በ100 ቀናት እርምጃ- ረጅም ርቀት

11 Jul 2018

የመደመር ዕሳቤን ይዞ አዲስ ምዕራፍ የገለፀው የለውጥ ጉዞ እንደተጋጋለ ቀጥሏል፡፡ ጊዜውም ተፈጥሮአዊ ዑደቱን ጠብቆ እየተጓዘ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ፋና ወጊ ሊባል በሚችል ደረጃ የአገሪቱ ርዕሰ መንግስት ለተተኪው ሥልጣንን በሠላማዊ መንገድ ያስረከበበት ሂደት ታይቷል፡፡ ለቀደመው መሪ ክብርና ምስጋና የተሞላው ደማቅ ሽኝትም ተደርጓል፡፡ ለብዙዎች ምሳሌ የሆነው የሥልጣን ሽግግር ተከናውኖ አንድ ሁለት…እያለ የቀጠለው ጉዞ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ የመቶ ቀናት ሻማውን ለኩሷል፡፡
ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መንበረ ሥልጣኑን የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሠላም ለማረጋገጥ ህዝቡ በአንድነት እንዲቆም ያደረጉት ጥረት ፍሬ አፍርቷል፡፡ ኃላፊነቱን እንደተረከቡ ሠላምን ማረጋገጥ ቀዳሚው ሥራቸው በማድረግ ከህዝቡ ጋር በመምከራቸውና በመወያየታቸው ደፍርሶ የነበረው የሠላም አየር ሊጠራ ችሏል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተዘጋጁት ህዝባዊ የምክክር መድረኮች የመደመር ዕሳቤውን ለፍሬ አብቅተዋል፡፡ ህዝቡ ለሠላሙ ዘብ ለመቆም ቁርጠኝነቱን በተለያዩ መንገዶች አሳይቷል፡፡ የመደመር ጥረቱ ብዙ ማገዶ ሳይፈጅ በህዝቡ ዘንድ አንድነትን የተላበሰ መነሳሳት ፈጥሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ለኤርትራ መንግስት ‹‹የጥሉ ግድግዳ ይፍረስ›› ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ለ18 ዓመታት እንደ ጠላት በሚተያዩት ኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሠላም እንዲወርድ ቁርጠኝነትን የተላበሰ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ መድረኮች የኤርትራ መንግስት የሠላም ጥሪውን እንዲቀበል ከማሳሰብ አልቦዘኑም፡፡ ጥረቱም ታዲያ ፍሬ አልባ አልሆነም፡፡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት የሠላም ጥሪውን በመቀበል ልዑካኑን ወደ አዲስ አበባ ልከዋል፡፡ ይህ ደግሞ በደም ለተሳሰሩት ኢትጵያውያንን ኤርትራውያን ትልቅ የምስራች ነበር፡፡ በአንድነት ተጉዘው በመካከል ከመለያየት አልፈው በጠላትነት እስከመፈራረጅ የደረሱት አገራት የሠላም ሂደቱን መጀመራቸው በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም ትልቅ ቦታ አሰጥቷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሠላም ወዳድነት ጥረት አንፀባርቋል፡፡
ባለፈው እሁድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኤርትራ በማምራት ከኤርትራው አቻቸው ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተዋል፡፡ እጅግ ደማቅ አቀባበል በተደረገበት ጉብኝት ሁለቱን አገራት የሚለየው ግንብ በድልድይ ተተክቷል፡፡ የኤርትራውያን ከፍተኛ ደስታ በተንፀባረቀበት ጉብኝት የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት በተግባር ዕውን መሆኑ በተለያዩ ስምምነቶች ተበስሯል፡፡ የአገራቱ ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩ በአገራቱ መሪዎች በይፋ ታውጇል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤትና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጅቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳ ፣በግብፅ፣በሶማሊያ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባደረጉት ጉብኝት በርካታ ትሩፋቶች ተገኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተጋረጡባት በርካታ ችግሮች ተላቃ በጋራ ጥቅም ላይ ወደ ተመሠረተ ብልጽግና ለመሸጋገር ጽኑ አቋም እንዳላት ለዓለም አሳይታበታለች፡፡ ለቀጣናው ሠላም መስፈንና የምጣኔ ሀብት ትስስር መጎልበት ያላትን ቁርጠኝነት አንፀባርቃለች፡፡ ከአገራቱ ጋር የመተማመን መንፈስ ለመፍጠር ረድቷታል፡፡ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብርን በተሻለ ደረጃ ለማስቀጠል የሚረዳ መሰረት ለመጣል ረድቷል፡፡
ከ90 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ወጭና ገቢ ንግድን ከምታስተናግደው ጅቡቲ ጋር ወደብን በጋራ ለማልማት የተደረሰው ስምምነት የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ ፖርት ሱዳንን በጋራ ከማልማት በተጨማሪ ሱዳንና ኢትዮጵያን በባቡር መሰረት ልማት ለማስተሳሰርም ከስምምነት ተደርሷል፡፡ በኬንያና በሌሎች አገራትም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገው ውይይትና ስምምነት የዲፕሎማሲው ጥረት ውጤት ነው፡፡ በየአገራቱ መካከል ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚረዱ ተግባራትን ለማከናወን ቁርጠኛ አቋም ተይዟል፡፡
