ሠላምና ወዳጅነትን ያስቀደመ ውሳኔ

13 Jun 2018

በ1990 ዓ.ም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተከሰተው የድንበር ጦርነት የሁለቱን አገራት የቀደመ የወዳጅነት ታሪክ ወደ ደም አፋሳሽነት በመቀየር ጥቁር ጥላውን አጥልቶ አልፏል፡፡ በጦርነቱ ከሁለቱም አገራት እስከ 70 ሺ የሚጠጉ ወገኖች ህይወታቸውን ማጣታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለከባድ የአካል ጉዳት የተዳረጉትም ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ጦርነቱ ከፍተኛ የንብረት ውድመትንም አስከትሏል፡፡
የአገራቱን ቅራኔ በህግ አግባብ ለመፍታት በወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በወቅቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያና ኤርትራ ከዛቻና ከኃይል ዕርምጃ ተቆጥበው በ1993 ዓ.ም በተፈረመው የአልጀርሱን የሠላም ስምምነትን መሰረት ገለልተኛ የድንበር ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ ይህን ተከትሎም አምስት አባላት ያሉት የድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ የሁለቱን አገራት ድንበር ይግባኝ በሌለው ውሳኔ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት እንዲፈፅም አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ኮሚሽኑም በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ሥራዉን አጠናቋል፡፡ ደንበሩን በወረቀት ላይ አስፍሯል፡፡ ሁለቱ ሃገራት ውሳኔውን ይተገብሩ ዘንድ ለሁለቱም ሃገራት ውሳኔውን ሰጥቷል፡፡
በደንበር ኮሚሽኑ በወረቀት ላይ በአሰፈረው ደንበር ማካለል ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ፣ ከኤርትራም ወደ ኢትዮጵያ የተካለሉ ቦታዎች አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በሁለቱም አገራት ግጭት መነሻ የሆነችው ባድመን እና የኢሮብ የተወሰኑ ቦታዎች ወደ ኤርትራ ያካለለ ሲሆን፣ በጾረናና በሌሎች አካባቢ ያሉ የኤርትራ ቦታዎችንም ወደ ኢትዮጵያ በማካለል ሥራውን ማጠናቀቁን አሳወቀ፡፡
ኢትዮጵያ ውሳኔውን ተቀብላ በአፈፃፀሙ ዙርያ ከኤርትራ ጋር ተጨማሪ ድርድር ማድረግ እንደምትፈልግ በወቅቱ አሳወቀች፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶችን አቀረበች፡፡ በውሳኔው መሰረት ድንበር የማካለል ሥራው ከተከናወነ ቤቶች፣ መቃብሮች ቤተ ክርስቲያናት ለሁለት የሚከፈሉበት እውነታ ስላለ አፈፃፀሙን በድርድር መፍታቱ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ተጨባጭ ምክንያት በማቅረብ አስገነዘበች፡፡ ኤርትራ ግን የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ እንደ ወረደ ተቀብሎ ከመተግበር ውጪ ሌላ ድርድር አያስፈልግም በማለቷ ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ 17 ዓመታትን አሳልፏል፡፡ በዚህም የተነሳ አካባቢው ጦርነትም ሠላምም የሌለበት ቀጣና ሆኖ ቆይቷል፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ተፈትቶ ሠላም እንዲወርድ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓመታትና አጋጣሚዎች የሠላም ጥሪ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በመንግሥት ከተደረገው ጥሪ ባሻገር የኢትዮጵያና የኤርትራ ምሁራንን ያሳተፈ መድረክ በማዘጋጀት ወንድማማችና እህትማማች ሕዝቦችን ለማቀራረብ ጥረት ተደርጓል፡፡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የሀገር ሽማግሌዎች የሁለቱን አገራት የቀደመ ታሪክ ለመመለስ የበኩላቸውን ሞክረዋል፡፡
እውነታው ይህ ቢሆንም ግን የኤርትራ መንግሥት ለሠላሙ ጥሪ ጀርባውን ከመስጠት ባለፈ ጉዳዩን ለመቀበል ፍቃደኛ ሲሆን አልተስተዋለም፡፡ በዚህም የተነሳ እስከ አሁን ድረስ በሁለቱ አገራት መካከል የተናፈቀው ሠላም ሳይወርድ ቆይቷል፡፡ በፖለቲካው ቀውስ የሚነፋፈቁት ህዝቦችም ተስፋን ሰንቀው ከመጓዝ ያለፈ ምንም ሊያደርጉ አልቻሉም፡፡
