Items filtered by date: Monday, 09 July 2018

ለርካቶች የወደፊት መንገዳቸውን ጠርጎላቸዋል፤ አንዷ ሜዳሊያ በዝታ ስኬታማ እንደምትሆናቸውም ማሳያ ነው። ወደ ታላቅ አትሌትነት በመሸጋገር ላይ ያሉ ወጣት አትሌቶች አቅማቸውን ከእኩዮቻቸው ጋር የሚመዝኑት በዓለም የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነው። በየሁለት ዓመቱ ሃገራት እየተፈራረቁ በሚያዘጋጁት በዚህ ውድድር ላይ ተስፋ የሚሆናቸውን አትሌቶችም ያፎካክሩበታል። ይህ ዕድሜያቸው ከ20ዓመት በታች የሆኑ ወጣት አትሌቶች ብቻ የሚሳተፉበት የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ ይካሄዳል።
የአዘጋጅነቱን ተራ ያገኘችው ደግሞ የፊንላንዷ ታምፔሬ ከተማ፤ ነገ ወጣቶቹን ማፎካከር ትጀምራለች። ለአምስት ቀናት በሚዘልቀው ሻምፒዮናው ላይም 44 የውድድር ዓይነቶች ይስተናገዳሉ። በውድድሩ የሚካፈሉትም፤ የትኛውንም ሃገር የማይወክሉ እና ስደተኛ አትሌቶችን ጨምሮ ከ156ሃገራት የተወጣጡ 1ሺ462 (በሁለቱም ጾታ) አትሌቶች ናቸው።
እአአ 1986 በግሪኳ አቴንስ የተጀመረው የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ በተለያዩ የዓለም ሃገራት እየዞረ ሲካሄድ ቆይቷል። ኢትዮጵያም ከመጀመሪያው ሻምፒዮና ጀምሮ እየተሳተፈችበት ሲሆን፤ በመድረኩ በሰበሰበቻቸው ሜዳሊያዎች ብዛትም ከዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። 34 የወርቅ፣ 30የብር፣ 25የነሐስ በጥቅሉ 89ሜዳሊያዎች ደግሞ ወጣቶቿ በመድረኩ ያስመዘገቧቸው ናቸው። የደረጃ ሰንጠረዡን አሜሪካ ስትመራ፤ ኬንያ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ኢትዮጵያ ደግሞ እስከ አምስት ያለውን ተርታ ይዘዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ላይ ባላት ተሳትፎ ለበርካታ ጊዜያት ከዓለም ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ ይህም ከፍተኛ ውጤቷ ነው። በአፍሪካ ደግሞ እአአ1996 በአውስትራሊያዋ የሲድኒ ከተማ በተካሄደው ሻምፒዮና፤ ስድስት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ውድድር ከፍተኛው ውጤቷ ነው። ብዙ ሜዳሊያዎችን የሰበሰበችው ደግሞ ፖላንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ባስተናገደችው እአአ የ2008ቱ ሻምፒዮና እንዲሁም እአአ በ2016 ፖላንድ በድጋሚ ባዘጋጀችው ሻምፒዮና 10ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበችበት ነው።
ከሁለት ዓመታት በፊት በፖላንዷ ባይዳጎዝ ከተማ አዘጋጅነት በተካሄደው 16ኛው የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና፤ ኢትዮጵያ አሜሪካና ኬንያን ተከትላ በደረጃ ሰንጠረዡ ከዓለም ሦስተኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ሆናለች። የተመዘገቡት 4 የወርቅ፣ 2የብርና 4የነሐስ በአጠቃላይ 10ሜዳሊያዎች እንዲሁም ስምንት ዲፕሎማዎችም በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ተሳትፎ የተሻለው ውጤት መሆኑ የታየበት ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያ በደረጃ ሰንጠረዡ ባገኘቻቸው የወርቅ ሜዳሊያዎች በኬንያ ትበለጥ እንጂ፤ በሜዳሊያ ብዛት ብልጫውን መያዝ የቻለችበትም ነበር።
ዕድሜያቸው ከ20ዓመት በታች የሆኑ ወጣት አትሌቶች ብቻ በሚሳተፉበት በዚህ ሻምፒዮና፤ ኢትዮጵያዊያን ወጣት አትሌቶች እንደተለመደው ተተኪነታቸውን ለማስመስከር ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ወደዚያው አቅንተዋል። ከወር በፊት አሰላ ላይ በተካሄደው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ከ20ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተሻለ ብቃት ያሳዩ አትሌቶችም በብሄራዊ ቡድኑ ተካተዋል። የተመረጡት አትሌቶች እና አሰልጣኞች ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ በአራራት ሆቴል ተቀምጠው ዝግጅታቸውን እያከናወኑ እንደነበርም ይታወሳል።
በዚህ ውድድርም ኢትዮጵያ ከ400 ሜትር ጀምሮ እስከ 10 ሺ ሜትር ባሉት ርቀቶች እንዲሁም በዕርምጃ ውድድርና በመሰናክል ውድድሮች ትካፈላለች። 29 አትሌቶች በልዩ ልዩ የአትሌቲክስ ውድድር መስኮች የሚካፈሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 15ቱ ወንዶች፣ 14ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው። ይህንን ሻምፒዮና ልዩ የሚያደርገውም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚኒማ በተሟላባቸው የአጭር ርቀት ውድድር፤ በተለይም በ400 ሜትር እና በ4በ400 ሜትር ድብልቅ ሪሌይ በሁለቱም ጾታዎች ተሳታፊ መሆኗ ነው።
በቡድን መሪነት ብሄራዊ ቡድኑን ይዘው ወደ ፊንላንድ ያቀኑት የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር በዛብህ ወልዴ ስለዝግጅቱ ከፌዴሬሽኑ ድረገጽ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር። በንግግራቸውም ላይ «ቡድኑ በቂ ትኩረትና ዝግጅት እንዲሁም በሥራ አስፈጻሚው የቅርብ ክትትል የተደረገለት በመሆኑ በጤናማ መንፈስ ላይ ይገኛል። በዚህ ውድድር ቁንጮ ከሚባሉት ሃገራት መካከል እንገኛለን፤ አሁንም እንደዚያው እንሆናለን ብለን እንጠብቃለን» ብለዋል።
ቡድን መሪው ጨምረውም የአትሌቶችን ፍላጎት ለመጠበቅ ሲባልም፤ የአብዛኞቹ የግል አሰልጣኞች አብረው የተመረጡ ናቸው። በቂ ሊባል የሚችል የህክምና ቡድንም አብሯቸው አለ። ይህም ለአትሌቶቹ ውጤት፣ ምቾትና ጤንነትም ጭምር ሲባል የተደረገ ነው፤ ስለሆነም የተለመደውን የቁንጮነት ውጤት እና ደረጃ ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ብሄራዊ ቡድኑ ይካፈል የተነበረው ከ800ሜትር በላይ በሆኑ ርቀቶች መሆኑን ያስታውሳሉ። በዚህ ውድድር ላይ ግን ፌዴሬሽኑ አጫጭር ርቀቶችም እንዲሳተፉ አድርጓል፤ በዚህም በ400ሜትር እና በ400ሜትር ዱላ ቅብብል ውድድሮች የሚካሄዱ ይሆናል። «በፖላንድ በተካሄደው ውድድር ከዓለም ሦስተኛ ሆነን ነበር ያጠናቀቅነው፤ በዚህ ሻምፒዮና ደግሞ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እና ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃም አስከብረን ለመመለስ አቅደናል» ብለዋል።
በውድድሩ ላይ በተለያዩ ርቀቶች ኢትዮጵያን የሚወክሉት አትሌቶችም የሚከተሉት ናቸው። 400ሜትር በወንድ አብዱራህማን አብዶ፣ ሞሳ ስዮም፣ መልካሙ አሰፋ፤ በሴት ደግሞ ፍሬዎት ወንዴ፣ ማህሌት ፍቅሬ፣ ጌትሽ ተስፋዬ ናቸው። 400ሜትር መሰናክል ደግሞ ጋዲሳ ባዬ ብቻ ሃገሩን ይወከላል። በወንድ 800 ሜትር ታደሰ ለሚ እና አዲሱ ግርማ በሴቶች በኩል ደግሞ ድርቤ ወልተጂ እና ፍሬዎይኒ ሀይሉ ይሳተፋሉ። በ1500ሜትር ወንዶች ደግሞ ብርሃኑ ሶሬሳ፣ ሳሙኤል ተፈራ፣ መለስ ንብረት እንዲሁም ድንቄ ፈርዴሳ እና አልማዝ ሀይሉ በሴቶች ይወዳደራሉ።
በ3ሺ ሜትር ሴቶች ብቻ በውድድሩ የሚካፈሉ ሲሆን፤ እነርሱም ፅጌ ገብረሰላም እና መሰሉ በርሄ ናቸው። በ3ሺ ሜትር መሰናክል በወንዶች ታከለ ንጋቱ እና ጌትነት ዋለ፤ በሴቶች ደግሞ እታለማሁ ስንታየሁ እና ሀገሬ በላቸው ይፎካከራሉ። በ5ሺ ሜትር ወንድ ሰለሞን ባረጋ እና ጥላሁን ሀይሌ፤ በሴት ደግሞ ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር እና እጅጋየሁ ታዬ ሲሳተፉ፤ በ10ሺ ሜትር ወንዶች ብቻ የሚወዳደሩ ሲሆን፤ በሪሁን አረጋዊ እና ዎሊቃ አዱኛ ደግሞ ተሳታፊዎች ናቸው። በዕርምጃ ደግሞ ዮሐንስ አልጋው በወንድ እንዲሁም ማሬ ቢተው በሴት ተሳታፊ ናቸው።
በብሄራዊ ቡድኑ ከተካተቱት አትሌቶች መካከል የዓለም አቀፍ ውድድር ልምድ ያላቸው መኖራቸው ቡድኑ ላቀደው የተሻለ ውጤት እንደሚረዳቸውም እሙን ነው። የመድረኩ ሻምፒዮና እንዲሁም ባሳለፍነው ሳምንት በሉዛን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቀው ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ እንደተለመደው ውድድሩን በድል ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከአምስት ወር በፊት በእንግሊዝ በርሚንግሃም በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በ1ሺ500 ሜትር ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው አትሌት ሳሙኤል ተፈራም በተመሳሳይ የወርቅ ሜዳሊያውን የግሉ የማድረግ ዕድሉ ሰፊ ነው። ጌትነት ዋሌ እና ሌሎቹ አትሌቶችም የውጤት ባለቤት እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ነገ በሚኖረው የውድድር መርሐ ግብር መሰረትም የወንዶች 400ሜትር እንዲሁም 1ሺ500ሜትር ማጣሪያ ሲካሄድ፤ በ10ሺ ሜትር ውድድርም ይደረጋል። በሴቶች በኩል ደግሞ 400ሜትር፣ 800ሜትር እና 3ሺ ሜትር ማጣሪያ እንዲሁም 5ሺ ሜትር ውድድሮች ይካሄዳሉ።

