‹‹ጉድለታችን በጋራ ጥረታችን ይሞላል››

28 Feb 2018

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ላለፉት 24 ቀናቶች ስብሰባ ኣካሂዷል፡፡ ይህን ተከትሎም የካቲት 19 ቀን 2010 ዓ.ም የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ የኮሚቴው የአቋም መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ የተካሄደው በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን እና አጠቃላይ ሃገራዊ ህልውናችን ከፍተኛ አደጋ ላይ በወደቀበትና ይህንኑ መሰረት ያደረገው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እያጋጠሙን ባሉ ፖለቲካዊና ሃገራዊ ችግሮች ዙሪያ ባደረገው ግምገማ አጠቃላይ መስማማት በመፍጠር ቀጣይ አቅጣጫዎችን ባስቀመጠ ማግስት ነው፡፡
በመሆኑም ማዕከላዊ ኮሚቴው ከወትሮው በከፍተኛ ጥልቀትና በተለየ ሁኔታ ዝርዝርና ፍፁም ነፃ ውይይት በማድረግ ሃገራዊ ህልውናችንን ማረጋገጥን እንደግብ አስቀምጦ ወደ ውይይት ገብቷል፡፡ በውይይቱም ያለንበትን ዓለማዊና ሃገራዊ ሁኔታ በተለይም ሃገሪቱ የምትገኝበትን የአፍሪካ ቀንድ (Geo –Politics) ሁኔታ በዝርዝር ፈትሿል፡፡ የሃገራችን ሰላምና ህልውና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ህልውና ያለውን ፋይዳና ትርጉም በዝርዝር ገምግሟል፡፡
በሃገራችን በአጠቃላይ ያለንበትን ፖለቲካዊ ሁኔታም በዝርዝርና ለወትሮው ከነበረን ሁኔታ በመሰረቱ የተለየና ጥልቀት ባለው ሁኔታ ለመወያየትና ለመነጋገር ተችሏል፡፡ የክልላችንንም ሁኔታ አሁን ሃገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንፃር በዝርዝርና በጥልቀት ገምግሟል፡፡
ግምገማችን እንደተለመደው ችግርን በመዘርዘር ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ ችግር የችግሩን ፈጣሪና ባለቤት በመለየት፤ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂነትና ሃላፊነት በመውሰድ መንፈስ የተካሄደ መሆኑ በርግጥም ልዩና ታሪካዊ ያደርገዋል፡፡ በርካታ ጉዳዮችን በስፋትና በጥልቀት የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከገመገመ በኋላ በሚከተሉትም ጉዳዮች ድምዳሜዎች ላይ ደርሷል፡፡
1. የድርጅታችን ደኢህዴን እና ኢህአዴግ ሊቀመንበር የሆነው ጓድ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከድርጅታችን ደኢህዴንና ኢህአዴግ ሊቀመንበርነትና ከሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በገዛ ፈቃዱ ከአብዮታዊነትና ከህዝባዊነት በመነሳት ስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ የስልጣን መልቀቅ ጥያቄው በሃገራችን እየተፈጠረ ላለው ችግር መንግስት እና ድርጅት እየወሰደው ላለው እርምጃ ውጤታማነትና በቀጣይ ለሚኖሩን የሀገር ግንባታና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትግሎች የመፍትሄው አካል መሆኑንም አሳውቆናል፡፡ ከደኢህዴን ሊቀመንበርነት ቦታ ለመልቀቅ ያቀረበውን ጥያቄ ደኢህዴን በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ ያጸደቀ ሲሆን ይህም የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ድላችንና የመሪያችን ብቃት ያመጣው መሆኑን በአግባቡ እንገነዘባለን፡፡ አሁንም ስልጣንን የሕዝብ አገልጋይነት መሣሪያ ከመሆን ይልቅ ለራስ ጥቅምና ክብር መጠቀሚያ የማድረግ ዝንባሌ ገኖ ባለበት ሃገርና አህጉር ስልጣንን በራስ ፍላጎት በመልቀቅ ለሃገሪቱም