ሶርያን ያየ በሰላም አይቀልድም

12 Mar 2018

ኢትዮጵያ ቀደምት ገናና ታሪክ ካላቸው የዓለም ሃገራት አንዷ መሆኗ ዓለም የመሰከረው እውነታ ነው፡፡ ለዚህም እስከዛሬ ድረስ ህያው ምስክርነታቸውን በመስጠት ላይ የሚገኙትን የአክሱም ሃውልት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት፣ የፋሲል ግንብ፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ ሶፍኡዑመር ዋሻ፣ የጀጎል ግንብ፣ ድሬ ሼህ ሁሴን መስጊድ እና ሌሎች በርካታ ቅርሶችን ማንሳት ይቻላል፡፡
እነዚህ የኋላ ታሪኮቻችን የሚነግሩን በርካታ ሚስጢርም አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ የታሪክ አሻራዎች እንዲህ አይነት ከፍተኛ ጥበብና እውቀት የሚጠይቅ ስራ እንዴት በዚያ ዘመን ሊሰራ ቻለ የሚል ጥያቄን እስከማጫር የደረሰ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ አሁንም ድረስ ሚስጥር እንደሆኑ የቀጠሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የአክሱምን ታሪክ ስንመለከት በዘመኑ ከነበረው የዓለም ስልጣኔ አንጻር እንዲህ አይነት ጥራት ያለውና አሁን በደረስንበት የቴክኖሎጂ ዘመን እንኳን ሊሰራ የሚከብድ ስራ እንዴት በወቅቱ ተሰራ የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሰራው የላሊበላ ውቅር ቤተ ክርስቲያን ጥበብም እንዲሁ አሁንም ድረስ የማይሞከሩ የኋላ ታሪኮቻን ነፀብራቆች ናቸው፡፡
እነዚህ የታሪክ ድርሳናትን ስንመለከት ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ምን ያህል በስልጣኔ ልቃ እንደሄደች የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህ ታሪኮቻችን ደግሞ ዛሬ ላይ የሞራል ስንቅና የጥንካሬ ምንጭ ሊሆኑን ይገባል፡፡ እንዲህ አይነት ስልጣኔ ላይ ደርሳ የነበረችው አገራችን ዛሬ ምን ላይ ነው ያለችው? ለምንስ ወደ ኋላ ተመለስን? እኛስ ከነሱ ምን እንማራለን የሚለው የየዕለት ጥያቄያችን ሊሆን ይገባል፡፡
አሁን ላይ የሰለጠኑ የምንላቸው በርካታ የአውሮፓና አሜሪካ ሃገራት እንዲህ አይነት የኋላ ታሪክ የሚጎድላቸው የታሪክ ድሆች ናቸው፡፡ እናም እንዲህ አይነት አንጻባራቂ የኋላ ታሪክ ባለቤቶች እንዲኖሩ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ከኋላ ታሪክ ይልቅ አሁን ላይ የደረሱበትን ደረጃ በማጉላት ታሪክ ተደብቆ እንዲኖር ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
እናም ሃገራችንን ከማሳደግና ከማልማት ጎን ለጎን የቀደመውን ታሪካችንን ጠብቀን ለትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት የኛ የኢትዮጵያውያን መሆን አለበት፡፡ በአንዳንድ አገሮች እንደተፈጠረው አይነት ታሪክን የማጥፋት ዘመቻ እንዳይከፈት ብርቱ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ ቀደምት ታሪክ ያላቸውን አንዳንድ ሃገራት ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ታሪካቸው እየጠፋ ያለበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ኢራቅ በርካታ ጥንታዊ ታሪክ ካላቸው የዓለም ሃገራት አንዷ ነበረች፡‹ ያም ሆኖ ግን አይ.ኤስ.አይ.ኤስ. በተሰኘ አሸባሪ ቡድን ይህ ታሪክ እየታደነ እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡ ከአንድ ሺህ በላይ አመታትን ያስቆጠረችውን የሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆንም ስንመለከት ይህ ታሪካዊ አሻራ ዛሬ ወደ ፍርስራሽ ቆሻሻ እየተለወጠ ነው፡፡ ሌሎች ጥንታዊ አሻራ ያረፈባቸው የአለም ሃገራትም በተመሳሳይ በጦርነት ምክንያት ይህ ቀደምት ማንነታቸው እየወደመ ይገኛል፡፡