ብርሃን ፈይሳ

Published in ስፖርት

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ትምህርትን በመሰሉ ዘርፎች ተደራሽነትን ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ ነው። ጥራትን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ስራም ተደራሽነቱን ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረቷን ካደረገች ሰነባብታለች። መሰረቱን በጥራት ላይ ያደረገ የትምህርት ስርዓትም በየትኛውም ደረጃ ተፈላጊና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት እንደሚረዳ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የትምህርት ጥራቱ በሚፈለገው ልክ አለመራመዱም እየታየ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ይነሳሉ።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮም፤ ቀድሞ የነበረውን የትምህርት ሰራዊት አደረጃጀት በመተው የትምህርት ጥራት አሰራርን ተከትሎ መስራት ጀምሯል። በዚህ ስራ ላይም ለባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቶ ሁሉም በዚህ አደረጃጀት እንዲሰራ በመደረጉ በተማሪዎች ውጤት ላይ ጅምር ለውጥ መታየቱን ተነግሯል፡፡ በዚህም የትምህርት ጥራት እና የተማሪዎች ውጤት ምን ላይ ደርሷል፣ እንዲሁም በቀጣይ ምን መስራት ይገባል፣ በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረክ ሰሞኑን በአዳማ አዘጋጅቶ ነበር።
የክልሉን ሁሉም ዞኖችንና ወረዳዎች የትምህርት ቢሮው ኃላፊዎችና አስተዳደሮች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ፤ የትምህርት ጥራቱ በሚፈለገው ልክ ማረጋገጥ አለመቻሉን ቢሮው አስታውቋል። በመድረኩ በቀረበው ገለጻም አብዛኛዎቹ ችግሮች በ2009 ዓ.ም የተለዩ እና በ2010 ዓ.ም ይቃለላሉ ተብሎ በእቅድ የተያዙ ነበሩ። ይሁን እንጂ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመትም ሳይፈቱ ለአዲሱ በጀት ዓመት መተላለፋቸው ታይቷል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በክልሉ 15ሺ 983 የትምህርት ተቋማት ሲኖሩ፤ 9ሚሊዮን 940ሺ 039 ተማሪዎችም በእነዚህ ተቋማት ይማራሉ። በመማር ማስተማር ስራውም 185ሺ 528 መምህራን ተሳታፊ ናቸው። ቢሮው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት(1-8) የተሻለ ስራ ቢያከናውንም፤ የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ (9-12) ትምህርት ቤቶች ግን በሚፈለገው ልክ ባለመሆናቸው ተጨማሪ ማስፋፊያ የሚፈልጉ መሆናቸው ተጠቁሟል። በክልሉ ያሉት 12 ኮሌጆችም ካለው የተማሪ ቁጥር አንጻር አነስተኛ የሚባል በመሆኑ ተጨማሪ ስራ የሚጠይቅ ነው።
ሌላው ለትምህርት ጥራት አለመረጋገጥ ማሳያ የሆነው ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎች ላይ የተሰራው ስራ አናሳ መሆን ነው። ይህ ችግር መኖሩ በ2009 ዓ.ም ተለይቶ የታወቀ ቢሆንም፤ በ2010 ዓ.ም የትምህርት ዘመንም ሳይፈታ ለሚቀጥለው ዓመት ሊሸጋገር ችሏል። በዚህ ረገድ የተነሱት ችግሮችም የቁሳቁስ፣ የመምህራን(በልዩ ፍላጎት ላይ የሰለጠኑ ባለሙያዎች) እንዲሁም የትምህርት ቤት ግንባታዎች ናቸው።
በቢሮው የእቅድና ዝግጅት ፕላኒንግ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ዋቅጅራ እንደሚሉት፤ የትምህርት ቤቶች ግንባታ ለእነዚህ ተማሪዎች ምቹ አለመሆኑንና በህብረተሰቡ ዘንድም አካል ጉዳተኞችን በማውጣትና በማስተማር ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት አለ። ትምህርት ቤቶችም እነዚህን ተማሪዎች ሊያግዙ የሚችሉ መምህራንን መቅጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ኮሌጆችም የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን የሚረዱ መምህራንን ማሰልጠን ይጠበቅባቸዋል፡፡
በተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትም በተመሳሳይ በተያዘው እቅድ ልክ መፈጸም አለመቻሉን ቢሮው ገምግሟል። በዚህ ዘርፍ የታየው ዋነኛው ችግር ደግሞ ተሳታፊዎቹ አዋቂዎች እንደመሆናቸው እነርሱ በሚፈልጉት ሰዓት ማስተማር አለመቻል ነው። በቀን ለሁለት ሰዓታት እንዲማሩ ማድረጉም ተቀባይነት ለማጣቱ ሌላኛው ክፍተት መሆኑንም አቶ ደሳለኝ ይጠቁማሉ። በትምህርት አሰጣጡ ላይ ከሌሎች ተቋማትም ጋር በቅንጅት የመስራት ባህል አለመዳበሩም ለዚህ ተደማሪ ችግር ነው።
ሌላው በትምህርት ጥራት ተጽእኖ እያሳደረ ያለው በትምህርት ቤቶች ያለው የግብዓት እጥረት መሆኑም በመድረኩ ተጠቁሟል። በመማሪያ መጽሐፍት ላይ ያለው እጥረት አሁንም ባለመቀረፉ ሁለት ተማሪዎች አንድ መጽሐፍ በጋራ ይጠቀማሉ። አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች እንደ ውሃ እና መብራት ያሉ መሰረታዊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ስላልተሟሉላቸው ለተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መቅረት ምክንያት ሆኗል። በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማሟላት ያሉባቸው ስታንዳርዶች (ቤተ-መጽሐፍት፣ ቤተ-ሙከራዎችና የመሳሰሉት) በበቂ ሁኔታ አለመኖር ተማሪዎች ተገቢውን እውቀት ቀስመው በሚፈለገው ልክ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
በመምህራን ላይ የሚታየው እጥረት እና ብቃትም በትምህርት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረ ሆኗል። ይህ በሁለት መልኩ የሚታይ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የመምህራን አቅርቦት ነው። የመምህራን ክፍያ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እንዲሁም ለመምህራን በሚሰጡ ጥቅማ ጥቅሞችና ማበረታቻዎች ላይ የተሰራው ስራ አናሳ መሆኑ ለእጥረቱ ምክንያት ሆኗል። ባሉት መምህራን አለመጠቀምም በትምህርት ቤት አመራሮች በኩል የታየ ደካማ አፈጻጸም ሆኗል።
ሁለተኛው ስታንዳርዱን የሚያሟሉ መምህራን አለመኖር ሲሆን፤ ይሄም ልዩ ትኩረት የሚፈልግ ስራ ነው። መምህራን እንደየደረጃቸው ሊኖራቸው የሚገቡ መመዘኛዎችን አለመሟላታቸው በስፋት የታየ ችግር ነው። ይህም በብቃታቸው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ከመምህራን የምዘና ውጤት ለመመልከት ተችሏል፡፡ ለአብነትም፣ በዓመቱ ምዘናውን ከወሰዱት 17ሺ 294 መምህራን መካከል 70 ከመቶና ከዚያ በላይ የሆነ ውጤት ያስመዘገቡት 18 ነጥብ 8 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ይህም መምህራኑን አሰልጥነው የሚያወጡት ኮሌጆች ድረስ ችግሮች መኖራቸውን በግልጽ የሚያመላክት ሆኗል።
ከላይ ለትምህርት ጥራት መጓደል መንስኤ ናቸው በሚል ለተዘረዘሩት ጉዳዮች ማሰሪያ የሚሆነው ዋነኛ ምክንያትም የበጀት ምደባው ነው። በተለይ ለትምህርት የሚመደበው በጀት ከሌሎች ዘርፎች አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑም በውይይት መድረኩ ላይ ተመላክቷል። ችግሩ ቀደም ብሎ የተለያየ በመሆኑም ከየዞኖቹና ወረዳዎቹ የትምህርት ቢሮ አመራሮች በተጨማሪ አስተዳዳሪዎችና የበጀትና ፋይናንስ ኃላፊዎችም በመድረኩ እንዲገኙ ተደርጎ በጋራ ለመፍትሄው ተመክሯል።
ቢሮውም በግብዓት በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት በሁሉም ደረጃ ትምህርት ትኩረት እንዲሰጠው በመድረኩ ላይ አሳስቧል። የተቀሩትን ችግሮች በመፍታት ረገድም የተጓዘባቸውን የመፍትሄ አቅጣጫ የእቅድና ዝግጅት ፕላኒንግ ኃላፊው አብራርተዋል። በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ በሙያው የሰለጠኑ መምህራንን በመቅጠር በኩል እጥረቶች መኖራቸው ታይቷል፤ በዚህም ላይ ለትምህርት ቢሮዎቹ መመሪያ አስተላልፏል። በተግባር ተኮር የአዋቂዎች ትምህርት ላይም ቢሮው ማኑዋል በማዘጋጀት እንዴት መካሄድ ይገባዋል በሚለው ላይም ሰርቷል። የመማሪያ መጽሐፍት እጥረት ላይም በ35 ሚሊዮን ብር የመጽሐፍት ሶፍትዌር በማዘጋጀት ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ ይገኛል።
«የመምህራን እጥረቱ ምን ያህል ነው? ምን ያህልስ ያስፈልጋሉ?» የሚለው መለየቱን የሚጠቁሙት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ማሞ ቦጋለ ናቸው። ለማሳያም ከ1-4ኛ ክፍል ድረስ 21ሺ መምህራን ቢያስፈልጉም እጥረት መኖሩን ያነሳሉ። አሁን ባለው ሁኔታም ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ባሉት ደረጃዎች ከ91ሺ በላይ መምህራን ያስፈልጋሉ። ስታንዳርዱን አሟልቶ ለመስራትም በዓመት ወደ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ችግሩን በየአቅጣጫው ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን በግንባታ፣ በቁሳቁስና በእድሳት ላይ ህብረተሰቡን ማሳተፍ እንደሚቻል ያመለክታሉ። ሌሎች ባለድርሻዎችና መንግስትም በጀት እንዲጨምሩ ማድረግ ይቻላል።
ሁለተኛውና ወሳኙ ችግር የአመራር በመሆኑ በዚህ ላይ ስታንዳርዱን ማሟላት ያስፈልጋል። የተሻለ የትምህርት ዝግጅት እንዲሁም ብቃትና ችሎታ ያላቸውን አመራር መልምሎ ወደ ስራ በማምጣት በኩል የሚታየውን ክፍተት እንዲያስተካክሉም ይረዳል። በተለይ እነዚህን አመራሮች ወደ ትምህርቱ ማምጣት ስራውን እንዲሁም ህብረተሰቡን የሚያንቀሳቅስ በመሆኑ፤ የጥራት ችግሮችን በጥረታቸውም ሆነ ህብረተሰቡን በማስተባበር ለመፍታት እንደሚችሉ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ይጠቁማሉ። የመምህራን አቅርቦትና ብቃት ላይ የሚታየው ክፍተት አንድም ኮሌጆች በሚሰጡት ስልጠና ላይ የጥራት ችግር መኖሩን የሚያሳይ በመሆኑ፤ ጥራቱን የማረጋገጥ ስራው ከቅድመ መደበኛ እስከ ኮሌጆች የሚደርስም ይሆናል። በቀጣዩ በጀት ዓመት በክልሉ 11 ሚሊዮን ተማሪዎች የሚኖሩ በመሆኑ፤ የመምህራኑን ቁጥር ወደ 200ሺ ለማሳደግ እንዲሁም በቁሳቁስ አቅርቦት ላይ የተሻለ ስራ ለማከናወን መታቀዱንም ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ፤ ችግሮችን ለመፍታት የችግርን መንስኤ መረዳት የመጀመሪያው እርምጃ መሆኑን ይገልጻሉ። በዚህም ለትምህርት ጥራት አለመሳካት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ለማሳየት መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። ተሳታፊዎቹ ግንዛቤ ከጨበጡ በኋላም ለትምህርት ጥራት መከናወን በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መፍትሄዎችን አስቀምጠው ለመጪው የትምህርት ዘመን የተሻለ ስራ ለመስራት እድል ይፈጥራል።
በመሆኑም ከግብዓት ጋር በተያያዘ የትምህርት ጥራትን የሚወስኑና በበጀት የሚመለሱ ጥያቄዎች የሚመለከታቸው አካላት የሚወስዱት የቤት ስራ ይሆናል። ገንዘብ የማይፈልጉና በአስተሳሰብ ላይ የተመሰረቱ ጉዳዮች ላይም የጋራ ነገር የሚያዝበት ነው፡፡ ከመምህራን መብቶች ጋር በተያያዘ ኃላፊነት ላለባቸው አካላት ችግሮቹን ጎላ አድርጎ በማሳየት ችግሩን እንዲረዱ መደረጉንም ኃላፊው ይጠቁማሉ። የመምህራን ቅጥር፣ ዝውውር፣ እድገትና የደመወዝ ጭማሪ ላይም በአስቸኳይ እንዲፈጸሙ አጽንኦት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

