በፀረ ሙስና ትግሉ ውስጥ

07 Aug 2017

ሰሞኑን መንግሥት እያካሄደ ባለው ፀረሙስና ትግል ውስጥ ያሉትን በርካታ ውስብስብ አሠራሮች ከዋናው ዐቃቤ ሕግ መግለጫ ለመረዳት ችለናል፡፡ ሕዝቡ ብዙ ቅሬታዎች ነበሩት፡፡ በተለይ የዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት ለመንግሥት ባቀረበው ሪፖርት ላይ ያሳያቸው የገንዘብ ጉድለቶችና የፋይናንስ ጉዳቶች ምንም እርምጃ ሳይወሰድባቸው መቅረቱ የሕዝቡ የቅሬታ ምንጮች ናቸው፡፡ ሙስና ዓይን አወጣ፣ ሙሰኞች አሸነፉ፣ ተንሰራፉ፣ ተስፋፉ፡፡ ሀይ ባይ አጡ ሕዝቦች ግብር ይከፍላሉ፡፡ ሙሰኞች የሕዝብ ገንዘብ ወደ ኪሳቸው ይከታሉ፡፡

 ከአንድ ሙሰኛ መኖሪያ ቤት ብቻ ወደ አራት ሚሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ተገኝቷል፡፡ በእንግሊዝ ፓውንድ፣ በአሜሪካ ዶላር በቻይና፣ በአረብ ኢሜሬት በኡጋንዳ ገንዘብ ሳይቀር ከተለያዩ የባንክ ደብተሮችና የቤትና የመሬት ባለቤትነት ካርታዎች ጋር ተይዟል፡፡ የሙስና አሠራራቸውም የረቀቀና የተወሳሰበ ነው፡፡ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ የራሱን የንግድ ድርጅት ከፍቶ ከሚሰራበት መስሪያ ቤት የሚታዘዙ ግዢዎችን ያለምንም ጨረታ እየወሰደ ሲሞስን ተይዟል፡፡ ተገዛ የተባለው ዕቃ ገቢ ሳይሆን ክፍያዎች ይፈፀማሉ፡፡ ከገረጋንቲው፣ ከሲሚንቶው፣ ከአርማታው፣ ከምንጣሮው… ወዘተ ሁሉ የሕዝብ ገንዘብ በሙሰኞች ሲመዘበር ከርሟል፡፡

በአገሪቱ ሥራዎች ውስጥ በሙሉ ሙሰኝነት ነግሷል፡፡ የግዢ መመሪያውን ሳይከተል ብዙ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ግዢ እየተፈፀመ በመንግሥት ፋይናንስ ላይ ጉዳት መድረሱ ተረጋግጧል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የውጭ አገር አበዳሪን ገንዘብና ፋይናንስ ሚኒስቴር ጋር በመገናኘት ሰበብ ለሦስት ደላሎች ተሰጥቷል፡፡ የአገሪቱ ሥራዎች በተመደበላቸው ጊዜና በጀት መሠረት አይሰሩም፡፡ በሁለት  ዓመት ያልቃል የተባለ ሥራ በአምስት ዓመትም አያልቅም በ300 ሚሊዮን ብር የተያዘ በጀት በ900 ሚሊዮን ብር የሚያልቅበት ሁኔታ አለ፡፡

በሙስና ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦችን በተመለከተ የዐቃቤ ሕጉ አካሄድ ትክክልና ተገቢ ነው፡፡ ማለትም የተያዙት ሥራውና ግድፈቱ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከላይ ያሉት ሚኒስትሮች የሌላውን አጠቃላይ አቅጣጫ ማስያዝና ፖለቲካዊ አመራር መስጠት ነው፡፡ ዋናውን ሥራ የሚሰሩት፣ ግዢ የሚፈፅሙት ጨረታ የሚያወጡትና አሸናፊውን የሚመርጡት ለአፈር ቆረጣና ለገረጋንቲ ማፍሰስ ሥራ ቀጥታ እጃቸውን የሚያስገቡት የተቋሙ ዋናና ምክትል ሥራ አስኪያጆች ዳይሬክተሮችና ቡድን መሪዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ተጠያቂዎችም እነዚሁ ሰዎች ናቸው፡፡

«ከሚኒስትሮች ጋር ንኪኪ ይኖራቸዋል፤ ለራሳቸው ሲበሉ ለሚኒስትሮቹም ያጐርሳሉ» የሚባል ነገር ሊኖር ከቻለ በሂደት በምርመራው በሚገኙ መረጃዎችና ማስረጃዎች የሚረጋገጥ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በ200ሺ ብር ባለ 15 ኪሎ ቮልት ጀኔሬተር እንዲገዛ በተፈቀደ በጀት ደረጃው ዝቅተኛ የሆነ ባለ 7 ቮልት ጀኔሬተር ግዢ ሲፈፀም ይህ ሚኒስትሩን ሳይሆን የዕቃ ግዢ ክፍሉን ሙስኝነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በራስ አቅም የተሰራውን የምንጣሮ ሥራ በኮንትራክተሩ የተሰራ በማስመሰል 10 ሚሊዮን ብር እንዲከፈል ማድረግ የሥራ ሂደቱን  ሙሰኝነት የሚያሳይ ነው፡፡

 የፀረ ሙስና ትግሉ እገሌ ከእገሊ አይልም ወደታች ብቻ ሳይሆን ከጐንና ከላይ የሚገኙትን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡ ዋናው ነገር በቁጥጥር ስር ለማዋልና ምርመራ ለማድረግ መነሻ የሚሆን ማስረጃ መኖር አለበት፡፡ ከፍተኛውን ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ያላቸው ሚኒስትሮችና ዴኤታዎች በዚህ ሂደት ውስጥ ተጠያቂነት የለባቸውም እያልን አይደለም፡፡ የሙስናው ተቋዳሽ ባይሆኑም በሥራቸው በሚተዳደር ተቋም ውስጥ ሙስና ሲፈፀም፣ ወይም በመንግሥት ፋይናንስ ላይ ጉዳት ሲደርስ… የማወቅና አሠራሩን መፈተሽ አለባቸው፡፡ ስለጉዳዩ መረጃ ሲደርሳቸው ዝም ማለታቸው ሊያስጠይቃቸው ይችላል፡፡ በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ጥፋቶች ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ይህም በአስተዳደርና ቅጥር ብቃት ማነስ በቸልተኝነት ወይም አውቆ ዝም በማለት… አስተዳደራዊ ቅጣት ሊደርስባቸው ይችላል እንጂ በሙስና ወንጀል አያስ ጠረጥራቸውም፡፡ የፖለቲካ ሹመኞች በመሆናቸው ተገምግመው ገለል ሊደረጉ ይችላሉ፡፡ የሙስና ወንጀሎቹ ዋና ተዋንያን ግን በእነሱ ስር ያሉ ሥራው በቀጥታ የሚመለከታቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በዙሪያችን ያለ እውነታውን ብንቃኝ ተመሳሳይ ጉዳይ ይገጥመናል፡፡ አቤቱታ ለማቅረብ ክፍለ ከተማ ብንሄድ ሙሰኝነት ያለው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ዘንድ አይደለም ሙስና የሚፈፀመው በእሱ ስር ባሉ ሰው ባለ ሹመኞችና ሥራ ፈፃሚዎች አማካኝነት ነው፡፡ ዋና ሥራ አስፈፃሚው በሚመራው ተቋም ውስጥ ሙስና እየተፈፀመና ሕዝቡ እየተማረረ መሆኑን እያወቀ ዝም ካለ ወይም የበታቾች በሙስና ካገኙት ወረት ላይ የሚቀራመት ከሆነ ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡ ከበላይ አለቆቹ ጋር ሙስናውን ተካፍሎ በልቶ ብቻውን የሚታሰርበት ምክንያት ስለሌለ በምርመራው ሂደት ማጋለጡ አይቀርም፡፡

የአገር ሹም በሙሉ ተጠራርጐ ዘብጥያ ይውረድ ባይባልም ቁጥራቸው በ51 ብቻ የሚወሰን መሆን የለበትም፡፡ ገና በጣም ብዙ ተጠርጣሪ ሙሰኞች መኖር አለባቸው። እነዚህ ከላይ የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙ በመቶ ሺህ ሳይሆን በሺህ ሚሊዮን ሙስና ስማቸው በሕዝብ አፍ በክፉ የሚነሳ ሰዎች አሉ፡፡ ሙስና ወንጀል በመሆኑ ያለ ማስረጃ ይታሰሩ አይባልም፡፡ ገሚሱ በጥርጣሬ በስሜት በአሉባልታ የሚያስበው ሊሆን ይችላል፡፡ ለአገራችን ክፉ የሚመኙ መሰሪ ጠላቶች ደግሞ እገሌና እገሊት ካልታሰሩ የፀረ-ሙስና ትግሉ ዋጋ የለውም፣ ወይም የውሸት ነው ወይም ቀውጢ ሲመጣ ሊያመልጥበት ያዘጋጀው ነው። በማለት ሕዝቡ በመንግሥት የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ ላይ ያለውን እምነት ለመሸርሸር ይጠቀሙበታል፡፡

