ሆድ ለባሰው...

11 Feb 2018

ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ በህይወት ዑደት ውስጥ ሁሉ የሰው ልጅ ሆድ ሲብሰው ኖሯል። በተፈጥሮ ጥቃት ሲደርስበት፣ በኃይለኞች ወረራ ሲፈፀምበት፣ በራሱ አገር መሪዎችና የአስተዳደር ስርዓቶች በደል ሲመጣበት ወይም የመጣበት መስሎ ሲሰማው ሆድ ይብሰዋል። ሆድ የባሰውን ሰው መነካካት አይገባም። ፋታ መስጠት ያስፈልጋል። ሆድ ለባሰው ሰው ማጭድ ካዋሱት ብሶት ይገነፍልና ወደ ማህበራዊ ሁከት አለያም በአግባቡ ከተመራ ወደ አብዮት ይቀየራል።
ህዝብ ሆድ የሚብሰው በበርካታ የተለያዩ ምክንያቶች ነው። ውሃ ሲዘገይ (በወረፋ ሲሆን)፣ መብራት ሲቋረጥ፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም ሲዳከም፣ የእርስ በርስ ግጭት ሲበረክት፣ ሰላም ሲጠፋ፣ ሥራ ሲጠፋ... ዜጋው በመንግሥቱ ላይ ሆድ ይብሰዋል። ዝም ማለት አይችልም። በዚህ ላይ መንግሥት ሞጋችና ጠያቂ ትውልድ ፈጥሯል። ህዝቡ ይሞግታል፣ ይጠይቃል፤ እስከዚህ ድረስ ጥሩ ነበር። ነገር ግን መላሽ (ምላሽ ሰጪ) አመራር አልተፈጠረም። መላሽና ምላሽ ሳይኖር ጠያቂና ተጠያቂው በዛ። ጥያቄና መልስ አልተመጣጠኑም። «አዛምድ» በሚለው የጥያቄ ዘርፍ ውስጥ እንኳ ማዛመድ አልተቻለም።
በመንግሥት ላይ የሚቀርብ ብሶት ከህዝብ ህዝብ ከሀገር ሀገር ይለያያል። እኛ ሀገር ለምሳሌ ውሃ ከፍተኛው የብሶት መሠረት ነው። ህዝቡ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በተለይ ሚዲያ የማግኘት ዕድሉ ካለው መተንፈስ የሚጀምረው ከውሃ ብሶት ነው። ውሃ 'ኮ አለ። ምናልባት በሳምንት ወር ተራ ገብቶ ሊሆን ይችላል እንጂ ውሃ አለን። ወር ከወር ውሃ የማይቋረጥባቸው አካባቢዎችም አሉን። ውሃ ጠፋ ሲባል እንኳ ማዕከላዊ በሆኑ አማካይ ቦታዎች በተተከሉ ሮቶዎች አማካይነት ይከፋፈላል።
በውሃ ረገድ ችግሮች ቢኖሩብንም ከተሞቻችን ደህና ናቸው። በሌሎች አገራት ከተሞች ውሃ ጭርሱን የሌለበት ሁኔታ ነው ያለው። ውሃ ቆጥቡ ለማለት እንኳ አልተመቸም። የት ያለውን ውሃ ይቆጥቡት? ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካዋን ኬፕታውን ከተማን የውሃ ችግር ጉዳይ ሳትሰሙ አልቀራችሁም። የከተማዪቱ ህዝቦች የእስከአሁን የውሃ መቁነን (አላዋንስ) በቀን ለእያንዳንዱ ሰው 87 ሊትር ነበር። አሁን ከጥር 24/2010 ዓ.ም (ፌብርዋሪ1/2018) ጀምሮ የእያንዳንዱ ሰው የውሃ ተጠቃሚነት ድርሻ ለእያንዳንዱ ሰው በቀን 50 ሊትር ብቻ ሆኗል።
