የሥራ ምዘና ፣ደረጃና ነገረ ደመወዝ

04 Apr 2016

 

የኢፌዴሪ መንግስት ሀገራችን እያስመዘገበች ያለችውን ፈጣንና ተከታታይ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ለማስቀጠል የተለያዩ የለውጥ መሳሪያዎችን ቀርፆ ገቢራዊ እያደረገ ነው። ከለውጥ መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም መሆኑ ይታወቃል። የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሙ በውስጡ አምስት ንዑሳን ፕሮግራሞችን ያቀፈ ሲሆን፤ ከእነርሱ ውስጥ አንዱ የሰው ሃይል ማሻሻያ ንዑስ ፕሮግራም ነው። የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ፕሮጀክት ደግሞ የዚህ ንዑስ ፕሮግራም አንዱ ክፍል ነው፡፡_

የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ የሲቪል ሰርቪስ ሥራዎችን በአንድ የተመረጠ ዘዴ በመመዘን ‘ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ’ የሚለውን መርህ በመተግበር ፍትሃዊ የክፍያ ሥርዓት መዘርጋትና የተረጋጋ ሲቪል ሰርቪስ እንዲፈጠር ማስቻል ነው፡፡ ይህን ዕውነታ ታሳቢ በማድረግም የፌዴራል መንግስት የሲቪል ሰርቪሱን ስራ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማሻሻል የስራ ዝርዝሮችን ተንትኖ በማስጠናት በሚያዚያ 2008 .ም በተመረጡ መስሪያ ቤቶች ለሙከራ አሰራሩ እንደሚዘረጋ ማሳወቁ የሚዘነጋ አይደለም።

በመሆኑም በዚህ ፅሑፍ ከፌዴራል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የተገኘውን መረጃ ዋቢ በማድረግ፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚናወኑ የስራ ዝርዝሮችን ተንትኖ በመለየት ስራን የማሻሻል ሂደት በምን ዓይነት ሁኔታ ሊከናወን እንደሚችል ለማየት እንሞክራለን። የዚህ ፅሑፍ ዋነኛ ዓላማም መንግስት አዲስ የደመወዝ ስኬል አማራጭን ለመወሰን በሚቀርቡለት ሃሳቦች ተንተርሶ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራትን እንደምን እንደሚጠቀምባቸው ማሳየት ነው።

እናም ፅሑፉ የሲቪል ሰርቪሱን የሥራ ትንተና፣ ምዘና እና ደረጃ አወሳሰን ምንነት፣ ዘዴዎች፣ ጥንካሬና ድክመት እንዲሁም የሲቪል ሰርቪስ ሥራዎችን ለመመዘን የተመረጠው የነጥብ የሥራ ምዘና ዘዴ ሂደትን በሚከተለው አኳኋን በመቃኘት በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ነው። በመጀመሪያ ግን የስራ ትንተና (Job Analysis) ምንድነው? ከሚለው አንኳር ነጥብ እንነሳ። የስራ ትንተና የአንድን መስሪያ ቤት ዓላማ ለማሳካት የተፈጠሩ የሥራ መደቦችን የሚመለከቱ ሁለንተናዊ ባሕሪያቸውን የመለየት ስራን የሚያካትት ነው።

በዚህ የትንተና ሂደት ውስጥም የኃላፊነት መጠን፣ ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልግ ብቃትን፣ ሥራው የሚከናወንበት አካባቢያዊ ሁኔታ፣ ሥራው የሚፈልገው ልዩ ሁኔታ፣ ከሌሎች ሥራዎች ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሁም ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልገው የቴክኖሎጂ፣ የመሣሪያዎች…ወዘተ. ግብዓቶችን በማጤን ልዩ ልዩ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ መተንተንና መረጃዎችን በየፈርጁ የማጠናቀር ስራዎች ይካተታሉ፡፡

