ሰላማችንን አጥብቀን እንያዛት

14 May 2018

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተከስቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት ጭምር ሳይቀር ስጋት የፈጠረ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ መንግስት በወሰደው ብልህ እርምጃ አሁን አሁን ችግሮቹ እየተቀረፉ ቢሆንም እንዲህ አይነት ችግሮች እንዳይደገሙ ግን መስራት ተገቢ ነው፡፡ በተለይ እንዲህ አይነት ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት ሰላምን ሊያናጉ የሚችሉ ችግሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል፡፡ እንዲህ አይነት ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ትተው የሚያልፉት ጥቁር ጠባሳ በዘላቂ ሰላም ላይ ጥቁር ነጥብ ትተው የሚያልፉ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እኔም ይህንን የቅርብ ጊዜ የሰላም እጦት ችግር እያሰብኩ በመካከሉ 27 ዓመታን ወደ ኋላ በትዝታ ተመለስኩ፡፡ የግንቦት ወር መጀመሪያ አካባቢ አገራችን የነበረችበትን ድባብም በአዕምሮዬ ጓዳ ፈተሽኩ፡፡ በርካታ ነገሮች በአይነ ህሊናዬ ተመላለሱ፤ ከነዚህ ውስጥ በተደጋጋሚ ፊት ለፊት የወጣው በወቅቱ የነበረው የሰላም ጉዳይ ነው፡፡
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ የልማት፣ የሰላማዊ ቤተሰብ፣ የተረጋጋ ማህበረሰብ፣ የነገው ትውልድ ተስፋ ወዘተ፡፡ ሰላም ከሌለ ማንም በሰላም ወጥቶ በሰላም ሊገባ አይችልም፤ ሰላም ከሌለ ልጅን ወልዶ ማሳደግና ለአገር መሰረት የሆነውን ማህበረሰብ መፍጠር አይቻልም፤ ሌላው ቀርቶ ህይወቱ ያለፈን ወዳጅ ዘመድ እንኳን በክብር ለማሳረፍ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ የአእምሮ እረፍትም ቢሆን ያለ ሰላም አይገኝም፡፡ ሰላም በሌለበት ሁኔታ አንዲት እናት ትምህርት ቤት ስለሄደው ልጇ ማሰብና መጨነቅ የግድ ነው፡፡ ከዚህም ከፍ ሲል ተረጋግቶ ለመኖር ያለንን ተስፋ ሁሉ ያጨልማል፡፡
ሰላም ዘርፈ ብዙ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ አገር ሰላም ከሌላት በኢኮኖሚ ጭምር መዳከሟ አይቀሬ ነው፡፡ ለምሳሌ አገር ከምታገኛቸው ገቢዎች አንዱ ከቱሪስት ፍሰት የሚገኝ ገቢ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው በሰላም ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን ለጉብኝት ቀርቶ ለስራም ቢሆን ሰላም ወደሌለበት አካባቢ የሚሄድ የውጭ ዜጋ አይኖርም፡፡
ስለ ሰላም ሲነሳ በ1983 ዓ.ም ያጋጠመኝና እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ ጓዳ ያልወጣውን አንድ ገጠመኝ ላውጋችሁ፡፡ እለቱ ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ማለዳ ነው፡፡ በወቅቱ የምኖረው አዲስ አበባ ከጄኔራል ዊንጌት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አልፍ ብሎ በሚገኝ አወልያ ትምህርት ቤት አካባቢ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረውን ከፍተኛ ውጥረት ተከትሎ የተለያዩ ተቋማትና የመንግስት መጋዘኖች ለዝርፊያ ተጋልጠው ነበር፡፡ ከነዚህም መካከል በሸጎሌ አካባቢ የሚገኘው የጥይት መጋዘን አንዱ ነው፡፡