Published in ማህበራዊ

የሰው ልጅ ኑሮውን እያሻሻለና እየለወጠ በሄደ ቁጥር የተሻለ ኑሮ ወደሚያገኝበት ስፍራ ማቅናቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከእነዚህ መዳረሻዎች መካከል ደግሞ ከተሞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም ተጨባጭ ሁኔታ ከተሜነት በፍጥነት እያደገ፣ የህዝብ ቁጥሩም እየጨመረ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ከተሞች ከመስፋፋት ባለፈ በሚፈለገው መጠን አለማደጋቸው፤ የህዝብ ቁጥራቸው ከመጨመር በዘለለ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ባለመሆናቸው የሚፈልገውን የከተሜነት ኑሮ ለማግኘት አለመቻላቸው በስፋት ሲነገር ይደመጣል፡፡
በዚህ መልኩ ከተሞች ላለማደጋቸውም ሆነ ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ላለመሆናቸው ከሚነሱ ምክንያቶች መካከል ደግሞ የከተሞች በፕላን አለመመራት እና የከተሞች የመሬት አጠቃቀም ችግር ስለመሆናቸው የዘርፉ ባለድርሻዎች ይናገራሉ፡፡ የከተሞች ፕላንና የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተ ሰሞኑን በጅማ ከተማ በተካሄደው የመጀመሪያው የኦሮሚያ ከተሞች ፎረም ላይ በጥናት የታገዘ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በወቅቱም ከተሞች ከመስፋትና የነዋሪዎቻቸው ቁጥር ከመጨመሩ ባለፈ በሚፈለገው ልክ ያላደጉና ለነዋሪዎቻቸውም ምቹ ያልሆኑ መሆናቸው ተነስቷል፡፡
በዚህም በተለይ ከተሞች በፕላን አለመመራ ታቸውና ተገቢውን የመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ባለመተግበራቸው ለነዋሪዎች ምቹ አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ለመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ መሆናቸው ተወስቷል፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን የከተሞች ፕላንና የመሬት አጠቃቀም በከተሞች ያለውን ገጽታ፣ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ በውይይት መድረኩ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሁለት የዘርፉ ባለሙያዎችን ሃሳብ ይዘን ቀርበናል፡፡
የመሬት አጠቃቀምና ፕላን በከተሞች
አቶ ብርሃኑ ታደሰ፣ በኦሮሚያ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት የፕላን ባለሙያ ናቸው፡፡ በውይይት መድረኩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችን መነሻ በማድረግ በከተሞች በሚስተዋለው የፕላን አተገባበር ዙሪያ የውይይት ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ስለከተሞች ፕላን ለማንሳት መጀመሪያ ስለ ከተሜነት ማንሳት ይገባል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከተሜነት በዓለም ላይ በተለይም ባደጉት አገራት የእድገት ደረጃው ከ77 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከተማ ውስጥ የሚኖረው ከ20 በመቶ በታች ሲሆን፤ አሁን ባለው እድገትና አገሪቱ በያዘችው ስትራቴጂክ ትራንስፎር ሜሽን መሰረት ደግሞ 5 ነጥብ 4 በመቶ በላይ እያደገ ይገኛል፡፡ ይህን የእድገት ምጣኔና ከተማ ውስጥ ያለውን ህብረተሰብ ደግሞ በከተማ ፕላን ተመርቶ እንዲሰፋ ማድረግ ካልተቻለ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ፕላን የሌለውና በዚሁ ልክ ለትውልድ የሚተላለፍ ከተማ ይፈጠራል፡፡ ይህ ደግሞ የከተማ ፕላን ለከተሞች እድገት ወሳኝ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
አቶ ቃሲም ፊጤ፣ ላለፉት አስር ዓመታት በከተማ መሬት ላይ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት የፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ በለስልጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በመድረኩም የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ላይ ትኩረት በማድረግ በከተሞች በሚስተዋል የመሬት አጠቃቀም ችግር ዙሪያ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥናት አቅርበዋል፡፡ አቶ ቃሲም እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ በከተሞች ልማት ዘርፍ በከተሞች የሚኖረው የህዝብ ቁጥር በገጠር ከሚኖረው አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ ከሚባሉትና ወደመጨረሻ ካሉት አገራት አንዷ ናት፡፡ በዛው ልክ ደግሞ ከተሞች እየሰፉ ያሉበት ፍጥነት ከየትኛውም አገር የበለጠና የፈጠነ ያለ ነው፡፡ ሆኖም ከግሎባላይዜሽን አኳያም እንደ አገርም ሆነ በከተሞች ደረጃ ያሉ የአገልግሎት አሰጣጦች፣ ወደ ኢንዱስትሪ ያላይዜሽን የሚደረጉ ፉክክሮች ኢንቨስትመንትን ለመሳብ መሬት ወሳኝ ነው፡፡ ለልማትም ትልቁ ግብዓት ነው፡፡
በመሆኑም የከተሞች መሬት ከብክነትና ብክለት የነጻ መሆን አለበት፤ በቁጠባ መጠቀምም ይገባል፡፡ ይሄን የመሬት ሀብት በማስተዳደር ሂደትም አሁን ዓለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ መድረስ እንኳን ባይቻል፤ ቶሎ ብሎ አሁን በከተሞች እየታዩ ያሉትን ህገ ወጥ ሰፈራዎችን መግታትና አቅርቦቱን የማሻሻል ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ከዚህ በፊት የተከማቹ ችግሮች ያሉበትና በዛው ልክ ትኩረትም ስላልተሰጠው የመሬት ዘርፍ ችግሮች ማጽዳትና በዛው ልክ ራስንም ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡
ይሄን ለማድረግ ደግሞ ከተሞች አቅም መፍጠር አለባቸው፡፡ ለዚህም አንደኛ ከአመራር ጀምሮ የሰው ኃይላቸው ስለ ከተማ የተወሰነ እውቀት ሊኖራቸው፤ ከሁኔታዎች ጋር ራስን እያበቁ መሄድንም ይጠይቃል፤ ለዚህ የሚሆን የሰው ኃይልም እያፈሩ መሄድ ይገባል፡፡ ህብረተሰቡንም ሆነ የግል ባለሀብቱን በዘርፉ የሚሳተፉበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡ ከላይ ያሉ የፖሊሲ አውጪዎችም ጉዳዩን በተለይ ከፖሊሲ አንጻር ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን ተከታትሎ ከጊዜው ጋር እያጣጣሙ፤ ሕጎችንም እያሻሻሉና ተደማሪ ድጋፍ እያደረጉ መሄድን ይሻል፡፡ በዚህ መልኩ በክልልም ሆነ በፌዴራል ያሉ አካሎች ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡
የመሬት አጠቃቀምና ፕላን ወቅታዊ ይዞታ
“እንደ አገርም ሆነ እንደ ኦሮሚያ ክልል ከተሞቻችን መጀመሪያውኑ አፈጣጠራቸው በተለያዩ ምክንያቶች እንደመሆኑ በፕላን ላይ የተመሰረቱ አይደሉም” የሚሉት አቶ ብርሃኑ፤ በዋናነትም የጦር ቀጣና መሆናቸው ወይም ለዚሁ ተግባር ስትራቴጂክ ቦታነታቸው ታይቶ የተፈጠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የመሬት አቀማመጣቸው ወጣገባ የበዛበት እንዲሆን በማድረጉ አሁን ላይ ለመስፋፋት አስቸጋሪ ሁኔታን መፍጠሩን በመጠቆምም፤ የከተሞች ምስረታ አመጣጥ በፕላን ባለመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ በፕላን ቢሰራ የሚሞቱ ከተሞች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ቀድሞ ገጠር የነበሩ፣ አሁን በተፈጠረው የገበያ ሁኔታ ያረጁ ከተሞችን በልጠው ራሳቸውን ወደከተማነት ያመጡና እያመጡ ያሉም ከተሞች የሚስተዋሉ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፤ ወደ ከተሜነት የሚለወጡትን እነዚህ አዳዲስና ትንንሽ ከተሞች በከተማ ፕላን መያዝ ወሳኝ ነው፡፡ ሆኖም ከተሞች እየተስፋፉ ቢመጡም የከተማ ፕላናቸውን እየተገበሩ አይደለም፡፡ በዚህም የከተማ ፕላን አፈጻጸም ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ምክንያትና ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው፣ ፕላኑ ራሱ ሲዘጋጅ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ከማድረግ አኳያ ጉድለት መኖሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የካርታ ፕላን ስራ በአገሪቱ የቅርብ ጊዜ ስራ የመሆኑ ውጤት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ፕላን ሲሰራ በአግባቡ ዳታ የመሰብሰብ ችግር አለ፡፡ ምክንያቱም የከተሞች ፕላን ስራ የማዳረስ ወይም የቁጥር ስራ ተደርጎ እንጂ በተገቢው መረጃ ላይ ተመስርቶና ለጥራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ አይደለም፡፡ ከእነዚህ በላይ አስቸጋሪ የሚያደርገው ደግሞ በተለይ ፕላንን ከማስፈጸም አኳያ ሲሆን፤ ይሄን ከማስፈጸም ጋር በተያያዘ የሚፈጽመው ባለሙያም ሆነ የሚያስፈጽ መው ኃላፊ ሙያው በሚፈቅደው መሰረት ስለማያስ ፈጽሙና ስለማያስተዳድሩ ነው፡፡ በዚህም አሁን ላይ ከተሞች በፕላን ይመራሉ፤ ፕላኖቻቸውም በአግባቡ ይፈጸማሉ ለማለት አይቻልም፡፡
አቶ ቃሲም በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አሁን ባለው ሁኔታ በከተሞች ያለው የመሬት አጠቃቀም ጤናማ ተብሎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ፣ በመደበኛነት ይሄንን ፍላጎት ለማሟላት ከተሞች ያላቸው አቅም (የገንዘብም ሆነ የሰው ኃይል) በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በአንጻሩ ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ሁለተኛም በከተሞች ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች በመሬታቸው መብት ያላቸው ቢሆንም፤ መሬቱ ለልማት ሲወሰድባቸው የሚያገኙት የካሳ መጠን በጣም አነስተኛ ነው፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ቀደም ሲል በግብርና ስራ ሲተዳደሩ የኖሩ እንደመሆናቸውም ወደ ከተማነት ሲጠቃለሉም አዲስ ሕይወት ነው የሚጠብቃቸው፡፡ በመሆኑም በህዝቡ በተለይም በአርሶ አደሩ አካባቢ ቀድሞ መፍራት ስላለ የከተሜነት ሽታ በመጣ ጊዜ አርሶ አደሩ ቶሎ ኢመደበኛ በሆነ መልኩ ወይም በህገ ወጥ መንገድ መሬቱን ያስተላልፋል፡፡
በዚህም ከተማው መሬቱጋ ሳይደርስ ጭምር ተወርሮ የሚጠብቅበት ሂደት አለ፡፡ ይህ ደግሞ አንደኛ፣ ቀድሞ የተያዙት ቦታዎች መሰረተ ልማት የተሟላላቸውና በፕላንም የተመሩ አይደሉም፤ ስለዚህ ለከተሜነት ሊውል የማይገባው መሬት ሁሉ ለከተሜነት እየዋለና ለእርሻ ትልቅ አቅም ያላቸው ቦታዎች ጭምር ወደከተማነት እየተቀየሩ ነው፡፡ በመሆኑም ይሄን ሀብት መልሶ ማግኘት በማይቻልበት አግባብ ሁሉ እየታጣ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ሁለተኛም፣ የከተሞች መስፋፋት ፕላንን ያልተከተለና የጎንዮሽ መስፋፋት እየፈጠረ ስለሆነ ይሄ በቀጣይ በከተሞች ላይ ትልቅ የወጪ ውጤት አለው፡፡ ምክንያቱም አሁን እየተስፋፋ ላለው ከተማ እንደ መንገድ፣ ውሃ፣ መብራትና የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን ማቅረብ ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ወጪ ነው የሚጠይቀው፡፡ አንድ ከተማ ወደ ጎን በተለጠጠ ቁጥር ለዛ የሚያስፈልገውን መሰረተ ልማት ለማቅረብ የሚፈልገው ወጪ በዛው ልክ ነው የሚጨምረው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ከተሞች ከመሬት ማግኘት ያለባቸውን ገንዘብ እያመነጩና እያገኙ አይደለም፡፡
ለከተሞች እድገትና መልካም አስተዳደር መስፈን እንደ ማነቆ
አቶ ብርሃኑ፣ የከተሞች በፕላን አለመመራት ለከተሞች እድገት ትልቅ እንቅፋት ከመሆኑ ባለፈ ለነዋሪዎቻቸው የመልካም አስተዳደር ምንጭ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ አንድ ከተማ ሲመሰረት የራሱ የሆነ ፕሮፋይል ያለው እንደመሆኑ የሚተዳደረውም በዚሁ የከተማው ፕሮፋይል መሰረት ነው፡፡ ከዚህ ፕሮፋይል ደግሞ ፕላን ይሰራል፡፡ ስለዚህ እዛ ላይ የተወከለ ኃላፊ ወይም ባለሙያም ከተማን ሳይሆን ፕላንን ነው የሚያስተዳድረው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ፕላኑን ወደጎን በመተው ከተማውን ለማስተዳደር (ከጸጥታ ስራ ጀምሮ ሌሎች በከተሞች ውስጥ ወደሚከናወኑ ተግባራት) ይኬዳል፡፡
በዚህ መልኩ የፕላን ትግበራን ወደጎን ትቶ ከተማን የማስተዳደር ስራ አሁን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ እንዲስፋፋ፤ ከተሞችም በደላላ እንዲተዳደሩ ያደርጋል፡፡ ለአብነት በኢስቲትዩቱ የተሰራ ፕላን በከተሞች ከንቲባ እጅ አይደም፤ ይሄን ስራ በሚሰሩ በደላሎች እጅ ነው ያለው፡፡ ይህ ደግሞ የከተሞች ፕላን ባለቤት ማጣቱን አመላካች ሲሆን፤ በዚህም በከተማ ደረጃም ባለቤት እንደሌለውና የኦሮሚያ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩትም የተሰጠው ኃላፊነት በጣም ውስን መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ምክንያቱም በክልሉ ከ640 በላይ ከተሞች አሉ፤ በአንጻሩ ኢንስቲትዩቱ አንድ ዋና መስሪያ ቤትና አራት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ነው ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ ኢንስቲትዩቱ ፕላኑን ለማዘጋጀት፣ ለማስፈጸምና ለመከታተል በቂ የሰው ኃይል እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ ነገር ግን ሲቋቋም መንግስት ትኩረት ሰጥቶታል፣ ከተሞች ሰዎች የሚኖሩባቸው እንደመሆናቸው፡፡
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፤ ከተማ ሲፈጠር ንጉስ የሚኖርበት፣ ህግ የሚወጣበትና የሚወሰንበት እንደመሆኑ፤ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንዲሆንና የአገሪቱንም ኢኮኖሚ እንዲደግፍ ተብሎ ነው ፕላን የሚወጣለት፡፡ ሆኖም ይህ እየተደረገ ባለመሆኑ ከተሞቹ በሚፈለገው ልክ እንዳያድጉ፣ ለነዋሪዎ ቻቸውም ምቹ እንዳይሆኑን የመልካም አስተዳደር ማዕከል እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለም ቀጣዩ ትውልድ ዋጋ የሚከፍልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን አሁን ላለው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ሆኖም ይቀጥላል፡፡
አቶ ቃሲም በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በከተሞች ያለው የመሬት አጠቃቀም ችግር በከተሞች እድገት ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል፤ ለነዋሪዎችም ችግር ሆኗል፡፡ ለአብነት፣ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶች ወደ ህጋዊነት ስላልመጡ ቢያንስ ዓመታዊ ግብር እንኳን እየገበሩ አይደለም፡፡ በመሆኑም ከተሞች በዚህ በኩልም ገቢ እያጡ ነው፡፡ ሁለተኛም፣ ወቅቱን የጠበቀና የጊዜውን ገበያ ያማከለ የዋጋ ክለሳም እየተደረገ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በኦሮሚያ ከተሞች ዋጋው ሳይከለስ ለብዙ ጊዜ የቆየና ከወቅቱ የመሬት ገበያ ጋር በጣም የተራራቀ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ከተሞች በአንድ በኩል አቅማቸው እየተመናመነ፣ በሌላ በኩል በህገ ወጥ መንገድ መስፋፋት እየታየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከተሞችን አቅማቸውንም ጭምር እየተፈታተነና አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ ነው፡፡
ይህ ሂደት ደግሞ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ተጽዕኖ ያለው ሲሆን፤ አንደኛ በህገ ወጥ መንገድ እየተስፋፉ ያሉ ቦታዎች ለኑሮ ምቹ የማይሆኑ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራት እንደሚታየውም በቀጣይ ለህገ ወጥነት እየተጋለጡ የሚሄዱበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ለአካባቢ ብክለት በመጋለጥ ለዜጎች ጤና ጉዳት የሚፈጥር ይሆናል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችም የከተማውን ነዋሪ ከከተሜነት ሕይወት ተጠቃሚ ሳይሆን ተጎጂ የሚሆንበትን እድል ያሰፉታል፡፡ በመሆኑም ይሄን ችግር ለመቀልበስ መስራት ያስፈልጋል፡፡
እንደ አቶ ቃሲም ገለጻ፤ ከዚህ ባለፈም የከተሞች የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የዓለም አጀንዳ ነው፡፡ ምክንያቱም የመልካም አስተዳደር በየመድረኩ ከሚወራው ያለፈ ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር በመታጣቱም ነው ወደ ህገ ወጥነቱ እየተሄደም ያለው፡፡ በህጋዊ መንገድ የመጣውን በማስተናገድ ሂደቱም የሚታዩ እጅጉን የተጓተቱ አሰራሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ነባር ይዞታዎችን ወደ ህጋዊነት በማምጣትና ካርታ የመስጠት ስራ መንግስት ከወሰነ ቆይቷል፡፡ ሆኖም በአብዛኛው እየተስተናገደ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት የመልካም አስተዳደር ችግር ሲሆን፤ ሌላኛው የሚሰጠው አገልግሎትም ትልቅ ችግር ውስጥ ያለ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንድም የኪራይ ሰብሳቢነት (ሌብነት)ና ጥቅም ፈላጊነት ጉዳይ በሴክተሩ ትልቅ ማነቆ የመሆኑ ውጤት ሲሆን፤ በችግር ላይ ችግር እየደረበ ያለበት አግባብ ነው ያለው፡፡
የመፍትሄ አቅጣጫዎች
በከተሞች ውጤታማ ፕላን ኖሮ ከተሞች እንዲያድጉና ለነዋሪዎቻቸውም ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ በመጀመሪያ ቅንጅት መኖር እንዳለበት አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በከተማም ሆነ በከተማ ፕላን ላይ የሚሰሩ፣ ፕላኑን የሚያቀርበውም ሆነ የሚያስፈ ጽመው አካል በቅንቅት ስራዎችን ማከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ላይ የተመደቡ የመንግስት አካላትም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻዎች የሰው ኃይልን ጨምሮ በተለያየ አቅም ግንባታ፣ በመሳሪያ ድጋፍና ሌሎችም የሀብት ድጋፎች ዙሪያ መቀናጀት ከቻሉ ስራውን ማሳለጥ ይቻላል፡፡ ሁለተኛም ፕላኑ የሚሰራው መሬት ላይ ቢሆንም ለህብረተሰቡ ነው የሚሰራው፡፡ በመሆኑም ለፕላኑ ውጤታማነት ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ህብረተሰቡ በዚህ መልኩ ተረድቶም ባለቤት ሊሆን ይገባል እንጂ፤ ሦስትና አራት ወይም ሃያ ሰው ሰብስቦ ህብረተሰቡ ተሳትፎ አድርጎበታል በማለት የሚሰራው ስራ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም ህብረሰተቡ ግንዛቤ ጨብጦና የባለቤትነት ስሜት ፈጥሮ የፕላኑ አስፈጻሚና ጠባቂ እንዲሆን ማድረግ የግድ ይላል፡፡
አቶ ቃሲም በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የከተሞች መሬት አጠቃቀም ችግርን ከማቃለል አኳያ ከሚቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ማማከር አንዱና ትልቁ የህብረተሰብ ተሳትፎን ማጠናከር ነው፡፡ ሁለተኛም፣ የሰው ሃይሉን ማብቃት ነው፡፡ የሰው ሃይሉን የማብቃት ሂደቱ ከአመለካከት ጀምሮ መስራትን የሚጠይቅ ሲሆን፤ ችግሩ የአንድና የሁለት ሰው ሳይሆን የዜጎችና የአገርም ችግር እንደመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡ ለዚህም ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ ሰዉ ያለ አግባብ ከመበልጸግ ይልቅ በላቡ ሰርቶ መበልጸግን አጀንዳ አድርጎ በማሰራት ይሄንን የሚጸየፍ ትውልድ መፍጠር መቻል ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው ትውልድም የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ፣ የተሻለ አመለካከት ያላቸውም ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡትንም እየለዩና እየሸለሙ በዓርዓያነት ሰው እንዲከተላቸው እያደረጉ መሄድም ተገቢ ነው፡፡ ወደ ህገወጥነት የሚሄደውንና ሰውን የሚያጉላላውን ደግሞ እየለዩ ከምክር እስከ ህጋዊ እርምጃ መውሰድም እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን የሚታየው የፍረጃና ሁሉንም ወደዛ የመግፋት አካሄድ መታረም የሚገባው ነው፡፡
ሆኖም ችግሩን ከመቀየር አኳያ ዋናው የመረጃ ጉዳይ ሲሆን፤ አሁንም የመረጃ ችግር ከመሰረቱ እስካልተፈታ ድረስ ዋሻነቱ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ለመልካም አስተዳደሩም ሆነ ለአገልግሎት መጓተቱ መንስኤዎቹ እነርሱ በመሆናቸው እዛጋ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ እነዚህ መረጃዎች ደግሞ ህብረተሰቡ በቀላሉ እንዲያገኛቸው ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፤ ህጎችም ግልጽና ተደራሽ መሆን አለባቸው፡፡ ምክንያቱም አሁን ላይ ብዙዎቹ የመሬት ሕጎች አይታወቁም፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ መብትና ግዴታውን በአግባቡ የሚረዳበትን መንገድ መፍጠር ይገባል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም በዚህ ዙሪያ ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትም በጥቂት ባለሙያዎችና ደላሎች እጅ ያሉ ህጎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ ህብረተሰቡ ላልተገባ ወጪ እንዳደረግ ማድረግ ይገባል፡፡

