ቀጣዩ የባቡር ጣቢያ …

20 Jul 2017

ክቡራትና ክቡራን አንባቢዎቻችን ጽሑፌን ለማንበብ ስለመረጣችሁ አመሰግናለሁ (የአዲስ አበባን ቀላል ባቡር ስለመረጣችሁ እንደሚ ባለው)፡፡ እንግዲህ የዛሬ ጽሑፍ የባቡር ውስጥ የጉዞ ማስታወሻ ነው፡፡ መቼም የጉዞ ማስታወሻ ሲባል በሽንጣም አውቶቡስ አገር አቋርጦ መክነፍ ወይም በሰማዩ ባቡር ባህር ተሻግሮ መሄድ ብቻ ይመስላል አይደል? በጭራሽ፡፡ ወዳጄ በዚህ ዘመን አንተ አውቶቡስ ተራ እስክትደርስ ወይም ከአየር መንገድ ትኬት እስክትቆርጥ ቤቱ ሶፋ ላይ ጋደም ያለ የቴክኖሎጂ ሰው ቀድሞህ ብዙ ሄዷል፡፡

የዛሬዋ ጉዞ ማስታወሻዬ ከአዲስ አበባ አትወጣም፡፡ ከተማዋን ልብ ብለን ካየናት ሰባቱንም አህጉር ከዞረ ሰው ያላነሰ ታስወራለች፡፡ እስኪ ለዛሬው በባቡር ውስጥ እንጓዝ፡፡ መነሻችን ጦር ኃይሎች መድረሻችን አያት ነው፡፡ ጎበዝ የሽርሽር አማራጮቻችሁን አቅም ያገናዘበ ልታደርጉ ይገባል፡፡ ሀብታም የዕረፍት ጊዜውን ከአዲስ አበባ ወጣ በማለት ሐይቅ ባለባቸው ከተሞች እየተዝናና ጊዜውን ያባክናል (ይቺ እንግዲህ የምቀኛ አስተያየት ናት)፡፡ እኔ የእረፍት ጊዜዬን የማባክነው ከአዲስ አበባ ጫፍና ጫፍ በባቡር፣ በባስና በታክሲ እየተጓዝኩ ነው፡፡ በዚያ ላይ በቅርቡ ደራሲ የመሆን ምኞት ስላለኝ (ምኞት ነው ያልኩት) ሀሳብ ለማግኘት እንዲረዳኝ ነው፡፡

የባጥ ቆጡን ስል የጉዞ ማስታወሻውን ረሳሁት አይደል? (ያው ይሄም የጉዞው አካል ስለሆነ ነው)፡፡ ከጦር ኃይሎች እስከ አያት ለመድረስ ምን ያህል የባቡር ጣቢያዎችን እንደማልፍ አስቡት፡፡ ከጣቢያዎቹ መብዛት የተነሳ ከዚያች ሴትዮ የተማርኩት ነገር እንግሊዝኛ ነው፡፡ The Next Station is… ካለች በኋላ የምትናገ ራቸው የማስጠንቀቂያ ቃላት አማርኛውን እየተከተልኩ ትርጉም እለማመዳለሁ፡፡ እስኪ ወደ አማርኛ ተናጋሪዋ እንመለስ፡፡

ክቡራትና ክቡራን ቀጣዩ ጣቢያ… ካለች በኋላ እባክዎ ለመውረድ በስተቀኝ ያሉ በሮችን ይጠቀሙ ትላለች፡፡ የተባለው ጣቢያ ሲደረስም እንዲሁ ትደግመዋለች፡፡ ቀጣዩን ጣቢያ ከተናገረች በኋላ ያለው ግን ትንሽ ረዘም ይላል፡፡ ክላሽ ይሁን ሽጉጥ ወይም ረጅም ምንሽር ባላውቅም መሣሪያ ይዞ መግባት ክልክል ነው ትላለች፡፡ እሺ ይሁን የትኛውም የጦር መሣሪያ ይዞ መግባት ክልክል ነው፡፡ ያልገባኝ ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዞ መግባት መከልከሉ ነው፡፡ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ካቃጠሉት እኮ የትኛውም ነገር ተቀጣጣይ ነው፡፡