በዲፕሎማሲ ጉዞው ከአገራቱ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በሚረዱ ጉዳዮች ዙርያ በመምከር የተለያዩ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ተፈራርመዋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በየአገራቱ በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው መሬት ለማብቃት ረድቷል፡፡ በዚህ በኩል የተገኘው ውጤት ከየትኛውም በላይ አመርቂና ያልተጠበቀ ነበር፡፡ እርምጃው መንግስት ለዜጎቹ ያለውን ተቆርቋሪነትና አሳቢነት በተጨባጭ ያሳየ ሆኖ አልፏል፡፡ በሳዑዲ አረቢያ ለ13 ዓመታት ያህል የአልጋ ቁራኛ የነበረው ብላቴና ተገቢውን ካሳ አግኝቶ በቤተሰቡ ፍቃድ ወደ አገሩ ተመልሶ ህክምናውን እንዲከታተል መደረጉም ሌላው ሰብአዊነትን ያስቀደመው ጉብኝት ውጤት ነው፡፡ በየአገራቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መብታቸው እንዲከበር ጠንካራ መግባባትና መተማመን ተፈጥሯል፡፡
የለውጥ ጉዞው በስኬት እንዲታጀብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለካቢኔ አባላትና ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ለመከላከያ ጄኔራሎችና ከፍተኛ አመራሮችም ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህሉ እንዲጠናክር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያለመታከት አሳስበዋል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚረዱ እርምጃዎችም ተወስደዋል፡፡ ለዚህም የትጥቅ ትግልን አማራጭ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሠላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ተዘግተው የነበሩ መገናኛ ብዙኃንና ጦማርያንም ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲያንሸራሽሩ ተፈቅዷል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሲባል መንግስት ልቡን ለይቅርታ ክፍት አድርጓል፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ወንጀሎች የተከሰሱና የተፈረደባቸው ፖለቲከኞች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የተለያዩ ሰዎች የይቅርታ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ከእስር ተለቀዋል፤ እየተለቀቁም ይገኛል፡፡ የይቅርታው ልብ በዚህ ብቻ የሚቆም አልሆነም፡፡ በመከላከያ ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩና በተለያየ ምክንያት ማዕረጋቸው ተገፎ የነበሩ አባላት ሙሉ ማዕረጋቸው ተመልሶ በክብር በጡረታ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡ በመከላከያና በደህንነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ከፍተኛ አመራሮችን በክብር ሸኝቶ በአዲስ አመራር የመተካት ሥራም ተከናውኗል፡፡ በመንግስት ተቋማት ውስጥም የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የሚረዱ ማሻሻያዎች (ሪፎርም) እየተደረጉ ነው፡፡
የይቅርታና የመቻቻልን አስፈላጊነት በአፅንዖት የሚናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተኮራረፉ አካላትም ዕርቀ ሠላም እንዲያወርዱ ከማሳሰብና ከማወያየት አላረፉም፡፡ ‹‹የውጭውና የአገር ውስጥ›› በሚል ለበርካታ ዓመታት ተራርቀው የቆዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሶች ሠላም እንዲያወርዱ ጥረቱን ገፍተውበታል፡፡ በተያዘው ሐምሌ ወር በአሜሪካ በሚያደርጉት ጉብኝትም አንዱ አጀንዳ ይሄው ጉዳይ ነው፡፡ ሲኖዶሶቹ ችግሮቻቸውን በውይይት በመፍታት ወደ አንድ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአወልያ ትምህርት ቤት አስተዳደርን መነሻው በማድረግ በሙስሊሞች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እንዲፈታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመለከታቸውን አካላት በተናጠልና በአንድነት አወያይተዋል፡፡ በመሆኑም በሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴና በኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ፅህፈት ቤት መካከል የቆየው አለመግባባት እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፡፡
