«የእኔን አያት ማለቴ ነው!»

18 Jul 2017

 

ሁሌም አባቷን የምትጠይቀው ጥያቄ አታጣም። አንደኛ ከእሱ መልስ አጥታ አታውቅም፤ ሁለተኛ ደግሞ አባቷ ሁሌም ትክክል ነው። አባቷ ደግሞ እንደ ልጅ «ልብስ ፤ ጫማ፤ ብስኩት ግዛልኝ» ብትለው ይቀለዋል። ጥያቄዎቿ ከብደውት አይደለም፤ ግን ለእሷ የሚመጥንና ሊገባት የምትችለውን መልስ ማግኘት ተራራ ይሆንበታል።

አንድ ነገር ከያዘች «አባዬ፤ ይሄን መኪና ማን ሠራው?» «እንዴት አድርጎ ሠራው?» «መሥሪያውን ከየት አገኘው?» «የሸጡለት ሰዎች ከየት አመጡት?» «ተፈጥሮ ምንድን ነውጥያቄዋ የሚያቆመው ሌላ የምትጠይቀው አዲስ ነገር ስታገኝ ነው። ሰልችቶት አያውቅም፤ ግን ግራ እንዳያጋባት ይሰጋል። ልጁ ሁለመናው ናት፤ ሰው በየደቂቃው የመኖሩን ምክንያት የሚያስብ ከሆነ እርሱ በየሽርፍራፊ ደቂቃ ስለልጁ ያስባል፤ በቃ! ልጁ ህይወቱ ናት።

ታዲያ ለዛ ሲል የሚገዛላትን መጻሕፍት የልጆች፣ የምትመለከተውን የቴሌቪዥን ስርጭት ለልጆች ተብሎ የተዘጋጀ፣ የምትሄድበት ስፍራ የልጆች የሆነ፤ ከአቅሟ በላይ እንዳትሆንበት ሲል የማታውቀውን አጥር አጥሮላታል። ይህ ግን ሙሉ አልሆነለትም። አንድ መውጫ መፍትሄ ትሆናለች ብሎ ያሰበው ደግሞ እናቱን ነበር፤ የልጁን አያት።

እናቱ ናቸው የሚሳሳላት ልጁን ማለዳ ትምህርት ቤት የሚወስዷትና ምሽትም የሚያመጧት። ታዲያ በጉዟቸው መካከል ለምታነሳው ጥያቄ የብልህ መልስ ይሰጡለት እንደሆነ ያስባል፤ ይመኛል። በልጅነቱ ይወራ የነበረውን ተረት ልጁ በአያቷ በኩል እንድትሰማ ይፈልጋል።

ታላላቆቿንና አያቶቿን ማክበር፣ የቀደመውን የአገሯን ታሪክም ማወቅ የምትችለው ከአያት ጋር በሚደረግ ወግ እንደሆነ ያምናል። ምክንያቱም እርሱን ያሳደጉት አያቱ በልጅነቱ ስለአገሩ የነገሩት ታሪክ፣ ያስተማሩትን ሁሉ ዛሬ ድረስ እየመነዘረ የሚጠቀምበት ሀብቱ ነው።

ሁሌም ለጓደኞቹ እንዲህ ይላቸዋል፥ «አያቴ ወታደር፣ ታሪክ ፀሐፊ፤ አልያም ምሁርና የሰለጠኑ አይደሉም። ከአንደበታቸው ይወጣ የነበረው ቃልና ትምህርት ግን ይኸው እኔን እንዲህ አድርጎ ሠርቶኛል። እድሜዬን ሙሉ አመስግኛቸው እንኳ የምጠግብ አይመስለኝም። አባቴ እንድወለድ ምክንያት ሆኗል፣ አያቴ ደግሞ ሰው እንድሆን አድርጎ ሠርቶኛል።» ይህን ሲል ታዲያ የእርሱም ልጅ ከእርሱ አባትነት የተሻለ ሰው አድርጎ ሊሠራት የሚችል አያት እንዳላት በማመንና በመመኘትም ጭምር ነው። እንዳሰበው ግን የሆነ አልነበረም፤ ይህንንም ያወቀው ልጁ ሌላ ጥያቄ ስታቀርብለት ነው!

እንዲህ ሆነ፥ ከተሳፈሩበት ታክሲ ውስጥ የተከፈተው ራዲዮ ስለባህልና ወግ ይወራበታል። አስገምጋሚ የሆነ ድምጽ ያለው ተናጋሪ በራዲዮኑ እንዲህ አለ፥ «ዛሬስ ብለን እንጠይቅ? የእኛ የምንለው ምን ቀረን? አባቶቻችንና አያቶቻችን ህይወታቸውን ሰውተው ነው አገራችንን፣ ከነባህልና ሥርዓቷ፤ ከነአንድነት ክብሯ፣ ከነመልኳ ያወረሱን። አለባበስና አነጋገራችን፤ አካሄድና አኗኗራችን ከእነርሱ የወረስነው ነው።...»

