‹‹የፀጥታ ችግር…›› መዘናጊያ አይሁን

16 Feb 2017

ጉዳዬን ሳሰላስል መተረት አማረኝ፡፡ .… አንድ ሰነፍ ተማሪ ነው አሉ፡፡ ሰርክ እንደተበላሸ ተሸከርካሪ የአስኳላን ደጃፍ የሚረግጠው ተገፍቶ ነው፡፡ ከወላጆቹም ቢሆን የዘወትር አተካራው ጥናት አለመውደዱና ትምህርት ቤት መጥላቱ ነበር፡፡ ብቻ እንደነገሩ የደንብ ልብሱን አጥልቆ ከቤት ውልቅ ይላል፡፡ ከወላጅ የከረረ ቁጣ ለማምለጥ ሲል ይሄን ዘወትር ሳይወድ ያደርገዋል፡፡ እንደምንም ክፍል ገብቶ ቢቀመጥም እንደ ብርቱ አቻዎቹ ቀልቡን ለመምህሩ አሳልፎ ከመቸር ይልቅ፤ ክፍለ ጊዜው ቶሎ አልቆለት ወደሚናፍቀው ስንፍና መቼ እንደሚመለስ ጠልቆ ያሰላስላል፡፡

ከእለታት አንድ ቀን ስንፍናውን በሚገባ የታዘቡ የሒሳብ መምህር፤ በድኑን ሰይሞ በሀሳብ ከሸፈተበት ዓለም ለመመለስ ቀላል ጥያቄ ያቀብሉታል፡፡ ልጁ ግን ስለመቀነስ የሒሳብ ስሌት ያስተማሩት ምንም ስላልገባው በጥያቄው ይደናገጣል፡፡ ብልሁ መምህር ግን ተስፋ በመቁረጥ ‹‹አንተን ከማጎበዝ ዶክተር ማደደብ ይሻላል›› አላሉትም፡፡ ይልቁኑም ጥያቄውን ይበልጥ ለማቅለል በማሰብ የእውቀት ማገዶ ፈጂውን ተማሪ በምሳሌ ማስረዳት ገፉበት፡፡

‹‹እሺ፤ በረት ውስጥ አምስት በጎች አሉህ››፤ ‹‹በጀ›› ተማሪው ቀጣዩን ይጠብቃል፡፡ ‹‹ከአምስቱ በጎች አንዱ ሾልኮ ቢያመልጥ ስንት ይቀሩሃል?›› ሲሉ ይጠይቁታል፡፡ ተማሪውም ቀበል አድርጎ ‹‹ኸረ መምህር ምንም አይቀረኝ›› ይላል፡፡ በምላሹ ብግን ያሉት መምህር ‹‹ይህ እንዴት አይገባህም?›› ብለው ቢጮሁ፤ ተማሪው እያለቀሰ ‹‹ኸረ መምህር የበጎችን አመል ጠንቅቄ ነው የማውቀው፤ አንዲቷ ካመለጠች ሌሎቹም ተከትለዋት ነው የሚጠፉት›› በማለት ስህተቱን አሽሞንሙኖ በብልጠት ለማምለጥ ሞከረ፡፡ መምህሩም በምላሹ ከመሳቅ ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡

ምን ያድርጉ? ‹‹ማሽላ እያረረች ትስቃለች!›› ይባል አይደል፡፡ በነገራችን ላይ በየመስኩ የሰነፉን ተማሪ ባሕሪ የተላበሱ አይጠፉም፡፡ በትምህርትም ባይሆን የታዘዙትን ስራ በአግባቡ ላለማከናወናቸው ማምለጫ እንዲሆን ከስሌት ያፈነገጠ አመክንዮ እየደረደሩ ዙሪያ ጥምጥም የሚሄዱ ብዙ ናቸው፡፡ መቼም የሒሳብ ቀመር ላይ የፍልስፍና ነፋስ ሽው ካላለ በቀር የአንድ ሲደመር አንድ ውጤቱ ሁሌም ከሁለት ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ለስንፍናቸው መከለያ ይሄን ስሌት የሚያዛቡ አይጠፉም፡፡

በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የታዘዙትን ስራ ወይም የተቋሙን ዓመታዊ ዕቅድ አቅርበው፤ ‹‹ምነው ይሄ አፈጻጸም ዝቅተኛ ሆነ?›› ሲባሉ፤ ለድክመቱ አሳማኝ ምክንያት ማስቀመጥ ይሳናቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ድክመትን በመቀበል ነገ ለመታረም ከመዘጋጀት ይልቅ ‹‹የበጎችን ባህሪ ጠንቅቄ አውቀዋለው›› የሚል አይነት ማምለጫ ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን በየትኛውም የስራ አፈጻጸም ውስጥ በትጋት የተሞላ ብቃትና ቁርጠኝነት ካለ ‹‹አንዱን አስወጥቶ ሌሎቹን በጎች ለማስቀረት›› ብልሃት አይጠፋም፡፡

