ተቀጽላውን ቆርጣችሁ ጣሉ!

13 Mar 2018

የኢህአዴግን አበቃቀልና የአስተዳደግ ባህል በአጽዕኖት ለተመለከተው፣ ኢህአዴግ ጸረ-ህዝብና ጸረ-ዴሞክራሲያዊ ሊሆን የሚችል ፓርቲ አይደለም። ምክንያቱም ኢህአዴግ የወለደው ጭቆና እና ብሶት ነው። ኢህአዴግ መሰረተ ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ ያለው ፓርቲ ነው። በእኛ፣ ከእኛ፣ ለእኛ የሆነ ፓርቲ በመሆኑ ነው። እውነት እውነቱን እንነጋገር ካልን ኢህአዴግ ለአገራችንና ለህዝብ የለውጥ መሰረት አልሆነምን? ኢትዮጵያ ማስመዝገብ ለቻለቻቸው ዘርፈ ብዙ ስኬቶች መሃንዲስ ኢህአዴግ አይደለምን? በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲፈነጥቅ ፊት አውራሪ አልነበረምን? ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸው እንዲኮሩና ራሳቸውን እንዲቀበሉ እንዲሁም ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የማይተካ ሚና አልተጫወተምን? በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የኢህአዴግ አስተዋጽዖ ወሳኝ አልነበረምን? ኢህአዴግ በዓለም ዓቀፉ መድረክ አገራችን አዲስ ገጽታ እንድትላበስ አላደረገምን?
በእርግጥ በአገራችን በርካታ ችግሮች አሉ። ሁሉም ችግሮች ግን በኢህአዴግ የተከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አይደሉም። ኢህአዴግ በራሱ የፈጠራቸው ችግሮችም ቀላል የሚባሉ እንዳልሆኑ እስማማለሁ። ይሁንና ለሁሉም ችግሮች ግን ምንጩ ኢህአዴግ እንዳልሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። አንዳንድ ግለሰቦች የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ሁሉንም ችግሮች ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ጋር ለማስተሳሰርና ኢህአዴግን ለማሳጣት የሚያደርጉትን ሩጫ ስመለከት አፍራለሁ። በመንግስት የአቅም እጦት መንገድ ያልተዘረጋላቸው ወይም ውሃና ኤሌክትሪክ ያልቀረበላቸው አካባቢዎች የመልካም አስተዳደር ችግር ተደርጎ መወሰድ የለበትም ባይ ነኝ።
ለአገራችን የሚበጃት ሁሉንም ችግሮች በየፈርጁ ብንመለከታቸውና በጋራ ሆነን መፍትሄ ብንፈልግላቸው እንጂ በነውጥና ሁከት መፍትሄ እናመጣለን በማለት የበሬ ወለደ ፖለቲካ ለአገራችንም ሆነ ለህዝብ የሚበጅ አካሄድ አይሆንም። ሁሉንም ነገር ወደ ኢህአዴግ መወርወር ኢህአዴግ ራሱ መፍትሄ ይፈልግ ማለት ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኢህአዴግም የእርሱ ጥፋት የሆነውንም ያልሆነውንም የእኔ ጥፋት ነው ብሎ ጠቅሎ መውሰድ አይገባውም። ኢህአዴግ ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ ሊያመጣ ከቶ አይቻለውምና።
መልካም አስተዳደር ማስፈን የዕለት ተግባር አይደለም። ሁለም ችግሮች ዕለቱን መፍትሄ አያገኙም። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል መንግስት ወይም ገዥው ፓርቲ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ናቸው። ይሁንና ሁሉም ችግሮች በአንዴ መፍትሄ ሊያገኙ አይችሉም። የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙት በሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት እንጂ በገዥው ፓርቲ ጥረት ብቻ የተፈለገው ውጤት ሊመጣ አይችልም።
በየትኛውም መስክ ለጥፋት ኃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት አንዱ የመንግስትና የገዥው ፓርቲ ተግባር መሆን መቻል ይገባል። የተሰጣ ቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና ህዝባዊ ድጋፍ የሌላቸው፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በፅናት መታገል ያስፈልጋል። ህዝቡ የነውጥና የሁከት ጋሻጃግሬዎች እነማን እንደሆኑ ጠንቅቆ ያውቃል። በመሆኑም እነዚህን አካላት ለህግ አሳልፎ መስጠት ይጠበቅታል።
ለአገራችን የሚበጃት፣ ለችግሮቻችን መፍትሄ መፈለግ ያለብን በሰከነና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ሲሆን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር የፊት ለፊት ውይይት በማድረግ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ መድረኮችን በማድረግ ላይ ነው። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ጅምር ቢሆንም፤ መነጋገርና መወያየት የሚያስችል ፖለቲካዊ ምህዳር አለ። ይህን መልካም ጅምር ልንጠቀምበት ይገባል። መስማማት ወይም አለመስማማት አንድ ነገር ሆኖ፤ ቁጭ ብሎ መነጋገር መቻል በራሱ የመጀመሪያውና ትልቁ መልካም ነገር ነው። ጤነኛ የሃሳብ ልዩነት የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫ ነውና።
የጥበትና ትምክህት ሃይሉ የጽንፈኛው የዳያስፖራ ሚዲያዎችንና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም አገር እንዳበቃላት አድርገው የተለያዩ መረጃዎችን በመንዛት ህብረተሰቡን በተለይ ወጣቱን ለሁከትና ነውጥ ለማነሳሳት የሚያደርጉትን ሩጫ ማጋለጥ የሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል። የነውጥ ሃይሎች የጥፋት ተልኳቸውን ትኩረት አድርገው እየሰሩ ያሉት የብሄር ግጭቶች እንዲፈጠሩና እንዲስፋፉ ማድረግ ላይ ነው። የጥበትና ትምክህት ሃይሎች ዓላማቸውን ለማሳካት ሁሌም ነውጥና ሁከትን ይመርጣሉ። ነውጥና ሁከት መፍጠርና በተለይ በብሄሮች መካከል የሚደረግ ግጭት የጥፋት ሃይሎች ዋንኛ ስትራቴጂያቸው ነው።
