የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ግብዓቶች

10 Jul 2018

በሀገራችን በዚህ ዓመት በፖለቲካው መስክ እየታዩ የሚገኙት ለውጦች ያለፈውንም መለስ ብለን በጥቂቱ እንድንቃኝ ጭምር የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ የንጉሡ አገዛዝ ወድቆ የደርግ ሥርዓት እንደተተካ እንዲሁም የደርግ ሥርዓት ተገርስሶ የኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን እንደተቆጣጠረ ሀገሪቱ የተለያዩ አመለካከቶችን ያራመዱ በርካታ ፓርቲዎችን ለአፍታም ቢሆን አይታለች፡፡ እነዚህም ለለውጦቹ እንደ ማጣፈጫነት አገለገሉ እንጂ የህዝብ ፍላጎት የሆነውን ዴሞክራሲ ለማምጣት ሳይታደሉ ቀርተዋል፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሆኑላቸው እየቀሩ የህዘብ ሥልጣን በብልጣ ብልጦችና አምባገነኖች እየተያዘ አባሎቻቸው በአሳዛኝ ሁኔታ እየተገደሉ፣ ለእስር እና ለስደት እየተዳረጉ ፓርቲዎቹም እንደ ጉም በነው ቀርተዋል፡፤
ከ1983 ወዲህ ያለውን ብንመለከት እንኳ የእነዚህ ፓርቲዎች መሪዎችና አባሎቻቸው ለእስር፣ ለስደት ተዳርገዋል፡፤ ህፃናት ሳይቀሩ ዶክተር እና ፕሮፌሰር መሆን እንዲጠሉ ያደረገ ክስተትም ታይቷል፡፡ የአንዳንዶቹ መሪዎች ምሁራን እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ አሁን ወቅቱ ጥሩ ነውና መናገር ይቻላል። መንግሥት እነዚህ ፓርቲዎች በህዝብ ዘንድ ትንሽ ተሰሚነት ባገኙ ጊዜ ይህቺ ጥሬ ካደረች አትቆረጠምም በሚል የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ ሲያሳድዳቸው ሲያስራቸው ሲያሰቃያቸው በዓይነ ቁራኛ ሲከታተላቸው ቆይቷል፡፡
ከእነዚህ ፓርቲዎች አመራሮች መካከል ጥቂት የማይባሉት ምሁራን ነበሩ፡፡ እነዚህ ምሁራን በሚከተሉት አመለካከት ሳቢያ ለእስር እየተዳረጉ ፍርድ ቤት ይመላለሱም እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህም በመገናኛ ብዙኃን ይገለጽ ነበር፡፤ ያኔ እንደ ዛሬው አማራጭ መገናኛ ብዙኃን አልነበሩምና ትንሹም ትልቁም አንድ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ብቻ ይከታተል ነበር እና ህፃናትም እኩል ተሰላፊ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፤
የምሁራኑን መታሰር እንዲሁም ፍርድ ቤት መመላለስ የተከታተሉ ህጻናት ‹‹አሉ›› የተባለውን ልነገራችሁ ነው። አባት ይሁን እናት እንጃ ልጃቸው በትምህርቱ ጥሩ ውጤት በማምጣቱ ተደስተው ለማበረታት ‹‹ጎበዝ የእኔ ልጅ አንተ ፕሮፌሰር ትሆናለሀ››ሲሉ አድናቆታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይህን የሰማው ተማሪ ከመበረታታት ይልቅ ምን ቢል ጥሩ ነው ‹‹እምቢ፤ አልፈልግም፤ ለመታሰር ነው ›› የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ ይህም በወቅቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ላይ ይደርስ የነበረው አፈና፣ እንግልት፣ እስርና ስደት በህፃናት ላይ ሳይቀር ምን ያህል ከፍተኛ ጫና አሳድሮ እንደነበር ያመለክታል፡፡
የፖለቲካ እንቅስቃሴው ከዓመታት እስር ቆይታቸው በኋላ የእስር ጊዜያቸውን አጠናቅቀው ሲፈቱ ተከታዮቻቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን ይቀጥላሉ ብለው ሲጠብቁ በወህኒ ቤት ምን አስነክተዋቸው ይሆን በሚያሰኝ መልኩ ሀገራቸውን ጥለው የወጡ ፖለቲከኞችም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች ከሀገር መውጣታቸው ላያስደንቅ ይችላል፡፡ የሚያስደንቀው ግን በውጭ ሀገር እየኖሩ ፖለቲካ ባለፈበት ሳያልፉ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡እነዚህ ‹‹የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ነው፤ ለመታ ቢሻን ጋኒ›› እንደተባለው ሁለተኛ ፖለቲካ ባለፈበት ታልፉና አልተባሉም ማለት ይከብዳል። ከእስር ሲለቀቁ በፖለቲካ ላይሳተፉ ፈርመው ነው ብሎ ለመገመትም ያስደፍራል፡፡ይህን ፈረመው ከሆነም ፊርማው ባህር ማዶ ድረስ መዝለቁም የሚያነጋግር ነው፡፡
