የመድኃኒት ያለህ

16 May 2018

ከዓመት በፊት ነው፡፡ አንዲት የካንሰር ህመምተኛ ወይዘሮ በካንሰር የተጎዳውን የሰውነት አካባቢ በጨረር የማቃጠል (የኬሞቴራፕ) ህክምና ታዞላት ትከታተላለች፡፡ ይህ ህክምና በተለይም በመጀመሪያዎቹ ቀናት በጣም ከባድ ነው፡፡ ህመምተኞቹ ህክምናውን ሲጀምሩ ከባድ ስቃይን ለማሳለፍ ይገደዳሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ኬሞቴራፒ ሌላ የጤና እክል የሚያስከትል የጎንዮሽ ጉዳት አለው፡፡ ግን ያለው አማራጭ ይኸው በመሆኑ ህክምናውን መውሰድ ግድ ነው፡፡
የካንሰር ታማሚዋ ወይዘሮም ህክምናውን እየተከታተለች ሳለ ህመሙ ይፀናባታል፡፡ ምግብ መውሰድ በማቆሟ ግሉኮስ እንድትጠቀም ተደረገ፡፡ ይህም የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ወይዘሮዋ አቅሟ እየተዳከመ የመኖር ህልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ወደቀ፡፡ በዚህን ጊዜ ሃኪሞቹ አማራጭ ያሉትን ሃሳብ አቀረቡ፡፡ የወይዘሮዋ ሰውነትን ለማጠናከርና በሽታውን የመቋቋም አቅሟን ለመጨመር የሚረዳ ሌላ ግሉኮስ እንድትወስድ አዘዙላት፡፡
የታዘዘውን መድሃኒት ለማግኘት ታዲያ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር ታሪኩን ያወጋኝ ጓደኛዬ ነግሮኛል፡፡ የወይዘሮዋ ቤተሰቦች በየመድሃኒት ቤቶች ቢንከራተቱም መድሃኒቱን ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ የቤተሰባቸውን አባል ለመታደግ ያደረጉት ሩጫ በሚፈለገው ጊዜ ሊደርስ አልቻለም፡፡ በዚህም ሳቢያ ወይዘሮዋ እስከ ወዲያኛው ለማንቀላፋት ተገዳለች፡፡
ደረጃውና ህመሙ ቢለያይም የመድሃኒት እጦት (መጥፋት) ብዙዎችን ለከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ዳርጓል፡፡ ለህመማቸው መፍትሔ ፍለጋ ወደ ጤና ተቋማት አምርተው፣ ህክምናውን አግኝተው፣ የታዘዘላቸውን መድኃኒት በማጣት የሚሰቃዩ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ በፈታኝ ውጣ ውረድ የሕክምና ማዕከላት ሄደው የታከሙ ሰዎች ለህመማቸው ማስታገሻና መፈወሻ መድኃኒት ካላገኙ መታከማቸው ትርጉም አልባ ነው፡፡ በሕይወትና በሞት መካከል ሆነው ለሚያጣጥሩ ህሙማን ደግሞ የመድኃኒት መጥፋት ትልቅ አደጋ ነው፡፡
የመድኃኒቶች እጥረት ዜጎችን ለእንግልትና ስቃይ ከመዳረጉ በተጨማሪ ጥራታቸውና ጤንነታቸውን ያልጠበቁ፣ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ለገበያ እንዲቀርቡ በር ይከፍታል፡፡ ይህ ደግሞ ከህመሙ መዳንን ለሚሻ ዜጋ ሞቱን ከማፋጠን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ጊዜ ባለፈባቸው መድኃኒቶች ብዙዎች እስከ ወዲያኛው ማሸለባቸው ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የመድኃኒት እጥረት ትልቁ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በተለይም ከበሽታዎቹ ባህርይ አንፃር በየጊዜው ሊወሰዱ ግድ የሆኑ የስኳር በሽታ ዓይነት መድኃኒቶች (ኢንሱሊን) ከገበያ ላይ ጠፍተው ነበር፡፡ በዚህም በርካቶች ለስጋትና ድንጋጤ ተዳርገዋል፡፡ የልብና የአስም መድሃኒቶችም ከገበያው ተሰውረው በመቆየት ዜጎችን ማንገላታቸው አይረሳም፡፡ ከተለመደው ሂሳብ በላይ የገዙና ውጭ አገር የሚኖሩ ዘመዶች እንዲልኩላቸው የእርዳታ ድምፃቸውን ያሰሙም ጥቂት አይደሉም፡፡ ህመማቸውን ከማስታገስ ይልቅ ቁጭ ብለው መማረርና ማልቀስን ሥራቸው ያደረጉ በርካታ ናቸው፡፡ የመድሃኒት መጥፋት ብዙዎችን አንገላቷል፤አሰቃይቷል፡፡
ህብረተሰቡ መድሃኒቶችን በገበያ ላይ ባለማግኘቱ እሮሮ ከማሰማት አልፎ ተስፋ ወደ መቁረጥ ደረጃ ደርሷል፡፡ ‹‹አትመመኝ አይባልም…›› እንደሚባለው ሰው ፈልጎና ፈቅዶ አይታመምም፡፡ በሽታ በአጋጣሚ ይከሰታል፡፡ ይህን የጤና ጠንቅ ለመከላከልና ለማስወገድ ቀዳሚው እርምጃ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ነው፡፡ ባለሙያው ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ለታማሚው መድኃኒት ያዛል፡፡ ህመምተኛውም የታዘዘለትን መድኃኒት ለመግዛት ወደ መድሃኒት ቤት ያመራል፡፡ እዛ ደርሶ ‹‹መድኃኒቱ የለም››ሲባል ግን ህመሙ ይብስበታል፤ተስፋ ይቆርጣል፡፡
