በተግባር ያልፈተሸው መመሪያ

12 Jun 2018

“ መቀመጥ መቆመጥ” ይላሉ አበው ሲተርቱ፡፡ ጥሎብኝ መቀመጥ አልወድም፡፡ ምንም ዓይነት ቀጠሮም ሆነ ሌላ ማህበራዊ ጉዳይ ባይኖረኝም ማለዳ ተነስቼ ከተማዋን ማካለል ምርጫዬ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከድንጋይ ድንጋይ የምዘልበት ወቅት እየጠወለገ ቢሆንም በፍጥነት እጅ መስጠትን የስንፍና መገለጫ መሆኑን እራሴን አሳምኘዋለሁ፡፡ በመሆኑም ሁልጊዜ ማለዳ ከምኖርበት ሰፈር በመነሳት በትንሹ እስከ አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር ደርሶ መልስ እጓዛለሁ፡፡ በነገራችን ላይ በቀን ቢያንስ ለ30 ደቂቃ ያህል በእግር መጓዝ ለጤና ጠቃሚ መሆኑን ከህክምና ባለሙያዎች ስለምሰማ የእግር ጉዞዬ ትርፍ እንጅ ኪሣራ እንደሌለው ተረድቻለሁ፡፡
የጽሁፌ ዋነኛ ማጠንጠኛ ግን በአሁኑ ወቅት የብዙ ወገኖቻችንን ህይወት እየቀማ ያለውን የትራፊክ አደጋ መዳሰስ ይሆናል፡፡ ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አደጋዎችም የሚከሰቱበት በመሆኑ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በገዳይነታቸው ከሚጠቀሱት ተላላፊና የማይተላለፉ በሽታዎች ባልተናነሰ የመኪና አደጋ አንዱ ገዳይ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡
ተምረው ሀገር ይረከበሉ ተብለው የሚጠበቁ ወጣቶች፣ጎልማሶች፣አረጋዊያንና ሌሎችም የህብረተሰቡ አካላት እንደወጡ መቅረት የተለመደ ሆኗል፡፡ በርከት ያለ ቁጥር የያዙት ወገኖቻችንም የአካል ጉዳት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ውሱን በሆነው የሀገሪቱ ንብረት ላይም ከፍተኛ ውድመት እየደረሰ ነው፡፡
ለትራፊክ አደጋው ገፊ ከሆኑት ምክንያት መካከል ጠጥቶ ማሽከርከር፣ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት፣ እግረኞች በሚጓዙበት ወቅት ግራና ቀኙን አለመመልከት፣ ጎን ለጎን የሚሽከረከሩ መኪናዎችን/ማለትም ተደርበው የሚሽከረከሩ/ መኪናዎችን መዘንጋት፣በሀሳብ ተውጦ የመኪና መንገዶችን ማቋረጥ ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም የመኪና መንገዶች መጥበብ፣ የእግረኞችና የተሸከርካሪዎች መንገዶች መደባለቅና የዜብራ መንገዶች ክትትል ማነስ ተጠቀሾች ናቸው፡፡ በተጨማሪም እንደ ቀበቶና ሌሎች ተዛማጅ የቁጥጥር ደንቦች አለመከበር በምክንያትነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ባደጉት ሀገራት ሙዝየም ላይ የገቡ ከ60-70 ዓመት ያስቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ከመንገድ ስለመውጣት ኃላፊነቱ በጎደለው ሁኔታ ለማይገባቸው ሰዎች መንጃ ፈቃድ መስጠት አደጋው እንዲይባባስ አድርጓል፡፡ የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የትራፊክ አደጋውን ለመቀነስ በተለያያ ወቅት መመሪያዎችን ቢያወጣም፣ነገር ግን የመመሪያው ተግባራዊነት ማንኛውም አሽከርካሪ ቀበቶ ማድረግ ግዴታ እንደሆነ ማንኛውም አሽከርካሪ እየነዳ ሞባይል ስልክ ማውራት በህግ እንደሚያስቀጣ ዜብራ መንገዶች ላይ ለእግረኞች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ተደንግጎ ነበር፡፡ እንዳቸውም ግን በተግባር ሲውሉ አይታዩም፡፡በተዘዋወርኩባቸው አንድ አንድ ስፍራዎች እነዚህ መመሪያዎች አለመተግበራቸው መታዘብ ችያለሁ፡፡ በርካታ አሽከርካሪዎች ቀበቶ አያደርጉም፣ ያደረጉትም ቢሆን ለደንቡ ያህል ይመስላል፡፡ በህግ አስከባሪው በኩል ተደጋግሞ እንደ ተነገረው ቀበቶ መጠቀም ለእግረኛው ብቻ ሳይሆን አሽከሪካሪውንም ከክፉ አደጋ ይታደጋል፡፡
« ከጠጡ አይንዱ ከነዱ አይጠጡ» የሚለውን የቆየ ይትበሃል እንዳለ « እየነዱ በሞባይል እያወሩ፣ ማውራት፣ከፈለጉ ደግሞ መኪናዋን ወደ ዳር አውጥቶ እንደፈለጉ ያውሩ» የሚለው ቢታከልበት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በርካታ አሽከርካሪዎች ቀበቶ ማድረጉን እርግፍ አድርገው የተውት ስለመሰለኝ ነው፡፡ በተለይ የትራፊክ መጨናነቅ በሚኖርበት ጧትና ማታ በተቻለ መጠን የተገኘውን ጠባብ እድል ተጠቅሞ መንገዱን መልቀቅ ሲገባ የቤት ጣጣም ሆነ የፍቅር ወሬ ማውራት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ « ለሁሉም ጊዜ አለው»እንደተባለው ለእነዚህ ማህበራዊ መስተጋብሮች ቦታና ጊዜ ብንመርጥላቸው ሁሉንም የሚያግባባ ይመስለኛል፡፡ የዜብራ መንገዶችን በተመለከተም የታዘብኩትን ለአንባቢዎቼ ሳልጠቁም አላልፍም፡፡
