ባለቤት አልባው የ”መረጃ” ምንጭ!

12 Feb 2018

ያለንበት ዘመን የኢንፎርሜሽን ዘመን ነው፡፡ በዚህ የመረጃ ዘመን ደግሞ ለመረጃ ቅርብ መሆን ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ከመረጃ በራቅን ቁጥር በርካታ ለሕይወታችን ወይም ለዕለት ተዕለት አኗኗራችን አጋዥ የሆኑ ቁምነገሮችን ልናጣ እንችላለን፡፡ ስለሆነም የመረጃ አጠቃቀማችን እንዴት ነው የሚለውንም ቆም ብሎ ማየት ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛና አስፈላጊ መረጃ የሚጠቅመንን ያህል የተዛባ መረጃ የሚያስከትለው ጉዳትም የዚያኑ ያህል ከባድ ነውና፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ መረጃ የሚሰራጭበትም ሆነ መረጃው ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ የተዛባ ሆኖ እናገኛለን፡፡ በተለይ የማህበራዊ ሚዲያው መስፋፋትና ተደራሽነቱም እያደገ መሄድ ለዚህ ትልቁን ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡
በዛሬው ጽሑፌ የማህበራዊ ሚዲያው ላይ ትኩረት በማድረግ ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ ለዚህ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያቴም በተለያዩ አጋጣሚዎች በፌስ ቡክ የተለቀቁ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ የተጋነኑና የተንሻፈፉ መረጃዎች ኅብረተሰቡ ጋር ሲደርሱና በእነዚህ መረጃዎችም አማካይነት በርካታ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሲጓዙ፣ አንዳንዶቹም እነዚህ በማህበራዊ ድረገፅ የሚሰራጩ መረጃዎች ሙሉ በሙሉ እውነት ናቸው ብለው አምነው መቀበላቸውና ሌሎችንም ለማሳመን ጥረት እስከማድረግ መድረሳቸው ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ ማህበራዊ ሚዲዎች የሚቀርቡ መረጃዎች በአሉባልታና በውሸት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም የውሸት ስያሜን ወይም አድራሻን እየያዙ በተሳሳተ ስም የተዛባ መረጃን የሚያሰራጩ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ ግለሰቦችና ድርጅቶች በስማቸው የተከፈቱ የፌስ ቡክ አድራሻዎች እንደማይወክሏቸው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በርግጥም በዚህ ዓይነት የውሸት ስም የሚንቀሳቀሱ በርካታ የፌስቡክ ድረገፆች መኖራቸውንና እነዚህንም ለመቆጣጠር የሚያስችል ሶፍትዌር ተግባራዊ እንደሚደረግ የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ሱከርበርግ በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር፡፡
በተለይ በታዋቂ ሰዎች ስም የሚፃፉና የሚሰራጩ አንዳንድ መረጃዎች ኃላፊነት የጎደላቸውና የሰዎችን ስምና ዝና እንዲሁም ሰብአዊ ክብርን እስከማዋረድ የሚዘልቁ ናቸው፡፡ ለአብነትም በሰላምና በፍቅር ከቤተሰቡ ጋር የሚኖርን አንድ ታዋቂ ሰው ስም በማንሳት “እከሌ ከትዳሩ ተፋታ”፣ “እከሌና እከሌ ተጣልተው ከባድ ችግር ተፈጠረ”፣”በዚህ አካባቢ ከባድ ጦርነት ተቀሰቀሰ”፣ “በዚህ አካባቢ በተከሰተ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት አለፈ”፣ ወዘተ የሚሉ አሉባልታዎችን በፌስ ቡክ ወይም በተለያዩ ድረገፆች ላይ መመልከት የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡
አንድ ገጠመኝ ላውጋችሁ፡፡ የዛሬ ሦስት ወራት ገደማ ነው፣ ጊዜው ጠዋት ሁለት ሰዓት አካባቢ ይሆናል፡፡ ከምኖርበት አካበቢ ተነስቼ ወደ መስሪያቤት በታክሲ እየሄድኩ ነው፡፡ በዚህ መካከል ሁለት ወጣቶች ባዩት ነገር በጣም ተደናግጠው እና ተረብሸው ሲጨዋወቱ ሰማሁ፡፡ ቀስ በቀስም የሚያወሩት ርዕሰ ጉዳይም ከጆሮዬ ገብቶ እኔንም ለድንጋጤ ዳረገኝ፡፡ ጉዳዩ አንድ ታዋቂ አርቲስት ሞቷል የሚል ዜና ነው፡፡ ይህ ሞቷል የተባለው አንጋፋ አርቲስት ደግሞ በወቅቱ ከአንድ ቀን በፊት በሚሌኒየም አዳራሽ ኮንሰርት ያቀረበ ሲሆን በዕለቱም እኔ በምሰራበት የሚዲያ ተቋም ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር ቃለምልልስ ለማድረግ ቀጠሮ ነበረው፡፡ ከዚያ በፊት ስለ ጤና ጉድለቱ ምንም የተባለ ነገር አልነበረምና ዜናው አስደንጋጭ ነበር፡፡ በዚህ መካከል እኔም ክስተቱ እያሳዘነኝ መውረጃዬ ደርሶ ከታክሲ ወረድኩ፡፡ ወደ ቢሮም እንደገባሁ ከአርቲስቱ ጋር ቀጠሮ ከያዘው ጋዜጠኛ ጋር ተገናኘሁ፡፡ ስለመረጃውም ለማረጋገጥ የሰማሁትን ስነግረው እሱም ስለጉዳዩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት መስማቱንና ነገር ግን እውነት መሆኑን አለማረጋገጡን ነገረኝ፡፡ ጥቂት ቦታዎች ከደዋወልን በኋላ በመጨረሻም ወሬው ውሸት መሆኑንና አርቲስቱም ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠመው ማረጋገጥ ቻልን፡፡ እናም የተባለው ነገር አርቲስቱ ጋርም ደርሶ ስለነበር ጉዳዩ በጣም እንዳሳዘነው ነገረን፡፡ እኛም እንዲህ በሚያደርጉ ግለሰቦች ከማዘን ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረንምና በጉዳዩ አዝነን አለፍን፡፡
በሌላ ጊዜም ተመሳሳይ ክስተቶች በፌስ ቡክ ወሬ በርካታ ሰዎች የሞራል ጉዳት እንደደረሰባቸው በተደጋጋሚ ሰምተን ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት የተሳሳቱ መረጃዎችን መስማት እንደወረርሽኝ ከተዛመተ ትንሽ ጊዜ ቆይቷልና፡፡ እንዲህ ዓይነት የሞራል ጉዳት ከደረሰባቸው ታዋቂ ሰዎች ውስጥም አርቲስቶች፣ ታዋቂ አትሌቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ነጋዴዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይገኙበታል፡፡
ሰሞኑን በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የተከሰቱ ግጭቶችን መነሻ በማድረግ በተለያዩ ድረገፆች የሚሰራጩ አንዳንድ መረጃዎች አሳዛኝም፣ አሳፋሪም ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ መረጃዎችም ሆን ተብለው ሕዝብን ከሕዝብ ለማበጣበጥና ለማጋጨት እንዲሁም ከፍ ሲልም አገሪቱን ለማፈራረስ ታስቦባቸው የሚፃፉ መሆናቸውን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይ ዘርን መሠረት በማድረግ የሚለቀቁት አንዳንድ መረጃዎች ምን ያህል አደገኛና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም ተሰምቶ የማይታወቅ እንዲሁም የሕዝቡን የርስ በርስ ቁርኝትና አብሮ የመኖር የቆየ እሴት ለመሸርሸር ታስቦ የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት በማይፈልጉ አካላት የሚሰራጭ መሆኑንም መገንዘብ ይቻላል፡፡
በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ሲከሰቱ የነበሩ አለመረጋጋቶች የተነሱበት ዋናው ምክንያት ኅብረተሰቡ በየጊዜው የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች በሚፈለገው ፍጥነት አለመሄዳቸው እንደሆነ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልፀው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከግምገማ በኋላ ያለውን ችግር በዝርዝር አስቀምጠውታል፡፡ ያም ሆኖ ግን እነዚህን ሃሳቦች ወደ ጎን በመተው የፌስ ቡክ አጀንዳ ሆኖ የከረመው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተነሱ ግርግሮች በመንግሥት የተወሰዱ እርምጃዎች ከልክ ያለፉ ስለመሆናቸው፣ አንድን ብሔር ከሌላው ብሔር የሚያጋጩ፣ የእርስ በእርስ መተማመንን እሴት የሚያጠፉ፣ ሀገራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩና መሰል ድርጊቶች ናቸው፡፡
በእርግጥ መንግሥት ለዜጎቹ ኃላፊነት እንዳለበት ማንም የማይክደው ሃቅ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በማንኛውም ጉዳይ ቅሬታ ላለውም ሆነ ለሌለው የኅብረተሰብ ክፍል እኩል ኃላፊነት እንዳለበት መረዳት አያዳግትም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሰላምን የማረጋገጥና ሰላማዊ ኑሮ እየኖሩ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግሥት ለሚወስደው እርምጃ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ይህንን ጉዳይ ሚዛናዊ ሆኖ ማየት