ ሲሠሩ፣ አርሶ አደሮች ሲያርሱና በመሳሰለው የሚገርሙ ጥበቦች ይወጣሉ። ሌላው መደበኛው ስም ያለው ነው። እርሱም እንደሙያ የያዘ፤ ሠርቶ፣ ፈጥሮ የሚሸጥ፤ የሚተዳደርበት ነው። ከያኒ ማን ነው? ብለን ስንነሳ ስም የለሹን የዘነጋነው እንደሆነ ምንጫችንን አናውቀውም ማለት ነው። ሰፈር ውስጥ በደቦ ሳይጨፍር ጨፋሪ የሆነ የለም። ሲጨፈርና ሲገጠም ሳያይ በድንገት ተነስቶ ዘፋኝና ገጣሚ የሆነ ሰው የለም። ያ ምንጭ መፍለቂያ ነው።
የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ አሊ ቢራ፣ ከበደ ሚካኤል፣ በዓሉ ግርማ፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ቦብ ማርሌ የሚጠቀሱ ባለሙያዎች ናቸው። የእነዚህ ሰዎች ጥበብና እውቀት ሊነገር የሚችል አይደለም። በቂውን ትውስታ ያገኙ አይመስልም፤ ወደፊት ይታሰባሉ ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ። ታዲያ ዛሬ ላይ ስንሠራ ትናንሽ የሚመስሉ ነገሮች ወደፊት በትውልድ ዓይን የሚፈተሹና የሚተቹ ሊሆን ስለሚችል እንደነዚህ ሰዎች ተጠንቅቀን መሥራት ያስፈልጋል።
ጸጋዬ ገብረመድኅን በተለይ በጀግንነት እሳቤው በጣም ነው የማደንቀው። ጸጋዬ አፄ ቴዎድሮስን ከመቃብር ያወጣው ለአፄ ቴዎድሮስ ብሎ አይደለም፤ የእርሱ ዓላማ ብዙ ቴዎድሮሶች እንዲፈጠሩ ነው። ጀግንነት ለሞተው ሰው አይደለም፤ ለሚፈጠረው ሰው ነው። ጸጋዬ በንግድ ሂሳብ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሂሳብ ነው ጀግና የፈጠረው።
ምክረ ሃሳብ- እቅድ
መጨረስ የሚባል ነገር ከአሸናፊነት ስነልቦና ጋር ይገናኛል። አሸናፊዎች ለሁሉም ችግር መልስ ያያሉ፤ ተሸናፊዎች ደግሞ ለሁሉም መልስ ችግር ያያሉ። የአሸናፊነትን አስተሳሰብ የሚያመጣው ታድያ ጥበብ ነው። እናንተ ድልድይ መፍጠር አለባችሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰባበረ ብዙ ድልድይ አለ። የእያንዳንዱ ቤት መጠን ትንንሽ ሆኖ ጊቢው ግን ትልልቅ አጥር ነው ያለው። በግንብ ሳይሆን በድልድይ ነው ሀብታም የሚሆነው። ድልድይ ያስፈልጋል፤ እሱን ኪነጥበብ ሥራዋን ብትሠራ ጥሩ ነው።
የከፋውንም የለማውንም ለማሳየት ጥበብ ትልቅ ሚና አለው። ጥበብ ሀብት ነው፤ ባለሙያውም እንደዛው። በአገራችን ብዙ የተደበቀ ሀብትም አለና ቆፍራችሁ በማውጣትና ሌሎችንም በመቀስቀስ ወደላቀ ነገር እንድንሻገር ነው። የመጀመሪያው ሥራ ለአዲስ ዓመት አዲስ ርዕይ ብላችሁ በየሙያችሁ ብትዘጋጁ፤ ያም የኤርትራን የኢትዮጵያን፣ የሶማሌን፣ የሱዳንን፣ በአፍሪካ ቀንድ ያለንን ግዝፈት፣ አንድነት፣ ሰላም እና ፍቅር የሚያሳይ ቢሆን።
ሌላው ሕዝብ ለሕዝብ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ መሥራት ነው። ይህን ለመሥራት በደንብ ተደራጁ፤ መንግሥት በጀት አይመድብም፤ ነገር ግን አንዳች ነገር ፈጥረን ገንዘብ ማስገኘት እንችላለን። ዳግም ሃሳቡን ሸጠን ስፖንሰር እንፈልጋለን፤ መጀመሪያ አገር ውስጥ እንሠራለን፤ ኢትዮጵያን አንድ እናደርጋለን። በዛ ሂደት የሚሰበሰብ ገንዘብና ዓላማውም እያደገ ሲሄድ ምስራቅ አፍሪካ ላይ፤ ከዛ በዓለም ላይ ማሳደግ ይቻላል።
የእናንተ (የኪነጥበብ ባለሙያዎች) ችግር አንድ ሁለት ሰው ለአንድ ሁለት ቀን ቀርበህ ካወያየህና ካናገርክ፤ በሦስተኛው ቀን ጓደኛ ነኝ፣ ቤተኛ ነኝ ይበዛል። እንደዚህ ጥሩ አይደለም። እኔ ከእናንተ ውስጥ ቤተኛም ጓደኛም የለኝም፤ ሁላችሁን በሙያችሁ በጣም ነው የምወዳችሁ እንጂ መነገጃ ሲሆን ጥሩ አይደለም። ሰላም!

 

ከጉዞ መልስ

 


ኢትዮጵያ በዓይን ከሚታየውና በጆሮም ከሚሰማው በላይ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ትገኛለች። ምን ኑሮ ቢደቁሰው፣ በምድራዊ ሕይወቱ ምን ያልተመቸው ነገር ቢኖር፤ ቢሰደድ፣ ቢንገላታ፤ የኢትዮጵያዊ መንፈስ ግን መልኩን አይቀይርም። ይህን ፍቅሩን የበለጠ «ምን ሊያበረታው ይችላል?» ብለን እንጠይቅ ይመስለኛል፤ ኢትዮጵያዊ አምኖ ከተቀበለው በላይ አገሩን ቢያውቃትና ቢያያት ከዚህም በላይ ፍቅሩ ይጨምራል።
በአገራችን የአገር ውስጥ ጉብኝት ብዙ አልተለ መደም። ብዙዎች በአብያተ ክርስቲያን አካባቢ፤ ለዓመታዊ ክብረ በዓል፣ ወይም መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት በሚንቀሳቀሱበት ሰዓት አገራቸውን ለማየት ዕድል ያገኘሉ። ከዛ በተረፈ ግን ተማሪዎች በዓመት አንዴ ወይም ሁለቴ፣ ተቋማትም ሠራተኞቻቸውን በተመሳሳይ ሁኔታ በመደበኛነት ከሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ወጣ ብለው እንዲያዩ ካላደረጓቸው በቀር፤ የራስን አገር የመጎብኘት ባህሉ እምብዛም አልተለ መደም።
ወደነገሬ ልግባ፤ አንዳንድ ሙያ ወይም የሥራ መስክ ደግሞ ጥሩ ነው፤ ከቦታ ቦታ የሚያንቀሳቅስ ይሆንና አገርን ለማየት ይረዳል። አገራችንን ደግሞ እንዲህ ወዲያ ወዲህ ብላችሁ ስታዩ «ልዩነታችን ውበታችን» የሚለው ብሂለ ፖለቲካ አካል ገዝቶ ታገኙታላችሁ። አገራችሁን የበለጠ ትወዳላችሁ፣ በተፈጥሮ ትደነቃላችሁ፣ ማንነታችሁም የበለጠ ያኮራችኋል። ታድያ ከሰሞኑ በሥራ አጋጣሚ ወደሻሸመኔ አቅንተን ነበር። የክረምቱን መግባት ተከትሎ ይመስላል ሻሸመኔ ነፋሻማና እርጥብ ሆና ነው ያገኘናት። ያም ቢሆን የለመደችው ሞቃታማነት ባህሪ ፈጽሞ አልተፋታትም፤ በቀኑ እኩሌታ ላይ ብቅ ብሎ መኖሩን አስታውሶ ያልፋል።
በከተማዋ ንግድ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸውና ተቋማት በሚገኙባቸው ቦታዎች አካባቢ በአንድ ጎን የግንብ አጥር ተደግፈው፤ ከለላ ይሆን ዘንድ ከላይ ሸራ ወጥረው «ኑ ቡና ጠጡ» የሚሉ ብዙ ያጋጥማሉ። ፈገግታቸውና ጨዋታቸው የንግድ ሰው ብቻ ሳይሆን የወዳጅነትም ነው። «ምን ላምጣ?» ስትባሉ ቡና የጠየቃችሁ እንደሆነ «ነጭ ነው ጥቁር?» ተከታዩ ጥያቄ ነው። ነጩ ቡና በወተት የሚቀርብ ነው፤ ቡና እና ወተት ተቀላቅለው እሳት ከመታቸው በኋላ «ነጭ ቡና» ይፈጠራል፤ ማክያቶ እንበለው ይሆን?
በብዛት የኦሮሚያ ተወላጆችን ይዛ በዛም ላይ ሰባት የሚደርሱ ብሔር ብሔረሰቦች መቀመጫና መኖሪያ ናት፤የምዕራብ አርሲ ማዕከል የሆነችው ሻሸመኔ። ኢትዮጵያን አገራችን ብለው፣ ከሕዝቡ ተዋደው፣ ተዛምደውና ተዋልደው የሚኖሩ ጃማይካውያንም ለኑሮ የመረጧት መገኛቸው ሻሸመኔ ናት። የከተማዋ ስም ከዚህ ጋር በተገናኘ ጥሩ ባልሆነ ሁኔታ ቢነሳም፤ ስሟ ሲጠራ ቀድሞ ትውስ የሚለን የአደንዛዥ እጾች ጉዳይ ቢሆንም፤ በተለያየ ባህል የደመቀች ከተማ ናት።
በሻሸመኔ የገዳ አባቶችና ሲንቄ የያዙ እናቶችም ሲንቀሳቀሱ ማየት የተለመደ ነው። በተለይም የተለያዩ ጉዳዮችን በሚመለከት በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ ባህላዊ ልብሳቸውን ለብሰው፣ በግርማ ሞገስና በውበት ይታያሉ። ክብ ሠርተው አልያም በትይዩ ሰልፍ ሆነው የሚያሰሙት ዜማ አንዴ ከሰማው ሰው ጆሮ ውስጥ በቀላሉ የሚጠፋ አይደለም። የገዳ አባቶች ምርቃትም አሜን ብሎ ለተቀበለው በረከት፣ ቁጣና እርግማናቸውም ለመከራ የሚዳርግ ነው።
የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ ደስታ ቡኩሉ በሻሸመኔ ከተማ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመፈቃቀር አብሮ የሚኖር ሕዝብ እና ቱባ ባህል አለ ይላሉ። በእርግጥ ኢትዮጵያዊ ባለበት ሁሉ ፍቅርና መተሳሰብ አብሮነትም አዲስ ነገር አይደለም። ከዛ በተጓዳኝ ግን አብሮነቱን ማዝለቅ፣ በፈተና ጊዜ ጸንቶ መገኘት እና ቱባ የተባለውን ቁሳዊም ይሁን መንፈሳዊ ባህል ተንከባክቦ ማቆየት አስፈላጊ ነው።
«ሻሸመኔ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መገኛ ብቻ ሳትሆን ጃማይካውያን ቋሚ ነዋሪዎች ናቸው። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊና የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ በዕድርና ማህበራዊ ጉዳዮች ይሳተፋሉ» ያሉት ከንቲባው ናቸው። ከዛ ባሻገር ደግሞ በከተማው ያሉ ነዋሪዎች ሁሉ ሊታይ የሚችለውን የባህል ገጽታ ሁሉ የሚያንጸባርቅበት ሰፊ አጋጣሚ እንዳለም ነው የጠቆሙት።
ከእነዚህም መካከል በስፋት እየተሠራባቸው ያሉ የባህል ማዕከላትን ያነሱ ሲሆን፤ ተጠናቅቆ በአግባቡ በሥራ ላይ ካለው የሻሸመኔ የባህል አዳራሽ ባሻገር በቁጥር አምስት የሚጠጉ ሌሎችም የባህል አዳራሾች እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሻሸመኔ አቀማመጥ ከሰጣት ጥቅም አንዱ አምስት መግቢያና መውጫ ያላት መሆኗ ነው። ይህም እንደ አቶ ደስታ ገለጻ የንግድ መዳረሻ አድርጓታል። «በደቡብ ኦሮሚያ ላሉ ዞኖችና ከተማዎችም መዳረሻ ናት» ይሏታል። ከዚህ መዳረሻነቷ በተጓዳኝ ብዝሃ ባህል እንዲገኝባት ያደረገ ሲሆን፤ ለኮንትሮባንድ ንግድ አጋላጭ ያደረጋትም ይኸው ሳይሆን አይቀርም። በተለይም በከተማዋ በየጥቂት እርምጃው የሚገኙ የመድኃኒት ቤቶች፤ ለተጠቃሚ የሚያከፋፍሏቸውን መድኃኒቶች የት አገኟቸው ለሚለው ጥያቄ መልሱ ከዚህ የራቀ አይደለም።
መቼም ስለባህል ማዕከል ካነሳንና ሻሸመኔንም የተለያዩ የማንነት ቀለማት ተዋህደው ደምቀው የሚታዩባት ከተማ ናት ካልን ልትታይ ይገባል ስንል፤ መሰረተ ልማትን ሳናነሳ አናልፍም። ከተማዋ የተሳካላት አንድ ትልቅ ነገር ቢኖር የቆሻሻ አወጋገድ ባህሏን አስተካክላ፤ ክምር ቆሻሻዎች ይገኙባቸው የነበሩ ስፍራዎችን አረንጓዴ መናፈሻ ማድረጓ ነው።
«ዳያስፖራ መናፈሻ» ይባላል ያሉንና የጎበኘነው ስፍራ፤ የበለጠ ሳቢና የሚጎበኝ እንዲሆን ሊሠራበት የሚገባ ብዙ ነገር ቢኖርም፤ ለውጡ ግን በጉልህ ይታይበታል። ስፍራው ከዋናው መንገድ በተቀራራቢ የሚታይ ሲሆን፤ ከየትኛውም ርቀት ዓይን ውስጥ በገባበት አቅጣጫ ጎብኙኝ፣ ተናፈሱብኝ የሚል ዓይነት ነው። ታድያ በዚህ ስፍራ አነስ አድርገን ስናይ በከተማዋ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ባህል ከፍ ሲል እንደ አገር በተቻለ መጠን ኢትዮጵያን የሚገልጹ ለምሳሌ ቅርጻ ቅርጾችን በማኖር ሌላ ገቢ መፍጠር ይቻላል። ከጸደቁ አይቀር አይደል ብሂሉ?
የኮብልስቶን ንጣፍ መንገዶቿ ሰፋፊ ናቸው። የእግረኛ መንገዶቿ ጠበብ ስለሚሉ እግረኛና ባለሶስት እግሮቹ ባጃጆች እኩል የሚንቀሳቀሱባቸውም ናቸው። ምንም እንኳን «አዎን ይህም ችግር ነው» ብሎ የነገረን ባይኖርም፤ የውሃ ጉዳይ ነዋሪውን ማስቸገሩ አልቀረም። ከዛም ባሻገር በሥራ ፈጠራ ዙሪያ አሁንም ከከተማዋና ከከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቅ ሥራ አለ። በእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ላይ ታድያ የከተማዋ ከንቲባ «በስፋት እየሠራንበት ነው» የሚል መልስ ሰጥተዋል።
ባህልን ለማስተዋወቅና ለማሳየት አስቀድሞ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል። አገራችን ከምንም በላይ የቱሪዝም ዘርፉን ገቢ ማስገኛ አድርጋ የመሥራት አማራጭ የሌለው ሰፊ ዕድል አላት። ለሻሸመኔም ከዛ የተለየ አይደለም፤ አለኝ ያለችውን ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ሀብት፤ የገዳውን ሥርዓትና የሲንቄ እናቶችን አቅም የገቢ ምንጭ ልታደርገው ትችላለች። ከዛ በላይ ግን አገሩን በሚገባ የሚያውቅ ዜጋን በመፍጠር ትርፋማ ልትሆን ይገባታል።
በዚህ ላብቃ፤ የባህል ሀብትን መንዝሮ መጠቀም ያለው ዋጋ እስካልተገለጠልን፤ ደግሞም እነዚህን ሀብቶች እንደው አሉን ብሎ ከማሞገስ በዘለለ፤ ተንከባክበን መያዝ እስካላወቅንበት ድረስ ስኬታማ የመሆናችን ነገር አይታሰብም። ኢትዮጵያን እየወደድን ከልባችን እንዳኖርናት ሁሉ፤ የእርሷ ብቻ የሆኑ መገለጫዎቿን እንድናውቅና እንድንጠብቅ ያስፈልጋል። በእንግዳ ተቀባይነት ባህል «እንኳን ደህና መጣችሁ» ያለችንን ሻሸመኔ፤ በሌላ የሕይወት አጋጣሚ እስክናገኛት ድረስ «ገለቶማ» ብለን አመስግነን ወጣን፤ ነጋቲ።

