ግንቦት ሀያን በአዲስ የፖለቲካ ስሜት

15 May 2018

በኢትዮጵያ የግንቦት ወር የሚታወስባቸው በርካታ አበይት ምክንያቶች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተጭኗቸው የቆየውን የደርግ የግፍ አገዛዝ አሽቀንጥረው የጣሉበት ግንቦት 20 ቀን ደግሞ ከእነዚህ ሁሉ ይገዝፋል፡፡

የ17 አመታት መስዋእትነትን ከጠየቀ ትግል በሁዋላ ኢህአዴግ አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት ይህ ቀን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት የተጫነባቸው የግፍ አገዛዝ ጭምር የተወገደበትና እነዚህ ህዝቦች የልማት የሰላምና የዴሞክራሲ ብርሃን ያዩበት ቀን በመሆኑም ልዩ ክብር ይሰጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም ይህን ቀን ላለፉት 26 አመታት የትግሉን ወቅት በማስታወስ እንዲሁም ከድሉ በሁዋላ የተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ድሎችን በማሰብ በሂደቱ የታዩ ክፍተቶችን መሙላት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር ሲያከብሩት ኖረዋል፡፡
ሀገሪቱ የግንቦት ሀያ ድልን ተከትሎ ለዘላቂ ሰላሟ መሰረት ፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርአቷና ልማቷ መደላድል የሆነውን ህገመንግስት በህዝብ ተሳትፎ ከማጽደቅ አንስቶ የፌዴራል ስርአቷን መገንባት የሚያስችሏትን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና አዋጆች መመሪያዎችና ደንቦች በማውጣት ልማቷን ለማረጋገጥ ተንቀሳቅሳ ስኬቶችንም አጣጥማለች፡፡
85 ከመቶ የሚሆነው ህዝቧ አርሶ አደር በሆነባት አገራችን መንግስት ያለውን ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬትና ጉልበት ታሳቢ በማድረግ የቀረፃቸው ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ስኬታማ መሆን በመቻላቸው ግብርናው አሁንም ድረስ የኢኮኖሚው መሰረት መሆኑን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስችለዋል፡፡ ለዚህም በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን የታየውን የግብርና ዘርፍ እንቅስቃሴ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በእቅድ ዘመኑ የአነስተኛ አርሶ አደሮች የመኸር ሰብል ምርት በ2002 የምርት ዘመን ከነበረበት 180 ሚሊየን ኩንታል በ2007 ወደ 270.3 ሚሊዮን ኩንታል ማደግ ችሏል፡፡ ይህም የ90 ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ የታየበት ነው፡፡ የምርት እድገቱ መሰረታዊ የእድገት አማራጩን ያሟላና አገራችን በምግብ ሰብል ራሷን እንድትችል ያስቻለ ነው፡፡ ይህ የግብ ስኬት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ትልቅ ፋይዳ ካላቸው አፈጻጸሞች መካከል የሚጠቀስም ሆኗል፡፡
የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ ዘመንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ግብርናው በአጠቃላይ ሌሎች የልማት ስራዎች መሰረት መሆኑንም ቀጥሏል፡፡ በ2009/2010 የምርት ዘመንም የተገኘው 306.1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የእድገቱን ቀጣይነት ይጠቁማል፡፡
በድርቅና በረሃብ ስትጠቀስ የኖረችው እና በዚህም የተነሳ አለም አቀፍ ተቋማትንና ለጋሽ አገሮችን በመማጸን ትታወቅ የነበረችው ኢትዮጵያ በእነዚህ የልማት መሳሪያዎች፣ በህዝቡ ንቁ ተሳትፎ እና በመንግስት ቁርጠኛ አመራር በተከናወኑ መጠነ ሰፊ ስራዎች የግብርናውን ምርትና ምርታማነት በአጠቃላይም ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ችላለች፡፡ በዚህም እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥም የተቻለ ሲሆን የድህነት ተራራም መናድ መጀመሩን ያሳያል፡፡
በሌላም በኩል ሀገሪቱ ላለፉት 15 አመታት ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ በቅታለች፡፡ እድገቱ እንደ ሌሎች እያደጉ እንደሚገኙ ሀገሮች በነዳጅ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በግብርናና በሌሎች ዘርፎች ላይ የተመሰረተ መሆኑም ታላቅ እድገት የሚያሰኘው ነው፡፡ ሀገሪቱ ፈጣን እና ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከሚያስመዘግቡ 10 ሀገሮችም ግንባር ቀደም ለመሆን በቅታለች፡፡ ይህ እድገት በአለም አቀፍ ተቋማት ጭምር አድናቆት የተቸረው ነው፡፡
መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለዘመናት ተሸክሞ ከኖረው ግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ራእይ ሰንቆ እየሰራ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሸን የእቅድ ዘመን ኢንዱስትሪው የሚጠበቀውን ያህል እድገት ባያስመዘግብም መንግሥት ይህን በሚገባ በመገምገም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን ለኢንዱስትሪው ትከረት ሰጥቶ መስራቱን ተያይዞታል ፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እየተገነቡ የሚገኙ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
ያለፉት አመታት የግንቦት ሀያ በአላትም እነዚህን ስኬቶች፣ ለስኬት ያበቁ ተግባራት እንዲሁም በሂደቱ ያጋጠሙ ፈተናዎችን በመመልከትና መፍትሄ በማመላከት ለበለጠ ስኬት ቃል በመግባት ተከብረዋል፡፡ የዘንድሮው ግንቦት ሃያ በዓልም እስከ አሁን የተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊና ማህበራዊ ስኬቶች ተጠናክረው በቀጠሉበት የስኬት ጎዳና ውስጥ ውስጥ ይከበራል፡፡
እንደሚታወቀው ፤በሀገራችን በተከታታይ ኢኮኖሚያዊ እድገት ቢመዘገብም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ፍላጎትም ከእድገቱ በበለጠ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህን ተከትሎ ደግሞ መንግስት እንዲያሟላ የሚጠበቅበት በርካታ ነገር መኖሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ ሆኖም ለወጣቶች በቂ የስራ እድል ካለመፍጠር ፣ ከመልካም አስተዳደር መጓደል፣ ከሙስናና ብልሹ አሰራር እየተንሰራፋ መምጣት ጋር በተያያዘ ባለፉት ሁለት አመታት የህዝብ ቅሬታ እየበዛ መምጣቱ ይታወሳል፡፡ ምን እንኳን እነዚህ ቅሬታዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋብ ቢሉም በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ችግሮች መሆናቸው ግን አይካድም፡፡
በሌላ በኩል መንግስት ችግሮቹን ለመፍታት የሄደበት ርቀት ቀላል አይደለም፤ የወጣቱን ጥያቄ ለመመለስ 10 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ እየሰራ ነው፡፡ በየደረጃው የሚታዩ የመልካም አስተዳደር፣ የሙስናና የብልሹ አሰራር ችግሮችንም ለመፍታትም የካቢኔ አባላቱን ጭምር በአዳዲስ አመራሮች በማጠናከር ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በየደረጃው ያለውን አመራርና ፈጻሚም በመገምገም ችግሮቹን ለማስተካከል እየሰራ ይገኛል፡፡
መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚያስችል ተግባር ለማከናወን ቃል በገባው መሰረትም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሲወያይ ቆይቷል፡፡ ውይይት ከተደረገባቸው አጀንዳዎች መካከልም የምርጫ ስርአቱን ከአብላጭ ድምጽ ወደ ቅይጥ የሚቀይረው አሰራር ይገኝበታል፡፡ በዚህም የህዝብ ድምጽ ሲባክን የኖረበት ሁኔታ እንዲለወጥ ፣ የተወካዮች ምክር ቤትም የሁሉም ድምጽ የሚሰማበት እና በሂደቱም ዴሞክራሲያዊ አሰራር እንዲጠናከር የሚያስችል ተግባር ተከናውኗል፡፡
በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የህዝቡን የመልካም አስተዳደር እና የወጣቱን የስራ አድል ጥያቄ ለመፍታት ርብርብ በሚያደርግበት በአሁኑ ወቅት ከወሰን ጋር በተያያዘ በተለይ በኦሮሚያ ክልልና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ተቀስቅሶ የዜጎች ህይወት አልፏል፤ አካል ጎድሏል፤ ለፍተው ያፈሩት ጥሪት ወድሟል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ከቀዬኣቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ቀደም ሲልም በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ እንዲሁም በሰሜን ወሎ የዜጎችን ሕይወት የቀጠፈ ግጭት መፈጠሩ ይታወሳል፡፡
