ሰንደቅ አላማህን ጠብቅ

12 Oct 2017

 

ጥቅምት 06 ቀን 2010 .ም በብሔራዊ ደረጃ የሰንደቅ አላማን ቀን እናከብራለን፡፡ ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ አላማቸው ያላቸው ክብርና ፍቅር ልዩ ነው፡፡ ሰንደቅ አላማ የሀገር ክብር መለያ፤ የሀገር ታላቅነት መገለጫ፤የሕዝቦች የጋራና የአብሮነት ሰላም ፍቅር መቻቻል መከባበር ሕብርነት አንድነት መገለጫ ነው፡፡ሀገርንና ሰንደቅ አላማን ከሁሉም በፊት መጠበቅ በዘመናት የሚፈራረቁት ትውልዶች ሁሉ ቀዳሚ ኃላፊነት ሆኖ ኖሯል፡፡ ወደፊትም በዚሁ ይቀጥላል፡፡

የብሔራዊ ፍቅር የብሔራዊ ማንነት መገለጫ አርማም ነው ሰንደቅ አላማ፡፡ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ክብር ታላቅ መስዋእትነት በየትውልዱ ፈረቃ ተከፍሏል፡፡ ሰንደቅ አላማ የመጨረሻው የብሔራዊ መለያና መታወቂያ የሀገር ማንነት ማሳያና መገለጫ፤ ከሁሉም በላይ ከፍ ብሎ በክብር በታላቅ ወታደራዊ ስነስርአት የሚውለበለብ መለያ ነው፡፡

ድሮ በትምህርት ቤት ተማሪዎች ጠዋት ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ተሰልፈው ባንዲራው ሲሰቀል ብሔራዊ መዝሙር መዘመር ግዴታቸው የነበረ ሲሆን ማታም ከተሰቀለበት ሲወርድ በአካባቢው የሚገኝ ሰው አይንቀሳቀስም ነበር፡፡ ሰንደቅ አላማ ክብሩ ከፍ ያለና የላቀ ነው፡፡

ሰንደቅ አላማ ከሁሉም በላይ ክብር ያለው መላውን ሀገርና ሕዝብ የሚወክል በመሆኑ የሚሰጠውም ስፍራ የተለየ ነው፡፡ ኢትዮጵያውን ለሰንደቅ አላማቸው ልዩ ክብርና ፍቅር አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ካለው ልዩ ክብር የተነሳ በሰርግ ወቅት ጥቅም ላይ ይውላል። በጥልቅ የሀዘን ወቅት ታዋቂ ሰው ለሀገሩ ብዙ የለፋ ያገለገለ ጀግና ወይንም መሪ ሲሞት አስከሬኑ በባንዲራ ተሸፍኖ ነው ስነስርአቱ የሚካሄደው፡፡ ይሄ ጥንትም በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ይደረግ የነበረ ባሕል ሆኖ ለዘመናት የዘለቀ ነው፤ ዛሬም አለ፡፡ ጠብቀን ልናሳድገውም ይገባል፡፡

ሰንደቅ አላማ የሀገር መለያ የሀገር ክብር መገለጫ ነው፡፡ አትሌቶቻችን በአለም አቀፋ መድረክ ለውድድር ተሰልፈው ሲያሸንፉ በመጀመሪያ የሚያውለበልቡት የሀገራቸውን የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሀገሬ የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው፤ ሀገሬ ክብሬ ፍቅሬ ነች ነው መልእክታቸው፡፡ ሰንደቅ አላማ ልዩ ስሜትን በዜጎች ላይ የሚፈጥር በልዩ ስሜት አንሰቅስቆ የሚያስለቅስም ነው፡፡

በተለይ ይህ ስሜት ጎልቶ የሚንጸባረቀው ከሀገራቸው በስደት ወጥተው በብዙ ሺ ማይልስ ርቀት በሚኖሩት የሀገርና የወገን ፍቅር በበረታባቸው ናፍቆቱ ከአቅማቸው በላይ በሆነባቸው የዳያስፖራ ዜጎቻችን ውስጥ ነው፡፡ የሀገር ፍቅር ልዩ ስሜት በዜጎቻችን ውስጥ የገዘፈ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ነጻነትና አንድነት ለማስጠበቅ በተደረጉት ትግሎች ሁሉ ሰንደቅ አላማችን ከፊት ቀድማ ስትሰለፍ ኖራለች፡፡ ዛሬም ይኸው ነው፡፡

ዜጎች ለሀገራቸውና ለሰንደቅ አላማቸወ ክብር ታላቅ መስዋእትነትን ለመክፈል በጋለ የሀገር ፍቅር ስሜት ቃልኪዳን ይገባሉ፡፡ ቃለመሀላ ይፈጽማሉ፡፡ ለሀገር መስዋእት መሆን ከክብሮች ሁሉ የላቀው ታላቅ ክብር ነው፡፡ በየዘመኑ ሆኗል፡፡ ዛሬም ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ በአገራችን ዘንድሮ ለአስረኛ ጊዜ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ይከበራል፡፡ መሪ መልዕክቱ «ራዕይ ሰንቀናል ለላቀ ድል ተነስተናል» የሚል ነው፡፡ በመሪ መልዕክቱ መሰረት በሀገራችን ሁሉም ክልሎች በደመቀ ሁኔታ እለቱን ለማክበር ከፍተኛ ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

