ድል ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን

07 Dec 2017

 

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ነገ ኅዳር 29 ቀን2010.ም በአፋር ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ ሰመራ ይከበራል፡፡ እንደተለመደው በመላ ኢትዮጵያ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሞቃታማዋ ሰመራ ከተማ በተዋቡ ባሕላዊ ልብሶቻቸው ደምቀው አፋርን ያሸበርቋታል፡፡ እስከዛሬ በተለያዩ ክልሎች በተከበረው በዓል በየፈረቃ በመዘዋወር ሲሸጋገር ቆይቶ ተረኛዋ የሰመራ ከተማ ዘንድሮ «ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼና እህቶቼ እንኳን ደህና መጣችሁ» በማለት ሁለት እጆችዋን ዘርግታ በመቀበል ላይ ትገኛለች፡፡

ከመላው ኢትዮጵያ ማለትም ከሰሜን፣ ደቡብ፣ ምስራቅና ምዕራብ ወደ አፋር ክልል ሰመራ በማቅናትም በሚያከብሩት በዓል ቃላቸውንም ያድሳሉ፡፡ «የተጀመረውን ሀገራዊ ልማትና እድገት እናስቀጥላለን፤ በጽናት ቆመን ሀገራዊ ሰላማችንን እናስጠብቃለን፤ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ከጸረ ሰላም ኃይሎች ነቅተን እንጠብቃለን፤ ጎሳ ከጎሳ ዘር ከዘር እየለዩ ሊያባሉን ሊያናክሱን የሚክለፈለፉትን የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማናጋት የሚራወጡትን በውጭ ኃይሎች የሚረዱ ቡድኖችን በጽናት ታግለን እናሸንፋለን» የሚሉት ሕዝባዊ ድምጾችም በሰመራ አየር ላይ ይናኛሉ፡፡

በአፋርዋ የሰመራ ከተማ ድል ለኢትዮጵያ የሚለው ሕዝባዊ አስገምጋሚ ድምጽ ደግሞ ደጋግሞ ከፍ ብሎ ይደመጣል፡፡ ከአፋሩ የነአሊሚራህ ምድር የሚወነጨፈው ምትሀታዊ ድምጽ እስከ ቀይ ባሕር ድረስ ዘልቆ ይሰማል፡፡ «እንኳን እኛ ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቁታል» የሚሉት አፋሮች በኢትዮጵያ ዊነታቸው የሚኮሩ በምንም መልኩ የማይደራደሩ መኩሪያ ወገኖቻችን ናቸው፡፡

«የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ሀገራችን የሞትና የሽረት ጉዳይ የሕልውናም መሰረት ስለሆነ ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈን አንሰጥም፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ባለቤቶች፣ ሰሪዎችም ሆንን አሰሪዎች የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ስለሆንን በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ለሚነሳ ማንኛውም ጥያቄ ወሳኝ ባለቤት እኛ ነን» የሚሉ እጅግ ወሳኝ ሀገራዊ ድምጾች በሰመራው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ ያስገመግሙበታል፡፡ ይሄን ሕዝባዊ ኃያል ድምጽ ለኢትዮጵያ መቼም የማይተኙት ጠላቶቻችንም በቅርብም በርቀትም የሚገኙት በሚገባ ይሰሙታል ብለን እናምናለን፡፡

አዎን ጥንትም ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላት የጠበቋት የተከላከሏት፣ በአንድነት ቆመው፣ በአንድነት መስዋዕትነት ከፍለው እንዲሁም በአንድ ጉድጓድ ወድቀው ያስከበሯት ልጆችዋ ብሔር ብሔረሰቦችዋ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና ሕብረት በሰፊና በማይናወጥ መሰረት ላይ የተገነባ በመሆኑ አይናድም፤ ጊዜ አይሽረውም፡፡ሊከፋፍሏቸውና እርስ በእርስ ሊያጋጯቸው ለሚሞክሩትም የመግቢያ ቀዳዳ የላቸውም፡፡

ይልቁንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ ይበልጥ አንድነታቸውን አጽንተው፣ ወገባቸውን አጥብቀው ሀገራቸውን ከድሕነት ለማውጣትና በልማት ለማሳደግ የሚተጉበት ወቅት ነው፡፡ ሀገራዊ ሰላማቸውን በሁሉም አቅጣጫ ዘብ ቆመው በጽናት ይጠብቃሉ፡፡

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እናት ነች፡፡ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባሕሎችና ኃይማኖቶች ያሉባት፣ በተፈጥሮ ውበት የታደለች አቻም የሌላት የብዙ ወንዞችና ኃይቆች፣ የብርቅዬ ዱር አራዊቶችና የቤት እንስሳት መገኛ፣ የተፈጥሮ አየር ንብረትዋ ለሁሉም ተስማሚ የሆነች ታላቅ ሀገር ነች፡፡

በኃይማኖቶች መካከል ሰፊ መቻቻልና መከባበር ያለባት፣ ልዩነቶችን አቻችላ የያዘች፣ ከ80 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን አቅፋ ለዘመናት የዘለቀች፣ ዛሬም እኩልነታቸውን አረጋግጣ የጋራ እናት ሀገራቸውን በጸና አንድነት ተሳስበውና ተከባብረው የሚጠብቁባት እንዲሁም በፍቅር የሚኖሩባት ሀገር ነች ኢትዮጵያ፡፡ የፌደራሊዝሙ ስርዓት በፈጠረው እድል ሀገራችን እመርታዊ የኢኮኖሚ እድገት በሁሉም መስክ አስመዝግባለች፡፡ ትናንት ያልነበሩ ዛሬ ግን በከፍተኛ ትግል የሀገራችንን ስምና ታሪክ የለወጡ ታላላቅ የኢኮኖሚ እድገት ስኬቶችን መጨበጥ ተችሏል፡፡

በመሰረተ ልማት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በከተሞችና መንገድ መስፋፋት፣ በግድብ ግንባታ፣ በኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች መስፋፋትና በሌሎችም በኩል ታላላቅ የተባሉ እድገቶችና ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከድሕነት ለመውጣት ባደረገችው ከባድ ትግል የሚታዩና የሚጨበጡ ለውጦችን አስመዝግባለች፡፡

ይህ ድልና ውጤት የብሔር፣ ብሔረሰቦቿና ህዝቦቿ ትግል ድልና ውጤት ነው፡፡ በመሰረቱ ሀገር የምትለማው በስሯ የሚገኙ ክልሎች ሲለሙና ሲያድጉ ነው፡፡ በግብርናውና በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመዘገበው ስኬት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትግላቸውን በሥራ በመለወጥ አዲስ ሀገራዊ ታሪክ ለማስመዝገብ ተግተው ይሰራሉ፡፡

በየዓመቱ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ሲከበር ሕዝቦች የጋራ የሆነችውን ሀገራቸውን የሚጠብቁበት፣ የሚያለሙበት፣ የበለጠም አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት እንዲሁም ሀገራዊ ሰላማቸውንም ለማጎልበት ጸንተው መቆማቸውን ቃል በመግባት የሚያረጋግጡበት ነው የሚሆነው፡፡

በውጭው ዓለም ከእኛም በላይ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ብሔር ብሔረሰቦች ያሏቸው ሀገራት አሉ፡፡ ሰላማቸውን፣ ሀገራቸውን፣ ልማታቸውን እንዲሁም እድገታቸውን ያለልዩነትና ያለግጭት ጠብቀው ሀገራቸው ታላቅ እንድትሆን ይሰራሉ፡፡ ከድሕነት ለመውጣት ያደረጉት ትግልም ተሳክቶላቸው ታላቅ ሀገርና ታላቅ ሕዝብ ለመሆን በቅተዋል፡፡ እኛም ልንከተለው የሚገባን መንገድ ይሄንኑ አይነት ነው መሆን ይኖርበታል፡፡

