የትም ፍጭው ሰላሙን አምጭው

11 Mar 2018

ሕገ መንግሥቱንና ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን፣ የአገርን አድነትና ሠላም ለማስጠበቅና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን አፋጥኖ አገራዊ ልማትን በማጠናከር ፀረ ድህነት ትግሉን በውጤታማነት ለማስቀጠል የሚያስችል ለሁሉም አገራት የሚሠራ የተሻለ ነው የሚባል አንድ አይነት ዘዴ የለም። ለአሜሪካ የሚሠራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለእኛ ላይሠራ ይችላል። አውስትራሊያና ካናዳ አንድነታቸውን የጠበቁበት ዘዴ ለእኛ ላይሆን ይችላል። ቻይና ያደገችበት የልማት ቅደም ተከተል ለእኛ ሂደት ላይገጥም ይችላል። እነሱም የራሳቸውን ዘዴ ይዘው ይቀጥላሉ። እኛም የሚጠቅመንንና በተጨባጭ ከፊታችን ለተደቀኑ ችግሮቻችን መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ዘዴዎችን መምረጥ ይጠበቅብናል።
ለአንድ ተመሳሳይ ችግር እንኳ አንድ ዘዴ ብቻ ሁልጊዜ ይሠራል ማለት አይቻልም። ለትናንቱ የፀጥታ ችግር መፍትሄ የተጠቀምንበት ዘዴ ለዛሬው የፀጥታ ችግራችን መፍትሄ ይሆናል ማለት አይደለም። እንደ ችግሩ መጠን፣ /ስፋት/ ጥንካሬና አስጊነት ችግሩ ከተከተላቸው አዳዲስ ዘዴዎች /ታክቲኮች/... ወዘተ አንፃር የእኛም የመፍትሄ ዘዴ በሚመጥን ደረጃ መቃኘት አለበት።
ካለፈው ሂደታችን የተገኙትን ልምዶች ቀምረን ለአሁኑ ችግር በሚሆን ሁኔታ መጠቀም መቻል አለብን። ወደ እኛ ጉዳይ ስንመጣ በሕገመንግሥቱና በሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ በአገራችን አንድነትና ሰላም ላይ፣ በሕዝቦች የዕለት ተዕለት ኑሮ፣ የመንቀሳቀስ ነፃነት ላይ የተደቀኑብንና ብሔርን/ዘርን/ ማዕከል አድርገው በሚንቀሳቀሱ በታኝ አመፆች ላይ የምንወስደው ርምጃ ይህንኑ ችግር በሚፈታ ደረጃ መሆን አለበት።
ለዚህ ችግር በርካታ መፍትሄዎች ቢኖሩም ችግሩን ባለበት ለማቆም ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንዱ ነው። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም ዓርብ የአድዋ ዕለት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ያፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአገራችን ጊዜያዊ ሁኔታ ለሚጠይቀው ጥያቄ ተመጣጣኝና ተገቢ መፍትሄ ነው። አዋጁ በፖለቲከኞችና በሕዝቦች ዘንድ እኩል አተያይ የለውም። ፖለቲከኞቹ አዋጁ አያስፈልግም ወይም መፍትሄው የበለጠ ዴሞክራሲ መስጠት እንጂ ማጥበብ አይደለም። የሚሉ ይበዛባቸዋል። ሕዝቦች ደግሞ አዋጁ የግድ ያስፈልገናል፤ ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ መብላት፣ ደክሞ መተኛት፣ የልጆቻችን ትምህርት ተስተጓጉሎብናል መፍትሔው አዋጅ ነው ብለው ያምናሉ።
አዋጁ መጽደቅ ያለበት መሆኑን የምናምን ዜጐች ደግሞ « አይፀድቅ ይሆን?» የሚል ስጋት ውስጥ ነው የከረምነው። የፓርላማ አባላት ለአዋጁ መጽደቅ ድምጽ እንዳይሰጡ ወይም አዋጁን እንዳይደግፉ በማኅበራዊ ድረ ገፆችና በስልክ ጭምር ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያዎች ሲረጩ ሰንብተዋል። በፓርላማ አባላት ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ፣ ቤት ንብረታቸው ላይ አደጋ እንደሚጥሉ ሲዝቱና ሲያሸማቅቁ ከርመዋል። አዋጁ የፀደቀው ይህን ሁሉ ፈተና አልፎ ነው። በእርግጥ በፓርላማው ውስጥ ከዚህ በፊት በነበሩት ዓመታት ሂደት ባልታየ መጠን 88 ተቃውሞዎችን አስተናግዷል። ብዙ ነው።