ሆነ ለአህጉራችን አዲስ ታሪክ በማስቀመጡ በመሪያችን በእጅጉ ኮርተናል፡፡ በአመራር ዘመኑም ላስመዘገባቸው አመርቂ ድሎችና ውጤቶች ተገቢውን ክብር እንሰጣለን፡፡ በየደረጃው ያሉት አመራሮች መላው ህዝባችንና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ጭምር ከዚህ ከመሪያችን ሌጋሲ ተገቢውን ትምህርት ይወስዳሉ ብሎ ደኢህዴን ያምናል፡፡ ቀጣይ የሃገራችን የስልጣን ሽግግር ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ደኢህዴን የበኩሉን ለመወጣት የተዘጋጀ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ያረጋግጣል፡፡
2. ደኢህዴን በሃገራችን ላለፉት 26 ዓመታት ባጠቃላይ እና በተለይም ከተሃድሶ በኋላ ባለፉት 15 ዓመታት በተከታታይ ለተመዘገበው ፈጣን ልማትና በሃገራችን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተደረገው ርብርብና ለተገኘው ለውጥ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን በፅናት ያምናል፡፡ በሃገራችን አንድ ሃገራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማሕበረሰብ ከመገንባት አንጻር ደኢህዴን የክልሉን ህዝቦች እንዲሁም የመላው ሀገራችን ህዝቦች ትስስር ከማጎልበት አንጻር እየጎለበተ የመጣ መሻሻል እንዲመዘገብ የበኩሉን አበርክቷል፡፡ ይህም ሆኖ አሁንም በርካታ ጉድለቶች እንዳሉና ለነዚህ ጉድለቶች የራሱ ድርሻ እንዳለው ገምግሟል፡፡ ባንድ በኩል ማሳካት የሚገባንና በላቀ ደረጃ ያላሳካናቸው በርካታ ችግሮች መኖራቸውን እንዲሁም ስኬቶቹ በራሳቸው የፈጠሩትንና የሚፈጥሩትን ተጨማሪ የማሕበረሰብ ፍላጎቶች ተከታትሎ ትርጉም ባለው ደረጃ መመለስ ባለመቻላችን የተፈጠረውን ቅሬታም ደኢህዴን በአግባቡ ይገነዘባል፡፡
3. ድርጅታችን ደኢህዴን የሚመራው ክልል ተመሳሳይ ብሄራዊና መደባዊ ጭቆና ሲፈራረቅባቸው የኖሩ 56 ብሄር ብሄረሰቦች በድርጅታችን ፖለቲካዊ አመራርና በሰፊው ህዝባችን መልካም ፈቃድ የፈጠሩት አንድነት ላለንበት ጠንካራ ትስስር አድርሶናል፡፡ በክልላችን የሚገኙ ብሄር፤ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ሲመሩ የነበሩትን 21 ድርጅቶችን በራሳችን ፈቃድና ይሁንታ በማዋሀድ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በመፍጠራችን በክልሉ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲያብብ በማድረግ ረገድ ሁነኛ ታሪካዊ ድል መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይህ ታሪካዊ ክንውንና ያስገኛቸው ውጤቶችም በሀገር ደረጃ ተምሳሌት እንደሚሆንና ለኢህአዴግ የአንድ ፓርቲነት ውጥኖችና ሀገራዊ አንድነት ልምድና እርሾ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በዴሞክራሲያዊ አንድነታችንም በርካታ ብዝሃነትና ትስስር ያላቸውን ብሄር/ብሄረሰቦችና ህዝቦችን በአንድ ድርጅትና በአንድ ክልላዊ መንግስት ስር አደራጅቶ ላለፉት 25 ዓመታት በማታገል በርካታ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድሎች አስመዝግበናል፡፡ በነዚህ ድሎች ዛሬም ደኢህዴን ኩራት ይሰማዋል፡፡ ሆኖም ይህ ብዝሃነትን ማዕከል ያደረገው አንድነት ያለምንም ችግር አልጋ ባልጋ ሆኖ የተፈጠረና ለወደፊቱም ከተግዳሮት የጸዳ እንዲሆን ይበልጥ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ደኢህዴን ያምናል፡፡ በተለያየ ወቅት የክልላችንን አንድነት የሚፈታተኑ ችግሮች ያጋጠሙንና እያጋጠሙን ያሉ ቢሆንም ዋናው ችግር ግን የኪራይ ሰብሳቢነት ሽፋን የሆነው ጠባብነት ነው፡፡ በመሆኑም ይህን አደናቃፊ አመለካከትና ተግባር ዛሬም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በፅናት በመታገል በሂደት የጀመርነውንና ዳር ያላደረስነውን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ማጠናከርና የክልሉን አንድነት በማጎልበት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንዳለብን ተገንዝበናል፡፡ በርግጥም የክልላችን ብሄር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ትስስርና አንድነት ጠንካራ እንዲሆን ሊሰሩ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉም ለይተናል፡፡ ዘላቂና ፅኑ መሰረት ያለውን የህብረተሰባችንን አንድነት በመፍጠር ለሃገራችን አንድነት አብዮታዊ ሚናችንን መጫወታችንን አጠናክረን መቀጠል እንዳለብን ተማምነናል፡፡
4. ዴሞክራሲ ለሃገራችን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ከመነሻው አምነን የገባንበት ጉዳይ ቢሆንም በዚህ በኩል የሄድንበት ርቀት በራሳችን መለኪያም ቢሆን መሆን በሚገባው ደረጃ አለመድረሱን ደኢህዴን በፅናት ያምናል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከመላ ዜጎች ነፃና የነቃ ተሳትፎ ውጪ ሊታሰብ የሚቻል አይደለም፡፡ በዚህ በኩል የዜጎችን የነቃ ተሳትፎ የሚገድቡ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ደኢህዴን አይቷል፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት ማለትም በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የብዙሃን ማህበራትም ሆነ የብዙሃን መገናኛዎች ህገ-መንግስታዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከማብቃትና ከማበረታታት ይልቅ በብዙ መልኩ የሚታዩ አደናቃፊ ሁኔታዎች ያላስወገድን መሆኑን በአግባቡ ተረድተናል፡፡ በመሆኑም ይህን ሁኔታ በመሰረቱ የሚቀይር አቅጣጫ ይዘን የዜጎችን ነፃና የነቃ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ከወትሮው የተለየ ትግል ለማድረግ ደኢህዴን ተዘጋጅቷል፡፡
5. ድህነትና ኋላቀርነት በሚያንገላታው ሃገር ውስጥ ያለ ፓርቲ ይህን ችግር ከመፍታት በላይ የሆነ አጀንዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ ደኢህዴን የክልሉን ሆነ የአገሪቱን ድህነትና ኋላቀርነት ማስወገድ የዘወትር ስራው አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በሂደቱም እስካሁን በርካታ ድሎች ቢኖሩም ዛሬም ይህ ጠላት ከሕብረተሰባችን ጫንቃ ጨርሶ ያልወረደ መሆኑን በአግባቡ ይረዳል፡፡ በሀገር ደረጃም ሆነ በክልላችን የልማት ስራዎች ጋር ተያይዞ አሁንም የሚነሱ በርካታ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች መኖራቸውንም ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ የሀገራችንን ብሎም የክልላችንን ህዝብ ህይወት የሚቀይሩ የትራንስፎርሜሽን ስራዎች ያስገኘናቸው ድሎች እንደተጠበቁ ሆነው አሁንም የተንጠባጠቡ ስራዎች መኖራቸውን ገምግመናል፡፡ ስኬቶቹን በማስፋትና ጉድለቶቹን በየደረጃውና በቀጣይ በመፈተሽ ሃገራዊ የልማት ስራችንም ሆነ ክልላዊ ልማታችን በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን ጨምሮ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚ ያደረገ እንዲሆን ደኢህዴን በፅናት ይታገላል፡፡ በሁሉም መስክ ተደማሪ ለውጥ ብቻ ሳይሆን ትራንስፎርሜሽን በማረጋገጥ ሂደት ምልዓተ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ደኢህዴን ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
6. የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ሥርዓት ካለ ዴሞክራሲያዊ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ተሣትፎ ሊረጋገጥ እንደማይቻል በፅንስ-ሃሳብ ደረጃ በደኢህዴን አስቀድሞ በቂ ግንዛቤና እውቀት የተያዘበት ጉዳይ ነው፡፡ ባለፉት አመታት ባካሄድነው ትግል አንጻራዊ ልምድና መሻሻሎች እንዳሉ የማይካድ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በተግባራዊ እንቅስቃሴአችን ግን በርካታ እጥረቶች እንዳሉብን ደኢህዴን በዝርዝር ገምግሟል፡፡ በቀጣይ ህገ መንግስታዊ ሥርአቱን ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ካሉ በሀገርና በክልል ደረጃ ከሚገኙ ተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲዎች በክልላችን ያለምንም ተፅእኖና እንቅፋት እንዲንቀሳቀሱ ሃላፊነታችንን ከመወጣትም በላይ ልዩነታችን እንደተጠበቁ ሆነው በሚያግባቡን የጋራ ክልላዊና ሃገራዊ ጉዳዮች ተደጋግፎ ለመስራት ደኢህዴን ያለውን ዝግጁነት በዚህ አጋጣሚ መግለፅ ይፈልጋል፡፡
7. ፌዴራላዊ ሥርዓታችን በአጠቃላይና ህገ መንግስታችን በተለይ የሃገራችን ዜጎች በሃገራችው ተዘዋውረው የመኖርና የመስራት ነፃነት እንዳላቸው በግልፅ ይቀበላል፤ ይደነግጋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወደህ በተለይ በጎላ ሁኔታ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች እየተከሰተ ያለው ብሄርን መሰረት ያደረገ ጥቃት፤ እንግልትና ስደት ደኢህዴን አምርሮ ይቃወማል፡፡ በሂደቱም ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ህይወት መጥፋትና እንግልት የተሰማንን መሪር ሃዘንና ቁጭት እንገልፃለን፡፡ የተፈናቀሉ ወገኖች በፍጥነት እንዲቋቋሙ የተጀመረውን ጥረት ለመደገፍ ያለንን ዝግጁነትም እንገልፃለን፡፡ ድርጅታችን በሃገራችን በአጠቃላይ ሆነ በክልላችን በተለይ ይህ አስነዋሪ ድርጊት በፍፁም እንዳይከሰት በፅናት ይታገላል፡፡
ለክልሉ ህዝቦች
ባለፉት ዘመናት በሃገራችን ተንሠራፍተው በነበሩት ጭቆናዎች የክልላችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲሁም የከተሞች ነዋሪዎች እንደሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረው ባይተዋር ከነበሩበት የግፍ አገዛዝ ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን ተፋልመው በማስወገድ የራሳችንን ጉዳዮች በራሳችን እየወሰንን በአዲስቱ ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት እኩል ተዋናይ በመሆን ሩብ ምዕተ አመታት ዘልቀናል፡፡ የሃገሪቱን ሰባ በመቶ ብዝሀነት በያዘው ክልላችን ስር በመሰባሰባችን አንጻራዊ እጥረቶቻችንን በአንፃራዊ ጥንካሬያችን በማካካስ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት በጋራ ተሳትፏችን በማረጋገጥ ፍትሐዊ ተጠቃሚነታችንን አሣድገናል፡፡ የተመዘገቡት አወንታዊ ለውጦች እንደተጠበቁ ሆነው በበቂ ደረጃ መጠቀም ያልጀመሩ የክልላችን የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን የደኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ በዝርዝር ባደረገው ግምገማ ተገንዝቧል፡፡ ድርጅታችን ደኢህዴን በሚመራው የክልሉ መንግስት በተለያዩ ደረጃ የታዩት ድክመቶች የክልላችንን እምቅ አቅም አሟጠን በመጠቀም