ሊድያ ተስፋዬ

የመጽሐፍ አዟሪዎች ህይወት- በክረምት

 

አንድ ዕለት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ካፌ ውስጥ ተቀምጠን አንድ መጽሐፍ አዟሪ መጣ፡፡ ጓደኛዬ አንባቢ ስለነበር ብዙ መጻሕፍትንና የብዙ ደራሲዎችን ሥራ ያውቃል፡፡ ወደካፌው የመጣውን መጽሐፍ አዟሪ ጠራው፡፡ ልጁ ወደተቀመጥንበት መጣ፡፡ የያዛቸውን መጻሕፍት ቃኘት ቃኘት አደረግን፡፡ አዳዲስ የወጡ ብሄር ተኮርና የፖለቲካ መጻሕፍት ይበዛሉ፡፡ ጓደኛዬ የሚፈልገውን መጽሐፍ አዟሪው አልያዘም ነበርና ‹‹የእገሌን ነበር የምፈልገው›› አለው፡፡ ልጁም ያ መጽሐፍ አሁን ገበያ ላይ እንደሌለ ተናገረ፡፡ ጓደኛዬና ልጁ በተለይም ገበያ ላይ ስለማይገኙ መጻሕፍት ብዙ አወሩ፡፡
እዚህ ላይ ነበር እኔ ግርምት የፈጠረብኝ፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ልክ ያልሆነ ግምት ነበረኝ፡፡ ያ ምስኪን ልጅ ያንን ሁሉ ታሪክና የደራሲዎች ስም ይይዛል ብየ አልገመትኩም፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፍ አዟሪ መሆኑ ያነባል ብሎ ለመገመት ቢያስችልም፤ በእንደዚያ አይነት የሩጫ ሥራ ግን ብዙ ያነባል የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ ምናልባት መጽሐፍት አዟሪ እኔ እንደማስበው ሳይሆን የተመቻቸ ጊዜና ቦታ ያለው ይሆን ብየም አሰብኩ፡፡ ከዚህ ሁሉ ግምት ግን ለምን የመጻሕፍት አዟሪዎችን ሕይወት አልቃኝም ብዬም አሰብኩ፡፡ በዛሬው የ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› አምዳችን የተለያዩ መጻሕፍት አዟሪዎችን ሕይወት ላስቃኛችሁ ወደድኩ። መልካም ንባብ፡፡