ከግንቦት 19 ጀምሮ በርካታ ሰዎች በዚህ የጥይት ማከማቻ ስፍራ በመገኘት የሚጠቅመውንም፣ የማይጠቅመውንም ንብረት ሲዘርፉ ቆዩ፡፡ ግንቦት 20 ቀንም የኢህአዴግ ሰራዊት አዲስ አበባ እየገባ ባለበት ሰዓትም ይኸው ቀጥሎ ነበር፡፡ በግምት አራት ሰዓት አካባቢ ግን አካባቢውን ያስደነገጠ ከባድ ፍንዳታ ተከሰተ፡፡ በዚህ ጊዜ ከሸጎሌ የወጣው ፍንዳታ ከአካባቢው አልፎ እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ቤቶችን ጭምር ለጉዳት የዳረገ ነበር፡፡ በእለቱ በአካባቢው ላለው እና ይህንን ትዕይንት ለተመለከተ ሁሉ የአዕምሮ እረፍትን የሚነሳ ክስተት ነበር፡፡ በዚህ ፍንዳታ ከአንድ ቤተሰብ እስከ አምስት ሰው ህይወት ያለፈበት ዘግናኝ ክስተት ተፈጥሮ አልፏል፡፡ በዚያው ሰሞን በበቅሎ ቤት አካባቢ በተከሰተው የነዳጅ ዴፖ ፍንዳታም በሌሊት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከከተማዋ የወጡ በርካታ ዜጎች ነበሩ፡፡
እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ሰላም ከመጥፋቱ ወይም በወቅቱ ከነበረው የሰላም መደፍረስ ችግር የመነጩ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን ግንቦት 20 እነዚህን ክስተቶች በመቀነስ ረገድ ያበረከተው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም፡፡ በታሪክ በጉልህ ከሚፃፉ የግንቦት 20 ገፀ በረከቶችም ውስጥ ሰላም አንዱ ነው፡፡
ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን ባልተረጋጋ ሁኔታ የመራው የደርግ መንግስት በተለይ በመጨረሻ ዘመኑ ላይ ተስፋ የቆረጠበት ዘመን እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው ላይ አንስቶ ለጦርነት ወደ ማሰልጠኛ እስከማስገባት መድረሱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደ ጦር ሜዳ በመላክ በጦርነት ድል አደርጋለሁ ብሎ ማሰብ ምን ያህል ድክመት እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡
በአንዳንድ አገራት ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ ጣቢያ ገብተው ስልጠና የሚወስዱበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይህ ግን ተማሪዎቹን በቀጥታ ወደ ጦርነት ለማሰማራት ሳይሆን አካላዊና አዕምሮአዊ ዝግጁነትን ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን ብዕርና ወረቀትን ብቻ ሲያዋድድ ለኖረ ወጣት በአንድ ጊዜ ተነስና ዝመት፣ ተዋግተህ ሙት ማለት አንድም ልጆቹን ለአደጋ ማጋለጥ፣ አልያም ማህበረሰቡን ተስፋ ከማስቆረጥ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
በዚህ አይነት ሁኔታ በትልቅ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የነበረው የደርግ መንግስት አገርን ለመጠበቅ የሚያስችል ቁመናና ብቃት ላይ ያልነበረበት ወቅት ነበር፡፡ በአጠቃላይ በወቅቱ በዚህ የግንቦት ወር መጀመርያ ላይ የነበረው ሁኔታ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የጭንቀት ወቅት ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመሩ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም አገሪቷ በዚህ ሂደት ላይ እንዳለች ጥለው መኮብለላቸው ህዝቡን ለጭንቀትና ለስጋት የዳረገበት ወቅት ነው፡፡