ተቃውሞው የነውጠኞቹ ማስፈራሪያና ዛቻ ይሁን ወይም በፓርላማው ውስጥ ያለው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና የአባላቱ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አጠቃቀም እድገት አሳይቶ ይሆን? በአዋቂዎች መጠናት ሊኖርበት ይችላል። መከራከሩ ጥሩ ነው። መቃወሙም ጥሩ ነው። ተቃውሞው ግን ብሔር ተኮር ሳይሆን መርህ ተኮር መሆን አለበት። በአንድ ብሔር ወገንተኝነት አካሄድ አገር ሲታመስ የከረመው አንሶ አሁን ፓርላማ እስከመግባትና እስከ ማመስ ድረስ እንዲዘልቅ ፊት ሊሰጠው አይገባም። አሁን የምንመራበትን ስልት አውቀናል። እስከጊዜው ድረስ (ቢያንስ ለ6 ወር) የምንመራው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሆኑን አረጋግጠናል።
የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ ክብደትና ቅለት፣ ርዝመትና እጥረት የሚወሰነው በእኛው የውስጥ ሁኔታ አይነት ነው። ሰላምና ፀጥታ ከሰፈነ ሊያዋጣን ይችላል። ይህ ካልሆነ ግን ኮማንድ ፖስት ማንኛውንም ርምጃ ይወስዳል። ከኢሰብአዊነት በመለሰ የሚያግደው የለም። ከዚያም ከባሰ አገሪቱ ወደ ወታደራዊ አስተዳደር የማትሸጋገርበት ምክንያት አይኖርም። የትም ፍጭው ሰላሙን አምጭው! የባሰ እንዳይመጣ እንፀልይ! ሰላማችንን በጋራ እናረጋግጥ።
በቀጣይ የሚነሳው ጉዳይ «ማን ይምራን?» የሚለው ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በቀር የሕዝቡ ጥያቄ የመሪ ማንነት ጥያቄ አይደለም። ማንም ይምራ ማን የሕዝቡ ችግር አይደለም። አቶ ኃይለማርያም የተነሱት በሕዝብ ጥያቄ አይደለም። ንፁህና የታረሙ ምሁር መሪ መሆናቸውን ሕዝቡ ያውቃል፤ ያምናል። የሕዝቡ ጥያቄ የዕለት ተዕለት ኑሮው ነው። ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ ሥራ፣ የልጆች ዋስትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ነው። ችግሩ አንዱ በይ! ሌላውን ተመልካች ያደረገው ሥርዓት ነው።
ሕዝቡ የሚፈልገው የሥርዓት ለውጥ እንጂ የግለሰቦች መቀያየርን አይደለም። የሚመራን ሰው ይህን የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት የሚችል መሆን አለበት። «እየሠራን እንታደሳለን። እየታደስን እንሠራለን» ማለት እዚያው በዚያው እንደ ፕላስቲክ ጣሳ እየተገላበጥን (ሪሳይክል እያደረግን) እንቀጥላለን ማለት አያዋጣም። ጠጋ ብሎ ላስተዋለው ሕዝቡን ካንገሸገሹት አማርኛዎች ዋነኞቹ «ተሀድሶ፣ ስልጠና፣ ግምገማ፣ ስብሰባ... ምናምን ወዘተ» የሚሉት ናቸው። 25 ዓመት ሙሉ ተሀድሶ፣ ሥልጠና፣ ግምገማ... ለሕዝብ ያስገኘለት ተጨባጭ ጠቀሜታ ምንድን ነው? ምንም! እዚያው እርስ በርስ ለመጠቃቀምና ለዕድገት መወጣጫ እንዲሆን እገሌ ሥልጠና ወስዷል፤ እገሌ ተሀድሶ ገብቷል፤ እያሉ እርስበርሳቸው ከፍ ዝቅ ሊደራረጉበት ካልሆነ በቀር ለሕዝብ ያስገኘው ፋይዳ የለም።
በየጊዜው «ለከፍተኛ አመራሮች፣ ለመካከለኛ አመራሮች፣ ለፈፃሚዎች... እየተባለ የሀገር ሀብት ከማሟጠጥ በስተቀር ለሕዝብ ያስገኘው ለውጥ የለም። በየጊዜው የሚካሄደው ተሀድሶ፣ ስልጠናና፣ ስብሰባ በማን ገንዘብ ? በማን ኪሳራ? በማን ወጪ? ነው። ትራንስፖርት፣ አልጋው፣ ሆቴሉ የውሎ አበሉ... ደሃው ሕዝብ መቀነቱን እየፈታ ከሚከፍለው ግብር ላይ የሚወጣ መሆኑ የታወቀ ነው። ይህ ወጪ ለሌላ ሕዝባዊ ጠቀሜታ መዋል አለበት። ይህም ቢሆን አረረም መረረም አንድ መሪ መኖር አለበት። የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ይሄን ያህል የሚመኙት ነገር አይደለም። እሾህ ላይ መቀመጥ ነው! እሳት ላይ መጣድ ነው! ይሁን እንጂ «እሆናለሁ» ያለ ሰው መወዳደር ይችላል።