ወንድወሰን ሽመልስ

Published in ፖለቲካ

ገና ከረፋዱ የወጣውና አናት በስቶ የመግባት ሃይል ያለው የፀሃይዋ ሙቀት ከነፋሻማው አየር ጋር ተደማምሮ አንዳች ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ምንም እንኳን አናቴ ቁልቁል በሚወርደው ሙቀት፤ ዓይኖቼም በነፋሱ ቢቸገሩም የምጓዘው ወደ አዳማ ከተማ ነውና ስለሷ ከተዜሙ ዘፈኖች መካከል የአንዱን በምስል የተደገፈ ሙዚቃ እያዳመጥኩ፣ እናት የቦለቄ ንፍሮ ጨብጠው ለልጁ ሲያሲዙት ስለሚያሳየው የተንቀሳቃሽ ምስል እያሰላሰልኩ የቦለቄ ምርትን ከሚቀበለው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዳማ ቅርንጫፍ ደረስኩ፡፡
በጊቢው ውስጥ በርካታ ቦለቄ የያዙ ማዳበሪያዎች ላይ በላይ ተደራርበውና ተሽከርካሪዎች ላይ ተጭነው ይታያሉ፡፡ ሜዳው ላይ በተነጠፈ ሸራ የተወሰነው ምርት ፈስሶ ሰራተኞች ስራቸውን ሲሰሩ ተመለከትን፡፡ ይሄኔ ታዲያ ምርቱ በዚህ መልኩ መያዙ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ የለም ይሆን? የሚል ጥያቄን አጫረብን፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸረችና በርካታ ተግባራትንም ለማከናወን መልከዓ ምድራዊ አቀማመጧ ምቹ እንደሆነ ሲገለፅ ቢደመጥም በዚህ ልክ ዕድገት ላለማስመዝገቧ ደግሞ የአፈፃፀም ችግር በሚል ምክንያት ይቀመጣል፡፡ እናም የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ለቦለቄ ምርት አመቺ መሆኑ ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመው ቅርንጫፍም ከዓመት ዓመት ገቢ የሚያደርገው ምርት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ተከትሎ ከቅርንጫፉ ኃላፊ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ፡፡
አጠቃላይ ሁኔታ
በ2002 ዓ.ም የተቋቋመው ቅርንጫፉ አራት ድርጅቶች በጋራ በሚጠቀሙበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ሰብል ምርትን ለመቀበል በሚል ስራውን እንደጀመረ የሚገልፁት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዳማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ጅራታ፤ ቅርንጫፉ ቦለቄ ላይ እንደሚሰራ ይናገራሉ፡፡ ከወረዳዎች ወደ ተቋሙ የገባውን ምርትም ደረጃ የማውጣት፣ ምርቱን ተቀብሎ በማቆያ ማስቀመጥ እንዲሁም የምርቱን መረጃ ለበላይ አካል ለግብይት ማስተላለፍ ስራዎችን ይሰራል፡፡ ምርቱ ሲሸጥም ለገዢው ማስተላለፍ የዚሁ ማዕከል ኃላፊነት ነው፡፡
ወደ ቅርንጫፉ ነጭና ቀይ የቦሎቄ ሰብል ዝርያዎች እንደሚገቡ የሚናገሩት አቶ ዘላለም፤ 95 በመቶ የሚሆነው ስራ ግን ነጭ ቦለቄ ላይ እንደሚሰራ ያስረዳሉ፡፡ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ እንዲሁም ከደቡብ ክልሎች የሚቀርበው ቦለቄ አፈፃፀሙም ካለፉት ዓመታት ጋር በንፅፅር ሲታይ በዘንድሮ በጀት ዓመት የተሻለ ነው፡፡ ምንም እንኳን በአገሪቱ ምርታማነቱን ማሳደግም ሆነ በጥራት የተሻለ አቅርቦት ማግኘት የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ቢኖርም፤ የተጠናከረ የጋራ አሰራር አለመኖሩና ህገ ወጥነቱ ሸብቦት ወደ ኋላ እየጎተተው ይገኛል፡፡ ይህም ባለው አቅም ልክ እየተሰራ አለመሆኑን ያመላክታል፡፡
ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የአቅርቦት መጠንም እስከ 2005 ዓ.ም የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ዋጋ ጥሩ ስለነበር ከ385 ሺህ ኩንታል እስከ 500 ሺህ ኩንታል ደርሶ እንደነበር አቶ ዘላለም ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ቅበላው ከአምስት መጋዘን ወደ አንድ ዝቅ በማለት 56 ሺህ ኩንታል ብቻ አድርጎታል፡፡ በዘንድሮ በጀት ዓመትም ምንም እንኳን በቂ ነው ባይባልም መልሶ ማንሰራራት በማሳየት የመቀበል አቅሙ ወደ 128 ሺህ ኩንታል ማድረግ ተችሏል፡፡
ችግሮች
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዳማ ቅርንጫፍ የጥራት ሱፐርቫይዘር አቶ አወቀ አቅናው ገለጻ፤ በዘርፉ የቅንጅት ጉድለት በመኖሩ 39 በመቶ ያክል ለዓለም ገበያ የማይውል ምርት እንዲገበያይ ይፈቅዳል፡፡ ላኪዎችም በመውሰድ ጥራቱን እንዲጠብቅ አድርገው ለውጭ ገበያ ያቀርቡታል፡፡ ይህ ደግሞ በአንድም በሌላ መልኩ ገቢ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አለ፡፡ ገበያ የተለያዩ አካላት ተሣትፎ ውጤት ቢሆንም ይህን ተገንዝቦ ቅንጅታዊ ስራ መስራት ላይ ግን ክፍተት ይታያል፡፡
በዚህም ያለፉት ሶስት ዓመታት መረጃ እንደሚያሳየው ከቀረበው ምርት 47 በመቶ ደረጃውን ባለማሟላቱ ጥራቱን ጠብቆ እንዲመጣ ተመላሽ ተደርጓል፡፡ ይህም የተለያዩ አካላት ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ በቅንጅት እየሰሩት ያለው ስራ ክፍተት እንዳለበት አመላካች ነው፡፡
እንደ አቶ አወቀ ገለፃ፤ የስራው ክፍተት በምርምር ማዕከል ምርጥ ዘር ከማቅረብ ይጀምራል፡፡ ከአርሶ አደሩ የማሣ ዝግጅት ጀምሮም ለውጭ ገበያ ቀርቦ ገቢ እስኪያመጣ ያለው ሂደት በጥንቃቄና በቅንጅት ካልተሰራ በአሁኑ ወቅት ቦለቄ ከአገሪቱ እጅ እየወጣ ነው፡፡
በዋናነት በዘርፉ ከሚስተዋሉት ችግሮች መካከል አንዱ የግንዛቤ ማጣት ነው፡፡ ይሄም አምራች፣ አቅራቢና የባለድርሻ አካላት ጋር ከታችኛው እስከ ላይኛው መዋቅር ተቀናጅቶ ያለመሰራቱ ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት እንዳያመጣ እያደረጉት ከሚገኙት ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከ2005 ዓ.ም በኋላም ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለ ሲሆን ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ዋጋ ነው፡፡
በዚሁ ችግር ላይ ተደማምሮም ህገወጥነት መስፋፋቱ ጥቂቶችን በማክበር በአገር ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ የትየለሌ እንደነበር ሥራ አስኪያጁ ያስታውሳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከታች ጀምሮ ያለው አሰራርና ቁጥጥር መላላቱ ከአምራች ጀምሮ እስከ አገር ጉዳት አድርሷል፡፡ በርካቶችም ከማረት እንዲወጡ አድርጓቸዋል፡፡ ከ2009 ዓ.ም በኋላም የዋጋ መነቃቃት በመፈጠሩ በተያዘው በጀት ዓመት የማንሰራራት ሁኔታ እየታየ ይገኛል፡፡
ምክረ ሀሳብ
መስሪያ ቤቱ ከብልሹ አሰራር ጋር ተያይዞ የሚነሱበት ችግሮች እንደነበሩ የሚያወሱት ሱፐርቫይዘሩ፤ ይህን ተከትሎ ባለፉት ሶስት ዓመታት ትልልቅ ቅሬታዎችን በማስተናገዱ ሁለት የለውጥ እርምጃዎችን አድርጓል፡፡ ትልቅ ማዕበል ውስጥ እንዳለ የሚያመላክቱም ችግሮች በመኖራቸው ተቋሙ ራሱን መፈተሸ እንዳለበት በማንሳት ባለሙያውም በብልሹ አሰራር ውስጥ የተዘፈቁ ካሉ መታገልና የጋራ ስራ መስራት ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን ትልቅ አስተዋፅዖ በመገንዘብ ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊወጣ የሚያስችለው ስራ መከናወን ይኖርበታል፡፡
ምርቱ በድንበር አካባቢ የሚመረት ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው በህገወጥ ንግድ ከአገር ይወጣል፡፡ ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ከመጉዳቱ ባሻገር የምርት ጥራት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ አስተዋፅዖም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ለዚህም ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ላይ ማተኮር የማይተካ ሚና አለው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ተቀናጅቶ በመስራት በህገወጥ መንገድ የሚወጣውን ምርት መቆጣጠር በተያያዥነት ሊሰራ እንደሚገባ ያመላክታሉ፡፡ በመሆኑም በዚህ ተግባር ላይ ተሣታፊ የሆኑ አካላትን ወደ ህጋዊነት ማሸጋገር ተገቢ ይሆናል፡፡ ጎን ለጎንም የሚጠበቅበትን ተግባር ያላከናወነም ተጠያቂ ሊደረግ ይገባል፡፡
በተለያዩ ችግሮች የታሰረው ይህ ዘርፍ ሰፊ ስራ ቢሰራም በቂ አገልግሎት መስጫ እንኳ እንደሌለው ሥራ አስኪያጁ ይጠቁማሉ፡፡ ድርጅቱ ከ325 በላይ ነጋዴዎችን፣ የአገልግሎት ህብረት ስራ ማህበራት፣ እንዲሁም በግል አምርተው የሚያቀርቡትን የሚያገለግል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የራሱ የሆነ ቢሮና መጋዘን እንዲሁም ሚዛን የለውም፡፡ በመሆኑም የተሰሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት እነዚህ ጉዳዮች በተጓዳኝነት ሊታዩ ይገባል፡፡
ቀጣይ አቅጣጫዎች
ባለሀብቶች ምርትን በጥሬው ከመላክ ይልቅ ዕሴት መጨመር ላይ የሚያተኩሩበት ሁኔታ ቢመቻች የተሻለ ገቢን መፍጠር እንደሚቻል አቶ አወቀ ይገልፃሉ፡፡ በሌላ በኩል ከተቋሙ ጋር መስራት ያለባቸው አካላት ባለስልጣኑን ጨምሮ በሚፈለገው ደረጃ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ በዚህም በህገወጥ መንገድ የሚወጡ ምርቶች ወደ ተቋሙ እንዲገቡ ማድረግ ላይ ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል፡፡
ትልቁ የትኩረት አቅጣጫ ከምርት ገበያ ባለስልጣን ጋር በመቀናጀትም የግንዛቤ ስራውን ማሳደግ ይሆናል፡፡ ይህም ከታች እስከ ላይ ያለውን ሂደት አጠናክሮ በማስቀጠል የጋራ ቁጥጥር ሥርዓቱን ለማሳለጥ ያስችላል በማለት በቀጣይ የሚሰሩት ስራዎች ዘርፉን ለማሳደግ የሚኖራቸውን ቀላል የማይባል ድጋፍ ሥራ አስኪያጁ ያመላክታሉ፡፡