ዛሬ ያለውን የሃገራችንን ነባራዊ ሁኔታም ስንመለከት ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ አንዳንድ ክስተቶችን እንመለከታለን፡፡ የምንሄድበት እንዳይጠፋን የመጣንበትን መርሳት የለብንም፡፡ ምክንያቱም እኛ በአንድ ወቅት ገናና ታሪክ የነበረን ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ምክንያቶቹ በውል በማይታወቁ ክስተቶች ወደ ኋላ የተመለስንና የኋልዮሽ ጉዞኣችንን ያፈጠንበት ወቅት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እነዚያ ደማቅና ጊዜ የማይሽራቸውን የታሪክ ቅርሶች ትተው ያለፉ የዘር ሃረጎቻችን ኢትዮጵያ ወደኋላ ተመልሳ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ የረሃብ ተምሳሌት ተደርገን በመዝገበ ቃላት ጭምር እንደማሳያ ስማችን መስፈሩን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን?
እነሆ ያም አልፎ ደግሞ አሁን ላይ በዚያ ቁጭት ተነስተን ድህትን ታሪክ ለማድረግ በተነሳንበትና በዓለም ማህበረሰብ ዘንድም አንገታችንን ቀና አድርገን መራመድና መናገር በጀመርንበት ወቅት ሃገራችንን ለማበጣበጥና የማያባራ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ለማስገባት በር የሚከፍቱ እና የሚደረጉ ጥረቶች እንዴት ይታያሉ? እውን እንዲህ አይነት ግጭቶችና አልፎ አልፎ እየታዩ ያሉ ድርጊቶችስ ወዴት ይወስዱናል?
እንደ መታደል ሆኖ ሃገራችን ሰፊ የማደግ እድል ያላት ሃገር ናት፡፡ አብዛኛው ህዝቧ ወጣት መሆኑ ሰርቶ ሃገርን ለመለወጥ የሚያስችል አቅም እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የህዝብ ቁጥራችንም ቢሆን ቀላል አይደለም፡፡ ከዓለም በ12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ህዝባችን ለልማት ትልቅ አቅም ነው፡፡ የሃገራችን የመሬት አቀማመጥና የቆዳ ስፋት፣ እንዲሁም መልካ ምድራዊ አቀማመጣችንና ያለን የተፈጥሮ ሃብትም ሃገራችንን ወደቀደመው ስልጣኔ ለመለወጥ የሚያስችል እድል ነው፡፡ ዛሬ ላይ የሚያስፈልገን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ በአንድ ልብ ሆነን ድህነትን ለማሸነፍና ሃገራችንን ለመለወጥ በቁርጠንነት መነሳት፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ በርካታ ፈተናዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የእድገት ጎዳና የማይፈልጉ በርካታ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ሃይሎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ በሃገራችን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችና የህዝብ ቅሬታዎችን መነሻ በማድረግ በዚህ ቀዳዳ ሾልከው በመግባት በተለይ ወጣቱን ሃይል መጠቀሚያ ለማድረግ ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የግጭት መነሳት ለአንዳንዶቹ ሰርግና ምላሽ ይሆንላቸዋል፡፡
በቅርቡ በተለያዩ የማህበራዊ ድረገጾች የምሰማውን አንዳንድ ጉዳዮች በዚህ አጋጣሚ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ አሁን በሃገራችን በተለያየ መንገድ ቅሬታውን እያቀረበ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ቅሬታው መቅረቡ መንግስት ችግሩን ተገንዝቦ እንዲስተካክል ለማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሰለጠኑትና በኢኮኖሚያዊ እድገታቸውም ከጫፍ ላይ ባሉት ሃገራት ጭምር የተለመደ ነው፡፡ በአሜሪካም ሆነ በሩስያ ወይም በሌሎች የአውሮፓ ሃገራት የህዝብ ቅሬታ የማይሰማበት የዓለም ክፍል አለመኖሩ ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል ይህ በኢትዮጵያ እየቀረበ ያለው ቅሬታ ደግሞ ልማትን ከመፈለግ እንጂ ጥፋትን ከመሻት እንዳልሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ያም ሆኖ ግን አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች በጅምር ላይ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ ወደኋላ የሚመልስ ድርጊት ታይቷል፡፡ ይህ መወገዝ ያለበትና እኛነታቻንን የማይገልጽ ተግባር ነው፡፡ ልማት የሚጠይቅ ዜጋ ልማትን አያወድምም፡፡
በሃገራችን የተፈጠረውን ይህንን ጊዜያዊ የህዝብ ቅሬታ መነሻ በማድረግ ግጭት እንዲፈጠርና ወደ ለየለት የርስ በርስ ግጭትና ወደማያባራ ጦርነት እንዲገባ ፍላጎት ያላቸው አካላት መኖራቸውን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ለዚህም አሁን አሁን ጥቂት ችግሮች ሲፈጠሩ በተፈጠረው ችግር ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ክብሪት የሚጭሩ አካላት መኖራቸው ማሳያ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ እነዚህ አካላት ራሳቸው የሚነደው እሳት እንዳይነካቸው ምቹ ቦታ ላይ ተቀምጠው እንደፈሪ አዋጊ ከርቀት በማህበራዊ ሚዲያውና በተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች አማካይነት ‹‹ግፋ በለው›› የሚል ነጋሪት ይጎስማሉ፡፡
አሁን አሁን በማህበራዊ ሚዲያው የሚለቀቁ አንዳንድ መረጃዎችን ስንመለከት እነዚህ አካላት ምን ያህል ኢትዮጵያን ለማበጣበጥ ተግተው እየሰሩ መሆኑን ማሳያ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያን በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል ህዝቦቿ ርስ በርስ እንዳይተማመኑና እንዳይቀራረቡ ከዚያም አልፎ የርስ በርስ ወደመጠራጠርና ከዚያም ከፍ ሲል ወደ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እነዚህ አካላት ልጆቻቸውንም ሆነ የቅርብ ዘመዶቻቸውን በአሜሪካና በአውሮፓ በማሸሽ እዚህ የጦርነት ቀጣና ለመፍጠር የሚሞክሩ ናቸው፡፡ አቀራረባቸውም ተቆርቋሪ በመምሰልና አንዱ በሌላ እየተበደለ እንደሆነ በማቅረብ እና ሆድ እንዲብሰው በማድረግ የሚሰራ ሴራ ነው፡፡ በሃገራችን አንድ አባባል አለ፡፡ ሃገራችን ውስጥ የርስ በርስ ችግሮች ቢፈጠሩ ተጎጂውም ሆነ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እኛው እዚሁ የምንኖር ዜጎች ነን፡፡ እነዚህ ‹‹ግፋ በለው›› የሚሉ የፌስ ቡክ አርበኞች ሁል ጊዜ ከውጭ ሆነው ከማበጣበጥ በዘለለ አንዳችም የሚፈይዱት ነገር አይኖርም፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን መረዳት ያለብን አንድ መሰረታዊ ጉዳይ አለ፡፡ ይህም ሰላም ምንያል አስፈላጊያችን እንደሆነ ነው፡፡ አሁን ሃላፊነት የሚሰማው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ የሚያስብበት ወቅት ነው፡፡ አዕምሮኣችንንም በአግባቡ መጠቀም የሚያስፈልገን አሁን ነው፡፡
ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ በሃገራችን የተፈጠረውን ችግር እልባት ለመስጠት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ የሚያሰላስልበትና ለሃገሩ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡ እያንዳንዳችንም ሁለት ምርጫዎች ቀርበውልናል፡፡ አንድም የምናነሳቸውን ጥያቄዎች በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ በማንሳት ሰላማዊ የትግል አቅጣጫን መከተል አልያም የተበታተነችና የጦርነት ቀጣና የሆነች አገር መፍጠር፡፡ ከዚህ አንፃር ማንም ሰላም ወዳድ ዜጋ ሁሉ ሁለተኛውን አማራጭ ይመርጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሃገሩ እንድታድግና የቀድሞ ገናና ታሪኳ ተመልሶ የተከበረችና የበለፀገች ሃገር ባለቤት መሆን ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሰከነና በበሰለ አእምሮ ሃገራችንን ማዳን ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡
እኛ ኢትዮጵዊያን በራሳችን አእምሮ የምናመዛዝንበት የጥሞና ጊዜ ሊኖረን ይገባል፡፡ የተሟላ አዕምሮ ባለቤቶች እስከሆንን ድረስ ለምን የሌሎችን ቅስቀሳና አውቅልሃለሁ የሚል ፕሮፖጋንዳ እንከተላለን፡፡ የሃገር መበታተን የሚመቻቸው ጥቂት አካላት ይኖራሉ፡፡ እነዚህ አካላት አንድም በግርግሩ መነሻነት የሌላውን ሃብትና ንብረት ለመዝረፍ ቋምጠው የሚጠብቁ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት በላባቸውና በጉልበታቸው ሰርተው ከመኖር ይልቅ ዘርፈው ለመኖር ፍላጎት ያላቸውና በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ስለሌላው ወይም ስለሃገር ግድ የሌላቸው ናቸው፡፡
ሁለተኛውና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት ደግሞ በውጭ የሚኖሩት እና በተለያየ ምክንያት ከሃገር ወጥተው በውጭ የተደላደለ ኑሮ የሚኖሩ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት አንድም ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› እንዳለችው እንስሳ እኔ ከሌለሁ ምን አገባኝ በሚል ስሜት ሆን ብለው የጥላቻ ፖለቲካን እያራመዱ በሃገሪቷ ውስጥ ብጥብጥ እንዲፈጠር ፍላጎት ያላቸው ሲሆን በሌላም በኩል ደግሞ ለሃገሪቷና ሃገሪቷን ለሚመራው መንግስት ባላቸው ከፍተኛ ጥላቻ ምክንያት ሆን ብለው ሃገርን በማበጣበጥ ከዳር ቆመው የሚነደውን እሳት ለመሞቅ የተዘጋጁ ናቸው፡፡
እነዚህ አካላት በዚህ አጋጣሚ ምናልባት ሃገር ስትበታተን ‹‹እኔም ቀዳዳ ከተገኘ ገብቼ ልፈተፍት እችላሁ›› የሚል ቀቢፀ ተስፋ ያላቸውና ራስ ወዳዶች በመሆናቸው ራሳቸውንና ራሳቸውን ብቻ ማየት የሚችሉ ናቸው፡፡
ሌላው አካል ደግሞ ችግሩ ሳይገባው ተጃምሎ የሚሄድ ነው፡፡ በሃገራችን የዚህ አይነት ችግር ውስጥ የሚገቡ አካላት በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአንድ በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ የሚካሄድ ሰልፍ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች መካከል ጥቂት ናሙና ወስደን ለምን ሰልፍ እንደወጡና ለዚህ ድርጊት ሃላፊነቱን ምን እንደሚወስድ፣ ምናልባት የሰልፉ ውጤት ቢያስገኝ ምን እንደሚፈጠር እንዲሁም በትክክል ከማን ምን እንደሚጠብቁ ቢጠየቁ ብዙም ግንዛቤው የሌላቸው ይበዛሉ የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ በኛ ሃገር ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም በእውቀት ላይ የተመሰረተ መነሻ ሃሳብ ይዞ ከሚንቀሳቀሰው ይልቅ ሌሎች ስላደረጉት ብቻ አብሮ የሚጓዝ አጃቢ እየበዛ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡
እኛ በርካታ ሃላፊነትና የቤት ስራ ያለብን ዜጎች ነን፡፡ ገና ያልንሰራነውና ለዘመናት ሲደማመር የመጣ ድህነት የሚባል ታሪካዊ ጠላት ያለብን ዜጎች ነን፡፡ ይህ ጠላት ደግሞ እንኳንስ ርስ በርስ ተከፋፍለንና ያለንን ጥቂት ልማት እያወደምን ቀርቶ ሰርተንም ብዙ ጥረትና ልፋትን የሚጠይቅ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ለዘመናት በላያችን ላይ ከተጫነው ከዚህ የድህነት በሽታ ለመላቀቅ መድሃኒቱ ጠንክሮ መስራት ብቻ ነው፡፡ ለዚያውም ከጀመርነው ፍጥነት በላይ በፍጥነት መጓዝ፡፡ እናም ከዚህ አንፃር ቆም ብሎ ማሰብ ይጠበቅብናል፡፡
ከዚህም ባሻገር ብልህ ከሌላው ስህተት ይማራል እንደሚባለው እኛ ርስ በርስ ግጭት ሳቢያ መከራና ፈተና ከበዛባቸው የአረብ አገራት በርካታ ቁምነገሮችን ልንማር ይገባል፡፡ ለምሳሌ የሶርያን ነባራዊ ሁኔታ ያየ የርስ በርስ ግጭት ምን ያህል አስከፊና አስፈሪ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ ይወስድበታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የዚች አገር ህዝቦች በአንድ ወቅት ከኛ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኙ እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ ህዝቦቻቸውም ቢሆኑ ሰላማዊና የጥይት ጩኸት የማያውቁ፣ ህፃናትም ጨዋታና ደስታ እንጂ ጦርነት ማለት ምን ማለት እንኳ በቅጡ የማይገነዘቡባት አገር ነበረች፡፡ ያ ግን አሁን ላይ ታሪክ ሆኗል፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት የምናየው የዚያች አገር ህዝቦች ስቃይ ከማሳዘን አልፎ በየቤቱ ስንቶችን ያስለቀሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ኢራቅ፣ ሊብያ፣ የመንና ደቡብ ሱዳንንም ያየ ሁሉ የዚህ አይነት ስሜት ሊሰማው ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ አገራት በአንድ ወቅት በሰላም ወጥተው በሰላም የሚገቡ ህዝቦች ባለቤት ነበሩ፡፡ ልጆቻቸውም ቢሆኑ በሰላም ወደ ትምህርት ገብተው የሚሄዱባቸውና በሰላም ከትምህርት ቤት ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚጫወቱባቸው ሰላማዊ አገሮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ጥቂት አጋጣሚዎችና ማስተዋል የጎደለው ህሊና ባስከተለባቸው የርስ ብርስ ግጭት ውስጥ በመግባት ለዜጎቻቸው ሲኦል እየሆኑ ናቸው፡፡ እናም ከዚህ አይነቱ ችግር ለመውጣት ቆም ብሎ ማሰብና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታ መሞከር ደግሞ ከመላው ህብረተሰብና ከመንግስት የሚጠበቁ ቁም ነገሮች ናቸው፡፡
ስለዚህ በአንድ በኩል መንግስት ህዝብ ለሚነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ህዝብን የማረጋጋት ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ህብረተሰቡም ደግሞ ለሚነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እስከሚገኝ ትዕግስት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሮም በአንድ ምሽት አልተገነባችም እንደሚባለው መንግስት ችግሮቹን ለማስተካከል ጊዜ መፈለጉ ትክክልም፣እውነትም በመሆኑ ህብረተሰቡ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ሌላውና ዋናው ጉዳይ ደግሞ ልማትን እያወደሙ ልማትን መጠየቅ የሚቃረኑ ተግባራት ናቸውና ከዚህ መቆጠብ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ባህላችንም ሆነ ማህበራዊ አኗኟራችን ርስ በርስ እንድንከባበርና እንድንተሳሰብ እድል የፈጠረልን በመሆኑ ይህንን ጥሩ ባህልና ማህበራዊ ልማድ ይዘን አዕምሮኣችንን ይበልጥ ለመልካም ነገር ልናውለው እችላለን፡፡ ከዚህ በተፃራሪው ግን ሌሎች እጃችንን ይዘው እንዳይዘውሩን መጠንቀቅ ይጠበቅብናል፡፡

ወርቁ ማሩ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።