እነዚህ መሪዎቹ ናቸው፡፡ ተከታዮቻቸው በተለይ በምርጫ 97 እና ማግስቱ በአደባባይ በጥይት ተገድለዋል፤በጸጥታ ሀይሎች ተቀጥቅጠዋል፤በደዴሳ ፣ በሸዋ ሮቢት ፣ በዝዋይ ፣እና በሌሎች የተለያዩ ወህኒ ቢቶች ማቀዋል፡፤እነሱ ብቻ አይደሉም ጋዜጣ ያነባሉ፤ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ይደግፋሉ፣ ገዥውን ፓርቲ ተቃውመዋል የተባሉ ዜጎችም ያላዩት ችግር እንደሌለ ይታወቃል፡፡ የሞተ ተጎዳ ነው የተባለው። ያልሞቱት አዲስ አመለካከት መጣና ተፈቱ። እነዚያ ወጣቶች ግን ደመ ከልብ ሆነው ቀሩ፡፤
ሀገሪቱ አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ወጣ ያለና የገዥውን ፓርቲ የሚቃወም ሆኖ ከተገኘ ወይም የሚቃወም ከመሰለ ከጎኑ ሌላ የገዥውን ፓርቲ የሚደግፍ እንዲያበቅል እየተደረገ ከሥራ ውጪ ሲደረግባት የቆየች፣ አንዳንዶች ኢህአዴግ ሠራሽ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም አሉ ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ እያደጉ አይከስሙ አይነት ፓርቲዎች ለሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ምንም ሳይፈይዱ በሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ ለማለት ያህል እንዲንቀሳቀሱ ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች አሁን ነፃነታቸውን አውጀው መንቀሳቀስ ቢጀምሩ ይበጃል፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና መንሰራፋትን፣ ሥራ አጥነትን እና የፖለቲካ ምህዳር መጥበብን ምክንያት ያደረጉ ተቃውሞዎች፤ ሁከቶችና ግጭቶችን ተከትሎ ባለፉት ሦስት ወራት ሀገሪቱ አዳዲስ ክስተቶችን ማስተናገድ ጀምራለች፡፡
በሀገሪቱ ስር እየሰደደ የመጣውን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና እንዲሁም ወጣቱ የሥራ ዕድል ያለህ እያለ ያቀረበውን ጥያቄ ለመፍታት ኢህአዴግ የተለያዩ አቅጣጫዎችንና ውሳኔዎችን ማሳለፉ ይታወሳል፡፡ የግንባሩ ሊቃነመናብርትም ባልተለመደ መልኩ በጋራ ግምገማውን አስመልክቶ መግለጫ መስጠታቸውም ይታወቃል። ይህም ፓርቲው ዘንድ ውጥረት እንደነበረ ያመለከተም ነው፡፡
ከሁሉም ከሁሉም ግን የሀገሪቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የችግሩ የመፍትሄ አካል ለመሆን በመወሰን ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ መወሰናቸው የሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አዲስ መልክ እንዲይዝ በር ከፍቷል፡፡ በሀገሪቱ አንድ መሪ ሥልጣን በገዛ ፈቃዱ ሲለቅም ይህ የመጀመሪያው እንደመሆኑ ኢትዮጵያንም ወግ ደረሳት አሰኝቷል፡፡ ግዙፍ ችግር የፈጠሩ፣ ሲፈጠር የተመለከቱ ለ27 ዓመታት ፓርቲዬ እስከ አመነብኝ ድረስ ፍንክች ያባ ቢለዋ ልጅ እያሉ ሥልጣናቸውን ማውረስ እስከሚቀራቸው ድረስ የፈለጉትን ሲያደርጉበት በኖሩባት ሀገር ይህ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄ በእርግጥም አዲስ ክስተት ነው። ዋናው ነገር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን መልቀቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ የሚያደርግ ሥርዓት ማበጀት ላይም ጭምር ነውና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡
የእርሳቸውን ከሥልጣን የመውረድ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎም የኢህአዴግ ምክር ቢት አዲስ ሊቀመንበር ይመርጣል፡፡ ይህ ከፍተኛ ፍልሚያ እንደተካሄደበት የሚነገርለት ምርጫም የኦህዴድ ሊቀመንበር የሆኑትን ዶክተር አብይ አህመድን የግንባሩ ሊቀመንበር አርጎ ሲመርጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴው ይበልጥ እየለየለት ወደ አዲስ ምእራፍ እየተሸጋገረ መጣ፡፡