በዚህ ወቅት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደየዕምነቱ በአገራችን ሰላም እንዲፈጠር የሚፀልይበት ወቅት ነበር፡፡ በተለይ አዲስ አበባ የነበረው ሁኔታ የተለየ ነበር፡፡ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የያዘውን ታንክና ከባድ መሳሪያ አንግቦ ወደ አዲስ አበባ ይተም የነበረው ሰራዊት አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ምን ይፈጠራል በሚል ስጋት እናት ልጇን የምታስገባበት ቦታ እስከሚጠፋት ድረስ ጭንቀት የሰፈነበት ጊዜ ነበር፡፡
ያም ሆኖ ግን ከዚህ ሁሉ የጭንቀት ጊዜ በኋላ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ነገሮች ተለወጡ፡፡ አዲስ አበባ የጦርነት ቀጣና ትሆናች ሲሉ የነበሩ ሁሉ ህልማቸው እውን ሳይሆን ቀርቶ በከተማዋ መረጋጋትና ሰላም ሰፈነ፡፡ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የነበረውን የአገራችንን የሚዲያ መረጃ የሚከታል ሁሉ የእያንዳንዷ ቀን የውሎ መረጃ ዜና ከጦርነት ጋር የተያያዘ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በሌላም በኩል 15 ዓመት የተጠጋው ወጣት ሁሉ ለእናቱ የስጋት ምንጭ የሆነበት ዘመን ነበር፡፡ ምክንያቱም በዘመኑ ወጣቶችን በአፈሳ ከየቤቱ እየለቀሙ ወደ ጦርነት ማጋዝ የተለመደ ስለነበር እናቶች ያለእረፍት ለመኖር የተገደዱበት ጊዜ ነው፡፡ የደረሰ ልጇን በቁም ሳጥን ውስጥ ደብቃ መቆለፍ ፣ በዱቁት እቃ ውስጥ ማሸግ፣ በጣሪያ ስር ኮርኒስ ላይ መደበቅ፣ ወዘተ የዘመኑ ትውስታዎች ናቸው፡፡
በዚህ አጋጣሚም በአንድ ወቅት የደረሰብኝን በጥቂቱ ላካፍላችሁ፡፡ ወቅቱ የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት የተጀመረበት ዘመን ነው፡፡ በቤታችን ውስጥ ከእናትና አባታችን በተጨማሪ ታላቅ እህቴና ታላቅ ወንድሜ አብረን እንኖራለን፡፡ ታላቅ ወንድሜ ገና አፍላ ወጣት በመሆኑ እናቴ ሁል ጊዜ እንቅልፍ አልነበራትም፡፡ ከዛሬ ነገ ይወስዱብኛል በሚል ስጋት ያለእንቅልፍ ማሳለፍ የዘወትር ስጋቷ ነበር፡፡ እንደፈራችውም አንድ ቀን ወንድሜ ከትምህርት ቤት ሲመለስ ከመንገድ ላይ ተይዞ ወደ ውትድርና ተወሰደ፡፡ ይህ ወቅት በቤታችን ውስጥ ትልቅ የሃዘን ስሜት የፈጠረ ነበር፡፡ በተለይ ለእናቴ ከዚህ በላይ ህመምና በሽታ አልነበረም፡፡ ይህ ወቅት እስከዛሬ ድረስ በውስጤ ይመላለሳል፡፡ አንድ ሰው ሳይፈልግ ወደ ጦርነት የሚወሰድበትና የሚሞትበት አገር፤ ያውም ባላመነበት ጦርነት፡፡
ይህ ዘመን እነሆ ታሪክ ሀኖ ካለፈ 27 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ካፈራናቸው ሀብቶቻችንም ውስጥ አንዱና ዋነኛው ሰላም ነው፡፡ በነዚህ ዓመታት ቢያንስ ተገዶ ወደ ጦርነት መጓዝ የለም፡፡ በየቀኑ ስለጦርነት የምንሰማበት ጊዜም አብቅቶ ስለልማትና ስለሰላም መስማት ተለምዷል፡፡ እንደቀይ ሽብር አይነት በአደባባይ የሚደረግ ርሸናና ለሞተው ልጅ አስከሬን ለመውሰድ ገንዘብ አምጡ መባልም የለም፡፡
ስለ ሰላም ለማውራት የግድ ጦርነት ውስጥ ገብተን ማየት አለብን የሚል የዋህ አስተሳሰብ ሊኖረን አይገባም፡፡ ብልህ ሰው ችግሮችን ከሌሎች ችግር ይማራል፡፡ ችግሩን ካላየሁ አላምንም የሚል ካለ ግን የዋህ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን ስላለፈው ሁኔታ ያልተረዱ አንዳንድ ወጣቶች ሰላምችንን ሊያሳጣን ወደሚችል ድርጊት ውስጥ ሲዘፈቁ ይታያል፡፡ ከዚህ አንፃር በአንድ ወቅት ያጋጠመኝም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ቦታው አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት፡፡ በእለቱ በዚህ አካባቢ ይከበር በነበረው የደመራ በአል ላይ ለመሳተፍ በርካታ የከተማችን ነዋሪዎች የተገኙበት እለት ነበር፡፡ በተለይ በርካታ የከተማችን ወጣቶች በስፍራው ታድመዋል፡፡