የክልላችንን አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን እንዲሁም የከተሞች ነዋሪዎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ አሉታዊ ሚና እንደነበራቸውም በቁጭት ገምግመናል፡፡ በመሆኑም እስከ አሁን ድረስ የተገኙትን ስኬቶች ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ በአዲስ መንፈስና ቁርጠኝነት ለመንቀሳቀስ ወስነናል፡፡ የድርጅቱ ጥረት የሚለካው በመላው የክልላችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲሁም የከተሞች ነዋሪዎች ያልተቆጠበ ጥረትና የነቃ ተሳትፎ ብቻ በመሆኑ እንደወትሮው ሁሉ ከጎናችን እንድትቆሙ በአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በየደረጃው ለሚገኙ የአመራር አካላትና የድርጅቱ አባላት
ድርጅታችሁ ደኢህዴን በክልላችን ድህነትና ኋላቀርነት ተወግደው ብልፅግናና የዴሞክራሲያዊ ባህል እውን እንዲሆን በሚታገልበትና ህዝባችንን በሚያስተባብርበት ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መስመራችን እየተመራን ያገኘናቸውን ድሎች ለማስቀጠልና በየደረጃው የሚገጥሙትን ተግዳሮቶችን መሻገር የሚቻለው እያንዳንዱ አባል በቅድሚያ ራሱን በመለወጥና በቀጣይነት በመማር የሚጫወተውን ሚና በማጠናከር ነው፡፡
ባለፉት አመታት በክልላችን ብሎም በሃገራችን ለተገኙት ስኬቶች የመላው አባሎቻችን ድርሻ የማይተካ የመሆኑን ያህል ለገጠሙን ፈተናዎችም በጋራና በተናጠል የምንወሰደው ኃላፊነት እንዳለብን የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም ጉድለታችንን በፍጥነት እያረምን የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመርነው ጥረት ከዳር እንዲደርስ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ቁርጠኝነት በመላበስ በአዲስ መንፈስ እንድንትቀሳቀሱ ድርጅታችሁ ደኢህዴን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡
ለክልሉ ሴቶችና ወጣቶች
የክልላችን ህብረተሰብ ግማሽ አካልና የድርጅታችን ማህበራዊ መሰረት የሆኑት ሴቶች እንዲሁም የአሁን ተዋናዮችና የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች በሃገራችን በምንገነባው ዴሞክራሲና በተጀመረው ልማት ሂደት ብቻ ሳይሆኑ በአሁኑ ወቅትም ሁነኛ ተዋናዮችና ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ያምናል፡፡ በክልላችን በተጀመረው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም የዴሞክራሲ ሥርዓታችን ግንባታ ሂደት ላሳያችሁት ብስለትና ተሳትፎ ደኢህዴን ትልቅ ግምት ይሰጣል፡፡ በዚህ መንፈስ ተሳትፎአችሁንና ተጠቃሚነታችሁን ለማሣደግና ለማስቀጠል ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ባለፉት አመታት የተደረጉት ጥረቶችና ምቹ ሁኔታዎች እንዲሁም የተገኙ ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆኖ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ነጻነት ለማረጋገጥ፤ የመዝናኛና የሰብዕና መገንበያ አስቻይ ሁኔታዎች አቅርቦት ችግር በበቂ ለመቅረፍ አለመቀረፉንና የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ተጠቃሚነታችሁን በራሳችሁ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የተኬደው ርቀት የናንተን ፍላጎትና አቅም የሚመጥን እንዳልሆነ ደኢህዴን በቁጭት ገምግሟል፡፡ በመሆኑም ዕቅዶቻችንንና አሠራሮቻችንን እንዲሁም