ይህ የሥራ ትንተና ውጤት ሥራውን በትክክል የሚገልጽ የሥራ መዘርዝር ለማዘጋጀት ወሳኝ ግብዓት ነው ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው በማንኛውም መስሪያ ቤት ውስጥ የሚከናወን ስራ፤ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ድርጊቶችን አቀናጅቶ በመፈጸም አንድን ግብ ለማሳካት ሠራተኛው የሚያከናወነው ተግባር ነው። ታዲያ የስራ መደቡ የሚፈጠረው መስሪያ ቤቱ ሊያሳካ የሚፈልገውን ግብ መሠረት በማድረግ ከሚዘጋጅ አደረጃጀት ሲሆን፤ ይህም ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ምጣኔ ሀብታዊ የሆነ የጊዜ፣ የሰው ሀብት ብቃትና ጉልበት እንዲሁም ሌሎች የጥሬ ዕቃዎችና ግብዓቶች አጠቃቀምን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ይሆናል።

በስራ ትንተና ላይ ይህን ያህል ከተግባባን ዘንዳ አሁን ደግሞ ወደ ስራ ምዘና ምንነት እናምራ። ‘ለመሆኑ አንድ ስራ የሚመዘነው እንዴት ነው?’...በማንኛውም ስራ ውስጥ የሚካሄድ ምዘና የሥራ ትንተናን መሠረት አድርገው የተዘጋጁ የሥራ ዝርዝሮችን መነሻ ያደርጋል። ከመነሻው በመነሳትም የሥራ መደቦችን ክብደትና ውስብስብነት ለመለካት እንዲቻል አንድን የተመረጠ የሥራ ምዘና ዘዴ በመጠቀም አንጻራዊ ደረጃቸውን የመወሰን ሂደት ‘ምዘና’ ይሰኛል። ታዲያ እዚህ ላይ በሥራ ምዘና ወቅት የሚመዘነው ሥራው እንጂ ሥራውን የሚያከናውነው ሠራተኛ አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል።

እንግዲህ አንድን ስራ መመዘን ካስፈለገ፣ የምዘናውን አስፈላጊነት አመክንዮዎችን ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል። የስራ ምዘና አስፈላጊነት ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ በስድስት ወሳኝ ነጥቦች ሊጠቃለል ይችላል። አንደኛው ግልፅና ተገቢ የሆነ አንጻራዊ የሥራዎች ደረጃና የደመወዝ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው ተመሳሳይ ባህርይና ክብደት ያላቸውን ሥራዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ለማስተዳደር እንዲያስችል ማድረግ ነው።

ሶስተኛው ነጥብ ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ የሚለውን መርህ ለማስጠበቅና አራተኛው ደግሞ በድርጅቱና በሠራተኞች መካከል መግባባት እንዲፈጠር የሚያደርግ ብሎም ፍትሐዊነትን የማስፈን ፅንሰ ሃሳብን የያዘ ነው። አምስተኛው በድርጅቱ ውስጥ በየጊዜው ለሚከሰቱ ለውጦች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ሲሆን፤ ስድስተኛው ነጥብ ደግሞ የሥራዎችን ደረጃ ለመወሰን ተጨባጭ መሠረት ለመጣል እንዲሁም ወጥ የሆነ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችሉ አንኳር ጉዳዮችን የያዘ ነው።

በምዘና ደረጃ አሰጣጡ ትንተናዊ መረጃ መሰረት ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ እንዲኖር ይደረጋል። ይህም ከዚህ በፊት በአንድ ዓይነት የሙያ መስክ ተመርቀውና ተመሳሳይ የስራ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ስለሚሰሩ ብቻ የሚከፈላቸው የተለያየ ደመወዝ አከፋፈል እንዲቀር ያደርጋል። በዚህ መሰረትም በሀገሪቱ ለተመሳሳይ ስራ የተለያየ ስያሜ የነበራቸው ስራዎች ወደ አንድ ስያሜ ተጠቃለው ለደመወዝ አከፋፈል የሚያመች ስራዎች ይከናወናሉ። ይህም ፍትሃዊ የክፍያ ሥርዓት በማስፈን የተረጋጋ ፐብሊክ ስርቪስ እንዲገነባ ያደርጋል።

