እናንተም ታደሱ፤ እኛም እንታደስ!

10 Jan 2018

ኢህአዴግ ለ17 ቀናት በስብሰባ ላይ በነበረበት ወቅት በማህበራዊ ሚዲያው ብዙ ግምቶች ነበሩ፡፡ ከስብሰባው በኋላ ‹‹ምን ይባል ይሆን?›› ብለው በጉጉት የጠበቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ ስብሰባው ተጠናቆ መግለጫ ተሰጠ፡፡ ከመግለጫው በኋላ ደግሞ ‹‹ምንም አዲስ ነገር የለውም›› የሚሉም አልጠፉም፡፡ ለመሆኑ አዲስ ነገር ምን ቢኖር ነበር? በመግለጫው ላይ አንድ ትልቅ ነገር አለ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ እስካሁን ለተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ኢህአዴግ ‹‹ይቅርታ!›› ጠይቋል፡፡ በፖለቲካም፣ በባህልም፣ በሃይማኖትም ብንሄድ ከይቅርታ በላይ ምንም የለም፡፡ ዋናው ነገር ወደፊት እንዴት ይሁን? የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ በጥልቅ የታደሰውን ተግባር ላይ ማዋል አለበት፡፡
የአገሪቱ ሁኔታ ግን የመንግስት ኃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በጥልቅ ልንታደስ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች በውጭ አገር ሆነው ‹‹ለአገር ተቆርቋሪ ነን›› የሚሉ አክቲቪስቶች ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የእነርሱ አጀንዳ አስፈጻሚ ሆነናል፡፡ አሁን ባለው የአገሪቱ ሁኔታ እኛም እነርሱም ጥልቅ ተሃድሶ የምናደርግበት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እነርሱ መለወጥ ካልቻሉ የእኛ መለወጥ ብቻ ለውጥ ያመጣል፡፡ አሁን መታደስ ያስፈለገን እኛ ነን፡፡ አንድ ‹‹የአገር ተቆርቋሪ ነኝ ባይ ›› አገር ሲያፈርስ አብረን እያፋረስነው ከሆነ መቼም ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ አሁን እኮ የሚቀለድበት ጊዜ አይደለም፡፡
ማንም በአገር ሙድ የሚይዝበት (የሚቀልድበት) ሁኔታ አይደለም፡፡ ይሄ በውጭ ሆኖ ‹‹በለው! ውቃው! ደብልቀው!›› የሚል አክቲቪስት ግን በአገር እየቀለደ ነው፡፡ እሱ አንተን አያይዞ ጭፈራ ቤት ‹‹አሸሸ ገዳሜ!›› ሲል ያድራል፡፡ ጋንጃና ሺሻውን እየማገ አገር ላይ ሙድ ይይዛል፡፡ በእነዚህ ‹‹አክቲቪስት›› ተብዬዎች የተጭበረበርን ይመስለኛል፡፡ የእነርሱ ዓላማ ኢህአዴግን ከሥልጣን ማውረድ ሳይሆን የዚህችን አገር ልማትና እድገት ከማይፈልጉ አካላት ጋር እየተወዳጁ አገር ማፍረስ ነው፡፡ የሚፈሰው እኮ የሰው ልጅ ደም ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ‹‹ኢህአዴግን በምን ትቃወሙታላችሁ?›› ቢባሉ ‹‹በብሄር ስለከፋፈለን›› ይላሉ፡፡ ይህን እያሉ ግን እያደረጉ ያሉት ‹‹እገሌ ብሄርን ውደድ፤ እገሌ ብሄርን አጥፋ›› ነው፡፡ እንዲህ ነው እንዴ ታዲያ የአገር ተቆርቋሪነት? እኛ እነርሱን መከተላችን ደግሞ ያሰቡት እንዲሳካላቸው አድርጓል፡፡ እነዚህን ሰዎች ዓላማቸውን እያሳካንላቸው ነው፡፡ መጀመሪያ ከመሬት ተነስተው ‹‹አምቦ ላይ ምድር ቀውጢ ሆናለች›› ይላሉ፡፡ በነጋታው ምድር ቀውጢ ይሆናል፡፡ ‹‹ይህን ያህል የአማራ ልጆች ተገደሉ፣ይህን ያህል የኦሮሞ ልጆች ተገደሉ›› ይላሉ፡፡ በሁለተኛውና ሦስተኛው ቀን እነርሱ ካሟረቱት በላይ የሰው ሕይወት ይጠፋል፡፡ ያንን ጥፋት ያደረሰው እዚሁ ያለ ሰው ነው፡፡ ያጠፋው የወገኑን ሕይወት ነው፤ ያወደመው የወገኑን ንብረት ነው፡፡ የገደልነው እኛ የሞትነውም እኛ ይሉሃል ይሄ ነው።
እዚህ ክልል ‹‹የመሰረተ ልማት ችግር አለ›› ይባላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያለውን ልማት አውድሙ ሲሉ ያዛሉ፤ ድብቁ አጀንዳቸው ያልገባቸው አፍላ ወጣቶቻችንም የታዘዙትን ያደርጋሉ። ይሄ ታዲያ በአገር መጫወት አይደለም? ወገኔ አትጭበርበር! ይሄ በውጭ ሆኖ ‹‹በዚህ ውጣ፣ በዚህ ውረድ፣ እገሌን አጥፋ…›› የሚልህ ከነቤተሰቦቹ አውሮፓና አሜሪካ ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ የአንተ ወገን ደሙን ሲረጭ እሱ ውስኪውን ነው የሚረጭ፡፡ የአንተ ወገን በሀዘን ሲያለቅስ እሱ ዳንኪራውን ነው የሚጨፍር፡፡ ፌስቡክ ላይ ሻማ እያቀለጠ ፕሮፋይሉን ጥቁር በጥቁር ቢያደርግ እውነት እንዳይመስልህ፤ እዚህ ያለው ግርግር ጭሱም አይነካው፡፡ አገሪቱን ትርምስ ውስጥ የከተታት፣ ዩኒቨርሲቲዎችን እስከመዘጋት ያደረሳቸው ከውጭ ሆነው አክራሪ ብሄርተኝነትን የሚነዙ ሰዎች ናቸው፡፡ እሱ ከውጭ ሆኖ በፌስቡክ ‹‹የእገሌን ብሄር