ተገቢ መሆኑን እያንዳንዱ ህሊናው የሚያመዛዝንና የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት አጥብቆ የሚመኝ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይረዳዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከዚህ አንጻር በእነዚህ ድረገፆች ላይ በተደጋጋሚ የሚለቀቁት መረጃዎች ምንም ዓይነት ጥፋት ሳይሰራ ችግር የደረሰበትን የኅብረተሰብ ክፍል ከመወገን ይልቅ በሕገወጥ መንገድ የሌላውን ንብረት ለሚያወድሙት የሚያደላ ነው፡፡ ለመሆኑ በአገሩ ላይ በሰላማዊ መንገድ ሰርቶ የመኖር መብት የሁሉም ዜጋ አይደለምን? በትክክልም እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ ላይ ሰርቶ የመኖር መብት አለው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት መብትም አለው፡፡ ነገር ግን ይህ እንዳይሆን የተለያየ ምክንያት በመፍጠር በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚጥሩ አካላት አሉ፡፡ በዚህ ብቻም ሳያበቁ ጥቂት ግርግር ሲነሳ ዜጎች ለዘመናት ለፍተው ያጠራቀሙትን ሀብትና ንብረት እንዲሁም የሁላችንም የጋራ ሀብት የሆኑትን የመንግሥት ንብረቶች የማውደም ዓላማን ይዘው የሚንቀሳቀሱም አሉ፡፡ እነዚህን ኃይሎች በፌስ ቡክ ሃይ የሚል ግን ብዙም አይታይም፡፡ ቢኖርም አደርባይ በሚል ይፈረጃል፡፡
ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በእነዚህ የፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ ድረገፆች በመጠቀም ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላት ለራሳቸው የተመቻቸ ቦታ እና ምቹ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሌሎችን ለዚህ ነውጥና ሁከት የሚጋብዙበት ሁኔታ በስፋት መኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ መኖሪያውን ውጭ አገር ያደረገው ጁሃር መሃመድ አንድ ሰሞን እዚያ ተቀምጦ እዚህ የጦር ጄኔራል ሲሆን ተመልክተናል፡፡
ከዚያም አልፎ ለራሱ ምንም ዓይነት አደጋና ችግር እንደማያጋጥመው ጥግ ይዞ ሌሎችን ተነስ ወደ ከመንግሥት ጋር ተዋጋ፣ ያለህበት ኑሮ ምቹ አይደለም፣ ሌሎች አካላት ከሚገዙህ እኔ ብገዛህ ይሻላል በሚል ስሜት ሌሎችን መገፋፋት እና ለጦርነት ማነሳሳት የቻለው በዚሁ በፌስ ቡክ ዘመቻ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ አንዳንድ ሰዎች የፌስ ቡክ መረጃዎችን የዕለት ተዕለት የመረጃ ምንጭ በማድረግ እከሌ እንዲህ አለ፤ እከሌ እንዲህ አደረገ በማለት ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ከራሳቸው አልፈው ወደ ሌሎችም ሲያሰራጩ መዋላቸው ነው፡፡
የሶሻል ሚዲያው ያስከተላቸው በርካታ ችግሮች ውስጥ አንዱ ደግሞ የባህል ወረራ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ሚዲያዎች በነፃነት የሚሰራጩ አንዳንድ መረጃዎችና ቪዲዮዎች በተለይ ወጣቱን ለከፍተኛ የሥነምግባር ብልሽት የሚዳርጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በእነዚህ ሚዲያዎች አማካይነት ልቅ የወሲብ ፊልሞች፣ ከባህል ውጪ የሆኑ ድርጊቶችና ሌሎች የሥነምግባር ችግር የሚያስከትሉ መረጃዎች ይተላለፋሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ልቅ ለሆነ የወሲባዊ ግንኙነትና በዚህም ሳቢያ ለኤች አይቪ/ኤድስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት የሚሆኑበት ሁኔታም ሰፊ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ማህበራዊ ሚዲዎች በቀላሉ በምንይዛቸው ሞባይል ስልኮቻችን አማካይነት ሊተላለፉና ሊሰራጩ የሚችሉ መሆናቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ እንዲያገኟቸው በር ከፍቷል፡፡ በተለይ ገና በለጋ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶችና ሕፃናት ጭምር በቀላሉ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን የሚያገኙበት ዕድል እየሰፋ በመጣበት በአሁኑ ወቅት እነዚህን የፌስ ቡክ መረጃዎች የሚያገኙበት ዕድልም በዚያው ልክ እየሰፋ መጥቷል፡፡
