አፋር ሰመራ ላይ

04 Dec 2017

 

«በሕገ መንግሥታችን የደመቀ ሕብረ ብሔረተኝነታችን ለሕዳሴአችን» በሚል መሪ ቃል ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኅዳር 29 ቀን 2010 .ም በአፋር ሰመራ ከተማ ሊከበር ዝግጅቱ ተጠናቋል። የአገራችን ህገ መንግሥት የፀደቀበት ዕለት ኅዳር 29 ቀን 1987 .ም ምክንያት በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሦስተኛው የፓርላማ ዘመን አንደኛ ዓመት የሥራ ጊዜ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ሚያዝያ 21 ቀን 1998 .ም ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት በኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ምክንያት የሆነው ሕገመንግሥት የፀደቀበት ቀን (ኅዳር 29) የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶችና ዘላቂ የልማት ሥራዎች እንዲከበር ተደርጓል።

ስያሜው «የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን» ይባል እንጂ የምናከብረው ህገ መንግሥታችን የፀደቀበት ቀን ነው። ሕገ-መንግሥት የፀደቀበት ቀን ደግሞ በማንኛውም አገር ይከበራል። በእኛም አገር መከበሩ ሕጋዊ ነው። በዚህ መነሻ ከኅዳር 29 ቀን 1999 .ም ጀምሮ በምክር ቤቱ አስተባባሪነት፤ በተለያዩ ክልሎች አስተናጋጅነት የሕዝቦች ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር በሚገልጽና ለአንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓትን ለማምጣት በሚያስችል መልኩ ይከበራል።

እስካሁን ድረስ ለ11 ጊዜያት ተከብሯል። የአሁኑ በአፋር ሰመራ በዓል ለ12ኛ ጊዜ የሚደረግ ነው። ከአፋር የመጀመሪያው የሰው ዘር መገኛ የሆነች ምድር፤ የሉሲ (ድንቅነሽ)፣ የሰላም የኢዳልቱ ካዳሙ እና የአርዲ ቅሬተ አካል የተገኘው ጥንተ ታሪካዊ አገር ነው።

አፋር ከሰው ዘር መገኛነቱ ባሻገር ድንቅና ማራኪ የተፈጥሮ ገፅታ፤ ውብ መልክዓ ምድር መሆኑን ለማረጋገጥ በኤርታ አሊ እና ዳሉል እሳተ ገሞራ የተፈጥሮ የህብረ ቀለማት ውህደትና በሚንተከተከው የእሳተ ጎሞራ ፍንጥቅጣቂ ዙሪያ ያለውን ድባብ ማየት ብቻ ይበቃል። ጨው የሚታፈስበትና የጨው አለት እየተደረመሰና እየተጠረብ በአሞሌነት የሚመረትበት አካባቢና የአፍዴራ ኃይቅ እንዲሁም የግመሎች ቅጥልጥልነት ቅፍለተ (Caravan) ያለውን ገፅታና ልዩ ትርኢት ማራኪነት በርካታ ቱሪስቶች የሚጎበኙት ቅዱስ ክልል ነው።

የአፋር ብሔራዊ ክልል በአገራችን ሰሜናዊ ምሥራቅ የሚገኝ አካባቢ ሲሆን፣ በሰሜን ምዕራብ በትግራይ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ከኦሮሚያ ክልል፣ በሰሜን ምሥራቅ ከኤርትራ መንግሥት እና በምሥራቅ ከጅቡቲ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር ይዋሰናል። የአፋር ህዝብ ቋንቋ አፋርኛ ሲሆን ከኩሽ የቋንቋ ቤተሰብ ይመደባል። ህዝቡ በአብዛኛው አርብቶአደር ሲሆን፣ የተወሰኑ በከፊል አርብቶ አደርና በማዕድን ጨው ማምረት ዘርፍ የተሰማሩ አሉ። የአፋር ህዝብ ሙሉ በሙሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ሲሆን የሌላውን ሃይማኖትና እምነት የሚያከብር፤ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ጋር በመተባበርና በመቻቻል ለረጅም ዘመናት አብሮ የኖረ ህዝብ ነው። ለአገራችን ሰንደቅ ዓላማ ጽኑ ልባዊ ፍቅር ያለው ህዝብ ነው። የኢትዮጵያን ባንዲራ እንኳንስ የአፋር ህዝብ ቀርቶ የአፋር ግመሎችም ያውቃሉ።