ፍዮሪ ተወልደ

Published in ኢኮኖሚ

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ወር አጋማሽ ላይ የናይጄሪያ ወታደራዊ ኃይል በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ጉዛማላ እና ቡርኖ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ከሁለት ሺ በላይ ሰዎች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የመከላከያ ቃል አቀባዩም ይህ እንቅስቃሴ ለመከላከያ ኃይሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ የጦር ኃይል አባል የሆኑት ሉተነት ጄነራል ታኩር ቡራታኢስ፤ በሰሜን ናይጄሪያ አካባቢ ከቡርኖ ከተማ የተሰደዱና ከቦታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአካባቢው የነበረውን የቦኮሀራም ሽብርተኛ ቡድን እንዲለቅ ከተደረገ በኋላ ብዙ ሰዎች ከፈረንጆቹ ሚያዝያ ጀምሮ ወደ አካባቢው መመለስ ጀምረዋል፡፡ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ወር አጋማሽ ላይ ጓዚማላ ከተማ የተሰደዱ ሰዎች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ በተደረገው ጥሪ ብዙዎች እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ የአካባቢው ባስልጣናትም በቦታው በመገኘት የአቀባበል ስነስርዓት እያደረጉላቸው ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው የመመለሱ ሁኔታ ላይ እክል የሚፈጥሩ ሁኔታች አልታጡም፡፡ ይሄም አንድም፣ ተፈናቃዮቹ ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱበት መንገድ ደህንነቱ የተጠበቀ ባለመሆኑ ሲሆን፤ ሁለተኛም ቀድሞ የሚኖሩበት ቤት የፈረሰ በመሆኑ መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ተፈናቃዮቹ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ወታደሮች እንዲያጅቧቸው እንደሚደረግ፤ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚሆኑ ቁሳቁሶች እየተሰጧቸው ይገኛሉ፡፡
ወታደራዊ ኃይሉ ተፈናቃዮቹን አጅቦ ወደ ቦታቸው እየመለሰ ቢሆንም የወታሮቹ ማጀብ የተፈናቃዮቹን ደህንነት ያስጠበቀላቸው አይመስልም፡፡ በአካባቢው የተጠናከረ ጥበቃ ባለመኖሩ ምክንያት ወደ አካባቢያቸው የተመለሱት ሰዎች በድጋሚ የመሰደድና የመሞት ዕጣ ተጋርጦባቸዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ጥሪ ከመደረጉ አንድ ቀን በፊት በዳምብዋና በቡርኖ ከተሞች ኢድ አልፈጥር በሚያከብሩ ሰዎች ላይ የቦምብ ጥቃት ተሰንዝሮ ነበር፡፡ በዚህ ጥቃት ብዙ ሰዎች ሂይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በጥቃቱ የቦኮሀራም እጅ እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን፤ ሽብርተኛ ቡድኑ በቅርቡ ከካሜሮን በመመለስ ላይ ባሉ ስደተኞች ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ነበር፡፡
በፈረንጆቹ ባለፈው ወር መጀመሪያ አካባቢ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ ባደረገው ሪፖርት በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ቦኮሀራም በንፁሐን ዜጎች ላይ በአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ እና ወታደራዊ ጥቃት አድርሷል፡፡ የዕርዳታ ሠራኞችና በአካባቢው የሚገኙ ሚሊሻዎች በአካባቢው በተለይ በቡርኖ ከተማ የፀጥታ ችግር መኖር ተመላሾቹ ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል እያስጠነቀቁ ይገኛሉ፡፡
የአገር ውስጥ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ደግሞ ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ የሚገኙት ነዋሪዎች የአመላለሱ ሁኔታ ብዙ ነገሮች የሚጎድሉት በመሆኑ ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ቫንጋርድ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በቡርኖ 350 ሺ ተመላሾች በአካባቢው ባለው ችግር የሚኖሩበት ካምፕ ውስጥ ለመቆየት ወስነው ነበር፡፡ ለዚህ ችግር መባባስ ደግሞ የናይጄሪያው ፕሬዚዳትን ቡሀሪ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በተለይ ቦኮሃራምን በተመለከተ የገቡትን ቃል አለመፈጸማቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡
እአአ 2015 በተደረገው የፕሬዚዳንት ምርጫ ላይ የተወዳደሩት መሀመድ ቡሀሪ ከተመረጥኩ ቦኮሀራምን ከአገሪቱ አስወጣለሁ ብለው ቃል ገብተው ነበር፡፡ እአአ የካቲት 2015 ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ ቦኮሀራም ከያዘው ይዞታ እደሚያስለቅቁት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ሁኔታ ቡሀሪ የሚሊዮን ናይጄሪያን ልብ ገዙ፡፡ ህዝቡም በተደረገው ምርጫ ድምፁን ሰጣቸው፡፡ ከተወዳዳሪዎቻቸው በመላቅ 53 በመቶ ድምፅ በማግኘት ስልጣን ጨበጡ፡፡
ሆኖም ቡሀሪ የፀጥታውን ሁኔታ ለማስጠበቅ እንቅስቃሴ የጀመሩ ቢሆንም የገቡትን ቃል በቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ኡማሩ ያር አዱአ እና እን ጎድላክ ጆናታን ወቅትም የነበሩ ጉዳዮችን የመፍታት ሃሳብ ነው፡፡ በመጀመሪያ የፕሬዚዳንትነት ንግግራቸው ሽብርተኞችን መዋጋት ላይ ከፍተኛ ሥራ ይጠብቀናል የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ በአካባቢው የሚገኘውን የቦኮሀራም ሽብርተኛ ቡድን ለማጥፋት ሁሉም ህዝብ መተባበር እንዳለበት በንግግራቸው ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በየአካባቢው ፍርሀቶችና በሰርጎ ገቦች ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ናይጄራውያን በፕሬዚዳንቱ የተገባላቸውን ቃል አይረሱም፡፡ የህዝቡ ተስፋ ዓመታት በሄዱ ቁጥር እያደገ ሲመጣ በመንግሥት ላይ ጫና መፍጠር ጀመረ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ስልጣን ከያዙ ሰባት ወራት በኋላ ቦኮሀራም በተለያዩ መንገዶች ከይዞታው እንዲለቅ መደረጉን አስታወቁ፡፡ ቦኮሀራም ይዞታን በመልቀቁ የተሰደዱ ሰዎች ወደ ቦታቸው መመለስ እንደሚችሉና ሌሎቹ ደግሞ መሰደድ እንዲያቆሙ ተገልፆም ነበር፡፡ በዚህ ንግግራቸው ብዙዎች የተበሳጩ ቢሆንም የናይጄሪያ መንግሥት ከቦታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ሥራ ለመጀመር እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመረ፡፡
ከሦስት ዓመት በኋላ በአገሪቱ ዳርቻዎች ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ህዝብ በላይ በመጠለያ ውስጥ ይገኛል፡፡ ቦኮሀራምም በየዓመቱ በተለያዩ አካባቢዎች በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መግደሉን አላቆመም፡፡ ይህ ሁኔታ ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ ዓመት በሚያደርጉት የፕሬዚዳንትነት ምርጫ እክል ይፈጥርባቸዋል፡፡
በአሁን ወቅት ቡሀሪ ላይ የተደቀነው ፈተና በተመረጡበት ወቅት ቦኮሀራምን ለማጥፋት የገቡትን ቃል አለመፈፀማቸው ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በገቡት ቃል መሰረት ባለመሥራታቸው ከተቃዋሚዎቻቸው ትችት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ቡሀሪ እአአ 2019 ላይ በሚደረገው ምርጫ ድምፅ ሊያሳጣቸው ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ባለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ቡሀሪ እየሠሩት ባለው ሥራ እየደረሰባቸው ያለው ትችት ተገቢ ነው ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ቡሀሪ የገቡትን ቃል አለመፈፀም ብቻ ሳይሆን እሳቸው የጀመሯቸው ሥራዎች አብዛኛዎቹ የወደቁ በመሆናቸው ተቃዋሚዎች እጃቸውን እንዲቀስሩባቸው አድርጓል፡፡ በአሁን ወቅት ሁሉም ናይጄራዊያን ቦኮሀራምን መንግሥታቸው እንዳላሸነፈ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን በሰሜን ናይጄሪያ አካባቢ ያለውን ቀውስና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መንግሥታቸው እንዲፈታላቸው ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡
የናይጄሪያ መንግሥትም በአካባቢው የፀጥታ ጥበቃ ለማድረግ ማስመስሎችና የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ እንቅስቃሴዎች ታይተዋል፡፡ በቦኮሀራም ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች በመርዳትም እአአ 2019 በሚደረገው ምርጫ ድምፅ ለማግኘት ጥረቶች ይታያሉ፡፡ ሁሉም ሰው ከቦኮሀራም ጋር ያለው ግጭት እንዲቆምና በተለያዩ ቦታዎችና አገራት የተሰደዱ ህዝቦች እንዲመለሱ ይፈልጋል፡፡ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችለው ግን በአገሪቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንዲረጋጋ በማድረግና ከቦታቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች መኖሪያ መሥራት ሲቻል እንዲሁም ከየአገሩ በመመለስ ላይ ለሚገኙት ተፈናቃዮች ለደህንነታቸው ትኩረት ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በፍጥነት መከናወን ካልቻሉ የቡሀሪ አስተዳደር ከፍተኛ እክል ሊገጥመው ይችላል፡፡
ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ቦኮሀራም በካሄደው ጥቃት ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ከሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ተፈናቅሏል፡፡ በተካሄደው መብት ጥሰት በሰሜን ምሥራቅ የሚገኙ አርሶ አደሮች በጉልበት ከይዞታቸው እንዲፈናቀሉ ተደርጓል፡፡ በተከታታይም በአገሪቱ የምርት ማሽቆልቆል፣ የምግብ ዋጋ መጨመር እና የምርቶች ተፈላጊነት በዓለም ገበያ መቀነስ እንደ የመን፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ገጥሟታል፡፡
የናይጀሪያው ገዥ ፓርቲ ኤ.ፒ.ሲ ለሁለት መከፈሉን የዓለም መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ይገኛሉ፡፡ መከፋፈሉ የተፈጠረው ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሀሪ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ ለመወዳደር እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት ነው፡፡ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2015 ወደ ሥልጣን የመጣው ኤ.ፒ.ሲ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ ነበር የመከፋፈል ስጋት ያንዣበበበት፤ ይህም ስጋት በቅርቡ በተደረገ ሀገራዊና አካባቢያዊ መሪዎች ምርጫ ላይ ፈንድቶ «አንዳንድ ቀንደኛ የፓርቲው አባላት በአግባቡ አልተስተናገድንም» እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡
የፓርቲው መከፈል የታወቀው ተከፍሎ የተደራጀውና ራሱን «ተራማጁ ኤ.ፒ.ሲ» ብሎ የሰየመው ቡድን በቀድሞው የፕሬዚዳንት ቡሀሪ ወዳጅ ቡባ ጋላዲማ መመራት መጀመሩ ሲገለጽ ነው፡፡ ተራማጁ ኤ.ፒ.ሲ ከፍተኛ የፖሊቲካ ሥልጣን ባላቸው የሕግ መወሰኛው ፕሬዚዳንት፣ በታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤና በአንዳንድ የክልል መሪዎች እንደሚደገፍም ተገምቷል፡፡ «የፕሬዚዳንት ቡሀሪ መንግሥት ብቃት የለውም» ማለታቸውም ታውቋል፡፡ በመጪው የካቲት በሚካሄደው ምርጫ ተገንጣዩ ቡድን ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር በመሆን ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡሀሪን እንደሚገዳደርም ተሰምቷል፡፡