ግምገማ የኢህአዴግ የጥንካሬ መሰረት ነው፡፡ ኢህአዴግን ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ እስከ አገርና ህዝብ መምራት ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት አበይት ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ቀዳሚው ይህ ጠንካራ የግምገማ ባህሉ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ይህ የግምገማ ባህሉ አባላቱ ጥሩ የስነ ምግባር ምንጭ እንደሆናቸው፣ ተጠያቂነትን እንዲያውቁና የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ካደረጋቸው ምክንያቶች ቀዳሚውና ዋነኛው ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ እነዚህ የኢህአዴግ ጠንካራ መሰረት እየተሸረሸሩ እንደመጡ አንዳንድ ሁኔታዎች ያመላክታሉ። ይሁንና ከድርጅቱ የቆየ ልምድ ኢህአዴግ ወደ ቀድሞው አቋሙ ለመመለስ የሚከብደው አይመስለኝም። ኢህአዴግ በቡድን አሰራር ላይ መሰረት ያደረገ ፓርቲ በመሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች ቢበላሹም ድርጅቱ ላይ የሚከሰተው ተጽዕኖ እጅግም ነው። ለዚህ ነው ኢህአዴግ ወደ ቀድሞው አቋሙ ለመመለስ አይከብደውም ለማለት የደፈርኩት። በኢህአዴግ ቤት ማንም በዛሬ አቅሙ እንጂ በትናንት ማንነቱ የማይለካው።
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በእያንዷንዷ የአገራችን ስኬት ላይ የኢህአዴግ ጉልህ አሻራ አርፎበታል። አገራችን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተመሰከረላት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለተከታታይ 15 ዓመታት በማስመዝገብ የዜጎች ህይወት መለወጥ ኢህአዴግ ከፍተኛ ድርሻ አለው፤ በአገራችን የህዝብን አንገት አስደፍቶ የነበረውን ድህነትን ከግማሽ በላይ እንዲቀንስ አድርጓል። በጦርነት ትታወቅ የነበረች አገር ዛሬ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ በመቻሏ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን በቅታለች፤ በስንዴ ልመና ትታወቅ የነበረች አገር ዛሬ ላይ በምግብ ሰብል ራሷን ችላለች፡፡ እጅግ ከባድ የተባለውን ከ2008 ጀምሮ ተጽዕኖው እስካሁን የዘለቀውን ድርቅ በአመዛኙ በራሷ አቅም መወጣት ችላለች።
አገራችን በምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ የዲፕሎማሲ የበላይነት እንዲኖራት በማድረግ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ተሰሚነት እንዲኖራት ኢህአዴግ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን አከናውኗል። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በአካባቢያዊም ሆነ አህጉራዊ እንዲሁም በዓለም ዓቀፋዊ መድረኮች ያላት ተሰሚነት እጅጉን አድጓል። በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንድትታወቅና አዲስ ገጽታ እንድትላበስ ኢህአዴግ የአንበሳውን ድርሻ አበርክቷል፤ በማበርከትም ላይ ይገኛል። እነዚህ ሁሉ ስኬቶች የኢህአዴግ አይደሉምን?
ባለፉት 23 ዓመታት ኢትዮጵያ ህገመንግስ ታዊና ጠንካራ አገር ለመሆን የበቃችው፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጻነትና እኩልነት የተረጋገጠው፣ ጅምር ቢሆንም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መለማመድ የጀመርነው፣ በተከታታይ ለ15 ዓመታት ባለሁለት አሃዝ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ ሁሉም በየደረጃው ፍትሃዊ ተጠቃሚ መሆን የጀመረበት፤ ድህነት እንዲቀንስ የተደረገው፤ የአገራችን ተሰሚነት በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እጅጉን ከፍ ያለው፤ አገራችን በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም በአፍሪካ ትኩረት የምትስብ አገር ለመሆን የበቃችው በኢህአዴግ አመራር ነው።
ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የምናስተውላቸው አንዳንድ ነገሮች ግን የኢህአዴግ ባህሪያትና ባህሎች አይደሉም። ኢህአዴግ ከቀድሞው አቋሙ እየተንሸራተተ ነው፤ ዛሬ በኢህአዴግ ቤት ህዝበኝነት እየገነገነ መጥቷል፤ ሁሉም በየቅሉ መጓዝን መርጧል። በዚህ አካሄድ የህዝብ ተጠቃሚነት አይረጋገጥም፤ የአገር አንድነት፤ የህዝቦች አብሮነት አይጠበቅም። ህዝበኝነት የህዝብን ስሜት በመኮርኮር የህዝቦችን አብሮነት ይሸረሽራል፤ ህዝብን ያባላል፤ አገርን ይበትናል። በመሆኑም ኢህአዴግ ውስጣዊ ችግሩን ለማስወገድ፣ በፍጥነት ወደ ቀድሞ አቋሙ ሊመለስ ይገባል። ሰሞኑን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እያደረገ ባለው ስብሰባ የእያንዳንዳችንን ህይወት የሚመለከት በመሆኑ የኢህአዴግ አመራሮች ሆይ ለህዝባችሁ፣ ለአገራችሁ እንዲሁም ለራሳችሁ ስትሉ ቆም ብላችሁ ሁኔታዎችን መርምሩ፤ ተቀጽላውን ቆርጣችሁ ጣሉ።

አባ መላኩ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።