መኮንን ሲሳይ
መኮንን ሲሳይ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በግሸን አምባ አካባቢ ነው፡፡ ገና የ13 ዓመት ልጅ እያለ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ አዲስ አበባ የመጣው የፈለጉትን ሥራ ሠርቶ የፈለጉትን አይነት የከተማ ኑሮ የሚኖር መስሎት ነበር፡፡ እንደመጣ ዘመድ ጋ ቢያርፍም ኑሮው ምቹ አልሆነለትም፡፡ ገና በልጅነት ዕድሜው የቀን ሥራ እየሠራ ራሱን በራሱ የማስተማር ኃላፊነትን አምኖ ተቀበለ፡፡ ያሰበውን ኃላፊነትም ተገበረው፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ቤት ተከራየና ትምህርት ቤት ገባ፡፡
መኮንን ትምህርት ሲጀምር ሥራ እየሠራ ነው፡፡ በኋላም መጽሐፍ የማዞር ሥራ ከትምህርቱ ጋር አብሮ የሚሄድ ሆኖ አገኘው፡፡ ጠዋት መጽሐፍ ያዞራል፣ ማታ ይማራል፣ ቅዳሜና እሁድ እና ትምህርት በማይኖርባቸው ቀናትም መጽሐፍ ያዞራል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ እራሱን በራሱ በማስተማር እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ተምሯል፡፡ ሆኖም ግን 10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ወደ መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚያስገባ ውጤት አልመጣለትም፡፡ ወደግል ኮሌጅ ገብቶ ለመማርም አቅም የሚፈቅድለት አልሆነም፤ ምክንያቱም ይህኛው ትምህርት እየሠሩ ለመማር ከበድ ማለቱ አልቀረም፡፡
መኮንን ገና በልጅነቱ ጀምሮት የነበረውን የመጽሐፍ አዟሪነት ሥራ አሁን ሥራዬ ብሎ ይዞታል፡፡ የነበሩትን የመጽሕፍት ቁጥር በመጨመርና በሙሉ ጊዜ በመሥራት አሁን የሚተዳደረው በዚሁ ሥራ ነው፡፡
መኮንን ከ10ኛ ክፍል በኋላ ይህንን ሥራ በሙሉ ቀን ሥራነት ከያዘው ሦስት ዓመት ሆኖታል፡፡ ስራው ከበርካታ መጻሕፍት፣ ደራሲዎችና አንባቢዎች ጋር አስተዋውቆታል፡፡ ይህ የሆነው ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ነው፡፡ ቀደም ሲል የመጻሕፍት አዟሪዎችን እንደ ህገ ወጥ ንግድ በማየት ይከለከሉ ነበር፡፡ ጫት፣ ሲጋራና የአልኮል መጠጥ በአደባባይ በሚሸጥበት አዲስ አበባ መጽሐፍ ማዞር እንደጥፋት መታየቱ መኮንን ያሳዝነው ነበር፡፡ በርካታ መጻሕፍትንም ተቀምቷል፡፡ ከደንብ አስከባሪዎች ጋር ድብብቆሽ መጫወት ሰልችቶት ተስፋ ቆርጦ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ደግነቱ ግን ይህ ችግር አሁን ላይ ተቀርፏል፡፡ በማንና እንዴት እንደተቀረፈ ባያውቅም አሁን ላይ አንድ ቦታ ሆኖ መሸጥ ባይቻልም፤ የትኛውም ቦታ ላይ ሆኖ መጽሐፍ ማዞር ይቻላል።
የመጽሐፍ አዟሪነት ሥራ በክረምት ወቅት ሁለት ገጽታ አለው፡፡ ዝናብ በተደጋጋሚ የሚዘንብበት ስለሆነ ድንገት እየመጣ ያስቸግራል፡፡ ይህ ሲሆን የመጽሐፍ ሽያጭ ያለው ደግሞ በክረምት ወቅት ነው፡፡ በተለይም በርከት ያሉ መጻሕፍትን ይዞ ለመንቀሳቀስ ያስቸግራል፤ በዚያ ላይ ሰው የሚፈልገው መጽሐፍ ላይያዝ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቀጠሮ በማምጣት ከደንበኛ ጋር መገናኘት ይኖራል፡፡ ይህ የሚሆነው ታዲያ ያ መጽሐፍ ገበያ ላይ በብዛት የሌለ ከሆነ እንጂ ካለ ደንበኛው ከሌላ ቦታ ስለሚገዛ ሁልጊዜ በቀጠሯቸው መገናኘት አይቻልም፡፡
የመጻሕፍት አዟሪዎች በሱቅ ውስጥ ሆነው እንዲሸጡ ይደረጉ እንጂ ለዚህ የተመቻቸ ሁኔታ ግን አልነበረም፡፡ በራሳቸው ሱቅ ተከራይተው ካልሆነ ጥቃቅንና አነስተኛ አደራጆች በመጽሐፍ በኩል ያዘጋጁት ቦታ የለም፡፡ እነመኮንን ይህን ተደራጅተው ለመሥራት ቢጠይቁም አደራጆቹ የመጽሐፍ ሽያጭ ጉዳዩ አዲስ የሆነባቸው ይመስላል፤ እንዲያውም የመጽሐፍ ሽያጩን ትተው በሌላ ነገር እንዲደራጁ ነው የሚመክሯቸው፡፡ በዚህ በኩል ምንም አላገዟቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ጎዳና ላይ ያለው ክልከላ መቅረቱ በራሱ እንደ ጥሩ አጋጣሚ እያዩት ነው፡፡
መኮንን አሁን ላይ ያለው ሀሳብ ከመጽሐፍ አዟሪነት ወጥቶ የራሱን ሱቅ ተከራይቶ ትልቅ የመጻህፍት መደብር መክፈት ነው፡፡ እያነበበም መጻፍ ይፈልጋል፡፡ የሚያነበውም ዓለማዊና መንፈሳዊ መጻሕፍት ስለሆነ የእውቀት አድማሱን አስፍቶለታል፡፡ ብዙ የማያውቃቸውን የአገሩን ታሪኮች፣ ባህሎችና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለማወቅ አስችሎታል፡፡ በተለይም በወጣቶች ላይ ከሚታዩ አጓጉል የሱስ ልማዶች እንዳይጠቃ አድርጎታል፡፡ ብዙ ጊዜ ውጤት ያልመጣላቸው ተማሪዎች ወደ ሱስ ይገባሉ፤ መኮንን ግን የሚያነበው ነገር ስላነጸው ወደምንም አይነት ሱስ እንዳይነካካ አድርጎታል፡፡ ወጣቱ በቀጣይም አንባቢ ብቻ ሳይሆን ጸሐፊ የመሆን ምኞት አለው፡፡
ብርሃኑ ማንደፍሮ
ብርሃኑ ማንደፍሮ ከጎጃም ገጠር አካባቢ ነው የመጣው፡፡ ዕድሜው ገና ከ18 ዓመት አልደፈነም፡፡ አራት ኪሎ አካባቢ መንገድ ዳር ካለ አንድ ጥግ መጻሕፍቱን አስደግፎ ቆሟል፡፡ ከያዛቸው መጻሕፍት አየት አየት አድርጌ ጭውውት ጀመርን፡፡
ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የጉልበት ሥራ እየሠራ ከተማ ለመኖር ነበር አመጣጡ፡፡ እንደመጣም በሁሉም ልጆች ላይ የሚታየው ችግር ነው ያጋጠመው፤ አዲስ አበባ ገጠር ሆነው እንደሚያስቡት ምቹ አልሆነለትም፡፡ የነበረው አማራጭ አንድ ብቻ ሆነ፡፡ ይሄውም ከልጆች እንደሚያየው ሎተሪ ማዞር፡፡ ሎተሪ በማዞርም ነገሮች እንደታሰበው አልሆኑለትም፡፡ የሎተሪ ማዞር ሥራው ከእጅ ወደ አፍ የሚሆን ገቢ አላስገኘለትም፡፡ ከጓደኞቹ ጋር በጋራ ሆነው ቤት ተከራይተው ቢኖሩም የጋራውን ክፍያ እንኳን ለመክፈል አላስቻለውም፡፡ ከሚያገኝበት ቀን የማያገኝበት ቀን ይበልጣል፡፡፡ በዚህ ሥራ ለአንድ ዓመት ያህል ቆይቷል፡፡
ብርሃኑ ዓይኑ የመጽሐፍ አዟሪዎች ላይ አረፈ፡፡ ምናልባትም ከሎተሪ ማዞር መጽሐፍ ማዞር የተሻለ መስሎ ታየው፡፡ ይህኛው ሀሳቡ ትንሽ የተሻለ ሆኖ አገኘው፡፡ በትንሽ መጻሕፍት ሥራውን ጀመረ፡፡ አሁን ገና ሁለት ወሩ ነው፡፡ በዚህ ሁለት ወር ውስጥ የመጽሐፍ አዟሪነት ሥራ ያዋጣል አያዋጣም ብሎ መናገር ቢከብደውም ያሉትን ችግሮች ግን የሥራው ሳይሆን የራሱ መስለው ነው የታዩት፡፡ የመጽሐፍ አዟሪነት ሥራ የማግባባት ክህሎት ይጠይቃል፡፡ ብርሃኑ ግን ለብዙ መጻሕፍትም ሆነ ደራሲዎች ስም አዲስ ነው፡፡ የትምህርት ደረጃውም ከ4ኛ ክፍል አላለፈም፡፡ ማንበብና መጻፍ ይቻል እንጂ በንባብ የታገዘ ስላልሆነ፣ ለዚህ ሥራም ገና አዲስ ስለሆነ ስለመጻሕፍቱ ለደንበኞቹ አያብራራም፡፡ ደንበኞቹ ራሳቸው የሚያውቁትን መጽሐፍ መርጠው ይገዙታል፡፡
የመጽሐፍ አዟሪነት ሥራ ማሳመንና ስለመጽሐፉ ማግባባት እንደሚያስፈልግ ያምናል፡፡ በየካፌው፣ በየትራንስፖርት ቦታውና ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ሁሉ እየሄዱ ማግባባት አዳዲስ የወጡ መጻሕፍትን ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፤ አሁን አሁን ግን በሂደት ነገሮችን እየለመዳቸው ነው፡፡ መጻሕፍትንም ማንበብ እየተለማመደ ነው፡፡ አዳዲስ የሚጡ መጻሕፍትን ከተዋወቃቸው ጓደኞቹ ይሰማል፤ ያመጣል፡፡ ይሁን እንጂ የተረጋጋ ጊዜ የለውም፡፡ የሚያነበው ለንባብ በሚሰጠው ጊዜና ቦታ ሳይሆን እንደመተከዣ ብቻ ነው፡፡ የተከራየው ከጓደኞቹ ጋር ስለሆነ ቤት ውስጥ ለማንበብ አይመችውም፡፡ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ የሚከራዩት ቤት ቋሚ ሳይሆን ለ15 ቀን ለአንድ ወር እየተባለ ነው፡፡ አንዳንድ ሰሞን ደግሞ ይባስ ብሎ ለዕለት ለዕለት የሚከራዩበት ጊዜም አለ፡፡
አሁን ብርሃኑን ፈተና የሆነበት የቤት ጉዳይ ነው፡፡ በርካታ መጻሕፍትን ይዞ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ በቀላሉ ለመንቀሳቀስ እንዲያመቸው በጥቂቱ ነው የሚይዘው፡፡ አንድ ዕለት ሁለት ሦስት መጻሕፍት ሸጦ ከሆነ የሚተካውም በተሸጡት ልክ ብቻ ነው፡፡ ብርሃኑ አሁን አሁን ሥራውን በትንሹም ቢሆን እየለመደውና እያነበበ የመጣ ቢሆንም ለጊዜው በዚህ ሥራ የመቀጠል ምኞት የለውም፤ አሁን እየኖረበት ያለው የመጽሐፍ አዟሪነት ሥራ ሎተሪ ይሠራ ከነበረው የተሻለ ቢሆንም በቋሚነት የሚያስቀጥል አይደለም፡፡ የመጽሐፍ አዟሪነት ሥራ ለብርሃኑ ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡
አገሬ ተናኜ
አገሬ ተናኜ ትባላለች፡፡ እንደሌሎቹ ልጆች ሁሉ እርሷም ትምህርቷን አቋርጣ ከክፍለሀገር ወደ አዲስ አበባ የመጣች ናት፡፡ የአዲስ አበባ ሕይወት እሷ ገምታው በነበረው ልክ አይደለም፡፡ ገና እንደመጣች የተለያዩ ሥራዎችን የሞከረች ቢሆንም መጽሐፍ ማዞርን ግን ለጊዜው የተሻለ ሆኖ አግኝታዋለች፡፡ የአገሬን ከሌሎች ለየት የሚያደርጋት መፅሀፍ ይዛ ባለመዞሯና አንድ ቦታ ይዛ መቀመጧ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አራት ኪሎ ከሚገኘው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠገብ ትቀመጣለች፡፡ በመጀመሪያ ይዞ በመንቀሳቀስና በአዟሪነት የጀመረች ቢሆንም አሁን ላይ ደግሞ አንድ ቦታ ይዞ በመቀመጥ ትሸጣለች፡፡
በዚህ ሥራ ለአንድ ዓመት ያህል ቆይታለች፡፡ ሆኖም ግን ሥራውን የምትሠራው ‹‹ቁጭ ከማለት›› በሚል ስሜት ነው፡፡ ሴት እንደመሆኗ ደግሞ የሚያጋጥሟት አስቸጋሪ ነገሮች አሉ፡፡ መጻሕፍቱን ይዞ በየካፌውና ህዝብ በየተሰበሰበባቸው ቦታዎች ስትሄድ ትንኮሳዎችና ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ስለሚያጋጥሟት አልተመቻትም፡፡ የያዘችውን መጽሐፍ ከማየት ይልቅ ሴትነቷን ነው የሚያዩት፤ ሴት ሆና እንዲህ አይነት ሥራ መሥራቷ ነው የሚገርማቸው፡፡ በዚያ ላይ እንደወንዶች ልጆች ማግባባትና መጽሐፉን እያነሱ ማሳየት ትፈራለች፡፡ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ የታዘበችው ነገር ሰው የሚያስፈልገውን ነገር እንኳን አግባብተው ካልነገሩት አይገዛም፡፡
አገሬ ‹‹ግዙ!›› እያለች መለፍለፍ ባትወድም ግን አንድ ነገር ታደርጋለች፡፡ አንድ ቦታ ይዛ የምትቀመጥ እንደመሆኗም መጽሐፉ አጠገብ ደርሰው ቆም ሲሉ ‹‹የማንን መጽሐፍ ፈልጋችሁ ነው?›› በማለት ትጠይቃቸዋለች፡፡ የሷ ብቃት ደግሞ መጻሕፍትን ታነባለች፡፡ ስለያዘቻቸው መጻሕፍት ይዘት መናገር ትችላለች፡፡ የምትናገረው ከጠየቋት ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ እያነሱ ሲያገላብጡ ስለመጽሐፉ ይዘትና ጭብጥ ትነግራቸዋለች፡፡