መርድ ክፍሉ

Published in ዓለም አቀፍ

አብዛኞቻችን ጠዋት ጠዋት ወደ ስራ ከመግባታችን በፊት ጫማችንን የማስጠረግ ልማድ አለን፡፡ እኔም ብዙውን ጊዜ የዚሁ ልማድ ተጋሪ ነኝ፡፡ ማለዳ ከቤት ከወጣሁ በኋላ ግማሹን መንገድ በታክሲ እጓዛለሁ፡፡ ቀሪውን መንገድ ደግሞ በእግሬ እጓዝና የምሰራበት ተቋም አካባቢ ስደርስ ወደ አንድ የሊስትሮ ደንበኛዬ ጎራ ብዬ ጫማዬን አስጠርጌ ወደ ቢሮ እገባለሁ፡፡
በዚህ የዘወትር እንቅስቃሴዬ ከሊስትሮው ጋር የብዙ ጊዜ ደንበኝነት በመመስረታችን ጨዋታው ከጫማ ማስጠረግም በላይ እንደ አንድ የስራ አካል ይናፍቀኛል፡፡ ምክንያቱም የዚህ ሊስትሮ መልካም ባህርይና ስነምግባር የተለየና ጥቂቶች ብቻ የሚጋሩት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከሚጠረገው ጫማ ይልቅ ከዚህ ወጣት ጋር የሚኖረኝ ቆይታ ይማርከኛል፡፡ በአገራችን የበለፀገ አዕምሮ የሚገኝባቸው ቦታዎች ብዙ መሆናቸውንም ያሳየኛል፡፡
ደሳለኝ ዘብሬ ይባላል፡፡ተወልዶ ያደገው በደቡብ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ አንዲት የገጠር ቀበሌ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም የተከታተለው በዚው አቅራቢያ በምትገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ቤተሰቦቹ በእርሻ ስራ የሚተዳደሩ ሲሆን አምስት ወንድሞችና አራት እህቶች አሉት፡፡ ቤተሰቡ ግን እነዚህን ሁሉ የቤተሰብ አባላት ለማስተዳደር የሚያስችል በቂ አቅም የለውም፡፡ በዚህ የተነሳ ሶስት ወንድሞቹና ሁለት እህቶቹ ከአካባቢው ለቀው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በተለያዩ ጥቃቅን ስራዎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን ይደጉማሉ፡፡
ደሳለኝም 15 አመት ሲሞላው ልክ እንደ ወንድሞቹ ሰርቶ ራሱን ሊችል ወደ አዲስ አበባ አቀና፡፡ አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ ያየው ነገር ግን እንደጠበቀው አልነበረም፡፡ የአዲስ አበባ የኑሮ ሁኔታ ጥሎት ከመጣው የአኗኗር ስርዓት የተሻለ ሊሆንለት አልቻለም፡፡ ቀደም ሲል አዲስ አበባ የገባው ታላቅ ወንድሙ የሰጠውን የሊስትሮ እቃና የጫማ ቀለም ይዞም ስራውን ከጀመረ እነሆ ስድስት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በመጀመሪያ የአዲስ አበባ ቆይታው ጫማቸውን ከሚያስጠርጉ አንዳንድ ሰዎች ጋር የገጠመው አለመግባባት፣ የሚያገኘው ጥቂት ሳንቲም ለቁርስ፣ ምሳና እራት በቂ አለመሆን እንዲሁም የማደሪያ ቦታ ምቹ አለመሆን ተደማምሮ ኑሮውን አስቸጋሪ አደረገበት፡፡ እሱ እንደሚለው አንድ ወቅት ላይ ሁሉንም ነገር ጥሎ ወደ ተወለደበት አካባቢ ለመመለስም ፈልጎ እንደነበር ያስታውሳል፡፡
ያም ሆኖ ግን ደሳለኝ ቀስ በቀስ ኑሮውንም፣ ስራውንም አካባቢውንም እየለመደ በመምጣቱ መረጋጋት ጀመረ፡፡ ስራውን መልመዱና ከአስተዳደጉም ጀምሮ ይዞት የኖረው መልካም ባህርይው ተደማምሮ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አደረገው፡፡ በርካታ ሰዎችንም በስራው አጋጣሚ ተዋወቀ እና የተሻለ ህይወትን በዚህ መልኩ ተለማመደ፡፡
ደሳለኝ በዚህ መልኩ ህይወቱን ካስተካከለና ስራውን ከተለማመደ በኋላ ስራውን እያሰፋ መጣ፡፡ በስራውም ጫማ ከመጥረግ በተጨማሪ የተለያዩ የጫማ ገበር፣ ማስቲካዎችና ከረሜላዎች፣ የሞባይል ካርድ፣ ብስኩቶች ወዘተ ይሸጣል፡፡ በዚህም ገቢው ቀስ በቀስ እየተሸሻለ መጣ፡፡ የወደፊት ህይወቱን ግን በዚህ መልኩ መግፋት አልፈለገም፡፡ እናም መማር እንዳለበት ወሰነ፡፡ ትምህርቱንም ካቋረጠበት መማር ቀጠለ፡፡
እነሆ ዛሬ ደሳለኝ በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በማታው የትምህርት መርሃግብር የሁለተኛ አመት የአካውንቲንግ ተማሪ ነው፡፡ ታናሽ ወንድሙንም ከገጠር በማስመጣት አብሮ ይሰራሉ፡፡ ወንድሙም ትምህርቱን እንዲቀጥል አድርጎ 10ኛ ክፍል ደርሷል፡፡ ደሳለኝን ልዩ ከሚያደርጉት ባህርያቱ ውስጥ አንዱ ደግሞ ባለው ትርፍ ጊዜ ሁሉ ጎበዝ አንባቢ መሆኑ ነው፡፡ አንድ ቀን በአጠገቡ ተቀምጦ የነበረውን ቦርሳ ሲከፍት በውስጡ የታጨቁትን መጻህፍት ስመለከትም ይህ ወጣት ምን ያህል የነገ ተስፋ ያለው መሆኑን አስገነዘበኝ፡፡ እናም እንዲህ አይነት ወጣቶች በአገራችን ቢበራከቱ የሚኖራቸውን አስተዋፅኦ ሳስብ ተስፋ አደረብኝ፡፡
የደሳለኝን የህይወት ተሞክሮ ያነሳሁት ያለምክንት አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ምን ያህል ወጣት ስራ የለም በሚል ቤቱ እንደተቀመጠና፣ ከፊሎቹም አገር ጥለው እንደሄዱ እንዲሁም ምን ያህሎቹ ለችግር እንደተዳረጉ በተለያዩ አጋጣሚዎች መረዳቴ የደሳለኝ ተሞክሮ ትምህርት ሊሆን ይችላል ከሚል መነሻ ነው፡፡
ደሳለኝ ካጫወተኝ ቁምነገሮች ውስጥ አንዱ ስደትን የተመለከተ ነው፡፡ እሱ እንደነገረኝ በተወለደበት አካባቢ አብዛኛው ወጣት ለስደት ተዳርጓል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ያልተሳካላቸው ሲሆን በዚህ አስከፊ ስደት የተነሳም ህይወታቸውን ያጡት በርካታ ናቸው፡፡
እሱና ወንድሞቹም በአንድ ወቅት የዚህ ስደት አካል ለመሆን ፍላጎት እንደነበራቸው ያስታውሳል፡፡ ሆኖም እሱ በልጅነት አእምሮው የስደትን አስከፊነት ከራሱ ሳይሆን ከጎረቤቶቹና ከሌሎች ዘመዶቹ በመማሩ ይህንን ሃሳብ እርግፍ አድርጎ በመተው በአገሩ ውስጥ ሰርቶ ለመለወጥ እንደወሰነ ይናገራል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ በአገራችን የሚገኙ እናቶችና አባቶችን እንዲሁም መላው ህዝባችንን ከሚያሳዝኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በስደት ምክንያት የሚፈጠር የዜጎቻችን ለአደጋ መጋለጥ ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣዎች በህገወጥ መንገድ በኮንቴይነር ተጭነው ሲጓዙ አልያም በርካታ አፍሪካውያንን በተለይም ‹‹ኢትዮጵያውያንን ይዛ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ሰጠመች፤ በውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሞቱ ወዘተ›› የሚሉ ዜናዎች የተለመዱ ናቸው፡፡ በሌላም በኩል በተለያዩ የአረብ አገራት በተለይ እህቶቻችን ከፎቅ ተወርውረው የመውደቃቸውና በአሰሪዎቻቸው በሚደርስባቸው ስቃይና እንግልት የተነሳ ለሞራልና ለስነልቦና ጉዳት ሲዳረጉ ማየትም የተለመደ ነው፡፡
እንዲህ አይነት ችግሮች የሚያጋጥሙን ደግሞ ውጭ አገር ሄጄ ካልሰራሁ እዚህ ሆኜ ሊያልፍልኝ አይችልም በሚል የተሳሳተ መንፈስ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ለመሄድ በሚደረግ ጥረት ነው፡፡ በርግጥ ውጭ አገር ሄዶ መስራት ወደ ፈለጉት ቦታ የመንቀሳቀስ ህገመንግስታዊ መብት ነው፡፡ ማንም ዜጋ የሚፈልግበት አገር ሄዶ ቢሰራ ከራሱም አልፎ አገር ሊጠቅም ይችላል፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥም ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማሰብና ለዚህ ዝግጁ መሆን ደግሞ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ እና ሰፊ የቆዳ ሽፋን አላት፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን 65-70 ከመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ በወጣት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ አምራች ኃይል ነው፡፡ ይህ ደግሞ በራሱ አገራችን ሰፊ ሀብት እንዳላት የሚያመላክት ነው፡፡
በሌላ በኩል መንግስትም የተለያዩ አሰራርና የመፈፀም ችግሮች ቢኖሩበትም በተለይ ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በአገር ውስጥ ሰርቶ ለመለወጥ የሚቻልባቸውን መልካም አጋጣሚዎች ፈጥሯል፡፡ ይህንን እድል ተጠቅመው የተለወጡና ከምንም ተነስተው ባለሀብት መሆን የቻሉ በርካታ ዜጎችን ማንሳትም ይቻላል፡፡
አንድ ህዝብ ለለውጥ ዝግጁ ከሆነና የመንግስት ቁርጠኝነት ከታከለበት ሊያድግ እንደሚችል በተጨባጭ ከዓለም ተሞክሮ አይተናል፡፡ የዚያኑ ያክልም ህዝብ ከልማት ይልቅ በፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሆኖ ግጭትና የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገባ ደግሞ የአገር ውድመት እንደሚከሰትም በተጨባጭ ተመልክተናል፡፡
ለእነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ቻይና፣ ህንድ እንዲሁም አንዳንድ የአረብ አገራት ጥሩ ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቻይና ከግማሽ ምዕተ አመት በፊት የነበረችበት ሁኔታ ዜጎቿ የሚበሉት እንኳ እስከሚያጡ ድረስ ለችግር የተዳረጉበት ክፉ ዘመናቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በሌላ በኩል የህዝብ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣ በመሆኑ የወደፊት ቻይናውያን ሕይወት ለአደጋ የተጋለጠ እንደነበርም ታሪክ ይነግረናል፡፡ በዚህ የተነሳ ከዚህ አስከፊ ድህነት ለመውጣት የመጀመሪያ እርምጃቸው ፀረ ድህነት ትግል ማካሄድ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ የስራ ባህላቸውን መለወጥ የመጀመሪያው እርምጃቸው ነበር፡፡
ቻይናውያን የስራ ብቻ ሳይሆን የአመጋገብ ስርዓታቸውም ከዚሁ ከድህነት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዘመኑ ለአንድ ቻይናዊ ምግባ ማግኘት ከባድና አስቸጋሪ ስለነበር ይህንን ለመቋቋም አመጋገብ ላይም ለውጥ ማምጣት ነበረባቸው፡፡ በዚህ የተነሳ በቻይና በሌሎች አገራት ከተለመደው መልኩ ወጣ ባለ ሁኔታ የሚበላ እፅዋትና እንስሳት ብዛት በርከት ይላል፡፡
ቻይናውያን በዚህ የፀረ ድህነት ዘመቻቸው በጥቂት አመታት ውስጥ ለውጥ አመጣ፡፡ ህዝባቸውን ከመመገብና አልፈውም ለሌላውም የሚተርፍና ዓለምን ሊመራ የተቃረበ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆን ቻሉ፡፡ የዚህ ለውጥ ዋነኛ መንስኤ በአንድ በኩል ስራን ሳይንቅ የሚሰራ ህዝብ መፈጠሩ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አንድነትና ህብረት ነው፡፡
ህንድም የእንዲህ አይነት ታሪክ ተጋሪ ናት፡፡ በዓለማችን በህዝብ ቁጥሯ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ህንድ የተማረ ህዝቧም ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል ህንድም በተመሳሳይ በድህነት ውስጥ ከነበሩ የዓለማችን አገራት አንዷ እንደነበረች ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ህንዶች የስራ ባህላቸው ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠታቸው ህዝባቸውን ከመመገብ አልፈው በአሁኑ ወቅት ወደ ብልፅና ከሚጓዙ አገራት አንዷ መሆን ችላለች፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ የቅርብ ጊዜውን የአረብ አገራት ነባራዊ ሁኔታ እንመልከት፡፡ ባለፉት ሃምሳ አመታት አብዛኛውን የአረብ አገራት የምናውቃቸው በነዳጅ ምርታቸውና በዚህም የተነሳ በህዝባቸው የተንደላቀቀ ኑሮአቸው ነው፡፡ በአገራችንም አረብ የሚለው ቃል የሀብታምነት መገለጫ እስከመሆንም ደርሷል፡፡ ነገር ግን ከነዚህ አረብ አገራት አንዳንዶቹ ካለፉት አስር አመታት ወዲህ ምቹ አልነበሩም፡፡የቆየ የተንደላቀቀ የህዝቦቻቸው ህይወትም ወደ ኋላ የተመለሰበትና ድህነት እና ጦርነት እንዲሁም የሚላስ የሚቀመስ እስከመጥፋት የደረሰበትን ነባራዊ ሁኔታ ተመልክተናል፡፡ ይህ በዋናነት ጠባቂ የሆነ ማህበረሰብ በመፈጠሩ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመጣ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ ከእነዚህ ችግሮችም ውስጥ አንዱ ቀስ በቀስ እየተዳከመ የመጣው የስራ ባህላችን ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስራን የማማረጥ ችግር አንዱ መገለጫችን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በተደጋጋሚ የሚነገር እውነታ አለ፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ዲቪ ደርሶት ወይም በሌላ መንገድ ወደ አሜሪካ ሲሄድ የሚሰራው ስራ እዚህ ቢሆን ዞር ብሎ ሊያየው የማይፈልገው ስራ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
በአንድ ወቅት አሜሪካ አገር ለሁለት አስርት አመታት ኖሮ የተመለሰ ኢትዮጵዊ ሲናገር እንደሰማሁት በአሜሪካ አገር ሲሰራ የኖረው ፈረሶችን የመመገብ እና ጤንነታቸውን የመንከባከብ ስራ እንደነበር አጫውቶኛል፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ በአገራችን አባባል የተከበረ ሰው አሜሪካን አገር በነዳጅ ማደያ ውስጥ ለዘመናት ሲሰራ እንደቆየ በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ሲናገሩም ታዝቤያለሁ፡፡
በአጠቃላይ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ለእኛ ለኢትዮጵውያን አዲስ ነገር አይደሉም፡፡ውጭ ስንወጣ የምንሰራቸው አንዳንድ ስራዎች በዚህ አገር እንኳንም በአብዛኛው ወጣት የሚሞከሩ ቀርቶ የሚታሰቡም አይደሉም፡፡ ህፃናትና አረጋውያንን መንከባከብ፣ የቤት እንስሳትን መጠበቅ፣ ቀበቶ መሸጥ፣ ወዘተ በአገራችን ትንሽ ተብለው የተፈረጁ ስራዎች ቢሆኑም ብዙ ገንዘብ አውጥተንና ተበድረን እነዚህን ስራዎች ለመስራት ባህር ማዶ የምንሻገር ግን ብዙዎች ነን፡፡
በርግጥ ለዚህ ምክንያት ተብለው የሚነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ በአገራችን ዝቅ ብለን ብንሰራም የሚፈለገውን ጥቅም አናገኝም፡፡ በዚህ የተነሳ በአገራችን እንዲህ አይነት ስራዎች የሚለውጡ ባለመሆናቸው ነው ሰው ለእነዚህ ስራዎች ተገቢውን ክብር የማይሰጠው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡
በከተማችን ከሚገኙና መንግስት ከሚሰራቸው የስራ ዘርፎች አንዱ የከተማ ፅዳት ነው፡፡ በዚህ ስራ ላይ ግን የሚሰማሩ ሰራተኞች በተለይ ወጣቶች ከሆኑ ሁል ጊዜ ፊታቸው እንዳይታይ መሸፋፈን የተለመደ ነው፡፡ እንዲህ ፊታቸውን የሚሸፋፈኑት ደግሞ አቧራውን ለመከላከል ሳይሆን ማንነታቸው እንዳይታወቅባቸው በሚል ስጋት እንደሆነ ብዙዎች የሚናገሩት እውነታ ነው፡፡
በሌላም በኩል በአገራችን ተግባራዊ የተደረገውና በርካታዎችን ባለሀብት ስላደረገው የጥቃቅንና አነስተኛ ልማትም ማንሳት ይቻላል፡፡ በአገራችን በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ በዚህ ዘርፍ ላይ ወጣቶችን ለማሰማራት ከፍተኛ ስራ ሰርቷል፡፡ ያም ሆኖ ግን ይህንን እውን ለማድረግ ያጋጠመው አንዱ ፈተና ከቤተሰብ ጀምሮ የሚታይ አመለካከት ነው፡፡ አንዳንድ ቤተሰብ ልጄ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ/ቃ እንዴት በጥቃቅንና አነስተኛ ትሰማራለች በሚል መንፈስ መንግስትን እስከማማረር የደረሱ አሉ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ በየወረዳው ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ለማደራጀት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ለመሆኑ ስራው ምንድን ነው የሚለው የመጀመሪያ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚያ በኋላም ጥቃቅንና አነስተኛ የሚለውን ስም መስማት የማይፈልጉ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡
በርግጥ አሁን ለተፈጠረው እንዲህ አይነት የስራ ማማረጥ ችግር በርካታ ምክንያቶች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ዋነኛው ምክንያት በአንድ በኩል አጠቃላይ የሙስናና ብልሹ አሰራሮች መስፋፋት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አንዱ ጥሮ ግሮ ሰርቶ ለመለወጥ ረጅም ጊዜን ሲጠብቅ ሌላው በአጭሩ በአቋራጭ መንገድ ብዙ ሳይለፋ ባለሀብት ሲሆን ማየት ከስራ ወዳድነት ይልቅ በአቋራጭ መክበርን መምረጥ ዋነኛ ምርጫ ይሆናል፡፡
በሌላም በኩል በአገራችን ያለው ባህል እንዲህ አይነት በአቋራጭ የሚመጣ ሀብትን የሚያወግዝ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ በቦሌም በባሌም ብለህ ገንዘቡን አምጣ የሚል ፈሊጥ ተበራክቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚል ፈሊጣዊ አነጋገር የማይወገዝበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በአገልግሎት አሳጣጡም ላይ ገንዘብ የሌለው አንድ አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ወረፋና ብዙ ጊዜን መጠበቅ /ያውም ከተሳካ/ ሲኖርበት ገንዘብ ያለው ግን በአቋራጭ ጉዳዩን የሚያስፈጽምበት ሁኔታ እየተለመደ መጥቷል፡፡ በአቋራጭ መንገድ ገብቶ ባለሀብት የሆነ አንድ ግለሰብ ሌባ ከመባል ይልቅ በአጭሩ ‹‹ቢዝነስ ሰርቶ›› ተለወጠ የሚል ሙገሳና ክብር ያጅበዋል፡፡ እነዚህና መሰል አገራችን ባህሎች መስፋፋት የስራ ጠልነት ችግሮች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆነዋል፡፡
ከላይ ያነሳሁት ወጣት ደሳለኝ ይህንን አይነት የአገራችንን ስራ ጠልነት አመለካከት ሙሉ ለሙሉ የሰበረ የዘመናችን ወጣት ተምሳሌት ነው፡፡ አሁን አገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሀኔታ ስንመለከት የስራ ባህላችንን ለውጠን በተገኘው የስራ መስክ ሁሉ የምንሰማራበትና ለለውጥ የምንጓዝበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ድህነት እንዳይውጠን መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ድህነት ደግሞ የርስ በርስ ግጭት መንስኤ በመሆን አገርን ያጠፋል፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ ያለ ወጣት ሁሉ ራሱን በስራ በመጥመድ ለውጥን ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡
ወጣት ደሳለኝ እንደሚለው አሁን እሱ ያለበት ደረጃ ገና ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬን ለመኖርም ሆነ ለነገ የተሻለ ተስፋን ይዞ ለመቀጠል ስራ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ለነገ ስንቅ እንዲሆን ጠንክሮ መማር አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ አባት እንዳሉት ከላይ የሚጀመር ነገር የጉድጓድ ቁፋሮ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ነገር ሁሉ ከታች ጀምሮ እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው በላቡ ሰርቶ ለመለወጥ ካቀደ ከትንሽ ስራ በመጀመር ለመለወጥ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሲሆን እኛም አገራችንም እንለወጣለን፡፡

