ተሃድሶው ለሁሉም የሚበጅ ስለሆነ ራሳችንን ብናይ!

17 Feb 2017

መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የመንግስት ሰራተኞች ግንባር ቀደም ሚና እንደሚጫወቱ እሙን ነው። የመልካም አስተዳደር እጦት በቅርቡ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ለተነሱ ሁከቶች ዋንኛ ምክንያት ነበር። መንግስት  ችግሮቹን ለመቅረፍ ከሚያ ደርጋቸው በርካታ ጥረቶች መካከል የመንግስት ሰራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ የሚፈተሽበት አካሄድ እንዲመቻች አድርጓል።

ሰሞኑን በተለያዩ የክልልና የፌዴራል  የመንግስት ሰራተኞች አካላት የተሃድሶ መድረኮች በመካሄድ ላይ ናቸው። እነዚህ የተሃድሶ መድረኮች እንዲካሄዱ መንግስት ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ እጅግ በጣም ጥሩ ይመስለኛል። የመንግስት ሰራተኞች ለህብረተሰቡ የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለማሻሻል የሚያስችለው በመሆኑ በጥልቀት የመታደስ መድረኮች ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አስባለሁ። አንዳንድ ሰዎች “በጥልቀት ተሃድሶ” የሚለውን አካሄድ ከኢህአዴግ ጋር ብቻ ሲያገናኙት ይታያሉ። ይሁንና ይህ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም። የተሃድሶ ዋንኛ አላማ የመንግስት አገልግሎቶችን በማሻሻል መልካም አስተዳደርን በማስፈን አገራችን የጀመረችውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና  ልማት ማፋጠን ነው።

ለመልካም አስተዳደር  መጠናከርም ሆነ መድከም  የመንግስት (የበላይ አመራሩ) ሚና የማይተካ ቢሆንም  የመንግስት ሰራተኞች  ሚናም  በቀላሉ የሚታይ አይደለም። መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የላይኛው የመንግስት አካል  የትኛውንም ያህል ጥረት ቢያደርግ  የታችኛው ፈጻሚ አካልና  አገልግሎት ተቀባይ (ህብረተሰቡ)  ግዴታቸውንና መብታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ማድረግ  ተገቢ ነው።  አሁን እነዚህን  የተሃድሶ መድረኮች በመጠቀም ሁሉም በየደረጃው በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ማለፍ  መልካም ነገር ነው።

የኢህአዴግ አመራርና አባላት ይታደሳሉ፤ የመንግስት ሃላፊና ፈጻሚ (የመንግስት ሰራተኞች) ይታደሳሉ፣ ህብረተሰቡ ይታደሳል። በእርግጥ የግምገማው ነጥቦች፣ ደረጃውና አካሄዱ ለየቅል ይሁን እንጂ   ሁሉም በየደረጃው በተሃድሶው ውስጥ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። መታደስ ማለት  “የመንግስት የስራ ሃላፊነት ለህዝብ አገልግሎት ማዋል” ማለት ነው። መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የመንግስት ሰራተኞች ለህዝብ  የሚሰጡትን አገልግሎት ማሻሻል የመጀመሪያ ተግባር ነው።  የመንግሥትን ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች እና ዕቅዶች የሚያስፈጽመውና  የሚፈጽመው የመንግስት ሰራተኞች በመሆናቸው አገልግሎቶችን ለማሻሻል  መታደስ የግድ ይላቸዋል፡፡  ይታደሳሉ ሲባል በፖለቲካ አመለካከታቸው ወይም ወገንተኝነታቸው ሳይሆን  ስራን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነው።

የመንግስት አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የነገሰበት እንዲሆን ህገመንግስቱ ይደነግጋል።  በመሆኑም እየተካሄደ ያለው  የተሃድሶ መድረኮች  የመንግስት ሰራተኞች ህዝብን ለማገልገል የገቡትን ቃል ለመፈጸም የሚያስችላቸውን አቅም የሚፈጥርበት መድረክ በመሆኑ በአግባቡ መካሄድ ይኖርበታል።  የመንግስት ሰራተኞች በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ በማለፍ ጠንካራ  የአገልጋይነት መንፈስ  መላበስ  የሚያስችላቸውን አቅም ስለሚያገኙ አገራችን የጀመረችውን  ፈጣን እድገት የሚያስ ቀጥሉበት አቅም ይፈጥርላቸዋል።

