አርባ ምንጭ - ደርሶ መልስ

19 Jul 2017

 

/የጉዞ ማስታወሻ/

ወዳጆቼ! ባለፈው ሳምንት ቆይታዬ ከሸገር ወደ አርባምንጭ ጉዞ ካየሁትና ካጋጠሙኝ ጉዳዮች በመነሳት የታዘብኩትን አስቃኝቼ አርባ ምንጭ ከተማ እንደገባሁ በቀጠሮ መለያየታችን የሚታወስ ነው። ለዛሬ ደግሞ የለምለሟ አርባምንጭ ከተማንና የጥቂት ቀናት እንግድነቴን አስመልክቶ ያየሁትን እውነት በወፍ በረር ላስዳስሳችሁ ወደድኩ።

እነሆ! አርባምንጭ ከተማ በእንግድነት ተቀብላኝ ውዬ ካደርኩ አንድ ቀን ተቆጥሯል። እኔን ጨምሮ ሌሎችም የመጣንበት ጉዳይ ዓለምአቀፉን የውሃ ሲምፖዝየም ለመታደም እንደመሆኑ አብዛኛው ተሳታፊ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው ገና በማለዳው ነበር። ለእኔ አሁንም የአካባቢው ለምለምነት እያስደነቀኝ ነው። አጋጣሚው ተመቻችቶ ሁሉንም ተዟዙሬ ለማየት ባልታደልም ከምንም በላይ ስላስገረመኝ የስፍራው አረንጓዴነት ግን ደጋግሜ ከመናገር ወደ ኋላ አላልኩም።

አርባምንጭ ሴቻና ሲቀላ ተብለው በተከፈሉ ሁለት ሠፈሮቿ በርካታ ነዋሪዎችን አቅፋ የምትኖር ከተማ ነች። ሲባል እንደሰማሁት ደግሞ እነዚህ ሰፈሮች የአንድ እናት ልጆች ቢሆኑም የአየር ንበረታቸው ሳይቀር ይለያያል። ሴቻ ቀዝቀዝ ስትል ሲቀላ ደግሞ ልክ እንደ ደማቅነቷ ሁሉ አየሯም ሞቅ የማለት ባህርይ አለው። ከተማዋ በተፈጥሮ ከተቸራት ውበት ባሻገር ለዕድገቷ መፋጠን እንደ ምክንያት ከሚነሱት መሀል አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የአምስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መገኛ መሆኗ ነው ሲሉ ብዙዎች ይስማማሉ።

የትምህርት ተቋማቱ ከተከፈቱ ወዲህ በከተማዋ የውስጥ ለውስጥ ቅያሶችና የአስፓልት መንገዶች ግንባታ ተካሂደዋል። ለትራንስፖርት አቅርቦቱ አመቺ መሆንም ዕድል ተፈጥሯል። ይህ በመሆኑም አርባምንጭ እንደ ዕድሜ እኩዮቿ አላደገችም ሲሉ ቅሬታ ለነበራቸው ወገኖች ተስፋ ሰጪ ምላሽ እንደሆነ ይታመናል። አካባቢው ፍራፍሬ አምራች እንደመሆኑ ጣፋጩን የሙዝ ዝርያ ጨምሮ ማንጎ፣አቡካዶና ሎሚን በቀላሉ መሸመት ብርቅ የሚባል አይደለም። ተአምረኛው የሽፈራው ቅጠል(ሞሪንጋ)ለዛ ስፍራ ልዩ መታወቂያው ነው። ከመድሀኒትነቱ አልፎ ለምግብነት ጭምር የሚውል መሆኑ ደግሞ ከየጓሮው የመገኘቱን ምስጢር አስደናቂ አያደርገውም።

ከአራት ዓመታት በፊት ሃምሳኛ ዓመቷን ያከበረችው እመት አርባምንጭ ለስሟ መጠሪያ በሆኗት አርባ ምንጮቿ ብዙዎች ያውቋታል። ምንጮቹ አርባ ይባሉ እንጂ ቁጥራቸው ከአንድ መቶ በላይ ስለመሆኑ ጠይቄ ተረድቻለሁ። በእነዚህ ምንጮች ዙሪያ ውሃ እየተራጩ በአስገራሚው የደን ይዞታ ሲቦርቁ የሚውሉ ሕፃናትም በርከት ይላሉ። እንደአለመታደል ሆኖ የምንጮቹን በረከት ለማየት ባይቻለኝም አካባቢውን በዓይነ ህሊናዬ በመሳል ስለመደመሜ ግን ልሸሸግ አልወድም።