አጋጣሚውን በመጠቀም ኪሳቸውን ለመሙላት የሚጥሩ አንዳንድ ሙያዊ ሥነ ምግባር የጎደላቸውና ህሊናዊ ዳኝነትን የረሱ ግለሰቦች መኖራቸው ደግሞ እጅጉን ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች መድሃኒቶቹ ቀደም ሲል ሲሸጡ ከነበሩበት ዋጋ በእጥፍ አሳድገው ሲቸረችሩ ተስተውሏል፡፡ የሚገርመው ደግሞ የዋጋ ጭማሪው ጠፉ በተባሉት መድኃኒቶች ላይ ብቻ አለመወሰኑ ነው፡፡ ህገ ወጥ ጥቅም ፈላጊዎቹ ‹‹የመድኃኒት ዋጋ ጨምሯል›› በሚል የፈጠራ ምክንያት ዋጋ እየቆለሉ ይሸጣሉ፡፡ የታመመ አማራጭ የለውምና በተባለው ዋጋ ገዝቶ ይሄዳል፡፡ እነዚህ ህሊናቸውን ያሳወሩ ግለሰቦች በህዝቡ ህመም ኪሳቸውን ለመሙላት ይሯሯጣሉ፡፡ መድኃኒቶችን ደብቀው ‹‹የለም›› በማለት በህሙማን ህይወት ላይ ይቆምራሉ፡፡
ሌሎች ስግብግቦችና ግዴለሾች ደግሞ ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች ለተጠቃሚዎች በማቅረብ በወንጀል የተጠቀለለ ገንዘብ ለመሰብሰብ ይሯሯጣሉ፡፡ ሞትን የሚያፋጥኑ መድኃኒቶችን በመሸጥ ካዝናቸውን ይሞላሉ፡፡ የዜጎች መሰቃየትና መሞት ምናቸውም አይደለም፡፡ የመድኃኒቱ ገቢ ማምጣት እንጂ የአገልግሎት ጊዜው ማለፍ አያሳስባቸውም፡፡
የመድሃኒት እጥረት መባባስን ተከትሎ የፌዴራሉ የመድኃኒት አቅርቦት ፈንድ ኤጀንሲ ችግሩ የማስፈፀም አቅም ማነስ መሆኑን ሲናገር ተሰምቷል፡፡ ሆስፒታሎች፣ የከነማ መድሃኒት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት በዓመት አራት ጊዜ የመድሃኒት ግዥ መፈፀም ቢኖርባቸውም ይህን አለማድረጋቸው ለእጥረቱ ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ የተደራሽነት ችግርም ሌላው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
ይህን ለመፍታትም ኤጀንሲው መፍትሔ ያለውን አማራጭ ወስዷል፡፡ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር ስምምነት በመፈራረም መድኃኒቶችን በቀይ መስቀል መድኃኒት ቤቶች በኩል ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ በመሆኑም ቀይ መስቀል ከኤጀንሲው መድሃኒቶችን በብድር በመውሰድ ለገበያ ያቀርባል፡፡ ከኤጀንሲው የሚረከባቸውን መድሃኒቶችም በስር ባሉ 40 መድኃኒት ቤቶች ለህብረተሰቡ ያሰራጫል፡፡
የአገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾች የአቅም ውስንነትም ለመድኃኒት እጥረት እንደ አንድ ምክንያት ሲጠቀስ ተሰምቷል፡፡ አምራቾች የሚፈለገውን መድኃኒት በብዛት የማቅረብ የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው ቢገለፅም፤ እነሱ በበኩላቸው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ነው የተናገሩት፡፡ ይህም መድኃኒቶችን ከአገር ውስጥ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት መፈታተኑ አይካድም፡፡
በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የአገሪቱ የጤና ወጪ 33 በመቶ በዜጎች፣ 33 በመቶ በመንግስት 34 በመቶ በዕርዳታ እንደሚሸፈን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከ2007 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ኢትዮጵያ 36 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድሃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን ከለጋሾች በመቀበል ጥቅም ላይ አውላለች። መንግስት የመድኃኒት እጥረትን ለመከላከል 20 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ በኤጀንሲው በኩል ግዥ ያከናውናል፡፡