የአፋር ክልልና ህዝብ የረጅም ዘመናት ታሪክ ባለቤት፣ የሰው ዘር መገኛ በመሆኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትታወቅ አድርጓታል። በዚህ ረገድም በዩኔስኮ ከተመዘገቡት ስምንት የአገራችን ቅርሶች መካከል ዋናው የአፋር ክልል የታችኛው አዋሽ ሸለቆ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረችው ሉሲን (ድንቅነሽ) ጨምሮ ሰላም፣ ኢዳልቱ፣ ካዳሙ እንዲሁም 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዓመታትን ያስቆጠረውና በቅርቡ የተገኘው አርዲ ቅሬተ አካል የአገራችንን የስልጣኔ ምንጭነት በዓለም ዙሪያ ከሚያስተጋቡ የሰው ዘር ቅሪተ አካላት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

የአፋር ሕዝብ ታሪክ እንደሚያስረዳው ክልሉ ከኢትዮጵያ በድንበር አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ከውጭ ለሚመጡ ጥቃቶችና ወረራዎች ባለመንበርከክ መክቶ በመከላከል የኢትዮጵያ አጥር በመሆኑ ለሀገሩ አንድነትና ነፃነት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ ህዝብ መሆኑ ይታወቃል። የአፋር ህዝብ በህብረት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ባህላዊ አስተዳደርና ማህበራዊ መስተጋብር ያለው ሲሆን በኢትዮጵያዊነቱ ፀንቶ የኖረ ለሀገሩና ለሰንደቅ ዓላማው የቆመ ህዝብ ነው። እንደማንኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የአፋር ህዝብ ለብዙ ዘመናት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን ተነጥቆ በፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ተረግጦ ሲማቅቅ የኖረ ህዝብ መሆኑ ይታወቃል። በጊዜው የነበረውን የጭቆና እና የአፈና አገዛዝ ለመገርሰስ ከሌላው ህዝብ ጋር በመታገል ዛሬ ላገኘነው ሕገመንግሥትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት መስፈን የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አፋር እንደ አዋሽ ያሉ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች እና በክረምት ጊዜ የሚሞሉ ውሃዎች የሚገኙበት ሰፊ የሆነው የአፍዴራ ኃይቅና ሌሎች የውሃ ቋቶች የሚገኙበት በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ፤ ሰፊ የሆነው የአፍዴራ ኃይቅና ሌሎች የውሃ ቋቶች የሚገኙበት በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ ሜዳማ፤ ለእርሻ አመቺ የሆነ መሬት ያለው በዳሉል አና በኤርታአሌ አካባቢ ካለው ድንቅ የተፈጥሮ ገጽታ ጋር የፍል ውሃና የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በመኖሩ በቱሪስት መዳረሻነት ተመራጭ አካባቢ ነው።

ክልሉ በ5 ዞኖች እና አርጐባ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በ32 ልዩ ወረዳዎችና በ370 ቀበሌዎች የተዋቀረ ነው። የክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ ሲሆን፣ ሌሎች ከተሞችም በተለይም በሎጊያ፣ አሳኢይታ፣ ዱብቲ፣ ሚሌ፣ አዳይቱ፣ ገዳማይቱ፣ አዋሽ አርባ፣ አዋሽ ሰባት እና ሌሎች ከተሞች ዛሬ በተሻለ ዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። አሁን ደግሞ ከ12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ጋር ተያይዞ በበዓሉ ምክንያት ከተገነቡት የመሰረተ ልማት ሥራዎች የክልሉን አቅምና ገጽታ በመለወጥ ረገድ ያላቸው አስተዋጽኦ ከተሞቹን የበለጠ ያጠናክራቸዋል። በተለይ ደግሞ በሰመራና ሎጊያ ከተሞች ያለው የልማት እንቅስቃሴ ከተማዎቹን ይበልጥ ዘመናዊ ያደርጋቸዋል ።

በሰመራ የተገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ የሚገኝበት ደረጃ ከአዲስ አበባው ቦሌ ቀጥሎ ትልቁ ሲሆን ዘመናዊ ስታዲየም እና ልዩ ልዩ ሆቴሎች በዘመናዊ መልክ መገንባታቸው ወደ ክልሉ ለሚመጡ ቱሪስቶችና የአገር ውስጥ እንግዶች የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጥሯል። ወደ አፋር የሚሄድ ሰው በቆይታው ሁለት ዓይነት የመኝታ አገልግሎት ያገኛል። መኝታ ክፍል መከራየት ወይም ውጭ በተዘረጋ የጠፍር (የሽቦ) አልጋ በአጐበር ጥላ ስር ማደር ይችላል። አሁን አየሩ ቀዝቀዝ ያለና ደህና የሚባል ነው። ከሰኔ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ግን ሞቃታማ የአየር ጊዜ ቢሆንም አፋር ዓመቱን ሙሉ የተመቸ አካባቢ መሆኑ ተመራጭ እየሆነ ይገኛል።