እነኚህና ሌሎች የወገን ጠላቶች የፀረ ሙስና ትግሉ ውስጥ መርዝ ለመጨመር ሂደት ከብሔር በተለይም ከዘረኝነት ፖለቲካ ጋር ያነካኩታል፡፡ የእገሌ ብሔር ሰዎች አልተነካም ወይም አይነኩም፣ ዘመቻው ያነጣጠረው የእገሌንና የእከሌን ብሔር ሰዎች ከሥልጣን ቦታዎች ለማንሳትና በምትካቸው የእገሌን ብሔር ሰዎች አምጥተው የሙስና ተጠቃሚ ለማድረግ ነው የሚል የመርዝ ብልቃት ይዘው ሕዝቡን እርስበርሱ ለማጋጨትና ማለቂያ የሌለው ትርምስና ጦርነት ለመፍጠር የሚንቀዠቀዙ የሰው ክፉዎች አሉ፡፡

መንግሥት የእነዚህን አፍራሽ ኃይሎች መርዝ ለማክሸፍ ምንም መጨነቅና ሥራ መፍታት የለበትም፡፡ ማለትም ለእነሱ አሉባልታ ምላሽ እንዲሆን የእገሌ ብሔር የሆኑትን ባለሥልጣኖች ወይም ባለሀብቶች ያለ ማስረጃ የሚያስርበት ወይም ተጠያቂ የሚያደርግበት ሁኔታ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ ለጠላት ወሬ ሲል ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉትን የሕዝብ ልጆች በዓይነ ቁራኛ ማየት አይኖርበትም፡፡

የመንግሥት ኃላፊነት በጥልቅ ተሃድሶው ውጤት የጀመረውን የፀረሙስና ትግል በማስረጃ በተደገፉና ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው አግባብ ተግባራዊ ማድረጉን መቀጠል ብቻ ነው፡፡ በሕዝቡ ግንዛቤ ውስጥ ውዥንብር እንዳይፈጠር ግን በፀረ ሙስና ትግሉ ውስጥ በየደረጃው የደረሰባቸውን የሥራ ውጤቶች በተከታታይ ለሕዝብ እንዲደርሱ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ዘመቻው የተዋፅኦ ማሟያ አለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የወንጀለኝነት ጉዳይ እንጂ የአሳታፊነት ጨዋታ አይደለም፡፡ ማለትም የፆታ ተዋጽኦን በሚመለከት ተጠያቂ የሚሆኑት ማስረጃ የተገኘባቸው እንጂ ከወንዶች ወንጀለኞች ቁጥር አንፃር የሴቶች ቁጥር አነስተኛ ነውና የሴቶችን ተዋጽኦ ለማመጣጠን ተጨማሪ ሴቶችን እንሰር የሚባልበት ሁኔታ የለም፡፡ ድሮም ቢሆን በሙሰኝነት ላይ የሚገኙ ሴቶች ቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ እገሊትን በስም እየጠሩ «ካልታሰረች» ማለትም ጠላትነት ነው፡፡ ማንም ይሁን ማ ያለሃጢአቱ፣ ያለወንጀሉ አይታሰርም፡፡ ወንጀለኛ ከሆነ ግን ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነውና ተጠያቂ ከመሆን አይድንም፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የብሔር ተዋጽኦ ማመጣጠንም የፀረ-ሙስና ትግሉ ዓላማ አይደለም፡፡የአንድ ብሔር ሙሰኞች ቁጥር አነስተኛ ሲሆን የሌሎች ብሔሮች ሙሰኞች ተጠርጣሪዎች ቁጥር ብዥታውና ይህን ለማመጣጠን የሁሉንም ብሔር ተጠያቂዎች ቁጥር እኩል እናድርግ የሚባል ፍልስፍናም የለም፡፡ ያጠፋና ማስረጃ የተገኘበት ይጠየቃል እንጂ ለቁጥር ማመጣጠኛ ተብሎ ንፁህ ሰው የሚታሰርበት ሁኔታ የለም፡፡ እየታየ ያለውኮ ኮሜዲ ድራማ አይደለም፡፡ ፍርደ ገምድልነት በፀረሙስና ሥራ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ በሕግና በሕግ አግባብ ብቻ እንጂ በሌላ ማንኛውም የጥላቻና የበቀል መንገድ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚሁ ጉዳይ ሳንወጣ ከጠላት ጐራ የሚናፈሰው ውዥንበር የዕድሜ ኮታን ማመጣጠን ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የታሳሪዎች ቁጥር በወጣቶችና በመካከለኛ የዕድሜ ክልል ሰዎች ብቻ ተሞላ… ከአንጋፋዎቹ የዕድሜ ባለጠጐች፣ ከነባሮች የተያዘ የለም ለማለት ነው ስለዚህ የዕድሜ ተዋጽኦን ለማረጋገጥ ሲባል ጥፋት ያልተገኘባቸውንና ማስረጃ ያልተያዘባቸው አንጋፋ አመራሮች ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም፡፡ ይህ ሁሉ ጠፍቷቸው አይደለም የፀረ-ሙስና ትግሉን አካሄድ አቅጣጫ ለማስለወጥና የሕዝቡን ማስገንዘብና ወቅታዊ መረጃ እንዲደርሰው ማድረግ የእኛ ፈንታ ነው፡፡