በተለይም ደግሞ ገና ማንበብ ለሚጀምሩ ሰዎች በሚገባ ታብራራላቸዋለች፡፡ አገሬ በዚህ ሥራዋ አንድ በጣም የምትደሰትበት ነገር አለ፡፡ ብዙ ወጣቶችን እንዲያነቡ አድርጋለች፡፡ ማንበብ ያልጀመሩትን ሁሉ አስጀምራለች፡፡ ብዙዎችም እሷ ማንበብ ያስጀመረቻቸው ወጣቶች እያመሰገኗት አሁን አሁን መጽሐፍ ሊገዟት ይመጣሉ፡፡ መጽሐፍ በምትሸጥበት ቦታ ብቻ ሳይሆን በምትኖርበት አካባቢም ሆነ በየትኛውም አጋጣሚ የምታውቃቸውን ታስነብባለች፡፡ በምትሰራበት ቦታም ቢሆን አንዳንዶች ‹‹እኔ አንብቤ አላውቅም፣ ምን እንዳነብ ትመክሪኛለሽ›› እያሉ ይጠይቋታል፡፡ እሷም እንደየ ባህሪያቸው ትሰጣቸዋለች፡፡ በተለይም ጀማሪ አንባቢዎች አንብበው የወደዱትን መጽሐፍ እንደ ምሳሌ ትይዘዋለች፤ ለሌሎችም ትሰጣቸዋለች፡፡ ታሪክ ለሚወዱ ታሪክ፣ ልቦለድ ለሚወዱ ልቦለድ ትሰጣቸዋለች፡፡ ሥራ ላይ እያለች ባገኘችው አጋጣሚ ቤት ስትገባ ታነባለች፡፡
አገሬ የግሏን ሥራ ለመሥራት ወይም ሌላ የተሻለ ሥራ እስከምታገኝ እንጂ በዚህ ሥራ የመቀጠል ፍላጎት የላትም፡፡ በዚህ ሥራ ብቻ መተዳደር ይቻላል ብላም አታምንም፡፡ መጻሕፍት የሚሸጡት የክረምት ወራትን ጠብቀውና አንድ ሰሞን ደግሞ የፖለቲካ መጻሕፍት ከወጡ ነው ገበያው የሚደራው፡፡ ከዚያ ውጪ አልፎ አልፎ የሚሸጥን የመጽሐፍ ማዞር ሥራ ተማምኖ መኖር እንደማይቻል ትናገራለች፡፡ አብዛኛው አንባቢ ደግሞ የሚፈልገው የፖለቲካ መጽሐፍና ታዋቂ ሰዎች ሲጽፉ ነው፡፡ እነርሱን ብቻ እየጠበቁ መኖር ይከብዳል፡፡ በአንድ ቀን ብዙ ተሸጠ ከተባለ 10 መጻሕፍት ነው፡፡ አንዳንድ ቀን ደግሞ ጭራሽ የማይሸጥበትም ይኖራል፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ የሚያስቸግራት በክረምት ወቅት ነው። ዝናብ ሲዘንብ መጽሐፍቱን መሸፈን ከባሰም ይዞ መጠለያ መፈለግ ሥራውን አሰልች አድርጎባታል። ቢሆንም ሌላ አማራጭ የላትምና ከዝናብ ጋ መሯሯጡን እየለመደችው መጥታለች።
የመጽሐፍ ሽያጭ ሥራ በቂ ማስተዳደሪያ ባይሆንም ከመስተንግዶና ሌሎች ሥራዎች የተሻለ ሆኖ አግኝታዋለች፡፡ ብትፈልግ ኖሮ ከሰው ቤት መሥራትም ይሁን መስተንግዶን ትችል ነበር፤ መጽሐፍ ማዞርን መርጣው ነው እየሠራችው ያለች፡፡ ይህ ሥራ ለህብረተሰቡ ተደራቢ ጥቅምም አለው፡፡ እንደመስ ንግዶ ባሉ ሥራዎች ውስጥ ራስን ለሱስ ማቅረብ እንጂ አዕምሮን መገንባት እንደማይቻል ታምናለች፡፡ የመጽሐፍ መሸጥ ሥራ በገንዘብ የማይተመነውን እውቀት እየሰጣት ነው፡፡ ማወቅ ብቻም ሳይሆን እያሳወቀች ነው፡፡ በዚህም የህሊና ደስታ ይሰማታል፡፡
ቀረብህ ስለሺ
ወጣት ቀረብህ ስለሺ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ከመጽሐፍ ማዞር ሥራው በፊት ሌሎች ሥራዎችን የሞከረ ቢሆንም ከደንብ አስከባሪዎች ጋር ያለው መሯሯጥ አሰልችቶታል፡፡ መጽሐፍ ማዞሩ ግን ነጻነት ያለው ሥራ ሆኖለታል፡፡፡ ራሱን ለመቻልም ቢሆን ይህኛውን ሥራ ነው የተሻለ ሆኖ ያገኘው፤ ያም ሆኖ ግን በዚህ ሥራ መቀጠል የቀረብህ ዘላቂ ምኞት አይደለም፡፡ የቤት ኪራይ ከፍሎ የዕለት ጉርሱን ችሎ ለዚሁ ሥራ መንቀሳቀሻ ያህል እንጂ ወደሌላ ትልቅ ሥራ ያሸጋግረኛል ብሎ አይተማመንበትም፡፡ መጽሐፍ ማዞር ፋሽኑ ያለፈበት ሥራም ይመስለዋል፡፡
ቀረብህ ለመጽሐፍ ማዞር ሥራ እንቅፋት መስሎ የሚታየው የማህበራዊ ድረ ገጾች ናቸው፡፡ ወጣቱ አሁን አሁን ሁሉንም ነገር ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ያገኛል፡፡ ይህ ደግሞ መጽሐፍ እንዳይገዛና እንዳያነብ አድርጎታል፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ መጽሐፍ ማዞርን አስተማማኝ ሥራ ማድረግ ይከብዳል፡፡ ይበልጥ የሚከብደው ግን ከክፍለ ሀገር ለመጡ ልጆችና ራሳቸውን በራሳቸው ለሚያስተዳድሩት ነው እንጂ ድጋፍ ለሚያገኙ አዋጪ ሊሆን ይችላል፡፡ ቤት ተከራይቶ ለሚኖር ግን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ቀረብህ የሚኖረው ብቻውን ቤት ተከራይቶ ነው፡፡ ከጓደኛ ጋር ሆኖ ለመከራየት አልፈለገም፡፡ ብዙ መጻሕፍት አሉት፡፡ መጻሕፍቱን እንደየተፈላጊነታቸው እየቀናነሰ ይዞ ይወጣል፡፡ ደንበኞቹ አምጣልን ሲሉትም የተባለውን ይዞ ያቀርባል፡፡ ለዚህ ለዚህ የሚመቸው ደግሞ ብቻውን ሲሆን ነው፡፡ የቤት ኪራይ እየከፈለ የዕለት ጉርሱን መቻል እንጂ ሥራውን አስፋፍቶ የመጽሐፍ መደብር ማድረግ ለጊዜው የሚቻል አልመሰለውም፡፡
ፀጋው ተመስገን
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ሰላሌ አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ በዚሁ አካባቢ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ተምሯል፡፡ የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ወደ መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚያስገባ አልነበረም፡፡ በፍቼ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ውስጥ ቢማርም አቋርጦት ወደ አዲስ አበባ መጥቷል፡፡ ራሱ ፀጋው እንደሚያምነው ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮም ቢሆን በትምህርት ጥሩ ውጤት አምጥቶ አያውቅም፡፡ የቤተሰብ አቅም ውስንነት ስለነበረበት ሌላ ሥራ መሥራትም አላሰበም፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ ውጣ ውረድ አጋጥሞታል፡፡ በተለይም በአዲሱ ገበያና ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ የማያውቀው የሀብታም ግቢ የለም፡፡ የግቢ ሳር ያጭዳል፣ ተክል ይከረክማል፣ የተቆረጠ ዛፍ ያነሳል፤ በአጠቃላይ ያሠሩትን የቀን ሥራ ሁሉ ይሠራ ነበር፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ አዲስ አበባ ውስጥ ለአራት ዓመታት ኖሯል፡፡
ፀጋው ለአራት ዓመታት ያህል በቀን ሥራም በምንም እያለ ኑሮን ሲገፋ ቆይቶ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በኮንትራት ሥራ ተቀጠረ፡፡ በዚሁ ሥራ ኮንትራቱ እስከሚያልቅም መቆየት አልቻለም፡፡ በብዙ ተቋማት ውስጥ ገባ ወጣ እያለ ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ውጣ ውረዶች ውስጥ ፀጋው አንድ ባህሪ ነበረው፡፡ መጻሕፍት ያነባል፤ የሚያነባቸው መጻሕፍት በብዛት የስነ ልቦና መጻሕፍት ናቸው፤ አልፎ አልፎም የታሪክ መጻሕፍትን ያነባል፡፡ የስነ ልቦናና ምክር አዘል መጻሕፍት ግን ሁሌም ከእጁ አይጠፋም፡፡
ፀጋው ይህ የማንበብ ልምዱ ነው ከብዙ የመጻሕፍት መደብሮች ጋር ያስተዋወቀው፡፡ ብዙ ደንበኞች አሉት፡፡ ይህ ደንበኝነት ታዲያ በሻጭና ገዥነት በአዋሽና ተዋሽነት ብቻ አልተገደበም፡፡ ፀጋው ከልጆቹ እያመጣ መጽሐፍ አዟሪ ሆነ፡፡ መጻሕፍቱን ከባለመደብሮች ሲያመጣ እንደየመጽሐፉ ዋጋ በመቶኛ ነው የሚካፈሉት፡፡ ይህም እንደየመጽሐፉ ብቻ ሳይሆን እንደየመደብሮችም ይለያያል፡፡ አንዳንድ መጻሕፍትን እየገዛ የሚሸጥ ሲሆን፤ አብዛኛውን ጊዜ ግን ከአከፋፋዮችና ከመጻሕፍት መደብር ጋር በመስማማት በመቶኛ ተሳስበው ነው የሚሸጠው፡፡
ፀጋው ከቀን ሥራ ጀምሮ ብዙ ሥራዎችን ሞክሯል፡፡ ተቀጥሮ እንደመሥራት ባይሆንም ከሌሎች የቀን ሥራዎች ግን መጽሐፍ ማዟር የተሻለ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ በተለይም አዳዲስ መጻሕፍት ሲወጡ ከመሃል ከተማ ወጣ በማለት እየሄደ ይሸጣል፡፡ ለደንበኞቹም በቀጠሮ መጽሐፍ ያመጣል፡፡ በመጽሐፍ ማዞር ሥራው ፈጣን ነው፤ ጥሩ ገበያም ያገኝበታል፤ የፀጋው ትልቁ ችግሩ ግን የመቆጠብ ልምድ የለውም፡፡ ከእርሱ በታች ገቢ ከሚያገኙ ጓደኞቹ ይበደራል፡፡ ‹‹ይቺ ተቆጥባ ምን ልትሠራ ነው›› የሚለው መጥፎ ልማድ ሆኖበታል፡፡ የተሻለ ገቢ በሚያገኝበት ጊዜም ዝቅተኛ ገቢ በሚያገኝበት ጊዜም ‹‹ሕይወት ተመሳሳይ ናት›› የሚል ፍልስፍና አለው፡፡ ፀጋው ለብቻው ቤት ተከራይቶ ቢኖርም አሁንም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ላይ ነው ያለው፡፡ በተለይ ደግሞ በክረምት መጽሐፍ ማዞር በጣም ከባድ ሆኖበታል። ብዙ መጽሐፎቹ በዝናብ እየተበላሹበት እንዳያከስሩት ሰግቷል። ኑሮ ካሉት እንዲሉ ሆኖበት ሥራው ህይወቱን እንደማይቀይረው ቢያውቅም አማራጭ በማጣቱ ዛሬም ምናልባትም ወደፊትም በመጽሐፍ አዟሪነቱ እንደሚቀጥል ያስባል።
የአምስቱም የመጽሐፍ አዟሪዎች ሕይወት በትንሹ ልዩነት ቢኖረውም ተመሳሳይነቱ ይጎላል፡፡ ሁሉም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚኖሩ ናቸው፡፡ አንደኛው ወጣት (መኮንን ሲሳይ) ብቻ የመጻሕፍት መደብር የመክፈትና ራሱም ጸሐፊ የመሆን ምኞት ሲኖረው አራቱ ግን የተሻለ ነገር ፍለጋ ላይ ናቸው፡፡ ይህ እንዲሆን ያደረጋቸው የኑሮ ጉዳይ እንጂ ሁሉም የመጽሐፍ አዟሪነት ሥራ ራስን ለማነጽ እንደሚጠቅም ያውቃሉ፡፡ ወደእዚህ ሥራ ከገቡ በኋላ ማንበብ የጀመሩም አሉ፡፡ ማንበብ መጀመር ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ወደንባብ እንዲሳቡ ያደረጉም አሉ፡፡
ሌላው የእነዚህ ወጣቶች የጋራ ባህሪ የሆነው ደግሞ ሁሉም ከክፍለ ሀገር የመጡ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የመጽሐፍ ማዞር ሥራን የጀመሩት መጽሐፍ ለሰው ልጅ ከፍተኛ ዋጋ ያለውና ተፈላጊ ነው በሚል ሳይሆን የዕለት ጉርስን ለመሸፈን ብለው ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳውም በአገሪቱ የመጽሐፍ ማዞር ሥራ አማራጭ የማጣት እንጂ እንደ ሥራ አለመታየቱ ነው፡፡ ከመጽሐፍ አዟሪዎቹ ህይወት እንደተረዳነውም ለዚህ ምክንያቱ ሰዎች መጽሐፍ የሚገዙት የስመጥር ሰዎችን ወይም የፖለቲካ መጻሕፍትን ብቻ መሆኑ ነው፡፡
በመዲናችን የመጽሐፍ አዟሪዎች ህይወት እንዲህ ነው፡፡ ከአንዱ ካፌ ወጥቶ ወደ አንዱ ካፌ፣ ከአንዱ ጎዳና ወደ አንዱ ጎዳና፣ የማይገዛው ሁሉ ሲያስቆም አውርዶ መበታተን ከዚያም እንደገና ማደራጀት፡፡ በተለይ በዚህ በክረምት ወራት ደግሞ ዝናብ በመጣ ቁጥር ወደ መጠለያ ፍለጋ መሯሯጥና በላስቲክ መሸፈን መዘርጋት፣ መጻሕፍት ከተበላሹና ከተሰረቁም መክሰር የመጽሐፍት የአዟሪዎቹ ሕይወት እንዲህ ነው፡፡