በአፋር ሰመራ የሚከበረው 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሌሎች ክፍሎች እንደተከበሩት በዓላት ሁሉ በህዝቦች መከባበርና መቻቻል የሚጠናከርባት፤ በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለህዳሴያችን ስኬት የበኩሉን አሻራ ጥሎ የሚያልፍ፤ በሰላም ተጀምሮ በሰላም የሚጠናቀቅ እንደሚሆን እናምናለን። ከሰመራው 12ኛ በዓል በቀጣይም በመጪዎቹ ዓመታት ይህ በዓል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እምነታችን ጽኑ ነው። የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ማለት ሕገ መንግሥት የፀደቀበት ቀን በመሆኑ በዓሉ ከመከበር የሚቋረጥበት ምክንያት መኖር የለበትም። የበዓሉ መከበር ይቁም ወይም ይቀጥል የሚል ጥርጣሬ አያስፈልግም። መቀጠል አለበት። የሕገ መንግሥታችንን ፋይዳ ወደ ውስጣችን ለማስገባት የፌዴራሊዝም ሥርዓታችንን አጠናክረን ለመቀጠል፤ የሕዝቦችን የእርስ በርስ መተዋወቅና ትስስር ለማስቀጠል፤ በዓሉ የማይተካ የራሱ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን እናምናለን። ምናልባት በበዓሉ ምክንያት በየዓመቱ የሚወጣው ወጪ መብዛት« ቢቀርስየሚል ጥያቄ ይቀሰቅስ ይሆናል። ይህ ግን ሰበብ እንጂ ምክንያት ሊሆን አይችልም። መፍትሔውም በዓሉን ማስቀረት ሳይሆን የፕሮግራሙን በጀት መቀነስና በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ነው። ከልክ በላይ የሆኑ ለታይታ ብቻ ለአንድ ጊዜ የወሬ ፍጆታ የሚውሉ የግንባታ ሥራዎችን ፈር ማስያዝ ሊያስፈልግ ይችላል። አውሮፕላን ማረፊያ ሊያስፈልግ ይችላል። ለቱሪስት ለእንግዶች ማረፊያ የሚሆኑ ሆቴሎችን መገንባት ሊያስፈልግ ይችላል። ስታዲየም መገንባትም ሊያስፈልግ ይችላል። ይሁን እንጂ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግዙፍ ሆቴልና ግዙፍ ስታዲየም « ይሁን አይሁን» በሚለው ላይ ረጋ ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ለወደፊቱ ትውልድ እያሰብን አሁን ያለውን ትውልድ ሃብት እንዳናባክን ወይም ለአሁኑ ትውልድ በቻ እያሰብን የወደፊቱን ትውልድ ራዕይ እንዳናጨልም፤ ከግብር ከፋዩ ሕዝብ የተገኘውን ገቢ በተገቢው መጠን አደላድሎ መጠቀም ከአመራሩ ይጠበቃል።

12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚከበርባት አፋር በርካታ አስደሳች ወግ፣ ባህልና ማህበራዊ መስተጋብር ያለባት ታሪካዊ ምድር ናት። ለማጠቃለል ያህል ባለፉት ዓመታት የተከበሩት በዓላት የትና መቼ እንደተከበሩ እናስታውሳችሁ።

አንደኛውና የመጀመሪያው በዓል የተከበረው በ1999 .ም በአዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል

ሁለተኛው በ2000 .ም ደቡብ ብሄር በሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አስተናጋጅነት ሀዋሳ ከተማ

ሦስተኛው በ2001 .ም በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ

አራተኛው በ2002 .ም በአምስቱ አጐራባች ክልሎች (አፋር፣ድሬዳዋ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ሐረሪ) አዘጋጅነት በድሬዳዋ

አምስተኛው በ2003 .ም በአዲስ አበባ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ

ስድስተኛው በ2004 .ም ትግራይ-መቀሌ

ሰባተኛው- 2005 .ም አማራ- ባህርዳር

ስምንተኛው በ2006 .ም ሶማሌ- ጅግጅጋ

ዘጠነኛው በ2007 .ም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ -አሶሳ

አሥረኛው በ2008 .ም ጋምቤላ

አሥራ አንደኛው በ2009 .ም ሐረር

መልካም ቀን ይሁንልን!

 

 

ግርማ ለማ

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።