በምዘናው ሂደት ውስጥ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተመሳሳይ ስራ እየሰሩ የተለያየ ደመወዝ የሚከፈላቸውን ሰራተኞች እንደየ ስራው ኃላፊነት፣ ክብደትና ቅለት እንዲሁም ውስብስብነት በአንድ የስራ ዓይነት ላይ የተለያየ ክፍያ ሊፈፀም የሚያስችል አካሄድም ገቢራዊ ይሆናል። ነገር ግን ተመሳሳይ የስራ ክብደትና ውስብስብ ለሆኑ ስራዎች የሚከፈለው ደመወዝ ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል። እናም የእያንዳንዱ የስራ ምዘናም ከየመስሪያ ቤቶቹ በተወሰደ የስራ ዝርዝር ላይ ተመርኩዞ እንደሚጠና እና የደመወዝ ስኬል እንዲዘጋጅለት ይደረጋል ማለት ነው።

እርግጥ የደመወዝ አወጣጡና የስራ ምዘናው ስራን ማዕከል ያደረገ ነው። ይህም በየመስሪያ ቤቱ የሚስተዋለውን አላስፈላጊ የደመወዝ ውድድርን እንዲቀር ያደርጋል። የተለያየ ክፍያ የሚያገኙ ሰራተኞችም የተሻለ ክፍያ ለማግኘት ሲሉ ወደ ተለያዩ ተቋማት የሚያደርጉትን ፍልሰትም ያስቀራል። ታዲያ በአዲሱ የደመወዝ አከፋፈልና ምዘና መሰረት ሰራተኞች እንደየ ስራ ባህሪያቸው የወር እና ልዩ ስራ ይከፈላሉ። የወር ስራዎች በአብዛኛው ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆናቸው የደመወዝ ሁኔታውም ተመሳሳይ ይሆናል። ልዩ የሚባሉት የስራ መደቦች ደግሞ በተለየ መልኩ ከበድ ያለ ሃላፊነትና የስራ ጫና ያለባቸው ናቸው፡፡

በአዲሱ ጥናት መሰረት ከተለዩት ሰባት ሺ ስራዎች መካከል 6 300 የሚሆኑት “የወል ስራዎች” እና ቀሪዎቹ “ልዩ ስራ” ተብለው ተለይተዋል። ከአሃዞቹ መረዳት እንደሚቻለው አብዛኛዎቹ ስራዎች “የወል” ተብለው የተመደቡ በመሆናቸው በደመወዝ አከፋፈል ረገድ የሚኖር ልዩነት አይኖርም። ይህም አብዛኛውን ደመወዝተኛ በተመሳሳይ ማዕቀፍ ውስጥ በማስገባት የልዩነት ደረጃውን ለማጥበብ ያስችላል። በዚህም ፍትሓዊነትን ያነግሳል።

እዚህ ላይ የሥራ ምዘና አስፈላጊነት ግልፅና ተገቢ የሆነ አንፃራዊ የሥራዎች ደረጃና የደመወዝ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ ‘ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ’ የሚለውን መርህ ለማስጠበቅ ያለመ እንጂ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር የማይያያዝ መሆኑን ማወቅ ይገባል። በአጭሩ ምዘናው አሰራርን ወጥ፣ ተገቢና ለሰራተኛው ምቹ እንዲሁም የሲቪል ሰርቪሱን የስራ ምህዳር የተረጋጋ ለማድረግ ከማለም እንጂ ደመወዝን ከመቀነስና ከመጨመር ጋር ቁርኝት የለውም።

ውድ አንባቢያን! ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የአሰራር ሂደቶችና የምዘና ነጥቦች በዚህ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። በሀገራችን ውስጥ ላለፉት 44 ዓመታት ስንጠቀምበት የቆየነውን የስራ ምደባ ዘዴን በመቀየር፤ በርካታ ሀገራት የሚጠቀሙበትን የነጥብ ምዘና ዘዴን ምንነትና ጠቀሜታን እንዲሁም የሀገራችንን ሲቪል ሰርቪስ ስራዎች ለመመዘን የተመረጡ መስፈርቶችን በክፍል ሁለት ፅሑፌ ይዤ ለመመለስ እሞክራለሁ።

 

ቶሎሳ ኡርጌሳ

 

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።