«አባዬ! መስዋት ምንድን ነውጥያቄዋ እንደጀመረ ገባው። «መስዋት ሳይሆን መስዋዕት ነው የሚባለው እሺ የኔ ማር! መስዋዕት መሆን ማለት ደግሞ ለአንድ ነገር መሰጠት ማለት ነው። ለምሳሌ አንቺ የምትወጂው መጽሐፍሽ ውሃ ውስጥ ቢገባብሽ ምን ታደርጊያለሽ

«አወጣዋለኋበሚጣፍጥ የልጅ አንደበት መለሰችለት። «ውሃው የሚቀዘቅዝ ቢሆንስጠየቃት፤

«ቶሎ ብዬ አወጣውና እጄ ቶሎ ቶሎ እንዲሞቅልኝ እንዲህ አደርገዋለሁኛሁለቱ ትንንሽ እጆቿን አፋተገቻቸው፤ እርሱም በስስት ግንባሯን ሳማትና። «አየሽ፤ ለምትወጂው መጽሐፍ ብለሽ ቅዝቃዜውን ቻልሽው ማለት ነው። በቃ! መስዋዕት መሆንም እንዲሁ ነው» አላት።

«ታዲያ አያቶቻችን ምንድን ነው መስዋት የሆኑትቀጠለች፤ «መስዋዕት ነው የሚባለው አላልኩሽም? አትርሺ እንጂብሎ ጉንጯን በፍቅር ቆንጠጥ አደረጋትና ቀጠለ፥ «የሆነ ጊዜ ላይ የሆኑ ሰዎች ኢትዮጵያችንን ሊወስዱብን መጡና...» አቋረጠችው፤ «ውስድ ውስድ ሊያደርጓት? ራሷን

«አዎና! ከዛ እንደመጡ ኢትዮጵያን ካልወሰድናት ብለው መደባደብ ጀመሩ። አያቶቻችን ደግሞ አዩና ኢትዮጵያችንን ለማንም አንሰጥም አሉ። ከዛ ተደባደቡ ተደባደቡና አሸነፉ። ልክ አንቺ አንደኛ የምትወጪው ጨዋታ ትተሽ እያጠናሽ እንደሆነ ሁሉ እነሱም አገራቸውን ማንም እንዳይወስድባቸው የራሳቸውን ኑሮ ትተው ለአገራቸው ሲሉ ተደባደቡና አሸነፉ። ከዛ ይኸው ኢትዮጵያችን ሳትወሰድ ቀረች።» አላት።

«ጎበዝ ናቸው አባቢ! አያቴምኮ ጎበዝ ናት ማለት ነውቀጠለች፤ «አዎንአላት፤ «ግን እሷ ምን መስዋት አድርጋ ነውበፈገግታ አያት፤ ቃሉን አስተካክላ እንድትጠራለት መጠበቁ ለራሱ ገረመው፤ ሃሳቡን ከተረዳች አነሰና ነው! «ጠፋብኛ አባቢአለችው፤ ፈገግታ ተለዋወጡና ቀጠለ፤ «መስዋዕት ነው የሚባለው፤ ለማንኛውም ግን አያትሽ...» ማሰብ እንደጀመረ ሃሳቡ አለቀ። የሚላት ደኅና ነገር አጣ... «አያቱ ምን መስዋዕት አድርጋለችልጁ ብዙ እስኪያስብ ጊዜ አልሰጠችውም።

«አያቴ ሞባይል ጌም ተጫውታ ስትጨርስ እኔንም ታጫውተኛለች፤ በዛ ላይ ጸጉሯ ላይ የምታደርገውን ቀለም ትልቅ ስሆን እንደምትገዛልኝ ነግራኛለች፤ ደግሞ የአሻንጉሊት ፊልም እንዳይሰለቸኝ ብላ ሌላ ትልልቅዬ ሰዎች ያሉበት ፊልም ታሳየኛለች፤ በዛ ላይ ለራሷ ታይት ስትገዛ ለእኔም ትገዛልኛለች። ደግሞ ደግሞ ከትምህርት ቤት ስንመለስ ጓደኞቿ ቤት ገብታ ባህር...ደግሞ ደግሞ ሞኳዲስ ስለምትባል ሴት ታወራለች፤ ደግሞም ታስቃቸዋለች። አያቴ ኢትዮጵያን አልሰጥም ብላ አልተደባደበችም እንዴ? አያቶቻችን ተደባድበዋል አላልክም

ምን ይበል? ግራ ገባው! እናቱ ያዋረዱት ያህል ነው የተሰማው። ግን እየተቁለጨለጩ በጥያቄ ለሚያዩት ለልጁ ዓይኖች መልስ መስጠት አለበት፤ «ብዬሻለሁ የኔ ማር! ግን አየሽ፤ የእኔን አያት ነው'ንጂ የአንቺን አያት አይደለምተሳፋሪው ዞር ዞር ብሎ በግራ መጋባትና በፈገግታ አየው፤ ልጁ ግን ገብቷታል። እርሱም የሚፈልገው ያንን ነበር።

ተመለከታት፤ በታክሲው መስኮት አሻግራ የተዘጋጋውን መንገድ ታይ ጀመራለች፤ ሌላ ጥያቄ ፍለጋ። እርሱም አስቀድሞ ከሰጣት መልስ የተሻለ ሃሳብ ይኖር እንደሆነ እያሰበ ነበር!!

 

ሊድያ ተስፋዬ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።