ዋለልኝ አየለ

Published in ማህበራዊ

በአንዲት አነስተኛ ከተማ የሚኖር አንደ ስስታም ባለፀጋ ሰው ነበር። ይህ ሰው በአካባቢው ካሉት ድሆች ጋር ሲነፃፀር እጅግ የገዘፈ ሀብት ነበረው። ይሁን እንጂ የሚኖረው ብቻውን ነው። ድሆችን ላለማየት የቤቱን ቅጥረ ግቢ በትልቅ ግምብ አጥር ነበር ያሰራው። የግቢው መግቢያ በርም እጅግ ግዙፍ በመሆኑ ከውስጥ ያለውን ነገር ማንም እንዳያይ አድርጎታል። ባለፀጋው ሰዎች የእርሱን ኑሮ እንዳያዩ ብቻም ሳይሆን እርሱም የእነርሱን ድህነት ላለማየት አብዝቶ ይጠነቀቅ ነበር።
ይህ በከተማዋ የታወቀ ባለፀጋ በአንድ ወቅት በዓል ይደርስና በግ ለመግዛት ወደ ገበያ ይሄዳል። በገበያው ከተደረደሩት በጎች መካከል ዓይኑ ያረፈበትን በግ ወደእርሱ ያስቀርብና መስባት አለመስባቱን ለማየት በጉን ሲጨብጥ ከበጉ ፀጉር ሥር የተደበቀች ትንሽ እሾህ ጣቱን ትወጋዋለች። የእሾኋ ህመም ብዙም ስላልጎዳው የመረጠውን በግ ገዝቶ ወደ ቤቱ ይሄዳል።
ሌሊት ላይ ጣቱ ውስጥ የተሰነቀረችው ትንሽ አሾህ መርዘኛ ነበረችና ልቡ እስኪጠፋ ታመዋለች። ህመሙ ሲጠናበት ወደ ሆስፒታል እንዳይሄድም እሾህ ወጋኝ ብሎ ገንዘብ ማውጣቱ ያበሳጨዋል። የነበረው አማራጭ እሾሁን የሚያወጣበት መርፌ መፈለግ ነበር። ይሁን እንጂ ሀብት በተትረፈረፈበት ግቢ ውስጥ ትንሿ መርፌ ልትገኝ አልቻለችም። ሌሊት በመሆኑ ወደ ሱቅ ሂዶ መግዛት አልቻለም። ህመሙ ሲጠናበት አማራጭ በማጣቱ ሊያያቸው ከሚፀየፋቸው ጎረቤቶቹ መርፌ ሊለምን ይወጣል። በሩን ከፍቶ ሲወጣ በአጋጣሚ እርሱም ሊያየው የሚፀየፈውና ከቤቱ አጥር ስር የወደቀውን ሰው ያገኛል።
በአጥሩ ስር የወደቀው የችግረኛ ባለፀጋውን ለመጀመሪያ ጊዜ በማየቱ ከአካባቢው ሊያባርረው እንደሆነ በማሰብ እሩጦ ለማምለጥ ሲንቀሳቀስ ባለፀጋው ሰው ያስቆመዋል። ያጋጠመውን ችግር ይነግረውና መርፌ እንዲያውሰው ይጠይቀዋል። ደሃው ሰው በደስታ መርፌውን አውጥቶ ይሰጠዋል። እሾሁንም ከጣቱ ላይ በማውጣት ከህመሙ ይገላግለዋል። በጣቱ ውስጥ የገባችው አሾህ መርዛማ በመሆኗ ትንሽ ቢቆይ ኖሮ ሊሞት እንደሚችልም ይነግረዋል።
ባለፀጋው ሰው በዚህ ጊዜ ነበር ወደ እራሱ መመልከት የጀመረው። ቤት ሙሉ ሀብትና ገንዘብ ቢኖርም እንደ ሰው ሊሆንለት እንደማይችልና ለሰው መድኃኒቱ ሰው መሆኑን ይረዳል። ያ የተፀየፈው ሰው የህይወቱ መድህን እንደሆነ ሲያስብ እራስ ወዳድነቱ ያበሳጨዋል። የናቃትና ቤት ውስጥ ፈልጎ ያጣት መርፌም በችግር ጊዜ አስፈላጊነቷ ምን ያህል እንደሆነ ይረዳል። ከዛን ዕለት ጀምሮ የወሰደው የመጀመሪያው እርምጃ ድሃ እንዳላይበት ብሎ የጋረደውን ግዙፍ አጥር ማፍረስ ነበር። አጥሩን ከማፍረስ ባለፈም በአካባቢው ሰዎች ጋር መልካም ጉርብትና በመፍጠር አብሮ በሰላም መኖር ነበር። አደረገውና በአካባቢው ህዝብ ዘንድ ተወዳጅና የችግር ጊዜ ደራሽ ሆነ።
ይሄን ታሪክ ስናስብ «ግምቡን እናፍርስ ድልድይ እንስራ» ወደሚለው ወቅታዊ እሳቤ ያደርሰናል። ይህ መሪ ሀሳብ ግዙፍ ዓላማ የያዘ ነው። በውጭ ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ለዘመናት ተጋርጦ የነበረውን የመጠላላት ግምብ ለማፍረስ ያለመ ነው። በተጨማሪም አሜሪካ የሚገኘውና በሀገር ውስጥ ያሉት የሲኖዶስ አባላት ለዓመታት ከልሏቸው የነበረውን ግምብ ለማፍረስና ሁለቱን የሚያቀራርብ ድልድይ ለመስራት የሚያስችል ነው። ይህ መልካም አሳቤ ይቅርታና አንድነትን የሚያጠናክር በመሆኑ የሁላችንም አጀንዳ ሊሆን ይገባል።
እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር ሲወያዩ የተናገሯትን አንድ ሃሳብ መዋስ ይቻላል። «የአሸናፊነትን አስተሳሰብ የሚያመጣው ጥበብ ነው። እናንተ ድልድይ መፍጠር አለባችሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰባበረ ብዙ ድልድይ አለ። የእያንዳንዱ ቤት መጠን ትንንሽ ሆኖ ግቢው ግን ትልልቅ አጥር ነው ያለው። በግንብ ሳይሆን በድልድይ ነው ሀብታም የሚኮነው። ድልድይ ያስፈልገናል፤ ግንቡን አፍርሶ ድልድዩን ለመገምባት ኪነጥበብ ሥራዋን ብትሠራ ጥሩ ነው» በርግጥም እራስን ከሌሎች ለመለየት የምንሰራው ግንብ ካልፈረሰ ሌሎችን ብሎም ራሳችንን ለማየት እንቸገራለን።
የቀደመ ታሪካችንን ከቃኘን ሊፈርስ የሚገባው ግንብ በየትኛውም ሙያ ላይ ተንስራፍቶ እንደሚገኝ በቀላሉ መረዳት እንችላለን። የኪነጥበብ ባለሙያዎችን አንድ የምታደርጋቸው ጥበብ ብትሆንም በውስጣቸው በርካታ ግምቦች ተሰርተው እርስ በርሳቸው ሲነቃቀፉ፣ በብሄር፣ በመንደር በጓደኝነት ተቧድነው በመሮጣቸው ጥበብ የምትጠብቅባቸውን ሚና በአግባቡ ሳይወጡ መቅረታችን ለመታዘብ እንችላለን።
በተለያዩ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ የመንግሥትም ሆነ የግል ሠራተኞችም ቢሆኑ ይህ እራስን በግምብ የማጠር አባዜ እንደተጠናወታቸው አይካድም። ኃላፊው ሠራተኞቹን የማያይበት የሃሳብ ግምብ ሲያጥር፤ ሠራተኞችም እርስ በርሳቸው በብሄር፣ በመንደርና በእምነት ወይም በሥራ ደረጃ ራሳቸውን በግንብ ይሸብባሉ። ይህ ደግሞ ለአንድ ዓላማ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ መተጋገዝና መደጋገፍ እንዳይኖር ያደርጋል። በመሆኑም ሁላችንም በተሰማራንበት የሙያ መስክ ሁሉ ሸብቦ የያዘንን የመለያየት ግንብ አፍርሰን የሚያገናኘንን ድልድል ልንገነባ ይገባል።