ከሁሉም በላይ በአሁኑ ወቅት ማህበራዊ ሚዲያውን እየከፋ እንዲሄድ ካደረጉ ችግሮች ውስጥ አንዱ ደግሞ የዘረኝነት ማስፋፊያ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይ ዘርን መሠረት በማድረግ የአንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ጥላቻ እንዲያሳድር ለማድረግ የተለያዩ ያልተፈጸሙ እና ሆን ተብለው የሚቀነባበሩ ሃሳቦችን በመለጠፍ እርስ በርስ ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶች ማህበራዊ ሚዲያው ኃላፊነት የጎደለው ሚዲያ መሆኑን እንድንገነዘብ የሚያደርግ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ የተለያዩ ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባትና የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ እንዲህ ባለችው አገር ዘርን መሠረት ያደረገ የጥላቻ ፖለቲካን የሚያራምዱ አካላት ፍላጎታቸው ማቆሚያ የሌለው የእርስ በርስ ግጭትና እልቂት ለመጋበዝ ካልሆነ በስተቀር ምን ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ያውም በተቀነባበረ ውሸት አማካይነት ሆን ብሎ ሰዎችን እርስ በርስ ለማጋጨት መሞከር ጤነኛ አስተሳሰብ ካለው ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ እናም ይህንን እኩይ ድርጊት የሚያራምዱ አካላት ኃላፊነት የጎደላቸውና በማህበራዊ ሚዲያ ተደብቀው ድብቅ አላማቸውን የሚያራምዱ አካላት መሆናቸውን መረዳት ተገቢ ነው፡፡
በርግጥ የሶሻል ሚዲያው ተጽዕኖ በአገራችን ብቻም ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ክፍሎችም የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለ መሣሪያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለአብነትም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የተጀመረውና የተለያዩ የአረብ አገራትን ያዳረሰው ግጭት ሊባባስ የቻለው በፌስ ቡክ አማካይነት ነው፡፡ በግብፅ በተደጋጋሚ ታህሪር አደባባይ ይወጡ የነበሩ ሰልፈኞች ፌስቡክን ዋነኛ የመገናኛ መስመር አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡
እነዚህ ሶሻል ሚዲያዎች በራሳቸው የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች በመሆናቸው በአግባቡ ብንጠቀምባቸው ጠቀሜታቸው እንደሚጎላ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን እነዚህን መሣሪያዎች ያለአግባብ መጠቀም ደግሞ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው፡፡ በተለይ በእነዚህ ሚዲያዎች የሚተላለፈው መረጃ ባለቤት የሌለው በመሆኑ ሁሉም ሰው እንደልቡ የሚያሰራጨው መረጃ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የሚተላለፉት መረጃዎች በግዴለሽነት የሚጻፉ፣ የተሳሳቱና ሆን ተብለው ሰዎችን ለማሳሳት የሚቀርቡ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡
ስለዚህ ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ካልተረዳነውና የመረጃ ምንጩን ከሌሎች የሚዲያ አካላት ሳናረጋግጥ እንደወረደ የምንወስደውና ያንኑ መልሰን ለሌሎች አካላት የምናስፋፋ ከሆነ እኛ ተሳስተን ሌሎችንም እንዳናሳስት ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ ሞተ ሲሉት ተሰበረ የሚል አንዳንዴም ከዚያም በላይ የራስ ፍላጎትን በፌስ ቡክ አማካይነት ለማራመድ መረጃዎችን የሚፈበርክ በርካታ ኃይል ባለበት ነባራዊ ሁኔታ እነዚህን መረጃዎች በጥንቃቄ መመልከትና መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በተለይ በእነዚህ መረጃዎች እየተመራን ባልተገቡ ድርጊቶች ውስጥ የምንሳተፍ ካለንም ቆም ብለን ማሰብ ይጠበቅብናል፡፡ ካልሆነ ግን የሚያስከትለው አደጋ የከፋ ይሆናልና፡፡

ወርቁ ማሩ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።