ሌላው በተናገረች ቁጥር የሚያስቀኝ ደግሞ «እንስሳት ይዞ መግባት ክልክል ነው» የምትለው ነው፡፡ ይህን ስትል ግራ ቀኝ እያማተርኩ በሬ፣ ላም፣ ፍየል፣ በግ እፈልጋለሁ፡፡ ዳሩ ግን ዶሮ የለም (ወፍ የለም አለ የአራዳ ልጅ)፡፡ ወይስ ለማዳ የዱር እንስሳት ዘለው ይገቡ ይሆን? እንደዚያ እንዳልል ደግሞ ይዞ መግባት ነው ያለችው፡፡ ማለት የነበረባት ግን «እንስሳት እንዳይገቡ ይከላከሉ» ነበር፡፡

አሁን ይሄ ሁሉ ትርጉሙ ጠፍቶህ ነው? የሚል ካለ እሷ ማለት የፈለገችው ቢገባኝም እኔ ተጨማሪ ትርጉም ይይዝብኛል፡፡ በዚያ ላይ ባቡር ውስጥ ማንበብም፤ ሬዲዮ ማዳመጥም ስለማይቻል ታዲያ አዕምሮዬ ምን ይሥራ? ታክሲ ውስጥ እንኳን ስሆን ብዙ ነገር አዕምሮዬን ይይዘዋል፡፡ የረዳትና የተሳፋሪ ንትርክ፣ የአሽከርካሪና የትራፊክ ፖሊስ ክርክር፤ በዚያ ላይ ደግሞ ቆንጆ ሴት በገባች ቁጥር የት ጋ ልትቀመጥ ይሆን? እያልኩ አስባለሁ፡፡ ይሄ ሁሉ ባይሳካ እንኳን ወደ ታክሲው ግድግዳዎች ዞር ዞር ብል ትልልቅ ፍልስፍና ያነገቡ ጥቅሶችን አነባለሁ፡፡ ባቡር ውስጥ ዞር ዞር ብትል የምታየው የላይኛውን ብረት ለመያዝ የሚንጠራራ ሰው ብቻ ነው፡፡ ወደፊት ካየህም ባቡሩ ሲመረቅ የነበረውን ሥነ ሥርዓት የሚያሳይ ስክሪን ነው፡፡

በነገራችን ላይ ባቡር ገና እንደተጀመረ ጥቅሶች ታስበውለት ነበር፡፡ በዚያ ሽንጣም ባቡር ላይ ጥቅስ ይጻፍበት ቢባል የወረቀቱ ወጪ በራሱ ኢኮኖሚ ያቃውሳል፡፡ ሆኖም ግን የታሰቡት ጥቅሶች በወቅቱ በፌስቡክ ላይም ቢሆን ተፅፈዋል፡፡ እስኪ ጥቂቶቹን ልጠቃቅስ፡፡

«የታክሲህን አመል እዚያው»

«ሾፌሩን ማነጋገር የሚቻለው መብራት ሲጠፋ ብቻ ነው»

«ሾፌሩን ማነጋገር የሚቻለው ቻይንኛ ከቻሉ ነው»