ሰሞኑን ታዲያ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ በመቀበል ለተግባራዊነቱ እንደምትሠራ አረጋግጧል፡፡ ለ17 ዓመታት የጥላቻ ግድግዳ የሆነውን ምክንያት ተቀብሎ ለሠላም መዘጋጀቱን በይፋ አድርጓል፡፡ የኤርትራ መንግሥትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ አሳስቧል፡፡ የኤርትራ መንግሥት የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሠራ ጥሪ ቀርቧል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ታዲያ ከኤርትራ መንግሥት የተሰጠ ግልጽ ምላሽ የለም፡፡
እንደሚታወቀው ለኢትዮጵያ ዕድገትና ለሕዝቦች ተጠቃሚነት ሰላም ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ውሳኔውም ይህን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ፋይዳው እጅጉን ሚዛን ይደፋል፡፡ ምክንያቱም ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነውና፡፡ ኢትዮጵያና ሠላም ደግሞ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ስም ሲነሳ ለሠላምና ነፃነት የምትሰጠው ቦታ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል፡፡ ከራሷ አልፋ ለምትገኝበት አህጉርና ዓለም ሠላም ትጨነቃለች፡፡ ለዚህም ግጭትና አለመረጋጋት በተከሰተባቸው የተለያዩ አገራት ሠላምን ለማስከበር ያደረገችውና እያደረገች ያለው ተሳትፎ ምስክር ነው፡፡
የአልጀርሱ ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ አለመደረጉ በአካባቢው ልማት እንዳይከናወን፤ ዜጎች በየዕለቱ በስጋት ውስጥ ተውጠው እንዲያሳልፉ አስገድዷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ደግሞ ሙሉ አቅሟን ወደ ልማት በማዞር የሚጠበቅባትን እንዳትወጣ የበኩሉን አሉታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱ አይካድም፡፡ እልባት ያላገኘ ጉዳይ ለልማት እንቅፋት መሆኑ ግልጽ ነውና፡፡ ዘላቂ መፍትሔ ያልተበጀለት ጉዞ ጊዜ ከመፍጀትና ጥላቻን ከማግዘፍ በስተቀር ለሁለቱም ህዝቦች የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም፡፡
ኢትዮጵያ ወደዚህ ውሳኔ መምጣቷ ለሠላም ያላትን ቁርጠኝነት በተጨባጭ የሚያሳይ ነው፡፡ ያልተዘጋውን የቅሬታ ዶሴ በመዝጋት ለሠላምና ለልማት ቆርጣ የመነሳቷ ምስክር መሆኑም አያጠያይቅም፡፡ ኤርትራ አሁን የኢትዮጵያን የሠላም ጥሪ ለመግፋት ምክንያት አይኖራም፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ፀጥታ ስጋት በመጥቀስ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ለመክሰስ የምታደርገው ጥረትም ሰሚ አያገኝም፡፡
የዘርፉ ምሁራን በተደጋጋሚ እንደሚያነሱት የኤርትራ መንግሥት የአልጀርሱ ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ አለመደረጉን በመጥቀስ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ አሁን ታዲያ ኢትዮጵያ የአካባቢውን የዲፕሎማሲ የስጋት ምንጮች በማምከኗ ኤርትራ የቀድሞ አካሄዷን ለመቀየር ትገደዳለች፡፡ ይህን የሠላም ጥሪ አለመቀበል ደግሞ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያሳድርባት ከማድረግ ያለፈ የሚያትርፍላት አንዳች ነገር አይኖርም፡፡ ለሠላም የተዘረጋን እጅ መግፋት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ውግዘት ሊያስከትልባት ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ ውሳኔ ለዓመታት የተራራቁ ወንድምና እህትማማች ህዝቦችን የመገናኘት ተስፋ ያበረታል፤ ያጠነክራል፡፡ የአገራቱን የቀደመ የወዳጅነት ታሪክን በማደስ ግንኙነቱን በአዲስ ምዕራፍ ለማስቀጠል ይረዳል፡፡ የሕዝብ ለህዝብ ትስስሩን በማጠናከር በቀጣናው ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ፣ ልማትን ለማፋጠንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ጉዞን ለማስቀጠል ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና ለአካባቢው የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂው መፍትሔ ነው፡፡ በደም፣ በባህል፣ በቋንቋ እና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ ለተሳሰሩት ህዝቦች ደግሞ ውሳኔው ትልቅ የምሥራች ነው፡፡ በፖለቲካዊ ችግር የተነሳ የአንድ ቤተሰብ አባላት በሁለቱ አገራት ለዓመታት ተለያይተው ለመኖር የተገደዱበት ጊዜ ያበቃል፡፡ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ተራርቀው በናፍቆት ለተቃጠሉ ሰዎች ትልቅ እፎይታን ይሰጣል፡፡ እናም በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች ጠቀሜታው ከቃላትም በላይ ነው፡፡
የተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙኃንም ይህንኑ እውነታ ነው ሲዘግቡ የሰነበቱት፡፡ የእንግሊዙ የዜና አውታር ቢቢሲ ‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ ረጅሙ የግጭት ታሪክ እንዲያበቃ የሚያስችል ዕድል ለኤርትራ ሰጥታለች›› በማለት የኢትዮጵያን ውሳኔ በማድነቅ ዘግቧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገት ንግግር ከኤርትራ ጋር ሠላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር ኢትዮጵያ ፅኑ ፍላጎት እንዳላት መናገራቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡ የአሁኑ የኢህአዴግ ውሳኔ ታዲያ ይህን ወደ መሬት በማውረድ የፍላጎት ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የደም ትስስር ያላቸውን ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር ቆርጦ መነሳቱን በተጨባጭ ያረጋገጠ ነው ብሏል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል መወሰኑ አገሪቱ ሙሉ በሙሉ ፊቷን ወደ ሰላም በማዞር ዓመታት የፈጀውን ስቃይ ለማቆም ማለሟን ያሳያል ብሏል፡፡
የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ(ኤኤፍፒ) በበኩሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ያለውን ውዝግብ ለመፍታት የሚያስችለውን ዕርምጃ መውሰዱ ኢትዮጵያ ለሠላም ያላትን ቁርጠኝነት ከማሳየቱም በላይ፤ ከጎረቤት አገራት ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት አመላካች እንደሆነ ጠቅሷል፡፡
‹‹በሁለቱ ሃገራት መካከል ለረጅም ጊዜ ጠፍቶ የቆየውን ሰላም ለማምጣት ኢትዮጵያ ወደ ተግባር ገብታለች›› ሲልም ጨምሮ ገልጿል፡፡ ከሁለቱ አገራት ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዞ ለየቅል እንደነበር ዘገባው አስታውሶ፤ ኤርትራ ከዓለም ሃገራት የመገለል ዕድሏ እየሰፋ ሲሄድ፤ የኢትዮጵያ ተሰሚነት ግን በፈጣን ኢኮኖሚ እየታጀበ መጨመሩን ነው ያመለከተው፡፡
የአሜሪካው ሲ.ኤን.ኤን ኤርትራ ከኢትዮጵያ የቀረበውን የሠላም ጥሪ በአግባቡ ካልተጠቀመችበት ውስጣዊ አለመረጋጋቱ እንዲበረታ ያደርጋል ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡ ሮይተርስና ሌሎች የዜና ምንጮችም የኢትዮጵያን ውሳኔ ዐቢይ ዜናዎቻቸው በማድረግ ሰፊ ዘገባ ሠርተዋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞችም ኢትዮጵያ ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት ውሳኔ ማሳለፏ እጅግ የሚደነቅ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ አሁን ቀሪው የቤት ሥራ የኤርትራ መንግሥት ነው ብለዋል፡፡
ለሠላም ሲባል፤በተለይም ለዘመናት በአንድነት ሲኖሩ ለነበሩና በደም ለተሳሰሩ ህዝቦች የኢትዮጵያ ውሳኔ ሚዛን ይደፋል፡፡ በስጋት ተወጥሮ የነበረ አካባቢ በሠላም አማራጭ እንዲረግብ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ህዝቦች ‹‹ከአሁን አሁን ምን ይፈጠር›› ከሚል ሰቀቀን ተላቀው በነፃነት እንዲኖሩ ምቹ መደላድል ይፈጥራል፡፡ በድንበሩ አካባቢ ለዓመታት የራቀው ሠላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ያግዛል፡፡ ልማቱ እንዲፋጠንና የህዝቡ ተጠቃሚነት ዕውን እንዲሆን ይረዳል፡፡ ከሁለቱ አገራት አልፎ በቀጣናው ሠላምና ፀጥታ እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋፅዖ አለው፡፡ በሠላም እጦት የሚናጠው ምሥራቅ አፍሪካ የሠላም አየር እንዲተነፍስ ምቹ መዳላድል ይፈጥራል፡፡ እናም ኢትዮጵያ ሠላምና ወዳጅነትን በማስቀደም ያሳለፈችው ውሳኔ በየትኛውም መመዘኛ ቢለካ አዎንታዊነቱ እጅጉን ሚዛን ይደፋል፡፡ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የበኩሉን ከተወጣ በአጭር ጊዜ ጥሩ ውጤት ማየት ይቻላል፡፡

ሠላም ዘአማን

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።