የመደመሩ የለውጥ ጉዞው በጥበብ ሲታገዝ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅኑ እምነት አላቸው፡፡ ጥበብ ኃያል ነው፡፡ በጥበብ ችግር ይፈታል፤ መፍትሔ ይቀመጣል፤ ትምህርት ይተላለፋል፡፡ ጥበብ የሚፈለገውን መልዕክት ማራኪና ሳቢ በሆነ መንገድና ቋንቋ ስለሚቀርብ የበርካቶችን ቀልብ የመሳብ አቅም አለው፡፡ በበርካቶች የሚወደደውን መንገድ በመጠቀም የሠላም፣ የልማትና የአንድነት ጉዞውን የሚያጠናክሩ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ከተቻለ የተራራ ያህል የከበደውን ችግር ማቃለል ይቻላል፡፡ ስለሆነም በተለያዩ ዘርፎች ለተሰማሩ አርቲስቶች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሰርተዋል፡፡ አርቲስቶቹ የያዙትን ትልቅ መሳርያ በመጠቀም ለህዝባቸውና አገራቸው የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፤ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን ለማብረድና ዳግም እንዳይነሱ የተሄደበት ጎዳናም በመልካም ውጤት ታጅቧል፡፡ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የተፈጠረውን ግጭትና ሁከት ለማብረድና ለማስወገድ ከህዝቡ ጋር ያደረጉት ውይይትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ግጭቱን ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ኃላፊነቱን ለአካባቢው ሽማግሌዎችና ወጣቶች በማስረከብ የተደረገው ጥረት ፍሬ አፍርቷል፡፡ ወጣቶችም ላጠፉት ጥፋት የአካባቢውን ማህበረሰብ ይቅርታ በመጠየቅ በአኩሪ አገራዊ ዕሴት ለሠላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይተዋል፡፡
ወጣቶች ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር በማዘመን በዕውቀትና ክህሎት በልፅገው አቅማቸውን አዳብረው የሚፈልጉት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የልህቀት አስተሳሰቦችና የሥራ ፈጠራ ዕሳቤዎችን ተንትነው አስረድተዋል፡፡ በተለይም በሚሊኒየም አዳራሽ ከ25ሺ በላይ ወጣቶች በተሳተፉበት የልህቀት ማስረፅ መድረክ ላይ ወጣቶች በወሳኙ የሥራ ዕድሜያቸው በቁርጠኝነት ከተንቀሳቀሱ ያሰቡትን ከዳር ለማድረስ ምንም እንደማያግዳቸው በምሳሌዎች በማስደገፍ አስረድተዋል፡፡ የለውጡ ዋናው ሞተር ወጣቱ ኃይል መሆኑን በአፅንዖት አሳስበዋል፡፡ ከየዩኒቨርሲቲዎቹ በከፍተኛ ውጤት ለሚመረቁ ወጣቶች በመንግስት የውጭ የትምህርት ዕድል እንደሚመቻች ቃል ተግብቷል፡፡
ሁሉም የለውጡ ተዋናይና ተጠቃሚ ነውና ከባለሀብቶችና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋርም ውይይት ተደርጓል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን ለህዝብ በማቅረብ ለህዝባቸውና ለአገራቸው ልማትና ዕድገት እንዲሰሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎችም ለአገራቸው ልማት እንዲተጉ በተደጋጋሚ መልዕክት ተላልፏል፡፡ በተያዘው ወርም በአሜሪካ ከሚገኙ ዳያስፖራዎች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡
ሠላምን ለማደፍረስና አንድነትን ለማላላት የሚጥሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጥብቅ መልዕክት በተደጋጋሚ ቀርቧል፡፡ በየደረጃው የሚገኝ አመራርም የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ጎትጉተዋል፡፡ ኃላፊነቱን ያልተወጣውም በራሱ ጊዜ ሥልጣኑን እንዲለቅ አማራጭ ቀርቦለታል፡፡ በዚህም ኃላፊነታቸውን የለቀቁ አመራሮችን ለማየት ተችሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና መንግስታቸው እያስመዘገቡት ያለውን ውጤት በማድነቅም ህዝቡ አድናቆቱን ችሯል፡፡ በተናጠል ከሚገለፀው በተጨማሪ ህዝቡ‹‹ ለውጥን እንደግፍ፤ ዲሞክራሲን እናበርታ›› በሚል መሪ ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማመስገን የድጋፍ ሠልፍ አድርጓል፡፡ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተጀመረው ሠልፍ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችም ተካሂዷል፡፡ በዚህም ከመንግስት ጎን በመቆም የሚጠበቅበትን ለመወጣት ቃል ገብቷል፡፡ ህዝቡ ሠላም እንዲረጋገጥ፣ ልማቱ እንዲፋጠን፣ ዲሞክራሲ እንዲጎለብትና አንድነቱ እንዲጠናከር በሠላማዊ ሰልፍ ያሳየው ቁርጠኝነትም በመንግስት ‹‹ምስጋና ይገባሃል›› ተብሏል፡፡ በሠላማዊ ሠልፍ ያሳየውን ድጋፍ በሥራ እንዲለውጠውም ጥሪ ቀርቦለታል፤ የአደራ መልዕክትም ተላልፎለታል፡፡
የአገራችን የዓመታት ችግሮች የሚቀረፉትና ወደተሻለ ደረጃ የሚሸጋገሩት በቀና መንፈስ የለውጥ ኃይል ሆኖ መስራትና መደመር ብቻ ሲቻል ነው። የሁሉም ችግሮች መፍትሄ ከአንድ አካል ብቻ እንደማይገኝ እሙን ነው፡፡ ለለውጥ ከተተጋ በ100 ቀናት እልፍ ሥራዎችን ማከናወን፤ ረጅም ርቀት መጓዝ እንደሚቻል ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የዜጎች ኑሮ ተለውጦ የአገር ዕድገትና ብልጽግና የሚመጣው ኢትዮጵያውያን ክንዳቸውን አስተባብረው በአንድነት ተደምረው ሲተጉ ነው፡፡ በ100 ቀናት እርምጃ ይህን ያህል መጓዝ ከተቻለ በዓመታት ብዙ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ታዲያ የጉዞው ፍጥነት ሊጨምር እንጂ ሊቀንስ አይገባውም፡፡
_

ሠላም ዘአማን

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።