ውቤ ከልደታ

Published in አጀንዳ

ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በተለያዩ አገራችን ክፍሎች ተከስቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ቀንሶ በአብዛኛው የአገራችን ክፍሎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የነበረው ሰላም ከሞላ ጎደል እየተሻሻለ የመጣበት ሁኔታ አበረታች ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚቀሰቀሱ ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀል ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠውና በአጭሩ ካልተቀጨ ዘላቂ ሰላማችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀርም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ተግባራትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ከሞላ ጎደል ቀንሰው የነበሩ የዝርፊያና የስርቆት እንዲሁም የቡድን ግጭቶች በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተለይ በአዲስ አበባ አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ነጋዴዎች ህግ የሌለ እስኪመስል ድረስ ዋጋን እንደፈለጉ የመወሰንና ገበያን የማዛባት እንቅስቃሴ ውስጥም ገብተው ይታያሉ፡፡ እነዚህና ሌሎች ግጭቶችና የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ተግባራትም መንግስት ገና በርካታ ስራዎች እንደሚጠበቅበት የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ የእነዚህ ግጭቶችና የዝርፊያ ተግባራት መንስኤ ስንመለከት ደግሞ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት መንግስት እየሰጠ ያለውን ይቅርታ በተዛባ መንገድ በመተርጎም ከዚህ በኋላ ተጠያቂነት የለም ከሚል የተዛባ ዝንባሌ ህገወጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ አካላት ተበራክተዋል፡፡
በተለያዩ የፍትሐብሄርና የወንጀል ክሶች ተጠርጥረው ክሳቸው በሂደት ላይ ያሉ ዜጎች ክሳቸው እንዲቋረጥና ከእስር እንዲፈቱ እንዲሁም በተለያዩ የክስ መዝገቦች የተፈረደባቸውን ጨምሮ በርካታ ታራሚዎችን በይቅርታ መፍታቱን በአወንታዊ ጎኑ የሚመለከቱ በርካታ የአገራችን ህዝቦች ቢኖሩም ጥቂቶች ደግሞ ይህንን የመንግስት ውሳኔ በተሳሳተ መልኩ በመተርጎም የህግ የበላይነት እየተዳከመ የመጣበት ሁኔታ እንዳለ የሚናገሩም አልጠፉም፡፡
መንግስት በማረሚያ ቤት የነበሩ የህግ ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎችን ሲፈታ የህግ የበላይነት እንዲሸረሸር ሳይሆን በአንድ በኩል የተጀመረውን የይቅርታ መንፈስ በሙሉ ልብ በመፈፀም ሁሉም ከባለፈው ትምህርት ወስዶ በአዲስ መንፈስ ለስራ እንዲነሳሳና የአንድነትና የፍቅር ባህል እንዲጎለብት በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ውስጥ ጉድለት የነበራባቸው አንዳንድ አሰራሮች በመኖራቸው እነዚህን ለማስተካከል እድል እንዲሰጥ ታስቦ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ነገር ግን በወንጀልም ሆነ በፍትሐብሄር ህግ ጥሶ የተገኘ አካል አሁንም ቢሆን ከተጠያቂነት እንደማይድን መታወቅ አለበት፡፡ በተለይ በህዝብ መካከል ሆነው ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማግለል የሚፈፀም የዘረኝነትና የወንጀል ድርጊት ዛሬም ሆነ ወደፊት በይቅርታ የሚታለፍ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በራሳቸው የተጀመረውን የይቅርታ በጎ አሰራር የሚያኮላሹ በመሆናቸው መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ በፅኑ የሚታገላቸው ናቸው፡፡
ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማ የ15 ሰዎች ህይወት የተቀጠፈበት እና የበርካታ ዜጎች መፈናቀል የተከሰተበት ድርጊት በብዙኃኑ ሰላም ፈላጊ ህዝብ የተፈፀመ ሳይሆን በጥቂት ቡድኖች አስተባባሪነት የተፈፀመ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በዚህ የሁከትና ብጥብጥ ተግባር ውስጥ እጃቸው የተገኘ ማንኛውም አካል ለፍርድ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንደሚያገኝም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታም በአመራር ላይ ያሉ አካላትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ተይዘው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው፡፡
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችም ዜጎች ከኖሩበት ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ ያደረጉ አመራሮችና ሌሎች እጃቸው በዚህ ችግር ውስጥ እንዳለ የተጠረጠሩ አካላት ከስራቸው ታግደው ጉዳያቸውም በህግ እየተጣራ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልም ተመሳሳይ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡ በተለይ በቅርቡ የፊቼ ጫምባላላ በአል በሚከበርበት ወቅት በተፈጠረው ግጭት ከአስር የማያንሱ ሰዎች መሞታቸውና በርካታ ዜጎችም ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን ተከትሎ የክልሉ ከፍተኛ የድርጅትና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡
በአጠቃላይ አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበትና ከዚህ ቀደም ያጋጠሙንን ችግሮች ሁሉ ወደኋላ ጥለን ስለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ የምናልምበት የይቅርታ፣ የፍቅርና የአንድነት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ ከሁከትና ከብጥብጥ በመራቅ መጪውን ጊዜያችንን ብሩህ ለማድረግ የእያንዳንዱ ዜጋ ብርቱ ጥረትና ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ለዚህ ደግሞ የህግ የበላይነት በማክበርና በማስከበር መንግስት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ የተጀመረው የአመራር ክፍተት ያሳዩ ኃላፊዎች ተጠያቂ የማድረግ ስራም አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

የኢትዮጵያ የቅርሶች ማህደርነት ከሚገለጽባቸው እውነታዎች አንዱ፣ በአገሪቱ ከተሞች በተዘዋወሩ ቁጥር አንድ መገለጫ ቅርስ ይዘው መገኘታቸው ነው፡፡ የአባ ጅፋሯ ጅማ ደግሞ ከእነዚህ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ እግር ጥሎት ጅማ የደረሰም የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ቀዳሚ መዳረሻው ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ሆኖም ዛሬ ላይ ነገሮች በተቃራኒው ሆነዋል፡፡ ቀድሞ ሰው የማይለየው የአባጅፋር ቤተ መንግሥት ጊቢ ጭር ብሏል፡፡

በቤቱ ዙሪያ በገመድ ተከልሎ «ማለፍ ክልክል ነው» የሚል ወረቀት ተንጠልጥሎበታል፡፡ ያ ውብ ገጽታ የነበረው ቤት፤ ካስማዎቹ እየተሰበሩ፣ ግድግዳውም እየረገፈ ነው፡፡ ዕድሜ ጠገቡ የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት የነበረ ገጽታውን አጥቷል፤ በነፋስ ኃይል እንኳን ተገፍቶ የሚወድቅ የሚመስለው ይህ ቤት በተለያዩ እንጨቶች ተደግፏል፤ ከቤትነት ወደ አፈርነት የመቀየር ጉዞውንም የጀመረ ይመስላል፡፡
እልህና ቁጭት የሚነበብባቸው የጅማ ከተማ ነዋሪዎችም በዚህ ቅርስ በዚህ ደረጃ መገኘት እጅጉን ማዘናቸውን ይናገራሉ፡፡ ቅርሱን ለመታደግ የሚችሉትን ሁሉ ቢጥሩም ሥራው ከእነርሱ አቅም በላይ በመሆኑ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ቅርሱን የሚታደጉበትን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ይገልጻሉ፡፡ የሚመለከተው አካልም የከተማዋ ብቻ ሳይሆን የአገር ቅርስ የሆነውን የአባ ጅፋር ቤተመንግሥት ከመፍረስ አደጋ እንዲታደገው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
«አሁን ላይ ቤተ መንግሥቱ በፅኑ ታሞ አልጋ ላይ እንደተኛ ህመምተኛ፣ ያውም ለሞት ከጫፍ የደረሰና በከፍተኛ ክትትል ስር እንዳለ ታማሚ ነው» የሚሉት የከተማዋ ነዋሪና የቅርስ ተቆርቋሪ የሆኑት አቶ አብዱልከሪም አባገሮ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ አንድ ሰው በጤንነቱ ሳለ ተገቢውን አገልግሎት ሲሰጥ ቢኖርም በጊዜው መድከሙ ወይም መታመሙ አይቀርም፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ከእርሱና በእርሱ ሲገለገሉ የነበሩ አካላት ሁሉ ለዚያ ሰው ፈውስ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥትም ተመሳሳይ ችግር ገጥሞታል፡፡
ምክንያቱም ቤተ መንግሥቱ በጅማ ከተማ ይገኝ እንጂ ሀብትነቱም ሆነ ጥቅሙ የአገር ነው፡፡ ሆኖም አሁን ላይ ቤተ መንግሥቱ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ገብቷል፡፡ አደጋውም እጅጉን የከፋ እንደመሆኑ በጽኑ የህክምና ክትትል ስር ያለ ሰው ተገቢውን የባለሙያ ክትትል ካላገኘ እንደሚሞት ሁሉ፤ ይህ ቤተ መንግሥትም በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ያለ እንደመሆኑ አጥሮ ለጎብኚዎች ዝግ ማድረግ መፍትሄ ስለማይሆን በተገቢው ባለሙያ ተገቢው ጥገና ሊደረግለት ያስፈልጋል፡፡
አቶ አብዱልከሪም እንደሚሉት፤ የሰው ልጅ ከሞተ ሕይወቱ መመለስ እንደማይችል ሁሉ ይህ ቤትም አንዴ ከፈረሰ በኋላ መልሶ መተካት አይቻልም፡፡ ይህ ቅርስ ደግሞ የቀደሙት አባቶች አኑረው ያለፉት አሻራ ነው፡፡ ይህን አሻራ ከትውልድ ተረክቦና ጠብቆ የማቆየት ድርሻ ደግሞ አሁን ያለው ትውልድ ነው፡፡ ሆኖም አሁን ባለበት ደረጃ ቅርሱ እየፈረሰ ብቻ ሳይሆን፤ ትውልዱም የተረከበውን የታሪክ አደራ ተሸካሚ መሆኑ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ በመሆኑም የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን ባለታሪኮች የሰሩትን ይሄን ቅርስ መጠገንና ጠብቆ ማቆየት ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ይሄን ቅርስ የከተማዋ ዓርማ ብቻ ሳይሆን የአገር ሀብት እንደመሆኑ የሚመለከተው አካል ተገቢው ትኩረት ሊሰጠውና ሊታደገው ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ፣ የነዋሪዎቹን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በአባ ጅፋር ቤተመንግሥት ላይ የተደቀነው ችግር ዛሬ የጀመረ ሳይሆን የቆየ ነው፡፡ ቅርሱን ለመጠገን ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ቢሆንም ከአስተዳደሩ አቅም በላይ ሆኗል፡፡ የችግሩን መባባስ ተከትሎም ባለፈው ዓመት ለክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አሳውቀዋል፡፡ በቢሮው ደረጃ የተደረገው ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ምክንያቱም ቅርሱ በዘርፉ ሙያና ልምድ ባላቸው እንጂ በሰፈር ባለሙያዎች የሚከናወን ከሆነ የባሰ አደጋ ላይ የሚወድቅ መሆኑ በ1997 ዓ.ም በተደረገ የጥገና ሥራ ታይቷል፡፡
ይሄን በመገንዘብም የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጉዳዩን ለፌዴራል አሳልፏል፡፡ ይሁን እንጂ በፌዴራል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መወሰድ የሚገባው እርምጃ የተጓተተ በመሆኑ ቤቱ የበለጠ ለአደጋ እየተጋለጠ ይገኛል፡፡ እናም ይህ የከተማው መለያ ብቻ ሳይሆን የአገር ሀብት የሆነው ቅርስ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ፣ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት፤ የአባ ጅፋር ቤተመንግሥት እስካሁን በክልል ስር ሲተዳደር የቆየ ነው፡፡ ለማስጠገን በሚልም ጨረታ አውጥቶ ሰጥቶ ስለነበረ፤ ይህ ጨረታ ተቋርጦ ውክልናውን ለባለሥልጣኑ መስጠት ነበረበት፡፡ ይህ እስኪሆንም ኤጀንሲው ዝም ብሎ አልተቀመጠም፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ጥናት እያስጠና ሲሆን፤ ጥናቱ እስኪጠናቀቅም ከክልሉ ጋር በመሆን መለስተኛ የጥበቃና እንክብካቤ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ባለሥልጣኑ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችሉ አሠራሮችን ለመከተል እንጂ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዘግይቷል የሚያስብል ሂደት አልወሰደም፡፡ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችለው ጥናትም መስከረም አጋማሽ ላይ ስለሚጠናቀቅ በመንግሥት ከሚበጀተው ፋይናንስ ባለፈ ለጥገና ሥራው የሚውል ፈንድ እየተፈላለገ ነው፡፡ እንደነ ላሊበላ ሁሉ የአባ ጅፋር ቤተመንግሥትም ቅድሚያ የተሰጠው ተግባር በመሆኑ ከመስከረም አጋማሽ በኋላ የዝናቡ ወቅት እንዳበቃ የጥገና ሥራው የሚጀመር ይሆናል፡፡

ዜና ሐተታ
ወንድወሰን ሽመልስ

 

Published in የሀገር ውስጥ

በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረገው ስደት በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እየተከሰቱ ሲሆን ይህ ደግሞ በአገር እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ፈጥሯል፡፡ 