አርባምጭ ለቤትና ለግቢ ውበት ማድመቂያነት የሚያስፈልጉ የአበባና የአትክልቶች መገኛ ስለመሆኗም ዓይኖቼ ታዝበዋል። አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎች ዓይቼ የማላውቃቸውን ውብ የሚባሉ አትክልቶችን በየበረንዳው ተደርድረው ማየት ለእንደኔ ዓይነቷ ተፈጥሮ አድናቂ እጅግ የሚያስገርም ነበር። አካባቢው በቅጠላቅጠሎችና በደን ይዞታ የተከበበ መሆኑ ደግሞ አመቺነቱ በሰውልጆች ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አላደረገውም። በዚህ ውብ ተፈጥሮ የሚማረኩ አዕዋፍና ሌሎች የዱር እንስሳትም ስፍራውን መኖሪያ ማድረጋቸው አልቀረም።

የአካባቢው ሙቀትና ልምላሜ በእጅጉ የሚመቻቸው የምድር ተሳቢዎችም ስፍራውን ለመኖሪያቸው ቢመርጡት የሚያስደንቅ አይሆንም። የሚገርማችሁ በወቅቱ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተገኘሁበት አጋጣሚ ያረጋገጥኩት እውነትም ይህንኑ ያሳያል። የዩንቨርሲቲው አጸድ በልምላሜ የተዋበ እንደመሆኑ አካባቢው በመልካም መዓዛና በአዕዋፍ ዝማሬ ሲታጀብ ይውላል። ይህም ብቻ አይደለም። በዚህ መሀል ወፎችን ለምግብነት አጥምዶ ለመሰልቀጥ የሚሹ እባቦች ድንገት ሊከሰቱ ይችላሉ።

በዕለቱም በዚያው ግቢ ውፍረትና እርዝመቱ ከግልገል ዘንዶ የማይለይ ትልቅ እባብ ወፎችን ለማደን ብቅ ብሎ ነበር ። እባቡ ቀኑ ስላልነበር ግን በለስ አልቀናውም። ያሰበውን ከማድረጉ አስቀድሞ ከሰዎች ዓይን ውስጥ ገባ። ያዩትም ፈጥነው ጭንቅላቱን በዱላና ድንጋይ በመቀጥቀጥ ሞቱን አፋጠኑት። ሆኖም የሙት አካሉ ቅሪት በመሬት ተዘርግቶ ሲታይ እጅግ ያስፈራ ነበር። ሲባል እንደሰማሁትም ይህ ግዙፍ ተልባማና ደረተ- ነጭ እባብ እጅግ መርዘኛ ከሚባሉት መደብ ነው። አስቀድሞ ሰዎችን ካገኘም በፍጥነት ህይወትን ሊነጥቅ ይችላል።

እዚያው አካባቢ ከሰሞኑ እንደተሰማውም የዚሁ ዓይነት ዝርያ ያለው መርዘኛ እባብ አንድ ቤተሰብን ለቀናት አግቶ መውጫና መግቢያ አሳጥቶ ነበር አሉ። ይህ ክፉ እባብ ድንገት እንግዳ ሆኖ በታደመበት ቤት አባወራው ዓይን ላይ ጉዳት በማድረስ ለአራት ቀናት ቆይቷል። ይህ መሆኑ ደግሞ እናት ከሁለት ሕፃናት ልጆቿ ጋር በፍርሀትና በጭንቀት እንድትዘልቅ አድርጓታል። በመጨረሻ ግን ሁለቱ ልጆች ባመጡት ጎማ የማጨስ ብልሀት እባቡ ከአካባቢው በመራቁ አባታቸውን በህይወት ለማትረፍ ችለዋል።

አርባ ምንጭ የአባያና ጫሞ ሀይቆች መገኛ እንደመሆኗ በርከት ባለው የዓሣ ምርቷ ትታወቃለች። አሁንም አጋጣሚው ቀንቶኝ ጥሬና ብስሉ ከሚመረጥበት የሐይቁ ዳርቻ ለመሄድ አልታደልኩም። ባለሁበት ሆኜ ግን የዓሣው በረከት ደርሶኛልና ቀጠሮዬን ለሌላ ጊዜ አዙሬዋለሁ። በዚህ አጋጣሚም አርባምጭ ውብ ምድርና ለምለም መሬት፣ አረንጓዴ ገጽታና ተስማሚ አየር እንዳላት ዋል አደር ብዬ አረጋግጫለሁ።