ሰንደቅ ዓላማችን የአንድነታችን፣ የሕብርነታችን፣ የብዙህነታችን፣ የአብሮነታችን፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር፣፣ የማንነታችን የተከበረውና በደምና አጥንት መስዋእትነት ጸንቶ የኖረው ነጻነታችን የክብርና የኩራታችን መለያ አርማችን ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነታችን ታላቅ ክብር ደምቆ የሚገለጽበት በአንድ ሰንደቅ አላማ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የሚወከልበት ነው፡፡

በአለም በየትኛውም ማእዘን የምንወከለው በሰንደቅ አላማችን ነው፡፡ በሀገራችን ላይ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ የባእዳን ወረራዎች ማጥቃት በሰነዘሩበት ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ጠላቶቻ ቸውን ለመዋጋት የሚዘምቱት ባንዲራውን ከፊት ለፊት አስቀድመው ነው፡፡ ይሄ በተለያዩ ዘመናት ተደርጎአል፡፡

አትሌቶቻችን መታወቂያቸውና መለያቸው የእነሱ ብቻ የሆነውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በአለም አቀፍ ውድድር ባሸነፉ ቁጥር ለብሰውት ሲዞሩ እኛም በቴሌቪዥን መስኮት ስናይ ሳናስበው ውስጣችን ሲደፈርስ አንዳች አይነት መግለጽ የማንችለው ልዩ ስሜት ሲወረን ሲያቁነጠንጠን እናገኘዋለን፡፡ የሀገር የባንዲራችን ጉዳይ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡

ያ ነው ሳናውቀው በደማችን ውስጥ ተሰራጭቶ ነፍስ ዘርቶ ያለውና የሚኖረው የሀገር ፍቅር ስሜት የምንለው፡፡ ብዙዎችም ስሜታቸው ደፍርሶ ያለቅሳሉ፡፡ ሀገር ማለት ሰው ነው፡፡ ሕዝብ ነው፡፡ ያደግንበት ሕብረተሰብ ባህሉ ወጉ ልምዱ እምነቱ ቋንቋው አመት በዓሉ አብሮ መብላቱ መጠጣቱ ክፉውን ደጉን በጋራና በአብሮነት ማሳለፉ የተወለድንበት ያደግንበት የልጅነት ትዝታችን ያለፈበት የቧረቅንበት ሜዳ የተራጨንበት ምንጭ ወንዙ ሜዳውና ሸንተረሩ ዘመዱ ጎረቤቱ መንደርና ቀዬው በአንድነታችን ውስጥ ያለው ፍቅር አብሮነት መከባበሩ ጋሼ እትዬ አክስቴ አጎቴ አብሮ አደጌ ወንድሜ እህቴ ጓደኛዬ የምንለው በአብሮነት ተሳስሮና ተጋምዶ የኖረውና ያለው ሁሉ በሀገር ውስጥ ይገለጻል፡፡በሰንደቅ አላማችንም ውስጥ ይጎላል፡፡

ሀገር ደግሞ በሰንደቅ አላማችን ትወከላለች፡፡ ለዚህም ነው የተለየ ክብር ያለው፡፡ ልዩ ስሜትም የሚፈጥረው፡፡ በየትኛውም ቦታ ሰንደቅ አላማችን ከፍ ብላ ስትውለበለብ የተለየ የደስታ ስሜት የሚሰማን ከእኛነታችን ጋር በጽኑ የተቆራኘ ከደም ከአጥንትና ከስጋችን ጋር አብሮ የተፈጠረና የተለሰነ የሰንደቅ አላማችን ፍቅር የሀገራችን ፍቅር የወገናችን የተንቀለቀለ በስሜታችን ውስጥ የሚነድ ፍቅር ስላለን ነው፡፡

አያቶቻችን አባቶቻችን ታላቅ የሕይወት መስዋእትነት ከፍለው በደም ዋጋ ጠላትን ሁሉ ድል አድርገው ያስረከቡንን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በላቀ ክብር ጠብቀን ለተከታዩ ትውልድ በክብር ማስከበር ይገባናል፡፡

ዛሬ ሀገራችን ከድህነት ለመውጣት ታላቅ ትግል በማድረግ ብዙ ስርነቀል ለውጦችን አስመዝ ግባለች፡፡ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በግብርናው፣ በከተሞች ልማትና መስፋፋት፣ በቤቶች ግንባታ፣ በኮንስትራክሽን፣ በመንገድ ግንባታ፣ በድልድዮችና ከፍተኛ ኃይል ማመንጨት የሚችሉ ግድቦችን በመገንባት በቅርቡም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ሀብ(ማእከል) ያደርጋታል የተባለለትን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ በተለያዩ ክልሎች በስፋት እየሰራች ትገኛለች፡፡ግብርናችን ዘመናዊ እንዲሆን በሂደትም ወደ ሜካናይዝድ እርሻ እንዲለወጥ በሂደት ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡

ለኢንዱስትሪው ግብአት የሚያቀርቡ የአግሮ ኢንዱስትሪዎችን ክልሎች የመገንባትና የማስፋፋት ስራ በማከናወን ላይ ናቸው፡፡ በዚህ ዘመን የሰንደቅ አላማችንን ክብር ከፍ አድርገን የምናውለበልበው ድህነትን ታግለን በማሸነፍ፤ ሀገራችንን በማልማትና በማሳደግ በቴክኖሎጂ እውቀት በማበልጸግ ነው፡፡

ወጣቶቻችን በሁሉም መስክ የእውቀት ጌታ ሁነው ሀገራቸውን የበለጠ እንዲያለሙ ሰንደቅ አላማቸውን የበለጠ እንዲያከብሩ እንዲያስከብሩ በማድረግ ነው፡፡ ክብር ለሰንደቅ አላማችን!

 

መሐመድ አማን

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።