ፀረ ሙስና ትግሉ ከየትም ይጀመር ከየት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ወደላይና ወደታችም ሆነ ወደ ጐን ብዙ ቅርጫፎች አሉት፡፡ መረቦች አሉት፡፡ ከውጭ ሆነው መንግሥትን ለማውረድ አጋጣሚውን ለመጠቀም ያሰፈሰፉ ጠላቶችም አሉ፡፡ ሁሉም ለየራሳቸው ዓላማ ሁኔታውን ለማራገብ ይሰራሉ፡፡ ሙስናው ራሱ ፀረ ሙሰኛውን ለመዋጋት ቆርጦ ይነሳል፡፡ ሙስናን በሚያጋልጡ እንደ ዋናው ኦዲተር ባሉ ሙስናውን ለማጥፋት በሚሰሩ የዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ስም የማጥፋት ብቻ ሳይሆን ሀሰተኛ ወንጀል በመፈብረክ ከአለቆቻቸው ጋር ለማቀያየም ይሰራል፡፡ ሙስና ራሱን ለመከላከልና ገንዘቡን ለመሰወር ሁሉንም የበቀል ዓይነት ለመተግበር ወደኋላ አይልም፡፡ አንዱ ሙሰኛ ሲነካ ሌለኛው ሙሰኛ ይደነግጣል፤ ብሩን በማጠብ ወይም ሕጋዊ ለማስመሰል ይለወጣል፤ አገር ለቆ ለመወጣትም ያደፍጣል ለዚህም ቅድመ ጥንቃቄው ሊደረግበት ይገባል፡፡ ምርመራውን በአጭር ጊዜ አጠናቅቆ ፍርድ ማስጠት መቻል አለበት፡፡

 መያዛቸው ብቻ ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ አይሆንም የእጃቸውን ማግኘታቸውን ሕዝቡ የማወቅ መብት አለው፡፡ ሙስና ወንጀል ነው ገንዘቡ ሲገኝ ደስ ሊል ይቻላል፤ ምንጩ ሲመረመርና ሲጋለጥ ግን መዘዙ ብዙ ነው፡፡ የተመዘበረው ገንዘብ በሕግ አግባብ ይመለሳል፤ የተገዛው ቤትና መሬትም ይወረሳል፤ የባንክ ሂሳብ ይታገዳል፤ በዚህም ቤተሰብ ይጐዳል፣ ይበተናል፣ ልጆች ተንደላቅቀው በተማሩበት ትምህርት ቤት ከዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር መቀጠል አይችሉም፡፡ የሙሰኛ ልጅ መባሉም ቅሌቱ ለቀረው ቤተሰብ ይከብዳል፡፡ ከዚህ ሁሉ በሥራቸው መጠን የሚከፈላቸውን ደመወዝ በአግባቡ እየተጠቀሙ ቤተሰብን ማስተዳደር ይበልጥ የማንነት ክብር፣ የቤተሰብ ክብር፣ የልጆች ክብር ከገንዘብ  ጥማትና ከሆድ በላይ ነው፡፡ ፈጣሪ ልቦና ሰጥቶ ከሙስና ይሰውረን፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥል የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን የማስጠበቅ ሂደት የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

ግርማ ለማ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።