በዚህ መካከል ጥቂት ወጣቶች በመንግስት ላይ ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ፡፡ ጠጋ ብዬ ወጣቶቹ የሚሉትን ለመስማት ጥረት አደረኩ፡፡ የወጣቶቹ ድምፅ “መንጌ ናፈቀኝ” የሚል ነበር፡፡ የወጣቶቹን እድሜ ስገምት አብዛኞቹ በአስራዎቹ መጨረሻ ወይም በሃያዎቹ መጀመርያ ላይ መሆናቸውን ለመገመት አላዳገተኝም፡፡ እነዚህ ወጣቶች ደግሞ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የተወለዱ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የነበረውን ሥርዓት የማያውቁ ብቻ ሳይሆን በቅጡ ያልተረዱ መሆናቸውንም ተረዳሁ፡፡ እናም የማያውቁትን መናፈቃቸው ገርሞኝ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡
ይህ የወጣቶቹ ድርጊት ለረጅም ጊዜ በአእምሮዬ ሲመላለስ ነበር፡፡ እውን እነዚህ ወጣቶች ምን እያሉ እንደሆነ በትክክል ያውቁታል? ስለሚናገሩት ሥርዓትስ በቅጡ ያውቃሉ? የሚሉ ሃሳቦች የአዕምሮዬን ጓዳ አጨናነቁት፡፡ በዚህ መካከልም በርካታ ሃሳቦችን ማውጣትና ማውረድ ጀመርኩ፡፡ ለዚህስ ተጠያቂው ማነው? የሚለው ጉዳይም ይበልጥ እንዳስብበት ገፋፋኝ፡፡
አገራችን በደርግ ዘመን ከነበረችበት የጭቆና ዘመን ተላቃ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርን መከተሏ ይታወቃል፡፡ የአገራችንን ነባራዊ እውነታ ስንመለከት ደግሞ አብዛኛው ህዝባችን ወጣት ነው፡፡ ይህም አብዛኛው ህዝባችን የዚህ ሥርዓት አካል እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ህዝብ ደግሞ የቀደመውን ሥርዓት ምንነትና ባህርይ በአግባቡ እንዲያውቅና እየተጓዘበት ያለውን መስመር በአግባቡ ተረድቶ ከመንግስት ጎን እዲቆም ማድረግ ከመንግስት ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ይህንን በአግባቡ ካላስገነዘብንና ካላሳወቅን አፈንጋጭ ትውልድ መፈጠሩ አይቀርም፡፡
ከቅርብ ዓመታ ወዲህ በአገራችን የታየውም ሁኔታ ከዚህ የመነጨ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ስለቀደመው ሥርዓቶች ታሪክን ከማስተማርና እየተሰራበት ያለውንም በአግባቡ እንዲያውቅ ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች አሉ፡፡ አሁን ላይ ስለሀገሩ የሚያውቅ ትውልድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደመጣ ብዙዎች ሲናገሩም መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡
በአጠቃላይ በአስተሳሰብ ቀረጻ ላይ እየሰጠን ያለነው ትምህርት አነስተኛ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል በነበሩ ሥርዓቶች ውስጥ ያለፉ ወላጆችም አሁን ላይ ላሉ ወጣቶች ስለነበረው ነባራዊ ሁኔታ ትክክለኛውን ነገር ከማሳወቅ አንፃር ትልቅ ክፍተት አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ልጆቻቸውን በኮርኒስ ውስጥ እስከመደበቅ የደረሱና እራሳቸውም በዚሁ ሁኔታ ያለፉ ዜጎች ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመጪው ትውልድ በግልፅ አለማሳወቅ እውነታን እንደመካድ ይቆጠራል፡፡
