ልብን ለማሸነፍ ከበሬ ጋር ፍልሚያ

10 Oct 2017

ዛሬ ዛሬ በከተማችን ዘመናዊ ስልጣኔ ጣራ በነካበት ዘመን የሴትን ልብ ለመማረክ ወንዶቻችን በርካታ ተግባራትን ሲፈፅሙ ይስተዋላል፡፡ ወንዱ ለሴቲቱ ያለውን ፍቅር ለመግለፅ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች መካከልም አማላይና ተወዳጅ ቃላቶችን ማዥጎድጎድ ይገኝበታል፡፡

በሌላ በኩልም በተለይም በከተሞች አካባቢ ከአበባ ጀምሮ እንደ መኪና ፣ገንዘብና ቤት የመሳሰሉ ነገሮችን በማቅረብ ልብን ለማሸፈት እንዲሁም የወደዷትን የራስ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት አለ፡፡

በሀገራችን ባህል በተለይም በገጠሩ አካባቢ ደግሞ ሁኔታው ሌላ ገጽታ ነው የሚኖረው ምክንያቱም መተጫጨቱም ሆነ አስፈላጊው ነገር በሙሉ የሚያልቀው በቤተሰብ በኩል በመሆኑ ነው።

ወንዶች ሴቶችን ለጋብቻ ለማጨት በርካታ ነገሮችን ቢያደርጉም የሄኛው ግን ፍፁም ከከተማውም ይሁን ከገጠሩ የተለየ ነው፡፡፡ ለአብነት እንኳን በደቡብ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሱርማ ባህል አንድ አፍላ ኮበሌ ቀልቡ የወደዳትን ልጃገረድ ለጋብቻ ለማጨት ከአቻው ጋር በረጃጅም ጠንካራ ልምጭ ይገረፋል፡፡ እድል ከቀናው ተቀናቃኙን ረቶ የተመኛትን ኮረዳ በእጁ ያስገባል፤ ካልሆነለትም ደሙን እያዘራ ለሚቀጥለው ፍልሚያ ራሱን ያዘጋጃል፡፡ በሐመር ደግሞ አንድ ወጣት አንዲትን ኮረዳ ማግባት የሚችልው ምን አልባትም ከአስር በላይ በተደረደሩ በሬዎች ጀርባ ላይ ተረማምዶ ሮጦ ማለፍ ከቻለ ብቻ ነው፡፡ የአንዱ ባህል ከሌላኛው የተሻለ ነው ማለት ባይቻልም ጉዳት ከመቀነስ አንፃር ግን የሐመሮቹ በጥቂቱም ቢሆን ሳይሻል አይቀርም ፡፡

ቢ ቢ ሲ ከሰሞኑ ከአፍሪካችን የደሴት ሀገር ማዳጋስካር ይዞት ብቅ ያለው ዘገባ የሴትን ልብ ለማሸነፍና ጋብቻ ለመፈፀም እንዲህም ይደረጋል እንዴ? ያስባለ ነው፡፡ ዘገባው እንደሚያሳየው ከሆነ በማዳጋስካር በየዓመቱ የሚካሄድ አንድ ትልቅ ባህላዊ ውድድር አለ፡፡ ይህውም «የቤስቲሊዮ» መንደር ወንዶች የሴቶችን ቀልብ ለመሳብና ለጋብቻ ለማጨት ከጠገቡ በሬዎች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ፍልሚያ ወንዶቹ በእጃቸው የሚይዙት አንዳችም ነገር አይኖርም፡፡ በቃ ባዶ እጃቸውን የበሬው ሻኛው ላይ በመንጠልጠል በሬውን አድክሞ ታግሎ መጣል ነው፡፡ ለውድድሩ የሚቀርቡት በሬዎችም እንደ ገዳይ ሳይሆን ቅዱስ ተደርገው ይቆጣራሉ፡፡ በዚህ ከበሬዎች ጋር በሚደረግ የፍልሚያ ውድድር ላይ ታዲያ ለልጃገረዶች ጥሩ የመዝናኛ አማራጭና እርስ በርስ የመገናኛ መድረክ ሲሆን ለተፋላሚ ወንዶች ደግሞ ለጋብቻ የሚሏትን ልጃገረድ ማግኛ ሁነኛ አማራጭ ነው፡፡

በውድድሩ በአብዛኛው ወንዶች ሴቶችን ለመማረክ ከበሬዎች ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያ ከከባድ ጉዳት እስከ ሞት ድረስ ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ ባጭሩ የወደዷትን ለማግኘት የህይወት መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ ውድድሩን አድርገው ተሸናፊ የሆኑ ወጣት ወንዶች የጋብቻ ጊዜያቸው ካለፈና ልጆች ካልወለዱ በማህበረሰቡ ስለሚወገዙና ከጎሳ አባልነታቸው ስማቸው ስለሚፋቅ በየዓመቱ ውድድሩን እስኪቀናቸው ድረስ ያካሂዳሉ፡፡

የሚገርመው ነገር አንድ ወጣት ከበሬ ጋር ተፋልሞ በውድድሩ መሰረት በሬውን አድክሞ ማሸነፉን ካረጋገጠ በኋላ ወደሚፈልጋት ሴት ሄዶ ለጋብቻ ቢጠይቃት ምን አልባት ከበሬው ጋር ሲፋለም ያሳየው ጥበብ ካልማረካት ‹‹አይ በሚቀጥለው ዓመት ሞክር ተወኝ›› ማለት መቻሏ ነው፡፡ ታዲያ ወንዱም በአሁኑ እንዳልተሳካለት ተረድቶ በቀጣይ ለእርሱ የምትሆነውን ልጃገረድ ለማጨት አሁንም ከበሬ ጋር ትግሉን ይቀጥላል፡፡

በዚህ በምስራቃዊ ማዳካስካር በቤስቲሊዮ መንደር በሚካሄደው ሳቫኪያ በተሰኘው ወጣት ወንዶች ሴቶችን ለጋብቻ ለማጨት ከበሬዎች ጋር በሚያደርጉት ትግል ቢያንስ እስካሁን 50 ወንዶች ህይወታቸውን እንዳጡም ነው የቢቢሲ ዘገባ የሚያስረዳው፡፡

 

አስናቀ ፀጋዬ

 

 

ማህበራዊ ድረገፃችንን ይጎብኙ

 

            በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው ኦፐሬቲንግ ሲስተም ኢትዮኑክስ ስርጭት ላለፉት 8 ዓመታት (1999-2007 ..) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላለፍት 2 ዓመታት እንዲሁም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወርሃዊ ጋዜጣ ላይ ላለፈው 1 ዓመት በተግባር ተሞክሮ ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ድረገጽ በኢትዮኑክስ ኦፐሬቲንግ ሲስተም ላይ ተገንብቶ የሚሰራ ነው።