በዚህ ብቻ ሳይወሰን ከሚያዝያ 13/2010 ዓ.ም (አፕሪል 21/2018) ጀምሮ «የቧንቧ ውሃ የሌለበት ቀን» (Day zero) መሆኑ ታውጇል። ኬፕታውን ከሚያዝያ 13/2010 ዓ.ም ጀምሮ የቧንቧ ውሃ የሚባል ነገር አይኖራትም። በአካባቢው ያለው ድርቅ ከፍተኛ በመሆኑ ከተማዪቱን በውሃ እጥረት ከዓለማችን ተቀዳሚ ከተማ አድርጓታል። ያቺን የመሰለች ንፁሕና ውብ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ዛሬ በውሃ እጥረት ጐሮሮዋ ደርቋል። የከተማዪቱ ከንቲባ ወይዘሮ ፓትሪሲያ ደሊሌ ምርር ብሏቸው ሲናገሩ «ከዚህ በኋላ ውሃ ቆጥቡ እያልን ህዝቡን አንጠይቅም። ያለብን ኃላፊነት ህዝቡን በማስገደድ ወደ ቁጠባ እንዲገባ ማድረግ ብቻ ነው። 60በመቶ የከተማዪቱ ነዋሪዎች በቀን ከ87 ሊትር በላይ ውሃ ሲጠቀሙ ነበር። ገላ ለመታጠብ (ሻወር) በደቂቃ 15 ሊትር ይፈጃል።»
(አምስት ደቂቃ ብትታጠብ 75 ሊትር መሆኑ ነው) ይሄ አይቻልም። የነዋሪው የቀን የውሃ ራሺን ከ50 ሊትር በታች እንዲሆን ይደረጋል። የግድቦች ውሃ 13ነጥብ5በመቶ ላይ ይደርሳል። የለም ማለት ይችላል። 70በመቶ ውሃ ለቤት ውስጥ አገልግለሎት የሚውል ነው። ለመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ማውረጃ በአንድ ጊዜ የሚለቀቀው ውሃ መጠን አይኖርም። በሳምንት ሁለት ቀን ገላ መታጠብ አይቻልም። መረጃው የቢቢሲ ነው። «Capetown urged to turn of toilet taps» « My wife doesnt Shower any more» በሚል ርዕሶች ስር ሰፍሮ ይገኛል። ነዋሪዎች በቀን ከተመደበላቸው 50 ሊትር በላይ ውሃ ከፈለጉ ረጃጅም ሰልፎችን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። «ዴይ ዜሮ» የኬፕታውን ቧንቧዎች በሙሉ የሚደርቁበት ዕለት ነው (the day the taps in the south African city of Cape town will run dry) ገላ ለመታጠብ 1ነጥብ5 ሊትር የወንዝ ውሃ ማፍላትና አንድ ሊትር የቧንቧ ውሃ በመጨመር በጥንቃቄ መጠቀም የግድ ይላል።
ከገላ እጣቢ የሚወርደውን ውሃ ደግሞ ለመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ማስወገጃ ይጠቀሙበታል። እንጂ ማንኛውንም ዓይነት ውሃ መድፋት አይቻልም። ዴይ ዜሮ የሚባለው የቧንቧ ውሃ ማጥፊያ ቀን ሚያዝያ 13/2010ዓ.ም ከመድረሱ በፊት ፈጣሪ መላ ካላበጀለት በቀር የኬፕታውን ህዝብ በውሃ ችግር መሰቃየቱ አይቀርም። ፈጣሪ ይታደጋቸው! ይህ ሁሉ ቢሆንም የኬፕታውን ህዝብ ሆድ ብሶት አልተነሳም፤ ከንቲባዪቱን አልተሳደበም፤ መንግሥት ላይ ድንጋይ አልወረወረም። ሰላማዊ ሰልፍ ስለማድረጉ እንኳ አልሰማሁም። መብቱን ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን ችግሩን ያውቀዋል። መንግሥት በግልጽ ያስረዳዋል፤ ይግባባሉ። ይህ ሁኔታ የተፈጠረው በእኛ ሀገር ቢሆን ኖሮ የማህበራዊ ድረ ገጾች አፍራሽ መልዕክቶች ተጨማምረውበት ስንትና ስንት ችግር በተፈጠረ ነበር።