አሁን ለጊዜው ተለይተው የታወቁ ሦስት ሰዎች አሉ። አብይ አህመድ፣ ደመቀ መኮንን፣ ሽፈራው ሹጉጤ! ሌላ ሰው ከውጭ አምጥቶ መሾም አይቻልም። በሕገመንግሥቱ ዝግ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል ይመረጣል! የምክር ቤት አባል ያልሆነ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን እድል የለውም። የኢህአዴግ ነገር አይታወቅም ሌላ ያልተጠበቀ ሰው ካላመጣብን በቀር ለጊዜው ያሉት ሦስቱ ናቸው።
ማን ይመረጥ ይሆን? አደገኛ ጥያቄ ነው! ጠንቃቃ ምላሽ የሚፈልግ ጥያቄ ነው። ኦሮሚያ ወንበሩን ለመያዝ ቆርጦ ተነስቷል። አሁን ጊዜው የእኔ ነው። እያለ ነው። ቄሮ ከጐጉ ነው። ከመደበኛው የሕግ ማስከበር አግባብ በላይ የሆነ ቡድን ነው። አብይ ተመረጠ ማለት ሦስቱም ሥልጣኖች ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አፈጉባዔ፣ ፕሬዚዳንት በኦሮሚያ መያዙ ነው። የሚያስኬድ አይመስልም። የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ለማግኘት ሲባል ፕሬዚዳንቱ በፈቃዳቸው ሥልጣን እንዲለቁ ማድረግ ወይም አባዱላ ከዚህ በፊት ያስገቡትን የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ አቧራውን አራግፈን ስናጠናው ቆይተናል፣ውሳኔ ላይ ደርሰናል። በጥያቄያቸው መሠረት ይልቀቁ ብለናል ማለት ይቻላል። ማንኛውም ግለሰብ የትኛውም ብሔራዊ ድርጅት ወክሎ ቀርቦ ቢመረጥ አይከፋንም፦
* የሚመረጠው ሰው ግን አገራችን የሚያስፈልጋት በራሷ ባህልና ታሪክ ላይ የተመሠረተ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት እንጂ ከየሀገሩ ተለቃቅሞ እንደተፈለገ ተተርጉሞ በተጫነብን ሰነድ አማካይነት የሚንቀሳቀስ ግዑዝ አሠራር አለመሆኑን የተገነዘበ መሆን አለበት።
* የሚመረጠው ሰው ሕዝባችንን ዛሬ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ በድሮው ዘዴ መምራትና ማስተዳደር የማይቻል መሆኑን የተገነዘበ መሆን አለበት።
* የሚመረጠው ሰው ሕዝቡ እስከአሁን መንግሥት ላይ እምነት ያጣ መሆኑን ተረድቶ ሕዝብና መንግሥት የሚተማመኑበትን ሥርዓት ለመዘርጋት ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆን አለበት።
* የሚመረጠው የአገሪቱ ችግር የዘዴ /ሜቶዶሎጂ/ የአስተዳደራዊ አሰራር ጉድለት፣ የቴክኒክ ችግር ሳይሆን የመሠረታዊ መርሆዎች ችግር መሆኑን ያጤነ መሆን አለበት። ችግራችን የሥርዓት ችግር ነው፤ የቴክኒክ አይደለም። አዲስ አቅጣጫ መቀመጥ አለበት።
* የሚመረጠው ሰው ልበ ሙሉ፣ ደፋርና ቆራጥ መሆን አለበት። «አይነኬ» ሆነው ያሉትን «እንደራደርባ ቸውም» የሚባሉትን ጉዳዮች እንደገና መመርመር መቻል አለበት። ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ የሚሻሻሉ አንቀፆች ወይም አገላለፆች ካሉ የአዋቂዎች ቡድን /ኮሚሽን/ ተቋቁሞ እንዲመረምር እድል ይሰጠው። የፌዴራሊዝም ሥርዓት በሕዝቦች አንድነት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ካለም ይመርመር፤ ይታይ፤ ይፈተሽ። እንደ ፀረ ሽብር ያሉ አንዳንድ ሕጐችም ይታዩ። ሁሉም ዓለም የሚጠቀምበት ነው አትበሉን። ለእኛ እንዲሆን በልካችን ይሰፋልን!
* የሚመረጠው የአገሪቱ ሕዝብ አገሪቱ ከምታመነጨው ገቢ እኩል ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መቻል አለበት። የመሬቱም ሆነ የልማቱ ተጠቃሚነት በፍትሐዊነት ሊከበር እንዲችል መሥራት አለበት። አንዱ ተጠቃሚ ሌላው ለቃቃሚ የሚሆንበት ሥርዓት መታረም አለበት። ዋናው ነገር ግን ሰላም ነው። የትም ፍጭው ሰላሙን አምጭው።

ግርማ ለማ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።