Published in ርዕሰ አንቀፅ

-የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስመረቁ

አዲስ አበባ፤- የሚወዷትን አገርና ህዝቧን ማገልገል መታደል መሆኑን አምነው ተመራቂዎች ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ታጥቀው ሊነሱ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 9 ሺ724 ተማሪዎችን ትናንትና በሚሌኒየም አዳራሽ አስመርቋል። በምረቃው ወቅት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እንደገለጹት፤ ተመራቂዎች የሚወዷትን አገርና ህዝቧን ማገልገል መታደል መሆኑን አምነው ለኢትዮጵያ እድገት ሊተጉ ይገባል። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ተስፋ የሆኑ ተመራቂዎች የዛሬዋን ኢትዮጵያ የተወሳሰቡ ችግሮች ከመፍታት አልፋው ለመጪው ትውልድ የተሻለችና የለማች አገር ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል።
እንደ ዶክተር ሙላቱ ገለጻ፤ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ተጠያቂነት እንዲጎለብት፣ ዴሞክራሲዋ የማይናወጥ እንዲሁም ታላቅነቷን ያስመለሰች ሀገር ገንብቶ ማስረከብ የተመራቂዎች የቤት ሥራ ነው። ይህን ዳር ለማድረስ አገሬ ከኔ ምን ትጠብቃለች ብላችሁ ራሳችሁን በመጠየቅ የአፍላ ጉልበትና ዕውቀት ባለቤት የሆናችሁ ወጣቶች ከፊት መሰለፍ ይኖርባችኋል ብለዋል።
መንግሥት የአገሪቷ አቅም በፈቀደ መጠን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብርሃን ለሆኑ ወጣቶች ብሩህ ተስፋን ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጣለሁ ያሉት ዶክተር ሙላቱ፣ የተመራቂዎች ቀጣይ ጊዜ የስኬትና የደስታ እንዲሆን ልባዊ ምኞታቸውን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ዶክተር ሙላቱ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከምርምር ሥራ ጋር ተያይዞ ያለበትን የበጀት እጥረት ለማቃለል ተገቢው እርምጃ መወሰድ እንዳለበት መንግሥት እንደሚገነዘብ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከአጠቃላይ ተመራቂዎቹ 6ሺ 44 በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር የተማሩ ሲሆኑ፤3 ሺ 407ቱ የሚሆኑት በማስትሬት ዲግሪ እና 273ቱ ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል። 3ሺ 680 ደግሞ በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከተመራቂዎቹ መካከል 2 ሺ 746 ሴቶች ናቸው።
በተያያዘ ዜና የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1ሺ460 ተማሪዎች ትናንት አስመርቋል። በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ እንደገለጹት፤ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ23 ዓመታት ጉዞው ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቆ ለአገር አስረክቧል። በዘንድሮው ዓመትም በተለያየ የትምህርት ዘርፍ 1ሺህ 460 ተማሪዎችን አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በፒ.ኤች.ዲ2፣ በማስተርስ ዲግሪ 997 እና በመጀመሪያ ዲግሪ 461 ተማሪዎችን ሲሆን፤ የዕለቱ የክብር እንግዳ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዳሙ አያና ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጎንደር፦ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 7ሺ187 ተማሪዎች አስመርቋል። ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሃግብሮች በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ 7ሺ187 ተማሪዎችን አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለቀጣይ ህይወታቸው መነሻ የሚሆናቸው እውቀትና ክህሎት መቅሰማቸውን ገልጸው፤ ባገኙት እውቀትና ክህሎት ለህዝቡ ትርጉም ያለው ሥራ እንዲሠሩ አሳስበዋል። ተመራቂዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት ተጠቅመው የሀገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ጅማ፦ የጅማ ዩኒቨርሲቲ በትናንትናው ዕለት ተማሪዎቹን አስመርቋል። ዩኒቨርሲቲው 41ሺ598 ተማሪዎችን በ194 ፕሮግራሞች በመደበኛ፣ በተከታታይና በርቀት ትምህርት መርሃ ግብሮች ሲሰጥ ቆይቷል። በመደበኛው፣ በማታውና በተከታታይና በርቀት መርሃ ግብር በግብርና፣ በህግና አስተዳደር፣ በጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት በመጀመሪያ ዲግሪ 3ሺ454 ተማሪዎችን አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በጥቅምት ወር 2ሺ129 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 179 የህክምና ዶክተሮች ያላቸው ናቸው። ሰኔ 23ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ 1ሺ156፣ በማስተርስ ስፔሻሊቲ ሰርተፍኬትና ፒ. ኤች.ዲ 626 ተማሪዎችን፣ በአጠቃላይ 2ሺ182 ተማሪዎችን አስመርቋል። ዩኒቨርሲቲው በአጠቃላይ በ2010 ዓ.ም 7 ሺህ 765 ተማሪዎችን ማስመረቅ ችሏል።
ዩኒቨርስቲው ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ የጅማ ዩኒቨርሲቲ በሰላምና ደህንነት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል። ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ ንግግር ያደረጉ ሲሆን «የሰጣችሁኝ ዕውቅና ለቀጣይ ጉዞ የሚያነሳሳና ስንቅ የሚሆን ነው» ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ በ2010በጀት ዓመት ሥልጠናቸውን አጠናቀው የተመዘኑና ከሥራ ጋር በመተሳሰር ላይ ያሉ 8ሺ930 ሠልጣኞችን ዛሬ በሚሌኒየም አዳራሽ ያስመርቃል።

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

 

 

 

 

 

