የ‹‹ሞት አልባው ጦርነት›› መቋጫ

11 Jun 2018

ኤርትራ የራሷን ሉኣላዊ አገርና መንግስት ከመሰረተች 27 አመታት ብታስቆጥርም ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት ከተቋረጠ ደግሞ 20 አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በነዚህ አመታት ጦርነት፣ የህዝቦች መለያየት፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት፣ የድንበር አካባቢ ውጥረት ወዘተ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ እነዚህ  ችግሮች እንዲወገዱ ግን በኢትዮጵያ በኩል ተደጋጋሚ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ለቀረበው የሰላም ጥሪ በኤርትራ በኩል ተገቢው ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ግን የሰላም ጥሪውን አላቆመም፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሃላ ቢፈፀሙ እለት የኤርትራን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አብይ አጀንዳ አድርገው ማንሳታቸው ይታወቃል፡፡ ይህንን ተከትሎም ይህ የሰላም ጥሪ በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል፡፡
የሁለቱን አገራት የኋላ ታሪክ ስንመለከት ጥብቅ ቁርኝት እናገኛለን፡፡ ሁለቱ አገራት በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት በላቀ ደረጃ የጋራ እሴቶች የገነቡ ናቸው፡፡ በተለይ በህዝቡ መካከል የነበረው መስተጋብር ሁለቱን አገራት በጥብቅ ያቆራኘ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቁርኝቱ በአንድ መንግስት ስር ለዘመናት መኖራቸው ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ህዝብ ዕርስ በርሱ መዋለዱና ተመሳሳይ ባህል፣ቋንቋ፣ የአኗኗር ዘይቤ እና ማህበራዊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች በመኖራቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ እስካሁንም ድረስ ስለኤርትራዊ ሲነሳ እንደ አንድ የኢትዮጵያ አካል የሚሰማቸው በርካታ ዜጎች አሉ፡፡ ይህ የተፈጠረው ደግሞ የጋራ እሴት የወለደው ዝምድና ነው፡፡
ባለፉት 20 አመታት ግን ይህ የሁለቱ አገራት ነባራዊ ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ ሁለቱ አገራት ወደ ግጭት መግባታቸው ብቻ ሳይሆን ከግጭቱ በኋላም ቢሆን ችግሮቻቸውን ፈትተው ወደ መልካም ጉርብትና ለመምጣትና ለዘመናት የቆየውን የሁለቱን አገራት ህዝቦች ጥብቅ ቁርኝት ለመመለስ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ በዚህ የተነሳም ሁለቱ መንግስታት እንደ ጠላት የሚተያዩና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እየተመለከተ አጠገቡ እንደተቀመጠ ፈንጂ የሚያይበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ለሚገኙ ህዝቦችም ሆነ በአካባቢው ለተሰማሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የዘወትር የቤት ስራ ሆኖ እቅልፍ የማያስተኛ የስጋት ቀጠና እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ከዚህም ባሻገር በሁለቱ አገራት ግጭት ምክንያት ያለሃጢያታቸው ከሁለቱ አገራት ዜጎች  በመወለዳቸው ብቻ መብታቸው ተነፍጎ አንዱ የሌላውን ወገንና ዘመድ እንዲሁም ቤተሰቡን ለማየት ያልቻለበት አሳዛኝ ሁኔታዎችም የዚህ የሁለቱ አገራት ሰላም አልባ መሆኑን ውጤቶች ሆነው  ቆይተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ከማውቃቸው ታሪኮች አንዱን ላውጋችሁ፡፡
አቶ ገብረየሱስ በየነ የተወለዱት በትግራይ ቢሆንም አብዛኛውን እድሜያቸውን የኖሩት በአስመራ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም የተከታተሉት በዚህችው ባደጉባት ከተማ ነበር፡፡ ከኤርትራዊት ባለቤታቸውም ጋር እስከሚለያዩ ድረስ በዚህችው ከተማ በፍቅርና በሰላም ኖረዋል፡፡ ሶስት ልጆቻቸውንም የወለዱት በዚህችው ከተማ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን  የመለያየት ወቅት መጥቶ እሳቸውን ወደ አዲስ አበባ ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ደግሞ አስመራ ለያይቶ እነሆ ለአስራ ሰባት አመታት የናፍቆትና የብቸኝነት ኑሮ እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል፡፡ አቶ ገብረየሱስ “ሁል ጊዜ ልጆቼ ይናፍቁኛል፡፡ ልጅን የሚያክል ነገር በባዕድ አገር ትቶ ነገ እንገናኛለን በማይባልበት ሁኔታ መኖር ከሞት አይተናነስም” ይላሉ፡፡ “አሁን የተጀመረው ሁለቱን አገራት የማገናኘት አጀንዳ ምነው ፈጥኖ እውን በሆነና ከልጆቼ ጋር ተገናኝቼ በሞትኩ” በሚልም ያላቸውን የልብ መሻት በጉጉት ይናገራሉ፡፡
