መከላከያ ሰራዊታችን ኩራታችን እራታችንም

15 Feb 2017

ብርሃኑ ተሰማ የተባለ ጸሀፊ ከዚህ በታች ያለውን ጽሁፍ አስፍሮ አገኘሁ። እኔም በጥቂቱ ተዋስኩና እንዲህ አድርጌ አቀረብኩት። (የጽሁፉን ምንጭ ተናገርኩ ማለት ነው) ጊዜው 1975 ዓ.ም ነበር።  የዛሬውን አያድርገውና ሊቢያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) የመሪዎች ጉባዔን ለማስተናገድ ሽርጉድ ከጀመረች ውላ አድራለች። በተቃራኒው ኃያሏ አገር አሜሪካ ግን በፕሬዚዳንቷ ሮናልድ ሬገን አማካይነት ጉባዔው እንዳይሳካ ጥረት ማድረግ ጀመረች። ሊቢያንና መሪዋን አሸባሪ በማለትም ጉባኤውን በተደጋጋሚ አስተጓጎለችው።

ከአንዴም ሁለቴ በአሜሪካ በአሸባሪነት በተፈረጀችው አገር እንዳይካሄድ የተፈረደበት ጉባዔ መጨረሻ ላይ ወደ ትውልድ አገሩ ይሂድና ጉባዔው ይካሄድ የሚል ውሳኔ ተላለፈበት። አ.አ.ድን የወለደችው አዲስ አበባም በአስቸኳይ መሪዎቿን ጠርታ ጉባኤውን አስተናገደች። የአገሪቱ መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም የዓመቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።

በወቅቱ የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሼሁ ሻጋሪ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ፤ "ድርጅቱ ወደተወለደበት አገር ሲመጣ ከሕመሙ ተፈወሰ’’ ሲሉ መናገራቸው ዛሬም ድረስ ይታወሳል፤ ሲል በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት ጸሀፊ ታሪኩን ነግሮናል።

  ይህ የኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግር ሁሉ ቀድሞ የመገኘት ታሪኳ ከዘመን ዘመን፤ ከመንግሥት መንግሥትም እየተጠናከረ ሲመጣ እንጂ ሲቀንስ አልታዬም። (ቆየት ብዬ በደርግ ዘመን መቀዛቀዙን ስጠቅስ እንዳይታዘቡኝ ከወዲሁ አደራ)  በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የማትመክርበት፣ የማትጋበዝበት የማትሰማራበትም የአፍሪካዊያን ችግር ያለ ሁሉ አይመስልም።

በተለይም በሰላም ማስከበርና በቅኝ ግዛት ስር ሲማቅቁ ለነበሩ አገራት ያደረገችው ድጋፍ አሁንም ድረስ የዘለቀው ታሪኳ ቢነገር ቢነገር የማይሰለችም ብቻ ሳይሆን የማይጠገብም ጭምር ነው። ለዚህም  ነው ኩራታችን ራታችንም ማለቴ። 

አገራችን በቅኝ አገዛዝና በአፓርታይድ ሥርዓት ሲሰቃዩ የነበሩ አፍሪካውያን የሞራል፣ የዲፕሎማሲና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ አገራቱ ነጻነታቸውን እንዲጎናጸፉ ያደረገችው አስተዋጾ ጉልህ ታሪኳ ነው። የእኛም ኩራታችን። በተለይም ለደቡብ አፍሪካ፣ ለናሚቢያና ለዚምባብዌ የነጻነት ትግል ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት ጭምር ያደረገችው አስተዋጽኦ ለራሳቸው ለአገራቱና ለእኛም ብቻ ሳይሆን ለተቀረው አፍሪካዊም ኩራት ነው።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር በኩል ታሪክ ማጻፍ የጀመረችው በኮሪያ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል። ኮሪያዊያን በአገራቸው ተቃጥቶባቸው በነበረው ወረራ የሚገቡበት ጠፍቷቸው፤ ቀኑ በጨለመባቸው ሰማዩም በተደፋባቸው ወቅት ቀድመው ከደረሱ አገራት መካካል አገራችን መሆኗን ስናስብ እጅግ የሚያስገርም ታሪክ ሆኖ እናገኘዋለን። ምክንያቱም በዚያ ጨለማ ዘመን ብዙ ሺህ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ላለች አገር የድረሱልኝ ጥሪ፤ ከጨለማዋ አህጉር ፈጥኖ መልስ መስጠት ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበው ህልም እንጂ እውን ላይመስል ሁሉ ይችላል።