አስወጡ›› ይላል፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ እነርሱን ሰምቶ በወገኑ ላይ ድንጋይ የሚወረውረው አሁን አሁን መብዛቱ ነው፡፡ አሁን ያለው የተማሪዎች ጥያቄ እኮ የትምህርት ጥራት ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የብሄር እየሆነ ነው፡፡ እያሉ ያሉት ‹‹የአማራ ተማሪ ይውጣ፣ የትግራይ ተማሪ ይውጣ፣ የሶማሌ ተማሪ ይውጣ…›› ነው፡፡ እንዲህ ነው እንዴ ታዲያ የአገር ተረካቢ? አሁን መንቃት ያለበት ህዝብ ነው፡፡ ህዝብ አንድ ከሆነ ነው መንግስትንም ማስተካከል የሚቻለው፡፡ መንግስት መታደስ ባይችል እንኳን ህዝብ ከታደሰ የግድ መንግስትን ማንቃት ይችላል፡፡ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ህዝብ ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ ከየት መጥታ የት እንደደረሰች ማጤን ግድ ይላል፡፡ የአገሪቱ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም፡፡ እስከ መቼ ነው የበለጸጉ አገራት መሳለቂያ የምትሆነው? አንድ ነገር ልብ እንበል! እነዚህ ‹‹በለው! አጥፋው፣ አቃጥለው!..›› የሚሉ ሰዎች ዓላማ ምንድነው? እሺ ሥልጣን መያዝ ነው እንበል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያለ መሰረተ ልማት ከወደመ፣ የሰው ልጅ ሕይወት ከጠፋ ምን አይነት አገር ነው የሚያስተዳድሩት? አገሪቱ እንደገና ከዜሮ ልትጀምር ማለት እኮ ነው፡፡ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዓለም አገራት በቴክኖሎጂ ዕድገት በሚወዳደሩበት ጊዜ እኛ ደግሞ ጭራሽ የነበሩትን ማውደማችን እንዴት መሳለቂያ አያደርገንም ታዲያ? ሕዝብ የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ለይቶ ማወቅ አለበት እንጂ በማንም ግፊት የሚነዳ ከሆነ የራሱን ንብረት ራሱ እያወደመ፣ የራሱን ወገን ራሱ እያጠፋ ነው ማለት ነው፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ የነገ የአገር ተረካቢ ናቸው የሚባሉትን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ልምድ እያበላሸን ነው፡፡ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ አገሩን ማወቅ የሚጀምረው ከዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ አንድ የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰደ ተማሪ በጣም የሚያጓጓው ነገር ቢኖር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብቶ ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ›› የምትባለዋን ማየት ነው፡፡ ከእሱ በፊት የነበሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሚነግሩት ሁሉ ይቀናል፡፡ ምክንያቱም የሚነግሩት ከፍተኛ ፍቅርና መነፋፈቅ እንዳለ ነው፡፡ አሁን ግን ዘረኝነትን በሚነዙ ሰዎች ይህ እየተሸረሸረ ነው፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ማለት ብዙ ነገር የሚያውቅ ነው፡፡ እንዴት በማንም አሉቧልታ ከወንድሙ ጋር ድንጋይ ይወራወራል?
ለመሆኑ ግን መንግስትስ ወጣቶች አገራቸውን እንዲያውቁ የሚያስችል ምን ሥራ ሰርቷል? ወጣቶችን በጋራ ጉዳይ ላይ የሚያወያዩ መድረኮች ነበሩ ወይ? በሥርዓተ ትምህርት ላይም ይሁን በመልካም አስተዳደር ላይ ከወጣቶች ጋር በቅርበት ተሰርቷል? የሚሉት ጥያቄዎች መንግስት ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ናቸው፡፡ በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በጥሩ ስነ ምግባር የታነፀ ወጣት እንዲፈጠር የሚያስችል ሥራ መሰራት አለበት፡፡ በተለያዩ ሱሶች የተጠመደ ተማሪ ማፍራት የለብንም፡፡ መጠጥ ቤቶችና የጫት መቃሚያ ቤቶች ከዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ምን ያህል የራቁ ናቸው? ለአገሪቱ ሰላምና ብልጽግና መሥራት የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ ከአመራሮቹ መታደስ ጋር ህዝብም መታደስ አለበት፡፡ በተለይም ሕዝቡ በውጭ ባሉት አካላት መነዳት የለበትም፡፡ እኛ ከታደስን እነርሱንም ልክ ማስገባት እንችላለን፡፡ ስለዚህም መታደሱ የሁላችንም መሆን አለበት፡፡

ዋለልኝ አየለ 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።