መረጃዎች ይህን ቢያመላክቱም አሁንም ታዲያ የመድኃኒት አቅርቦትና ፍላጎት አልተጣጣመም፡፡ ህብረተሰቡ በመድኃኒት ቤቶች፣ ጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች የሚፈልገውን መድኃኒት፤ በሚፈልገው ጊዜና መጠን እያገኘ አይደለም፡፡ ትላልቅ የሚባሉ የመንግስት ሆስፒታሎችና መድኃኒት ቤቶች በመድኃኒት ምች ተመትተው ሰንብተዋል፡፡
18ሺ የጤና ኬላዎች፣ አራት ሺ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች እንዳሏት የሚነገርላት ኢትዮጵያ የህክምና ተቋማቱ አስፈላጊዎቹን መድኃኒት ካልያዙ አገልግሎታቸው ከግማሽ አይዘልም፡፡ ህመምተኞች በህክምና ተቋማት ከምርመራ በተጨማሪ መድኃኒት ያስፈልጋቸዋልና፡፡ ተቋማቱ ይህን ማሟላት ካልቻሉ ተልዕኮዋቸው ከማማከር የዘለለ ውጤት አይኖረውም፡፡ ህመምተኛው በሽታውን አውቆ ተገቢውን መድኃኒት ካልወሰደ ውጤቱ ባዶ ነው የሚሆነው፡፡ እናም የህክምና ተቋማት ለምርመራና ከምርመራ በኋላ የሚሰጡ መድኃኒቶችን አሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡
ይህን ችግር የመፍታቱ ጥረት በደንብ ሊጠናከር ይገባል፡፡ ጉዳዩ የአንድን አካል ጥረት ሳይሆን የብዙዎችን የተባበረ ክንድ ይፈልጋል፡፡ መድኃኒት ቤቶች፣ አምራቾች፣ አቅራቢዎችና አከፋፋዮች የድርሻቸውን ሊወጡ ግድ ይላል፡፡ መድኃኒትን በመግዛት የሚያቀርበው መንግስታዊው የመድኃኒት አቅርቦት ፈንድ ኤጄንሲ ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ የእጥረቶችን መንስዔ በማጣራት ለመፍትሔ መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ ወቅታዊ የመድኃኒት ፍላጎትን መሰረት ያደረገ አቅርቦት እንዲኖር መስራት አለበት፡፡
መድኃኒት ቤቶች የሙያውን ሥነ መግባር ጠብቀውና ህጉን አክብረው መድኃኒቶችን ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ መድኃኒቶችን በመከዘን በሰው ህይወት ላይ በመቆመር የተሻለ ገንዘብ ፍለጋ የሚማትሩ አንዳንድ ግለሰቦችም ከህገ ወጥ ድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው፡፡ የጥራት ደረጃውን የጠበቀና ጤናማነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት በፍትሃዊ ዋጋ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ግድ ይላል፡፡ የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች አቅማቸውን በማጠናከር የመድኃኒት እጥረት እንዳያጋጥም የቤት ሥራቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ‹‹የመድሃኒት ያለህ›› ለሚለው ዜጋ መድረስ አለባቸው፡፡ በሂደቱም መድኃኒቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የተያዘውን ዕቅድ ያሳካሉ፡፡
ለመድኃኒት እጥረት ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች በመለየትና በመፈተሽ አፋጣኝና ዘላቂ መፍትሔዎችን ማስቀመጥ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶች በማረምና ጉድለቱን በመሙላት በቂና የጥራት ደረጃውን የጠበቀ መድኃኒት ለተጠቃሚዎች ለማድረስ መስራት ይገባል፡፡ በ‹‹መድኃኒት ያለህ›› የሚሰቃየውን ዜጋ ፍላጎት ለማረጋገጥ ትግሉ መፋፋም ይኖርበታል፡፡ በተለይም መድኃኒትን በመከዘን በሰው ሰራሽ ምክንያት እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር በደንብ መጠናከር አለበት፡፡ ለዚህ የሚረዳ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

ሠላም ዘአማን

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።