እስኪ በቅድሚያ እድሜያችን ከ30 ዓመት በላይ የሆነን ዜጎች አንድ የጋራ የቤት ስራ ወስደን እንሞክር፡፡ በርግጥ ከ30 ዓመት በላይ ስል ሁሉም ያንን ሥርዓት በትክክል ያውቀዋል ለማለት እንዳልሆነ ልብ በሉ፡፡ አንዳንዶቻችን በጭላንጭልም ቢሆን ከወላጆቻችን ሁኔታ ውን ተረድተን ይሆናል ከሚል ግምት የተወሰደ ነው፡፡ እናም በወቅቱ በየቤታችን የነበረውን ጭንቀትና ነገ ምን ይሆን እያልን እናሰላስል፡፡ አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር በቀላሉ ህይወታችንን ሊቀጥፍ የሚችልበት ነባራዊ ሁኔታ አልነበረም? በዘመኑ የነበረው ወጣትስ የሚፈልገውን ሃሳብ ሰብሰብ ብሎ ለመነጋገር ነፃነት ይሰማው ነበር? እነዚህን ሃሳቦች ለራሳችን አእምሮ ትተን ወደ ዛሬ እንመለስ፡፡
በርግጥ ዛሬም ቢሆን በአገራችን በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ግን ከሰላም ይልቅ የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ የጥረት ሜዳው ተዘርግቷል፡፡ በዚህ ሜዳ ሰርቶ ለመለወጥ የተሻለ ጊዜ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን አገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ የህዝብ ቅሬታዎች ማስተናገድና እዚህም እዚያም ግጭቶችን መስማት የተጀመረበት ሁኔታ እናገኛለን፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገራችን እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና የሰላም እጦት ችግሮች እየተባባሱ መጥተው መንግስት ከአንድም ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ አስገድዶታል፡፡
ያም ሆኖ ግን ባለፉት 27 ዓመታት አገራችን ሰላማዊ ምድር በመሆኗ ያገኘናቸው በርካታ ድሎች አሉ፡፡ በነዚህ ዓመታት የህዝብን በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ነፃነት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነት የኢኮኖሚ ድቀት ጠንቅ በመሆኑ ይህንን ለጦርነት ይውል የነበረ ሀብት ሀገርን ለማሳደግ ተጠቅመንበታል፡፡ አገራችን አሁን ከደረሰችበት ደረጃ የደረሰችው ላለፉት ዓመታት ሰላም በመኖሩ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሰላም ባይፈጠር አሁን ላይ ከህዝብ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሄድ ጋር ተደምሮ አስከፊ ሁኔታ ይፈጠር እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡
ከሁሉም በላይ ግንቦት ሃያ ይህንን የሰላም በረከት ይዞልን መምጣቱ አንድ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ይህንን የሰላም በረከት ደግሞ መጠበቅ የኛ ፈንታ ነው፡፡ ይህ እድል ከእጃችን ካመለጠ ነገ ልንመልሰው አንችልም፡፡ የሰላም አስከፊው ገፅታው አንዴ ከእጅ ካመለጠ ለመመለስ አስቸጋሪ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ከነ ሶማሊያ ሶርያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ እና ሌሎች አገራት ተሞክሮ በቅርበት አይተናል፡፡ እነዚህ አገራት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች አገራት የሚተርፉ እንዳልነበሩ ዛሬ ላይ ግን የሰላም እጦት በአንድ ጊዜ ቁልቁል እንዲወርዱና የድህነትን ወለል እንዲረግጡ አድርጓቸዋል፡፡ እናም “ሞኝ ከራሱ፣ ብልህ ከሌላው ይማራል” እንደሚባለው ሰላማችንን አጥብቀን እንያዛት፡፡

ውቤ ከልደታ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።