ኢትዮጵያና ኢትዮጰያዊያን ግን ነጸነትንና ጥቅሙን አጣጥመው የሚያውቁ ህዝብና አገር ናቸውና ለኮሪያዊያን ጥሪ ቀድመው ደርሰዋል። ቃኘው ሻለቃ የተባለው ጦራችንም ከሌሎች 16 አገራት ወታደሮች ጋር በመሆን እጅግ አኩሪ ታሪክ ፈጽሞ ተመልሷል። ይህ የኢትዮጵያ ጦር የሚያስገርመው በኮሪያ በፈጸመው ጀብዱም ብቻ  ሳይሆን አንድም የህይወት መስዋዕትነት አለመክፈሉም ጭምር ነው።  በወቅቱ ሦስት ሺህ 518 የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በሶስት የተለያዩ ዙሮች የተሳተፈ ሲሆን፤ 238 ውጊያዎችን በማድረግም ዓለም አቀፋዊ ወታደራዊ ግዳጁን መወጣት ችሏል። ከዚህ በላይ ኩራት ይኖር ይሆን? ለእኔ በጭራሽ።

በኮንጎ የተደረገው የሰላም ማስከበር ስራም ቀጣዩ የአገራችን የዓለም ሰላም ዘብነት ታሪክ የተጻፈበት አጋጣሚ  ነበር። የቤልጂዬም ጦር ኮንጎ ላይ በማን አለብኝነት ጥቃት በመሰንዘሩ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ፓትሪስ ሉሙምባ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  የድረሱልኝ ጥሪ ያቀርባሉ። ድርጅቱም ይሄንን ተከትሎ ባደረገው ጥሪ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት አሁንም ቀድሞ በመድረስ ለኮንጎዎች የሰላምና የነጻነት ዘብ ሆኖ ተመልሷል።

ይሄኛው ጦር ደግሞ “ጠቅል” በሚል ስያሜ የዘመተና ኮንጎ በገባ በአጭር ጊዜ ውስጥም በተሰጠው ቀጣና ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ የቻለ ጀግና ጦር ነበር። በእርግጥ ኢትዮጵያ ገና ማልዳ ለሌሎች አገራት ሰላም ፈጥና የመድረስ ታሪኳ የደርግ ስርዓት ከመጣ በኋላ ተኮላሽቷል። በእርግጥ በደርግ ዘመንም ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ለእንደ ደቡብ አፍሪካና ናምቢያ ያሉ አገራት ነጸናት ትግል ያበረከተው አስተዋጽኦ አይካድም። ሆኖም ከሰላም ማስከበር አንጻር ግን ደርግ  የሚጠቀስ ታሪክ መስራት ሳይችል ቀርቷል።

እዚህ ላይ አንድ ነገር ጠቅሼ ልለፍ። እንዳልኩት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በንጉሱ ዘመን ወደር የሌለው እንደነበር ታሪኩ ይነግረናል። ደርግም ቢሆን ለተጠቀሱት አገራት የነጻነት ትግል ያደረገው ድጋፍ አይካድም። ነገር ግን "የውጭ አልጋ የውስጥ ቀጋ" እንዲሉ የሁለቱም መንግሥታት ወታደሮች በውጭ አገራት ዘንድ የሚነገር ታሪክ ቢፈጽሙም በአገር ውስጥ ግን ወታደሮቻቸው የሰላም ዘብ፤ የልማት ሀይል ከመሆን ይልቅ ህዝቡን የሚያስሩ፣ የሚገድሉና የሚያሰቃዩ እንደነበሩ መዘንጋት የለበትም። ለውድቀታቸውም መንስኤ የሆነው ይሄ ህዝባዊ ያልሆነው ባህሪያቸው ነው።

ወደ ሰላም ማስከበሩ ታሪክ ልመለስ።

ከንጉሱ ዘመን በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው ደርግ እንኳንስ ለሌሎች አገራት ሰላም ሊተርፍ ይቅርና ለአገር ውስጥ እንኳን የሚሆን ሰላምን ማምጣት ተሳነው። የተዛባው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውም ከአየአቅጣጫው ጠላት እንጂ ወዳጅ ሊያፈራለት አልቻለም። ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ግብጽና ሌሎች አገራት ደርግን በግራና በቀኝ ወጠሩት፤ ቁም ስቅሉንም አሳዩት። በውስጥም ነጻነትና ዴሞክራሲ ናፋቂ ወጣቶች ደርግን ሰቅዘው ያዙት። ወታደራዊው መንግሥትም "ሁሉም ነገር ወደጦር ግንባር" ወደ ሚል የሞኝ መርህ ተዘፈቀና አረፈው።