የእርስ በእርስ ብጥብጥና ግጭት ሀገራትን ሲያፈራርስ እንጂ ሲያለማና ሲያሳድግ አላየንም፡፡ ይሄንን አላማ የሚያራምዱትን እኩይ ኃይሎች መንጥሮ በማውጣት ለሀገራዊ ሰላም መቆም እና የሀገርን ልማትና እድገት መጠበቅ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡ብዝሐነት ውበት ከመሆኑም በተጨሪ መከበር የሚገባውና የበለጠ መተሳሰርና መደማመጥን የሚፈጥር ጉልበትም ውበትም ነው፡፡

በአንድ ሀገር ላይ የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረ ሰቦችና ህዝቦች መኖራቸው የብዝሐነት መገለጫ ሲሆን፣ የእኩልነት መብታቸውን፣ ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚነታቸውን በእኩልነት ማረጋገጥና ነጻነታቸውን ማክበር የበለጠ ሀገራቸውን በጋራ ቆመው እንዲያገለግሉ፣ በፍቅርም እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል፡፡ እየተሰራ ያለውም በዚህ መልኩ ነው፡፡

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት በእኩልነት ካልተከበረ በሀገራት ውስጥ ለሚከሰቱት መሰረታዊ ችግሮች ሁሉ ዋነኛው መነሻ ጉዳይ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን መብት ያረጋገጠ በመሆኑ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አብሮነትን፣ መቀራረብን፣ መተዋወቅን አሳድጓል፡፡ በዓሉ ሲከበር በአንድ አካባቢ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች መጥተው በጋራ ስለሚያሳልፉ የበለጠ መቀራረብ፣ መግባባት እንዲሁም መተዋወቅ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ የበለጠም በጋራና በእኩልነት መንፈስ እንዲቆሙ ያስቻለም ነው፡፡

ተዘንግተው የነበሩ ብሔረሰቦች ከስልጣኔውም ከሀገራዊ እድገቱም ተካፋይ የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም ልጆቻቸውን በቋንቋቸው ከማስተማር ባለፈ በቋንቋቸው መዳኘት እስከ መቻል ተችሏል። በክልሎች አስተዳደር ውስጥ በየራሳቸው ውክልና መሰረት ድምጻቸው የሚሰማበት፣ ለመብታቸው የሚከራከሩበት መድረክም ተጎናጽፈዋል፡፡ ይኸው መብታቸው በጊዜ ሂደት ውስጥ እየጎለበተና እየጠነከረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በሩቅ አካባቢ በሚኖሩት ብሔረሰቦች ዘንድ መሰረተ ልማትን የማስፋፋት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፊ ሥራዎችን አጠናክሮ መስራት ይጠይቃል፡፡

የከብቶቻቸውን ጭራ ተከትለው ውሃና መኖ በሚያገኙበት አካባቢ ኑሯቸውን በመንከራተት ሲገፉ የነበሩትን በሰፈራ ተሰባስበው እንዲኖሩና በዚህም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡

አርብቶ አደሮች እርሻን እንዲለምዱ፣ ለቤተሰባቸው ከሚሆነውም ፍጆታ በላይ ያለውን ለገበያ አቅርበው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ልጆቻቸው የትምሕርት እድል በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራዎች ዛሬም በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡

ይህም የእኩልነት መብታቸውን ከማረጋገጥ፣ የዜግነት መብታቸውን አክብሮ ከማስከበርም የመነጨ ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የእኩልነት መብት የተከበረበት፣ ብዝሀነት ውበት እንጂ የማይለያይ መሆኑ የሚወደስበት፣ አብሮነት የሚጎለብትበት፣ ሁሉም የጋራ ሀገሩን ሰላምና ደሕንነት እንዲሁም ልማትና ሀገራዊ እድገቱን ለማስቀጠልና ለመጠበቅ የበለጠ ቃል የሚገባበት ቀንም ነው፡፡ ድል ለብሔር ብሔረሰቦች ቀን!

 

መሐመድ አማን

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።