ወቅቱ በዩኒቨርሲቲው ያሉ ተማሪዎች ትምህርት ማጠናቀቂያ እንደመሆኑ እምብዛም እንቅስቃሴ የሚታይበት አልነበረም። ይሁን እንጂ የመጨረሻ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎች ግቢውን ተሰናብተው የሚሄዱበት ጊዜ መድረሱ ደግሞ የተለመደውን የምርቃት መሰናዶ አላቀዛቀዘውም። ይህ በሆነበት አጋጣሚ ታዲያ ዩኒቨርሲቲውን ጨምሮ ሌሎቻችንን ኀዘን የሚያላብስ ድንገተኛ ዜና ለጆሯችን ደረሰ። በዩኒቨርሲቲው የመጨረሻ ዓመት የሲቪል ኢንጅነሪንግ ተማሪ የነበረው ወጣት በሞተር ሳይክል ሲጓዝ በነበረበት አጋጣሚ በደረሰበት አደጋ ህይወቱ ማለፉ ተሰማ።

ወዳጆቼ ! ይህ እውነት እንኳንስ ለፍተው ላሳደጉት ወላጆቹ፣ ኮትኩቶ ላስተማረው ዩኒቨርሲቲና አብረውት ለቆዩት ጓደኞቹ ቀርቶ ለማንም ቢሆን እጅግ አስደንጋጭ የሚባል ነው። የዚህ ወጣት ትውልድና ዕድገት በዚያው አካባቢ እንደሆነ ሰማን። ወላጆቹም ልጃቸውን ለማስመረቅ በጀመሩት ልዩ መሰናዶ የጥሪ ካርዶችን እየበተኑ ነበር። ዓመታትን በትምህርት ያሳለፈው ተማሪ ውጤቱን የሚያይበት ጊዜው ደርሷልና የመመረቂያ ልብሱን ለማምጣት በሞተር እየፈጠነ ነበር። «ኩልፎ» ከተባለው ወንዝ አጠገብ ሲደርስ ግን ከድልድዩ ጋር ተጋጭቶ ወደ ውስጥ ወደቀ።

ይህ ክፉ አጋጣሚ ብርቱውን ተማሪ ከወደቀበት አላስነሳውም። እሱን ጨምሮ ቤተሰቦቹ ሲናፍቋት ለነበረው በጣት የምትቆጠር ድንቅ ቀንም ለመድረስ አላደለውም። ሁሉም ዓላማና ህልም በአፍታ አጋጣሚና በኩልፎ ወንዝ እንቅፋት መና ሆኖ ቀረ። የግቢ ጓደኞቹ ተማሪ ሰለሞን ጌታቸውን በታላቅ የኀዘን ስሜት እያነቡ ተሰናበቱት። ይህ ጊዜም በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ክፉ ጠባሳውን አትሞ አለፈ። ከሁሉም ግን የወጣቱ ስንብት የትራፊክ አደጋ መንስኤ መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። ወዳጆቼ! ይህ የትራፊክ አደጋ ስንቱን ባለ ራዕይ ከዓላማው ሳይገናኝ አለያየው ? ስንቱንስ ቤተሰብ ያለሰብሳቢ በተነው?

አሁን ወደ አርባምንጭ አዞ ራንች ለመሄድ ጉዞ ጀምሬያለሁ። እኔን ጨምሮ ሌሎች በርከት ያሉ ጎብኚዎችም በተዘጋጁልን አውቶቡሶች ውስጥ ተገኝተናል። መቼም አርባምንጭ ተገኝቶ የአዞ እርባታውን ሳያዩ መመለስ አለመታደል ይመስለኛል። አሁን ግን እኔ ከታደሉት መሀል ተሰልፊያለሁና ልቤን ደስ ይለው ጀምሯል። ከከተማው ወጣ ብሎ የሚገኘውን የአዞ እርባታ ለመጎብኘት ዳርና ዳር የበቀሉ በርካታ የሙዝ ተክሎችን እየቃኙ ማለፍ ግድ ይላል። የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ መግቢያን በስተቀኝ ትተው ወደ ግቢው መዳረሻ ሲቃረቡ ደግሞ በርከት ያሉ ዝንጀሮዎች በግርምታ እያዩ ይሸኙዎታል።