የሌሎች የነጻነት ቀንዲል የሰላምም ዘብ የነበረችው አገር ሰላሟ ጠፋ፤ ልማቷ የኋልዮሽ ሆነ። ልጆቿ ስደትን አንደኛ አማራጫቸው አደረጉት። የውጭ ግንኙነቷም ሻከረ፡፡ ስርዓት አልበኝነት ነገሰ። ማንም በሰላም ወጥቶ ስለመግባቱ እርግጠኛ መሆን አቃተው።

በዚህም ምክንያት ለ30 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያ ከሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውጭ ሆነች። ይህ ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተቀየረው፤ የደርግ ስርዓት በቁርጥ ቀን ልጆች ከተወገደና ግብአተ መሬቱ ከተፈጸመ በኋላ ነበር። ኢትዮጵያ ወደነበረችበት የሰላም ማስከበር ታሪክ ለመመለስ ቅድሚያ ያደረገችው የተዛባውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መቀየር ነበር። አደረገችውም። በዚህም ሰላሟ ተመለሰ፤ ልማቷም መቀጣጠል  ጀመረ።

በዘህ መሀል ወንድም የሩዋንዳ ህዝብ ሰላሙ መጥፋቱ እርስ በርስም መገዳደል ጀመረ። ይሄ ጉዳይ ያሳሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደተለመደው የሰላም ማስከበር ጥሪ ሲያደርግ ኢትዮጵያ ቀድማ አለሁ አለች። በድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ቁጥር 40 መሠረትም የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሃይል በ1986 ዓ.ም ሩዋንዳ ተሰማራ። ልብ ይበሉ፤ በ1986 ነው ያልኩት።

ይህ ወቅት ገና መንግሥት ከተመሰረተ የሶስት ዓመት እድሜ ብቻ መቆጠሩ ነበር። አገራችን ግን ለሰላም ያላት ዋጋና አመለካከት ላቅ ያለ ስለሆነ ገና ከተመሰረተ ሶስት ዓመት እንከን ያልሆነዉ የሽግግር  መንግሥት ሰላም አስከባሪ ጦር ለሩዋንዳ ለመላክ አላቅማማም። ይሄ መከላከያ ሰራዊታችን ያጎናጸፈን ኩራታችን ነው። ያውም ደረት የሚያስነፋ።

ወደ ሩዋንዳ የተሰማራው ሰራዊታችንም በሁለት ዙር ተልዕኮውን በአስተማማኝ መንገድ ተወጣ፡፡ ሰራዊቱ በጥሩ ስነምግባር ከመታነጹም በላይ ለአካባቢው ህዝብ በሚያደርገው የተለያየ እገዛና በሚያሳየው ፍቅር የማይዘነጋ ታሪክ አጽፎ መምጣቱን የሩዋንዳን ታሪክ በቅርበት የሚያውቁት ሁሉ የመሰከሩት ሀቅ ነው።

ሩዋንዳ ዛሬ በአፍሪካም ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከሚያስመዘግቡ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ አገራት ተርታ መሰለፍ ችላለች። ይህ የሩዋንዳዊያን ስኬት ለእኛ ኩራታችን ነው። ሩዋንዳዊያንም በወቅቱ ላደረግልናቸው ሁሉ ምስጋናቸውን የአገሪቱን ከፍተኛ ሜዳሊያ ለታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በመሸለም ገልጸውልናል። ይሄ አሁንም ኩራታችን ነው።

የኢትዮጵያ ቀጣዩ የሰላም ማስከበር ታሪክ የሚመዘዘው ደግሞ ከወደ ብሩንዲ ነው። በብሩንዲ መንግሥትና በአማጺያኑ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ሰምምነት በመጣሱ፤  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ ይወስናል። ኢትዮጵያም እንደተለመደው አንድ ሺህ ሰራዊቷን ወደ ቡርንዲ አሰማራች፡፡ ሰራዊቱም የተሰጠውን አገራዊና አህጉራዊ ሃላፊነት በተገቢው መንገድ ተወጥቶ ኩራትም አላብሶን ተመልሷል።

ላይቤሪያ ቀጣይዋ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት የተሰማራባትና የተጠቀመች አገር ናት። አሁንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በላይቤሪያ ለተሰማራው ጦራችን የተኩስ አቁም ስምምነቱን መፈፀሙን መቆጣጠር፣ ትጥቅ ማስፈታትና ሰላምን ማረጋገጥ የሚል ሃላፊነት ሰጥቶት በአግባቡ ተወጥቶም ወደ አገሩ ተመልሷል።