የዜብራ መንገዶች ዋነኛ ዓላማ እግረኞችና አሽከርካሪዎች ተጠባብቀው እንዲታላለፉ ይመስለኛል፡፡ በተዘዋወርኩባቸው ሥፍራዎች እንደታዘብኩት ግን በርካታ አሽከርካሪዎች ለእግረኞች ቅድሚያ ሲሰጡ አላስተዋልኩም፡፡ ህፃናት በተለይ ዕድሜ ጠገቦቹ በከዘራ የሚንቀሳቀሱ አረጋውያን የዜብራውን ጠርዝ ይዘው ቆመው እያዩ አንዳችም ርህራሄ የሌላቸውን አሽከርካሪዎች መታዘብ ችያለሁ፡፡ «ህፃናት ተዋቸው ወደኔ ይመጡ ዘንድ »በማለት ፈጣሪ ክብር ለሰጣቸው ታዳጊዎች ያልራራ ልብ ምን ይሉታል? አረጋዊያኑንስ ቢሆኑ በየተሰማሩበት የስራ መስክ የድርሻቸውን ተወጥተው በማረፊያ ጊዜያቸው ለምን ቅድሚያ አያገኙም?
በደንብ አስከባሪው በኩል ህፀፅ መስሎ የታየኝንም መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ የዜብራ መንገዶችን አሽከርካሪዎች ትኩረት ቢነፍጉትም ለእግረኞች ትልቅ ጥቅም እንዳለው እኛ እግረኞች በደንብ እናውቀዋለን፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል መመሪያው ውሎ ሲያድር መከበሩ ቀረ፡፡ የሚመለከታቸው አካላትም ዜብራ መንገዶች ቀደም ሲል የተቀቡት ቀለም በመጥፋት ጥቁር ሰሌዳ መስሎ እየተመለከቱ እርምጃ አልወሰዱም፡፡ እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛነሽ እንደተባለው፣እንኳን የዜብራው መንገድ ምልክት ጠፍቶ ቦግ ብሎ እየታየም እንኳን ደንቡ መከበር ተስኖታል፡፡
በኢትዮጵያ የመንገድ ትራፊክ አደጋዎች አዝማሚያ መንስኤና የሚያስከትሉትን /የሚያስከፍሉትን/ዋጋ በተመለከተ በዘርፉ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው እአ.አ ከ2006-2015 በአሮሚያና በአዲስ አበባ ከፍተኛ የሞት አዳጋ ተመዝግቧል፡፡
ከፌዴራል መንገድ ባለስልጣን ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ የተካሄደው ይኸው ጥናት እንደጠቆመው በተለይ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ዋነኛ ተጎጆች እግረኞች ናቸው፡፡ እንደ ጥናቱ ግኝት ከሆነ ለአደጋው መከሰት ከፍተኛውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት በዋናነት አሮጌ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ እንዲሁም ጠጥቶ መንዳት፣ በቂ ሥልጠና ሳያገኙ መንጃ ፈቃድ ማግኘትና የትራፊክ መመሪያው ያስቀመጣቸውን ክልከላዎች አለመተግበር ይገኝበታል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የትራፊክ አደጋ የህዝብ ጤና እና የልማት ጉዳይ በመሆን ላይ እንደሚገኝ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የትራፊክ አደጋው የመንግስት፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የቢዝነስና የማህበረሰብ አመራሮችን ትኩረት እየሳበ መምጣቱም አመልክቷል፡፡
በዓለም አቀፍ ጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ6ነጥብ25 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በትራፊክ አደጋ እየሞተ ነው፡፡ ከእነዚህ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ ከ30 እስከ 70 ከመቶ እንደሚሆን ሪፖርቱ ግምቱን አስቀምጧል፡፡ የትራፊክ አደጋ በመላው ዓለም በገዳይነታቸው ከሚታወቁት የበሽታ ዓይነቶች ተከትሎ በዘጠነኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ የትራፊክ አደጋው እአ.አ በ2030 ሰባተኛው ገዳይ እንደሚሆን ግምት ተሰጥቷል፡፡ አደጋው በተለይ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የከፋ ሲሆን፣ በነዚሁ ሀገራት እስከ 5 ከመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ዓመታዊ ገቢ እንደሚያሳጣ ተመልክቷል፡፡ ይህም በተለያዩ ድጋፍ ሰጭ ሀገራት ለልማት የሚያገኙትን እርዳታ ከእጥፍ በላይ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ ሀገራትን በተመለከተ ክፍለ ሀገሩ ከሌሎች ክፍላተ አህጉራት ከፍተኛውን የሞት አደጋ የያዘ ሲሆን ይህም በመቶኛ 26 ነጥብ 6 ከመቶ መሆኑን ጥናቱ ገልጿል፡፡ በአህጉሩ የሚገኙት ተሽከርካሪዎች መጠን በዓለም ላይ 2 ከመቶ ያልዘለለ ሆኖ ሳለ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአደጋው መጠን 16 ከመቶ መሆኑ አነጋጋሪ እንደሆነም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