ወደ ነጥባችን እንመለስ፡፡ ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት  አንስቶ አሁን እስከምንገኝበት ዓመት መግቢያ ድረስ በዘለቀ የሰላም ችግር ማለፏ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተነሳው የሰላም መደፍረስ ያስከፈለው አገራዊ ዋጋ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በኢኮኖሚው በርካታ የአገር ውስጥና የውጪ ኢንቨስትመንቶችን ጨምሮ በቱሪዝም፣ በግብርና እንዲሁም በንግድና ሌሎች ምጣኔ ሀብቶች አፈጻጸም ላይ አሉታዊ አሻራውን አትሟል፡፡ በረጅም ጊዜ የአገሪቱ  ዕቅዶችም ላይ የተወሰነ መጓተትን ፈጥሯል፡፡ በአጠቃላይ የሰላም አይተመኔ ዋጋ በሰላሙ መናጋት ወቅት በሚገባ ተንፀባርቋል፡፡ 

ለዚያም ነው፤ መንግስት የችግሮቹን ጥልቀት በሚገባ መዝኖ መንግስታዊ ግዴታውን በተለያየ መልኩ በመወጣት ተግባር ተጠምዶ የከረመው፡፡ ከምንም በላይ ለዘላቂ ልማት ዋልታና ማገር የሆነውን የሰላም አየር ለመመለስ ብዙ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ችግሩን ‹‹የሌሎች ጥፋት›› በሚል ቸልታ ከማለፍ ይልቅ፤ ጥንስሱን ከመሰረቱ መለየት በሚያስችል ደረጃ ‹‹ውስጤን እመለከትበታለሁ›› በማለት መንግስታዊ መዋቅሩን በጥልቅ የተሃድሶ ወይራ ሲያጥን ሰንብቷል፡፡

ከመንግስት ሹማምንት ቀጥሎ ወደ ፈጻሚው የወረደው የተሃድሶ መድረክ በሲቪል ሰርቫንቱ በተለይም በፈጻሚው ውስጥ ያለውን የአመለካከት ክፍተት ለማመላከት እንዳስቻለው አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን የተሿሚዎቹን የስራ ብቃት ፈትሾ የአመራር ለውጥ የማድረጉን ያህል ለአፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ‹‹የሰላም መደፍረስ ያመጣው ነው›› በሚል ‹‹ሽፋን›› ላለፈ የውስጥ ድክምቶቻቸው መጋረጃ የሚያደርጉትን መለየት ይገባዋል፡፡ በእርግጥ የሰላም መደፍረሱ ያመጣውን ችግር በፍፁም መካድ አይቻልም፡፡ ሆኖም ችግሩን ከዕቅድ ትግበራ ወቅትና ስፍራ ጋር ሳያገናዝቡ ደጋግሞ በምክንያትነት እየጠቀሱ ከተጠያቂነት ለማምለጥ መዳዳት አዋጭ አይሆንም፡፡          

ሰሞኑን በስራ አጋጣሚ በተገኘሁባቸው ጥቂት የማይባሉ የዕቅድ ግምገማ መድረኮች ‹‹የፀጥታ ችግር›› የሚለው ምክንያት በዝቶ ታዝቤያለሁ፡፡ እንደሚታወቀው የምንገኝበት ወር የዓመቱ ስራ አፈጻጸም በየዘርፉ የመንፈቅ ተሞክሮ የሚፈተሽበት ነው፡፡ በተገኘሁባቸው የተቋማት የስድስት ወራት ዕቅድ አተገባበር ፍተሻ ወቅት ለተለያዩ ንዑስ ዘርፎች ዝቅተኛ መሆን የጠቀስኩት ምክንያት ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡

ምክንያት መኖሩ ባልከፋ፡፡ ነገር ግን ከታማኝነት ያፈነገጡ ዙሪያ ጥምጥም ምክንያቶችን መደርደር የዛሬን ስንፍና ለመቀበል ፈቃደኛ ካለመሆን ባሻገር በቀጣይም ለመሻሻል የፍላጎት ዋስትና ይነፍጋል፡፡ ይሄ ደግሞ ከማስተዛዘብ አልፎ የሚያስጠይቅ ድክመት ይሆናል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ አንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ጠርቶ ‹‹በስድስት ወሩ ምን አቅደህ፤ ምን ተገበርክ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ መስሪያ ቤቱ ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ግኝት የአንበሳውን ድርሻ የሚወጣ ግዙፍ ዘርፍን ይመራል፡፡ ይሄ ዘርፍ በጥቂት መዘናጋት ብዙ አገራዊ ጥቅም የሚታጣበት፤ ይበልጥ በተጉ ቁጥር ደግሞ ብዙ ጥቅም የሚያሳፍስ ወሳኝ መስክ ነው፡፡