ሰሞኑን በጅማ ከተማ በተካሄደ የኦሮሚያ የከተሞች ፎረም ላይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ስደት መሠረት በማድረግ የቀረበ ጥናት እንዳመለከተው፤ በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ከገጠር ወደከተማ የሚደረገው ስደት ለበርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መከሰት የጎላ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡
ዶክተር ደገፋ ቶሎሳ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ስደት ሲባል በቋሚነት የመኖሪያ ቦታ የሚለወጥበት የሕዝብ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስደት ከሚመለከታቸው እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ ከገጠር ወደከተማ የሚደረገው ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ይኸው ከገጠር ወደከተማ የሚደረገው ስደት ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንደኛ፣ ሰዎች ከነበሩበት ቦታ የሚገፋቸው ምክንያት ሲኖር፤ ሁለተኛ፣ የሚሰደዱበት ቦታ የሰዎችን ስሜት ሳቢ የሆነ ነገር ሲኖረው የሚከሰት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሁለቱም ምክንያት የሚከናወን ስደት ጥለውት በሚሄዱት የገጠር መንደርም ሆነ ለሚሄዱበት ከተማ የሚያሳድረው ተጽዕኖ የጎላ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ደገፋ ገለጻ፤ ድህነት ፣ የተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ፖለቲካዊ ሁኔታና መሰል ነገሮች ሰውን ከመኖሪያ አካባቢው በሚፈጠሩ ነገሮች ተገፍተውም ሆነ በሚሄዱበት ከተማ የሚያገኙትን ተስፋ አድርገው የሚሰደዱ ሰዎች ተስፋቸውና ምኞታቸው እውን የሚሆነው በመዳረሻቸው ከተማ ለሥራ ዕድሉም ሆነ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ማግኘት ምቹ መሠረተ ልማቶች መኖር ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ሆኖም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ከተሞች በዚህ ረገድ ምቹ ባለመሆናቸው ከተሞቹም ለውጥረት፤ ስደተኞቹም ለችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ በገጠር አካባቢ ሰዎች ለመሠረታዊ ኑሯቸው የሚያስፈልጓቸው ነገሮች አለመሟላት፣ በቂ ገቢ ማጣት፣ እንዲሁም ችግሮች ሲከሰቱ ቶሎ አደጋዎችን የመቋቋም ሁኔታዎች አለመኖር ለችግሮች መፈጠር ድርሻቸው የጎላ ነው፡፡ በዚህም በስደት በመነሻም ሆነ በመዳረሻ ቦታዎች ላይ በቂ የሆኑ የመሠረታዊ የኑሮ ግብዓቶች አለመኖርን በመፍጠር ተጽዕኖውን ያገዝፈዋል፡፡
ዶክተር ደገፋ እንዳሉት አሁን ላይ በኢትዮጵያ ወደ 17 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚኖረው ባልተወለደበት ቦታ ነው፡፡ ከወንዶች የበለጠም ሴቶች የዚህ ስደት ተጋላጮች ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ የሚገለጸው ስደትም የስደት መነሻ አካባቢዎች የሕዝብ ቁጥር እንዲቀንስ፤ የስደት መዳረሻ ከተሞች የሕዝብ ቁጥር ደግሞ እንዲጨምር በማድረግ ለአንድ ቦታ ሕዝብ መጨመር ወይም መቀነስ ምክንያት ይሆናል፡፡ ይህን ዓይነት ስደት ደግሞ በተለይ በታዳጊ አገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ችግር መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ከተማውም በደንብ አለመልማቱ፣ በቂ ዝግጁነት አለመኖሩና የሚሰደደውም እርግጠኛ ሆኖ ስለማይሄድ፣ እዚያ ከደረሰ በኋላ በርካታ ችግሮች ይደርሱበታል፡፡ በከተማው ነዋሪዎችም የመጨናነቅና የአገልግሎት መተፋፈግ ያስከትላል፡፡
እንደ ዶክተር ደገፋ ገለጻ፤ በዚህ መልኩ የሚገለጸው ስደት እያስከተለ ያለውን ችግር ከመነሻና ከመዳረሻ ቦታዎች አኳያ በሁለት መልኩ መመልከት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የመዳረሻ ቦታዎች ላይ የሚያስከትለው ችግር ሲሆን፤ ከችግሮቹ መካከልም አንዱ የሥራ አጥነት ነው፡፡ ሁለተኛም በእነዚህ ከተሞች በሚሰጠው በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ ነው፡፡ ይህ ጫና ደግሞ ለነዋሪውም ሆነ ለተሰዳጁ ከመኖሪያ ቤት ጀምሮ የጤና፣ የትምህርት፣ የሥራና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት የማያስችሉ ሁኔታዎችን እያስከተለ ይገኛል፡፡
መዳረሻ ከተሞች ደግሞ በዚህ መልኩ አገልግሎቶችን ለነዋሪዎች ማቅረብ ሲሳናቸው ሰዎች ወዳልተፈለገና በሕግም ወደተከለከለ ተግባር እንዲገቡ እያደረጋቸው ነው፡፡ በመዳረሻ ከተሞችም ላይ የጎላ የጸጥታና ደህንነት ተጽዕኖ እየፈጠረባቸው ይገኛል፡፡ ስደተኞችም በሚኖራቸው ሕይወት አስበውት በመጡት ልክ የሚፈልጉትን ካላገኙ ከሚደርስባቸው የሥነልቦና ጫና ባለፈ፤ የመደፈር አደጋ ሲያጋጥማቸው፣ ኤች.አይ.ቪ ኤድስን ለመሳሰሉና ሌሎች በሽታዎችም በስፋት ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡ ለስደት መነሻ የሚሆኑ አካባቢዎችም ቢሆኑ ለሥራ የደረሰና የመስራት አቅም ያለው የሰው ኃይል ከመመናመን ጀምሮ የሚገለጹ በርካታ ችግሮች እያጋጠማቸው ይገኛል፡፡
በጥናቱ እንደተመላከተው፤ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በቅርቡ ወደ 1ነጥብ6 ሚሊዮን ሕዝብ በግጭት ምክንያት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሷል፤ ተፈናቅሏልም፡፡ በከተሞች ያለው የሕዝብ እድገትም በየዓመቱ 4በመቶ በሚጠጋ ፍጥነት እየጨመረ ነው፡፡ በዚህም የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር በእጅጉ እያደገ ሲሆን፣ ከተሞችም በፍጥነት እየተስፋፉ ይገኛል፡፡ ሆኖም ከተሞች በነበራቸው አቅም እያደገ የመጣውን የነዋሪዎቻቸውን ቁጥር መሸከም፣ አስፈላጊውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማት ማቅረብ ሲሳናቸው ተስተውሏል፡፡
በአገራችን እየጨመረ ያለው ከገጠር ወደከተማ የሚደረግ ስደት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ወጣቶች ለሥራ ፍለጋም ሆነ የተሻለ ኑሮ ፈልገው ለስደት እንዳይነሳሱ ወይም በደረሱበት ችግር እንዳይገጥማቸው ለማድረግ በተለይ ገጠሩና ከተሞች ተቀናጅተው የሚለሙበትን አሠራር መፍጠር ይገባል፡፡ በፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚደረግን ስደት ለመቀነስም ፖለቲካዊ መፍትሔ በመስጠትም፤ በስደት በመነሻም ሆነ በመዳረሻ ቦታዎች ላይ በቂ የሆኑ የመሠረታዊ የኑሮ ግብዓቶችን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህን መስራት ካልተቻለና ከገጠር ወደከተማ የሚደረገው ስደት በዚሁ ልክ የሚቀጥል ከሆነ፤ የገጠር አካባቢዎች የልማት ኃይል እያጡ፤ ከተሞችም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጡ፤ እንዲሁም ፖለቲካዊ ትኩሳቶች እያየሉና ሕገወጥነትም እየተበራከተ መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ 

ዜና ትንታኔ
ወንድወሰን ሽመልስ

 

Published in የሀገር ውስጥ

በአሁኑ ወቅት የመንግሥትም ይሁን የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተከታታይና የርቀት የትምህርት መርሃ ግብር በመዘርጋት ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ በተቋማቱ የሚሰጡት የተከታታይና የርቀት የትምህርት ሥርዓት ግን ጥራቱን በጠበቀ መንገድ እየተከናወኑ አይደሉም፡፡

በትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ወይዘሮ ፍሬወይኒ ገብረእግዚአብሔር እንደሚሉት፤ በመንግሥትና በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከታታይና የርቀት ትምህርት ጥራቱን በጠበቀ ሁኔታ በአግባቡ እየተሰጠ አለመሆኑ በጥናት ታይቷል፡፡ በጥናቱም በብዛት በተከታታይና በርቀት የትምህርት መርሃ ግብር ለመማር የሚመዘገቡት ተማሪዎች ውጤታቸው አነስ ያለና ቀን ላይ ሥራ የሚሰሩት ናቸው፡፡ በመመሪያው መሠረትም የመጀመሪያ ዲግሪ ለመማር የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ያለፉ ተማሪዎች መሆን ሲገባቸው ተግባር ላይ ግን ይህ ሁኔታ አይታይም፡፡
የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ያላለፉ ተማሪዎች መዝግቦ ማስተማር በመንግሥትና በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አለ የሚሉት ወይዘሮ ፍሬወይኒ፤ ለትምህርት የሚያስፈልግ ግብዓት ሳይሟሉ ትምህርት ማስጀመር፣ የተከታታይና የርቀት ትምህርት መርሃ ግብር ለማሟያ እንጂ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ትኩረት አለመስጠት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን አለማከበር፣ ተከታታይ ምዘና አለመኖር፣ የትምህርት መርሃ ግብሮች ሲከፈቱ ለተከታታይና ለርቀት መርሃግብር የሚሆኑ አሠራሮችን በጥናት አለመለየት ጥራት ላይ ችግር መፍጠሩን ያስረዳሉ፡፡
ለተከታታይ ትምህርት የተቀመጠውን ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመው ያለመጨረስ እና የሚሰጠውንም ትምህርት በአግባቡ ያለመከታተል ችግሮች በዘርፉ በስፋት እንደሚታዩም ኃላፊዋ ይናገራሉ፡፡ በአንዳንድ ተማሪዎች ውስጥ ስለከፈልን መውደቅ የለብንም የሚል ዕምነት እንዳላቸውና ሰርተፍኬት በመፈለግ ብቻ የሚማሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ መምህራንም በክረምት የሚወስዱት ትምህርት ዘግይተው ስለሚጀምሩና የተፈለገውን ትምህርት በአግባቡ መሸፈን ስለማይችሉ የትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡
እንደ ወይዘሮ ፍሬወይኒ አባባል፤ የተከታታይና የርቀት ትምህርት ክፍል ሲከፈት የትምህርት አሰጣጡ እንዴት መሆን እንዳለበት አለመጠናቱ፣ ለትምህርቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች አለመኖር እንዲሁም የተማሪዎች የምዘና ሁኔታ በተለይ በርቀት ተማሪዎች አካባቢ ማርክ ያለአግባብ ከፍ አድርጎ መሰጠት ጥራቱ ላይ ክፍተት ፈጥሯል፡፡ በተከታታይና በርቀት ትምህርት የተማሪዎች መውደቅ አለመኖር እና ተማሪዎቹ ተምረው የሚጨርሱበት ዓመት ላይ የተቀመጠ የቀን ገደብ አለመኖር ሌላኛው ክፍተት እንደሆነ በጥናቱ ተለይቷል፡፡
በትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ነገዎ በበኩላቸው በተከታታይና በርቀት የትምህርት መርሃ ግብር ጥራት ላይ የተለያዩ ችግሮች እንደሚስተዋሉበት ይናገራሉ፡፡ የተከታታይና የርቀት የትምህርት ሥርዓት ላይ በርካታ ተማሪዎች የመማር ፍላጎት እየጨመረ ቢመጣም በዋናነት የትምህርት ክፍሉ አከፋፈት ላይ ባሉ ችግሮችና ጥናት በተደረገባቸው ተቋማት ከኢንተርኔት፣ ከመጽሐፍ፣ ከመብራትና ከኮምፒዩተር ጋር እጥረቶች መኖር ጥራት እንዳይመጣ ማድረጉን ይጠቅሳሉ፡፡
የተከታታይና የርቀት ተማሪዎች በሥራ ላይ ሆነው በትርፍ ሰዓት የሚማሩ በመሆናቸው በአግባቡ አንብበው እውቀት ለማግኘት ጊዜ እንደማይኖራቸው አቶ ተስፋዬ ጠቅሰው፤ በማሳያነት የርቀትና የክረምት ተማሪዎችን ያነሳሉ፡፡ የርቀት ተማሪዎች ዋነኛ መሠረታቸው ሞጁል ብቻ በመሆኑ ተጨማሪ ነገር ማግኘት አለመቻል እንዲሁም የመምህራን እውቀት ማነስ በተለይ እውቀት በሌላቸው ትምህርት ላይ ማስተማር የትምህርት ጥራቱ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ይጠቁማሉ፡፡
በማታ ትምህርት ክፍል ተማሪውና መምህሩ በድካም መንፈስ ወደ ክፍል ስለሚመጡ በአግባቡ የመማር ማስተማር ሥራው እንደማይከናወንና አርፍዶ መግባት ቶሎ መውጣት ሁኔታዎች እንዳሉ አቶ ተስፋዬ ያመለክታሉ፡፡ በተጨማሪም በርቀት ትምህርት መርሃ ግብር የሚሰጠውን የቲቶሪያል ክፍል ተማሪዎች በአግባቡ ስለማይከታተሉ የርቀት ትምህርት መርሃ ግብር ሰጪ ተቋማት የቲቶሪያል ትምህርት ማቆማቸውን ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ ተስፋዬ አባባል፤ ተማሪዎቹ የሚመዘኑበት መንገድም በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ በተከታታይና የርቀት ትምህርት ላይ አብዛኛው የቤት ሥራ ወይም መልመጃ በቡድን የሚሰጥ በመሆኑ በዚህ ሥራ እያንዳንዱ ተማሪ መሳተፍ ቢኖርበትም አንድ ተማሪ ሰርቶ ሌላው እኩል ውጤት ያገኛል፡፡ በርቀት ትምህርት መርሃ ግብር የሚማሩ አንዳንድ ተማሪዎች የሚሰጣቸውን የቤት ሥራ በሌሎች ሰዎች አሰርተው ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡበት ሁኔታም ይስተዋላል፡፡
የትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ጥናት እንደሚያሳየው፤ በመንግሥትና በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እአአ 2000 እስከ 2015 ድረስ በማታ ትምህርት መርሃ ግብር 180 ሺ 896፤ በርቀት የትምህርት መርሃ ግብር ደግሞ 101 ሺ 585 እንዲሁም በክረምት ትምህርት መርሃ ግብር 101 ሺ 585 ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እያደረገ ባለው ዘርፈብዙ ጥረት ውስጥ የተከታታይ ትምህርት መርሃግብርም አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ካልተሰራ በትምህር ዘርፉ ለማምጣት የታቀደው አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራም ግቡን ሊመታ አይችልም፡፡ ይህ ደግሞ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች በሁለንተናዊ የአገር እድገት ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባቸውን ድርሻ በአግባቡ እንዳይወጡ ያደርጋል፡፡

ዜና ትንታኔ
መርድ ክፍሉ

 

Published in የሀገር ውስጥ
Page 1 of 2

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።