አደረጃጀቶቻችንን በመፈተሽ የተጀመሩትን ጥረቶችንና የተገኙትን ስኬቶች በማስፋት በራሳችሁ የነቃ ተሳትፎ ተጠቃሚነታችሁን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ የላቀ ጥረት ለማድረግ ማዕከላዊ ኮሚቴው ወስኗል፡፡ የክልላችን ሴቶች እስካሁን ድረስ ለድርጅታችን ላሳያችሁት ጽኑ ድጋፍ አክብሮታችንን እየገለጽን እንደከዚህ ቀደሙ ከጎናችን በተለመደው ጽናታችሁ እንድትቆሙ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ የክልላችን ወጣቶችም እስከአሁን ድረስ ላሳያችሁት ምክንያታዊነት ጨዋነት፤ ታጋሽነትና ተሳትፎ ድርጅታችን ያለውን ትልቅ አክብሮት እየገለፀ አሁንም ከድርጅታችን ደኢህዴን ጎን በመቆም ጉድለታችንን አርመን ድሎቻችንን እንድናሰፋ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ለመንግስት ሰራተኞችና ምሁራን
በክልላችን ባለፉት አመታት ላስመዘገብናቸው ውጤቶች የመንግስት ሰራተኞችና ምሁራን ሚና የማይተካ እንደሆነ ደኢህዴን ይገነዘባል፡፡ የክልላችንን ልማት በማፋጠን የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ለሃገራችን ዕድገት አስተዋፅኦ ለማበርከት እያንዳንዱ ሰራተኛ ያለ አድሎ በቅንነትና በቅልጥፍና እንዲሁም በውጤታማነት የሚሰጠው አገልግሎት የህዝባችንን ምርታማነት በማሳደግ ልማታችን በማፍጠን ረገድ የሚጫወተው ሚና ጉልህ ነው፡፡ በመሆኑም ላበረከታችሁት አስተዋፅኦ ደኢህዴን ያለውን አክብሮት ይገልፃል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ችግሮች እንዳሉ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና ለማሻሻል ተከታታይ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም ህዝባችንን ለምሬት የዳረጉ ልማታችንንም የሚጎቱቱ መንግስታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በርካታ መሆናቸውን የደኢህዴን ማ/ኮሚቴ በቁጭት ገምግሙዋል፡፡ የእያንዳንዳችሁ ጥረት የሁላችንንም ውጤትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ በእያንዳንዱ ዕለት የምትሰጡት የተሳለጠ አገልግሎት በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ለራሳችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ የምትሠጡት አገልግሎት መሆኑን በመገንዘብ በአዲስ መንፈስ እና ቁርጠኝነት እንድትተጉ ደኢህዴን ጥሪውን ያቀርባላችዋል፡፡
በየደረጃው ለሚገኙ የህዝብና የሙያ አደረጃጀቶችና ማህበራት
በሃገራችን ባለፉት ሩብ ምዕተ አመታት በጀመርነው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ ግንባታ ሂደት የመደራጀትና ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብቶች ሕገመንግስታዊ ዋስትና አግኝተዋል፡፡ በርካታ አደረጃጀቶች ተፈጥረው የአባሎቻቸውን መብቶች ለማስከበር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ለማጎልበት የተግባር አውዶች ሆነው የማይናቅ ድርሻ መጫወታቸውን ማ/ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ ህገመንግስታዊ መሰረት መጣሉና ጅምር እንቅስቃሴው እየጎለበተ የመጣ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዴሞክራሲ ባህላችን አለመዳበር የመነጩ በርካታ ማነቆዎች እንዳሉም እንገነዘባለን፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለህዝባዊና የሙያ አደረጃጀቶች የነቃ ተሳትፎ የማይታሰብ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ የሚታዩትን ክፍተቶች በዝርዝርና በየደረጃው በመፈተሸ በናንተው የነቃ ተሳትፎ እየቀረፍን ለመሄድ ማእከላዊ ኮሚቴ አፅንኦት ሰጥቶ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በመሆኑም መላው የክልላችን የሙያና ህዝባዊ አደረጃጀቶችና ማህበራት የጋራ ክልላችንን በጋራ ጥረታችን ለመገንባት፤ የዴሞክራሲ ሥርዓታችንን በማጠናከር ለመጪው ትውልድ የተሻለች ክልልና ሃገር ለማቆየት በምናደርገው ርብርብ ከጎናችን እንድትቆሙ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡
በመላው አለም ለሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች
በየሄዳችሁበትና በምትኖሩበት አካባቢ ሁሉ የሚገጥሙዋችሁን ፈተናዎች በመቋቋም ራሳችሁን ለመለወጥ ባደረጋችሁት ጥረት ጥሪት እየቋጠራችሁ ልምድና እውቀት እያካበታችሁ ቤተሰቦቻችሁን ከመርዳት ባሻገር ባለፉት አመታት በተለያየ ደረጃ በጅምር ደረጃም ቢሆን እንደየአቅማችሁ በክልላችንና በሃገራችን ልማት በመሳተፍ የበኩላችሁን ጠጠር በመጣል ላበረከታችሁት አስታዋፅኦ ደኢህዴን ያለውን አክብሮት ይገልፃል፡፡ ለወደፊቱም ይህንን ጥረታችሁን በማሳደግ በኢንቨስትመንት፣ በማማከር ወይም በማስተማርና በቴክኖሎጂ ሽግግር የላቀ አስተዋፅኦ እንድታበረክቱ ደኢህዴን ጥሪውን ያቀርብላችሁዋል፡፡ በዚህ ረገድ የሚገጥሟችሁን እንቅፋቶች ለመቅረፍም ደኢህዴን ቁርጠኛ አቋም መውሰዱን እናረጋግጥላችኋለን፡፡
ለእህት እና አጋር ድርጅቶች
ባለፉት ሩብ ምዕተ አመታት የሃገራችንን የቁልቁለት ጉዞን በመግታት አንፃራዊ ሰላም ልማትና ዴሞክራሲ ለመገንባት በጋራ ተንቀሳቅሰናል፡፡ እየጎለበተ የመጣ ስኬትም አስመዝግበናል፡፡ ከተመዘገቡት ስኬቶች ባሻገርም ነባርና በተገቢው ደረጃ ያልተቀረፉ ችግሮች እንዲሁም ከስኬታችን ጋር የተያያዙ አዳዲስ ፈተናዎችም እያጋጠሙን መጥተናል፡፡ በየጊዜው የገጠሙንን ፈተናዎች እየተቋቋምን አንፃራዊ አቅማችንን በማጠናከር ተከታታይ ውጤቶችን እያስመዘገብን እንደመጣነው ሁሉ በቀጣይም የላቀ ጥረት በማድረግ እጥረቶቻችንን እየቀረፍን፣ የህዝቦቻችንን ተሳትፎ እያጎለበትን ልማታችንና ዴሞክራሲያችንን እያሰፋን የጀመርነውን ሁለንተናዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስና የጀመርነው ትግል ይበልጥ ፍሬ እንዲያፈራ በጋራ መንቀሳቀስ እንዳለብን እናምናለን፡፡ ድህነትና የዴሞክራሲ አለመዳበር ሰላማችንን እንደሚፈታተነው ሁሉ የሰላማችን መደፍረስን የተጀመሩትን ለውጦች የሚቀለብስና በሁላችንም ኪሳራና አገራዊ ጥፋት እንዲጠናቀቅ የሚያደርግ ፈተና ነው፡፡ የጎደለው ይሞላ ዘንድ በንቁ ተሳትፎና ትጋት ጥያቄዎችን እያቀረቡ ተጠያቂነትን ማረጋገጥና ለመፍትሄው በሃላፊነትና በሰከነ መንገድ መንቀሳቀስ የግድ ይላል፡፡ በመሆኑም ድርጅታችን በሁላችንም ዘንድ የሚታየውን ድክመቶቻችንን እያረምን የህዝቦቻችንን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበትና ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት እንደወትሮ ሁሉ በጋራ በጽናት እንድንቆም የደኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡
ለሀገሪቱ ህዝቦች
በብዝሀነት ላይ የተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ ሥርአታችን የየራሳችንን ጉዳይ በራሳችን በነጻነት እየወሰንን ሀገራዊ ትስስራችንን ይበልጥ እንድናጠናክር ዕድል የፈጠረ ነው፡፡ ብዝሃነታችንን መቀበልና ማክበር የአንድነታችን መሰረት እንጂ የመለያየት ምንጭና ሰበብ እንዳልሆነ በጽኑ እናምናለን፡፡ ይህንንም ባለፉት ሩብ ምዕተ አመታት በክልላችን በተግባር አረጋግጠናል፡፡