ወደ አዞ ራንቹ እንደገባን ሲጠብቁን ከነበሩት አስጎብኚዎች ከአንዱ ጋር ተገናኘን። ወደ ውስጥ ከመዝለቃችን በፊት ግቢውን ለመቃኘት ሞከርኩ። ዝንጀሮዎች፣ሳር የሚግጡ ከርከሮዎችና በርከት ያሉ አዕዋፍ በአካባቢው ይታያሉ። አሁን አዞዎቹ ይገኙበታል ወደ ተባለው ስፍራ አልፈናል። እንደ ዕድሜ መጠናቸው ተለይተው የሚኖሩት አዞዎች አገር ምድሩን አጥለቅልቀውታል። በአቅራቢያቸው የተዘጋጀ ሰፊ የውሃ ስፍራ ቢኖርም የአብዛኞቹ ምርጫ ግን እሱ አልነበረም። ሁሉም በዙሪያው ተኮልኩለው ተኝተዋል። ይህን የሚያደርጉት ፀሐይ ለመሞቅ እንደሆነ ሰማን። አብዛኞቹ ስለማይን ቀሳቀሱም ህይወት ያላቸው አይመስሉም። ድንገት ተነሰተው የሚዘዋወሩ ትናንሽ አዞዎችን በርቀት ሲመለከቷቸው ሸለምጥማጥ ይመስላሉ።

ከአስጎብኚው እንደተረዳነውም አንዲት አዞ በአባያና ጫሞ ሀይቆች በዓመት ከሠላሳ እስከ ሰባ የሚደርሱ ዕንቁላሎችን ትጥልና ሃምሳ ሜትር ጥልቀት ካለው አሸዋ ውስጥ ትቀብራለች። የት እንደምትጥልና መቼ እንደምትፈለፍል ስለሚታወቅም ዕንቁላሎቹ ተሰብስበው ወደ ማራቢያው ይመጣሉ። አዞዎቹን ለተፈለገው ጥቅም ለማዋል እንዲቻል ትልልቅ የሚባሉት በጥይት ይገደላሉ። ብዙ ጊዜም አዞዎችን ለመያዝ በሸምቀቆ ገመድ መጠቀምም የተለመደ ነው።

አዞ በባህሪው ለማዳ የሚባል እንስሳ አይደለም። ብዙ ጊዜም ትልልቆቹ ትናንሾቹን የመብላት ልማድ አላቸውና አብረው እንዲኖሩ አይደረግም። ድንገት የተነከሰና የቆሰለ አዞ ካለም በጋራ ስለሚመገቡት ለብቻው እንዲቆይ ይደረጋል። በአካባቢው የሚያዘወትሩ ዝንጀሮዎችም ውሃ ለመጠጣት ብቅ ሲሉ አዞዎቹ ሊተናኮሏቸው መሞከራቸው አይቀርም። ይሁን እንጂ ዝንጀሮው ጸጥ የሚልበትንና ከውሃ ውጪ ሲሆኑ ኃይል የማያገኙበትን ጊዜ ጠብቆ ስለሚጠጣ ለአደጋ አይጋለጥም። አዞዎች ድምፅ ይረብሻቸዋል። ጫጫታና ሁካታም አይወዱም። ጎብኚዎች ታዲያ ብርቱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመከራሉ።

የአዞ ራንቹን ስንጎበኝ ለብቻው የተከለለ ሰፊ የውሃ ገንዳ መኖሩን አስተውለናል። በገንዳው ከሌሎች ተነጥለው የሚኖሩ ሁለት ግዙፍ አዞዎች ይገኙበታል። እነዚህ አዞዎች ባልና ሚስት ሲሆኑ ከአስር ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ ለሃያ ዘጠኝ ዓመታት በትዳር አብረው ኖረዋል። ብዙ ጊዜ ሠራተኞች ለፅዳትና ውሃ ለመቀየር ሲገቡ የሚጠቀሙበት ጊዜ የአዞዎችን በውሃ ውስጥ ያለመኖር ሲሆን፤ አዞዎቹ ፀሐይ የሚሞቁ ከሆነ በበትር ብቻ እየተመሩ ያሻቸውን ማድረግ እንደሚችሉ ጠባቂው ዘብ ነግረውናል። እኔም አርባ ምንጭን ከነልዩ ተፈጥሮዋ የተሰናበትኳት በዚሁ ጉብኝት ላይ ሆነ።

አሁን ቆይታዬን አጠናቅቄ የጎዞ መልስ ለማድረግ በአውሮፕላን ውስጥ እገኛለሁ። ዕለቱ ጭጋጋማ ስለመሆኑ ተነግሮናል። የአርባአምስት ደቂቃው የአየር ጉዞ ሲጀመር የመነሻዬን ፍርሐት ዳግም አስታወስኩ። ደግነቱ አሁን ስጋቴ እንደመጀመሪያው አልነሆነም። ጉዞው ተጠናቆ አዲስ አበባ ስንደርስ ጭጋጉ ወደ ዝናብ ተቀይሮ ሸገር የተቀበለችን በኃይለኛ ዶፍ ነበር። ወይ ጉድ! የነበርኩበት መልካም የአየር ሁኔታ መልሶ ትዝ አለኝ። ቻው ቻው አርባምጭ!

 

መልካምሥራ አፈወርቅ

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።