Published in የሀገር ውስጥ

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና የደረጃዎች መዳቢ ኤጀንሲ በግንባታ የመስታወት አጠቃቀም ዙሪያ የተለያዩ አዋጆችንና መመሪያዎችን አውጥተዋል። ሆኖም ህጉን አሳውቆ ማስተግበር ላይ ክፍተት በመኖሩ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመስታወት ህንፃዎች በመገንባት ላይ ናቸው። 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የህንፃና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ደረጃና ቁጥጥርን በተመለከተ የጥር 2004 ዓ.ም የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ እንደተመላከተው፤ «የመስታወት ግድግዳ የሚገጠምላቸው ህንፃዎች የመስታወት ደረጃ ሊወጣለትና ለተጠቃሚውም ሆነ ለሌሎች አካላት ጉዳት የማያስከትል መሆን አለበት» ቢልም በናሙና በታዩት ሻሸመኔ፣ አዳማ፣ ሀዋሳና ባህር ዳር ከተሞች በህንፃዎች ላይ የሚገጠሙ መስታወቶች ከውበት አንፃር እንጂ፤ የአካባቢ ብክለትንም ሆነ ሙቀት የማይፈጥሩና አንፀባራቂ ያልሆኑ መሆናቸው በሚገባ የታየ እንዳልሆነ አረጋግጧል።
በባህር ዳር ከተማ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ በመስተዋት ላይ እስከ አሁን የተሠራ ሥራ እንደሌለ ኃላፊዎች እንደገለጹ መረጃው ያስነብባል። አብዛኛው ሰው የመስተዋት አይነት ለይቶ መጠቀም እንዳለበት የማያውቅ በመሆኑ የማሳወቅ ተግባራት ያልተሠራ መሆኑን ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ የመስታወቶች ጥራትን አስመልክቶ መመሪያ መውጣቱን ደግሞ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የገለጹት በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ኃይሌ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ ቁጥጥሩ የላላና መመሪያውም ክፍተት ያለበት ነው። ደረጃዎች መዳቢም ቢሆን ያወጣው መመሪያ የመስታወት አጠቃቀምን በተመለከተ አስገዳጅ አይደለም። በዚህም በህግ ትግበራው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸር እና ከተማ ፕላኒግ ዘርፍ መምህር የሆኑት አቶ እሸቱ ኢሳያስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚከብድ ይናገራሉ። ምክንያቱም ቀጥታ የውጭውን ቴክኖሎጂ ተቀብሎ ለመሥራት የአገሪቱ ሁኔታ አይፈቅድም። ለአብነት ፀሐይን መሰረት ያደረገ የህንፃ ግንባታ እንዲከናወን ህጉ ያስቀምጣል። ኢትዮጵያ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ፀሐይ የምታገኝ አገር ናት። በዚህም የመስታወት ግብዓቷ ብርሃን በጥቂቱ ሊያስገባና ፀሐይን በመጠኑ ሊያገኝ በሚችልበት መልኩ መሠራት ነበረበት፤ አፅዳቂዎቹ ግን ሙሉ ለሙሉ መስታወትን የመጠቀሙ ሁኔታ በዲዛይን ደረጃ ያፀድቁታል። ይህ ደግሞ ህጉና ነባራዊ ሁኔታው እንዳይጣጣም አድርጓል ይላሉ።
ትልቅና ሰፊ የሆነ መስኮት መጠቀም በአገሪቱ ደረጃ አይፈቀድም። በህግ ደረጃ ግን የፀሐይን አቅጣጫ ተከትሎ መሥራት እንደሚቻል ተቀምጧል። በመሆኑም ከዚህ ውጪ እውቀትን ተጠቅሞ መሥራት ህጉን አለመፈጸም ተደርጎ ስለሚወሰድ ዲዛይነሩም ሆነ ህንፃ አሠሪዎቹ ከዚህ የራቀ ተግባር ይከውናሉ። በዚህም ለህጉ ተግባራዊነት ፈታኝ ጉዳዮች እያጋጠሙ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ ህንፃዎች በአጠቃላይ መስታወታቸው ሲከፈት ዝናብና መሰል ነገሮችን ያስገባሉ የሚሉት አቶ እሸቱ፤ የመስታወት አጠቃቀምን በሚገባ አውቆ ያለመተግበር ከማንጸባረቁ ባሻገር በቤቱ ላይ የሚፈጥረው አደጋ ሰፊ ነው። ከአምስት እስከ ሰባት ዲግሪ ላቲቲውድ ላይ ያሉ ከተሞች ሰፋፊ መስታወት መጠቀም እንደሌለባቸው ህግ ወጥቷል። ነገር ግን ተግባራዊ አይደረግም። ለዚህ ደግሞ ሦስቱ አካላት ተጠያቂነቱን መውሰድ አለባቸው። የመጀመሪያው ዲዛይነሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው አጽዳቂውና ባለቤቱ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ባለሙያው በትክክለኛውና የመስታወት አጠቃቀሙን በተማረው መሰረት ሰርቶ ሲያቀርብ አይሆንም ባዩ ይበዛል። የተማረውን ወደጎን ትቶ ህጉን መሰረት አድርጎ ሲሠራ ደግሞ ባለቤቶች ጫና ያሳርፋሉ። በዚህም ህጉ በተግባር መተርጎም እንዳልቻለ ይገልጻሉ። «መንገዱ በዛ፣ መስኮቱ ሰፋ፣ መስታወቱ አንጸባራቂ ነው፤ የተጠቀምከው የመስታወት ጥራት ትክክል አይደለም» ብሎ የሚያስፈርስ አካል አለመኖሩ ህጉን ለማስከበር እንዲሁ ፈተና ሆኗል። በተጨማሪም አዋጁ በሁሉም አካላት በሚገባ አልታወቀም። በተለይ ዲዛይነሮች ይህንን መመሪያ ተገንዝበው እንዲሠሩና እንዲያማክሩ አለመሰራቱም ችግሩን እንዳጎላው ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የአርክቴክት ባለሙያ የሆኑት አማረ ሙላው እንደሚናገሩት፤ የመስታወት አጠቃቀምን በተመለከተ ችግሩ ሊነሳ የሚችለው ከዲዛይነሩ፣ ከባለቤቱና ከአጽዳቂው አካል ነው። ከ2009ዓ.ም በፊት በነበሩት የህንፃ ግንባታዎች ላይ ውበት የሚመጣው በመስታወት ብቻ ህንፃን ማስዋብ ነው ተብሎ ይታመን ነበር። በዚህም ብዙዎቹ ህንፃዎችን ሲሠሩ ዙሪያውን መስታወት ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ በትራፊክ አደጋ መከሰት ላይ ትልቅ የአደጋ ጥላ አጥልተው ቆይተዋል።
እንደ አርክቴክት አማረ ገለጻ፤ ህጉን ባለሙያው አያውቀውም። በዚህም በትምህርት ያገኘውን ብቻ ይተገብራል። ትምህርትን በተግባር ማዋል ደግሞ በአገሪቱ ደረጃ ብዙም ያልተለመደ በመሆኑ ሥራው የተለየ ቅርጽ ይኖረዋል። ትምህርቱንና ትግበራውን አጣጥሞ ለመጓዝ ሲሞከርም ህጉ ይገድባል። ስለሆነም ባለሙያው ከሚያገኘው ገንዘብ አኳያ ሥራዎችን እያየ እንዲከውን አድርጎታል። በተለይም በትግበራ ወቅት በባለቤቱ ፍላጎት ማስተካከሉ ህጉ ተፈጻሚነቱን እንዲያጣ አድርጎታል።
ሌላው ፈተና ቁጥጥሩ የለም በሚባል ደረጃ ላይ መቀመጡ እንደሆነ የሚገልጹት አርክቴክት አማረ፤ ዲዛይነ መጀመሪያ እንዲጸድቅ አድርጎ ከሠራው በኋላ ወደ ትግበራ ሲገባ ይቀይረዋል። ሲተገበር የሚያየው ስለሌለና ተጠያቂ ስለማይሆን ለማስፀደቅ ብቻ የሚሠራው ሥራ ተበራክቷል። ይህ ደግሞ ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ እንደማያስችል ይናገራሉ።
«አንድን ህንፃ መስታወት ብቻ በመጠቀም ዘመናዊ ነው ማለት አይቻልም። ይልቁንም መስታወቱን ከአገልግሎት አንጻር፣ ከሚሰጠው ጥቅም አኳያና ተጠቃሚው ወይም ባለቤቱ ምን ያህል ደንበኛን ይስብበታል የሚሉትን አይቶ መሥራት ሲቻል ነው ዘመናዊ ህንፃ ሊያስብል የሚችለው» የሚሉት አርክቴክት አማረ፤ በአገሪቱ ደረጃ ይህ እየተተገበረ አይደለም፤ በተቃራኒው መስታወቶች ጥቅም ላይ ሲውሉ ጥራታቸው ሳይሆን ዋጋቸው፤ የሚሰጡትን አገልግሎት ሳይሆን ጊዜ የማይወስዱ መሆናቸው ታይቶ እንደሚሠራበት ይገልጻሉ።
እንደ አርክቴክት አማረ ማብራሪያ፤ ተግባራዊነቱን በሚገባ እያየ መፍትሄ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ ህግ እንደሚጣስ የሚረዳ አካል አይኖርም። በዚህም እግረኛና አሽከርካሪዎች ላይ መስታወቶቹ በማንጸባረቃቸው የመኪና አደጋና የዓይን ህመም ችግሮች በስፋት እየተፈጠሩ ናቸው። ህጉ መስታወት ለግብዓትነት መጠቀም ሲያስፈልግ መሰረታዊ ነገሮች እንዲኖሩት ያዛል። ነገር ግን በዚህ ይቀጣ የሚለው ነገር ስለሌለው አያስቀጣም፤ አያስተምርም። በዚህም ችግሮች ተፈጥረዋል።
የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በግንቦት 2003 ዓ.ም ተዘጋጅቶ የጸደቀው የህንፃ መመሪያ የፊት መስታወት ዓይነት ወይንም ተመሳሳይ ውጤት እንዲኖረው የተደረገ መስታወት ለግንባታ የውጭ አካል አገልግሎት መጠቀም አይቻልም፤ የውጭ መስኮቶች አንፀባራቂነትም እንዲሁ የነዋሪውን ደህንነትና የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚያውክ መሆን የለበትም ይላል። በተመሳሳይ የግንባታ ግብአቶች ምን መምሰል አለባቸው የሚለው ሲታይ በአገሪቱ በተለያየ ጊዜ የወጣው የኮንስትራክሽን ፖሊሲና የቋሚ ህንጻ አዋጅ እንዲሁም ማስተግበሪያ መመሪያ ማንኛውም ለግንባታ የሚውል ግብዓት ደረጃውን የጠበቀና በደረጃዎች መዳቢ ኤጀንሲ እውቅናን ሊያገኝ እንደሚገባ ያስቀምጣል።
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ እስካሁን በአገር ደረጃ ደረጃውን የጠበቀና በደረጃዎች መዳቢ ኤጀንሲ እውቅና ያገኙ 13 አስገዳጅ ህግ ያላቸው የግንባታ ግብዓቶች ሲሆኑ፤ ከ30 በላይ የሆኑት ደግሞ አስገዳጅ ያልሆኑት ህጎች አላቸው። ከእነዚህ መካከልም የመስታወት ግብዓት አጠቃቀምን በተመለከተ በ2009ዓ.ም ስታንዳርድ ወጥቶለታል። ህጉ አንጸባራቂና ደህንነትን የሚያውክ እንዳይሆን ያስቀምጣል። ይሁን እንጂ ቁጥጥሩ የሳሳ በመሆኑ የተነሳ ተግባራዊ ሲሆን አይታይም። ደረጃውም አስገዳጅ ስላልሆነ አፈጻጸሙ የጎላ እንዳይሆን አድርጎታል።
ችግሩ በዚህ ከቀጠለ የትራፊክ አደጋውን ያባብሰዋል። የሰው ህይወትም ይቀጠፋል። ብርሃኑን የሚያጣ ዜጋ ይኖራል። አደጋውን አድራሾቹም ተጠያቂነት ይበዛባቸዋል። በዚያ አካባቢ የሚንቀሳቀስ ሰው ቦታውን በመጥላት አካባቢውን አይመርጠውም። በዚህም ቦታውን ተከራይቶ የሚሠራው ወይም ባለቤቱ ከቦታው የሚያገኘውን ጥቅም ያጣል። ህንፃው በራሱ ዝናብ የሚያስገባበት አጋጣሚም ስለሚፈጠር ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። 

 

ዜና ትንታኔ
ጽጌረዳጫ ጫንያለው

 

 

 

 

 

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ ልዩ ስብሰባ ረቂቅ አዋጆችንና ልዩ ልዩ ሹመቶችን መርምሮ አጽድቋል። 

የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅን አሻሽሎ አጽድቋል። የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ በከተማ አስተዳደሩ በ2010ዓ.ም ምርጫ መከናወን የነበረበት ቢሆንም በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።
የምክር ቤቱና የከተማው አስፈጻሚ አካላት የሥልጣን ጊዜ ከሰኔ ወር 2010ዓ.ም በኋላ ይጠናቀቃል። ሆኖም የምክር ቤቱ አባላትና የአስፈጻሚ አካላት ህጋዊነት ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ቀጣይ ምርጫ እስከሚከናወን ድረስ የምክር ቤቱና አስፈጻሚ አካላት ባሉበት ሥራዎችን እየሠሩ እንዲቆዩ አዋጁን ተሻሽሏል።
ከተማ አስተዳደሩን በምክትል ከንቲባነት የሚመራ አካል ከምክር ቤቱ አባላት ወይም ውጭ ከሆኑ ሰዎች መምረጥ ወይም መሾም የሚቻልበት ህጋዊ ሁኔታ ለማስቀመጥና ብቃት ያለው ሰው የሚገኝበትን ሁኔታ ለማስፋትም አዋጁ መሻሻሉ ተገልጿል።
በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ መልምሎ ያቀረባቸውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 49፣ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 74 በአጠቃላይ የ123 እጩ ዳኞች ሹመትን አጽድቋል። ከእነዚህ ውስጥ ስምንት ሴት ዳኞች ለከፍተኛ እና 16 ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተሹመዋል።
በተያያዘ ዜና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህጻናትና የሴቶች ሰብዓዊ መብት ጉዳይ እጩ ኮሚሽነር አቅራቢ ኮሚቴ ወይዘሮ መሰረት ማሞ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የህጻናትና የሴቶች ሰብዓዊ መብት ጉዳይ ኮሚሽነር ሆነው እንዲያገለግሉ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አጽድቋል። ምክር ቤቱ በተጓደሉ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የቦርድ አባላት ምትክ አቶ አህመድ ሺዴ፣ ወይዘሮ ሃሊማ ባድገባ፣ አቶ ፍስሃ ይታገሱ፣ ዶክተር መረራ ጉዲናን የቦርድ አባል በማድረግ ሹሟል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለፌዴራል እና ለክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያቀረባቸውን ተሿሚ ዕንባ ጠባቂዎች ሹመታቸውን ያጸደቀ ሲሆን፤ ዶክተር እንዳለ ኃይሌን ለፌዴራል ዋና ዕንባ ጠባቂነት፣ አቶ አህመድ ሁሴን ዓሊን ለሰመራ፣ አቶ ጀምስ ዴንግ ቲያፕን ለጋምቤላ፣ አቶ ፍቃዱ ታደሰ መንገሻን ለአሶሳ ቅርንጫፎች እንባ ጠባቂ ሆነው እንዲያገለግሉ ምክር ቤቱ ሹመቱን ሰጥቷል።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ለማደራጀት በወጣው አዋጅ ቁጥር 113/1987 አንቀጽ 7 መሰረት የአዲስ የቦርድ አባላት ስም ዝርዝር ቢላክለትም የተሟላ መረጃ ባለመላኩ ሹመቱ ሳያፀድቀር ቀርቷል።

ዑመር እንድሪስ

 

 

 