ሌላዋ ወጣት ብርክቲ አስፍሃ ደግሞ አባቷ ኤርትራዊ በመሆናቸውና በግጭቱ የተነሳ ወደ ኤርትራ በመሄዳቸው የአባቷን ፍቅር ሳታገኝ ላለፉት 20 አመታት መኖሯን በሃዘን ታስታውሳለች፡፡ ብርክቲ “ባለፉት 20 አመታት እኮ በርካታ ቤተሰቦች ተበታትነዋል፤ እስኪ አስቡት በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሰዎች የሚጋቡት ዘርን ቆጥረው አልነበረም፡፡ በዚህ የተነሳ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረች ሰዓት በርካታ ኤርትራዊያንና ኢትዮጵውያን ተዋልደዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ሁለቱን አገራት ለመለየት እኮ በጣም ከባድ ነው፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ የሁለቱ አገራት ግጭት የአንድ ቤተሰብ መበተን ማለት ነው፡፡ ቤተሰብ ሲበተን ደግሞ ምን ያህል ልጆች ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ማስታወስ ግድ ይላል”ትላለች፡፡
በርግጥ ከግጭቱ በኋላ ሁለቱን አገራት ለማስማማት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ በኩል በታላቁ መሪ መለስ ዜናም ሆነ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሰላም ስምምነት ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡ እነዚህ የሰላም ጥረቶች ግን በጎ ምላሽ ባለማግኘታቸው ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ቁርሾ እንዲያበቃ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚያም በዘለለ የሰላም ድርድሩ እንዲሳካም ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
ሰሞኑን በተካሄደው ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባም የሰላሙን ስምምነት እውን ለማድረግ በኢትዮጵያ በኩል እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ማናቸውንም ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ ኮሚቴው ባካሄደው ስብሰባ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበል አስታውቋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ለሰላም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ቁርጠኛ መሆኗን ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የኤርትራ መንግስት ይህንን የሰላም ጥሪ ሊቀበል ይገባል፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ይህንን ላለመቀበል የሚያስችል ምንም አይነት ምክንያት አይኖርምና፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ረቡዕ አገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጉባኤ ሲካሄድ ባደረጉት ንግግራቸው ውስጥ የኤርትራን ጉዳይ አንስተው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ሁኔታ ‹‹ ሞት አልባ ጦርነት›› ሲሉ ገልፀውታል፡፡ ለዚህም ያቀረቡት ምክንያት ባለፉት 20 አመታት በአካባቢው የነበረው ነባራዊ ሁኔታ ማሳያ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
በነዚህ አመታት በአካባቢው ሰላም ባለመኖሩ ሁሉም ለጦርነት የሚያስፈልጉ ወጪዎች፣ ሁሌም ዝግጅት፣ ሁሌም ስልጠናና ውጥረት እንደነበር በማስታወስ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይም የስነልቦና ስቃይ ሆኖ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ባለፉት 20 አመታት ከኤርትራ ጋር በነበራት ግንኙነት ያተረፈችው ውጥረት ብቻ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ደግሞ ሁለቱም አገራት ተጎጂዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን የሰላም እጦት ለመፍታት ባለፉት ሁለት ወራት በተደረጉ ጥረቶች የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ሰላም በአፍሪካ ቀንድም ያስፈልገናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት እንዲስተካከል በኛ በኩል መስራት ያለብንን ስራ መስራት ይገባናል የሚል መልዕክትም አስተላል ፈዋል፡፡
ስለዚህ ሙሉ አቅማችንንና ጉልበታችንን ወደ ሰላም፣ ወደ ፍቅር እንዲሁም ወደ እርቅ ለማሸጋገርና የኢትዮጵያን ህዳሴ እውን ለማድረግ ሃሳባችንን ከሚከፋፍሉ ማናቸውም ነገሮች ሁሉ ወጥተን ፊታችንን ወደ ዋነኛው የአገራችን ጠላት ወደሆነው ድህነት በማዞር የኢትዮጵን እድገት፣ ሰላም እና ብልፅግና ለማረጋገጥ በጋራ እንድንሰራም ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው ካነሷቸው ሃሳቦች መካከል አንዱ የሁለቱን አገራት ቀጣይ አቅጣጫ የሚያመላክት ነው፡፡ “በአስመራና በአዲስ አበባ መካከል አውቶቡስና ባቡር እንዲመላለስ እፈልጋለሁ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ይህ የተስፋ ቃል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር ኢትዮጵያ ምን ያህል ለሁለቱ አገራት ግንኙነት ጠንክራ እየሰራች መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡
በአገራችን “አንድ በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” የሚል አባባል አለ፡፡ ይህ አባባል ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ አገራት የተረጋጋ ሰላም፣ ልማትና እድገት እንዲያስመዘግቡ ሰላም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ነገር ግን በርካታ ሰላም ፈላጊ በተሰበሰበበት ሁኔታ አንድም ቢሆን ሰላምን የሚያደፈርስ አካል ካለ ሰላም ሊመጣ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያም ዋነኛ አጀንዳዋ ሰላምን ማስፈንና በዚህም ሰላም ውስጥ የህዝቦችን እድገትና ብልፅግና ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ በውስጥም ሆነ በውጭ ያለውን የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ  ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ባለፉት ሁለት ወራት በአገራችን ሰላም እየሰፈነ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጭምር እስከማንሳት ደርሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ስንመለከትም ሰላማዊ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት ከኤርትራ በስተቀርም የነበረው ግንኙነት በጠንካራ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱ ለጀመረችው የልማት እንቅስቃሴ እውን መሆን ከፍተኛ አወንታዊ ሚና ያለው ነው፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከኤርትራም ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ስኬታማ ለማድረግ ከመንግስት በተጨማሪ ምሁራን፣ አገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ግለሰቦች የሚሳተፉበት አንድ ድርጅትም ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል፡፡ ሰለብረቲ ኢቨንትስ በሚል የሚታወቀው ይህ ድርጅት በተለይ የሁለቱ አገራት ህዝቦች የጉዳዩ ባለቤቶች በመሆናቸው ግፊት ማድረግ አለባቸው በሚል የሁለቱን አገራት ህዝቦች ያስተሳሰረ ግንኙነት ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡
ይህ ሁለቱን አገራት የማቀራረብ እንቅስቃሴ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በምስራቅ አፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ጉዳይ ላይ ለበርካታ አመታት ምርምሮችን ሲደርጉ የቆዩትና በእንግሊዝ ኪንግስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት  ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት  የሁለቱ አገራት ግጭት በአካባቢው ሰላምም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ያስከተለ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡
እነዚህ አገራት በግጭት ውስጥ መቆየታቸው የሁለቱን አገራት ህዝቦች በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳና የህዝቦችን ነፃነት የገደበ ተግባር ከመሆኑን ባሻገር የምስራቅ አፍሪካ አካባቢን ወደ አንድ ለማምጣት በሚደረገው አህጉራዊ ጥረትም እንቅፋት ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ አገራት ግጭት ሊበቃ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ለሁለቱም አገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡
የሁለቱ አገራት ግጭት በሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንጻርም ያስከተለው ችግር ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ የወደብን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል፡፡ ኤርትራ የያዘችው አሰብም ሆነ የምፅዋ ወደቦች ለኢትዮጵያ የተሻለ ስትራቴጂያዊ ቦታዎች ናቸው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት በሰላም ላይ የተመሰረተ ቢሆን ኢትዮጵያ እነዚህን ወደቦች ለመጠቀም ያስችላታል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡
በሌላ በኩል ኤርትራም ቢሆን ከዚህ ወደብ ይበልጥ ጥቅም ልታገኝ የምትችለው ከኢትዮጵያ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ እነዚህ ሁለት ወደቦች ለኢትዮጵያ በሚሰጡት ጠቀሜታ ኤርትራ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ማግኘት ያስችላታል፡፡
በአጠቃላይ በሁለቱ አገራት መካከል ከ17 አመታት በላይ የዘለቀው “ሞት አልባ ጦርነት” ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የዳረገ ነው፡፡ በተለይ አፍሪካን በተለያዩ የልማት ኮሪደሮች ለማስተሳሰር ዘርፈብዙ የልማት ስራ እየተሰራ በሚገኝበትና በዚህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች በምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ በአካባቢው የሚፈጠር ሰላም ለሁለቱም አገራት ከሚሰጠው ጠቀሜታም ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ እና ለአፍሪካ ጭምር ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ በአካባቢው ሰላምን መፍጠር ጠቃሚ ነው፡፡

ውቤ ከልደታ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።