እንደራሴዎቹ ብቻ ሳይሆኑ መንግስትና ሕዝብ ከአፈጻጸሙ ብዙ የሚጠብቁበት በመሆኑ ግምገማቸው ብርቱ ነበር፡፡ ሆኖም የተቋሙ ሪፖርት በአብዛኛው እንደሚያመላክተው በስድስት ወራት ውስጥ ብዙ አቅዶ ያሳካው አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ የግምገማ ደንብ ነውና በጉዳዩ ላይ ምላሽና ማብራሪያ ለመስጠት ከሚኒስቴሩ ከፍተኛ ሃላፊዎች እስከ መካከለኛ አመራሮች በስፍራው ታድመዋል፡፡ ለተነሱት ጥቄዎችም ‹‹መልስ›› ያሉትን ዘረዘሩ፡፡ የሚያስገርመው ነገር በስራ ሃላፊዎቹ ሲጠቀስ እንደሰማሁት ከእያንዳንዱ ደካማ አፈጻጸም ጀርባ ‹‹የፀጥታ ችግር›› የሚለው ተደጋግሞ በምክንያትነት መሰማቱ ነው፡፡

የገዛ ትዝብቴ የእንደራሴዎቹም ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ እያንዳን ዳቸውን ምላሾች እያነሱ ‹‹የሰላም መደፍረስ የነበረባቸው ስፍራዎች ውስን ናቸው፤ በተጨማሪም የሰላም መደፍረሱ ጊዜና የዕቅዱ መፈጸሚያ ወቅት የተናበቡ አይደሉም›› በሚል ከሁሉም ድክመቶች ጀርባ መነሳቱ እንዳላስደሰታቸው ጠቀሱ፡፡ ሃላፊዎቹ ግን ‹‹የበጎችን አመል ጠንቅቄ አውቀዋለሁ›› በሚል አይነት አቋማቸው ገፉ፡፡ እደግመዋለሁ፤ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁኔታው አሳማኝ ቢሆን እንኳን አመለካከቱ በተመሳሳይ መልኩ ከገፋ የቀጣዩ ስድስት ወራት ክንውንም ስጋት ውስጥ ይወድቃል፡፡

ከጠቀስኩት ተቋም በተጨማሪ ‹‹ከፀጥታ ችግሩ ጋር በቀጥታ የመገናኘት እድላቸው አነስተኛ ነው›› ተብሎ በሚገመቱትም ሳይቀር ምክንያቱ መደጋገሙ ስጋቴ ከንቱ እንዳይሆን አደረገው፡፡ አሁን አገሪቱ ወደተረጋጋ መስመር እየገባች ነው፡፡ በመሆኑም ቀጣዮቹ ጊዜዎች ካለፈው ስድስት ወር በእጥፍ ትጋትን የሚጠይቁ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በሰላም መደፍረስ የባከኑትን ወርቃማ የልማት ጊዜያት ማካካስ ያስፈልጋል፡፡ የአገሪቱ ቁልፍ የልማት ጥያቄዎች የሚመለሱበት መንገድ ‹‹ከናዳው በፈጠነ›› ቅልጥፍና መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

እናም እኔ ይሄን እላለሁ፤ ከምንም በላይ የሰላም ጥቅም መተኪያ የለውም፡፡ ስለዚህ ሰላም ለማንም ተብሎ የሚተው ተራ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ድክመታችንን ተከትሎ ለሚሰነዘር ሂስ የማያባሩ ሰበብ አስባቦችን ደጋግሞ መደርደር እምነት ይሸረሽርብናል፡፡ ሰላም ለልማት እንደሚስፈልግ ሁሉ ሰላምም የአገር ልማትን አጥብቆ ይሻል፡፡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥቄዎችም መልስ የሚያገኙት በቁርጠኝነት ማገልገል ሲቻል ነው፡፡ ያኔ ሰላም ለልማት፤ ልማቱም በሰላም ተደጋግፈው ይዘልቃሉ፡፡ እስከመቼ? ድህነት እስኪረታ! እስከየት? እስከ ብልፅግና መዳረሻ!

ሚሊዮን  ሺበሺ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።