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፦ የአሜሪካው እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽህፈት ቤቶች ተቀራርበው በመሥራት ልዩነታቸው ወደ አንድነት እንዲቀየር የተጀመረውን ጥረት እንደሚደግፉ በኢትዮጵያ የሚገኙ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት ኃላፊዎች በጋራ በጻፉት ደብዳቤ ጠየቁ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ጥንታዊ ገዳማት አስተዳዳሪዎች እና አበምኔቶች ሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አዲስ አበባ ኢትዮጵያ እና ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ዋሽንግተን ዲሲ፣ አሜሪካ በሚል ደብዳቤ ጽፈዋል።
በደብዳቤው እንደተመላከተው፤ አንድ እረኛ አንድ መንጋ መሆኑ ቀርቶ ሁለት እረኛ ሁለት መንጋ በአንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ መፈጠሩ አግባብ አይደለም። በመሆኑም መቀመጫቸውን በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ አድርገው የተከፋፈሉት ሲኖዶሶች አንድነት መፍጠር አለባቸው። በተፈጠረው አሳዛኝ መለያየት ቤተክርስቲያን በማትፈቅደው አግባብ ክፍተት ተፈጥሯል።
አስተዳዳሪዎቹ በደብዳቤያቸው ባስተላለፉት መልዕክት «ብፁአን አባቶቻችን ሆይ የተሰጣችሁ አደራ ክፍተት በመፈጠሩ ምክንያት በእኛ ቤተ-ክርስቲያን ዘንድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተፈጠረው አሳዛኝ መለያየት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ለሀገርና ለትውልድ ለሚጨነቁት ወገኖች ሁሉ ቤተክርስቲያን በማትፈቅደው አግባብ መንጋውን የሚያደናግር እንግዳ ነገር ተከሰተብን። ልዩነቱ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ የታዩ እና እየታዩ ያሉ ነገሮች በቶሎ መፍትሄ ካላገኙ መለያየቱ ለቤተክርስቲያኒቷ ምን ያህል ከባድ ፈተና እንደሆነ በግልጽ ይታያል» ይላል።
ችግሩ እንዲፈታ እስከአሁን ለደከሙ አባቶች ሁሉ ክብር ይገባል። ሆኖም ችግሩ እስከዛሬ ባለመፈታቱ የቤተክርስቲያናችን ጉዳይ አሳስቦናል የሚሉት አባቶች፤ ለትውልዱ መለያየትን አውርሰን እኛም እናንተም የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን እንታቀብ። በእግዚአብሔር ዘንድም ዋጋ የሚያሳጣ ሥራ ይዘን መቅረብ የለብንም የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። «ይህ ጉዳይ በበረሃ በወደቁና በዝጉሓን ገዳማውያን አባቶች ተመክሮበት ታምኖበት እና ተጸልዮበት የተላከ መልዕክት ስለሆነ እስከአሁን የተደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው የምንመኘው አንድነት አማናዊ ሆኖ ለማየት እንችል ዘንድ በዚህ መንገድ ላይ የሚያጋጥሙ ማንኛውንም መሰናክል ሁሉ አልፋችሁና አሸንፋችሁ የምንናፍቀውን የቅድስተ ቤተክርስቲያን አንድነት ታሳዩን ዘንድ እንማጸናለን» በማለት አሁን የተጀመረውን የማወያየት ጥረት እንደሚደግፉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ደብዳቤውን የጻፉት የደብረሊባኖስ አቡነ ተክለሐይማኖት አንድነት ገዳም ዋና አስተዳዳሪ፣ የማህበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም አበምኔት፣ የዋልድባ እንዳልሽሃ ኪዳነ ምህረት አንድነት ገዳም አበምኔት፣ የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድሥት ሥላሴና አቡነሳሙኤል ገዳም አስተዳዳሪ፣ የዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ አንድነት ገዳም አስተዳዳሪ፣ የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገዳም አስተዳዳሪ፣ የሐይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ገዳም አስተዳዳሪ፣ የክብሯ ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም አበምኔት፣ የደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም አስተዳዳሪ እና የምሁር ኢየሱስ ገዳም አበምኔት ናቸው።

ጌትነት ተስፋማርያም

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፦ በመላው ዓለም ተዘርፈው እና ተሰርቀው የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ቅርሶቹ የት እና በማን እጅ እንደሚገኙ ለመመዝገብ እንዲቻል በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲተሳተፉ ጥሪ ቀረበ።

የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዳይዘረፉ ለመከላከል እና የተዘረፉትን በምን መልኩ ማስመለስ ይቻላል? የሚል ውይይት ሰሞኑን ተካሂዶ ነበር። በወቅቱ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በ18ኛው እና በ19 መቶ ክፍለ ዘመኖች የተወሰዱባትን ቅርሶች ለማስመለስ በቅድሚያ የት እንደሚገኙ እና በማን እጅ እንዳሉ መመዝገብ አለባቸው። በመሆኑም በምዝገባው ሂደት በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ወሳኝነት አለው።
ቅርሶች በሚታወቅም ሆነ በማይታወቅ መንገድ ከኢትዮጵያ መውጣታቸውን የሚገልፁት አቶ ዮናስ ቅርሶቹን በማስመለስ ጥረት በቅድሚያ የትኞቹ የኢትዮጵያ ሀብቶች በየት አካባቢ ይገኛሉ? የሚለውን ለመለየት በሚደረግ ጥረት ዳያስፖራው ማህበረሰብ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል። በአገር ውስጥ ያሉትም ቅርሶች በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት ሙሉ ለሙሉ ምዝገባ ተደርጎላቸው አለመጠናቀቁ እንዳለ ሆኖ በመንግሥት አቅም ብቻ በውጭ ያሉትን ቅርሶችም ለመለየት የሚያስችል ሥራ ላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መሳተፉ ዓይነተኛ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ዮናስ ገለጻ፤ አብዛኛዎቹ ቅርሶች በእንግሊዝ ጣልያን፣ ጀርመን እና የተለያዩ የዓለም አገራት በህገወጥ መንገድ ወጥተዋል። የት እንዳሉ እና በማን እጅ እንደሚገኙም በውል አይታወቅም። ቅርሶችን ለማስመለስ ደግሞ በቅድሚያ ያሉበትን ቦታ እና በማን ስር እንዳሉ ማጣራት ተገቢ ነው። የዓለም አቀፍ ለቅርስ ማስመለስ የሚረዱ ህግጋትን በመፈረም እና ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር በቀጣይ የኢትዮጵያን ሃብቶች ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ምዝገባ ማካሄዱ እንደ አንድ እርምጃ ይወሰዳል። በመሆኑም የእንግሊዝ ሙዚየሞች በድፍረት በክፍት ሙዚየም ያስጎበኟቸው የኢትዮጵያን ቅርሶች ጨምሮ በመላው ዓለም የተዘረፉ ሃብቶችን በዝርዝር ለይቶ ለመከራከር እንዲቻል የዳያስፖራው ማህበረሰብ እርዳታ ከምን ጊዜውም በላይ አስፈላጊነቱ የጎላ ነው ብለዋል።
የዩኔስኮ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አና ሳንታ አልፎንሶ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1970 በዩኔስኮ የወጣውን የባህላዊ ቅርሶችና ንብረቶች የባለቤትነት መብት ዓለም አቀፍ ህገደንብ ዘንድሮ ፈርማ መቀበሏ ቅርሶችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት አጋዥ እንደሚሆን ገልጸዋል። በዓለም ላይ የሚገኙ 137 አገራት የቅርስ ህገደንቡን በመቀበላቸው ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ለማስመለስ በምታደርገው ጥረት በጋራ መስራት እንደሚችሉም ገልጸዋል።
እንደ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን መረጃ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ቅርሶች ከመቅደላ ጦርነት በኋላ በእንግሊዝ የተዘረፉ ናቸው። የተለያዩ ብራናዎች እና ታሪካዊ ሃብቶች ደግሞ በስርቆት እና በዝርፊያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ከአገር ወጥተው በአውሮፓ፣ አሜሪካ እና እስያ ሙዚየሞች እና በግለሰቦች እጅ ይገኛሉ።

ጌትነት ተስፋማርያም

 

Published in የሀገር ውስጥ

አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ባህል ማእከል «በኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ ኢትዮጵያዊነት አለን» በሚል ርእስ በሁለት ምሁራን በቀረበ የመነሻ ፅሁፍ የፊልም ባለሙያዎችን እና ባለድርሻ አካላትን ተወያይተዋል። በቀረበው የመወያያ ጽሁፍ ላይ «ኢትዮጵያዊነት» በፊልም ስራዎች ላይ በሚፈለገው ልክ አለመንፀባረቁ ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ ሆቴል ሰሞኑን በርካታ የፊልም ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የመነሻ ፅሁፍ ያቀረበው የቴአትር እና የፊልም ባለሙያው አቶ ኤፍሬም ለማ የአገር ውስጥ ፊልሞች ኢትዮጵያዊ ይዘት አላቸው የምንለው እንዴት ነው? ለሚለው ጉዳይ እንደ መነሻ በአቀረበው ፅሁፍ ላይ እንደተናገረው፤ በፊልሞች ላይ ኢትዮጵያዊነት ተንፀባረቀ ማለት የሚቻለው በብዝሀነት ውስጥ ያለው ውብ የአኗኗር፣ ቁሳዊ ባህል፣ አመጋገብ፣ የደስታ እና የሀዘን ስነስርአቶችን በስራዎች ውስጥ ማግኘት ሲቻል ነው። በተለይ በጋራ የመስራት ባህል እና እኗኗር ማህበራዊ ትስስሩ በራስ የተቃኘ ፍልስፍና ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ መገለጫዎች በሚፈለገው መጠን አልተንፀባረቁም።
«ጤዛ፣ አትሌቱ፣ ታዛ፣ ረቡኒ፣ኢትዮጵያ እና ሌሎች ጥቂት የቅርብ ጊዜ ፊልሞች ኢትዮጵያዊነትን ጉዳይ አድርገው ማሳየት የቻሉ ናቸው» ያሉት አቶ ኤፍሬም ሆኖም ግን አብዛኞቹ ፊልሞች ኢትዮጵያዊነትን ሙሉ በሙሉ አላነሱም ባይባልም ዋና ጉዳይ በማድረጉ ረገድ ላይ ክፍተት አለባቸው ብለዋል።
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የፊልም ባለሙያዎች «በኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ ኢትዮጵያዊነት አለን?» በሚለው ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት እና ክርክር አድርገዋል። ትክክለኛውን ኢትዮጵያዊነት በፊልሞቻቸው ላይ ለማንፀባረቅ ቢፈልጉም እንቅፋቶቹ እና ተግዳሮቶቹ ሰፊ መሆናቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበር የህዝብ ግንኙነት እና የጥናት ኃላፊ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር የቦርድ አባል አርቲስት ደሳለኝ ሃይሉ እንደገለፀው፤ የኢትዮጵያ ፊልም ከግለሰብ እና ቡድኖች ፍላጎት በዘዘለ አገራዊ መልክ እንዲኖረው አቅጣጫ ተቀምጦለት ፖሊሲ ወጥቷል። አካታች እንዲሆንም ጥረት እየተደረገ ነው ብሏል።
«እስካሁን ድረስ የፊልም ኢንዱስትሪው የሚጓዝበት መመሪያ አለመኖሩ ኢትዮጵያዊነትን የሚያንፀባርቁ ፊልሞች በስፋት ላለመኖራቸው እንደምክንያት የሚጠቀስ ነው። በሌላ በኩል ጠንካራ ተቋማቶች እና የገንዘብ አቅም ሌላኛው ምክንያት ነው» የሚለው አርቲስቱ፤ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ ተቋማት በተጠናከረ መልኩ ከተቋቋሙ ችግሩን መፍታት ይቻላል በማለት አስተያየቱን ይሰጣል።
የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ ሰነድ በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀ ከ8 ወራት በኋላ ዋነኛ አስፈፃሚ መስሪያ ቤት በሆነው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መታተሙ የሚታወስ ነው።

ዳግም ከበደ

 

Published in የሀገር ውስጥ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።