ለማንኛውም ሆድ የባሰውን ህዝብ በሆነ ባልሆነው አትነካኩት፣ እለፉት! ብሶት የትም ቦታ ቢኖርም ከአገራችን ከተሞች እንደ አዲስ አበባ ብሶት የበዛበት የለም። የአዲስ አበባ ብሶት ዘርፈ ብዙ ነው። የፌዴራል መስሪያቤቶችን የሠራተኛ ፍላጐት ለማሟላት ሲባልና በከተማዪቱ ያሉ የሥራ ዕድሎችን ለመጠቀም ከየክልሉ በሚጐርፈው ህዝብ ብዛት ከተማዪቱ ተጨናንቃለች። ትራንስፖርት «የለም» ማለት ይቻላል። ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት ድረስ ወደ ሥራ ለመሄድ የትራንስፖርት ጥበቃ ሰልፉ ጉድ የሚያሰኝ ነው። የሥራ መግቢያ ሰዓቱ ከ2፡30 ወደ 4፡00 የተቀየረ እስኪመስል ድረስ ህዝቡ ተሰልፎ ነው የሚውለው።
መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራ ለመሆኑ ምልክቶች አሉ። አንበሳና ሸገር ትራንስፖርት ባለፎቅ መኪኖችን አሰማርተዋል። አሊያንስ እየሠራ ነው። የሲቪል ሰርቪስ መኪኖች የታክሲ አገልግሎት ለህዝብ እየሰጡ ነው። ሚኒባስ ታክሲዎችም ትርፍ እየጫኑ፣ መንገድ እያቆራረጡና የስሙኒ መልስ እየነፈጉም ቢሆን እየሠሩ ነው። ሚኒባስ ታክሲዎች ባይኖሩ ኖሮ ከተማዪቱ በምኗ ሄዳ ሥራ እንደምትሠራ ማሰቡ ይጨንቅ ነበር። በሰው ህይወትና አካል ላይ የሚያደርሱት ጉዳትና የንብረት ጥፋቱ ያንኑ ያህል ከባድ ነው።
በትራፊክ ደንብ ጥሰት በአንድ ቀን ከሺህ በላይ አሽከርካሪ በክትትል የሚገኝበት ሁኔታ ነው ያለው። ያለመንጃ ፈቃድ የሚነዳው፣ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይና ከደረጃ በታች የሚያሽከረክረው ጥፋተኛ ሹፌር ቁጥሩም ብዙ ነው። ህዝቡ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ብሶት አለበት። ከብሶትም በላይ ተማርሯል። አሁን ደግሞ ለታክሲ መንጃ ፈቃድ የ10ኛ ክፍል ትምህርት ማጠናቀቅ ያስፈልጋል ተብሏል። አዋጁ ከዚህ በፊት ባልታየ የፓርላማ ክርክር በ67 ተቃውሞና በ30ተአቅቦ ፀድቋል። ህዝቡም ስጋት ላይ ወድቋል።
ምን ያህሉ የታክሲ ሹፌር የ10ኛ ክፍል ያጠናቀቀ ሊሆን ይችላል? ለወደፊቱ ነው ቢባል እንኳን አሁን ያሉት ነጂዎች ምን ይሆናሉ? ይታገዳሉ? «ድምፃችን ይሰማ» ብለው ቢነሱ መፍትሔው ምንድን ነው? የትራንስፖርት እጥረቱ ሊባባስ ነው? ወይስ ሌላ ተጨማሪ ዘዴ አለን? አንድ እውነት አለ፤ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን እንጠራጠርም። የታክሲ ትራንስፖርት ስርዓቱ በህግ መሰረት መመራት አለበት። ዘርፉ ስርዓት መያዝ አለበት። በታክሲ ሹፌሮች የተነሳ ለሞትና ለአካል ጉዳይት ተዳርገናል! ንብረታችን ወድሞብናል! በዚህ ሁኔታ መቀጠል አንፈልግም! አንችልም! ጊዜውም ዛሬና አሁን ነው! ይህ አንድ ነገር ሆኖ በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ሆድ የባሰው የከተማዪቱ ነዋሪ በአዋጁ በራሱና ወደታች ሲወርድ በሚኖረው አፈፃፀም ምክንያት የባሰ ሆድ እንዳይብሰው የማድረግ ስትራቴጂ መቀየስ ያስፈልጋል።
አገራችን ካለችበት አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ ጋርም እያስተያየን ወደ ግጭትና ጤናማ ወደሆነ ተቃውሞ እንዳያመራ በጥንቃቄ መምራት አለብን፡፡ ሆድ ለባሳው... ያልንበት አንዱ ሃሳብ ይህ ነው። ሌላም ሃሳብ አለን የአዲስ አበባን የቀበሌ ቤቶችን የተመለከተ ጉዳይ ነው። የቀበሌ ቤት ነዋሪው የ2010 ዓ.ም ውል አድሷል። ከወር በፊት ደግሞ ውል ያደሳችሁበትን ማስረጃ ፎቶ ኮፒ ከፎቶግራፍ ጋር አያይዛችሁ በክላሰር ይዛችሁ ኑ ተብለው ሲተራመሱ ከርመዋል። በአንዳንድ ወረዳ ተዘዋውሬ አይቻለሁ።