በከፍተኛው የከተሜነትና የተሽከርካሪ ትርምስ አህጉሩ ወደፊትም ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ሞት የሚከሰትበት እንደሚሆን የጥናቱ ትንበያ አስቀምጧል፡፡ በኢትዮጵያም የትራፊክ አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲቀመጥ ከፍተኛ ስፍራ መያዙን ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
በድርጅቱ ጥናት መሰረት እ.አ.አ በ2013 ብቻ 4984 ነጥብ 3 የሞት አደጋ ተመዝግቧል፡፡ ይህም ከሰሀራ በታች ከሚገኙት ሀገራት በእጅጉ እንደሚበልጥ ተመልክቷል፡፡ ጠቅለል ብሎ ሲቀመጥ የትራፊክ አደጋ እየከፋና መጠኑም ከጊዜ፣ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑን ነው ጥናቱ ያስረዳው፡፡
በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋ ከአስሩ ከፍተኛ የሞት መንስኤዎች አንዱ መሆኑንም ገልጿል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ እ.አ.አ በ2013 በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ያጡት ዜጎች ቁጥር በሀገሪቱ በወባ ከሞቱት ዜጎች እኩል መሆኑን አመልክቷል፡፡ በመሆኑም የትራፊክ አደጋ ሞትና የአካል ጉዳት ችግሩን ለማስወገድ ጠንካራ እርምጃ ካልተወሰደ የኑሮ መሰረትና የምጣኔ ሀብት መጉዳቱን እንደሚቀጥል ጥናቱ ገልጿል፡፡ የትራፊክ አደጋው ቀደሞውኑ በበቂ ሁኔታ ባለአደገው ብሔራዊ የምጣኔ ሀብት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነና የችግሩ አስፈሪነትና ስፋት አደጋም መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ የትራፊክ አደጋውን ለመቀነስ አስገዳጅነት ያለው የመንገድ ደህነትና ህግ ተግባራዊ ማድረግ፣ ለአሽከርካሪዎችም ሆነ ለእግረኞች የአቅም፣ የግንዘቤ ማዳበሪያ ስልጠና መስጠት፣ በመንግስትና በባለድርሻ አካላት መካከል ጠቁሟል፡፡ እንዲሁም መንገዶችና አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህጉን በማክበር ሊንቀሰቀሱ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡ ከምንም በላይ ህይወት ለመታደግ ዘመኑን የተከተለ የትራፊክ ምልክቶች በተገቢው ቦታ ማስቀመጥ ለነገ የማይባል እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት የትራፊክ አደጋ ሞት የከፋ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በዘርፉ በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ አለም አቀፋዊ አህጉራዊና ክልላዊ ጥናት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ጉዳቱ የትየሌሌ ነው፡፡ በትራፊክ አደጋው ገና ሮጠው ያልጠገቡ ታዳጊዎች እንደወጡ ቀርተዋል፡፡
ሀገሪቱ በሌላት አቅም የአስተማረቻቸው ወጣቶችና ጎልማሶች በትራፊክ አደጋ ውድ ህይወታቸውን እያጡ ነው፡፡ የተለያየ እውቀት ያላቸው ዜጎች የመኪና አደጋ ሰለባ እየሆነ ነው፡፡ የሀገሪቱ ውስን ሀብትም ከምንም በላይ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ከድህነት አረንቋ ለመውጣት ደፋ ቀና በምትልበት ወቅት የችግሩ መጠን ብሶ መቀጠሉ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሊያስብበት ይገባል፡፡ ስለሆነም ባለድርሻ አካላት መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራትና ሌሎችም ጉዳዩ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በተለይ የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን በጊዜው የሚያወጣቸውን መመሪያዎች ተግባራዊነት መቆጣጠር ይገባዋል፡፡ ህግና ደንብ ማውጣት በራስ ግብ አለመሆኑን ባለስልጣኑ ተገንዝቦ በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ለነገ የማይባል ነውና ትኩረት ይሰጥ፡፡

ከገላውዲዮስ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።