በወቅቱም የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሃይል ከ13 ሺህ በላይ አማጺያንን ትጥቅ በማስፈታትና ከ21 ሺህ 629 በላይ ስደተኞች ወደ ቀያቸው አንዲመለሱ ማድረግ ችሏል። በአገሪቱ ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድም የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ዛሬ ሁላችንም እንደምናውቀው ላይቤሪያ ያላችበት ሰላምና ልማት ላቅ ያለ ነው። ከዚህ ሰላምና ልማት በስተጀርባ ደግሞ እኛ አለን። ይሀ ታሪክ ሌላው በመከላካያ ሰራዊታችን ያገኘነው ኩራታችን ነው። 

የመከላከያ ሰራዊታችን አኩሪ ታሪክ ቀጥሎ በሶማሊያና በሱዳንም ያበረከትነውና እያበረከትን ያለነው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የጣሉበት አደራና ያሳደሩበት እምነት ደግሞ ከምንም በላይ ነው። አገራቱ በሚወዛገቡባት የአብዬ ግዛት ውስጥ የማንንም አገር ጦር አንፈልግም፤ ኢትዮጵያ ብቻ ብለው መርጠውን መግባታችን የሰራዊታችንን ህዝባዊነት ያረጋገጠ ነው።

በተለይ ደግሞ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መንግሥት አልባ ሆና በኖረችው ሶማሊያ የመከለከያ ሰራዊታችን የፈጸመውና እየፈጸመ ያለው ገድል ታላቅነት የሰራዊቱን ታላቅነት የሚመሰክር ነው። ሰራዊታችን በሶማሊያ የገባው አንድም ለሶማሊያዊያን ወንድሞቻችን ሰላም ሲል ነው። ሌላም ለራሳችን ዘላቂ ሰላም እንደሆነ ከተልዕኮው ጀርባ ያለው ታሪክ ይነግረናል።

ሰራዊታችን ሶማሊያ ባይገባ ኖሮ ትላንት የእስላማዊ ፍርድቤቶች ህብረት፤ ዛሬ ደግሞ የአልሸባብ መቀለጃ መሆናችን አይቀርም ነበር። ነገር ግን ምስጋና ኩራትም ራትም ለሆነው ሰራዊታችን ይሁንና ይሄ አልሆነም። ኢትዮጵያ ሽብርተኞችን የምታስጎመጅ እንጂ የምትቀመስ አገር አልሆነችም። ይሄ የጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ውጤት ነው። ዛሬ አገራችን ስራ ላይ ናት። ከስራችን ጀርባ ያለው ደጀናችን ሰለማችን ነው። የሰለማችን ዘብ ደግሞ አሁንም መከላከያችን ነው። ይህ የህዝብ ልጅ የሆነ መከላከያ በአህጉርና በዓለም ደረጃ በታሪኩና በጀግንነቱ ኩራትን ሲያላብሰን፤ በአገር ውስጥ ደግሞ ልማትን እንድናጣጥም ስላደረግን ራታችንም ሆኗል።

እነሆ ትላንትም በጅግጅጋ ከተማ የሰራዊታችን ቀን ተከብሯል።  “በህዝባዊ መሰረት የተገነባው ጀግንነታችን እየታደሰ ይኖራል" በሚል መሪ ቃል  በተከበረው አምስተኛው የመከላከያ ቀን ላይ የተነገረው የሰራዊታችን ገድልም እጅግ አኩሪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በተገኙበት በዚህ በዓል ላይ ሰራዊታችን ደምቆ ውሏል። ይህ ቢያንሰው እንጂ የሚበዛበት አይደለም። የሰራዊቱ አባላት የአልሸባብን ቅስም በመስበር ላደረጉት ተጋድሎም የክብር ሽልማት በመቀዳጀታቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የመከላከያ ሰራዊቱ ለማንም የማይበገር ሰራዊት ሆኖ እንዲቀጥል መንግሥት የሚያደርገውን ጥረትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

እኔም የምለው ይሄንኑ ነው። መንግሥት በዓመቱ መጀመሪያ  ላይ ለዚህ የህዝብና የአገር ዘብ ለሆነው ሰራዊት አድርገዋለሁ ያለው የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ በአፋጣኝ ይደረግለት። ትላንት  የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍሎ ይሄን አገር ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሯል። ሚሊዮኖችንም የልማቱ ተቋዳሽ አድርጓል። ዛሬ ደግሞ ተራው የእርሱ ነው። በደሙና በላቡ የገነባት አገር መልሳ የላቡንም ሆነ የደሙን ልትከፍለው ጊዜው አሁን ነው፡፡  ስለሆነም እላለሁ ኩራትም እራትም ለሆነን ሰራዊታችን ብድሩን እንክፈለው። አበቃሁ።

 

አርአያ ጌታቸው

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።