መንግስት በሀገሪቱ የተቀጣጠሉት እነዚህ እንቅስቃሴዎች በዜጎች ወጥቶ መግባት ፣በሀገር ኢኮኖሚና ማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም በባለሀብቶች ንብረት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደራቸውን ተከትሎ ጉዳዩ በመደበኛው ጸጥታን እና ደህንነትን በማስከበር መንገድ ሊከናወን እንደማይችል በመገንዘብ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከአንድም ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዘንድሮ ለ17 ቀናት ባካሄደው ጥልቅ ተሃድሶና ግምገማም ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችሉ ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ ከሰማይ በታች ምንም እንዳይቀር ብሎ በመከረበት በዚህ ስብሰባው ሁሉንም ነገር አውጥቶ መምከሩን የኢህአዴግ አባል አራት ድርጅቶች መሪዎች በጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
መንግስት በገባው ቃል መሰረትም በእስር ላይ የሚገኙና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላት እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡ ይህም የፓለቲካ ምህዳሩን ማስፋትን ታሳቢ ያደረገ ታላቅ እርምጃ ነው፡፡ በዚህም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ከእስር እየተፈቱ እና ክሳቸው እየተቋረጠ ህብረተሰቡን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸው በራሳቸው ፈቃድ ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄም በሀገሪቱ የፓለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የተሰጠው ሆኗል፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በዓለም ማህበረሰብ ጭምር ታላቅ ድርጊት መሆኑ የተመሰከረለት ክስተት ነው፡፡
የኢህአዴግ ምክር ቤትም ለቀናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲመክር ቆይቶ የግንባሩ ሊቀመንበር በነበሩትና ይህን ኃላፊነታቸውን በራሳቸው ፈቃድ በለቀቁት በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ምትክ ዶክተር አብይ አህመድን ሲመርጥ ታየ የተባለው ዴሞክራሲያዊ ሂደት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መገንባቱን ያስመሰከረ ተግባር ሆኖ አልፏል፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃለ መሀላ ፈጽመው በተለያዩ ክልሎች ጉብኝትና ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውንም በጎረቤት ሀገሮች በማድረግ ጅቡቲን፣ ሱዳንና ኬንያ ጎብኝተዋል ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉብኝት በሄዱባቸው ክልሎች ፣ በአዲስ አበባም በሚሊኒየም አዳራሽና በብሄራዊ ቤተመንግስት ባካሄዷቸው መድረኮች የሕዝቡን ጥያቄዎች አዳምጠው መልስ ሰጥተዋል፡፡ መንግስት ጥያቄዎቹን ለመመለስ ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደሚንቀሳቀስ በማረጋገጥ አቅም የፈቀደው ሁሉ እንደሚከናወን ቃል ገብተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ በርካታ ፈተና እንደሚገጥማቸው የተለያዩ ወገኖች ሲገልጹ ተሰምቷል፡፡መንግስታቸውም መፈታት ያለባቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉ ያምናል፡፡ የህዝቡን ጥያቄ አስቀድመው ቢያውቁም ፣ ከ‹‹ፈረሱ አፍ›› እንደሚባለው ጉብኝትና ውይይት ባደረጉባቸው ክልሎች የህዝብን ጥያቄ አዳምጠዋል፡፡
ቀጣዩ ስራቸውም እነዚህን ከህዝብ የሰበሰቡትን አስተያየትና ጥያቄ ለመፍታት በሚያስችል ተግባር ውስጥ በመግባት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ የግንቦት ሃያ በአልም ሀገሪቱ እያስመዘገበች የምትገኘውን ስኬት በማጠናከር እንዲሁም ዘንድሮ የታዩትን እነዚህ ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ፍሬያማ በሚሆኑበት ላይ አተኩሮ መከበር ይኖርበታል፡፡
በፖለቲካው ዘርፍ ዘንድሮ የተከናወኑት እነዚህ ለውጦች ኢህአዴግ ማጠናከር ለሚፈልገው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ፋይዳቸው ከፍተኛ እንደመሆኑ ለውጦቹ የግንቦት ሀያ ስኬቶች ተደርገው ሊታዩ ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም የዘንድሮውን ግንቦት ሀያ በአል ሲያከብር ይህን ተስፋ ሰጪ ለውጥ እንዳጣጣመው ሁሉ በቀጣይም በልማቱ ስራም ሆነ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን አገሩን ለማልማት በመንቀሳቀስ ሊሆን ይገባል።

መልካም የግንቦት ሀያ በአል!!

ዘካሪያስ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።