የደቡብ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ተወላጆች በመላው ሃገራችን ተሰራጭተው የሁሉም የሃገራችንን ህዝቦች እንደ ህዝባቸው ክልሎችንም እንደቤታቸው በመቁጠር ከጉልበት እስከ አዕምሮ ስራ ድረስ ተሸማርተው በታታሪነት በመሰማራት በስራቸውም ራሳቸውንና የሚኖሩባቸውን ክልሎች ልማትና ተጠቃሚነት በማሳለጥ ረገድ አወንታዊ ሚና ሲጫወቱ ኖረዋል፡፡ የክልላችን ተወላጆች በመላው ሃገራችን ክልሎች የመሰማራቸውን ያህል ክልላችንም የመላው ሃገራችን ህዝቦች ተወላጆች በነፃነት እንደቤታቸው የሚኖሩበትና ለመኖር የሚመርጡት ክልል ነው፡፡ ይኸው የመቻቻል ባህል አንድ የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ ማህበረሰብን ለመገንባት በተያያዝነው በብዝሀነት ላይ ለተመሰረተው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታን ለሃገራዊ አንድነታችን ጉልህ አብነት እንደሆነ ደኢህዴን ይገነዘባል፡፡ በሀገራችን በተገቢው ደረጃ ካልተቀረፉት የኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ችግሮች ጋር ተጣብቀው በአሁኑ ወቅት ብቅ ብቅ የሚሉት ጠባብነትና ትምክህት አብሮነታችንን መፈታተናቸውን አላቆሙም፡፡ በመሆኑም እነዚህ ችግሮች ለዘመናት ያቆያችሁትን አንድነታችሁንና መተሳሰራችሁን እንዳይሸረሽሩት ድርጅታችን ደኢህዴን አጥብቆ በመታገል የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን እንደሚቀጥል ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡ መላው የሀገራችን ህዝቦችም የቆየውንና አለም የመሰከረለትን አንድነታችሁንና ትስስራችሁን አጠናክራና አንዲት ኢትዮጵያን ለመገንባት የጀመራችሁትን ጥረት አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ደኢህዴን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡
ለተፎካካሪ ፓርቲዎች
ካለፉት ሩብ ምእተ አመታት ጀምሮ በሃገራችን በተጀመረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ጋር ተያይዞ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለማዳበር እየወደቅን እየተነሳን መጥተናል፡፡ በሂደቱም የራሱ አወንታዊ ፋይዳ ያለው ልምድ እየቀሰምን አንፃራዊ አቅም ፈጥረናል፡፡ በሂደቱ የተገኘውን ልምድ እጥረትና ስኬት እየፈተሽን አሰራሮቻችንን ለማሻሻልም ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ጥረቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው በድርጅታችንም ሆነ ድርጅታችን በሚመራው መንግስት እንዲሁም በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ መሻሻል የሚገባቸው ከዴሞክራሲ ባህል አለመዳበር ጋር የተሳሰሩ ቀላል የማይባሉ ጉድለቶች መኖራቸውን ማእከላዊ ኮሚቴያችን ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም በሚያለያዩን ጉዳዮች ዙርያ ልዩነቶቻችንን በማንጠር በሰለጠነ መንገድ ለመተጋገል፣ በሚያግባቡን ክልላዊና ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተመካከርንና እየተባበርን በመንቀሳቀስ በምክንያት የሚቃወምና በምክንያት የሚደግፍ ትውልድ በማነፅ በሃገራችን የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል እንዲገነባ ደኢህዴን ዝርዝር ግምገማ በማድረግ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በሰለጠነ መንገድ ለመተባበርና ለመተጋገል በሃላፊነት መንፈስ በመንቀሳቀስ የድርሻቸሁን እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።