የመንግስት ሰራተኞች ህብረተሰባዊ አስተሳሰብን መላበስ ለአገልግሎት አሰጣጥ አስፈላጊ ናቸው። የታደሉት ለህዝባዊነት ሲሉ ህይወታቸውን ገብረዋል፤ አካላቸውን አጉድለዋል። ይህ ትውልድ ያን አይነት መስዋዕትነት አይጠበቅበትም። ይልቁንም ከዚህ ትውልድ የሚጠበቀው  በተሰማራበት መስክ የተጣለበትን አደራ  በአግባቡ መወጣት መቻል ነው። ለህብረተሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት ሲሻሻል  የአገራችን ዕድገት ይፋጠናል በዚህም እኔም ተጠቃሚ እሆናለሁ የሚል አስተሳሰብ ሊያዳብር ይገባል።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12/1/ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ባለው  መንገድ መከናወን አለበት በሚል በተደነገገው መሠረት የመንግስት ሰራተኞች ለዜጎች የሚሰጡት አገልግሎት ከአድልዎ የፀዳ በመርህ ላይ የተመሠረተ መሆን መቻል አለበት፡፡ በመሆኑም የመንግስት ሰራተኞች  የአገልግሎት መሻሻል ከህልውናቸው ጋር  የተያያዘ  መሆኑን  በመረዳት እንዚህን የተሃድሶ መድረኮች በአግባቡ መጠቀም ይኖርበታል።  ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ይባላል። እውነት ነው፤ የመንግስት ሰራተኞች መረዳት ያለባቸው ነገር የአገልግሎት አሰጣጡ ሲሻሻልና ህብረተሰቡ መንግስት በሚሰጠው አገልግሎት እርካታ ቢያገኝ የአገራችን ዕድገት ይፋጠናል የሚለውን ነው።

አገር  ስታድግ፣ ህዝብ ሲጠቀም እኔም እጠቀ ማለሁ የሚል አስተሳሰብ  መዳበር  ይኖርበታል። በአድልዎና  እምነትን በማጉደል ወዘተ... ለጊዜው ጥቅም ይገኝ ይሆናል።  ነገር ግን ዘላቂ እርካታ አይገኝም፣ አገር አይገነባም፣ ትውልድ አይታነጽም። በመሆኑም በታማኝነትና በቅንነት ህዝብና አገርን የማገልገል መንፈስ  መዳበር አለበት። ሁሉም በተሰማራበት የስራ መስክ  ሃላፊነቱን በአግባብ መወጣት ከቻለ አገር ትለወጣለች። የመንግስት ሰራተኞች ለሕዝቦችና ለአገራቸው  ያላቸውን ወገናዊነት የሚያሳዩት  በተሰማሩበት መስክ  በቅንነት፣ በታማኝነትና በቁርጠኝነት ማገልገል ሲችሉ ብቻ ነው። 

መንግሥታዊ አገልግሎቶች ለሕብረተሰቡ በሚፈለገው ጊዜ፣ መጠንና ቦታ የማይሰጥ ከሆነ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌዎች በአግባቡ ተተግብረዋል ማለት አይቻልም።ኅብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን አገልግልቶች በህግ  የመጠየቅ መብት አለው፤ በሌላ በኩል የመንግስት ሰራተኞች  አገልገሎት የመስጠት ህጋዊ ግዴታ ወይም ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በመሆኑም የመንግስት ሰራተኞች ተግባር የመንግሥት ፖሊሲዎች ማስፈፀሚያ ሥርዓት እንደመሆኑ ከላይ የተገለፁትን መርሆዎች መሰረት በማድረግ ውስጡ የሚታዩትን የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሙስናና ብልሹ አሠራሮች ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ ይህን ደግሞ እውን የሚያደርገው በእንደዚህ ያሉ የተሃድሶ መድረኮች ላይ በንቃት በመሳተፍ ብቻ ነው።

ለመልካም አስተዳደር  እንቅፋት የሆኑ  ለዘላቂ ልማት ስጋት የሚሆኑ ድርጊቶችን በማስወገድ ድህነትን ለማሸነፍ የመንግስት ሰራተኞች የስራ ስነምግባር  በሚያዘው መሰረት ማገልገል ይኖር ባቸዋል፡፡  ህዝብን በቅንነት  ማገልገል ህዝባዊ አደራን መወጣት በመሆኑ ታላቅ ኩራት ነው።ቃል የተገባውን  ህዝባዊ ተልዕኮዎች በታማኝነት  መወጣት ከተቻለ መልካም አስተዳደር ይሻሻላል። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓትም ይጎለብታል። የተጀመሩ የልማት ስራዎችም ይፋጠናሉ። ይህ ሲሆን  የመንግስት ሰራተኞች ህይወትም በዘላቂነት ይቀየራል።

ለሁሉም ዜጋ የመንግስትን አገልግሎት በእኩልነት የማግኘት ሕገ-መንግስታዊ መብት አለው። የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊት ልማትን የሚጎትቱ ከመሆናቸውም ባሻገር የሕዝቦችን በአንድነትና በሰላም የመኖር እሴት የሚሸረሽሩ  መሆናቸው የመንግስት ሰራተኞች ይህንን ተገንዝበው በጽኑ ሊታገሏቸው ይገባል፡፡ የሃይማኖት አክራሪነት፣ ጥበትና ትምክህት የስርዓቱ  አደጋዎች ተብለው የተለዩ  በመሆናቸው  የሁሉንም ትግል ይጠይቃሉ።

  አባ መላኩ 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።