«ቤቱ ሊሰጣችሁ ነው» የሚል ወሬ መጣ። አሰጣጡ እንዴት ነው? በነፃ ነው? በሊዝ ነው? ለስንት ዓመት? በካሬ ሜትር በምን ያህል ብር? አከፋፈሉስ እንዴትና ከየት ነው? ምናልባት የባንክ ብድር ተመቻችቶላቸው ይሆን? በዓመት ስንት ብር እየከፈሉ በስንት ዓመት ይጨርሳሉ? የባለቤትነት ካርታ ከተሰጣቸው በኋላ አስፈቅደውም ቢሆን በቦታው ላይ የራሳቸውን ቤት መሥራት ይችላሉ? ባለሁት ፎቅ (G+2) መሥራት ይጠበቅባቸዋል? ቦታው የመኖሪያ ነው ወይም የንግድ ቦታ ነው? የንግድ ማዕከል ሥራ መባል ይመጣል? ካልቻለስ? ለሚችል ባለሀብት ተሰጥቶ እሱ (ባለይዞታው) ካሳ ተከፍሎትና ምትክ ቦታ ተሰጥቶት እንዲለቅ የሚደረግበት ሁኔታ አለ?
የቀበሌ ቤት በአብዛኛው «ሀ» እና «ለ» (ሀ/ለ) የሚባል አንዱ ቤት ለሁለት ሰው የተያዘበት ሁኔታ አለ። አብዛኛው ክርክር ላይ ነው፤ ውሣኔ አላገኘም። በዚህ ሁኔታ እያሉ ካርታ ከተሰጠ ለማን ይሆናል? ይህ የቀበሌ ቤት ጉዳይ ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ተነስቶ ነበር። አሁን ወደተግባር ሊለወጥ ነው፤ ብዙ ጣጣ አለው! የከተማችን የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች ስለዚህ ጉዳይ ግራ የተጋቡበት ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ዓይተናል። አንዳንዶቹ ደርግ በነፃ የሰጣቸውን ቤት ሊነጠቁ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። «በያዝከው ጽና» መባሉን እንጂ «ገዝተህ የራስህ አድርግ» መባልን ለመስማት ዝግጁ ያልሆነም አለ።
በዚህ ላይ የቀበሌ ቤት ኪራይ በወር 3 ብር በመሆኑ ደስተኞች ነበሩ። በተጨማሪም በያዙት የቀበሌ ቦታ ላይ ሁለትና ሦስት ክፍል ቤት ጭቃ እየለጠፉ በወር እስከ 500 ብር ድረስ እያከራዩ የሚጠቀሙ አሉ። ነገሩ ከጥቅም ጋር የተያያዘ የመሬት ጉዳይ በመሆኑ በጥንቃቄ መስተናገድ ያለበት (sensitive) ጉዳይ ነው። ይህ ነገር አሁን ካለው የግጭት ሁኔታ ጋር ተያይዞ አጀንዳ እንዳይሆንና ችግር እንዳያስነሳ ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል። በዋናነት ከላይ የተነሱትን ጥያቄዎች በአግባቡ ማስተናገድና ከህዝቡ ጋር በቅርበትና በግልጽ መወያየት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በቋፍ ያለን ወገን በሆነው ባለሆነው መነካካት ሆድ ለባሰው ... ዓይነት እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ግርማ ለማ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።