የግንባሩ ሊቀመንበር የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ይታወቃልና ብዙዎች ዶክተር አብይ ሊቀመንበር ከሆኑባት ሰዓት አንስቶ የፖለቲካው አየር መቀየሩን በእርግጠኛነት እስከ መናገር ደርሰዋል። ዶክተር አብይም በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው በተባለ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መጡ፡፡ ይህ በራሱ ለሀገሪቱ እና ለዜጎቿም ሲናፈቅ የኖረ አዲስ ክስተት ነበርና ህዝቡ አድናቆቱን ገልጾለታል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢህአዴግን ፖሊሲ የሚያራምዱ እንደመሆናቸው ብዙም ለውጥ ያመጣሉ ብለው ባይገምትም በወቅቱ የነበረውን ለውጥ ግን በአድናቆት ሳይመለከቱት አላለፉም፡፡ የለውጡ ተጠናክሮ መቀጠል ይህን ጥርጣሬ እንደሚያስወገደው ይታመናል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን መምጣት ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ቀደም ሲል የጀመረውን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመነጋገር፣ ጅማሮ በማስፋት የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት እና በክስ ላይ የሚገኙትንም ክሳቸው እንዲቋረጥ እያደረጉ በመልቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይበልጥ አስፍተውታል፡፡ በዚህም በርካታ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላትና ሌሎች ከእስር ተፈትተዋል፤ በክስ ላይ የሚገኙትም እንዲሁ ክሳቸው እየተቋረጠ ተለቀዋል፡፡ እርምጃው በእርግጥም አንዱ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፊያ መንገድ መሆን ችሏል፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ቁርጠኝነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ ሀገር ሆነው በትጥቅ ትግልም ሆነ በተለያየ መንገድ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ አመለካከታቸውን እንዲያራምዱ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ይገኛሉ፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም እነዚህን ወገኖች አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ከመቀበል ባለፈም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው እየተቀበሉ አነጋግረ ዋቸዋል፡፡ ይህ የልብ የሆነ አቀባበል በኢትዮጵያን ዘንድ ስለፖለቲካ ማሰብ እንዲያንሰራራ የሚያደርግም ነው፡፡
በሚያራምዱት የፖለቲካ አቋም የተነሳ እስራትና ስቃይ የደረሰባቸው አልፎም ተርፎ ሞት የተፈረደ ባቸውና ከእስር እንፈታለን ብለው ጨርሰው ባልገመቱበት ሁኔታ ከእስር ተለቀው ከቤተሰባቸው እንዲቀላቀሉ ብቻም ሳይሆን የፖለቲካ አመለካከታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያራምዱ የሚያስችል ሁኔታም የተፈጠረላቸው በመሆኑ እንዳለፉት የፖለቲካ መሪዎች ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ የማይሉበት ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የተለያየ አመለካከት የሚያራ ምዱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ይገኛሉ። እነዚህ ፓርቲዎች ገና ምርጫ ቦርድ እየቀረቡ አልተመዘገቡምና ይህን ያህል ናቸው ማለት ባይቻልም በርካታ ስለመሆናቸው የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥትን ማሳደድ ፈርተው በድንበር በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እያደረጉ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው በዚያው በመከተማቸው ሳቢያ ሀገሪቱ ስትጎዳ ቆይታለች፡፡ የነበሩባቸው ሀገሮች መንግሥታት ኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያስተናግድ ሥርዓት የላትም እያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ለጋሽ ሀገሮች በሀገሪቱ ላይ ጫና እንዲደረግ ተጽእኖ ሲፈጥሩ ቆይተዋል፤ ዜጎች ወደ ሀገራቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ በባንክ በኩል እንዳይላክ በማድረግ ሀገሪቱ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እንድትፈታ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ይህ ተጽእኖ የድንጋይ ላይ መቀመጫ እና የእናት ሞት እያደር ይሰማል እንዲሉ እነዚህ ወገኖች ይህን በማድረጋቸው ሀገር ቀስ በቀስ ትጎዳለች። በሀገራችን የተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተከሰተው አንድም በእዚህ አይነቱ መንገድ ነው፡፡ ይህን የሚያቀሉ ካሉ ጤንነቱ ያጠራጥራል፡፡
የመንግሥት እርምጃ በሽብርተኝነት የፈረጃቸውን ኦነግን፣ ግንቦት ሰባትንና ኦብነግን ከአሸባሪነት መዝገብ እስከ መሰረዝ ደርሷል፡፡ ይህን እርምጃ ለመውሰድም መንግሥት የምህረት አዋጅ በአስቸኳይ በማዘጋጀት አስፈላጊው ሁሉ በሚመለከታቸው አካላት እንዲደረግበት በማድረግ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ አድርጓል፡፡ ይህም ገና ወደ ሀገራቸው ያልገቡና መንግሥት ወደ ሀገራችሁ ገብታችሁ በሰላማዊ መንገድ ታገሉ እያለ የሚያቀርበው ጥሪ በህግ ማዕቀፍ እንዲደገፍ ለሚፈልጉ ፓርቲዎች ዋስትና በመሆኑም በቅርብ ጊዜ ውስጥም ሌሎች ፓርቲዎች ወደ ሀገራቸው እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ሥልጣን ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ እንደማይያዝ የሚያደርግ አሰራር እንደሚዘረጋ ተናግረዋል፡፡ ይህም መንግሥታት አምባገነን እንዳይሆኑ ከማድረጉም በላይ የሚችሉ ሰዎች ሥልጣኑን እንዲይዙትና ሀገራቸውን እንዲለውጡ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የሚጠቁሙት፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግሥት እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት እንዲሁም እየወሰደ ያለው እርምጃ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የዴሞክራሲ ተቋማት ኃላፊነታቸውን የሚወጡበትን አሰራር ለመዘርጋቱ ሥራ ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን፣ በፍትህ ሥርዓቱ፣ በምርጫ ቦርድ ላይ በትኩረት በመሥራት በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ለውጡ ወደ ኋላ እንዳይመለስ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው እውነተኛ ሆኖ እንዲቀጥል ያስችላል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችም መንግሥት የፈጠረውን የፖለቲካ ምህዳር ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ለመጠቀም መዘጋጀት፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ በመድረስ በሠለጠነ አግባብ አመለካከታቸውን ማራመድ ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓቱ ግብዓት የሚሆኑት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ይገኛሉ። በሀገሪቱ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ የሚታየውን ይህን የአመለካከት ብዝሃነት በጸጋነት በማየት ሀገሪቱ በጽኑ ለምትፈልገው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዋል ከሁሉም ይጠበቃል፡፡

ዘካርያስ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።