እንዲህ እንዲህ የመሳሰሉ ጥቅሶችን በማጣቴ ነው ባቡር ውስጥ አዕምሮዬ ሥራ የፈታው፡፡ እኔም መፅሐፍ እንዳላነብ በሁለቱም እጆቼ ሽቅብ ተንጠልጥዬ ነው የምጓዘው፡፡ ይሄም ቢሆን ዕድሉ ከተገኘ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እንኳን ብረት ልደገፍ እጄን የት እንደማደርገው ራሱ ቦታ አጣለሁ፡፡ እወድቃለሁ ተብሎ አይታሰብ ነገር ወዴት ይወደቃል፤ ግራቀኝ፣ ከፊትም ከኋላም ሰው ሰንጎ ይይዘኛል፡፡ እንዲውም አንዳንድ ጊዜ (በተለይ በሩ ተከፍቶ ሲገቡና ሲወጡ) ከእግሬ ሁሉ ያስለቅቁኛል፡፡ የዚህን ጊዜ የምሄደው በባቡር ሳይሆን በሰው ታዝዬ ይሆናል፡፡

በባቡር ላይ ባደረኩት ተከታታይ ጉዞ አጭር ጥናት መሥራት ጀመርኩ (የጥናትና ምርምር ተቋም አንድ ሊለኝ ይገባል)፡፡ በዚህም መሠረት እንዲህ ዓይነት የተጨናነቀ ጉዞ ያለው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ሁለት ተኩልና እስከ ሦስት ሰዓት ባለው ጉዞ ነው፡፡ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ነው የባቡሩን ሙሉ አካል ማየት የሚቻለው፡፡ ከዚህኛው ጫፍ ሆነህ ከዚያኛው ጫፍ ጓደኛ ካለህ የምትገናኙት ወይ በስልክ ወይ በፌስቡክ ብቻ ነው፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ አንድ የታዘብኩት ነገር አለ፡፡ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ያቺ ሴትዮ የት እንደምትሄድ አላውቅም የለችም፡፡ ቀጣዩን የባቡር ጣቢያ ማወቅ የሚቻለው ከፊት ለፊት ባለው ስክሪን ላይ በጽሑፍ በማንበብ ነው፡፡ እሺ ማንበብ የማይችል ሰው ቢኖርስ? ስል አሰብኩ፡፡

ምናልባት የታሰበው ነገር እንዲህ ይመስለ ኛል፡፡ ከሦስት ሰዓት በኋላ ባቡሩ ባዶ ስለሚሆን በመስኮት እያሻገሩ ማየት ይቻላል፤ አካባቢውንም ማወቅ ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን ይህም መፍትሔ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ እንዲያው ማንበብ ባልችል እንኳን ወደ ውጪ አሻግሬ ማየት ጀመርኩ፤ የአንዱ የመብራት አምፖል ከሌላኛው ጋር እየተንጸባረቀ በግልጽ ማወቅ አይቻልም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ሁሉም ሰው ሁሉንም አካባቢ ያውቃል ማለት አይደለም፡፡ ግራ ሲገባኝ ሌላ መጽናኛ ፈጠርኩ፤ ማን ያውቃል ይቺ ሴትዮ እኔ የምኖር ዕለት ብቻ ይሆናል የምትጠፋው (ያው በአጋጣሚ ማለት ነው) ስል ተስፋ አደረኩ፡፡

በባቡር ውስጥ አንድ የሚያስፈራኝ ነገር ደግሞ የበሩ ድንገት መዘጋት ነው፡፡ ይህ ነገር ግን ከብዙ ልምድ በኋላ የተገለጠልኝ ዘዴ ነበረው፡፡ ባቡሩ ላይ የተገጠሙ ሁለት መብራቶች አሉ፡፡ እነዚህ መብራቶች በሩ ሊከፈት ሲል ይበራሉ፤ ሊዘጋ ሲልም ይበራሉ፡፡ እነርሱ ከበሩ በኋላ ለመውጣት ያሰበ ተጋጬ ማለት ነው፡፡ በሉ አሁን ወደ አያት አካባቢ ልንደርስ ነው፡፡

ክቡራትና ክቡራን አያት፤ ይህ የመጨረሻው ጣቢያ ነው… የአዲስ አበባን ቀላል ባቡር ስለመረጡ እናመሰግናለን፡፡

 

ዋለልኝ አየለ

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።